Wazema Media / Radio
48.9K subscribers
191 photos
36 videos
7 files
935 links
Wazema Radio other contents are available either in our website/social media or FM radio stations in Ethiopia. www.wazemaradio.com
Download Telegram
February 1, is a critical day for Ethiopia and Somaliland with respect to their recent MoU. Pursuant to the MoU signed on January 1, 2024, detailed cooperation agreement was scheduled to be completed within one month. However, Ethiopia faces major diplomatic hurdles and overwhelming global condemnation. Read more tinyurl.com/e3nwuthh
ለቸኮለ ! ዓርብ ጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1-የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ነሐሴ 08 ቀን 2015 ዓ.ም በአማራ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት አራዝሟል።ምክር ቤቱ፣ የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዎን ጢሞቴዎስ በአዋጁ መራዘም አስፈላጊነት ላይ ያቀረቡትን ማብራሪያ ተከትሎ አባላቱ ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ በኹለት ተቃውሞ እና በሦሥት ድምፀ-ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ እንዲራዘም መደረጉን ገልጿል። ምክር ቤቱ፣ የአዋጁን መራዘም ተከትሎም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ የሥራ ዘመንንም በኹለት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል። ነገር ግን ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ; ምክር ቤቱ ለአዋጁ መራዘም በምክንያትነት ቀርቧል የተባለውን ማብራሪያ ይፋ አላደረገም።

2-በቢጂአይ ኢትዮጵያ ስር የሚገኙት አምስት የቢራ ፋብሪካዎች በጥሬ ዕቃ እጥረት ምክንያት ከፍተኛ የምርት መስተጓጎል እንደገጠማቸው ዋዜማ ከፋብሪካው ሠራተኞች ሰምታለች።
እንደ ገብስ፣ብቅል፣ጌሾ፣በቆሎ እና ሌሎችም ለምርት አስፈላጊ የሆኑ ኬሚካሎችን ለፋብሪካዎቹ ለማቅረብ እጅግ አዳጋች መሆኑን የፋብሪካው ሠራተኞች ለዋዜማ ተናግረዋል።
አብዛኞቹ የጥሬ ዕቃ ግብዓቶች የሚመጡት ከኦሮሚያ እና ከአማራ ክልሎች ቢሆንም ክልሎቹ ላይ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ጥሬ ዕቃዎችን ማቅረብ አለመቻሉን ጠቁመዋል።
ለአብነትም ከአሰላ ይመጣ የነበረው የገብስና የብቅል ግብዓት ባለፈው አንድ ወር አለመቅረቡን ሠራተኞቹ ለዋዜማ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ባሕርዳር ከሚገኘውና የበቆሎ ቅንጬ ከሚያመርተው ጨጨሆ ፋብሪካ ምርቱን ይቀበሉ እንደነበር በመግለጽ፣በአካባቢው ካለው የጸጥታ ሁኔታ ጋር በተገናኝ ምርቱን ማቅረብ አዳጋች መሆኑን አስረድተዋል። ጌሾ እና ሌሎች አስፈላጊ ኬሚካሎችም ከአሜሪካና ከጀርመን ይገቡ ነበር ያሉት ሠራተኞቹ፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ መቆሙን ተናግረዋል።
አልፎ አልፎም ቢሆን በከፍተኛ የጭነት ዋጋና በሌሎች ተለዋዋጭ መንገዶች ጥሬ እቃዎቹን ለማቅረብ የተሞከረ ሲሆን፣ይህም ከፍተኛ ኪሳራ ማስከተሉን ጠቁመዋል።ይህን ለማካካስ በቢራ ዋጋ ላይ ጭማሪ ለማድረግ ቢወሰንም፣ በመንግሥት ክልከላ ምክንያት ጭማሪው እስካሁን አለመደረጉን ዋዜማ ከሠራተኞቹ ሰምታለች።

3-የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም እና ይኽም በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚኖሩት እንድምታዎች ኮሚሽኑን እጅጉን እንደሚያሳስበው ገልጸዋል። ዳንኤል፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከማራዘሙ ሰዓታት ቀደም ብሎ በ”ኤክስ” ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ መንግሥት እና ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊነት; ሕጋዊነት እና ተመጣጣኝነት በቅጡ ሊመለከቱት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
የአዋጁ መራዘም; በሰብዓዊ ጉዳቶች፣ ሰብዓዊ ቀውስ እንዲባባስ እንዲሁም ሰዎች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለረዥም ጊዜ በእስር እንዲቆዩ ማድረግ የሚሉት በኮሚሽነሩ የተጠቀሱ የአዋጁ መራዘም አሉታዊ እንድምታዎች ናቸው። ዳንኤል፣ ችግሮችን ለመፍታት ውይይት ቁልፍ መንገድ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

4-የምሥራቅ ወለጋ ዞን መቀመጫ በሆነችው ነቀምት ከተማ የእጅ ቦንቦች በተደጋጋሚ እየተጣሉ እንደሆነና ይህም ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረባቸው ነዋሪዎች ለዋዜማ ተናግረዋል።
ባልተለመደ መልኩ ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚጣለው የእጅ ቦንብ፣የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጠርቶታል ከተባለው አድማ ጋር የተያያዘ ሳይሆን እንዳልቀረ ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል። በሌላ በኩል ማክሰኞ ጥር 21/2016 ዓ.ም. የተጠራውን አድማ ጥሳችኋል በማለት በከተማዋ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሁለት ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች በታጣቂ ቡድኑ እንደተቃጠሉም አስረድተዋል። በከተማዋ መደበኛ እንቅስቃሴ ከተቋረጠ ዛሬ አምስተኛ ቀኑን መያዙን የገለጹት ነዋሪዎች; ምሽት ላይ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ቡድኑ አባላት መካከል ከፍተኛ የሆነ የተኩስ ልውውጥ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ከሰኞ ጥር 20/2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ባንኮች፣ትምሕርት ቤቶች፣የንግድ ቤቶች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በአመዛኙ ዝግ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በመንግሥት ኃይሎች በኩል ተቋማቱን እንዲከፍቱ ከፍተኛ ጫና እየተደረገ መሆኑን ዋዜማ ከነዋሪዎቹ ካሰባሰበችው መረጃ መረዳት ችላለች።

5-የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለማርያም እና የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የኢትዮጵያ ተወካይ ራሚዝ አላክባሮቭ በጋራ ባወጡት መግለጫ; በኢትዮጵያ በቀጣዮች ጥቂት ወራት ውስጥ አስከፊ የምግብ እጥረት የሚያጋጥማቸው ዜጎች ቁጥር እንደሚጨምር ገልጸዋል። በተለይም ከሰኔ መጨረሽ እስከ ነሐሴ ባሉት ጊዜያት ከፍተኛ የምግብ እጥረት የሚያጋጥማቸው ዜጎች ቁጥር 10 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ጠቁመዋል።
የኤልኒኖ የአየር ንብረት ክስተትን ተከትሎ በተለይ ለኹለት ዓመታት በተከሰተው ጦርነት የተነሳ እስከ አኹን ሙሉ ለሙሉ ማገገም ባልቻሉት እና በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙት ተጋላጭ ማኅበረሰቦች ዘንድ ችግሩ እንደሚያይል ተጠቅሷል።መግለጫው፣ ቀውሱ እንዳይባባስ ለመከላከል ያለው ዕድል ጠባብ መሆኑን በመጥቀስ፣ ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድም አሳስቧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ቅዳሜ ጥር 25/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን፣ አገሪቱ ለአውሮፓ ገበያ የምትሸጠው የቡና ምርት አውሮፓ ኅብረት ያወጣውን አዲስ የደን ጭፍጨፋ ደንብ ያከበረ መኾኑን ለማረጋገጥ ኮሚቴ ማቋቋሙን ሪፖርተር ዘግቧል። ኮሚቴው፣ ከባለሥልጣኑ፣ ከቡና አምራችና ላኪ ማኅበራት፣ ከቡና አምራች ገበሬዎች፣ ከኢምባሲዎችና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች የተውጣጡ አባላትን እንዳካተተ ዘገባው ጠቅሷል። አውሮፓ ኅብረት፣ አባል አገራቱ ከውጭ የሚገዙት ቡና ደኖችን በመጨፍጨፍ የተመረተ እንዳይኾን ለማረጋገጥ ያወጣው ደንብ፣ በተያዘው የአውሮፓዊያን ዓመት ተግባራዊ መኾን ይጀምራል። ኢትዮጵያ፣ ደንቡ በኢትዮጵያ የሚኖረው ተፈጻሚነት እንዲራዘም ጠይቃለች ተብሏል። ኢትዮጵያ ባለፈው ሩብ በጀት ዓመት 117 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ አቅርባ 571 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች።

2፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ፣ መንግሥት በአማራ ክልል ያወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማራዘሙ "በእጅጉ እንዳሳሰበው" ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጱ አስታውቋል። አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ባስተላለፉት በዚኹ መልዕክት፣ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የቀጠሉትን ጨምሮ የአገሪቱን ውስብስብ ፖለቲካዊና የጸጥታ ችግሮች መፍታት የሚቻለው በንግግር መኾኑን ገልጸዋል። ችግሮችን በንግግር ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት፣ አሜሪካ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መኾኗንም አምባሳደሩ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

3፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፣ የብሪታኒያ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንድሪው ሚቸል ከመሩት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ጋር ትናንት መቀሌ ውስጥ መወያየታቸውን በ"ኤክስ" (የቀድሞው ትዊተር) ገጻቸው አስታውቀዋል። ውይይቱ፣ በፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት አተገባበር ተግዳሮቶችና የጦርነቱን ተፈናቃዮች በመመለስ ዙሪያ እንደኾነ ጌታቸው ገልጸዋል።
ሚቸል፣ የኤርትራ ጦር ከትግራይ እንዲወጣ መጠየቃቸውን የዘገበው ደሞ የክልሉ ቴሌቪዥን ነው። ልዑካን ቡድኑ፣ የመቀሌውን አይደር ሪፈራል ሆስፒታል እንዲኹም ከመቀሌ 37 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አጉላ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮችን እንደጎበኘ ዘገባው አመልክቷል።

4፤ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ድንበር አካባቢ በሚገኙ ኹለት ወረዳዎች እንስሳትን እየዘረፉና አርሶ አደሮችን አፍነው እየወሰዱ ስለመኾኑ ከአንድ የተመድ የዳሰሳ ሰነድ መመልከቱን ጠቅሶ አሶሴትድ ፕሬስ ዘግቧል። ጥር 13 ቀን፣ ስምንት የትግራይ ከብት ጠባቂዎች በኤርትራ ወታደሮች ታፍነው እንደተወሰዱ ዘገባው ጠቅሷል። ኅዳር 26 ደሞ ስድስት ሰዎችንና በርካታ ግመሎችን ጨምሮ 56 የቤት እንስሳትን መወሰዳቸውን ሰነዱ መጥቀሱን ዘገባው አመልክቷል። የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገ/መስቀል ግን፣ ውንጀላውን "ሐሰት" በማለት ትናንት ማስተባበላቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

5፤ አሜሪካ፣ ቶም ፓሪዮሎን ለሱዳን ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ ልትሾም መኾኗን ሮይተርስ ዘግቧል። ፔሪዮሎ፣ ቀደም ሲል ዲሞክራቲክ ፓርቲውን በመወከል የኮንግሬስ አባልና በታላላቅ ሐይቆች አገራት የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ የነበሩ ናቸው። ከፔሪዮሎ በፊት፣ ባኸኑ ወቅት በሱዳን የአሜሪካ አምባሳደር የኾኑት ጆን ጎድፍሬይ እና የቀድሞዋ የአሜሪካ ዓለማቀፍ ተራድዖ ድርጅት ሃላፊ ጌይል ስሚዝ ታጭተው ነበር ተብሏል። የአሜሪካ ኮንግሬስ አባላት፣ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለሱዳኑ ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄ እንዲገኝ የሚያግዙ ልዩ መልዕክተኛ እንዲሾሙ ሲወተውቱ መቆየታቸው ይታወሳል። በተያያዘ፣ አምባሳደር ጆን ጎድፍሬይ በቅርቡ ከሃላፊነት እንደሚለቁ ዘገባው ጠቅሷል።

6፤ አፍሪካ ኅብረት በተያዘው አውሮፓዊያን ዓመት መገባደጃ ታኅሳስ ላይ በሰላም ሽግግር ተልዕኮው ሥር በሱማሊያ የተሠማሩ ወታደሮቹን ሙሉ በሙሉ እንደሚያስወጣ በድጋሚ አረጋግጧል። የኅብረቱ የፖለቲካ፣ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ይህን ያረጋገጠው፣ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በአገሪቱ ተገኝቶ የጸጥታ ኹኔታውን ከገመገመ በኋላ ነው። ልዑካን ቡድኑ፣ በጉብኝቱና ከኅብረቱ ተልዕኮ መውጣት በኋላ በሱማሊያ ሊኖር ስለሚችለው የጸጥታ ኹኔታ፣ ለኅብረቱ የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤትና ለተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ሪፖርት ያቀርባል። የኅብረቱ ተልዕኮ፣ በሦስተኛው ዙር እስከ ሰኔ ድረስ አራት ሺህ ወታደሮችን ለማስወጣት ካኹኑ ዝግጅቱን ጀምሯል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ሰኞ ጥር 27/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በርካታ የፌደራልና ክልል መንግሥታት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ትናንት በአማራ ክልል 15 ከተሞች ከሕዝቡ ጋር ውይይት አድርገዋል። በባሕርዳር፣ ጎንደር፣ ፍኖተሰላም፣ ደብረታቦር፣ ሰቆጣና ሌሎች ከተሞች የተካሄዱትን ውይይቶች ከመሩት ባለሥልጣናት መካከል፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሺመልስ አብዲሳ፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ኡመር፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ተስፋይ በልጅጌ፣ የገንዘብ ሚንስትር አሕመድ ሽዴና የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይገኙበታል። ውይይቶቹ "ሕብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ኹለንተናዊ ብልጽግና" በሚል ርዕስ የተካሄዱት፣ የክልሉን ሕዝብ ችግሮች ለመረዳትና የመፍትሄ ሃሳቦችን ለመስማት እንደኾነ ተገልጧል። ባለሥልጣናቱ፣ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ በነፍጥ ማሳካት እንደማይቻል በውይይቶቹ ላይ አጽንዖት ሰጥተዋል።

2፤ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ሺፈራው ተ/ማርያም ድርቅን ለፖለቲካዊ ዓላማ መጠቀም "ተገቢ ያልኾነ" እና "ፍጹም ተቀባይነት የሌለው" ድርጊት ነው በማለት መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል። የዓለማቀፍ ተቋማት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርቡ ያካሄዱት የዳሰሳ ጥናት፣ በኢትዮጵያ ባኹኑ ወቅት የተከሰተው ድርቅ እንጂ ርሃብ እንዳልኾነ ማረጋገጡን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል ተብሏል። ኮሚሽነር ሺፈራው፣ ባኹኑ ወቅት በአገሪቱ 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊ እንደኾኑ መግለጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል። መንግሥት ባለፉት ስድስት ወራት፣ በ11 ቢሊዮን ብር ወጪ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል የዕርዳታ እህል ለተረጂዎች ማከፋፈሉን እንደጠቀሱ ዘገባው አመልክቷል።

3፤ የቡናና ሻይ ልማት ባለሥልጣን ክፍያ ያልፈጸሙ ኹለት ዓለማቀፍ ኩባንያዎችን ስለማገዱ መስማቱን ካፒታል ጋዜጣ ዘግቧል። አገሪቱን የውጭ ምንዛሬ አሳጥተዋታል ተብለው እገዳ የተጣለባቸው ኹለት ዓለማቀፍ ኩባንያዎች፣ ከኢትዮጵያዊያን ላኪዎች ቡና ገዝተው ለቻይና ገበያ ሲያቀርቡ የነበሩ እንደኾኑ ዘገባው ጠቅሷል። ባለሥልጣኑ ኩባንያዎቹ የቡና ሽያጭ ውል እንዳይፈጽሙ ለኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር እንዳያሳወቀና ብሄራዊ ባንክም አንዳችም ኮንትራት እንዳይፈጽሙ እንዲያግዳቸው እንዳሳሰበ ዘገባው አመልክቷል።

4፤ አፍሪካ ኅብረት ለሱዳን ያቋቋመው ከፍተኛ ቡድን ሥራውን በይፋ መጀመሩን የኅብረቱ ኮሚሽን አስታውቋል። ቡድኑ፣ አፍሪካ ኅብረት በሱዳን ሰላም ለማስፈን የቀረጸውን ስትራቴጂ ተግባራዊ ላይ የማዋልና ጦርነቱ ቆሞ ኹሉን አካታችና ዘላቂ የሰላም ሂደት እንዲጀመር ኹኔታዎችን የማመቻቸት ኃላፊነት አለበት። ሦስት አባላት ያሉትን የኅብረቱን ከፍተኛ ቡድን የሚመሩት፣ በአፍሪካ የኅብረቱ የግጭት ማቆም ከፍተኛ ተወካይ ሞሃመድ ቻምባስ ናቸው። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሰኞ ጥር 27/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ትላንት እና ዛሬ በመቀሌ ከተማ ሊያደርገው የነበረውን ጠቅላላ ጉባዔ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መከልከሉን ፓርቲው ለዋዜማ ገልጧል። የፓርቲው መስራች እና ሊቀመንበር አረጋዊ በርሄ ለዋዜማ እንደተናገሩት፣ ፓርቲያቸው ለሁለት ቀናት ሊያደርገው ያሰበው ጠቅላላ ጉባዔ መስተጓጎሉን ተናግረው፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ግን የጉባዔውን መካሄድ አልከለከልኩም በማለት እያስተባበለ ይገኛል ብለዋል። ፓርቲያቸው ጉዳዩን እየተከታተለ እንደኾነ የገለጹት አረጋዊ፣ ፓርቲው በቀጣዮቹ ሁለት እና ሦስት ቀናት በጉዳዩ ላይ አንድ እልባት ላይ እንደሚደርስ ተናግረዋል። የጉባዔው ዓላማ፣ በክልሉ ያለው የመልካም አሥተዳደር እጦትና የምግብ እጥረት ለፖለቲካ ፍጆታ መዋሉ ንጹሃንን እየጎዳ እንደሆነ ለመግለጽ ያለመ እንደኾነ ዋዜማ ተረድታለች።

2፤ የብሪታንያ የዓለማቀፍ ልማት ሚንስትር ደዔታ አንድሪው ሚቸል፣ በኢትዮጵያ የተከሰተው ከፍተኛ የምግብ እጥረት ከባድ የሰብዓዊ ቀውስ ስጋት ፈጥሯል ማለታቸውን ፋይናንሻል ታይምስ ዘግቧል። ሚቸል፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ሦስት ሚሊዮን ሰዎች ከፍተኛ የርሃብ አደጋ እንዳንዣበበባቸው የገለጡት፣ ባለፈው ሳምንት በትግራይ ጉብኝት አድርገው ከተመለሱ በኋላ በሰጡት ቃል ነው። የብሪታንያ መንግሥት ነፍሰ ጡር እናቶችን ጨምሮ ለሦስት ሚሊዮን ተረጅዎች የተመጣጠነ ምግብ እና መድሃኒት ለማቅረብ የሚውል 100 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡን ሚቸል መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ሚቸል፣ በኢትዮጵያ ያንዣበበው የርሃብ አደጋ በዩክሬን፣ ጋዛ እና ሱዳን ባሉ ሰብዓዊ ቀውሶች ተውጧል ማለታቸውንም ጋዜጣው አውስቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በሰሜኑ ክፍል ርሃብ እንዳልተከሰተ በመግለጽ፣ ድርቁን ለፖለቲካዊ ዓላማ የሚያውሉ አካላት አሉ በማለት ይከሳል።

3፤ ተቃዋሚው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከዓላማው በተቃራኒ ቆመዋል በማለት ያሰናበታቸው ስድስት የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮቹ በስሙ ለሚያደርጉት ሕገወጥ እንቅስቃሴ ኃላፊነት እንደማይወስድ አስታውቋል። ስድስቱን የቀድሞ አመራሮች ከሦስት ዓመታት በፊት ማገዱን የጠቀሰው ኦነግ፣ ይሁንና አመራሮቹ በዚያው ዓመት የፓርቲውን ዋና ጽሕፈት ቤት የመቆጣጠርና አመራሮችን በሌላ የመተካት ሙከራ ማድረጋቸውን ገልጧል። የቀድሞዎቹ አመራሮች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በኅብረተሰቡ ዘንድ ግርታን መፍጠሩንና ማናቸውም እንቅስቃሴያቸው ግን ፓርቲውን እንደማይወክል ኦነግ አስታውቋል።
ግለሰቦቹን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በተደጋጋሚ በቃል እንደነገራቸው የገለጠው ፓርቲው፣ ከእንቅስቃሴያቸው አልቆጠብ ሲሉ ግን መግለጫ ለማውጣት መገደዱን ግንባሩ ገልጿል። ግለሰቦቹ ጉዳያቸው በፓርቲው ሕግና ሥነምግባር ኮሚቴ እየታየ እንደኾነነ ኦነግ ጠቁሟል። ከስድስቱ ግለሰቦች መካከል፣ ቀጀላ መርዳሳ እና አራርሳ ቢቂላ ይገኙበታል።

4፤ ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ በባሕርዳር ከተማ በሚካሄደው የጣና ፎረም ስብሰባ ዝግጅት ዙሪያ የፎረሙ ሴክሬታሪያት ከአማራ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ጋር ዛሬ መወያየቱን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል። የውይይቱ ትኩረት፣ በጉባዔው ዝግጅትና በጉባዔው ዝግጅት በሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት መካከል የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ዙሪያ እንደኾነ ሚንስቴሩ ገልጧል። ከሚያዝያ 11 እስከ 13 በአፍሪካ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚመክረው ዓመታዊው የጣና ፎረም ስብሰባ ዘንድሮ ሊካሄድ የነበረው ባለፈው ጥቅምት ወር ነበር። ኾኖም የስብሰባው አዘጋጅ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም "ያልተጠበቁ ኹኔታዎች" እንዳጋጠሙት በመግለጽ፣ ስብሰባውን ወደ ሚያዝያ ማዘወሩን መግለጡ ይታወሳል።

5፤ የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በብሪታንያ መንግሥት ላይ ያለውን ቅሬታ ለመግለጽ በአሥመራ የብሪታንያ ጉዳይ አስፈጻሚን መጥራቱን የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገ/መስቀል በ"ኤክስ" ገጻቸው አስታውቀዋል። የብሪታንያ ጉዳይ አስፈጻሚ ማብራሪያ እንዲሰጡና የአሥመራን ቅሬታ ለመንግሥታቸው እንዲያስተላልፉ የተጠሩት፣ የብሪታንያ ባለሥልጣናት በኤርትራ ላይ የ"ሐሰት" ውንጀላ" ማቅረብ በመቀጠላቸው እንደኾነ የማነ ገልጸዋል። ጉዳይ አስፈጻሚው የተጠሩት፣ የብሪታንያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደዔታ አንድሪው ሚቸል ባለፈው ሳምንት በትግራይ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ስለመጠየቃቸው በተዘገበ ማግስት ነው።

6፤ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የሱዳን ሲቪል ኃይሎች ስብስብ እና የሱዳኑ ወታደራዊ መሪዎች ንግግር እንዲጀምሩ ለማስተባበር ቃል መግባታቸውን የሱዳን ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ፕሬዝዳንት ኪር ይህን ቃል የገቡት፣ የሲቪል ኃይሎቹ ስብስብ ልዑካን ቡድን ባለፈው ሳምንት ዓርብ ወደ ጁባ ተጉዞ ጥያቄውን ካቀረበላቸው በኋላ ነው። የስብስቡ ልዑካን ቡድን፣ ጦርነቱን ለማስቆም በሚያስችል ፍኖተ ካርታ ዙሪያ ከጀኔራል ቡርሃን ጋር መምከር እንደሚፈልግ ለፕሬዝዳንቱ ገልጦላቸዋል ተብሏል። የቀድሞው የሱዳን ሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ የሚመሩት ስብስቡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ እንደተመሠረተ ይታወሳል።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ2067 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ3308 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 68 ብር ከ4763 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ8458 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ61 ከ1585 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ3817 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
Audio/Video ⬇️

https://youtu.be/dvuUP4LAEbw?si=VsUshOb5SdZHk39o
ለቸኮለ ማለዳ! ማክሰኞ ጥር 28/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በሱማሊያ ዕሁድ ምሽት ባልታወቁ ታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ ስድስት ኢትዮጵያዊያን መገደላቸውን የሱማሊያ ዜና ምንጮች የዓይን እማኞችን ጠቅሰው ዘግበዋል። ዘገባዎቹ፣ በጥቃቱ ሌሎች ስድስት ኢትዮጵያዊያን እንደቆሰሉ አመልክተዋል። ጥቃቱ የተፈጸመው፣ በኢትዮጵያ እና ሱማሊያ ድንበር በለድ-ሃዎ ከተማ በኢትዮጵያዊዋኑ መኖሪያ ቤተ ውስጥ እንደኾነ ተገልጧል።

2፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፌደራል መንግሥቱ ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት በአዋዛጋቢ አካባቢዎች "ሕዝበ ውሳኔ" እንዲካሄድ ከትግራይና አማራ ክልሎች አመራሮች ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር በማለት ያወጣውን መግለጫ ውድቅ አደርጎታል። የቃለ አቀባዩ መግለጫ “ተቀባይነት የለውም” ያለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ መግለጫው ከፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት መንፈስ ጋር የሚጋጭ መኾኑን ገልጧል። አንዳንድ "ትክክለኛ ተፈናቃዮች ወደቀያቸው ተመልሰዋል" መባሉንም “አደገኛ አባባል” በማለት፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ውድቅ አድርጎታል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ በኃይል በተያዙ አካባቢዎች ሕገወጥ አስተዳዳሪዎች ከቦታቸው ሳይነሱ፣ እንደዚህ ዓይነት መግለጫዎች መስጠት ፌደራል መንግሥቱ ከመፍትሄው ይልቅ "የችግሩ አካል" መኾን የሚፈልግ አስመስሎበታል በማለትም ተችቷል። የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚቃወሙ ወገኖች “የተሳሳተ" አቋማቸውን እንዲገፉበት የሚያበረታቱ መግለጫዎች አደገኛ መዘዝ ያስከትላሉ በማለትም ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስጠንቅቋል።

3፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ዛሬ በ14ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የምክር ቤቱ አባላት ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ይሰጣሉ። ዐቢይ በምክር ቤቱ ተገኝተው ምላሽና ማብራሪያ የሚሰጡት፣ ምክር ቤቱ በአማራ ክልል የታወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለአራት ወራት ባራዘመ ማግስት ነው። ዐቢይ፣ ከሶማሊላንዱ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ጋር ከአንድ ወር በፊት በተፈራረሙት አወዛጋቢ የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ዙሪያ እስካኹን ለሕዝብ ይፋዊ ማብራሪያ እንዳልሰጡ ይታወቃል።

4፤ ንግድ ሚንስቴር የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር እየተሸጠበት በሚገኘው ዋጋ እንደሚቀጥል አስታውቋል። በተያዘው ወር ያለው የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ፣ ቤንዚን በሊትር 77 ብር ከ65 ሳንቲም ሲኾን፣ ኬሮሲን በሊትር 79 ብር ከ75 ሳንቲም ነው። በተመሳሳይ፣ ነጭ ናፍጣ በሊትር 79 ብር ከ75 ሳንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ በሊትር 61 ብር ከ16 ሳንቲም እንዲኹም ቀላል ጥቁር ናፍጣ በሊትር 62 ብር ከ36 ሳንቲም በመሸጥ ላይ ይገኛል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ማክሰኞ ጥር 28/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የመንግሥት የጸጥታ ሃይሎች ዛሬ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሃፊና የኒውዮርክና አካባቢው አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጴጥሮስ ቦሌ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ እንዳይገቡ መከልከላቸውን የቤተክርስቲያኗ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ አስታውቋል። ሕዝብ ግንኙነት መምሪያው፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ሊቀ ጳጳሱ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሃፊ መኾናቸውን ከግምት በማስገባት ወደ አገር እንዲገቡ እንዲፈቅዱ ቤተክርስቲያኗ መጠየቋን ገልጧል። ይህንኑ ተከትሎ ሊቀ ጳጳሱ በምን ኹኔታ ላይ እንዳሉ፣ ቤተክርስቲያኗ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ተጨማሪ መረጃ አልሰጠችም። አቡነ ጴጥሮስ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለቤተክርስቲያኗ ሐዋሪያዊ ተልዕኮ ወደ ሰሜን አሜሪካ መጓዛቸውን ሲኖዶሱ ገልጦ እንደነበር ይታወሳል።

2፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከአማራ ክልል ለሚነሳው የሕገመንግሥት ማሻሻያ ጥያቄ በአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አማካኝነት ምላሽ ለመስጠት መንግሥት እየሠራ መኾኑን ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል። በአማራ ክልል በተደረጉ ውይይቶች በዋናነት የሕገመንግሥት ማሻሻያ፣ የወሰንና የልማት ጥያቄዎች መነሳታቸውን የጠቀሱት ዐቢይ፣ መንግሥት የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎችን በውይይትና ዘላቂ ሰላምን በሚያረጋግጥ አኳኋን እንዲፈቱ ይፈልጋል ብለዋል። ዐቢይ፣ የትግራይና የአማራ ምሁራን ለአስተዳደር ወሰን ውዝግቡ የተሻለ ሰላማዊ መፍትሄ ካመጡ፣ ፌደራል መንግሥቱ ለመተባበር ዝግጁ እንደኾነም ገልጸዋል። ዐቢይ ከወራት በፊት ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ፣ በአወዛጋቢ ግዛቶች ሕዝበ ውሳኔ ማካሄድ የተሻለ አማራጭ እንደኾነ ገልጠው እንደነበር ይታወሳል። የኦሮሚያ፣ ሶማሌና አፋር ክልሎችም፣ የሕገመንግሥት ጥያቄ እንደሚያነሱ ዐቢይ ጠቅሰዋል።

3፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እስካኹን በአገሪቱ በርሃብ የሞተ ሰው አለመኖሩን ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ላይ ተናግረዋል። ዐቢይ፣ በርሃብ ላይ ሌሎች ችግሮች ሲጨመሩ ሰዎች መቋቋም አቅቷቸው ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ግን በማብራሪያቸው ገልጸዋል። መንግሥት ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለተረጂዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ 15 ቢሊዮን ብር ማውጣቱን የገለጡት ዐቢይ፣ መንግሥት ድርቁን ችላ ብሎታል የሚባለው ስህተት ነው ብለዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ በትግራይ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች እንዲኹም በምስራቅ ኢትዮጵያ ድርቅ መኖሩን በመጥቀስ፣ በኢትዮጵያ በርሃብ የሚሞት ሰው ከኾነ መንግሥት የልማት ፕሮጀክቶችን አጥፎ ሕይወት ለመታደግ እንደሚሠራ ገለጸዋል።

4፤ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚንስቴር የግሉ ዘርፍ በደረቅ ወደብ ልማት እንዲሰማራ የሚፈቅድ ረቂቅ መመሪያ ማዘጋጀቱን ካፒታል ዘግቧል። የጭነት አስተላላፊዎች ግን ረቂቅ መመሪያው እውነታውን ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው የሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ረቂቅ መመሪያው ደረቅ ወደቦች በሚሰጡት አገልግሎት ልክ፣ ለግል ኩባንያዎች ሊኖራቸው የሚገባውን የመሬት ስፋት ዘርዝሮ አስቀምጧል ተብሏል። የአገር ውስጥ ወይም የውጭ ባለሃብቶች እንደሚሰጡት አገልግሎት ፍቃድ ለማግኘት፣ በራሳቸው ይዞታ ሥር የሚገኝ ከ2 እስከ 80 ሄክታር መሬት ለፈቃድ ማቅረብ እንዳለባቸው በረቂቁ ላይ እንደተገለጠ ዘገባው ጠቅሷል። ኾኖም ከትልላቅ ባለሃብቶች ወይም የውጭ አልሚዎች በስተቀር፣ በመመሪያው መሠረት በጭነት ማስተላለፍ ሥራ የተሰማሩ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች በዘርፉ ለመሳተፍ ይከብዳቸዋል የሚል ቅሬታ መቅረቡን ዜና ምንጩ አውስቷል። እስካኹን ባለው አሠራር፣ ደረቅ ወደቦችን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ድርጅት ነው።

5፤ እናት ፓርቲ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ2015 ዓ፣ም ጀምሮ በጣለው የጣሪያና ግድግዳ ወይም የንብረት ገቢ ግብር ላይ ለመሠረተው ክስ፣ ፍርድ ቤት ለየካቲት 20 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን አስታውቋል። የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ፣ የክስ ሂደቱ በመገናኛ ብዙሃን መዘገቡ የሕዝብን ጥቅም ይነካል በማለት ፍርድ ቤቱ በመገናኛ ብዙኀን ላይ እገዳ እንዲጥል መጠየቁን ፓርቲው ጠቅሷል። ቢሮው ባቀረበው የክስ መቃወሚያ ላይ ትናንት የቃል ክርክር መካሄዱን ፓርቲው ገልጧል። ኾኖም ፓርቲው ቢሮው የክርክሩ ሂደት በመገናኛ ብዙኀን እንዳይዘገብ ፍርድ ቤቱ እግድ እንዲጥል ባቀረበው አቤቱታ ላይ መቃወሚያ ካለው በጽሑፍ እንዲያቀርብ መታዘዙንና ፍርድ ቤቱም በዚሁ ጉዳይ ላይ የካቲት 4 ብይን እንደሚሰጥ መግለጡን ፓርቲው ጨምሮ አመልክቷል።

6፤ ፌደራል ፖሊስ፣ ኮኬይን የተባለውን አደገኛ ዕፅ ውጠው የተገኙ የብራዚልና የኢንዶኔዥያ ዜግነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች ቦሌ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ዛሬ አስታውቋል። የብራዚል ዜግነት ካላት አንዲት ተጠርጣሪ መንገደኛ በእንክብል መልክ የተዘጋጀ 2 ነጥብ 9 ኪሎ ግራም ኮኬይን እንደተያዘ የገለጠው ፌደራል ፖሊስ፣ ሰባት ፍሬ ኮኬይን ደሞ ከሆዷ መውጣቱን ጠቅሷል። በተመሳሳይ የኢንዶኔዥያ ዜግነት ያለው አንድ ተጠርጣሪ፣ በሆዱ ከዋጠው የኮኬን እንክብሎች በተጨማሪ 6 ነጥብ 7 ኪሎ ግራም ኮኬይን በሻንጣ ውስጥ ሰፍቶ ለማለፍ ሲሞክር በቁጥጥር ሥር ውሏል ተብሏል። ቦሌ ላይ በኤክስሬይ ምርመራ የታያዙት ኹለቱም ተጠርጣሪዎች፣ ከብራዚል እና ኢንዶኔዥያ የተነሱ እንደኾኑ ተገልጧል።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ2236 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ3481 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 67 ብር ከ4605 ሳንቲም እና መሸጫው 68 ብር ከ8097 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ60 ከ4347 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ61 ብር ከ6434 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ረቡዕ ጥር 29/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ኢሰመጉ፣ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን መርዓዊ ከተማ በመንግሥት ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ጥር 20 ቀን የተካሄደውን ግጭት ተከትሎ የመንግሥት ጸጥታ ሃይሎች በበርካታ ንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ፣ የአካል ጉዳት ማድረስና ድብደባ ፈጽመዋል በማለት ከሷል። ጸጥታ ሃይሎች በከተማዋ የቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ በግጭቱ ምንም ዓይነት ተሳትፎ የሌላቸውን በርካታ ሰዎች መግደላቸውን ኢሰመጉ ዓይን እማኞችን ጠቅሶ ገልጧል። ኢሰመጉ፣ በግጭቱ ወቅት በነበረው የተኩስ ልውውጥና በጸጥታ ኃይሎች ግድያ፣ ኹለት ሴቶችንና አንድ የ17 ዓመት ታዳጊን ጨምሮ በጠቅላላው ከ80 በላይ ንጹሃን መገደላቸውን ጠቅሷል። ጸጥታ ኃይሎች በርካታ ወንዶችን ከቤታቸው ካወጡ በኋላ በአደባባይ እንደረሸኗቸውና በማግስቱ በጅምላ መቃብር እንደተቀበሩ የዓይን እማኞች መናገራቸውን የገለጠው ኢሰመጉ፣ ድርጊቱን ተከትሎ ነዋሪዎች ከከተማዋ እየሸሹ ነው ብሏል።

2፤ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በመንግሥት ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭቶች መቀጠላቸውን ዋዜማ ከምንጮች ሰምታለች። በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማ ዙሪያ ትናንት ግጭት መካሄዱን ምንጮች ተናግረዋል። በደቡብ ወሎ፣ በደቡብ ጎንደርና በሰሜን ጎንደር ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎችም ግጭቶች መካሄዳቸው ተሰምቷል። ግጭቶች መቀጠላቸው የተሰማው፣ የፌደራልና የተለያዩ ክልሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት በክልሉ 15 ከተሞች በክልሉ ሕዝብ ጥያቄዎችና በመፍትሄ ሃሳቦች ዙሪያ ከሕዝቡ ጋር ውይይት ማድረጋቸው በተገለጠ ማግስት ነው።

3፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ በኢትዮጵያ የርሃብ አደጋ ላንዣበበባቸው ሦስት ሚሊዮን ሰዎች በቅርቡ የምግብ ዕርዳታ ሥርጭት ለመጀመር ጥረቱን ማጠናከሩን አስታውቋል። ኹለት ሚሊዮኑ ተረጂዎች በትግራይ ክልል እንደሚገኙ ድርጅቱ ገልጧል። ድርጅቱ፣ እስከ ሰኔ ወር የምግብ ዕርዳታ ጉድለቱን ለመሙላት ተጨማሪ 142 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው አመልክቷል። ተጨማሪውን ገንዘብ ካላገኘኹ ሚያዝያ ወር በአገሪቱ ለተጠለሉ ስደተኞች የማቀርበውን የምግብ እርዳታ ለማቋረጥ እገደዳለኹ ያለው ድርጅቱ፣ ከሱዳን 200 ሺህ ተጨማሪ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ ይችላሉ ብሏል። ድርጅቱ፣ አዲስ የተረጂ ልየታ ሥርዓት ከዘረጋ ወዲህ፣ በትግራይ፣ አማራ፣ አፋርና ሱማሊያ ክልሎች 6 ነጥብ 2 የአደጋ ተጋላጮችን መመዝገቡንም ጠቅሷል።

4፤ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኩባንያ እስካለፈው ታኅሳስ መጨረሻ ከኤምፔሳ አገልግሎቱ 280 ሺህ 625 ዶላር ገቢ ማግኘቱን ዘ ስታር ጋዜጣ አስነብቧል። በኢትዮጵያ የኩባንያው የኤምፔሳ አገልግሎት ተመዝጋቢዎች ቁጥር ወደ 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ማሻቀቡንና የኤምፔሳ ገንዘብ ዝውውር መጠኑም 115 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን ዘገባው አመልክቷል። ኩባንያው፣ የድምጽ፣ የመልዕክት ልውውጥና ዳታን ጨምሮ ባጠቃላይ በዘጠኝ ወራት ከአገልግሎቶቹ ያገኘው ገቢ 30 ሚሊዮን ዶላር መድረሱንም ዘገባው ጠቅሷል። ይህ ገቢ ኩባንያው በ2023 በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ካገኘው ገቢ የ74 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል።

5፤ የዓለማቀፉ ፍልሰት ድርጅት (አይ ኦ ኤም) ምክር ቤት ሊቀመንበር አምባሳደር ካታሪና ስታስች ከትናንት ጀምሮ በኢትዮጵያ የሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው። ስታስች፣ ትናንት ከአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ሺፈራው ተ/ማርያም ጋር በፍልሰትና ፍልሰተኞች ዙሪያ ተወያይተዋል። ሃላፊዋ፣ ከአፍሪካ ኅብረትና ከተመድ ባለሥልጣናትና ከለጋሽና የልማት አገራት ተወካዮች ጋር በፍልሰትና በፍልሰት ምላሽ አሰጣጥ ዙሪያ እንደሚወያዩም ድርጅቱ አመልክቷል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ረቡዕ ጥር 29/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ነገ አዲስ ሚንስትሮች እንዲሾሙላቸው ዕጩ ተሿሚዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባሉ። ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚያቀርቡትን የሚንስትሮች ሹመት ለማጽደቅ በነገው'ለት እንደሚሰበሰብ ዛሬ ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል። ዐቢይ ከሚያቀርቧቸው አዲስ ዕጩ ተሿሚዎች መካከል፣ ከኹለት ሳምንት ገደማ በፊት ከሥልጣን የተሰናበቱትን የምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ምትክ እንደሚገኙበት ይጠበቃል። ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የሜዳይ፣ ኒሻንና ሽልማት እንዲኹም የሕዝባዊ በዓላትን አከባበር ለመወሰን በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ እና በሌሎች ረቂቅ አዋጆች ላይ እንደሚወያይ ገልጧል።

2፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በቀጣዮቹ ሳምንታት በኢትዮጵያ በግጭት፣ ድርቅና ጎርፍ ለተጎዱ ሦስት ሚሊዮን ሰዎች የምግብ ድጋፍ ለማቅረብ በፍጥነት እንቅስቃሰ መኾኑን አስታውቋል። በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እያሽቆለቆለ መሄዱ በእጅጉ ያሳስበኛል ያለው ደርጅቱ፣ ሠራተኞቹ የርሃብ አደጋ ላንዣበበባቸው ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መኾኑን አመልክቷል። ድርጅቱ፣ ባለፈው ታኅሣሥ ወር መጀመሪያ የምግብ አቅርቦት ሥራውን እንደገና ከጀመረ ወዲህ፣ በአፋር፣ አማራ፣ ትግራይና ሱማሌ ክልሎች ለ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ ዕርዳታ ማሠራጨቱን ገልጿል። ድርጅቱ አዲሱን አሠራሩን ከዘረጋ ወዲህ፣ በተጠቀሱት ክልሎች ለአደጋ ተጋላጭ የኾኑ 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎችን በዲጅታል መመዝገቡንም ጠቁሟል። እስከ ሰኔ ወር ተጨማሪ 142 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ያመለከተው ድርጅቱ፣ ገንዘብ ካልተገኘ በሚያዝያ ወር ለስደተኞች የሚያቀርበውን የምግብ እርዳታ ለማቋረጥ እገደሚገደድ አስጠንቅቋል።

3፤ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ከየካቲት 04 ዓ.ም ጀምሮ ለካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፍቃድ መስጠት እንደሚጀምር ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ባለሥልጣኑ፣ ከመጭው ሰኞ ጀምሮ 15 አዳዲስ የካፒታል ገበያ ፍቃዶችን መስጠት እንደሚጀምርም ገልጿል። ባለሥልጣኑ፣ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፍቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር መመሪያ አዘጋጅቼ ወደ ሥራ ገብቻለኹ ብሏል። በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢንቨስትመንት ባንኮች ፍቃድ መስጠት እንደሚጀመር የገለጸው ባለሥልጣኑ፣ አምስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም በዚህ ማዕቀፍ ለመካተት ዝግጅት ማድረጋቸውን አመልክቷል። ሦስት የውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮች በአገሪቱ መስራት በሚችሉበት ኹኔታ ዙሪያ ጥያቄ አቅርበው፣ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል ተብሏል።

4፤ መከላከያ ሠራዊት፣ በሕገወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ የነበረ 30 በርሚል ነዳጅ መያዙን ዛሬ ገልጧል። ነዳጁን የጫነው ኮድ 3 የኾነ ተሽከርካሪ፣ ከሶማሌ ክልል ከአፍዴር ዞን፣ ዶሎ ባይ ከተማ በመነሳት ወደ ጎረቤት ሱማሊያ ጁባላንድ ራስ ገዝ አስተዳደር ሊሻገር ሲሞክር በሥፍራው በነበሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በቁጥጥር ስር መዋሉን ሠራዊቱ አመልክቷል። በሕገወጥ መንገድ ወደ ሱማሊያ ሊወጣ የነበረው ነዳጅ 750 ሺሕ ብር የሚገመት ዋጋ ያለው እንደኾነም ሠራዊቱ ጠቅሷል። መከላከያ ሠራዊት፣ በአገሪቱ ውስጥ የዋጋ ንረትን በመፍጠር የአገርን ጥቅም የሚያሳጡ ነጋዴዎችን በኹሉም ዓለማቀፍ የድንበር መግቢያና መውጫዎች ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መኾኑንም ጠቁሟል። ነዳጁን ወደ ሱማሊያ ያጓጉዙ የነበሩት አካላት በቁጥጥር ሥር ስለመዋላቸው ወይም አለመዋላቸው ሠራዊቱ አልገለጠም።

5፤ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኩባንያ እስካለፈው ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ከአገር ውስጥ ምንጮች የሰበሰበው የብድር መጡን 117 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን ቢዝነስ ደይሊ ዘግቧል። ኩባንያው፣ ከኢትዮጵያ የፋይናንስ ገበያ የተበደረው የገንዘብ መጠን ባለፈው ሰኔ ወር 95 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ዘገባው አመልክቷል። ኩባንያው፣ በብድር ያገኘውን ገንዘብ በኢትዮጵያ ለሚያስፋፋው አገልግሎትና ለሥራ ማስኬጃ እንደሚያውለው ዘገባው ጠቅሷል። ኩባንያው እስካለፈው ታኅሳስ መጨረሻ ከኤምፔሳ አገልግሎቱ 280 ሺህ 625 ዶላር ገቢ እንዳገኘና በኢትዮጵያ የኩባንያው የኤምፔሳ አገልግሎት ተመዝጋቢዎች ቁጥርም ወደ 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን እንዳደገ ተገልጧል። ኩባንያው እስካለፈው ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ከአገሪቱ ጠቅላላ ሕዝብ ለአንድ ሦስተኛው ተደራሽ መኾን መቻሉንም ዘገባው አመልክቷል።

6፤ ብሔራዊ ባንክ፣ በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ውስጥ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂ ናቸው ያላቸው 12 የቀድሞ የባንኩ የቦርድ አባላት ለስድስት ዓመታት በአገሪቱ በየትኛውም የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ እንዳያገለግሉ ባለፈው ሳምንት በጻፈው ደብዳቤ ማገዱን ሪፖርተር ዘግቧል። ብሔራዊ ባንክ በባንኩ የቦርድ አመራሮች ላይ ዕገዳውን የጣለው፣ ግለሰቦቹ ባንኩ ለገባበት ችግር በጋራም ኾነ በተናጠል ተጠያቂነት እንዳለባቸውን በምርመራ አረጋግጫለኹ በማለት ነው። የንብ ባንክ የቀድሞ የቦርድ አመራሮች እገዳ የተጣለባቸው፣ የገንዘብ አስቀማጮችን ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶችንና ሌሎች ግድፈቶችን ፈጽመዋል ተብለው ነው። ከታገዱት መካከል፣ የቀድሞው የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር ወልደ ተንሳይ ወልደ ጊዮርጊስ ይገኙበታል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ሐሙስ ጥር 30/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የሚያቀርቡለትን የአዳዲስ ሚንስትሮች ሹመት ያጸድቃል። ዐቢይ ከሚያቀርቧቸው አዲስ ዕጩ ተሿሚዎች መካከል፣ ከሥልጣን የተሰናበቱት የምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ምትክ እንደሚገኙበት ይጠበቃል። ምክር ቤቱ፣ የኢትዮጵያ የሜዳይ፣ ኒሻንና ሽልማት እንዲኹም የሕዝባዊ በዓላትን አከባበር ለመወሰን በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅና በሌሎች ረቂቅ አዋጆች ላይ ጭምር እንደሚወያይ ገልጧል።

2፤ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትና እናት ፓርቲን ጨምሮ አምስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ጥር 20 ቀን በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን መርዓዊ ከተማ ከ50 በላይ ንጹሃን ዜጎችን ገድለዋል ወይም ረሽነዋል በማለት በጋራ ባወጡት መግለጫ ከሰዋል። በድርጊቱ ሕጻናት፣ ሴቶች፣ አዛውንቶችና ካህናት ጭምር እንደተገደሉና እንደተረሸኑ መረዳታቸውን ፓርቲዎቹ ገልጸዋል። የመንግሥት ጸጥታ ሃይሎች ርምጃውን የወሰዱት፣ በከተማዋ በመንግሥት ወታደሮችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መካሄዱን ተከትሎ እንደኾነ ተገልጧል። ፓርቲዎቹ ድርጊቱ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ የጠየቁ ሲኾን፣ በክልል የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተራዘመው “የክልሉን ሕዝብ ስቃይ ለማራዘም ነው” በማለትም ከሰዋል።

3፤ በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ከትግራይ መቀሌ ከተማ ሞሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ኮዱ 3 በኾነ ተሽከርካሪ ወደ አማራ ክልል ባሕርዳር ሲጓጓዝ የነበረ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ትናንት አስታውቋል። የአስተዳደሩ ኮምንኬሽን ቢሮ፣ ጦር መሳሪያው በቁጥጥር ሥር የዋለው ወልድያ ከተማ ኬላ ላይ ነው ብሏል። በቁጥጥር ሥር ከዋለው ጦር መሳሪያ መካከል፣ 48 የሞርታር ቅንቡላዎች፣ 855 የዲሽቃና 389 የብሬን ጥይቶች እንደሚገኙበት ተገልጧል።

4፤ የኢትዮጵያ እስልምናን ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ የመሩት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ትናንት በመቀሌ በተካሄደ የሰላም ኮንፈረንስ ላይ መሳተፉን ምክር ቤቱ አስታውቋል። ልዑካን ቡድኑ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰበትን ነጃሺ መሰጂድም ጎብኝቷል ተብሏል። ልዑካን ቡድኑ ትናንት ወደ መቀሌ ያቀናው፣ ጠቅላይ ምክር ቤቱ እና የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በመካከላቸው ተፈጥሮ የነበረውን መቃቃር በእርቅ መፍታታቸውን ተከትሎ ነው።

5፤ የዓለማቀፉ የፍልሰት ድርጅት ምክር ቤት ሊቀመንበር ጀርመናዊቷ አምባሳደር ካታሪና ሳስች ትናንት ወደ መቀሌ አቅንተው ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳና ከዓለማቀፍ አጋር ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል። ውይይቱ፣ ለትግራይ የድርቅ ተጎጂዎች እየቀረበ በሚገኘው ሰብዓዊ ዕርዳታ ዙሪያ እንደኾነ አይ ኦ ኤም ገልጧል። ሃላፊዋ፣ በመቀሌ የሚገኝ በአይ ኦ ኤም ዕርዳታ ለ9 ሺህ 300 ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያደርገውን የተፈናቃዮች ጣቢያ ጎብኝተዋል ተብሏል። ካትሪን ኢትዮጵያ የገቡት፣ ለሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ነው።

6፤ የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ከፍተኛ ልዑካን ቡድኖች ባሕሬን ውስጥ ባለፉት ጥቂት ቀናት ሦስት ጊዜ እንደተገናኙና በመርሆዎች መግለጫ ላይ እንደተስማሙ መስማቱን ሮይተርስ ዘግቧል። ቀደም ሲል ጅዳ ላይ ከተካሄዱት ንግግሮች በተለየ በባሕሬኑ ስብሰባ ላይ በጦር ሠራዊቱ በኩል ጀኔራል ሸምሰዲን ካባሺ እንዲኹም በፈጥኖ ደራሹ ኃይል በኩል የጀኔራል መሃመድ ደጋሎ ወንድም ሐምዳን ደጋሎ እንደተገኙ ተገልጧል። በስብሰባው ላይ፣ የኹለቱ ባላንጣ ወገኖች ደጋፊዎች የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶችና የግብጽ ባለሥልጣናት ጭምር ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተገኙ ዘገባው አመልክቷል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሐሙስ ጥር 30/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ላለፉት ሦስት ዓመታት የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር ኾነው በማገልገል ላይ የሚገኙትን ተመስገን ጥሩነህን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አድርጎ ሹሟል። ተመስገን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ኾነው የተሾሙት፣ ከኹለት ሳምንት በፊት ከሥልጣናቸው በፍቃዳቸው በለቀቁት ደመቀ መኮንን ምትክ ነው። ለበርካታ ዓመታት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና በኋላም የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አማካሪ የነበሩት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ደሞ በደመቀ መኮንን ምትክ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኾነው ተሹመዋል። በተመሳሳይ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከጤና ሚንስትርነታቸው ባነሷቸው ዶክተር ሊያ ታደሠ ምትክ ዶክተር መቅደስ ዳባን አቅርበው አስሹመዋል። ዶክተር መቅደስ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ረዳትና የድርጅቱ ባለሙያ የነበሩ ናቸው። ሦስቱም ሹመቶች በሙሉ ድምጽ እንደጸደቁ ምክር ቤቱ ገልጧል።

2፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪያቸውን ሬድዋን ሁሴንን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አድርገው ሹመዋል። ሬድዋን የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ኾነው የተሾሙት፣ የቀድሞው የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ተመስገን ጥሩነህ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ኾነው መሾማቸውን ተከትሎ ነው። ዐቢይ በተመሳሳይ፣ ትዕግስት ሃሚድን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ወይም በምሕጻረ ቃሉ የኢንሳ ዋና ዳይሬክተር አድርገው ሹመዋል።

3፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለፉት ስድስት ወራት ለጎረቤት አገራት ከሽጠው ኤሌክትሪክ ኃይል 47 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን አስታውቋል። ኩባንያው በ6 ወራት ለኬንያ፣ ለሱዳንና ለጅቡቲ 1 ሺህ 82 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ በመመሸጥ 66 ነጥብ 27 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ እንደነበር ገልጧል። አገራቱ የገዙት ግን፣ 762 ነጥብ 8 ጊጋ ዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ እንደኾነና ይህም የዕቅዱ 71 በመቶ ብቻ እንደኾነ ኩባንያው ጠቅሷል። ለሱዳን የ11 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ታቅዶ እንደነበር የጠቀሰው ኩባንያው፣ በአገሪቱ በሚካሄደው ጦርነት ሳቢያ የተሸጠው ግን የ8 ሚሊዮን ዶላር ኤሌክትሪክ ብቻ እንደኾነ ገልጧል። ለኬንያ የተሸጠው ኃይልም፣ የ20 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደኾነ ኩባንያው ጠቅሷል። ኬንያ አንድ ኪሎ ዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ የምትገዛው በ6.5 የአሜሪካ ሳንቲም ነው።

4፤ ኦነግ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከነበሩት ለማ መገርሳ እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከነበሩት ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ከአምስት ዓመት በፊት አሥመራ ላይ የደረስንበትን ስምምነት ያፈረሰው የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት ነው በማለት ከሷል፡፡ ዐቢይ ማክሰኞ'ለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው፣ "ኦነግ ሥራውን በሠላማዊ መንገድ እየሠራ ነው፤ የታጠፈ ቃል የለም"ማለታቸው እንዳሳዘነው ኦነግ ገልጧል፡፡ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ መከልከሉንና ከፍተኛ አመራሮቹ እስከ ዛሬ ድረስ በእስር ላይ መኾናቸውን የጠቀሰው ኦነግ፣ በአዲስ አበባ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን ዋና ጽሕፈት ቤቱን ጨምሮ በርካታ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቹ ተዘግተው በመንግሥት ኃይሎች እየተጠበቁ እንደኾነ ገልጧል፡፡ መንግሥት፣ በአሥመራ ከኦነግ አመራሮች ጋር ተደረሰበት የተባለው ስምምነት ይዘቱ ምን እንደኾነ ይፋ አድርጎ አያውቅም።

5፤ በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ወደ ኬንያ የገቡ ሦስት ኢትዮጵያዊያን ትናንት ሜሩ አውራጃ ውስጥ በተሽከርካሪ አደጋ ሕይወታቸው ማለፉን ዘ ስታር ጋዜጣ ፖሊስን ጠቅሶ ዘግቧል። በአደጋው ሌሎች ስምንቱ ከባድ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸውና ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱ ዘገባው አመልክቷል። በተያያዘ፣ ባለፈው ማክሰኞ በሰሜን ምሥራቅ ኬንያ ኢሴሎ አውራጃ ወደ ናይሮቢ በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት በታጠቁ ግለሰሶች ታጅበው በሞተር ሳይክል ሲጓዙ የነበሩ ስምንት ኢትዮጵያዊያን በፖሊስ እንደተያዙና ሌሎች ሰባት ኢትዮጵያዊያን ግን በታጠቁ አጃቢዎቻቸውና በፖሊስ መካከል የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ ከአካባቢው እንዳመለጡ ተገልጧል። በመርሳቢት ግዛትም፣ በተመሳሳይ በታጣቁ ግለሰቦች ታጅበው ሲጓዙ የነበሩ 25 ኢትዮጵያዊያን ተይዘዋል ተብሏል።

6፤ በጎረቤት ሱማሊያ ጌዶ አውራጃ ዶሎው ከተማ አካባቢ የሠፈሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች በከተማዋ የሌሊት እንቅስቃሴ ገደብ እንደጣሉ የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የኢትዮጵያ ወታደሮች በከተማዋ ላይ የሰዓት ገደብ የጣሉት፣ ባለፈው ሳምንት ዕሁድ በአካባቢው በለድ ሃዎ በተባለች ከተማ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ስድስት ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን መግደላቸውን ተከትሎ ነው። በኢትዮጵያዊያኑ ላይ ተፈጸመ ለተባለው ግድያ፣ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ሃላፊነት የወሰደ አካል የለም። በግድያው ዙሪያ፣ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴርም ኾነ በሞቃዲሾ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ያሉት ነገር የለም።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ2517 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ3767 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 67 ብር ከ8166 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ1729 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ60 ከ5606 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ61 ብር ከ7718 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ዓርብ የካቲት 1/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ኢትዮጵያ፣ የቡና የወጪ ንግዷን ከአውሮፓ ኅብረት የደን ጭፍጨፋ ደንብ ጋር ለማጣጣም የነደፈችውን ብሄራዊ የድርጊት መርሃ ግብር ከትናንት ወዲያ ዓለማቀፍ የልማት አጋሮች በተገኙበት የምክክር መድረክ ላይ ይፋ አድርጋለች። የአውሮፓ ኅብረት ደንብ፣ ደን በመጨፍጨፍ የተመረተ የቡና ምርት ከተያዘው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ወደ አውሮፓ ገበያ እንዳይገባ ያግዳል። የገንዘብ ሚንስትር ደዔታ ሠመሬታ ስዋሰው፣ ኢትዮጵያ ደንቡ ተፈጻሚ መኾን የሚጀምርበት ቀነ ገደብ እንዲራዘም ላቀረበችው ጥያቄ በጎ ምላሽ አገኛለኹ የሚል ተስፋ እንዳላት በመድረኩ ላይ ተናግረዋል። ብሄራዊ የድርጊት መርሃ ግብሩ፣ የኅብረቱ ደንብ አገሪቱ ወደ አውሮፓ በምትልከው ቡና ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ መቀነስ የሚያስችሉ አማራጮችን የያዘ ነው። በምክክር መድረኩ ላይ ከሠመሬታ በተጨማሪ፣ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ፣ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ምክትል መልዕክተኛ ዴቪድ ክሪቫኔክና የኅብረቱ አባል አገራት ኢምባሲዎች ተወካዮች ተገኝተዋል።

2፤ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ጃራ ጊዜያዊ መጠለያ የተጠለሉ ተፈናቃዮች የምግብ ዕርዳታ ተቋርጦብናል በማለት ትናንት ተቃውሟቸውን በሰላማዊ ሰልፍ እንደገለጡ ዶይቸቨለ ዘግቧል። ሰልፈኞቹ ከኹለት ወራት በላይ የምግብ ዕርዳታ እንዳላገኙ መግለጣቸውን ዘገባው አመልክቷል። የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤትን በበኩሉ፣ ተፈናቃዮቹ በቀጣዮቹ 10 ቀናት የምግብ እርዳታ ይደርሳቸዋል ማለቱን ዘገባው ጠቅሷል። በጃራ ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች፣ ከኦሮሚያ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በግጭቶችና ብሄር ቾ-ተኮር ጥቃቶች ባለፉት አራት አመታት የተፈናቀሉ ናቸው።

3፤ የጋምቤላ ክልል መንግሥት ተደጋጋሚ ግጭት በሚከሰትባት ኢታንግ ልዩ ወረዳ በድጋሚ ሕዝባዊ የሰላም ውይይቶችን ጀምሯል። በክልሉ፣ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ባለሦስት እግር ባጃጆችን ጨምሮ በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚፈጸሙት ጥቃቶች አኹንም መቀጠላቸውን ዋዜማ ከምንጮቿ ተረድታለች። በተለይ በኢታንግ ልዩ ወረዳ የኢታንግ ከተማን ከክልሉ ዋና ከተማ ጋምቤላ ጋር በሚያገናኘው መንገድ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እየተፈጸሙ እንደኾነ ምንጮች ተናግረዋል። ለአብነትም ከኹለት ቀናት በፊት በኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ ባንድ ባጃጅ ላይ በተፈጸመ ጥቃት በሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል ተብሏል።

4፤ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት፣ የሥር ፍርድ ቤት በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሠፋ መዝገብ በሽብር ወንጀል የተከሰሱ ተከሳሾች ክስ እንዲቋረጥ የወሰነውን ውሳኔ ትናንት ሽሯል። ችሎት ባለመቅረባቸው ክሳቸው እንዲቋረጥ የተወሰነላቸው ምሬ ወዳጆን ጨምሮ 27 ተከሳሾች ናቸው። የሥር ፍርድ ቤቱ ክሱ እንዲቋረጥ የወሰነው፣ ተከሳሾቹ ጫካ ስለመግባታቸው ፖሊስ ባቀረበለት ማስረጃ ላይ ተንተርሶ ነበር። መንግሥትን በኃይል የመገልበጥ ክስ ከተመሠረተባቸው 50 ተከሳሾች መካከል፣ 23ቱ በእስር ላይ ኾነው የፍርድ ሂደታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።

5፤ ሱማሊያና ቱርክ ትናንት የመከላከያና የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል። የመከላከያ ትብብር ስምምነቱ፣ ኹለቱ አገሮች የወታደራዊና የፋይናንስ እንዲኹም የጸረ-ሽብር ትብብር ለማድረግ የሚያስችላቸው ነው። የመከላከያ ትብብር ስምምነቱን አንካራ ውስጥ የተፈራረሙት፣ የኹለቱ አገራት የመከላከያ ሚንስትሮች ናቸው። ቱርክና ሱማሊያ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሲኾን፣ ቱርክም ሱማሊያ ውስጥ ወታደራዊ ጦር ሠፈር አላት። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ዓርብ የካቲት 1/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የነበሩትን ሥራዎችና መሻሻሎች ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ሹማምንት ጋር መገምገም መጀመራቸውን ጽሕፈት ቤታቸው አስታውቋል። ዛሬ ጧት የተጀመረው ግምገማ፣ በድኅረ-ግጭት መልሶ ግንባታና በፕሪቶሪያው ግጭት ማቆም ስምምነት ስምምነቱ አፈጻጸም ላይ ያተኮረ እንደኾነ ጽሕፈት ቤቱ ገልጧል። በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት በተጀመረው የግምገማ መድረክ ላይ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት እና ከትግራይ በኩል ደሞ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፣ የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል፣ የክልሉ ጸጥታ አስተዳደር ሃላፊ ጄኔራል ታደሠ ወረደ እና የክልሉ ካቢኔ አባል ጀኔራል ጻድቃን ገብረ ተንሳይ መገኘታቸው ተገልጧል።

2፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፣ በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን መራዊ ከተማ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተፈጽሟል የተባለው ግድያ በጥልቅ እንዳሳሰበው ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። አምባሳደሩ፣ ገለልተኛ የሰብዓዊ መብት ተቆጣጣሪዎች ወደ ሥፍራው እንዲገቡ እንዲፈቀድላቸው፣ ግድያውን የፈጸሙ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ በክስተቱ ዙሪያ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል። መራዊ ላይ ተፈጸመ ከተባለው ድርጊት በፊትም፣ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙ መረጃዎች ሲወጡ መቆየታቸውን አምባሳደሩ ገልጸዋል። አምባሳደር ማሲንጋ፣ ለአገሪቱ ችግሮች መፍትሄው ግጭት ሳይኾን፣ ንግግር እንደኾነ በመልዕክታቸው አስፍረዋል። ጥር 20 በመንግሥት ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መካሄዱን ተከትሎ፣ የመንግሥት ወታደሮች በከተማዋ የቤት ለቤት አሰሳ ጭምር በማድረግ ከ80 በላይ ሰዎችን እንደገደሉና እንደረሸኑ ሲዘገብ ሰንብቷል።

3፤ የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣ ኢትዮጵያ የፈረመችውን በአውሮፓ ኅብረትና በአፍሪካ፣ ፓስፊክና ካሪቢያን አገራት መካከል የተደረሰውን የሳሞአ የንግድና የኢኪኖሚ ትብብር ስምምነት የኢትዮጵያ መንግሥት ባስቸኳይ እንዲሰርዘው ጠይቋል። የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔው ይህን ጥያቄ ያቀረበው፣ የሳሞአ ስምምነት በውስጡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የሐይማኖትና ባሕል እሴቶች ጋር የሚጻረሩ ጽንሰ ሃሳቦች ስላሉት መኾኑን ገልጧል። ጉባዔው፣ የሳሞአ ስምምነት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት የሚያደርጉ ሰዎች መብቶች፣ የጾታ መቀየርና የጽንስ ማስወረድ መብቶችና እጅግ አደገኛ ይዘት ያለው ለልጆችና ታዳጊዎች ኹሉን ዓቀፍ የስነ ጾታ ትምህርት እንዲሰጥ የሚያስገድድ አንቀጽ በስምምነቱ ተካቷል ብሏል። ስምምነቱ በውስጡ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡና ትውልድን ብሎም አገርን እጅግ የሚጎዱ በርካታ አንቀጾች የተካተቱበት ነው በማለትም ጉባዔው ተቃውሞውን ገልጧል። አውሮፓ ኅብረት ባለፈው ኅዳር ከአፍሪካ፣ ከካሪቢያንና ከፓስፊክ አገራት የተፈራረመው የንግድና ኢኮኖሚ ትብብር ስምምነት፣ ለ20 ዓመታት የሚዘልቅ ሲኾን፣ ስምምነቱን ከፈረሙት የአፍሪካ የአፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት።

4፤ መከላከያ ሠራዊት በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተዘግተው የቆዩ መንገዶችን ማስከፈት መቻሉን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የምዕራብ ወለጋ ዞን ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ረሻድ ኢብራሂም፣ ሠራዊቱ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን እና በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን መካከል ተቋርጦ የነበረውን የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴ እንደገና እንዲጀምር ማደረጉን ገልጸዋል ተብሏል። ክፍለ ጦሩ ከግዳጁ ጎን ለጎን፣ አማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አውድሟቸው የነበሩ ትምህርት ቤቶችን በማደስ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉ ተገልጧል። አማጺ ቡድን ባካባቢው በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሳቢያ፣ የምዕራብ ወለጋ ዞንን ከካማሺ ዞን የሚያገናኘው ዋናው የአስፓልት መንገድ ላለፉት አምስት ዓመታት ለትራንስፖርት ተዘግቶ መቆየቱ ይታወቃል።

5፤ የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት፣ የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች በስዊዘርላንድ ንግግር እንዲቀመጡ ተመድ ያቀረበውን ሃሳብ ውድቅ አድርጓል። የጀኔራል ቡርሃን መንግሥት፣ ጅዳ ላይ ከተጀመረው አሜሪካና ሳዑዲ ዓረቢያ ከሚመሩት ንግግር ውጭ ሌላ የንግግር መድረክ አያስፈልግም ብሏል። ሱዳን ይህን ያስታወቀችው፣ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ሃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ "ኹለቱ ተፋላሚ ወገኖች በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ዙሪያ ስዊዘርላንድ ውስጥ ለመነጋገር ተስማምተዋል" በማለት ከተናገሩ በኋላ ነው። የጀኔራል ቡርሃን መንግሥት፣ በቅርቡ በሌላ ሦስተኛ አገር በጦር ሠራዊቱና በፈጥኖ ደራሹ ኃይል መካከል ንግግር ተካሂዷል ተብሎ የተሠራጨው መረጃ "ሐሰት ነው" በማለት አስተባብሏል። የኹለቱ ወገኖች ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች በቅርቡ ባሕሬን ውስጥ ባደረጉት ሚስጢራዊ ንግግር "የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት" መፈራረማቸውን ሮይተርስ ዘግቦ ነበር።

6፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ2635 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ3888 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 67 ብር ከ7233 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ0778 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ60 ከ5452 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ61 ብር ከ7561 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ቅዳሜ የካቲት 2/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ ኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረትን አዲሱን የደን ጭፍጨፋ ደንብ ባከበረ መልኩ የቡና ምርቷን ወደ አውሮፓ መላክ እንድትቀጥል ለማስቻል ጀ ዲ ኢ ፒትስ እና ኢንቬሪታስ ከተሰኙ ከባንያዎች ጋር ትናንት ስምምነት ተፈራርሟል። ኢንቬሪተስ ኩባንያ፣ በሳተላይትና ሌሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ የኢትዮጵያ ቡና በተጨፈጨፉ ደኖች ላይ የተመረተ አለመኾኑን የማረጋገጥ ሃላፊነት ይኖረዋል። ጀዲኢ ኩባንያ በበከሉ፣ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ደን ተጨፍጭፎ ቡና የለማባቸውን አካባቢዎች ወደነበሩበት ለመመለስ እገዛ ያደርጋል። ኅብረቱ ከመጭው ዓመት ታኅሳስ ጀምሮ ተግባራዊ የሚያደርገው ደንብ፣ ከፈረንጆች 2020 ዓ፣ም ጀምሮ በቡና አምራች አገራት በደን ጭፍጨፋ የተመረተ ቡና ወደ አውሮፓ ገበያ እንዳይገባ ያግዳል። ደንቡ፣ በተጨፈጨፉ ደኖች ላይ የተመረተ ቡና ልከው የሚገኙ አገራት፣ ቡናቸው ጨርሶ ከአውሮፓ ገበያ እንዲታገድ ያዛል።

2፤ መንግሥት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ እንዲቀርጽ ያቋቋመው የባለሙያዎች ቡድን የሽግግር ፍትህ ረቂቅ ፖሊሲ ዝግጅቱን አጠናቆ እንደተበተነ ለሸገር ተናግሯል። ቡድኑ፣ ያዘጋጀኹትን ባለ 270 ገጽ ረቂቅ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሰነድ ሰኞ'ለት ለመንግሥት አስረክቤያለኹ ማለቱን ዘገባው ጠቅሷል። ከዚህ በኋላ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲውን ተግባራዊ የማድረግ ሃላፊነት የፍትህ ሚንስቴር እንደኾነ ተገልጧል። አስገድዶ መድፈርና ማፈናቀልን ጨምሮ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን የፈጸሙ አካላት ምህረት እንደማያገኙ በረቂቅ ሰነዱ ላይ እንደተደነገገ ዜና ምንጩ አመልክቷል።

3፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 26 ከተሞች ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መሉ በሙሉ እንደተቋረጠባቸው ዶይቸቨለ ዘግቧል። የኤሌክትሪክ ኃይል የተቋረጠው፣ በደቡብ ኦሞ፣ በባስኬቶ፣ ጎፋ፣ አሌ እና በከፊል በጋሞ ዞኖች እንደኾነ የክልሉ ኤሌክትሪክ ኃይል ሃላፊዎች መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል። በዞኖቹ የኤሌክትሪክ ኃይል የተቋረጠው፣ ከወላይታ ዞን ወደ ጎፋ ዞን የተዘረጉ አራት የከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ ምስሶዎች በዘራፊዎች በመሠረቃቸው ነው ተብሏል።

4፤ ተቃዋሚው የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ የሲዳማ ክልል መንግሥት በአመራሮቹ ላይ የሚፈጸመውን እስር መቀጠሉን አስታውቋል። ፓርቲው፣ የክልሉ ጸጥታ ኃይሎች የማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉን ማቲዮስ ጋልፋቶን ትናንት እንዳሠሩ ገልጧል። የክልሉ መንግሥት አመራሮቼን ማሠር የቀጠለው፣ የሲዳማን ሕዝብ "ተቆርቋሪና ተቋም አልባ" በማድረግ "በሥልጣን ላይ ለመቆየት" ነው በማለት ፓርቲው ከሷል። ፓርቲው፣ የክልሉ ጸጥታ ኃይሎች ሀዋሳ የሚገኘውን ዋና ጽሕፈት ቤቱን ሰብረው ገብተው፣ በዲሲፕሊን ጥሰት ለታገዱ አባላት ሰጥተዋል በማለት ከሳምንታት በፊት መክሰሱ ይታወሳል።

5፤ ተመድ፣ በምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ለሚሠማራው የቀጠናዊው የደቡባዊ አፍሪካ አገራት ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ጦር የሎጅስቲክስ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁነቱን ገልጧል። ተመድ፣ ኤም23 የተሰኘው አማጺ ቡድን ባስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲያደርግም አሳስቧል። ኮንጎ የደቡባዊ አፍሪካ ቀጠናዊ ጦር በምሥራቃዊ ኮንጎ እንዲሠማራ ጥያቄ ያቀረበችው፣ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ጦር ከኮንጎ ከመውጣቱ በፊት ነበር። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ፣ አማጺው ቡድን በአገሪቱ መንግሥት ጦር ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍቷል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ቅዳሜ የካቲት 2/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚንስትሩ ሞሊ ፊ ከየካቲት 4 እስከ 9 በኢትዮጵያ ቆይታ እንደሚያደርጉ አስታውቋል። ከሞሊ ፊ ጋር፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር እና የአሜሪካ ዓለማቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስአይዲ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሞንዴ ሙያንግዋ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ መስሪያ ቤቱ ገልጧል። ሞሊ ፊ፣ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሏል። ሞሊ ፊ የሚመሩት ልዑክ በዋናነት ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዘው፣ አዲስ አበባ ከ6 እስከ 10 በምታስተናግደው የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍና ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ጋር ለመወያየት እንደኾነ ተገልጧል።

2፤ ገንዘብ ሚንስቴር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዘጠኝ ጥቅም ላይ ያልዋሉ መሬቶችን ለመንግሥት ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን እንዲያስረክብ ማዘዙን ሪፖርተር ዘግቧል። ኮርፖሬሽኑ በከተማዋ ጥቅም ላይ ያልዋሉ መሬቶችን ለልማት በማዋል ኪሳራ ከገጠማቸው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የተረከበውን ዕዳ እንዲያካክስ ሥልጣን ተሰጥቶታል። በከተማዋ የሚገኙት ጥቅም ላይ ያልዋሉት መሬቶች፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ከመሸጣቸው በፊት የድርጅቶቹ ንብረት የነበሩ ናቸው። ኾኖም አንዳንዶች መሬቶች በደርግ ጊዜ ከግለሰቦች የተወረሱ በመኾናቸው፣ ገና የፍርድ ቤት ክርክር እንዳለባቸው ኮርፖሬሽኑ መግለጡን ዘገባው አመልክቷል።

3፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ዛሬ በክልሉ በ20 የክልሉ ከተሞች ሕዝባዊ ውይይቶችን አድርጓል። ሕዝባዊ ውይይቶቹ የተካሄዱት፣ "ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ለዘላቂ ሠላምና ኹለንተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ሃሳብ እንደኾነ ተነግሯል። ውይይቶቹን የመሩት፣ የፌደራል መንግሥት ሚንስትሮች፣ ሌሎች ባለሥልጣናትና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ናቸው። ሕዝባዊ ውይይቶቹን ማካሄድ ያስፈለገው፣ በአገራዊ ሠላምና ልማት ዙሪያ የጋራ መግባባት ለመፍጠር በማሰብ እንደኾነ ተገልጧል። ከቀናት በፊት ተመሳሳይ ሕዝባዊ ውይይቶች በአማራ ክልል 25 ከተሞች መካሄዳቸው ይታወሳል።

4፤ ለንደን የሚገኘው የብሪታንያ ነገሥታት ቤተክርስቲያን ዌስትሚንስተር አቤ፣ በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የብሪታንያ ወታደሮች የዘረፉትን አንድ ታቦት ለኢትዮጵያ ሊመልስ ማሰቡን የእንግሊዝ ጋዜጦች ዘግበዋል። ቤተክርስቲያኑ ለበርካታ ዓመታት ታቦቱን ላለመመለስ ሲያንገራግር ነበር። ቤተክርስቲያኑ ታቦቱን ከመለሰ፣ የብሪታንያ ሙዚዬምም ተመሳሳይ ርምጃ እንዲወስድ ግፊት ሊፈጥርበት እንደሚችል ዘገባው አመልክቷል። የብሪታንያ ሙዚዬምና ሌሎች አካላት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ የአጼ ቴዎድሮስን የጸጉር ዘለላ ጨምሮ የተለያዩ ከመቅደላ የተዘረፉ ቅርሶችን መመለሳቸው ይታወሳል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ሰኞ የካቲት 4/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚንስትር ሞሊ ፊ እና የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ። ሞሊ ፊ እና ሐመር ከዛሬ እስከ ቅዳሜ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ይወያያሉ። ሞሊ ፊ የሚመሩት ልዑክ በዋናነት ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዘው፣ አዲስ አበባ ከየካቲት 6 እስከ 10 በምታስተናግደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍና ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ጋር ለመወያየት ነው። የአሜሪካ ዓለማቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስአይዲ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሞንዴ ሙያንግዋ፣ ከልዑኩ አባል እንደኾነ የሞሊ ፊ መስሪያ ቤት ገልጧል።

2፤ ሱማሊያ፣ አፍሪካ ኅብረትና የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ላይ "በመርህ ላይ የተመሠረተ" አቋም እንዲይዙ ጠይቃለች። ሱማሊያ፣ ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቴና የግዛት አንድነቴ ላይ ፈጸመችብኝ ያለችውን "ወረራ" ድርጅቶቹ እንዲያወግዙም አሳስባለች። ሱማሊያ፣ የኢትዮጵያ አደገኛ ድርጊት አፍሪካ ኅብረት የቆመበትን መሠረት የሚንድና ያስመዘገበቻቸውን አወንታዊ ርምጃዎች የሚቀለብስ እንደኾነም ባወጣችው አዲስ መግለጫ ገልጣለች።

3፤ አልሸባብ ቅዳሜ'ለት በሞቃዲሾው ጀኔራል ጎርዶን ወታደራዊ ማሠልጠኛ ላይ በፈጸመው ጥቃት ሦስት የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ወታደሮች ተገድለዋል። በጥቃቱ፣ አንድ ሌላ የባሕሬን ወታደር እና ኹለት የሱማሊያ ወታደሮች መገደላቸውን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። በወታደራዊ ማሠልጠኛው ላይ ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ፣ ከኹለት ዓመት በፊት ከአልሸባብ ከድቶ እጁን ለመንግሥት የሰጠ የቡድኑ የቀድሞ ተዋጊ ነው።

4፤ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ትናንት በሞቃዲሾ ሊያደርጉት የነበረውን ይፋዊ ጉብኝት ለሌላ ጊዜ አስተላልፈዋል። ፕሬዝዳንት ሲሲ ጉብኝታቸውን ያራዘሙት፣ አልሸባብ ቅዳሜ'ለት በሞቃዲሾው ጀኔራል ጎርዶን ወታደራዊ ማሠልጠኛ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ እንደኾነ የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ፣ ፕሬዝዳንት ሲሲ ሱማሊያን እንዲጎበኙ ባለፈው ወር ግብዣ ያቀረቡላቸው፣ በሱማሊያና ኢትዮጵያ መካከል በባሕር በር መግባቢያ ዙሪያ ውጥረት መፈጠሩን ተከትሎ ካይሮን በጎበኙበት ወቅት ነበር።

5፤ የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማዔል ኦማር ጌሌ፣ ሱዳን ወደ ኢጋድ አባልነቷ እንድትመለስ ለማግባባት ልዩ ልዑክ ወደ ፖርት ሱዳን ልከዋል። የጅቡቲው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሞሃመድ ዓሊ የሱፍ፣ ኢጋድ የሱዳኑ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥረት ከማድረግ ውጭ ሌላ አጀንዳ የለውም በማለት ለቻይናው ሲጂቲኤን ተናግረዋል። ሱዳን፣ ኢጋድ በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ ይገባል በማለት፣ ከሦስት ሳምንት በፊት ከድርጅቱ አባልነት መውጣቷ ይታወሳል። ወደ ፖርት ሱዳን አጋባቢ ልዑክ የላኩት የጅቡቲው ፕሬዝዳንት፣ የኢጋድ የወቅቱ ሊቀመንበር ናቸው። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሰኞ የካቲት 4/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ተቀባይነት እንዲኖረው የሚደረጉ ኹለገብ ማግባባቶችና ተጽዕኖዎች እንዲኹም ስምምነቶች በኢትዮጵያ መንግሥት ዘንድ ተቀባይነት እንዳያገኙ በጥብቅ አሳስባለች። ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የሚደግፉ አሳሪ ስምምነቶች ውስጥ እንድትገባ የተጀመረውን ሂደት መንግሥት እንዲፈትሸው ጠይቋል። የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ያካተቱ ስምምነቶች የአገሪቱን ኃይማኖታዊና ስነ ልቦናዊ እሴቶች ይጥሳሉ ያለው ሲኖዶሱ፣ ኹሉም ዜጎች ሂደቱን እንዲቃወሙ ጥሪ አድርጓል። ሲኖዶሱ፣ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት "በሰው ልጅ ሰብዓዊ አኗኗር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው" እና "ለትውልድና ለአገር መውደም" ምክንያት የሚኾን ድርጊት መኾኑንም በመግለጫው ገልጧል።

2፤ የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ፣ 52 በመቶው የክልሉ የእርሻ መሬት በአማራና በኤርትራ ኃይሎች ተይዟል በማለት መክሰሱን ሪፖርተር ዘግቧል። የክልሉ ግብርና ቢሮ፣ መንግሥት የፕሪቶሪያውን የግጭት ማቆም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ባለማድረጉ፣ ከፍተኛ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች በኤርትራና በአማራ ኃይሎች ማለቱን ዘገባው ጠቅሷል፡፡ በክልሉ በ2016 ግማሽ በጀት ዓመት 15 ሚሊዮን ኩንታል እህል ለመሰብሰብ ታቅዶ እንደነበር የገለጠው ግብርና ቢሮው፣ መሰብሰብ የተቻለው ግን አምስት ሚሊዮን ኩንታል ወይም የዕቅዱ 37 በመቶ ብቻ እንደኾነ መናገሩንም ዘገባው አመልክቷል። ቢሮው፣ መታረስ ከሚችለው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ፣ የታረሰው 640 ሺሕ ሄክታር መሬት ብቻ መኾኑንም ገልጧል ተብሏል።

3፤ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ወገል ጤና ከተማ በቅርብ ርቀት በሚገኝ አንድ ማዕድን ማውጫ ሥፍራ ከ20 በላይ ባሕላዊ ማዕድን ቆፋሪ ወጣቶች በመሬት መደርመስ ሳቢያ ጉድጓድ ውስጥ እንደተዳፈኑ የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ልዩ ስሙ "ቆቅ ውሃ" በተባለው የኦፓል ማዕድን ማውጫ ሥፍራ የመሬት ናዳ ተከስቶ ማዕድን ቆፋሪዎቹ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ የተዳፈኑት፣ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሌሊት ላይ እንደኾነ የአካባቢው ነዋሪዎች መናገራቸውን ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ፣ ማዕድን ቆፋሪዎቹን ለማውጣት እንዳልተቻለ የዞኑ አስተዳደር ገልጧል ተብሏል።

4፤ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ዛሬ እንደገለጠ የአገር ውስጥ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አረዓያ፣ ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል በስተቀር በኹሉም ክልሎች በ1 ሺህ 400 ወረዳዎች ውይይቶች ማካሄዱን ዛሬ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩ ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ኮሚሽኑ በመጀመሪያው ምዕራፍ ያጠናቀቀው ሥራ፣ የአገራዊ ምክክር ሂደቱ ተሳታፊዎችን ልየታ ማካሄድ ነው። በቀጣዩ ምዕራፍ፣ በክልሎች፣ በፌዴራል እና በውጭ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች አጀንዳዎችን የማሰብሰብ ሥራ እንደሚሠራ የገለጡት ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን፣ አጀንዳ የማሰብሰብ ምዕራፉ ሙሉ በሙሉ ከተጠናቀቀ በኋላ የአጀንዳ መረጣ እንደሚካሄድ ማስታወቃቸው ተገልጧል።

5፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ አዲስ የተገነባውን ጎዴ ኡጋዝ ሚራድ አውሮፕላን ማረፊያ ዛሬ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ማድረጋቸውን የክልሉ ኮምንኬሽን አስታውቋል። አውሮፕላን ማረፊያው በአንድ ጊዜ አራት ቦይንግ 737 የመንገደኞች አውሮፕላኖችን ማስተናገድ እንደሚችል ቢሮው ገልጧል። ዐቢይ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሠፈሩት መልዕክት፣ አዲሱ የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናልና አውሮፕላን ማረፊያ ፍትሐሃዊ የልማት ተደራሽነትን የሚያረጋግጥ መኾኑን ገልጠዋል፡፡ የአውሮፕላን ማረፊያውን ተርሚናል ግንባታ ያከናወነው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው።

6፤ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፣ በድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያውን ግዙፍ የነዳጅ ዴፖ ሊገነባ እንደኾነ መግለጡን ካፒታል ጋዜጣ አስነብቧል፡፡ የድርጅቱ ሃላፊዎች፣ ዴፖው ከጅቡቲ የሚገባው ነዳጅ እየተራገፈ ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚሠራጭበት እርጥብ ወደብ እንዲኾን እንደታሰበ መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል፡፡ የነዳጅ ዴፖው 300 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ የመያዝ አቅም እንደሚኖረውና ግንባታውም በ16 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እንደሚያርፍ የድርጅቱ ሃላፊዎች ገልጸዋል ተብሏል። የነዳጅ ዴፖውን ለመገንባት ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የመሬት ካሳ ክፍያ እንደተፈጸመ ዘገባው አመልክቷል። ዴፖው ተገንብቶ ሲጠናቀቅ በአገሪቱ 14ኛው የነዳጅ ዴፖ የሚኾን ሲኾን፣ የዴፖው ግንባታም ከ150 ሚሊዮን ዶላር በላይ አጠቃላይ ወጪ ይጠይቃል ተብሏል።

7፤ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ዋና አዛዥ ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ፣ ጦራችን ጦርነቱን በጥቂት ቀናት ውስጥ በወታደራዊ ኃይል ሊቋጨው ይችላል በማለት ዝተዋል። ጀኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን የሚመሩት ጦር ሠራዊት ጦርነቱ በሰላም እንዳይፈታ እንቅፋት ኾኗል በማለት የከሰሱት ጀኔራል ደጋሎ፣ በቅርቡ በኹሉም ግንባሮች ከባድ ውጊያ እንደሚደረግ ተናግረዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ጀኔራል በርሃን ፈጥኖ ደራሹ ኃይል በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲገባ እንደማይፈቅዱ አስታውቀዋል። ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአገሪቱ አብዛኛው ክፍሎች ቴሌኮምንኬሽንና ኢንተርኔት የተቋረጠ ሲኾን፣ ለክስተቱ ጦር ሠራዊቱና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ርስበርሳቸው በመወነጃጀል ላይ ናቸው።

8፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ2804 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ4060 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 67 ብር ከ7383 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ0931 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ60 ከ6027 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ61 ብር ከ8148 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ማክሰኞ የካቲት 5/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይና ከሌሎች የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ባደረገው ግምገማ የሕወሃትን ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ ከስምምነት እንደተደረሰ ትናንት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ ዘንድሮ ለትግራይ የተመደበው የበጀት ድጎማ ተመሳሳይ የሕዝብ ብዛት ካላቸው ክልሎች ያነሰ ነው የሚል ቅሬታውን ለፌደራሉ መንግሥት ማቅረቡንም ጌታቸው ገልጠዋል። ጌታቸው፣ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የታሠሩ የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባላትን ጉዳይ በፍጥነት ለመፍታት መግባባት ላይ እንደተደረሰም ተናግረዋል። በኃይል በተያዙ አካባቢዎች አኹን ባለው ተጨባጭ ኹኔታ ሕዝበ ውሳኔ ማካሄድ እንደማይቻልም ጊዜያዊ አስተዳደሩ አቋሙን ለፌደራል መንግሥቱ እንዳሳወቀ ተገልጧል።

2፤ አዲስ አበባ ላይ ዕሁድ'ለት የተጀመረው የኢትዮጵያና ሩዋንዳ የሚንስትሮች የጋራ ኮሚሽን ሦስተኛ ስብሰባ አዳዲስ የትብብር ስምምነቶች ይፈራረማል ተብሎ እንደሚጠበቅ በኢትዮጵያ የሩዋንዳ ኢምባሲ አስታውቋል። የጋራ ኮሚሽኑ ስብሰባ፣ አዳዲስ የኹለትዮሽ የትብብር መስኮችን ጭምር እንደሚለይ ተገልጧል። የጋራ ኮሚሽኑ እየተወያየባቸው የሚገኙት የኹለትዮሽ የትብብር መስኮች፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ግብርና፣ መከላከያ፣ ትምህርት፣ ፖለቲካና ዲፕሎማሲያዊ ትብብር እንደኾኑ ኢምባሲው ጠቅሷል።

3፤ የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ፣ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር ለመወያየት ወደ ጅግጅጋ እንደሚያቀኑ የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ፕሬዝዳንት ቢሂ ከዐቢይ ጋር የሚወያዩት፣ ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ በተፈራረሙት የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ዙሪያ እንደኾነ ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ዐቢይ፣ ትናንት ወደ ሶማሌ ክልል አቅንተው አዲሱን የጎዴ አውሮፕላን ማረፊያ የመረቁ ሲኾን፣ ቢሂ ጅግጅጋ ስለመግባታቸው ግን የወጣ ኹነኛ መረጃ የለም። የመግባቢያ ስምምነቱ ተግባራዊ መኾን ይጀምራል የተባለበት ቀነ ገደብ አልፏል።

4፤ ትናንት በጋምቤላ ክልል አብዛኞቹ አካባቢዎች የስልክ አገልግሎት ተቋርጦ መዋሉን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች የስልክ አገልግሎቱ የተቋረጠው ሙሉ በሙሉ ሲኾን፣ በሌሎች አካባቢዎች ደሞ በከፊል እንደተቋረጠ ተነግሯል። በክልሉ የስልክ አገልግሎት ለምን እንደተቋረጠ ለጊዜው አልታወቀም። የክልሉ መንግሥትም በጉዳዩ ላይ ትናንት ያወጣው መግለጫ የለም።

5፤ ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በደረስኩበት የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ዙሪያ ሱማሊያ ያወጣችውን መግለጫ ውድቅ አድርጋለች። ሱማሊያ ስምምነቱን ሕጋዊነት የሌለው በማለት ማጣጣሏ፣ የሶማሌላንድን የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብት የሚጥስ ነው ያለችው ሶማሌላንድ፣ ከማናቸውም ነጻ አገር ጋር ስምምነት የመፈራረም መብት እንዳላት ገልጣለች። ሶማሊላንድ ይህን መግለጫ ያወጣችው፣ ተመድና አፍሪካ ኅብረት በመግባቢያ ስምምነቱ ዙሪያ "በመርህ ላይ የተመሠረተ አቋም" እንዲይዙ ሱማሊያ ለጠየቀችበት መግለጫ በሰጠችው ምላሽ ነው። [ዋዜማ]
#Alert
The Tigray multifaceted vulnerability paves the way for the Federal government to leverage its influence on the future of the region. On the other hand, TPLF needs economic and political support from PM Abiy to address the dire issues and to stay relevant. Read full briefing - http://tinyurl.com/2fmcdcwu
ለቸኮለ ማለዳ! ረቡዕ የካቲት 6/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ ኦነግ እና ኦፌኮ እስካኹን አብረውት እየሠሩ እንዳልኾነ ለሪፖርተር ተናግሯል። ኮሚሽነር ኂሩት ገ/ሥላሴ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ ኸለቱን ፓርቲዎች ማነጋገሩንና ፓርቲዎቹ ግን የምክክር ሂደቱ ውጤታማ ይኾናል ብለው እንደማያምኑ መግለጣቸውን ጠቁመዋል። ኾኖም ኮሚሽኑ ከሂደቱ ራሳቸውን ያገለሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲቀላቀሉት ጥረቱን እንደሚቀጥል ኮሚሽነር ኂሩት ገልጸዋል። ኂሩት፣ አማጺ ቡድኖችም ከኮሚሽኑ ጋር አብሮ ለመስራት አማራጭ የተከተሉትን ፓርቲዎች ፈለግ ይከተላሉ የሚል ተስፋ አለን ብለዋል።

2፤ የጠቅላይ ሚንስትሩ የገንዘብ ፖሊሲ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ ኾነው እንደተሾሙ ፎርቹን ዘግቧል። ተክለወልድ በመንግሥት ድርጅቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሐብታሙ ኃይለ ሚካኤል ፊርማ የተሾሙት፣ በተገኝወርቅ ጌቱ ምትክ ነው። ተክለ ወልድ እስከ አዲሱ ሹመታቸው ድረስ የንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር ነበሩ። በተክለወልድ ምትክ፣ የገንዘብ ሚንስትሩ አሕመድ ሽዴ የንግድ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ ኾነዋል።

3፤ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቺቡኬ ዳንዔል በተባለው በአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪነት በተከሰሰ ናይጀሪያዊ ላይ ትናንት የ12 ዓመት ጽኑ እስራት ወስኗል። ጥፋተኛው ናይጀሪያዊ፣ ባለፈው መስከረም 5 ቀን ከሌጎስ ወደ ኬንያዋ ሞምባሳ ከተማ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ከ7 ሺህ ግራም በላይ ኮኬይን ሊያሳልፍ ሲል በቁጥጥር ሥር የዋለ ነው። ተከሳሹ ዳንዔል ወንጀሉን መፈጸሙን ለፍርድ ቤቱ እንዳመነ ፌደራል ፖሊስ ገልጧል።

4፤ ደቡብ አፍሪካ፣ በምሥራቃዊ ኮንጎ ሪፐብሊክ 2 ሺህ 900 ወታደሮቿን ላንድ ዓመት ያህል እንደምታሠማራ አስታውቃለች። የደቡብ አፍሪካ ወታደሮች በኮንጎ የሚሠማሩት፣ በደቡባዊ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ጥላ ሥር ነው። የቀጠናው ማኅበረሰብ በምሥራቅ ኮንጎ ጦሩን ለማሠማራት የወሰነው፣ ባለፈው ግንቦት ነበር። ቀጠናዊው ጦር ከአማጺው "ኤም-23" ጋር ፊት ለፊት የመዋጋት ተልዕኮ ይኖረዋል። በኪንሻሳ መንግሥትና በአማጺ ቡድኑ መካከል ሰሞኑን ከፍተኛ ውጊያ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

5፤ ደቡብ አፍሪካ፣ እስራኤል በጋዛ እና ግብጽ ድንበር በራፋ መተላለፊያ ላይ ልትከፍተው ያሰበችውን ወታደራዊ ዘመቻ የሚያስቆም ውሳኔ እንዲያሳልፍ ለተመድ ፍርድ ቤት አስቸኳይ አቤቱታ አቅርባለች። እስራኤል በሚሊዮን የሚቆጠሩ የጦርነት ተፈናቃዮች በተጠለሉባት ራፋ በቅርቡ እጀምረዋለሁ ያለችው ወታደራዊ ዘመቻ፣ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ያስከትላል ተብሎ ተሰግቷል። ደቡብ አፍሪካ በፍርድ ቤቱ ካኹን ቀደም በእስራኤል ላይ በመሠረተችው የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ፣ ፍርድ ቤቱ እስራኤል የዘር ማጥፋት ወንጀልን የሚያስቀሩ ርምጃዎችን እንድትወስድ ማዘዙ ይታወሳል። [ዋዜማ]