ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
5.85K subscribers
1.06K photos
7 videos
37 files
247 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#ጥቅምት_20

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ጥቅምት ሃያ በዚህች ቀን ክቡርና ገናና የሆነ #የአባ_ዮሐንስ_ሐፂር እና የስሙ ትርጓሜ ጠባቂና አዳኝ የሆነ #የታላቁ_ነቢይ_ኤልሳዕ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ዮሐንስ_ሐፂር

ጥቅምት ሃያ በዚህች ቀን ክቡርና ገናና የሆነ አባ ዮሐንስ ሐፂር አረፈ። የዚህ ቅዱስ ወላጆቹ ከላይኛው ግብጽ ናቸው እነርሱም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ናቸው ግን ከእርሱ በቀር ልጅ የላቸውም የዚህ ዓለምም ብልጽግና ቢሆን የላቸውም ነገር ግን በበጎ ሥራ ባለጸጎች ናቸው ይህንንም ቅዱስ እያስተማሩ በበጎ አስተዳደግ አሳደጉት ።

የዚህም ቅዱስ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ሲሆነው የእግዚአብሔር ቸርነት አነሣሥታው የመላእክት የሆነ አስኬማን ይለብስ ዘንድ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ ይኸውም የምንኵስና ልብስ ነው።

ከዚያም በደረሰ ጊዜ አባ ባይሞይ የሚባለውን አንዱን አረጋዊ አባት ተገናኘው ዮሐንስም ሰገደለትና ወደ እርስ እንዲቀበለው ለመነው ሽማግሌውም አባት ልጄ ሆይ ያንተ በዚህ መኖር ልክ አይደለም በዚች ገዳም የሚኖሩ በእጆቻቸው ይሠራሉ በቀንና በሌሊት ይጾማሉ ይጸልያሉ በሚተኙም ጊዜ ያለ ምንጣፍ በምድር ላይ ይተኛሉ አንተ ወጣት ጎልማሳ ስለሆንክ ይህን ሁሉ ችግር አትችልም። ነገር ግን ወደ ዓለም ተመልሰህ እንደ ሰው ሁሉ በጎ አኗኗርን ትኖር ዘንድ ይሻልሃል የዚች ገዳም ኑሮ ጭንቅ ነውና አለው።

አባ ዮሐንስም እንዲህ አለው እኔ በጥላህ ሥር ልኖር መጥቼአለሁና ስለ እግዚአብሔር ብለህ ተቀበለኝ እንጂ አትመልሰኝ ይህም አባ ባይሞይ እግዚአብሔርን ሳይጠይቅ ምንም ሥራ አይሠራምና በዚያን ጊዜ ሥራውን ይገልጥለት ዘንድ ስለ ዮሐንስ ሐፂር እግዚአብሔርን ለመነው የእግዚአብሔርም መልአክ ተገልጦለት እርሱ የተመረጠ መሳሪያ ይሆናልና ተቀበለው ብሎሃል አለው።

ከዚህም በኋላ ዮሐንስ ሐፂርን ወስዶ ወደ ቤተ ክርስቲያን አስገባው የምንኵስና ልብሶችንም አምጥቶ በላያቸው ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ጸለየ ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጾ በመስቀል ምልክት በልብሶቹ ላይ አማተበ ሽማግሌውም እነዚያን ልብሶች ለአባ ዮሐንስ አለበሰው ።

ከዚያቺም ቀን ጀምሮ አባ ዮሐንስ ተጋድሎንና አገልግሎትን ጀመረ አባ ባይሞይም ሊፈትነው ወደደ በአንዲትም ቀን ደብድቦ ከአንተ ጋር መኖር አልሻም ብሎ ከበዓቱ አስወጥቶ አባረረው የከበረ አባ ዮሐንስም ከሜዳ መካከል በውጭ ቆመ በየቀኑም በጥዋት እየወጣ ከእዚህ ላይህ አልሻም እያለ ይመታዋል እርሱ ግን አባቴ ሆይ ይቅር በለኝ ብሎ ከእግሩ በታች ይሰግዳል ።

በሰባተኛዪቱም ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊሔድ ሽማግሌው አባ ባይሞይ ወጣ አባ ዮሐንስንም ሰባት መላእክት ከበው አክሊላትን ሲያቀዳጁት አያቸው ከዚያንም ጊዜ ወዲህ መፈተኑን ተወው ወደ መኖሪያውም አስገባው።

ከዚህም በኋላ በአንዲት ቀን አባ ባይሞይ የደረቀ ዕንጨት አግኝቶ ወስዶ ለአባ ዮሐንስ ሰጠውና ይህን ዕንጨት ትከለው እስከሚበቅልና እስከሚአፈራ ድረስ ውኃን አጠጣው አለው ። አባ ዮሐንስም ለአባቱ ታዛዥ በመሆን ተቀብሎ ወስዶ ተከለው በየቀኑም ሁለት ሁለት ጊዜ ያጠጣዋል ውኃውም ዐሥራ ሁለት ምዕራፍ ያህል የራቀ ነው።

ከሦስት ዓመትም በኋላ ያ ዕንጨት አቈጥቊጦ በቀለ ታላቅም ዛፍ ሁኖ አብቦ ጣፋጭ ፍሬን አፈራ። አባ ባይሞይም ከፍሬው ለቅዱሳን አረጋውያን ወሰደላቸውና የታዛዡንና የትሑቱን ፍሬ እነሆ ብሉ አላቸው እነርሱም ይህን ድንቅ ተአምር አይተው አደነቁ ለመምህሮቻቸው ለሚታዘዙ እንዲህ ያለ ጸጋ የሚሰጥ እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።

አባ ባይሞይም ዐሥራ ሁለት ዓመት ያህል በጽኑዕ ደዌ ውስጥ ተይዞ ኖረ አባ ዮሐንስም ያገለግለው ነበር አባ ዮሐንስን እንደፈተነው የተመረጠ መሥዋዕትን ይሆን ዘንድ በዚህ ደዌ እንዲፈተን እግዚአብሔር ፈቅዷልና።

በሚሞትበትም ጊዜ አባ ባይሞይ ቅዱሳን አረጋውያን መነኰሳትን ሰበሰባቸውና አባ ዮሐንስንም እጁን ይዞ እርሱ ሰው ያይደለ መልአክ ነውና ተቀብላችሁ ጠብቁት ብሎ ሰጣቸው ። እርሱንም ደግሞ እንዲህ አለው ከእረፍቴ በኋላ ያን ዕንጨት ወደ ተከልክበት ቦታ በዚያ ኑር እግዚአብሔር ላንተ ያዘጋጀልህ ነውና ብዙዎችም በአንተ እጅ ይድናሉ መታሰቢያህም በዚያ ጸንቶ ይኖራል ዜናህም በዓለም ሁሉ ይወጣል ይህንንም ተናግሮ አረፈ አክብረውም ቀበሩት።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ አባ ዮሐንስ አረጋዊ አባቱ አባ ባይሞይ እንደነገረው ወደዚያ ቦታ ሒዶ ኖረ ዜናውም በዓለም ሁሉ እጅግ እስከ ተሰማ ድረስ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ።

በራሱ ቤተ ክርስቲያንም አበ ምኔት ሁኖ ተሾመ በሹመቱም ጊዜ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ እጆቹን በራሱ ላይ ሲጭን አክዮስ አክዮስ አክዮስ የሚል ቃል ከሰማይ ተሰማ ይህም ይገባዋል ይገባዋል ይገባዋል ማለት ነው ። የቊርባን ቅዳሴን በሚቀድስ ጊዜ ቅዱስ ቁርባንን መቀበል የማይገባቸውን ይለያቸዋል ዛሬስ ሒዳችሁ ንስሓ ግቡ ከዚያም በኋላ ተመልሳችሁ ሥጋውን ደሙን ተቀበሉ ይላቸዋል።

ይህን አባ ዮሐንስንም ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ የቅዱሳን የሠለስቱ ደቂቅን ሥጋቸውን እንዲአመጣለት ወደ ባቢሎን ልኮታል ይህም በግንቦት ወር በዐሥረኛው ቀን ተጽፎአል ። በአንዲትም ዕለት አንድ መነኰስ ሊጎበኘው ወደ በዓቱ ቢመጣ አባ ዮሐንስን ተኝቶ አገኘው የእግዚአብሔርም መላእክት በላዩ ይጋፉ ክንፎቻቸውንም ያርገበግቡ ነበር አንዱም ሌላውን ተወኝ ክንፌን በላዩ ላኑር ይለዋል ይህንንም አይቶ እግዚአብሔርን አመሰገነው ።

ከዚህም በኋላ የመነኩሳቱን መንደር ሊበረብሩ የበርበር አረማውያን ወደ አስቄጥስ ገዳም በመጡ ጊዜ አባ ዮሐንስም ወደ አባ እንጦንስ ገዳም ወደ ቁልዝም ሔደ በዚያም በአባ እንጦንስ ገዳም በጎኑ በአለ ቦታ ተቀመጠ እስከ ሚያርፍባትም ቀን ድረስ የሚያገለግለው አንድ የታመነ ሰውን እግዚአብሔር አመጣለት ።

ከዚህም በኋላ ከዚህ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው በወደደ ጊዜ እግዚአብሔር ቅዱሳን ጻድቃኖቹን አባ እንጦንስን፣ አባ መቃርስን፣ አባ ጳኵሚስን ከእርሳቸውም ጋር መንፈሳዊ አባቱ አባ ባይሞይን ያረጋጉትና ከዚህ ከኃላፊው ዓለም መለየቱን ይነግሩት ዘንድ ወደርሱ ላካቸው ። እነርሱም እንዲህ ብለው አረጋጉት ደስ ይበልህ እግዚአብሔር የማያልቅ ተድላ ደስታን አዘጋጅቶልሃልና ክብር ይግባውና ጌታችንም እንዳዘዘ በእሑድ ቀን ሁለተኛ ወዳንተ መጥተን ወደ ዘላለም ሕይወት እንወስድኻለን ባርከውትም ከእርሱ ዘንድ ተመለሱ ።

በዐርብ ቀንም አገልጋዩን ወደ አንድ ቦታ ላከው ከዚህም በኋላ ጥቂት ታመመ በእሑድም ቀን ሌሊት ዶሮ ሲጮህ እሊያ ቅዱሳን ከሁሉም ቅዱሳን ማኅበር ጋር መጡ የመላእክትም ሠራዊት ሁሉ ወደርሱ መጡ በአያቸውም ጊዜ ደስ ብሎት በእግዚአብሔር እጅ ነፍሱን ሰጠ መላእክትም እያመሰገኑና እየዘመሩ በታላቅ ክብር ነፍሱን አሳረጓት በዚያንም ጊዜ ረድኡ መጣ ነፍሱንም ከበው እያመሰገኑ ሲያሳርጓት የጻድቃንና የመላእክትን ማኅበር አይቶ እያደነቀ አንድ ሰዓት ያህል ቆመ ። ከመላእክትም አንዱ ወደርሱ መጥቶ የቅዱሳንን ስማቸውን በመጥራት በጣቱ እያመለከተ ይህ አባ ዕገሌ ነው ብሎ አስረዳው ረድኡም መልአኩን እንዲህ ብሎ ጠየቀው ይህ በፊታቸው ያለ ፊቱ እንደ ፀሐይ የሚበራ ማን ነው መልአኩም የመነኰሳቱ ሁሉ አባት አባ እንጦንስ ነው ብሎ መለሰለት።
#ሚያዝያ_3
#አንድ_አምላክ_በሆነ_በአብ_በወልድ_በመንፈስ_ቅዱስ_ስም
ሚያዝያ ሦስት በዚች ቀን የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ የከበረ አባት #አባ_ዮሐንስ አረፈ፣ የከበረ አባት በእስክንድርያ ለተሾሙ አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሰባ አንደኛ የሆነ #አባ_ሚካኤል አረፈ፣ ክርስቲያናዊ ነጋዴ #ቅዱስ_መርቄ አረፈ፣ በተጨመሪም #እግዚአብሔር በእግር የሚራመዱ በክንፍ የሚበሩና በልብ የሚሳቡ በየብስ የሚኖሩ ፍጥረታትን ፈጠረ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ዮሐንስ

ሚያዝያ ሦስት በዚች ቀን የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ የከበረ አባት አባ ዮሐንስ አረፈ። የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ የኦሪት ምሁራን የሆኑ አዋቂዎች ነበሩ የኦሪትን ሕግ ትምህርቶችንም እያስተማሩት አሳደጉት።

ክርስቲያኖችን በጸና ልቡና የሚከራከራቸውና የሚጣላቸው ነበር መጻሕፍትን አዘውትሮ ከመመርመሩ የተነሣ የ ክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ወደ ዓለም እንደመጣና ሰውም እንደሆነ በሞቱም ዓለምን እንደ አዳነ አመነ። እርሱም የ#ባሕርይ_አምላክ እንደሆነ አምኖ በኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ በአባ ዮስጦስ እጅ ተጠመቀ ዲቁናም ሾመው ከዚያም በኢየሩሳሌም ሀገር ኤጲስቆጶስነት ለመሾም እስቲገባው ድረስ በበጎ ስራና በዕውቀት አደገ።

ኤልያስ የሚባለው እንድርያኖስም በነገሠ ጊዜ ከኢየሩሳሌም ሀገር የፈረሰውን ሕንፃ ሁሉ እንዲያንፁና በስሙ ኤልያስ ተብሎ እንዲጠራ አዘዘ። ከዚህም በአይሁድ ምኲራብ ደጃፍ ላይ ታላቅ ግምብ ሠሩ ከከበረ ድንጊያም ሠሌዳ ሠርቶ በላዩም ስሙን ኤልያስን ጽፎ በመግቢያው አኖረው በዘመኑም ኢየሩሳሌም አሕዛብንና አይሁድን ተመላች ሠለጡኑባትም።

ክርስቲያኖችም ሊጸልዩ ወደ ጎልጎታ ሲመጡ በአዩአቸው ጊዜ አሕዛብ ይከለክሉአቸው ነበር በዚያ ዝሁራ በሚባል ኮከብ ስም መስጊድ ሠርተው ነበርና። ስለዚህም #ክርስቲያኖችን በዚያ እንዳያልፉ ይከለክሏቸው ነበር።
በዚህም አባት ላይ ከአሕዛብ ታላቅ መከራና በምድር ላይም ጐትተውታልና አጐሳቁለውታልና እርሱም ነፍሱን ወደርሱ ይቀበል ዘንድ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን ለመነው ጌታም ልመናውን ሰምቶ በሰላም አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ሚካኤል_ዘእስክንድርያ

በዚህችም ቀን ደግሞ የከበረ አባት በእስክንድርያ ለተሾሙ አባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሰባ አንደኛ የሆነ አባ ሚካኤል አረፈ። ይህ አባት ከታናሽነቱ ጀምሮ የምንኲስና ልብስ ሊለብስ ወደደ በአስቄጥስ ገዳም በአባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያን መንኲሶ እስከ ሸመገለ ድረስ በዚያ ኖረ።

በብዙ መነኰሳትም ላይ አበ ምኔት ሆኖ ተሾመ በዘመኑ ሁለየ መልካም ተጋድሎ በመጋደል #እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው። በወንጌላዊው ማርቆስ ወንበር ላይ ሊቀ ጵጵስና ለመሾም እስቲገባው ድረስ ፍጹም ተጋድሎ በመጋደል ደከመ።

ከእርሱ በፊት የነበረ ሊቀ ጳጳሳት አባ ገብርኤል በአረፈ ጊዜ የወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ያለ ሊቀ ጳጳሳት አራት ወር ኖረ ለዚች ሹመት የሚሻል ሲመረምሩና ሲመርጡ ብዙ ደከሙ። ከብዙ ድካምም በኃላ ሦስት የገዳም ሰዎችን መርጠው ስማቸውን በሦስት ክርታስ ጻፉ የክብር ባለቤት የ#ጌታችንን_ኢየሱስ_ክርስቶስንም ስም በአንዲት ክርታስ ጽፈው እየአንዳንዳቸውን አሽገው በመሠዊያው ውስጥ አኖሩአቸው። ቸር ጠባቂ ይሾምላቸው ዘንድ ኤጲስቆጶሳቱና ካህናቱ እስከ ሦስት ቀን እየጸለዩና እየቀደሱ #እግዚአብሔርን በመማለድ ኖሩ።

ከሦስት ቀኖችም በኃላ አንድ ታናሽ ብላቴና ጠርተው ከእነዚህ ከሦስቱ ስሞች አንዱን አንሥተህ ስጠን አሉት። ያም ብላቴና የዚህን አባት የአባ ሚካኤል ስም ያለበትን ያንን ክርታስ አወጣ። ሁሉም እግዚአብሔር እንደመረጠው አውቀው ይገባዋል ይግባዋል ይገባዋል እያሉ ሊቀ ጵጵስና ሾሙት እርሱም በሹመቱ ላይሆኖ እንደሚገባ በመልካም አመራር ሥራውን መራ።

የሚጽፍለትም ጸሐፊ መረጡለት ስለ ምእመናን አጠባበቅና ስለማስተማር ወደ ሀገሮች ሁሉና ወደ ኤጲስቆጶሳቱ መልእክትን ይልክ ነበር። እርሱም ከኃጢአታቸው ተመልሰው ንሰሐ እንዲገቡ ሕዝቡን ይመክራቸውና ይገሥጻቸው ነበር እግዚአብሔርን ይፈሩት ዘንድ።

ንጽሐ ነፍስ ንጽሐ ልቡና ያለው ሆነ የዚህን አለም ጣዕም ያለውን ምግብ አይሻም አይመኝም ክብሩንም ቢሆን ወይም ጥሪቱን ድኆችንና ችግረኞችን አስቦ ይመጸውታቸው ነበረ እንጂ፡፡ ከእነርሱ የሚተርፈውንም ለቤተ ክርስቲያን ማሠሪያ ያደረገው ነበር። ይህ አባት ሙሉ ዓመት አልኖረም ከዚያ የሚያንስ ነው እንጂ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_መርቄ_ጻድቅ

በዚህችም ቀን ዳግመኛ ክርስቲያናዊ ነጋዴ መርቄ አረፈ። ይህም ቅዱስ ከአንጾኪያ ሰዎች ወገን ነው ጉዝፋርም ጣዖት የሚያመልክ ከሀዲ ነው ከሃይማኖት በቀር በምንም በምን አይለያዩም። ከዕለታትም በአንዲቱ መርቄና ጉዝፋር ነበግዱድ ወደሚባል አገር ለንግድ ሒደው ሰው በሌለበት በበረሀ ውስጥ አምስት ቀን ተጓዙ ክርስቲያናዊ መርቄም ባለጸጋ ነው ከእርሱ ጋርም አርባ ልጥረ ወርቅ ነበረ።

በጐዳና በጉዞ ላይም እያሉ ለሞት የሚያደርስ ደዌን መርቄ ታመመ ከዚያም ራሱን አጽናንቶ እንዲህ ብሎ ጻፈ። "ከባሪያህ ልጅ ከባሪያህ መርቄ ለእኔ ያለ በጥቁር በቅሎ የተጫነ አርባ ልጥረ ወርቅ ለአንተ ይሁን #ጌታ_ኢየሱስ_ክርስቶስ የሕያው #እግዚአብሄር_ልጅ የክብር ባለቤት ሆይ ስለ በደሌ ይቅር ብለኸኝ መንግሥተ ሰማያትን ትሰጠኝ ዘንድ ለልጆቼ ለሚስቴም ወይም ለዘመዶቼ አይሁን ብዬአለሁ።"

ይቺን ደብደቤ ጠቅልሎ ወዳጄ ጉዝፋርን ጠራው የሚለውን ሁሉ ያደርግለት ዘንድ አማለው። ከዚያም በምሞትበት ጊዜ አትንካኝ ግን ይህን አርባ ልጥረ ወርቅ እንደተጫነ ከበቅሎው ጋራ ወስደህ የክብር ባለቤት ለሆነ ለሕያው #እግዚአብሔር_ልጅ_ለጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ በእጁ ስጠው። ለልጆቼ እንዳትሰጥ ከእርሱ በቀር ለማንም ቢሆን አትስጥ አለው።

ጉዝፋርም እንዲህ ብሎ መለሰለት አንተ ራስህ ሞቶ ተነስቶ ወደ ሰማይ ወጣ የምትል አይደለምን እኔ ወደ ሰማይ ወጥቼ ልሰጠው እችላለሁን። መርቄም እንዲህ አለው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒድ ራሱ ወደ አንተ ይመጣል እጅ በእጅ ስጠው።

ከዚህ በኃላ መርቄ ለመሞት ሲቃረብ ራቀወ ብሎ በመቀመጥ ጉዝፋር መሞቱን ይጠብቅ ነበር። ወደርሱም መላእክት የብርሃን ልብስ ይዘው ሲወርዱ አየ ከእርሳቸውም ጋራ ጻድቃን ሰማዕታት አሉ ዳዊትም በመስንቆ ያመሰግን ነበር መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በስጋው ላይ ሦስት ጊዜ ዞረ ያንጊዜም የመርቄ ነፍስ ከሥጋዋ ተለይታ ወደ ሰማይ እንዲህ ባለ ሁኔታ ዐረገች። ሁለት አንበሶችም መጡ ምድሩንም ቆፍረው ቀበሩት።

ጉዝፋርም ተነሣ የመርቄንም ወርቅ ጭኖ ስለአየው ሁሉ እያደነቀ ሔደ። አንጾኪያም በደረሰ ጊዜ የቤተ ክርስቲያኑን አስተዳዳሪ ቀሲስ ታዴዎስን አግኝቶ መርቄ እንዳለው ነገረው። ቀሲስ ታዴዎስም ሊረከበው ወደ ጉዝፋር ሔደ። ግን የክብር ባለቤት ከሆነ ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለማንም አልሰጥም ወዳጄ መርቄ እንዳማለኝ እጅ በእጅ እሰጠዋለሁ እንጂ ብሎ ከለከለው።

ከዚያም ሒዶ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር ግቢ ገባ።ቀሲስ ታዴዎስም ደጁን ከፈተለት የተጫነውንም ወርቅ አውርዶ በፊቱ አኑሮ በዚያ ቆመ። ከሌሊቱ እኩሌታ ላይ እንደ ነጐድጓድ ድምፅ ያለ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰማ። ታላቅ ብርሃንም ወጣ #ጌታችንም ከሰማይ ወርዶ በመሠዊያው ላይ ተቀመጠ መላእክትም ከእርሱ ጋር አሉ።
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞ ✞ እንኩዋን ለአራቱ ቅዱሳን አበው ሰማዕታት
ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ ✞

=> #4ቱ_ቅዱሳን አበው የዘመነ ሰማዕታት ፍሬዎች ሲሆኑ
ስማቸው #አባ_አክራ : #አባ_ዮሐንስ : #አባ_አብጥልማ
እና #አባ_ፊልዾስ ይባላሉ:: ከመከራ ዘመን በፊት
(ማለትም በቀደመ ሕይወታቸው) ካህናትና ሃብታሞች
ነበሩ:: ሀብቱ ግን በሥራ ብቻ የተገኘ ነው::

+ታዲያ ቅዱሳኑ በያሉበት ሆነው በሀብታቸው እንግዳ
እየተቀበሉ: ድሆችን እያበሉ: በክህነታቸው ደግሞ
እያስተማሩና እየናዘዙ ትጉሃን ስለ ነበሩ በሰውም ሆነ
በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ ነበራቸው:: በእንዲህ ያለ
ግብር ሳሉ ዘመነ ሰማዕታት አሐዱ አለ:: "ክርስቶስን ካዱ:
ለጣዖት ስገዱ" እያሉ መኩዋንንቱና ነገሥታቱ ሕዝበ
ክርስቲያኑን ያሰቃዩ ገቡ::

+በዚህ ጊዜ 4ቱ ቅዱሳን አንድ ነገር መከሩ:: በየእሥር
ቤቱ የተጣሉ ክርስቲያኖችን ለማገልገል ቆረጡ:: እግረ
መንገዳቸውን እያስተማሩ እሥረኞችን ያጽናኑ ገቡ::
የራበውን ያበላሉ: የተሰበረውን ይጠግናሉ: በቁስሉም ላይ
መድኃኒትን ያደርጉ ነበር:: የመከራው ዘመን ግን እየረዘመ:
ግፉም ከልክ እያለፈ መጣ::

+በዚህ ጊዜ 4ቱ ቅዱሳን ትልቁንና የመጨረሻውን ውሳኔ
አስተላለፉ:: ከሰማዕታት ወገን ይቆጠሩ ዘንድ
መርጠዋልና: ክርስቶስን በሞቱ ይመስሉት ዘንድ ሽተዋልና:
የሩጫቸው መጨረሻ ሰማዕትነት እንዲሆን መረጡ::

+አራቱም ያላቸውን ንብረት ሁሉ ሰብስበው ለነዳያን
አካፈሉ:: በትከሻቸው ካለች አጽፍ በቀር ስባሪ ገንዘብ
ከሃብታቸው አላስቀሩም:: ከዚያ ጉዞ ወደ ምስክርነት
አደባባይ (ዐውደ ስምዕ) አደረጉ::

+በዙፋኑ የተቀመጠው የመኮንኑ ግርማ: መሬት ላይ
የፈሰሰው የወገኖቻቸው ደም: የሠራዊቱ ድንፋታ ቅዱሳኑን
አላስፈራቸውም:: በይፋ "ክርስቲያን ነን" ሲሉ ተናገሩ::
በዘመኑ እንዲሕ ብሎ መናገር አንገት የሚያስቆርጥ ትልቅ
ድፍረት ነበር::

+መኮንኑም ከበጐ ሃይማኖታቸው ይለያቸው ዘንድ በእሳት
አቃጠላቸው:: እግዚአብሔር አዳናቸው:: በቀስትም:
በስለትም: በብረትም ለቀናት አሰቃያቸው:: ቅዱሳኑ ግን
አምላካቸውን አምነው ሁሉን በአኮቴት ተቀበሉ::
በመጨረሻ ግን በዚሕች ዕለት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው
ተገድለዋል:: ስለ ምጽዋታቸው: በጎ አገልግሎታቸውና
ሰማዕትነታቸው ጻድቅ: ፈራጅ ከሆነ ፈጣሪ አክሊልን
ተቀብለዋል::

=>የበረከት አምላክ ከወዳጆቹ ጸጋ ክብርን ያድለን::

=>ሰኔ 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱሳን አበው ሰማዕታት (አባ አክራ: አባ ዮሐንስ: አባ
አብጥልማ: አባ ፊልዾስ)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
2.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
3.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
5.አባ ስምዖን ገዳማዊ
6.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
7.እናታችን ቅድስት ነሣሒት

=>+"+ እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ: እስከ
አሁንም ስለምታገለግሏቸው ያደረጋችሁትን ሥራ:
ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመጸኛ
አይደለምና:: በእምነትና በትእግስትም የተስፋውን ቃል
የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ
ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ
መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን::+"+ (ዕብ. 6:10-13)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

https://t.me/zikirekdusn
#መስከረም_27

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሃያ ሰባት በዚች ቀን #ቅዱስ_ኤዎስጣቴዎስ ሁለቱ ልጆቹና ሚስቱም በሰማዕትነት አረፉ፣ ያለ ደም ማፍሰስ ሰማዕት የሆነች #ቅድስት_ጤቅላ አረፈች፣ የቀራጮች አለቃ የነበረ #ቅዱስ_አንጢላርዮስ አረፈ፣ የደብረ ጽጌ #አባ_ዮሐንስ አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ኤዎስጣቴዎስ

መስከረም ሃያ ሰባት በዚች ቀን ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ሁለቱ ልጆቹና ሚስቱም በሰማዕትነት አረፉ።

ይህ ቅዱስም ለሮም መንግሥት የጭፍራ አለቆች ከሆኑት ውስጥ ነው የቀድሞ ስሙ ቂዶስ ነው #እግዚአብሔርንም አያውቅም ነበር ግን ብዙ ምጽዋትን በመስጠት ለድኆችና ለችግረኞች ይራራል ስለዚህም ክብር ይግባውና #ጌታችን ድካሙ ከንቱ ሁኖ እንዲቀር አልወደደም።

በአንዲት ቀንም አውሬ ሊያድን ኤዎስጣቴዎስ ወደ ዱር ወጣ እርሱ አዳኝ ነውና ዋልያም አግኝቶ በቀስት ሊነድፈው ወደደ ያን ጊዜም በዋልያው በቀንዶቹ መካከል በ #መስቀል አምሳል #ጌታ ተገለጸለት። የ #መስቀሉም ብርሃን እስከ ደመና ደርሶ ነበር ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም በዚያ ብርሃን ውስጥ ተናገረው ስሙንም አስረዳው ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ወደ ኤጲስቆጶስ ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን እንዲጠመቁ አዘዘው።

ክብር ይግባውና #ጌታችንም ከዚህ በኋላ ችግርና ፈተና እንደሚመጣበት በመጨረሻም ስለ ከበረ ስሙ ምስክር ሁኖ ደሙን አፍስሶ እንደሚሞት አስረዳው። ኤዎስጣቴዎስም ሰምቶ ከተራራው ወርዶ ወደ ቤቱ ሔደ። #ጌታችን ያዘዘውንም ለሚስቱ ነገራት ከዚህም በኋላ ወደ ኤጲስቆጶሱ ሔደው ከልጆቻቸው ጋራ የክርስትና ጥምቀትን ተጠመቁ የቀድሞ ስሙንም ለውጦ ኤዎስጣቴዎስ ተባለ።

ከጥቂት ቀኖች በኋላ በዚያች አገር ታላቅ ችግር መጣ የኤዎስጣቴዎስም ገንዘቡ ሁሉ አልቆ ወንዶችና ሴቶች ባሮቹ ተበተኑ ወደሌላ አገርም ሊሰደድ ወዶ ልጆቹንና ሚስቱን ይዞ በመርከብ ተጫነ። ወደ ወደቡም በደረሱ ጊዜ መርከበኞች የመርከብ ዋጋ ከእርሱ ፈለጉ የሚሰጣቸው የመርከብ ዋጋ ባላገኘ ጊዜ ስለ መርከብ ዋጋ የመርከቡ ሹም ሚስቱን ወሰዳት የአታክልት ጠባቂም አደረጋት።

ከዚያም ኤዎስጣቴዎስ እያዘነና እያለቀሰ ሁለቱን ልጆቹን ይዞ ሔደ ውኃ ወደ መላበትም ወንዝ ደረሰ አንዱንም ልጁን ከእርሱ ጋር ሊአሻግረው ይዞት ገባ አሻግሮትም ከወንዙ ዳር አኖረውና ሁለተኛውን ልጁን ሊአሻግረው ተመለሰ ግን አላገኘውም። ተኵላ ወስዶታልና ያሻገረውንም አንበሳ ነጥቆ ወሰደው ኤዎስጣቴዎስም ከሚስቱና ከልጆቹ ስለ መለየቱ ታላቅ ኀዘንን አዝኖ መሪር ልቅሶን አለቀሰ ምክሩ ታላቅ የሆነ ሥልጣን ያለው #እግዚአብሔር ግን ሁሉንም በየአሉበት ያለ ጥፋት ጠበቃቸው።

ከዚህ በኋላም ኤዎስጣቴዎስ ወደ አንዲት አገር ሒዶ በዚያ የአትክልት ጠባቂ ሁኖ ብዙ ቀኖችን ኖረ። ከእነዚያ ቀኖችም በኋላ የሮም ንጉሥ ሙቶ በርሱ ፈንታ ለኤዎስጣቴዎስ ወዳጁ የሆነ ሰው ነገሠ ኤዎስጣቴዎስንም ፈለገው ግን አላገኘውም ኤዎስጣቴዎስንም ይፈልጉት ዘንድ ወደ ሀገሩ ሁሉ መልእክተኞችን ላከ። ከመልእክተኞችም አንዱ ኤዎስጣቴዎስ ወዳለበት ደርሶ በአታክልቶች ዘንድ አግኝቶት አወቀው እርስ በርሳቸውም ተሳሳሙ ከዚህም በኋላ ወደ ንጉሡ ወሰደው ንጉሡም በበጎ አቀባበል ተቀብሎ የጭፍራ አለቃ አድርጎ ሾመው።

ከዚህም በኋላ ንጉሡ ከሚገዛቸው አገሮች ሁሉ ወጣቶችን ሰብስቦ የጦር ሠራዊት ጭፍራ ያዘጋጅ ዘንድ ኤዎስጣቴዎስን አዘዘው እነዚያ ተኵላና አንበሳ የወሰዳቸው የኤዎስጣቴዎስ ሁለት ልጆቹ በአንዲት አገር አድገዋል። ግን እርስበርሳቸው አይተዋወቁም ወጣቶችንም የሚመለምሉ መልምለው ወደ አባታቸው ኤዎስጣቴዎስ አቀረቧቸው እርሱም ሳያውቃቸው የመዛግብት ቤት ጠባቂዎች አደረጋቸው።

እናታቸውንም አረማዊ የሆነ የመርከቡ ሹም በወሰዳት ጊዜ የአታክልቶች ጠባቂ አደረጋት። #እግዚአብሔር ከክፉ ነገር ሁሉ በንጽሕና ጠብቋታልና እነዚያ ሁለቱ ልጆቿ እርሷ ወዳለችበት የአታክልት ቦታ ደረሱ እነርሱም የልጅነታቸውን ነገር ይነጋገሩ ነበር። እርሷም ሰምታ ልጆቿ እንደሆኑ አውቃ ያን ጊዜ ጠራቻቸውና እርሷ እናታቸው እንደ ሆነች ነገረቻቸው አንገት ላንገት ተያይዘው አለቀሱና እርስ በርሳቸው ተሳሳሙ ወደ ኤዎስጣቴዎስም ሔደው ከእነርሱ የሆነውን ሁሉ ነገሩት። እርሱም እርሷ ሚስቱ እንደሆነች እነዚያም ልጆቹ እንደ ሆኑ አወቀ እርስ በርሳቸውም ተሳሳሙ ታላቅ ደስታም ደስ አላቸው ምስጉን የሆነ #እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።

ከዚህም በኋላ በእነርሱ ላይ ስለ አደረገው በጎ ነገር እያደነቁና #እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በአንድነት በአንድ ቦታ ኖሩ።

ኤዎስጣቴዎስንም የሚወደው ንጉሥ በሞተ ጊዜ በእርሱ ፈንታ ጣዖት የሚያመልክ ሌላ ንጉሥ ነገሠ። ኤዎስጣቴዎስንም ጠርቶ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ወደርሱ አቅርቦ ለአማልክት ዕጣን አሳርጉ አላቸው። እሊህ ቅዱሳንም እንዲህ ብለው መለሱለት እኛ የረከሱ አማልክትን አናመልክም የሕያው #እግዚአብሔር ልጅ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስን እናመልከዋለን እንጂ። በዚያንም ጊዜ በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ እንዲአሠቃዩአቸው አዘዘ ጽኑ ሥቃይንም አሠቃዩአቸው #እግዚአብሔርም ያለ ጥፋት አስነሣቸው።

ሁለተኛም በበሬ አምሳል በተሠራ ነሐስ ውስጥ እንዲጨምሩአቸው አዘዘና በዚያ ጨምረው እሳትን በላያቸው አነደዱ ነፍሳቸውንም በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጡ። ክብር ይግባውና ከ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ዘንድ የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ጤቅላ

በዚህችም ቀን ያለ ደም ማፍሰስ ሰማዕት የሆነች ቅድስት ጤቅላ አረፈች። የዚች ቅድስት ወላጆቿ ከመቄዶንያ ሰዎች ውስጥ ባለጸጎች ናቸው እርሷንም እንደ ሀገራቸው ባህል በተግሣጽ በምክር አሳደጓት እነርሱ ጣዖትን የሚያመልኩ ናቸውና።

ሐዋርያ ጳውሎስም ወደዚች አገር በደረሰ ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም እንዲህ እያለ ሊአስተምር ጀመረ ዐውቀው ድኆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው መንግሥተ ሰማያት ለነርሱ ናትና። ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው እነርሱ ደስ ይላቸዋልና።

ስለ ዕውነት የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው መንግሥተ ሰማያት ለእነርሱ ናትና። ሚስት እያላቸው እንደ ሌላቸው የሚሆኑ ብፁዓን ናቸው። እነርሱ የዘላለም ሕይወትን ይወርሳሉና። ይህንንና ይህን የመሰለውን በሰማች ጊዜ ቅድስት ጤቅላ ከቤቷ ደርብ ሳትወርድ ያለ መብልና መጠጥ ሦስት ቀን ኖረች። እናቷም ከቤትሽ ደርብ የማትወርጂ ለምንድን ነው እህልስ ለምን አትበዪም አለቻት።

ከዚህም በኋላ በጭልታ ወረደች ለሚጠብቃትም ዘበኛ እንዳይናገርባት የወርቅ ወለባዋን ዋጋ ሰጠችውና ወደ ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ ሔደች። እርሱም በደስታ ተቀብሎ የክርስቶስን ሃይማኖት አስተማራት።

በማግሥቱም እናቷ እየፈለገቻት በመጣች ጊዜ ከቅዱስ ጳውሎስ ዘንድ አብራ ተቀምጣ አገኘቻት ከዚያም ወደ መኰንን ሒዳ ልጇን ክርስቲያን እንደሆነች ከሰሰቻት። መኰንኑም ከቅዱስ ጳውሎስ ጋራ እንዲያመጧት አዘዘ አስቀድመው ቅዱስ ጳውሎስን ወደ እሳት እንዲወረውሩት አዘዘ #እግዚአብሔርም አዳነው።

መኰንኑም የቅድስት ጤቅላን ቅጣት እንዲያዩ የሀገር ልጆችን ሰበሰበ ከዚህም በኋላ ወደ እሳት እንዲወረውሩዋት አዘዘ። በዚያን ጊዜ በክርስቶስ ማዕተብ ራሷን አማትባ ራስዋን በራስዋ ወደ እሳት ወረወረች ማንም ያያት ሳይኖር ከእሳት ውስጥ ወጥታ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሔደች የራስዋን ጠጒር ቆርጣ ወገቧንም ታጥቃ ቅዱስ ጳውሎስን ተከተለችው።
መኰንኑም ደኅንነቷን በሰማ ጊዜ ያዛት ሃይማኖቷንም እንድትተው አስገደዳት አይሆንም ባለችውም ጊዜ አንበሶችና ድብ ከሚያድሩበት እንዲጨምሩዋት አዘዘ። እነርሱም ሰገዱላትና የእግሮቿን ትቢያ ላሱ። ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው መኰንኑና ወገኖቹ አመኑ አንድ አምላክ በሚሆን በ #አብ#ወልድ#መንፈስ_ቅዱስ ስም ተጠመቁ በ #ክርስቶስም መንጋዎች ውስጥ ሆኑ።

እርሷ ቅድስት ጤቅላም ክብር ይግባውና የ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ወንጌልን በማስተማር ቅዱስ ጳውሎስን እያገለገለችው ኑራ በሰላም አረፈች።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድስቷ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አንጢላርዮስ

በዚህችም ቀን የቀራጮች አለቃ የነበረ ቅዱስ አንጢላርዮስ አረፈ። ይህም ቅዱስ አስቀድሞ በማንም ላይ ርኅራኄ የሌለው ነበረ በአንዲትም ዕለት ድኆች በአንድ ቦታ እያሉ በአንጻራቸው አልፎ ሲሔድ በአዩት ጊዜ ስለርሱ እንዲህ አሉ።

ይህ ባለጸጋ በድኆች ላይ ምንም ምን ርኅራኄ የሌለው ነው ከእነርሱም አንዱ እኔ ሔጄ ከእርሱ ምጽዋት ተቀብዬ ብመጣ ምን ትሰጡኛላችሁ አላቸው እነርሱም አንተ ከእርሱ ምጽዋትን ካገኘህ ያልከውን እንሰጥሃለን አሉት በዚህም ነገር ከተከራከሩ በኋላ ወደ አንጢላርዮስ ቤት ሒዶ ምጽዋትን ለመነው አንጢላርዮስም ከመሶቡ እግር የደረቀ ለከት ዳቦ አንሥቶ በመበሳጨት ወርውሮ የድኃውን ራስ ፈቃው ድኃውም ወደ ባልንጀሮቹ ተመልሶ ያንን ለከት አሳያቸው።

በዚያቺም ሌሊት አንጢላርዮስ በሕልሙ ራእይን አየ እርሱ በፍርድ አደባባይ ቁሞ ሳለ የጠቆሩ ሰዎች ስለ ክፋቱ ብዛት ሲከራከሩት ብርሃን የለበሱ ሰዎች ደግሞ ከዚች ለከት ዳቦ በቀር በርሱ ዘንድ ያደረገውን ምጽዋት አላገኘንም ብለው ሲያዝኑ በሚዛንም በመዘኑዋት ጊዜ ከኃጢአቱ ሁሉ ተስተካከለች። በዚያንም ጊዜ ነቃ በልቡም ሳልወድ የሠራሁት ይህን ያህል ጠቃሚ ከሆነ ወድጄ ብሠራውማ እጥፍ ድርብ የሆነ ዋጋ የማገኝ አይደለምን አለ።

ከዚህም በኋላ ተነሥቶ ገንዘቡን ጥሪቱን ሁሉ አውጥቶ ለድኆችና ለችግረኞች መጸወተ። ገንዘቡንም ሁሉ ከጨረሰ በኋላ ከሩቅ ቦታ ድኆች መጥተው ምጽዋትን ለመኑት እርሱም ገንዘቡን ሁሉ እንደ ጨረሰ ነገራችውና እጅግ አዘኑ እንዳዘኑም አይቶ እንዲሸጡት ፈቀደላቸው እነርሱም ሸጡትና የሽያጩን ገንዘብ ተከፋፈሉ።

በተሸጠበትም እንደባሪያ እያገለገለ ኖረ የጌታው ባሮችም በሚያሳዝኑት ጊዜ ብርሃናዊ ሰው ተገልጦ አትዘን የተሸጥክበትን ዋጋ እኔ ተቀብዬዋለሁ እነሆ በእጄ ውስጥ አለና ይለዋል።

ከዚህም በኋላ አስቀድሞ ከነበረበት የመጡ ሰዎች ሥራውን በገለጡበት ጊዜ በሥውር ሸሽቶ ወደ ከተማው በር ደረሰ በሩን የሚጠብቀውም ዲዳና ደንቆሮ ነበር። አንጢላርዮስም በሩን ክፈትልኝ በአለው ጊዜ ከአፉ በእሳት አምሳል ወጥቶ በረኛውን ነካው ያን ጊዜ አንደበቱ ተፈታ ጆሮዎቹም ሰሙ በሩንም ከፍቶለት ወደ በረሀ ሔደ በዚያም ገድሉን ፈጽሞ አረፈ።

ሰዎችም በአጡት ጊዜ ወደ በሩ መጡ በረኛውም የሆነውን ሁሉ ነገራቸው ከቅድስናውና ከተአምራቱም የተነሣ እጅግ አደነቁ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ አንጢላርዮስ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ዮሐንስ_ዘደብረ_ጽጌ

በዚህችም ቀን ደግሞ የደብረ ጽጌ አባ ዮሐንስ አረፈ። ይህም ቅዱስ አብዝቶ ከመጾሙ ተግቶም ከመጸለዩ የተነሣ ሥጋው ጠውልጎ እንደ ደረቀ ምድር ሆነ። በአንዲትም ቀን በጋን የመላ ውኃ በአፈሰሱበት ጊዜ ከሥጋው ድርቀት ብዛት የተነሣ ከእርሱ ምንም አልነጠበም።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም)