ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#አቡነ_በኵረ_ድንግል

የአቡነ ብፁዐ አምላክ ረድእ የነበሩ ሲሆን እርሳቸውም ካረፉ በኋላ ተመርጠው በደብረ ምዕዋን ገዳም ላይ አበ ምኔት ሆነው ተሾመው ብዙ አገልግለዋል" ጻድቁ በምድረ ኤርትራ በምንኩስና እና በብሕትውና ጸንተው ለትልቅ ሰማያዊ ክብር የበቁ ታላቅ ጻድቅ ናቸው። በዓለ ዕረፍታቸው ሰኔ 9 ነው።

የአቡነ በኵረ ድንግል፦ አባታቸው ማርቆስ እናታቸው እግዚእ ክብራ የሚባሉ ሲሆን ጻድቁ ገና በእናታቸው ማሕፀን ሳሉ ብዙ ተኣምራት ይሠሩ ነበር" ሲወለዱም የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ከነልጇ (ምስለ ፍቁር ወልዳ) በልባቸው ላይ ተሥላ ተገኝታለች" በማሕፃን ሳሉ ተመርጠዋልና በአኵሱም ሲወለዱ እንደሌሎቹ ቅዱሳን አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ›› ብለው ስመ ሥላሴን ጠርተው አመሰገኑ። በዚያ የነበሩና ይህንን የተመለከቱ ሰዎችም ባዩትና በሰሙት ነገር እጅግ ተደነቁ።

በ40ኛው ቀናቸውም በጥምቀት የሥላሴን ልጅነት እንዲቀበሉ ወላጆቻቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲወስዷቸው በወቅቱ የነበሩት ጳጳሱ አቡነ ሰላማ ሕፃኑ ትልቅ መነኵሴና የአቡነ ብፁዐ አምላክ ደቀ መዝሙር እንደሚሆን ተገልጾላቸው ትንቢት ተናገሩ። ዳግመኛም ጳጳሱ ቅብዓ ሜሮን ሊቀቡት ሲሉ ሥዕለ ማርያም ከነልጇ በሕፃኑ ደረት ላይ ተሥላ አይተዋት ደነገጡ ወዲያውም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ተገልጸ ሳይፈሩ ሥርዓተ ጥምቀቱን እንዲፈጽሙ አዘዛቸው ዳግመኛም ..… "ስሙን በኵረ ድንግል አለው ትርጉሙም በልቡ ላይ ያየኸው ሥዕል ነው" ብሎ ነገራቸው" ሕፃኑም ከተጠመቀ በኋላ እመቤታችን ከነልጇ ጋር ተገልጻ በትእምርተ መስቀል ባረከችው ያ ትእምርተ መስቀልም ዳግመኛ በሰውነታቸው ላይ ተሳለ።

ከዚህም በኋላ አቡነ በኵረ ድንግል አድገው ቤተሰቦቻቸውን እየረዱ በእረኝነት እያገለገሉ በመልካም አስተዳደግ አደጉ" ዕድሜአቸው ለትምህርት እንደደረሰ ወላጆቻቸው ለንቡረ እድ ዮፍታሔ ሰጧቸውና አስተማሯቸው። ከቋንቋዎች ግእዝ፣ ዐረብ ዕብራይስጥ፣ ጽርዕ እና ሮማይስጥ ተማሩ፤ ብሉይንና ሐዲስን እንዲሁም ቅዱሳት መጻሕፍትን ሁሉ አጠናቀው ተማሩ። ቅኔ ድጓ ጾመ ድጓ እና የቅዱስ ያሬድን ዜማዎችም በሚገባ አጠኑ። ትምህርታቸውንም ከጨረሱ በኋላ መምህራቸው ወደ ሊቀ ጳጳስ ወሰዱአቸው በልባቸው ያለች የእመቤታችን ሥዕልም ለጳጳሱ ተገልጣ "ይህ የምወደው ልጄ ስለሆነ በልቡ ተሳልሁ ስለዚህ ዲቁና ቅስና ስጠው፣ ኤጲስ ቆጵስነትም ሹመው" አለቻቸው። ጳጳሱም ባዩትና በሰሙት ነገር ተደንቀው ተነሥተው እንደተባሉት በሦስቱ መዕረግ ሾሟቸው። ከሹመታቸውም በኋላ በአከባቢው ያሉ ሰዎች አቡነ በኩረ ድንግልን ብርሃን ለብሰው ስላዩዋቸው በጣም ተደነቁ።

ከዚህም በኋላ አቡነ በኵረ ድንግል ለአቅመ አዳም ሲደርሱ ወላጆቻቸው በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ሚስት ሲያጩላቸው አቡነ በኩረ ድንግል ግን "እኔስ ፍላጎቴ በድንግልና መኖር እንጂ ማግባት አይደለም" ብለው ሌሊት ተነሥተው ከቤታቸው ጠፍተው ወደ እግዚአብሔር ቤት ሔደው "አቤቱ ጌታ ሆይ! ከዘለዓለም እሳት ከዲያብሎስ እሥራት ሰውረኝ መጥፎውን ሐሳብ ከእኔ አርቀህ ፍቃድህን እፈጽም ዘንድ እርዳኝ የእመቤታችን ሥዕል ከነልጇ በልቤ አለና ወደ ጋብቻ ዓለም ለመግባት ኅሊናዬ አልፈቀደልኝም ስለዚህ ፍቃድህ ቢሆንልኝ እንደ መላእክት ንጹሕ ሁኜ እንድኖር እለምንሃለሁ፣ አንተ ድኃና ምስኪን የማትንቅ አምላክ መሆንህን ዐውቃለሁና…" እያሉ ጸለዩ። እየጸለዩ ሳለ ክብርት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ገብርኤል አስከትላ ተገለጠችላቸውና "ልጄ ሆይ! ጸሎትህ ተሰምቷልና ወደ ደብረ ዳሞ ወደ አባትህ ሒድ፣ እንዲሁም ደግሞ ወደ ደብረ ናዝሬት ወደ ብፁዐ አምላክ ዘንድ ሒድ የብዙዎች አባትም ትሆናለህ" በማላት ከባረከቻቸው በኋላ ተሰወረች።

ከዚህም በኋላ ጻድቁ መጋቢት 9 ቀን በቦታቸው ሆነው በተመስጦ እየጸለዩ ሳሉ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል በደመና ተሸክሞ ወስዶ ደብረ ዳሞ የቅዱሳን ማረፍያ ቦታ አደረሳቸው። እመቤታችን እንደነገረቻቸው በገዳሙ አስቀድማ እንደነገረቻቸው ለረጅም ዓመታት በትሕትና ካገለገሉ በኋላ ወደ አባታቸው ወደ አቡነ ብፁዐ አምላክ ከረጅም ጉዞ በኋላ መጡ። አቡነ ብፁዐ አምላክም አስቀድመው መምጣታቸውን ያውቁ ነበርና አሁን ሲያገኗቸው እግዚአብሔርን አመስግነው በታላቅ ደስታና ትሕትና ተቀበሏቸው።

በገዳማቸውም በትሕትና እያገለገለ ከቆዩ በኋላ አንድ ቀን አቡነ ብፁዐ አምላክ "ዛሬ በእጅህ ቍርባን እንድንቀበል አንተ ቀድስ" አሏቸው። አቡነ በኩረ ድንግልም ቅዳሴ ገብተው አሐዱ አብ ቅዱስ… ብለው ሲጀምሩ ከመሬት ወደላይ 5 ሜትር ያህል ከፍ ብለው ታዩ፤ ይኽንንም አይተው አቡነ ብፁዐ አምላክ በጣም ተደንቀው እግዚአብሔርን አመሰገኑ። አቡነ በኵረ ድንግልም በእንዲህ ያለ ሕይወት አባታቸውን አቡነ ብፁዐ አምላክን ካገለገሉ በኋላ አቡነ ብፁዐ አምላክ ታኅሣሥ 9 ቀን የገዳማት መነኰሳትን ሰብስበው "ዛሬ ለሁላችሁ መሪ የሚሆን ትሑትና ደግ መምህር እሰጣችኋለሁ ከእኔ በታች እርሳቸውን ስሟቸው ታዘዙአቸውም" ብለው ነገሯቸው።

ዳግመኛም አባታችን አቡነ ብፁዐ አምላክ የዕረፍታቸው ጊዜ ሲደርስ የገዳሙን መነኰሳት ሰብስበው ከእርሳቸው በኋላ አባት እንዲሆኗቸው አቡነ በኵረ ድንግልን እጃቸውን ጭነው ባርከው ሾሟቸው። ከዚህም በኋላ አቡነ በኵረ ድንግል በጾም በጸሎት በስግደት ለገዳሙና በገዳሙ ለሚኖሩ መነኰሳት ሁሉ በትሕትና እያገለገሉ በታላቅ ተጋድሎ ኖሩ። የገዳሙ መነኰሳትም በጣም ወደዷቸው። ተጋድሏቸውንና አገልግሎታቸውንም በፈጸሙ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአቡነ በኵረ ድንግል እንዲህ የሚል ቃልኪዳን ገባላቸው።

"በስምህ ዝክር የሚዘክር ስምህን የሚጠራ በዕረፍትህ ቀን የታመሙትንና የታሰሩትን የጎበኘ በስምህ የተራበ ያበላ ያጠጣ የታረዘ ያለበሰ የልጁን ስም በስምህ የጠራ ይህን ሁሉ ያደረገውን እምረዋለሁ ክፉም አይነካውም፤ በደብረ ምዕዋን በአባትህ በብፁዐ አምላክ ቦታ በአንተም ቦታ የተቀበረ በቦታው ቅዱስ ቍርባን የተቀበለ ክፉ አያገኘውም፣ እምረዋለሁ፣ ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌምም አስገበዋለሁ ብሔረ ሕያዋንና ብሔረ ብፁዓንንም አወርሰዋለሁ…" የሚሉ ታላላቅ የምሕረት ኪዳናትን ከእግዚአብሔር ከተቀበሉ በኋላ ሰኔ 9 ቀን ትንሽ የራስ ምታት ሕመም ጀመራቸው። የገዳሙ መነኰሳትና ሌሎቹም ታላላቅ ቅዱሳን አባቶች እንደእነ አቡነ ዮሐንስ ዘደብረ ቢዘን ያሉት እንደየ ደረጃቸው ከያሉበት ተሰበሰቡ። በዚህም ጊዜ ሥሉስ ቅዱስ ተገልጸውላቸው ድጋሚ ቃልኪዳን ገብተውላቸው አረጋጓቸውና ቅድስት ነፍሳቸው ከሥጋቸው ተለየች።

አባታችንም ካዐረፉ በኋላ በደብረ ምዕዋን ቅድስት ሥላሴ ደብረ ናዝሬት ከአባታቸው ከአቡነ ብፁዐ ኣምላክ ጋር ተቀበሩ። የአቡነ ብፁዕ አምላክ እና የአቡነ በኩረ ድንግል ገዳም ደቀ መሐሪ ጎደይቲ አካባቢ ይኛል። እነርሰም ካረፉ በኋላ እየተገለጡ በጠበላቸው አጋንንት ያደሩባቸውን ሰዎች ሁለ እየፈወሱ፣ በመቃብራቸው አፈር ሙት እያስነሡ የተለያዩ ድንቅ ድንቅ ተኣምራት ሲሠሩ ታይተዋል። የሠሯቸውም ተዓምራት ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደለም። ከአባታችን ከአቡነ በኩረ ድንግል እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን። በጸሎታቸው ይማረን። ምንጭ፦ በእንተ ቅዱሳን ኅሩያን።