ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ
18.7K subscribers
361 photos
91 videos
152 files
243 links
This channel is not operated by Deacon Yaregal Abegaz

https://youtube.com/@yaregalabegaz?si=1f5NHTaQ2l2LbxWQ

“ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው።”
— 2ኛ ቆሮ 11፥28
Download Telegram
ጌታችንም ጊዜው ሲደርስ ከሐዋርያት ጋር በአንድነት መጣ፤ ስምዖንም ከቤቱ ወጥቶ ሮጦ ከጌታ እግር ሥር ሰገደ፤ ወደ ቤቱም ከሐዋርያት ጋር አስገባቸው፡፡ ይሁዳ ግን ይህን ሰዓት አልነበረም፤ ውጪ ከሻጭና ለዋጭ ጋር ገንዘብ ሲደራደር ነበር፤ ስምዖንም ለሚስቱ አክሮሲና ጌታና ሐዋርያት የሚገቡበት በእግራቸው የሚረግጡት ምንጣፍ እንድታነጥፍ አዘዛት፡፡ አክሮሲና ግን የጌታን መልክ አታውቀውም ነበር፤ ያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ጸሎት ሲጸልዩ አይታ ‹‹ከእናንተ ውስጥ መምህሩ ማነው›› አለቻቸው፤እነርሱም ዝም አሉ፤ መልከ መልካም ወደ ሆነውና የጌታ ወዳጅ ወደሆነው ዮሐንስ ተመልክታ እርሱ ይሆን አለች፤ ጴጥሮስ ግን ቀበል አድርጎ ‹‹ጌታ ኢየሱስ ከውስጠኛው ክፍል ቆሞ ይጸልያል፤ ጌታ እርሱ ነው›› አላት፡፡ እርሷም ገብታ ሰገደችለት፤ ይሁዳም በመጨረሻ ሳጥን ተሸክሞ መጣ፤ ጠባቂውንም እኔ የጌታ ደቀ መዝሙር ነኝ አለው፡፡ በር ጠባቂውም እለእስክንድሮስም የተነጠፈውን እስካጥፍ ጠብቅ ብሎ ዘለፈው፤ ልብሱንም አንስቶ አስገባው፤ /ግብረ ሕማማት ፭፻፹፫-፫፻፹፭/፡፡

በአንደኛው ሰዓት ሌሊት (ሐሙስ ለአርብ ምሽት)፤

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ልብሱን አኖረ፤ማበሻ ጨርቅም አንስቶ ወገቡን ታጠቀ፤ ይህችውም ሥራ የምታሠራና የምታስጌጥ ናት፤ ለዛሬው የመነኮሳት መታጠቂያ አብነት ናት፡፡ ለምሳሌ፡- ኢዮአብ ወደ ሰልፍ ሲገባ እየለበሳት ይገባ እንደነበረችው ያለ ዓይነት ነው፤ ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጥብ ዘንድ በጴጥሮስ ጀመረ፤ ጴጥሮስ ግን እኔ ባንተ ልታጠብ አይገባኝም አለ፤ ጌታችንም መልሶ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ እኔ እግርህን ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም›› (ዮሐ.፲፫፥፰)፡፡ ሌሎቹንም ሐዋርያት አጠባቸው፤ አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳንም እግሩን አጠበው፡፡ ጌታ አሳልፎ እንደሚሰጠው ሳያውቅ ቀርቶ አልነበረም፤ ፍቅርን ሲያስተምረውና ለንስሐ ጊዜ ሲሰጠው ነው እንጂ፤ እኛንም ለሚወደን ብቻ ሳይሆን ለሚጠላን እንኳን በጎ ማድረግ እንደሚገባ ሲያስተምረን ነው፡፡

ጌታችን ጾመና ጹሙ አለን፤ተጠመቀና ተጠመቁ አለን፤ ጸለየና ጸልዩ፤ ሰገደናም ስገዱ አለን፤ የሐዋርያትንም እግር አጥቦ እናንተም እንዲህ አድርጉ ብሎ መምህረ ትሕትናነቱን ገለጠልን፡፡ ዛሬም ከፓትርያርኩ ጀምሮ ሊቃነ ጳጳሳት፤ካህናት በየመአርጋቸው የምእመናኑን እግር በማጠብ የጌታን የትሕትና ሥራ ያስቡታል፡፡

ለሐዋርያት ትሕትናን ሲያስተምራቸው ጌታችን እግራቸውን እንደ አጠባቸው ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ ከዚያም ዝ ውእቱ ሥጋየ ዝ ውእቱ ደምየ ብሎ ሥጋውንና ደሙን ሰጣቸው፤ ዛሬም የልጅነት ጥምቀት የሚቀበሉ ምእመናን በዚያኑ ዕለት ከክርስትና ቤት ወደ ቤተ መቅደስ ሔደው የጌታን ክቡር ሥጋና ደም ይቀበላሉ፤ መሠረቱም ጌታችን ለሐዋርያት ያደረገውን ተመርኩዞ ነው፡፡ ከፍ ከፍ ሊል የሚወድ ራሱን ዝቅ ያድርግ ብሎም አስተምሯቸዋል፤ አባ ጊዮርጊስ በመጽሐፈ ምሥጢር ጌታ ለጴጥሮስ ‹‹እኔ እግርህን ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም›› ያለውን ሲተረጉሙ ‹‹እኔ በአገልጋይ አምሳል እግርህ ካላጠብኩህ አንተም ከበታችህ ላሉት ራስህን ዝቅ ለማድረግ አትችልም፤ ራስህን ዝቅ ዝቅ ካላደረግህ አለቃ ልትሆን አትችልም›› ለማለት ነው ብለው ተርጉመውታል፡፡ ጌታችን ደግሞ አምላክ ፈጣሪ መምህር ሳለ ዝቅ ብሎ እንዳጠባቸው እነርሱም ክህነታቸውንና መምህርነታቸውን በትሕትና እንዲጀምሩ ሲያስተምራቸው ነው፡፡

በሁለተኛው ሰዓተ ሌሊት ምሽት፤

ጌታችን ሕብስቱን ባርኮ ለዐሥራ ሦስት ፈትቶ ሰጣቸው፤ ዐሥራ ሦስተኛውን እርሱ የሚቀበለው ነውና ነገር ግን የሚረባውና የሚጠቅመው አይደለም፤ ‹‹ዝ ውእቱ ሥጋየ ዝ ውእቱ ደምየ›› ብሎ ሕብስቱን ባርኮ ‹‹ይህ ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ ›› ወይኑንም ባርኮ ‹‹ይህ ደሜ ነው እንካችሁ ጠጡ›› ብሎ ሰጣቸው፡፡አስራ ሦስት አድርጎ መፈተቱ ሐዋርያትን እንዳይገርማቸው (እንዳያስፈራቸው) ነው፤ እራሱም ጥዒሞ አጥዐሞሙ/ቀምሶ አቀመሳቸው/ እንዲል አብነት ለመሆን፤ አንድም ነገ በመልዕተ መስቀል አስራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል እቀበላለሁ ሲል ነው፤ ጌታ ይህን ባያደርግ ኖሮ ዛሬ ካህኑ የጌታን ሥጋና ደም ሳይቀበል አቀብሎ ብቻ በሄደ ነበርና ለእነርሱ ለማስተማር ነው፡፡

ማዕዱንም እየበሉ ጌታችንም ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ! ከእናንተ መካከል አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል›› አላቸው፤ (ዮሐ.፲፫፥፳፩)፡፡ ሐዋርያት ሁሉ ደነገጡ! እርስ በርሳቸው ተያዩ፤‹‹እኔ እሆን? እኔ እሆን?›› ተባባሉ፤ ጴጥሮስም ዮሐንስን ጠጋ ብሎ ‹‹ማነው አሳልፎ የሚሰጠህ ብለህ ጌታን ጠይቀው›› አለው፤ወንጌላዊው ዮሐንስም ጌታን ጠጋ ብሎ ጠየቀው ጌታችንም ‹‹ከእኔ ጋር እጁን ከወጪቱ የሚያገባ እርሱ አሳልፎ ይሰጠኛል›› አለ፤ (ማቴ.፳፮፥፳፫/ሉቃ.፳፪፥፳፩)፡፡ ሐዋርያትም ‹‹ሁላችን ከወጪቱ የምንጠቅስ አይደለምን?›› ሲሉ ጌታችን ‹‹እኔ ከወጡ አጥቅሼ የምሰጠው ነው›› አላቸው፤ ያንጊዜ አጥቅሶ ለአስቆሮቱ ይሁዳ ሰጠው፤ ስለዚህ ወንጌላውያኑ ይህን ታሪክ ይዘው አንድ ሳለ በተለያየ አገላለጥ ገለጡልን፡፡

ይሁዳም እንደቸኮለ ሰው ይቅበዘበዝ ነበር፤እርሱም ጌታን እንዴት አሳልፎ እንደሚሰጠው በልቡ እያሰበ ነበር፡፡ ጌታም ወደ ይሁዳ ጠጋ ብሎ ‹‹ወዳጄ ይሁዳ ሆይ! ልትሠራው የምትሻው ሥራ ካለ ሒድ›› አለው፤ (ዮሐ.፲፫፥፳፯)፤ ይሁዳም ፈጥኖ ወጥቶ ወደ አይሁዳውያን ጌታን አሳልፎ ሊሰጥ ዋጋ ሊነጋገር ሔደ፡፡

ከሦስተኛው ሰዓተ ሌሊት እስከ አምስተኛይቱ ሰዓተ ሌሊት ድረስ

ለደቀ መዛሙርቱ ሲመክራቸው የመንፈስ ቅዱስንም መምጣት አብዝቶ ሲነግራቸው፤ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ አቀና፤ እርሱ ከአባቱ ጋር አንድ እንደሆነም ነገራቸው፤ ለብቻው ፈቀቅ ብሎ ወዙ እንደ ደም እስኪፈስ እየሰገደ ጸለየ፤ወደ ደቀ መዛሙርቱ ተመለሰ፤ ተኝተው አገኛቸው፤ ቀሰቀሳቸው፤ ጴጥሮስንም አንድ ሰዓት ያህል እንኳን ከእኔ ጋር መትጋት አቃታችሁን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ አለው! (ሉቃ.፳፪፥፲፬-፵፮)፡፡

የጌታችን በአይሁድ መያዝ (ስድስተኛው ሰዓተ ሌሊት)

ጌታችንም ከአብ ጋር ስላለው አንድነትና ክብር ለሐዋርያት ካስተማራቸው በኋላ ‹‹ኢየሱስም ይህን ተናግሮ አትክልት ወደ አለበት ስፍራ ወደ ቄድሮስ ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ በዚያም ገባ›› (ዮሐ.፲፰፥፩)፡፡ወንዙን ተሻግሮ ያለውን ዛፍ አልፎ ወዳለው ዱር ገባ፡፡ ይሁዳም ይህችን ስፍራ ቀድሞ ጌታ ይመጣባት ስለነበር ያውቃት ነበርና ጭፍሮችንና የካህናት አለቆችን ፈሪሳውያን ሌሎች ፋና ጋሻ ጦርም የያዙትን አስከትሎ መጣ፡፡ ጌታችንም ‹‹ተነሡ እንሂድ! እነሆ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል›› አላቸው ወደ እነርሱ መጥቶ ቀረበ፤ ይሁዳም ወደርሱ ቀርቦ፤ ‹‹መምህር ሆይ ቸር ውለሃል፤ ሰላም ላንተ ይሁን›› ብሎ ሳመው፤ ይህ መሳም ለአይሁድ ጥቆማ ወይም ምልክት ነበር፡፡ ምክንያቱም የጌታ መልክና የወንጌላዊው የዮሐንስ መልክ ይመሳሰልባቸው ነበርና ሲለይላቸው ነው፤ ጌታችንም ‹‹በስኢምኑ ታገብኦ ለወልደ ዕጓለ እመሕያው፤ የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጠዋለህን?›› አለው (ሉቃ.፳፪፥፵፰)፡፡
ይሁዳም ከጭፍሮቹ ጋር መጣ፤ ጌታ ኢየሱስንም ከበውት ወደ ሽማግሌዎችና የካህናት አለቃ ቀያፋ ወዳለበት ወሰዱት፤ ጴጥሮስ ግን ከሩቅ ሆኖ ይከተለው ነበር፤ የነገሩንም ፍጻሜ ያይ ዘንድ ከአንደኛው ቅጥር ግቢ ገብቶ ተቀመጠ፡፡ አይሁድም በክርስቶስ ላይ ሁለት የሐሰት ምስክሮችን አመጡ ‹‹ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስተኛው ቀን እሰራዋለሁ›› ብሏል ብለው ከሰሱት፤ ሊቀ ካህናቱም ተነስቶ ‹‹እንዲህ ሲያጣሉህ አትሰማምን›› አለው፡፡ ጌታችን ግን ምንም አልመለሰለትም፤ሊቀ ካህናቱም ‹‹ክርስቶስ ተብሎ የተነገረልህ የእግዚብሔር ልጅ አንተ እንደሆንክ ንገረኝ›› አለው፡፡ ጌታችንም ‹‹አንተ አልክ›› አለው፤ ያን ጌዜ ሊቀ ካህናቱ ተናዶ ልብሱን ቀደደው፤ራሱንም በብረት ዘንግ መቱት፤ የስቃዩ ጅማሬ ይህን ጊዜ ነበር፡፡
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
"ሁሉን የያዘውን ያዙት፤ ሁሉን የሚገዛውን አሠሩት፤ የህያውን አምላክ ልጅ አሠሩት፤ በቁጣ ጎተቱት፤ በፍቅር ተከተላቸው። በሚሸልተው ፊት እንደማይናገር እንደ የዋህ በግ በኋላቸው እየተከተለ ወሰዱት፤ ሊቃነ መላእክት በመፍራት እና በመንቀጥቀጥ ከፊቱ የሚቆሙለትን በአደባባይ አቆሙት፤

ኃጢአትን ይቅር የሚለውን ኃጥእ አሉት፥ በመኳንንት የሚፈርደውንም በእርሱ ፈረዱበት፤ ለሱራፌል ዘውድ የሚያቀዳጃቸውን የሾህ ዘውድ አቀዳጁት፤ ለኪሩቤል የገርማ ልብስ የሚያለብሳቸውን ለመዘበት ቀይ ግምጃ አለበሱት፤ ኪሩቤል በእሳት ክንፍ ተሸፍነው በፊቱ የሚሰወሩለትን እርሱን ክፉ ባሪያ አሥሮ ፊቱን ጸፋው፤ የመላእክት ሠራዊት በፍጹም መደንገጥ የሚሰግዱለት እየዘበቱበት በፊቱ ተንበረከኩ፡፡

ይህን ያህል ትህትና እንደምን ያለ ትህትና ነው? ይህን ያህል ትእግስት እንደምን ያለ ትእግስት ነው? ይህን ያህል ዝምታ እንደምን ያለ ዝምታ ነው? ይህን ያህል ቸርነት እንደምን ያለ ቸርነት ነው? ኃያል ወልድን ፍቅር ከዙፋኑ ሳበው እስከ ሞትም አደረሰው በደል የሌለበትን እንደበደለኛ ሰቀሉት፡፡ ህይወትን የሠራውን ከበደለኞች ጋር ቆጠሩት፤ አዳምን የሠሩ እጆች በመስቀል ቀኖዎት ተቸነከሩ፤  ወዮ በገነት የተመላለሱ እግሮች በመስቀል ተቸነከሩ፡፡

ወዮ በአዳም ፊት የህይወት እስትንፋስን እፍ ያለ አፍ ከሃሞት ጋር የተቀላቀለ የኮመጠጠ መፃፃን ጠጣ፤... ወዮ የወልድን መከራውን የሚናገር ምን አፍ ነው? ምን ከንፈር ነው? ምንስ አንደበት ነው? የፍቁሩ የጌታ ህማማት በተነገረ ጊዜ ልብ ይለያል፤ ህሊናም ይመታል፤ ነፍስም ትንቀጠቀጣለች፤ ሥጋም ይደክማል የማይሞተው ሞተ፤ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ፤ ሙታንን ያድናቸው ዘንድ ሞተ። የምትወዱት ሰዎች ፈጽሞ አልቅሱለት፡፡"

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
ዓርብ ስቅለት (የድኅነት ቀን)

እንኳን አደረሰን!

ዓርብ ስቅለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ ‹የድኅነት ቀን› ይባላል፡፡ ጌታችን ከተያዘባት ሰዓት አንሥቶ አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አደሩ፡፡ ሲነጋ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ አደባባይ አስረው ወሰዱት (ማቴ. ፳፯፥፩-፶፯)፡፡ አይሁድ ይህን አጥፍቶአል የሚሉት ነጥብ ሳይኖራቸው ነውና ጌታችንን ለፍርድ ያቀረቡት ጲላጦሰ እነርሱ ወደ ተሰባሰቡበት ቦታ ወጥቶ ‹‹ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደል ምንድን ነው?›› ሲል በጠየቃቸው ጊዜ በቂ ምላሽ አላቀረቡም፡፡

‹‹ክፉ የሠራ ባይኾንስ ወደ አንተ ባላመጣነውም ነበር›› በሚል የሸፍጥ ቃል ሲያጕረመርሙ ጲላጦስ መልሶ ‹‹እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም፤ እናንተወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁ ፍረዱበት፤›› አላቸው፡፡ አይሁድም ኦሪት ‹‹ኢትቅትል ብእሴ ጻድቀ ወኀጥአ ኢታኅዩ፤ ጻድቅን ሰው አትግደል፤ ኀጥኡንም ከፍርድአታድን፤›› ትላለችና ‹‹እኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም፤›› ብለዋል (ዮሐ. ፲፰፥፳፰-፴፩)፡፡ ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ‹‹በሕጋችን ጻድቀ ባሕርይክርስቶስን መግደል አይገባንም ሙሉ በሙሉ ጥፋተኞች ነን፤›› ሲያሰኛቸው ነው፡፡ በኋላም እርሱ ሞቶ ዓለም ይድን ዘንድ ወደ ምድር መጥቷልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ጥፋቱ ሞት ተፈረደበት፡፡ ስለዚህም ገርፈው ሰቀሉት፡፡

ጌታችን ሲሰቅልም የሚከተሉት ሰባት ተአምራት ተፈጽመዋል፤

፩. ፀሐይ ጨለመ፤

፪. ጨረቃ ደም ኾነ፤

፫. ከዋክብት ረገፉ፤

፬. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ተቀደደ፤

፭. አለቶች ተፈረካከሱ፤

፮. መቃብራት ተከፈቱ፤
፯. ሙታን ተነሡ (ማቴ. ፳፯፥፶፩-፶፬)፡፡

ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ የሚከተሉትን ሰባት ዐበይት ቃላት አሰምቶ ተናግሯል፤

፩. ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ (አምላኪየ አምላኪየ ለምን ተውኸኝ?)››፤

፪. ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ››፤

፫. ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው››፤

፬. እመቤታችንን ‹‹ሴትዮ ሆይ፣ እነሆ ልጅሽ››፤ ደቀ መዝሙሩንም ‹‹እናትህ እነኋት›› በማለት የቃል ኪዳን እናትነትና ልጅነት ማከናወኑ፤

፭. ‹‹አባት ሆይ በአንተ እጅ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ››

፮. ‹‹ተጠማሁ››፤

፯. ‹‹ዅሉ ተፈጸመ›› (ማቴ. ፳፯፥፵፭-፵፮፤ ሉቃ. ፳፫፥፵፫-፵፮፤ ዮሐ. ፲፱፥፲-፴)፡፡

ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጨለማ ኾኖ ከቈየ በኋላ ከዘጠኝ እስከ ማታ እንደ ተለመደው ብርሃን ኾኖአል፡፡ ‹‹ወፍና ሠርክ ይበርህ ብርሃነ ፀሐይ›› እንዲል (ዘካ. ፲፬፥፯)፡፡ በዚህ ዕለት ሰባት መስተፃርራን (ጠበኞች) ታረቁ፤ ተስማሙ፡፡ እነዚህም፡- ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ነፍስና ሥጋ ናቸው (ኤፌ. ፪፥፲፤ ቈላ. ፩፥፳)፡፡ ጌታችን ጠዋት በሦስት ሰዓት ተገረፈ፤ በስድስት ሰዓት ተሰቀለ (ማቴ. ፳፯፥፩-፴፯፤ ሉቃ. ፳፫፥፩-፵፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፩)፡፡

በዘጠኝ ሰዓት ጌታችን በውኃው ተጠምቀን፣ ደሙን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንኾን ዘንድ ከቀኝ ጎድኑ ጥሩ ውኃ፣ ትኩስ ደም አፈሰሰልን (ዮሐ. ፲፱፥፴፬)፡፡ በዐሥራ አንድ ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው ሽቶ እየረበረቡ በድርብ በፍታ ገንዘው ቀበሩት (ሉቃ. ፳፫፥፶-፶፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፴፰-፵፪)፡፡ ቅድስት ነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዳ ነፍሳትን ነጻ አወጣች (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፱)፡፡ በዚህ ጊዜ በርሃነ መለኮቱ በሲኦል ተገለጠ፡፡ ስለዚህም ‹‹ንሴብሖ ለእግዚአብሔር›› እየተባለ ይዘመራል፡፡ ከሆሣዕና አንሥቶ ተከልክሎ የነበረው ኑዛዜ ይናዘዛል፤ ጸሎተ ፍትሐት ይደረጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
በዓለ ትንሣኤን በትንሣኤ ልቡና እናክብር!

ፋሲካ ማለት መሻገር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ እኛን ከወደቅንበት አንሥቶና ተሸክሞ ከዚኽ ምድር ወደ ሰማያት ተሻግሯልና (ተነሥቶ ዐርጓልና)፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ፡- ‹‹እንግዲኽ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችኁ፣ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን ሹ፤ በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም፡፡ ሞታችኋልና፤ ሕይወታችኁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሯልና፡፡ ሕይወታችኁ የኾነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችኁ፤›› እንዳለን /ቈላ.፫÷፩-፬/፣ በጥምቀት ውኃ ሞቱን በሚመስል ሞት ስንሞት፣ አሮጌው ሰውነታችን እንደ ግብጻውያን ተቀብሮ ቀርቷል፡፡ አዲሱ ሰውነታችን ግን እስራኤላውያን ባሕሩ ተከፍሎላቸው እንደ ተሻገሩ ተሻግሯል (ተነሥቷል)፡፡

ብልየት ያለበት የቀዳማዊ አዳም ሰውነታችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተቀብሮ አዲሱ ሰውነታችን ሕይወትን አግኝቶ ተነሥቷል፡፡ መሬታዊው ሰውነታችን ሞቶ ሰማያዊው ሰውነታችንን ለብሰን መንፈሳውያን ኾነን ተነሥተናል፡፡ ወደ ጥንተ ተፈጥሯችን ተመልሰናል፡፡ አኹን ከእኛ የሚጠበቀው ይኽ ተፈጥሯችንን ሳናቆሽሽ መጠበቅ ነው፤ እንደ ተነሣን መዝለቅ፡፡ ይኽን ለማድረግም ተራራ መውጣት፣ ምድርን መቆፈር፣ የእሳት ባሕርን መሻገር አይጠበቅብንም፡፡ ይኽን ጠብቀን እንድንቈይ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ፈቃዳችንን፡፡ የሚሠራው እርሱ ራሱ ነውና /ዮሐ.፲፭÷፭/፡፡ መጽንዒ (የሚያጸና) መንፈስ ቅዱስን ያደለንም ስለዚኹ ነው፡፡

የምናመልከውን አምላክ መስለን በሕይወት ሳንሻገር የመሻገርን በዓል (ፋሲካን) የምናከብረው ምን ጥቅም እንዲሰጠን ነው? ከጨለማ ሥራ ወደ ብርሃን ሥራ፣ ከፍቅረ ዓለም ወደ ፍቅረ ክርስቶስ ሳንሻገር ፋሲካን የማክበራችን ትርጕሙ ምንድነው? እኛው ሳንነሣ የመነሣት በዓልን ማክበራችን በፍርድ ላይ ፍርድ በበደል ላይ በደል ከመጨመር ውጪ የሚሰጠን ጥቅም ምንድን ነው? የምንነሣውስ መቼ ነው? በዐይናችን ጉድፍ ብትገባ ስንት ደቂቃ እንታገሣታለን? ታድያ በነፍሳችን ላይ የተጫነውን የኃጢአት ግንድ መቼ ነው የምናስወግደው? መቼ ነው ወደ ላይኛው ቤታችን ቀና የምንለው? ብዙዎቻችን በሕይወታችን ሳንሻገር ነው በዓለ ፋሲካን የምናከብረው፡፡ ክርስቲያን ኾኖ በመብልና በመጠጥ ብቻ ፋሲካን ማክበር ኢ ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡

አዲሱን ሰውነታችን ለብሰን ከተነሣን በኋላ እንደ ቀድሞ ምልልስ የምንጓዝ ከኾነ ግን ተመልሰን ወድቀናል፤ አዲሱ ሰውነታችንን አውልቀን አሮጌውን ሰውነታችንን በድጋሜ ለብሰነዋል፡፡ በእኛነታችን ውስጥ ፍቅረ ንዋይ፣ ፍቅረ ሲመት፣ ፍትወት፣ ይኽንንም የመሰሉ ዅሉ ካለ አዲሱ ሰውነታችን ከእኛ ጋር የለም፤ ቢኖርም ታሟል፡፡ በኃጢአት የመቃጠል ስሜት፣ ርኵሰትና ክፉ ምኞት ከእኛ ዘንድ ካለ አሮጌ ሰው ኾነናል፤ ትንሣኤ ልቡናን ገንዘብ አላደረግንም፡፡ ስለዚኽ ከልቡና ሞት እንነሣና ፋሲካን እናክብር፡፡ እስከ አኹን በኃጢአት ውስጥ ካለን ወደ ብርሃን ክርስቶስ እንምጣ (እንሻገርና) የመሻገርን በዓል እናክብር፡፡ ከክፉ ሥራ ወደ ጽድቅ ሥራ እንሻገርና የእውነት ፋሲካን እናክብር፡፡ ከኃይል ወደ ኃይል እንሻገርና ፋሲካን እናክብር፡፡ ከሞት ሥራ ወደ ሕይወት ሥራ እንነሣና የመነሣትን በዓል እናክብር፡፡

እግዚአብሔር የሚወዳችሁ አንድም እግዚአብሔርን የምትወዱት ሆይ! እኛን የሚያሰነካክል ደግሞም የሚጥለን ፈርዖን (ዲያብሎስ) ተሰነካክሎ ወድቋልና ከግብጽ ሕይወታችን እንውጣ፡፡ ተነሥተንም እንሻገር፡፡ ተሻግረንም ሰማያዊውን ፋሲካ እናክብር፡፡ በግብጽ የነበሩት እስራኤላውያን የበጉን ደም በጉበኑና በኹለቱም መቃን ሲቀቡት አጥፊው ከቤታቸው እንዳለፈ አንብበናል /ዘፀ.፲፪÷፲፫/፡፡ ይኸውም በጉ በራሱ ያንን የማድረግ ኃይል ስለ ነበረው አይደለም፤ ደሙ የክርስቶስ ደም አምሳል ስለ ነበር ነው እንጂ፡፡ እኛ ግን የአማናዊውን በግ /ዮሐ.፩፡፳፱/ ደም በልቡናችን፣ በአስተሳሰባችንና በሰውነታችን ዅሉ እንቀባና (እንቀበልና) እንሻገር፡፡

ይኽን ስናደረግ በእባቡና በጊንጡ ይኸውም በዲያብሎስና በሠራዊቱ ላይ ሥልጣን ይኖረናል /ሉቃ.፲÷፲፱/፡፡ የምንበላው በግ ራሱ ሕይወት ስለ ኾነ ሞት በእኛ ላይ አይነግሥም /ዮሐ.፲፬÷፮/፡፡ በዚኽ ዓለም ሳለን ከዚኽ ደስታ ተካፋዮች ከኾንን (የመዠመሪያውን ትንሣኤ ልቡና በንስሐ ከተነሣን) በሚመጣው ዓለምም በክብር ላይ ክብር፣ በሹመት ላይ ሹመት እንቀበላለን (ኹለተኛውን ትንሣኤ እንነሣለን) /ሉቃ.፳፪÷፲፭-፲፮/፡፡ ብንወድቅ እንኳን መልሰን በመነሣት ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ክብር፣ የክብር ክብር፣ ጌትነት የባሕርዩ በሚኾን፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰጭነት በመንግሥተ ሰማያት ጸጋ ክብር እናገኛለንና የጭንቅ ቀን ሳይመጣ በዓለ ትንሣኤን እናክብር፡፡ ለዚህም ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የመከረንን የሚከተለውን ኃይለ ቃል በተግባር ላይ ብናውለው እንጠቀማለን፤

‹‹በምነግራችኁ ነገር እያበሳጨኋችሁና እያሳመምችሁ እንደ ኾነ ይገባኛል? ግን ምን ላድርግ? እኔም እናንተም በምግባር በሃይማኖት የታነጽን እንኾን ዘንድ ብቻ ሳይኾን ከዚያም እናመልጥ ዘንድ ነው፡፡ ነገር ግን በኃጢአት ከመጨማለቃችን የተነሣ እንዴት አድርጌ ላሳምማችኁ እችላለኁ? ብትሰሙኝና ብትለወጡስ እኔም ማረፍ እንኳን በቻልኩ ነበር፡፡ ስለዚኽ እስካልተለወጣችሁ ድረስ እናንተን መገሠፄንና መምከሬን አላቆምም፡፡ ስለ ገሃነመ እሳት ተደጋግሞ ሲነገር የሚበሳጭ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ እኔ ግን ‹ከዚኽ የበለጠ ያማረ የተወደደ አስደሳች ትምህርት የለም› እለዋለኁ፡፡ ‹እንዴት ይኽ አስደሳች ትምህርት ነው ትለናለህ?› ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ እኔም ‹ወደዚያ መጣል ከደስታ ዅሉ የራቀ ነውና› ብዬ እመልስላችኋለሁ፡፡ ስለዚኽ ነፍሳችን ከመታሠሯ በፊት የነቃን የተጋን እንኾን ዘንድ ይኽን ደጋግሜ እነግራችኋለሁ፡፡ ንስሐ ይግባ እንጂ ማንም እንደ ተወቀሰ አያስብ፤ በንግግሬም የሚቆጣ አይኑር፡፡ ዅላችንም ወደ ጠባቢቱ መንገድ እንግባ፡፡ እስከ መቼስ በስንፍና አልጋ እንተኛለን? ዛሬ ነገ ማለት አይበቃንም ወይ? ሰማያዊ ቪላችንን ቀና ብለን ብንመለከት እኮ በዚኽ ምድር ይኽንን ለመሥራት ባልደከምን ነበር፡፡ እስቲ ንገሩኝ! ሩጫችንን ስንጨርስ ከሬሳ ሳጥንና ከመግነዝ ጨርቅ ውጪ ይዘነው የምንሔድ ነገር ምን አለ? ታድያ ለምን እንከራከራለን?›› (ሰማዕትነት አያምልጣችሁ እና ሌሎች፣ ገጽ ፻፶፮ – ፻፶፯)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ለምን አንጾምም?

ተወዳጆች ሆይ የተሃድሶ መናፍቃን በዓለ ሃምሳን ለምን አትፆሙም ሲሉ ይደመጣሉ ከዛም አልፎ በዓቢይ ጾም የጾማችሁትን ለማካካስ ነው በማለት ይተቻሉ ቅድስት ቤተክርስቲያናችንስ ምን ትላለች?

ጥያቄ:- በበዓለ ሃምሳ ለምን አንጾምም?
በፍትሐ ነገሥት ላይ እንዲህ የሚል ትዕዛዝ አለ፦ "ዳግመኛ በየሳምንቱ ዓርብ እና ረቡዕን መጾም ነው፡፡ በዓለ ሃምሳ፣ የልደት እና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልሆነ በቀር" /ዐንቀጽ 15:566/።

"የዓርብን እና የረቡዕን ጾም ግን ከልደት፣ ከጥምቀት እና ከበዓለ ሃምሳ በቀር ዘወትር ይጹሙ" /ዐንቀጽ
15:603/። የዐቢይ ጾምን ፍቺ ተከትሎ ለ50 ቀናት የማንጾምበት ምክንያት
ብዙ ጥልቅ ምሥጢር ያለው ሥርዓተ ሃይማኖት ነው። በምሳሌ ለማስረዳትም ፦ ከትንሣኤ በፊት ያለውን አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ብለን የምናስበው ዘመነ ኦሪት እንደሆነ በማሰብ ነው።
በዚኸ ሳምንት ከሌሎች ድርጊቶች በተጨማሪ መስቀል አንሳለምም። ይኸ የሆነበት ምክንያት በዘመነ ኦሪት መስቀል በክርስቶስ መለኮታዊ ደም ተባርኮ አልተሰጠም'ና ነው። ልክ
እንደዚሁ ከትንሣኤ ዕለት ጀምሮ አስከ በዓለ ጰራቂሊጦስ (አስከ የሐዋርያት ጾም መግቢያ ድረስ) ያሉት 50 ቀናት እንደ አንድ ቀን ነው የሚታዩት። ይህም ማለት ሰው ከትንሣኤ በኃላ ፍጹም
ያለ ድካም እንደሚኖር ለማስተማር ጾም እና የንስሐ ቀኖና አይሰጡም።
ከዕለተ ትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ

ከዕለተ ትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ባሉት ዕለታት በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሚፈጸመው መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ልክ እንደ መጀመሪያው የትንሣኤ ሥርዓት ኾኖ ይከናወናል፡፡ ከትንሣኤ እሑድ ጀምሮ እስከ ሳምንቱ እሑድ ድረስ የሚገኙት ዕለታትም ‹ሰሙነ ፋሲካ› ወይም ‹ትንሣኤ› እየተባሉ ይጠራሉ፤ የየራሳቸው ምሥጢራዊ ስያሜም አላቸው፡፡ ስያሜአቸውንም በአጭሩ እንደሚከተለው እንመለከታለን፤

ሰኞ

የትንሣኤው ማግሥት ዕለተ ሰኞ ‹ፀአተ ሲኦል› ወይም ‹ማዕዶት› ትባላለች፡፡ ይህቺውም ጌታችን በትንሣኤው ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ ወደ ገነት አሻግሮ ለማስገባቱ መታሰቢያ ናት (ዮሐ. ፲፱፥፲፰፤ ሮሜ. ፭፥፲-፲፯)፡፡

ማክሰኞ

ይህቺ ዕለት፣ ለሐዋርያው ቶማስ መታሰቢያ ትኾን ዘንድ ‹ቶማስ› ተብላ ትጠራለች፡፡ የትንሣኤው ዕለት እሑድ ማታ ጌታችን በዝግ ቤት ገብቶ ለሐዋርያት ሲገለጽ ቶማስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም፡፡ በመጣ ጊዜ ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሣኤውን ቢነግሩት ‹‹ሳላይ አላምንም›› ብሎ ነበር፡፡ በሳምንቱ እርሱ በተገኘበት ጌታችን በድጋሜ ለሐዋርያት ተገለጸ፡፡ ስለዚህም ይህቺ ዕለት በሐዋርያው ቶማስ ስም ተሰይማለች (ዮሐ. ፳፥፳፬-፴)፡፡

ረቡዕ

ጌታችን ከሞተና ከተቀበረ ከአራት ቀናት በኋላ ከመቃብር ጠርቶ ላስነሣው ለአልዓዛር መታሰቢያ ናት፡፡ በክርስቶስ ሥልጣን የአልዓዛርን ከሞት መነሣት አይተው ብዙ ሕዝብ በጌታችን ስለ አመኑ ዕለቲቱ (ረቡዕ) ‹አልዓዛር› ተብላ ትታሰባለች (ዮሐ. ፲፩፥፴፰-፵፮)፡፡
ኀሙስ

ይህቺ ዕለት ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም) ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤›› ተብሎ ቃል የተገባለት የአዳም ተስፋው ተፈጽሞ ከነልጅ ልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ኾና ‹የአዳም ኀሙስ› ወይም ‹አዳም› ተብላ ትከበራለች (ሉቃ. ፳፬፥፳፭-፵፱)፡፡

ዐርብ

የትንሣኤ እሑድ ስድስተኛዋ ዐርብ ደግሞ በክርስቶስ ደም ለተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መታሰቢያ ትኾን ዘንድ ‹ቤተ ክርስቲያን› ተብላ ትጠራለች (ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፱፤ ሐዋ. ፳፥፳፰)፡፡

ቀዳሚት ሰንበት

በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ቀዳሚት ሕዝቡ ከአንዳንዱ በቀር ገበያ እንኳን ስለማይገበያይባት ‹የቁራ ገበያ፣ የገበያ ጥፊያ› ተብላ ትጠራለች፡፡ በቤተ ክርስቲያን ደግሞ ጌታችን በዘመነ ሥጋዌው በገንዘባቸውና ጕልበታቸው ላገለገሉት፤ በስቅለቱ ጊዜ እስከ ቀራንዮ ድረስ ለተከተሉት፤ በትንሣኤው ዕለት በሌሊት ወደ መቃብሩ ሽቱና አበባ ይዘው ለገሰገሱት፤ በትንሣኤውም ጌታችንን ከዅሉ ቀድሞ ለማየት ለበቁት ሴቶች መታሰቢያ ትኾን ዘንድ ‹ቅዱሳት አንስት› ተብላ ትጠራለች (ማቴ. ፳፭፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፫፥፳፯-፴፫፤ ፳፬፥፩-፲)፡፡

እሑድ ሰንበት

በዋናው ትንሣኤ ሳምንት የምትመጣዋ ዕለተ እሑድ ‹ዳግም ትንሣኤ› ተብላ ትዘከራለች፡፡ ከላይ እንደ ተጠቀሰው ጌታችን በትንሣኤው ዕለት ማታ በዝግ በር ገብቶ፣ በቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ተገኝቶ ‹‹ሰላም ለዅላችሁ ይኹን!›› በማለት ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር፡፡ በኋላ ከሔደበት ሲመጣ ጌታችን እንደ ተነሣ እና እንደ ተገለጸላቸው ሐዋርያት በደስታ ሲነግሩት ‹‹በኋላ እናንተ ‹አየን› ብላችሁ ልትመሰክሩ፤ ልታስተምሩ፤ እኔ ግን ‹ሰምቼአለሁ› ብዬ ልመሰክር፤ ላስተምር? አይኾንም፡፡ እኔም ካላየሁ አላምንም›› አለ፡፡

ስለዚህም የሰውን ዅሉ፤ ይልቁንም የመረጣቸው የወዳጆቹን የልብ ዐሳብ የሚያውቀው፣ ቸርነቱ ወሰን የሌለው የባሕርይ አምላክ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ልክ እንደ መጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት አበው ሐዋርያት በተዘጋ ቤት በአንድነት ተሰባስበው እንዳሉ በሩን ሳይከፍት ገብቶ ‹‹ሰላም ለዅላችሁ ይኹን!›› በማለት በመካከላቸው ቆመ፡፡ ቶማስንም ‹‹ያመንህ እንጂ ተጠራጣሪ አትኹን፤ እነሆ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን፣ የተወጋ ጐኔንም ናና እይ፤›› ብሎ አሳየው፡፡

እርሱም ምልክቱን በማየቱ፣ በመዳሰሱ ትንሣኤውንና አምላክነቱን እንደ ፍላጎቱ በመረዳቱ ‹‹ጌታዬ፣ አምላኬ ብሎ መስክሮ›› የክርስቶስን ትንሣኤ አመነ፡፡ የሳምንቷ ዕለተ ሰንበት፣ የትንሣኤው ምሥጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት በመኾኑ የትንሣኤው ሳምንት እሑድ ‹ዳግም ትንሣኤ› ተብሎ ይጠራል፤ ይከበራል (ዮሐ. ፳፥፳፬-፴)፡፡

ብርሃነ ትንሣኤውን የገለጸልን አምላካችን ለብርሃነ ዕርገቱም በሰላም ያድርሰን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
በቅርብ ቀን በዐበይት ወቅታዊ ጉዳዮች ይጠብቁን!

በማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ብቻ!

* ከግንቦት እስከ ግንቦት

* የቅድስት ቤ/ክ ማእከላዊነት ላይ የተደቀኑ ፈተናዎች

* የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና መጠበቅ

* የመንግሥትና የሃይማኖት ድንበር

* ኦርቶዶክሳዊ ኅብረት ለምን?

* ዛሬ ምእመናን ከአባቶች ምን ይጠብቃሉ?

* መልሶ ማልማትና የሰንበት ት/ቤቶች አገልግሎት
ልደታ ለማርያም

በግንቦት አንድ ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደች። እርሷም ለሰው ሁሉ ወገን ድኅነት የሆነባት ናት፡፡ ከወንዶች ወገን የከበረ አባቷም ስሙ ኢያቄም ከሴቶች ወገን የከበረች ሚስቱ ሐና ይባላሉ፡፡ ሁለቱም ልጅ በማጣት ሲያዝኑ ኖሩ። በዚያ ወራት የመካኖች መብዓ ካህናቱ አይቀበሉም ነበርና፡፡ እነርሱም ከሰው የሚደርስባቸውን ሽሙጥና ኅዘናቸውን ያርቅላቸው ዘንድ በቀንና በሌሊት ወደ እግዚአብሔር ፈጽሞ ይማልዱ ነበር፡፡

ሰውን የሚወድ እግዚአብሔርም ከዘራቸው ለዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ይሆን ዘንድ መልካም የሆነ ሐሳባቸውን ተመለከተ፡፡ ክቡር ኢያቄምም አርባ ቀን እስኪፈጸም በተራራ ውስጥ ቁሞ ሲጸልይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተገለጸለትና ለዓለሙ ሁሉ ድኅነት የሚደረግባት ዘር እንደሚሰጠው አበሠረው፡፡

በፍጹም ልብ አምኖ ከተራራው ወረደ፤ ለተመሰገነች ሚስቱ ለሐናም ከእግዚአብሔር መልአክ የሰማውን ያንን ራእይ ነገራት። ቃሉ እውነት እንደሆነ እርሷም አመነች። ልዑል እግዚአብሔርንም አመሰገነች። የተመሰገነች ቅድስት ሐናም ከእርሷ የሚወለደውን በዘመኑ ሁሉ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ታደርገው ዘንድ ለእግዚአብሔር ስለትን ተሳለች፡፡

ከዚህም በኋላ ይህችን የከበረች ሕፃን ፀንሳ ወለደች። ስሟንም ‹ማርያም› ብላ ሰየመቻት። ትርጓሜውም ‹እመቤት› ነው። ‹ደግሞም ሀብታና ስጦታ› ማለት ነው፡፡ በእውነት የዓለሙ ሁሉ እመቤት ሁላችን በእርሷ ሰማያዊ ሀብት ልጅነትን ያገኘንባት ናትና።

የሥጋና የነፍስ መድኃኒት የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከቷም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ለዘለዓለሙ ይኑር፤ አሜን፡፡

ከመጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ግንቦት