ፈለገ ጥበብ ሚዲያ felegetbeb media
980 subscribers
8.39K photos
102 videos
99 files
1.2K links
ይህ ቻናል የደብረ ዘይት ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ወ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ፈለገ ጥበብ ሰንበት ት/ቤት የመረጃ ሚዲያ እና ህዝብ ግንኙነት ክፍል ሲሆን ይህ ቻናል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሆኑ አስተምህሮቶች በየእለቱ የሚለቀቅበት ቻናል ነው ቻናላችን ስለተቀላቀሉ በእግዚአብሔር ፅኑ ፍቅር እናመሰግናለን ።

#የፈለገ_ጥበብ_ሰንበት_ትምህርት_ቤት_የመረጃ_ሚዲያ_እና_ህዝብ_ግንኙነት_ክፍል
#FTM
Download Telegram
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

❖ ሰኔ ፬ ❖

✞✞✞ እንኩዋን ለታላቁዋ ሰማዕት "ቅድስት ሶፍያ" እና ለቅዱስ "ዮሐንስ ዘሐራቅሊ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*" #ሶፍያ (SOPHIA) "*+

=>ሶፍያ ("ያ" የሚለው ላልቶ ይነበብ) በቀደመው ዘመን በነበሩ ክርስቲያኖች ዘንድ ተወዳጅ ስም ነበር:: ዛሬ ብዙ አሕዛብ ሲጠሩበት ብንሰማም ትርጉሙ "ጥበበ ክርስቶስ" የሚል ነው:: በዚህ ስም የሚጠሩ አያሌ ቅዱሳት አንስት ሲኖሩ አንዷ ዛሬ ትከበራለች::

+*" ቅድስት ሶፍያ ተጋዳሊት "*+

=>ቅድስቷ የተወለደችው በምሥራቅ ሮም ግዛት ውስጥ በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ዘመኑ የጭንቅ : የመከራ በመሆኑ ሕዝቡ በስደት ይኖር ነበር::

+የቅድስት ሶፍያ ወላጆች ክርስቲያኖች ናቸውና በመልካሙ መንገድ በንጽሕና አሳድገዋታል:: ባለጠጐች በመሆናቸው አገልጋይ ቀጥረውላት : ያማረ ቤት ሰርተውላት በዚያ ትኖር ነበር:: ሁሉ ያላት ብትሆንም ሁሉን ንቃ በጾምና በጸሎት ትኖር ነበር::

+ለዐቅመ ሔዋን በደረሰች ጊዜ ወላጆቿ ለከተማው መኮንን (ገዢ) ሊድሯት መሆኑን አወቀች:: ወደ ቤቷ ገብታ 100 ጊዜ ሰገደች:: ወደ ፈጣሪዋም ጸለየች:- "ጌታየ ሆይ! የዚህን ዓለም ቀንበር አታሸክመኝ:: አልችለውምና:: ያንተው ቀንበር ግን የፍቅር ነውና እችለዋለሁ" አለች::

+አገልጋዩዋን ጠርታ ብዙ ወይን አጠጥታት ልብስ ተቀያየሩ:: በሌሊትም ወጥታ ወደ በርሃ ሔደች:: ዓላማዋ ምናኔ ቢሆንም የእግዚአብሔር ፈቃዱ ግን ሌላ ነበር:: በመንገድ ብዙ ክርስቲያኖች በመከራ ብዛት ሲሰደዱ አገኘቻቸው:: እርሷ ስደትን አልመረጠችም::

+እያጠያየቀች "ሰው በላ" ከተባለው አረመኔ ንጉሥ ዲዮቅልጢያኖስ ደረሰች:: በንጉሡ ፊት ቀርባ "እኔ ክርስቲያን ነኝ" አለችው:: ንጉሡ ከመልኩዋ ማማርና ከድፍረቷ የተነሳ አደነቀ::

+ሊያባብላት: ሊያስፈራራትም ሞከረ:: ግን
አልተሳካለትም:: ወታደሮቹ መሬት ላይ ጥለው ጦር ባለው
የብረት ዘንግ
ደብድበዋታልና ደም አካባቢውን አለበሰው:: መሬት
ለመሬት እየጐተቱ እሥር ቤት ውስጥ ጣሏት:: ቅዱስ
ገብርኤል መጥቶ
ፈውሷት ሔደ::

+አንዴ በእሳት: አንዴም በስለት: ሌላ ጊዜም በግርፋት
አሰቃዩዋት:: ከሃይማኖቷ ግን ሊያነቃንቁዋት አልቻሉም::
በመጨረሻ አንገቷን እንድትሰየፍ ንጉሡ አዘዘ::
ወታደሮቹም ፈጸሙት:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወርዶ
ቅድስት ሶፍያን
በክብር አሳረጋት:: "ስምሽን የጠራ: መታሰቢያሽን ያደረገ
ምሕረትን ያገኛል" አላት::

+"+ ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ +"+

=>ቅዱሱ የነበረው በተመሳሳይ በዘመነ ሰማዕታት ነው::
አባቱ ዘካርያስ: እናቱ ኤልሳቤጥ: እርሱ ደግሞ ዮሐንስ
ይባላል:: የሚገርም መንፈሳዊ ግጥጥሞሽ ነው:: የቅዱሱ
ወላጆች የሃገረ ሐራቅሊ አስተዳዳሪዎች ሲሆኑ
የተመሰከረላቸው
ደጐች ነበሩ::

+ዘካርያስ አርፎ ዮሐንስ በመንበሩ የተቀመጠው ገና በ20
ዓመቱ ነበር:: በወቅቱ ከ2 አንዱን መምረጥ ነበረበት::

1.ለጣኦት ሰግዶ በምድራዊ ክብሩ መቀጠል
2.ወይ ደግሞ በክርስትናው መሞት

+ቅዱስ ዮሐንስ ግን ልቡ በክርስቶስ ፍቅር የተሞላ ነውና
2 ከባባድ ነገሮችን ፈጸመ:: በመጀመሪያ በአካባቢው ያሉ
ጣዖት
ቤቶችን አወደመ:: ቀጥሎ ወደ ንጉሡ ሔዶ በመኩዋንንቱ
ፊት "ክርስቶስን የተውክ ሰነፍ" ብሎ ገሠጸው::

+ከዚህ በኋላ በቅዱሱ ላይ የተፈጸመው መከራ የሚነገር
አይደለም:: ያላደረጉት ነገር አልነበረም:: እሳቱ: ስለቱ:
ሰይፉ: መንኮራኩሩ . . . ከሁሉ የከፋው ግን ቆዳውን
ገፈው በእሳት ጠብሰውታል:: እርሱ ግን ስለ ሃይማኖቱ
ይሕንን
ሁሉ ታግሶ በዚህች ቅን አንገቱን ተሰይፏል::

=>አምላካችን እግዚአብሔር ግፍዐ ሰማዕታትን አስቦ
እኛን ከሚመጣው መከራ ሁሉ ይሰውረን:: ከበረከታቸውም
ይክፈለን::

=>ሰኔ 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅድስት ሶፍያ ተጋዳሊት ወሰማዕት
2.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)
3.ቅዱስ ሳኑሲ ሰማዕት
4.ቅድስት ማርያ ሰማዕት
5.ቅዱስ አርቃድዮስና ባልንጀሮቹ (ሰማዕታት)
6.ቅዱስ አሞን ሰማዕት

❖ወርኃዊ በዓላት
1፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ
2፡ ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ

=>+"+ እንግዲሕ አትፍሯቸው:: የማይገለጥ የተከደነ:
የማይታወቅም የተሠወረ ምንም የለምና:: በጨለማ
የምነግራችሁን
በብርሃን ተናገሩ:: በጀሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ
ስበኩ:: ሥጋንም የሚገድሉትን: ነፍስን ግን መግደል
የማይቻላቸውን አትፍሩ:: ይልቅስ ነፍስንም: ሥጋንም
በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ:: +"+ (ማቴ.
10:26)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
https://t.me/felegetibebmedia
††† እንኳን ለጻድቅና ሰማዕት አባ ቴዎድሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አባ ቴዎድሮስ †††

†††አባ ቴዎድሮስ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ ግብፃዊ አባት ነው:: ተወልዶ ባደገባት የእስክንድርያ ከተማ ብሉያትንና ሐዲሳት በወቅቱ ከነበሩ አበው ሊቃውንት ተምሯል:: ጊዜው ምንም መናፍቃን የበዙበት ቢሆን በዛው ልክ እነ ቅዱስ እለ እስክንድሮስና ቅዱስ አትናቴዎስን የመሰሉ ቅዱሳን ሊቃውንት ነበሩና ከነሱ የሚገባውን ወስዷል::

አባ ቴዎድሮስ "አባ" ያሰኘው ሥራው:- ሲጀመር ገና በወጣትነቱ ድንግልናንና ምንኩስናን በመምረጡ ነበር:: ምንም እንኳ ሐብት ከእውቀት ጋር ቢስማማለትም ይሕ እርሱን ከምናኔ ሊያስቀረው አልቻለም:: ከከተማ ወጥቶ: በዓት ወስኖ በጾምና በጸሎት ተወሰነ::

በ340ዎቹ ዓ/ም አካባቢ ግን በምዕመናን ላይ ከባድ ችግር ደረሰ:: የወቅቱ ነገሥታት በስመ ክርስቲያን አርዮሳውያን ነበሩና ሕዝቡን ማስገደድ: አንዳንዴም የአርዮስን እምነት ያልተቀበለውን ማስገደል ጀመሩ:: በዚህ ምክንያትም ታላቁ የኦርቶዶክስ ጠበቃ ቅዱስ አትናቴዎስን ከመንበሩ አሳደዱት:: በምትኩም አርዮሳዊ ሰው ዻዻስ ተብሎ ተሾመ:: ይህን ጊዜ ነው እንግዲህ እውነተኛ እረኛ ያስፈለገው::

በበዓቱ የነበረው አባ ቴዎድሮስ አላቅማማም:: ቤተ ክርስቲያን ትፈልገዋለችና መጻሕፍትን ገልጾ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ምዕመናንን ያጸናቸው ጀመር:: መናፍቃኑን ተከራክሮ ምላሽ በማሳጣት ሕዝቡን ከኑፋቄ በመጠበቅ የሠራው ሥራ ሐዋርያዊ ቢያሰኘውም ለአርዮሳዊው ዻዻስ (ጊዮርጊስ ይባላል) ሊዋጥለት አልቻለም::
በቁጣ ወታደሮችን ልኮ አባ ቴዎድሮስን ተቆጣው:: እንዳያስተምርም ገሰጸው:: አባ ቴዎድሮስ ግን እሺ ባለማለቱ ግርፋት ታዘዘበት::

ወታደሮች እየተፈራረቁ ሲገርፉት ረድኤተ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና ከዛ ሁሉ ግርፋት አንዲቷም አካሉ ላይ አላረፈችም:: በዚህ የተበሳጨው አርዮሳዊ ዻዻስ የአባ ቴዎድሮስን እጅና እግር ከፈረስ ጋሪ በኋላ አስረው በኮረኮንች መንገድ ላይ በፍጥነት እንዲያሮጧቸው አዘዘ::

ፈረሶቹ መሮጥ ሲጀምሩ የአባ ቴዎድሮስ አካሉ ይላላጥ ጀመር:: ትንሽ ቆይቶ ግን እጆቹ ተቆረጡ:: በኋላም ራሱ ከአንገቱ ተለይታ መንገድ ላይ ወደቀች:: አካሉ በሙሉ መሬት ላይ ተበታተነ:: እግዚአብሔር ቅድስት ነፍሱን ተቀብሎ አሳረጋት::

††† ለቅዱሱም 3 አክሊል ከሰማይ ወርዶለታል:-
1.ስለ ፍጹም ምናኔውና ድንግልናው
2.ስለ ሐዋርያዊ የወንጌል አገልግሎቱ
3.ስለ ሃይማኖቱ ደሙን አፍስሷልና
"እምአባልከ ተመቲራ ለእንተ ሠረረት ርዕስ:
እግዚአብሔር አስተቄጸላ በአክሊል ሠላስ" እንዳለ መጽሐፍ::
ምዕመናን ሥጋውን ሰብስበው በዝማሬና በማኅሌት በክብር ቀብረውታል::

††† አምላካችን ከቅዱሱ በረከት ይክፈለን::

††† ሰኔ 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ቴዎድሮስ ሰማዕት
2.አባ ገብረ ክርስቶስ
3."40" ሰማዕታት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
7.ቅድስት ሰሎሜ
8.አባ አርከ ሥሉስ
9.አባ ጽጌ ድንግል
10.ቅድስት አርሴማ ድንግል

††† "መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ:: ሩጫውን ጨርሻለሁ:: ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ:: ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል:: ይህንም ጻድቅ: ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያሰረክባል:: ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም::" †††
(2ጢሞ. 4:7)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://t.me/felegetibebmedia
††† እንኳን ለታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ †††

††† በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በደራሲነታቸው : በወንጌል አገልግሎታቸውና በቅድስናቸው ከተመሠከረላቸው ዐበይት ሊቃውንት አንዱ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ነው::

ሊቁ የተወለደው መጋቢት 27 ቀን በ433 ዓ/ም ሲሆን ሃገሩ ሶርያ ነው:: ወላጆቹ ክርስቲያኖች ለዚያውም አባቱ ሊቀ ካህናት ነበር:: ቅዱስ ያዕቆብ ገና በልጅነቱ ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔር የጠራው ነውና በብዙ ነገሩ የተለየ ነበር::

አንድ ቀን በዕለተ ሰንበት : ገና በ3 ዓመቱ : እናቱ አቅፋ ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደችው:: ምዕመናን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበሉ ሕጻኑ ያዕቆብም ይቆርብ ዘንድ ቀረበ:: ሊቀ ዻዻሱ ደሙን በዕርፈ መስቀል ሊያቀብለው ሲል መልአኩ መጥቶ "በጽዋው ጋተው" አለው:: የጌታን ደም በጽዋ ቢጠጣ ምስጢር ተገለጸለትና "አንሰ እፈርሕ ሠለስተ ግብራተ - እኔስ 3 ነገሮች ያስፈሩኛል" ሲል አሰምቶ ተናገረ::

††† ዻዻሱና ሕዝቡ ወደ ሕጻኑ ያዕቆብ ቀርበው "ምን ምን?" አሉት:: እርሱም:-
1.ነፍሴ ከሥጋየ ስትለይ::
2.ቅድመ እግዚአብሔር ለፍርድ ስቀርብ::
3.ከፈጣሪየ የፍርድ ቃል ሲወጣ" አላቸው::
ያን ጊዜ ሕዝቡና ሊቀ ዻዻሳቱ "እግዚአብሔር በዚሕ ሕጻን አድሮ ዘለፈን" እያሉ ለንስሃ በቅተዋል::

ቅዱስ ያዕቆብ 7 ዓመት ሲሞላው ይማር ብለው ወደ ጉባዔ አስገቡት:: በ5 ዓመታት ብሉይ ከሐዲስ ጠንቅቆ በ12 ዓመቱ ሊቅ ሆኗል:: በዚህ ወቅት የነበሩ ታላላቅ ሊቃነ ዻዻሳት ወደ እርሱ ተሰበብስበው "እንግዳ ድርሰት ድረስልን:: አዲስ ምሥጢር ንገረን" አሉት:: እርሱ ግን ሲቻለው ስለ ትሕትና "አልችልም" አላቸው::

"እንግዲያውስ ትንቢተ ሕዝቅኤልን ተርጉምልን" ቢሉት ባጭር ታጥቆ አመሥጥሮላቸው ተደስተዋል:: ፈጣሪንም አመስግነዋል::

ቅዱስ ያዕቆብ ከዚህ በኋላ ወደ ገዳም ገብቶ ትሕርምተ አበውን : ዕጸበ ገዳምን : ሕይወተ ቅዱሳንን በተግባር ተምሯል:: በድንግልናው ጸንቶ : ጾምና ጸሎትን እያዘወተረ ኑሯል:: በፈቃደ እግዚአብሔር የሥሩግ (በኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች መካከል የምትገኝ የሶርያ ግዛት ናት) ኤዺስ ቆዾስ ሆኖ ተሹሟል::

††† በዘመኑም:-
1.የ451ን የኬልቄዶን ጉባኤ አውግዟል::
2.ብዙ መናፍቃንን ተከራክሮ ምላሽ አሳጥቷል::
3.በወንጌል አገልግሎት መልካም እረኝነቱን አሳይቷል::
4.ዛሬ የምንገለገልበትን መጽሐፈ ቅዳሴውን ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል::

በመጨረሻም ከብዙ የተጋድሎና የቅድስና ዓመታት በኋላ በተወለደ በ72 ዓመቱ በ505 ዓ/ም በዚሕች ቀን አርፏል:: አንዳንድ ምንጮች ደግሞ ሰኔ 27 ቀን እንዳረፈ ይናገራሉ:: ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ለቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ተወዳጅ ልጇ ነውና በእጅጉ ታከብረዋለች::

††† አምላከ ቅዱሳን ከታላቁ ሊቅ በረከት ይክፈለን::

††† ሰኔ 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ
2.ቅዱስ : ቡሩክና አሸናፊ አባ አበስኪሮን (ታላቅ ሰማዕትና ባለ ብዙ ተአምራት ነው)
3."16,000" ሰማዕታት (በአንድ ቀን የተገደሉ)
4.የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን የተከፈተበት በዓል (ከ1ሺ ዓመታት በፊት ምስር (CAIRO) ውስጥ)

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
2.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
3.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
4.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
5.አባ ባውላ ገዳማዊ
6.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
7.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)

††† "ይሕንን እዘዝና አስተምር :: በቃልና በኑሮ : በፍቅርም : በእምነትም : በንጽህናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው:: እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር : ለማስተማርም ተጠንቀቅ::" †††
(1ጢሞ. 4:11)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር ††† https://t.me/felegetibebmedia
††† እንኳን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ የተድላና የደስታ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† በዚሕች ቀን ለ40 ዓመታት በመላው ዓለም የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት የተከፈቱበት ቀን ይታሠባል:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ልቡና ታስባ : በዓለመ መላእክት ከታየች በኋላ:-
¤አበው ተስፋ ሲያደርጓት
¤ነቢያት ትንቢት ሲናገሩላት
¤ሱባኤ ሲቆጥሩላት
¤ምሳሌም ሲመስሉላት ኑረዋል::

††† ዘመኑ በደረሰ ጊዜ በአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ :-
¤በመጸነሱ ተጸንሳ
¤በመወለዱ ተወልዳ
¤በጥበብና በሞገስ አብራው አድጋ
¤በጥምቀቱ ተጠምቃ
¤በትምሕርቱ ጸንታ
¤በደሙ ተቀድሳ
¤በትንሣኤው ከብራ
¤በዕርገቱ ሰማያዊነቷን አጽንታ
¤በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ ወርዶላት በይፋ ለልጆቿ ተሰጥታለች::

††† አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት በመላው ዓለም ዞረው በብዙ ድካም የሠሯት ቤተ ክርስቲያን ለ200 ዓመታት እጅግ የበዙ መከራዋችን አሳልፋለች:: በ265 ዓ/ም የመጣባት መከራ ግን በዓለም ታሪክ እስካሁን አልታየም:: የወቅቱ ኃያላን ነገሥታት (ዲዮቅልጢያኖስና መክስምያኖስ) ዓለምን ለ2 ተካፍለው ክርስቲያኖችን የማጥፋት ዘመቻ ጀመሩ::

በመጀመሪያም በዓለም ያሉ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እንዲቃጠሉ ካልሆነም እንዲዘጉ : በፈንታቸው ደግሞ አዽሎን: አርዳሚስ የተባሉ ጣዖቶች እንዲተኩ ትዕዛዝ ተሰጠ:: ለ40 ዓመታት ክርስቲያን ስለሆኑ ብቻ ሚሊየኖች ተገደሉ: ታሰሩ: ተሰቃዩ: ተሰደዱ:: መጻሕፍት ተቃጠሉ: አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ወደሙ::

በአባቶቻችንና እናቶቻችን ላይ ልንናገረው ከምንችለው በላይ ጭንቅና መከራ ደረሰ:: ነገር ግን ቅዱሳኑ ያን ሁሉ ችለው ጸኑ:: 47 ሚሊየን የሚያሕሉትን ደግሞ ሰይፍና እሳት በላቸው:: በዛ ዘመን አንድ ቤተ ክርስቲያን ለማግኘት ከአሕጉር አሕጉር መሔድን ይጠይቅ ነበር::

ከዚሕ ሁሉ በኋላ ግን እግዚአብሔር "ግፍ ይበቃል" ሲል በ305 ዓ/ም ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ነገሠ:: መክስምያኖስን በጦርነት ሲማርከው አውሬው ዲዮቅልጢያኖስ ግን አብዶ ሞተ:: ይህ ከተደረገ ከዓመታት በኋላ (በ313 ዓ/ም) ታላቁ ቆስጠንጢኖስ የዓለም መሪዎችን በዚሕች ቀን ጠርቶ አዋጁን በአዋጅ ሻረው:: "ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ይከፈቱ:: በፈንታው ደግሞ ሁሉም ጣዖት ቤቶች ይዘጉ" አለ::

በሺሕ የሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናትን በወርቅ አስለበጠ:: በዚሕ ምክንያት ይህች ቀን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን "ዕለተ ትፍሥሕት (የደስታ ቀን)" ተብላ ትከበራለች::

††† ቸሩ አምላክ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከመከራ ይሠውርልን:: ከበረከቷም ያድለን:: ትውልዱ ደካሞች ነንና ከማንችለው ፈተናም ይጠብቀን::

††† ሰኔ 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
2.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ
3.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት (ከታላላቆቹ ሶፍያዎች አንዷ ናት)
4.ቅዱሳት ሰማዕታት ደባሞንና ብስጣሞን (የቅድስት ሶፍያ ልጆች)
5.ቅዱስ አውሎጊስ ሰማዕት
6.ቅዱስ ዋርስኖፋ ሰማዕት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
2.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
3.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
4.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
5.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
6.ቅዱስ ዕፀ መስቀል

††† "ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሒድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ::
ኢየሩሳሌም ሆይ እግሮቻችን በአደባባይሽ ቆሙ::
ኢየሩሳሌምስ እርስ በርሷ እንደ ተገለጠች ከተማ ተሠርታለች . . .
ስለ ወንድሞቼ ስለ ባልንጀሮቼም በውስጥሽ ሰላም ይሁን አልሁ::
ስለ አምላካችን ስለ እግዚአብሔር ቤት ላንቺ መልካምነትሽን ፈለግሁ::" †††
(መዝ. 121:1-9)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
https://t.me/felegetibebmedia
††† እንኳን ለታላቁ ሰማዕት ማር ገላውዴዎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት †††

††† ቅዱስ ገላውዴዎስ የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ዘ በድሮው የሮም ግዛት በአንጾኪያ (አሁን ሶርያ ውስጥ) ነው:: አባቱ አብጥልዎስ የሮም ቄሣር የኑማርያኖስ ወንድም ነበር:: በዚህ ምክንያት ቅዱሱ ያደገው በቤተ መንግሥት ውስጥ ነው::

ወቅቱ መልካምም ክፉም ነገሮች ነበሩት:: መልካሙ ነገር በቤተ መንግሥት አካባቢ ይኖሩ የነበሩት ልዑላኑ አብዛኞቹ በፍቅረ ክርስቶስ የታሠሩ ነበሩ:: ከእነዚህ መካካከል "ቅዱስ ፋሲለደስ:
ቅዱሳኑ:- ፊቅጦር: ቴዎድሮስ: አባዲር: አውሳብዮስ: ዮስጦስ: አቦሊ: እስጢፋኖስ . . ." ነበሩ::
ቅዱሳቱ "ማርታ: ታውክልያ: ኢራኢ: ሶፍያ. . ." ነበሩ::

አስቸጋሪው ነገር ደግሞ ነጋ መሸ ኑሯቸው ጦርነት ነበር:: የዘመኑ የፋርስና የቁዝ መሪዎች ጦረኞች ነበሩና ዕለት ዕለት ፍልሚያ ነበር:: በዚህ ምክንያት ቅዱስ ገላውዴዎስ የተመሠከረለት አርበኛና የተባረከ ንጹሕ ክርስቲያን ሆኖ አድጓል:: ከልጅነቱ ጀምሮ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማጥናቱ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ጨውነት ታሽቷል:: እርሱ የነገሥታቱ ቤተሰብ ነው:: ማዕዱ በየዓይነቱ ሞልቶ ካልመሸ እህል አይቀምስም::
ጸሎቱ ስሙር:
ስግደቱ ከምድር:
አኗኗሩ በፍቅር ሆነ:: በዚያውም ላይ በድንግልናው የጸና ኃያል ነበር::

በጊዜው የቅዱስ ገላውዴዎስን ያህል መልኩ ያማረ (ደመ ግቡ) በአካባቢው አልነበረም:: ይህ ግን ሊያታልለው አልቻለም:: ሁሉ በእጁ ቢሆንም ለእርሱ ግን ብቸኛ ምርጫው ሃይማኖተ ክርስቶስ ነበር::

ቅዱስ ገላውዴዎስ ለጦርነት ወጥቶ ሲመለስ ንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ሃይማኖቱን ክዶ: ሕዝቡን ለጣዖት ሲያሰግድ: ክርስቲያኖችን ሲገድል ደረሰ::

††† ቅዱሱ ኃያል የጦር ሰው ነውና ንጉሡን መግደል ሲችል ተወው:: በዚያ ሰሞንም ለገላውዴዎስ ሁለት ምርጫዎች ቀረቡለት:-
1.ክርስቶስን ክዶ የንጉሡ ተከታይ መሆን:
2.በክርስትናው ደሙን ማፍሰስ::

የቅዱሳኑ ምርጫቸው የታወቀ ነውና ታስሮ ወደ ግብጽ ተጋዘ:: በዚያ ከመኮንኑ ጋር ስለ ሃይማኖት ተከራክረው መኮንኑ ስለተበሳጨ ቅዱሱን በረዥም ጦር ጐኑን ወጋው:: ዘለፍ ብሎ ነፍሱን ሰጠ:: ሕዝበ ክርስቲያኑ በድብቅ መጥተው የቅዱሱን ሥጋ ሽቱ ቀብተው: ከዝማሬ ጋር ገነዙት:: የጓደኛው እናት ቅድስት ሶፍያ መጥታ ወደ ሶርያ ወስዳዋለች::

††† ተወዳጅ: ኃያል: ቡሩክና መልካም ሰው ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት በሆነባት በዚሕች ዕለት በመላው ኦርቶዶክሳውያን ይከበራል::

††† አምላካችን የቅዱሱን መንኖ ጥሪት: ትዕግስት: ጸጋና በረከት ያሳድርብን:: አሜን::

††† ሰኔ 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት (ሕይወቱ መላእክትን የመሰለ)
2.አንድ ሺ ሰማንያ ስምንት ሰማዕታት (የቅዱስ ገላውዴዎስ ማኅበር)
3.አባ ክርዳኑ ሊቀ ጳጳሳት
4.እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ክብራ ኢትዮጵያዊት (የአቡነ በጸሎተ ሚካኤል እህት)
5.የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዳሴ ቤቱ (ግብጽ)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ያሬድ ካህን
2.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
3.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና
4.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ

††† "የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ:: ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ: ፀሐይ: ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ . . . አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ: ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ::
ሰባኪው:- "ከንቱ: ከንቱ: ሁሉ ከንቱ ነው" ይላል::" †††
(መክ. ፲፪፥፩-፱)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
https://t.me/felegetibebmedia
††† 🌹እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† በዚህች ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤልን ጨምሮ ቅዱስ ላሊበላ: ቅድስት አፎምያና ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ ይከበራሉ::

††† ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት †††

††† ቅዱስ ሚካኤል በጥንተ ተፈጥሮ በኢዮር: ኃይላት በተባሉት ነገደ መላእክት ተሹሞ ነበር:: ሳጥናኤል በካደ ጊዜ እግዚአብሔር ባወቀ: አንድም በትሕትናውና ደግነቱ በ99ኙ ነገደ መላእክት ላይ ሁሉ ተሹሟል::

ከፍጥረት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የቅዱስ ሚካኤልን ያሕል ክብርና ርሕሩሕ የለም:: በምልጃውም: በረዳትነቱም የታወቀ መልአክ ነው:: መጽሐፍ "መልአከ ምክሩ ለእግዚአብሔር" ይለዋል:: "ወስሙ መስተሣሕልም" ይለዋል:: ቂም የሌለው: ለምሕረት የሚፋጠን: ደግ መልአክ ነውና::

በብሉይ ኪዳን በመከራ ለነበሩ ቅዱሳን ሁሉ ሞገስ: ረዳትና አዳኝ ቢሆናቸው "መጋቤ ብሉይ" ተሰኝቷል:: እሥራኤልን 40 ዘመን በበርሃ መርቷል: መግቧልም:: ቅዱስ መጽሐፍ ስለ እርሱ ብዙ ይላል:: (ዘፍ. 48:16, ኢያ. 5:13, መሳ. 13:17, ዳን. 10:21, 12:1, መዝ. 33:7, ራዕይ. 12:7)

ደስ የሚለው ደግሞ ርሕሩሑ መልአክ ከእመቤታችን ጋር ልዩ ፍቅር አለው:: ከእናቷ ማሕጸን ጀምሮ እስከ ዛሬ እነሆ አብሯት አለ:: ደስ ብሎት ይታዘዛታል:: ማማለድ ሲፈልግም "እመቤቴ ሆይ! ቅደሚ" ይላታል:: ወደ እሳት መጋረጃ አብረው ገብተው ለዓለም ምሕረትን: በረከትን ያወርዳሉ::

ቅዱስ ሚካኤልን በዚሕች ዕለት ስለ እነዚህ ነገሮች እናከብረዋለን:-
1.በመላእክት ሁሉ ላይ አለቃ ሆኖ መሾሙን
2.ቅዳሴ ቤቱን (ግብፅ ውስጥ)
3.ቅድስት አፎምያን መርዳቱን
4.ቅዱስ ባሕራንን መጎብኘቱን
5.ቅዱስ ላሊበላን ወደ ሰማያት ማሳረጉን
6.ለፍጥረታት ሁሉ ምሕረት የሚጠይቅበት ዕለት ነውና::

††† ሊቀ መላእክት በክንፈ ረድኤቱ ከክፉ ሁሉ ይጠብቀን::

††† ቅዱስ ላል ይበላ ንጉሥ †††

††† በ12ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ ላይ በሃገራችን የነገሠው ቅዱስ ላሊበላ:-
¤በብሥራተ መልአክ ተወልዷል
¤ቅዱሳት መጻሕፍትን ገና በልጅነቱ አጥንቷል
¤የንጉሥ ዘር ቢሆንም በጾምና ጸሎት: በትሕርምት አድጓል
¤በወንድሙ ቢገረፍም ቂም አልነበረውም
¤ስለ ወዳጆቹ ፍቅር መርዝ ጠጥቷል
¤በዙፋን ላይ የኢትዮዽያ ንጉሥ ሆኖ ቢቀመጥም እርሱስ አኗኗሩ ገዳማዊ ነበር
¤ከተባረከች ሚስቱ ቅድስት መስቀል ክብራ ጋር አንዲት ማዕድ ብቻ በቀን ይቀምሱ ነበር:: ለዛውም ለምለሙን ለነዳያን ሰጥተው እነርሱ የሚበሉት የእንጀራውን ቅርፍት (ጠርዝ) ብቻ ነበር::

በአካለ ሥጋ ወደ ሰማያት ተነጥቆ ብዙ ምሥጢራትን አይቷል
¤በምሳሌውም ሃገረ ሮሃን (ላስታን) ገንብቷል
¤ዛሬም ድረስ ምስጢር የሆኑት ፍልፍል አብያተ መቃድስ የእጆቹ ሥራዎች ናቸው::

ሥራውን ከፈጸመ በኋላ መንግሥቱን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አውርሶ: በመንኖ ጥሪትና በቅድስና ኑሮ በዚሕች ቀን አርፏል:: ጌታችን ስምህን ያከበረ: ዝክርህን የዘከረ: ከቤትህ ያደረውን: ከርስተ መንግስተ ሰማያት አካፍለዋለሁ ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል::

††† በረከቱን: ክብሩን ያድለን::

††† ቅድስት አፎምያ †††
ከቅዱስ አስተራኒቆስ ጋር በተቀደሰ ትዳር የኖረች
¤ምጽዋትን ያዘወተረች
¤በፍቅረ ቅዱሳን የጸናች
¤ንጽሕናዋን ጠብቃ ሰይጣንን ያሳፈረች ደግ እናት ናት:: ዛሬ የቅዱስ ሚካኤልን ስዕል ታቅፋ: በትእምርተ መስቀልም አማትባ አርፋለች: ቅዱሱ መልአክም ወደ ገነት አሳርጓታል::

††† ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ †††

የደጋግ ክርስቲያኖች ግን የድሆች ልጅ:
¤በሕጻንነቱ በግፍ ወደ ባሕር የተጣለ:
¤በእግዚአብሔር ጥበብ አድጎ የግፈኛውን ንብረት የወረሰ:
¤በመልካም ትዳር በቅስና ያገለገለ:
¤ምጽዋትን ያዘወተረ: አብያተ ክርስቲያናትን ያሳነጸ ደግ ክርስቲያን ነው::
¤በዚህች ቀን አርፎ ቅዱስ ሚካኤል ወዳጁ በዕረፍተ ገነት አኑሮታል::

††† አምላካችን እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ በረከት ይክፈለን:: አሜን:: †††

††† ሰኔ 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
3.ቅድስት አፎምያና ባለቤቷ ቅዱስ አስተራኒቆስ
4.ቅዱስ ባሕራን ቀሲስ
5.ቅዱስ እለ እስክንድሮስ ሊቅ
6.አባ ዮስጦስ ሊቀ ዻዻሳት (የሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ ደቀ መዝሙር)
7.አባ ቄርሎስ ሊቀ ዻዻሳት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ ድሜጥሮስ
3.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
4.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
5.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
6.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

††† "በሰማይም ሰልፍ ሆነ:: ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ:: ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ:: አልቻላቸውምም:: ከዚያም ወዲያ በሰማይ ሥፍራ አልተገኘላቸውም:: ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ወደ ምድር ተጣለ::" †††
(ራዕይ. 12:7)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
https://t.me/felegetibebmedia
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞ ✞ እንኩዋን ለአራቱ ቅዱሳን አበው ሰማዕታት
ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ ✞

=> #4ቱ_ቅዱሳን አበው የዘመነ ሰማዕታት ፍሬዎች ሲሆኑ
ስማቸው #አባ_አክራ : #አባ_ዮሐንስ : #አባ_አብጥልማ
እና #አባ_ፊልዾስ ይባላሉ:: ከመከራ ዘመን በፊት
(ማለትም በቀደመ ሕይወታቸው) ካህናትና ሃብታሞች
ነበሩ:: ሀብቱ ግን በሥራ ብቻ የተገኘ ነው::

+ታዲያ ቅዱሳኑ በያሉበት ሆነው በሀብታቸው እንግዳ
እየተቀበሉ: ድሆችን እያበሉ: በክህነታቸው ደግሞ
እያስተማሩና እየናዘዙ ትጉሃን ስለ ነበሩ በሰውም ሆነ
በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስ ነበራቸው:: በእንዲህ ያለ
ግብር ሳሉ ዘመነ ሰማዕታት አሐዱ አለ:: "ክርስቶስን ካዱ:
ለጣዖት ስገዱ" እያሉ መኩዋንንቱና ነገሥታቱ ሕዝበ
ክርስቲያኑን ያሰቃዩ ገቡ::

+በዚህ ጊዜ 4ቱ ቅዱሳን አንድ ነገር መከሩ:: በየእሥር
ቤቱ የተጣሉ ክርስቲያኖችን ለማገልገል ቆረጡ:: እግረ
መንገዳቸውን እያስተማሩ እሥረኞችን ያጽናኑ ገቡ::
የራበውን ያበላሉ: የተሰበረውን ይጠግናሉ: በቁስሉም ላይ
መድኃኒትን ያደርጉ ነበር:: የመከራው ዘመን ግን እየረዘመ:
ግፉም ከልክ እያለፈ መጣ::

+በዚህ ጊዜ 4ቱ ቅዱሳን ትልቁንና የመጨረሻውን ውሳኔ
አስተላለፉ:: ከሰማዕታት ወገን ይቆጠሩ ዘንድ
መርጠዋልና: ክርስቶስን በሞቱ ይመስሉት ዘንድ ሽተዋልና:
የሩጫቸው መጨረሻ ሰማዕትነት እንዲሆን መረጡ::

+አራቱም ያላቸውን ንብረት ሁሉ ሰብስበው ለነዳያን
አካፈሉ:: በትከሻቸው ካለች አጽፍ በቀር ስባሪ ገንዘብ
ከሃብታቸው አላስቀሩም:: ከዚያ ጉዞ ወደ ምስክርነት
አደባባይ (ዐውደ ስምዕ) አደረጉ::

+በዙፋኑ የተቀመጠው የመኮንኑ ግርማ: መሬት ላይ
የፈሰሰው የወገኖቻቸው ደም: የሠራዊቱ ድንፋታ ቅዱሳኑን
አላስፈራቸውም:: በይፋ "ክርስቲያን ነን" ሲሉ ተናገሩ::
በዘመኑ እንዲሕ ብሎ መናገር አንገት የሚያስቆርጥ ትልቅ
ድፍረት ነበር::

+መኮንኑም ከበጐ ሃይማኖታቸው ይለያቸው ዘንድ በእሳት
አቃጠላቸው:: እግዚአብሔር አዳናቸው:: በቀስትም:
በስለትም: በብረትም ለቀናት አሰቃያቸው:: ቅዱሳኑ ግን
አምላካቸውን አምነው ሁሉን በአኮቴት ተቀበሉ::
በመጨረሻ ግን በዚሕች ዕለት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው
ተገድለዋል:: ስለ ምጽዋታቸው: በጎ አገልግሎታቸውና
ሰማዕትነታቸው ጻድቅ: ፈራጅ ከሆነ ፈጣሪ አክሊልን
ተቀብለዋል::

=>የበረከት አምላክ ከወዳጆቹ ጸጋ ክብርን ያድለን::

=>ሰኔ 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱሳን አበው ሰማዕታት (አባ አክራ: አባ ዮሐንስ: አባ
አብጥልማ: አባ ፊልዾስ)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
2.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
3.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)
5.አባ ስምዖን ገዳማዊ
6.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
7.እናታችን ቅድስት ነሣሒት

=>+"+ እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ: እስከ
አሁንም ስለምታገለግሏቸው ያደረጋችሁትን ሥራ:
ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመጸኛ
አይደለምና:: በእምነትና በትእግስትም የተስፋውን ቃል
የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ
ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ
መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን::+"+ (ዕብ. 6:10-13)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
https://t.me/felegetibebmedia
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

እንኳን አደረሳችሁ ❖

✞ ✞ እንኩዋን ለሰማዕቱ #ቅዱስ_ሚናስ ዓመታዊ
የቅዳሴ ቤት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞ ✞

+"+ #ቅዱስ_ሚናስ ምዕመን ሰማዕት +"+

=>ቅዱስ ሚናስ ( #ማር_ሚና ) በምድረ ግብጽ ተወዳጅ
ከሆኑ ሰማዕታት ዋነኛው ነው:: ልክ በሃገራችን
#ቅዱስ_ጊዮርጊስ ልዩ ቦታ እንዳለው ሁሉ ግብፃውያን
ማር ሚናስን ጠርተው አይጠግቡትም::

+ምክንያቱም ከታላላቅ ሰማዕታት አንዱ በመሆኑና ዛሬም
ድረስ ለጆሮና ለዐይን ድንቅ የሆኑ ተአምራትን ስለሚሠራ
ነው:: በተለይ ለታመመ: ለደከመና ለተጨነቀ ፈጥኖ
ደራሽ: ባለ በጐ መድኃኒት ፈዋሽና አማላጅ ነው::

+ግብጽ ውስጥ ቅዱሱን የማያውቅ ሰው ካገኛችሁ እርሱ
ኦርርቶዶክሳዊ አይደለም ማለት ነው ሲባልም ሰምተናል::
በነገራችን ላይ ለቅዱሳን ተገቢውን ክብር በመስጠት:
ታሪካቸውን በመጻፍ: በማጥናት: በመጽሔት: በፊልምና
በመሳሰሉት ለሕዝብ በማስተዋወቅ ግብጻውያኑ ከእኛ ብዙ
ርቀት ሒደዋል:: ዛሬ እንኩዋ የምንጠቀምበትን ስንክሳር
80 ከመቶ እጁን ያዘጋጁት እነርሱ ናቸው::

+አባቶቻችንና እናቶቻችን #ኢትዮዽያውያን_ቅዱሳን ግን
አብዛኞቹ ተረስተው ቀርተዋል:: መጽሐፈ ገድላቸውንም
ብል በልቶታል:: ዛሬም የቤት ሥራው የእኛ ብቻ ነው::

+ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ ሚናስ (ትርጉሙ
ታማኝና ቡሩክ ማለት ነው):-
¤በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ የደጋግ ክርስቲያኖች ልጅ
¤በልጅነቱ የቅድስና ሕይወትን ያጣጣመ
¤በዘመኑ ሰው እጅግ ተወዳጅ የነበረ
¤ሃብትን: ክብርን: ሥልጣንን ንቆ በጾምና በጸሎት የተወሰነ
¤በመጨረሻም በክርስቶስ ስላመነ አላውያን የገደሉት
ሰማዕት ነው::

+እርሱ ሰማዕት ከሆነ ከበርካታ ዘመናት በሁዋላ
ምዕመናን ክቡር አካሉን ፈልገው ያጡታል::

+የሚገለጥበት ጊዜ ሲደርስ ግን እርሱ የተቀበረበት
ምድረ በዳ የበጐችና የእረኞች መዋያ ነበርና ተአምራትን
አደረገ:: አንድ እረኛ በጐቹ ድውያን ሆኑበት:: በዚያ ሰሞን
ከቅዱሱ መቃብር ላይ ጸበል ፈልቆ ነበርና እረኛው ተርታ
ውሃ ነው ብሎ በጎቹን ሲያጠጣቸው አንዱ ድውይ በግ
ወደ ጸበሉ በመዘፈቁ ዳነ::

+በዚህ የተገረመው እረኛ ሁሉንም የታመሙ በጐቹን
አምጥቶ ነከራቸው:: እነርሱም ተፈወሱ:: ይህ ዜና
በምድረ ግብፅ ሲሰማ ድውያን ሁሉ እየመጡ ይፈወሱ
ገቡ:: ግን እነሱም ሆነ እረኛው ምክንያቱን ማወቅ
አልቻሉም::

+ነገሩ በሮም ንጉሥ ዘንድ ሲሰማ ሴት ልጁን ከሠራዊቱ
ጋር ላካት:: ምክንያቱም እርሷ ከብዙ ዘመን ጀምራ
መጻጉዕ ነበረችና ፈውስን አጥታ ነበር:: መጥታ
ተጠመቀች: ፈጥናም ተፈወሰች:: እርሷ ግን እንደ ሌሎች
ያዳናትን ማንነት ሳታውቅ መሔድ አልፈለገችምና ሱባዔ ገባች::

+#ቅዱስ_ሚናስ በሌሊት ራዕይ መጥቶ ሥጋው እንዳለ
ነገራት:: እርሷም መሬቱን አስቆፍራ የቅዱሱን አካል
በክብር አስወጣች:: ከዚያም በንጉሡ ትዕዛዝ ምድረ
በዳው ከተማ እንዲሆን ተቀየረ:: ስሙም " #መርዩጥ "
ተባለ:: ጸበሉ የነበረበት ቦታም ላይ የማር ሚናስ
#ቤተ_ክርስቲያን ታንጾበት በዚህች ዕለት ቅዳሴ ቤቱ
ተከብሯል::

=>አምላካችን ከቅዱሱ ሰማዕት በረከትን ይክፈለን::

=>ሰኔ 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ሚናስ (ማር ሚና) ሰማዕት (ቅዳሴ ቤቱ)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
3.ቅድስት እንባ መሪና
4.ቅድስት ክርስጢና

=>+"+ ፈጥኜ ወደ አንተ እንድመጣ ተስፋ አድርጌ ይሕን
እጽፍልሃለሁ:: ብዘገይ ግን በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት
መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ::
ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት የሕያው እግዚአብሔር
ቤተ ክርስቲያን ነው:: እግዚአብሔርንም የመምሠል
ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው:: +"+ (1ጢሞ.
3:14)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
https://t.me/felegetibebmedia
እንኩዋን ለሐዲስ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

#ቅዱስ_ጊዮርጊስ_ሐዲስ

=>ሰማዕቱ የተወለደው በምድረ ግብጽ አሕዛብ (ተንባላት) በሰለጠኑበት የመጀመሪያው ዘመን ነበር:: በተለይ ተንባላቱ ግብፅና ሶርያን ከያዙ በሁዋላ ባልተጠበቀ ፍጥነት በኃይልም በሰውም ተደራጅተው ነበር:: ቅዱስ ጊዮርጊስ (ልብ በሉልኝ ሊቀ ሰማዕታት አይደለም) የተወለደው በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ነበር::

+እናቱ የተመሠከረላት ክርስቲያን ብትሆንም እንዳለመታደል አባቱ ተንባላታዊ (አሕዛብ) ነበር:: ስሙንም መዛሕዝም ይሉታል:: ሕጻኑ እንደተወለደ ያወጡለት ስም አሕዛባዊ ከመሆኑ ባለፈ በሰዓቱ መጠመቅ አልቻለም:: የወቅቱ ሕግ ከወላጆቹ አንዱ አሕዛባዊ ከሆነና አጠምቃለሁ ቢባል የሚከተለው ሰይፍ ነበር:: በዚሕ ምክንያት ሳይጠመቅ 7 ዓመት ሞላው::

+እናቱ ግን ሕጻን ቢሆንም ፍቅረ ክርስትናን ታስተምረው ነበር:: ባይጠመቅም ጸበሉን: እመቱን ትቀባው ነበር:: ደብቃ ቅዳሴ ታሰማውም ነበር:: አንድ ቀን ግን ሕጻናት ሲቆርቡ አይቶ ካልቆረብኩ ብሎ አለቀሰ:: ምን ታድርገው? ወደ ውጪ አውጥታ ከአውሎግያ (የሰንበት በረከት) አበላችው:: "ጌታየ! ልጄን እርዳው" አለች::

+ልክ በአፉ ሲቀምሳት መዓዛ መንፈስ ቅዱስ አደረበትና ፍጹም ተደሰተ:: ትንሽ ከፍ ሲል ለምን እንደማይጠመቅና እንደማይቆርብ እናቱን ጠየቃት:: "ልጄ ሆይ! ይገድሉሃል" አለችው::
ከዚህች ቀን ጀምሮ የሚጠመቅበትን ዘዴ ይፈልግ ጀመር::

+አስቀድሞ ትምሕርተ ክርስትናን ተማረ:: ለአካለ መጠን ሲደርስ አፈላልጐ ጠንካራ ክርስቲያን የሆነች ሴት አገባ:: ጥቂት ጊዜ ከቆየ በሁዋላ ሚስቱን ስለ መጠመቅ አማከራት:: "ሌላ ሃገር ሒደህ ተጠመቅ" አለችው:: ከግብፅ ተነስቶ ሶርያ ገባ:: አባቶችን አፈላልጎ ተጠመቀ:: ቀጥሎም መንገዱን ወደ ልዳ አደረገ::

+ወደ ደብሩ ተጠግቶ አባቶችን "ስም አውጡልኝ" ቢላቸው #መንፈስ_ቅዱስ አናግሯቸው "#ጊዮርጊስ" አሉት:: እሱም ደስ እያለው: ባጭር ታጥቆ የልዳውን ቅዱስ ጊዮርጊስ ያገለግለው ገባ:: ትንሽ ቆይቶ ሁከት መንፈሳዊ ተሰማው:: ማለትም ስለ ሃይማኖቱ ደሙን ማፍሰስ ፈለገና ወደ ግብፅ ተመለሰ::

+በዚያ ያሉ አሕዛብ በክርስትና ስም: ልብስና ሞገስ ሲመለከቱት ተበሳጩ:: ዕለቱኑ አሠሩት:: ሌሊት እናቱና ሚስቱ መጥተው አሉት:- "አደራ! ፍቅረ ዓለም እንዳያታልልህ:: ሰማዕት ብትሆን ላንተም ክብር: ለእኛም ሞገስ ነው" ብለውም አጽናኑት:: (እንዲሕ ያሉ እናትና ሚስት ማግኘትም ታላቅ እድል ነው!!!)

+ሐዲስ ጊዮርጊስም ጸና:: ከዚያች ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ደበደቡት: አካሉን ቆራረጡት: ደሙንም መሬት ላይ አንጠፈጠፉት:: በየመንገዱ እየጎተቱ ተሳለቁበት:: እርሱ ግን #ክርስቶስን ወዷልና ሁሉን ታገሰ:: ሌሊት በሆነ ጊዜም ጌታችን ተገልጦ "ከሰማዕታት ተቆጠርህ" አለው::

+በማግስቱ በአደባባይ አንገቱን በሰይፍ ቆረጡት:: ክፋታቸው የጸና ነውና ሥጋውን በእሳት አቃጠሉት:: ወደ ባሕርም ጣሉት:: እናቱ ከባሕር ስታወጣው ግን ምንም አላገኘውም ነበር:: በዚሕች ቀን እናቱና ሚስቱ በክብር ቀብረውታል::

=>ቸሩ አምላክ ከሰማዕቱ ጽናትን: ትእግስትን: ጸጋ በረከትን ይክፈለን::

=>ሰኔ 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሐዲስ ሰማዕት
2.አባ ብሶይ አኖብ ሰማዕት (በአንበሳ ጀርባ ላይ የተቀመጠ አባት)
3.ቅዱሳን "5ቱ" ጭፍሮች (በብዙ ስቃይ ሰማዕት የሆኑ ባልንጀሮች)
4.አባቶቻችን የደብረ ቁዋዐት ጻድቃን

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
3.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
4.አቡነ ስነ ኢየሱስ
5.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

=>+"+ ስለዚሕ #ወንድሞቼ_ሆይ! ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ:: ልባሞች እንደመሆናችሁ እላለሁ:: በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ:: የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? . . . እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን:: ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና:: +"+ (1ቆሮ. 10:14-18)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር

https://t.me/felegetibebmedia
††† እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ሕንጸተ ቤታ (ሕንጸታ) በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

††† በዓለ ሕንጸታ †††

††† በዚሕች ቀን : በሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በአምላክ እናት ስም ታንጻለች::
ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን "ሑሩ ወመሐሩ ኩሎ አሕዛበ" (አሕዛብን ሁሉ ሒዱና አስተምሩ) /ማቴ. 28:19/ ባላቸው ቃል መሠረት ዓለምን በወንጌል ያርሷት ዘንድ በዕጣ ተካፍለዋታል::

የሰው ልጅ ድኅነቱ የሚፈጸመው ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበል ነውና (ዮሐ. 6:56) አበው ሐዋርያት ቁርባንን በተመረጡ ሰዎች ቤት እያዘጋጁ ቀድሰው ያቆርቡ ነበር::

በመጀመሪያ በጽርሐ ጽዮን: ቀጥሎም በተለያዩ ሰዎች ቤት እንዲሕ ይከናወን ነበር:: ለጸሎት ሥራ ደግሞ አንዳንዴ ምኩራበ አይሁድን ይጠቀሙ ነበር:: እየቆየ ሲሔድ ግን ከአሕዛብ ያመኑ ሰዎች ቁጥር እጅጉን በዛ::

በተለይ ቅዱስ ጳውሎስ ያሳመናቸው ለጸሎት እያሉ ወደ ጣዖት ቤት መግባት አመጡ:: በዚሕ ምክንያት መምሕራን ሕዝቡን "ካመናችሁ በኋላ እንዴት ወደ ጣዖት ቤት ትገባላችሁ?" ቢሏቸው "እኛ ምን እናድርግ! የምንጸልይበት እንደሆን የለን" ሲሉ መለሱላቸው::

ነገሩ ሲያያዝ ከደጋጉ ሐዋርያት ጳውሎስና በርናባስ ደረሰ:: ወዲያውኑ አንዳንድ ወንድሞች "ለምን አናንጽም" ብለው ነበር:: ቅዱስ ጳውሎስ ግን "ሊቀ ሐዋርያቱ ሳይፈቅድ አይሆንም" አለ:: (ለዚሕ ነው ዛሬም ሊቀ ጳጳስ ካልፈቀደ ቤተ ክርስቲያን የማይታነጸው::)

ከዚያ ቅዱሳን ጳውሎስና በርናባስ ሐዋርያቱ ወዳሉበት ሔደው ነገሩን ለቅዱስ ጴጥሮስ አስረዱ:: ሊቀ ሐዋርያቱም "የጌታችን ፈቃዱ መሆኑን እናውቅ ዘንድ ተያይዘን ሱባዔ እንግባ" ብሎ አዋጅ ነገረ::

በዓለም ያሉ ክርስቲያኖች ሁሉ በአንድ ልብ ሱባዔ ገቡ:: በሱባዔአቸው መጨረሻም ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግርማ ወደ እነርሱ ወረደ::

ሁሉንም ሐዋርያት በደመና ጭኖ ፊልጵስዩስ አደረሳቸው:: ከከተማ ወጣ ብሎ ባለ መሬት ላይም "ቤተ ክርስቲያንን በእናቴ ስም አንጹ" ብሎ አዘዛቸው:: ለቅዱስ ጴጥሮስም ሦስት ዓለቶችን ሰጠው::

እነዚያን መሬት ላይ ተክሎ : ጌታችን ቆሞለት : ሐዋርያቱ እየተራዱት : ግርምት የምትሆን ሦስት ክፍል ያላትን የመጀመሪያዋን ቤተ ክርስቲያን በ52 ዓ/ም በዚህች ቀን አንጿል::

¤ቤተ ክርስቲያኗን ነገ ጌታችን ቀደሳት የምንል ነንና ይቆየን::

††† አምላካችን የድንግል እናቱን ፍቅር : የተቀደሰች ቤቱን ጸጋ : የቡሩካን ሐዋርያቱን በረከት ያሳድርብን::

††† ሰኔ 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም
2.ቅድስት ቤተ ክርስቲያን
3.ቅዱሳን ሐዋርያት
4.ቅዱስ ኤልሳዕ ነቢይ (ዕረፍቱ)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት (ሰማዕት)
2.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
3.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
4.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
5.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
6.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት

††† "በድካም: አብዝቼ በመገረፍ: አብዝቼ በመታሠር: አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ:: በድካምና በጥረት: ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት: በራብና በጥም: ብዙ ጊዜም በመጦም: በብርድና በራቁትነት ነበርሁ . . . የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው::" †††
(፪ቆሮ. ፲፩፥፳፫-፳፰)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††


""ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን""::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
https://t.me/felegetibebmedia