ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ
22.4K subscribers
380 photos
97 videos
169 files
284 links
This channel is not operated by Deacon Yaregal Abegaz

https://youtube.com/@yaregalabegaz?si=1f5NHTaQ2l2LbxWQ

“ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።”
— 2ኛ ቆሮ 11፥28
Download Telegram
#ግንቦት_1

#ልደታ_ለማርያም

በግንቦት አንድ በዚህችም ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደች እርሷም ለሰው ሁሉ ወገን ድኀነት የሆነባት ናት። ከወንዶች ወገን የከበረ አባቷም ስሙ ኢያቄም ከሴቶች ወገን የከበረች ሚስቱ ሐና ይባላሉ። ሁለቱም ልጅ በማጣት ሲያዝኑ ኖሩ በዚያ ወራት የመካኖችን መብዓ ካህናቱ አይቅበሉም ነበርና።

እነርሱም ከሰው የሚደርስባቸውን ሽሙጥና ኅዘናቸውን ያርቅላቸው ዘንድ በቀንና በሌሊት ወደ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይማልዱ ነበር። ሰውን የሚወድ እግዚአብሔርም ከዘራቸው ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ መልካም የሆነ ኀሳባቸውን ተመለከተ።

ክቡር እያቄምም አርባ ቀን እስኪፈጸም በተራራ ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጸለትና ለዓለሙ ሁሉ ድኀነት የሚደረግባት ዘር እንደሚሰጠው አበሠረው።

በፍጹም ልብ አምኖ ከተራራው ወረደ ለተመሰገነች ሚስቱ ለሐናም ከእግዚአብሔር መልአክ የሰማውን ያንን ራእይ ነገራት ቃሉ እውነት እንደሆነ እርሷም አመነች ልዑል እግዚአብሔርንም አመሰገኑት።

የተመሰገነች ቅድስት ሐናም ከእርሷ የሚወለደውን በዘመኑ ሁሉ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ታደርገው ዘንድ ለእግዚአብሔር ስለትን ተሳለች። ከዚህም በኋላ ይቺን የከበረች ሕፃን ፀንሳ ወለደች ስሟንም ማርያም ብላ ሰየመቻት ትርጓሜውም እመቤት ነው ደግሞም ሀብትና ስጦታ ማለት ነው።

በእውነት የዓለሙ ሁሉ እመቤት ናት ሁላችን በእርሷ ሰማያዊ ሀብት ልጅነትን ያገኘንባት። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የሥጋና የነፍስ መድኃኒት የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን በረከቷም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት)
#ግንቦት_5

#ቅዱስ_ኤርምያስ_ነቢይ

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ግንቦት አምስት በዚች ቀን የካህኑ ኬልቅዩ ልጅ ታላቅ ነቢይ ኤርምያስ አረፈ። ይህም እውነተኛ ነቢይ የአሞጽ ልጅ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ሦስት ዓመቱ ማስተማር ጀመረ።

ከዚያም በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ዘመን ዐሠራ አንዱ የሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥቱ እስከሚፈጸም በአምስተኛው ወር ኢየሩሳሌም እስከ ተማረከችበት ጊዜ ያስተምር ነበር።

ስለ ራሱ እንዲህ ሲል ራሱ ተናገረ የእግዚአብሔር ቃል ወደኔ መጣ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ "በእናትህ ማሕፀን ሳልፈጥርህ ወደድኩህ ከእናትህም ማሕፀን ሳትወጣ መረጥኩህ ለአሕዛብም መምህር አደረግሁህ አለኝ።" ይህም ነቢይ የእግዚአብሔርን አምልኮና ሕጉን በመተዋቸው እንዲህ ሲል የእስራኤልን ልጆች ገሠጻቸው። ተጠበቁ ንስሐም ግቡ የእግዚአብሔር ቁጣው በላያችሁ እንዳይመጣ።

ሁለተኛም እንዲህ ብሎ አስረዳቸው ወደ ፈጣሪያችሁ እግዚአብሔር ካልተመለሳችሁ ያለዚያ የከላውዴዎንን ንጉሥ ናቡከደነጾርን በላያችሁ እርሱ ያሥነሣዋል ይማርካችኋልም እንደቃሉም ሆነ። ሁለተኛም ሕዝቡ ተማርከው ሰባ ዘመን እንደሚኖሩ ትንቢት ተናገረ።

ደግሞ የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ለኩነተ ሥጋ እንደሚመጣና መከራ እንደሚቀበል የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደሚሸጠውና ሠላሳ ብር እንደሚወስድ ተናገረ። ስለ ብዙ ሥራዎችም ተናገረ አይሁድ ግን ሊገድሉት ወደው ገርፈው አሥረው በጒድጓድ ውሰጥ ጣሉት እግዚአብሔርም አዳነው። እርሱ ግን ስለእነርሱ ይለምንና ይማልድ ነበር እግዚአብሔርም ስለ እርሳቸው ወደእኔ አትማልድ እነርሱ ከክፋታቸው አይመለሱምና አለው።

ናቡከደነጾርም የኢየሩሳሌምን ሕዝብ በማረከ ጊዜ ከእሳቸው ጋራ አልማረከውም። ነገር ግን ከምርኮ የቀሩት ወደ ግብጽ አገር ወሰዱት የግብጽን ሰዎች ሲያጠፉአቸው የነበሩ በግብጽ ወንዞች የሚኖሩ አራዊትን በእርሱ ጸሎት እግዚአብሔር አጠፋቸው።

ከዚያም ወደ ባቢሎን አገር ወሰዱት በዚያም የእስራኤል ልጆች ከምርኮ እስኪመለሱ ትንቢት እየተናገረ ሕዝቡን ሲአስተምር ኖረ። የትንቢቱ ወራትም በተፈጸመ ጊዜ አይሁድ በደንጊያዎች ወገሩት ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በነቢዩ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት)
#ግንቦት_11

#ቅዱስ_ያሬድ_ካህን_ወማኅሌታይ

ግንቦት ዐሥራ አንድ በዚህች ዕለት የሱራፌል አምሳላቸው የሆነ ኢትዮጵያዊው ማኅሌታይ ያሬድ የተሰወረበት ነው። ይህም ቅድስ ከአባ ጌዴዎን ዘመዶች ወገን ነው እርሱም በኢትዮጵያ አገር ከታነፁ አብያተ ክርስቲያን ለምትቀድም ከአክሱም ካህናት ውስጥ ነው እርሷም አስቀድሞ የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት በውስጥዋ የተሰበከና አምላክን በወለደች በእመቤታችን በከበረች ድንግል ማርያም ስም የከበረች ናት።

ይህም አባ ጌዴዎን ትምህርትን ሊአስተምረው በጀመረ ጊዜ መቀበልም ማጥናትም እስከ ብዙ ዘመን ተሳነው። በአንዲት ዕለትም መምህሩ በእርሱ ላይ ተበሳጭቶ መትቶ አሳመመው። ያሬድም ሸሽቶ ከዱር ውስጥ ገባ ከኀዘኑም ብዛት የተነሣ ከዛፍ ሥር ተጠለለ። ወደ ዛፉ ላይም ትል ሲወጣ አየ ትሉም ከዛፉ እኩሌታ ደርሶ ይወድቅ ነበረ እንዲሁም ብዙ ጊዜ ከአደረገ በኋላ በጭንቅ ከዛፉ ላይ ወጣ።

ቅዱስ ያሬድም የትሉን ትጋት በአየ ጊዜ ወደ መንፈሳዊ መምህሩ ተመልሶ አባቴ ሆይ ይቅርታ አድርግልኝና እንደ ወደድክ አድርገኝ አለው መምህሩም ተቀበለው።

ከዚህ በኋላ በብዙ ልቅሶ ወደ እግዚአብሔር በለመነ ጊዜ ልቡናው ብሩህ ሆኖለት በአጭር ጊዜ የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍትን ተምሮ ፈጸመ ዲቁናም ተሾመ።

በዚያም ወራት እንደ ዛሬ በከፍተኛ ቃል የመዝሙር ማኅሌት የለም ነበር በትሑት እንጂ። እግዚአብሔርም መታሰቢያ ሊአቆምለት በወደደ ጊዜ ከኤዶም ገነት ሦስት አዕዋፍን ላከለት እነርሱም በሰው አንደበት ተናግረውት ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ከእሳቸው ጋራ አወጡት በዚያም ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ የሚያመሰግኑበትን ማኅሌታቸውን ተማረ።

ወደ አነዋወሩ ወደ ምድርም በተመለሰ ጊዜ በአክሱም ዳር ወደ ከበረች ቤተ ክርስቲያን በሦስት ሰዓት ገባ በታላቅም ቃል ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ የጽዮንም ደገኛዋ ሰማይን ፈጠረ። ዳግመኛም እንዴት እንደሚሠራት የድንኳንን አሠራር ለሙሴ አሳየው አስተማረው አለ።

ይቺንም ምስጋና አርያም ብሎ ጠራት። የቃሉንም ድምፅ በሰሙ ጊዜ ንጉሡም ንግሥቲቱም ጳጳሱም ከካህናቱ ሁሉ ጋራ የመንግሥት ታላቆችና ሕዝቡ ሁሉ ወደርሱ ሮጡ ሲሰሙትም ዋሉ።

ከዚያም በኋላ ከዓመት እስከ ዓመት በየክፈለ ዘመኑ በክረምትና በበጋ በመጸውና በጸደይ በአጽዋማትና በበዓላት በሰንበታትም እንዲሁም በመላእክት በዓል በነቢያትና በሐዋርያት በጻድቃንና በሰማዕታት በደናግልም በዓል የሚሆን አድርጎ በሦስቱ ዜማው ሠራ ይኸውም ግዕዝ ዕዝል አራራይ ነው።

የሰው ንግግር የአዕዋፍ የእንስሳትና የአራዊት ጩኸት ከዚህ ከሦስቱ ዜማው አይወጣም።
በአንዲት ዕለትም ቅዱስ ያሬድ ከንጉሥ ገብረ መስቀል እግር በታች ቁሞ ሲዘምር ንጉሡም የያሬድን ድምፅ እያዳመጠ ልቡ ተመሥጦ የብረት ዘንጉን በያሬድ እግር ላይ ተከለው ከእርሱም ደምና ውኃ ፈሰሰ። ያሬድም ማኅሌቱን እስከ ሚፈጽም አልተሰማውም።

ንጉሡም አይቶ ደነገጠ በትሩንም ከእግሩ ላይ ነቀለ ስለ ፈሰሰው የደምህ ዋጋ የፈለግኸውን ለምነኝ ብሎ ለያሬድ ተናገረው ያሬድም ላትከለክለኝ ማልልኝ አለው። ንጉሥም በማለለት ጊዜ ወደገዳም ሔጄ እመነኲስ ዘንድ አሰናብተኝ አለው ንጉሡም ሰምቶ ከመኳንንቱ ጋራ እጅግ አዘነ ተከዘም እንዳይከለክለውም መሐላውን ፈራ እያዘነም አሰናበተው።

ከዚህ በኋላም ቅዱስ ያሬድ ወደ ቤተክርስቲያን ገብቶ በታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ ፈጽሞ የከበረሽና የተመሰገንሽ ከፍ ከፍም ያልሽ የብርሃን መውጫ የሕይወት ማዕረግ የሆንሽ የሚለውን ምስጋና እስከ መጨረሻው በተናገረ ጊዜ ክንድ ያህል ከምድር ከፍ ከፍ አለ።

ከዚህ በኋላ ወደ ሰሜን አገር ሒዶ በጾም በጸሎት ተወስኖ ሥጋውን እጅግ እያደከመ ኖሮ ገድሉን በዚያ ፈጸመ። እግዚአብሔር ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጥቶታል።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባታችን ያሬድ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት)