ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#መስከረም_11

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ዐሥራ አንድ በዚህች ቀን #ቅዱስ_ፋሲለደስ በሰማዕትነት አረፈ፣ #ቅዱስ_ቆርኔሌወስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው፣ #ቅድስት_ታዖድራ አረፈች፣ #ቅድስት_በነፍዝዝ የስሟ ትርጓሜ ጣፋጭ የሆነ በሰማዕትነት አረፈች፣ #ሦስቱ_ቅዱሳን_ገበሬዎች (#ሱርስ#አጤኬዎስ#መስተሐድራ) በሰማዕትነት አረፉ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ፋሲለደስ_ሰማዕት

መስከረም ዐሥራ አንድ በዚህች ቀን ለአንጾኪያ ነገሥታት አባታቸውና መካሪያቸው የሆነ ቅዱስ ፋሲለደስ በሰማዕትነት አረፈ።

እርሱም ለሮም ንጉሥ የሠራዊት አለቃ ነው መንግሥቱም ሁለመናዋ በእርሱ ምክር የጸናች ናት። ብዙዎችም ወንዶችና ሴቶች የቤት ውልዶች አገልጋዮች አሉት።

ዝምድናውም እንዲህ ነው ስሙ ኑማርያኖስ የተባለ የሮም ንጉሥ ለቴዎድሮስ በናድሌዎስ እናቱ የሆነች የቅዱስ ፋሲለደስን እኅት አግብቶ ዮስጦስን፣ ገላውዴዎስን፣ አባዲርን ወለደችለት እሊህም ለቅዱስ ፋሲለደስ የእኅቱ ልጆች ናቸው። የቅዱስ ፋሲለደስም ሚስት ለቅዱስ ፊቅጦር እናት እኅት ናት ከእርሷም ስማቸው አውሳብዮስና መቃርስ የተባሉ ሁለት ልጆችን ወለደ።

በዚያም ወራት የቊዝና የፋርስ ሰዎች የሮምን ሰዎች ሊወጓቸው በላያቸው ተነሡ ያን ጊዜ የንጉሥ ልጅ ዮስጦስን የፋሲለደስ ልጅ አውሳብዮስን ከጦር ሠራዊቶቻቸው ጋር ለውጊያ ላኳቸው።

ንጉሡ ኑማርዮስም ሌሎች ጠላቶች በተነሡበት በኩል ለጦርነት ሒዶ በውጊያው ውስጥ ሞተ የሮም መንግሥትም የሚጠብቃትና የሚመራት የሌላት ሆነች።

እንዲህም ሆነ በዚያ ወራት ስለ ጦርነት ለመደራጀት የሮም ሰዎች ከሀገሩ ሁሉ አርበኞች የሆኑ ሰዎችን ሰበሰቡ ከውስጣቸውም ከላይኛው ግብጽ ስሙ አግሪጳዳ የሚባል የፍየሎች እረኛ የሆነ አንድ ሰው አለ። እርሱንም መኳንንቱ ወስደው በመንግሥት ፈረሶች ላይ ባልደራስ አድርገው ሾሙት እርሱም በጠባዩና በሥራው ሁሉ ኃይለኛና ብርቱ ነበር።

ከንጉሥ ኑማርያኖስ ሴቶች ልጆች አንዲቱ ወደርሱ በመስኮት ተመለከተች ወደደችውም መልምላም ወስዳ አገባችው ስሙንም ዲዮቅልጥያኖስ ብላ ሰይማ አነገሠችው። ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ሰማይና ምድርን የፈጠረ #እግዚአብሔርን ትቶ ጣዖታትን አመለከ ቅዱስ ፋሲለደስም ሰምቶ እጅግ አዘነ የመንግሥትንም አገልግሎት ተወ።

ከዚህም በኋላ የንጉሥ ኑማርያኖስ ልጅ ዮስጦስና የፋሲለደስ ልጅ አውሳብዮስ ጠላቶቻቸውን ድል አድርገው የጠላቶቻቸውንም አገሮች አጥፍተው ደስ ብሏቸው ተመለሱ። ነገር ግን የነገሠው ዲዮቅልጥያኖስ የክብር ባለቤት #ክርስቶስን ክዶ አምልኮ ጣዖትን አቁሞ አገኙት እጅግም አዘኑ ተቆጥተውም ተነሡ ሰይፎቻቸውን መዝዘው ዲዮቅልጥያኖስን ገድለው የንጉሥ ኑማርያኖስን ልጅ ዮስጦስን ሊያነግሡ ወደዱ ፋሲለደስም ከዚህ ሥራ ከለከላቸው።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ፋሲለደስ ዘመዶቹን፣ ሠራዊቱን፣ አገልጋዮቹንም ሁሉ ሰበሰባቸውና በክብር ባለቤት በክርስቶስ ስም ደሙን ሊያፈስ እንደፈለገ አስረዳቸው ሁሉም እንዲህ ብለው መለሱለት አንተ በምትሞትበት ሞት እኛ ከአንተ ጋር እንሞታለን በዚህም ምክር በአንድነት ተሰማሙ።

ከዚህም በኋላ በንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ፊት ቁመው ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመኑ ከእርሳቸውም ግርማ የተነሣ ታላቅ ፍርሃትን ፈራ እነርሱ የመንግሥት ልጆች ናቸውና።

የቅዱስ ፊቅጦር አባት ኀርማኖስም ወደ ግብጽ አገር ይልካቸው ዘንድ በዚያም እንዲያሠቃዩዋቸው መከረው ሁሉንም እየአንዳንዳቸውን ለብቻቸው አድርጎ ላካቸው አባዲርንና እኀቱ ኢራኒን ወደ አንዲት አገር፣ አውሳብዮስንና ወንድሙ መቃርስን ወደሌላ ቦታ፣ ገላውዴዎስንም እንዲሁ አደረጉ። በናድሌዎስ ቴዎድሮስም እሼ በሚባል ዕንጨት ላይ በመቶ ሃምሳ ሦስት ችንካር ተቸንክሮ ገድሉን ፈጸመ።

ቅዱስ ፋሲለደስን ግን አምስት ከተማዎች ወዳሉበት ወደ አፍሪካ ምድር ወደ መኰንኑ ወደ መጽሩስ ላከው መጽሩስም በአየው ጊዜ መንግሥቱን ክብሩን ስለ ተወ እጅግ አደነቀ።

ክብር ይግባውና #ጌታችን_ክርስቶስም መልአኩን ልኮ በመንፈስ ወደ ሰማይ አውጥቶ በብርሃን ያጌጠ መንፈሳዊ ማደሪያን አሳየው ነፍሱም እጅግ ደስ አላት ከዚህም በኋላ ወደነበረበት መለሰው። ባሮቹን ግን ነፃ ያወጣቸው አሉ የቀሩትም ከእርሱ ጋር የሰማዕትነት አክሊልን የተቀበሉ ሰባት ሺህ ሠላሳ ሦስት የሚሆኑ አሉ።

ቅዱስ ፋሲለደስንም ታላቅ ስቃይን አሰቃዩት በመንኰራኲርና በተሣሉ የብረት ዘንጎች ሥጋውን ሰነጣጥቀውት ሞተ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም ያለ ጥፋት ከሞት አድኖ አስነሣው አሕዛብም ሁሉ ይህን ድንቅ ተአምር በአዩ ጊዜ አደነቁ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም አመኑ መኰንኑንም ረገሙት ጣዖቶቹንም ሰደቡ በእነርሱ ላይም ተቆጥቶ ራሶቻቸውን በሰይፍ ይቆርጧቸው ዘንድ ወታደሮቹን አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ ቊጥራቸውም ዐሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ወንዶች ሠላሳ ሰባት ሴቶች ናቸው።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ፋሲለደስን ሥጋው ሁሉ ቀልጦ እንደ ውኃ እስከሚሆን በብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት መኰንኑም በተራራ ላይ ጥልቅ ጒድጓድ ቆፍረው በዚያ እንዲቀብሩት አዘዘ እንዲሁም አደረጉ። ያን ጊዜም ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ቅዱስ ፋሲለደስን ከሞት ደግሞ አስነሣው ወደ መኰንኑም መጥቶ እንዲህ ብሎ ጮኸ መኰንን መጽሩስ ሆይ እፈር ከሀዲ ንጉሥህም የረከሱ ጣዖቶችህም ይፈሩ እነሆ ክብር ይግባውና #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ ያለ ጉዳት ከሞት ጤነኛ አድርጎ አስነሥቶኛልና።

ሕዝቡም ይህን ተአምር በአዩ ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት ሞቱ ቁጥራቸውም ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ሆነ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ፋሲለደስን በውስጧ መጋዝ ካላት መንኰራኲር ላይ አውጥቶ ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው ዳግመኛም በብረት ዐልጋ ላይ በሆዱ አስተኝተው ከበታቹ እሳትን አነደዱ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ተገለጠለት ከዚያ ስቃይም ውስጥ አንስቶ ያለ ጉዳት ጤነኛ አደረገው እንዲህም ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠው ፋሲለደስ ሆይ ዕውቅ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ ወይም ለድኆች በስምህ ምጽዋትን ለሚሰጥ ወይም ለተራቈተ ልብስን ወይም በመታሰቢያህ ቀን ለቤተ ክርስቲያን መባ ለሚሰጥ በብዙም ቢሆን በጥቂት መታሰቢያህን ለሚያደርጉ ሁሉ እኔ በደላቸውን ሁሉ እተውላቸዋለሁ መኖሪያቸውንም በመንግሥተ ሰማያት ከአንተ ጋራ አደርጋለሁ።

ጌታችንም ይህን ካለው በኋላ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ ቅዱስ ፋሲለደስም በፍጹም ደስታ ደስ ተሰኘ።

ከዚህም በኋላ መጽሩስ መኰንን ከአማካሪዎቹ ጋር ተማከረ እንዲህም አላቸው ስሙ ፋሲለደስ ስለሚባል ስለዚህ ሰው ምን ላድርግ እርሱን ያላሠቃየሁበት የሥቃይ መሣሪያ ምንም የቀረ የለም ከሐሳቡም አልተመለሰም እነርሱም እንዲህ ብለው መከሩት ራሱን በሰይፍ ቆርጠህ ከእርሱ ተገላገል እነሆ የዚች አገር ሰዎች በእርሱ ምክንያት አልቀዋልና።

በዚያንም ጊዜ የቅዱስ ፋሲለደስን ራስ በሰይፍ እንዲቆርጡ መኰንኑ አዘዘና ቆረጡት የድል አክሊልን ተቀበለ ንቆ ሰለ ተዋት ምድራዊት መንግሥት ፈንታም ሰማያዊት መንግሥት አገኘ። ከሥጋውም ድንቆች የሆኑ ታላላቅ ተአምራት ተገለጡ ከእርሱም ጋር ሰማዕት ሁነው የሞቱ ሁሉም ቊጥራቸው ሃያ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ዘጠና ሦስት ሆነ።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ፋሲለደስና በሰማዕታት ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ቅዱስ_ቆርኔሌዎስ_ሐዋርያዊ

በዚህችም ቀን የጭፍራ አለቃ የሆነ ትሩፋቱና ገድሉም ያማረ ጻድቅ ሰው ቆርኔሌዎስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው እርሱም በቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት ዘመን #እግዚብሔርን ያገለገለ ነው።

#እግዚአብሔር መልአክም ተገልጦለት ሐዋርያ ጴጥሮስን ይጠሩት ዘንድ ሰዎችን እንዲልክ ጴጥሮስም ወደርሱ እንዲመጣ ሊሠራው የሚገባውን ከእርሱ ከጴጥሮስ እንዲሰማ አዘዘው።

ጴጥሮስም ወደርሱ በደረሰ ጊዜ የ #እግዚአብሔርን ቃል አስተማረው ለርሱና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ ከሁሉ ቤተሰቡ ጋር አምኖ ተጠመቀ። ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ ለእስክንድርያ አገር ቅስና ሾመው ወደርሷ በደረሰ ጊዜ የጣዖታትን አምልኮ ተመልታ አገኛትና አስተማራቸው ብዙዎችንም ወደቀናች ሃይማኖት መልሶ አጠመቃቸው መኰንኑ ድሜጥሮስም አምኖ ከወገኖቹ ጋር በእርሱ እጅ ተጠመቀ።

የኑሮውን ዘመንና ሐዋርያዊ ተጋድሎውን አድርሶ በሰላም አረፈ እርሱም ከአሕዛብ አስቀድሞ ያመነ የመጀመሪያ አማኒ ነው።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሱ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ታዖድራ

በዚህችም ቀን ከእስክንድርያ አገር በንጉሥ ዘይኑን ዘመን ቅድስት ታዖድራ አረፈች።

ይችንም ቅድስት ሌላ ሰው አስገድዶ ከባሏ ወስዶ ከባሏ ጋር ያላትን አንድነት አበላሸ ያን ጊዜም ታላቅ ኀዘን በማዘን ተጸጸተች መሪር ልቅሶንም አለቀሰች የወንዶችንም ልብስ ለብሳ ወንድ መሰላ ከእስክንድርያ በሥውር ወጣች ስሟንም ቴዎድሮስ ብላ ሰየመችና ወደ ወንዶች ገዳም ገባች የምንኲስና ልብስንና የመላእክትን አስኬማ ለበሰች።

የሚያዩዋት ሁሉ እርሷ እንደ ጃንደረባ የሆነች ወንድ ትመስላቸው ነበር እርሷ ግን በረኃብ፣ በጽምዕ ሌሊት በመትጋት ቀን በመቆም ጸንታ በመጋደል ላይ ታገሠች እንዲህም በመጋደል ተጠምዳ ብዙ ዘመን ኖረች።

በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ አንድ ሰው ከአንዲት ብላቴና ጋር አመነዘረ እርሷም ፀንሳ ወንድ ልጅን ወለደች ወላጆቿም ድንግልናሽን ያጠፋው ማነው ብለው ጠየቋት እርሷም በገዳም ውስጥ የሚኖር አባ ቴዎድሮስ እርሱ ደፍሮኝ ከእርሱ ፀነስኩ ብላ በዚች ቅድስት ታኦድራ ላይ በሐሰት ተናገረች።

ወላጆቿም በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ ሕፃኑንም ወደዚያ ገዳም አበ ምኔት ወሰዱት እንዲህም አሉት ይህ ሕፃን የልጅህ የመነኵሴው የቴዎድሮስ ልጅ ነው ። ያን ጊዜም አበ ምኔቱ ይቺን ቅድስት ታኦድራን ጠራትና እንዲህ አላት ይህን ክፉ ሥራ ለምን ሠራህ በመነኰሳቱም ሁሉ ላይ ኀፍረትንና ጒስቁልናን አመጣህ እርሷ ሴት መሆኗን አላወቀምና እርሷም አባቴ ሆይ በድያለሁና ይቅር በለኝ አለችው።

አበ ምኔቱም ተቆጥቶ ከገዳሙ አስወጥቶ አባረራት በበረሀ ውስጥ ሰባት ዓመት ኖረች ያም ሕፃን ከእርሷ ጋር ሁኖ ከሰይጣናት በሚመጡባት በብዙ መከራዎች ብዙ መከራዎች ላይ ታገሠች ብዙ ሥቃያትንም ፈጽሞ አሠቃዩዋት።

ከዚህም በኋላ ዳግመኛ ተቀብለው ወደ ገዳም አስገቡአት ጥቂት ቀንም ኖረች መልካም ተጋድሎዋንም ፈጽማ በሰላም አረፈች ነፍሷንም በ #እግዚአብሔር እጅ ሰጥታ የዘላለም ሕይወትን አገኘች።

#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_በነፍዝዝ_ሰማዕት

በዚህች ቀን የስሟ ትርጓሜ ጣፋጭ የሆነ የከበረች በነፍዝዝ በሰማዕትነት አረፈች። ይቺም ቅድስት በእድሜዋ ፈጽማ የሸመገለች ነበረች በፋርስ ንጉሥ በሳቦር ዘመንም መከራ ተቀበለች ከዘጠኝ መቶ ክርስቲያን ጋር ማርከው ወስደው አሠሩዋት የሠራዊቱም አለቃ ታላቅ ሥቃይን አሠቃይቶ ከዚያ በኋላ ራሷን በሰይፍ ቆረጠ።

ራሷንም ከአስቆረጣት በኋላ ከአንገቷ የፈሰሰው ደም እስከ ራቀ ድረስ ወደ ላይ ወጣ ከዚያ የተቀመጡ ጠላቶችም ኃይላቸው ደከመ። የፀሐይ ብርሃንም ጨለመ በዚያም ቦታ ደግሞ ጣፋጭ የሆነ መዐዛ ተመላ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሦስቱ_ቅዱሳን_ገበሬዎች
(ሱርስ፣ አጤኬዎስ፣ መስተሐድራ)

በዚህችም ቀን ስማቸው ሱርስ፣ አጤኬዎስ፣ መስተሐድራ የሚባል ሦስት ገበሬዎች የእስና አገር ሰዎች በሰማዕትነት አረፉ ። አርያኖስም ከሀገሪቱ በስተደቡብ ምንም ሳያስቀር ወታደሮቹ እስከ ደከሙ ድረስ ሰይፋቸውንም ወደ አፎቱ መልሰው ነበር የአገር ሰዎችን ጨርሶ ገድሎ ሲመለስ እሊህ ሦስቱ ገበሬዎች ከዱር ሲመለሱ በከተማ መካከል በተገናኙት ጊዜ እኛ ክርስቲያኖች ነን ብለው በግልጥ ጮኹ አርያኖስም ሰምቶ ወታደሮቹን እሊህን ገበሬዎች ትገድሏቸው ዘንድ ይገባል አላቸው።

ወታደሮቹም እኛ ደክመናል ሰይፎቻችንንም ወደ አፎታቸው አስገብተናል አሉት እሊህ ቅዱሳንም ሰምተው እነሆ መቆፈሪያዎች ከእኛ ጋራ አሉ በእነርሱ ግደሉን አሉ ከዚያም አንገታቸውን በደንጊያ ላይ አድርገውላቸው ቆረጡአቸው።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም_11)