ፒያሳ መሃሙድ ጋ ጠብቂኝ
243K subscribers
289 photos
1 video
16 files
240 links
እዚህ Channel ላይ ያስተምራሉ ያዝናናሉ ብለን የምናስባቸውን
ተከታታይ ልቦለድ
ግጥም
ወግ
ሳይኮሎጂ
ምክር
መነባንብ

#ማንኛውም አይነት ፅሁፎች📕 ከፈለጉ ይቀላቀሉን
የተለያዩ PDF መፅሐፍት ከፈለጉ @Eyosibooks
አስተያየት ካሎት👇👇
+251933324708
☎️ +251922788490
📩@Eyos18
Download Telegram
😎ጠላፊዎቹ

#ክፍል_ሰላሳ_ሦስት

#በኬንፎሌት

#ትርጉም_ወንዳየሁ_ንጉሴ


ማርጋሬት ኦክሰንፎርድ በአባቷ አድራጎት ስላፈረች መሬት ተከፍታ ብትውጣት በወደደች፡ የአይሮፕላኑ ተሳፋሪ ሁላ በተፈጠረው አስከፊ ሁኔታ የአባቷን ጋጠወጥ ባህሪ እሷም ትጋራ ይሆን?› እያለ እያሰበ የሚያፈጥባት መሰላት፡ የሰዉን አይን ማየት ፈራች:

ሄሪ ማርክስ የቀራት እንጥፍጣፊ ክብሯ ሳይገፈፍ ደረሰላት፡ ቀልጠፍ
ብሎ ተነስቶ በማክበር ወምበሯን ያዝ አድርጎላት፣ ሶቶ እንድትይዘው
ክንዱን ሰጥቷት ከመብል ክፍሉ እንድትወጣ አገዛት፧ ያደረገው ነገር ትንሽ
ቢሆንም እሷን ግን ልቧን ነክቷታል።

አባቷ ለዚህ እፍረት ስለዳረጓት በእጅጉ አንገብግቧታል፡፡ ራት ከተበላ በኋላ በመብል ክፍሉ ውስጥ ለሁለት ሰዓት ያክል የሚከብድ ጸጥታ ነግሶ ቆየ፡ የአየሩ ሁኔታ እየተበላሸ ሲመጣ አባባ እና እማማ የቀን ልብሳቸውን
አውልቀው የመኝታ ልብሳቸውን ለበሱ፡
ፔርሲ ‹‹ይቅርታ እንጠይቅ›› አላት ማርጋሬትን ድንገት፡
ፔርሲ ይህን ሲላት ይቅርታ መጠየቁ የበለጠ እፍረት ውስጥ እንደሚጥላቸው ገመተች፡ ‹‹እኔስ ይቅርታ ለመጠየቅ ድፍረቱ የለኝም››
አለችው ወንድሟን፡፡

‹‹ባሮን ጋቦንና ፕሮፌሰር ሃርትማን ጋ ሄደን አባታችን ስላሳየው ያልተገባ ባህሪ ይቅርታ ብንጠይቅ ነው የሚሻለው›› አለ ፔርሲ፡
የአባቷን ጥፋት ለማለዘብ ይቅርታ መጠየቁ ጥሩ ሳይሆን አይቀርም ስትል አሰበች፡፡ እሷም ቀለል ይላታል፡፡ ‹‹አባባ ግን ይናደድብናል›› አለች
አበዛው! አብዷል መስለኝ ከዚህ በኀላ አልፈራውም›› አለ ፔርሲ፡

‹‹እሱ ማወቅ የለበትም ቢናደድ ደግሞ ግድ የለኝም፧ አሁንስ
ፔርሲ ከዚህ በኋላ አልፈራውም› ያለው እውነት መሆኑን ማርጋሬት
አላወቀችም: ህጻን ሆኖ አባታቸውን ፈርቷቸው እያለ ‹አልፈራውም› ይል
ነበር፤ አሁን ግን ህጻን አይደለም፡፡

ፔርሲ ከአባታቸው ቁጥጥር ውጭ እየሆነ መምጣቱ ማርጋሬትን አሳስቧታል፡ አባቷ ብቻ ናቸው የፔርሲን
ያልተገባ ባህሪ ሊያርቁ
የሚችሉት፤ ፔርሲ ሸረኝነቱን እንዲተው ካልተደረገ አይቻልም፡፡

‹‹በይ እንጂ! አሁን እንሂድና ይቅርታ እንጠይቃቸው፤ ያሉበትን ቦታ እኔ አውቀዋለሁ›› አለ ፔርሲ፡
ማርጋሬት ይቅርታ ለመጠየቅ ፈራ ተባ አለች እያለች ነው አባቷ
ያስቀየሟቸው ሰዎችጋ መሄድና ይቅርታ መጠየቅ ከብዷታል፤ የሆነውን
ሁሉ መተውና አርፎ መቀመጥ ነው የሚሻላቸው ቁስላቸውን መነካካቱ
ምንም ፋይዳ የለውም፡ ሆኖም የዘር መድሎን ለመቃወም እጅ ለእጅ
መያያዝ ያስፈልጋል።

በመጨረሻ ማርጋሬት ሰዎቹን ይቅርታ ለመጠየቅ ወሰነች፡ መቼም ጥሎባት ቦቅቧቃ ናት፡ ከዚህ ቀደም ላጠፋችው ጥፋት ፈርታ ይቅርታ ሳትጠይቅ መቅረቷ ሁልጊዜ ይጸጽታታል፡
አይሮፕላኑ በወጀቡ እየተወዛወዘ ቢሆንም የወንበሯን መደገፊያ ጠበቅ
አድርጋ ይዛ ተነሳችና ‹‹እሺ እንሂድ›› አለችው ወንድሟን፡
የአይሮፕላኑ መወዛወዝ በፍርሃት መንቀጥቀጧን ደብቆላታል፡ ሁለቱ
ሰዎች ወዳሉበት ክፍል አመራች፡፡

ጋቦንና ሃርትማን ግምባር ለግምባር ተቀምጠዋል፡ ሃርትማን የሂሳብ መጽሐፍ ላይ በተመስጦ አፍጠዋል፡፡ ጋቦን የሚሰሩትን አጥተው በጉዞው ተሰላችተው ተቀምጠዋል፡ በመጀመሪያ ማርጋሬትንና ፔርሲን ያይዋቸው እሳቸው ናቸው፡ ማርጋሬት አጠገባቸው መጥታ ወምበራቸውን ተንገዳግዳ ስትይዝ አዩና ፊታቸውን አኮሳተሩ።

ማርጋሬት ቶሎ ብላ ‹‹ይቅርታ ለመጠየቅ ነው የመጣነው›› አለች፡
‹‹ደፋር ነሽ!›› አሉ ጋቦን የፈረንሳይኛ ቋንቋ ቅላጼ ባለው እንግሊዝኛ፡
ማርጋሬት እንዲህ ያለ ምላሽ ይገጥመኛል ብላ ባታስብም ጥረቷን
ቀጠለች፡ ‹‹በአባታችን አድራጎት በጣም አዝኛለሁ፤ ወንድሜም እንዲሁ
ለፕሮፌሰር ሃርትማን ያለኝ አድናቆት ከፍተኛ ነው፡ ይህንንም ከዚህ ቀደም
ነግሬያቸዋለሁ›› አለች፡:

ሃርትማን ንባባቸውን አቋርጠው ይቅርታውን መቀበላቸውን ራሳቸውን
በመነቅነቅ አመለከቱ፡ ጋቦን ግን አሁንም በቁጣ አበያ በሬ እንደመሰሉ ነው
‹‹እንደ እናንተ ላሉ ሰዎች ይቅርታ መጠየቅ ቀላል ነው›› ሲሉ ማርጋሬት
የምታደርገው ጠፍቷት በድንጋጤ መሬት መሬቱን ታያለች፡፡ ‹ምነው
ባልመጣሁ አለች በሆዷ፡ ‹‹ጀርመን ውስጥ እየተደረገ ያለው ነገር በጣም
እንደሚያሳዝናቸው የሚነግሩን ጨዋ ሰዎች ብቻ ናቸው›› ሲሉ ቀጠሉ ‹‹ግን ምን አደረጉልን፤ እናንተስ ምንድነው የምታደርጉልን?›› አሉ ጋቦን፡፡
ማርጋሬት ፊቷ በድንጋጤ በርበሬ መሰለ፡፡ ምን እንደምታደርግ ግራ ግብት አላት።

‹‹ፊሊፕ ዝም በል እንጂ›› አሉ ሃርትማን ለስለስ ባለ አነጋገር ልጆች እኮ ናቸው›› ወደ ማርጋሬትም ዞር አሉና ‹‹ይቅር ብለናል እናመሰግናለን››

‹‹ጌታዬ ተሳሳትን ይሆን?›› ስትል ጠየቀች::

‹‹በፍጹም›› አሉ ሃርትማን ‹‹እንደውም ጥሩ ነው ያደረጋችሁት ይባርክሽ፧ ጓደኛዬ በጣም ስሜቱ ስለተነካ ነው እንዲህ የሆነው፤ በኋላ እንደእኔ ሲገባው ከንዴቱ መለስ ይላል፡››

‹‹እንግዲህ እንሂድ›› አለች ማርጋሬት እንደከፋት፡
ሃርትማን በመስማማት ራሳቸውን ነቀነቁ፡፡
ፔርሲም በተራው ‹‹ይቅርታ አድርጉልን›› አለና ከእህቱ ጋር ተያይዘው
ሄዱ፡፡

ወንድምና እህቱ በአይሮፕላኑ ውዝዋዜ እየተንገዳገዱ ወደ ቦታቸው
ተመለሱ፡፡ ዴቭ መኝታቸውን እያነጣጠፈላቸው ነው፡፡ ሄሪ በቦታው የለም፡ ምናልባትም ወደ መታጠቢያ ቤት ሄዶ ይሆናል፡፡ ማርጋሬት ልብስ
ለመለወጥ ቦርሳዋን አንጠልጥላ ወደ መታጠቢያ ቤት ሄደች፡ እናቷ የመኝታ ልብሳቸውን ለብሰው እምር ድምቅ ብለው ከመጸዳጃ ቤት እየወጡ ስለነበር
‹‹ደህና እደሪ የኔ ማር›› ቢሏትም እሷግን ዝግት አድርጋቸው ገባች:
በሴቶች በሞላው መታጠቢያ ቤት ውስጥ የመኝታ ልብሷን ቶሎ ለውጣ ወጣች፡፡ የመኝታ ልብሷ ሌሎቹ ሴቶች ከለበሱት ደመቅመቅ ካሉትና ከሃር ከተሰሩት ልብሶች ጋር ሲነጻጸር ኋላ ቀር መሆኑ ግድ አልሰጣትም፡፡ ባሮን
ጋቦን በኋላ ያሉት እውነት በመሆኑ ይቅርታ መጠየቁ የፈየደው ነገር የለም ለችግሩ ምንም መፍትሄ ሳያመጡ ይቅርታ› ማለት ቀላል ነው።

ወደ ቦታቸው ሲመለሱ እናትና አባቷ መጋረጃቸውን ጋርደው ተኝተዋል፡፡ አባቷ አገር አማን ነው ብለው ያንኮራፋሉ፡፡ ማርጋሬት የእሷ መኝታ እስኪዘጋጅ ቁጭ ብላ ጠበቀች፡፡

ከቤተሰቦቿ ቁጥጥር ነፃ ለመሆን አንድ መንገድ ብቻ ነው ያላት  እነሱን ትታ እየሰራች መኖር አሁን ይህን ለማድረግ ቆርጣለች፡፡ የገንዘብ፣ የስራና የመኖሪያ ቦታ ችግሯን ለመቅረፍ ግን ገና ነች፡፡

ፎየንስ ላይ የተሳፈረችው ዘናጯ ናንሲ አጠገቧ መጥታ ተቀመጠች።
ሴትየዋ የመኝታ ልብስ ነው የለበሰችው፡፡ ‹‹አስተናጋጁ ብራንዲ እንዲያመጣልኝ ፈልጌ ነበር፤ እሱ ግን እረፍት የለውም፧ እዚህ እዚያ ይንከወከዋል
አለች፡ ሲያይዋት ዘና ብላለች፡ ተሳፋሪው እንዲያያት እጇን አውለበለበች
‹‹ለምን ፓርቲ አንጨፍርም፤ ምን ትያለሽ?›› አለቻት ማርጋሬትን፡፡
‹‹ያልሽው ነገር እንግዳ ነው የሆነብኝ›› አለቻት ማርጋሬት፡፡
ናንሲ የመቀመጫ ቀበቷን አጠባበቀች፡ ደስ ደስ ብሏታል። ‹በፒጃማ
ስትሆኚ መከባበር ብሎ ነገር የለም፤ የወዳጅነት ስሜት መስፈን ነው
ያለበት፡፡ ፍራንክ ጎርደን እንኳን ፒጃማው አምሮበታል፡››

ማርጋሬት በመጀመሪያ ስለማን እንደምታወራ  አልገባትም ነበር፡፡
ወዲያው ግን ካፒቴኑና የኤፍ.ቢ.አይ መርማሪው ሲጨቃጨቁ ፔርሲ ሰምቶ
የነገራት ነገር ትዝ አላት
‹‹እስረኛውን ማለትሽ ነው?›› ስትል ጠየቀቻት።
‹‹አዎ››
‹‹አንቺ አትፈሪውም?››
‹‹አይ አልፈራውም፧ ምን ያደርገኛል!››
‹‹ሰዎች ግን ነፍሰ ገዳይ ነው ይሉታል››