ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#ነሐሴ_21

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሃያ አንድ በዚህች ቀን #ቅድስት_ኄራኒ ሰማዕትነት የተቀበለችበት፣ #የንግሥተ_ሳባ እና #ንግሥት_ዕሌኒ የተወለዱበት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ኄራኒ_ሰማዕት

ነሐሴ ሃያ አንድ በዚህች ቀን ቅድስት ኄራኒ የስሟ ትርጓሜ ሰላም ፍቅር የሆነ ለንጉሥ ሉክያኖስ ልጁ ምስክር ሁና ሞተች ። እርሱም አባቷ ያማረ አዳራሽን ሠራላት መስኮቶቹንም ስምንት አደረገ ቅጽሩንም በዙሪያው ዐሥራ ሁለት አደረገ ማዕድንም ሠራላት። የወርቅና የብር የሆኑ ሣህኖችና ጽዋዎችንም አዘጋጀላት የሚያስተምራትም አንድ ሽማግሌ ሰው አደረገላት።

ከዚህም በኋላ በዚያች አዳራሽ ውስጥ አኖራት የሚያገለግሏትም ሦስት አገልጋዮችን በእርሷ ዘንድ አድርጎ ደጃፎችን በላይዋ ዘጋ መምህርዋም በውጭ ሆኖ ያስተምራታል።

ዕድሜዋም ሰባት ዓመት ሆናትና ያን ጊዜ ራእይን አየች በማዕዷ ላይ ርግብ ስትቀመጥ በአፍዋም የወይራ ቅጠል አለ ። በማዕዱም ላይ አኖረችው ሁለተኛም ንስር መጣ ከእርሱ ጋር አክሊል አለ በማዕዷ ላይም አኖረው ። ደግሞ ቊራ መጣ ከእርሱ ጋራ ከይሲ አለ በማዕዷ ላይም አኖረው ። ደነገጠችም ለመምህርዋም ነገረችው እርሱም እንዲህ ብሎ ተረጐመላት ርግብ የሕግ ምልክት ናት የዘይቱም ቅጠል የክርስትና ጥምቀት ናት፣ ንስርም ድል አድራጊነት ነው አክሊልም ለሰማዕታት የሚሰጥ ክብራቸው ነው ። ቊራ የንጉሥ ምሳሌ ነው ከይሲውም መከራ ነው አንቺም የክብር ባለቤት በሆነ #ክርስቶስ ስለ ስሙ ትጋደዪ ዘንድ አለሽ አላት።

ከዚህም በኋላ ይጐበኛት ዘንድ አባቷ ወደርሷ መጣና ልጄ ሆይ ከመንግሥት ታላላቆች ለአንዱ ላጋባሽ እኔ እሻለሁ አላት እርሷ ግን ከልቡናዬ እስተምመክር ሦስት ቀኖችን አባቴ ሆይ ታገሠኝ ብላ መለሰችለት።

አባቷም በሔደ ጊዜ በጣዖታቱ መሠዊያ ፊት ተነሥታ ቆመችና ስለጋብቻ የሚሆነውን ይገልጡላት ዘንድ ለመነቻቸው እነርሱም ምንም ምን ከቶ አልመለሱላትም።

ከዚህም በኋላ ዐይኖቿን ወደ ሰማይ አቅንታ የክርስቲያን አምላክ ሆይ ወደምትፈቅደው ምራኝ ብላ ጸለየች ያን ጊዜ የ #እግዚአብሔር መልአክ መጥቶ እንዲህ አላት። እነሆ ነገ ከጳውሎስ ደቀ መዛመርት አንዱ ወደዚች አገር ይመጣል እርሱም የክርስትና ጥምቀትን ያጠምቅሻል።

በማግሥቱም ያ ሐዋርያ መጥቶ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃት። በሦስተኛውም ቀን እንደቀጠረቻቸው አባቷና እናቷ መጡ እርሷም እንዲህ አለቻቸው እኔ ሰማይና ምድርን በፈጠረ በሕያው #እግዚአብሔር ልጅ በ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ የማምን ክርስቲያን ነኝ።

አባቷም ሰምቶ በእርሷ ላይ ተቆጣ ወደ ከተማው መካከልም አውጥተው በጐዳና ላይ እንዲጥሏትና በፈረሶች እግር እንዲአስረግጧት አዘዘ። ወታደሮችም ንጉሥ አባቷ እንዳዘዘ አደረጉባት ግን ምንም ምን ክፉ ነገር ከቶ አልደረሰባትም። ይህንንም ድንቅ ሥራ አባቷና እናቷ በአዩ ጊዜ የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመኑ መንግሥታቸውንም ትተው ለርሷ ወደተሠራው አዳራሽ ሔደው በውስጡ ተቀመጡ።

በጐረቤታቸው ያለ ንጉሥም ዜናቸውን በሰማ ጊዜ ወደ ርሳቸው መጥቶ ወደ መንግሥታቸው እንዲመለሱ ተናገራቸው። እነርሱም አልፈለጉም እርሱም መንግሥታቸውን ያዘ ቅድስት ኄራኒንም ይዞ አሠቃያት ከዚያም አንበሶችን፣ እባቦችን በላይዋ ሰደደ ምንም አልቀረቧትም ። ሁለተኛም በመጋዝ መገዛት በአንገቷም ውስጥ ታላቅ ደንጊያ አሥሮ ከባሕር ጣላት የክብር ባለቤት #ጌታችንም ከዚህ ሁሉ አድኖ ያለ ጥፋት በጤና አሥነሣት።

ከዚህም በኋላ እርሷን ያጠመቀ ሐዋርያን አባቷ ጠርቶ ከቤተሰቦቹ ሁሉ ጋር ተጠመቀ ቊጥራቸውም ሦስት መቶ ሆነ ከዘመዶቹና ከሀገር ሰዎችም ብዙዎች ተጠመቁ።

ከዚህም በኋላ ከሀዲው ንጉሥ ኑማርያኖስ የቅድስት ኄራኒን ዜናዋን ሰማ ወደርሱም አስቀርቦ ቀላኒካ ወደሚባል አገር ወሰዳት ። በዚያም ጽኑ ሥቃይን አሠቃያት በበሬ አምሳል በተሠራ የነሐስ በርሜል ውስጥ ዘጋባት የክብር ባለቤት #ጌታችንም ያንን በሬ ሰብሮ ቅድስት ኄራኒን ያለ ጥፋት በጤና አወጣት።

ከዚህም በኋላ ኑማርያኖስ ሙቶ በርሱ ፈንታ ሳፎር ነገሠ እርሱም የቅድስት ኄራኒን ዜና በሰማ ጊዜ ወደ ርሱ አስቀርቦ በእጁ ውስጥ በአለ በታላቅ ጦር ወጋትና ነፍሷን አሳለፈች የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ከሞተ አስነሣት።

ንጉሥ ሳፎርም በአየ ጊዜ እጅግ አደነቀ ሰገደላትም በ #ጌታችን_ኢየሱስም አመነ ። ከእርሱም ጋራ ከሀገር ሰዎች ብዙ ወገኖች አመኑ ቁጥራቸውም ሠላሳ አንድ ሺህ ሆነ።

ከዚህም በኋላ በዚያች አዳራሽ ውስጥ አባቷና እናቷ አረፉ እርሷን ግን አምላካዊት ኃይል ተሸከመቻት ወደ ኤፌሶን አገርም አድርሳት በዚያ ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራቶችን አደረገች።

በፋርስ ነገሥታት በመቄዶንያ፣ በቀላኒካና በቊስጥንጥንያ ነገሥታት ፊት በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ከመሰከረች በኋላ ወደ ወደደችው #ክርስቶስ ሔደች ። የድልና የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበለች ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ንግሥተ_ሳባ

ይህቺ ኢትዮዽያዊት ንግሥት ከ3 ሺ ዘመናት በፊት የነበረች ደግ እናት ናት። በሥጋዊ ደረጃ ከታንዛንያ እስከ የመን ያስተዳደረች ስመ ጥር ንግሥት ስትሆን በመንፈሳዊው ደረጃ ደግሞ #እግዚአብሔር የቀባውን ሰው ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዛለች።

ከዚያውም አምልኮተ #እግዚአብሔርን ከሥርዓተ ኦሪት ጋር አምጥታለች። ድንግልናዋን ለታላቁ ንጉሥ ሰሎሞን ሰጥታ ቀዳማዊ ምኒልክን ወልዳለች።

ይህቺ ንግሥት በጌታችን (በፈጣሪ) አንደበትም ተመስግናለች። (ማቴ. 12፥42) በስምም ሳባ፣ አዜብና ማክዳ ተብላ ትታወቃለች። ዛሬ ዕለተ ልደቷ ነው::

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ዕሌኒ_ንግሥት

በዚህች ቀን የጻድቅ ንጉሥ ቈስጠንጢኖስ እናት ቅድስት ዕሌኒ ተወለደች። ይቺም ቅድስት በፊት የአንድ ነጋዴ ሰው ሚስት ነበረች እርሱም በነገረ ሠሪ ንጽሕት ሁና ሳለች ወደ ባሕር ጣላት። የክብር ባለቤት በሆነ በ #ጌታችን ፈቃድም ሮሐ ከሚባል አገር ደርሳ የበራንጥያ ንጉሥ ቊንስጣ አገኛት። ውበቷንና ደም ግባቷንም አይቶ አገባት። ለክርስቲያን ነገሥታት መጀመሪያቸው የሆነውን ቈስጠንጢኖስን ወለደችው ምግባርንና ሃይማኖትን በማስተማር በመልካም አሳደገችው።

ልጇም በነገሠ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ሒደሽ የክብር ባለቤት የሆነ የ #ክርስቶስን_መስቀል ግለጪ የከበሩ ቦታዎችንም ሥሪ የሚላትን በሕልሟ አይታ እንዴት እንዳየች ይህን ለልጇ ነገረችው እርሱም ከብዙ ሠራዊት ጋራ ሰደዳት። በደረሰችም ጊዜ የክብር ባለቤት ስለሆነ ስለ #ጌታችን_መስቀል መረመረች አዳኝ የሆነ #መስቀሉንም ሁለቱ ወንበዴዎች ከተሰቀሉባቸው መስቀሎች ጋራ አገኘችው። የክብር ባለቤት የ #ክርስቶስ_መስቀል የትኛው እንደሆነ ታውቅ ዘንድ በወደደች ጊዜ ከራሱ በላይ ይህ የናዝሬቱ #ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው የሚል በእንጨት የተቀረጸበት ጽሑፍ ያለው እንደሆነ የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ ቅዱስ መቃርስ ነገራት።

ከዚህ በኋላ ከእርሱ ምልክት ታይ ዘንድ ፈለገች የሞተ ሰውም አግኝታ መስቀሎችን በበድኑ ላይ አኖረች አልተነሣም። ከዚህ በኋላ ሦስተኛውን #መስቀል በላዩ አኖረች። ያን ጊዜ ምውት ተነሣ ሃይማኖቷም ጸና ደስታዋም በዛ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_21_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁵ ስለ ደናግልም የጌታ ትእዛዝ የለኝም፥ ነገር ግን የታመንሁ እሆን ዘንድ ከጌታ ምሕረትን የተቀበልሁ እንደ መሆኔ ምክር እመክራለሁ።
²⁶ እንግዲህ ስለ አሁኑ ችግር ይህ መልካም ይመስለኛል፤ ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው።
²⁷ በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ።
²⁸ ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል፥ እኔም እራራላችሁ ነበር።
²⁹ ዳሩ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፥
³⁰ የሚያለቅሱም እንደማያለቅሱ፥ ደስ የሚላቸውም ደስ እንደማይላቸው፥
³¹ የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና።
³² ነገር ግን ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤
³³ ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንዲያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፥ ልቡም ተከፍሎአል።
³⁴ ያልተጋባች ሴትና ድንግል በሥጋም በነፍስም እንዲቀደሱ የጌታን ነገር ያስባሉ፤ የተጋባች ግን ባልዋን እንዴት ደስ እንድታሰኘው የዓለምን ነገር ታስባለች።
³⁵ ይህንም ለራሳችሁ ጥቅም እላለሁ፤ በአገባብ እንድትኖሩ ሳትባክኑም በጌታ እንድትጸኑ ነው እንጂ ላጠምዳችሁ ብዬ አይደለም።
³⁶ ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ።
³⁷ ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ግድ የለበትም፥ የወደደውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል፤ ድንግልናውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና፥ መልካም አደረገ።
³⁸ እንዲሁም ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ ያላገባም የተሻለ አደረገ።
³⁹ ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ቢሞት ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነጻነት አላት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ዮሐንስ 1
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² በእኛ ስለሚኖርና ከእኛ ጋር ለዘላለም ስለሚሆን እውነት፥ እኔ ሽማግሌው በእውነት ለምወዳቸውና እኔ ብቻ ሳልሆን እውነትን የሚያውቁ ሁሉ ደግሞ ለሚወዱአቸው ለተመረጠች እመቤትና ለልጆችዋ፤
³ ከእግዚአብሔር አብና ከአብ ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም በእውነትና በፍቅር ከእኛ ጋር ይሆናሉ።
⁴ ትእዛዝን ከአብ እንደ ተቀበልን ከልጆችሽ በእውነት የሚሄዱ አንዳንዶችን ስለ አገኘኋቸው እጅግ ደስ ብሎኛል።
⁵ አሁንም፥ እመቤት ሆይ፥ እርስ በርሳችን እንድንዋደድ እለምንሻለሁ፤ ይህች ከመጀመሪያ በእኛ ዘንድ የነበረች ትእዛዝ ናት እንጂ አዲስ ትእዛዝን እንደምጽፍልሽ አይደለም።
⁶ እንደ ትእዛዛቱም እንሄድ ዘንድ ይህ ፍቅር ነው፤ ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁ፥ በእርስዋ ትሄዱ ዘንድ ትእዛዙ ይህች ናት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 16
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹³ በሰንበት ቀንም ከከተማው በር ውጭ የጸሎት ስፍራ በዚያ መሆኑን ስላሰብን ወደ ወንዝ አጠገብ ወጣን፤ ተቀምጠንም ለተሰበሰቡት ሴቶች ተናገርን።
¹⁴ ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት።
¹⁵ እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ፦ በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፥ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን።
¹⁶ ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን።
¹⁷ እርስዋ ጳውሎስንና እኛን እየተከተለች፦ የመዳንን መንገድ የሚነግሩአችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑል አምላክ ባሪያዎች ናቸው ብላ ትጮኽ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_21_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"አዋልደ ንግሥት ለክብርከ። ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኊብርት"። መዝ 44፥9።
“የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው፤ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።” መዝ 44፥9።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_21_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 25
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች።
² ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ።
³ ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤
⁴ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ።
⁵ ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ።
⁶ እኩል ሌሊትም ሲሆን፦ እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ።
⁷ በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ።
⁸ ሰነፎቹም ልባሞቹን፦ መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው።
⁹ ልባሞቹ ግን መልሰው፦ ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው።
¹⁰ ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ።
¹¹ በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና፦ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን አሉ።
¹² እርሱ ግን መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም አለ።
¹³ ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።
¹⁴ ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታች_የማርያም ቅዳሴ ነው፡፡ መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️