ቃለ ጽድቅ ዘመካነ ሕይወት | የመ/ሕ/ሰ/ት/ቤት ሰሌዳ መጽሔት ንዑስ ክፍል
1.02K subscribers
2.78K photos
44 videos
102 files
781 links
ይኽ በፈረንሳይ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን መካነ ሕይወት ሰ/ት/ቤት መንፈሳዊ ጽሑፎችና መልእክቶች የሚለቀቁበት ሚዲያ ነው።
https://linktr.ee/kaletsidkizm
Download Telegram
ጓደኛ ያበዛ ፣ መከራ አበዛ

ለወጣቶች መልክት ነው

ሁሉን ሰው መውደድ እንጂ ሁሉን ጓደኛ ማድረግ አይቻልም ፤ ደግሞም ተገቢ አይደለም ። #ሁሉን ሰው በእኩል ማየት እንጂ ለሁሉ ሰው ጓዳን መግለጥ ተገቢ አይደለም ፤ ደግሞም ጎጂ ነው ።

#በሚጠሉህ መሐል ወዳጅህን እንደምታገኘው ፤ ከሚወዱህ መሐልም የሚጠላህን ታገኘዋለህ ። ሁሉ ይወደኛል ብሎ የሚያስብ ጅል ብቻ ነው ። ሁሉ ይጠላኛል ብሎ የሚያስብም ትላንትን ያልረሳ ነው ።

#አንተ ቀድሞ ትጠላቸው የነበሩትን አሁን በጣም ትወዳቸዋለህ ፣ ቀድሞ በጣም ትወዳቸው የነበሩትን አሁን ባሰብካቸው ቊጥር ትታመማለህ ። ሰዎችም እንዳንተ ናቸው ።

#ሳያውቁህ ሊጠሉህ ይችላሉ ፣ ጥላቻ ስሜት ነውና ስሜቱ ሲሄድ እንደገና ይወዱሃል ። ይወዱህ የነበሩም ከዓይናቸው ጆሮአቸውን አምነው ሊርቁህ ይችላሉ ። #የሄደው ይመጣል ፣ የመጣውም ይሄዳል ። በዚህ ዓለም ላይና በሚመጣው ዓለም ቋሚው #መንግሥተ #ሥላሴ #ብቻ ነው ።

#እግዚአብሔርን ከማያምኑና እናምናለን ከሚሉ ግብዞች ተጠንቀቅ ። #ክርስቲያን ሁነው ጭካኔን የሚለማመዱ እንደ አርዮስ በልብ ክደው በአፍ የሚያምኑ ናቸው ። የእነዚህ ሰዎች ወዳጅነት እንደ ፍግ እሳት ነው ፣ ውስጥ ውስጡን ሂዶ መጨረሻ ላይ ያቃጥላል ።

ጻድቅ ለመምሰል ከሚሞክሩ ስጦም ውያለሁ ፣ #ስጸልይ አድሬአለሁ ከሚሉ ፣ ለወሬ እየነቁ ለቃለ እግዚአብሔር ከሚተኙ ፣ ሌሎችን ሲኰንኑ ከሚውሉ ፣ ለመናገር እንጂ ለመስማት የተፈጠሩ ከማይመስላቸው ሰዎች ጋር ያለህን ወዳጅነት እንደገና መርምረው ። #እነዚህ ሰዎች አንተን በተለያየ ነገር ተገዥአቸው ሊያደርጉህ ይፈልጋሉ ። ድራማቸውን ከነቃህበት እንደ ጠላት ያዩሃል ።

እንባ ሊያበዙ ፣ ተጎዳሁ የሚል ድርሰት ሊያነቡልህ ይችላሉ ። የሚናገሩት የተጠና የመከራ ታሪክ አላቸው ፤ ተሳስተው ከሚጎዱህ አልመው የሚጎዱህ እነዚህ ናቸውና ተጠንቀቅ። የአየር ትራፊክ ሠራተኛ ብዙ አውሮፕላኖችን አየር ላይ ደርድሮ አንዱ አንዱን ሳያይ ሲያሳርፍና ሲያስነሣ እንደሚውል እነዚህ ሰዎችም የተለያዩ ወገኖችን ለተለያየ ጥቅም የሚጠቀሙ ስልታዊ ናቸው ።

የሚደልሉላቸው ብዙ ሠራተኞች ፣ ጽድቃቸውን እያወሩ የሚከፈላቸው ሎሌዎች አሉአቸውና ተጠንቀቅ ።

#የታወቁ ሰዎችን ለማወቅ አትጣር ። ከሹም ጋር ለመታየት ጥረት አታድርግ። ከባለጠጎች ጋርም ጊዜ ለማጥፋት አትሻ ። ዝነኞችንም በቤትህ ለመጋበዝ አትከጅል ።

እነዚህ ሁሉ የነፋስ ጎረቤቶች ናቸውና ሲጠረጉ አብረህ ትጠረጋለህ ። በእነዚህ መንደር ስላደረጉት ጀብዱ ስለሚፈጽሙት በቀል እንጂ ስለ ሕይወት አይወራምና ወዳጅነታቸውን አትውደደው ። ደግሞም በሩቅም በቅርብም ውብ #እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን አትዘንጋ ።

በሥራ ሰነፎች የሆኑ ፣ በየቤቱ እየዞሩ በጸሎት ስም አድማ የሚረጩ ሰዎች አብረውህ ቢቆዩ እንኳ ስለ ሆዳቸው እንጂ ስለ ፍቅር አይደለምና ወዳጆችህን የሚያጠፉብህ እነዚህ ስለሆኑ በቶሎ ሸኛቸው ።

#አለዝዘው የሚገድሉ ረጅም ሞት ማለት እነዚህ ናቸው ። እምነት የሚመስል ግዴለሽነት ፣ ትዕግሥት የሚመስል ስንፍና እንዳላቸው ልብ በል ። #ሥራ ስትላቸው ዋናው ጸሎት ነው የሚሉና ጸሎትን የስንፍና መጋረጃ ያደረጉ ናቸውና ከእነዚህ ዘባቾች ጋር ከቻልህ ጎረቤት አትሁን ።

ገለባ እንደማይበቅል ሰነፍም ወዳጅ አይሆንም ። አፈ ቅቤ የሆኑትን ተጠንቀቅ ። #እግዚአብሔር ተናጋሪውን አሮንን ሳይሆን ኮልታፋውን ሙሴን እንደ መረጠ እወቅ ። ተናጋሪ ሰው መጨረሻው ጥፋት ነው ።

የሚያቆላምጡህን አትውደድ ፣ የስምህም ጥገኛ ሁነህ የሚያሞካሹህን አትጋብዝ ። እነዚህ ሰዎች አዝማሪ ናቸውና ለሞቀበት የሚዘፍኑ ናቸው ።

እኔ ብቻ ነኝ ያንተ ወዳጅ የሚሉህንም አትመን ። እነዚህ ሰዎች አንተን በማምለክና አንተን የፈጠሩህ በሚመስል ስሜት ያበዱ ናቸው ።

#በማምለክ ስሜታቸው ያለ አንተ የሚኖሩ አይመስላቸውም ፣ በመፍጠር ስሜታቸው እነርሱ ሳያውቁ ማንንም እንድትወድ አይፈቅዱም ። እነዚህ ሰዎች ፍቅር በሚመስል ነገር በቅኝ የሚገዙህ ናቸውና ተጠንቀቅ ።

ራስህን ነጻ ያወጣህ ቀን ለእኔ ካልሆነ ለማንም አይሁን በሚል ስሜት ሊያጠፉህ ይነሣሉ ። የጅል ጠብ ማብቂያ የለውምና እባክህ ተጠንቀቅ ።

#ለሚያደርሱብህ ጉዳትም ጸጸት አይሰማቸውም ። ምክንያቱም በፈጠሩት ላይ የፈለጉትን የማድረግ ስሜት ስለሚሰማቸው ነው ። ቆንጥር እንደያዘው ልብስ ቀስ ብለህ ተላቀቅ ።

ሌሎችን የሚያዋርዱ ሰዎች አንተን እያከበሩህ ቢቀርቡ አትመናቸው ። #ኃይለኛ ውሻ እንኳ የሚወድህ ለሌላ ውሻ ደግነት ስታደርግ ሲያይህ ነው ። ይህ ሰው የእኛ ወዳጅ ነው ብሎ አላስቀርብ ያለ ውሻ ይቀርብሃል ።

ይለዝብልሃል ። ውሻ እንኳ በሌላ ውሻ ከለካህ አንተም ሰውን በሰው ለካው ። #ባለጌ የሚሰድበውን ሲጨርስ ወዳንተ ይዞራል ። ስድብ ሥራው ነውና ። #በተሾምህበት ስፍራ አብሮ አደጎችህን ይዘህ አትሂድ ።

በር ዘግተህ ካልሆነም ከአብሮ አደጎች ጋር አትጫወት ። #ልክና ዕረፍት ያጣ ወዳጅነትን ተጠንቀቅ። እሳትን የሚያነደው እፍ እንደሆነ ሁሉ የሚያጠፋውም እፍ ነው ። ያበዱለት ወዳጅነት አድራሻው እስኪጠፋ ብን ይላል ። ሁሉን በልክ አድርገው ። የዓመቱን በዕለት አትሥራው ።

አሰቃቂ ነገርን በራሳቸው ላይ የሚናገሩትን ፣ ራሴን አጠፋለሁ የሚሉትን ሰዎች በጥንቃቄ ተመልከት ። #አንዳንዶች ኑሮ ከፍቶባቸው እንዲህ ይላሉና እዘንላቸው ።

ሌላውን እስረኛ ለማድረግና ሌላው ሲጨነቅ በመስተዋት እያዩ ለመሳቅ ፣ ሌላውን አንቅተው እነርሱ ለመተኛት እንዲህ የሚሉ ሰውን የኅሊና እስረኛ በማድረግ የሚረኩ ሰዎች እንዳሉ አትዘንጋ ።

#ርኅራኄህን ካገኙት በኋላ ያሰቃዩሃል ። እነዚህ ሰዎች በጣም ራስ ወዳድ ናቸውና ሁሉን ነገርህን እንዳያራቁቱብህ ተጠንቀቅ ።

#አበድ አበድ የሚሉ ሰዎችን እብደት መታወቂያ እንዲሆንላቸው የሚፈልጉ ሰዎችን ገስሥ እንጂ አትደንግጥላቸው። እብደት ለአንዳንድ ሰው የኑሮ ቄንጥ እንደሆነ እወቅ ።

#እነዚህ ሰዎች አንድ ቀን ቀድመው ባስመዘገቡት እብደት ቤትህንና ኑሮህን ሊያወድሙ ይችላሉ ።

#ለወዳጆችህ እኩል ፊት አሳይ ፣ ለአንዱ ትንሽ ለሌላው ብዙ ነገር አታድርግ። ፍቅር አነሰብኝ የሚለው ጠላትህ ይሆናልና ።

ቢቻልህ እስከ ሞት ድረስ ወዳጅ ሁን ። #ሰዎች ከተንሸራተቱብህ ግን ዛሬ ባገኘኸው ሰው ደስ ይበልህ ።

#እግዚአብሔር ከሌለበት ወዳጅነት እግዚአብሔር ያለበት በረሃ የተሻለ ነው ። ስሜትህን ሁሉ አትግለጥ ። ሁሉ በልቡ ይንቅሃል ፣ ወይም እንደ እብድ ያይሃል ።

#ከልክ በላይም ድብቅ አትሁን ። አንዳንድ ምሥጢር ሲገለጥ የነፋስ እርግዝና ነው ። ነፋስ ሲያረግዙት ያስጨንቃል ፣ ሲወለድ ግን አይጨበጥም ። #በሆንከው ደስ ይበልህ ። ዕድገትህን ኑሮህን ቀባብተህ አታቅርብ ።

እንደውም ተደስተህ ተርከው ። የራቀህን ወዳጅ ምክንያቱን ባወቅሁት አትበል ። እርሱ የጨረሰበት ምክንያት አንተን ቂም ያስጀምርሃልና ። ደንበኛ እንኳ ሲሄድ አመስግኖ ነው ። ይህ ከደንበኛ ያነሰ ነውና ተወዉ ።

#የበታችነት ከሚሰማቸው ሰዎች ጋር አትዋል ። ምልክታቸው የበላይነት ስሜት ይሰማቸዋል ። ዓለም እየታመሰ ያለው በእነዚህ ሰዎች ነው ። ዘሬ ፣ ክብሬ ፣ ስሜ የሚሉ እነዚህ ሰዎች ናቸው ።

#ጓደኛ አታብዛ መከራህ እንዳይበዛ !!



እግዚአብሔር የሚስፈልገን ጓደኛ ይስጠን