ወግ ብቻ
19.3K subscribers
506 photos
11 videos
20 files
49 links
በየቀኑ ምርጥ ምርጥ የጥበብ ስራዎችን ለማግኘት የቻነላችን ተከታይ ስለሆኑ እናመሰግናለን።

@getem @serenity13
@wegoch @Words19
@seiloch
@zefenbicha

Creator @leul_mekonnen1
Download Telegram
የአይነስውሩ ማስታወሻ.
_______

መምህር አብርሀም እባላለሁ ከሰንዳፋ ወጣ ብላ በምትገኝ ሶኮሩ አንደኛ ደረጃ ትምህርትቤት ውስጥ የአማርኛ መምህር ነኝ. ሶኮሩ ገና በዳዴ እየሄደች ያለችና ነዋሪዎቿም  እንደማንኛውም ኢትዮጲያዊ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የእርሻ ስራ የሚኖሩባት የገጠር ከተማ ነች. የሶኮሩ ሰው #አደራ ተይልዬ ሴና. ብሎ በኦሮሚኛ አንደበት እንግዳን ሲቀበል አንጀት ያላውሳል. ትርጉሙም በተክልዬ ጎራበሉ እንደማለት ነው ትምህርት ቤቱ ያለበት ስፍራ ለአካልጉዳተኞች አስቸጋሪ ከመሆኑ በተጨማሪ በቂ የብሬል መፅሀፍት እንዲሁም የአይናማ ፅሁፎችን የሚያነብልኝ ሰው አለመኖሩ ስራዬን ፈታኝ ቢያደርገውም  እኔ ግን የዚህን የዋህ እና ገራገር ህዝብ ልጆች ሳስተምር ታላቅ የሆነ የመንፈስ እርካታ ይሰማኛል. በዚህች ቦታ የገበያ እንቅስቃሴው ደካማ በመሆኑ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ቅዳሜ ቅዳሜ ወደሰንዳፋ ሄጄ የመሸመት ልምድ አለኝ. ሰንዳፋ በፍጥነት እያደጉ ካሉ ከተሞች አንዷ ስትሆን ከ አዲሳበባ ቅርብ ርቀት ላይ መገኘቷ ለዚህ እድገቷ ትልቅ አስተዋፆ አለው. እንደተለመደው በአንደኛው ቅዳሜ ከሰንዳፋ እቃ ሸምቼ የተፈጥሮ ግዴታዬን ለመወጣት እንዲሁም የሆዴን አመፃ ለማስቆም የሰንዳፋ መናሀርያ ውስጥ በሚገኘው መፀዳጃ ቤት ለመጠቀም ስገባ የመፀዳጃ ቤቱ ጥበቃ በተለመደችው የከንፈር መጠጣ ተቀበለኝ. ይህች ከንፈር መጠጣ እንኳን ከዚህ ሰው አብረን ከምናስተምረው መምህራን ጭምር  አለፍ ሲልም ከነዋሪው ሳይቀር ስለምትደርሰኝ አይምሮዬ ኖርማል ከማድረጉ የተነሳ ሰላም የሚሉኝ ስለሚመስለኝ እግዚአብሄር ይመስገን ለማለት አስብና ተወዋለሁ. መፀዳጃ ቤት ውስጥ እንደ ደራሲ ስብሀት ገብረእግዚአብሄር አዲስ ሀሳብ ሳላመነጭ የባጥ የቆጡን ሳስብ የሆነ ሀሳብ መጣልኝ: ጋሽ ስብሀት ግን ድርሰቶቹ ትንሽ ወጣ ያሉት ሀሳቡ ሽንትቤት ውስጥ ስለሚመጣለት ይሆን እንዴ? እያልኩ ሳሰላስል ቶሎ እየወጣችሁ የሚለው  የመፀዳጃ ቤቱ ጥበቃ ሰላላ ድምፅ ከሀሳቤ መለሰኝ. ወትሮውንም እዛ መቆየት ማልወደው እኔ ሱሬዬን እያስተካከልኩ ሽንትቤት ውስጥ ከ 30 እስከ 40 ደቂቃ #ትመጪንደው የሚለውን የሚካኤል በላይነህን ሙዚቃ እየሰማ የሚቆየው ጓደኛዬ እና እንዲሁም አለምን የቀየሩ የሳይንስና የፍልስፍና ውጤቶች እዚህ ቦታላይ እንደተወጠኑ ማንበቤ ታወሰኝ. ከመፀዳጃ ቤቱ ወጥቼ  ከሆቴል እንደወጣ ሰው ሂሳብ ስንት ነው? ብዬ ጥበቃውን ጠየኩት ጥበቃውም በሀዘኔታ ድምፅ አምስት ብር ሲለኝ ኪሴ የቀረችውን አስር ብር አውጥቼ ሰጠሁትና መልስ መጠበቅ ጀመርኩ: ጥበቃውም አምስት የብር ሳንቲሞች እየሰጠኝ አይዞህ መንገድ ላይ ኪሽ ኪሽ እያረክ ለመሄድ ይጠቅምሀል ሲለኝ በድንጋጤ ሳንቲሞቹን ለቀኳቸውና የምለው ስለጠፋብኝ በደመነፍስ የምመራበት ኬኔን ዘርግቼ ሳወናጭፍ ጥበቃው ጎንበስ በማለቱ ኬኔ አየሩን ሰንጥቆ ወደኔው ተመለሰ. ይህን ሲከታተል የነበረ አንድ በድምፁ ስገምተው ወደ ሀምሳዎቹ መጀመሪያ ያለ ጎልማሳ መሀላችን በመግባት አረጋጋን ከዛም ጥበቃውን ገሰፀውና ሳንቲሞቹን ከመሬት ለቅሞ ሲሰጠኝ እኔ በበኩሌ አልቀበልም, ከተቀበልኩ ፈጣሪ አይቀበለኝ. ይልቁንስ ለሱ ስጠው ብዬ መልስ ሳልጠብቅ በጣም ተናድጄ ስለነበር በፍጥነት በመውጣት ሄድኩኝ. እናንተዬ ግን እስከመቼ ይሆን አንዳንድ ሰዎች ሁሉም አይነስውር ለማኝ የሚመስላቸው? በኔ በኩል ሚዲያላይ የሚቀርቡ አንዳንድ ፊልሞችና ድራማዎች አይነስውራንን ለማኝ አድርገው በመሳላቸው , በቂ የሆነ ግንዛቤ ባለድርሻ አካላት ባለመስጠታቸውና እንዲሁም ሁሉንም በአንድ የመፈረጅ ማህበራዊ በሽታ ጉልህ ድርሻ አላቸው ብዬ አስባለሁ. እንደመፍትሄም ባለድርሻ አካላት አስተማሪ በሆነ  ኪነጥበባዊ መንገድ የአይነስውራንን ውስጣዊ ብቃት ማሳየት ቢችሉ, መንግስትና መንግስታዊ  ያልሆኑ ድርጅቶች ተናበው ለይስሙላ ያልሆነና ለህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤን የሚፈጥር ስራን በብቁ ባለሞያዎች ቢሰሩ, አይነስውራን ከትምህርት ጎን ለጎን ያላቸውን ሞያ ወይም ውስጣዊ ክህሎት አውጥተው ቢጠቀሙ, ለዚህም መምህራን አይነስውራን ተማሪዎችን ገና ከልጅነታቸው በውስጣቸው ያለውን ነገር እንዴት አውጥተው መጠቀም እንደሚችሉ ቢያግዟቸው ጥሩ ውጤት ያስገኛል  ብዬ አስባለሁ

By ጫላ መኮንን

@wegoch
@wegoch
@paappii