DW Amharic
43.2K subscribers
3.27K photos
758 videos
69 files
13.4K links
ይህ የዶይቼ ቬለ ይፋዊ የቴሌግራም ገፅ ነው። ትኩስ ዜና፣ በአበይት ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ትንታኔ ያቀርባል።
Download Telegram
የሱዳን ተቃዋሚዎች እና ሀገሪቱን የሚገዛው ወታደራዊ ምክር ቤት ሥልጣን የሚጋሩበትን ሰነድ ዛሬ ጠዋት ፈረሙ። ሰነዱ በሱዳን ዋና ከተማ በካርቱም የተፈረመው ትናንት ለሊት በጥድፊያ ከተካሄደ ንግግር በኋላ ነበር። ስምምነቱ መፈረሙን ዛሬ ጠዋት ያበሰሩት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ኃላፊ ጀነራል ሞሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ ፊርማው በመሳካቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
«ዛሬ ጠዋት ለህዝባችን መልካም ምኞቴን ስገልጽ በጣም ደስ እያለኝ ነው። ወታደራዊው ምክር ቤት እና የነጻነት እና የለውጥ አራማጅ ኃይሎች የመጀመሪያውን ሰነድ መፈራረማቸው በሱዳን ህዝቦች ህይወት ውስጥ እንደ አንድ ታሪካዊ ወቅት የሚቆጠር ነው።»
የሰነዱ መፈረም ወታደሩ የቀድሞውን የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ኧል-በሽርን ባለፈው ሚያዚያ ከሥልጣን ካስወገደ ወዲህ የተወሰደ ትልቅ እርምጃ ተብሏል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ እና አደራዳሪ አምባሳደር መሐሙድ ድሪርም ሁለቱ ወገኖች አወድሰዋል።
«የሱዳን ህዝብ እዚህ ታሪካዊ ወቅት ላይ መድረሱ ታላቅ ጉዳይ ነው። የተለያዩ የሱዳን አካላት አልልም ከዚያ ይልቅ አንድ አካል የጀግናውን የሱዳን ጦር፣የሽግግር ምክር ቤቱን፣ለዴሞክራሲ በመቆም አደባባይ የወጣውን አብዮታዊውን ወጣት፣ምሁራንን እና ፋናወጊዎችን የሚወክል የተባበረ ግንባር ነው የምለው።»
ሆኖም ሁለቱ ወገኖች በጣም አወዛጋቢ በሆነው ሥገ-መንግሥታዊ የሥራ ክፍፍል ላይ የጀመሩትን ድርድር ግን አልጨረሱም። ዛሬ የተፈረመው ሰነድ የሲቪል እና የወታደሩ የጋራ ሉዓላዊ ምክር ቤት እንዲመሰረት ያደርጋል።የጋራው ምክር ቤትም ከሦስት ዓመት በመጠኑ ከፍ ለሚል ጊዜ ሱዳንን ይመራል።በዚህ ጊዜም ለምርጫ ዝግጅት ይደረጋል።11 አባላት የሚኖሩትን ምክር ቤት በመጀመሪያዎቹ 21 ወራት የሚመራው ወታደራዊ መሪ ሲሆን ከዚያ የሚቀጥሉትን 18 ወራት ሲቪል ይመራል።የካቢኔ አባላት የሚሰየሙት በተቃዋሚዎች ነው።ሽግግሩ በተጀመረ በሦስት ወራት ውስጥ ሁለቱ ወገኖች በፓርላማው አመሰራረት ላይ መስማማት ይጠበቅባቸዋል። ከአሁን በኋላም በሉዓላዊው ምክር ቤት የሥልጣን ክፍፍል በካቢኔው እና በፓርላማው አመሰራርት ላይ መስማማትም ይኖርባቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የሱዳን ወታደራዊ ሽግግር ም/ቤት እና የነፃነትና የለውጥ ኃይሎችን ለማቀራረብና የሲቪል መንግስት ለመመስረት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ያስጀመሩት ጥረት ከአፍሪካ ህብረት ጋር በተደረገ የተቀናጀ ጥረት ውጤት ማስገኘቱን አስታውቋል።የድርድሩ ሂደትም የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን መፍታት እንደሚቻል እና ኢትዮጵያም በቀጠናው ሠላምና ጸጥታን ለማስፈን ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጠችበት መሆኑን ገልጿል።
የሲዳማ ህዝብ ከዓመታት በፊት ያቀረበዉ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ዘግይቶም ቢሆን ምላሽ ማግኘት በመጀመሩ መላው የሲዳማ ብሔር እንዲረጋጋ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ጠየቀ።የንቅናቄው ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ደስላኝ ሜሳ፣ «ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ተቀብሎ ህዝበ ውሳኔ ለማድረግ መዘጋጀቱን አረጋግጧል።» ብለዋል።በዚሕም ምክንያት የሲዳማ ሕዝብ የህዝበ ውሳኔውን ሂደት እንዲጠባበቅ ንቅናቄው ጥሪ ማስተላለፉን አቶ ደሳላኝ ለሐዋሳዉ ዘጋቢያችን ለሸዋንግዛዉ ወጋየሁ በሰጡት ቃለ መጠይቅ አመልከተዋል ።ይሁንና አቶ ደሳለኝ እንደሚሉት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ዉሳኔዉ ሊደረግ ከሚገባዉን ቀን አዘግይቷል ብሎ ንቅንቄያቸዉ እንደሚያምን ጠቅሰዉ ለዚሕም ቦርዱ፣ ሕዝቡን ይቅርታ መጠየቅ ይገባዋል ብለዋል።በሲዳማ ዞን የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ( ሲአን ) ፣ የሲዳማ ሀድቾ ዴሞክራሲያዊ ደርጅት ( ሲሀዴድ ) እና የሲዳማ ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ( ሲብዴፓ )፣ የሲዳማ ህዝብ በክልል ለመደራጀት የሚያስችለው የህዝበ ውሳኔ የሚደረግበትን ቀን መንግሥት በአምስት ቀናት ዉስጥ ይፋ እንዲያድርግ ባለፈዉ ሳምንት መጀመሪያ ጠይቀዉ ነበር። የተቀሩት ሁለቱ ፓርቲዎች አስከአሁን ሥለ ጉዳዩ በይፋ ያሉት ነገር የለም።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እና የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሁለቱ ሐገራትና በአካባቢያዊ ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ አስመራ ዉስጥ ተወያዩ።ለኢትዮጵያ መንግስት ቅርበት ያላቸዉ መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ለሁለት ቀናት ጉብኝት አስመራ የገቡት ዛሬ ጠዋት ነዉ።ጠቅላይ ሚንስትሩ አስመራ እስኪገቡ ድረስ ሥለ ጉብኝቱ በይፋ የተዘገበ ነገር አልነበረም።ሁለቱ መሪዎች ያደረጉትና የሚያደርጉት ዉይይትም በሁለቱ ሐገራት ግንኙነትና «በቀጠናዊ» ጉዳዮች ላይ ከመባሉ በስተቀር ዝርዝር ይዘቱ በይፋ አልተዘገበም።ጠቅላይ ሚንስትሩ አስመራን የሚጎበኙት ሲዳማ ጨምሮ አስር የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔሮች ያነሱት የራስ ገዝ አስተዳደር ጥያቄ በተካረረበት፣የትግራይና የአማራ ክልል ገዢ ፓርቲዎች ዉዝግብ በናረበት ወቅት ነዉ።ከአካባቢዉ ሐገራትም የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይላት በኢትዮጵያ ሸምጋይነት የሰላም ዉል በተፈራረሙበትና ሶማሊያ በአሸባሪዎች ጥቃት በርካታ ዜጎችዋ በተገደሉበት ማግስት ነዉ።
ደቡብ ኢትዮጵያ መስተዳድር ርዕሠ ከተማ ሐዋሳ ዉስጥ የሲዳማ ዞን የክልል መስተዳድር ሥልጣን እንዲሰጠዉ በሚጠይቁ ወጣቶችና በፀጥታ አስከባሪዎች መካካል ዛሬ በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ አንድ ሰዉ ተገደለ፣ ሶስት ሰዉ ቆሰለ።ዝርዝሩን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ጠብቁን።
የአቶ ወልደአማኑኤል ዱባለ ልጅ ናቸዉ።አቶ ወልደአማኑኤል ዱባለ ከሌሎች የሲዳማ ፖለቲከኞች ጋር ሆነዉ በ1970 የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን ባጭሩ)ን ሲመሠርቱም ወጣቱ ፖለቲከኛ አብረዋቸዉ ነበሩ።የሲዳማ ፖለቲከኞች ንቅናቄዉን በተመሠረቱ በስድስተኛ ወሩ የትጥቅ ትግል ለመጀመር ወደ ሶማሊያ ሲሰደዱም ከአባታቸዉ ጎን አልተለዩም።አቶ ደጀኔ ወልደአማኑኤል ዱባለ።በ1983 ኢትዮጵያ ዉስጥ የሽግግር መንግሥት ሲመሠረት አሁንም ካባታቸዉ ጋር ከስደት ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ።ብዙም ሳይቆዩ እንደገና ተሰደዱ።ዛሬ ሲዊትዘርላንድ ይኖራሉ።«ትግላችን ለሲዳማ ሕዝብ የራስ ገዝ አስተዳደር እንጂ ለመገንጠል አልነበረም፣ አይደለምም።» ይላሉ። አቶ ደጀኔ እንደሚያምኑት የሲዳማ ዞን የወደፊት እስተዳደርን ለመወሰን የሚሰጠዉ ድምፅ (ሕዝበ ዉሳኔ)ም በሲዳማ ዞን የሚኖሩ የሁሉም ብሔረሰብ ተወላጆች የሚሳተፉበት እንጂ የሲዳማ ሕዝብ ብቻዉን የሚወስንበት መሆን የለበት። የሲዳማ ሕዝብ የወደፊት አስተዳደሩን ለመወሰን ሕዝበ ዉሳኔ መደረግ የነበረበት እስከ ዛሬ ነበር ብለዉ የሚያምኑ የሲዳማ ተወላጆች ግን ዛሬ ከፀጥታ አስከባሪዎችና ከሌሎች ብሔር ተወላጆች ጋር እየተጋጩ ነዉ።አቶ ደጀኔ ግን ሰዎች ከሌላ አካባቢ መጥተዋልና «አያገባችሁም» ሊባሉ አይገባም ባይ ናቸዉ።ዝርዝር ቃለ መጠይቁን ከስርጭታችን ይከታተሉ።
ዋና ዋና ዜናዎቹ፤
የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ለዛሬ ለማወጅ መቀጠሩን ተከትሎ በሐዋሳ እና አካባቢዋ ግጭት ተቃውሞ መከሰቱ እየተነገረ ነው። እስካሁን የአንድ ሰው ሕይወት አልፏል። በርካቶችም ተጎድተዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት በዴሞክራቲክ ኮንጎ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ አጣዳፊ የጤና ስጋት መሆኑን ይፋ አደረገ። እንዲያም ሆኖ የአጎራባች ሃገራት ድንበራቸውን መዝጋት እንደማይገባቸው አሳስቧል።
40 ስደተኞችን ከመስጠም በማዳን ወደ ጣሊያን ደሴት ያለፈቃድ በማስገባት የተከሰሰችው የጀርመን የርዳታ መርከብ ነጂ ካሮላ ራኬተ፤ አዲስ ፕሬዝደንት የመረጡት የአውሮጳ ሃገራት ስደተኞችን ለመቀበል ዝግጁ ይሆናሉ የሚል ተስፋ እንዳላት አመለከተች። ዛሬም ፍርድ ቤት ቀርባለች።
https://p.dw.com/p/3MHKo?maca=amh-RED-Telegram-dwcom
👉🏾 @dwamharicbot
ሐዋሳ፤ ተቃውሞ እና ግጭት መቀስቀሱ
የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ለዛሬ ለማወጅ መቀጠሩን ተከትሎ በሐዋሳ እና አካባቢዋ ግጭት ተቃውሞ መከሰቱ እየተነገረ ነው። የጥያቄ አራማጆች ለአዣንስ ፍራንስ ፕረስ እንደገለፁት የሲዳማ ሽማግሌዎች እና ወጣት የጉዳዩ አቀንቃኞች ዛሬ ጠዋት ሊያካሂዱት ያቀዱት ስብሰባ አካባቢውን በዘጉት በፀጥታ ኃይሎች ተደናቅፏል። ባለሥልጣናት ወደዚያ ባለመምጣታቸው፤ እና ወደ መሰብሰቢያው ስፍራም እንዳያልፉ ያገዷቸው የፀጥታ ኃይሎች ላይ ወጣቶቹ ድንጋይ መወርወራቸውንም ዘገባው አመልክቷል። ሐዋሳ ከተማ ላይ በቁጣ ወደ ጎዳና የወጡት ዜጎች ጎማ በማቃጠል ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረው ግጭትም ቢያንስ የአንድ ሰው ሕይወት መጥፋቱን ሌሎች ደግሞ መጎዳታቸውን የሆስፒታል ምንጮች ለዶይቼ ቬለ «DW» ገልጸዋል። የሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዝናው ሳርሚሶ ጭንቅላቱን በጥይት መመታቱ የተገለፀው ተጎጂ ወደ ሐኪም ቤት ከሄደ በኋላ ሕይወቱን ማጣቱን ለሐዋሳው ዘጋቢያችን ሸዋንግዛው ወጋየሁ ገልጸዋል።
«መጀመሪያ ላይ ትንሽ ጭንቅላቱ ላይ የቆሰለ ሰው ገብቷል። እሱ የመጀመሪያ ርዳታ ሰጥተን ወደ ቤቱ ሄዷል። ከዚያ ቀጥሎም ደግሞ አንድ ሴት ነበረች የመጣችው። ባጠቃላይ አራት ወንድ እና አንድ ሴት ነበር የመጡት። አንደኛው ከአዳሬ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የመጣ ከዚያ ሪፈር የተደረገ ሰው ነበረ ጭንቅላቱ ላይ ነበር ቆስሎ የነበረው፤ ቁስሉ አሁን ሀኪሞች እንዳረጋገጡት በጥይት የተመታ ይመስላል። ከፍተኛ የሆነ ቁስል ነው።። እሱ አዳሬም ወደ እኛ እንደላከ እኛ ጋርም ብዙ ሳይቆይ ሊያርፍ ችሏል።»
ሌሎቹ ተጎጂዎችን በተመለከተ የሚታየው እስካሁን ለከፋ አደጋ የሚያደርስ እንዳልሆነም አክለው ገልጸዋል። ግጭት ተቃውሞው በሐዋሳ ከተማ የተወሰነ እንዳልሆነ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ተገቢውን ምላሽ ካላገኙ ዛሬ ማለትም ሐምሌ 11 ቀን 2011ዓ,ም የሲዳማን ክልልነት ለማወጅ መዘጋጀታቸውን የጉዳዩ ጠያቂዎች ሲያሳስቡ መሰንበታቸው ይታወቃል። ዛሬ ከቀትር በፊት የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ሲአን የሲዳማ ተወላጆች እንዲረጋጉ አሳስቦ ነበር። የሲአን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደስላኝ ሜሳ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄውን ተቀብሎ ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ እንዲቻል ቅድመ ዝግጅት በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ለዶቼ ቨለ «DW» አረጋግጠዋል። እንዲያም ሆኖ እስካሁን አካባቢው ስለመረጋጋቱ የተሰማ ነገር የለም።
ኮንጎ፤ ኢቦላ ዓለም አቀፍ አጣዳፊ ስጋት መሆኑ ይፋ ሆነ
የዓለም የጤና ድርጅት በዴሞክራቲክ ኮንጎ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ አጣዳፊ የጤና ስጋት መሆኑን ይፋ አደረገ። በሽታው መሠረተ ልማት ባልተስፋፋባቸው የኮንጎ ግዛቶች ተወስኖ እንዲቆይ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቢቆይም በዚህ ሳምንት ጎማ በተባለችው ከተማ አንድ በተሐዋሲው መያዙ የተረጋገጠ ታማሚ ሕይወት አልፏል። አጋጣሚው ጎማ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያለባት ከተማ በመሆኗ ወደሌሎች አካባቢዎች በሽታው እንዳይዛመት ስጋት ፈጥሯል። የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የተሐዋሲው መስፋፋት ስጋት ማስከተሉን ይፋ አድርገዋል።
«ሊስፋፋ ይችላል በሚለው ስጋት ምክንያት ኮሚቴው አጣዳፊ ዓለም አቀፍ ስጋት መከሰቱን እንዳውጅ በመከረኝ መሠረት ይፋ አድርጋለሁ። እኔም ምክሩን ተቀብዬ።»
የዓለም የጤና ድርጅት አስቸኳይ የጤና ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር ሮበርት ሽቴፋን በበኩላቸው ምንም እንኳን የተሐዋሲው የመስፋፋት አጋጣሚ አሳሳቢ ቢሆንም ሃገራት ድንበራቸውን እስኪዘጉ ግን ያደርስም ይላሉ።
«የዴሞክራቲክ ኮንጎ ጎተቤት ሃገራትም ሆኑ በሌላ አካባቢ ያሉ ድንበሮች መዘጋት አይኖርባቸውም። ምክንያቱም ይህ በተጎዱት አካባቢዎች ኤኮኖሚ ላይ አስከፊ ተፅዕኖ ይኖረዋል።»
የዓለም የጤና ድርጅት የኢቦላ ተሐዋሲን ለመከላከል አስፈላጊው ክትባትም ሆነ መድኃኒት እንዳለ በማመልክትም፤ ውጤት እንዲገኝ ሁሉም ወገኖች ተባብረው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስቧል። ምዕራብ አፍሪቃ ላይ በሽታው ከፍተኛ ጉዳት ካስተከተለ በኋላ የተቀሰመው ትምህርትም መዘናጋት እና ጊዜ መውሰድ የከፋ ውጤት እንደሚያስከትል ማሳየቱንም አመልክቷል። ከኮንጎ የምትጎራበተው ዩጋንዳ በተለይም ከኮንጎ በተሰደዱ ወገኖች ዘንድ በሽታውን አስመክልቶ ያለውን ቁጥጥር እና ክትትል አጠናክራለች።
ሮም፤ ስደተኞችን በመርዳት የተከሰሰችው የመርከብ ካፒቴን
ስደተኞችን ከመስጠም በማዳን ወደ ጣሊያን ደሴት ያለፈቃድ በማስገባት ክስ የተመሠረተባት የጀርመን የረድኤት አገልግሎት መርከብ ነጂ ካሮላ ራኬተ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረበች። ከሞት ያተረፈቻቸውን 40 ስደተኞችን እንደጫነች ወደ ጣሊያን የባሕር ወደብ እንዳትጠጋ የተደረገውን እገዳ በመጣስ ለወሰደችው ርምጃም በሕገወጥ መንገድ ስደተኞችን ለመርዳት በሞመከር ነው የተከሰሰችው። በወቅቱም የጣሊያን የባሕር ወደብ ጠባቂ ፖሊስን ጀልባ በመግጨትም ተጨማሪ ክስ ቀርቦባታል። በጣሊያን ደቡባዊ ግዛት ሲሲሊ፣ አግሪጌንቶ ከተማ ፍርድ ቤት ዛሬ የቀረበችው የሲዎች መርከብ ካፒቴን ራኬተ፤ ለሦስት ቀናት ከታሰረች በኋላ በአቃቢያነ ሕግ የቀረበባትን ክስ ወደጎን በማድረግ ዳኛው በሰብዓዊነት ድርጊቱን መፈጸሟን ገልጸው እንዳስፈቷት ይታወሳል። ሆኖም ግን አሁንም በአቃቤ ሕግ ምርመራ እየተካሄደባት መሆኑ ተገልጿል። ከፍርድ ቤት ቆይታዋ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጠችው አጭር መግለጫ፤ አዲስ ፕሬዝደንት የመረጡት የአውሮጳ ሃገራት ስደተኞችን ለመቀበል ዝግጁ ይሆናሉ የሚል ተስፋ እንዳላት ተናግራለች።
«አዲስ ፓርላማ የመረጠው የአውሮጳ ኮሚሽን እንዲህ ያሉ ነገሮች እንዳይደገሙ ይከለክላል ብዬ ከልቤ ተስፋ አደርጋለሁ። ከዚህም ሌላ ሁሉም የአውሮጳ ሃገራት ሲቪሎች ከአደጋ የሚያድኗቸውን ሰዎችም ለወደፊት ለመቀበል አብረው ይሠራሉ ብዬም አስባለሁ።»
በዛሬው ዕለትም ፍርድ ቤት ቀርባ ባለፈው ሰኔ 5 ቀን የተፈጠረውን በዝርዝር ለማስረዳት ዕድል በማግኘቷ መደሰቷንም ገልጻለች።
ቶኪዮ፤ ሰው ሰራሽ ምስሎችን የሚያቀናብር ስቱዲዮ ቃጠሎ
ቶኪዮ ጃፓን ውስጥ ሰው ሰራሽ ምስሎችን የሚያቀናብር ስቱዲዮ ላይ በደረሰ ቃጠሎ ከ25 የሚበልጡ ሰዎች መሞታቸውን፤ 36 የሚሆኑ ደግሞ መጎዳታቸውን ባለሥልጣናት አመለከቱ። በተለይ ሴት ተማሪዎች የተካተቱበትን ዝና ያተረፉ ታሪኮች በማቅረቡ በርካታ አድናቂዎች እንዳሉት የተገለጸውን ስቱዲዮ «ትሞትላችሁ!» እያለ በመጮህ ወደ ስፍራው የገባ ሰው እንደለኮሰው ፖሊስ አስታውቋል። ግለሰቡ የረጨው ምንነቱ ያልታወቀ ነገርም እሳቱን አባብሶ ሕንጻውን እንዳጋየው አሶሲየትድ ፕረስ ከቶኪዮ በላከው ዜና አመልክቷል። የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡትም ምናልባት እሳቱ ከመውጫ በሩ አቅራቢያ በመለኮሱ ሠራተኞቹ መውጫ ለማግኘት ሲሞክሩ ጊዜ ወስዶባቸው ለከፋ አደጋ ሳያጋልጣቸው አይቀርም። እሳቱን የለኮሰው የ41 ዓመት ጎልማሳም ተጎድቶ ሃኪም ቤት እንደሚገኝም ፖሊስ አስታውቋል። ምክንያቱ ግን አልተገለፀም።
ኢዝላማባድ፤ የቀድሞው የፓኪስታን ጠ/ሚኒስትር ታሠሩ
የቀድሞው የፓኪስታን ጠ/ሚኒስትር ሻሂድ ካህቃን አባሲ በሙስና ኮሚሽኑ ዛሬ መታሰራቸው ተነገረ። የሀገሪቱ ብሔራዊ የተጠያቂነት ቦርድ ቃል አቀባይ አባሲ የታሰሩት በፀረ ሙስና ኮሚሽኑ ነው ከማለት ውጭ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። የክሱ ቅጂ እንደደረሰው ያመለከተው የፓኪስታን ሙስሊም ሊግ ፓርቲ በበኩሉ በሙስና እና በሙስና ተግባር ተጠርጥረው መታሠራቸውን ማመልከቱ ተዘግቧል። ከጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሻሪፍ ቀጥሎ በጎርጎሪዮሳዊው 2017 ዓ,ም ለወራት ሥልጣኑን ተረክበው የነበረው አባሲ፣ ዛሬ በምሥራቃዊቱ ከተማ ላሆር ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት በተዘጋጁበት ወቅት መያዛቸው ነው የተነገረው። የፓኪስታን ብሔራዊ የተጠያቂነት ቦርድ በእሳቸው እና በናዋዝ ሻሪፍ ላይ ከፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ምርመራ እንዲደረግ ባለፈው ዓመት ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ለሰባት ዓመታት የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሻሪፍም በሙስና ተከሰዋል።