Ethio Fm 107.8
19.6K subscribers
6.49K photos
16 videos
4 files
2.28K links
በፍቅር ላይ የተመሰረተ ኢትዮጵያዊነት እንዳይላላ ከልቡ የሚተጋ፣ መከባበርና መተሳሰብን የሚያስቀድም ኤፍ ኤም ሬዲዮ ነው!!!
Download Telegram
የዛሬ የሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም የከሰዓት እና የምሽት ፕሮግራሞቻችን
የሐማስ ከፍተኛ መሪ ኢራን ውስጥ ተገደሉ ።
እስማኤል ሐኒዬህ የሐማስ ፖለቲካል ጽ/ቤት መሪ ነበሩ ። ከፍተኛ መሪው ኢራን ውስጥ ከአየር በተሰነዘረ ጥቃት ተገድለዋል ሲል የኢራን አብዮታዊ ዘብ ዛሬ ዐሳውቋል ።
ለግድያው ኃላፊነት ወዲያው የወሰደ አካል ግን የለም ። ሆኖም እስራኤል እስማኤልን ለመግደል በተደጋጋሚ ስትዝት ነበር ። 1,200 እሥራኤላውያን ለተገደሉበት እና 250 ሰዎች ለታገቱበት የመስከረም 26ቱ የሐማስ ድንገተኛ ጥቃት እሥራኤል የሐማሱን መሪ ሐኒዬህ ተጠያቂ አድርጋ ቆይታለች ።
ስለ እስማኤል ሐኒዬህ ግድያ ግን ከእሥራኤል በኩል ወዲያው የተሰማ ነገር የለም ።
እስራኤል፤ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ኅብረት፣ ብሪታንያና ተከታዮቻቸዉ በአሸባሪነት የፈረጁት የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ ግድያውን፦ «ጽዮናዊ ጥቃት» ሲል እሥራኤልን ተጠያቂ አድርጓል ።
ኢራን በበኩሏ ስለ ሐማሱ ከፍተኛ መሪ መገደል ይፋ ከማድረግ ውጪ ዝርዝር መረጃዎችን አለመስጠቷን የፈረንሣሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) ዘግቧል ።
ሆኖም የኢራን ጠቅላይ መሪ ዓያቶላህ ዓሊ ካህሜኒ እሥራኤል ላይ የበቀል ያሉት «እጅግ ብርቱ ቅጣት» እንደሚከተል ዝተዋል ።
እስማኤል ሐኒዬህ ቴህራን ከተማ የተገኙት የኢራን አዲሱ ፕሬዚደንት ማሱድ ፔዜሽኪን በዓለ ሲመት ላይ ለመታደም ነበር ። አዲሱ የኢራን ፕሬዚደንት እስማኤል ሐኒዬህን በተመለከተ፦ «ትናንት እጁን ከፍ አድርጌ ነበር ዛሬ ደግሞ ልቀብረው ነው» ሲሉ የቀድሞው ትዊተር ኤክስ ማኅበራዊ መገናኛ አውታር ላይ ጽፈዋል ።
ከሦስት ወራት በፊትም፦ እሥራኤል ሰሜን ጋዛ ሠርጥ ውስጥ በወሰደችው የአየር ጥቃት የሐማስ ኃላፊ የእስማኤል ሐኒዬህ ሦስት ልጆች እና አራት የልጅ ልጆች መገደላቸውን የሐማስ ታጣቂ ቡድኑ ገልጦ ነበር ። ሌሎች ተጨማሪ ዐሥር ልጆች እንዳላቸው የሚነገርላቸው የሐማስ መሪ ስለ ቤተሰቦቻቸው መርዶ ሲነገራቸው የሚያሳይ የቪዲዮ ምስልም በወቅቱ ታይቷል ። ከወራት በፊት በተሰነዘረው በዚሁ የአየር ላይ ጥቃት የእሥራኤል ጦር ተሽከርካሪ ውስጥ እንዳሉ የተገደሉት የሐማስ ወታደራዊ አባላት ናቸው ተብሎ ነበር ።
የእስማኤል ሐኒዬህ የአስክሬን ሽኝት ሐሙስ ኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ እንደሚከናወን ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዘግቧል ።
ከዚያም የጸሎት ሥርዓት እና ቀብራቸው በስደት ይኖሩባት በነበረችው የኳታር ዋና ከተማ ዶሐ ውስጥ እንደፈጸም የዜና ምንጩ አክሎ ዘግቧል ።

ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
የሱዳኑ አል-ቡርሃን ከድሮን የግድያ ሙከራ ጥቃት ማምለጣቸዉ ተነገረ

የሱዳኑ ጦር አዛዥ አብዱልፈታህ አል ቡርሃን በምስራቅ ሱዳን በጌቢት በተካሄደው ወታደራዊ የምረቃ ስነስርዓት ላይ ከሰው አልባ አውሮፕላን / ድሮን የግድያ ሙከራ ተርፈዋል ተብሏል።

ጥቃቱ በቀይ ባህር ግዛት እንደተሞከረና ተማሪዎች እና አንድ መኮንን ጨምሮ አምስት ሰዎች ተገድለዋል፡፡

ጌቢት የበርካታ የመንግስት ሚኒስቴሮችና የውጭ ኤምባሲዎች መኖሪያ ስትሆን ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ እንደ አማራጭ ዋና ከተማ ሆና በማገልገል ላይ ያለች ከተማ ናት።

የሱዳን ጦር ቃል አቀባይ ከጣላት የተላኩ ድሮኖቹን መቶ መጣሉንም አስታዉቋል፡፡

አሁን ላይ አል-ቡርሃን በሰላም ወደ ፖርት ሱዳን መመለሳቸዉም ተነግሯል።

ልዑል ወልዴ

ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
አምስተኛው ዙር የኢትዮጵያ የሥነ-ሕዝብ እና ጤና ቆጠራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት አስታውቋል።

በየአምስት አመቱ የሚከናወነው የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብና ጤና ዳሰሳ ጥናት (EDHS) መካሄድ ከነበረበት ጊዜ በኮቪድ እና በሌሎች ልዩ ልዩ ምክንያቶች ሳይካሄድ በ 3 ዓመታት መጓተቱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ሳፊ ገመዳ እንደተናገሩት ጥናቱ ከ 2016-2018 ዓም በሚቆየው የ ስታትስቲክስ ልማት ፕሮግራም ትግበራ ወቅት እንዲካሄድ በእቅድ ተይዞ ካለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 20/2016 ዓም ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል።

ከ 22 ዓመታት በኋላ የሚካሄደው ሁለተኛው ዙር የግብርና ምርቶች ቆጠራ በናሙና የተመረጡ አርሶ አደሮች የግብርና ምርት አመራረትና የግብዓት አጠቃቀማቸውን የሚመለከትበት ነው።

ከ 40ሺ በላይ ሰዎች በቆጠራው ይሳተፋሉ ተብሏል።

ሁሉንም ጥናቶች በ2017 ዓ.ም ለመጀመር ታቅዶ እንቅስቃሴ መጀመሩን እና በ 2018 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እቅድ መያዙን ሀላፊው ተናግረዋል።

እስካሁን ለሦስት ጊዜያት ያክል የህዝብ እና ቤት ቆጠራ ያካሄደችው ኢትዮጵያ አራተኛው የኢትዮጵያ የህዝብ እና ቤት ቆጠራ መካሄድ ከነበረበት 2010 ዓም ሳይካሄድ ለስድስት ጊዜያት ያክል መራዘሙ ይታወሳል።

ለመዘግየቱ መንስኤ በኢትዮጵያ የተረጋጋ ሰላም እና ያልተገደበ እንቅስቃሴ አለመኖር እንዲሁም በአዲስ አበባ እና በሌሎችም የሃገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ የዴሞግራፊ ለውጦች መሆናቸው የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በኸር ሻሌ እንደምክንያት ጠቅሰዋል።

ለ 3 ዓመታት የሚቆየው የስታትስቲክስ ልማት ፕሮግራም ትግበራ ተቋሙ የልህቀት ማዕከል እንዲሆን ታስቦ እየተሰራ መሆኑንም ተነግሯል።

ለአለም አሰፋ

ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
የወባ በሽታ በኦሮሚያ ክልል በወረርሺኝ መልክ ህክምናዉ እየተሰጠ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በክልሉ ከ2014 ጀምሮ ሪፖርት የሚደረገዉ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በወባ እየተጠቁ ያሉ ወረዳዎች ቁጥር እንዲሁም ሪፖርት የሚያደርጉት የህመምተኞች ቁጥርም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን የሚገልጹት በክልሉ ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና ቁጥጥር እና አደጋ ምላሽ ሰጪ እንዲሁም የላቦራቶሪ አገልግሎት አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ ከበበዉ ናቸዉ፡፡

ቁጥሩ ከፍተኛ በመሆኑ የተነሳም በወረርሺኝ መልክ ህክምናዉ እየተሰጠ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ለወባ በሽታ መስፋፋት የአየር ሁኔታ ለዉጥ መኖሩ የመጀመሪያዉ ምክንያት መሆኑን የአለም ጤና ድርጅት መግለጹን የሚያነሱት ዶ/ር ተስፋዬ፤ ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ የተለያየ ክፍል ያለዉ የጸጥታ ሁኔታ ሌላዉ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለወባ በሽታ መከላከል የሚሰጥ ድጋፍ ደግሞ አነስተኛ መሆኑ ሌላዉ ምክንያት ነዉ ሲሉ ዶ/ር ተስፋዬ ነግረዉናል፡፡

የታካሚዎች ቁጥር ሲጨምር መድሃኒት ፍላጎትም በዛዉ ልክ ይጨምራል ያሉት ሃላፊዉ፤በዚህም የመድሃኒት እጥረት እንዳይኖር እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡

የመከላከል ስራዉ መቀጠሉን የሚያነሱት ሃላፊዉ ፤ በሶስት ዞኖች ላይ ኢሉባቦር ፣ ምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች ላይ የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑን እና ስራዉ ወደመጠናቀቅ መድረሱንም ነዉ የሚያነሱት፡፡

ችግሩ በጣም ብዙ ወረዳዎች ላይ ግን በወረርሺኝ መልክ መከሰቱንም ዶ/ር ተስፋዬ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡


እስከዳር ግርማ

ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
በደሴ ከተማ ከባድ ዝናብን ተከትሎ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት ተከስቷል ተባለ፡፡

በደሴ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ጀሜ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት መከሰቱን የደሴ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡

በደረሰው የመሬት መንሸራተት አንድ የአስፓልት መንገድ ፣ የጠጠር መንገድ እና በአካባቢው የነበሩ ቤቶች የመሰንጠቅ አደጋ እንዳጋጠማቸው የደሴ ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮምኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ ነስረዲን ሀይሌ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

አንድ መስጅድ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ የመፍረስ አደጋ እንዳጋጠመው አንስተዋል፡፡

በአካባቢው በተፈጠረው የመሬት መንሸራተት በሰው ህይወት ላይ የደረሰ አደጋ አለመኖሩንም ገልፀዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ እና ክፍለ ከተማው በጋራ በመሆን ኮሚቴ በማዋቀር ቦታው ላይ ሄደው ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ማህበረሰቦች እና በተለይ ስጋት አለባቸው ተብለው የተለዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ሰዎች ካምፕ ተዘጋጅቶ እዛ አንዲቆዩ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

ችግሩ ሲታይም ሰፋ ያለ እንደሚመስል እና መስመሩ እንዳይዘጋም ተለዋጭ መንገድ ስላለ አሽከርካሪዎች ያን መንገድ እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በከተማው ስጋት አለባቸው ተብለው በተነገሩ አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችም በአካባቢው መኖራቸውን እንዲያቆሙ የሚል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ሐመረ ፍሬው

ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
በ2016 በጀት ዓመት በትራፊክ አደጋ የ383 ዜጎች ህይወት ማለፉ ተነገረ

በአዲስ አበባ ከተማ የተሳለጠ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር እና የትራፊክ አደጋን ለመከላከል የተለያዩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መከናወናቸውን የገለጹት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ የትራፊክ ሞያ እና ህዝብ ግንዛቤ ዲቪዝን ሀላፊ ኢንስፔክተር ሰለሞን አዳነ ናቸው፡፡

በ2015 በጀት ዓመት 393 የሞት አደጋ ተከስቶ እንደነበር ያስታወሱ ሲሆን፤ በዘንድሮ 2016 በጀት ዓመት በትራፊክ አደጋ ምክንያት የ383 ዜጎች ህወታቸው ማለፉ ኢንስፔክተር ሰለሞን ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

በ2016 ዓ.ም 2 ሺህ 92 ከባድ አደጋዎች የደረሱ ሲሆን፤ 1ሺህ 9 መቶ 9 ከባድ አደጋዎች በ2015 በጀት አመት መድረሱን እና ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከባድ አደጋዎች መጨመራቸው ተጠቁሟል፡፡

ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች፣ በትምህርት ቤቶች እና የጥንቃቄ መልክቶች የያዙ በራሪ ወረቀቶችን በመጠቀም ለትራፊክ አደጋ የሚያጋልጡ ምክንያቶችን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች መከናወናቸውን እና ደንብ የማስከበር ስራ ሰርተናል ብለዋል፡፡

ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋርም ፣ የትራፊክ ፍሰቱን የተሳለጠ አና ምቹ ለማድረግ የክረም እና የበጋ በጎ ፈቃደኞችን እንዲሁም የተማሪ ትራፊኮችን በመመልመል የማስተባበር የማስተላለፍ እና የስነ ምግባር ስልጠናዎችን በመስጠት ወደ ስራ የማስገባት ሂደት ተከናውኗል ያሉት ሀላፊ ኢንስፔክተር ሰለሞን አዳነ አሽከርካሪዎች እንዲሁም እግረኞች የትራፊክ ደንብን አክብረው እንዲንቀሳቀሱም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

እሌኒ ግዛቸው

ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ዶላር ጨምሯል በሚል የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መዉሰዱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በ13 የንግድ ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መዉሰዱን ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታወቋል፡፡

ቢሮዉ ባደረገዉ የክትትል ስራ በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ 11 እንዲሁም በየካ ክ/ከ 2 በድምሩ 13 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃመዉሰዱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ሰውነት አየለ ለጣቢያችን ተናግረዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ በምርቶች ላይ ጭማሪ ባሳዩ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መዉሰዱን ነግረዉናል፡፡

ንግድ ቢሮዉ በከተማዉ በሚገኙ የንግድ ድርጅቶች ላይ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ና ህብረተሰቡ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ድርጅቶችን ሲመለከት 8588 የነፃ መስመር ጥቆማ እንዲያደርስ አሳስበዋል ፡፡

አቤል እስጢፋኖስ

ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
የነገ የሐምሌ 25 ቀን 2016 ዓ.ም የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8  ፕሮግራሞቻችን