ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
4.97K subscribers
919 photos
5 videos
33 files
239 links
የዲ.ን ሄኖክ ሀይሌን ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#ነሐሴ_11

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ አንድ በዚህች ቀን #አባ_ሞይስስ አረፈ፣ #የቅዱስ_ፋሲለደስ_ማኅበርተኞች በሰማዕትነት ሞቱ፣ #ቅዱስ_አብጥልማዎስ በሰማዕትነት ሞተ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ኤጲስቆጶስ_አባ_ሞይስስ

ነሐሴ ዐሥራ አንድ በዚህች ቀን የአውሲም አገር ኤጲስቆጶስ አባ ሞይስስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ከታናሽነቱ ጀምሮ ንጹሕ ድንግልም ነበረ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትንም ሁሉ ተምሮ ዲቁና ተሾመ። ከዚህም በኋላ ወጥቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ገባ። በአንድ ጻድቅ ሰው ዘንድም መነኰሰ በዚያም እያገለገለ በጠባብዋ መንገድም ተጠምዶ ያለመብልና መጠጥ ያለእንቅልፍም እየተጋደለ ዐሥራ ስምንት ዓመት ኖረ።

ከብዙ ፍቅርና ትሕትና ጋር ዘወትር በጾምና በጸሎት ይተጋ ነበር። ትሩፋቱም በበዛ ጊዜ ከአባ ገሞስ በኋላ በአውሲም ከተማ ኤጲስቆጶስ ይሆን ዘንድ #እግዚአብሔር መረጠው። ይህም አባ ሞይስስ በተሾመ ጊዜ ትሩፋት መሥራትን አብዝቶ ጨመረ ስለ እነርሱም በጸሎት እየተጋ መንጋዎቹን ነጣቂዎች ከሆኑ ከዲያብሎስ ተኲላዎች ጠበቀ።

በሕይወቱም ዘመን ሁሉ ከዚህ ከኃላፊው ዓለም ገንዘብ የሚሰበስብ አልነበረም። አባ ሚካኤልም በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜና ደሙ ሳይፈስ ሰማዕት በሆነ ጊዜ ይህ አባ ሞይስስ በእሥር ቤት ከእርሱ ጋር ነበር ብዙ ስለገረፉት እግሮቹንም ለረጅም ጊዜ በእግር ብረት አሥረው ስለ አሠቃዩት ብዙ መከራ ደረሰበት።

በዚህ አባት ሞይስስ እጅም #እግዚአብሔር ብዙዎች ድንቆችንና ተአምራቶችን አደረገ የሚያውቁትም በተአምራቶቹ ደግነቱንና ትሩፋቱን ተረዱ። ዳግመኛም ሀብተ ትንቢት የተሰጠው ከመሆኑም በፊት ብዙ ነገርን ተናገረ እንደተናገረውም ይሆን ነበር። የምስር ኤጲስቆጶስ ስለሆነው ስለ አባ ቴዎድሮስ ከሔደበት እንደማይመለስ ትንቢት ተናግሮበት እንዲሁ ተፈጸመበት።

ዳግመኛም ሀብተ ፈውስ ተሰጥቶት ነበር። ብዙዎች ሕሙማንንም ፈወሳቸው። ገድሉንም በመልካም ሽምግልና ፈጸመ። #እግዘአብሔርንም አገልግሎ ጥቂት ታመመ የሚያርፍበትንም ጊዜ አውቆ ሕዝቡን ጠራቸውና ባረካቸው በቀናች ሃይማኖትም ጸንተው እንዲኖሩ አዘዛቸው። ከዚህም በኋላ አረፈ። አለቀሱለትም ለኤጲስቆጶሳትም እንደሚገባ በዝማሬና በማኀሌት በታላቅ ክብር ገንዘው ቀበሩት ከሥጋውም ታላላቅ ተአምራቶች ተገለጡ ለሕሙማንም የሚሆን ፈውስ ተገለጠ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ፋሲለደስ_ማኅበርተኞች

በህች ቀን በአንጾኪያ ከተማ የሠራዊት አለቃ ከነበረው ከቅዱስ ፋሲለደስ ጋራ ሦስት መቶ ሰዎች በማዕትነት ሞቱ።

ከሃዲው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ በሚገዛበት አገር ሁሉ ክርስቶስን ያልካዱትን ምእመናን ማስገደልና ማሳደድ ጀመረ፡፡ ብዙ ሰማዕታትም ወደ ንጉሡ የሰማዕትነት አዳባባይ እየመጡ በ #ጌታችን ስም ደማቸውን አፈሰሱ፡፡ ቅዱስ ፋሲለደስም ሰማዕት ይሆን ዘንድ ወደ #ጌታችን ይጸልይ ጀመር፡፡ በመኝታም ሳለ ቅዱስ ሚካኤል ታዞ ወደ እርሱ መጥቶ ሰላምታ ሰጠውና ‹‹በምድር አለቃ ሆነህ ሆነህ ሁሉን እንደምታዝ በሰማይም የ #ክርስቶስ ወታደሮቹ የሆኑ የሰማዕታት አለቃ ሆነሃልና ደስ ይበልህ›› አለው፡፡ ዳግመኛም ‹‹ወደ #ጌታህ ዘንድ አደርስህ ዘንድ ተነሥ›› አለውና በክንፎቹ ተሸክሞ ወደ ሰማይ አሳረገውና በ #ጌታችን ፊት አቆመው፡፡ #ጌታችንም ለቅዱስ ፋሲለደስ ሰላምታ ከሰጠው በኋላ ስለ ስሙ ይቀበል ዘንድ ስላለው መከራና በሰማይም ስለሚያገኘው ክብር ነገረው፡፡ ሰማዕታት ይሆኑ ያላቸውንም ሁሉን ስማቸውን እየጠራ ነገረው፡፡ አባድርና እኅቱ ኢራኒ፣ የህርማኖስ ልጅ ፊቅጦር፣ ምሥራቃዊ ቴዎድሮስ፣ ገላውዴዮስ፣ አራቱም ልጆቹ አውሳብዮስና መቃርስ እንዲሁም ሁለቱ ሴቶች ልጆቹ፣ የንጉሡ ልጅ ዮስጦስና አቦሊ ሚስቱም ታውክልያ… እነዚህንና ሌሎቹንም ሁሉ ስማቸውን እየጠራ #ጌታችን ሰማዕት እንደሚሆኑ ለቅዱስ ፋሲለደስ ነገረው፡፡ እርሱ ግን ከብዙ ተጋድሎ በኋላ ሰማዕት እንደሚሆን ነገረው፡፡ በሌሎቹ ሰማዕታትም ሆነ በእርሱ ላይ የሚደረስበትን መከራ እና በኋላም የሚያገኙትን ክብር ሁሉ በዝርዝር ነገረው፡፡ ብዙ ቃልኪዳንም ገባለት፡፡ የሰማዕታትንና የቅዱሳንን መኖሪያ ካሳየው በኋላ ሰማዕትነቱን ሲፈጽም የሚያገኘውን ክብር መሆኑን ነግሮት በገነት ውኃ በምለአኩ እጅ እንዲጠመቅ ካደረገው በኋላ ወደ ምድር መለሰው፡፡ ከዚህም በኋላ ንጉሡ ብዙዎቹን ታላላቅ ሰማዕታት እጅግ አሠቃይቶ ሁሉንም በየተራ ገደላቸው፡፡ ቅዱስ ፋሲለደስን ግን አምስት ከተማዎች ወዳሉበት አፍሪካ ላኩት፡፡ በዚያም ብዙ እጅግ አሠቃቂ ሥቃዮችን አደረሱበት፡፡ ከእርሱ ጋር ያመኑ ከ7 ሺህ በላይ ክርስቲያኖችን ሰየፏቸው፡፡ ቅዱስ ፋሲለደስንም ሰውነቱን በመንኰራኩር ፈጭተው በመጋዝ ሰነጣጥቀው ገደሉት፡፡ ነገር ግን #ጌታችን ከሞት አስነሣው፡፡ እጅግ ብዙ አሕዛብም በአምላከ ፋሲለደስ አመኑ፡፡ ጣዖቶቻቸውንም ረገሙባቸው፡፡ በዚህም ወቅት 14ሺህ 737 ሰዎችን አንገታቸውን በሰይፍ ቆረጧቸው፡፡ ሰማዕትነታቸውንም ፈጸሙ፡፡ ቅዱስ ፋሲለደስን ዳግመኛ በምጣድ ላይ አስተኝተው እሳት አነደደዱበት፡፡ በተራራ ላይ ጥልቅ ጉድጓድ ቆፍረው በዚያ ቀበሩት፡፡ አሁንም #ጌታችን ከሞት አስነሥቶት በመኰንኑ ፊት እንዲቆም አደረገው፡፡ ንጉሡንም ‹‹አምላኬ ፍጹም ጤነኛ አድርጎ አስነሥቶኛልና እፈር፣ የረከሱ ጣዖቶችህም ይፈሩ›› አለው፡፡ ሕዝቡም ይህን ተአምር ባዩ ጊዜ በ #ጌታችን አምነው አንገታቸውን ተሰይፈው በሰማዕትነት ሞቱ፡፡ ቁጥራቸውም 2300 ነበሩ፡፡ ቅዱስ ፋሲለደስንም ደግመኛ ሰውነቱን በመንኰራኩር ከፈጩት በኋላ በብረት ምጣድ ላይ አስተኝተው ከሥሩ እሳት አነደዱበት፡፡ #ጌታችንም ከቁስሉ ፈውሶት ትልቅ ቃልኪዳን ሰጠውና ሰማዕትነቱን በትዕግስት እንዲፈጽም ነገረው፡፡ ንጉሡም አማካሪዎቹን ምን ማድረግ እንዳለበት ሲያማክራቸው ‹‹ፋሲለደስን ምንም ብናሠቃየው ሊሞት አልቻለም በእርሱም ምክንያት የሀገሩ ሰዎች ሁሉ አልቀዋልና ራሱን ቆርጠን ብንጥለው ይሻላል›› አሉት፡፡ መኰንኑም ራሱን እንዲቆርጡት አዘዘና ቅዱስ ፋሲለደስ መስከረም 11 ቀን ሰማዕትነቱን ፈጸመ፡፡ የቅዱስ ፋሲለደስ ማኅበርተኞች ቁጥራቸው 2 ሺህ ሰባት ሰዎች መስከረም 7 ቀን ዐረፉ፡፡ እንዲሁም መስከረም 9 ቀን ቁጥራቸው 14 ሺህ 737 ማኅበርተኞቹ በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ የሰማዕታቱ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አብጥልማዎስ_ሰማዕት

በዚችም ቀን ከላይኛው ግብጽ ከመኑፍ ከተማ ቅዱስ አብጥልማዎስ በሰማዕትነት ሞተ። ይህንንም ቅዱስ ክርስቲያን እንደሆነ በመኰንኑ ዘንድ ነገር ሠሩበት።

መኰንኑም በአስቀረበው ጊዜ በፊቱ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመነ ጽኑዕ የሆነ ሥቃይንም አሠቃይቶ ራሱን በሰይፍ አስቆረጠው የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታቱ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ_11 እና #ከገድላት_አንደበት)
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#ነሐሴ_11_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ቆሮንቶስ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹¹ አሁን ግን ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ወይም ገንዘብን የሚመኝ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካር ወይም ነጣቂ ቢሆን ከእርሱ ጋር እንዳትተባበሩ እጽፍላችኋለሁ፤ እንደነዚህ ካለው ጋር መብል እንኳን አትብሉ።
¹² በውጭ ባሉ ሰዎች ላይ መፍረድ ምን አግዶኝ? በውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ እናንተ አትፈርዱምን?
¹³ በውጭ ባሉቱ ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ዮሐንስ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁴ አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጐበዞች ሆይ፥ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር ክፉውንም ስለ አሸነፋችሁ እጽፍላችኋለሁ።
¹⁵-¹⁶ ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።
¹⁷ ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።
¹⁸ ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ የክርስቶስም ተቃዋሚ ይመጣ ዘንድ እንደ ሰማችሁ አሁን እንኳ ብዙዎች የክርስቶስ ተቃዋሚዎች ተነሥተዋል፤ ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን።
¹⁹ ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 12
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁸ በነጋም ጊዜ፦ ጴጥሮስን ምን አግኝቶት ይሆን? ብለው በጭፍሮች ዘንድ ብዙ ሁከት ሆነ።
¹⁹ ሄሮድስም አስፈልጎ ባጣው ጊዜ ጠባቂዎችን መረመረ ይገድሉአቸውም ዘንድ አዘዘ፤ ከይሁዳም ወደ ቂሣርያ ወርዶ በዚያ ተቀመጠ።
²⁰ ከጢሮስና ከሲዶና ሰዎችም ጋር ተጣልቶ ነበር፤ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ መጡ፥ የንጉሥንም ቢትወደድ ብላስጦስን እሺ አሰኝተው ዕርቅ ለመኑ፥ አገራቸው ከንጉሥ አገር ምግብ ያገኝ ነበረና።
²¹ በተቀጠረ ቀንም ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ በዙፋን ተቀመጠ እነርሱንም ተናገራቸው፤
²² ሕዝቡም፦ የእግዚአብሔር ድምፅ ነው የሰውም አይደለም ብለው ጮኹ።
²³ ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው በትልም ተበልቶ ሞተ።
²⁴ የእግዚአብሔር ቃል ግን ያድግና ይበዛ ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_11_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ህየንተ አበውኪ ተወልዱ ለኪ ደቂቅ። ወትሠይም(ሚ)ዮሙ መላእክተ በኵሉ ምድር። ወይዘክሩ ስመኪ በኵሉ ትውልደ ትውልድ"። መዝ 44፥16-17።
"በአባቶችሽ ፋንታ ልጆች ተወለዱልሽ፥ በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ። ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ፤ ስለዚህ ለዓለምና ለዘላለም። አሕዛብ ይገዙልሃል"። መዝ 44፥16-17።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#ነሐሴ_11_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሉቃስ 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
²⁰ እርሱም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዓይኑን አነሣ እንዲህም አላቸው፦ እናንተ ድሆች ብፁዓን ናችሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ነውና።
²¹ እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ፥ ትጠግባላችሁና። እናንተ አሁን የምታለቅሱ ብፁዓን ናችሁ፥ ትስቃላችሁና።
²² ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ።
²³ እነሆ፥ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና በዚያን ቀን ደስ ይበላችሁ ዝለሉም፤ አባቶቻቸው ነቢያትን እንዲህ ያደርጉባቸው ነበርና።
²⁴ ነገር ግን እናንተ ባለ ጠጎች ወዮላችሁ፥ መጽናናታችሁን ተቀብላችኋልና።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #እመቤታች_የማርያም_ቅዳሴ ነው። መልካም የእመቤታችን የጽንሰት በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️