ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ
22.4K subscribers
380 photos
97 videos
169 files
284 links
This channel is not operated by Deacon Yaregal Abegaz

https://youtube.com/@yaregalabegaz?si=1f5NHTaQ2l2LbxWQ

“ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።”
— 2ኛ ቆሮ 11፥28
Download Telegram
«ወንድምህን አትናቀው»

ወዳጄ ሆይ! ክርስቲያን ነህን? እንኪያስ በፍጹም ወንድምህን አትናቀው። እህትህን አትናቃት። ምንም ይሁን ምን ሰው አትናቅ። ይህ የምትንቀው ወንድም በተለይ ክርስቲያን ከሆነ ክርስቶስን እየሰደብከዉ እንደሆን አስተውል። "እንዴት?"  ያልከኝ እንደሆንም ይህ የምትንቀው ወንድምህ የክርስቶስ ሕዋስ (ብልት) ኾኗል። የክርስቶስ ሕዋስ ከኾነ ደግሞ እሱን ናቅኸው ማለት ክርቶስን ናቅኸው ማለት ነው። ወንድምህን የምትንቅ ከሆነም በጲላጦስ አደባባይ ጌታን ከገረፉት፣ እራቁቱን ከሰቀሉት፣ ሐሞትንና ከርቤን ቀላቅለው ከሰጡት፣ በፊቱ ላይም ከተፉበት ሰዎች በምንም አትተናነስም። ስለዘህ ወንድምህን ከመናቅ ተጠንቀቅ።

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
የምክር ቃል

ጸሎት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግስት የምታደርስ ቀጭኗ ጎዳና ናት፡፡ ከኃጢአት በመራቅ የሚቀርብ ጸሎት ፍጹም የሆነ ሥራን ይሰራል፡፡ ከባልንጀራህ ጋር በጠብ እኖርክ በእግዚአብሔር ስም ለጸሎት የምትቆም ከሆነ እርሱን እንደመሳደብ ይቆጠርብሃል፡፡ ህሊናህም ከጸሎትህ አንዳች ፍሬ እንደማታገኝ ያስታውቅሃል፡፡ በጸሎት ተመስጠህ ልብህን ወደ እግዚአብሔር አንሳ፡፡

አጠገብህ ስሌለው ሰው ድክመት በተናገርክ ቁጥር ሰይጣን ይዘፍንበት ዘንድ ምላስህን በገና አድርገህ እንደሰጠኸው ቁጥር ነው፡፡ ጥላቻ በልቦናህ ነግሶ ከሆነ የዳቢሎስ እርዳታ እጅግ ታላቅ ይሆናል፡፡

የተንኮል ቃልን አትናገር፤ ለባልንጀራህ ጉድጓድ አትቆፍር፤ ወደ አመንዝራም ሴት አትመልከት የፊቷም ደምግባት አያጥምድህ፡፡ በእርሷ መረብ እንዳትጠመድ ከአንደበቷ ከሚፈልቁት ጣፋጭ ቃሎች ተከልከል፡፡ ከእርሷ ፈጽሞ ሽሽ፡፡

በሰዎች ውድቀት አትደሰት፡፡ በደለኛ እንዳትሆን ጠላትህ ክፉ ሲደርስበት አይተህ ደስ አይበልህ፡፡ ጠላትህ በኃጢአት ተሰነካክሎ ብታይ ስለ እርሱ እዘንለት አልቅስለት፡፡ እጆችህን ለሥራ አትጋቸው፤ ከንቱ ንግግር አትውደድ ለነፍስና ለሥጋ ብሩህነት በሥራ መጠመድን ውደድ፡፡

#ቅዱስ_ኤፍሬም_ሶርያዊ
(ምንጭ፡- ስብከት ወተግሳጽ ዘቅዱስ ኤፍሬም፣ በመ/ር ሽመልስ መርጊያ፣ ገጽ 65-66)
"ቁጡ ሰው ከመኾን ገር ሰው ወደ መኾን ከተለወጥህ፣ ጨካኝ ሰው ከመኾን ቸር ሰው ወደ መኾን ከተቀየርህ [በተግባር] አሳየኝ እንጂ 'ለአያሌ ቀናት ጾምሁ፤ ይህን ወይም ያን አልበላሁም፤ ወይን አልቀመስሁም፤ መሻቴን ገትቻለሁ' እያልህ አትንገረኝ፡፡ [እስከ አሁን] ቁጣን የተሞላህ ከኾነ ለምን ሥጋህን ታስጨንቃለህ?  ቂምና በቀል በልቡናህ ውስጥ ካሉ፥ [ወይንን ሳይኾን] ውኃ የምትጠጣው ለምንድን ነው?  ረብ ጥቅም የሌለውን ጾም አትጹም፤ ጾም ብቻዋን ወደ ላይ አታርግምና፡፡"

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
"ሁሉን የያዘውን ያዙት፤ ሁሉን የሚገዛውን አሠሩት፤ የህያውን አምላክ ልጅ አሠሩት፤ በቁጣ ጎተቱት፤ በፍቅር ተከተላቸው። በሚሸልተው ፊት እንደማይናገር እንደ የዋህ በግ በኋላቸው እየተከተለ ወሰዱት፤ ሊቃነ መላእክት በመፍራት እና በመንቀጥቀጥ ከፊቱ የሚቆሙለትን በአደባባይ አቆሙት፤

ኃጢአትን ይቅር የሚለውን ኃጥእ አሉት፥ በመኳንንት የሚፈርደውንም በእርሱ ፈረዱበት፤ ለሱራፌል ዘውድ የሚያቀዳጃቸውን የሾህ ዘውድ አቀዳጁት፤ ለኪሩቤል የገርማ ልብስ የሚያለብሳቸውን ለመዘበት ቀይ ግምጃ አለበሱት፤ ኪሩቤል በእሳት ክንፍ ተሸፍነው በፊቱ የሚሰወሩለትን እርሱን ክፉ ባሪያ አሥሮ ፊቱን ጸፋው፤ የመላእክት ሠራዊት በፍጹም መደንገጥ የሚሰግዱለት እየዘበቱበት በፊቱ ተንበረከኩ፡፡

ይህን ያህል ትህትና እንደምን ያለ ትህትና ነው? ይህን ያህል ትእግስት እንደምን ያለ ትእግስት ነው? ይህን ያህል ዝምታ እንደምን ያለ ዝምታ ነው? ይህን ያህል ቸርነት እንደምን ያለ ቸርነት ነው? ኃያል ወልድን ፍቅር ከዙፋኑ ሳበው እስከ ሞትም አደረሰው በደል የሌለበትን እንደበደለኛ ሰቀሉት፡፡ ህይወትን የሠራውን ከበደለኞች ጋር ቆጠሩት፤ አዳምን የሠሩ እጆች በመስቀል ቀኖዎት ተቸነከሩ፤  ወዮ በገነት የተመላለሱ እግሮች በመስቀል ተቸነከሩ፡፡

ወዮ በአዳም ፊት የህይወት እስትንፋስን እፍ ያለ አፍ ከሃሞት ጋር የተቀላቀለ የኮመጠጠ መፃፃን ጠጣ፤... ወዮ የወልድን መከራውን የሚናገር ምን አፍ ነው? ምን ከንፈር ነው? ምንስ አንደበት ነው? የፍቁሩ የጌታ ህማማት በተነገረ ጊዜ ልብ ይለያል፤ ህሊናም ይመታል፤ ነፍስም ትንቀጠቀጣለች፤ ሥጋም ይደክማል የማይሞተው ሞተ፤ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ፤ ሙታንን ያድናቸው ዘንድ ሞተ። የምትወዱት ሰዎች ፈጽሞ አልቅሱለት፡፡"

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
#ደስተኛ_መኾን_ትፈልጋለህን?


በርግጥ የተባረከ ቀንን እንዴት ማሳለፍ እንደሚገባ ማወቅ ትሻለህን? አንድ መንፈሳዊ መጠጥ እሰጥሃለሁ፡፡ ይህ መጠጥ ሰካራም ሰዎች እንደሚጠጡትና ንግግርን የሚያጠፋው ዓይነት መጠጥ አይደለም፡፡ ይህ መጠጥ አንደበታችን እንዲኮላተፍ የሚያደርግ አይደለም፡፡ ይህ መጠጥ ዓይናችን በአግባቡ ማየት እንዲሳነው የሚያደርግም አይደለም፡፡

መዝሙር መዘመርን ተማር !

ያን ጊዜም ደስታን በርግጥ ታየዋለህ፡፡ በንቁ ሕሊና በተከተተ ልቡና መዘመር የሚችሉ ሰዎች በቀላሉ በመንፈስ ቅዱስ ይሞላሉ (ያድርባቸዋል)፡፡ የዲያብሎስ መዝሙራትን ብቻ የምታዜም ከኾነ ግን ወዲያው በርኵስ መንፈስ ትሞላለህ (ያድርብሃል)፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
#ቅዱስ_ጎርጎርዮስ_ዘእንዚናዙ ለንስሓ ልጁ #በሰርጓ ቀን መገኘት ባለመቻሉ የላከላት ደብዳቤ

“ልጄ! ለሰርግሽ የነፍስ አባትሽ እኔ ጐርጐርዮስ ይህን ግጥም ስጦታ አድርጌ ልኬልሻለሁ፡፡ አባት ለሚወዳት ልጁ ሊሰጣት የሚችለው የተሻለው ምክርም ይህ እንደ ኾነ አምናለሁ፡፡

“ኦሎምፒያታ ሆይ፥ እውነተኛ ክርስቲያን ለመኾን ያለሽን ፍላጎት ዐውቃለሁና በደንብ አድምጪኝ! እውነተኛ ክርስቲያን እንዲሁ መኾንን የሚመኝ ብቻ ሳይኾን እንደዚያ ለመኾን ሊጥር ይገባዋል፡፡

“ከኹሉም በላይ፥ እግዚአብሔርን ልታከብሪውና ልትወጂው ይገባሻል፡፡ ከእርሱ ቀጥሎም በቅዱስ ወንጌል እንደ ታዘዘው እንደ ጌታችንና መድኃኒታችን [ኢየሱስ ክርስቶስ] አድርገሽ ባልሽን ልታከብሪውና ልትወጂው ይገባሻል፡፡ ስለዚህ እጠይቅሻለሁ! ጌታዋንና ፈጣሪዋን [ኢየሱስ ክርስቶስን] የማታከብርና የማትወድ ሴት በዚህ መንገድ ባልዋን እንዴት አድርጋ ልታከብረውና ልትወደው ትችላለች?

“በጋብቻሽ ውስጥ የትዳር አጋርሽ ይኾን ዘንድ እግዚአብሔር መርጦ ለሰጠሽ ባል ያለሽ መውደድ፣ ስሜትና ፍቅር እጅግ ኃያል ሊኾን ይገባዋል፡፡ ይህ ሰው አሁን የሕይወትሽ ዓይን፣ የልብሽም ደስታ ነውና፡፡

“እግዚአብሔርን እንደምትወጂው፥ ባልሽንም ያለ ቅድመ ኹኔታ ልታከብሪውና ልትወጂው ይገባሻል፡፡ አንቺ ሴት እንደ ኾንሽና ታላቅ የኾነ ዓላማና ግብ እንዳለሽ፥ ኾኖም ዓላማሽና ግብሽ የቤትሽ ራስ ሊኾን ከሚገባው ባልሽ የተለየ እንደ ኾነ ዕወቂ፤ ተረጂም፡፡ ባንቺ ዕድሜ ላይ ያሉት አንዳንዶች ኹለቱም ፆታዎች እኩል [ራስ ናቸው] ብለው የሚሰብኩትን አትስሚ፤ የጋብቻንም ግዴታ [ወይም ዋና ዓላማ] አስቢ፡፡ እነዚህን ግዴታዎች [ወይም ዓላማዎች] ስታውቂ የቤተሰብሽን ተግባራት ለማከናወን እንደ ምን ያለ ትዕግሥትና ጽናት እንደሚያስፈልግሽ ታውቂያለሽና፡፡ እንደ ሚስት እጅግ ጥንካሬን ገንዘብ የምታደርጊውም በዚህ መንገድ ነው፡፡

“ወንዶች እንዴት በቀላሉ የሚቈጡ መኾናቸውን በርግጥ ልታውቂ ይገባሻል፡፡ አይችሉም፤ ብዙ ጊዜም እንደ በረኻ አንበሳ ይኾናሉ፡፡ እንግዲህ ሚስት ጸንታ ልትቆምና የነፍስ ልዕልናዋን ልታሳይ የሚገባት በዚህች ቅጽበት ነው፡፡ አንበሳን የማስለመድ ሥራ መሥራት አለብሽ፡፡ አንበሳን የሚያስለምድ ሰው አንበሳ ሲያገሳ የሚያደርገው ምንድን ነው? ከየትኛውም ጊዜ በላይ ዝም ጸጥ ይላል፡፡ በጸጥታውና በርጋታውም የአንበሳውን ቊጣ ይቈጣጠራል፡፡ በርጋታና በለሆሳስ ኾኖ ያናግረዋል፤ ይደባብሰዋል፤ በቀስታ ያሻሸዋል፤ በጥቂት በጥቂቱም አንበሳው ቊጣውን ይተዋል፡፡

“ባልሽ ስሕተት ሲሠራ በፍጹም ልትነቅፊው፣ ልትንቂው ወይም ልታስነውሪው አይገባም፡፡ በተመሳሳይ መንገድ አንድ መሥራት ያለበትን ነገር ባይሠራና ከዚሁ የተነሣም ውጤቱ ደስ የማያሰኝ ቢኾን፣ ወይም እጅግ የምትፈልጊውና አግባብ ነው ብለሽ የምታስቢውን ባያደርግ እንኳን ባልሽን መናቅ ከአንቺ ልታርቂ ይገባል፡፡ ክፉዎች አጋንንት ዘወትር ቤታችሁን ለማፍረስና የጥንዶች መንፈሳዊ አንድነትን ለመበተን እንደሚሞክሩ ዕወቂ፡፡”

(#ከገብረ_እግዚአብሔር_ኪደ ከትንሿ ቤተክርስቲያን መጽሐፍ የተወሰደ)
#አበው_ስለ_እመቤታችን_እንዲህ_አሉ

"አምላክ ከንጉሥ ሔሮድስ ሴት ልጅ ቢወለድ ኖሮ አልጋ ወራሽ በሆነና ባልተሰደደ ነበር። እርሱ ግን የድሆች ልጅ የሆነችውን ድንግል መረጠ"
#አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ

"ታላቁ ተራራ ሆይ ታናሽዋ ብላቴና የተሸከመችህ ራስህን በሚቻላት መጠን አድርገህላት ነው ፣ ታላቁ እሳት ሆይ ታናሽዋ ብላቴና ተሸክማህ ያልተቃጠለችው ኃይልን ትችል ዘንድ አጽንተሃት ነው "
#ቅዱስ_ኤፍሬም_ሶርያዊ

"ይህ ዓለም የእግዚአብሔርን ልጅ በቀጥታ ከእግዚአብሔር አብ እጅ ለመቀበል የተገባ ሆኖ ስላልተገኘ ፣ ዓለም ከእርስዋ ይቀበል ዘንድ አንድያ ልጁን ለድንግል ማርያም እናት ትሆነው ዘንድ ሠጣት"
#ቅዱስ_አውግስጢኖስ

"ሔሮድስ የማይያዘውን ይይዝ ዘንድ ተነሣ ፣ ዓውሎ ነፋስንም በቤቱ አስገብቶ ሊዘጋ ታገለ"
#አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ

"ጌታ ሆይ እናትህን ማን ብለን እንጥራት? እናት ብቻ እንዳንላት ድንግል ሆና አገኘናት ፣ ድንግል እንዳንላት ልጅ ታቅፋ አየናት። ጌታ ሆይ እናትህን ለመጥራት እንዲህ የሚያስቸግር ከሆነ አንተን ከቶ ምን ብለን እንጠራሃለን??"
#ቅዱስ_ኤፍሬም
#ግንቦት_5

#ቅዱስ_ኤርምያስ_ነቢይ

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ግንቦት አምስት በዚች ቀን የካህኑ ኬልቅዩ ልጅ ታላቅ ነቢይ ኤርምያስ አረፈ። ይህም እውነተኛ ነቢይ የአሞጽ ልጅ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ሦስት ዓመቱ ማስተማር ጀመረ።

ከዚያም በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን ዐሠራ አንዱ የሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥቱ እስከሚፈጸም በአምስተኛው ወር ኢየሩሳሌም እስከ ተማረከችበት ጊዜ ያስተምር ነበር።

ስለ ራሱ እንዲህ ሲል ራሱ ተናገረ የእግዚአብሔር ቃል ወደኔ መጣ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ "በእናትህ ማሕፀን ሳልፈጥርህ ወደድኩህ ከእናትህም ማሕፀን ሳትወጣ መረጥኩህ ለአሕዛብም መምህር አደረግሁህ አለኝ።" ይህም ነቢይ የእግዚአብሔርን አምልኮና ሕጉን በመተዋቸው እንዲህ ሲል የእስራኤልን ልጆች ገሠጻቸው። ተጠበቁ ንስሐም ግቡ የእግዚአብሔር ቁጣው በላያችሁ እንዳይመጣ።

ሁለተኛም እንዲህ ብሎ አስረዳቸው ወደ ፈጣሪያችሁ እግዚአብሔር ካልተመለሳችሁ ያለዚያ የከላውዴዎንን ንጉሥ ናቡከደነጾርን በላያችሁ እርሱ ያሥነሣዋል ይማርካችኋልም እንደቃሉም ሆነ። ሁለተኛም ሕዝቡ ተማርከው ሰባ ዘመን እንደሚኖሩ ትንቢት ተናገረ።

ደግሞ የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ለኩነተ ሥጋ እንደሚመጣና መከራ እንደሚቀበል የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደሚሸጠውና ሠላሳ ብር እንደሚወስድ ተናገረ። ስለ ብዙ ሥራዎችም ተናገረ አይሁድ ግን ሊገድሉት ወደው ገርፈው አሥረው በጒድጓድ ውሰጥ ጣሉት እግዚአብሔርም አዳነው። እርሱ ግን ስለእነርሱ ይለምንና ይማልድ ነበር እግዚአብሔርም ስለ እርሳቸው ወደእኔ አትማልድ እነርሱ ከክፋታቸው አይመለሱምና አለው።

ናቡከደነጾርም የኢየሩሳሌምን ሕዝብ በማረከ ጊዜ ከእሳቸው ጋራ አልማረከውም። ነገር ግን ከምርኮ የቀሩት ወደ ግብጽ አገር ወሰዱት የግብጽን ሰዎች ሲያጠፉአቸው የነበሩ በግብጽ ወንዞች የሚኖሩ አራዊትን በእርሱ ጸሎት እግዚአብሔር አጠፋቸው።

ከዚያም ወደ ባቢሎን አገር ወሰዱት በዚያም የእስራኤል ልጆች ከምርኮ እስኪመለሱ ትንቢት እየተናገረ ሕዝቡን ሲአስተምር ኖረ። የትንቢቱ ወራትም በተፈጸመ ጊዜ አይሁድ በደንጊያዎች ወገሩት ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በነቢዩ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት)
በቤትህ ያለው ዳቦ ለተራበው ሰው የሚውል(ንብረቱ) ነው፥ በልብስ ማስቀመጫህ ውስጥ ያለው የማትጠቀመው ኮት የችግረኛው ገንዘቡ ነው፥ በጫማ ማስቀመጫህ ውስጥ አልፈልገውም ብለህ ሊበላሽብህ የሆነው ጫማ የደሃው ጫማ (ጫማ ለሌለው ገንዘቡ) ነው ፥ ያከማቸኸው ገንዘብ ለድሃው የሚገባው ነው....

ዛፍ በፍሬው ይታወቃል፥ ሰውም በድርጊቱ፡፡ መልካም ስራ መቼም አይጠፋም፡፡ መልካም እርዳታን የሚዘራ፥ ወዳጅነትን ያጭዳል፡፡ ደግነትን የሚተክል ፍቅርን ይሰበስባል፡፡

"ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ ብቻ የለብንም፥ ነገር ግን ካነበብነው ተምረን ማደግ አለብን፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ምንም የማይጠቅም ነገር እንዳልተጻፈ ተገንዘብ፡፡

አሁንም ለጥንካሬ፣ ለመታገስ፣ ለመዳን፣ ለመለወጥ ጊዜ አለህ! ተኝተሃልን? ንቃ! ኃጢአት ሰርተሃልን? እንግዲያውስ  መስራቱን አቁም፡፡

#ቅዱስ_ባስልዮስ_ዘቂሳርያ
ሐኪማችን የሚደክም፤ የሚሰላችም አይደለም፡፡ እልፍ ጊዜ ብንቆስል ያድነናል፤ ስለዚህ ጥበብ በማጣት በአካላችን ላይ ትንሽ ብንቆስልም ሐኪማችን ሁል ጊዜ ሊያድነን ይተጋል፡፡ እርሱ በኤርምያስ እጅ ለተነሳሕያን በተላከ ደብዳቤ ላይ በነቢዩ አፍ ድምጹን ከፍ አድርጎ ‹‹አሁንም መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ፤ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፧ እግዚአብሔርም የተናገረባችሁን ክፉ ነገር ይተዋል›› ይለናል (ኤር ፳፮፥፲፫)፡፡ ስለዚህ ነቢዩ በመሓላ ቃል ‹‹በኃጢአተኛው ሞት አልደሰትም›› ይላል፡፡

ለአዳም ልጆች ሁሉ ተስፋ ቃል ኪዳን እንደ ገባላቸው ወደ በሩ መጥተው ለሚያንኳኩ ሁሉ የእግዚአብሔር በር ሁል ጊዜ እንደ ተከፈተ ነው፡፡ የቸርነቱ ፍቅር በንስሓ ለሚመላለሱት ይደሰታል፤ ስለዚህ እጆቹን ዘርግቶ ይቀበላቸዋል፡፡

ክብሩ ተነሳሕያንን ይረዳቸዋል፤ በእቅፉ ውስጥ መሆን ይቅርታን ያስገኛል፡፡ እርሱ በወንጌል ‹‹ንስሓ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኙ ጻድቃን ይልቅ ንስሓ ስለሚገባ ስለ አንድ ኃጢአተኛ በሰማያት ፍጹም ደስታ ይሆናል›› አለ (ሉቃ ፲፭፥፯)፡

በሰማያት ያሉ መላእክትን ደስ ይላቸዋል፣ የቅዱሳን ማኅበርም ሐሴት ያደርጋሉ፡፡ ጠባቂ መላእክትም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሆሣዕና እያሉ ይዘምራሉ፤ ሊቃነ መላእክትም በኅብረት ድምጻቸውን አሰምተው ይዘምራሉ፡፡

በአስፈሪ ግርማ ሞገስ የገነትን በር የሚጠብቅ ኪሩቤል እናንተ ተነሳሕያን እንኳን ደኅና መጣችሁ ብሎ ይቀበላችኋል፤ እናንተ አዲሶቹ የገነት ወራሾች ናችሁ ብሎ ደመ ማኅተሙን ከመስቀል ይዞ እንደ ሔደ ቀማኛ የምታጓጓዋን የገነት በር ይከፍትላችኋል።

ከሕይወት ዛፍም ትበላላችሁ ትጠግባላችሁም፡፡ የገነት ዛፍ ሕያው ፍሬውን ይሰጣችኋል፡፡ የኤደን አትክልትም ዙርያችሁን ይሞላል፡፡ የበለጸጉ ዛፎችም ይከባችኋል፡፡ በዚያ ከቅዱሳን ጋር ተሰምቶ የማያውቅ ምስጋናን ለአምላካችሁ ታቀርባላችሁ። በዚያ ቅዱሳኖቹ ይጠብቋችኋል፤ ባሸበረቀው አዳራሽ ውስጥ ታላቅ ደስታ በዚያ ይጠብቋችኋል፡፡ እናንተም የዚህ ታላቅ በዓል ታዳሚዎች ትሆናላችሁ፡፡

በዚያ በብርሃን በተሞላ ግዛት ውስጥ ብዙ ቅዱሳን አሉ፤ እናንተም ለቅዱሳን የሚሰጥ አክሊል ተዘጋጅቶላችሁ እየጠበቃችሁ ነውና። እንግዲህ ጠቢባን ሁኑ፤ ከንስሓ ወደ ኋላ በመመለስ ከዚህ ክብር አትራቁ፡፡

እናንተ በንስሓ ውስጥ ያላችሁ ሰዎች ሆይ እንግዲህ ሙሽራው እስኪመጣ ድረስ መጠበቅ፣ መዘግየትም የለባችሁም፡፡ ይልቁን ለሰርግ የሚገባውን ልብስ፤ የክብር ካባ ለብሳችሁ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ እንጂ፡፡ ወደ ሰርጉ ለመግባት የሙሽራውን ነጭ ልብስ ውሰዱ፡፡ የሙሽራው መምጫ ሳይደርስ የመብራቱን ዘይት አዘጋጁ፡፡ የመለከቱ ድምፅ ሳይሰማ በፊት በእጃችሁ ያለውን አሳዩ፡፡

እናንተ ኃጥአን ሆይ ዕዳችሁ የተተወላችሁ ይመስል በቸልታ መቀመጥን፣ ስንፍናንስ ማን አስተማራችሁ? እርሱ ዝም ብሎ ቢያያችሁ ትዕግሥቱን ሲያሳችሁ ነውና እንግዲህ በንስሓችሁ ዕንባ ነፍሳችሁን አድኑ፤ መጸጸታችሁንም አሳዩት፡፡ ይቅር ባይነቱ ታግሦአችኋልና እንግዲህ ዲናሩን ከነ ትርፉ መልሱለት፡፡

ጌታ ሆይ በሁሉም መንገድ ቸርነትህ ትጠራኛለች በቃልኪዳኖችህም ሁሉ ክብርህ እና ፈቃድህ ሕይወት እንድናገኝ ነው፡፡ ጌታ ሆይ ታላቅ የሆነ ቸርነትህን ለሰው ልጆች ሁሉ ሰጠህ። ለምዕመናንም፣ ለዘማውያንም መረብህን ዘረጋህ፡፡ አመጸኛው ሰላማዊ ይሆን ዘንድ፤ የጠፉትም ይገኙ ዘንድ፡፡ ለድኅነታችን ይሆን ዘንድ በታላቅ ይቅርታው በቸርነት ዓይኖቹ አየን፡፡

ጌታ ሆይ ወፍ ከአዳኝ ወጥመድ እንደምታመልጥ እኔም ከኃጢአት አመለጥኩ፤ በመስቀልህ ሥርም መሸሸጊያ ጎጆን ሠራሁ፡፡ ወደዚህ ሥፍራ አሳች ከይሲ ሊደርስ አይችልምና፡፡

ጌታ ሆይ እርግብ ከመረብ እንደምትወጣ ከኃጢአት ወጥመድ ወጣሁ። በመስቀልህም ሥር ሆኜ ወደ ላይ እወጣለሁ፡፡ በዚያ ክፉ ጠላት የሆነ ዘንዶ ሊያገኘኝ አይችልምና፡፡ በዚያ ሆኜ ሕይወት የሚሰጠውን ስምህን የልጅህንም ስም የእውነት መንፈስ የመንፈስ ቅዱስንም ስም አመሰግናለሁ፡፡

#ቅዱስ_ኤፍሬም

(በእንተ ንስሐ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ወ አፍርሐት ገጽ 35-38 ➛በዲ/ን መዝገቡ የተተረጎመ)
"አንተ ራስህ ለገዛ ወንድምህ ጨካኝና ይቅር የማትል ኾነህ ሳለስ እግዚአብሔር እንዲራራልህና እንዲምርህ እንዴት መለመን ይቻልሃል?

"ባልንጀራህ ምናልባት ንቆህ ሊኾን ይችላል፡፡ አዎ! አንተ ግን እግዚአብሔርን ኹልጊዜ እንደናቅኸው ነው፡፡ በባልንጀራና በእግዚአብሔር መካከልስ ምን ንጽጽር አለ? ባልንጀራህ ምናልባት ጉዳት ሲደርስበት ሰድቦህ ይኾናል፤ አንተም በዚህ ተበሳጭተህ ይኾናል፡፡ አንተ ግን ምንም ሳይጎዳህና በአንተ ላይ ክፉ ሳያስብ ይልቁንም ዕለት ዕለት በረከቱን እየተቀበልክ እያለ እግዚአብሔርን ሰድበኸዋል፡፡ እንግዲህ ተመልከት! ነቢዩ፡- “እመሰ ኃጢአተኑ ትትዐቀብ እግዚኦ መኑ ይቀውም - አቤቱ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ ማን ይቆማል?” ብሎ እንደ ተናገረ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ የምንፈጽመውን በደል ቢመረምር ኖሮ አንዲት ቀንስ እንኳን በሕይወት መቆየት አንችልም ነበር (መዝ.129፡3)፡፡

እያንዳንዱ በደለኛ ሰው ለራሱ የሚያውቀውንና ሌላ ሰው የማይመሰክርበትን እግዚአብሔር ብቻዉን ግን የሚያውቀውንስ ይቅርና የተገለጠውና ሰው ኹሉ የሚያውቀው ኃጢአታችንን እንኳን እግዚአብሔር ቢቈጣጠር ኖሮ ከእነዚህ ኃጢአቶች በኋላ የምንጠብቀው ምንድን ነው? እግዚአብሔር ንዝህላልነታችንንና ጸሎት ስናደርስ የምናሳየው ግድየለሽነታችንን፣ ሠራተኞች ለአሠሪዎቻቸው ወታደሮችም ለአለቆቻቸው ጓደኛሞች ለጓደኞቻቸው የሚያሳዩትን ፍርሐትና ክብር ያህልስ እንኳን ለጸሎትና ለልመና በፊቱ በቆምን ጊዜ አለማሳየታችንን ቢቈጣጠር ኖሮ ምን ነበር የምንኾነው?

አንተ ከጓደኛህ ጋር ስትነጋገር ለምታደርገው ማንኛውም ነገር ትጠነቀቃለህ፡፡ ስለ በደሎችህ እግዚአብሔርን ስትጠብቀው፣ ለብዙ መተላለፎችህ ይቅርታን ስትጠይቀው፣ ሥርየትን ለማግኘት ስታሳስበው ግን [በፊቱ ላይ] ኹልጊዜ ግድየለሽ ትኾናለህ፡፡ ጉልበትህ በምድር ላይ ተንበርክኮ ሳለ ልቡናህ ግን እዚህም እዚያም፣ በገበያ ሥፍራም፣ በቤት ውስጥም ይዋልላል፤ ከንፈርህ በከንቱና እንዲሁ ያነበንባል፤ ይህን የምንፈጽመው ደግሞ አንዴ ወይም ኹለቴ ሳይኾን ኹልጊዜ ነው።

እንግዲህ እግዚአብሔር ይህን ብቻ እንኳን ቢመረምር ይቅርታን ወይም ምሕረትን እንደምናገኝ ታስባለህን? በእውነት አይመስለኝም!"

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

#ትምህርት_በእንተ_ሐውልታት_መጽሐፍ
ገብረ እግዚአብሔር ኪደ የተረጎመው
ከገቢረ ኀጢአት ሳይወጡ አዲስ ዓመት ሲመጣ መደሰት፣ ብዙ መብልና መጠጥ ማዘጋጀት፣ አዲስ ልብስም መልበስ ጥቅም የለውም፡፡ ነፍሳችን በኀጢአት እየተጨነቀች፣ ነፍሳችን ተርባና ተጠምታ ሳለ፣ የተዳደፈ የኀጢአት ልብስም ተጆቡና ሳለ አዲስ ዓመት ማክበር ለእኛ ምን ጥቅም ይሰጠናል? እንዲህ ከገቢረ ኀጢአት ሳይወጡ አዲስ ዓመትን ማክበር ማለት ለእኔ እንደ ልጆች የዕቃ ዕቃ ጨዋታ ነው፡፡

ክርስቶስ ከዚሁ ሥራ አውጥቶናል፡፡ ከሕፃንነት አዕምሮ ወደ ማወቅ አሸጋግሮናል፡፡ ከምድራውያን ለይቶ ከሰማያውያን ጋር ደባልቆናል፡፡ ስለዚህ “መልካሙን ሥራችሁን ዐይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” እንደ ተባለ አፍአዊ ሳይኾን መንፈሳዊውን ብርሃን ልናበራ ይገባናል (ማቴ.5፡16)፤ በአዲሱ ዓመት፡፡ ይህም ብርሃን ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን የሚያስገኝ ነው፡፡

ወዳጄ ሆይ! ቤቱ ቆሽሾ ሳለ ውጫዊ በሩን ብቻ ለማሽቀርቀር ለምን ትጨነቃለህ? ነፍስህ በኀጢአት ተዳድፋ ሳለ ሥጋህን ብቻ ለማስደሰት ለምን ትሮጣለህ? አስቀድመህ ቤቱን (ነፍስህን) ለማስዋብ አትሽቀዳደምምን? አስቀድመህ ለነፍስህ የምታስብ ከኾነ ከሰው እጅ ሳይኾን ከክርስቶስ እጅ ሹመት ሽልማት ትቀበላለህ፡፡ ኹል ጊዜ “የማደርገው ነገር እግዚአብሔር ይከብርበታልን?” ብለህ አስብ እንጂ እንዲሁ በዘልማድ የምትመላለስ አትኹን ብዬ እመክርኻለሁ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲመክረን፡- “እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትኾኑ ወይም ማናቸውም ነገር ብታደርጉ ኹሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” ያለንም ስለዚሁ ነውና በአዲሱ ዓመት በድርጊቶቻችን ኹሉ እግዚአብሔርን ለማክበር እንዘጋጅ (1ኛ ቆሮ.10፡31)፤ አዲስ ዓመት ማክበር ማለት ይኼ ነውና፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
(ሰማዕትነት አያምልጣችሁ መጽሐፍ - #ገብረ_እግዚአብሔር_ኪደ)
ጾም ሙሽሪትን ትመስላለች፤ ሙሽሪትን በሠርግ አዳራሽ ኾነው የሚቀበሏት ሰዎች ቤቱን ያስጌጡታል፤ ይሸልሙታል፡፡ ወደ ሠርጉ አዳራሽ የሚገባውን ሰው የሠርግ ልብስ ለብሶ እንደኾነ፣ የቆሸሸ እንዳልኾነ አይተው ያስገቡታል፡፡ እኛም እንዲኽ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ልቡናችንን በማንጻት፣ ልል ዘሊል ከመኾን በመራቅ፣ የክፋት እርሾን በማስወገድ፣ ከጾም ጋር አብረው የሚመጡትን የሚያጅቧትን መልካም ምግባራትንም ለመቀበል የልቡናችንን ውሳጤ በመክፈት የምግባር እናት፣ የማስተዋል እንዲኹሉም ለሌሎች ምግባራት ኹሉ ንግሥት የምትኾን ጾምን ልንቀበላት ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ይኽን ያደረግን እንደኾነ ታላቅ ሐሴት እናደርጋለን፤ ርሷም ቁስለ ነፍሳችንን ትፈውስልናለች፡፡

በሌላ አገላለጽ ብነግራችኹ ሐኪሞች በአንድ ታማሚ ሰውነት ውስጥ ያለውን ቆሻሻ፣ መርዘኛ ፈሳሽን ማስገድ ሲፈልጉ መጀመሪያ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር ታማሚው ምግብ ከመውሰድ እንዲቈጠብ ነው፡፡ ታማሚው ለጊዜው ምግብን ከመብላት ካልተከለከለ ሓኪሞቹ የሚሰጡት መድኃኒት እንደተፈለገው ውጤት አይሰጥም፡፡

እኛም ቁስለ ነፍስ ቁስለ ሥጋ የምትፈውሰውን ጾም ስንቀበላት ከዚኽ በላይ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስን የምንሻ ከኾነ ልቡናችንን ንጹሕና ንቁ በማድረግ ልንወስዳት ይገባናል፡፡ እንዲኽ ካልኾነ ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ያመዝናል፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
የቤት ዕቃዎችን መግዛት ስንፈልግ፥ በጣም እንጠነቀቃለን፡፡ የሻጮቹን ማንነት አይተን፣ የዕቃዉንም ጥንካሬ አገላብጠን ተመልክተን ነው የምንሸምተው፡፡ ሚስት ስናገባም ከዚህ የበለጠ ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡ የገዛነው ዕቃ ችግር ቢኖርበት ለሸጠልን ሰው መመለስ እንችላለን፡፡ ሚስት ስናገባ ግን ወደ ቤተሰቦቿ መመለስ አንችልም፤ እስከ ዕድሜአችን ፍጻሜ ድረስ ከእኛ ጋር ነው የምትኾነው፡፡ ክፉ ናት ብለን ብንመልሳት፥ በሕገ እግዚአብሔር መሠረት አመንዝራ እንኾናለን፡፡ ስለዚህ ሚስት ስትመርጡ የሀገራችሁን ሕገ መንግሥትን ብቻ አታንብቡ፤ ከኹሉም በፊት ሕገ ቤተ ክርስቲያንን አንብቡ እንጂ፡፡

#ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ_ህይወቱና_ትምህርቱ_በዲያቆን_ያረጋል_አበጋዝ.pdf
214.8 KB
ወደ ቤተ ክርስቲያን ስላልመጡ ምዕመናን

የሚያስጨንቅህ የዚህ ዓለም ጉዳይ አለብህ? እዚህ በምታሳልፈው ጊዜ የእግዚአብሔርን ርዳታና ምሕረት ታገኝ ዘንድ፣ በመረጋጋትና በመጽናናት መንፈስ ሆነህ ትሄድ ዘንድ ስለዚህ ምክንያት ወደዚህ ና፡፡ እርሱ ኃይልሀና ጋሻህ ይሆን ዘንድ፣ በሰማያዊ ሥልጣን በመጠበቅ ለጠላቶችህ ለአጋንንት የማትሸነፍ ትሆን ዘንድ ወደዚህ ወደ ጸጋው ዙፋን ና፡፡ በአባቶች ከሚደርሰው ጸሎት ሱታፌ ካለህ፣ በማኅበር ጸሎት ከተሳተፍክ፣ ቅዱስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ከሰማህ፣ የእግዚአብሔርን ርዳታ ካገኘህ፣ እነዚህን መሣሪያዎች ከታጠቅህ የትም ብትሄድ እንዳንተ ያሉ ሥጋ የለበሱ ጠላቶችህ ክፉዎች ሰዎች ይቅርና ዲያብሎስ ራሱ ፊትህን ማየት አይችልም፡፡ ነገር ግን ከቤትህ እንደ ተነሣህ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሳትመጣ ወደ ገበያ፣ ወደ ሥራ፣ ወዘተ ብትሄድ ብቻህን ያለ ምንም መንፈሳዊ ትጥቅና ጸጋ እግዚአብሔር ስለምትሆን ሁሉም ነገር በአንተ ላይ ይበረታብሃል፤ ጠላቶችህም በቀላሉ ያጠቁሃል

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ_ህይወቱና_ትምህርቱ

#ዲያቆን_ያረጋል_አበጋዝ
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
"ሁሉን የያዘውን ያዙት፤ ሁሉን የሚገዛውን አሠሩት፤ የህያውን አምላክ ልጅ አሠሩት፤ በቁጣ ጎተቱት፤ በፍቅር ተከተላቸው። በሚሸልተው ፊት እንደማይናገር እንደ የዋህ በግ በኋላቸው እየተከተለ ወሰዱት፤ ሊቃነ መላእክት በመፍራት እና በመንቀጥቀጥ ከፊቱ የሚቆሙለትን በአደባባይ አቆሙት፤

ኃጢአትን ይቅር የሚለውን ኃጥእ አሉት፥ በመኳንንት የሚፈርደውንም በእርሱ ፈረዱበት፤ ለሱራፌል ዘውድ የሚያቀዳጃቸውን የሾህ ዘውድ አቀዳጁት፤ ለኪሩቤል የገርማ ልብስ የሚያለብሳቸውን ለመዘበት ቀይ ግምጃ አለበሱት፤ ኪሩቤል በእሳት ክንፍ ተሸፍነው በፊቱ የሚሰወሩለትን እርሱን ክፉ ባሪያ አሥሮ ፊቱን ጸፋው፤ የመላእክት ሠራዊት በፍጹም መደንገጥ የሚሰግዱለት እየዘበቱበት በፊቱ ተንበረከኩ፡፡

ይህን ያህል ትህትና እንደምን ያለ ትህትና ነው? ይህን ያህል ትእግስት እንደምን ያለ ትእግስት ነው? ይህን ያህል ዝምታ እንደምን ያለ ዝምታ ነው? ይህን ያህል ቸርነት እንደምን ያለ ቸርነት ነው? ኃያል ወልድን ፍቅር ከዙፋኑ ሳበው እስከ ሞትም አደረሰው በደል የሌለበትን እንደበደለኛ ሰቀሉት፡፡ ህይወትን የሠራውን ከበደለኞች ጋር ቆጠሩት፤ አዳምን የሠሩ እጆች በመስቀል ቀኖዎት ተቸነከሩ፤  ወዮ በገነት የተመላለሱ እግሮች በመስቀል ተቸነከሩ፡፡

ወዮ በአዳም ፊት የህይወት እስትንፋስን እፍ ያለ አፍ ከሃሞት ጋር የተቀላቀለ የኮመጠጠ መፃፃን ጠጣ፤... ወዮ የወልድን መከራውን የሚናገር ምን አፍ ነው? ምን ከንፈር ነው? ምንስ አንደበት ነው? የፍቁሩ የጌታ ህማማት በተነገረ ጊዜ ልብ ይለያል፤ ህሊናም ይመታል፤ ነፍስም ትንቀጠቀጣለች፤ ሥጋም ይደክማል የማይሞተው ሞተ፤ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ፤ ሙታንን ያድናቸው ዘንድ ሞተ። የምትወዱት ሰዎች ፈጽሞ አልቅሱለት፡፡"

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
#ግንቦት_11

#ቅዱስ_ያሬድ_ካህን_ወማኅሌታይ

ግንቦት ዐሥራ አንድ በዚህች ዕለት የሱራፌል አምሳላቸው የሆነ ኢትዮጵያዊው ማኅሌታይ ያሬድ የተሰወረበት ነው። ይህም ቅድስ ከአባ ጌዴዎን ዘመዶች ወገን ነው እርሱም በኢትዮጵያ አገር ከታነፁ አብያተ ክርስቲያን ለምትቀድም ከአክሱም ካህናት ውስጥ ነው እርሷም አስቀድሞ የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት በውስጥዋ የተሰበከና አምላክን በወለደች በእመቤታችን በከበረች ድንግል ማርያም ስም የከበረች ናት።

ይህም አባ ጌዴዎን ትምህርትን ሊአስተምረው በጀመረ ጊዜ መቀበልም ማጥናትም እስከ ብዙ ዘመን ተሳነው። በአንዲት ዕለትም መምህሩ በእርሱ ላይ ተበሳጭቶ መትቶ አሳመመው። ያሬድም ሸሽቶ ከዱር ውስጥ ገባ ከኀዘኑም ብዛት የተነሣ ከዛፍ ሥር ተጠለለ። ወደ ዛፉ ላይም ትል ሲወጣ አየ ትሉም ከዛፉ እኩሌታ ደርሶ ይወድቅ ነበረ እንዲሁም ብዙ ጊዜ ከአደረገ በኋላ በጭንቅ ከዛፉ ላይ ወጣ።

ቅዱስ ያሬድም የትሉን ትጋት በአየ ጊዜ ወደ መንፈሳዊ መምህሩ ተመልሶ አባቴ ሆይ ይቅርታ አድርግልኝና እንደ ወደድክ አድርገኝ አለው መምህሩም ተቀበለው።

ከዚህ በኋላ በብዙ ልቅሶ ወደ እግዚአብሔር በለመነ ጊዜ ልቡናው ብሩህ ሆኖለት በአጭር ጊዜ የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍትን ተምሮ ፈጸመ ዲቁናም ተሾመ።

በዚያም ወራት እንደ ዛሬ በከፍተኛ ቃል የመዝሙር ማኅሌት የለም ነበር በትሑት እንጂ። እግዚአብሔርም መታሰቢያ ሊአቆምለት በወደደ ጊዜ ከኤዶም ገነት ሦስት አዕዋፍን ላከለት እነርሱም በሰው አንደበት ተናግረውት ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ከእሳቸው ጋራ አወጡት በዚያም ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ የሚያመሰግኑበትን ማኅሌታቸውን ተማረ።

ወደ አነዋወሩ ወደ ምድርም በተመለሰ ጊዜ በአክሱም ዳር ወደ ከበረች ቤተ ክርስቲያን በሦስት ሰዓት ገባ በታላቅም ቃል ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ የጽዮንም ደገኛዋ ሰማይን ፈጠረ። ዳግመኛም እንዴት እንደሚሠራት የድንኳንን አሠራር ለሙሴ አሳየው አስተማረው አለ።

ይቺንም ምስጋና አርያም ብሎ ጠራት። የቃሉንም ድምፅ በሰሙ ጊዜ ንጉሡም ንግሥቲቱም ጳጳሱም ከካህናቱ ሁሉ ጋራ የመንግሥት ታላቆችና ሕዝቡ ሁሉ ወደርሱ ሮጡ ሲሰሙትም ዋሉ።

ከዚያም በኋላ ከዓመት እስከ ዓመት በየክፈለ ዘመኑ በክረምትና በበጋ በመጸውና በጸደይ በአጽዋማትና በበዓላት በሰንበታትም እንዲሁም በመላእክት በዓል በነቢያትና በሐዋርያት በጻድቃንና በሰማዕታት በደናግልም በዓል የሚሆን አድርጎ በሦስቱ ዜማው ሠራ ይኸውም ግዕዝ ዕዝል አራራይ ነው።

የሰው ንግግር የአዕዋፍ የእንስሳትና የአራዊት ጩኸት ከዚህ ከሦስቱ ዜማው አይወጣም።
በአንዲት ዕለትም ቅዱስ ያሬድ ከንጉሥ ገብረ መስቀል እግር በታች ቁሞ ሲዘምር ንጉሡም የያሬድን ድምፅ እያዳመጠ ልቡ ተመሥጦ የብረት ዘንጉን በያሬድ እግር ላይ ተከለው ከእርሱም ደምና ውኃ ፈሰሰ። ያሬድም ማኅሌቱን እስከ ሚፈጽም አልተሰማውም።

ንጉሡም አይቶ ደነገጠ በትሩንም ከእግሩ ላይ ነቀለ ስለ ፈሰሰው የደምህ ዋጋ የፈለግኸውን ለምነኝ ብሎ ለያሬድ ተናገረው ያሬድም ላትከለክለኝ ማልልኝ አለው። ንጉሥም በማለለት ጊዜ ወደገዳም ሔጄ እመነኲስ ዘንድ አሰናብተኝ አለው ንጉሡም ሰምቶ ከመኳንንቱ ጋራ እጅግ አዘነ ተከዘም እንዳይከለክለውም መሐላውን ፈራ እያዘነም አሰናበተው።

ከዚህ በኋላም ቅዱስ ያሬድ ወደ ቤተክርስቲያን ገብቶ በታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ ፈጽሞ የከበረሽና የተመሰገንሽ ከፍ ከፍም ያልሽ የብርሃን መውጫ የሕይወት ማዕረግ የሆንሽ የሚለውን ምስጋና እስከ መጨረሻው በተናገረ ጊዜ ክንድ ያህል ከምድር ከፍ ከፍ አለ።

ከዚህ በኋላ ወደ ሰሜን አገር ሒዶ በጾም በጸሎት ተወስኖ ሥጋውን እጅግ እያደከመ ኖሮ ገድሉን በዚያ ፈጸመ። እግዚአብሔር ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጥቶታል።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባታችን ያሬድ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት)
#ሳታቋርጡ_ጸልዩ

"ሥራ የሚሠራ ሰው ቀኑን ሙሉ በጸሎት ተጠምዶ መዋል አይችልም" አትበለኝ፤ ይችላል። በጸሎት የሚያስፈልገው ድምፅ ሳይሆን ሀሳብ ነው ፤ እጅ ሳይሆን እደ ልቦናን ማንሣት  ነው፤   አፍአዊ ሳይሆን ውስጣዊ አኳኋን ነው ።ይህን ለማድረግ ደግሞ ቦታም ጊዜም አይገድብህም። በጉልበትህ ባትንበረከክ፤ ደረትህንም ባትደቃ እንኳ መንፈስህ ትጉ ከሆነ ጸሎትህ ሥልጡን ነው ።

    #ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
«ወንድምህን አትናቀው»

ወዳጄ ሆይ! ክርስቲያን ነህን? እንኪያስ በፍጹም ወንድምህን አትናቀው። እህትህን አትናቃት። ምንም ይሁን ምን ሰው አትናቅ። ይህ የምትንቀው ወንድም በተለይ ክርስቲያን ከሆነ ክርስቶስን እየሰደብከዉ እንደሆን አስተውል። "እንዴት?"  ያልከኝ እንደሆንም ይህ የምትንቀው ወንድምህ የክርስቶስ ሕዋስ (ብልት) ኾኗል። የክርስቶስ ሕዋስ ከኾነ ደግሞ እሱን ናቅኸው ማለት ክርቶስን ናቅኸው ማለት ነው። ወንድምህን የምትንቅ ከሆነም በጲላጦስ አደባባይ ጌታን ከገረፉት፣ እራቁቱን ከሰቀሉት፣ ሐሞትንና ከርቤን ቀላቅለው ከሰጡት፣ በፊቱ ላይም ከተፉበት ሰዎች በምንም አትተናነስም። ስለዘህ ወንድምህን ከመናቅ ተጠንቀቅ።

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
በእንተ_ሥጋዌ_በዲያቆን_ያረጋል_አበጋዝ.pdf
147.8 KB
በእንተ ሥጋዌ

ለተማሪዎቹ የሚያስብ ርኀሩህ አስተማሪ አንዳንዶቹ ተማሪዎቹ ረቀቅና መጠቅ ያለው ትምህርት እንዳልገባቸው ሲያይ ወደ እነርሱ ደረጃ ዝቅ ብሎ እነርሱ በሚገባቸው በማንኛውም ሁኔታ እንደሚያስተምራቸው ሁሉ የእግዚአብሔር ቃልም እንዲሁ አደረገ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም እንዲህ እንዳለ፡- በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኗልና፡፡»"

#ቅዱስ_አትናቴዎስ_ሐዋርያዊ_ህይወቱና_ትምህርቱ

#ዲያቆን_ያረጋል_አበጋዝ