ውሉደ ብርሀን ሰ/ት/ቤ/ት(ጫንጮ)
1.66K subscribers
92 photos
4 files
104 links
ሰንበት ትምህርት ቤት የመልካም ወጣት የመልካም ትውልድ መፍለቂያ ናት! ትውልድን ለበጎ ነገር የምታበቃ ናት፡፡


የጫንጮ ከተማ ደ/ብ/ቅ/እግዚአብሔር አብ እና ደ/ሲ/ቅ/ ኪዳነ ምህረት ቤ/ክ ው/ብ/ሰ/ት/ቤት ቻናል
ለሀሳብ እና አስታየት @weldebirhanbot @ty1921 ይጠቀሙ

ወንድሞች በህብረት ቢቀመጡ መልካም ነው፡፡
Download Telegram
✞በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ
አሃዱ አምላክ አሜን✞
•••✞✞✞•••✞✞✞•••✞✞✞•••
#ምስጢረ_ስላሴ_በጥቂቱ
•••✞✞✞•••✞✞✞•••✞✞✞•••
እኛ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች የእግዚአብሔር አንድነቱ ሦስትነቱን ሳይጠቀልለው፤ ሦስትነቱ አንድነቱን ሳይከፋፍለው በአንድነትና በሦስትነት የሚመሰገን አንድ ሕያው አምላክ በሆነው በእግዚአብሔር እናምናለን፡፡ #አንድ_ሲሆን_ሦስት_ሦስት_ሲሆን_አንድ_በአካል_ሦስት_ሲሆን_በመለኮት_በአንድ_አምላክ_በሆነው_በልዑል_እግዚአብሔር ብቻ ነው የምናምን፡፡ ይህ ምስጢር ስጋን በለበሰ ህሊናችን ተመራምሮ ማወቅ አይቻልም በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ካልሆነ በስተቀር፡፡ ለዛም ነው ቤተ ክርስቲያናችን አምስቱ አዕማደ ምስጢራትን ስታስተምር በመጀመሪያ ምስጢረ ስላሴን መማር እንዳለብን ያስቀመጠችልን፡፡ ምስጢር ማለት፦ እጅግ ጥልቅ፣ የተሰወረ፣ የረቀቀ፤ ከመሆኑ የተነሳ #ምስጢር ይባላል፡፡ #ስላሴ ማለት ደግሞ "ሰለሠ" ወይም ሦስት አደረገ ማለት ሲሆን ትርጉሙም፦ ሦስትነት ማለት ነው፡፡
✞✞✞
#የስላሴ_አንድነትና_ሦስትነት
✞✞✞
☞✞ #የስላሴ_አንድነት ፦ በአገዛዝ፣ በስልጣን፣ ይህን አለም በመፍጠርና በማሳለፍ፣ በህልውና፣ በመለኮት፣ በልብ፣ በቃል፣ በእስትንፋስ፤ በእነዚህ ሁሉ የመለኮት ባህርይ #አንድ ነው፡፡
#የእግዚአብሔር_ሦስትነት_ስንል፦እግዚአብሔር የማይለያይና የማይቀላቀል ፍጹም የሆነ ሦስትነት አለው ማለታችን ነው። የእግዚአብሔር ሦስትነትም፦ በስም፣ በግብር፣ በአካል ነው።
☞✞ እግዚአብሔር #በስም ሦስት ነው ስንል ሦስት የተለያዩ ስሞች አሉት ማለታችን ነው። እነዚህም፦ #አብ #ወልድ #መንፈስ_ቅዱስ የሚባሉት ሲሆኑ እርስ በርሳቸው አይወራረሱም፤ አንዱ በሌላው ስም አይጠራም። "ዘፍ፡1፥2 ፣ ምሳ፡30፥4" ።
☞✞ እግዚአብሔር #በግብር ሦስት ነው ስንል፤ ሦስት የተለያዩ የአካል ሥራዎች አሉት ማለት ነው። እነሱም፦
መውለድና ማስረጽ =የአብ፤
መወለድ=የወልድ፤ መስረጽ =የመንፈስ ቅዱስ፤ የሚሉት ሲሆኑ የአካል ግብር ይባላሉ። "መዝ፡2፥7"
☞✞ እግዚአብሔር በአካል ሦስት ነው ማለት ደግሞ
#ለአብ፦ ፍፁም መልክ፤ ፍፁም ገጽ፤ ፍፁም አካል አለው።
#ለወልድ ፤ ፍፁም መልክ፤ ፍፁም ገጽ፤ ፍፁም አካል አለው ።
#ለመንፈስ_ቅዱስ ፤ፍፁም መልክ፤ ፍፁም ገጽ፤ ፍፁም አካል አለው ማለታችን ነው።
☞✞ የሦስቱ የእግዚአብሔር ስሞች ትርጉም፦
#አብ፦ ማለት አባት ማለት ሲሆን የሚወልድ፤የሚያሰርጽ ወይም የሚያስገኝ ያለ እናት ወልድን የወለደ፤ መንፈስ ቅዱስን ያሰረጸ ነው።
#ወልድ፦ ልጅ ማለት ሲሆን የሚወለድ ወይም ያለ እናት ቅድመ ዓለም፤ ያለ አባት ድህረ ዓለም የተወለደ ነው። "መዝ፡2፥7" #መንፈስ_ቅዱስ፦ ረቂቅ፣ ልዩ፣ ንፁህ ከፍጡራን መናፍስት ሁሉ የተለየ ማለት ነው። "እዮ፡26፥13"
✞በመጽሐፍ_ቅዱስም ከበቂ በላይ ሁኖ ተገልፆልናል፡፡
ዘፍ፡1፥26 ፣ ዘፍ፡11፥7 ፣ ኢሳ፡6፥1-3 ፣ ኢሳ፡48፥16 ፣ ማቴ፡3፥16 ፣ ማቴ፡28፥19 ሉቃ፡1፥35 ፣ ዮሐ፡14፥25 ፣ ማቴ፡21፥18 ፣ 1ኛ ቆሮ፡12፥3 ፣ 2ኛ ቆሮ፡13፥14 ፣ ዘፍ፡3፥22 ፣ ማር፡10፥6 ፣ ማር፡10፥18 ፣ ዘፍ፡1፥3 ፣ ዘፅ፡5፥1 ፣ ዘፅ፡7፥17 ፣ ኢያ፡3፥17 ፣ ሐዋ፡1፥23 ወዘተ.... ከዚህም በላይ ስለአንድነትና ሦስትነታቸው እናገኛለን፡፡


🌾✞✞✞ #​​ቅድስት_ሥላሴ ✞✞✞🌾

#ሥላሴን_ቅድስት_ሥላሴ_እያልን_የመጥራታችን_ምስጢር_ምንድን_ነው

💠 አንዲት ሴት ወይም እናት ልጆቿን አልወለደችም ተብላ አትጠረጠርም፤ ሥላሴም ይህንን ዓለም ፈጥረዋል እናም አልፈጠሩም ተብለው አይጠራጠሩም።

💠 አንዲት ሴት በባሕሪይዋ ልጅን ታስገኛለች፤ ሥላሴም ይህንን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥተው ስለፈጠሩት በሴት አንጻር ቅድስት ተብለው ይጠራሉ።

💠 አንድም ሴት አዛኝ ናት፤ ለታናሹም ይሁን ለታላቁ ትራራለች ሥላሴም እንደዚሁ ለፍጥረት ሁሉ ያዝናሉ፥ ይራራሉ፥ ምህረት ይሰጣሉ።
👉 ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንዲህ ይላል። ምህረታችሁ ከልክም በላይ የበዛ በሴት አንቀጽ ቅድስት ተብላችሁ የተጠራችሁ ሥላሴ በማለት ያመሰጥራል። ስለዚህ ቅድስት ለምን ተባሉ ቢባል በረከታቸው፥ ርህራሄያቸውና፥ ይቅር ባይነታቸው መሆኑን ማወቅ አለብን።

💠 አንድም ሴት ልጇ ቢታመምባት አትወድም፤ ሥላሴም አንድም ልጅ በዲያብሎስ እጅ ተይዞ በኃጢአት እንዲታመሙ አይወዱም፥ አይፈቅዱም በመሆኑም ቅድስት ይባላሉ።

💠 አንድም ሴት ልጅ የልጇን ነውር አትጠየፍም ልጄ ቆሽሿል፥ ተበላሽቷል ብላ ፊቷን አታዞርም። ሥላሴም የሰውን በኃጢአት መቆሸሽ ሳይፀየፉ በቸርነታቸው ጎብኝተዉ ለንስሐ ያደርሱታል።

💠 ይህንን የፅድቅ አየር የምንምገው ያማረውንም ብርሃን የለበስነው ስለ ፅድቃችን ሳይሆን በሥላሴ ቸርነት ነውና ስለዚህም ሥላሴን በሴት አንቀፅ ቅድስት እንላቸዋለን።

💠 አንድም ሴት ልጆቿን ፈጭታና ጋግራ ትመግባቸዋለች ሥላሴም እንደዛው ናቸው። በዝናብ አብቅለው በፀሐይ አብሥልው ፍጥረታትን ሁሉ ይመግባሉ። ስለዚህ ሥላሴ እንደ እናት ሁሉንም ይመግባሉና በሴት አንቀጽ ቅድስት ይባላሉ።

የእግዚአብሔር አብ በረከት፣
የእግዚአብሔር ወልድ ፍቅር፣
የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት፣
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡
✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ልዑል ✞
@yeberhanljoche
@yeberhanljoche
@yeberhanljoche
​​​​እንኳን ለታላቁ ነቢይና ሰማዕት ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

#ቅዱስ_ዮሐንስ_መጥምቅ

ቅዱስ ወንጌል ላይ ከእመቤታችን ቀጥሎ የነ ዘካርያስን ቤተሰብ ያህል ክብሩ6 የተገለጠለት ፍጡር ይኖራል ብሎ መናገሩ ይከብዳል:: #ቅዱስ_ሉቃስ ወንጌሉን የጀመረው በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ ነውና መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ሲል አጽፎታል:: "#ዘካርያስ ካህኑና #ቅድስት_ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)

¤የሰውን እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ መኖር ምን ይረቅ? ለዚህ አንክሮ (አድናቆት) ይገባል!

¤እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ 100 ደግሞ ደርሶ ነበር::

¤ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው የተነገረለት (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::

¤ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው ጸንሳ ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል #እመቤታችን ደጋ ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት የእህትማማች ልጆች ናቸው::

¤የአምላክ እናቱ ስትደርስና "#ሰላም" ስትላቸው መንፈስ ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ ደግሞ ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በሁዋላ ሰኔ 30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ ተፈትቶለታል::

¤ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ #ሰብአ_ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ ሕጻናትን ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት የዘጋ: ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና እሱንም ግደል" አሉ::

¤እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል:: አረጋይት ኤልሳቤጥም ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን እዚያው በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና #ስምዖን ወርደው ቀበሯት::

¤ሕጻኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ #ድንግል_ማርያም ስንት አገር አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ ጋር በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም "እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን "ለአገልግሎት እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት:: ባርካው: አጽናንታውም ተለያዩ::

¤ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በሁዋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ25 (23) ዓመታትም በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም አልቀመሳትም::

¤ከዚህ በሁዋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ ተናገረው:: "ሒድ! የልጀን ጐዳና ጥረግ" አለው:: ነቢያት ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና:: (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1) አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕጻን ነቢየ ልዑል ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. 1:76) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን ተናግሮ ነበርና::

¤ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ #መንፈስ_ቅዱስ እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት: አከበሩት:: ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ: ጸጉሩ የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ: ግርማው የሚያስፈራ ገዳማዊ ነውና::

¤ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሃ ሰበከ:: ለንስሃም በርካቶችን አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ ጌታችን ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ: ምድርን ከነ ልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ' ብሎ ሲመጣ ደነገጠ:: የሚገባበትም ጠፋው::

¤"እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን "ፈቅጄልሃለሁ" አለው:: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት ይሔው እስከ ዛሬም "#መጥምቀ_መለኮት" ሲባል ይኖራል:: ቅዱስ ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው:: ንጉሡም ተቀይሞ ለ7 ቀናት አሠረው::

¤በዚህች ቀንም ልደቱን ባከበረ ጊዜ ወለተ ሔሮድያዳ በዘፈን አጥምዳ አስማለችው:: እርሱም የታላቁን ነቢይ ራስ አስቆርጦ በወጪት አድርጐ ሰጣት:: አበው "እምሔሶ ለሔሮድስ ይብላዕ መሐላሁ - ሔሮድስ መሐላውን በበላ በተሻለው ነበር" ይላሉ:: የቅዱስ ዮሐንስ ራሱ በርራ ስትሔድ አካሉን ግን ደቀ መዛሙርቱ ቀብረውታል:: (ማቴ. 3:1, ማር. 6:14, ሉቃ. 3:1, ዮሐ. 1:6)

¤ርጉም ሔሮድስ አንገቱን ካስቆረጠው በሁዋላ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ራሱ የጸጋ ክንፍ ተሰጥቷት ጌታችን ወዳለበት #ደብረ_ዘይት ሔዳ በፊቱ ሰገደች:: #ቅዱሳን_ሐዋርያት በአዩት ነገር ተገርመው ራሱን እጅ ነሷት::

¤ከዚሕ በሁዋላ ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ለቅዱስ ዮሐንስ ራስ የማስተማር ስልጣን ሰጥቶ አሰናበታት:: በመላው ዓለም ለ15 ዓመታት ስትሰብክ ኑራ በዚህች ቀን ዓረቢያ ውስጥ ዓርፋለች::

<<¤ አስማተ-ዮሐንስ መጥምቅ (የመጥምቁ ዮሐንስ ስሞች) ¤>>
1.ነቢይ
2.ሐዋርያ
3.ሰማዕት
4.ጻድቅ
5.ካሕን
6.ባሕታዊ/ገዳማዊ
7.መጥምቀ መለኮት
8.ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ)
9.ድንግል
10.ተንከተም (የብሉይና የሐዲስ መገናኛ ድልድይ)
11.ቃለ አዋዲ (አዋጅ ነጋሪ)
12.መምሕር ወመገሥጽ
13.ዘየዐቢ እምኩሉ (ከሁሉ የሚበልጥ)

=>ጌታችን #መድኃኔ_ዓለም የመጥምቁ ዮሐንስን ምትረት አስቦ ይቅር ይበለን:: ጸጋውን: በረከቱንና ክብሩንም ያሳድርብን::
#ወስብሐት_ለእግዚአብሔር
https://t.me/yeberhanljoche