Ethio Fm 107.8
19.5K subscribers
6.18K photos
16 videos
4 files
2.27K links
በፍቅር ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነት እንዳይላላ ከልቡ የሚተጋ፣ መከባበርና መተሳሰብን የሚያስቀድም ኤፍ ኤም ሬዲዮ ነው!!!
Download Telegram
ኢትዮጵያ 22 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች የኮቪድ-19 ክትባት ልትሰጥ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እስከ ፈረንጆቹ 2021 መጨረሻ ድረስ ለ22 ሚሊዮን ዜጎች ኮሮና ቫይረስ ክትባት ልትሰጥ መሆኗን አስታውቃለች፡፡

የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ እስከ ፈረንጆቹ 2021 ድረስ 20 ከመቶ የሚሆነው ህዝብ ለመከተብ ታቅዷል ብለዋል፡፡

እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ 2.4 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎቿን የከተበች ሲሆን በኮቫክስ ጥምረት አማካኝነት 22 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች እስከ 2021 ድረስ ይከተባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን በአንድ ሳምንት ብቻ እስከ 10ሺህ ያህል ዜጎች በቫይረሱ እየተያዙ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በአጠቃላይ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 308ሺህ 134 የደረሰ ሲሆን 276 ሺህ 842 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።

እንደዚሁም 4 ሺህ 675 ያህል ዜጎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል፡፡

ሔኖክ ወ/ገብርኤል
ነሐሴ 26 ቀን 2013 ዓ.ም
የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት በ 257 የፖሊስ መኮንኖች ይጠበቃሉ

የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በ257 የፖሊስ አባላት ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን መንግስት ይፋ አድርጓል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የካቢኔ ፀሐፊ ፍሬድ ማቲያንጊ ትላንት ለፓርላማው የደህንነት ኮሚቴ እንደገለፁት የምክትል ሩቶን መኖሪያ ቤት በሚጠብቁ የፖሊስ ክፍሎች ውስጥ የተደረጉ ለውጦች እንዳሉ ገልፀው ነገሩ ግን “መደበኛ” እና የተለመደ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ምክትል ፕሬዝደንቱ ሩቶን ከሚጠብቋቸው መኮንኖች መካከል 74 እጅግ ምርጥ የሚባሉ ፕሬዝደንታዊ ጠባቂዎች ናቸው ብለዋል።

ይህ ብቻ አይደለም የእኚህ ሰው ሁለት ሄሊኮፕተሮች በአውሮፕላን ማረፊያ ሆነው የሚጠብቁ ሌሉች የፖሊስ መኮኑኖች መኖራቸውን ሚቲያንጊ ተናግረዋል ሲል ቢቢሲ አፍሪካ ዘግቧል።

በሀገሪቱ የምክትል ፕሬዝደንት ታሪክ እጅግ ጥበቃ የሚደረግላቸው ሰው ስለመሆኑም ተነግሯል፡፡

ሰውዬው ከፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬኒያታ ጋር ቅራኔ እንዳላቸው ይነገራል እንደውም በቀጣይ አመት ከስልጣናቸው ለማንሳት ኡሁራ አስበዋል ተብሏል፡፡

የምክትል ፕሬዝደንቱና ደጋፊዎቻቸው በእጅጉ በአይነ ቁራኛ የሚታዩ ናቸው ፡፡

ሰውዬው ከተቀናቃኙ ራይላ ኦዲንጋ ጋር የልብ ወዳጆች ናቸውም ይባላል፡፡

ያይኔ አበባ ሻምበል
ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም
ታሊባን እና አሜሪካ ዳግም የዲፕሎማሲ ግንኙነት የማይጀምሩበት ምንም ምክንያት የለውም አሉ አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን

ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባሉት የአሜሪካ የሕግ አውጪው ግሪጎሪ ሜይክስ ለታሊባን እውቅና መስጠት ይችላል ብለዋል

የምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ዴሞክራቲክ ሊቀመንበር ግሪጎሪ ሜይክስ ወደፊት በታሊባን የሚመራውን መንግስት ዕውቅና እንደማያገኝ መናገር ልክ አይደለም ብለዋል፡፡

ቡድኑ ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበር የገባውን ቃል ማክበር እንዳለበት አሳስበዋል።

ሜይክስ ለኤም.ኤስ.ቢ.ሲ ሲናገሩ አሜሪካ ከቬትናም ከወጣች በኋላ ከቬትናም መንግስት ጋር የነበረው ግንኙነት በአንድ ወቅት የማይቻል መስሎ ነበር ፣ ነገር ግን ዋሽንግተን አሁን ከሃኖይ ጋር ሞቅ ያለ ግንኙነት አላት ብለዋል፡፡

ሜይክስ ሲያክሉ “ስለዚህ ከታሊባኑች ጋርም ይህ በጭራሽ አይሆንም አትሉም ፣ ግን ታሊባኖች በእውነት የሰብአዊ መብት መርሆዎች እንደሚጠብቁ ለማሳየት ብዙ ማድረግ አለባቸው ” ብለዋል ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።

ያይኔ አበባ ሻምበል
ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም
"ሀገር አቀፍ የፆምና የፀሎት ምህላ አዋጅ"

የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አዲሱን አመት በሰላም ለመቀበል ያለመ ለ5 ቀናት የፀሎት መርሐግብር አወጀ።

የፀሎት መርሐ ግብሩ ከጷጉሜ 1 እሰከ 5 የሚቆይ መሆኑም ተገልጿል።

ጉባኤው አዲስ አመትን ምክንያት በማድረግ የሰላም ጥሪን በሚመለከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

አገሪቱ ያጋጠማት ወቅታዊ ችግር በይቅርታና በፍቅር እንዲፈታ የተለያዩ እምነት የሚከተሉ ዜጎች በየሐይማኖታቸው የልዩ ፀሎቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጉባኤው ጥሪ አቅርቧል ሲል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

በሁለቱም ወገኖች ያሉና በትግል ውስጥ ያሉ አካላት ለእርቅ ዝግጁ ሆነው አገሪቷን ማሻገር ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም
“ሸኔ” በምእራብ ወለጋ ዞን 10 ሰዎችን ማገቱን መንግስት አስታወቀ

ባንክ እና ፍርድ ቤትን ጨምሮ ከ34 በላይ የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና ተቋማት ላይም ዝርፊያ ፈጽሟል።

የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የፈረጀው “ሸኔ” በምእራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ ወረዳ በፈፀመው ጥቃት በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን መንግስት አስታወቀ።

የቆንዳላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ቡላ ደመረ በወረዳው “ሸኔ” በፈጸመው ጥቃት የንጹሃን የተገደሉ ሲሆን፣ በርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተዘርፈው በእሳት ተቃጥለዋል ማለታቸውን ኢዜአ በአፋን ኦሮሞ ገጽ አስነብቧል።

“በጥቃቱ ሸኔ 10 ሰዎችን አግቶ ወስዷል” ያሉት አቶ ቡላ ደመረ፤ 24 ንጹሃን ዜጎችን መግደሉንም አስታውቀዋል።

ቡድኑ የወረዳውን ፍርድ ቤት እና የአቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ሙሉ በሙሉ በእሳት ማጋየቱን በመጥቀስ፤ 4 የመንግስት አመራሮች መኖሪያ ቤቶችንም አቃጥሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቆንዳላ ቅርንጫፍን አንዲሁም በ34 የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና ተቋማት ላይ ዝርፊያ መፈጸሙን ያስታወቁት የወረዳው አስተዳዳሪ፤ በወረዳው የሚገኝ የ2ኛ ደረጃ ትምህት ቤት ንብረት እና የተማሪዎችን ማስረጃ ማውደሙንም ተናግረዋል።

የ“ሸኔ” ታጣቂዎች በአጠቃላይ በወረዳው ከነሃሴ 9፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ በፈጸሙት ጥቃት ከ200 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የቆንዳላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ቡላ ደመረ ገልጸዋል።

“ህብረተሰቡ የሸኔ የሽብር ብድን የጥፋት ተግባርን ተረድቶ በአንድነት በመሆን የቡድኑን የጠላትነት ተግባር ሊያጋልጥ ይገባል” ሲሉም ዋና አስተዳዳው ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም
ክላውድ ወርልድ ዋይድ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሄሎ ታክሲ ለብሄራዊ ፓርኮች 11 የቱሪስት አምቡላንሶችን ለመስጠት ቃል ገባ።


የሜትር ታክሲ አገልግሎት ከሚሰጡት መካከል የሚገኘው ሄሎ ታክሲ በሀገራችን ለሚገኙ ብሄራዊ ፓርኮች 11 ቱሪስት አምቡላንሶችን ለመስጠት ቃል መግባቱ ተሰምቷል።

በዛሬው ዕለትም የሄሎ ታክሲ ባለቤት አቶ ዳንኤል ዮሀንስ የ3 አምቡላንሶችን ቁልፍ ማስረከባቸውን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ጌታቸው ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።


በዛሬው ዕለት የተረከቡት አምቡላንሶች ለሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ለባሌ ብሄራዊ ፓርክ እና ለነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።አክለውም ብሄራዊ ፓርኮችን የመረጥነው በብዛት ቱሪስቶች የሚጎበኟቸው ስለሆነ ነው ሲሉ ተናግረዋል።


የሄሎ ታክሲ መስራች አቶ ዳንኤል ዮሀንስ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ አንዱ አምቡላንስ እስከ 600ሺ ብር እንደወጣበት ነግረውናል።
አምቡላንሶቹን ልንሰጥ የተነሳሳንበት ዋነኛው ምክንያትም በሀገራችን የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ቱሪስቶች ወሳኝ ሚና አላቸው ብሄራዊ ፓርኮቻችን ላይ የቱሪስት አምቡላንስ መኖሩ ቱሪስቶች እንደምናከብራቸው ማሳያ እንዲሆን አስበን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በመቅደላዊት ደረጀ

ነሃሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም
ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ በድንገተኛ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

“ተማር ልጄ” በሚለው ዘመን ተሻጋሪ ዘፈኑ የብዙዎችን ቀልብ የማረከው ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ ነሐሴ 27፣2013 እኩለ ሌሊት በድንገት ማረፉ ነው የታወቀው።

"ተማር ልጄ ሌት ፀሀይ ነው ላልተማረ ሰው ግን ቀኑ ጨለማ ነው..." እያለ ሚሊየኖችን በዜማው መክሯል።

አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ በሚጫወታቸው የሙዚቃ ስራዎቹ 'ኤልቪስ ፕሪስሊ' የሚል ቅፅል ስምም ተሰጥቶት ነበር።

ስቀሽ አታስቂኝ" ፣ " እንደ አሞራ ክንፍ አውጥቼ ልብረራ"፣ " ማን ይሆን ትልቅ ሰው" ፣ " ምሽቱ ደመቀ"፣ "አዲስ አበባ ቤቴ" ፣ "የወይን ሃረጊቱ" ፣ "የሰው ቤት የሰው ነው"፣ "ደንየው ደነባ"፤ "ትማርኪያለሽ"፣ "ወልደሽ ተኪ እናቴ" እና " ተማር ልጄ" ከአለማየሁ እሸቴ ሙዚቃዎች በዋናነት የሚጠቀሱለት ናቸው።

የድምፃዊው ድንገተኛ ህልፈት ተከትሎ ብሔራዊ ቴአትርን ጨምሮ አድናቂዎቹ ሀዘናቸውን እየገለፁ ይገኛል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም በድምፃዊው ህልፈት የተሰማውን ሀዘን አየገለፀ ለቤተሰቦቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹና አድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል።
(FBC)
የአውሮፓ ህብረት ለታሊባን እውቅና እንደማይሰጥ አስታወቀ

የአውሮፓ ህብረት ታሊባንን እንደ አዲስ የአፍጋኒስታን መንግስት አልቀበልም ማለቱ ተሰምቷል።

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሀላፊ ጆሴፕ ቦሬል ማንኛውም ተሳትፏችን ጥብቅ በሆኑ ሁኔታዎች የሚገዛ እና የአፍጋኒስታንን ህዝብ የሚደግፍ ብቻ ነው ብለዋል።

ዋሽንግተን ተመሳሳይ አቋም ወስዳለች ፣ ሩሲያ እና ቻይና ግን ለስላሳ አቋም ይዘዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በስሎቬኒያ በተካሄደው የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ “እኛ በተቀናጀ መልኩ ለመስራት ወስነናል የፀጥታ ሁኔታው ከተሟላ” ብለዋል።

በተጨማሪም የአውሮፓ ህብረት በአፍጋኒስታን ላይ ከአሜሪካ ፣ ከቡድን 7 ፣ ከ ቡድን 20 እና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን “በጥብቅ” ያስተባብራል ፣ እንዲሁም ከሀገሪቱ ጎረቤቶች ጋር “ክልላዊ የፖለቲካ የትብብር መድረክ” ይጀምራል ብለዋል።

ከቀናት በፊት አንድ የአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ዴሞክራቲክ ሊቀመንበር ግሪጎሪ ሜይክስ ወደፊት በታሊባን የሚመራውን መንግስት ዕውቅና እንደማያገኝ መናገር ልክ አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ሜይክስ ለኤም.ኤስ.ቢ.ሲ ሲናገሩ አሜሪካ ከቬትናም ከወጣች በኋላ ከቬትናም መንግስት ጋር የነበረው ግንኙነት በአንድ ወቅት የማይቻል መስሎ ነበር ፣ ነገር ግን ዋሽንግተን አሁን ከሃኖይ ጋር ሞቅ ያለ ግንኙነት አላት ብለዋል፡፡

ሜይክስ ሲያክሉ “ስለዚህ ከታሊባኖች ጋርም ይህ በጭራሽ አይሆንም አትሉም ፣ ግን ታሊባኖች በእውነት የሰብአዊ መብት መርሆዎች እንደሚጠብቁ ለማሳየት ብዙ ማድረግ አለባቸው ” ማለታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።

ያይኔ አበባ ሻምበል
ነሐሴ 28 ቀን 2013 ዓ.ም
መጭውን በዓላት ምክንያት በማድረግ 108 አማራጭ የገበያ ቦታዎች ማዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ገለጸ፡፡

ቢሮዉ ቀጣዩን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ እየሰራ ካለው ስራ አንዱ ህብረተሰቡ አማራጭ እና ተደራሽ የገበያ ስፍራ እንዲያገኝና የሚፈልጋቸውን ምርቶች በቀጥታ ከአምራች ገበሬው ማግኘት እንዲችልና እየተስተዋለ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት እየሰራ መሆኑን ቢሮዉ ለጣቢያችን በላከዉ መግለጫ አሳዉቋል፡፡


በአዲስ አበባ ከተማ 108 የመገበያያ ቦታዎችን እና ከ250 ሺህ ኩንታል በላይ ተጨማሪ የግብርና ምርት የተዘጋጀ መሆኑን ቦሮዉ ጠቁሟል፡፡

በሁሉም ክፍለ ከተሞች ስራ የጀመሩት መሸጫዎቹ በከተማዋ የሚስተዋለዉን የኑሮ ዉድነት በማረጋጋት በተለይም የግብርና ውጤት የሆኑ የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን እንዲሁም ለበዓል አስፈላጊ የሆኑ እንደ እንቁላል እና አይብ ያሉ የእንስሳት ተዋጽኦ አቅርቦትን ይበልጥ ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋፆ እንደሚኖራቸውም ተገልጿል።

ከነዚህም ውስጥ 56 የቁም እንሰሳት የገበያ ስፍራዎች ሲሆኑ 52ቱ የአትክልትና ፍራፍሬ መሸጫዎች ናቸው ተብሏል፡፡

አዳዲስ የግብይት ቦታዎቹ በሁሉም ክፍለ ከተሞች አገልሎት መስጠት የጀመሩ ሲሆን መሸጫ ስፍራዎቹ ከአርሶ አደሩ በቀጥታ ተቀብለዉ ለሸማቹ ህብረተሰብ ምርት በቀጥታ ከአርሶ አደሩ ከማቅረባቸው በተጨማሪ ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ እንዲችሉ የተዘጋጁ አማራጭ የገበያ ስፍራዎች መሆናቸዉ ተነግሯል፡፡

በረድኤት ገበየሁ
ነሃሴ 28 ቀን 2013 ዓ.ም
ነገ ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም "የኢትዮጵያዊነት ቀን" አስመልክቶ  በመስቀል አደባባይ በሚካሄደው ዝግጅት ምክንያት  ከጠዋቱ 11:30 ጀምሮ ፕሮግራሙ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች:-

- ከመገናኛ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ አሽከርካሪዎች ኡራኤል ቤ/ክ
- ከቦሌ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ ኦሎምፒያ
- ከሸራተን ሆቴል ወደ መስቀል አደባባይ ሀራምቤ ትራፊክ መብራት
- ከሜክሲኮ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ ለገሃር ትራፊክ መብራት ላይ
- ከአራት ኪሎ ወደ መስቀል አደባባይ  ብሄራዊ ቤተ መንግስት
- ከተክለሀይማኖት  ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ አሽከርካሪዎች  ብሔራዊ ቲያትር
- ከቸርቸል ጎዳና ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ አሽከርካሪዎች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት
- ከጎተራ  ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ ጥላሁን አደባባይ ዝግ የሚሆን ሲሆን
ለከባድ ተሽከርካሪ ከጎተራ ወደ መስቀልአደባባይ ለሚመጡ መንገዱ አጎና ሲኒማ ላይ የሚዘጋ ይሆናል።

ከዚህም በተጨማሪ በነዚህ መንገዶች ላይ ተሽከርካሪን ለአጭርም ሆነ ለረጅም ሰዓት አቁሞ መሄድ ተከልክሏል።

ስለሆነም አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክት አስተላልፏል።
                                                 
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል ድረ ገጻችንን https://ethiofm107.com/ ይጎብኙ::
ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም
የሱዳን መንግስት ጦር መምዘዙን አቁሞ ከኢትጵያ ጋር በሰላማዊ መንገድ እንዲደራደር የአገሪቱ ምሁራን ጠየቁ፡፡


ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር ቆይታ ያደረጉት ሱዳዉያን ምሁራን፣ ኢትዮጵያና ሱዳን በቀላሉ የሚለያዩ ባለመሆናቸዉ መንግስታቸዉ ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመጣ ግፊት እንደሚያደርጉም አስታዉቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ እና የሱዳን ዉጥረት መነሻዉ ምን ይሆን? የሱዳን ህዝብ ፍላጎትስ ምንድነዉ? ስንል ከሱዳናዉያን ምሁራን ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡


ዶክተር ኦማር ላሚን አህመድ በሱዳን ዩንቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ ናቸዉ፡፡

እርሳቸዉ ዘመናትን ስላስቆጠረዉ ስለ ኢትዮጵያና ሱዳን ቤተሰባዊ ግንኙነት አንስተዉ የድንበር ዉዝግቡ የሁለቱ አገራት ፍላጎት ሳይሆን የቅኝ ዘመን ርዝራዦች ፍላጎትና ሃሳብ ነዉ ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ዉዝግባቸዉን በአፈ ሙዝ ሳይሆን የሁለቱን አገራት ህዝብ በማቀራረብ የዲፕሎማሲ ስራን በመስራት ነዉ የሚሉት ሱዳናዊ ምሁር፤ ለዚህም የሁለቱ አገራት መሪዎች የህዝቡን ፍላጎት ማዳመጥ አለባቸዉ ነዉ ያሉት፡፡


ከድንበር ዉዝግቡ ባለፈ ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያልተገባ ጥያቄ እንደምተነሳ ይታወቃል፡፡

ለመሆኑ ግድቡ የሁለቱ አገራት መጨቃጨቂያ መሆን ነበረበት ስንል ዶክተር ኦማር ላሚንን የጠየቅን ሲሆን፤ ሁለቱም አገራት በቂ ዉሃ አላቸዉ፤ ግድቡ የልማት እንጅ የልዩነት አጀንዳ ሊሆን አይገባም ብለዋል፡፡

ሌላኛዉ የሱዳን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲ ተመራማሪዉ ፕሮፌሰር አብዱ ኦስማን በበኩላቸዉ፣ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ጦር እንዲማዘዙ እንቅልፋቸዉን አጥተዉ ትርፋቸዉን ለማጋበስ የሚጠባበቁ ሃይሎች ስለመኖራቸዉ አንስተዉ፤ በዚህም ሁለቱ አገራት የእነዚህ መጠቀሚ መሳሪያ እንዳይሆኑ ብልህ ሊሆኑ ይገባል ነዉ ያሉት፡፡


መንግስት ለመንግስት ከሚደረገዉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተጨማሪ፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር እንደሚገባ ያሳሰቡት ሱዳናዊ ፕሮፌሰር አብዶ ኦማር፣ ለዚህ ደግሞ የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ሱዳን በቀላሉ የሚለያዩ አይደሉም የሚሉት እነዚህ የሱዳን ዩንቨርሲቲ ምሁራን፤ ይልቁንም ሁለቱ አገራት ጦር እንዲማዘዙ አሰፍስፈዉ የሚጠባበቁ ሃይሎችን ምኞት በጋራ ማምከን ይገባል ብለዋል፡፡


የህዳሴ ግድቡም ሆነ የድንበር ጥያቄዉ በሃይል የሚመለስ አይደለም ያሉት ምሁራኑ፣ የሱዳን ህዝብ ከኢዮትጵያ ወገኑ ጋር ወደ ግጭት መግባት አይፈልግም፤ ስለዚህ የሱዳን ባለስልጣናት በሌሎች ሃይሎች መገፋታቸዉን ትተዉ የህዝባቸዉን ስሜት እንዲያዳምጡ ግፊት እንደሚያደርጉም አስታዉቀዋል፡፡

በአባቱ መረቀ
ጳጉሜ 03 ቀን 2013 ዓ.ም
ግብጽ ከቱርክ ጋር ያላትን የሻከረ ግንኙነት ለማሻሻል ያልተቆጠበ ጥረት እያደረገች ነዉ፡፡

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በትናንትናዉ እለት እንዳስታወቁት ሀገራቸው ከቱርክ ጋር የነበራትን ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ የምትፈልግ መሆኗን እና ከህዳሴ ግድቡ ጋር ተያይዞም ከኢትዮጵያ ጋር በትጥቅ ግጭት ውስጥ ለመግባት ፍላጎት እንደሌላት ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሜህ ሽክሪ ከብሉምበርግ ቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ግብፅ “ከአንካራ ጋር መደበኛ ግንኙነቷን ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ” እና ፈጣን እርምጃዎችን ለማግኘት ጓጉታ የነበረ ቢሆንም ተጨማሪ ሥራ መሰራት አለበት ብለዋል።

በቱርክ ዋና ከተማ እየተካሄደ ባለው የሁለተኛ ዙር ውይይቶች “አሁንም ውጤቱን መገምገም አለብን” ብለዋል።
ግብፅ ያልተፈቱ ጉዳዮች እንዲፈቱ ለተጨማሪ እድገት በሩ ክፍት ይሆናል ብለዋል ሽክሪ።
ቱርክ ለሙስሊም ወንድማማቾች ህብርት ድጋፍ ታደረጋለች በሚል ቅራኒ ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወሳል፡፡


ይባስ ብሎም ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሙርሲ በ 2013 በወታደራዊ ሀይል ከሥልጣን መውረድ ጋር ተያይዞም ግንኙነታቸው ተዳክሟል።

ቱርክ ትሪፖሊ ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኘውን የሊቢያ መንግሥት ስትደግፍ ፣ ግብፅ ደግሞ በምሥራቃዊው ኃያል ካሊፋ ሃፍታር የሚመራውን ትደግፋለች።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኅዳር ወር መመረጣቸውን ተከትሎ ሁለቱ አገራት በክልሉ ውስጥ ያለውን የሀይል ሚዛን ለመከፋፈል እየተገፋፉ ነው፡፡


የዓባይ ግድብን በተመለከተም ከኢትዮጵያ ጋር በተፈጠረው ውጥረት ላይ ግብፅ ለድርድር ቁርጠኛ መሆኗን እና ከማንኛውም ዓይነት ወታደራዊ ግጭት ለመራቅ ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።
የግብፅ ባለሥልጣናት ቀደም ሲል ሁሉም አማራጮች ክፍት እንደሆኑ ተናግረው ነበር ሲል ሚዲል ኢስት ሞኒተር ዘግቧል።

እንዲሁም የግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲ የውሃ ድርሻ ለሀገራቸው የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ መሆኑን እና ሊታለፍ የማይችል “ቀይ መስመር” ነው ሲሉ መደመጣቸውን አናዶሉ ዘግቧል።

በያይኔአበባ ሻምበል
ጳጉሜ 04 ቀን 2013 ዓ.ም
ሱዳን ከተሳሳተው መንገዷ እንድትመለስ አሁንም ኢትዮጵያ ትጠይቃለች ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታወቁ

ሱዳን በተጠናቀቀው አመት የኢትዮጵያን ድንበር አልፋ የተለያዩ ትንኮሳዎችን ማድረጓን ያስታወሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ አሁንም ሱዳን ከተሳሳተው መንገዷ እንድትመለስ ኢትዮጵያ ትጠይቃለች ብለዋል ።

የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ውዝግብ በትዕግስት መከታተሉንም አንስተዋል።

በተጠናቀቀው 2013 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከገጠሟት ችግሮች መካከል የሱዳን ድንበር ውጥረት አንዱ መሆኑን ያስታወቁት ቃልአቀባዩ ፣ችግሩ ባይፈታም ኢትዮጵያ ግን ጉዳዩን በበሳል ዲፕሎማሲ እይታ ተከታተለዋለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ሱዳን እየሄደችበት ያለው መንገድ የተሳሳተና የማይጠቅማት በመሆኑ ከድርጊቷ ብትቆጠብ መልካም እንደሆነ ተናግዋል፡፡

ከእንደዚህ አይነት ድርጊት በዘለለ የአፍካውያን ኩራት በሆነው አየር መንገዳችን ስም ለማጠልሸት የሚደረገውንም ድርጊት ኮንነዋል፡፡

በአባቱ መረቀ
ጳጉሜ 04 ቀን 2013 ዓ.ም
ቡሩንዲ ከኢትዮጵያ ግድብ ግንባታ ይልቅ ለግብፃውያን የመኖር መብት ቀዳሚ ነው አለች

ቡሩንዲ የግብፅን የመኖር መብት ከኢትዮጵያ የማልማት መብት ከማግኘት በፊት ሊቀድም ይገባል ብሎ እንደሚያምን የሀገሪቱ ከፍተኛ ዲፕሎማት አስታወቁ።

ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚ ዕድገቷ እና ለኃይል አቅርቦት ወሳኝ ነው ብላ በምትከራከረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ነው አስተያየት የሰጡት።

ፕሮጀክቱ በግብፅ እና በሱዳን የውሃ እጥረት እና ደህንነት ላይ ስጋት ፈጥሯል ፣ እነሱም በአባይ ወንዝ ውሃ ላይ ጥገኛ ናቸው ብለዋል አናዶሉ እንደዘገበው።

በመዲናይቱ ካይሮ ከግብፁ አቻቸው ሳሜህ ሹክሪ ጋር በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የብሩንዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልበርት ሺንሺሮ እንደተናገሩት የውሃ ኃይል ፕሮጀክቱ በጣም ስሱ ጉዳይ ቢሆንም የውሃ ተደራሽነት የግብፃውያን “የሕይወት ወይም የሞት” ጉዳይ ነው።

“የመኖር መብት ሁል ጊዜ ከእድገት መብት በፊት መቅደም አለበት ምክንያቱም የሕይወት መብት ከሌለ የልማት መብት ሊከበር አይችልም እዚህ ያለው ምርጫ ግልፅ ነው ”ብለዋል ሺንጊሮ።

ከፍተኛው የቡሩንዲ ዲፕሎማት ጉዳዩን ለመፍታት ወታደራዊ አማራጭን በማስወገድ የግድቡን ውዝግብ በድርድር ፣ በትብብር እና በሕጋዊ ስምምነቶች ለሁሉም ወገኖች በሚስማማ መልኩ መፍታት እንዳለበት አስምሮበታል።

ሺንጊሮ “በዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እና በመልካም ሥራዎች ኃይል እናምናለን” ብለዋል።

በያይኔአበባ ሻምበል
ጳጉሜ 04 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ በህገ ወጥ እርድ ምክንያት በአመት 1.2 ቢሊዮን ብር ታጣለች

አዲስ አበባ በአመት በህገ ወጥ እርድ ምክንያት በአመት 1.2 ቢሊዮን ብር እንደምታጣ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የኢንፎርሜሽንና ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አታክልቲ ገብረሚካኤል ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

ለመጪውን የዘመን መለወጫ በአል የስጋ ውጤቶችን በጥራትና በተመጣጠነ ዋጋ ለማድረስ ዝግጅት መደረጉን ነግረውናል፡፡

በመሆኑም ድርጅቱ ለ2014 አዲስ ዓመት በአል ከ2 ሺህ 500 በላይ የዳልጋ ከብት እና ከ1 ሺ 500 በላይ በግና ፍየሎችን ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ድርጅቱ ለአንድ በሬ የእርድ አገልግሎት 867 ብር፣ ለፍየል እና ለበግ ደግሞ 120 ብር በማከፈል ቤት ድረስ ለማቅረብ እንደሚጠየቅ እና ለዚህም ከ40 በላይ ዘመናዊ የቄራ ተሽከርካሪዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

ለበዓሉ ህብረተሰቡ ከንጋቱ 11 ሰአት ጀምሮ ወደ ድርጅቱ በሬ፣ በግና ፍየል በማምጣት ከ30 እስከ 40 ደቂቃ ባለ ጊዜ አሳርዶ መውሰድ ይችላል ብለዋል።

ለቅርጫ የተዘጋጁም ካሉ በሬውን አምጥተው በማስመርመር የእርድ አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ ነው ያሉት።

ከእርድ በኋላ ድርጅቱ የሚፈለግበት ቦታ ድረስ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚያቀርብም ገልጸዋል።

በዋናው መስሪያ ቤት እና አቃቂ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በሚገኙ ሱቆች በኪሎ የበግ ስጋ 210 ብር እንዲሁም የበሬ ስጋ በ285 ብር መግዛት እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ቄራዎች ደርጅት በቀን በአማካይ 3 ሺህ 500 ሰንጋዎችን በማረድ ለተጠቃሚዎች የማቅረብ አቅም አለው ሲሉ ሃላፊው ነግውናል።

በረድኤት ገበየሁ
ጳጉሜ 04 ቀን 2013 ዓ.ም
ቮዳፎን ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ከአዉሮፓ ኮሚሽን ፈቃድ አገኘ፡፡

ኮሚሽኑ ቮዳፎን ከሳፋሪ ኮም ጋር በሚኖረዉ ሽርክና ያልተገባ የንግድ ዉድድር ሊፈጠር ይችላል በሚል ምርመራ ሲያደረግ መቆየቱን የኢስት አፍሪካን ሪፖርት ያሳያል፡፡

ይሁንና ኮሚሽኑ ያደረገዉ የምርመራ ዉጤት ጥምረቱ ፍትሃዊ ዉድድር ለማድረግ ምንም የሚገድብ ነገር እንደሌለ አመላክቷል፡፡
በዚህም ቮዳፎን ሳፋሪ ኮም በሚመራዉና የእንግሊዝ የልማትና ፋይናንስ ኤጀንሲ ሲዲሲ ግሩፕ እና የጃፓኑ ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን በሚገኙበት ጥምረት እንዲቀላቀል ፈቃድ ማግኘቱ ታዉቋል፡፡

ከአዉሮፓ ህብረት ጋር የሚሰሩ ድርጅቶች ጥምረት በሚፈጥሩበት ወቅት በመካከላቸዉ ምንም አይነት ያልተገባ የንግድ ዉድድር እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸዉ ህብረቱ እንደሚያዝዝ ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡


“የግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ” ድርጅት አንዱ የሆነው የጃፓኑ ሱሚቶሞ፣ በቴሌኮም ኦፕሬሽን ፈቃድ ጨረታውን ማሸነፉ የሚታወቅ ሲሆን በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ ከሁለት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው መግለጹ ይታወሳል፡፡


ምንጭ፡- Mobaile Europe.com

በሙሉቀን አሰፋ
ጳጉሜ 04 ቀን 2013 ዓ.ም
በከተማችን አዲስ አበባ 51 ህገ-ወጥ እርድ ተይዞ በግብረ-ሃይሉ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ተገለጸ፡፡

በአራት ክፍለ ከተሞች በተለዩ ቦታዎች በተደረገ አሰሳ 51 ህገ-ወጥ እርድ ሲያከናኑ መያዛቸውን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታዉቋል፡፡

በከተማ ደረጃ ገበያን ለማረጋጋት ከሳምንታት በፊት የተቋቋመው ግብረ-ሀይል በአራት ክፍለ ከተሞች ማለትም ቦሌ፤ ንፍስ ስልክ ላፍቶ፤ ኮልፌ ቀራንዮ ና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች ውስጥ ህገ-ወጥ እርድ የሚከናወንባቸው ቦታዎችን ለይቶ ባደረገው ክትትል መሰረት በዛሬው እለት 51 በህገወጥ መንገድ እርድ ሲያከናን እጅ ከፍንጅ በመያዝ እርምጃ መውሰዱን ቢሮው አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በእነዚህ አካባቢዎች 229 በግና ፍየሉች በህገ-ወጥ መንገድ ሊታረዱ ሲሉ መያዛቸውን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ሚዬሶ ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቀዋል፡፡

በረድኤት ገበየሁ

ጳጉሜ 04 ቀን 2013 ዓ.ም
በህገ ወጥ መንገድ የህክምና ፍቃድ ሳይኖረው የኮቪድ -19 ህክምና ማዕከል በመክፈት አገልግሎት እየሰጠ የነበረ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለፀ።

በአዲስ አበባ ከተማ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ጃፓን ኤምባሲ አካባቢ የህክምና ፍቃድ ሳይኖረው ክሊኒክ በመክፈት የኮሮና ቫይረስ ህክምና ለተለያዩ ሰዎች ሲሰጥ ነው፡፡

የአየር መንገድ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ከቦሌ ክፍለ ከተማ የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ባለሙያዎች ጋር በሰሩት ጥናት ፍቃድ ሳይኖረው ክሊኒክ በመክፈት የኮሮና ቫይረስ ህክምና አገልግሎት ሲሰጥ የነበረውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት እንደሆነ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገልጿል።

በክፍለ ከተማው የወረዳ 2 የምግብ እና መድሀኒት ቁጥጥር ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጦና እንደተናገሩት ግለሰቡ ምንም አይነት የህክምና ፍቃድ ሳይኖረው በከፈተው የህክምና ማዕከል የውጪ ሃገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች ጭምር ህክምና ፈልገው መምጣታቸውን ገልፀዋል፡፡

በወቅቱ በርካታ መድሀኒቶች የተገኙ ሲሆን ለምን አይነት ህመም የሚያገለግሉ መድሃኒቶች እንደሆኑም በማጣራት ላይ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ጳጉሜ 05 ቀን 2013 ዓ.ም