መዝገበ ቅዱሳን
20.7K subscribers
1.92K photos
9 videos
6 files
24 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
#ጥቅምት_5

ጥቅምት አምስት ቀን የታላቁ አባት #አቡነ_ገብረ_መንፈስ_ቅዱስ (ገብረ ሕይወት) የዕረፍታቸው መታሰቢያ፣ የቊስጥንጥንያው #ሊቀ_ጳጳሳት_አባ_ጳውሎስ እረፍት፣ የሐዋርያው #ቅዱስ_ያዕቆብ_ወልደ_እልፍዮስ መታሰቢያው፣ የከበረ ጳጳስ #ቅዱስ_ኪራኮስ ከእናቱ #ከቅድስት_ሐና ጋራ በሰማዕትነት ያረፈበት ቀን ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ገብረ_መንፈስ_ቅዱስ (ገብረ ሕይወት)

ጻድቁ የተወለዱት ግብፅ (ንሒሳ አካባቢ) ሲሆን አባታቸው ስምዖን እናታቸው አቅሌስያ ይባላሉ። አባታችን ገብረ ሕይወት የጻድቃን አለቃ የቅዱሳን የበላይ ተጋድሎአቸውና ድንቅ ተአምራቸው እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ቅዱስ ሰው ናቸው። የጻድቁን ክብር መናገር የሚችል ምን አነደበት ይኖራል? እንደ ምንስ ባለ ብራና ይጻፋል? ዜናቸውንስ ለመስማት የታደለ እንደ ምን ዓይነት ሰው ይሆን?

አባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለ562 ዓመታት በዚህች ዓለም ሲኖሩ እህል ያልቀመሱ /ምግባቸው ምስጋና ነውና/ ልብስ ያልለበሱ /ጠጉር አካላቸውን ይሸፍን ነበርና/ ሐዋርያዊ ሆነው ከግብፅ እስከ ኢትዮዽያ ብዙ ነፍሳትን ያዳኑ አባት፤ ሃገራችንን አስምረው አስራት እንድትሆናቸውም ተቀብለው ምድረ ከብድ አካባቢ አርፈዋል።

ጻድቁ ገብረ መንፈስ ቅዱስም ገብረ ሕይወትም ይባላሉ። በ562 ዓመታት ሕይወታቸው እንደ ሐዋርያት ከምድረ ግብፅ እስከ ኢትዮዽያ ወንጌልን ሰብከዋል። በዚህም በሚሊየን (አእላፍ) ለሚቆጠሩ ነፍሳት የድኅነት ምክንያት ሆነዋል።

ጻድቁ እንደ ሰማዕታትም ከከሃዲ ሰዎች ብዙ መከራን ተቀብለዋል። እንደ ባሕታውያን ለብዙ መቶ ዓመታት ሰው ሳያዩ ቆይተዋል። ለየት የሚለው ግን የጽድቅ ሕይወታቸው ነው፤ ከእልፍ አዕላፍ አጋንንት ጋር ተዋግተው ድል ማድረግ ችለዋልና።

የንሒሳው ኮከብ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቀር አላቸው። ስለ ሃገሪቱና ሕዝቧ ፍቅር ሲሉ ለ100 ዓመታት በደብረ ዝቋላ መከራን ተቀብለዋል። ምሕረትን ሲለምኑ ሥጋቸው አልቆ በአጥንታቸው ቁመው ነበርና ሃገራችን አሥራት ሆና ተሰጠቻቸው።

ስለዚህም ነው በሃገሪቱ ውስጥ ከ2,000 በላይ የጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳማትና አድባራት ዛሬም ድረስ ያሉት። በ8ኛው ክ.ዘ አካባቢ የተወለዱት አባታችን ያረፉት በ14ኛው መቶ ክ.ዘ አካባቢ ነው። ፍጥረታትን ሁሉ አዘው መጋቢት 5 ቀን ሲያርፉ ግሩማን መላእክት ገንዘው አካላቸውን ሠውረዋል።

ሥላሴን የተሸከመ አካላቸው በጐልጐታ ተቀብሯል የሚሉም አሉ። "ሰላም ለመቃብሪከ ዘኢተከሥተ ለባዕድ: ከመ መቃብሩ ለሙሴ ወልደ ዮካብድ: ዜና መቃብሪከሰ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጸማድ: ቦ ዘይቤ በኢየሩሳሌም አጸድ: ወቦ ዘይቤ ኀለወ በከብድ።" እንዲል።

ጻድቁ አባታችን አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ እረፍቱ መጋቢት 5 ቀን ነው ይህ ደግሞ በታላቁ ዓብይ ጾም ወቅት ነው ፍትሃ ነገስት አንቀጽ 15 ላይ በዓብይ ጾም በዓል ማክበር ይከለክላል የሀዘን ወቅት ነውና ከበሮ አይመታም እልልታና ጭብጨባ የለም ፍጹም ሀዘን እንጂ የመጋቢት 27 ስቅለት ጥቅምት 27 ቀን እንደሚከበረው ሁሉ ወደ ጥቅምት 5 ቀን ተዛውሮ እንዲከበር ተደረገ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሊቀ_ጳጳሳት_አባ_ጳውሎስ

ጥቅምት አምስት በዚች ቀን የቊስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ጳውሎስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ከእርሱ አስቀድሞ በቁስጥንጥንያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ለነበረው ለአባ እለእስክንድሮስ ደቀ መዝሙሩ ነው። አባ እለእስክንድሮስም በሞተ ጊዜ በርሱ ፈንታ ይህ አባት አባ ጳውሎስ ተሾመ።

በጵጵስናውም ወንበር በተቀመጠ ጊዜ የአርዮስን ወገኖች ከቊስጥንጥንያ አገር ከአውራጃውም ሁሉ አውግዞ አሳደዳቸው። ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ ከሞተ በኋላ ልጁ ሁለተኛው ቈስጠንጢኖስ በቊስጥንጥንያ አገር ላይ ነገሠ ወንድሙ ቊንስጣም በሮሜ ሀገር ነገሠ። ይህ ቈስጠንጢኖስም አርዮስን ይወደዋል በረከሰች ሃይማኖቱም ያምናል ቅዱስ አባ ጳውሎስም አርዮሳውያንን አውግዞ እንዳሳደዳቸው ሰምቶ እጅግ አዘነ።

አባ ጳውሎስንም ከእንግዲህ የአርዮስን ወገኖች ተዋቸው አታውግዛቸው አለው እርሱ ግን ንጉሡን አልሰማውም ስለዚህም አባ ጳውሎስን ከቊስጥንጥንያ አገር አሳደደው።

እንዲህም ሆነ ከእርሱ አስቀድሞ ከእስክንድርያ ሀገር አባ አትናቴዎስን አሳድዶት ነበርና በሮሜ አገር በሊቀ ጳጳሳት በቅዱስ አባ ዮልዮስ ዘንድ ሁለቱም ተሰበሰቡ። እርሱም በመልካም አቀባበል በፍቅር ተቀበላቸው ወደ ንጉሡም ወደ ሁለተኛው ቈስጠንጢኖስ እንዲህ ብሎ መልእክትን ጻፈላቸው "እነርሱ እውነተኞች የተማሩ አዋቂዎች ሃይማኖታቸውም የቀና ናቸው ልትቀበላቸው ልታከብራቸውም ይገባል።"

ሊቃነ ጳጳሳቱም አባ ጳውሎስና አባ አትናቴዎስ ወደ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ በደረሱ ጊዜ የመልእክቱን ደብዳቤ ሰጡት አነበባትም ከሮሜው ሊቀ ጳጳሳት ቃል የተነሳ ፈራ። ተቀብሎም በየቦታቸው በሹመታቸው ወንበር አኖራቸውና ጥቂት ቀኖች በእነርሱ ላይ ታገሰ።

ከዚህም በኋላ ሁለተኛ አሳደዳቸው እነርሱም ወደ ሮሜ ወደ ሊቀ ጳጳሳት ዮልዮስ ተመልሰው ንጉሡ በእነርሱ ላይ ያደረገውን ሁሉ ነገሩት ሊቀ ጳጳሳት ዮልዮስም ወደ ወንድሙ ወደ ንጉሥ ቊንስጣ ይዟቸው ገብቶ ወንድሙ ቈስጠንጢኖስ በእነርሱ ላይ ያደረገውን ነገረው።

ይህም ንጉሥ ቊንስጣ ይቀበላቸው ዘነድ ወደ ወንድሙ መልእክትን ጻፈ እንዲህም ብሎ አዘዘው። እሊህን አባቶች ካልተቀበልካቸው ከእንግዲህ በመካከላችን ፍቅር አንድነት አይሆንም ሊቀ ጳጳሳቱም እንዲሁ ሁለተኛ ደብዳቤ ጻፈ።

ንጉሥ ቈስጠንጢኖስም የወንድሙን የንጉሥ ቊንስጣንና የሊቀ ጳጳሳቱን መልእክት ተቀበሎ ወደ ሹመታቸው ወንበር መለሳቸው።

ንጉሥ ቊንስጣም በአመጸኞች እጅ ከተገደለ በኋላ ያን ጊዜ ቈስጠንጢኖስ አባ ጳውሎስን ወደ አርማንያ አገር አጋዘውና በዚያ ጥቂት ቀን አሠረው። ከዚህም በኋላ ከአርዮስ ወገን አንዱን በእሥር ቤት በሥውር አባ ጳውሎስን ይገድለው ዘንድ አዘዘው አንዱ አርዮሳዊም በሌሊት ገብቶ አንቆ ገደለው መላ ዕድሜውም አርባ ዓመት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ያዕቆብ_ወልደ_እልፍዮስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ መታሰቢያው ነው። ቅዱሱ አባቱ እልፍዮስ ወይም ቀለዮጳ ይባላል፡፡ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ሲሆን በቅዱስ ወንጌል ላይ በአብዛኛው የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ እየተባለ ተጠርቷል፡፡ ማቴ 10፥3፣ ማር 3፦17፣ ሉቃ 6፥15፣ ሐዋ 1፥13፡፡

በሌላም በኩል ከታላቁ ያዕቆብ ከዘብድዮስ ልጅ ለመለየት ሲባል ታናሹ ያዕቆብ እየተባለ ተጠርቷል፡፡ ማር 5፥40፡፡ የእመቤታችን እኅት (ዘመድ) የቀለዮጳ ሚስት ማርያም ልጅ በመሆኑ ‹‹የጌታ ወንድም›› ተብሏል፡፡ ማቴ 13፡55፣ ማር 6፡3፣ ገላ 1፡19፡፡ ሦስት ወንድሞች ያሉት ሲሆን እነርሱም ይሁዳ፣ ስምዖንና ዮሳ ናቸው፡፡

ሐዋርያው ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ ብዙ ሀገራት ላይ ዞሮ ወንጌልን ካስተማረና ብዙዎችን ካጠመቀ በኋላ ተመልሶ ወደ ኢየሩሳሌም ገብቶ በምኩራባቸው አስተማረ፡፡ ክፉዎች አይሁድም ‹‹ደሙ በእኛ ላይ ይሁን›› ብለው ከመካከላቸው አውጥተው ወስደው ለሮማው ንጉሥ ለቄሳር እንደራሴ ለሆነው ለንጉሥ ቀላውዴዎስ አቅርበውት "ይህ ሰው ስለ ቄሳር ሳይሆን ስለ ሌላ ንጉሥ ይሰብካል" ብለው ወነጀሉት፡፡ ንጉሡም ይህን ሲሰማ በድንጋይ ወግረው እንዲገድሉት አዘዘና ፈጥነው ወስደው ወግረው ገደሉት፡፡ ዕረፍቱ የካቲት 10 ነው፤ በዚህችም ቀን መታሰቢያው እንደሆነ የጥቅምት አምስት ስንክሳር ይናገራል።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ካራኮስ