ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
7.08K subscribers
1.29K photos
8 videos
37 files
262 links
የዲ.ን ዮርዳኖስ አበበ ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#መስከረም_22

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ሃያ ሁለት በዚህች ቀን የፋርስ ንጉሥ የሳቦር ልጆች #የከበሩ_ኮቶሎስና_እኅቱ_አክሱ#የከበረ_ዮልዮስ በሰማዕትነት ያረፉበት መታሰቢቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ኮቶሎስና_እኅቱ_ቅድስት_አክሱ

መስከረም ሃያ ሁለት በዚች ቀን የፋርስ ንጉሥ የሳቦር ልጆች የከበሩ ኮቶሎስና እኅቱ አክሱ በሰማዕትነት አረፉ።

ለቅዱስ ኮቶሎስም ጣጦስ የሚባል ክርስቲያን ወዳጅ አለው ይህም ንጉሥ ሳቦር እሳትን የሚያመልክ ነው ብዙዎች ምእመናንን ስለሚያሠቃያቸው ክብር ይግባውና የ #ክርስቶስን ስም ይጠራ ዘንድ በዚያ ወራት የደፈረ የለም።

ይህም ጣጦስ በአንዲት አገር ላይ ገዥ ነበር እርሱ ክርስቲያን እንደሆነ በንጉሡ ዘንድ ወነጀሉት። ንጉሡም ስለርሱ የተነገረው እውነት እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያረጋግጥ ዘንድ ሌላውን መኰንን ወደርሱ ላከ። ሁለተኛም ክርስቲያንን ያገኘ እንደሆነ ጽኑዕ ሥቃይ እንዲያሠቃይ አዘዘው።

የንጉሥ ልጅ ኮቶሎስም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ወዳጁ ጣጦስ ወደአለባት ወደዚያች አገር ሔደ ያ መኰንንም በደረሰ ጊዜ ጣጦስን በንጉሥ እንደ ወነጀሉት እንዲሁ ክርስቲያን ሁኖ አገኘው በዚያን ጊዜም የእሳት ማንደጃ ሠርተው ጣጦስን እንዲአቃጥሉት አዘዘ ቅዱስ ጣጦስ ግን በ #መስቀል ምልክት በእሳቱ ላይ አማተበ እሳቱም የኋሊት ተመልሶ ጠፋ።

ኮቶሎስም ይህን ተአምር በአየ ጊዜ እጅግ አድንቆ ጣጦስን ወንድሜ ሆይ ይህን ሥራይ እንዴት ተማርክና አወቅህ አለው። ጣጦስም ይህ ከሥራይ አይደለም ክብር ይግባውና ከ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ሃይማኖት ይህ ድንቅ ተአምር እንጂ ብሎ መለሰለት።

ኮቶሎስም እኔ በ #ክርስቶስ የማምን ከሆንኩ እንደዚህ ልሠራ እችላለሁን? አለው ጣጦስም እንዲህ ብሎ መለሰለት በእርሱ ካመንክበት ከዚህ የሚበልጥ ተአምራት ታደርጋለህ።

በዚያንም ጊዜ ቅዱስ ኮቶሎስ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመነ በዚያን ጊዜም ነበልባሉ እጅግ ከፍ ከፍ እስከሚል እሳቱን አነደዱ ቅዱስ ኮቶሎስም ቀረብ ብሎ በእሳቱ ላይ በ #መስቀል ምልክት አማተበ እሳቱም ወደ ኋላ ዐሥራ ሁለት ክንድ ተመለሰና ጠፋ።

ከዚህም በኋላ መኰንኑ ወደ ንጉሥ ሳቦር ከመኰንኑ ከጣጦስና ከልጁ ከኮቶሎስ የሆነውን ሁሉ ጻፈ ንጉሡም ሰምቶ ጭፍራ ልኮ አስቀረባቸው የቅዱስ ጣጦስንም ራሱን በሰይፍ ቆረጠውና የሰማዕትነትን አክሊል ተቀበለ።

ልጁን ቅዱስ ኮቶሎስን ግን ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየውና ደግሞ እንዲአሠቃየው ለሌላ መኰንን ሰጠው እርሱም ብዙ ካሠቃየው በኋላ አሠረው። እኅቱም አክሱ ወደ እሥር ቤት ወደርሱ መጣች ወደ ቀድሞ ሥራው እንዲመለስ ትሸነግለው ዘንድ አባቷ ልኳታልና። እርሱ ግን እኅቱን ገሠጻት መከራት የቀናች ሃይማኖትንም አስተማራት ያን ጊዜም ከስኅተቷ ተመልሳ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመነች።

ከዚህም በኋላ ወንድሟ ቅዱስ ኮቶሎስ ወደ አንድ ቄስ ላካት እርሱም የክርስትና ጥምቀትን በሥውር አጠመቃት። ወደ አባትዋም ተመልሳ እንዲህ አለችው አባቴ ሆይ ለእኔና ለወንድሜ ለኮቶሎስ የሆነው ላንተ ቢደረግልህ ይሻልሃል ክብር ይግባውና ሰማይና ምድርን በውስጣቸውም ያለውን ሁሉ ከፈጠረ ከ #ጌታዬ_ኢየሱስ_ክርስቶስ በቀር ሌላ አምላክ የለምና።

ይህንንም ነገር አባቷ ከእርሷ በሰማ ጊዜ በእርሷ ላይ እጅግ ተቆጥቶ ነፍሷን በ #እግዚአብሔር እጅ እስከ ሰጠች ድረስ ጽኑዕ ሥቃይን እንዲአሠቃዩአት አዘዘ በዚህም ምስክርነቷን ፈጽማ የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለች።

ወንድሟን ቅዱስ ኮቶሎስን ግን በፈረሶች ጅራት ውስጥ አሥረው በተራራዎች ላይ አስሮጧቸው ሥጋውም ተቆራርጦ ተበተነ ነፍሱንም በፈጣሪው እጅ ሰጠ። የቀረ ሥጋውንም ወደ ሦስት ቆራርጠው የሰማይ ወፎች ይበሉት ዘንድ በተራራ ላይ ጣሉት በእንደዚህም ሁኔታ ምስክርነቱን ፈጽሞ የሕይወት አክሊልን በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

ወታደሮችም ሲመለሱ የሰማዕታትን ሥጋ ይወስዱ ዘንድ በሀገር አቅራቢያ ያሉ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን #እግዚአብሔር አዘዛቸው እነርሱም በሌሊት ሔደው የቅዱሳን ሰማዕታትን ሥጋቸውን ወስደው በታላቅ ክብር ገነዙአቸው እንደ በረዶም ነጭ ሁነው አግኝተዋቸዋልና። የመከራው ወራትም እስቲፈጸም ድረስ በመልካም ቦታ አኖሩአቸው።

ከዚያም በኋላ ያማረች ቤተ ክርስቲያን ተሠርታላቸው የቅዱሳን ሥጋቸውን በዚያ አኖሩ ከሥጋቸውም ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዮልዮስ_በሰማዕትነት

በዚችም ቀን የከበረ ዮልዮስ በሰማዕትነት ያረፈበት መታሰቢያው ነው። ይህም ቅዱስ አቅፋሐስ ከሚባል አገር ነው ክብር ይግባውና #ጌታችንም ስለ ቅዱሳን ሰማዕታት ለሥጋቸው እንዲአስብ ገድላቸውንም እንዲጽፍ ሥጋቸውንም ገንዞ እየአንዳንዱን ወደ ሀገራቸው እንዲልክ ያቆመው ነው።

#እግዚአብሔርም በመኳንንቱ ልብ መታወርን ስለ አመጣ ለሰማዕታት ይህን ያህል በጎ ሥራ ሲሠራ ምንም ነገር አይናገሩትም ስለ ጣዖት አምልኮም አያስገድዱትም ነበር። ጽሕፈትም የሚያውቁ ሦስት መቶ አገልጋዮች አሉት እነርሱም የሰማዕታትን ገድላቸውን እየተከታተሉ ይጽፋሉ።

በመሠቃየትም ሳሉ ሰማዕታትን ያገለግላቸዋል በቊስላቸውም ውስጥ መድኃኒት ያደርግላቸዋል ሰማዕታትም ይመርቁታል እንዲህ ብለውም ትንቢት ይናገሩለት ነበር። አንተም ክብር ይግባውና ስለ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ደምህ ይፈስ ዘንድ አለህ ከቅዱሳን ሰማዕታትም ጋራ ትቈጠራለህ።

የከሀዲው ዲዮቅልጥያኖስ የግዛቱ ዘመን በተፈጸመ ጊዜ ዮልዮስን ከቅዱሳን ሰማዕታት ከቁጥራቸው አንድ ሊአደርገው ወዶ ቅዱሳን ሰማዕታትም ትንቢት እንደተናገሩለት በመኰንኑ ፊት ስለ ከበረ ስሙ ይታመን ዘንድ ለግብጽ አገር ደቡብ ወደሆነች ወደ ገምኑዲ ወደ መኰንኑ አርማንዮስ እንዲሔድ ክብር ይግባውና #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አዘዘው።

ወዲያውኑ ተነሥቶ ሔደ ከዚያም ደርሶ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ታመነ መኰንኑም ታላቅ ሥቃይን ብዙ ጊዜ አሠቃየው #እግዚአብሔርም ያለ ጥፋት በጤና ያነሣው ነበር። ከዚህም በኋላ ምድር አፍዋን ከፍታ ጣዖታቱን ትውጣቸው ዘንድ ቅዱስ ዮልዮስ ክብር ይግባውና ወደ #እግዚአብሔር ጸለየ ወዲያውኑ አፍዋን ከፍታ ሰብዓ ጣዖታትን መቶ ሠላሳ የሆኑ ካህናቶቻቸውን ዋጠቻቸው።

በዚያንም ጊዜ ቅዱስ ዮልዮስን አምጥተው ለአማልክት በግድ እንዲአሰግዱት መኰንኑ አዘዘ ጣዖታቱን ግን ከካህናቶቻቸው ጋር ጠፍተው አገኙአቸው በዚያ ያሉ ሕዝቦችም ይህን አይተው እጅግ አደነቁ። ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስም አመኑ መኰንኑ አርማንዮስም ጣዖታቱ ከካህናቶቻቸው ጋር እንደ ጠፉ በአየ ጊዜ ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አመነ። ከቅዱስ ዮልዮስም ጋር ወደ አትሪብ ሔደው በመኰንኑ ፊት ክብር ይግባውና በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ስም ታመኑ የአትሪብ መኰንን ግን ቅዱስ ዮልዮስን እጅግ ጭንቅ የሆነ ሥቃይን አሠቃየው ክብር ይግባውና #ጌታችንም ያለ ጥፋት ያነሣው ነበር።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
#መስከረም_22_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበቡት_መልእክታት👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
2ኛ ቆሮ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁷ ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤
⁸ በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤
⁹ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤
¹⁰ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን።
¹¹ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የሆንን ከኢየሱስ የተነሣ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለንና።
¹² ስለዚህ ሞቱ በእኛ ሕይወቱም በእናንተ ይሠራል።
¹³ ነገር ግን፦ አመንሁ ስለዚህም ተናገርሁ ተብሎ እንደ ተጻፈ ያው አንዱ የእምነት መንፈስ ስላለን፥ እኛ ደግሞ እናምናለን ስለዚህም እንናገራለን፤
¹⁴ ጌታን ኢየሱስን ያስነሣው እኛን ደግሞ ከኢየሱስ ጋር እንዲያስነሣን ከእናንተም ጋር እንዲያቀርበን እናውቃለንና።
¹⁵ በብዙዎች በኩል የተትረፈረፈው ጸጋ ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋናን ያበዛ ዘንድ፥ ሁሉ ስለ እናንተ ነውና።
¹⁶ ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል።
¹⁷-¹⁸ የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት፥ ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና፤ የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
1ኛ ጴጥሮስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹² ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤
¹³ ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ።
¹⁴ ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ።
¹⁵ ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጒዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤
¹⁶ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።
¹⁷ ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፤ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን?
¹⁸ ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው?
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ሐዋርያት 19
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁸ ወደ ምኵራብም ገብቶ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተነጋገረና እያስረዳቸው ሦስት ወር ያህል በግልጥ ይናገር ነበር።
⁹ አንዳንዶች ግን እልከኞች ሆነው በሕዝብ ፊት መንገዱን እየሰደቡ ባላመኑ ጊዜ፥ ከእነርሱ ርቆ ደቀ መዛሙርትን ለየ፥ ጢራኖስም በሚሉት በትምህርት ቤት ዕለት ዕለት ይነጋገር ነበር።
¹⁰ በእስያም የኖሩት ሁሉ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም የጌታን ቃል እስኪሰሙ ድረስ ሁለት ዓመት ያህል እንዲህ ሆነ።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_22_ቀን_በቅዳሴ_ሰዓት_የሚነበበው_የሚዜመው_የቅዳሴ_ምስባክ👇

✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
"እስመ አቡየ ገደፉኒ። ወእግዚአብሔር ተወከፈኒ። ምርሀኒ እግዚኦ ፍኖተከ"። መዝ 26፥10-11 ወይም መዝ 33፥19።
"አባቴና እናቴ ትተውኛልና፥ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ። አቤቱ፥ መንገድህን አስተምረኝ፥ ስለ ጠላቶቼም በቀና መንገድ ምራኝ"። መዝ 26፥10-11 ወይም መዝ 33፥19።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️

#መስከረም_22_ቀን_የእለቱን_ወንጌል_እናንብብ📖👇
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
ማርቆስ 13
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
⁹ እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል በምኵራብም ትገረፋላችሁ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ።
¹⁰ አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል።
¹¹ ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፥ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።
¹² ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ። ይገድሉአቸውማል፤
¹³ በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️
የሚቀደሰው ቅዳሴ የ #ቅዱስ_ዮሐንስ_ወልደ_ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።
✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️✝️