Addis Standard Amharic
17.7K subscribers
4.04K photos
101 videos
3 files
3.24K links
አዲስ ስታንዳርድ በጃኬን አሳታሚ ኃ.የተ.የግ.ማ. ባለቤትነት ስር የሚታተም በኢትዮጵያ የሚገኝ ነፃ እና ገለልተኛ ሚዲያ ነው። አዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የአዲስ ስታንዳርድ እንግሊዝኛ ሕትመት አካል ነው።
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
Download Telegram
ዜና: በኢትዮጵያ የጋዜጠኞች አፈና፣ የዘፈቀደ እስራት እና ስወራ እንዳሳሰበው #ሲፒጄ አስታወቀ

የዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ) የሪፖርተር ጋዜጣ አዘጋጅ ዮናስ አማረ መታፈኑን፣ የሶማሌ ክልል ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ከድር መሐመድ ኢስማኤል በዘፈቀደ መታሰሩን እንዲሁም የአሐዱ ሬዲዮ 94.3 “ቅዳሜ ገበያ” ፕሮግራም አዘጋጁ አብዱልሰመድ መሐመድ የት እንዳለ ሳይታወቅ መቆየቱ ስጋት እንደፈጠረበት አስታወቀ።

የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ትናንት ረቡዕ ነሐሴ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የጋዜጠኞቹን ሁኔታ በዝርዝር አስቀምጧል።

ጉዳዩን አስመልክቶ የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ለፌዴራል እና ለአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ እንዲሁም ለሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያቀረባቸው ጥያቄዎች መልስ አለማግኘታቸውን ጠቁሟል።

የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ሙቶኪ ሙሞ “ኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ላይ አሳሳቢ ሪከርድ” እንዳላት እንዲሁም “ለጋዜጠኞች ከጊዜ ወደ ጊዜ አስቸጋሪ እየሆነች መምጣቷን” ጠቁመው ባለሥልጣናት ጋዜጠኛ ዮናስ አማረ ያለበትን እንዲያጣሩ፣ ጋዜጠኛ ከድር እና ጋዜጠኛ አብዱልሰመድን በአስቸኳይ እንዲፈቱ አሳስበዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:
https://addisstandard.com/Amharic/?p=8973
ዜና: የውጭ ዜጎች በመንግሥት ተቋም ለሚያገኙት የሕክምና አገልግሎት እጥፍ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ መመርያ መዘጋጀቱ ተገለጸ

የጤና ሚኒስቴር ማንኛውም የውጭ ዜጋ #በኢትዮጵያ በመንግሥት የጤና ተቋም ሲገለገል፣ ለእያንዳንዱ አገልግሎት የወጣውን ተመን እጥፍ እንዲከፍል የሚያስገድድ መመርያ ማዘጋጀቱ ተጠቆመ።

የውጭ ዜጋ በመንግሥት የጤና ተቋማት ለእያንዳንዱ አገልግሎት የወጣውን ተመን እጥፍ እንዲከፍል እንደሚገደድ ሚኒስቴሩ የፋይናንስ ሥርዓት ዝርዝር አፈጻጸምን ለመደንገግ ባወጣው መመርያ መካተቱ ተገልጿል።

ሆኖም የስደተኞች የጤና አገልግሎት የሚሸፈነው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ድርጅቶች ጋር በሚደረግ ስምምነት መሠረት እንደሚሆን የሚኒስቴሩን መመሪያ ማመላከቱን ከሪፖርተር ጋዜጣ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

በሌላ በኩል መመሪያው ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ሌሎች የጤና ተቋማት አግባብነት ባለው ሕግ መሠረት የአገልግሎት ክፍያ እንደሚያስከፍሉ የሚደነግግ ሲሆን ፣ የፌዴራልና የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የአገልግሎት ተመን በየሦስት ዓመቱ እንደሚከለስ ተመላክቷል።

በተጨማሪም በክልሎች የሚገኙ የጤና ተቋማትን በሚመለከት በክልሎች ሕግ መሠረት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ እንደሚከለስ የተገለፀ ሲሆን የጤና አገልግሎት ተመን ክለሳ ሲደረግም የማኅበረሰቡን የመክፈል አቅም ታሳቢ እንደሚደረግ፣ ተመኑ ሲሰላም የጤና ተቋማትን ደረጃና የሚገኙበትን ቦታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሚሆን ዘገባው አስታውቋል።

================
የአዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይቀላቀሉ፡
ቴሌግራም: https://rb.gy/rekjr
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
ድረገጽ: https://rb.gy/5td6n
ቲክቶክ፡ https://rb.gy/jgdsjm
ዜና፡ #የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል አንድ አመራሩ በታጣቂዎች መገደላቸውን አስታወቀ

በአማራ ክልል ሰላም ካውንስል የሰሜን #ጎጃም ዞን የካውንስሉ መሪ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩ አመራሩ በታጣቂዎች መገደላቸውን አስታወቀ።

መልዓከ ምህረት ነቃጥበብ ገነት የተባሉ የካውንስሉ የሰሜን ጎጃም ዞን አመራሩ “የታጠቁ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር እንዲወያዩ፣ ሰላም እንዲሰፍን እና የክልሉ ሕዝብ ስቃይም እንዲያበቃ ሲማጸኑ መቆየታቸውን” ካውንስሉ የጻፈለትን ደብዳቤ ዋቢ በማድረግ የክልሉ ቴሌቪዢን ባሰራጨው ዘገባ አስታውቋል።

በአከባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች “ሐምሌ 01 ቀን 2017 ዓ.ም ምሽት ላይ እኒህ አባት ከሚያገለግሉበት ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ታጥቀው በመግባት አፍነው ወስደዋቸዋል” ሲል መግለጫው ማውሳቱን ዘገባው አካቷል።

ታጣቂዎቹ የካውንስሉን አመራር “ዳህና ማርያም ወደተባለው የታጣቂዎች ምሽግ በመውሰድ ለስቃይ ሲዳርጓቸው መቆየታቸውን” እና “ነሐሴ 06 ቀን 2017 ዓ.ም ደግሞ በታጣቂዎቹ መገደላቸውን” የካውንስሉ መግለጫ ማስታወቁን ዘገባው አካቷል።

https://addisstandard.com/Amharic/?p=8976
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
ዜና: በፋብሪካዎች የሚሰሩ ሰራተኞች ወርሃዊ ገቢ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን የ #ኢሰማኮ ፕሬዝዳንት ጥሪ አቀረቡ

የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሰማኮ) ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በፋብሪካዎች የሚሰሩ ሠራተኞች እጅግ በጣም አነስተኛ ደመወዝ የሚያገኙ በመሆኑ መንግሥት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን እንዲወስን ጠየቁ።

አቶ ካሳሁን ፎሎ መንግሥት በቅርቡ የመንግስት ሰራተኞችን ደመወዝ እንደሚጨምር ማስታወቁን በአዎንታ እንደተቀበሉት ገልጸው በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚሰሩ ሠራተኞች ከ1,000 ብር (7 ዶላር) እስከ 3,000ብር (22 ዶላር) የሚደርስ ወርሃዊ ደሞዝ እንደሚያገኙ ገልፀዋል፤ ይህም ለመኖር ከሚያስፈልገው ደመወዝ እጅግ በጣም ያነሰ መሆኑን ጠቁመዋል።

አክለውም ለችግሩ አስቸኳይ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ አጽንዖት በመስጠት መንግስት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን እንዲወስን ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ካሳሁን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን ለመወሰን ሕጋዊ መሠረት እንዳለ ተናግረዋል። "በ2011 የአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን" መቀመጡን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ አዋጁ በተግባር ላይ እንዲውል ጠይቀዋል።
ዜና: ለውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ተጠቃሚዎች አገልግሎት የሚሰጥ "ለመንገዴ" የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ይፋ ተደረገ

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከዓለም የሥራ ድርጅት ጋር በመተባባር ለውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ተጠቃሚዎች አገልግሎት የሚሰጥ "ለመንገዴ" የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ይፋ መደረጉ ተገለፀ፡፡

መተግበሪያው በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ተጠቃሚ የሚሆኑ ዜጎች ከቅድመ ጉዞ በፊት ማድረግ ስለሚኖርባቸው ቅድመ ዝግጅቶች፣ መብትና ግዴታዎቻቸውን ጨምሮ የተለያዩ መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት እንዲያገኙ እንደሚያግዛቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ነቢሃ መሐመድ ገልጸዋል፡፡

መተግበሪያው በራስ አቅም በልጽጎ ወደ ሥራ የገባ መሆኑን የገለጹት ሚንስትሯ፤ ይህም በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪቱ የዜጎችን መብት፣ ደህንነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከመረጃዎቹ ባሻገርም ምንም አይነት ቅሬታም ሆነ ችግር በሚገጥማቸው ወቅት ለሚመለከተው አካል በቀላሉ ማሳወቅ እንዲችሉ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የዓለም የሥራ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኩምቡላ ዳባ በበኩላቸው፤ መተግበሪያው መልከ ብዙ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው መሰል ሥራዎችን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ይሰራል ብለዋል።

በተጨማሪም መተግበሪያው በአማርኛ፣ በአረብኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች በቴሌብር ማግኘት እንደሚቻል ተገልጿል።

================
የአዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይቀላቀሉ፡
ቴሌግራም: https://rb.gy/rekjr
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
ድረገጽ: https://rb.gy/5td6n
ቲክቶክ፡ https://rb.gy/jgdsjm
ዜና፡ በ #ምዕራብ_ጎንደር ቋራ ወረዳ ታጣቂዎች የመንግስት ተቋማትን “ማውደማቸው” እና “የአመራሮችን ንብረት መዝረፋቸው” ተገለፀ

#አማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን #ቋራ ወረዳ ገለጉ ከተማ ታጣቂዎች ፈፀሙት በተባለ ጥቃት የመንግስት እና የአመራሮች ንብረት መዘረፉ፣ 74 ቢሮዎች መውደማቸውና በ20 ግለሰቦች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መደረሱን የወረዳው ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት አስታወቀ።

የቋራ ወረዳ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ትናንት ነሐሴ 15 ቀን ባወጣው መግለጫ፣ “ፅንፈኛ” ሲል የጠራቸው አካላት፤ “በ24 የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች 74 ቢሮዎችን በማውደም፣ 3 መኪኖችን በማቃጠል፣ 1 መኪና በመውሰድ ጉዳት አድርሰዋል” ብሏል።

"በጥቃቱ በእያንዳንዱ ተቋማት በተለያዩ ቢሮዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል" ያለው የጽ/ቤቱ መግለጫ፤ ለጥቃቱ “ፅንፈኛ” ሲል የጠራቸውን አካላት ተጠያቂ አድርጓል።

መግለጫው አክሎም፤ የሁሉም የወረዳው የፓሊስ አባላት አልባሳትና የቤት ንብረታቸው መውደሙና መወሰዱን የመረጃ አጣሪ ኮሚቴ ተናግሯል ብሏል። በተጫማሪም፤ ታጣቂዎቹ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ አስማረ አንዳርጋቸው “የቤት እቃው ሙሉ በሙሉ ማውደማቸውንና መውሰዳቸውን” ተገልጿል።

ተጨማሪ ያንብቡ፡ https://addisstandard.com/Amharic/?p=8983
በሐምሌ ወር ወደ ውጭ ከተላከ ቡና 268 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተነገረ

#ኢትዮጵያ በሐምሌ ወር ውጭ ሀገራት ከተላከችው ቡና 268 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

#ጀርመን#ሳውዲ_አረቢያ እና #ቤልጂየም ብዙ መጠን ያለው የኢትዮጵያ ቡና የተላከባቸው ሀገራት ናቸው ተብሏል። ቻይና፣ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች የኢትዮጵያን ቡና ከገዙ ሀገራት መካከል መሆናቸው ባለስልጣኑ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ህዝብ ግንኙነት እና ኮሙንኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳህለማርያም ገብረመድህን እንደገለጹት፤ በ2018 በጀት ዓመት ሐምሌ ወር ላይ 53 ሺህ 480 ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 216 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ሲሆን በተጠቀሰው ወር ውስጥ 38 ሺህ 663 ቶን ቡና ወደ ውጭ ሀገራት ተልኳል። በዚህም 268 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።

ወደ ተጠቀሱት ሀገራት የተላከው ቡና መጠን ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር በመጠን የሁለት በመቶ ቅናሽ ሲያሳይ በገቢ ደግሞ የ53 በመቶ ጭማሪ ያሣየ መሆኑን አቶ ሳህለማርያም ገብረመድህን ለኢፕድ ተናግረዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላከው ቡና 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም በታሪክ ከፍተኛው እንደሆነ መገለፁ ይታወሳል።

በተያዘው የበጀት አመትም ወደውጪ ከሚላክ 600ሺህ ቶን ቡና ውስጥ ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት እቅድ መያዙን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገልጿል።
ዜና: ሚዲያዎች ሰላምን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን የብሔራዊ ጥቅም አካል አድርገው መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ

ሚዲያዎች ሰላምን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን የብሔራዊ ጥቅም አካል አድርገው መስራት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ ሚዲያ ልኅቀት ማዕከል ምስረታን አስመልክቶ ከተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ከተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት ነሐሴ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል፡፡

በዚሁ ወቅት ንግግር ያደረጉት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) ሚዲያዎች ሰላምን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን የብሔራዊ ጥቅም አካል አድርገው መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

"ሚዲያዎች ረጅም የአየር ሰዓት ወስደው ስለሰላም የመዘገብ ልምድ እንደሌላቸው" የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በሀገሪቱ የሰላም ጋዜጠኛ እራሱን ችሎ ሊኖር ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሚዲያው ሰላምን ዋና ተልዕኮ እና ራዕዩ አድርጎ መስራት ግዴታው ሊሆን ይገባል ሲሉ ገልጸው፤ ማንኛውም ሚዲያ ሲመሰረት ፍቃድ የሚሰጠው ስለሰላም ይሰራል ተብሎ ሲታሰብ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም የሚዲያውን ዘርፍ አቅም ለማሳደግም ታስቦ የሚዲያ ልኅቀት ማዕከል መገንባቱን መናገራቸውን የዘገበው ኢቢሲ ነው፡፡

================
የአዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይቀላቀሉ፡
ቴሌግራም: https://rb.gy/rekjr
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
ድረገጽ: https://rb.gy/5td6n
ቲክቶክ፡ https://rb.gy/jgdsjm
ዜና፡ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ ያልተመለሱበት #አማራ ክልል በቀጣይ ሳምንት የ2018 የትምህርት ዘመን ምዝገባ እንደሚጀምር አስታወቀ

ባለፉት አመታት በጸጥታ ችግር በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታ ያልተመለሱበት የአማራ ክልል በ2018 የትምህርት ዘመን ሙሉ በሙሉ ለማስጀመር ዝግጅት ማድረጉን እያስተዋወቀ ይገኛል።

ክልሉ የተማሪዎች ምዝገባ በይፋ ነሃሴ 19 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚጀምር እና እስከ ነሃሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይም አስታውቋል።

በአማራ ክልል ባለፉት ሁለት አመታት በጸጥታ ችግር ምክንያት በሚሊየኖች የሚቆጠሩ የክልሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው አመመለሳቸውን የክልሉ የትምህርት ቢሮ መረጃ ያሳያል። የመማር ማስተማሩ ሂደት የተቋረጠባቸው የክልሉ ቦታዎችም በርካታ ናቸው፡፡

ክልሉ በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን 7 ሚሊየን ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ቢያቅድም፤ የተመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ብቻ ናቸው።

https://addisstandard.com/Amharic/?p=8987
ዜና: ግብፅ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ከምትከተለው ፖሊሲ ጋር የሚፃረር አዲስ የዲፕሎማሲያዊ ቅስቀሳ እና የማግባባት ስራ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ላይ ጀምራለች ተባለ

ግብፅ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ከምትከተለው ፖሊሲ ጋር የሚጻረር አዲስ የዲፕሎማሲያዊ ቅስቀሳ እና የማግባባት ስራ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ላይ ጀምራለች ተባለ።

የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ትናንት ሐሙስ ዕለት ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከጅቡቲ፣ ከዩጋንዳ፣ ከኬንያ እና ከሶማሊያ አቻዎቻቸው ጋር በስልክ መነጋገራቸውን የግብጽ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ሚኒስትሩ በንግግራቸውም “በናይል ተፋሰስ ላይ ዓለም አቀፍ ህግን የሚጥሱ የአንድ ወገን እርምጃዎችን ግብፅ ውድቅ ማድረጓን በድጋሚ አረጋግጠዋል” ሲል የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ዋስትና ብትሰጥም እንዲሁም የዓባይን ወንዝ ፍትሐዊ አጠቃቀም የተመለከተው የዓባይ (ናይል) ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) ከጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 2024 ጀምሮ በይፋ ሥራ ላይ ቢውልም የግብፅ ዲፕሎማሲያዊ ግፊት አልተቋረጠም።

ተጨማሪ ያንብቡ:
https://addisstandard.com/Amharic/?p=8990
ዜና: የ #ሶማሊላንዱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ለኖቤል የሰላም ሽልማት አጩ

የሶማሊላንዱ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሀመድ አብዱላሂ (ኢሮ) የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ለኖቤል የሰላም ሽልማት በይፋ እጩ አድርገው አቀረቡ።

ኢሮ ትራምፕን ለሽልማቱ እጩ አርገው ያቀረቡትም በዓለማችን ላይ በጣም አሳሳቢ የሆኑ ግጭቶችን ለመፍታት ላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን በመግለጽ ነው።

የሶማሊላንድ ሁለተኛ ዋና ከተማ በሆነችው ቡሮአ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ኢሮ፤ በሩሲያና ዩክሬን መካከል ያለውን ጦርነት እንዲሁም በእስራኤልና በኢራን መካከል የነበረውን ውጥረት ጨምሮ አሜሪካ የተለያዩ ግጭቶችን ለማስቆም ላደረገችው ጥረት ምስጋናቸውን ገልጸው፤ ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኖቤል የሰላም ሽልማት እንዲሰጥ ድምፃቸውን እንደሚያሰሙ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሀመድ አብዱላሂ (ኢሮ) በንግግራቸውም "የሶማሊላንድ ሪፐብሊክን እውቅና ለመስጠት ላሰቡት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ" ያሉ ሲሆን፤ "ዛሬ እኔ እንደ ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ግጭቶችን ለመፍታት እና በመላው ዓለም ሰላምን ለማምጣት ላደረጉት ጥረት ዕውቅና በመስጠት ለፕሬዝዳንት ትራምፕ የኖቤል የሰላም ሽልማት እንዲሰጣቸው ለመደገፍ ከዓለም አቀፍ መሪዎች ጎን መሰለፌን በይፋ አውጃለሁ" ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ኢሮ ይህን የገለጹት በትራምፕ አስተዳደር በቀጣናው በተለይም በሶማሊላንድ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ለውጥ ይመጣል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ሲሆን፤ ሶማሊላንድም ከሶስት አስርት ዓመታት በኋላ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለማግኘት እየጣረች በምትገኝበት ወቅት መሆኑን ሆርን ዲፕሎማት ዘግቧል።
ርዕሰ አንቀፅ: በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በተከፋፈሉ ተቀናቃኞች መደሰትን ማቆም አለበት

“በአጭር ጊዜ ጦርነት ዘላቂ መፍትሄ ይመጣል ብሎ ማመን እጅግ ጥንታዊና አደገኛ ከሆኑ የተሳሳቱ የሰው ልጆች አመለካከቶች መካከል አንዱ ነው” – ሮበርት ሊንድ (እ.ኤ.አ 1879–1949)

የአውሮፓ ጦርነቶች ያስከተሉትን ውድመት ተከትሎ ሮበርት ሊንድ ከመቶ ዓመት በፊት የሰጠው ይህ ማስጠንቀቂያ ዛሬ ኢትዮጵያ ላለችበት ሁኔታ ጠቃሚ መልዕክት ነው። ሊንድ “ጦርነት በአጭር ግዜ ዘላቂ መፍትሄ ያመጣል” የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት አስመልክቶ የሰጠው ማስጠንቀቂያ፤ የኃይል እርምጃ መውሰድና ተቃዋሚዎችን መከፋፈል የፖለቲካ ውዝግቦችን በፍጥነት ሊፈታ ይችላል ብለው የሚያምኑ መሪዎች በተደጋጋሚ ችላ የሚሉትን ልምድ ያሳያል።

ከአንደኛው የዓለም ጦርነት አንስቶ እስከ ቬትናም፣ አፍጋኒስታን፣ የመን፣ ሶሪያ እና ሊቢያ ድረስ ያለው ታሪክ፤ “ጦርነት በአጭር ግዜ ዘላቂ መፍትሄ ያመጣል” የሚለው የተሳሳተ አመለካከት ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ መከራን፣ የረጅም ጊዜ አለመረጋጋትን እና ብዙ ጊዜም የአገር መፍረስን እንደሚያስከትል አመላክቷል።

ኢትዮጵያ እየተስፋፉ ያሉ ወታደራዊ ግጭቶቿን በፍጥነት የመፈታት ተስፋዋ እየመነመነ መጥቷል። የትኛውም ወገን ወሳኝ ድልን ሊጎናጸፍ ያልቻለበት ዑደት ተፈጥሯል።ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ስትራቴጂ የሥልጣን የሚያጠናክር ሊመስል ቢችልም፣ የሀገሪቱን መሠረት ቀስ በቀስ እያዳከመ እና ዘላቂ ሰላምን እንዳይሰፍን እያደረገ ይገኛል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ እጅግ አሳሳቢ ሲሆን የተሞከረና የከሸፈ እንዲሁም ዘላቂ ሰላም የሚገኝበትን መሰረት የሚያዳክም ነው።

ሙሉ ርዕሰ አንቀፁን ለማንበብ፡ https://addisstandard.com/Amharic/?p=8995
ዜና፡ ጋዜጠኛ ዮናስ አማረ እና ጋዜጠኛ አብዱል ሰመድ መሀመድ መለቀቃቸው ተገለጸ

የሪፖርተር ጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዮናስ አማረ እና በአሀዱ ኤፍ ኤም 94.3 FM ሬዲዮ የቅዳሜ ገበያ ፕሮግራም አዘጋጅ ጋዜጠኛ አብዱል ሰመድ መሀመድ መለቀቃቸው ተገለጸ።

ጋዜጠኛ ዮናስ አማረ ትናንት ዓርብ ነሐሴ 16 ቀን 2017 ዓም ምሽት ከሶስት ሰዓት በኋላ መለቀቁን ሪፖርተር ዘግቧል። የቅዳሜ ገበያ ሾው አዘጋጅ ጋዜጠኛ አብዱልሰመድ መሀመድም መለቀቁ ተገልጿል።

ጋዜጠኛ ዮናስ ከእስር የተለቀቀው አስረኛ ቀኑ ላይ ሲሆን፣ ጋዜጠኛ አብዱል ሰመድ ደግሞ በ12ኛ ቁኑ ላይ ነው። ጋዜጠኞቹ በማን ታፍነው እንደተወሰዱ፣ የት እንደቆዪና አካላዊ ጉዳት ይድረስባቸው ወይም አይድረስባቸው የሚያሳይ ዝርዝር መረጃ አልተገኘም ብሏል ዘገባው።

https://addisstandard.com/Amharic/?p=9025
ዜና፡ "የገደብ ወንዝ ድልድይ የጥገና ሥራ ሙሉ በሙሉ አልተጠናቀቀም፣ ለአገልግሎትም ክፍት አይደለም” ተባለ

በደብረ ማርቆስ #ባህር ዳር መስመር #አማኑኤል ከተማ የሚገኘው የጌደብ ወንዝ ድልድይ የተገጣጣሚ ብረት ተሰርቶለት በአሁኑ ሰዓት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ፤ ቀሪ ሥራዎች እንደሚቀሩትም ጠቁሟል።

የተገጣጣሚ ብረት ድልድዩ “በአሁኑ ሰዓት በመጠናቀቅ ላይ” ይገኛል ያለው አገልግሎቱ “ቀሪ ሥራዎች እንደተጠናቀቁ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል” ሲል አስታውቋል፡፡

“በመሆኑም ድልድዩ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ እስኪገለጽ የመንገዱ ተጠቃሚዎች በተለመደው ትዕግስት እንዲጠብቁ” ሲል ጠይቋል።

ድልድዩ ለአገልግሎት ዝግጁ ሲሆን ወዲያዉኑ ለሕዝብ ግልጽ የሚደረግ መሆኑን ጠቁሟል።

“በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በአሁኑ ሰዓት ድልድዩ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሆነ እየተገለጸ ያለው መረጃ መስተካከል ያለበት” ሲል አሳስቧል፤ “መሆኑን የመንገዱ ተጠቃሚዎች አውቀው በትዕግስት እንዲጠብቁ” ሲል ጠይቋል።

“ድልድዩ ሁለት መኪና በአንዴ ማስተላለፍ ስለማይችል በመጠባበቅ እንዲተላለፉ፣ ድልድዩ የሚገኝበት ቦታ ኩርባ ላይ ስለሆነ ፍጥነት በመቀነስ እና ቅድሚያ በመስጠት በትዕግስት እንዲተላልፉ” ሲል የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

በደብረ ማርቆስ ባህር ባሕር ዳር መስመር አማኑኤል ከተማ የሚገኘው የጌደብ ወንዝ ድልድይ ነሐሴ 3 ቀን 2017 ዓ.ም ሌሊት በጮቄ ተራራ ዙሪያ የጣለው ከባድ ዝናብ በፈጠረው ጎርፍ ፈርሱን መዘገባችን ይታወሳል።
“ዓላማችን ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚረዱ በጣት የሚቆጠሩ ጠንካራ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ ነው”_ የ11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ሰብሳቢ

#ኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ 11 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ጠንካራ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ያግዛል ያሉትን ጥምረት ነሐሴ 14፣ 2017 ዓ/ም መመስረታቸውን አስታውቀዋል።

ፓርቲዎቹ ወደ አንድ ጥምረት ለመምጣት የመረጡት በብቸኝነት ከመታገል ይልቅ፣ ከየአቅጣጫው የመጡ ዜጎችን በአንድነት በማሰባሰብ የህዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅና የጋራ ጥያቄዎችን ለማቅረብ እንደሆነ የጥምረቱ ሰብሳቢ አቶ ሳይመን ቱት ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

አቶ ሳይመን ቱት፣ የጥምረቱ ዋና ዓላማ "ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚረዱ በጣት የሚቆጠሩ ጠንካራ ፓርቲዎችን መፍጠር እና ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ነው" ብለዋል። አቶ ሳይመን ይህ ጥምረት ወደፊት ወደ አንድ ጠንካራ ፓርቲ ወይም ግንባር ለመምጣት መንገድ የሚጠርግ መሆኑን ገልጸዋል።

https://web.facebook.com/AddisstandardAmh/posts/pfbid02myzV2djNTT2GZw7QaEjHZ6Sm6KJaXVTygFJMTYaPfTFZB4Fvd8G494YHXnPSk8wKl
ዜና: በመቀሌ ከተማ የሰዎች አፈናና ድንገተኛ መሰወር ነዋሪዎችን አስደንግጧል

በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ የሰዎች አፈና፣ ለገንዘብ ተብሎ የሚፈጸሙ እገታዎች፣ ዝርፊያ እና ምክንያቱ ያልታወቀ የሰዎች ደብዛ የመጥፋት እና መሰወር ሁኔታዎች በፍርሃት ውስጥ እንዲገቡ እንዳደረጋቸው ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

በቅርቡ አቶ ፊልሞን ገብረህይወት የተባሉ የካሜራ ባለሙያ እና የፊላሪ ፕሮዳክሽን ባለቤት ከጠፉ ከሳምንት በላይ የሆናቸው ሲሆን እስከአሁን የት እንደደረሱ አልታወቀም።

የአቶ ፊልሞን ባለቤት ወይዘሮ ገነት እዝራ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ለመጨረሻ ጊዜ የባለቤታቸውን ድምጽ የሰሙት እሑድ ነሐሴ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ምሽት ላይ በባጃጅ ወደ ቤቱ እየገባ በነበረበት ሰዓት ነው። “ወደ ቤት እየመጣሁ ነው አለኝ። እንደገና ደወልኩለት ነገር ግን አላነሳም በኋላ ላይ ስልኩ ጠፋ” ሲሉ ስለ ሁኔታው አስረድተዋል።

መሰል ክስተቶች በመቐለ ከተማ ከቅርብ ወራት ወዲህ እየተባባሱ ስለመምጣታቸው ነዋሪዎች ይገልጻሉ። የ30 አመቱ ግርማይ ሃፍቴ “ከጦርነቱ በኋላ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ትግራይን ለማስተዳደር ኃላፊነት የተጣለባቸው ሃይሎች ሰላም እና ጸጥታን ከማረጋገጥ ይልቅ በውስጥ የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ ገብተዋል” በማለት ሁኔታውን “ፍፁም ውድቀት” ሲሉ ገልጸውታል።


ተጨማሪ ያንብቡ:
https://addisstandard.com/Amharic/?p=9028
ዜና: በ #አማራ ክልል ትናንት በደረሱ ሁለት የትራፊክ አደጋዎች የ11 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 17 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ደረሰ

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላና ጠራ ወረዳ እንዲሁም በምዕራብ ጎጃም ዞን ጅጋ ንዑስ ወረዳ በተለምዶ ለዛ ወንዝ ከተባለው ስፍራ ትናንት እሁድ ነሐሴ 18 ቀን 2017 ዓ.ም በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች የ11 ሰው ህይወት ሲያልፍ 17 ሰዎት ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት መድረሱን የአማራ ክልል ፖሊስ አስታወቀ።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላና ጠራ ወረዳ አደጋው የደረሰው 19 ተሳፋሪዎችን ጭኖ ከደብረብርሀን ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሲጓዝ የነበረ በተለምዶ ሀይሩፍ በሚል የሚታወቀው አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ መሆኑ ተገልጿል።

የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር በልኬ ይርጋ ፍጥነት ላይ የነበረው ተሽከርካሪ ጨኪ ቀበሌ ልቼ ጎጥ አካባቢ ጎማ ፈንድቶበት ሊገለበጥ ችሏል ሲሉ ጠቁመዋል።

በዚህም የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ አስር ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት እንዲሁም ሰባት ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው አመልክተዋል።

በተመሳሳይ በምዕራብ ጎጃም ዞን ጅጋ ንዑስ ወረዳ በተለምዶ ለዛ ወንዝ ከተባለው ስፍራ ከፍኖተ ሰላም ወደ አዲስ አበባ እየተጓዘ የነበረ ተሳቢ የጭነት መኪና ከባጃጅ ጋር ተጋጭቶ ባጃጅ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩ ሰባት ሰዎች እና ሁለት እግረኞች በድምሩ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት አልፏል ተብሏል።

================
የአዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ይቀላቀሉ፡
ቴሌግራም: https://rb.gy/rekjr
ፌስቡክ: https://rb.gy/xwxb3
ትዊተር (X)፡ https://rb.gy/34uh4
ድረገጽ: https://rb.gy/5td6n
ቲክቶክ፡ https://rb.gy/jgdsjm