Wazema Media / Radio
48.9K subscribers
191 photos
36 videos
7 files
933 links
Wazema Radio other contents are available either in our website/social media or FM radio stations in Ethiopia. www.wazemaradio.com
Download Telegram
ለቸኮለ! ሰኞ መጋቢት 16/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የአማራ ክልል መንግሥት በኃይል የተቆጣጠራቸውን የትግራይ ግዛቶች የሥርዓተ ትምህርቱ አካል በማድረግ ተማሪዎችን እያስተማረ እንደኾነ ደርሼበታለኹ ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ከሷል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ የክልሉ ሥርዓተ ትምህርት "ሃላፊነት የጎደለው" እና "ትግራይን በመቆራረስ የማጥፋት ዘመቻው አካል ነው" ብሏል። የአማራ ክልል መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ላይ እየፈጸመ በሚገኘው ግፍ በኋላ ከመጸጸት ይልቅ፣ ባስቸኳይ ታሪካዊ ስህተቶቹን ማረም አለበት በማለትም ጊዜያዊ አስተዳደሩ አሳስቧል። በዚህ ረገድ የአማራ ሕዝብና ሌሎች የአገሪቱ ሕዝቦች ከትግራይ ሕዝብና ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን እንዲቆሙም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጠይቋል።

2፤ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ በክልሉ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ መሬት ላልወሰዱ የክልሉ መምህራን ቦታ እንዲሰጣቸው መመሪያ ማስተላለፋቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል። የክልሉ መንግሥት ከዚህ ቀደም ለክልሉ መምህራን በገጠር ተሰርቶ ያለቀ ቤት እንዲኹም በከተሞች የቤት መስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው መመሪያ ወጥቶ እንደነበር የጠቀሰው ቢሮው፣ ከመሬት አሰጣጥ ሂደት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ታግደው እንዲቆዩ በመደረጉ መምህራኑ መሬቱን እንዳልወሰዱ አስታውሷል። ኾኖም በቢሮው ጥያቄ መሠረት፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት እገዳውን ላንድ ጊዜ ብቻ በማንሳት መኖሪያ ቤት የሌላቸውና የቤት መስሪያ ቦታ ያልወሰዱ መምህራን መሬት እንዲሰጣቸው ማዘዙን ቢሮው ገልጧል።

3፤ የኢትዮጵያ የሰነድ መዋዕለ ንዋይ ገበያ፣ ከቀነ ገደቡ አስቀድሞ መነሻ ካፒታሉን ሙሉ በሙሉ ማሰባሰብ መቻሉን ለሸገር ተናግሯል። ኾኖም ኩባንያው ቀደም ሲል እስካስቀመጠው ቀነ ገደብ መጋቢት 20 ድረስ የአክሲዮን ድርሻ ሽያጩንና የካፒታል ማሰባሰብ ሥራውን እንደሚቀጥልና ከዚያም ወደ ሥራ እንደሚገባ አስታውቋል። የሰነድ መዋዕለ ንዋይ ገበያው መነሻ ካፒታል ከኾነው 1 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ 25 በመቶውን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ቀደም ሲል መግዛታቸው ይታወሳል። 50 በመቶውን ድርሻ ደሞ ንግድ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ገዝተውታል። የውጭ ኩባንያዎች በሰነድ መዋዕለ ንዋዩ የአክሲዮን ድርሻ በመግዛት ረገድ ያሳዩት ፍላጎት ግን እንደተጠበቀው እንዳልኾነ ኩባንያው ገልጧል። በሰነድ መዋዕለ ንዋይ ኩባንያው የተቀመጠው ዝቅተኛው የባለቤትነት ድርሻ 10 ሚሊዮን ብር ሲኾን፣ ከፍተኛው ድርሻ ደሞ 150 ሚሊዮን ብር ነው።

4፤ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ የቆንስላ ጉዳዮች ረዳት ሚንስትር ሪና ቢተር ከመጋቢት እስከ በኢትዮጵያ እና ናይጀሪያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ቢተር በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው፣ ከኢትዮጵያ ኢምግሬሽን ባለሥልጣናት እና ከአሜሪካ ኢምባሲ ቆንስላ ሃላፊዎች ጋር እንደሚወያዩ መስሪያ ቤቱ ገልጧል። መስሪያ ቤቱ፣ የረዳት ሚንስትሯ ጉብኝት አሜሪካ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ዜጎቿ የደኅንነት ጥበቃ እንዲኹም በአሜሪካ ለመኖርም ኾነ ለሌላ ዓላማ ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የሚደረጉ ሕጋዊ ጉዞዎችን ለማቀላጠፍ ያላትን ቁርጠኝነት ያረጋግጣል ብሏል።

5፤ የኬንያ ፖሊስ በመርሳቢት አውራጃ ሞያሌ አካባቢ በሚገኝና በቅርቡ በተዘጋ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ቦታ ኹለት ሴቶችን ጨምሮ አምስት ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን ማሠሩን ዘ ስታር ጋዜጣ ዘግቧል። ፖሊስ ከኢትዮጵያዊያኑ ጋር አራት ጄነሬተሮች፣ ኹለት የማዕድን ማውጫ መሳሪያዎችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን እንዳገኘ ዘገባው ገልጧል። ኢትዮጵያዊያኑ ወደ ኬንያ በሕገወጥ መንገድ በመግባት እና ሕገወጥ የማዕድን ቁፋሮ በማካሄድ ክስ ይመሠረትባቸዋል ተብሏል።
የአገሪቱ መንግሥት የወርቅ ማዕድን ማውጫው እንዲዘጋ ያዘዘው፣ በማዕድን ማውጫ ቦታ ይዞታ ፉክክር በተቀሰቀሰ ጥል ኹለት ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው። ፖሊስ፣ በኬንያዋ ኢሲዮሎ አውራጃም ሌሎች አምስት ኢትዮጵያዊያን ማዕድን ቆፋሪዎች እንዳሠረ ተገልጧል።

6፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ5947 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ7266 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 67 ብር ከ9977 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ3577 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ61 ከ2015 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ4255 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
-ዘንድሮ ከ261 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ሥራ ፈላጊዎች ወደ ውጭ አገራት ተልከዋል
-መንግስት ግማሽ ሚሊየን ዜጎችን በዚህ ዓመት ወደ ውጪ ሀገር ለመላክ እየሰራሁ ነው ብሏል
ዝርዝሩን ያንብቡት- https://tinyurl.com/nhfvpzy2
ለቸኮለ ማለዳ! ማክሰኞ መጋቢት 17/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን የፋኖ ታጣቂዎች አግተዋቸው የነበሩ 271 የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጋርዱላና አሌ ዞኖች ተወላጆች የኾኑ የቀን ሠራተኞች ትናንት አርባምንጭ ገብተዋል። ባለፈው ሳምንት ዓርብ የተለቀቁት ታጋቾች በአርባምንጭ ከተማ የስነ ልቦና ማገገሚያ ሥልጠና እየወሰዱ መኾኑን የጋርዱላ ዞን አስተዳደር ገልጧል። የዞኑ አስተዳደር፣ ታጋቾቹ የተለቀቁት ፌደራል መንግሥቱ፣ የአማራ ክልል መንግሥትና የኃይማኖት አባቶች ባደረጉት ጥረት መኾኑን ባለፈው ሳምንት መግለጡ ይታወሳል። ከሦስት ሳምንታት በፊት ወደ ሕዳሴ ግድብ ለምንጣሮ ሥራ በአውቶብስ በመጓዝ ላይ ሳሉ የታገቱት ታጋቾች 273 እንደነበሩ የገለጠው የዞኑ አስተዳደር፣ የቀሪዎቹን የኹለቱን ታጋቾች እጣ ፋንታ ለጊዜው አለማወቁን ገልጧል።

2፤ ኢሰመጉ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲውን "በግልጽ" እና "ኹሉን አሳታፊ" በኾነ መንገድ እንዲተገብር ጥሪ አድርጓል። ኢሰመጉ በፖሊሲው ዙሪያ ግልጽነት መኖሩና ኹሉን አሳታፊ መኾኑ፣ የመብት ጥሰት ተጠያቂነትን ለማሰፈን፣ ለተጎጂዎች የካሳ ክፍያን ለማስገኘት እንዲኹም ከባድ የመብት ጥሰቶች በድጋሚ እንዳይከሰቱ ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ገልጧል። ፌደራል መንግሥቱና የክልል መንግሥታት የሽግግር ፍትህን ለማስፈን "ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት" እና "ትብብር" እንዲያሳዩ የጠየቀው ኢሰመጉ፣ በዚህ ረገድ ሰሞኑን ዘመቻ መጀመሩን አስታውቋል።

3፤ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፣ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ 20 የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ትናንት በከተማዋ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አስታውቋል። በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩት የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች "ቬሎሲቲ ኤክስፕረስ" የተባለ የግል ድርጅት ያሠማራቸውና የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የገጣጠማቸው ናቸው። አውቶብሶች፣ ከቦሌ በአራት ኪሎና ስድስት ኪሎ በኩል ወደ ሽሮ ሜዳ መስመር የሚያገለግሉ እንደኾኑና አገልግሎት የሚሰጡት እስካኹን ባለው ታሪፍ እንደኾነ ቢሮው ገልጧል።

4፤ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዓሊ ሳዲቅ እና የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አዛዦች፣ ኢራን ለሱዳን ጦር መሳሪያ አላቀረበችም በማለት አስተባብለዋል። ከጦር ሠራዊቱ አዛዦች አንዱ ጀኔራል ኢብራሂም ጃቢር፣ ሱዳን ከኢራን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ማሻሻሏ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ከመጀመር አያግዳትም በማለት መናገራቸውን ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል። ሱዳንና ኢራን ኢምባሲዎቻቸውን ለመክፈት ቀደም ሲል ተስማምተው ነበር። ኢራን በሱዳን የቀይ ባሕር ዳርቻ የባሕር ኃይል ጣቢያ ልትከፍት እንደኾነ የተሠራጩ መረጃዎችን፣ ኹለቱም አገሮች በቅርቡ ማስተባበላቸው ይታወሳል።

5፤ የተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮች ቢሮ ረዳት ዋና ጸሃፊ ማርቲን ግሪፊትስ "በጤና ምክንያት" በመጭው ሰኔ ወር ሥልጣን ሊለቁ መኾኑን ትናንት አስታውቀዋል። ግሪፊትስ፣ ከሥልጣን እንደሚለቁ ለተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ማሳወቀቸውን ገልጠዋል። ግሪፊትስ ቢሮውን ላለፉት ሦስት ዓመታት የመሩ ሲኾን፣ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳቢያ በተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ለጸጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ ሪፖርቶችን ማቅረባቸውና ዓለማቀፍ ረድዔት ድርጅቶችም ለጦርነቱ ተጎጂዎች ዕርዳታ እንዲለግሱ ግፊት ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ማክሰኞ መጋቢት 17/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ወረዳ ዶዶላ ከተማ የታጠቁ ኃይሎች ትናንት ምሽት በፈጸሙት ጥቃት ኹለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልጋዮችን ጨምሮ ሰባት ሰዎች እንደተገደሉ ዋዜማ በሥፍራው ከሚገኙ ምንጮቿ ሰምታለች። በጥቃቱ በዶዶላ ከተማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን በተለያዩ የሃላፊነት ደረጃዎች ሲያገለግሉ የነበሩት መሪጌታ ሠምረ ምናሴ እንዲኹም ባለቤታቸውና ኹለት ልጆቻቸው በቤታቸው ውስጥ እንዳሉ መገደላቸውን ዋዜማ ተረድታለች። የዶዶላ ደብረ ቅዱሳን ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ዲያቆን ዳንዔል የተባሉ አገልጋይ፣ ባለቤታቸውና አክስታቸው በታጣቂዎቹ በተመሳሳይ ሁኔታ መገደላቸውን ምንጮች አስረድተዋል፡፡ የጸጥታ ኃይሎች ባካባቢው ሲደረሱ ታጣቂዎቹ መሠወራቸውን የገለጹት ምንጮች፣ ባካባቢው መሰል ሐይማኖት-ተኮር ጥቃት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው እንዳለኾነ ጠቁመዋል፡፡

2፤ የሥራና ክህሎት ሚንስቴር ከ261 ሺሕ በላይ ሥራ ፈላጊዎችን መንግሥት የሥራ ሥምሪት ውል ወደተዋዋለባቸው አገራት መላኩን ለዋዜማ ገልጧል። በ2015 ዓ፣ም ከ102 ሺሕ በላይ ሥራ ፈላጊዎች ወደ ውጭ አገራት ተልከዋል ያለው ሚንስቴሩ፣ ዘንድሮ 500 ሺሕ ዜጎችን ለመላክ ማቀዱን የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊው አበበ አለሙ ተናግረዋል። ከ99 በላይ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ወደ ውጭ ለሚላኩት ሠራተኞች ሥልጠናና የብቃት መመዘኛ እየሰጡ እንደኾነም ዋዜማ ተረድታለች። በዋናነት ኢትዮጵያዊያን የቤት ውስጥ ሠራተኞችን ለመቀበል ከመንግሥት ጋር ውል የፈረሙት፣ የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች፣ ሳውዲ ዓረቢያ፣ ኳታር እና ዮርዳኖስ እንደኾኑ ተገልጧል። መንግሥት የሥራ ሥምሪት መዳረሻዎቹን በማስፋት፣ ለሙከራ ወደ ጀርመን የላካቸው መሃንዲሶች እንዳሉም አበበ ተናግረዋል።

3፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፣ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን በተፈጰሙ ጥቃቶች ንጹሃን ሰዎች መገደላቸው፣ መቁሰላቸውና መፈናቀላቸው አስደንጋጭ እንደኾነ አስታውቀዋል። አምባሳደሩ፣ ማንኛውም የግጭቱ ተዋናይ ኃይልን በመጠቀም ሰዎችን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረግ እንደሌለበት ገልጠዋል። ንጹሃን ከጥቃት እንዲጠበቁ ጥሪ ያደረጉ ሲኾን፣ የኢትዮጵያን ውስብስብ የፖለቲካና ጸጥታ ችግሮች ለመፍታት ለንግግር ቁርጠኛ መኾን እንደሚያስፈልግም አምባሳደር ማሲንጋ አሳስበዋል። አምባሳደር ማሲንጋ ይህን መልዕክት ያስተላለፉት፣ ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ጋር በተነጋገሩ ማግስት ነው።

4፤ ንግድ ባንክ መጋቢት 06 ቀን በፋይናንስ አገልግሎት ሥርዓቱ ላይ ባጋጠመው ችግር በሕገወጥ መንገድ የተወሰደበት አጠቃላይ የገንዘብ መጠን ከ801 ሚሊየን ብር በላይ እንደኾነ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ባንኩ፣ ከተወሰደበት ገንዘብ ውስጥ 78 በመቶውን ማስመለሱን ገልጧል። ባንኩ በመጀመሪያው ቀን ብቻ በሕገወጥ መንገድ ብር ከወሰዱ ከ10ሺ 727 ደንበኞቼ አካውንት ውስጥ በቂ ገንዘብ በማግኘቴ ከ44 ሚሊዮን በላይ አስመልሻለሁ ብሏል። ከ9 ሺ በላይ የራሳቸው ያልኾነ ገንዘብ የወሰዱ ደንበኞች በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት ገንዘቡን ሙሉ በሙሉ እንደመለሱ የገልጠው ባንኩ፣ ከ5 ሺ በላይ የሚኾኑ ደንበኞች ደሞ ከወሰዱት የራሳቸው ያልኾነ ገንዘብ ውስጥ በከፊል መልሰዋል ብሏል። ባንኩ እስከ ትናንት ድረስ 623 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ማስመለሱንና 567 ደንበኞች ግን ከወሰዱት ገንዘብ ውስጥ ምንም ገንዘብ ተመላሽ እንዳላደረጉም ገልጧል።

5፤ ንግድ ባንክ በፋይናንስ አገልግሎቱ ላይ ችግር ባጋጠመው ወቅት የማይገባቸውን ገንዘብ ወስደው እስካኹን ያልመለሱ 565 ደንበኞቹን ስም፣ የሒሳብ ቁጥር እና ሒሳባቸው የሚገኝበትን ቅርንጫፍ ዝርዝር ዛሬ በድረገጹ ይፋ አድርጓል። ባንኩ፣ የራሳቸው ያልኾነ ገንዘብ የወሰዱ ደንበኞች ገንዘቡን እንዲመልሱ እስከ ቀጣዩ ቅዳሜ ምሽት 11:00 ሰዓት ድረስ ተጨማሪ ቀነ ገደብ ሰጥቷል። ባንኩ፣ በቀነ ገደቡ ገንዘቡን የማይመልሱ ደንበኞቹን ስም ዝርዝርና ፎቶ በወንጀል መጠርጠራቸውን ጭምር በመጥቀስ፣ በመገናኛ ብዙሃን እንደሚገልጽና ከሕግ አካላት ጋር በመተባበር የወንጀል፣ የፍትሃ ብሄርና አስተዳደራዊ ርምጃዎችን እወስዳለሁ በማለት አስጠንቅቋል።

6፤ ሶማሊላንድ፣ የሱማሊያ የአየር በረራ ተቆጣጣሪዎች ዕሁድ ሌሊት የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢምሬቶች አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላኖች በሱማሊያ አየር ክልል ውስጥ ባንድ የበረራ መስመርና ከፍታ በተመሳሳይ ሰዓት እንዲበሩ የተሳሳተ መመሪያ ሰጥተው ነበር በማለት ከሳለች። የበረራ ቁጥሩ 690 የኾነው የኢትዮጵያ አየር መንገድና የበረራ ቁጥሩ 722 የኾነው የኢምሬቶች አውሮፕላን ለጥቂት ከመላተም የተረፉት፣ የሶማሊላንድ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ጣልቃ ገብተው በተለያየ ከፍታ እንዲበሩ የበረራ መመሪያ በመስጠታቸው እንደኾነ የሶማሊላንድ ሲቪል አቬሽን አስታውቋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪም፣ በፍጥነት የአውሮፕላኑን ከፍታ ከ37 ሺህ ጫማ ወደ 39 ሺህ ጫማ በመጨመሩ ሊከሰት የነበረውን አደጋ መቀልበስ እንደቻለ ባለሥልጣኑ ገልጧል። ባለፈው ወር፣ የሱማሊያ የበረራ ተቆጣጣሪዎች ተመሳሳይ የተሳሳተ መመሪያ በመስጠታቸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሌላ አየር መንገድ አውሮፕላን ጋር ከመላተም እንደተረፈ ይታወሳል።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ5998 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ7318 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 68 ብር ከ3281 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ6947 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ61 ከ3089 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ5331 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ረቡዕ መጋቢት 18/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ሰኞ ሌሊት 10:00 እስከ ማክሰኞ እኩለ ቀን ገደማ ራያ ውስጥ በመሆኒ እና በአላማጣ መካከል በርተክላይ በሚባል ቦታ በትግራይ ኃይሎች እና ባካባቢው ሚሊሻዎች መካከል ግጭት መካሄዱን ዋዜማ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምታለች። የአካባቢው ሚሊሻዎች ተጨማሪ ኃይል ከአላማጣ ወደ ቦታው ለማሳለፍ ሲሞክሩ፣ በቦታው የሠፈረው መከላከያ ሠራዊት እንዳገዳቸውና ይህንኑ ተከትሎ የተኩስ ልውውጥ እንደተደረገ ምንጮች ተናግረዋል። ግጭቱን ተከትሎ፣ መከላከያ ሠራዊት ከአላማጣ ወደ በርተኽላይ በሚወስደው መንገድ ላይ ሚሊሺዎችና ወጣቶች እንዳያልፉ መንገዱን መዝጋቱንና ከአላማጣ ወደ መቀሌ የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡን ዋዜማ ተረድታለች።

2፤ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ፣ በኢትዮጵያ በየካቲት ወር ብቻ በወባ በሽታ 764 ሰዎች እንደሞቱ አዲስ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል። በየካቲት በበሽታው የሞቱት ሰዎች ብዛት በጥር ወር ከሞቱት ጋር ሲነጻጸር በ25 በመቶ እንደጨመረ ቢሮው ገልጧል። በተያዘው ዓመት በአገሪቱ በበሽታው 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች እንደተያዙ የገለጠው ቢሮው፣ በበሽታው በተያዙ ሰዎች ብዛት ኦሮሚያ ክልል ቀዳሚ መኾኑንና አማራ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች በቅደም ተከተል እንደሚከተሉ ጠቅሷል።

3፤ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይዎት ታምሩ የመንግሥትና የግል የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች ደንበኞች ብዛት በድምሩ 85 ሚሊዮን መድረሱን ትናንት በዲጂታል ማስፋፊያ ዙሪያ በተካሄደ አንድ መድረክ ላይ ተናግረዋል። ኢትዮ ቴሌኮም እና ሳፋሪኮም ኩባንያ በጠቅላላው ለ96 ሚሊዮን ደንበኞች አገልግሎት መስጠት የሚችል የኔትዎርክ መሠረተ ልማት መዘርጋታቸውንም ፍሬሕይዎት ገልጸዋል። በአገሪቱ ባኸኑ ወቅት የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚው ሕዝብ ብዛት ከ40 ሚሊዮን በላይ እንደደረሰም ተገልጧል።

4፤ የኬንያ መንግሥት የፕላስቲክ መያዣዎች ከኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ እንዳይገቡ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ሊጀምር መኾኑን ዘ ስታር ጋዜጣ ዘግቧል። የኬንያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የፕላስቲክ መያዣዎች እንዳይገቡ ለመከላከል ሞያሌ የድንበር መቆጣጠሪያ ጣቢያ ላይ የራሱን ቢሮ ለመክፈት ዝግጅት ላይ እንደኾነ ዘገባው ጠቅሷል። ኬንያ፣ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ስትል የፕላስቲክ መያዣዎች እንዳይመረቱና ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ሕግ አውጥታ ተፈጻሚ ማድረግ ከጀመረች ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ረቡዕ መጋቢት 18/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ዛሬ በጋምቤላ ክልል ባንድ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ በተፈጸመ ጥቃት በትንሹ ሦስት ሰዎች እንደተገደሉና ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች እንደቆሰሉ ዋዜማ ሰምታለች። ጥቃቱ የተፈጸመው አውቶብሱ መንገደኞችን አሳፍሮ ከጋምቤላ ከተማ ወደ ኑዌር ዞን ላሬ ወረዳ በመጓዝ ላይ ሳለ በጋምቤላ ዙሪያ ወረዳ ከአቦል ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ እንደኾነ ታውቋል። በአውቶብሱ ላይ ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች ማንነት ለጊዜው እንዳልታወቀ ዋዜማ ተረድታለች።

2፤ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ድርጅት፣ የኢትዮጵያን ገቢ እና ወጪ ሸቀጦች ያጓጉዙ የነበሩ የንግድ መርከቦች በቀይ ባሕር ላይ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሳቢያ ወደ ጅቡቲ ወደብ መምጣት በማቆማቸው የአገሪቱን ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ችግር እንደፈጠረ አስታውቋል። በዚህ ሳቢያ በአገሪቱ የወጪና ገቢ ንግድ ላይ መስተጓጎል እንዳይፈጠር፣ ድርጅቱ ብዛት ያላቸው ገቢ ሸቀጦች ወደሚነሱባቸው ወደቦች የራሱን መርከቦች በብዛት በማሠማራት የካርጎ ጭነቶች እንዲገቡ በማድረግ ላይ እንደኾነ ገልጧል። ላኪዎች የድርጅቱ መርከቦች በቋሚነት በሚመላለሱባቸው የቻይናው ቲያንጂ እና ሻንጋይ ወደቦች፣ የሕንዶቹ ሙንድራ እና ናቫ ሺቫ ወደቦች እንዲኹም የኤምሬቶች ጀበልዓሊ እና ሻርጃ ወደቦች በኩል መጠቀም እንደሚችሉም ድርጅቱ ጠቁሟል።

3፤ እናት ፓርቲ፣ መንግሥት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በኦርቶዶክስ ኃይማኖት አባቶችና ምዕመናን ላይ የሚፈጸሙ አሰቃቂ ግድያዎችን እንዲያስቆምና ከንጹሃን ደም ነጻ መኾኑን ባስቸኳይ እንዲያረጋግጥ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። ፓርቲው፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ከተማ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ካህናትና ሌሎች ንጹሃን ላይ የታጠቁ አካላት በፈጸሙት ጥቃት፣ የደብረ ቅዱሳን ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አገልጋይ መርጌታ እና አንድ ዲያቆን እንዲኹም ቤየተሰባቸው አባላትን ጨምሮ ሰባት ሰዎች እንደተገደሉ ማረጋገጡን ገልጧል። ከደቡቡ የአገሪቱ ክፍል ሂደው በከተማዋ በጉልበት ሥራ ይተዳደሩ የነበሩ እራት ንጹሃንም በታጣቂዎቹ ጥቃት መገደላቸውን የጠቀሰው ፓርቲው፣ ሌሎች በጥቃቱ የቆሰሉ ሰባት ሰዎች ደሞ በዶዶላ አጠቃላይ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ተረድቻለኹ ብሏል።

4፤ የኬንያ ፖሊስ በኢትዮጵያ አጎራባች መርሳቢት አውራጃ ሞያሌ አካባቢ ወደሚገኝ አንድ የተዘጋ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ሥፍራ ሲጓዙ ያገኛቸውን ሰባት ኢትዮጵያዊያን ሰኞ'ለት ማሠሩን ዘ ስታር ጋዜጣ ዘግቧል። የአገሪቱ ፖሊስ በቅርቡ በተዘጋው የማዕድን ማውጫ ቦታ ባለፈው ዕሁድ ወርቅ በማውጣት ላይ የነበሩ አምስት ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን ማሠሩን ጋዜጣው መዘገቡ ይታወሳል። የአገሪቱ መንግሥት የወርቅ ማዕድን ማውጫውን ሥፍራ የዘጋው፣ የተለያዩ የታጠቁ ማዕድን ቆፋሪ ቡድኖች የማዕድን ማውጫ ቦታውን ለመቆጣጠር በፈጠሩት አምባጓሮ ሳቢያ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ እንደኾነ ዘገባው አመልክቶ ነበር።

5፤ ኢጋድ ለሱዳኑ ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄ ለማፈላለግ ደቡብ ሱዳናዊውን የሕግ ባለሙያ ሎረንስ ኮርባንዲን ልዩ መልዕክተኛው አድርጎ ሾሟል። ልዩ መልዕክተኛው፣ ተፋላሚ ወገኖችን በማነሃገር መፍትሄ የሚያፈላልጉ ሲኾን፣ ኢጋድ ለጦርነቱ መፍትሄ ለማስገኘት ምን ዓይነት አቅጣጫዎችን መከተል እንዳለበትም ያማክራሉ። ሱዳን ኢጋድ በጦርነቱ አድሏዊ ኾኗል በማለት ከድርጅቱ ጋር ግንኙነቷን ያቋረጠች ቢኾንም፣ ኢጋድ ግን ጦርነቱ እንዲያበቃ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ማድረጉን እንደሚቀጥል በመግለጽ ላይ ይገኛል። የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ አፍሪካ ኅብረት እና አሜሪካም፣ ለሱዳን ቀደም ሲል ልዩ ልዑኮችን ሰይመዋል።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ6083 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ7405 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 68 ብር ከ4195 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ7879 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ61 ከ4370 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ6657 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሐሙስ መጋቢት 19/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ዛሬ ከቀኑ 09:46 ጀምሮ ከባሕርዳርና አካባቢው በስተቀር በመላ አገሪቱ ኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦ እንደነበር አስታውቋል። ተቋሙ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በመላ አገሪቱ ተቋርጦ የነበረው፣ በሲስተም ላይ በተፈጠረ ችግር ነበር ብሏል። ኾኖም ከምሽቱ 11:30 ገደማ ጀምሮ፣ አዲስ አበባና አብዛኞቹ እንደገና ኃይል እንዳገኙ ተቋሙ የገለጠ ሲኾን፣ በስም ያልተጠቀሳቸው ቀሪዎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ኃይል እንዲያገኙ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መኾኑን አስታውቋል።

2፤ የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች ላይ ትንኮሳ ጀምሯል በማለት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ከሷል። የክልሉ መንግሥት፣ የሕወሃት ኃይሎች በትናንትናው ዕለት የተወሰኑ የራያ አላማጣ ወረዳ ቀበሌዎችን በመቆጣጠር ነዋሪዎችን እየገደሉና እያሰቃዩ ነው ብሏል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ የአማራ ክልል በትምህርት ሥርዓቱ የተሳሳተ ካርታ አካቷል በማለት ያወጣው መግለጫ፣ "የሕዝቦችን ታሪካዊ እውነታ"፣ "ተጨባጭ ማስረጃዎች" እና "ነባራዊ ሐቅ" የካደ፣ "አሳሳች" እና "የጠብ አጫሪነት ፍላጎትን የተሸከመ" መግለጫ ነው በማለት የአማራ ክልል መንግሥት አውግዞታል። የክልሉ መንግሥት፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አገሪቷንና ኹለቱን ክልሎች ወደ ቀውስ ከሚያስገቡ ተግባራትና ከአጓጉል "የካርታ ፖለቲካ" እንዲወጣና ሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረጉ ውይይቶች ላይ እንዲያተኩርም ጠይቋል።

3፤ አብን፣ ሕወሃት ለአዲስ ዙር ጦርነት ቅስቀሳ እያደረገ ነው ሲል ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ከሷል። ፓርቲው፣ በግጭት ማቆም ስምምነቱ መሠረት የሕወሃት ተዋጊዎች ሙሉ በሙሉ ትጥቅ ሳይፈቱና መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ጸጥታ ለማስከበር ሳይሠማራ ሕወሃት ለሌላ ዙር ጦርነት ፕሮፓጋንዳ በመለፈፍ ተጠምዷል ብሏል። የፌደራሉና የአማራ ክልል መንግሥታት የሕወሃትን የጠባጫሪነት ቅስቀሳ በትኩረት እንዲከታተሉና በአማራ ክልል የሚካሄደው ግጭት "በንግግር" እና "ድርድር" እንዲፈታም አብን ጠይቋል። የአማራ ሕዝብ ሕወሃት ሊያደርስበት የሚችለውን ጥቃት ለመከላከል በአንድነት እንዲቆም የጠየቀው ፓርቲው፣ የትግራይ ሕዝብም ራሱን ከሕወሃት ቀንበር እንዲያላቅቅ ጥሪ አድርጓል።

4፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በድጋሚ የሚያገረሽበት ዕድል ዝግ ነው በማለት ትናንት ከቻይናው ሲጂቲኤን ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል። ያለፈው ጦርነት የትግራይ ሕዝብ ፍላጎት አልነበረም ያሉት ጌታቸው፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርና የትግራይ ሕዝብ ድጋሚ ጦርነት እንዳያገረሽ የተቻላቸውን ጥረት ኹሉ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል። ጌታቸው ይህን ያሉት፣ በአላማጣ አቅራቢያ በትግራይ ኃይሎች እና ባካባቢው ሚሊሻዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ በተደረገ ማግስት ነው።

5፤ ዓቃቤ ሕግ ያለመከሰስ መብታቸው በተነሳባቸው የሕዝብ ተመራጮች ክርስቲያን ታደለ፣ ዮሐንስ ቧያለው. እና ካሳ ተሻገር ላይ የሽብር ወንጀል ክስ መስርቷል። በክስ መዝገቡ ከተካተቱት 52 ተከሳሾች መካከል፣ እስክንድር ነጋ፣ ጫኔ ከበደና ዘመነ ካሴ ይገኙበታል። ዓቃቤ ሕግ በክሱ፣ ተከሳሾቹ የፖለቲካ ርዕዮታቸውን በኃይል ለማስፈጸም በማሰብ፣ በኅቡዕ የተቋቋመውን የአማራ ፋኖ አንድነት ምክር ቤትን ዓላማዎች ለማስፈጸምና የአማራ ሕዝብ ርሥቶች ናቸው የሚሏቸውን አካባቢዎች በወታደራዊ ኃይል ለማስመለስ የተደራጁ ነበሩ ብሏል። ዓቃቤ ሕግ፣ ተከሳሾቹ ከ1 ሺህ 100 በላይ ለሚኾኑ የጸጥታ አባላትና ሲቪሎች ሞትና 5 ሺህ 689 በላይ ታራሚዎችን በማስመለጥ ወንጀልም ተጠያቂ አድርጓቸዋል።

6፤ "አፍሮ ባሮ ሜት" የተሰኘው የጥናትና ምርምር ተቋም፣ በፈረንጆች 2023 ከ10 ኢትዮጵያዊያን ስድስቱ በከፋ ወይም በመካከለኛ ድህነት ውስጥ ማለፋቸውን በጥናት ማረጋገጡን ገልጧል። ተቋሙ ከበፈረንጆች 2020 ጋር ሲነጻጸር፣ በከፋ ወይም መጠነኛ ድህነት ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር በ7 በመቶ መጨመሩን አስታውቋል።በጥናቱ መሠረት፣ በ2023 የምጣኔ ሃብት ኹኔታው "በጣም መጥፎ" ወይም "መጥፎ" መኾኑን ለጥናቱ የገለጡ ኢትዮጵያዊያን 65 በመቶ ሲኾኑ፣ በ2020 ግን ቁጥሩ 45 በመቶ ብቻ እንደነበር ተገልጧል። ጥናቱ፣ 18 በመቶ ያህሉ ኢትዮጵያዊያን ዓመቱን በከፋ የምግብ ዕጦት እንዳሳለፉና 42 በመቶዎቹ የሚኾኑት ደሞ አልፎ አልፎ ወይም ብዙ ጊዜ የምግብ እጥረት እንደገጠማቸው ማመልከቱንም ተቋሙ ጠቅሷል።

7፤ የጅቡቲው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሞሃመድ ዓሊ የሱፍ፣ ኢትዮጵያ ከሱማሊላንድ ጋር በደረሰችበት የባሕር በር ስምምነት ሳቢያ ኢትዮጵያ እና ሱማሊያ በመካከላቸው በተፈጠረው ውዝግብ ዙሪያ ናይሮቢ ውስጥ መነጋገራቸውን ይፋ እንዳደረጉ የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ዘገባዎቹ፣ ኹለተኛው ዙር ንግግር ጅቡቲ ውስጥ ይካሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዓሊ መናገራቸውን አመልክተዋል። የኹለቱ አገራት የናይሮቢ ንግግር መቼ እንደተካሄደ ግን ዘገባዎቹ አልጠቀሱም። ኾኖም ባለፈው ወር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ኬንያን በጎበኙበት ወቅት፣ የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድም ለሌላ ዓለማቀፍ ጉባዔ ናይሮቢ ውስጥ እንደነበሩ ይታወሳል። [ዋዜማ]
በክፍያ የሚገኘውን የዋዜማን ሁነኛ መረጃ ገፅ በነፃ እንድታላምዱ ጋብዘናችሁ ለተቀላቀላችሁን ሁሉ ምስጋና እናቀርባለን። በቀሪዎቹ ቀናት መቀላቀል ለምትፈልጉም በሩ ክፍት ነው። በዚህ ሊንክ- https://tinyurl.com/wuuh7t43
ለቸኮለ ማለዳ! ዓርብ መጋቢት 20/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በአፋር ክልል፣ በአፋር እና ኢሳ ሱማሌ ጎሳዎች መካከል በድጋሚ በተያዘው ሳምንት ግጭት ማገርሸቱን ዋዜማ ሰምታለች። ግጭቱ የተከሰተው፣ በገቢ ረሱ ዞን (ዞን ሦስት) አሚባራ ወረዳ ውስጥ አፋርና ሱማሌ ክልሎች በሚወዛገቡበት ገዳማይቱ ቀበሌ እንደኾነ ታውቋል። በግጭቱ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ሳይገደሉና ሳይቆሰሉ እንዳልቀሩ ተነግሯል።

2፤ ፖሊስ የኢሕአፓን ሊቀ መንበር ዝናቡ አበራን ማክሰኞ'ለት አዲስ አበባ ውስጥ እንዳሠረ የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ዝናቡ ረቡዕ'ለት ፍርድ ቤት ቀርበው፣ ዓቃቤ ሕግ የጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀባቸው ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ፖሊስ የፓርቲውን ሊቀመንበር በምን ምክንያት እንዳሠራቸው ግን ዘገባዎቹ አልጠቀሱም።

3፤ የኬንያ ፖሊስ ረቡዕ'ለት ናይሮቢ መንገድ ላይ ባገኘው የአንድ ኢትዮጵያዊ አስከሬን ላይ ምርመራ እያደረገ እንደኾነ ዘ ስታር ዘግቧል። አስከሬኑ ተመስገን ወሎሮ ሙጆሞ የተባለ የ30 ዓመት ወጣት ኢትዮጵያዊ እንደኾነ የጠቀሰው ዘገባው፣ ሟቹ ፍልሰተኛ ሳይኾን እንደማይቀር ፖሊስ መናገሩን አመልክቷል። በጥር ወር ብቻ አምስት ኢትዮጵያዊያን በሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ወደ ኬንያ ሲገቡ እንደሞቱና በዚያው ወር ፖሊስ ከ500 በላይ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያንን ከሰው አዘዋዋሪዎች ነጻ ማውጣቱን ዘገባው ጠቅሷል።

4፤ ሩሲያ ከኤርትራ ጋር የባሕር ኃይል ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ የላከቻት የጦር መርከብ ትናንት ከኤርትራዋ ምጽዋ ወደብ ደርሳለች። ወታደራዊ መርከቧ፣ በምጽዋ ወደብ አካባቢ ለዘጠኝ ቀናት እንደምትቆይ የሩሲያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ሩሲያ የባሕር ኃይል መርከቧን ወደ ምጽዋ የላከችው፣ ይችኑ መርከብ ጨምሮ ሌሎች መርከቦቿ ከቻይና እና ኢራን ባሕር ኃይሎች ጋር በኦማን ባሕረ ሰላጤ የጋራ የባሕር ኃይል ልምምድ ባደረጉ ማግስት ነው። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፈው ዓመት በሞስኮ ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት፣ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር በኹለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸው ይታወሳል።

5፤ አዲስ የሚቋቋመው የአፍሪካ ኢነርጂ ባንክ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት በ5 ቢሊዮን ዶላር መነሻ ካፒታል ሥራ እንደሚጀምር ሮይተርስ ዘግቧል። የባንኩ ዓላማ፣ በአሕጉሪቱ ለሚካሄዱ የጋዝና ነዳጅ ኢንቨስትመንቶች ብድር ማቅረብ ነው። እስካኹን ናይጀሪያ፣ አንጎላ እና ጋና በመቋቋም ላይ ለሚገኘው ባንክ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ያስቀመጡ ሲኾን፣ እያንዳንዱ አባል አገር ለባንኩ በትንሹ 83 ሚሊዮን ዶላር ማዋጣት ይጠበቅበታል። ዓለማቀፍ አበዳሪዎች አፍሪካ ውስጥ የሚካሄዱ ታዳሽ ያልኾኑ የነዳጅና የጋዝ ፕሮጀክቶች የአካባቢ ብክለት ያስከትላሉ በሚል ምክንያት፣ ብድር መከልከል ከጀመሩ ሰነባብተዋል። [ዋዜማ]
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
ደብረብርሃን ትመለሳለች?
አንድ ወቅት የሀገሪቱ የኢንደስትሪ ማዕከል የመሆን ዕድል እንዳላት ሲነገርላት የነበረው ደብረብርሃን አሁን የጦርነት መዘዝ ከጉዞዋ ያሰናከላት ይመስላል። የዋዜማ ዘጋቢ ወደ ስፍራው አቅንቶ ነበር።
ለቸኮለ! ዓርብ መጋቢት 20/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በአፋር ክልል፣ በአፋር እና ኢሳ ሱማሌ ጎሳዎች መካከል በድጋሚ በተያዘው ሳምንት ግጭት ማገርሸቱን ዋዜማ ሰምታለች። ግጭቱ የተከሰተው፣ በገቢ ረሱ ዞን (ዞን ሦስት) አሚባራ ወረዳ ውስጥ አፋርና ሱማሌ ክልሎች በሚወዛገቡበት ገዳማይቱ ቀበሌ እንደኾነ ታውቋል። በግጭቱ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ሳይገደሉና ሳይቆሰሉ እንዳልቀሩ ተነግሯል። ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ፣ በአፋሮች እና ኢሳ ሱማሌዎች መካከል የሚደረጉ በትጥቅ የተደገፉ ግጭቶች ተበራክተዋል።

2፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ተመስገን ጥሩነህ የሥራ አመራር ቦርዱ ሰብሳቢው ኾነው እንደተሾሙለት አስታውቋል። ተመስገን፣ ትናንት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና መስሪያ ቤት ተገኝተው ከአመራሮቹ ጋር ትውውቅ ማድረጋቸውንና የኩባንያው አመራሮችም ስለ ኩባንያው የሥራ እንቅስቃሴ ገለጻ እንዳደረጉላቸው ኩባንያው ባሠራጨው መረጃ ገልጧል። በማቋቋሚያ አዋጁ መሠረት ኩባንያው ከተቋቋመ ጀምሮ የበላይ ሥራ አመራር ቦርዱ ሰብሳቢ ጠቅላይ ሚንስትሩ ነበሩ። በዚህም መሠረት ኩባንያው በሥሩ የታቀፉ ግዙፍ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን የሥራ አፈጻጸም ከጥቂት ሳምንታት በፊት ሲገመግም፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በቦርድ ሊቀመንበርነታቸው የግምገማ መድረኮቹን መምራታቸው ይታወሳል።

3፤ በኢትዮጵያ የሚተገበረው የምግብ ለሥራ ወይም ሴፍቲኔት መርሃ ግብር፣ ዘንድሮ ለተረጂዎች የሚሰጠውን የምግብ እና ጥር ገንዘብ ድጋፍ ቀንሷል። መርሃ ግብሩ ስምንት ሚሊዮን ተረጂዎችን ያቀፈ ሲኾን፣ ለጋሾች በቂ ዕርዳታ ባለመስጠታቸውና የምግብ ዋጋ በማሻቀቡ በቀጣዮቹ ኹለት ዓመታት ለሚያቀርባቸው ድጋፎች የ195 ሚሊዮን ዶላር ጉድለት ገጥሞታል። በዚህ ሳቢያ ዘንድሮ የመርሃ ግብሩ አብዛኞቹ ተጠቃሚዎች ለስድስት ወራት ያገኙት የነበረው የምግብ እና ጥሬ ገንዘብ ወደ አራት ወራት ዝቅ እንደሚደረግ ኒው ሂውማኒተሪያን ዜና ምንጭ ዘግቧል። በከፍተኛ ደረጃ ለጉዳት ተጋላጭ የኾኑ የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች የሚያገኙት ድጋፍ ደሞ፣ ዘንድሮ ከ12 ወራት ወደ 10 ወራት ዝቅ ተደርጓል ተብሏል። መርሃ ግብሩ በምግብ ለሥራ መርሃ ግብር ለታቀፉ ሰዎች በወር 15 ኪሎ ግራም ጥራጥሬ ወይም ጥሬ ገንዘብ ይሰጣል።

4፤ ማዕድን ሚንስቴር ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ላስመዘገቡ አራት ኩባንያዎች የማዕድን ማምረት ፍቃድ መስጠቱን አስታውቋል። ሚንስቴሩ የኢንቨስትመንት ፍቃዱን የሰጠው፣ ሚንስትሮች ምክር ቤት የአገሪቱ የብሮሚን፣ የግራናይት፣ የድንጋይ ከሰል እና የደለል ወርቅ ማዕድናት እንዲለሙ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት እንደኾነ ገልጧል። የማምረት ፍቃድ የተሰጣቸው ኩባንያዎች፣ የቻይናው ብሮሚን ማዕድን አምራች ጄሬህ ኬሚካል ኢንዱስትሪያል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አንዱ ሲኾን፣ ወደ ማዕድን ልማቱ ለመግባት ከ39 ሚሊዮን ዶላር በላይ አስመዝግቧል ተብሏል። በድንጋይ ከሰል ልማት የተሠማራው ኢትዮጵያዊያን ባለሃብቶች ያቋቋሙት ኩባንያ፣ በደለል ወርቅ ማዕድን ልማት የተሠማራው የኢትዮጵያዊያን ባለሃብቶች ንብረት የኾነው ኦሮሚያ ማይኒንግ ከባንያ እና በግራናይት ማዕድን ልማት የሚሠማራ የዮርዳኖስ ኩባንያ ቀሪዎቹ ኩባንያዎች እንደኾኑ ሚንስቴሩ ገልጧል።

5፤ አማራ ባንክ ዛሬ ከኢትዮጵያ የሰነድ መዋዕለ ነዋይ ገበያ የ90 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ድርሻ ገዝቷል። ባንኩ የገዛው ድርሻ፣ በሰነድ መዋዕለ ንዋይ ገበያው ውስጥ የ10 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ እንዲኖረው ያስችለዋል። የአማራ ባንክ የአክሲዮን ድርሻ ብዛት፣ በሰነድ መዋዕለ ንዋይ ገበያው እስካኹን የአክሲዮን ድርሻ ከገዙ ኩባንያዎች ኹሉ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ኩባንያ ያደርገዋል። አዋሽ ባንክ ቀደም ሲል በ70 ሚሊዮን ብር የሰባት በመቶ ድርሻ በመያዝ የመሪነቱን ቦታ ይዞ ቆይቶ ነበር። የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችለውን የ1 ቢሊዮን ብር ካፒታል ዛሬ ከሚያበቃው ቀነ ገደቡ በፊት ማሰባሰብ እንደቻለ ከጥቂት ቀናት በፊት መግለጡ ይታወሳል።

6፤ ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ ከኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ የ20 ሚሊዮን ብር ድርሻ ገዝቷል። ኢንሹራንስ ኩባንያው ዛሬ የገዛው ድርሻ፣ በመዋዕለ ንዋይ ገበያው የ2 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ ባለቤት ያደርገዋል። የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ በይፋ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት፣ መስራች መኾን ለሚፈልጉ ኩባንያዎች የአክሲዮን ድርሻዎችን ለመሸጥ ያስቀመጠው ቀን ገደብ ዛሬ አብቅቷል።

7፤ የግብጽ የመስኖ ሚንስትር ሃኒ ስዊላም፣ የሕዳሴ ግድብ በግብጽ ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ኢትዮጵያ ዋጋ ትከፍልበታለች በማለት ማስጠንቀቃቸውን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ሚንስትሩ፣ ግብጽ በናይል ወንዝ ላይ ያላት ጥቅም ከተነካባት፣ አስፈላጊ የኾኑ ርምጃዎችን ትወስዳለች በማለት እንደዛቱ ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ሚንስትሩ፣ በድርቅ ጊዜ ምን መደረግ እንዳለበት እንዲኹም በግድቡ ውሃ አሞላል ሂደት እና በውሃ ሃብት አጠቃቀም ዙሪያ አስገዳጅ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል ተብሏል። የሦስቱ አገራት የመርኾዎች ስምምነት፣ በታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ላይ ጉዳት ያደረሰ አገር የጉዳት ማካካሻ እንዲከፍል ያስገድዳል ማለታቸውን የጠቀሱት ዘገባዎቹ፣ እስካኹን ባለው የድርድሩ ቅርጽ ሌላ ዙር ድርድር ማድረግ ጊዜ ማባከን እንደኾነም መናገራቸውን አመልክተዋል።

8፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ6236 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ7561 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 68 ብር ከ3299 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ6965 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ61 ከ1818 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ4054 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ቅዳሜ መጋቢት 21/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ፣ በሕልውናዬ ላይ የተደቀኑ ችግሮች ካልተፈቱ ከአገራዊ ምክክር ሂደቱ ልወጣ እችላለኹ ሲል ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በጻፈው አቤቱታ አስጠንቅቋል። ፓርቲው በመስከረም ወር ከኮሚሸኑ ጋር አብሮ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረመ ወዲህ፣ የሲዳማ ክልል መንግሥታዊ አካላትና ምርጫ ቦርድ በሕልውናው ላይ አደጋ ላይ እንደደቀኑበት ገልጧል። ፓርቲው፣ በአመራሮቹና አባሎቹ ላይ የሚደርሰውን እስር፣ ወከባና የዋና ቢሮውን ቁልፍ በዲስፕሊን ለታገዱ አመራሮች ተላልፎ በመሰጠቱንቦ ዙሪያ፣ ለክልሉ ፍርድ ቤትና ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ ቢያቀርብም፣ መፍትሄ አለማግኘቱም ገልጧል። የምክክር ኮሚሽኑ፣ አመራሮቹ እንዲፈቱ፣ ዋና ጽሕፈት ቤቱ እንዲመለስለትና የምርጫ ቦርድን አካሄድ እንዲያስቀይርለትም ፓርቲው ጠይቋል።

2፤ የፌደራሉ ፍርድ ቤት የሕዝብ ተመራጮቹ ክርስቲያን ታደለ፣ ዮሃንስ ቧያለው እና ካሳ ተሻገር ከትናንት ጀምሮ መደበኛ እስረኞች እንደኾኑ ወስኗል። ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ጥያቄ ሳይቀበለው ቀርቷል። ዮሃንስ ቧያለውና ክርስቲያን ታደለ፣ በጨለማ ውስጥ እና በካቴና መታሠርን ጨምሮ የተለያዩ ኢሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽሞብናል በማለት ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱ ለቀጣዩ ዓርብ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። በትናንቱ ችሎት የቀረቡት 14 ተከሳሾች ናቸው።

3፤ የኢትዮጵያ የሰነድ መዋዕለ ንዋይ ገበያ የአክሲዮን ድርሻ ለመሸጥ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ ትናንት ምሽት ተጠናቋል። በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር የሚተዳደሩ መንግሥታዊ የልማት ድርጅቶች 25 በመቶ ድርሻ መግዛታቸው ይታወሳል። የመንግሥትና የግል ንግድ ባንኮች እንዲኹም የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎችም የተለያየ ብዛት ያላቸውን የአክሲዮን ድርሻዎችን ገዝተዋል። እስከ ትናንት ድረስ የአክሲዮን ድርሻዎችን የገዙ ኩባንያዎች፣ የሰነድ መዋዕለ ንዋይ ገበያው መስራቾች ኾነዋል።

4፤ ስድስት ኬንያዊያን በኬንያና ሱማሊያ ድንበር ላይ በምትገኝ የሱማሊያ የጠረፍ ከተማ ሰሞኑን እንደተገደሉ የኬንያ ጋዜጦች ዘግበዋል። ኬንያዊያኑ በከተማዋ በአነስተኛ ንግድ የተሠማሩ እንደነበሩ የጠቀሱት ዘገባዎቹ፣ ገዳዮቹ የአልሸባብ ታጣቂዎች ሳይኾኑ እንደማይቀር ጠቅሰዋል። ኬንያ የአልሸባብ ሰርጎ ገቦችን ለመከላከል ስትል ከሱማሊያ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ከዘጋች በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል።

5፤ የሱማሊያ ፓርላማ አወዛጋቢውን የተሻሻለ ሕገመንግሥት ዛሬ ያጸድቃል ወይም ውድቅ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። የተሻሻለው ሕገ መንግሥት፣ ፓርላሜንታዊውን የመንግሥት አወቃቀር በፕሬዝዳንታዊ አወቃቀር የሚቀይር፣ የጠቅላይ ሚንስትርነትን ሥልጣን የሚያስቀር፣ የምርጫ ሥርዓቱን ቀጥተኛ ካልኾነ የምርጫ ሥርዓት ወደቀጥተኛ የምርጫ ሥርዓት የሚቀይርና አገሪቱ ኹለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ እንዲኖሯት የሚያደርግ ነው። የፑንትላንድ ራስ ገዝ አስተዳደር፣ ተቃዋሚዎችና የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዝዳንቶች፣ ረቂቁ ጊዜያዊውን የአገሪቱ ሕገመንግሥት ከሥረ መሠረቱ የቀየረ እንጂ ማሻሻያ ሊባል አይችልም በማለት ውድቅ አድርገውታል። ሂዋማን ራይትስ ዎች በበኩሉ፣ የተሻሻለው ሕገመንግሥት የሕጻናትን መብት ይጥሳል በማለት ተቃውሞታል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ቅዳሜ መጋቢት 21/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጋር በቀጣዩ ሰኞ ለመወያየት ቀጠሮ እንደያዙ ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። ዐቢይ ኹሉንም አገር ዓቀፍና ክልላዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለውይይት ወደ አዲስ አበባ እንደጠሩ ታውቋል። ከአገር ዓቀፍ ፓርቲዎች ከእያንዳንዳቸው ስድስት ተወካዮች እንዲኹም ከክልላዊ ፓርቲዎች ሦስት ተወካዮች ለውይይቱ እንደተጋበዙ ዋዜማ ተረድታለች። በውይይቱ የሚሳተፉ የፓርቲዎች ተወካዮች ከውይይቱ በኋላ ማክሰኞ'ለት ሥልጠና ይወስዳሉ ተብሏል። ኾኖም ኦፌኮንና ኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባርን ጨምሮ የበርካታ ፓርቲዎችን ያቀፈው የፓርቲዎች ኮከስ አባላት የኾኑ ዘጠኝ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የጠቅላይ ሚንስትሩን የውይይት ጥሪ እንዳልተቀበሉት ምንጮች ጠቁመዋል።



2፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፣ ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ከአሜሪካ የላይኛው የሕግ አውጭ ምክር የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ አባላት ጋር በፕሪቶሪያው ግጭት ማቆም ስምምነት አተገባበር ዙሪያ እንደተወያዩ የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። ጌታቸው፣ የግጭት ማቆም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለመኾኑ፣ የትግራይ ሕዝብ ለተለያዩ ችግሮች እንደተዳረገ ለልዑካን ቡድኑ ማብራራታቸውን ዘገባው አመልክቷል። የትግራይ ግዛቶች ወደነበሩበት እንዲመለሱ፣ የጦርነቱ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱና ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲኾን የአሜሪካ መንግሥትን ጨምሮ ኹሉም አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጌታቸው ጥሪ ማድረጋቸውን ዘገባው ጠቅሷል። የልዑካን ቡድኑም፣ ለግጭት ማቆም ስምምነቱ ተግባራዊነት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል ተብሏል።

3፤ አበዳሪ አገራት ለኢትዮጵያ እስከ ቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ድረስ የሰጡትን የብድር መክፈያ እፎይታ ሊያጥፉ እንደሚችሉ ያስቀመጡት ቀነ ገደብ በነገው ዕለት ያበቃል። አበዳሪ አገራቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለማቀፉ ገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ጋር በፈረንጆች አቆጣጠር እስከ መጋቢት 31 ማለትም ነገ ዕሁድ አዲስ የብድር ስምምነት ላይ ካልደረሰ፣ ለአገሪቱ የሰጠነውን የብድር መክፈያ እፎይታ እንሰርዘዋለን በማለት ቀደም ሲል ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል። የአይ ኤም ኤፍ ልዑካን መንግሥት ለአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ ማስፈጸሚያ በጠየቀው የ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ዙሪያ ከባለሥልጣናት ጋር ለመደራደር አዲስ አዲስ አበባ የገባው ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ነበር። ልዑካን ቡድኑ በአዲስ አበባ ላንድ ሳምንት እንደሚቆይ ታማኝ ምንጮች ዘግበው የነበረ ሲኾን፣ በድርድሩ የተገኘ ውጤት ይኑር ወይም አይኑር፣ መንግሥትም ኾነ ድርጅቱ እስካኹን በይፋ የገለጡት ነገር የለም።

4፤ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ፣ ለዓለማቀፉ አማካሪ ኩባንያ ደሎይት በካፒታል ገበያ ውስጥ የኢንቨስትመንት አማካሪነት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ፍቃድ እንደሰጠ ዛሬ ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል። ተቀማጭነቱን ለንደን ያደረገው ደሎይት ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ኢንቨስትመንት የአማካሪነት አገልግሎት ፍቃድ በማግኘት የመጀመሪያው ኩባንያ ነው። ኩባንያው በዘርፉ በዓለማቀፍ ደረጃ የበርካታ ዓመታት ልምድ አለው። የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣ በቀጣዮቹ ሳምንታት በካፒታል ገበያ ዘርፍ የመጀመሪያው የኢንቨስትመንት ባንክና የመጀመሪያው የካፒታል ገበያ የድለላ ኩባንያ ፍቃድ እንደሚያገኙ መናገሩን የዘገበው ደሞ ሪፖርተር ነው።

5፤ በአማራ ክልል የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና መቀመጫ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር የማዕከላዊ ጸጥታ ዕዝ በከተማዋ ጥሎት የቆየውን የሰዓት እላፊ ገደብ ማላላቱን አስታውቋል። ማዕከላዊ የጸጥታ ዕዙ፣ ተሽከርካሪዎች ከምሽቱ 1:00 ሰዓት በኋላ በከተማዋ እንዳይንቀሳቀሱ የጣለውን ገደብ እስከ ምሽቱ 2:00 ሰዓት ማራዘሙን ገልጧል። ማዕከላዊ የጸጥታ ዕዙ፣ የሰዎች እንቅስቃሴ እስከ ምሽት 2:00 ሰዓት ድረስ ብቻ እንዲኾን የተጣለው ገደብም፣ ከምሽቱ 3:00 ሰዓት ጀምሮ ተግባራዊ እንዲኾን ወስኗል። የጸጥታ ዕዙ በከተማዋ የጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ያሻሻለው፣ የከተማዋ የጸጥታ ኹኔታ በመሻሻሉ እንደኾነ ገልጧል።

6፤ የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት ካለፉት ኹለት ዓመታት ወዲህ በክልሉ የብሄር ግጭቶች፣ "ጽንፍ የወጣ ብሄርተኝነት"፣ ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርና የሽብር ተግባራት እየተስፋፉ መኾኑን አስታውቋል። የክልሉ መንግሥት፣ "ጽንፈኛ ብሄርተኝነትን"፣ የብሄር ግጭትና ሌሎች ወንጀሎችን በሚቀሰቅሱና በድርጊቶቹ በሚሳተፉ አካላት ላይ "ጥብቅ ርምጃ እወስዳለኹ" በማለት አስጠንቅቋል። የክልሉ የተወሰኑ አመራሮች "የጽንፈኛ ብሄርተኝነት አራማጅ" መኾናቸውን የገለጠው የክልሉ፣ መንግሥት፣ ኢመደበኛ አደረጃጀቶችና በውጭ አገራት የሚገኙ አንዳንድ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም ለችግሩ ሚና አላቸው ብሏል። በተለይ በኢታንግ ልዩ ወረዳ በአኝዋክና ኑዌር ጎሳዎች መካከል በርካቶች የተገደሉባቸው ግጭቶች የተከሰቱ ሲኾን፣ በተለያዩ አካባቢዎችም የታጠቁ ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል። የክልሉ መንግሥት ከችግሩ ጋር በተያያዘ፣ በርካታ አመራሮችን ከሃላፊነት ማንሳቱን ቀደም ሲል ቢገልጥም፣ አኸንም ችግሩ ይበልጥ እየተባባሰ ሄደ እንጂ አልተቃለለም ብሏል።

7፤ ዓለም ባንክ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ በኾኑ የኢትዮጵያ ቆላማ አካባቢዎች ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚውል የ340 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማጽደቁን ዛሬ ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል። ባንኩ በቆላማ አካባቢዎች ለሚተገብረው ፕሮጀክት የሚውለው የገንዘብ ድጋፍ የተገኘው፣ የባንኩ አካል ከኾነው ዓለማቀፉ የልማት ድርጅት እንደኾነ ባንኩ ገልጧል። የገንዘብ ድጋፉ በቆላማ አካባቢዎች የሚኖሩ ለድርቅ ተጋላጭ የኾኑ ሦስት ሚሊዮን አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ድርቅን ጨምሮ የተለያዩ የአየር ንብረት ለውጦችን የመቋቋም አቅማቸውን ለማጎልበትና የተፈጥሮ አደጋ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቶችን ለማጠናከር ባንኩ ለዘረጋው ፕሮጀክት ኹለተኛ ምዕራፍ ትግበራ የሚውል ነው። [ዋዜማ]
የወሰን ይገባኛል የሚነሳባቸውን አካባቢዎች (የራያ ፣ ጠለምት እና ወልቃይት) በተመለከተ የትግራይና የአማራ ክልል አመራሮች የፕሪቶሪያውን የሰላም ውል ተንተርሰው በደረሱት የመተግበሪያ ስምምነት መሰረት ታጣቂዎችን ማስወጣት ተፈናቃዮችን መመለስና አዲስ የአስተዳደር መዋቅር መዘርጋትን ጨምሮ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ መታቀዱን ዋዜማ ስለጉዳይ ከሚያውቁ መንግስታዊ ምንጮች ያገኘችው የሰነድ መረጃ ያመለክታል። ዝርዝሩን ያንብቡት- https://tinyurl.com/24sztxh7
#Tigray and Amhara regional leaders have agreed to implement the most contentious part of #Pretoria Peace agreement. Though the implementation of the plan seems like a master stroke by Prime Minister Abiy Ahmed’s administration, it could aggravate the ongoing war in #Amhara region. Even ethnic Amhara individuals inside the ruling Prosperity Party have covertly resisted the plan. Read More- https://tinyurl.com/9eb84fmn
ለቸኮለ ማለዳ! ሰኞ መጋቢት 23/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የትግራይና አማራ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው የራያ፣ ጠለምትና ወልቃይት፣ ታጣቂዎችን የማስወጣት፣ ተፈናቃዮችን የመመለስና አዲስ የአስተዳደር መዋቅሮችን የመዘርጋት እንቅስቃሴዎች በጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚጀመሩ ዋዜማ ካገኘችው ሰነድ ተረድታለች። ውዝግቡን ለመፍታት የተሰየመው ብሄራዊ ኮሚቴ፣ መከላከያ ሠራዊት ይህንኑ ሂደትና ጸጥታውን እንዲያስተባበር ኃላፊነት እንደሰጠና የትግራይ የተፈናቃዮችን ዝርዝር ለመከላከያ እንዲሚያቀርብ በሰነዱ ላይ ተገልጧል። የትግራይ ተወላጅ የኾኑ ታጣቂዎችና ሚሊሻዎችም እንደታጣቂ ሳይኾን እንደተፈናቃይ ወደቀያቸው እንደሚመመለሱና የአካባቢው ተወላጅ የኾኑ የአማራ ታጣቂዎች እንደ ነዋሪ መቆየት እንዲችሉ ተወስኗል። ከጦርነቱ በኋላ የተመሠረቱ የአስተዳደርና የጸጥታ መዋቅሮች ፈርሰው የቀበሌና የወረዳ አመራሮች ምርጫ ይደረግና ነባራዊ ሁኔታው ሲመቻች ሕዝበ ውሳኔ ይካሄዳል- ይላል ሰነዱ። Link- https://tinyurl.com/24sztxh7

2፤ ንግድ ባንክ የራሳቸው ያልኾነ ገንዘብ የወሰዱ ደንበኞቹ ገንዘቡን እንዲመልሱ የሰጠውን ቀነ ገደብ ከዛሬ ጀምሮ በሦስት ቀናት ማራዘሙን ትናንት አስታውቋል። ባንኩ ያስመለሰው ገንዘብ 86 በመቶ መድረሱንና ያልተመለሰው ገንዘብ ወደ 112 ሺህ 389 ዝቅ ማለቱን ገልጦ፣ ገንዘቡን ሙሉ በሙሉ የመለሱ ግለሰቦች ቁጥር ወደ 10 ሺህ 857 ከፍ ማለቱንና ገንዘብ መመለስ ያልጀመሩ ግለሰቦችም 222 ብቻ መኾናቸውን ጠቅሷል። ባንኩ ገንዘብ መመለሻውን ቀን ያራዘመው፣ የወሰዱትን ገንዘብ ወደ አቋማሪ ኩባንያዎች ያዛወሩና ሌሎች ችግሮች የገጠሟቸው ደንበኞች ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው በመጠየቃቸው እንደኾነ አስታውቋል።

3፤ የብሪታንያ የኢንፎርሜሽን ተቆጣጣሪ ቢሮ፣ የብሪታንያ ሙዚዬም ከእይታ ደብቆ በሚስጢር አስቀምጧቸዋል ባላቸው 11 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታቦታት ዙሪያ ምርመራ መጀመሩን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል። አንድ በቅርሶች ዙሪያ የሚሠራ አቤቱታ አቅራቢ ተቋም፣ ሙዚዬሙ ስለ ታቦታቱ መረጃ እንዲሰጥ ቢጠይቅም፣ ሙዚዬሙ ግን ዝርዝር መረጃ እንዳልሰጠ በመግለጽ ለገለልተኛው የኢንፎርሜሽን ምርመራ ቢሮ ቅሬታ ማቅረቡን ዘገባው ጠቅሷል። አቤቱታ አቅራቢው ተቋም፣ ሙዚዬሙ ታቦታቱን ለምን ለኢትዮጵያ መመለስ እንዳልቻለ ግልጽ ማብራሪያ መስጠት አልቻለም ብሏል ተብሏል። ታቦታቱ በመቅደላ ጦርነት ወቅት የተዘረፉ እንደኾኑ በዘገባው ላይ ተገልጧል።

4፤ ፑንትላንድ ራስ ገዝ ለሱማሊያ ፌደራል መንግሥት እውቅና መንፈጓንና ከፌደራል መንግሥቱ መውጣቷን አስታውቃለች። ፑንትላንድ፣ ኹሉም የሚስማማበት የፌደራል ሕገመንግሥት "በሕዝበ ውሳኔ" እስኪጸድቅ ድረስ ራሴን የቻልኩ ሉዓላዊ አገር ኾኛለሁ ብላለች። ፑንትላንድ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው፣ የሱማሊያ ፓርላማ አወዛጋቢውን የሕገመንግሥት ማሻሻያ ማጽደቁን ተከትሎ ነው። የሕገመንግሥት ማሻሻያው፣ አገሪቱ በፓርላሜንታዊ የመንግሥት አወቃቀር ፋንታ ፕሬዝዳንታዊ የመንግሥት አወቃቀር እንድትከተልና ጎሳን መሠረት ባደረገው የምርጫ ሥርዓት ፋንታ ቀጥተኛ የምርጫ ሥርዓት እንዲኖር የሚደነግግ ነው። ፕሬዝዳንት ሞሃመድ፣ የተሻሻለውን ሕገመንግሥት ትናንት በፊርማቸው አጽድቀውታል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሰኞ መጋቢት 23/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች



1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ከአገር ዓቀፍና ከክልላዊ ፓርቲዎች ጋር መወያየታቸውን አስታውቀዋል። የውይይቱ ዓላማ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት ላይ አስተያየቶችና ትችቶችን ማሰባሰብና ለፖሊሲ ግብዓት አስፈላጊ የኾኑ እርማቶችንና ማስተካከያዎችን መለየት እንደነበር ዐቢይ ገልጸዋል። በውይይቱ እንዲገኙ ጥሪ ከቀርበላቸው 60 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ውስጥ የፓርቲዎች ኮከስ አባላት የኾኑ 13ት ፓርቲዎች ጥሪውን እንዳልተቀበሉ መስማቱን ሸገር ዘግቧል። የኮከሱ አባል የኾነው የኅብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ግርማ በቀለ፣ ፓርቲዎቹ በውይይቱ የማይሳተፉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ካኹን ቀደም ከነጋዴዎች፣ ከኃይማኖት ተቋማትና ሌሎች አካላት ጋር ያደረጓቸው ተመሳሳይ ውይይቶች የገጽታ ግንባታን ዒላማ ያደረጉ እና የገዥው ብልጽግና ፓርቲ መወድስ የሚቀርብባቸው መኾናቸውን በመረዳታቸው እንደኾነ ለሸገር ተናግረዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች፣ ነገ ማክሰኞ የኔዘርላንድ መንግሥት ባዘጋጀላቸው ሥልጠና ላይ እንደሚገኙ መስማቱን ዘገባው አመልክቷል።


2፤ በአማራ ክልል ባንዳንድ አካባቢዎች በመንግሥት ወታደሮች እና በፋኖ ሚሊሺያዎች መካከል ግጭቶች ቀጥለዋል። በተለይ በጎንደር ከተማ ባንዳንድ ክፍለ ከተሞች እንዲኹም በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በደሃና ወረዳ በርካታ አካባቢዎች በኹለቱ ወገኖች መካከል ውጊያ መካሄዱን ዋዜማ ከምንጮች ተረድታለች። ሰሞኑን በምሥራቅ ጎጃም ዞን በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረው ውጥረት ሳቢያ፣ ባሕርዳር እና ደብረማርቆስ ከተሞችን የሚያገናኘው ዋናው መንገድ እንደተዘጋና የትራንስፖርት እንቅስቃሴም እንደተገደበ ዋዜማ ሰምታለች።


3፤ የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሥልጣናት ወደ አገሪቱ በሕገወጥ መንገድ ለመግባት ሞከረዋል ያሏቸውን ከ560 በላይ ኢትዮጵያዊያን ባንድ ሳምንት ውስጥ ማሥራቸውን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። በሕገወጥ መንገድ ለመግባት ከሞከሩት 966 የውጭ ዜጎች መካከል፣ 59 በመቶዎቹ ኢትዮጵያዊያን ናቸው ተብሏል። የአገሪቱ ጸጥታ ኃይሎች የድንበር፣ የመኖሪያ ፍቃድ እና የሥራ ሕጎችን ጥሰዋል በማለት በጠቅላላው ባንድ ሳምንት ውስጥ ያሠሩት፣ ከ21 ሺህ 500 በላይ የውጭ ዜጎችን እንደኾነ ዘገባዎቹ አመልክተዋል። 14 ሺህ 610 ያህሉ የታሠሩት፣ የመኖሪያ ፍቃድ ሕጎችን በመተላለፋቸው ሲኾን፣ 4 ሺህ 457ቱ ደሞ በሕገወጥ መንገድ የአገሪቱን ድንበር ጥሰው ለመግባት በመሞከራቸው ነው ተብሏል። ኢትዮጵያዊያኑ መታሠራቸው የተሰማው፣ መንግሥት በሳዑዲ ዓረቢያ  እስር ቤቶች ባስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ የሚገኙ 70 ሺህ ዜጎችን ለመመለስ እንቅስቃሴ በጀመረበት ወቅት ነው።


4፤ ብሄራዊ ባንክ፣ ሁሉም የፋይናንስ ድርጅቶች የወለድ ነጻ ባንኮች የሸሪያ ሕጎችን ማክበር አለማክበራቸውን የሚቆጣጠር ብሄራዊ ቦርድ ለማቋቋም ለሚደረገው ጥናት ትብብር እንዲያደርጉ መጠየቁን ፎርቹን ዘግቧል። ቦርዱን ለማቋቋም የሚደረገውን ጥናት እንዲያስተባብር ሃላፊነት የተሰጠው፣ ለኢትዮጵያ ባንክ ባለሙያዎች ማኅበር እንደኾነ ዘገባው አመልክቷል። ማኅበሩ፣ ኹሉም ባንኮች፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለወለድ ነጻ ባንክ አገልግሎት የሰው ኃይል እንዲመድቡና በጥናቱ እንዲሳተፉ ጠይቋል ተብሏል። 


5፤ የሶማሊላንድ መንግሥት፣ ሰማሊያ በቅርቡ የጀመረችው የሕገመንግሥት ማሻሻያ የውስጥ ጉዳይዋ እንጂ ሶማሊላንድን የሚመለከት ጉዳይ በመኾኑ በሶማሊላንድ ላይ ተፈጻሚ የሚኾንበት ሕጋዊ መሠረት የለም ብሏል። የሶማሊላንድ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ፣ በሶማሊላንድና ሱማሊያ መካከል በጋራ ስምምነት የተደረሰበት የጋራ ሕገመንግሥት ኖሮ እንደማያውቅ ገልጧል። የሱማሊያ ሕዝብ በ1961 ተረቅቆ የነበረውን የጋራ ሕገመንግሥት ቢያጸድቀውም፣ የሶማሊላንድ ሕዝብ ግን እንዳላጸደቀው የሶማሊላንድ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በመግለጫው አስታውሷል። በሶማሊላንድ ሉዓላዊ ግዛት ላይ የራሳቸውን ሕግ ተፈጻሚ ለማድረግ የሚደረጉ የውጭ ሙከራዎችን ሶማሊላንድ እንደማትቀበል መግለጫው ጠቅሷል።


6፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ6286 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ7613 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 68 ብር ከ2332 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ5979 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ61 ከ0797 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ3013 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ማክሰኞ መጋቢት 24/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አደም ፋራህን ትናንት በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አድርገው ሹመዋል። አደም አዲሱ መንግሥታዊ ሸመት የተሰጣቸው፣ ከብልጽግና ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርነት ሥልጣናቸው ሳይለቁ ነው። አደም ፋራህ በአዲሱ ሹመታቸው፣ የዲሞክራሲ ተቋማትን የማስተባበር ሃላፊነት ይኖራቸዋል።

2፤ ኢሠማኮ፣ መንግሥት የመንግሥት ሠራተኞች እንዳይደራጁ የሚከለክለውን ሕግ እንዲያሻሽል መጠየቁን ሸገር ዘግቧል። በኢትዮጵያ አሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ላይ የመንግሥት ሠራተኞች እንዳይደራጁ መከልከላቸው በኅብረት መብታቸውን ለማስከበር እንዳይችሉ አድርጓል ሲሉ የኢሠማኮ ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ኢሠማኮ በመንግሥት ሠራተኞች ላይ በሚደርሰው የመብት ጥሰት ዙሪያ መከራከር እንዳልቻለም ካሳሁን ገልጸዋል ተብሏል። ኢትዮጵያ የዓለም ሥራ ድርጅትን የመንግሥት ሠራተኞችን የመደራጀት መብት የሚፈቅደውን ሕግ ያጸደቀች ቢኾንም፣ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ የመደራጀት መብት ያላቸው ግን የግልና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሠራተኞች ብቻ ናቸው።

3፤ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ድርጅት ጣና ሐይቅ ላይ ለሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት እንዲያገለግሉ ከውጭ የተገዙ ኹለት ዘመናዊ ጀልባዎች ጅቡቲ ወደብ መድረሳቸውን ትናንት ምሽት አስታውቋል። አንደኛዋ ጀልባ፣ "ጣና ነሽ ፪" የተባለች ዘመናዊ የሕዝብ ትራንስፖርት ጀልባ ስትኾን፣ ሌላኛዋ መለስተኛ ፈጣን ቃኝ ጀልባ እንደኾነች ድርጅቱ ገልጧል። "ጣናነሽ ፪" 38 ሜትር ርዝመትና ባንድ ጊዜ 188 ሰዎችን የመጫን አቅም አላት ተብሏል።

4፤ ንግድ ባንክ ያላግባብ የወሰዱትን ገንዘብ እስከ ትናንት ያልመለሱ ደንበኞቹን የመጀመሪያ ዙር ፎቶግራፍ ትናንት ምሽት በድረ-ገጹና በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ይፋ አድርጓል። ባንኩ ፎቶግራፋቸውን ይፋ ያደረገባቸው ደንበኞቹ፣ ከ108 ሺህ እስከ 305 ሺህ ብር የወሰዱ ናቸው ተብሏል። ባንኩ፣ በተራዘመው ቀነ ገደብ ማለትም በመጪው ረቡዕ ገንዘቡን የማይመልሱ ደንበኞቹን ለሕግ እንደሚያቀርብ ገልጧል። እስከ ትናንት ገንዘቡን ሙሉ በሙሉ የመለሱ ደንበኞች ብዛት 10 ሺህ 857 መድረሱን ባንኩ ጠቅሷል።

5፤ የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገ/መስቀል፣ የሩሲያ ባሕር ኃይል ምክትል ዋና አዛዥ አድሚራል ቭላድሚር ካሳቶኖቭ የመሩት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ትናንት ምጽዋ መግባቱን የኤርትራ መንግሥት አስታውቀዋል። የማነ፣ ልዑካን ቡድኑን የኤርትራ ጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ፊሊጶስ ወልደማርያም እንደተቀበሉት ገልጸዋል። የሩሲያ ባሕር ኃይል አንዲት ወታደራዊ መርከብ ከኤርትራ ባሕር ኃይል ጋር ለዘጠኝ ቀናት የሚቆይ ልምምድ በቀይ ባሕር ላይ ለማድረግ ባለፈው ሳምንት ዓርብ ምጽዋ መድረሷ ይታወሳል። [ዋዜማ]