TechIn2
1.22K subscribers
1.47K photos
1 video
120 files
500 links
Technology & Innovation Institute (TechIn2), Ethiopia

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት

ጠቃሚና ወቅታዊ የሆኑ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራ፣ ጤና እና ሰብአዊ-ኣቅም ግንባታ(Human Development)መረጃዎችንና ምክሮችን በየእለቱ እናደርሶታለን።
Download Telegram
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብረሀም በኢንስቲትዩታችን ጉብኝት አድርገዋል
=======================
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶ/ር አብረሀም በላይ ከአመራር ቡድን አባላቶቻቸው ጋራ በመሆን የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል፡፡ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ወቅት ተቋሙ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ማዕከል ሆኖ ከተነሳበት ወቅት አንስቶ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንቲትዩት ሆኖ ከቆመ በኋላም በተሰሩ ስራዎች እና ባጋጠሙ ተግዳቶች ዙርያ በኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳንዶካን ደበበ ገለፃ ቀርቦላቸዋ፡፡ አቶ ሳንዶካን በገለፃቸው ወቅት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ልዩ ልዩ ድጋፍ ይደረግላቸው ዘንድ ጥያቄ ሲያቀርቡ ሚንስትሩ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሰሩ በውይይቱ አስታውቀዋል፡፡
የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ለኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተጠሪ ከሆኑ ተቋመት አንዱ ሲሆን ሚኒስትሩ ዶ/ር አብረሀምም ከቅርቡ ሹመታቸው ወዲህ መሰል ጉብኝትን ወደ ኢንስቲትዩቱ ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።
የኮሮና ቫይረስ እና መልስ ሊሰጣቸው የሚገቡት ጉዳዮች
*******************************
የኮሮና ቫይረስ ወይም በይፋዊ ስሙ COVID-19 ከቻይናዋ ሁቤይ ግዛት ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ ወደ ሌሎች የአለማችን ክፍሎች እስከተዳረሰበት የአጭር ወራት ጊዜ ውስጥ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም ብዙዎችን ሲያነታርኩ እና ሲያከራክሩ የቆዩ ጉዳዮችም ሲሰሙ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡ በተለይም ቫይረሱ ሰዎችን ካጠቃ በኋላ ምልክቶችን በትክክል ለመመልከት ምን ያህል ቀን ይፈጃል የሚለው ጉዳይ እና ምልክቶችስ ከመታየታቸው በፊት ቫይረሱ ወደሌሎች የመተላለፍ እድሉ ምንያህል ነው የሚሉት ጥያቄዎች አሁንም ተገቢ ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡
እንደሚታወቀው ተመራማሪዎች በኮሮና ቫይረስ የተጠቃ ሰው ከስንት ቀናት በኋላ ምልክቶችን ማሳየት እንደሚጀመር ለመረዳት ሰፊ ጥናት ሲያደርጉ እንደነበር በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ ይህ incubation period of a virus በመባል የሚታወቀው ፅንሰ ሃሳብ የትኛውም ቫይረስ ሰዎችን ካጠቃ በኋላ ምልክቶችን ለማሳየት የሚወስድበትን የጊዜ መጠን የሚያሳይ ሲሆን፤ አብዛኛውን ጊዜም እንደቫይረሱ ዓይነት እና እንደተጠቃው ግለሰብ የአቅም ሁኔታ የተለያየ ውጤት እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
ታዲያ SARS-CoV-2 የተሰኘው የቫይረስ በሽታ ሰዎችን ካጠቃ ወይም infected ካደረገ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ምልክቶችን በትክክል ማሳየት እንደሚጀምር ለማወቅ በተደረገ ሰፊ ጥናት ብዙዎችን ሊያስማማ የሚችል አዲስ ግኝት በጆንስ ሆፕኪነስ ዩኒቨርስቲ ይፋ ሆኗል፡፡ ጥናቱ የ SARS-CoV-2 ወይም የኮሮና ቫይረስ ኬዝ ያለባቸው 181 የቻይና ዜጎች ላይ ትኩረት አድርጎ የተሰራ ሲሆን፤ በአማካኝም 97.5 በመቶ የሚሸፍኑት ተጠቂዎች 5.1 በሚሆን ቀናት ውስጥ ምልክቶቹ ሊታይባቸው እንደቻለ የምርምር ቡድኑ አስታውቋል፡፡ ይህም እስካሁን ሲደረግ የነበረውን የአስራ አራት ቀናት የለይቶ ማቆያ ጊዜ (quarantine period) ምክንያታዊ ቢያደርገውም የተቀረው 2.5 በመቶ የሚሸፍነው የቫይረሱ ተጠቂ ግን ሌሎች አከራካሪ ነጥቦች እንዲነሱ ምክንያት የሆነ ነው፡፡
በዚህ ስሌት መሰረት ጥናቱ የተደረገባቸው አብዛኞቹ (97.5%) የቫይረሱ ተጠቂዎች 11.5 በሚሆኑ ቀናት ውስጥ ዋና ዋናዎቹን የትኩሳት፣ የደረቅ ሳል እና የትንፋሽ መቆራረጥ ምልክቶች በየተራ ማሳየት የቻሉ ቢሆንም 2.5 በመቶ የሚሆኑት ግን ከ14 ቀን በላይ ምልክቶች ሳታይታይባቸው እንደቆየ የጥናት ቡድኑ የምርምር ውጤት ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ በሌላ አገላለፅ በለይቶ ማቆያ ውስጥ የገቡ 10,000 ሰዎች ቢኖሩ እና ቫይረሱ እንዳለባቸው ለማረጋጋጥ 14 ቀን ቢቆዩ፤ ከእነዚህ ውስጥ 101 የሚሆኑት በተገለሉባቸው 14 ቀናት ውስጥ ምንም ምልክት ሳይታይባቸው ከለይቶ ማቆያ ወይም (quarantine) ከወጡ በኋላ ምልክቶችን ማሳየት ይጀምራሉ ማለት ነው፡፡ ይህም እንደተመራማሪዎቹ ትንተና አሁን እየተሰራበት ያለው የ14 ቀን የለይቶ ማቆያ ጊዜ መቶ በመቶ ውጤታማ ያደርጋል የሚለውን መከራከሪያ ጥያቄ ውስጥ ያስገባል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከላይ በጥያቄ ለማንሳት እንደተሞከረው በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ምልክቶቹን ከማሳየቱ በፊት ወደ ሌሎች ቫይረሱን የማስተላላፍ እድሉ ምን ያህል ነው የሚለው ጥያቄ ሌላው ትንታኔ የሚስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም በዚህ ሃሳብ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን እና የሃገራት ኬዞችን የሚተነትኑ ባለሙያዎች እንደሚያነሱት ይህ ጉዳይ ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው የኮሮና ቫይረስ አሁን ለደረሰበት ከፍተኛ ስርጭት ትልቅ አስተዋፆኦ እንዳበረከተ ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ፀሃፊዎች በትንታኔያቸው ላይ ለአብነት ያስቀመጡትን የማሳቹሴትስ ጉዳይ ለምሳሌ ብናነሳ በዚህ ግዛት ተመዝግበው የነበሩ 82 ኬዞች የስርጨት መነሻቸው በቫይረሱ የተጠቁና ምንም ምልክት ሳይታይባችው የቆዩ ጥቂት ግለሰቦች እንደነበሩ ከማስረጃ ጋር አያይዘው ጠቅሰዋል፡፡ ይህ በአሜሪካ አንድ ግዛት የታየ ጉዳይ ቢሆንም በሌሎች ሃገራት የነበሩ ሁኔታዎችን ስንመለከት ቫይረሱ ከሚታሰበው በላይ የስርጭት መጡኑ ከፍተኛ የሆነበት ምክንያት ሌሎች ያልተመለሱ ጥቄዎች እንዳሉ ሆነው ይህ ጉዳይም አስፈላጊውን ትኩረት እንዳለገኘ የሚያሳይ ነው፡፡ በመሆኑም እንደአጥኚዎቹ እና እንደተንታኞቹ መከራከሪያ ከሆነ ለእነዚህ ጉዳዮቹ የተሰጠውን ትኩረት ይበልጥ በማሳደግ የቀረቡ ጥናቶችን ከግምት ውስጥ ባማስገባት እና ትንተናዎችን በመመልከት የጤና መመሪያና ፖሊሲዎችን ከጉዳዮቹ ጋር አጣጥሞ ማስኬዱ ይበልጥ እንደሚበጅ ምክረ ሃሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡
ምንጭ፡ https://edition.cnn.com/2020/03/14/
health/coronavirus-asymptomatic-spread/index.html እና https://bigthink.com/politics-current-affairs/coronavirus-incubation
አስቸኳይ ጥሪ ለፈጠራ ባለሙያዎች በሙሉ
=============================
የኢትዮጵያ ኢኖቬተርስ አሶሴሽን የኮሮና ቫይረስ (COVID -19) ስርጭትን ለመቆጣጠር እና ለመግታት የሚያግዝ የፈጠራ ሐሳብ ያላችሁ ሁሉ ኑ በጋራ እንስራ ይላችኋል፡፡ የበለጠ መረጃ በደብዳቤው ላይ በተገለጽት አድራሻዎች የምታገኙ ይሆናል፡፡
COVID-19 የመግደል ምጣኔው ምን ይመስላል?
********************************
ኮቪድ-19 የሚል ስያሜ የተሰጠው ቻይና ውስጥ የተቀሰቀሰው ተላላፊ በሽታ እስካሁን ድረስ 182,000 ሰዎችን ሲያጠቃ 7,100 የሚሆኑትን ደግሞ ህይወታቸውን የነጠቀ ነው፡፡ ቫይረሱ ከአፍንጫ አንስቶ እስከ ሳምባ ያሉትን የመተንፈሻ አካላት የሚያጠቃ በሽታ ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ውስን ቀናት ከሚታየው ትኩሳት በማስከተል ደረቅ ሳል የሚኖረው ወረርሽኝ እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ቫይረሱ ከሳምንት በኋላ የትንፋሽ ማጠርን እንዲሁ የሚያስከትል ሲሆን፤ በዚህም ሳቢያ አንዳንድ በበሽታው የተያዙ ሰዎች የህክምና እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።
የቻይና የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል በሀገሪቱ ተመዝግበው በነበሩ የኮሮናቫይረስ ኬዞች ተመርኩዞ በሚያወጣቸው የተለያዩ መረጃዎች መሰረት COVID-19 የከፋ በሚሆንበት ጊዜ እንደነ ኒሞኒያ፣ ሳርስና እና ሌሎች የውስጥ አካላትን ሥራ እንዲያቆሙ በማድረግ በጤናችን ላይ ችግር የሚፈጠሩ በሽታዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ መተንፈሻ አካላትን የሚያዳክም ሲሆን ሌሎች በሽታዎች ሲጨመሩበት ደግሞ ሞትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ቫይረሱ በዕድሜ የገፉ እና እንደአስም፣ የስኳር በሽታ፣ የልብ ህመም የመሳሰሉ የጤና ችግሮች ያሉባቸውን ሰዎች ይበልጥ በመጉዳት በህይወት የመቆየት እድላቸውን በእጅጉ ሊያጠበው እንደሚችል ቢገመትም ከነዚህ መረጃዎች ተነስቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተረጋገጠ ውሳኔ ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ እንደሚሆን ይነገራል።
ከታች በምስሉ እንደሚታየውም ቫይረሱ አጠቃላይ የሞት ምጣኔው እድሜያቸው በገፉ ሰዎች ላይ እና ተጨማሪ የጤና ችግር በተመዘገበባቸው ሰዎች ላይ አደገኛ በመሆኑ የቫይረሱን ስርጭት በሚቻለው አቅም በመቆጣጠር የሞት መጠኑን መቀነስ እንደሚቻል ከማዕከሉ በወጣው መረጃ ማየት ይቻላል፡፡ ቫይረሱ በተለይም ከመተንፈሻ አካል ጋር የተያያዘ ችግር ያለባቸውን እና የካንስር በሽታ ያለባቸውን ሰዎች ይበልጥ በመጉዳቱ እነዚህ ኬዞች ላይ ትኩረት በማድረግ እና አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት መሞከር ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡
የኮሮና ቫይረስ የመተንፈሻ አካል ችግርን የሚያመጡ ተህዋሲያን ውስጥ የሚመደብ አንደመሆኑ መጠን በዚህ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች በሚያስሉበትና በሚያስነጥሱበት ወቅት የሚያወጧቸው ጥቃቅን ጠብታዎች (droplets) በሽታው ከሰው ሰው እንዲተላለፍ ዋና ምክንያት በመሆናቸው፤ ስናስልና ስናስነጥስ አፍንጫና አፋችንን በሶፍት ወይም በክርናችን በመሸፈን፤ እጃችንን ሳንታጠብ ፊታችንን ባለመንካት እንዲሁም ከታመሙ ሰዎች ጋር የቀረበ ንክኪ ባለማድረግ በሽታውን በሚገባ መከላከል እንችላለን።
በቻይና የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል የተሰራውን የምርምር ውጤት በዚህ ቻርት ይመልከቱ
ቢቢሲ
የዓለማችን ፈጣኑ ሱፐር ኮምፒውተር "Summit" የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለማቆም የሚያግዝ አዲስ መላ አግኝቷል
************************
ወቅታዊው የዓለማችን አደጋ COVID-19 የስርጭት መጠኑ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ በመላው ዓለም የሚገኙ የምርምር ተቋማትን በእጅጉ ያሳሳበ ጉዳይ ነው፡፡ አብዛኞቹ በእነዚህ የምርምር ተቋማት የሚሰሩ ሳይንቲስቶች በኮሮናቫይረስ ዙሪያ የሚያደርጉት የምርምር ስራ ቅልጥፍና የታከለበት ቢሆንም ከእነሱ ፍጥነት በላይ ቫይረሱ የሚሰራጭበት ሁኔታ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ብዙዎችን ያሳሳበ ነው፡፡
ይሁንና "Summit" ለተሰኘው ፈጣን ሱፐር ኮምፒውተር ክብር ይግባውና ምናልባት ከዚህ በኋላ ብዙ ወራቶችን ሊወሰድ የነበረው የተሳካ የምርምር ውጤት በዚሁ ኮምፒውተር የተነሳ ሊያጥር ችሏል፡፡ ሱፐር ኮምፒውተሩ በተገጠሙለት የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ግብዓቶች አማካኝነት በሺዎች የሚቆጠሩ ማስመሰያዎችን (simulations) በማንቀሳቀስ ቫይረሱ የሚያርፍባቸውን ተጠቂ ህዋሳት በመመርመር የትኞቹ የመድኃኒት ውህዶች (drug compounds) ቫይረሱን ማቆም እንደሚችሉ ፍንጭ የሰጠ ነው፡፡ ሱፐር ኮምፒውተሩ ይህን ሰፊ ትንተና ሲያደርግ በጥቅሉ 77 የሚሆኑ ኬሚካሎችን ወይም የመድሃኒት ውህዶችን መለየት የቻለ ሲሆን በጥቅሉም ውጤታማ የሆነ የክትባት መድሃኒት ለመስራት በሚደረገው ጥረት ላይ መልካም ጅምር እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
ኦክ ሪጅ የተሰኘው ታዋቂ የምርምር ተቋም በአጋርነት የሰራው ይህ ጥናት በፈረንጆቹ ጥር ወር ላይ በተሰራው የኮሮናቫይረስ spike protein መለያ ጥናት ላይ ተመርኩዞ የተከናወነ ሲሆን፤ ይኸውም ቫይረሱ ሰዎችን በሚያጠቃበት ጊዜ በሚያርፍባቸው ህዋሳት ላይ የሚፈጠረውን የመባዛት እና የመሰረጨት መጠን የሚጠቁም ነበር፡፡ ታዲያ ተመራማሪዎቹ ሱፐር ኮምፒውተሩን በመጠቀም እንደተረዱት የተጠቀሟቸው ብዛት ያለቸው ማስመሰያ ውህዶች በቫይረሱ spike protein ላይ በመጣበቅ ቫይረሱ በማረፊያ ህዋሳት ላይ የሚኖረውን ስርጭት መግታት እንደሚቻልና፤ ከዚህ ውስጥም ከ1 እስከ 77 የሚደርሱት የኬሚካል ውህዶች አስገራሚ ውጤት እንደነበራቸው ለመረዳት የቻሉበት ነው፡፡
በዚህ ፍሬያማ ጥናት ላይ ምርምሩን በበላይነት የመሩት የኦክ ሪጅ ብሄራዊ ላብራቶሪ ዳይሬክተር ጄርሚ ስሚዝ ግኝቱ ኮሮናቫይረስን ማከም የሚችል መድሃኒተ አገኘን ማለት ባይቻልም ክትባቱን ለመስረት በምናደርገው ጥረት ላይ የተሻለ እርምጃ የተራመድንበት ነው ብለዋል፡፡
የምርምር ስራውን ሲያቀላጥፍ የነበረው "Summit" ሱፐር ኮምፒውተር በ2019 በአሜሪካ የኢነርጂ ዲፓርትመንት እና በIBM አማካኘነት የተሰራ የዓለማችን ፈጣኑ ሱፐር ኮምፒውተር ሲሆን፤ በሰኮንድ 200 ኳድሪሊዮን (15 ዜሮዎችን የሚስከትል) ስሌቶችን ኮምፒውት በማድረግ መሰል ጥናቸን የሚያቀላጥፍ ወደር የማይገኝለት ቴከኖሎጂ ነው፡፡ ኮምፒውተሩ 200 petaflops አጠቃላይ አቅም ያለው በመሆኑ ፈጣን ከሚባሉት ላፕሎቶፖች አንድ ሚሊዮን እጠፍ ስራውን ማከናወን እንደሚችል ይነገራል፡፡
ለበለጠ https://edition.cnn.com/2020/03/19/us/fastest-supercomputer-coronavirus-scn-trnd/index.html
የኢትዮጵያ የኮቪድ-19 መቆጣጠሪያ ሥርዓት በይፋ ስራ ጀመረ
========================
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭት ያለበትን ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ አዳዲስ መረጃዎች በየጊዜው ይፋ የሚያደርግ የመቆጣጠሪያ ሥርዓት በማበልጸግ ለኢፌዲሪ የጤና ሚኒስቴር በትናንትናው ዕለት አስረክቧል፡፡
ኤጀንሲው ያዘጋጀው “የኢትዮጵያ የኮቪድ-19 መቆጣጠሪያ ሥርዓት” የበሽታው ምልክት የታዩባቸው ወይም ስጋት ያደረባቸው ዜጎች ጥቆማ የሚሰጡበት ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ የኮሮኖ ቫይረስ በሽታን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን አሳሳቢ ችግር በተቀናጀ መልኩ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎችን በቀጥታ እንዲመዘገቡ የሚያስችል መሆኑን የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው በርክክቡ ጊዜ ተናግረዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት የመቆጣጠሪያ ሥርዓቱ ህብረተሰቡ በኮቪድ-19 በሽታ ላይ ያለውን ግንዛቤ የሚያሳድጉና ወቅታዊ መረጃዎችን የሚሰጥ ከመሆኑም ባሻገር የበሽታው ምንነት፣ የበሽታው ምልክቶች፣ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዘዴዎቹ እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን የሚያቀርብ ነው ብለዋል፡፡
ፕላትፎርሙ ከችግሩ አንገብጋቢነት አንጻር ኤጀንሲው እንደ ተቋም ምን ማድረግ አለብኝ በሚል በአጭር ጊዜ ውስጥ የበለጸገ መሆኑን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ ፕላትፎርሙ በአማረኛ እና በእንግሊዘኛ የቀረበ ሲሆን በቀጣይ ሌሎች ተጨማሪ ቋንቋዎች በሲስተሙ እንደሚካተትበት ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ተናግራዋል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው በመንግስት እየተወሰደ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት የመከላከል ሥራን ለማገዝ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አዘጋጅቶ ባቀረበው “የኢትዮጵያ የተቀናጀ የኮቪድ-19 መቆጣጠሪያ ሥርዓት” ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡ ሥርዓቱ ለህብረተሰቡ በበሽታው ዙሪያ ወቅታዊ መረጃ እና አገልግሎት ለመስጠት እየተደረገ ያለውን ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ እንደሆነም ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ቫይረሱን ለመከላከል በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን አስተዋጽ ማድረጉን የገለጹት ሚኒስትሯ ቫይረሱን ለመግታት ቴክኖሎጂው ጠቃሚ መሆኑ ባያጠያይቅም ውጤታማ መሆን የሚቻለው ቴክኖሎጂውን በአግባቡ መጠቀም ሲቻል መሆኑን አንስተዋል፡፡
የበሽታው ምልክት የታዩባቸውም ሆነ ማንኛውንም ጥንቃቄ የሚጠይቁ ምክሮችን የሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች በፕላትፎርሙ የተቀመጠውን የነጻ የስልክ መስመር በመደወል መረጃ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ ዜጎች በአቅራቢያቸው ስለሚገኙ ሆስፒታል፣ ፋርማሲ ወይም የፖሊስ ጣቢያ መረጃ እንዲያገኙ የሚያስችል ሥርአት መሆኑ ተገልጿል፡፡
ወደ ፕላትፎርሙ ለመግባት ይህን ሊንክ መጫን ይችላሉ
http://www.etwisdom.gov.et/covid-19
ምንጭ፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ
በኮሮና የተስተጓጎለውን ትምህርት ማገዣ መንገዶች
=======================
የኮሮና ቫይረስ በጉዳት እጆቹ ከጎበኛቸው መደበኛ የህይወት እርምጃዎቻችን መካከል ትምህርት ይገኝበታል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ የዓለማችን ሀገራት ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፤ ተማሪዎችም በቤታቸው ይገኛሉ፡፡ ታድያ በነዚህ ወቅቶች ልጆች ከትምህርታቸው እንዳይርቁ የመማሪያና አጋዥ መፅሐፍቶችን እንዲያነቡ ማድረግ ተገቢና ላለንበት የትምህርት ስርዓትም ቀዳሚው ምርጫ መሆን ያለበት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ለልጆችም ሆነ ወላጆች ጠቃሚ የሆኑ የመማሪያ ድረ-ገፆችን ልናስተዋውቃችሁ ወደድን፡፡
BBC Bitesize ( bbc.co.uk/bitesize )
ይህ ገፅ በሁሉም የዕድሜ ክልል እና ትምህርት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ተማሪዎች የሚሆኑ ትምህርቶችን ይዟል፡፡ የተለያዩ የትምህርት ዓይነቶችን አካቶ ከመያዙም በተጨማሪ በአንፃራዊነት ቀለል ብሎ ተቀምጧል፡፡
BBC Teach ( bbc.co.uk/teach/live-lessons )
እንደ ዩትዩብ ካሉ ምንጮች የሚገኙ የቪዲዮ ምስሎች ለልጆች እጅጉን ጠቃሚ ሊሆኑ ቢችሉም ቁም ነገሩን ለይቶ ማውጣት አዳጋች ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ BBC Teach ለልጆች የሚበጁ የቪዲዮ ምስሎችን አደራጅቶ የያዘ መሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ ገፁ ሌሎች ለተማሪዎች የሚጠቅሙ የቢቢሲ ዝግጅቶችን እንዲከታተሉ የሚያስችልና ስትከታተሏቸው የነበሩ ምስሎችንም እየተከታተለ መረጃ የሚሰጥ ነው፡፡
Khan Academy ( khanacademy.org )
በKhan Academy የሚገኙት ማንኛውም የትምህርት ግብዓቶች በነፃ ከመቅረባቸውም ባሻገር ተማሪዎች መሻሻላቸውን እንዲከታተሉ ያግዛል፡፡ ከድረ-ገፅ በተጨማሪ በስልክ መተግበሪያዎች በኩልም መከታተል ያስችላል፡፡
Duolingo ( duolingo.com )
Duolingo በተለይ ሌሎች ቋንቋዎችን መማር በሚሹ ሰዎች ዘንድ ታዋቂ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ልጆች በቋንቋ ትምህርታቸው ላይ እንዲሻሻሉ ጥሩ እገዛን የሚያደርግም ነው፡፡ ድረ-ገፁ እገዛውን የሚጀምረው ልጆች ያሉበትን የቋንቋ ደረጃ በመገምገም ሲሆን በመቀጠልም ቃላት እና ሀረጋትን በማስተዋወቅ እንዲሁም ፈተናዎችን በመስጠት ይረዳቸዋል፡፡ Duolingo የንግግር እና የፅሁፍ ችሎታን የሚያዳብሩ ትምህርቶችን ሲያቀርብ ፈጣን እና የገንዘብ ፍጆታውም እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ እንደ Khan Academy ሁሉ ይህ ገፅም በስልክ መተግበሪያ አማካኝነት አገልግሎቱን ያቀርባል፡፡
The Artful Parent ( artfulparent.com )
ይህ ገፅ ከተለምዶው የድረ ገፅ መማር ማስተማር ሂደት በተለየ ልጆችን እያዝናኑ የፈጠራና ችሎታቸውን በሚያዳብሩና የአስተሳሰብ አድማሳቸውን በሚያሰፉ ሀሳቦች የተሞላ ነው፡፡ ስዕሎችን ከመሳል ቅርፃቅርፆችን እስከመስራት ባሉ እና ሌሎችም እንቅስቃሴዎችን ልጆችን ሳይጫን ያግዛል፡፡ በተጨማሪም ፈጠራና በራስ መተማመንን ማሳደግ በሚቻልበት መንገድ ላይ ምክርን የሚሰጥ ሲሆን በመደበኛ ትምህርታቸው ላይ የሚረዷቸው እና መነሳሳትንም የሚለግስ ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ ድረ-ገፆች ጠቃሚነታቸው ባይካድም ለኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች የሚሆነውን መምረጥ ግን አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይም እነዚህ ትምህርቶች በሌላ ሀገር የትምህርት ስርዓት ላይ ተመስርተው የሚሰጡ ከመሆናቸው ጋራ በተያያዘ ከእኛ ሀገር የትምህርት ስርዓት የተለዩ ሊሆኑ ስለሚችሉ ለተማሪዎች የሚስማሙትን የትምህርት አይነቶች እና አሰጣጥ መንገዶች መርጦ መውሰዱ ለጥያቄ መቅረብ የለበትም፡፡
ምንጭ፡ techradar
የኮሮና ወረርሺኝ እና የኢውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው ተስፋ ሰጪ እርዳታ
=======================
የኮሮና ቫይረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ መስፋፋቱን ተከትሎ ብዙ ታላላቅ ኢንዱስትሪዎች ምርት ስጠት ማቆማቸው ይታወቃል፡፡ አሁን ታድያ እነዚህ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ እጥረት እየተከሰተባቸው ያሉ የህክምና ዕቃዎችን ለማምረት እንቅስቃሴ ላይ ናቸው፡፡
ግዙፉ የመኪና አምራች ኩባንያ ፊያት ቼስለር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እጥረት የተከሰተበትን የፊት ማስክ ማምረት እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ በዚህ አንድ ወር ውስጥም አንድ ሚሊዮን የፊት ማስኮችን በማምረት ሀገራት ውስጥ በሚገኙ ሆስፒታል፣ ክሊኒክ፣ ፖሊስ ጣብያ እና እሳት አደጋ መከላከል ለሚሰሩ ሰራተኞች ማሰራጨት እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ ይህን የምርት ለውጥ ለማድረግ ፊያት ቼስለር ብቸኛው የመኪና አምራች አይደለም፡፡ ሌሎችም በእሲያ አውሮፓ እና አሜሪካ እሚንቀሳቀሱ የመኪና አምራቾችም በተመመሳሳይ እጥረት የተከሰረተባቸውን የህክምና ቁሳቁሶችን ለማምረት በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ ባሳለፍነው ማክሰኞ ፎርድ ከጀነራል ኤሌክትሪክ እና 3ኤም ጋር በመተባበር የፊት መከለያዎችን እና የትንፋሽ መሳሪያዎችን (ventilator) ለማምረት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ፎርድ በአሁኑ ሰዓትም ቢሆን ለሆስፒታል ሰራተኞች ይሆን ዘንድ የፊት መከላከያዎችን በማምረት ላይ ሲሆን 75 ሺህ ያህሉን በዚህ ሳምንት ብቻ እንደሚያመርት ገልጿል፡፡
ዓለም አቀፍ እጥረት የተከሰተባቸው እነዚህን የህክምና ቁሳቁሶች ለማምረት እና እርዳታ ለመለገስ ከተሰናዱት ሌሎች የዘርፉ ተቋማት ውስጥ ኒሳን፣ ቴስላ፣ ማክላረን እንዲሁም የፎርምዩላ 1 መኪና ውድድር ተሳታፊ ቡድኖች ይገኙበታል፡፡ ከመኪና አምራች ኢንዱስትሪዎችም በተጨማሪ እንደ ዳይሶን፣ እና ኤርባስ ያሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የስራው ተካፋይ ለመሆን ከመንግስት አካላት ፍቃድ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡
ሆኖም ይህ መንገድ አልጋ በአልጋ እንደማይሆን የሚጠቁሙ ባለሙያዎች አሉ፡፡ የትንፋሽ መሳሪያዎች አምራቹ ሀሚልተን ሜዲካል ሀላፊ የሆኑት ጄምስ ሀልክ መሳሪያዎቹ ከፍ ያለ ዕውቀትን የሚጠይቁ ናቸው ይላሉ፡፡ እንደ እርሳቸው ከሆነ እነዚህ መሳሪያዎች ከቁሳዊ ይዘታቸው ባሻገር ብዙ ሶፍትዌሮችን የሚፈልጉና በውስጥ ከሚካተቱት ግብዓቶች መካከል አንዱም እንኳን በትክክል አለመስራት ሙሉ መሳርያውን ጥቅም አልባ ያደርገዋል፡፡
ሌሎች ኢንዱስትሪዎች የህክምና ቁሳቁሶችን እንዲያመርቱ ከመንግስታት እና ልዩ ልዩ ፖለቲከኞችም ከፍተኛ ፍላጎት እየታየ ይገኛል፡፡ እየአሜሪካን የምግብ እና መድሃኒት አስተዳደር (FDA) በገበያው ላይ ያለውን እጥረት እንዲቀርፉ በማሰብ ቁሳቁሶቹን በማምረት ረገድ ያለውን የፍቃድ አሰጣጥ ስርዓት ማሻሻሉን አስታውቋል፡፡
ምንጭ፡ Drivetribe፣ BBC እና The Guardian
!ሰበር ዜና! የኮሮና ቫይረስን በሳይንሳዊ ምርምር በተደገፈ የሀገር በቀል እውቀት ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር በማቀናጀት ቫይረሱን ለማከም የተሰራው መድሃኒት መሰረታዊ የምርምር ሂደት በማለፍ ተደጋጋሚ የቤተ ሙከራ ሞዴሊንግ ሂደቶችን በስኬት ማለፉን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ምርምሩ የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ መከሰቱ ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ ከተለያዩ በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጪ ከሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ተደጋጋሚ የምርመር ሂደት አልፎ ወደ ምርት እና ቀጣይ የእንስሳት ፍተሻ እና ክሊኒካል ፍተሻ ስራዎች እንዲሸጋገር ተደርጓል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር ኢንጂ.)፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰና ከኢትዮጵያዊያን የባህል ሃኪሞች ጋር እና የህክምና ተመራማሪዎች ጋር በመሆን የሀገር በቀል እውቀቶችን በሳይንሳዊ ሂደቶች በማሳለፍ ለዘመን አመጣሹ ኮሮና ቫይረስ( ኮቪድ -19) ወረርሽኝ ህክምና የተዘጋጀውን መድሃኒት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችላቸውን ስራ በመስራት ላይ ይገኛሉ።
መድሃኒቱ የመከላከል አቅም የሚጨምር፣ መርዛማነት የሌለው እና አዋጭነቱ የተረጋገጠ ነው፡፡
የምርምር ሂደቱ ተጠናቅቆ ወደ ምርት ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን ዝርዝር መረጃዎችን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ እንደሚሰጥ ተነግሯል፡፡
ምንጭ፡ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
ስለኮሮና እገዛ የሚሰጥዎ የስልክ መተግበሪያ (mobile app)
====================
በአሁኑ ሰዓት ለኢትዮጵያና መላው ዓለም ትልቅ ስጋት ስለሆነው የኮሮና ቫይረስ መረጃ የሚሰጥ የስልክ መተግበሪያ (mobile app) በተቋማችን ሰራተኞች ተሰርቶ ቀርቦልዎታል፡፡ መተግበሪያው ለእርስዎ እንዲመች ተደርጎ በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ የሚሰራ ነው፡፡ ይህን ጠቃሚ መተግበሪያ እንድሮይድ ስልክ ያላችሁ በሙሉ አውርዳችሁ ትጠቀሙበት ዘንድ ምክራችን ነው፡፡ ለወዳጅ ዘመድዎ ማጋራቱን እንዳይረሱት፡፡