Wazema Media / Radio
47.2K subscribers
262 photos
37 videos
7 files
1.07K links
Wazema is Radio other contents are available either in our website/social media or FM radio stations in Ethiopia. www.wazemaradio.com
Download Telegram
ለቸኮለ! ረቡዕ፣ ግንቦት 19፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ 24ኛ የአገር ውስጥ መዳረሻው የሆነውን የነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያን ዛሬ አስመረቀ። አውሮፕላን ማረፊያው፣ ዘመናዊውን ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን የማስተናገድ አቅም ያለው ነው። አውሮፕላን ማረፊያው በሳምንት ሦስት በረራዎችን ያስተናግዳል ተብሏል። አውሮፕላን ማረፊያውን መርቀው የከፈቱት፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ናቸው። ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ መንግሥት የሚገነባው እያንዳንዱ አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ ርቀትን በማጥበብ ትስስር እንደሚፈጥር፣ የክልሎችን ኢኮኖሚያዊ አቅም እንደሚያነቃቃና ሕዝቡን ይበልጥ እንደሚያቀራርብ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሠፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

2፤ የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ፣ በግል የጤና ተቋማትና መድኃኒት መደብሮች ውስጥ የሚቀጠሩ አዲስ ባለሙያዎች ከዚህ በኋላ የቅጥር ውል ሲፈጽሙ በየደረጃው በሚገኙ የመንግሥት የጤና መዋቅሮች እውቅና እንዲኾን አዘዘ። የግል የጤና ተቋማት አዲስ የሚቀጥሯቸው ባለሙያዎች ሥራ ከጀመሩበት ቀን አንስቶ ሙሉ መረጃቸውን ለክልሉ ጤና ቢሮ መላክ እንዳለባቸውም መታዘዛቸውንም ቢሮው በክልሉ ለሚገኙ 21 የዞን የጤና መምሪያዎች ከጻፈው ደብዳቤ ላይ ዋዜማ ተመልክታለች። ቢሮው፣ በግል የጤና ተቋማትና መድኃኒት መደብሮች ውስጥ ለሚቀጠሩ አዲስ ባለሙያዎች የሚከፈላቸው ደመወዝ በመንግሥት የጤና ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩ ባለሙያዎች ከሚከፈላቸው ደመወዝ ማነስ እንደሌለበት ጭምር ትዕዛዝ አስተላልፏል። በደብዳቤው ላይ የተጠቀሱትን ትዕዛዞች ተፈጻሚ በማያደርጉ የግል የጤና ተቋማት ላይ አስፈላጊውን ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ቢሮው አስጠንቋል።

3፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ ማግኘት ስላለበት "ልዩ ጥቅም" በግልጽ ውይይት እንደተጀመረ ተናገሩ። ከዚህ ቀደም ክልሉ ከከተማዋ ማግኘት ስላለበት "ልዩ ጥቅም" በግልጽ የተቀመጠ ነገር አለመኖሩን አዳነች የጠቀሱ ሲኾን፣ አሁን ግን በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት እንደተጀመረ የገለጡት ከቢቢሲ ጋር በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ባደረጉት ቃል ምልልስ ላይ ነው። ኾኖም ውይይቱ የተጀመረው፣ በአስተዳደሩ ውስጥ፣ በክልሉ መንግሥት ደረጃ ወይም በአስተዳደሩና በክልሉ መንግሥት መካከል ይሁን አይሁን በቃለ ምልልሱ ላይ በግልጽ አልተጠቀሠም። አዳነች፣ ከተማዋ ከሕግ አግባብ ውጪ በዙሪያዋ ወዳሉ አካባቢዎች እንዳትስፋፋ ወሠን እንደተበጀላትም ጠቁመዋል። የከተማዋ አስተዳደር በከተማዋ ትምህርት ቤቶች በሚያካሂደው የተማሪዎች ምገባ መርኃ ግብር በክልሉና በከተማዋ አዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ ተማሪዎችን ጭምር በማቀፍ የአዋሳኝ አካባቢዎችን ተማሪዎች የምገባ ወጪ አስተዳደሩ እየሸፈነ መኾኑንም ከንቲባዋ ተናግረዋል።

4፤ አፍሪካ ኅብረት በመጪው ሰኞ የሚካሄደውን የኢትዮጵያን ጠቅላላ ምርጫ የሚታዘብ ቡድን ላከ። የኅብረቱን ታዛቢ ቡድን የሚመሩት፣ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ናቸው። ታዛቢ ቡድኑ አምባሳደሮችን፣ የምርጫ አስተዳደርና የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎችንና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮችን ጨምሮ 73 አባላት ያሉትና ከ37 አገራት የተውጣጣ መኾኑን ኅብረቱ ገልጧል። ቡድኑ ግንቦት 26 አዲስ አበባ ውስጥ በሚሠጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን ይፋ የሚያደርግ ሲሆን፣ ከሁለት ወራት በኋላ ደሞ የመጨረሻ ሪፖርቱን ይፋ ያደርጋል ተብሏል።

5፤ የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጋሞ ዞን በቁጫ ምርጫ ክልል የሚካሄደው ቀጣዩ ምርጫ "ነጻ"፣ "ፍትሃዊ"፣ "አሳታፊ"፣ "ተዓማኒ" እና "ቅቡልነት" አይኖረውም በማለት ምርጫው እንዲታገድ ጠየቀ። ምርጫ ቦርድ፣ ፌዴራል መንግሥቱና የሰብዓዊ መብት ተቋማት የቁጫ ሕዝብ የመምረጥና የመመረጥ መብቶች እንዲረጋገጡ "አስቸኳይ ሕጋዊ እርምጃ" እንዲወስዱ ጥሪ ያደረገው ፓርቲው፣ ምርጫ ቦርድም ጥሠቶች እንዲታረሙ በማድረግ በሁለት ወራት ውስጥ ሌላ ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ጠይቋል። ችግሮች ባልተፈቱበትና "ለአንድ ወገን በሚያደላ" መልኩ በሚካሄድ ምርጫ የሚመጣውን ውጤት እንደማይቀበል ፓርቲው አስታውቋል። ፓርቲው፣ በገዥው ፓርቲ መዋቅርና በጸጥታ ኃይሎች ከ16 በላይ ጽሕፈት ቤቶቹ በኃይል እንደተዘጉበት፤ በአደባባይ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ እንዳይችል እንደተከለከለ፤ አባላቱና ደጋፊዎቹ ለሰብዓዊ መብት ጥሠቶች እንደተጋለጡና መራጮች ፓርቲውን እንዳይመርጡ "ማስፈራሪያ" እና "ድብደባ" እንደተፈጸመባቸው በመጥቀስ ከሷል።

6፤ የዛምቢያ ኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት ሉሳካ ከተማ ውስጥ ሕጋዊ ሰነድ የላቸውም ያሏቸውን ከ12 እስከ 50 የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ 25 ኢትዮጵያዊያን ሰሞኑን በቁጥጥር ሥር አዋሉ። ኢትዮጵያዊያኑ ከተማዋ ውስጥ የተያዙት፣ ባንድ የእንግዳ ማረፊያ ውስጥ የኢምግሬሽን አካላት ፍተሻ ባደረጉበት ወቅት መኾኑን የአገሪቱ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። ሁለት ዛምቢያዊያን ደሞ ከዚሁ እንግዳ ማረፊያ 17 ኢትዮጵያዊያንን በተሽከርካሪ አሳፍረው ወደ ሌላ ቦታ ሊሄዱ ሲሉ በቁጥጥር ሥር ውለዋል ተብሏል።

7፤ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ የኮሎምቢያ ተዋጊ ቅጥረኞች ለሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ለመዋጋት የተሠለፉት በተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ተቀጥረው መኾኑን አዲስ ባወጣው የምርመራ ሪፖርት አስታወቀ። ድርጅቱ፣ ኮሎምቢያዊያን ቅጥረኞቹ ሱዳን ከመግባታቸው በፊት በኢምሬቶች ወታደራዊ ጦር ሠፈሮች በኩል እንዳለፉና ሥልጠና እንደወሠዱ ማረጋገጡን ገልጧል። ቅጥረኞቹን በመቅጠር የተሳተፈው፣ 'ግሎባል ሴኩሪቲ ሠርቪስስ ግሩፕ' የተባለ ከኢምሬቶች መንግሥት ጋር ግንኙነት ያለው የግል የጸጥታ ኩባንያ ነው ተብሏል። ሂውማን ራይትስ ዎች፣ ሌሎች አገራት የኢምሬቶች ባለሥልጣናትን ጨምሮ በጉዳዩ ተሳታፊዎች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የሚያስችል ምርመራ እንዲደረግ ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቋል። አገራት ከኢምሬቶች ጋር ያላቸውን ወታደራዊ ትብብርና ለአገሪቱ የጦር መሳሪያ መሸጥ እንዲያቆሙ የጠየቀው ድርጅቱ፣ የአውሮፓ ኅብረት አገራት ደሞ ኢምሬቶች ለፈጥኖ ደራሹ ኃይል ድጋፍ መስጠት እንድታቆም በባለሥልጣናቷ ላይ ግፊት እንዲያደርጉ ጥሪ አድርጓል።

እንዲሁም:-

1.የ"Founders' Lounge" ዝግጅት አራተኛው ዙር፣ ነገ ሐሙስ ግንቦት 20 ቀን 2018 ዓ.ም. በቦሌ አትላስ አካባቢ በሚገኘው አዶር አዲስ ይካሄዳል።ከምሽቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄደው በዚህ ዝግጅት ላይ፣ የኢትዮጵያን የኮርፖሬት አመራር፣ የፈጠራ ስራዎች እና የአገር በቀል ኢኮኖሚ ተፅዕኖ ሚዳስስ ሰፊ ውይይት ይደረጋል።ባለሞያዎችም ልምዳቸውን ያካፍላሉ።

2. "ሚኒ ፖፕ-አፕ ማርኬት" የተሰኘ የገበያ ዐውደርዕይ ቦሌ አካባቢ በሚገኘው አትሞስፌር መዝናኛ ማዕከል ተዘጋጅቷል። ከግንቦት 22 እስከ 23 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ይካሄዳል። [ዋዜማ]
76👍7😍1
ለቸኮለ! ሐሙስ፣ ግንቦት 20፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የ1 ቢሊዮን ዶላር የዩሮ ቦንድ አበዳሪ ዓለማቀፍ ባለሃብቶች በእዳ አከፋፈል ዙሪያ ሲያደርጉት የቆዩት ሌላ ዙር ድርድር ሳይሳካ ቀረ። ድርድሩ ያልተሳካው፣ የዓለማቀፍ ቦንድ ያዥዎች መንግሥት በእዳ አከፋፈሉ ዙሪያ አሻሽሎ ያቀረበውን ሀሳብ ውድቅ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው። መንግሥት ሁሉም የውጭ አበዳሪዎች በቡድን 20 የአበዳሪዎች ማዕቀፍ ሥር የእዳ ሽግሽግ ሊያደርጉ ይገባል በሚለው አቋሙ የጸና ሲሆን፣ ኢትዮጵያ አኹንም የአበዳሪዎችን እኩልነት መርህ የሚያረጋግጥ “በገበያ ላይ የተመሠረተ መፍትሄ” ለመተግበር ቁርጠኛ መኾኗን ገልጧል። ድርድሩ ሲካሄድ የቆየው፣ መንግሥትና የዩሮ ቦንድ አበዳሪዎች ባለፈው ጥር ወር በመርህ ደረጃ የደረሱበትን ስምምነት የሁለትዮሽ አበዳሪ አገራት ኮሚቴ ሳይቀበለው ከቀረ በኋላ ነበር።

2፤ ስምረት ፓርቲ፣ ሕወሃት ከመላዋ ትግራይ ወጣቶችን በግዳጅ በማፈስ ወዳልታወቁ ካምፖች እየወሠደ ይገኛል ሲል ከሠሠ። ፓርቲው፣ በዚህ ድርጊት በመሳተፍ ላይ ያሉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል። በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ዳግም ጦርነትን የሚቃወሙ ወጣቶችና እናቶች እየተደበደቡና እየታሠሩ እንደሚገኙ ፓርቲው ገልጧል። ፌዴራል መንግሥቱና ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ሁኔታውን እንዲከታተሉ፣ ጣልቃ እንዱገቡና የግጭት ማቆም ስምምነቱን በይፋ የጣሱ አካላትን ተጠያቂ እንዲያደርጉ ፓርቲው ጠይቋል። ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች የተሠኘው የመብት ተሟጋች ተቋምም፣ በትግራይ የግዳጅ የወጣቶች ምልመላ እየተካሄደ ስለመኾኑ መረጃዎች እንደደረሱትና ምርመራ እያደረገ መኾኑን አስታውቋል።

3፤ ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን፣ ከ1 ሺሕ 540 በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች በአማራና አፋር ክልሎች ከሚገኙ የተሃድሶ ማዕከላት ሥልጠና አጠናቅቀው ወደ ማኅበረሰቡ መመለሳቸውን ገለጠ። በጎንደር-ጠዳ የተሃድሶ ማዕከል ከ720 በላይ የቀድሞ ታጣቂዎቹ ሥልጠና ሲያጠናቀቁ፣ በኮምቦልቻ 520 እንዲኹም በአፋር በጉሊና የተሃድሶ ማዕከል 300 የቀድሞ ታጣቂዎች ሥልጠና እንዳጠናቀቁ ኮሚሽኑ አስታውቋል። የአማራ ክልል የተሃድሶ ሥልጠና የአሁኑ አራተኛው ዙር እንደሆነ ኮሚሽኑ ጠቅሷል። የቀድሞ ተዋጊዎቹ ከኅብረተሰቡ ጋር ሲቀላቀሉ፣ መቋቋሚያ ገንዘብ ተሠጥቷቸዋል ተብሏል። ኮሚሽን ከኅዳር 2017 ዓ፣ም ጀምሮ እስካኹን በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋርና በኦሮሚያ ክልሎች 90 ሺሕ የሚሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎችን በተሃድሶ ማዕከላት አሠልጥኖ ከኅብረተሰቡ ጋር መቀላቀሉን ዛሬ ባሠራጨው መረጃ ጠቅሷል።

4፤ ኢጋድ፣ በመጪው ሰኞ ለሚካሄደው ሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ታዛቢ ቡድን ላከ። የምርጫ ታዛቢ ቡድኑን የሚመሩት፣ የቀድሞው የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዝዳንት ስፒሲዮዛ ዋንዲራ-ላዚቢዌ መኾናቸውን ድርጅቱ ገልጧል። ታዛቢ ቡድኑ 26 አባላት ያሉት ሲኾን፣ ከአባል አገራት የምርጫ ባለሙያዎች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ከሴቶችና ወጣት ማኅበራት የተውጣጣ ነው ተብሏል። ቡድኑ በአብዛኛዎቹ የአገሪቱ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች በመሠማራት፣ ከምርጫ ጣቢያዎች መከፈት እስከ ድምጽ ቆጠራ የሚኖረውን ሂደት እንደሚታዘብ ተገልጧል። ቡድኑ በመጪ ረቡዕ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን በጋዜጣዊ በጋዜ የሚያቀርብ ሲሆን፣ የመጨረሻ ሪፖርቱን ደሞ ምርጫ ቦርድ የመጨረሻውን የምርጫውን ውጤት ከገለጠ በኋላ ያቀርባል ተብሏል።

5፤ ታዋቂው የኬንያ የሰብዓዊ መብት ተቋም ካቲባ ኢንስቲትዩት፣ አሜሪካ ክትባት ባልተገኘለት የኢቦላ በሽታ ተይዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ ዜጎቿን የምትከታተልበት፣ የምታቆይበትና ሕክምና የምትሠጥበት ማዕከል ኬንያ ውስጥ ለማቋቋም የምታደርገውን እንቅስቃሴ የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲያግደው አቤቱታ አስገባ። ተቋሙ፣ የኬንያ መንግሥት የማዕከሉን መቋቋም እንዳይፈቅድና በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎች ወደ ኬንያ እንዳይገቡ እንዲያግድ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሠጥ ጠይቋል። ማዕከሉ ለጊዜው 50 አልጋዎችን የሚይዝ ሆስፒታል እንደሚኖረው የአሜሪካ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። አሜሪካ ይህን እቅድ ያቀደችው፣ ኢቦላ በሽታ በዲሞክራሲያዊት ኮንጎ ሪፐብሊክ እና ኡጋንዳ መስፋፋቱን ተከትሎ ነው።

እንዲሁም:-

1. የአርጀንቲና ኤምባሲ በኢትዮጵያ፣ የታንጎ ውዝዋዜና የሙዚቃ ፕሮግራም አዘጋጅቷል። እውቅ የአርጀንቲና እና የኢትዮጵያ አርቲስቶች የሚሳተፉበት ዝግጅቱ ነገ አርብ ከምሽቱ 1:00 ጀምሮ በፈንድቃ የባሕል ማዕከል ይካሄዳል።

2.በሚጻፋቸው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ስላቅ(ሳታየር) ጽሑፎቹ የሚታወቀው ተስፋዬ ኃ/ማርያም ያዘጋጀው "የባሻዬ ውጎች" የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ በቅርቡ ለንባብ ይበቃል። [ዋዜማ]
46👍12🙏4🥰1😁1
ለቸኮለ! ዓርብ፣ ግንቦት 21፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በመጪው ጠቅላላ ምርጫ ዋዜማ ላይ የመገናኛ ብዙኀን ተቋማትን ዝም ለማሠኘት "አፈናቸውን አጠናክረዋል" በማለት ወቀሠ። የድርጅቱ የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ዳይሬክተር ታይገሬ ቻጉታህ፣ ባለሥልጣናት በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚያካሂዱትን "የአፈና ዘመቻ" ሊያቆሙ ይገባል በማለት አሳስበዋል። ዳይሬክተሩ፣ የኢትዮጵያ የልማት አጋሮችና ቀጠናዊና ዓለማቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የአገሪቱን ነጻ መገናኛ ብዙኀን ለማጥፋት የሚፈጸመውን "ስልታዊ" አካሄድ ማውገዝ አለባቸው ሲሉ ጥሪ አድርገዋል። ስድስት የመገናኛ ብዙኀን ተወካዮች "በጸረ-መገናኛ ብዙኀን" ዘመቻው ሳቢያ ስለ ምርጫው ለመዘገብ እንደተቸገሩ እንደነገሩትም ድርጅቱ ጠቅሷል። የአገሪቱ ምርጫ ቦርድም፣ ምርጫውን ለመዘገብ ፍቃድ የሚጠይቁ መገናኛ ብዙኀን የስነ ምግባር ግዴታዎችን እንዲያከብሩ የሚያስገድድ "ቃለ መሐላ" በቅድሚያ እንደሚያስገባ ተቋሙ ገልጧል። ኾኖም የተቋሙ ዳይሬክተር የቃለ መሐላ ሠነዱ የመረጃ መቆጣጠሪያ መሳሪያ ነው በማለት ተችተዋል።

2፤ ኢዜማ፣ በሐረሬ ክልል ያቀረባቸው እጩ የሐረሬ ብሄረሰብ ተወላጅ አይደሉም በሚል ምርጫ ቦርድ "ሕጋዊ ባልኾነ" ውሳኔ ላይ በመመሥረት የጣለው እገዳ እንዲነሳ ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ እንደተደረገበት ገለጠ። ፓርቲው፣ ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ ምርጫ ቦርድን ሳያስቀርብ ራሱ የተከሳሽን የመከራከርያ ነጥቦች በማንሳት ውሳኔ አሳልፏል በማለት ተችቷል። ከፍተኛው ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ "አግባብነት ያለው" እና "ፍትሐዊ" ነው ብሎ እንደማያምን ፓርቲው አስታውቋል። ኢዜማ፣ የሐረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የብሄረሰብ ማንነትን መስፈርት በማድረግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረብኳቸውን እጩ ከምርጫው ውጪ አድርጎብኛል በማለት የከሠሠው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር።

3፤ በአማራ ክልል ታጣቂዎች ከዛሬ ጀምሮ በጣሉት የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ገድብ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ እንዲሁም በክልሉ ከተሞች መካከል የሚደረጉ የተሽከርካሪ ጉዞዎች ከፍተኛ መስተጓጎል እንደገጠማቸው ዋዜማ ሠምታለች። ለአብነትም፣ ከጎንደር እና ጎጃም ዞኖች በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በኩል ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ ጉዞዎች በከፍተኛ ደረጃ እንደተስተጓጎሉ ዋዜማ ተረድታለች። ከጎንደር ከተማ ወደ ደባርቅ፣ ባሕርዳር፣ ጎርጎራ፣ መተማ እንዲሁም ዳንሻ በተሽከርካሪ የሚደረጉ ጉዞዎችም መስተጓጎል እንደገጠማቸው ምንጮች ነግረውናል። ከባሕርዳር ከተማ ወደ ደብረማርቆስ፣ አዴት፣ መራዊ፣ ቡሬ እንዲሁም ሞጣ ከተሞች የሚደረጉ የተሽከርካሪ ጉዞዎች በተመሳሳይ መስተጓጎላቸውን ምንጮች ገልጸዋል። ኾኖም በከተሞች ውስጥ የታክሲዎች እና ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እንዳልተቋረጠ ታውቋል። የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳደር ግን፣ በዛሬው ዕለት የተዘጋ መንገድ አለመኖሩንና የረጅምና የአጭር ርቀት ተሽከርካሪዎች መደበኛ እንቅስቃሴ እንደቀጠለ መኾኑን ቀትር ላይ ባወጣው መግለጫ አስተባብሏል።

4፤ የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕወሃት በክልሉ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እያደረገ መኾኑን ገለጡ። ዓረና ትግራይ፣ የሕወሃት ቡድን የቀድሞ ተዋጊዎችን፣ ሚሊሻዎችንና የትግራይ ወጣቶችን በግዳጅ ለወታደራዊ ሥልጠና በመመልመል ላይ ይገኛል በማለት ከሷል። ፓርቲው፣ ድርጊቱ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሠት ነው በማለት አውግዟል። የትግራይ ወጣቶች ድርጊቱን በመቃወም የጋራ ትግል እንዲጀምሩ ፓርቲው ጥሪ ያደረገ ሲኾን፣ ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ፣ አፍሪካ ኅብረት፣ አውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካና ብሪታንያ ድርጊቱን እንዲያወግዙና አስፈላጊውን የዲፕሎማሲ ጫና እንዲያደርጉ ጠይቋል። የትግራይ ነጻነት ፓርቲም፣ የግዳጅ ምልመላ በክልሉ እየተካሄደ መኾኑን ጠቅሶ፣ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤትና አፍሪካ ኅብረት ድርጊቱ እንዲቆም ጫና እንዲያደርጉ ጠይቋል።

5፤ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከአውሮፓውያኑ 2010 እስከ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ ለኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ልማት ከአፍሪካ 54 አገራት መካከል 31ኛ ደረጃ ሠጣት። በተጠቀሠው የ15 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ባንኩ ለኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማት የሠጠው ነጥብ፣ ከ0 ነጥብ 47 ወደ 0 ነጥብ 52 አድጓል። አገሪቱ በመካከለኛ የኢንዱስትሪ ልማት ደረጃ ላይ እንድትወሠን አስተዋጽኦ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል፣ ዋነኛው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፏ ደካማ አፈጻጸም እንደኾነ ሪፖርቱ ጠቅሷል። ባንጻሩ፣ አገሪቱ በኢንቨስትመንት፣ መሠረተ ልማት እና የሰው ሀብት ልማት መካከለኛ ውጤት አስመዝግባለች። ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካን በመቅደም በአፍሪካ ግንባር ቀደም በኢንዱስትሪ ልማት በከፍተኛ ደረጃ ያደገች አገር መኾኗን ሪፖርቱ አመልክቷል።

6፤ የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሜሪካ በኢቦላ በሽታ የተጋለጡ ዜጎቿን ለመከታተል፣ ለማቆየት እና ለማከም ኬንያ ውስጥ ማዕከል እንድታቋቋም የአገሪቱ መንግሥት የሠጠውን ፍቃድ አገደ። ፍርድ ቤቱ የኬንያን መንግሥት ውሳኔ ያገደው፣ ካቲባ ኢንስቲትዩት የተባለ ታዋቂ የአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተቋም ባቀረበው አቤቱታ መሠረት ነው። ተቋሙ፣ የኬንያ መንግሥት የማዕከሉን መቋቋም እንዳይፈቅድና በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎች ወደ ኬንያ እንዳይገቡ እንዲያግድ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሠጥ አቤቱታ ያስገባው ትናንት ነበር። ተቋሙ በዚሁ አቤቱታው፣ የመንግሥት ውሳኔ በአገሪቱ ሕዝብ ጤና ላይ አደጋ ያስከትላል ብሏል።

እንዲሁም

1.ድምጻዊያኑ ዳዊት ጽጌ እና ኃይሉ አመርጋ በጥምረት የሙዚቃ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት "ፔፕሲ ሜዳ" የሙዚቃ ኮንሰርት ነገ ቅዳሜ አመሻሽ ላይ በአዲስ ዓለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ይካሄዳል።

2.በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የተዘጋጀውና በአገር በቀል እውቀት ሥርዓት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት በመጪው ሀሙስ ግንቦት 27 2018 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 ጀምሮ በአዲስ አበባ ቴክኖሎጂና ቢልት ኢንቫይሮመንት ኮሌጅ (አአዩ-5 ኪሎ ካምፓስ) ይከናወናል።
[ዋዜማ]
81👍14🥰1👏1🙏1
ለቸኮለ! ቅዳሜ፣ ግንቦት 22፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ ብሄራዊ ባንክ፣ በፍራንኮ ቫሉታ እቃዎችን ለሚያስገቡ አስመጪዎች አዲስ መመሪያ አወጣ። መመሪያውን የሚጥሱ አካላት የሚጣልባቸው ቅጣትና የወንጀል ተጠያቂነት በመመሪያው ላይ ሠፍሯል። መመሪያው ያስፈለገው፣ በውጭ ምንዛሬ ፍላጎትና በውጭ ምንዛሬ ቁጥጥርና በሕገወጥ መንገድ ከአገሪቱ በሚወጣው ገንዘብ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመድፈን መኾኑን ጠቅሷል። ፍራንኮ ቫሉታ ከተፈቀደላቸው አካላት መካከል፣ በኢኮኖሚ ቀጠናዎች የሚገኙ አምራቾች፣ የዲያስፖራ ባለሀብቶች፣ ውጭ ባለሀብቶች የተያዙ የማኑፋክቸሪንግና የኢንዱስትሪ ተቋማት፣ ዲፕሎማቶች፣ ዓለማቀፍ ድርጅቶችና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች፣ ዕርዳታ ተቀባይ የኃይማኖትና ሲቪክ ማኅበራት፣ የግል ንብረት የሚያስገቡ ግለሰቦችና በቋሚነት ወደ አገር የሚመለሱ ኢትዮጵያዊያን ይገኙበታል። ማናቸውም በፍራንኮ ቫሉታ የሚካሄዱ ግብይቶች በማዕከላዊ የውጭ ምንዛሬ መቆጣጠሪያ ማዕከል አማካኝነት ቁጥጥርና ምዝገባ ይካሄድባቸዋል ተብሏል።

2፤ ሰኞ ለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የተመዘገቡት ድምጽ ሠጪዎች ብዛት 54 ሚሊዮን 57 ሺሕ 861 መሆኑን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ቦርዱ፣ የመራጮች ብዛት 50 ነጥብ 5 ሚሊዮን መሆኑን ከሳምንታት በፊት የመራጮችን ምዝገባ ባጠናቀቀበት ወቅት ገልጦ ነበር። በአማራ ክልል በአምስት የምርጫ ክልሎች እንዲኹም በጋምቤላ ክልል በአራት የምርጫ ክልሎች እስከ ትናንት የምርጫ ቁሳቁሶችን ማድረስ እንዳልተቻለ ቦርዱ ገልጧል። ምርጫውን ለመታዘብ 55 የአገር ውስጥ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች 1 ሺህ 562 ታዛቢዎችን ያሠማራሉ ተብሏል።

3፤ ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪካ የላከችው ልዑካን ቡድን ደቡብ አፍሪካ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ደኅንነት ዙሪያ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር መከረ። ሁለቱ ወገኖች ወንጀሎች መቆም እንዳለባቸውና ኾኖም ሕጋዊ ሠነድ ላላቸውም ኾነ ለሌላቸው ስደተኞች የአገሪቱ መንግሥት የደኀንነት ዋስትና የመስጠት ኃላፊነት እንዳለበት መተማመን ላይ መድረሳቸውን በፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል፡፡ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ በወንጀልና ሕገወጥ ሥራዎች የሚሳተፉ ስደተኞች ሕጋዊ እርምጃ ሊወሠድባቸው እንደሚገባም ሁለቱ ወገኖች መግባባት ላይ እንደደረሱ ኤምባሲው ገልጧል። የደቡብ አፍሪካ ጸረ-ስደተኛ ሠልፈኞች ሁሉም ሰነድ አልባ ስደተኞች እስከ ሰኔ 23 ገደማ ከአገሪቱ እንዲወጡ በመጠየቅ ላይ ናቸው።

4፤ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የአንጎት ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ተመስገን ያረጋል የወረዳው አስተዳደር "ሰርጎ ገብ" ባላቸው ታጣቂዎች ጥይት ተመተው ሕይወታቸው አለፈ። ተመስገን በጥይት የተመቱት፣ ሥራቸውን ሲያከናውኑ ውለው ለእረፍት ምሽት ላይ ወደ ቤታቸው ሊገቡ መኾኑን የወረዳው አስተዳደር ገልጧል። ሃላፊው ላለፉት 21 ዓመታት በተለያዩ ሃላፊነቶች ላይ ማገልገላቸውን የጠቀሠው የወረዳው አስተዳደር፣ የሃላፊው የቀብር ስነ ሥርዓት በአንጎት ወረዳ አሁንተገኝ ከተማ ተከስቴ ቅድስት ስላሴ ቤተ-ክርስቲያን በዛሬው ዕለት መፈጸሙን አውስቷል።

5፤ የደቡብ ሱዳን መንግሥት፣ ግብጽ በአገሪቱ ውስጥ በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ ያቋቋመችውን ጦር ሠፈር እንድትዘጋ ማዘዙን የዓረብኛ የዜና ምንጮች ዘገቡ። ወታደራዊ ጦር ሠፈሩ፣ ወታደራዊ ስልጠና የመስጠትና የናይል ወንዝ ፍሠትን የመቆጣጠር ዓላማ ያለው ሲሆን፣ የወታደራዊ ሥልጠና ባለሙያዎችን ጨምሮ 260 የሰው ኃይል እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ። ጦር ሠፈሩ በደቡብ ሱዳኗ ላይኛው ናይል ግዛት ፓጋክ በተባለ አካባቢ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አቅራቢያ የሚገኝ ነው። ግብጽ ጦር ሠፈሯን እንድትዘጋ ደቡብ ሱዳን ያሳለፈችው ውሳኔ፣ አገሪቱ የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን ከመፈረሟ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ታዛቢዎች ተናግረዋል ተብሏል።

6፤ የኢትዮጵያ አጎራባች በኾነችው የሶማሊያዋ ሳውዝ ዌስት ፌደራል ግዛት መቀመጫ ባይደዋ በድጋሚ ዛሬ ግጭት ተቀሠቀሠ። ግጭቱ የቀሠቀሠው፣ በቅርቡ በፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ ገብነት ከሥልጣን የተባረሩት የግዛቲቷ ፕሬዝዳንት አብዲአዚዝ ላፍታጋሪን ታማኞች የኾኑ የታጠቁ ኃይሎች ከተማዋን ጥሠው መግባታቸውን ተከትሎ መኾኑን የግዛቲቱ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። ታጣቂዎቹ የከተማዋን በርካታ አካባቢዎች ከተቆጣጠሩና ከፌደራሉ መንግሥት ኃይሎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ፣ ከከተማዋ ለቅቀው ወጥተዋል ተብሏል። ፌደራል መንግሥቱ ባለፈው መጋቢት ወታደሮቹን ልኮ ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን እንዲለቁ ያስገደደው፣ የግዛቲቱ መንግሥት የፌደራል መንግሥቱ ያጸደቀውን የቀጥተኛ ምርጫ ሕግ ውድቅ በማድረጉ ነበር።

እንዲሁም:-

ነገ እሁድ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር፣በአዲስ አበባ ቴአትርና ባሕል አዳራሽ፣ ሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር እንዲሁም በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤቶች የሚቀርቡ ተውኔቶችን ዝርዝር እነሆ:-

እሁድ (ግንቦት 23 ቀን 2018 ዓ.ም)

➤በአዲስ አበባ ቴአትር እና ባሕል አዳራሽ:-

ከሰዓት 8:00 ሰዓት:- "ባልቻ አባ ነፍሶ" ተውኔት ይቀርባል

➤ በሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት:-

ከሰዓት 8:00 ሰዓት:- "ወህኒ አምባ" ተውኔት ይቀርባል

➤በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት፦

ከሰዓት 8፡00 ሰዓት፦ "ንጉሥ አርማህ"

ከቀኑ 11፡00 ሰዓት፦ "እምዬ ብረቷ" የተሰኙ ተውኔቶች ለተመልካች ይቀርባሉ

➤በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት፦

ከሰዓት 8፡00 ሰዓት፦ "የመጨረሻው ፍርድ" ተውኔት ይቀርባል [ዋዜማ]
79🙏3👍2😁2
The election may grant Abiy Ahmed and the Prosperity Party another five-year mandate, but it is unlikely to resolve Ethiopia’s underlying challenges.

Ultimately, the durability of Ethiopia’s stability will depend less on the outcome of today’s vote than on the government’s ability to address the political grievances, security challenges, and economic pressures that continue to shape the country’s future. Read our MEMO - https://open.substack.com/pub/wazema/p/ethiopia-votes-but-the-real-challenges?r=1e0ce8&utm_medium=ios
47👍11👎10👌4👏2
ለቸኮለ! ሰኞ፣ ግንቦት 24፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ምሽት 12 ሰዓት ይጠናቀቅ የነበረውን የድምጽ መስጪያ ጊዜ እስከ እኩለ ሌሊት 6 ሰዓት ድረስ ማራዘሙን አስታወቀ። የድምጽ መስጫ ሰዓቱ የተራዘመው፣ ድምጽ ለመስጠት እስከ 12 ሰዓት ድረስ የተሠለፉ መራጮች ድምጽ ሠጥተው እስኪጨርሱ ድረስ መሆኑን ቦርዱ ገልጧል። ቦርዱ በተወሠኑ የአማራና ኦሮሚያ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት የድምጽ መስጠት ሂደቱ መቋረጡን ቀደም ሲል የገለጠ ሲሆን፣ በሁለቱ ክልሎች በ143 የምርጫ ጣቢያዎች በጸጥታ ምክንያት ሳይከፈቱ እንደቀሩም ተናግሯል። ቦርዱ በአማራ ክልል በስምንት የምርጫ ክልሎች ዛሬ ምርጫ እንደማይካሄድ ቀደም ሲል አስታውቆ ነበር። በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘጋቢዎቹ ትናንት የምርጫ ዝግጅቱን ለመቃኘት በአዲስ አበባ ከተማ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ሲንቀሳቀሱ የምርጫ አስፈጻሚዎችና ጸጥታ ኃይሎች እንደከለከሏቸው ጣቢያው ገልጧል። ምርጫ ቦርድ፤ መገናኛ ብዙኃን ለዘገባ ሲንቀሳቀሱ ከሥራ ማስቆም “የተሳሳተ” ድርጊት ነው በማለት ተችቷል።

2፤ ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለከተማ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ነዋሪዎቿ ድምጽ በሠጡባት አዲስ አበባ በተለያዩ መንገዶች ላይ ብረት ለበስ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች፣ አድማ በታኞችና ሌሎች የጸጥታ ኃይል አባላት በስፋት ሲንቀሳቀሱ መዋላቸውን ዋዜማ ተመልክታለች። ባንጻሩ፣ በከተማዋ የሰዎችና የሌሎች ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ በእጅጉ ተቀዛቅዞ ውሏል። ለምርጫው መደበኛ የመንግሥትና የግል ሥራ ዝግ ኾኖ ቢውልም፣ ከይፋዊ የበዓል ቀናት በተለየ መዲናዋ ጭር ብላ መዋሏን ታዝበናል። ቦሌ እና መገናኛን ጨምሮ በአዘቦት ቀናት በሰዎችና በተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ይጨናነቁ የነበሩ አካባቢዎችና ግዙፍ የገበያ ማዕከላት ያሉባቸው ሕንጻዎችም ዝግ ኾነው ውለዋል። በዛሬው እለት እንዲዘጉ ግዴታ ያልተጣለባቸው በርካታ የከተማዋ የሕክምና ተቋማትና መድሐኒት ቤቶች ጭምር መዘጋታቸውን ዋዜማ ተመልክታለች።

3፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ የዛሬው ጠቅላላ ምርጫ እንዲስተጓጎል "የኢትዮጵያ ጠላቶች" ብዙ ሥራ ሠርተዋል በማለት ከሰሱ። ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዳይካሄድ "የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች" የተለያዩ ኃይሎችን ገዝተው በስፋት አሠማርተዋል በማለት የከሰሱት ዐቢይ፣ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ አትቻልም የሚል እምነት እንዲፈጠር ጥረት ተደርጓል ሲሉ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን በሻሻ የምርጫ ክልል ድምጽ ከሠጡ በኋላ ለጋዜጠኞች በሠጡት ቃል ተናግረዋል። የጸጥታ ችግሮች ባሉባቸው የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሰላም በመንግሥት ፍላጎት ብቻ የሚመጣ ተደርጎ መወሠድ የለበትም በማለት ዐቢይ የተናገሩ ሲሆን፣ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት እራሳቸው የሚመሩት ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ቢመረጥም ባይመረጥም የጸጥታ ችግሮች እንዲፈቱ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

4፤ የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ፣ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምርጫ ቦርድ በሲዳማ ክልል የሚያካሂደውን ምርጫ እንዲያግድ ያቀረበውን አቤቱታ "ከፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት" በተጻረረና "ሥውር የተጽኖ እጅ" እንዳለበት በሚያሳብቅ ሁኔታ እንዳዘገየበት በመግለጽ ወቀሠ። ፓርቲው ቦርዱ የጣለበትን እገዳ በመቃወም ባለፈው ወር የክስና የእግድ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ኾኖም ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ሲያሸጋግር ቆይቶ፣ ምርጫው አንድ ቀን ሲቀረው ግንቦት 22 ቅዳሜ ጉዳዩን በይርጋ አግዷል በማለት ፓርቲው ተችቷል። ሂደቱን የፖለቲካ ተፎካካሪ ፓርቲን ከምርጫ ለማግለል በሚደረገው ሴራ ውስጥ "የተቀናጀ ሴራ" አካል አድርጎ እንደሚመለከተው የጠቀሠው ፓርቲው፣ በዚህ ሳቢያ በዛሬው ምርጫ እንዳልተሳተፈ አስታውቋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደሞ፣ ጎጎት ፓርቲ በወልቂጤ ምርጫ ጣቢያ የምርጫ ታዛቢዎች ተደብድበው ከምርጫ እንዲወጡ ተደርጓል በማለት ከሷል። የምርጫ ወረቀት በፌስታል ተይዞ ሲበተን ተመልክተናል ያለው ፓርቲው፣ በወልቂጤ የምርጫ ክልል የሚደረገው ምርጫ እንዲቆም ለምርጫ ቦርድ ምርጫው አቤቱታ ማቅረቡንና አፍጣኝ ምላሽ እንደሚፈልግ ገልጧል። ፓርቲው፣ በጌታ ወረዳ ጉመር -1 ምርጫ ክልል ባሠማራቸው ታዛቢዮቹና ቤተሰቦቻቸው ላይ "ማስፈራሪያ" እና "ዛቻ" እንደተፈጸመባቸው በመግለጽ ጭምር ከሷል።

5፤ ከጦርነቱ በፊት ተቃቁሞ የነበረውና በቅርቡ ወደ ሥራ የተመለሠው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ሕወሃት ያቀረባቸውን የአዲስ የካቢኔ አባላት፣ የዞን አስተዳዳሪዎችና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሹመት ዛሬ ማምሻውን አጸደቀ። የሕወሃት ምክትል ሊቀመንበር አማኑኤል አሠፋ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንትና የፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ኾነው እንደተሾሙ የክልሉ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። 70 በመቶ ያህሉ የካቢኔ አባላት ከሕወሃት የተውጣጡ ሲሆኑ፣ 30 በመቶዎቹ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ከምሁራን የተውጣጡ እንደሆኑ ተገልጧል። በተመሳሳይ፣ ወልደአብርሃ ገብረጻዲቅ የሰሜን ምዕራብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ ሺሻይ ግርማይ የማዕከላዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ ዝናቡ ገብረመድኅን የደቡባዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ ግዴይ አዘናው የምዕራብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ ፍስሃ ኃይላይ የምሥራቅ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እንዲሁም ከለሊ ሐጋዚ የደቡብ ምስራቅ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኾነው እንደተሾሙ ዘገባዎቹ ጠቅሠዋል።

እንዲሁም:-

1.በአፍሪካ ጃዝ ቪሌጅ ዕውቅ የጃዝ ሙዚቀኞች የሚሳተፉበት ልዩ የጃዝ ሙዚቃ ዝግጅት ዛሬ ግንቦት 24 ከምሽቱ 2:00 ጀምሮ ይካሄዳል። በዝግጅቱ ላይ የኢትዮ-ጃዝ መስራች ሙላቱ አስታጥቄ እና አንጋፋው ድምፃዊ ግርማ በየነ የሙዚቃ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ይሆናል።

2.ሞሶብ ባንድ ልዩ የሙዚቃ ዝግጅቱን ዛሬ (ግንቦት 24) ከምሽቱ 2:30 ጀምሮ በሞሶብ የሙዚቃ ማዕከል ያቀርባል።
[ዋዜማ]
70👍15👎5🙏5🤔1
ለቸኮለ! ማክሰኞ፣ ግንቦት 25፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ የ1 ቢሊዮን ዶላር ቦንድ አበዳሪዎች ኮሚቴ ከኢትዮጵያ መንግሥት የእዳ አከፋፈል ዙሪያ ሌላ አዲስ ሃሳብ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ገለጠ። ኾኖም የተወሠኑ የኢትዮጵያ ቦንድ ያዥ ዓለማቀፍ ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያን በፍርድ ቤት የመክሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ኮሚቴው መናገሩን ሮይተርስ ዘግቧል። የቦንድ ያዦች የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበውን አዲስ ሀሳብ ባለፈው ሳምንት ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል። ኢትዮጵያ ለቦንድ ያዦች ኮሚቴ አዲስ ሀሳብ ያቀረበችው፣ መንግሥትና ኮሚቴው በእዳ አከፋፈል ዙሪያ ባለፈው ጥር ወር የደረሱበትን ስምምነት የሁለትዮሽ አበዳሪ አገራት ኮሚቴ ስምምነቱ ከቡድን 20 ማዕቀፍ መርኾዎች ጋር አይጣጣምም በማለት ውድቅ ካደረገው በኋላ ነበር።

2፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የምስራቅ አርሲ አገረ ስብከት፣ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በአሰኮ፣ ሺርካ እና ሆንቆሎ ዋቤ ወረዳዎች ታጣቂዎች ከትናንት በስቲያ እሁድ እና ትናንት ሰኞ በፈጸሙት "ሐይማኖት ተኮር ጥቃት" 13 ዩኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መገደላቸውን ገለጠ። በጥቃቱ ከ280 በላይ ምእመናን ከቀያቸው መፈናቀላቸውንና የ101 ዓመት እድሜ ያለው የጠለታ ጨፋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሙሉ ለሙሉ በእሳት መቃጠሉን አገረ ስብከቱ አስታውቋል። ዋዜማ በጥቃቱ ዙሪያ ያነጋገራቸው የአሰኮ ወረዳ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ይልማ ተረፈ፣ ታጣቂዎቹ በአሰኮ ወረዳ ካራ ቀበሌ ተመሳሳይ ጥቃት መክፈታቸውን ገልጸውልናል። ሊቀ ክህናት ይልማ፣ ነዋሪዎች ጥቃቱን በመሸሽ "ሱንቴ" ወደሚባል ቦታ እየተፈናቀሉ መኽኑንም ነግረውናል።

3፤ ኢሰመኮ፣ ትናንት በኢትዮጵያ የተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ፣ “ሰላማዊ”፣ “አሳታፊ” እና “አካታች” ነበር አለ። ኢሰመኮ፣ ከምርጫው ጋር በተያያዘ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሠቶች እንዳልተፈጸሙና ምርጫው ዓለማቀፍ የምርጫ መስፈርቶችን ባሟላ ሁኔታ መካሄዱን ዛሬ በሠጠው መግለጫ ላይ እንደገለጠ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል። ከ180 በላይ የምርጫ ክልሎች የክትትል ቡድኖቹ ክትትል ማድረጋቸውን የጠቀሠው ኢሰመኮ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ከቀረቡለት 104 አቤቱታዎች መካከል 93ቱ ከምርጫ ቦርድ ጋር ባደረገው የመረጃ ልውውጥ መፍትሄ ማግኘታቸውን ገልጧል ተብሏል። አራቱ አቤቱታዎች በሂደት ላይ ሲኾኑ፣ ሰባቱ ደሞ "ተጨማሪ መረጃ የሚሹ" እንደኾኑ ኢሰመኮ መናገሩንም ዘገባው ጠቅሷል።

4፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ሳቢያ ወደ ኩዌት አቋርጦት የቆየውን በረራ በድጋሚ ሊጀምር መኾኑን አስታወቀ። አየር መንገዱ፣ ወደ ኩዌት እንደገና በረራ የሚጀምረው ከሰኔ 9 ጀምሮ መኾኑን ዛሬ ባሠራጨው መረጃ ገልጧል። አየር መንገዱ ወደ ኩዌት እና ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ መዳረሻዎች የሚያደርጋቸውን እለታዊ በረራዎች ያቋረጠው በየካቲት ወር መገባደጃ ገደማ ነበር። በጦርነቱ ሳቢያ የኩዌት ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መዘጋቱን ተከትሎ፣ አየር መንገዱ ተጓዦችን ከኩዌት ወደ ዳማም እና ሪያድ በየብስ በመውሠድ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎች ዓለማቀፍ መዳረሻዎች ማጓጓዝ ጀምሮ እንደነበር አይዘነጋም። የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ወደ አፍሪካዊቷ ሞሪሺዬስ በሳምንት ሦስት በረራ ሊጀምር መሆኑንም አስታውቋል።

5፤ አሜሪካ፣ አፍሪካ ውስጥ ቪዛ የሚሠጡ ኤምባሲዎቿን ቁጥር ልትቀንስ መኾኗ ተሠማ። አሜሪካ ቪዛ የሚሠጡ ኤምባሲዎቿን ቁጥር ለመቀነስ ያሰበችው፣ ከ50 ወደ 20
መኾኑን ጠቅሶ የዘገበው አሶሴትድ ፕሬስ ነው። እቅዱ ተግባራዊ ከኾነ፣ አብዛኛዎቹ በአፍሪካ አገራት የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ቪዛ መስጠት አቁመው አሜሪካዊያን ዜጎችን በመርዳት ላይ ብቻ እንደሚያተኩሩ ዘገባው ጠቅሷል። ቪዛ መስጠት እንዲቀጥሉ ከተመረጡት ኤምባሲዎች መካከል፣ አዲስ አበባ፣ ናይሮቢ፣ ጅቡቲ፣ ካምፓላ፣ ኪጋሊ፣ አክራ፣ ኬፕታውን እና ጆሃንስበርግ የሚገኙ ኤምባሲዎች ይገኙበታል ተብሏል። 30 ያህል የአሜሪካ ኤምባሲዎች በሚገኙባቸው አገራት የሚገኙ የቪዛ አመልካቾች፣ ቪዛ የመስጠት ፍቃድ ያላቸው ኤምባሲዎች ወደሚገኙባቸው አገራት ለመጓዝ ሊገደዱ እንደሚችሉ ዘገባው አመልክቷል።

6፤ የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መንግሥት አሜሪካ ኬንያ ውስጥ በኢቦላ በሽታ ለተጠረጠሩ አሜሪካዊያን መከታተያና ማከሚያ ማዕከል እንድታቋቁም የደረሠበትን ስምምነት ዝርዝር ይፋ እንዲያደርግ አዘዘ። ፍርድ ቤቱ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊያዊት ሪፐብሊክ እና አጎራባች አገራት በበሽታው ተይዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ አሜሪካዊያን ወደ ኬንያ እንዳይገቡና ማዕከሉም እንዳይቋቋም ጊዜያዊ እገዳ የጣለው ባለፈው ሳምንት ዓርብ ሲኾን፣ ይህንኑ እገዳ ዛሬ ለሦስት ሳምንታት አራዝምታል። ኾኖም መንግሥት ማዕከሉ እንዲቋቁም የደረሠበትን ስምምነት እንደሚገፋበት ገልጧል። ይህንኑ ተከትሎ፣ ማዕከሉ ይቋቋምበታል በተባለበት አካባቢ ትናንት ተቃውሞ ተቀስቅሶ የሁለት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን የአገሪቱ የዜና ምንጮች ዘግበዋል።

እንዲሁም:-

1.የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባሕል ማዕከል የሚያዘጋጀው ጥበባዊ መርሐ-ግብር ነገ ረቡዕ ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም ከምሽቱ 11:00 ጀምሮ ይከናወናል። "የፍቅር ግርማ" በሚል መጠሪያ በተሰናዳው በዚህ መርሐግብር ላይ ድምጻዊት ፀደንያ ገብረማርቆስ የክብር እንግዳ በመሆን ትቀርባለች።

2.የደስታ የጃዝ ባንድ የሙዚቃ ዝግጅት በየሳምንቱ ረቡዕ ሀያት ሪጀንሲ ስር በሚገኘው ፈንድቃ የባሕል ማዕከል እየቀረበ ይገኛል። የጃዝ ሙዚቃ ዝግጅቱ ከምሽቱ 3:00 ሲል ይጀምራል።
[ዋዜማ]
60👍7😁5😍3🤔1🙏1
ለቸኮለ! ረቡዕ፣ ግንቦት 26፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የአፍሪካ ኅብረትና የኢጋድ የምርጫ ታዛቢዎች በኢትዮጵያ የተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ "ስላማዊ" እና "ሥርዓቱን የጠበቀ" እንደነበር ዛሬ በሠጡት መግለጫ ገለጡ። የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድን፣ ትግራይና የጸጥታ ችግር ያለባቸውን አንዳንድ የአማራ እና ኦሮሚያ የምርጫ ክልሎች ጨምሮ በ48 የምርጫ ክልሎች ድምጽ እንዳልተሠጠ ገልጧል። ኾኖም ወደፊት "ሁኔታዎች ሲፈቅዱ" ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ምርጫ እንደሚካሄድ ምርጫ ቦርድ ማረጋገጫ እንደሠጠው ቡድኑ አስታውቋል። የምርጫ ሃላፊዎች የምርጫ ሳጥን አያያዝንና መራጮችን ማረጋገጥን ጨምሮ የምርጫ ሕግጋትን ማክበራቸውንና የጸጥታ አካላት በድምጽ አሠጣጡ ወቅት ጣልቃ ሳይገቡ ሥርዓት ማስከበራቸውን ቡድኑ ጠቅሷል። የኅብረቱ ታዛቢ ቡድን ሊቀመንበር ኡሁሩ ኬንያታ፣ በአገሪቱ የጸጥታና አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በፖለቲካ ኃይሎች መካከል ንግግር እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ሠጥተዋል። ሁለቱ ቡድኖች ወደፊት ከምርጫ በፊት የጸጥታ ሁኔታዎች መሻሻል አለባቸው በማለት ምክረ ሀሳብ ሠጥተዋል።

2፤ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሰኞ'ለት በኢትዮጵያ የተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በሂደቱ ከቀደሙት ምርጫዎች፣ "ከአሳሳቹ" 97 በመቶ የአስቻይነት ሪፖርትና ትንተና፣ ከኢሕአዴግ "የጥርነፋ ውርስ ባሕርይ" እና "ከጥቅለላ አባዜ" ያልተላቀቀ ነው በማለት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ተቸ። ምርጫው "እጅግ የተወሳሰበውን" የአገሪቱን ችግር ከድጡ ወደ ማጡ ከመውሠድ የዘለለ ዴሞክራሲን አያዋልድም በማለት ያጣጣለው ትብብሩ፣ የትኛውም ዕጩ በትብብሩ ስም ምክር ቤት ቢገባ ፍጹም ተቀባይነት የለውም ብሏል። ትብብሩ፣ ሕዝብን ያሳተፈ ሰላማዊ ትግል ለማካሄድ የተሟላ መግለጫ በቅርቡ እንደሚሠጥም አስታውቋል። ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ፣ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡና ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኀን መንግሥት ከፖለቲካ ኃይሎች ጋር እስከሚደራደር ድረስ ምንም ዓይነት እውቅና የመስጠት የሚመስል መልዕክት ከማስተላለፍ እንዲቆጠቡም ትብብሩ ጠይቋል።

3፤ የቁጫ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በቁጫ ምርጫ ክልል ሰኞ'ለት የተካሄደው ምርጫ "ተጭበርብሯል" አለ። የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የገዥው ፓርቲ ታዛቢዎች፣ የቀበሌ አመራሮችና የጸጥታ አካላት ከመራጮች እጅ የድምጽ መስጫ ወረቀት እየነጠቁ ለገዥው ፓርቲ ድምጽ ሠጥተዋል በማለት የከሠሠው ፓርቲው፣ ምርጫው የመራጩ ሕዝብ ድምጽ ውጤት ተደርጎ ሊወሠድ አይችልም በማለት አቋሙን ገልጧል። በምርጫ ክልሉ የተሠጠው ድምጽ የቁጫን ሕዝብ ድምጽ ተደርጎ እንዳይቆጠርና እንዳይገለጽ፣ የድምጽ መስጫ ወረቀት በመንጠቅ ለአንድ ፓርቲ ድምጽ የሠጡ የምርጫ አስፈጻሚዎች በሕግ እንዲጠየቁና ምርጫው እንዲሠረዝ ፓርቲው ጠይቋል። ፓርቲው፣ መራጩ ሕዝብ የሚፈልገውን ፓርቲ እንዳይመርጥና ያልፈለገውን ፓርቲ ተገዶ እንዲመርጥ የማድረግ፤ ለቁሕዴፓ ዕጩዎች ድምጽ የሚሠጡ መራጮችን የመስደብ፤ መራጮች የሠጡትን የድምጽ መስጫ ወረቀት ገልጦ በማየት ቁሕዴፓን የመረጡ መራጮች ስም ዝርዝርን መዝግቦ የመያዝና ለጸጥታ አካላት አሳልፎ የመስጠትና በቁሕዴፓ መራጮች ላይ አካላዊ ጥቃት የመፈጸም ጥሠቶች እንደተፈጸሙ ዘርዝሯል።

4፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ሰሞኑን በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ የተፈጸመውን ''አሠቃቂ ጥቃት'' አወገዙ። ፓትርያርኩ፣ ጥቃቱ የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ ሃላፊነት ያለባቸውን የጸጥታ አካላትና የመንግሥት ኃላፊዎችን በታሪክ የሚያስጠይቅ መሆኑን ዛሬ ባወጡት መግለጫ ገልጸዋል። በምሥራቅ አርሲ ዞን በተደጋጋሚ የሚፈጸመው "በደል" እና "ግፍ" በሁሉም ልቡና ውስጥ "እስከ መቼ?" የሚል የቁጭት እና የኀዘን ጥያቄን መፍጠሩን ፓትርያርኩ አውስተዋል። ከመቶ ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረው የጠላታ ጨፋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መቃጠሉንና የካራ ኩፍቴና መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን መዘረፉን የጠቀሱት ፓትርያርኩ፣ በርካታ ምእመናን በግፍ መሠዋታቸውንና በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ከጥቃቱ ለመሸሽ ከቀያቸው መፈናቀላቸውንም ፓትርያርኩ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሠዋል።

5፤ ኢዜማ፣ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ አርሲ ዞን በንጹሃን ላይ ለተፈጸመው ጥቃት መንግሥት አስፈላጊውን ማጣራት አድርጎ ኃላፊነት የሚወስዱ አካላትን በመለየት "ሕጋዊ የእርምት እርምጃ" እንዲወስድ ጠየቀ። ፓርቲው፣ "ማንነትን" ወይም "ኃይማኖትን" መሠረት ባደረገ ጥቃት በርካታ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ የኾኑ ዜጎች ለጊዜው "ማንነቱ ባልታወቀ" አካል እንደተገደሉ፣ ቤተክርስቲያን እንደተቃጠለና ከጥቃቱ የሸሹ ነዋሪዎች ከቀያቸው እንደተሠደዱ መረዳቱን ገልጧል። ለዚህ ዐይነቱ "ማንነትን መሠረት" ያደረገ ጥቃት ምንጬ የአገሪቱ ፖለቲካ "በማንነት ላይ የተመሠረተ" መኾኑ ነው ያለው ፓርቲው፣ በማንነት ላይ የተመሠረተው ፖለቲካ መፍትሔ እንዲበጀለት የኹሉም ባለድርሻ አካላት የቤት ሥራ መኾኑን አጽንዖት ሠጥቷል። ኢዜማ፣ በምስራቅ አርሲ ዞን ውስጥ በንጹሃን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በመከላከል ረገድ የአካባቢው አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በተደጋጋሚ ተፈትነው ወድቀዋል በማለት ተችቷል።

6፤ የአዲስ ስታንዳርድ አሳታሚ ጃኬን አሳታሚ ኃላፊነቱ የተወሠነ የግል ማኅበር፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን የአዲስ ስታንዳርድን የምዝገባ የምስክር ወረቀት ባለፈው የካቲት ወር መሠረዙን በመቃወም ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፍትሐብሔር የክለሳ አቤቱታ አቀረበ። አሳታሚው፣ ፍርድ ቤቱ በክሱ ላይ ሕጋዊ ውሳኔ እስኪሠጥ የባለሥልጣኑ ውሳኔ ታግዶ እንዲቆይ ማመልከቱን አስታውቋል። ውሳኔው “ተገቢውን አስተዳደራዊ ሕጋዊ ሂደት ሳይከተል” የተላለፈ ነው ያለው አሳታሚው፣ ወደ ፍርድ ቤት ከመሄዱ በፊት ለባለሥልጣኑና ለሥራ አመራር ቦርዱ ቅሬታ ማቅረቡንና ኾኖም ምንም ዓይነት ምላሽ አለማግኘቱን ጠቅሷል። ባለሥልጣኑ በወቅቱ የአዲስ ስታንዳርድን የምዝገባ ወረቀት ሲሠርዝ፣ አዲስ ስታንዳርድ “የሚዲያ ሥነ ምግባርን"፣ "የኢትዮጵያን ሕጎች" እንዲሁም "የአገርንና የሕዝብን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ አስተላልፏል” በማለት ከስሶ ነበር።

እንዲሁም:-

1.በAWiB የተዘጋጀው የኢትዮጵያን የጀማሪ ኩባንያዎች ሥነ-ምህዳር ዕድገትና ተግዳሮቶች ላይ የሚያተኩር ውይይት ነገ ሐሙስ ግንቦት 27 ቀን 2018 ሂልተን ሆቴል ያካሂዳል። ተጋባዥ ተናጋሪዎችም ሀሳቦቻቸውን ያጋራሉ።ዝግጅቱ ነገ ከቀኑ 10:00 ጀምሮ  ይከናወናል።መግቢያው 2500 የኢትዮጵያ ብር ነው።

2. ECA ግቢ ውስጥ የሚገኘው የታሪካዊው የአፍሪካ አዳራሽ ዕድሳት መጠናቀቁን ተከትሎ፣ አዳራሹ በዘመናዊ የኮንፈረንስ እና የባሕል ማዕከልነት እንዴት እንደተዋቀረ፣ ታሪካዊ የጥበብ ሥራዎች እንዴት እንደተጠበቁና አዲሱ ሥነ-ሕንጻዊ ይዘቱ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ የጉብኝትና ገለጻ መርሐግብር ተዘጋጅቷል። ዝግጅቱ ዓርብ፣ ግንቦት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. ከጠዋቱ 4:00 ጀምሮ ይከናወናል።መግቢያው 1000 ብር ነው። [ዋዜማ]
58👍14😱3😍3🙏2👌2
ለቸኮለ! ሐሙስ፣ ግንቦት 27፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ ሕወሃት፣ ዲፕሎማቶችና አጋር አገራት በትግራይ በድጋሚ ሊቀሰቀስ የሚችለውን ጦርነት ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቀረበ። ቀውሱን ለመፍታት በሚያስችል ፖለቲካዊ ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ መኾኑን የገለጠው ሕወሃት፣ ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ ሁለቱን የፕሪቶሪያ ስምምነት ተፈራራሚ ወገኖች ወደ ጠረጴዛ ለማምጣት ንቁ ሚና እንዲጫወት ለዓለማቀፉ ኅብረተሰብ እና ለአጋር አገራት በጽሁፍ ጠይቋል። ሕወሃት፣ በትግራይ ድጋሚ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚለው ስጋት መላ ምት ሳይሆን እውን ለመኾን የተቃረበ መኾኑንና ዳግም ግጭት ከተቀሰቀሰ ደሞ ግጭቱ ቀጠናዊ የመሆን እድሉ ከፍተኛ እንደሆነ በመጥቀስ አስጠንቋል። ሕወሓት፣ መከላከያ ሠራዊት የትግራይን ድንበሮች መክበቡ በሕዝቡ ዘንድ ከባድ ጭንቀት ፈጥራል ብሏል። በምዕራብ ትግራይ ያለው "ሕገወጥ" አስተዳደር እና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ የፌደራል መንግሥቱ አጋሮቹ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሠቶችን መፈጸም ቀጥለዋል በማለት ሕወሃት የከሠሠ ሲኾን፣ ከአካባቢው አዳዲስ መፈናቀሎች መቀጠላቸውንም ገልጧል።

2፤ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን በአሰኮ፣ ሽርካ፣ ሆቆሎ፣ ዋቤ እና ሙኔሳ ወረዳዎች የተፈጸመውን የንጹሃን ግድያና የአብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎ አወገዘ። በተጠቀሱት ወረዳዎች በቤተክርስቲያኗ አገልጋዮችና ምዕመናን ላይ "አሰቃቂ" ግድያ መፈጸሙንና አብያተ ክርስቲያናትን የማውደም ድርጊት እንደተፈጸመ በመጥቀስ ቤተክርስቲያኗ ያወጣችውን መግለጫ "በታላቅ ልብ ስብራት" እና "ጥልቅ ሀዘን" መረዳቱን ጉባኤው ገልጧል። ጉባኤው፣ መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት የማረጋገጥ ተቀዳሚ ኃላፊነቱን እንዲወጣና በጥቃቱ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎችና በአካባቢው የጥቃት ስጋት ላለባቸው ወገኖች "አስተማማኝ ጥበቃ" እንዲያደርግ ጥሪ አድርጓል። መንግሥት ይህን "አሠቃቂ" ወንጀል የፈጸሙት አካላትን ለፍርድ እንዲያቀርብና ሂደቱን ለሕዝብ እንዲያሳውቅም ጉባኤው ጠይቋል። ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብት የተባለው የመብት ተሟጋች በበኩሉ፣ በጥቃቱ መሠረታዊ ምክንያቶች ዙሪያ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግና የጥቃቱ ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በበኩሉ፣ ጥቃቱ ብሄርንም ኾነ ሐይማኖትን መሠረት ያላደረገ እንደኾነ ጠቅሶ፣ ለጥቃቱ ኦነግ ሸኔን ተጠያቂ አድርጓል።

3፤ ምርጫ ቦርድ፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ለጠቅላላ ምርጫው ድምጽ የሚሠጡት በቀጣዩ ሳምንት ሰኔ 2 መኾኑን አስታወቀ። ቦርዱ የምርጫውን የመጨረሻ ውጤት ይፋ ለማድረግ ያቀደው ሰኔ 4 ቀን ነው። ቦርዱ ከሚያዝያ 18 እስከ ሚያዝያ 24 "በልዩ ሁኔታ" ባካሄደው የመራጮች ምዝገባ፣ 28 ሺሕ 632 ተፈናቃዮችና 126 ሺሕ 498 የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንደተመዘገቡ በወቅቱ ገልጧል። የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፣ የቁጫ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በቁጫ ምርጫ ክልል የተካሄደው ምርጫ እንደተጭበረበረ ጠቅሶ በጽሁፍ ቅሬታ ማቅረቡን ተናግረዋል። ሰብሳቢዋ፣ የቦርዱ የሕግ ክፍል በፓርቲው አቤቱታ ዙሪያ ክትትል እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

4፤ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን በወልመራ ወረዳ፣ በፍርድ ቤት የፍትሃብሄር ክርክር ወቅት ተከሳሽ ችሎት ውስጥ በተኮሠው ጥይት የፍርድ ቤቱ ሴት የመሃል ዳኛ ወርቅነሽ ፈከንሳን እና ከሳሽ ሚስቱን መግደሉን ዋዜማ ሠምታለች። ችሎቱ ተጣልተው በክርክር ላይ ባሉ ባል እና ሚስት መዝገብ ላይ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ዛሬ ሐሙስ ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ ተሠይሞ እንደነበር ዋዜማ ተረድታለች። ተከሳሹ ደብቆ ወደ ችሎቱ ባስገባው ሽጉጥ ግድያውን የፈጸመው፣ ዳኛዋ በግለሰቡ ላይ የቅጣት ብይን ማሳለፋቸውን ተከትሎ እንደኾነ ምንጮች ነግረውናል። ተከሳሹ ዳኛዋን እና ሚስቱን ከገደለ በኋላ ራሱንም በያዘው ሽጉጥ መምታቱንና ኾኖም ሕይወቱ መትረፉን ምንጮች ገልጸዋል። በጥቃቱ በችሎቱ ላይ የነበሩ ሌሎች ሰዎች ጉዳት እንደደረሠባቸውና ለሕክምና እርዳታ ወደ ሆለታ ሆስፒታል መወሠዳቸውን ዋዜማ የደረሳት መረጃ ያመለክታል።

5፤ ሊቲዌኒያ ውስጥ ሁለት ኢትዮጵያዊያን ሴቶችን በማዘዋወር ወንጀል አንድ የብሪታንያ የመኖሪያ ፍቃድ ያለው ኤርትራዊ ክስ ተመሠረተበት። ኢትዮጵያዊያኑ ደሞ ሐሰተኛ የማንነት ሠነዶች በመጠቀም ክስ እንደተመሠረተባቸው የአገሪቱ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። ኢትዮጵያዊያኑ በቁጥጥር ሥር የዋሉት፣ ሪጋ ከተባለች የሊቲዌኒያ ከተማ ወደ ፖላንድ ዋና ከተማ ዋርሶ ባለፈው ጥር ወር በአውቶብስ ሲጓዙ እንደነበር ዘገባዎቹ ጠቅሠዋል። ኢትዮጵያዊያኑ የግሪክ መኖሪያ ፍቃድ እንዳላቸው የሚያሳየው ሠነዳቸው ሐሰተኛ እንደነበርና ቤላሩስ ውስጥ በስደተኞች መጠለያ ውስጥ የሚኖሩ እንደነበሩ ፖሊስ ተናግሯል ተብሏል።

6፤ የሶማሊያ መንግሥት ወታደሮች እና ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር በወገኑ ሚሊሻዎች ትናንት ሌሊቱን ሞቃዲሾ ውስጥ የተኩስ ልውውጥ አደረጉ። ግጭቱ የተቀሠቀሠው፣ ተቃዋሚ ቡድኖች ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐሙድ ግንቦት 7 የተጠናቀቀውን የሥልጣን ዘመናቸውን በአንድ ዓመት ማራዘማቸውን በመቃወም ዛሬ ሞቃዲሾ ውስጥ የተቃውሞ ሠልፍ ለማድረግ እየተዘጋጁ በነበሩበት ሰዓት ላይ ነው። የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ሐሰን አሊ ካሃይሬ ሰላማዊ ተቃውሞውን ለመምራት እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት፣ የመንግሥት ወታደሮች ድንገተኛ ጥቃት እንደፈጸሙባቸው በመግለጽ ከሠዋል። በሞቃዲሾ የአሜሪካ ኤምባሲ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረው ግጭት፣ "ግድየለሽነት የተሞላበት ነው" በማለት የኮነነ ሲኾን፣ ሁለቱ ወገኖች ውጥረቱን በማብረድ በንግግር እንዲፈቱ ጠይቋል።

እንዲሁም:-

1.በአርባን አዲስ የሚዘጋጀው "Groove: The Jazz Show" የተሰኘው የሙዚቃ ዝግጅት ለሁለተኛ ጊዜ ነገ ዓርብ፣ ግንቦት 28 ቀን 2018 ዓ.ም. ከምሽቱ 1:00 ጀምሮ በደስክ አዲስ ይካሄዳል።

2."ኩታ ፋሽን እና አርት" የተሰኘው ዘመናዊ ፋሽንን፣ የሥነጥበብ ሥራዎችን እና የቀጥታ ሙዚቃ ዝግጅትን አቀናጅቶ የያዘ ትርዒት ቅዳሜ፣ ግንቦት 29 ቀን 2018 ዓ.ም. በኢትዮ-ኮሪያ ዘማቾች መታሠቢያ ፓርክ ከቀኑ 10:00 ጀምሮ ይከናወናል። [ዋዜማ]
62👍7😁2🙏2👏1😢1
ለቸኮለ! ዓርብ፣ ግንቦት 28፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ አርሲ ዞን በንጹሐን ዜጎችና በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ለተፈጸሙ ጥቃቶችን ቤተሰባቸውንና ወዳጆቻቸውን ላጡ፣ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸውና ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ወገኖቻች የተሠማቸውን "ጥልቅ ሐዘን" ገለጡ። ጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ማምሻውን በምርጫው ዙሪያ ባወጣው መግለጫ፣ ጥቃቱን የፈጸሙት የኦነግ ሸኔ ዐማጺያን መኾናቸውን ገልጧል። ጽሕፈት ቤቱ፣ ጥቃቶች የአገሪቱን ዕድገት ለማደናቀፍ ከሚሹ አካላት፣ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ አማጺ ቡድኖችና ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት "ጥላቻ" ካላቸው የውጭ ኃይሎች ጋር በጥምረት የተፈጸመ ነው ብሏል። ‎እነዚህ ኃይሎች "ዐመፅ" እና "ሁከት" ለማስነሳት፣ ከተሞችን "በሽብር ጥቃት" ለማወክ፣ በመንገዶች ላይ የደፈጣ ጥቃት በመፈጸም እንቅስቃሴ ለመገደብና በተወሠኑ አካባቢዎች ዒላማ አድርገው ነጥሎ ለማጥቃት ተንቀሳቅሰዋል በማለት ጭምር የወነጀለው ጽሕፈት ቤቱ፣ በደቡባዊ ትግራይ በሚገኙ አዋሳኝ የአማራ ክልል አካባቢዎች ትንኮሳ እንደተፈጸም ለአብነት ጠቅሷል።

2. ምርጫ ቦርድ፣ ገለልተኛ የሕግ ባለሞያዎች ቡድን አደራጅቶ ሰኞ'ለት በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ አካላት የቀረቡ ቅሬታዎችን በመመርመር ላይ መሆኑን አስታወቀ። ከቀረቡለት ቅሬታዎች መካከል አንዳንዶቹ በየደረጃው በሚከናወነው የምርጫ ሂደት መቅረብ የነበረባቸውና በምርጫ ክልሎች ደረጃ ሊቀርቡ የሚገባቸው መኾናቸውን የጠቀሠው ቦርዱ፣ ሌሎቹ ደሞ በማዕከል ደረጃ የሚመረመሩ መኾናቸውን ገልጧል።

3፤ ኢዜማ፣ ሰኞ"ለት የምርጫውን ሂደቱ ለማስተባበር የተመደቡ የምርጫ ቦርድ አስፈጻሚዎች ሕጋዊ ኃላፊነታቸውን በሌሎች የመንግሥት አስተዳደር አካላትና ግለሰቦች ሲነጠቁ ዝምታን መርጠዋል በማለት ከሠሠ። ኢዜማ፣ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የቦርዱ የምርጫ አስፈጻሚዎች በተግባር የገዢው ፓርቲ ታማኝ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ኾነው መገኘታቸውን ገልጧል። መንግሥት ለሕዝብ አገልግሎት የሚውሉ ንብረቶችን ለገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ጥቅም ማዋሉን፣ "የሰላም ሠራዊት" ተብለው የተደራጁ አካላት፣ የወረዳ ሥራ አስፈጻሚዎችና የመንግሥት ሠራተኞች በሕግ ባልተፈቀደላቸው የምርጫ ተግባራት መሳተፋቸውን፣ የጸጥታ አካላትና የገዢው ፓርቲ አመራሮች የተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢዎችን ማስፈራራታቸውንና ከጣቢያዎች በኃይል ማስወጣታቸውን ኢዜማ ጠቅሷል። ኢዜማ፣ "ትስስር፣ የብልጽግና ቤተሰብ" በሚባል ጥርነፋ ገዥውን ፓርቲ የማይመርጡ ዜጎች የማኅበራዊ ጥበቃ፣ የትምህርት ቤት ምገባና መሠረታዊ አገልግሎቶች እንደሚያጡ የማስፈራራት ድርጊቶች እንደተፈጸሙና ካድሬዎች በምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ "ስንዴን ምረጡ" እያሉ መቀስቀሳቸውን ተጨማሪ ጥሠቶች አድርጎ ጠቅሷል።

4፤ በእስር ላይ የሚገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ክርስቲያን ታደለ እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባሉ ዮሃንስ ቧያለው ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም ያስተላለፋቸውን ትዕዛዞች ማረሚያ ቤቱ በተግባር እንዲተረጉማቸው ባለማስገደዱ እስካኹን ምንም ዓይነት ፍትሕ አላገኘንም በማለት ቅሬታቸውን ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ አቀረቡ። የተከሳሾቹ ጠበቆች፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ እየደረሠባቸው ስላለው ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብቶች ጥሠትና ስላገጠማቸው የጤና እክል ለችሎቱ ማስረዳታቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል። ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት ውስጥ 60 ሰዎች ባሉበት እጅግ ጠባብ በኾነ አንድ ክፍል ውስጥ ታስረው እንደሚገኙና ቤተሰቦቻቸውን ማግኘት እንደማይችሉ ጠበቆቻቸው ገልጸዋል። ችሎቱ የመከላከያ ብይን ለመስማት ዛሬ ተሠይሞ የነበረ ቢኾንም፣ ዓቃቤ ሕግ የማስረጃ ውጤት አለመድረሱን አስረድቷል። ፍርድ ቤቱ የተከሳሾች ጠበቆች ባቀረቡት የሰብዓዊ መብት ጥሠት አቤቱታ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠትና አቃቤ ሕግ ባቀረባቸው ማስረጃዎች ላይ የመከላከያ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 3 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሠጥቷል።

5፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ልዑካን ቡድን፣ በምሥራቅ አርሲ ዞን በቤተክርስቲያኗ ተከታዮች ላይ በተፈጸመው ጥቃት ዙሪያ ከኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር መከረ። ልዑካን ቡድኑ መንግሥት የችግሩን ምንጭ አጣርቶ ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈልግና በአካባቢው አስተማማኝ የሆነ ሰላም እንዲያሠፍን መጠየቁን የቤተክርስቲያኗ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ አስታውቋል።

6፤ ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች – ኢትዮጵያ፣ የትግራይ ጸጥታ ኃይሎች በክልሉ መጠነ ሠፊ "አፈሳ" እና "የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ" እየተካሄደ መኾኑን በምርመራ ማረጋገጡን ገለጠ። ድርጊቶቹ ከሚፈጸሙቧቸው አካባቢዎች መካከል፣ ሰሜን ምስራቅ ዞን፣ ማዕከላዊ ዞንና ምሥራቃዊ ዞን እንደሚገኙበት ተቋሙ ጠቅሷል። ኾኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከመቀሌና ሌሎይ ጥቂት አካባቢዎች በስተቀር አፈሳው በመላዋ ትግራይ መስፋፋቱን ተቋሙ አስታውቋል። አፈሳው ባብዛኛው ዒላማ ያደረገው የቀድሞ ተዋጊዎችንና ወጣቶችን እንደኾነ መረዳቱን የጠቀሠው ተቋሙ፣ በጦርነቱ ተዋጊ ያላዋጡ ቤተሰቦች አንድ ምልምል እንዲያዋጡ እየተገደዱ ይገኛሉ ብሏል። ተቋሙ የትግራይ ባለሥልጣናት አፈሳውን ባስቸኳይ እንዲያስቆሙ፣ በጊዜያዊ ማቆያ የያዟቸውን ግለሰቦች እንዲለቁና ጊዜያዊ መጠለያዎችን ለሰብዓዊ መብት ተቋማት ክፍት እንዲያደርጉ የጠየቀ ሲኾን፣ አፍሪካ ኅብረት፣ አውሮፓ ኅብረትና አሜሪካም አፈሳው እንዲቆም ግፊት እንዲፈጥሩ ጥሪ አድርጓል።

7፤ የፌደራል ጠበቆች ማኅበር፣ በኦሮሚያ ክልል ወልመራ ወረዳ አንድ ተከሳሽ በወረዳው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የመሃል ዳኛ ወርቅነሽ ፈርከንሳ ላይ ትናንት ችሎት ውስጥ የፈጸመውን ግድያ አወገዘ። ማኅበሩ፣ ፍርድ ቤት ውስጥ የሚፈጸም ማንኛውም ዓይነት "የኃይል" እና "የጥቃት" ድርጊት በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚፈጸም "ከባድ ጥቃት" መሆኑን ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ ገልጧል። ማኅበሩ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ክስተቱን በተሟላ ሁኔታ እንዲያጣሩ ፣ በመላ አገሪቱ የዳኞች፣ የጠበቆች፣ የዓቃቢያነ ሕግ፣ የተከራካሪዎችና ሌሎች ተዋናዮች የደኅንነት ሁኔታ በተጠናከረ ሁኔታ እንዲጠበቅ አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ ጠይቋል። ዳኞች እና ሌሎች የፍርድ ቤት ተዋንያን ያለ "ፍርሃት" እና "ጫና" ሕጋዊ ሃላፊነታቸውን የሚወጡበት ከባቢ መፍጠር የፍትሕ ሥርዓቱን ለማጠናከር ወሳኝ መኾኑን ማኅበሩ አጽንዖት ሠጥቷል።
እንዲሁም:-

1.ጉንጉን የባሕል ባንድ ዛሬ አርብ ከምሽቱ 3:30 ጀምሮ በፈንድቃ ባሕል ማዕከል የሙዚቃ ዝግጅቱን  ያቀርባሉ።

2."ሆሄ ምዕራፍ" የመጽሐፍ ዳሠሣ መሰናዶ "ከማይጨው እስከ ኦጋዴን" በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ነገ ቅዳሜ ከረፉዱ 4:30 ጀምሮ  በብሔራዊ ቤተመጻሕፍትና ቤተመዛግብት አገልግሎት (ወመዘክር) አዳራሽ ውይይት ያካሂዳል።

3."ፈለገ ኪን" የኪነጥበብ ዝግጅት ነገ ቅዳሜ ግንቦት 29 2018 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ዓይነስውራን ብሔራዊ ማኅበር ግቢ ውስጥ ይካሄዳል። የኪነጥበብ ባለሞያዎቹ ተፈሪ አለሙ፣ምዕራፍ ተክሌና ሀይማኖት ግርማ ሀሳቦቻቸውን ያጋራሉ። [ዋዜማ]
66👍8👎6👌5🙏4😁1
#NewsAlert
በትግራይ ክልል ከሽራሮ ከተማ ወጣ ብለው በሚገኙት ልዩ መጠሪያቸው "ገማህሎ" እና "ተቀማጢ" ተብለው በሚጠሩት አካባቢዎች የድሮን ጥቃት መፈፀሙን ዋዜማ ሰምታለች።

በትላንትናው እለት ምሽት 5 ሰአት ተኩል ገደማ ለአንድ ሰአት ያህል የቆየ የድሮን ጥቃት መፈፀሙን እና ወታደራዊ ካምፖችን ኢላማ ማድረጉንም የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውናል።

እኩለ ለሊት ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ መሰማቱን ተከትሎ "ጦርነት ተቀስቅሷል" የሚል ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውን የገለፁት ነዋሪዎቹ፤ ጉዳት የደረሰባቸው የትግራይ ሃይል አባላት በመኪና ተጭነው ወደ ህክምና ቦታዎች ሲወሰዱ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በጥቃቱ ምን ያህል ሰዎች እንደተጎዱም ሆነ ጥቃቱ በማን እንደተፈፀመ ማረጋገጥ አልተቻለም። [ዋዜማ]
39👍22😢21😁10🤔4👌3👎1
ለቸኮለ! ቅዳሜ፣ ግንቦት 29፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ ‎ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት የትግራይ አስተዳደር፣ ፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን ሽራሮ አካባቢ በፈጸመው የድሮን ጥቃት በትግራይ ታጣቂዎች ላይ የሞትና የመቁሠል አደጋ ደርሷል በማለት ማምሻውን ባሠራጨው መግለጫ ከሠሠ። በትግራይ ክልል ከሽራሮ ከተማ ወጣ ብለው በሚገኙት ልዩ መጠሪያቸው "ገማህሎ" እና "ተቀማጢ" በተባሉ አካባቢዎች ትናንት ከምሽቱ 5 ሰዓት ገደማ የድሮን ጥቃት እንደተፈጸመ ዋዜማ ቀደም ብላ መዘገቧ ይታወሳል። ለአንድ ሰዓት ያህል የቆየው የድሮ ጥቃትን ዒላማ ያደረገው፣ ወታደራዊ ካምፖችን መኾኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለዋዜማ ተናግረዋል። በአካባቢው እኩለ ለሊት ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ መሠማቱን ተከትሎ፣ "ጦርነት ተቀስቅሷል" የሚል ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውን የገለፁት ነዋሪዎቹ፤ ጉዳት የደረሠባቸው የትግራይ ኃይል አባላት በመኪና ተጭነው ወደ ሕክምና ጣቢያዎች ሲወሠዱ መመልከታቸውን ተናግረዋል። ሆኖም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በጥቃቱ ምን ያህል ሰዎች እንደተጎዱም ሆነ ጥቃቱ በማን እንደተፈጸመ ማረጋገጥ አልተቻለም።

2፤ አፍሪካ ኅብረት ከብሪታንያ እና ኦስትሪያ ተወካዮች ጋር በፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት አፈጻጸም ዙሪያ መምከሩን አስታወቀ። ውይይቱ፣ በኅብረቱ የስምምነቱ መቆጣጠሪያና ማረጋገጫ ሥርዓት፣ በኅብረቱና በዓለማቀፍ አጋሮቹ መካከል ባለው ቅንጅታዊ አሠራርና የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታትና መልሶ ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀላቀል ሂደቱ አተገባበር ዙሪያ ያተኮረ እንደነበር ኅብረቱ ገልጧል። በትግራይ ባሁኑ ወቅት ያለው ሰብዓዊ ሁኔታና የኅብረቱ አደራዳሪ አካል ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ በጀመሩት አዲስ የሰላም ጥረት ዙሪያ ጭምር ውይይት እንደተደረገ ኅብረቱ ትናንት ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል።

3፤ ኢዜማ በአምስት ምርጫ ክልሎች የምርጫው ውጤት ተሠርዞ በድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ ለምርጫ ቦርድ አቤተታ አስገባ። ፓርቲው ለቦርዱ አቤቱታ ያስገባውው፣ በአምስቱ የምርጫ ክልሎች የምርጫውን ውጤት የቀየሩ ችግሮች ተፈጽመዋል ብሎ ስለሚያምን መኾኑን ዛሬ ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል። ፓርቲው አቤቱታ ያስገባባቸው የምርጫ ክልሎች፤ ባኮ ጋዘር ቁጥር 1 የምርጫ ክልል፣ ላስካ መደበኛ የምርጫ ክልል፣ ቢጣ ጌሻ የምርጫ ክልል፣ ፈለገ ሠላም የምርጫ ክልል እና ማረቃ ጌና የምርጫ ክልል መኾናቸውን ጠቅሷል። ፓርቲው፣ በሌሎች የምርጫ ክልሎችም በተመሳሳይ አቤቱታዎችን እየመረመር መኾኑን ገልጧል።

4፤ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ዳኞች ከማንኛውም ዓይነት "ዛቻ"፣ "ጫና" ወይም "ጥቃት" ነጻ ኾነው የሕግ ተግባራቸውን ማከናወን ይገባቸዋል ሲል በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በወልመራ ወረዳ ችሎት ውስጥ በተተኮሰ ጥይት የተገደለችውን ዳኛ ወርቄ ፈከንሳ አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት አሳሰበ። ፍርድ ቤቱ፣ ዳኛዋ በጦር መሣሪያ ጥቃት ሕይወታቸው በማለፉ የተሠማውን ሐዘን ገልጧል። ‎የዳኞች ደኅንነትና ነጻነት የፍትሕ ሥርዓቱ መሠረታዊ ዋስትና መኾኑን የጠቀሠው ፍርድ ቤቱ፣ ኾኖም በዳኛዋ ላይ የተፈጸመው ድርጊት በአንድ ዳኛ ላይ የተፈጸመ ወንጀል ብቻ ሳይኾን "በሕግ የበላይነት"፣ "በዳኝነት ነጻነት" እና "በፍትሕ ሥርዓቱ" ላይ የተቃጣ ከባድ ጥቃት ነው በማለት አውግዟል። በዳኞች ወይም በሌሎች የፍትሕ ሥርዓት ተዋናዮች ላይ የሚፈጸሙ የኃይል ድርጊቶች የሕግ "የበላይነትን ለማዳከም" የሚፈጸሙ ተግባራት እንደሆኑም ፍርድ ቤቱ አጽንዖት ሠጥቷል። ፍርድ ቤቱ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሕግ አስከባሪ አካላት ጉዳዩን "በፍጥነት"፣ "በተሟላ" እና "በግልጽ" ሁኔታ እንዲያጣሩና ተጠያቂዎችን ለሕግ እንዲቀርቡና ዳኞችና ሌሎች የፍትሕ ዘርፍ ባለሙያዎች ላይ ተመሳሳይ ጥቃቶች እንዳይፈጸሙ አስፈላጊ የጥበቃ እርምጃዎች እንዲወሠዱ አሳስቧል።

5፤ የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አብዲራህማን ዳሂግ ባካል፣ ሶማሊላንድ በባሕር በር ዙሪያ አሁንም ከኢትዮጵያ ጋር ለመተባበር ዝግጁ መኾኗን ለሪፖርተር በሠጡት ቃለ ምልልስ ገለጡ። ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት መብት አላት ብላ ሶማሊላንድ እንደምታምን የተናገሩት ባካል፣ ኢትዮጵያ በርበራ ወደብን እንደፈለገች መጠቀም ትችላለች ማለታቸውን ጋዜጣው ጠቅሷል። ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ አግኝቻለሁ ያለችው የ19 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ባካል ኢትዮጵያ ወደቡን በሙሉ አቅሙ እስካሁን አልተጠቀመችበትም የሚል አጭር ምላሽ መስጠታቸውን ተገልጧል። ኢትዮጵያ የሶማሊላንድን ቁልፍ አጋርነት ከግምት አስገብታ አንድ ቀን ለሶማሊላንድ እውቅና ትሠጣለች የሚል እምነት እንዳላቸው ባካል የገለጡት ሲኾን፣ ኾኖም ኢትዮጵያ እውቅና እንድትሠጣት ሶማሊላንድ ግፊት ማድረግ እንደማትፈልግ ተናግረዋል ተብሏል።

እንዲሁም:-

1. በሠዓሊ ጥበብ ሲራክ የተዘጋጀው "ሳንክተም" የተሰኘ የግል የሥነጥበብ ዐውደርዕይ ዛሬ ግንቦት 29 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ ሀውስ ኦፍ ካልቸር በይፋ ተከፍቷል። ይህ ዐውደርዕይ እስከ ሰኔ 21 2018 ዓ.ም በዕይታ ላይ ይቆያል ተብሏል።

2. በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተዘጋጀውና ከ40 በላይ የመጽሐፍ አከፋፋዮችና ሻጭች የሚገኙበት የመጽሐፍት ዐውደርዕይ የፊታችን ሰኞ ሰኔ 1 2018 ዓ.ም  ስድስት ኪሎ በሚገኘው የዩኒቨርስቲው ዋና ግቢ ውስጥ ይከፈታል።ዐወደርዕዩ እስከ ሰኔ 7 ይቆያል።
[ዋዜማ]
91👍18🙏4😍4
የኦሮሚያ ክልል ለሐይማኖትና ማህበራዊ ተቋማት የመሬት ይዞታ መመሪያ አወጣ።
ዝርዝሩን ያንብቡት- cutt.ly/gt2St8Nm
👎33😁138😍3
ለቸኮለ! ሰኞ፣ ሰኔ 1፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ ስምረት ፓርቲ፣ በትግራይ ክልል ላይ ተደቅኗል ያለውን የኅልውና አደጋ ለመቀልበስ ከሌሎች ለውጥ ፈላጊ እና የሰላም ኃይሎች ጋር የተቀናጀ ሕዝባዊ የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ አዲስ አቅጣጫ ማቀየሱን አስታወቀ። በክልሉ የሕወሃት ደጋፊ የሆኑ የጸጥታ ሃይሎች የሚያካሂዱት የወጣቶች የግዳጅ ምልመላ፣ አፈሳ እና ከፍተኛ ስደት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መሄዱን የገለጠው ፓርቲው፣ ይህ ሁኔታ ክልሉን ከማናቸውም ጊዜ በላይ ለከፋ የጦርነት ድባብ ዳርጎታል ብሏል። ፓርቲው፣ ሥልጣን በኃይል የነጠቀው አካል ወጣቶችን ወደ ሱዳን በማሻገር ለውክልና ጦርነት እየዳረጋቸው ይገኛል በማለት ከሷል። በቅርቡ በክልሉ ታሕታይ አዲያቦ አካባቢ ልዩ ስሙ ‘ገምሃሎ’ በተባለ አካባቢ ደርሷል ባለው "የወጣቶች እልቂት" ማዘኑን ጭምር ፓርቲው ገልጧል። ሕወሃት፣ በታሕታይ አዲያቦ መንግሥት ባለፈው ሳምንት ፈጸመው ባለው የድሮን ጥቃት በተዋጊ ኃይሎቹ ላይ ጉዳት እንደደረሠ መግለጡ ይታወሳል።

2፤ ኢሰመኮ፣ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ ግንቦት 23 እና 24 በተፈጸመው ጥቃት ዙሪያ ካሰባሰባቸው መረጃዎችና ማስረጃዎች ተጠያቂው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መኾኑን አስታወቀ። ኢሰመኮ፣ በጥቃቱ የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላትና ሲቪሎች መገደላቸውን፣ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውንና ንብረት መውደሙን ገልጧል። በአሰኮ ወረዳ ደለተ ጫፋ ቀበሌ በቡድኑና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ኃይሉ ንጉሴ እና ሠሙ አባይነህ የተባሉ የክርስትና እምነት ተከታዮችና ባቶ ሠፈኖ የተባለ የእስልምና እምነት ተከታይ መገደላቸውንና ከ2 ሺሕ 650 በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ተቋም ጠቅሷል። ኢሰመኮ፣ መንግሥት ጥቃት በተፈጸመባቸው አካባቢዎች ጸጥታ ኃይሎችን እንዲያሠማራና ሰላምና ደኅንነትን በማረጋገጥ ነዋሪዎችን ወደተረጋጋ ሕይወት እንዲመልስ ጭምር ኢሰመኮ አሳስቧል።

3፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሠው፣ ለአገር ውስጥና ለቀጠናዊ በረራ የሚያገለግሉ 25 ጠባብ የጎን ስፋት ያላቸውን አውሮፕላኖችን ለመግዛት እያሰበ መኾኑን ሪዮዲጄኔሮ ላይ ሰሞኑን በተካሄደው የዓለማቀፉ አየር መንገዶች ማኅበር ጉባኤ ላይ ተናገሩ። አየር መንገዱ ከቦይንግ፣ ኢምብራየር እና ኤርባስ ኩባንያዎች አውሮፕላኖችን እያማረጠ መኾኑን የገለጡት መስፍን፣ አውሮፕላኖቹ ኤርባስ A220፣ ኢምብራየር E2 እና ቦይንግ 737 ማክስ 7 መኾናቸውን መስፍን ገልጸዋል። አየር መንገዱ በ25ቱ አውሮፕላኖች ግዥ ዙሪያ በቀጣዮቹ ሦስት ወራት የመጨረሻ ውሳኔ ላይ እንደሚደርስም ጠቁመዋል። በተያያዘ፣ አየር መንገዱ በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ሳቢያ ከድሮው አንጻር 60 በመቶ ተጨማሪ ወጪ ለነዳጅ እያወጣ መኾኑን መስፍን ተናግረዋል።

4፤ አማራ ክልል የሕክምና ማኅበር፣ በክልሉ በሚገኙ የጤና ተቋማት የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች የአምስት ወራት የተረኝነት ክፍያቸው እንዲከፈላቸው በመጠየቃቸው ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች "ዛቻ"፣ "ማስፈራሪያ" እና "አስተዳደራዊ" ጫናዎች እየደረሱባቸው ይገኛል በማለት ከሠሠ። ማኅበሩ፣ "ያለምንም ቅድመ ሁኔታ" የባለሙያዎች የተረኝነት ክፍያ የበጀት ዓመቱ ከመዘጋቱ በፊት "በአስቸኳይ" እንዲከፈል አሳስቧል። በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በባለሙያዎች ላይ የሚያደርሱትን "ተጽዕኖ" እና "ዛቻ" በአስቸኳይ እንዲያቆሙም ማኅበሩ ጠይቋል። የጤና ባለሙያዎች ተስፋ ከቆረጡና መሠረታዊ ጥቅማቸውን ከተነፈጉ፣ በጤና መዋቅሩ ላይ ከባድ ጠባሳ እንደሚጥል ማኅበሩ አስጠንቅቋል።

5፤ ከተያዘው ሰኔ እስከ መስከረም ባሉት ወራት በአፍሪካ ቀንድ ከመደበኛው ያነሰ ዝናብ ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢጋድ የአየር ንብረት ትንበያ ማዕከል አስታወቀ። ማዕከሉ፣ በተለይ በማዕከላዊ፣ በሰሜን ምስራቅና ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ደቡባዊ ሱዳን፣ ሰሜናዊ ኡጋንዳ፣ ከመደበኛው ያነሰ ዝናብ ይጥላል የሚል ከፍ ያለ ትንበያ መኖሩን ጠቅሷል። በተጠቀሱት የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሰኔ እና ሐምሌ የአዝመራ መዝሪያ ወቅቶች ናቸው። ባንጻሩ፣ ደቡባዊ ምስራቅ ኢትዮጵያን ጨምሮ አንዳንድ የቀጠናው አካባቢዎች ከፍ ያለ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ ማዕከሉ ተንብዩዋል። በመደበኛው ጊዜ ወይም ቀድመው ዝናብ ያገኛሉ ከተባሉት የቀጠናው አካባቢዎች መካከል ደሞ፣ የሰሜናዊ መካከለኛው ኢትዮጵያ አካባቢዎች ይገኙበታል።

6፤ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ፣ ሕገወጥ ፍልሠትን ማስቆም አለብን በማለት ለሕዝባቸው ተናገሩ። ደቡብ አፍሪካ በርካታ ችግሮች እንዳሉባት የጠቀሱት ራማፎዛ፣ ኾኖም ሕገወጥ ፍልሠተኞች የአገሪቱ ችግሮች ምንጭ እንዳልሆኑ ለሕዝባቸው ባስተላለፉት መልዕክት ላይ ገልጸዋል። ራማፎዛ፣ ከመንግሥት ውጭ ማንም አካል ሕገወጥ ፍልሠትን ለማስቆም ማናቸውንም እንቅስቃሴ ማድረግ አይችልም በማለትም አስጠንቅቀዋል። መንግሥታቸው ሕገወጥ ፍልሠትን ለመከላከል የድንበር ቁጥጥሩን እንደሚያጠብቅና በኢምግሬሽን አሠራር ላይ የሚታየውን ሙስና እንደሚዋጋ ራማፎዛ ቃል ገብተዋል። ፕሬዝዳንቱ ይህን የተናገሩት፣ የተደራጁ ጸረ-ፍልሠተኛ ቡድኖች ሕጋዊ ሠነድ የላቸውም ባሏቸው አፍሪካዊያን ላይ ጥቃት መሠንዘራቸውን ተከትሎ ነው።

እንዲሁም:-

1.ፕሪስቴጅ አዲስ በአሜሪካ ኤምባሲ የሚያዘጋጅው ልዩ የእንግዳ ዝግጅት ነገ ማክሰኞ ሰኔ 2 2018 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ጀምሮ ይካሄዳል። በክብር እንግዳነት አርቲስት ሔኖክ ወንድሙ ይገኝበታል። የዝግጅት መግቢያ ቀድሞ መመዝገብ እንደሆነ አዘጋጆቹ አስታውቋል።

2.የአኮርዲዮን እና መሰንቆ ሙዚቃ ዝግጅት ነገ ማክሰኞ ከምሽቱ 2:00 ጀምሮ በሞሰብ የሙዚቃ ማዕከል ይካሄዳል።መግቢያው በነፃ ነው።
[ዋዜማ]
70👍12👎5
ለቸኮለ! ማክሰኞ፣ ሰኔ 2፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን በማፍረስ ሥልጣን በኃይል የያዘው በደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የክልሉ አስተዳደር፤ አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላን የሚፈቅድና ማዕከላዊ ኮማንድ ፖስት የሚያቋቁም ረቂቅ አዋጅ አዘጋጀ። ዋዜማ የተመለከተችው ረቂቅ አዋጅ፤ ዕድሜው የደረሠ ማንኛውም የክልሉ ነዋሪ የክተት ጥሪውን ተቀብሎ በወታደራዊ ግዳጅ እንዲሳተፍ ግዴታ የሚጥል ሲሆን፤ ጥሪውን የማይቀበል ከ10 ሺሕ እስከ 50 ሺሕ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚጣልበት ደንግጓል። የክተት ጥሪውን መሸሽ ለሚፈልጉ ግለሰቦች ሀሰተኛ የሕክምና ማስረጃ የሚሠጡ የጤና ባለሙያዎችም እስከ 50 ሺሕ ብር ቅጣት እንደሚጠብቃቸው በረቂቁ ላይ ሠፍሯል። ማዕከላዊ ኮማንድ ፖስቱን በበላይነት የሚመራው የክልሉ ፕሬዝዳንት፣ የተዋጊ ኃይሎች የበላይ አዛዥ እንደሚኾን ተጠቅሷል። በጦር ግንባር የተከፈለውን መስዋዕትነትና የሕዝቡን ትግል የሚያሳንስ ወይም የሚያጠለሽ ጽሑፍ፣ ንግግር ወይም ምስል ማሰራጨት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣም ተደንግጓል።

2፤ የሚንስትሮች ምክር ቤት ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከ2 ትሪሊዮን 339 ቢሊዮን በላይ በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቀረበ። ረቂቅ በጀቱ፣ ለመደበኛ ወጪዎች፣ ለካፒታል ወጪዎች፣ ለክልል መንግሥታት ድጋፍ እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ የሚውል መኾኑን ምክር ቤቱ አስታውቋል። ረቂቅ በጀቱ የተዘጋጀው፣ የ2019 የፌዴራል መንግሥት በጀት የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አካል የኾነው የ2019-2021 የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችንና የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚና የፊሲካል ማዕቀፍን መሠረት በማድረግ መኾኑን ተገልጧል። ለተያዘው በጀት ዓመት የተመደበው 1 ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮኑ ለመደበኛ ወጪ እና 415 ነጥብ 2 ቢሊዮኑ ለካፒታል ወጪ የተመደበ ነው።

3፤ ከኦሮሚያ ክልል ምእራብና ምሥራቅ ሐረርጌ ዞኖች ወደ አዲስ አበባ እና አዳማ ከተሞች ጫት ጭነው በሌሊት በሚጓዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ የተደራጁ ቡድኖች በሚያደርሱት ጥቃት ከአንድ ወር ወዲህ ቢያንስ የ10 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ዋዜማ ሠምታለች። ማንነታቸው በውል ያልታወቁ ናቸው የተባሉት ቡድኖች ይህንኑ ጥቃት የሚፈጽሙት፣ በክልሉ ምሥራቅ ሸዋ ዞን በአዳማ እና መተሐራ ከተሞች መካከል መሆኑን ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል። በተለይ ከአንድ ወር ወዲህ ጥቃቱ በተደጋጋሚ እየተፈጸመ መኾኑን የጠቀሱት ምንጮች፣ ቡድኖቹ ሾፌሮችንና ረዳቶቻቸውን አፍነው በመውሠድ ጭምር በሚሊዮኖች የሚቆጠር ማስለቀቂያ ገንዘብ እንደሚጠይቁ ገልጸዋል። በዚሁ የደኅንነት ስጋት ሳቢያ ሾፌሮች የጫት ምርት ጭነው መጓዝ ባለመቻላቸው፣ ጫት አምራቾች ለከፍተኛ ኪሳራ እየተዳረጉ መኾኑን ዋዜማ የደረሳት መረጃ ያመለክታል።

4፤ ምርጫ ቦርድ በልዩ ሁኔታ ባቋቋማቸው ወታደራዊ ካምፖችና የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ዛሬ ድምጽ ሲሠጥ ዋለ። በአማራ ክልል ድምጽ ከተሠጠባቸው ጣቢያዎች መካከል፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ የቻይና፣ የወይንሸት እና ባቂሎ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ 21 የምርጫ ጣቢያዎች፣ በሰሜን ወሎ ዞን ጃራ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ አራት የምርጫ ጣቢያዎች እንዲሁም በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ዙሪያ ወረዳ ገራዶ ቁጥር አንድ ጣቢያ ይገኙበታል። በሶማሌ ክልል ራሶ፣ በኦሮሚያ ክልል ደሎ መና፣ በአፋር ክልል ጉዋኔ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድባጤ እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡሌ የምርጫ ጣቢያዎችም በተመሳሳይ ድምጽ እንደተሠጠ ቦርዱ ገልጧል። ቦርዱ፣ በተለያዩ የተፈናቃይ መጠለያዎች 28 ሺሕ 632 ሺሕ ተፈናቃዮችን ለምርጫው መመዝገቡን መግለጡ ይታወሳል።

5፤ በጋምቤላ ከተማ ትናንት ማምሻውን አንድ የፌዴራል ፖሊስ አባል ድንገተኛ ተኩስ ከፍቶ እንደነበር የክልሉ መንግሥት አስታውቋል። ክስተቱን ተከትሎ የክልሉና የፌዴራል ጸጥታ አካላት በቅንጅት በመንቀሳቀስ ኹኔታው ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይሸጋገር ፈጣንና ተገቢ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን የክልሉ መንግሥት ገልጧል። በዚህም ሂደት የጸጥታ አካላት ኹኔታውን ለማረጋጋት ባደረጉት ጥረት በከተማዋ የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል ተብሏል። ከክስተቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ተጠራተው ተገቢው እርምጃ እንደሚወሠድ የክልሉ መንግሥት ገልጧል። በተኩስ ልውውጡ በሰዎች ላይ የደረሠ ጉዳት ይኑር አይኑር አልተገለጠም።

6፤ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተወሠኑ የአፍሪካ አገራት ጋር የተፈራረማቸው የጤና ስምምነቶች የሕይወት አድን ድጋፎችን ቁልፍ የጤና መረጃዎችን ለመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች አሳልፎ ከመስጠት ጋር የሚያስተሳስሩ ናቸው በማለት ወቀሠ። ተቋሙ፣ አሜሪካ በቅርቡ ከኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጄሪይል፣ ሩዋንዳ፣ ላይቤሪያ፣ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ጋር የተፈራረመቻቸውን ስምምነቶች መመርመሩን ገልጧል። ተቋሙ፣ መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶችን አደጋ ላይ የሚጥሉ የጤና ስምምነቶችን እንዲቀበሉ አሜሪካ እያስገደደች መኾኗን ገልጧል። የጤና ስምምነቶቹ በግለሰቦች የጤና መረጃዎች ሚስጢራዊነት ላይ ስጋት ሊደቅኑ የሚችሉ ናቸው ያለው ተቋሙ፣ የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጄሪያ እና ኡጋንዳ ጋር የተፈራረማቸውን ስምምነቶች በድረገጹ ላይ ይፋ ካደረገ በኋላ መልሶ አንስቷቸዋል ብሏል። አሜሪካ፣ ከስምምነቶቹ ጋር በተያያዘ ከአገራቱ ጋር በማዕድን ዙሪያ እያካሄደቻቸው ያሉትን ድርድሮች ይፋ እንድታደርግም ተቋሙ ጠይቋል።

እንዲሁም:-

1.በእስራኤል እና ኢትዮጵያ የጃዝ እና የባሕል ሙዚቃ ባለሙያዎች ትብብር የሚቀርብ የሙዚቃ ኮንሰርት ነገ ረቡዕ ሰኔ 3 በኢንተርላግዠሪ ሆቴል፤ ከምሽቱ 1:00 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል።

2.የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባሕል ማዕከል የሚያዘጋጀው ጥበባዊ መርሐ-ግብር ነገ ረቡዕ ሰኔ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ከምሽቱ 11:00 ጀምሮ ይከናወናል። "የሳቅ ምሽት" በሚል መጠሪያ በተሰናዳው በዚህ መርሐግብር ላይ አርቲስት መኮንን ላዕከ የክብር እንግዳ በመሆን ይቀርባል። [ዋዜማ]
60👌9🙏3👎1👏1😁1🤔1
መንግስት ጥቅል ሀገራዊ ምርትን (Gross Domestic Product-GDP) የሚለካበትን ስሌት ለመቀየር ለመቀየር እየተዘጋጀ መሆኑን ዋዜማ ያሰባሰበችው መረጃ ያመለክታል።

መንግስት ከመስከረም ወር 2019 ዓ. ም ጀምሮ በሚተገብረው አዲስ ጥቅል ሀገራዊ ምርት (GDP) ምጣኔ ስሌት መሰረት ኢትዮጵያ አሁን አላት ተብሎ የተሰላው ሀገራዊ ምርት ከሃያ እስከ አርባ በመቶ ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ከወዲሁ የባለሙያዎች ግምት ተቀምጧል። ይህም ሀገሪቱን በአፍሪቃ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ያሰልፋታል ተብሎ ይጠበቃል። ዝርዝሩን ያንብቡት cutt.ly/5t9p6nlK
😁9734👎16🥰3👏2🤔2😱1
ለቸኮለ! ረቡዕ፣ ሰኔ 3፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ መንግሥት ጥቅል አገራዊ ምርትን የሚለካበትን ስሌት ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ለመቀየር መዘጋጀቱን ዋዜማ ካሰባሰበችው መረጃ ተረድታለች። አዲሱ ስሌት፣ የአገሪቱን ጥቅል አገራዊ ምርት ከ20 እስከ 40 በመቶ ከፍ ሊያደርገውና ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ሊያስመድባት እንደሚችል ተገምቷል። ባሁኑ ወቅት የአገሪቱ ጥቅል ምርይ 170 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው። ላለፉት ዓመታት ለጥቅል አገራዊ ምርት የዋጋ ስሌት መነሻው የተደረገው 2008 ዓ፣ም ሲሆን፣ ቴሌ ብር፣ ሳፋሪኮም፣ ሕዳሴ ግድብና በከፍተኛ ደረጃ በማደግ ላይ ያለው የወርቅ የውጭ ገቢ በስሌቱ ውስጥ አልተካተቱም፡፡ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ግን እነዚህን አዳዲስ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ከግምት በማስገባት 2017 ዓ፣ም የስሌቱ መነሻ እንዲኾን መመረጡ ታውቋል። መንግሥት የስሌት ዓመቱን መቀየር የፈለገው፣ በዋነኛነት የአገሪቱ ኢኮኖሚ በቁጥር ደረጃ ግዙፍ መስሎ እንዲታይ ለማድረግ ነው ሲሉ አንድ እውቅ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ነግረውናል። -cutt.ly/5t9p6nlK

2፤ የኦሮሚያ ክልል የመሬት ቢሮ ለተለያዩ ሐይማኖታዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች የሚውሉና ሕጋዊ የባለቤትነት የይዞታ ማረጋገጫ ሠነድ ወይም ካርታና ፕላን ለሌላቸው የከተማ ይዞታዎች የሕጋዊነት ማረጋገጫ ሠነድ ሊሠጥ መኾኑን ዋዜማ ሠምታለች። የይዞታ ማረጋገጫ ከሚያገኙት መካከል፣ ለጋራ ማኅበረሰባዊ ጥቅም የሚውሉት እንደ ጥምቀት፣ ዋቄፈና እና ኢሬቻ ለመሳሰሉ ሐይማኖታዊና ባሕላዊ በዓላት የሚከበሩባቸው መሬቶች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ማምረቻና የእንሰሳት ማደለቢያና እርባታ ቦታዎች እና በወጣቶች፣ በሴቶች በመምህራንና በከተማ ነዋሪዎች የተያዙ የኅብረት ሥራ ማኅበራት እንደሚገኙበት ዋዜማ ቢሮው ካወጣው መመሪያ ላይ ተመልክታለች። ከይዞታ ማረጋገጫ መስፈርቶቹ መካከል፣ የክልሉ የከተማ መሬት ሊዝ አዋጅ ከጸደቀበት 2005 ዓ፣ም በፊት ይዞታው አገልግሎት መስጠቱ፣ በመሬቱ ላይ ቋሚ ንብረት መኖሩ፣ ከ2001 ዓ፣ም በፊት ቢያንስ ሦስት ጊዜ የከተማ የቤት ግብርና የመሬት ኪራይ የተከፈለበት ደረሠኝ ማቅረብ መቻል ተጠቅሠዋል።Link -cutt.ly/gt2St8Nm

3፤ የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ፣ በክልል ደረጃ ብቻ ከሚሠጡ 10 አገልግሎቶች መካከል ሰባቱ በዞን ደረጃ እንዲሁም ሦስቱ በወረዳ ደረጃ እንዲሠጡ መወሠኑን ዋዜማ ከደረሳት አንድ የቢሮው ሠነድ ላይ ተመልክታለች። ቢሮው ከክልል ወደ ዞን ካወረዳቸው አገልግሎቶች መካከል፣ ለባዛርና ኤግዚቢሽኖች የንግድ ፈቃድ መስጠት፣ ለአዳዲስ ማኅበራትና የንግድ ምክር ቤቶች የሕጋዊነት የምስክር ወረቀት መስጠትና ፈቃድ ማደስ፣ ለነዳጅ ማደያዎች ፈቃድ መስጠት፣ ለአገር ውስጥ የቡና የጅምላና የችርቻሮ ንግዶች የንግድ ፈቃድ መስጠትና ማደስ እንዲሁም በዞንና በከተማ አሥተዳደሮች አዲስ ለሚቋቋሙ የነዳጅ ማደያዎች ለፌዴራሉ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የድጋፍ ደብዳቤ መጻፍ ይገኙበታል። ወደ ወረዳ ደረጃ ከወረዱት አገልግሎቶች መካከል ደሞ፣ በወጪ ንግድ ፈቃድና የፍቃድ እድሳት ዙሪያ ለፌዴራል ተቋማት ደብዳቤ መጻፍ እና ለቡና ማከማቻ መጋዘንና ለቡና ጫኝ ተሽከርካሪዎች የንግድ ፈቃድ መስጠትና ማደስ ይገኙበታል።

4፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የከተማ ልማትና መሠረተ ልማት ቢሮ፣ ከእንግዲህ በከተሞች የጭቃ ቤቶችን መሥራት እንደማይቻል ትዕዛዝ ማስተላለፉን ዋዜማ ሠምታለች። ቢሮው በክልሉ ላሉት የ12ቱ ዞኖች የከተማ ልማትና መሠረተ ልማት መምሪያ የጻፈው ደብዳቤ፣ በክልሉ ከተሞች ከእንግዲህ የሚሠሩ ቤቶች ብሎኬት፣ ጡብ እና ሌሎች ማራኪ የኾኑ ግብዓቶችን በመጠቀም ብቻ እንዲኾን እንደሚያዝ ዋዜማ ተመልክታለች። የደን መመናመንና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ድርቅና የጎርፍ አደጋ ለመከላከል፣ በእንጨትና በጭቃ የሚሠሩ ቤቶችንና ሌሎች ግንባታዎችን ማስቀረት እንደሚያስፈልግ ቢሮው ገልጧል።

5፤ የቀድሞዋ የኢሰመኮ ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ የተመድ የአካል ጉዳተኞች ኮሚቴ አባል ኾነው ተመረጡ። የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ትናንት በሠጠው ድምጽ፣ ርግበ የ131 አባል አገራትን ከፍተኛ ድጋፍ አግኝተው ነው የተመረጡት። ለአፍሪካ ለተሠጡት ሁለት የኮሚቴው ወቀመጫዎች፣ ሰባት እጩዎች ተወዳድረው ነበር። ርግበ የኮሚቴው አባል ኾነው መመረጣቸው፣ የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበር ያላቸው እውቀትና ቁርጠኝነት ላይ ዓለማቀፍ አመኔታ ማትረፉን ያረጋግጣል ሲል ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አድናቆቱን ገልጧል።

6፤ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣ ለሸራተን ሆቴል ማስፋፊያ የሚውል የ80 ሚሊዮን ዶላር የረዥም ጊዜ የብድር ስምምነት ከዓለማቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ጋር ተፈራረመ። ኩባንያው፣ በብድሩ ሸራተን ሆቴልን በዘመናዊ መልኩ እንደሚያድስና በሸራተን ደረጃ በሸራተን የንግድ ምልክት የሚጠራ አዲስ ሆቴል እንደሚገነባ አስታውቋል። የሸራተን ሆቴል እድሳት የሆቴሉን ገጽታ በእጅጉ ይለውጠዋል ተብሏል። ይህ አጋርነት፣ የአገሪቱን የሆቴልና መስተንግዶ ዘርፍ ለማዘመንና ቀጣይነት ያለው የሥራ ዕድል ፈጠራን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የሁለቱ ኩባንያዎች ሃላፊዎች መናገራቸውን ሚድሮክ ካሠራጨው መረጃ ላይ ተመልክተናል።

7፤ የደቡብ አፍሪካው ስታንቢክ ባንክ በኢትዮጵያ በብቸኝነት በባለቤትነት የሚያስተዳድረውን ራሱን የቻለ ባንክ ለማቋቋም እያሰበ መኾኑ ተሠማ። ባንኩ ራሱን የቻለ ባንክ ለማቋቋም ያሰበው፣ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኩባንያ የኢንቨስትመንት ወጪ እየቀነሠና ገቢው እየጨመረ መሄዱን እንደ ጥሩ ምሳሌ በመውሠድ እንደኾነ የአገሪቱ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። ስታንቢክ ባንክ የግዙፉ የደቡብ አፍሪካ ስታንዳርድ ባንክ አንድ ካል ነው። ብሄራዊ ባንክ ያወጣው ሕግ፣ በአገር ውስጥ ባንክ የአክሲዮን ድርሻ መግዛት የሚፈልጉ የውጭ ባንኮች ድርሻቸው ከ49 በመቶ እንዳይበልጥ ገደብ ይጥላል።

እንዲሁም:-

ነገ ሀሙስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር፣ በሀገር ፍቅር ቴአትር እንዲሁም በዓለም ሲኒማ የሚቀርቡ ተውኔቶችን ዝርዝር እነሆ:-

ሀሙስ ( ሰኔ 4  ቀን 2018 ዓ.ም)

➤በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት፦

ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት፦ "ሸምጋይ" የተሰኘ ተውኔት ይቀርባል

➤በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት፦

ከምሽቱ 11፡30 ሰዓት፦ "ነገሩ አይቆምም " ተውኔት ይቀርባል

➤ በዓለም ሲኒማ:-

ከምሽቱ 12:00 ጀምሮ "የኮኮቡ ሰው" ተውኔት ለታዳሚያን ይቀርባል። [ዋዜማ]
65👍7👎4😁4
ለቸኮለ! ሐሙስ፣ ሰኔ 4፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ በትግራይ በኃይል ሥልጣን የያዙት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ዛሬ በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ በመኾኑት ኦሊሶጎን ኦባሳንጆ የተመራ የልዑካን ቡድን ጋር መቀሌ ውስጥ ተነጋገሩ። ውይይቱ፣ በትግራይ እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ እና ውይይት ለማስጀመር ያለመ እንደኾነ ኦባሳንጆ መናገራቸውን የክልሉ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። ከመቀሌው ውይይት በኋላ፣ ልዑካን ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ከፌደራል መንግሥቱ ባለስልጣናት ጋር ተመሳሳይ ውይይት እንደሚያደርግ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የሕወሃት አመራር አባል አዲስ ዓለም ባሌማ ተናግረዋል ተብሏል።

2፤ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አማካሪ ጌታቸው ረዳ እና የደኅንነት ሹሙ ሬድዋን ሁሴን፣ የሕወሃት ቡድን በኤርትራ መንግሥት ድጋፍ ከፍተኛ ተዋጊ ኃይል በማሠልጠን ላይ ይገኛል በማለት ከሰሱ። ቡድኑ ሰላሚ ፈላጊና የግጭት ማቆም ስምምነቱ ደጋፊ የኾኑ ግለሰቦችን መንጥሮ አስወጥቷል ሲሉ አልጀዚራ ላይ በጻፉት ሃተታ ገልጸዋል። ሕወሓት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር አዲስ ግጭት ውስጥ ለመግባት እያሟሟቀ ይገኛል ያሉት ጸሃፊዎቹ፣ በሕወሃትና በኤርትራ መንግሥት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችሉ አካላት ድጋሚ ግጭት እንዳይቀሰቀስ ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል። ድጋሚ ግጭት ከተቀሠቀሠ፣ ቀጠናዊ አንድምታ እንደሚኖረው ጸሃፊዎቹ አስጠንቅቀዋል።

3፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ለእስር ተዳርገው የነበሩ 1 ሺሕ 655 ኢትዮጵያዊያን የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ ምኅረት እንደተሠጣቸው አስታወቀ። ኢትዮጵያዊያኑ ምኅረት ያገኙት፣ መንግሥት ሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ እና ጂዳ የሚገኘውን ቆንስላ ጽሕፈ ቤትን በማስተባበር ባደረገው የዲፕሎማሲ ጥረት መኾኑን ገልጧል። ሕብረተሰቡ ከሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ሀሰተኛ ማታለያ ራሱን እንዲጠብቅ ያሳሰበው ሚንስቴሩ፤ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን የሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብሏል። የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በበኩሉ፣ አራት የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ኢትዮጵያዊያን በስቅላት እንደተቀጡ አስታውቋል።

4፤ ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከተያዘው 2 ነጥብ 34 ትሪሊዮን የፌደራል መንግሥት በጀት ውስጥ ከ542 ቢሊዮን ብር የሚኾነው ለዕዳ ክፍያ ተመደበ። ለውጭ ዕዳ ክፍያ 293 ነጥብ 3 ቢሊዮን ሲያዝ፣ ለአገር ውስጥ ዕዳ ክፍያ ደሞ 248 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ተመድቧል። የአገሪቱ አጠቃላይ ብድር መጠን 51 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደኾነ መንግሥት ከሁለት ወራት በፊት አስታውቆ ነበር። ለክልሎች ከ520 ቢሊዮን ብር በላይ የድጎማ በጀት የተያዘ ሲሆን፣ በዘንድሮው በጀት ዓመት የድጎማ በጀት ያልተመደበላት አዲስ አበባ 74 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ተመድቦላታል።

5፤ ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ የወንጀል ፍርደኞችን ለመለዋወጥ ተስማሙ።
የፍርደኞች ልውውጥ ስምምነትን አዲስ አበባ ውስጥ የተፈራረሙት፣ የኢትዮጵያ ፍትሕ ሚንስትር ሃና አርዓያ ሥላሴ እና የናይጄሪያ አቻቸው ላቲፍ ፋግበሚ ናቸው። ስምምነቱ በሀለቱ አገራት የፍትሕ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ያስችላል ተብሏል። የፍርደኞች ልውውጥ ስምምነቱ የተፈረመው፣ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ከናይጀሪያዋ አቻቸው ኦዱሜጉ ኦጁኩ ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ከተወያዩ በኋላ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ 100 ያህል ናይጀሪያዊያን እስረኞች እንዳሉ የአገሪቱ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር፣ ሁለቱ አገራት በፍርደኞች ልውውጥ ዙሪያ ንግግር ከጀመሩ ወዲህ ብቻ በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ከሚገኙ ናይጄሪያዊያን የአራቱ ሕይወት አልፏል ማለታቸውን ዘገባዎቹ ጠቅሠዋል።

6፤ ኦፌኮ፣ ኢትዮጵያ ያካሄደችው ጠቅላላ ምርጫ "በመሠረታዊ ግድፈቶች የተሞላ" እና "የዜጎችን የመምረጥ መብት በገፍ በነፈገ ሁኔታ" የተካሄደ ነበር በማለት አጣጣለ። ገዥውን ፓርቲ ወክለው የሚሠሩ የሚመስሉ የምርጫ አስፈጻሚዎች የፈጸሙት "አድሏዊነት"፣ በመራጮች ላይ የተፈጸመ "ማስፈራራት" እና በተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች ላይ የደረሠ "ተከታታይ ትንኮሳ" እና "ከምርጫ ጣቢያ በኃይል የማስወጣት" ድርጊት መታየታቸውን ኦፌኮ ጠቅሷል። ፓርቲው፣ የአፍሪካ ኅብረትና የኢጋድ ታዛቢ ልዑካን ያወጡት የቅድመ-ምርጫ መግለጫ "እጅግ የሚያሳዝን" እና "የዴሞክራሲን መርህ ያቃለለ" ነበር በማለትም ተችቷል። ኦፌኮ፣ ግጭቶች በዓለማቀፍ ታዛቢዎች ክትትል በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ እንዲፈቱና ዘላቂ አገራዊ መግባባትን ለማረጋገጥ ሁሉን ዓቀፍ የፖለቲካ ውይይት እንዲካሄድና ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ መንግሥት ሐቀኛና ሁሉን ዓቀፍ አገራዊ ውይይት እንዲያካሂድ ትርጉም ያለው ጫና እንዲያሳድር ጠይቋል።

7፤ ኢዜማ፣ የትግራይን ሕዝብ ካላስፈላጊ መከራ ለመታደግ በሕዝብ ላይ ምንም ዓይነት መስዋዕትነት በማያስከትል መልኩ መንግሥት በሕወሃት ሕገወጥ ቡድን ላይ ብቻ ያነጣጠረ አስፈላጊ ሕጋዊ እርምጃ ሊወስድ ይገባል አለ። ኢዜማ፣ ሕወሃት የግዳጅ የጦርነት ምልመላ አዋጅ ማውጣቱና ከግዳጅ ምልመላና ጦርነቱትን ካለመደገፍ ጋር በተገናኘ በቅርቡ ባወጣው አዋጅ ያካተታቸው ቅጣቶች ሕዝቡ በጦርነት ለመሣተፍ ፍላጎት እንደሌለውና በዚህም ቡድኑ ስጋት እንዳደረበት ያሳያል ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ አውስቷል። ኢዜማ፣ የትግራይ ሕዝብ አሁን ለጦርነት እያሳየ ያለውን "እምቢተኝነት" በተጠናከረ መልኩ ሊገፋበት ይገባል በማለት ጥሪ አቅርቧል።

8፤ በነባሩ የተሽከርካሪ ሠሌዳ ላይ የሚገኘው "ET" የሠሌዳ ኮድ የግብጽ መለያ ኮድ መሆኑ በመረጋገጡ ወደ "ETH" የተቀየረው የአዲሱ ሠሌዳ ሥርጭት በአዲስ አበባ ከተማ ዛሬ እንደተጀመረ የከተማዋ አስተዳደር የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዛሬ አስታወቀ። አዲሱ ታርጋ ባሁኑ ወቅት ሥራ ላይ የሚውለው አዲስ ለሚገዙ ተሽከርካሪዎች እንደኾነና ከዚህ በፊት ሠሌዳ ላልተሠጣቸው ተሽከርካሪዎች ደሞ አገልግሎቱ በቅርብ እንደሚጀመር ተነግሯል። የሕዝብ ትራንስፖርት ሠጪዎች በአነስተኛ ታሪፍ የሚስተናገዱ ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የማበረታቻ ቅናሽ ተደርጎላቸዋል። ባንጻሩ በነዳጅ የሚሠሩ የግል ተሽከርካሪዎች ከዝቅተኛው 11 ሺሕ ብር ጀምሮ እስከ 56 ሺሕ ብር እንዲከፍሉ ይደረጋሉ ተብሏል።

እንዲሁም:-

1.“በእውነት ቅኔ" የተሰኘ የሙዚቃ ዝግጅት ነገ አርብ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ 24 አካባቢ በሚገኘው ሞሰብ የሙዚቃ ማዕከል ውስጥ ይካሄዳል።መግቢያ በነፃ።

2.በፈንድቃ ባሕል ማዕከል የሚዘጋጀው የ"ኢትዮ-ከለር” ባንድ ትርኢት፣ ነገ አርብ ከምሽቱ 3፡00 ጀምሮ ይካሄዳል። ትርዓቱም ሦስት ትውልድን የሚያሳትፍና የኢትዮጵያን የባሕል ሙዚቃ ከዘመናዊ የውዝዋዜ ስልቶች ጋር አቀናጅቶ የሚያቀርብ መሆኑ ተገልጿል።

3. በአፍሪካ ጃዝ ቪሌጅ ዛሬ ነገ ዕውቅ የጃዝ ሙዚቀኞች የሚሳተፉበት ልዩ የሙዚቃ ድግስ ከምሽቱ 3:00 ጀምሮ ለታዳሚዎች ይቀርባል። [ዋዜማ]
83👍9👎4🙏4😁1
ለቸኮለ! ዓርብ፣ ሰኔ 5፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የተመድ ሕጻናት ድርጅት ዩኒሴፍ፣ በኢትዮጵያ በበርካታ ክልሎች ያለው የጸጥታ መደፍረስ ለሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት መሠናክል ኾኖ ቀጥሏል አለ። በአገሪቱ በግጭት፣ በስደተኞች ቁጥር መጨመር፣ በአየር ንብረት ለውጦች እና በኢኮኖሚያዊ ጫና ሳቢያ የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት አሁንም ከፍተኛ መኾኑን ሰሞኑን ባወጣው ከመጋቢት እስከ ሚያዝያ በሚሸፍነው ሪፖርት ገልጧል። በተለይ በኦሮሚያ፣ አማራ እና ሶማሌ ክልሎች በምግብ ዋስትና ችግር ሳቢያ የቀነጨሩ ከአምስት ዓመት በታች የኾኑ ሕጻናት ቁጥር ከፍተኛ መኾኑን ድርጅቱ ጠቅሷል።

2፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የፈረንሳዩ የካቶሊክ ጋዜጣ የሆነው ላ ክሮክስ ዘጋቢ የሆነችውን አውግስቲን ፓሲሊን ከአገር አባረረ። ጋዜጠኛዋ ባለፈው ወር ወደ ትግራይ ተጉዛ እንደነበር የጠቀሠው የፈረንሳዩ የዜና ወኪል፣ ኾኖም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣናት ባስቸኳይ ከትግራይ እንድትመለስ በስልክ እንዳዘዟትና የጸጥታና ፖለቲካ አለመረጋጋት ወዳለበት አካባቢ ሂዳ በመዘገቧ ትችት እንዳቀረቡባት ጠቅሷል። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋዜጠኛዋን ለምን ከአገር እንዳስወጡ በይፋ ማብራሪያ አልሠጡም ተብሏል። ጋዜጣው ዘገቢዋ የጣሠችው ሕግ እንደሌለ ገልጦ፣ ውሳኔው በፕሬስ ነጻነት ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው ማለቱን ዘገባው አመልክቷል። ዘጋቢዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት አራት ዓመታት በጋዜጣው ዘጋቢነት በመስራት ላይ እንደነበረች ተገልጧል።

3፤ ጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን እና ምሥራቅ ጉራጌ ዞን በስምንት የምርጫ ክልሎች የምርጫውን ውጤት ሊቀይሩ የሚችሉ ጥሠቶች ተፈጽመዋል አለ። ጎጎት፣ ገዢው ፓርቲ ራሱ ተወዳዳሪ፣ ራሱ የምርጫ አስፈጻሚ፣ ራሱ ድምጽ ሠጪ እና ቆጣሪ ኾኗል በማለት ከሷል። ድምጽ ሠጪዎችን ከቦታ ቦታ በማመላለስ አንድ ሰው ከአንድ በላይ ድምጽ እንዲሠጥ የማድረግ፣ የሐሰተኛ ድምጽ መስጫ ወረቀቶችን በብዛት የመጠቀም፣ መራጮች የትኛውን ፓርቲ እንደሚመርጡ በአስገዳጅ ሁኔታ የመጠየቅና በድምጽ ቆጠራ ወቅት የፓርቲውን ወኪሎች በማስፈራራት የማስወጣት ጥሠቶች ጭምር እንደተፈጸሙ ፓርቲው ገልጧል። ምርጫ ቦርድ፣ በጉራጌ ዞኖች በስምንት የምርጫ ክልሎች ላይ ከጎጎት አቤቱታ መቀበሉን ገልጧል።

4፤ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ እና የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ፣ የሊቀ ጳጳስነት ኃላፊነታቸውን በጡረታ ምክንያት ማስረከባቸው ተሠማ። ቤተክርስቲያኗ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣችው መግለጫ፣ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ ከኃላፊነት የመነሳት ጥያቄያቸውን ለሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዎ 14ኛ አቅርበው እንደነበር ጠቅሳ፣ ጥያቄያቸው በዛሬው ዕለት ተቀባይነት ማግኘቱን ገልጧል። ይህ ውሳኔ በቅድሥት መንበር ልዩ መልዕክተኛ ብፁዕ ካርዲናል ክላውዲዮ አማካይነት ይፋ መደረጉን ቤተክርስቲያኗ የጠቀሠች ሲኾን፣ በብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ ምትክ የቀድሞው የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ተስፋሥላሴ የአዲስ አበባ አገረ ስብከት አዲስ ሊቀ ጳጳስ ሆነው መሾማቸውን ገልጿል።

5፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ወደ ደብረ ማርቆስ ከተማ ቅድመ-ምረቃ በረራዎችን ከሰኔ 6 ጀምሮ እንደሚያደርግ አስታወቀ። አየር መንገዱ፣ ወደ ደብረ ማርቆስ መጓዝ የሚፈልጉ መንገደኞች የበረራ ቲኬቶችን በሁሉም የቲኬት መሸጫ ቢሮዎች ማግኘት እንደሚችሉ ዛሬ ባሠራጨው መረጃ ላይ ገልጧል። ኾኖም አየር መንገዱ ወደ ደብረ ማርቆስ በሳምንት ስንት በረራዎችን ለማድረግ እንዳሰበ አልገለጠም። አዲሱ የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ከሦስት ሳምንት በፊት አንድ የሙከራ በረራ ማስተናገዱ ይታወሳል።

6፤ የናይጄሪያ የቀድሞ የአቬሽን ሚንስትር ሃዲ ሲሪካ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር ከአገልግሎት ውጭ የሆነው የናይጄሪያ አየር መንገድ በድጋሚ የተቋቋመ ለማስመሰል በመሞከር ሥልጣናቸውን ያላግባብ ተጠቅመዋል በሚል ክስ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። የአቬሽን ሚንስትሩ፣ የናይጄሪያ አየር መንገድ በድጋሚ ወደ አገልግሎት የተመለሠ ለማስመሠል የሞከሩት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የኾነ አንድ አውሮፕላን ለሦስት ቀናት ተከራይተው በአውሮፕላኑ ላይ የናይጄሪያ አርማ በመለጠፍ አቡጃ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የምረቃ ስነ ሥርዓት በማድረግ እንደነበር ምስክሮች ለፍርድ ቤቱ መናገራቸውን የአገሪቱ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። ኾኖም አውሮፕላኑ ከስነ ሥርዓቱ በኋላ ወደ ባለቤቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መመለሱን ምስክሮቹ እንደገለጡም ዘገባዎቹ ጠቅሠዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለ30 ዓመታት ከአገልግሎት ውጭ የኾነውን የናይጄሪያ አየር መንገድን መልሶ በማቋቋምና የ49 በመቶ ድርሻ በመያዝ በድጋሚ ሥራ ለማስጀመር ከቀድሞው የአገሪቱ መንግሥት ጋር ስምምነት ተፈራርሞ የነበረ ሲኾን፣ የአሁኑ የአቡጃ መንግሥት ግን ስምምነቱ ግልጽነት የጎደለው እንደኾነ በመጥቀስ እንዳገደው አይዘነጋም።

7፤ ግብጽ፣ በናይል ውሃ ጉዳይ ዙሪያ በተፋሰሱ አገራት መካከል ትብብር እንዲጠናከር እና መግባባት እንዲሠፍን ጠየቀች። ግብጽ ይህን ጥሪ ያቀረበችው፣ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብድል ፈታህ አል-ሲሲ እና የዲሞክራሲያዊት ኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ፈሊክስ ቲሽስኬዴ ከትናንት ወዲያ ካይሮ ውስጥ በተወያዩበት ወቅት መኾኑን የግብጽ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። አል-ሲሲ፣ ኮንጎ የናይል ወንዝ ተፋሰስ አገራት ማናቸውንም የተናጥል ርምጃ መውሠድ እንደሌለባቸውና ይልቁንም በቀናኚነት መንፈስ በመግባባት ላይ የተመሠረተ ትብብር ማድረግ እንዳለባቸው አቋም መያዟን አድንቀዋል ተብሏል። የናይል ኢንሼቲቭ የሚንስትሮች ምክር ቤት፣ የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን ያልፈረሙትን የሱዳን እና ግብጽን ስጋቶች ለመፍታት ከአንድ ዓመት በፊት አንድ ኮሚቴ ማቋቋማቸው ይታወሳል። የትብብር ማዕቀፉን ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት አገራት አጽድቀውት ወደ ተግባር የገባ ሲኾን፣ የማዕቀፉ ፈራሚዎች ኬንያ እና ዲሞክራሲያዊት ኮንጎ ግን ገና አላጸደቁትም።

እንዲሁም

1. በሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ግጥሞች ላይ የተመሠረተው "እሳት ወይ አበባ" ተውኔት በድጋሚ ለመድረክ ሊበቃ ነው። ተውኔቱ በድጋሚ ነገ ቅዳሜ ሰኔ 6 2018 ዓ.ም በ11:30 በአዲስ አበባ ቴአትርና ባሕል አዳራሽ (ማዘጋጃ ) መቅረብ ይጀምራል።
2.ዋልያ መጻሕፍት “ዋልያ ዘመን” በተሰኘው አዲስ ዝግጅቱ ደራሲ ፍቅረማርቆስ ደስታን በእንግድነት ጋብዟል። መርሐግብሩ ነገ ቅዳሜ ሰኔ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ጀምሮ አራት ኪሎ በሚገኘው አዳራሹ ይካሄዳል። [ዋዜማ]
62👍11👌4👎2🙏1
ለቸኮለ! ቅዳሜ፣ ሰኔ 6፣ 2018 ዓ፣ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ አገር ዓቀፉ የምክክር ኮሚሽን፣ ከቀጣዩ ሐምሌ 8 ጀምሮ አገራዊው የምክክር ጉባዔ በአዲስ አበባ አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል እንደሚጀመር አስታወቀ። ለ15 ቀናት በሚቆየውና አራት ሺሕ ጉባኤተኞች በሚሳተፉበት ጉባኤ፣ በተለያዩ ክልሎች በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ የመጨረሻው ምክክር እንደሚደረግ ኮሚሽኑ ገልጧል። ጉባኤው ከሚመክርባቸው ጉዳዮች መካከል፣ የሕገመንግሥት ማሻሻያ፣ የማንነት ጥያቄ፣ የክልሎች ድንበር አከላለል፣ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ከብሄራዊ ሠንደቅ ዓላማ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ይገኙበታል። ኮሚሽኑ፣ 1 ሺሕ 234 የአገሪቱ ወረዳዎች በእስካሁኑ የምክር ሂደት ተሳታፊ እንደኾኑና ባጠቃላይ የአገሪቱ 93 በመቶ በሂደቱ እንደሸፈነ ጠቅሷል። ይህ የምክክር ሂደት ትግራይ ክልል ውስጥ እንዳልተካሄደና የክልሉ የፖለቲካ ኃይሎችም ኾኑ ሌሎች አካላት እንዳልተሳተፉ ይታወሳል።

2፤ ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ፈረንሳዊቷን የላ ክሮይክስ ጋዜጣ ዘገቢ አውግስቲን ፓሲሊን ከአገር ያባረሩበትን ውሳኔ እንዲቀይሩ ጠየቀ። ጋዜጠኛዋ ከአገር የተባረረችው፣ ወደ ትግራይ ተጉዛ ነዋሪዎች በድጋሚ ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ዘገባ መስራቷን ተከትሎ መኾኑን ተቋሙ ጠቅሷል። ውሳኔው ጋዜጠኛዋ ከትግራይ ኾና በመዘገቧ "የበቀል ርምጃ" ነው ያሉት በአፍሪካ የተቋሙ ዳይሬክተር አንጀል ኩዊንታል፣ ባለሥልጣናት የጋዜጠኛዋን የሥራና የመኖሪያ ፍቃድ ባስቸኳይ እንዲመልሱና ገለልተኛ ጋዜጠኞችን መቅጣት እንዲያቆሙ ጋዜጠኛዋ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ጋዜጠኛዋ ባስቸኳይ ከትግራይ እንድትመለስ ካዘዛት በኋላ፣ ከአገር እንደተባረረች የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ዘግቦ ነበር።

3፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ዛሬ ወደ ደብረ ማርቆስ ከተማ የቅድመ-ምረቃ በረራ ጀመረ። ኾኖም አየር መንገዱ ወደ ደብረ ማርቆስ በሳምንት ስንት በረራዎችን እንደሚያደርግ ዛሬ ባሠራጨው መረጃ ላይ አልገለጠም። አየር መንገዱ ወደ አዲሱ የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ የመጀመሪያውን የሙከራ በረራ ያደረገው ከሦስት ሳምንት በፊት ነበር።

4፤ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል፣ የኢትዮጵያ የደኅንነት ሃላፊ ሬድዋን ሁሴን እና የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አማካሪ ጌታቸው ረዳ አልጀዚራ ላይ ከትናንት ወዲያ ባወጡት መጣጥፍ በኤርትራ ላይ ላቀረቡት ውንጀላ ምላሽ ሠጡ። አኹን በኤርትራ ላይ ክስ የሚያቀርቡት አካላት፣ የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ከመፈረሙ ከወራት በፊት በጅቡቲ እና ሲሸልስ በሚስጢር ተገናኝተው በኤርትራ ላይ ወረራ ለመፈጸም አሲረው ነበር በማለት የማነ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሠፈሩት መልዕክት ወንጅለዋል። የማነ፣ በኤርትራ ላይ በጋራ ሊፈጸም ነበር ያሉትን የጋራ የወረራ ምክክር ጌታቸው ረዳ ካሁን ቀደም ተናግረውታል በማለት በምላሻቸው ላይ አስፍረዋል። ኾኖም ጌታቸው ይህን ሚስጢራዊ ውይይት አስመልክተው መቼ እና የት እንደተናገሩ የማነ አልገለጡም። ሬድዋን እና ጌታቸው፣ ሕወሃት በኤርትራ መንግሥት ድጋፍ በፌደራል መንግሥቱ ላይ በጥቂት ቀናት ውስጥ ጦርነት ሊከፍት ተዘጋጅቷል በማለት በመጣጥፋቸው ላይ ክስ አቅርበው ነበር።

5፤ ሶማሊላንድ ታይዋን ውስጥ የከፈተችውን የዲፕሎማቲክ ቢሮ በይፋ ሥራ አስጀመረች። ሐርጌሳ ለሶማሊላንድ ዲፕሎማሲ ቢሮዋ፣ አምባሳደር ማሃሙድ አደም ጃማን መሾሟን አስታውቃለች። ሶማሊያ እና ቻይና ሶማሊላንድ ከታይዋን ጋር የምታደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በጥብቅ ሲቃወሙ ቆይተዋል። አምባሳደር ጃማ፣ ሶማሊላንድ እና ታይዋን ለሶማሊያ እና ቻይና ተጽዕኖ እንደማይንበረከኩና ሶማሊላንድም ከማናቸውም አገር ጋር ግንኙነት የመመስረት መብት እንዳላት መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

6፤ ሌጋል አክሽን ዎርልድዋይድ እና አፍሪካን ሴንተር ፎር ጀስቲስ ኤንድ ፒስ ስተዲስ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ ኬንያ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዦች ላይ ምርመራ እንድትከፍት ለኬንያ ዓቃቤ ሕግ ማመልከቻ አስገቡ። አቤቱታ አቅራቢዎቹ ኬንያ ምርመራ እንድትጀምርባቸው የጠየቁት፣ "በጦር ወንጀል" እና "በሰብዓዊነት" ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች በሚጠረጠሩ 10 የቡድኑ አዛዦች ላይ መኾኑን ዘ ስታር ጋዜጣ ዘግቧል። ድርጅቶቹ አቤቱታውን ያቀረቡት፣ በሱዳኑ ጦርነት ጉዳት የደረሠባቸውን 12 ሱዳናዊያን ተጎጅዎች ወክለው መኾኑን ዘገባው አመልክቷል። ድርጅቶቹ፣ ምርመራ እንዲከፈትባቸው ከጠቀሷቸው ተጠርጣሪዎች መካከል አንዳንዶቹ የኬንያ ዜግነት እንዳገኙና ኬንያ ውስጥ በነጻነት እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል ተብሏል። በኬንያ ሕግ የአገሪቱ ዓቃቤ ሕግ በሌላ አገር ውስጥ የተፈጸሙ ዓለማቀፍ ወንጀሎችን የመመርመር ሥልጣን አለው።

እንዲሁም:-

1."አዲስ ኦፕን ኤር ሲኒማ" የተሰኘ ልዩ የመዝናኛ ዝግጅት፣ ነገ እሁድ ሰኔ 7 ቀን 2018 ዓ.ም በማርዮት ኤግዚኪውቲቭ አፓርትመንትስ ይካሄዳል። መግቢያው 999 ብር ነው።

2. ሞሰብ የሙዚቃ ማዕከል፣ ነገ እሁድ ሰኔ 7 ቀን 2018 ዓ.ም የሳልሳ የሙዚቃ ምሽት አዘጋጅቷል።በሙዚቃ ዝግጅቱ ላይ እሺ ሃቫና ቱ ጄነሬሽን ባንድ የቀጥታ የሙዚቃ ስራዎቹን ለታዳሚዎች ያቀርባል። [ዋዜማ]
48👍6👎3🙏3👏1👌1