ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#መስከረም_27

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሃያ ሰባት በዚች ቀን #ቅዱስ_ኤዎስጣቴዎስ ሁለቱ ልጆቹና ሚስቱም በሰማዕትነት አረፉ፣ ያለ ደም ማፍሰስ ሰማዕት የሆነች #ቅድስት_ጤቅላ አረፈች፣ የቀራጮች አለቃ የነበረ #ቅዱስ_አንጢላርዮስ አረፈ፣ የደብረ ጽጌ #አባ_ዮሐንስ አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ኤዎስጣቴዎስ

መስከረም ሃያ ሰባት በዚች ቀን ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ሁለቱ ልጆቹና ሚስቱም በሰማዕትነት አረፉ።

ይህ ቅዱስም ለሮም መንግሥት የጭፍራ አለቆች ከሆኑት ውስጥ ነው የቀድሞ ስሙ ቂዶስ ነው #እግዚአብሔርንም አያውቅም ነበር ግን ብዙ ምጽዋትን በመስጠት ለድኆችና ለችግረኞች ይራራል ስለዚህም ክብር ይግባውና #ጌታችን ድካሙ ከንቱ ሁኖ እንዲቀር አልወደደም።

በአንዲት ቀንም አውሬ ሊያድን ኤዎስጣቴዎስ ወደ ዱር ወጣ እርሱ አዳኝ ነውና ዋልያም አግኝቶ በቀስት ሊነድፈው ወደደ ያን ጊዜም በዋልያው በቀንዶቹ መካከል በ #መስቀል አምሳል #ጌታ ተገለጸለት። የ #መስቀሉም ብርሃን እስከ ደመና ደርሶ ነበር ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም በዚያ ብርሃን ውስጥ ተናገረው ስሙንም አስረዳው ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ወደ ኤጲስቆጶስ ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን እንዲጠመቁ አዘዘው።

ክብር ይግባውና #ጌታችንም ከዚህ በኋላ ችግርና ፈተና እንደሚመጣበት በመጨረሻም ስለ ከበረ ስሙ ምስክር ሁኖ ደሙን አፍስሶ እንደሚሞት አስረዳው። ኤዎስጣቴዎስም ሰምቶ ከተራራው ወርዶ ወደ ቤቱ ሔደ። #ጌታችን ያዘዘውንም ለሚስቱ ነገራት ከዚህም በኋላ ወደ ኤጲስቆጶሱ ሔደው ከልጆቻቸው ጋራ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቁ የቀድሞ ስሙንም ለውጦ ኤዎስጣቴዎስ ተባለ።

ከጥቂት ቀኖች በኋላ በዚያች አገር ታላቅ ችግር መጣ የኤዎስጣቴዎስም ገንዘቡ ሁሉ አልቆ ወንዶችና ሴቶች ባሮቹ ተበተኑ ወደሌላ አገርም ሊሰደድ ወዶ ልጆቹንና ሚስቱን ይዞ በመርከብ ተጫነ። ወደ ወደቡም በደረሱ ጊዜ መርከበኞች የመርከብ ዋጋ ከእርሱ ፈለጉ የሚሰጣቸው የመርከብ ዋጋ ባላገኘ ጊዜ ስለ መርከብ ዋጋ የመርከቡ ሹም ሚስቱን ወሰዳት የአታክልት ጠባቂም አደረጋት።

ከዚያም ኤዎስጣቴዎስ እያዘነና እያለቀሰ ሁለቱን ልጆቹን ይዞ ሔደ ውኃ ወደ መላበትም ወንዝ ደረሰ አንዱንም ልጁን ከእርሱ ጋር ሊአሻግረው ይዞት ገባ አሻግሮትም ከወንዙ ዳር አኖረውና ሁለተኛውን ልጁን ሊአሻግረው ተመለሰ ግን አላገኘውም። ተኵላ ወስዶታልና ያሻገረውንም አንበሳ ነጥቆ ወሰደው ኤዎስጣቴዎስም ከሚስቱና ከልጆቹ ስለ መለየቱ ታላቅ ኀዘንን አዝኖ መሪር ልቅሶን አለቀሰ ምክሩ ታላቅ የሆነ ሥልጣን ያለው #እግዚአብሔር ግን ሁሉንም በየአሉበት ያለ ጥፋት ጠበቃቸው።

ከዚህ በኋላም ኤዎስጣቴዎስ ወደ አንዲት አገር ሒዶ በዚያ የአትክልት ጠባቂ ሁኖ ብዙ ቀኖችን ኖረ። ከእነዚያ ቀኖችም በኋላ የሮም ንጉሥ ሙቶ በርሱ ፈንታ ለኤዎስጣቴዎስ ወዳጁ የሆነ ሰው ነገሠ ኤዎስጣቴዎስንም ፈለገው ግን አላገኘውም ኤዎስጣቴዎስንም ይፈልጉት ዘንድ ወደ ሀገሩ ሁሉ መልእክተኞችን ላከ። ከመልእክተኞችም አንዱ ኤዎስጣቴዎስ ወዳለበት ደርሶ በአታክልቶች ዘንድ አግኝቶት አወቀው እርስ በርሳቸውም ተሳሳሙ ከዚህም በኋላ ወደ ንጉሡ ወሰደው ንጉሡም በበጎ አቀባበል ተቀብሎ የጭፍራ አለቃ አድርጎ ሾመው።

ከዚህም በኋላ ንጉሡ ከሚገዛቸው አገሮች ሁሉ ወጣቶችን ሰብስቦ የጦር ሠራዊት ጭፍራ ያዘጋጅ ዘንድ ኤዎስጣቴዎስን አዘዘው እነዚያ ተኵላና አንበሳ የወሰዳቸው የኤዎስጣቴዎስ ሁለት ልጆቹ በአንዲት አገር አድገዋል። ግን እርስበርሳቸው አይተዋወቁም ወጣቶችንም የሚመለምሉ መልምለው ወደ አባታቸው ኤዎስጣቴዎስ አቀረቧቸው እርሱም ሳያውቃቸው የመዛግብት ቤት ጠባቂዎች አደረጋቸው።

እናታቸውንም አረማዊ የሆነ የመርከቡ ሹም በወሰዳት ጊዜ የአታክልቶች ጠባቂ አደረጋት። #እግዚአብሔር ከክፉ ነገር ሁሉ በንጽሕና ጠብቋታልና እነዚያ ሁለቱ ልጆቿ እርሷ ወዳለችበት የአታክልት ቦታ ደረሱ እነርሱም የልጅነታቸውን ነገር ይነጋገሩ ነበር። እርሷም ሰምታ ልጆቿ እንደሆኑ አውቃ ያን ጊዜ ጠራቻቸውና እርሷ እናታቸው እንደ ሆነች ነገረቻቸው አንገት ላንገት ተያይዘው አለቀሱና እርስ በርሳቸው ተሳሳሙ ወደ ኤዎስጣቴዎስም ሔደው ከእነርሱ የሆነውን ሁሉ ነገሩት። እርሱም እርሷ ሚስቱ እንደሆነች እነዚያም ልጆቹ እንደ ሆኑ አወቀ እርስ በርሳቸውም ተሳሳሙ ታላቅ ደስታም ደስ አላቸው ምስጉን የሆነ #እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።

ከዚህም በኋላ በእነርሱ ላይ ስለ አደረገው በጎ ነገር እያደነቁና #እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በአንድነት በአንድ ቦታ ኖሩ።

ኤዎስጣቴዎስንም የሚወደው ንጉሥ በሞተ ጊዜ በእርሱ ፈንታ ጣዖት የሚያመልክ ሌላ ንጉሥ ነገሠ። ኤዎስጣቴዎስንም ጠርቶ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ወደርሱ አቅርቦ ለአማልክት ዕጣን አሳርጉ አላቸው። እሊህ ቅዱሳንም እንዲህ ብለው መለሱለት እኛ የረከሱ አማልክትን አናመልክም የሕያው #እግዚአብሔር ልጅ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን እናመልከዋለን እንጂ። በዚያንም ጊዜ በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ እንዲአሠቃዩአቸው አዘዘ ጽኑ ሥቃይንም አሠቃዩአቸው #እግዚአብሔርም ያለ ጥፋት አስነሣቸው።

ሁለተኛም በበሬ አምሳል በተሠራ ነሐስ ውስጥ እንዲጨምሩአቸው አዘዘና በዚያ ጨምረው እሳትን በላያቸው አነደዱ ነፍሳቸውንም በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጡ። ክብር ይግባውና ከ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ዘንድ የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ጤቅላ

በዚህችም ቀን ያለ ደም ማፍሰስ ሰማዕት የሆነች ቅድስት ጤቅላ አረፈች። የዚች ቅድስት ወላጆቿ ከመቄዶንያ ሰዎች ውስጥ ባለጸጎች ናቸው እርሷንም እንደ ሀገራቸው ባህል በተግሣጽ በምክር አሳደጓት እነርሱ ጣዖትን የሚያመልኩ ናቸውና።

ሐዋርያ ጳውሎስም ወደዚች አገር በደረሰ ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም እንዲህ እያለ ሊአስተምር ጀመረ ዐውቀው ድኆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው መንግሥተ ሰማያት ለነርሱ ናትና። ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው እነርሱ ደስ ይላቸዋልና።

ስለ ዕውነት የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው መንግሥተ ሰማያት ለእነርሱ ናትና። ሚስት እያላቸው እንደ ሌላቸው የሚሆኑ ብፁዓን ናቸው። እነርሱ የዘላለም ሕይወትን ይወርሳሉና። ይህንንና ይህን የመሰለውን በሰማች ጊዜ ቅድስት ጤቅላ ከቤቷ ደርብ ሳትወርድ ያለ መብልና መጠጥ ሦስት ቀን ኖረች። እናቷም ከቤትሽ ደርብ የማትወርጂ ለምንድን ነው እህልስ ለምን አትበዪም አለቻት።

ከዚህም በኋላ በጭልታ ወረደች ለሚጠብቃትም ዘበኛ እንዳይናገርባት የወርቅ ወለባዋን ዋጋ ሰጠችውና ወደ ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ ሔደች። እርሱም በደስታ ተቀብሎ የክርስቶስን ሃይማኖት አስተማራት።

በማግሥቱም እናቷ እየፈለገቻት በመጣች ጊዜ ከቅዱስ ጳውሎስ ዘንድ አብራ ተቀምጣ አገኘቻት ከዚያም ወደ መኰንን ሒዳ ልጇን ክርስቲያን እንደሆነች ከሰሰቻት። መኰንኑም ከቅዱስ ጳውሎስ ጋራ እንዲያመጧት አዘዘ አስቀድመው ቅዱስ ጳውሎስን ወደ እሳት እንዲወረውሩት አዘዘ #እግዚአብሔርም አዳነው።

መኰንኑም የቅድስት ጤቅላን ቅጣት እንዲያዩ የሀገር ልጆችን ሰበሰበ ከዚህም በኋላ ወደ እሳት እንዲወረውሩዋት አዘዘ። በዚያን ጊዜ በክርስቶስ ማዕተብ ራሷን አማትባ ራስዋን በራስዋ ወደ እሳት ወረወረች ማንም ያያት ሳይኖር ከእሳት ውስጥ ወጥታ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሔደች የራስዋን ጠጒር ቆርጣ ወገቧንም ታጥቃ ቅዱስ ጳውሎስን ተከተለችው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_27_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሮሜ 5
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁸ ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።
⁹ ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን።
¹⁰ ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤
¹¹ ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን አሁን መታረቁን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ያዕቆብ 2
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁵ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ለሚወዱትም ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምን?
⁶ እናንተ ግን ድሆችን አዋረዳችሁ። ባለ ጠጎቹ የሚያስጨንቁአችሁ አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤትም የሚጎትቱአችሁ እነርሱ አይደሉምን?
⁷ የተጠራችሁበትን መልካሙን ስም የሚሰድቡ እነርሱ አይደሉምን?
⁸ ነገር ግን መጽሐፍ፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ እንደሚል የንጉሥን ሕግ ብትፈጽሙ መልካም ታደርጋላችሁ፤
⁹ ለሰው ፊት ግን ብታደሉ ኃጢአትን ትሠራላችሁ፥ ሕግም እንደ ተላላፊዎች ይወቅሳችኋል።
¹⁰ ሕግን ሁሉ የሚጠብቅ፥ ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ማንም ቢኖር በሁሉ በደለኛ ይሆናል፤ አታመንዝር ያለው ደግሞ፦ አትግደል ብሎአልና፤
¹¹ ባታመነዝርም፥ ነገር ግን ብትገድል፥ ሕግን ተላላፊ ሆነሃል።
¹² በነጻነት ሕግ ፍርድን ይቀበሉ ዘንድ እንዳላቸው ሰዎች እንዲህ ተናገሩ፥ እንዲህም አድርጉ።
¹³ ምሕረትን ለማያደርግ ምሕረት የሌለበት ፍርድ ይሆናልና፤ ምሕረትም በፍርድ ላይ ይመካል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 17
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በአንፊጶልና በአጶሎንያም ካለፉ በኋላ ወደ ተሰሎንቄ መጡ፥ በዚያም የአይሁድ ምኵራብ ነበረ።
² ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ እነርሱ ገባ፥ ሦስት ሰንበትም ያህል ከእነርሱ ጋር ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ይነጋገር ነበር፤
³ ሲተረጉምም ክርስቶስ መከራ እንዲቀበልና ከሙታን እንዲነሣ ይገባው ዘንድ እያስረዳ፦ ይህ እኔ የምሰብክላችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው ይል ነበር።
⁴ ከእነርሱም አንዳንዶቹ ተረድተው ከሚያመልኩም ከግሪክ ሰዎች ብዙ ከከበሩትም ሴቶች ጥቂቶች ያይደሉ፥ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ።
⁵ አይሁድ ግን ቀንተው ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ ሕዝብንም ሰብስበው ከተማውን አወኩ፥ ወደ ሕዝብም ያወጡአቸው ዘንድ ፈልገው ወደ ኢያሶን ቤት ቀረቡ፤
⁶ ባላገኙአቸውም ጊዜ ኢያሶንንና ከወንድሞች አንዳንዶችን ወደ ከተማው አለቆች ጎትተው፦ ዓለምን ያወኩ እነዚህ ወደዚህ ደግሞ መጥተዋል፥ ኢያሶንም ተቀብሎአቸዋል፤
⁷ እነዚህም ሁሉ፦ ኢየሱስ የሚሉት ሌላ ንጉሥ አለ እያሉ የቄሣርን ትእዛዝ ይቃወማሉ ብለው ጮኹ።
⁸ ሕዝቡና የከተማውም አለቆች ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ ታወኩ፥
⁹ ከኢያሶንና ከሌሎቹም ዋስ ተቀብለው ለቀቁአቸው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_27_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"ወረከብናሁ ውስተ ኦመ ገዳም። ንበውዕ እንከሰ ውስተ አብያቲሁ ለእግዚአብሔር። ወንሰግድ ውስተ መካን ኅበ ቆመ እግረ እግዚእነ"። መዝ. 131፥6-7።
"እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ በዱር ውስጥም አገኘነው። ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን፤ እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን"። መዝ. 131፥6-7።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_27_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማቴዎስ 19
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹⁶ እነሆም፥ አንድ ሰው ቀርቦ፦ መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ? አለው።
¹⁷ እርሱም፦ ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው፤ ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ አለው።
¹⁸ እርሱም፦ የትኞችን? አለው። ኢየሱስም፦ አትግደል፥ አታመንዝር፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥
¹⁹ አባትህንና እናትህን አክብር፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው።
²⁰ ጐበዙም፦ ይህንማ ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፥ ደግሞስ የሚጐድለኝ ምንድር ነው? አለው።
²¹ ኢየሱስም፦ ፍጹም ልትሆን ብትወድ፥ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፥ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ አለው።
²² ጐበዙም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነ ሄደ።
²³ ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ለባለጠጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ጭንቅ ነው።
²⁴ ዳግመኛም እላችኋለሁ፥ ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል አለ።
²⁵ ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው እጅግ ተገረሙና፦ እንኪያስ ማን ሊድን ይችላል? አሉ።
²⁶ ኢየሱስም እነርሱን ተመልክቶ፦ ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል አላቸው።
²⁷ በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን? አለው።
²⁸ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ።
²⁹ ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።
³⁰ ነገር ግን ብዙዎቹ ፊተኞች ኋለኞች፥ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈ_ወርቅ ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️