ቅዱሳን ኅሩያን የዲ°ን ዮርዳኖስ ትምህርቶች
4.84K subscribers
723 photos
5 videos
13 files
233 links
የዲ.ን ሄኖክ ሀይሌን ስብከት በድምጽ እንለቃለን
ለአስተያየት @EMNE_TSYON @unitte_bot
በቴሌግራም ከፈለጉን @henokhailee
በfacebook ከፈለጉን https://www.facebook.com/tewahidosewhone/
በyoutube ከፈለጉን https://youtube.com/channel/UCq2ueVG6O3ZuKHJ485y7hfg
Download Telegram
#ነቢይ_ወሰማዕት_ቅዱስ_ኤርምያስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ኤርምያስ” ማለት “እግዚአብሔር ከፍ ከፍ ያደርጋል” ማለት ነው፡፡ ከአራቱ ዓበይት ነቢያት አንዱ ሲኾን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን አባቱ “ኬልቅያስ” ይባላል፡፡ እናቱ ደግሞ “ማርታ” እንደምትባል የቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ትውፊት ያስረዳል፡፡ አገሩ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ካለው ከተማ ከ“ዓናቶት” ነው፤ ትውልዱም ከካህናት ወገን እንደነበረ ተጽፏል /ኤር.፩፡፩/፡፡

#ነቢዩ_ኤርምያስ ለነቢይነት የተለየው ከእናቱ ማኅፀን ዠምሮ ነው /ኤር.፩፡፮/፡፡ ይኸውም እንደ ነቢዩ ሳሙኤል፤ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ማለት ነው፡፡ አንድም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “በእናቴ ማኅፀን ሳለኹ የለየኝ …” እንዳለው ነው /ገላ. ፩፡፲፭/፡፡
#ነቢዩ_ኤርምያስ ለእስራኤል ብቻ ሳይኾን ለአሕዛብም ጭምር ነቢይ እንዲኾን በተጠራ ጊዜ ደንግጧል፤ “ሕፃን አንድም ሕፃነ አእምሮ ነኝና ወዮልኝ” በማለትም አመንትቷል፡፡ በዃላ ግን እግዚአብሔር፡- “እስራኤልና አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፣ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ትመልሳቸዋለኽና ሕፃን ነኝ አንድም ሕፃነ አእምሮ ነኝ አትበል” ተብሎ በተሰጠው ተስፋ መሠረት በረታ፡፡

#በነቢዩ_ዘመን በይሁዳ ነግሠው የነበሩት ነገሥታት አምስት ናቸው፡፡ እነርሱም፡-
1, ባዕድ አምልኮን ለማስወገድ፣ የእግዚአብሔርን ቤትና አምልኮ ለማሳደስ ብዙ የደከመው፣ በመሞቱም ነቢዩ ያለቀሰለት /፪ኛ ዜና ፴፬-፴፭/ ኢዮስያስ፤
2, በነገሠ በ፫ኛው ወር የግብጽ ንጉሥ አስሮ የወሰደው የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአክስ (ሰሎም) /፪ኛ ዜና ፴፮፡፩-፬፣ ኤር.፳፪፡፲-፲፪/፤
3, ፈርዖን ኒካዑ በወንድሙ በኢዮአክስ ምትክ በይሁዳ ያነገሠው፣ አስቀድሞ ለግብጽ በኋላም ለባቢሎን የተገዛው /፪ኛ ዜና ፴፮፡፬-፰/፣ በ፲፩ የንግሥና ዘመኑ እጅግ ክፉ የነበረው /ኤር.፳፪፡፲፫-፲፱/፣ የእግዚአብሔርን ቃል በመናቅ ኤርምያስን የተቃወመው መጽሐፉንም ያቃጠለበት /ኤር.፴፮/ ኢዮአቄም፤
4, ከአባቱ ከኢዮአቄም በኋላ በኢየሩሳሌም ለሦስት ወራት የነገሠ፣ በ፭፻፺፯ ከክ.ል.በ. ላይ ከቤተሰቦቹና ከአለቆቹ በጠቅላላ ከዐሥር ሺሕ ሰዎች ጋር ወደ ባቢሎን ተማርኮ የሔደው /፪ኛ ነገ.፳፬፡፰-፲፯፣ ኤር.፳፪፡፳፬-፴/ ዮአኪን (ኢኮንያን)፤
5, ከኢዮስያስ ልጆች ሦስተኛ የኾነው፣ የወንድሙ ልጅ ዮአኪን በተማረከ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከ፭፻፺፯-፭፻፹፯ ከክ.ል.በ. በይሁዳ ያነገሠው፣ ከነቢዩ ኤርምያስ ምክር ላይጠቀምበት ምክርን ይጠይቅ የነበረው፣ በክፋቱ የጸና፣ ከአራት ዓመት በኋላ ወደ ባቢሎን ተወስዶ የተመለሰው /ኤር.፶፩፡፶፱/፣ በኋላ ላይ በግብጽ ተማምኖ ባቢሎን ንጉሥ ላይ ያመፀው፣ ከዓመት ተመንፈቅ በኋላ ተይዞ የተማረከና ዕዉር ኾኖ በግዞት ቤት ሳለ የሞተው ሴዴቅያስ ናቸው፡፡

#ነቢዩ_ኤርምያስ የነበረበት ነባራዊ ኹኔታ....

#ነቢዩ_ኤርምያስ አገልግሎቱን የዠመረው የይሁዳ ንጉሥ ኢዮስያስ (ከ፮፻፵-፮፻፱ ከክ.ል.በ.) በነገሠ በ፲፫ኛው ዓመት ላይ ነበር፡፡ ይኸውም በ፮፻፳፮ ከክ.ል.በ. መኾኑ ነው፡፡ ይኽ ዓመት ደግሞ እጅግ በጣም ወሳኝ የኾነ ወቅት ነበር፡፡ በአንድ በኵል ንጉሥ ኢዮስያስ ባዕድ አምልኮን ለማስወገድ፣ የ #እግዚአብሔርን ቤትና አምልኮ ለማሳደስ ከዠመረ አንድ ዓመት ኾኖታል፡፡ በሌላ በኵል ደግሞ ባቢሎናውያን ከአሦር አገዛዝ ነፃ ለመውጣት አንድ ዓመት ይቀራቸው ነበር፡፡ ስለዚኽ ነቢዩ ኤርምያስ አገልግሎቱን የዠመረው በቤተ ክህነቱም በፖለቲካውም ወሳኝ ኩነቶች የሚፈጸሙበት ሰዓት ላይ ነበር ማለት ነው፡፡ ከዚኹ ጋር በተያያዘ የሰሜኑ ክፍል ሕዝብ ወደ ሶርያ ተማርኮ ከፈለሰ ገና ፻ ዓመቱ ነው (የተማረኩት በ፯፻፳፪ ከክ.ል.በ. መኾኑ ከዚኽ በፊት መነጋገራችን ያስታውሱ)፡፡
የሕዝቡን ግብረ ገብነት ስንመለከት ደግሞ፥ #በቤተ_መቅደስ ሔደው መሥዋዕት ስላቀረቡ ብቻ #እግዚአብሔርን ከልባቸው ያመለኩት ይመስላቸው ነበር፡፡ #እግዚአብሔር ግን ከመሥዋዕት ይልቅ #ልብን ነው የሚፈልገው፡፡ ይኸውም ሊቁ #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ፡- “እግዚአብሔር ከወርቃማ ምሥዋዕት ይልቅ ወርቃማ ነፍሳትን ይሻል” እንዳለው ነው፡፡ #ነቢዩ_ኤርምስያስ ይኽን የግብዝነት ምልልሳቸውን እንዲያስተካክሉ ነገራቸው፡፡ መፃተኛውን፣ ድኻ አደጉን፣ መበለቲቱን እየበደሉ እልፍ ጊዜ መሥዋዕት ማቅረባቸው ቤተ መቅደሱን የወንበዴዎች ዋሻ ማድረግ እንደኾነ አሳሰባቸው /ኤር.፯፡፰-፲/፡፡ ካልተመለሱ ግን እነርሱ በባዕድ ንጉሥ እንደሚማረኩ፥ ቤተ መቅደሱም እንደሚፈርስ በቤተ መቅደሱ በር ኾኖ በመጮኽ በግልጽ ነገራቸው /ኤር.፯፡፬/፡፡ ሕዝቡና ካህናቱ ግን አላመኑትም፡፡ ይባስ ብለዉም
#መቱት /ኤር.፳፡፪/፤
#በእግር ግንድ ያዙት፤
#በጭቃ ጕድጓድ ጣሉት፤
#ኹለት ጊዜ አሰሩት /ኤር.፴፯፡፲፫-፳፩/፤ #አብዷል አሉት /ኤር.፳፱፡፳፮/፡፡
ተወዳጆች ሆይ! እኛስ? እኛስ መፃተኛውን አልበደልንምን? ድኻ አደጉን አላንከራተትንምን? መበለቲቱን አላስከፋታንምን? ይኽን እንድናስተካክልስ እግዚአብሔር ስንት ጊዜ ተናገረን? ታድያ ቤተ መቅደሱ ሰውነታችን እስኪፈርስ ድረስ እየጠበቅን ነው? ወይስ እንደ ነቢዩ ቃል ተመልሰናል? እግዚአብሔር እስከ ዛሬ ድረስ የጠበቀን ከኀጢአታችን ጋር ተስማምቶ ሳይኾን የንስሐ ጊዜ ሲሰጠን ነው፡፡

#ነቢዩ_ኤርምያስ ልዩ ባሕርያት👇

1, በ #መጽሐፍ_ቅዱስ ውስጥ ስለ ደረሰበት መከራ እንደ ኤርምያስ ያለቀሰ ሰው የለም፡፡ በስነ መለኮት ምሁራን ዘንድ፡- “ #አልቃሻው_ነቢይ” እየተባለ መጠራቱም ይኽን ባሕርዩን የሚያመለክት ነው፡፡ ሰቆቃወ ኤርምያስ ማንበብም ይኽን ሐሳብ ግልጽ ያደርግልናል፡፡

2, የ #ጸሎት_ነቢይ ነው፡፡ ነቢዩ ኤርምያስ ከሌሎች ነቢያት ለየት የሚያደርገው ሌላኛው ነጥብ ከእግዚአብሔር ጋር የሚነጋገረው በጸሎት መኾኑ ነው፡፡ ትንቢቱን፣ ራዕዩን የሚገለጽለት ሲጸልይ ነው፡፡ ሲከፋው የሚያወያየው ወዳጅ ሚስት የለውም፤ አላገባምና፡፡ ልጅም የለውም፡፡ ስለዚኽ ሲከፋው፣ የወንድሞቹን ስቃይ ሲያይ፣ ቤተ መቅዱስን መፍረስ ሲመለከት ያለቅሳል፡፡ #እግዚአብሔርም ያናግሯል፡፡

3, #ነቢዩ ምንም እንኳን ኢየሩሳሌምንና ሕዝቡን ቢወድም /ኤር.፰፡፲፰-፱፡፩/፣ ፲፫፡፲፯/ መማረካቸው እንደማይቀር ሊነግራቸው ተገድዷል፡፡ ከዚኽም በላይ፡- “ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ስጡ፤ ተገዙም፤ ምርኮኞችም እስከ ፸ ዓመት ድረስ አይመለሱም” ብሎ የተገለጠለትን የ #እግዚአብሔርን ቃል ስለተናገረ ተጠላ፡፡ ብዙዎችም ሊገድሉት አሰቡ /ኤር.፲፩፡፳፩፣ ፳፮፡፲፩፣ ፴፮፡፲፮፣ ፴፰፡፮-፲/፡፡ #ተመታ /ኤር.፳፡፪/፤ #በእግር ግንድ ተያዘ ፤ #በጭቃ ጕድጓድ ተጣለ፤ #ኹለት ጊዜ ታሰረ /ኤር.፴፯፡፲፫-፳፩/፤ #አብዷል ተባለ /ኤር.፳፱፡፳፮/፡፡ ስለዚኽ ነቢዩ በራሱ መጽሐፍ ላይ ስለ ራሱና ስለደረሰበት መከራ ብዙ ስለ ጻፈ ከሌሎች ነቢያት ይልቅ ጠባዩና ኹኔታው ተገልጿል፡፡

4, ከዚኹ ኹሉ ጋር ለሕዝቡ ምልክት እንዲኾን ሚስት እንዳያገባ፣ ወደ ግብዣ ወይም ወደ ልቅሶ እንዳይሔድ ተከልክሏል /ኤር.፲፮/......።

#ትንቢተ_ኤርምያስ
#ነቢዩ_ኤርምያስ ትንቢቱን የተናገረው ከላይ በገለጽናቸው አምስት የይሁዳ ነገሥታት ዘመን ነው፡፡ እግዚአብሔር ኤርምስያስን በጠራው ጊዜ፡- “የይሁዳ ሕዝብ እኔን ትተው ሌሎች አማልክትን ስላመለኩ ከሰሜን ጠላት አስነሣባቸዋለኹ” ብሎ ነገረው /ኤር.፩፡፲፫-፲፮/፡፡ ኤርምያስም ሕይወታቸው ወደ ኾነው #እግዚአብሔር እንዲመለሱ ያለማቋረጥ ለ፳፫ ዓመታት ይጠራቸው ነበር፤ እነርሱ ግን አልሰሙትም /ኤር.፳፭፡፫-፯/፡፡ በዚያም፥ በተጠራ በ፳፫ኛው ዓመት ከሰሜን የሚመጣባቸው ንጉሥ ናቡከደነፆር በባቢሎን ነገሠ /ኤር.፳፭፡፩/፡፡ እርሱም በይሁዳ ላይ ብቻ ሳይኾን በብዙ ሕዝቦች ላይ እንደሚመጣ፣ እስከ ፸ ዓመትም ድረስ እነዚኽ ሕዝቦች ለባቢሎን እንደሚገዙ ተነበየ /ኤር.፳፭፡፰-፲፩/፡፡ ከዚኽም በኋላ ባቢሎን እንደሚወድቅ ገለጠ /ኤር.፳፭፡፲፪-፲፬/፡፡ ይኽን ከባድ የፍርድ መልእክት ለመናገር የበቃው በአምላኩ ኃይል እንጂ በራሱ ችሎታ አልነበረም /ኤር.፩፡፮-፲/፡፡ በእነዚኽም ፳፫ ዓመታት የተናገረው ትንቢት ኹሉ ተጽፎ ሲነበብለት ንጉሥ ኢየአቄም ጽሑፉን ቆራርጦ አቃጠለው፤ #ኤርምያስ ግን እንደገና በ #ባሮክ እጅ አስጻፈው /ኤር.፴፮/፡፡

ተወዳጆች ሆይ! እኛስ ስንት ጊዜ ተመለሱ ተብለን ይኾን? ስንት ጊዜስ የእግዚአብሔርን ቃል ችላ ብለን ተኝተን ይኾን? እስኪ ኹላችንም የየራሳችንን እንመልከት!!!

ሴዴቅያስ ከነገሠ ጊዜ ዠምሮ #ኤርምያስ፥ ሴዴቅያስን፡- “ለባቢሎን ንጉሥ ተገዙ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ ኢየሩሳሌምም አትጠፋም” ይለው ነበር /ኤር.፳፯፡፲፪-፲፯/፡፡ ሴዴቅያስ ግን በግብጽ ስለተማመነ /ኤር.፴፯፡፫-፲/፣ ደግሞም ስላመካኘ /ኤር.፴፰፡፲፱/ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ አልሰጠም፡፡ ከዚኽም የተነሣ በእርሱና በኢየሩሳሌም ላይ የደረሰው ፍርድ የባሰ ኾነ /ኤር.፴፱፡፩-፲፣ ፪ኛ ዜና ፴፮፡፲፩-፳፩/፡፡

#ነቢዩ_ኤርምያስ የፍርድን መልእክት ብቻ የተናገረ አይደለም፤ ጨምሮም የተስፋ ቃልን ተናግሯል፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከምርኮ እንደሚመልስ፣ ኢየሩሳሌም ታድሳ “#እግዚአብሔር ጽድቃችን” እንደምትባል /ኤር.፴፫፡፲፮/፣ #እግዚአብሔርም ከሕዝቡ ጋር አዲስ ኪዳንን እንደሚያደርግ፣ ከዳዊት ዘር የኾነው ንጉሥ ነግሦ፣ ስሙ “ #እግዚአብሔር ጽድቃችን” እንደሚባል ተንብዮአል /ኤር.፳፫፡፩-፮፣ ፴-፴፫/፡፡

የ#ትንቢተ ኤርምስያስ ዋና መልእክት፡-

#እግዚአብሔር_ታላቅና_ቅዱስ ስለኾነ ሕዝቡ ከክፋት ተመልሰው በፍጹም ልብ እንጂ በሐሰት እንዳያመልኩት ማስገንዘብ ነው፡፡ ይኸውም፡- “ወምስለ ኵሉ ኢተመይጠት ኀቤየ ኅሥርተ ይሁዳ እኅታ በኵሉ ልባ - አታላይቱ ይሁዳ በሐሰት እንጂ ብፍጹም ልብዋ ወደ እኔ አልተመለሰችም” /ኤር.፫፡፲/፤ ካህናቱና ነቢያቱ እግዚአብሔርን ስለመፍራት፣ በቅንነትም ስለመኖር ሳይኾን ሕዝቡን፡- “የ #እግዚአብሔር_ቤት እዚኽ ነው፤ እናንተም ሕዝቡ ናችሁ፤ አይዞአችሁ፤ ምንም አይደርስባችሁም” እያሉ ማታለላቸው /ኤር.፯፡፫-፲፩፣ ፲፬፡፲፫-፲፰፣ ፳፫፡፱-፵/ ለዚኹ ምስክር ነው፡፡ #እግዚአብሔር ግን የሚያየው ደጋግመን እንደተናገርነው #ልብን ነው፤ በፍጹም ልባቸው እግዚአብሔርን የሚፈልጉትም ያገኙታል፡፡

#መጽሐፉን እንደሚከተለው መክፈል እንችላለን፡-
1, የነቢዩ መጠራት (፩)፤
2, ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ የሚል ጥሪና የማስጠንቀቂያ መልእክቶች (፪-፳)፤
3, ዮአኪን ከተማረከ በኋላ ለነገሥታት፣ ለሕዝቡና ለምርኮኞች የተሰጡ መልእክቶች (፳፩-፳፱፣ ፴፭-፴፮፣ ፵፭)፤
4, የኢየሩሳሌም ልማትና የአዲስ ኪዳን ተስፋ (፴-፴፫)፤
5, የኢየሩሳሌም መከበብና ውድቀት (፴፬፣ ፴፯-፴፱)፤
6, ኤርምያስ በይሁዳ ከቀሩት አይሁድ ጋር መኖሩ (፵-፵፪)፤
7, የኤርምያስ በግብጽ መኖር (፵፫-፵፬)፤
8, በአሕዛብ ላይ የተነገሩ ትንቢቶች (፵፮-፶፩)
9, ተጨማሪ የታሪክ ክፍል ፣ የኢየሩሳሌም መውደቅ (፶፪)፡፡

#ሰቆቃወ_ኤርምያስ

#ሰቆቃ ማለት ሙሾ፣ ለቅሶ ማለት ነው፡፡ መጽሐፉ በዚኽ ስያሜ እንዲጠራ የኾነበት ዋና ምክንያትም ኢየሩሳሌም በጠላት እጅ ወድቃ፣ ቤተ መቅደሷና አጥሮቿ በጠላት ፈራርሳ፣ እናቶች ልጆቻቸው በረሃብ አልቀው በማየት ዝም እስከማለት የደረሱበት ረሃብና ጥም ጸንቶባቸው፣ ካህናትና ነቢያት መገደላቸውን አይቶ የጻፈው ስለኾነ ነው፡፡ መጽሐፉ አምስት ምዕራፎችን የያዘ ሲኾን በውስጡ ከለቅሶው በተጨማሪ የእግዚአብሔር ቊጣና ቅጣት እንዲኹም ስለ ተስፋ ድኅነት በስፋት ተገልጾበታል፡፡

#ተረፈ_ኤርምያስ

የሰቆቃወ ኤርምያስ ቀጣይ ክፍል ነው፡፡ መጽሐፉ ስለ ጣዖት አምልኮ ከንቱነት በስፋት ስለሚያትት “አርአያ መጽሐፍ ዘኤርምያስ - ኤርምያስ ፊት የጻፈውን መጽሐፍ የሚመስል መጽሐፍ፤ አንድም የጣዖትን መልክ ለይቶ ለይቶ የሚያሳይ መጽሐፍ” ተብሎ ይጠራል፡፡

#መጽሐፈ_ባሮክ

የዚኽ መጽሐፍ ጸሐፊ የነቢዩ ኤርምያስ ታማኝ ወዳጅ፣ ደቀ መዝሙርና ጸሐፊ የነበረው ባሮክ ነው /ኤር.፴፮፡፩-፴፪/፡፡ ምንም እንኳን ጸሐፊው ባሮክ ቢኾንም በይዘቱና እግዚአብሔር ለነቢዩ ኤርምያስ የገለጠለት በመኾኑ ከትንቢተ ኤርምያስ ጋር በመደመር አንድ ኾኖ ይቈጠራል፡፡ መጽሐፉ፥ ባሮክ በተማረከበት አገር በባቢሎን ሳለ ለኢየሩሳሌም ኗሪዎች ጽፎ የላከላቸው ነው፡፡ በውስጡም በምርኮ ስላሉት የአይሁድ ኑሮ፣ ስለ ኃጢአት ኑዛዜ ንስሐና ጸሎት እንዲኹም ለአይሁድ የቀረቡ ልዩ ልዩ ምክሮችን ይዟል፡፡

#ተረፈ_ባሮክ

ይኽ መጽሐፍ የመጽሐፈ ባሮክ ቀጣይ ጽሑፍ ሲኾን እግዚአብሔር ለባሮክ፣ ለአቤሜሌክና ለኤርምያስ የተናገረው ቃል ሲኾን እስራኤላውያንን በባቢሎን በምርኮ በነበሩበት ዘመን እንዴት ጠብቆ እንዳሳለፋቸውና በኤርምያስ መሪነት ምርኮኞቹ ወደ ኢየሩሳሌም እንዴት እንደተመለሱ የሚተርክ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ ከላይ ለመግለጥ እንደሞከርነው እግዚአብሔር ለነቢዩ ኤርምያስ የገለጠለትና በባሮክ እጅ የተጻፈ ነው፡፡ ለዚኽም ምስክራችን፥ #ወንጌላዊው_ማቴዎስ፡- “በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተባለው ከእስራኤል ልጆችም አንዳንዶቹ የገመቱትን፥ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ያዙ፥ ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪ መሬት ሰጡት የሚል ተፈጸመ” ብሎ የተናገረው ቃል በዚኹ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ መኾኑ ነው /ማቴ.፳፯፡፱-፲/፡፡ ቃሉም ቃል በቃል እንዲኽ ይላል፡- “ኤርምያስም ጳስኮርን እንዲኽ አለው፡- እናንተስ በዘመናችሁ ኹሉ ከአባቶቻችሁና ከእናንተ በኋላ ከሚመጡ ልጆቻችሁ ጋር ጽድቅን ትቃረኗታላችሁ፡፡ እነርሱስ ከአባቶቻችሁ ይልቅ እጅግ የተናቀች ኀጢአትን ሠሩ፡፡ እነርሱም ዋጋ የማይገኝለትን ይሸጡታል፤ ሕማማትን የሚያስወግደውን እንዲታመም ያደርጉታል፤ ኀጢአትን የሚያስተሰርየውንም ይፈርዱበታል፡፡ የእስራኤል ልጆች የተስማሙበትን የክብሩን ዋጋ ሠላሳ ብር ይቀበላሉ፤ ያንም ብር ለሸክላ ሠሪ ቦታ አድርገው ይሰጡታል፡፡ እግዚአብሔርም እንዳዘዘኝ እንዲኹ እናገራለኹ፡፡ ስለዚኽ ንጹሕ ደምን ፈርደው አፍስሰዋልና ፍርድና ጥፋት በእነርሱ ላይ፥ ከእነርሱም በኋላ በልጆቻቸው ላይ ይወርድባቸዋል” /ተረ.ባሮ.፩፡፩-፭/፡፡

#የነቢዩ_የመጨረሻ_ዕረፍት