ፈለገ ጥበብ ሚዲያ felegetbeb media
995 subscribers
8.92K photos
102 videos
110 files
1.38K links
ይህ ቻናል የደብረ ዘይት ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ወ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ፈለገ ጥበብ ሰንበት ት/ቤት የመረጃ ሚዲያ እና ህዝብ ግንኙነት ክፍል ሲሆን ይህ ቻናል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሆኑ አስተምህሮቶች በየእለቱ የሚለቀቅበት ቻናል ነው ቻናላችን ስለተቀላቀሉ በእግዚአብሔር ፅኑ ፍቅር እናመሰግናለን ።

#የፈለገ_ጥበብ_ሰንበት_ትምህርት_ቤት_የመረጃ_ሚዲያ_እና_ህዝብ_ግንኙነት_ክፍል
#FTM
Download Telegram
#ሰኔ_21

#እመቤታችን_ቅድስት_ድንግል_ማርያም (ህንጸተ ቤተክርስቲያን)

ሰኔ ሃያ አንድ በዚች ዕለት የአዳምና የዘሩ ድኅነት የተደረገባት አምላክን የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የታላቁ በዓል መታሰቢያና በዓለም ሁሉ የቤተ ክርስቲያን መታነፅ መታሰቢያ ነው።

ከሁሉ አስቀድሞ ያቺ ቤተ ክርስቲያን በሐዋርያት ዘመን ብቻዋን ታነፀች።

ይኸውም ጳውሎስና በርናባስ በአሕዛብ ውስጥ በሰበኩ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ ከሰዎች ቤቶች በቀር ቅዱስ ቊርባንን የሚቀበሉበት ቤተ ክርስቲያንም አልነበራቸውም ነበር። ስለዚህም ወደ ጴጥሮስና ወደ ሐዋርያት ሁሉ ስለ ቤተ ክርስቲያን መታነፅ ጉዳይ እየለመኑ መልእክትን ላኩ።

ሐዋርያትም እንዲህ ብለው መለሱላቸው ክብር ይግባውና ያለ ጌታችን ፈቃድ እኛ ምንም ምን አንሠራም። ነገር ግን የምንሠራውን እስኪያስረዳን ድረስ ወደ እግዚአብሔር እየጸለዩና እየማለዱ አንድ ሱባኤ ይጾሙ ዘንድ ወደ ሃይማኖት የተመለሱ አሕዛብን እዘዙአቸው እንዲህም አዘዙአቸው።

በሱባዔውም ፍጻሜ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጸላቸው ሐዋርያትንም ሁሉ ከየአገሮች ሁሉ እስከ ፊልጵስዮስ በደመና ሰበሰባቸው ከእርሳቸውም ጋር ጳውሎስና በርናባስ ነበሩ ጌታችንም ባረካቸው እንዲህም ብሎ ነገራቸው "ይቺ ዕለት በእናቴ በማርያም ስም በአራቱ ማእዘነ ዓለም አብያተ ክርስቲያናት እንድታንፁ የፈቀድኩባት ናት።"

ይህንንም ብሎ ከከተማዋ በስተ ምሥራቅ በኲል አወጣቸው የቤተ ክርስቲያኒቱንም ቦታና መሠረቷን ወሰነላቸው ከእርሳቸውም ጋራ የእግዚአብሔር ኃይል ነበረ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕንፃዋ እስከ ተፈፀመ ድረስ ደንጊያዎች በሐዋርያት እጆች ውስጥ ይለመልሙ ነበረ ጌታችንም ነዋየ ቅድሳቷን አልባሳትዋንና መሠዊያዋን አዘጋጀ።

ከዚህ በኋላ ጌታችን እጁን በጴጥሮስ ራስ ላይ ጭኖ በአራቱ ማእዘነ ዓለም ውስጥ "አርሳይሮስ" ብሎ ሾመው ይህም "ሊቀ ጳጳሳት" ማለት ነው። ለሐዋርያት አለቃ ጴጥሮስ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የጳጳሳት አለቃ ይሆን ዘንድ ይገባዋል ይገባዋል ይገባዋል እያሉ ሰማያውያን መላእክትና ምድራውያን ሰዎች ሦስት ጊዜ አሰምተው ተናገሩ።

ከዚህም በኋላ ጌታችን ሐዋርያትን የቊርባኑን ቅዳሴ ሥርዓት ያከናውኑ ዘንድ ለሕዝቡም ሥጋውን ደሙን ያቀብሏቸው ዘንድ አዘዛቸው እንዲህም የሚል አለ ራሱ መድኃኒታችን ቀድሶ ሥጋውንና ደሙን ለሐዋርያት አቀበላቸው። እንዲህም አላቸው በዚች ቀን የእጃቸውን ሥራ እንዳይሠሩ ሕዝቡን ሁሉ እዘዙአቸው ይኸውም በሰኔ ወር ሃያ አንድ ቀን ነው።

ከዚህም በኋላ መድኃኒታችን ከእርሳቸው ዘንድ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ። ከዚያችም ቀን ጀመሮ አባቶቻችን ሐዋርያት በዓለሙ ሁሉ ውስጥ አምላክን በወለደች በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ቤተ ክርስቲያን የሚያሳንፁ ሆኑ።

በቂሣርያው ሊቀ ጳጳሳት በባስልዮስ ዘመን እንዲህ ሆነ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ቤተ ክርስቲያን በሠራ ጊዜ በውስጡ የእመቤታችን የማርያምን ሥዕል ይሥልበት ዘንድ ሠሌዳ ፈለገ ሰዎችም በአንድ ባለጸጋ ዘንድ ስለ አለ አንድ መልካም ሠሌዳ ነገሩት።

ቅዱስ ባስልዮስም ሠሌዳውን እንዲሰጠው ወደ ባለጸጋው ላከ ባለጸጋውም ይህ ሠሌዳ ለልጆቼ ነው አለ እንጂ ፈቃደኛ አልሆነም። ከዚያም አልፎ በመድፈር በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ላይ የስድብ ቃል ተናገረ ወዲያውኑም በድንገት ወድቆ ሞተ ልጆቹም ፈሩ ያንንም ሠሌዳ ከብዙ ወርቅና እንቊ ጋራ ወደ ቅዱስ ባስልዮስ አምጥተው የአባታቸውን በደል ያቃልልለት ዘንድ ለመኑት።

ቅዱስ ባስልዮስም ያንን ሠሌዳ ወስዶ የእመቤታችንን ሥዕል ይሥልበት ዘንድ ለሠዓሊ ሰጠው። እመቤታችንም ቅድስት ድንግል ማርያም በሌሊት ራእይ ለቅዱስ ባስልዮስ ተገለጸችለት ሥዕሏንም በዚያ ሠሌዳ ላይ እንዳይሥል ከለከለችው። ከዐመፀኛ ሰው እጅ ወስዶታልና። እጅግም ያማረ የእመቤታችን ሥዕሏ የተሣለበት የሁለት ደናግልም ሥዕል ያንዲቱ በቀኝ ያንዲቱ በግራ ሆኖ የተሣለበት ቀይ ሠሌዳ ያለበትን ቦታ ነገረችው።

ቅዱስ ባስልዮስም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ አመለከተችው ወደዚያ ቦታ ሔደ ያንንም ሠሌዳ አገኘው ወደዚያች ቤተ ክርስቲያንም በታላቅ ደስታ አመጣው።

ከዚህም በኋላ ዳግመኛ በአንድ ጣዖት ቤት ሁለት ምሰሶዎች እንዳሉ አስረዳቸው እነርሱንም አምጥቶ በመቅደሱ ፊት ለፊት እንዲአቆማቸው በላያቸውም ሥዕሏን እንዲያኖር አዘዘችው።

ቅዱስ ባስልዮስም እነዚያን ምሰሶዎች ያመጣቸው ዘንድ ሔደ መሠርያኑም ሊከለክሉት ፈለጉ ጌታችንም ኃይላቸውን ደመሰሰ እነዚያንም ምሰሶዎች አምጥቶ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አቆማቸው በላያቸውም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕሏን አስቀመጠ እግዚአብሔርም ከእነዚያ ምሰሶዎች በታች የውኃ ምንጭ አፈለቀ በውስጥዋም የሚታጠብ ሁሉ ከአለበት ደዌ ሁሉ የሚድን ሆነ።

እንዲሁም ከእመቤታችን ማርያም ሥዕል በሽተኞችን ሁሉ የሚፈውስ የዘይት ቅባት ፈሰሰ ይህ ሁሉ የሆነ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በከበረችበት በሰኔ ወር በሃያ አንድ ቀን ነው።

በዚያችም ቀን እንዲህ ሆነ አንዲት ሴት መጥታ ታጠበች ወዲያውኑም ሁለመናዋ በለምጽ ተሸፈነ ቅዱስ ባስልዮስም ወደርሱ አስቀርቦ በእርሷ ላይ የሆነውን ጠየቃት እርሷም የእኅቷን ባል እንደወደደችና እኅቷን በመርዝ ገድላ እንዳገባችው ነገረችው። ቅዱስ ባስልዮስም ታላላቅ ሦስት ኃጢአቶችን ሠራሽ ግን ወደ እግዚአብሔር ንስሐ ግቢ ምንአልባት በደልሽን ይቅር ይልሽ እንደ ሆነ አላት በዚያን ጊዜም ምድር ተሠንጥቃ እንደ ዳታን ዋጠቻት እርሷ የረከሰች ስትሆን ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባትን ደፍራለችና።

እኛ ሁላችን የክርስቲያን ወገኖች አምላክን ለወለደች ለእመቤታችን ለከበረች ድንግል ማርያም ለመታሰቢያዋ መንፈሳዊ በዓልን ልናደርግ ይገባናል ሰለ እርሷ ለአዳምና ለሁላችን ለልጆቹ ድኅነት ሆኖአልና ይህንንም በዓል ለማድረግ የሚተጋ የተመሰገነ ነው።

እርሷን ለመረጣትና ለወደዳት በሥጋም እንድትወልደው ላደረግ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእርሷ በእመቤታችን ድንግል ማርያም አማላጅነት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን ።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሰኔ@sinksarzetewahido የተወሰደ)


#ፈለገ_ጥበብ_ሚዲያ

#FTM