Wazema Media / Radio
48.9K subscribers
191 photos
36 videos
7 files
934 links
Wazema Radio other contents are available either in our website/social media or FM radio stations in Ethiopia. www.wazemaradio.com
Download Telegram
This media is not supported in your browser
VIEW IN TELEGRAM
የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ይሰበሰባል
Media is too big
VIEW IN TELEGRAM
በሳዑዲ 70 ሺህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በስቃይ ላይ ይገኛሉ:: ዋዜማ ታሳሪዎቹን በቀጥታ አግኝታለች:: ይኸው
ለቸኮለ! ሰኞ ጥር 20/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በኦሮሚያ ክልል ለኹለተኛ ዙር የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጠርቶታል በተባለው የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ አድማ ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰኑ ቀናት ተግባራዊ መኾን መጀመሩን ዋዜማ ካሰባሰበቻቸው መረጃዎች መረዳት ችላለች። በምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምት ከተማ የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ጨምሮ እስከ ዛሬ እኩለ ቀን ድረስ ባንኮች፣ ንግድ ቤቶች፣ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ዝግ መኾናቸውን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። በምዕራብ ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተማ እንዲኹም መነሲቡ እና ቆንዳላ ወረዳዎች፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሻምቡ ከተማ እና የተለያዩ ወረዳዎች፣ በምዕራብ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች የተለያዩ ወረዳዎች እንዲኹም በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ከጭሮ ከተማ ወደ ድሬዳዋ መሉ ለሙሉ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴዎች መቆሙን ለማወቅ ተችሏል። በምሥራቅ ሸዋ ዞን ከአምቦ ከተማም፣ የሚወጣም ኾነ የሚገባ ተሽከርካሪ እንደሌለ ዋዜማ ባደረገችው ማጣራት የተረዳች ሲኾን፣ ወደ አዳማ እና አዲስ አበባ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ብዛትም በአንጻራዊነት መቀነሱን ምንጮች ገልጸዋል። በተጠቀሱት አካባቢዎች የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት በመሄድ ባለንብረቶች ተሽከርካሪዎቻቸውን እንዲያወጡና የንግድ ቤቶችን እንዲከፍቱ ጫና እያደርጉ እንደኾነ ዋዜማ ተረድታለች።

2፤ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ዛሬ ምሽት በኢትዮጵያና ሶማሊያ ውጥረት ዙሪያ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል። ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ ለመምከር የወሰነው፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት የተመድን ቻርተር ይጥሳል በሚል ምክር ቤቱ እንዲሰበሰብና ውሳኔ እንዲያሳልፍ በጠየቀችው መሠረት ነው። በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ፣ የተመድ የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ሃና ስርዌ ቴተ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሏል። ኢትዮጵያ ችግሩን በንግግር ለመፍታት ዝግጁ እንደኾነች ገልጥል፣ ምክር ቤቱ በጉዳዩ እንዳይመክር ባለፈው ሳምንት ለምክር ቤቱ በጻፈችው ደብዳቤ ጠይቃ ነበር።

3፤ በትግራይ ክልል የኢሮብ ማኅብረሰብ ከሚገኝባቸው ስምንት ቀበሌዎች አራቱ አኹንም ድረስ በኤርትራ ሠራዊት ቁጥጥር ስር መኾናቸውን የኢሮብ ወረዳ አስተዳደር መግለጡን ሪፖርተር ዘግቧል። የወረዳው አስተዳዳሪ ኢያሱ ምሥግና፣ ኹለቱ ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ እና ቀሪዎቹ ኹለት ቀበሌዎች ደሞ በከፊል በኤርትራ ወታደሮች ተይዘው እንደሚገኙ መናገራቸውን ዘገባው ገልጧል። 60 በመቶ የሚኾነው የብሄረሰቡ ግዛት፣ በኤርትራ ሠራዊት ቁጥጥር ስር መኾኑን አስተዳዳሪው ተናግረዋል ተብሏል። በኤርትራ ይዞታ ስር ባሉት አራቱ ቀበሌዎች የሚገኙ ሕጻናት ትምህርት እየተማሩ የሚገኙት በኤርትራ የትምህርት ሥርዓት እንደኾነና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ስር ባሉት የኢሮብ ቀበሌዎች ደሞ ትምህርት እንዳልተጀመረ ተገልጧል። አዲግራት ከተማን ከኢሮብ ጋር የሚያገናኘውን መንገድ የኤርትራ ወታደሮች እንዳፈረሱትም አስተዳዳሪው መግለጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

4፤ ተቃዋሚው እናት ፓርቲ፣ ከፍተኛ አመራሩ ደርበው ንጉሤ ባለፍው ቅደሜ ከወልዲያ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ተደርጎ ሜክሲኮ በሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መታሠራቸውን ገልጿል። ደርበው የእናት ፓርቲ የወልዲያ ቅርንጫፍ ማስተባባሪያ ቢሮ ተጠሪ መኾናቸውን ጠቅሷል። የታሳሪውን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተለ መኾኑን የገለጸው ፓርቲው፣ ደርበው ጥር 8 ምሽት በጸጥታ ኃይሎች ከቤታቸው ተወስደው በወልዲያ ስታዲየም መታሰራቸውን ከቀናት በፊት አስታውቆ ነበር። የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች አመራሩን ለምን እንዳሠሯቸው ፓርቲው አልገለጠም።

5፤ ኢትዮ ቴሌኮም በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍሎች በኹለት ከተሞች አምስተኛውን ትውልድ የኢንተርኔት አገልግሎት ዛሬ መጀመሩን አስታውቋል። ኩባንያው ዛሬ ፈጣኑን የኢንተርኔት አገልግሎት የጀመረው፣ በሐረር እና ሐሮማያ ከተሞች መኾኑን ገልጧል። ኩባንያው ባለፈው ቅዳሜ፣ በድሬዳዋ ከተማ አምሰኛውን ትውልድ የኢንተርኔት አገልግሎት መጀመሩ ይታወሳል።

6፤ የሱዳን ወታደራዊ መሪ ጀኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን፣ አልጀሪያ የሱዳኑን ጦርነት እንዲቆም ቁልፍ ሚና እንድትጫዎት መጠየቃቸውን የሱዳን ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ጀኔራል ቡርሃን ለአልጀሪያ ጥያቄውን ያቀረቡት፣ ትናንት ወደ አልጀርስ ተጉዘው ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት አብዱልመጂድ ተቡኔ ጋር ከተወያዩ በኋላ በሰጡት የጋራ መግለጫ ላይ ነው። ፕሬዝዳንት ተቡኔ፣ የሱዳኑ ጦርነት እንዲያበቃ የአፍሪካም ኾኑ የዓረብ አገራት በሚያስተባብሯቸው የሰላም ንግግር ጥረቶች ውስጥ አስተዋጽኦ ለማድረግ ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ማረጋገጫ መስጠታቸውን ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ጀኔራል ቡርሃን፣ አንዳንድ ቀጠናዊና ዓለማቀፋዊ ኃይሎች ሱዳንን ለማፍረስ እያሴሩ ነው በማለት በመግለጫቸው ላይ ከሰዋል ተብሏል። አልጀሪያ ለቀጣዮቹ ኹለት ዓመታት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ኾና በቅርቡ መመረጧ ይታወሳል።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ1522 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ2752 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 68 ብር ከ3402 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ7070 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ61 ከ0431 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ2640 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ማክሰኞ ጥር 21/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የብቃት ምዘና ከወሰዱ 3 ሺህ 861 የሦስት ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ምዘናውን ያለፉት 1 ሺህ 680 ወይም 44 ነጥብ 39 በመቶዎቹ ብቻ እንደኾኑ አስታውቋል። ተፈታኞቹ ከመሬት ይዞታ፣ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ቢሮ፣ ከመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮና ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተውጣጡ እንደኾኑ የከተማዋ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ገልጧል። ምዘናውን ያለፉት፣ ከማዕከል አስከ ቅርንጫፍ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች በሚገኙ ጽሕፈት ቤቶች እንደሚደለደሉ ተነግሯል። ከ30 አስከ 35 በመቶ ውጤት የሚያዘው ከመመዘኛ ፈተናው ውጤት መኾኑን የገለጠው፣ ቀሪው የሥራ አፈጻጸም፣ የሥራ ልምድና ስነ ምግባር መሠረት ያደረገ ይኾናል ብሏል።

2፤ በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ታስረው የቆዩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ክርስቲያን ታደለና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባሉ ዮሃንስ ቧያለው ዕሁድ'ለት ወደ አዲስ አበባ መዛወራቸውን ቢቢሲ አማርኛ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል። ኸለቱ ግለሰቦች ባኹኑ ወቅት ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ታስረው እንደሚገኙ መስማቱን ዘገባው ጠቅሷል። የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባሉ ካሳ ተሻገር እና የበይነ መረብ ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ደሞ፣ ለሕክምና ከአዋሽ አርባ ወደ አዲስ አበባ የተዛወሩት ከኹለት ሳምንት በፊት እንደኾነ ምንጮች መናገራቸውን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል። ካሳ ለሕክምና ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ዋዜማ ባለፈው ሳምንት መዘገቧ ይታወሳል።

3፤ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሞባይል ኤምፔሳ አገልግሎት ተመዝጋቢዎች ቁጥር በአራት ወራት ውስጥ በሦስት እጥፍ ጨምሮ ወደ ሦስት ነጥብ 1 ማሽቀቡን ቢዝነስ ደይሊ ዘግቧል። ኤምፔሳ በመስከረም መጨረሻ የነበረው የደንበኞች ብዛት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ነበር። ኩባንያው፣ ከተጀመረበት ነሃሴ እስከ መስከረም መጨረሻ ያዘዋወረው የገንዘብ መጠን 18 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ሲኾን፣ ገንዘቡ በታኅሳስ መገባደጃ ላይ ወደ 115 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ማደጉን ዘገባው ጠቅሷል። ኩባንያው፣ ከኤምፔሳ አገልግሎቱ ከነሃሴ እስከ ታኅሳስ መጨረሻ ድረስ 280,625 ዶላር ገቢ አስገብቷል ተብሏል።

4፤ የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በሕገወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ በተሽከርካሪ ሲገቡ የነበሩ 25 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞችን ቅዳሜ'ለት በቁጥጥር ስር ማዋሉን የዚምባብዌው ክሮኒክል ጋዜጣ ዘግቧል። ኢትዮጵያዊያኑ ፍልሰተኞች ከዚምባብዌ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲገቡ የተያዙት፣ በኹለት ተሽከርካሪዎች ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች እንደኾኑ በተጠረጠሩ የታጠቁ ግለሰቦች ታጅበው እንደኾነ ዘገባው አመልክቷል። ፍልሰተኞቹ ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 40 መኾኑን የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ መናገሩን የጠቀሰው ዘገባው፣ በሕገወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ በመግባት ክስ እንደተመሠረተባቸው አመልክቷል።

5፤ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ትናንት ምሽት በኢትዮጵያና ሱማሊያ ውዝግብ ላይ መክሯል። ከምክር ቤቱ ስብሰባ ቀደም ብሎ የምክር ቤቱ የወቅቱ ሊቀመንበር ፈረንሳይ፣ አፍሪካዊያኑን የምክር ቤቱ ተለዋጭ አባላት አልጀሪያን፣ ሞዛምቢክንና ሴራሊዮንን እንዲኹም ጉያናን በጉዳዩ ዙሪያ በዝርዝር ያማከረች ሲኾን፣ አራቱ አገራትም ኢትዮጵያንና ሱማሊያን ማነጋገራቸው ተገልጧል። ዓረብ ሊግና የእስልምና አገራት ካውንስል፣ የሱማሊያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንዲከበር ለጸጥታው ምክር ቤት ቀደም ሲል ደብዳቤ አስገብተው ነበር። ከዓረብ አገራት መካከል፣ የጸጥታው ምክር ቤት አባል የኾነችው አልጀሪያ ብቻ ናት። የስብሰባው ውጤት ይህን ዘገባ እስካጠናቀርንበት ሰዓት ድረስ አልተገለጠም።

6፤ የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትር ጆርጂያ ሜሎኒ፣ ጣሊያን ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ለኢንቨስትመንት የ5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዩሮ መመደቧን አስታውቀዋል። ጣሊያን የመደበችው ገንዘብ፣ የኢነርጂ ትስስሮችን ለማጎልበትና ሕገወጥ ስደትን ለመቆጣጠር የሚውል እንደኾነ ተገልጧል። ሮም ላይ ለኹለት ቀናት በተካሄደው የጣሊያንና አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይንና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ የ25 አገራት መሪዎች ተሳትፈዋል።[ዋዜማ]
ለቸኮለ! ማክሰኞ ጥር 21/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በራያ የሚገኙ ስድስት ወረዳዎች ሕዝበ ውሳኔ ተደርጎ የማንነት ጥያቄያቸው ባለመፈታቱ ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን የኮረም ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ገብረ እግዚዓብሔር ደረጀ ለዋዜማ ተናግረዋል። ባለፈው ነሐሴ በቅርቡ ሕዝብ ውሳኔ ይደረጋል በሚል ከመከላከያ ሠራዊት አመራሮች ጋር ውይይት ተደርጎ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው፣ ከዚያ በኋላ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳልተደረገ ተናግረዋል። የፌደራል መንግሥቱ ከጦርነቱ በኋላ ለትግራይ ክልል የተለያዩ ድጎማዎችን ሲያደርግ ራያን ለይቶ ትቶታል ያሉት ኃላፊው፣ ባኹኑ ወቅት የአካባቢው አስተዳደር የሚንቀሳቀሰው የአማራ ክልላዊ መንግሥት በሚያደርግለት ውስን ድጎማ ነው ብለዋል። በበጀት እጥረት ምክንያት የጤና ተቋማት የተሟላ አገልግሎት እንደማይሰጡ፣ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት መኖሩን እንዱኹም የወደሙ የትምህርት ቤቶች አለመጠገናቸውንና የመንገድና ሌሎች መሠረት ልማት ማስፋፊያዎች አለመኖራቸውን ኃላፊው ገልጸዋል። ሕዝብ ውሳኔ እንዲደረግላቸው የሚጠየቁት፣ በዋግኽምራ ዞን ሥር የኮረም ከተማ አስተዳደር፣ ወፍላ እና ዛታ ወረዳዎች እንዲኹም በሰሜን ውሎ ዞን አላማጣ ከተማና ራያ አላማጣ እና ራያ ባላ ወረዳዎች መኾናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

2፤ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ ነቀምት ካምፓስ ከትላንት ጀምሮ ይህ ዜና እየተጠናቀረ እስካላበት ዛሬ እኩለ ቀን ድረስ የመማር ማስተማር ሂደት ሙሉ ለሙሉ መቋረጡን ዋዜማ ከምንጮቿ ባሰባሰበችው መረጃ አረጋግጣለች። ዩኒቨርሲቲው ሦስት ካምፓሶች ያሉት ሲኾን፣ ከዋናው ግቢ ነቀምት ካምፓስ በስተቀር በሻምቡና ጊምቢ ካምፓሶች መደበኛው የመማር ማስተማር ሂደት እየተካሄደ እንደኾነ ምንጮች ለዋዜማ ገልጸዋል። በነቀምት ካምፓስ የመማር ማስተማር ሂደቱ የተቋረጠው፣ ሰሞኑን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በመላው ኦሮሚያ ጠርቶታል የተባለውን የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ የማስቆም አድማን ተከትሎ ተማሪዎች አንማርም ብለው በማመጻቸው እንደኾነ ዋዜማ ተረድታለች።

3፤ ኢሰመጉ በአማራና ትግራይ ክልሎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ወደቀያቸው ባለመመለሳቸው ለሞት፣ ለከፍተኛ ርሃብ እና የተለያዩ ሰብዓዊ ቀውሶች ተጋልጠዋል ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ገልጧል። ኢሰመጉ፣ በትግራይ ክልል በሽረ፣ አክሱም፣ አቢአዲ፣ መቀሌ እና አዲግራት ከተሞች የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ የረድዔት ድርጅቶች የምግብ ዕርዳታ በመቋረጡና የፌደራሉና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በቂ ሰብዓዊ ድጋፍ ባለማቅረባቸው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በርሃብ ለሞት እንደተዳረጉ አረጋግጫለኹ ብሏል። በአማራ ክልልም በማዕከላዊ ጎንደር፣ በደቡብ ወሎ፣ በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን፣ በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞንና በሰሜን ጎንደር ዞን የጃናሞራና ጠለምት አካባቢዎች፣ ከባድ ድርቅ እንደተከሰተ ኢሰመጉ አስታውቋል።
በድርቁ ሳቢያ በርካታ ሰዎችና እንስሳት እየሞቱ ነው ያለው ኢሰመጉ፣ ባካባቢዎቹ ባለው የጸጥታ ኹኔታ ሳቢያ በቂ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ እንዳልተቻለ መረዳቱንም ኢሰመጉ ጠቅሷል።

4፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በትግራይና በአማራ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅና ድርቁ የደረሰውን ሰብዓዊ ጉዳት አስመልከቶ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ በትግራይ ማዕከላዊ ዞን 351 ሰዎች በምግብ እጥረት ሲሞቱ፣ 15 ሺሕ 565 ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ገልጧል። በርካታ ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መኾናቸውን ተቋሙ አስታውቋል። በአማራ ክልልም፣ በድርቅ ከ325 ሺህ በላይ መሬት ከምርት ውጪ መኾኑ፣ በዘጠኝ ዞኖች ከ 1 ሚሊዮን 800 ሺሕ በላይ ዜጎች ለከፋ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ እንደተዳረጉና ከ26 ሺህ በላይ ሰዎች በወባና ኮሌራ በሽታዎች መጠቃታቸውን ኢሰመጉ ጠቅሷል። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙና በቂ የሆነ ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዳልኾነም ኢሰመጉ ገልጧል።

5፤ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር፣ ከአፋር ክልል አሳይታ ከተማ በአፋምቦ በኩል ከጅቡቲ ድንበር ጋር የሚያገናኘው የመንገድ ግንባታ መጠናቀቁን አስታውቋል። አዲሱ መንገድ የ50 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ እንዳለው አስተዳደሩ ገልጧል። መንገዱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያን በአሳይታ በኩል ከጅቡቲ ጋር ከማገናኘት በዘለለ፣ የአገሪቷን የገቢ እና ወጪ ንግድ ይበልጥ ለማቀላጠፍ እንደሚያስችል ተገልጧል። የመንገድ አስተዳደሩ፣ አዲሱ መንገድ ከአፋር ክልል ሚሌ ከተማ በዲቼ ኦቶ እና ጋላፊ በኩል እስከ ጅቡቲ ወደብ የሚያገናኘውን ነባሩን መንገድ በ30 ኪሎ ሜትር ያሳጥረዋል ተብሏል። የመንገዱ ግንባታ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት የጠቀሰው አስተዳደሩ፣ ወጪውን ሙሉ ለሙሉ የሸፈነው የኢትዮጵያ መንግሥት እንደኾነም ገልጧል።

6፤ በአሜሪካ ሕግ መምሪያ የእንደራሲዎች ምክር ቤት አባል ትውልደ ሱማሊያዊቷ ኢልሃን ኦማር፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ተፈጻሚ ሊኾን አይችልም በማለት መናገራቸውን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ኢልሃን ኦማር ሚኖሶታ ግዛት ውስጥ ለሱማሊያዊያንና ትውልደ ሱማሊያዊያን በሱማሊኛ ቋንቋ ባደረጉት ንግግር፣ እኔ የአሜሪካ ኮንግሬስ ውስጥ ተቀምጩ የሱማሊያን መሬት ማንም ፈጽሞ ሊወስደው አይችልም በማለት መዛታቸውን ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ሱማሊያ ድሮ የተወሰዱባት ግዛቶች አሉ ያሉት ኦማር፣ አንድ ቀን ግዛቶቻችን እናስመልሳለን በማለት መዛታቸውንም ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። የኦማር ዛቻ፣ የኢትዮጵያው ኦጋዴንና የሰሜናዊ ኬንያ አካባቢዎች የታላቋ ሱማሊያ አካል ናቸው የሚለውን የተስፋፊውንና ወራሪውን የቀድሞው የሱማሊያ ወታደራዊ መሪ ጀኔራል ዚያድ ባሬን ፖሊሲ የሚያራምድ ነው በሚል በርካታ ትችት እየተሰነዘረባቸው ይገኛል።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ1612 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ2844 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 68 ብር ከ0722 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ4336 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ60 ከ7608 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ61 ብር ከ9760 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ረቡዕ ጥር 22/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1-ሂውማን ራይትስ ዎች የዓለም እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ጥር 19 ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የሰጠው ሽልማት በአገሪቱ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ እና በጦርነት ጊዜ የተፈጸሙ ግፎችን ችላ ያለ ነው ሲል ትናንት ባወጣው መግለጫ ከሷል። ተቋሙ፣ በኢትዮጵያ ካለው አስከፊ ሰብዓዊ ቀውስ እና መጠነ ሰፊ የምግብ ዋስትና እጦት አንጻር ሽልማቱ ያልተጠበቀ ነውም ብሏል። የኢትዮጵያ አደጋ መከላከል ኮሚሽን በቅርቡ ካወጣው መረጃ; ለኹለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ሳቢያ በሰሜን ኢትዮጵያ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲሁም በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎችም ብዙ የተራቡ ዜጎች መኖራቸውን ተረድቻለሁ ብሏል። ተቋሙ፣ የዓለም መሪዎች መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ስለሚታገሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አስከፊ የሰብዓዊ ቀውሱ እውነታ; እንዲኹም በመንግሥት አካላት ሆን ተብለው ስለሚወሰዱ ቀውሱን የሚያባብሱ እርምጃዎችን መገንዘብ ይኖርባቸዋል ሲል ገልጿል። ፋኦ፣ ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ "አግሪኮላ" የተባለውን ትልቁን ሽልማቱን የሰጣቸው፣ በምግብ ዋስትና፣ በግብርና ምርታማነት እና የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦትን ለማሳደግ ላሳዩት አመራር እና ቁርጠኝነት እንደኾነ መግለጡ ይታወሳል።

2- ኢትዮጵያ ከሱማሊላንድ ጋር የደረሰችበትን የባህር በር ስምምነት በተመለከተ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ስብሰባ እንዲጠራ ጠይቃለች:: ኢትዮዽያ በአወዛጋቢው የሱማሊላንድ ስምምነት ዙሪያ ለአባል አገራት ጉዳዩን ማብራራት እንደምትፈልግ መግለጿን ብሉምበርግ ዘግቧል:: ኢትዮጵያ በስምምነቱ ዙሪያ ብርቱ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ የገጠማት ሲሆን፣ ጉዳዩን ከሱማሊያ ጋር በውይይት ለመፍታት እንደምትፈልግ ስትገልፅ ቆይታለች:: ሱማሊያ ግን ስምምነቱ ካልተሰረዘ ድርድር አይታሰብም ብላለች::

3- በብሔራዊ ባንኩ ገዢ ማሞ ምህረቱ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ; በሞስኮ እየተካሄደ ባለው የብሪክስ አባል አገራት የተወካዮች ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ እንደሚገኝ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ገልጿል። ማሞ፣ በስብሰባ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር; ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል አገራት ጋር ተቀራርቦ በመስራት የኢኮኖሚ አጋርነቷን ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን እና የብሪክስን የኢኮኖሚ አጋርነት ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ በንቃት እንደምትሳተፍ መግለጻቸውንም ሚኒስቴሩ ጠቅሷል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በጤና፣ በትምህርት፣ በሳይንስ፣ በግብርና፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢነርጂ እና በአየር ንብረት ለውጥ ዘርፎች የተለያዩ የብሪክስ የትብብር መድረኮችን ለመቀላቀል ፍላጎት እንዳላት በስብሰባው መናገራቸው ተመላክቷል። ማሞ፣ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ከአባል አገራቱ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማሳደግ፣ የተረጋጋ እና ተገማች የገበያ ሁኔታን ለመፍጠር እንዲሁም የመሰረተ ልማት የፋይናንስ አቅርቦት ክፍተተን ለመሙላት እና የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለማዘመን ዕድል እንደሚፈጥር መግለጻቸውንም ሚኒስቴሩ ገልጿል። በሞስኮ እየተካሄደ ያለው የብሪክስ የተወካዮች መደበኛ ስብሰባ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ከሆነች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችበት ጉባኤ ነው።

4-በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት; በኢትዮጵያ የሙስና ወንጀሎች መጨመራቸውን ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ተቋም ገልጧል። ተቋሙ ትናንት ይፋ ባደረገው ሪፖርት; ኢትዮጵያ በመመዘኛዎቹ ከመቶ 37 ነጥብ በማግኘት ከ180 አገራት 98ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን አስታውቋል። እ.ኤ.አ. በ2022 ተቋሙ ባደረገው ጥናት ኢትዮጵያ በሙስና ነክ ወንጀሎች ልኬት ከዓለም 94ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ እንደነበር ገልጿል። በ180 አገራት ውጤት መሠረት የሙስና ውጤት 43 ነጥብ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ከአማካኝ በታች በስድስት ነጥብ ዝቅ ብላ እንደምትገኝ ተጠቁሟል።

5- በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች አገር ውስጥ እንዳደይገቡ በመከልከል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ብቻ እንዲገቡ ይደረጋል በሚል የተሰራጨው መረጃ ትክክል እንዳልሆነ የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሕግ አማካሪ ዋሲሁን አባተ ለሪፖርተር ተናግረዋል። ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ማገድ በዓለም የንግድ ድርጅት ሕግ መሠረት የማይቻል ነው ያሉት አማካሪው; የአገሪቱን የቀረጥ ሥርዓት በመጠቀም ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚጠቅሙትን ማበረታት፣ ጎጂ የሆኑትን ደግሞ እንዳይስፋፉ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡ በገንዘብ ሚንስቴር በኩል ያለው አሰራር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ ለማበረታታት እና በነዳጅ የሚሠሩት በብዛት እንዳይገቡ ለማድረግ ብቻ እንደሆነም ዋሲሁን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥቅምት 4/2015 ዓ.ም ይፋ እንዳደረገው ወደ አገር እንዳይገቡ ክልከላ ከተደረገባቸው 38 ምርቶች ውስጥ በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችን አላካተተም ሲሉም ጨምረው ተናግረዋል። የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ; ከትላንት በስቲያ የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ በነዳጅ የሚንቀሳቀሱ አውቶሞቢሎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ውሳኔ መተላለፉን መናገራቸው ይታወሳል።

6- በአሜሪካ ሕግ መምሪያ የእንደራሴዎች ምክር ቤት አባል ትውልደ ሶማሊያዊቷ ኢልሃን ኦማር፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት በመቃዎም የሰነዘሩትን ሀሳብ ተከትሎ፣ የፍሎሪዳ ግዛት አስተዳዳሪ ሮን ዲሳንቲስ ኦማር ከአሜሪካ እንዲባረሩ መጠየቃቸውን የውጭ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ዲሳንቲስ ኦማር ከአሜሪካ ኮንግሬስ አባልነታቸው ብቻም ሳይሆን፣ ከአሜሪካ ጭምር መባረር አለባት ማለታቸውን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። የምክር ቤቱ አባል ቶም ኢመር በበኩላቸው ኦማር ለአሜሪካ ሕዝብ ለመስራት ቃለመሃላ መፈፀማቸውን ጠቅሰው፣ “አስደንጋጭ ንግግሯን ተከትሎ በሃፍረት ከአባልነቷ ልትለቅ ይገባል” ሲሉ በ”ኤክስ” ገፃቸው ገለፀዋል። የሱማሌላንድ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ርሆዳ ኢልሚ በተመሳሳይ በ”ኤክስ” ገጻቸው፣ የምክር ቤት አባል የሆኑት ኦማር ሕዝባዊ መድረክ ላይ ያደረጉት ንግግር የሚያበሳጭ ነው ብለዋል። የኦማር ንግግር “የሶማሌላንድ እና አሜሪካን ትብብር የዘነጋ እንዲሁም ለብዙ ሞትና ጥፋት ምክንያት የሆነውን የታላቋን ሶማሊያ ትርክት የሚያስተጋባ ነው” ብለውታል። ኢልሃን ኦማር በቅርቡ በአሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት ውስጥ ለሶማሊያዊያንና ትውልደ ሶማሊያዊያን በሶማሊኛ ቋንቋ ባደረጉት ንግግር፣ “እኔ የአሜሪካ ኮንግሬስ ውስጥ ተቀምጩ የሶማሊያን መሬት ማንም ፈጽሞ ሊወስደው አይችልም” ብለዋል።

7- የሱዳን ጦር ዋና አዛዥ ጄኔራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን ሠራዊቱ እና ተባባሪ የታጠቁ ቡድኖች የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ መጠነ ሰፊ የጥቃት ዘመቻ እንዲከፍቱ ትዕዛዝ መስጠታቸውን የሱዳን የዜና ምንጮች ዘግበዋል። አልቡርሃን በካሳል ግዛት ተገኝተው ለወታደሮቹ ባደረጉት ንግግር፣ ከዚህ በኋላ ከዳርፉር፣ ምስራቃዊ፣ ማዕከላዊ እና ሰሜናዊ ግዛቶች በመነሳት በኹሉም አቅጣጫ ከመከላከል ወደ ማጥቃት እንሻገራለን ማለታቸውንም ዘገባው አመልክቷል።አልቡርሃን ጦርነቱ በፈነዳ ጊዜ ወታደሮቻቸው ለመከላከል የሚያደርጉት እርምጃ ቅድሚያ እንዲሰጡ እና ከማጥቃት እርምጃ እንዲቆጠቡ ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ፦ ሐሙስ ጥር 23 2016 ዓ/ም የዋዜማ ዜናዎች

1. የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን፣ ተፈኗቅዮች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱና ከፌደራል መንግስቱ ጋር ውይይት እንዲጀመር የትግራይ ተወላጆች ግፊት እንዲያደርጉ የትግራይ ክልል የቀድሞው ገዥ ፓርቲ ሕወሓት ጠየቀ። የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ለ40 ቀናት ያደረገውን ጉባዔ ሲያጠናቅ ቅ ባወጣው መግለጫ የትግራይ ክልል ሉዐላዊነት እንዲከበርና በጦርነቱ ወቅት የመብት ጥሰት የፈፀሙ በዓለማቀፍ ደረጃ እንዲጠየቀ መደረግ አለበት ብሏል። ከኤርትራ ሕዝብ ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለመቀጠል ዝግጁነቱን ገልፆ፣ በመላው አለም የሚኖሩ ኤርትራውያን የኤርትራ ጦር ከትግራይ ሙሉ በሙሉ ለቆ እንዲወጣ ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቋል።

2. በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስር ያለው ሞሐ የለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ በፀጥታ ችግር ምክንያት ሦስት ፋብሪካዎቹን ሥራ ማስጀመር አልቻልኩም ማለቱን ካፒታል ጋዜጣ ዘግቧል። የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አካለወልድ አድማሱ፣ ባለዉ የፀጥታ ችግር ምክንያት ሦስቱን ፋብሪካዎች ሥራ አልጀመሩም ማለታቸውን ዘገባው ገልጿል። አካላወልድ ለሦስቱ ፋብሪካዎች ጥሬ እቃ መጓጓዝና ምርቱን ማከፋፈል እንዳልተቻለ መናገራቸው የጠቀሰው ዘገባው፣ የሞሐ ለስላሳ መጠጦች ኢንዱስትሪ በተቀሩት ፋብሪካዎቹ በተወሰነ ደረጃ ምርት መጀመሩን አመልክቷል።

3. ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሶስት አዳዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕውቅና (የምዝገባ ሰርተፍኬት) ሰጠ። ዕውቅና የተሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ‘የወሎ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ’ (ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ) ፤‘የኩሽ ህዝቦች ብሔራዊ ንቅናቄ’ (ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ) እና ‘ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ’ ( ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ) ነው፡፡

4. ኬንያ 2 ቢሊየን ዩሮቦንድ ልትገዛ ነው። ኬንያ 300 ሚሊየን ዶላር ዩሮቦንድ ባለፈው ሐምሌ ወር ልትገዛ አቅዳ በወለድ መብዛት ሳቢያ ሳይሳካ መቅረቱት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ለሮይተርስ ተናግረዋል። አሁን ያለው የገበያ ሁኔታ የሚያደፋፍር ስለሆነ ቢበዛ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ኬንያ 2 ቢሊየን ዩሮ ቦንድ ለመግዛት ወስናለች። ዕዳዋን መክፈል ያቅታት እንደሆነ የተጠየቀት ሩቶ፣ የሚያሰጋን ነገር የለም ብለዋል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! የጥር 23 ቀን 2016 ዓም የዋዜማ ዜናዎች

1-የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ትናንት ምሽት በፌደራል ፖሊስ አባላት ተወስደው መታሰራቸውን የአገር ውስጥ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። ደሳለኝ ምሽት 3 ሰዓት ተኩል ላይ በፖሊስ አባላቱ ለጥያቄ ትፈልጋለህ በሚል ከመኖሪያ ቤታቸው ተወስደው ሜክሲኮ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ታስረው እንደሚገኙ የቅርብ ቤተሰባቸው መናገሩን ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ዛሬ ጠዋትም መኖሪያ ቤታቸው በፌደራል ፖሊስ አባላት ፍተሻ እንደተደረገበት የዜና ምንጮቹ ጠቅሰዋል። ተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን ወክለው በ6ኛው አገራዊ ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ደሳለኝ፣ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ለእስር የተዳረጉ ኹለተኛው የፓርቲው የምክር ቤት አባል ሆነዋል።

2-በኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት ለመፍታት እና በፋኖ ታጣቂዎች እና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ድርድር እንዲካሄድ ለመገፋፋት “ፍላጎታችን ነው” ሲሉ በአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሃመር; በበይነ መረብ በተካሄደ አንድ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ መናገራቸውን ቪኦኤ ዘግቧል። በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መሥተዳድር ጌታቸው ረዳ: በክልሉ ላንዣበበው ከባድ ረሃብና ለወደመው መሰረተ ልማት መልሶ ግንባታ ዲያስፖራው ድጋፍ እንዲያደርግ መማጸናቸውን ሃመርም የሚደግፉት ሃሳብ እንደሆነ በዘገባው ተጠቅሷል። ሃመር; ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ከተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ጋራ በተያያዘ፣ ከሶማሊያ ጋራ የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ያነሡ ሲሆን፣ የቀንዱ አገራት አካባቢው የማይችለውን ሌላ ግጭት እንዲያስወግዱ ጥሪ ማቅረባቸውም ተጠቅሷል።

3-የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሻምቡ ካምፓስ ከዛሬ ጥር 23/2016 ዓ.ም. ማለዳ ጀምሮ ይህ ዜና እየተጠናቀረ እስካለበት ሰዓት ድረስ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሙሉ ለሙሉ መቋረጡን ዋዜማ በስፍራው ካሉ ምንጮቿ አረጋግጣለች፡፡ "ተማሪዎች ወደ መማሪያ ክፍል ገብተው እንዳይማሩ" የሚልና ሌሎችንም መልዕክቶችን ያካተተ በራሪ ወረቀት በግቢው ወስጥ ለሊቱን መታየቱንም ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች ከካምፓሱ ቅጥር ግቢ መውጣት እንደማይፈቀድላቸው የተገለጸ ሲሆን; በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች በኩል ተማሪዎች ወደ መማሪያ ክፍሎቻቸው ገብተው እንዲማሩ ጫና እየተደረገ እንደሆነ ምንጮች ለዋዜማ አስረድተዋል፡፡ በግቢው የመማር ማስተማር ሂደቱ የተቋረጠው ሰሞኑን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በመላው ኦሮሚያ ጠርቶታል የተባለውን አድማ ተከትሎ እንደሆነ ዋዜማ መረዳት ችላለች።

4- ሕወሓት በድጋሚ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዕውቅና ሰርተፍኬት እንዳገኘ ተደርጎ የሚሰራጨው መረጃ ሐሰተኛ መሆኑን ቦርዱ ኮምኒኬሽን የስራ ክፍል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል:: ባገኘነው መረጃ ሕወሓት ከሁለት ዓመት በፊት በህገወጥነት ተፈርጆ የምዝገባ ሰርተፍኬቱ ከተሰረዘ ወዲህ አዲስ ምዝገባ አድርጎ ዕውቅና አላገኘም። በማህበራዊ ሚዲያ እየተሰራጨ ያለው መረጃም ሐሰተኛና አሳሳች ነው። ቦርዱ ከትናንት በስቲያ ለሌሎች ሶስት አዳዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕውቅና መስጠቱን አስታውቆ ነበር። 

5-የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አሥተዳደር; በ2016 ዓ.ም. በጀት ዓመት የመጀመሪያ መንፈቅ; ከፍተኛ የአደጋ ደረጃ ያላቸው የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መፈፀማቸውን ገልጿል፡፡ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ; ከ2015 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር በ115 በመቶ መጨመሩን ገልፀዋል፡፡
በዚኽኛው በጀት ዓመት የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት; በአጠቃላይ 4 ሺሕ 623 የሳይበር ጥቃቶቸ መመዝገባቸውን የገለጹት ሰሎሞን; ከዚህ ውስጥ 130ዎቹ የተሳኩ የሳይበር ጥቃቶች ናቸው ብለዋል። እነዚህን የሳይበር ጥቃቶች በመለየት 98.56 በመቶ የሚሆኑትን ምላሽ ተሰጥቶባቸው የተጠናቀቁ ሲሆን; 1.44 በመቶ የሚሆኑት በሂደት ላይ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ በዚህም አገሪቱ ላይ ሊደርስ የነበረውን ከ10 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ከኪሳራ ማዳን ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት፣የጸጥታ እና ደኅንነት ተቋማት፤መገናኛ ብዙኃን፤ቁልፍ የመንግሥት ተቋማት፤ ሚንስቴር መሥሪያ ቤቶች፤ የክልል ቢሮዎች፤ የሕክምና እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የጥቃቱ ዒላማ እንደነበሩም ጠቁመዋል፡፡

6-የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት; ከቀደመው ሚያዚያ ወር አጋማሽ ጀምሮ በኩምሩክ ኬላ በኩል ከ20 ሺሕ በላይ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂ ሱዳናውያን ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ለዋዜማ በላከው መግለጫ ገልጿል። የተቋሙ ዳይሬክተር ጠይባ ሃሰን እና የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዴ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚገኘውን የአሶሳ የስደተኞች መጠለያ መጎብኘታቸውን የገለጸው ተቋሙ፣ ኮሚሽነር ፍሊፖ; ኢትዮጲያ አንድ ሚሊየን ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በመቀበሏ ምስጋና ማቅረባቸውን ጠቅሷል። በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የሱዳን ስደተኞችን አኹን ካሉበት ወደተሻለ ቦታ ለማዛወር እና በአጭር እና በረዥም ጊዜ ችግሮችን ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን ተቋሙ በመግለጫው ጠቁሟል። ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ የተቀሰቀሰውን የሱዳንን የእርስ በእርስ ጦርነት ተከትሎ፣ በአማራ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በኩል በየቀኑ በርካታ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ እንደሆነ ሲዘገብ ቆይቷል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ፦ ዓርብ ጥር 24 2016 ዓ/ም የዋዜማ ዜናዎች

1. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለስድስት ወራት የቆየውን የአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማራዘም ዛሬ ስብሰባ መጥራቱን ዋዜማ ከምክር ቤት አባላት ሰምታለች። ዋዜማ ያነጋገረቻቸው አንድ የምክር ቤቱ አባል፣ ዛሬ በተጠራው ልዩ ስብሰባ የመጀመሪያው አጀንዳ የአማራ ክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማራዘመ መሆኑን ተናግረዋል። በዚሁ አጀንዳ ላይ በትናትናው ዕለት የብልጽግና ፓርቲ የሆኑ የምክር ቤት አባላት ተሰብስበው እንደነበር ገልጸዋል። ምክር ቤቱ በአማራ ክልል ነሐሴ 08 ቀን 2015 ዓ.ም ያጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ቀነ ገደቡ ጥር 8 2016 ዓም ተጠናቋል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከማራዘም በተጨማሪ፣ ፕላንና በጀትን በተመለከት አዋጅ፣ ብሔራዊ በዓላትን እንዲሁም ኒሻንና ሜዳይን የሚመለከቱ አጀንዳዎች ላይ እንደሚወያይ ለዋዜማ አስረድተዋል።

2. የፍትህ ሚንስትር ጌዴዎን ጢሞቲዎስ የአገር ሃብት ይዘው ወደ ውጪ አገራት የሚኮበልሉ ተጠርጣሪዎች በብዛት የሚኮበልሉባቸው አገራትን በመለየት በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ስምምነቶች እየተፈፀሙ መሆኑን ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት መናገራቸውን ም/ቤቱ ገልጿል።
ሚንስትሩ፣ ሃብት ይዘው የሚሸሹ ተጠርጣሪዎች በብዛት ከሚኮበልሉባቸው አገራት የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እና ደቡብ አፍሪካ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡ የኦዲት ግኝት ያለባቸውን ተቋማት ተጠያቂ ለማድርግ ደግሞ በዘርፉ ዕውቀትና እና ልምድ ያለው የሰው ሃይል ዕጥረት መኖሩን ጠቅሰዋል። ሚንስትሩ ባቀረቡት ሪፖርት በአገር አቀፍ ደረጃ፣ 107 ሺሕ 260 ታራሚዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሸዋሮቢት እና ዝዋይ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል።

3. የፍትሕ ሚንስትሩ ጌዲዎን ጢሞቲዎስ ለፓርላማው ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት የግል የመገናኛ ብዙሀን ወደ ስብሰባው እንዳይገቡ መከልከላቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘግቧል። ፓርላማው በዝግ እንዲካሄድ ውሳኔ ያልሰጠበትን የፍትሕ ሚንስትሩን ሪፖርት አምስት መንግስታዊ ሚዲያዎች ብቻ እንዲዘግቡ ተፈቅዶ ሌሎች መመለሳቸውን ዘገባው ገልጿል። ፓርላማው ስብሰባዎቹን ባማህበራዊ ሚዲያ ጭምር በቀጥታ ሲያስተላልፍ መቆየቱ ይታወሳል።

4.የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ለማድረግ መንግሥት ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖረውም ቆጠራውን ለማድረግ የሚያስችሉ ኹኔታዎች ባለመኖራቸዉ እስካሁን ማድረግ አለመቻሉን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል። የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ; መንግሥት በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የሕዝብና ቤት፣ የኢኮኖሚ እንዲሁም የግብርና ቆጠራ ለማድረግ ማቀዱን የተናገሩ ሲሆን ፕሮግራሙ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል። የግብርና ቆጠራ የተደረገው ከ25 ዓመታት በፊት መሆኑን በፕሮግራሙ ይፋ ማድረጊያ ላይ የተናገሩት ፍፁም ቆጠራው በግብርና ስርዓቱ ውስጥ የገቡ የበጋ ስንዴ ልማትን ጨምሮ የተደራጀ የግብርና ዘርፍ መረጃ እንዲኖር ያደርጋል ብለዋል።

5. የፈረንሳዩ ካናል ፕላስ ቴሌቭዥን ጣቢያ የደቡብ አፍሪቃውን ዲኤስ ቲቪ (መልቲቾይስ) ለመግዛት ጥያቄ አቀረበ። ካናል ፕላስ ለእያንዳንዱ የዲኤስ ቲቪ ባለድርሻ ጠቀም ያለ ክፍያ በመፈፀም ድርጅቱን ለመጠቅለል ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል። ቀደም ባሉት አመታት ሁለቱ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች በአፍሪቃ ውስጥ ተፎካካሪ ሆነው የቆዩ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ካናል ፕላስ በአፍሪቃ ያለውን የገበያ ድርሻ እያሰፋ በመምጣቱ በየሀገራቱ እየተስፋፋ ይገኛል። ሁለቱም ጣቢያዎች መዝናኛና የስፖርት ዝግጅቶች በማቅረብ ይታወቃሉ። [ዋዜማ]
February 1, is a critical day for Ethiopia and Somaliland with respect to their recent MoU. Pursuant to the MoU signed on January 1, 2024, detailed cooperation agreement was scheduled to be completed within one month. However, Ethiopia faces major diplomatic hurdles and overwhelming global condemnation. Read more tinyurl.com/e3nwuthh
ለቸኮለ ! ዓርብ ጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1-የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ነሐሴ 08 ቀን 2015 ዓ.ም በአማራ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት አራዝሟል።ምክር ቤቱ፣ የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዎን ጢሞቴዎስ በአዋጁ መራዘም አስፈላጊነት ላይ ያቀረቡትን ማብራሪያ ተከትሎ አባላቱ ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ በኹለት ተቃውሞ እና በሦሥት ድምፀ-ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ እንዲራዘም መደረጉን ገልጿል። ምክር ቤቱ፣ የአዋጁን መራዘም ተከትሎም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ የሥራ ዘመንንም በኹለት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል። ነገር ግን ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ; ምክር ቤቱ ለአዋጁ መራዘም በምክንያትነት ቀርቧል የተባለውን ማብራሪያ ይፋ አላደረገም።

2-በቢጂአይ ኢትዮጵያ ስር የሚገኙት አምስት የቢራ ፋብሪካዎች በጥሬ ዕቃ እጥረት ምክንያት ከፍተኛ የምርት መስተጓጎል እንደገጠማቸው ዋዜማ ከፋብሪካው ሠራተኞች ሰምታለች።
እንደ ገብስ፣ብቅል፣ጌሾ፣በቆሎ እና ሌሎችም ለምርት አስፈላጊ የሆኑ ኬሚካሎችን ለፋብሪካዎቹ ለማቅረብ እጅግ አዳጋች መሆኑን የፋብሪካው ሠራተኞች ለዋዜማ ተናግረዋል።
አብዛኞቹ የጥሬ ዕቃ ግብዓቶች የሚመጡት ከኦሮሚያ እና ከአማራ ክልሎች ቢሆንም ክልሎቹ ላይ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ጥሬ ዕቃዎችን ማቅረብ አለመቻሉን ጠቁመዋል።
ለአብነትም ከአሰላ ይመጣ የነበረው የገብስና የብቅል ግብዓት ባለፈው አንድ ወር አለመቅረቡን ሠራተኞቹ ለዋዜማ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ባሕርዳር ከሚገኘውና የበቆሎ ቅንጬ ከሚያመርተው ጨጨሆ ፋብሪካ ምርቱን ይቀበሉ እንደነበር በመግለጽ፣በአካባቢው ካለው የጸጥታ ሁኔታ ጋር በተገናኝ ምርቱን ማቅረብ አዳጋች መሆኑን አስረድተዋል። ጌሾ እና ሌሎች አስፈላጊ ኬሚካሎችም ከአሜሪካና ከጀርመን ይገቡ ነበር ያሉት ሠራተኞቹ፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ መቆሙን ተናግረዋል።
አልፎ አልፎም ቢሆን በከፍተኛ የጭነት ዋጋና በሌሎች ተለዋዋጭ መንገዶች ጥሬ እቃዎቹን ለማቅረብ የተሞከረ ሲሆን፣ይህም ከፍተኛ ኪሳራ ማስከተሉን ጠቁመዋል።ይህን ለማካካስ በቢራ ዋጋ ላይ ጭማሪ ለማድረግ ቢወሰንም፣ በመንግሥት ክልከላ ምክንያት ጭማሪው እስካሁን አለመደረጉን ዋዜማ ከሠራተኞቹ ሰምታለች።

3-የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም እና ይኽም በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚኖሩት እንድምታዎች ኮሚሽኑን እጅጉን እንደሚያሳስበው ገልጸዋል። ዳንኤል፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከማራዘሙ ሰዓታት ቀደም ብሎ በ”ኤክስ” ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ መንግሥት እና ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊነት; ሕጋዊነት እና ተመጣጣኝነት በቅጡ ሊመለከቱት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
የአዋጁ መራዘም; በሰብዓዊ ጉዳቶች፣ ሰብዓዊ ቀውስ እንዲባባስ እንዲሁም ሰዎች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለረዥም ጊዜ በእስር እንዲቆዩ ማድረግ የሚሉት በኮሚሽነሩ የተጠቀሱ የአዋጁ መራዘም አሉታዊ እንድምታዎች ናቸው። ዳንኤል፣ ችግሮችን ለመፍታት ውይይት ቁልፍ መንገድ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

4-የምሥራቅ ወለጋ ዞን መቀመጫ በሆነችው ነቀምት ከተማ የእጅ ቦንቦች በተደጋጋሚ እየተጣሉ እንደሆነና ይህም ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረባቸው ነዋሪዎች ለዋዜማ ተናግረዋል።
ባልተለመደ መልኩ ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚጣለው የእጅ ቦንብ፣የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጠርቶታል ከተባለው አድማ ጋር የተያያዘ ሳይሆን እንዳልቀረ ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል። በሌላ በኩል ማክሰኞ ጥር 21/2016 ዓ.ም. የተጠራውን አድማ ጥሳችኋል በማለት በከተማዋ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሁለት ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች በታጣቂ ቡድኑ እንደተቃጠሉም አስረድተዋል። በከተማዋ መደበኛ እንቅስቃሴ ከተቋረጠ ዛሬ አምስተኛ ቀኑን መያዙን የገለጹት ነዋሪዎች; ምሽት ላይ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ቡድኑ አባላት መካከል ከፍተኛ የሆነ የተኩስ ልውውጥ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ከሰኞ ጥር 20/2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ባንኮች፣ትምሕርት ቤቶች፣የንግድ ቤቶች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በአመዛኙ ዝግ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በመንግሥት ኃይሎች በኩል ተቋማቱን እንዲከፍቱ ከፍተኛ ጫና እየተደረገ መሆኑን ዋዜማ ከነዋሪዎቹ ካሰባሰበችው መረጃ መረዳት ችላለች።

5-የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለማርያም እና የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የኢትዮጵያ ተወካይ ራሚዝ አላክባሮቭ በጋራ ባወጡት መግለጫ; በኢትዮጵያ በቀጣዮች ጥቂት ወራት ውስጥ አስከፊ የምግብ እጥረት የሚያጋጥማቸው ዜጎች ቁጥር እንደሚጨምር ገልጸዋል። በተለይም ከሰኔ መጨረሽ እስከ ነሐሴ ባሉት ጊዜያት ከፍተኛ የምግብ እጥረት የሚያጋጥማቸው ዜጎች ቁጥር 10 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ጠቁመዋል።
የኤልኒኖ የአየር ንብረት ክስተትን ተከትሎ በተለይ ለኹለት ዓመታት በተከሰተው ጦርነት የተነሳ እስከ አኹን ሙሉ ለሙሉ ማገገም ባልቻሉት እና በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙት ተጋላጭ ማኅበረሰቦች ዘንድ ችግሩ እንደሚያይል ተጠቅሷል።መግለጫው፣ ቀውሱ እንዳይባባስ ለመከላከል ያለው ዕድል ጠባብ መሆኑን በመጥቀስ፣ ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድም አሳስቧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ቅዳሜ ጥር 25/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለሥልጣን፣ አገሪቱ ለአውሮፓ ገበያ የምትሸጠው የቡና ምርት አውሮፓ ኅብረት ያወጣውን አዲስ የደን ጭፍጨፋ ደንብ ያከበረ መኾኑን ለማረጋገጥ ኮሚቴ ማቋቋሙን ሪፖርተር ዘግቧል። ኮሚቴው፣ ከባለሥልጣኑ፣ ከቡና አምራችና ላኪ ማኅበራት፣ ከቡና አምራች ገበሬዎች፣ ከኢምባሲዎችና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች የተውጣጡ አባላትን እንዳካተተ ዘገባው ጠቅሷል። አውሮፓ ኅብረት፣ አባል አገራቱ ከውጭ የሚገዙት ቡና ደኖችን በመጨፍጨፍ የተመረተ እንዳይኾን ለማረጋገጥ ያወጣው ደንብ፣ በተያዘው የአውሮፓዊያን ዓመት ተግባራዊ መኾን ይጀምራል። ኢትዮጵያ፣ ደንቡ በኢትዮጵያ የሚኖረው ተፈጻሚነት እንዲራዘም ጠይቃለች ተብሏል። ኢትዮጵያ ባለፈው ሩብ በጀት ዓመት 117 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ አቅርባ 571 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች።

2፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ፣ መንግሥት በአማራ ክልል ያወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማራዘሙ "በእጅጉ እንዳሳሰበው" ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጱ አስታውቋል። አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ባስተላለፉት በዚኹ መልዕክት፣ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የቀጠሉትን ጨምሮ የአገሪቱን ውስብስብ ፖለቲካዊና የጸጥታ ችግሮች መፍታት የሚቻለው በንግግር መኾኑን ገልጸዋል። ችግሮችን በንግግር ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት፣ አሜሪካ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መኾኗንም አምባሳደሩ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

3፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፣ የብሪታኒያ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንድሪው ሚቸል ከመሩት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ጋር ትናንት መቀሌ ውስጥ መወያየታቸውን በ"ኤክስ" (የቀድሞው ትዊተር) ገጻቸው አስታውቀዋል። ውይይቱ፣ በፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት አተገባበር ተግዳሮቶችና የጦርነቱን ተፈናቃዮች በመመለስ ዙሪያ እንደኾነ ጌታቸው ገልጸዋል።
ሚቸል፣ የኤርትራ ጦር ከትግራይ እንዲወጣ መጠየቃቸውን የዘገበው ደሞ የክልሉ ቴሌቪዥን ነው። ልዑካን ቡድኑ፣ የመቀሌውን አይደር ሪፈራል ሆስፒታል እንዲኹም ከመቀሌ 37 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አጉላ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮችን እንደጎበኘ ዘገባው አመልክቷል።

4፤ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ድንበር አካባቢ በሚገኙ ኹለት ወረዳዎች እንስሳትን እየዘረፉና አርሶ አደሮችን አፍነው እየወሰዱ ስለመኾኑ ከአንድ የተመድ የዳሰሳ ሰነድ መመልከቱን ጠቅሶ አሶሴትድ ፕሬስ ዘግቧል። ጥር 13 ቀን፣ ስምንት የትግራይ ከብት ጠባቂዎች በኤርትራ ወታደሮች ታፍነው እንደተወሰዱ ዘገባው ጠቅሷል። ኅዳር 26 ደሞ ስድስት ሰዎችንና በርካታ ግመሎችን ጨምሮ 56 የቤት እንስሳትን መወሰዳቸውን ሰነዱ መጥቀሱን ዘገባው አመልክቷል። የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገ/መስቀል ግን፣ ውንጀላውን "ሐሰት" በማለት ትናንት ማስተባበላቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

5፤ አሜሪካ፣ ቶም ፓሪዮሎን ለሱዳን ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ ልትሾም መኾኗን ሮይተርስ ዘግቧል። ፔሪዮሎ፣ ቀደም ሲል ዲሞክራቲክ ፓርቲውን በመወከል የኮንግሬስ አባልና በታላላቅ ሐይቆች አገራት የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ የነበሩ ናቸው። ከፔሪዮሎ በፊት፣ ባኸኑ ወቅት በሱዳን የአሜሪካ አምባሳደር የኾኑት ጆን ጎድፍሬይ እና የቀድሞዋ የአሜሪካ ዓለማቀፍ ተራድዖ ድርጅት ሃላፊ ጌይል ስሚዝ ታጭተው ነበር ተብሏል። የአሜሪካ ኮንግሬስ አባላት፣ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለሱዳኑ ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄ እንዲገኝ የሚያግዙ ልዩ መልዕክተኛ እንዲሾሙ ሲወተውቱ መቆየታቸው ይታወሳል። በተያያዘ፣ አምባሳደር ጆን ጎድፍሬይ በቅርቡ ከሃላፊነት እንደሚለቁ ዘገባው ጠቅሷል።

6፤ አፍሪካ ኅብረት በተያዘው አውሮፓዊያን ዓመት መገባደጃ ታኅሳስ ላይ በሰላም ሽግግር ተልዕኮው ሥር በሱማሊያ የተሠማሩ ወታደሮቹን ሙሉ በሙሉ እንደሚያስወጣ በድጋሚ አረጋግጧል። የኅብረቱ የፖለቲካ፣ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ይህን ያረጋገጠው፣ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በአገሪቱ ተገኝቶ የጸጥታ ኹኔታውን ከገመገመ በኋላ ነው። ልዑካን ቡድኑ፣ በጉብኝቱና ከኅብረቱ ተልዕኮ መውጣት በኋላ በሱማሊያ ሊኖር ስለሚችለው የጸጥታ ኹኔታ፣ ለኅብረቱ የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤትና ለተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ሪፖርት ያቀርባል። የኅብረቱ ተልዕኮ፣ በሦስተኛው ዙር እስከ ሰኔ ድረስ አራት ሺህ ወታደሮችን ለማስወጣት ካኹኑ ዝግጅቱን ጀምሯል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ሰኞ ጥር 27/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በርካታ የፌደራልና ክልል መንግሥታት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ትናንት በአማራ ክልል 15 ከተሞች ከሕዝቡ ጋር ውይይት አድርገዋል። በባሕርዳር፣ ጎንደር፣ ፍኖተሰላም፣ ደብረታቦር፣ ሰቆጣና ሌሎች ከተሞች የተካሄዱትን ውይይቶች ከመሩት ባለሥልጣናት መካከል፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሺመልስ አብዲሳ፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ኡመር፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ተስፋይ በልጅጌ፣ የገንዘብ ሚንስትር አሕመድ ሽዴና የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይገኙበታል። ውይይቶቹ "ሕብረ ብሄራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት ለዘላቂ ሰላምና ኹለንተናዊ ብልጽግና" በሚል ርዕስ የተካሄዱት፣ የክልሉን ሕዝብ ችግሮች ለመረዳትና የመፍትሄ ሃሳቦችን ለመስማት እንደኾነ ተገልጧል። ባለሥልጣናቱ፣ የአማራን ሕዝብ ጥያቄ በነፍጥ ማሳካት እንደማይቻል በውይይቶቹ ላይ አጽንዖት ሰጥተዋል።

2፤ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ሺፈራው ተ/ማርያም ድርቅን ለፖለቲካዊ ዓላማ መጠቀም "ተገቢ ያልኾነ" እና "ፍጹም ተቀባይነት የሌለው" ድርጊት ነው በማለት መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል። የዓለማቀፍ ተቋማት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርቡ ያካሄዱት የዳሰሳ ጥናት፣ በኢትዮጵያ ባኹኑ ወቅት የተከሰተው ድርቅ እንጂ ርሃብ እንዳልኾነ ማረጋገጡን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል ተብሏል። ኮሚሽነር ሺፈራው፣ ባኹኑ ወቅት በአገሪቱ 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊ እንደኾኑ መግለጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል። መንግሥት ባለፉት ስድስት ወራት፣ በ11 ቢሊዮን ብር ወጪ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል የዕርዳታ እህል ለተረጂዎች ማከፋፈሉን እንደጠቀሱ ዘገባው አመልክቷል።

3፤ የቡናና ሻይ ልማት ባለሥልጣን ክፍያ ያልፈጸሙ ኹለት ዓለማቀፍ ኩባንያዎችን ስለማገዱ መስማቱን ካፒታል ጋዜጣ ዘግቧል። አገሪቱን የውጭ ምንዛሬ አሳጥተዋታል ተብለው እገዳ የተጣለባቸው ኹለት ዓለማቀፍ ኩባንያዎች፣ ከኢትዮጵያዊያን ላኪዎች ቡና ገዝተው ለቻይና ገበያ ሲያቀርቡ የነበሩ እንደኾኑ ዘገባው ጠቅሷል። ባለሥልጣኑ ኩባንያዎቹ የቡና ሽያጭ ውል እንዳይፈጽሙ ለኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር እንዳያሳወቀና ብሄራዊ ባንክም አንዳችም ኮንትራት እንዳይፈጽሙ እንዲያግዳቸው እንዳሳሰበ ዘገባው አመልክቷል።

4፤ አፍሪካ ኅብረት ለሱዳን ያቋቋመው ከፍተኛ ቡድን ሥራውን በይፋ መጀመሩን የኅብረቱ ኮሚሽን አስታውቋል። ቡድኑ፣ አፍሪካ ኅብረት በሱዳን ሰላም ለማስፈን የቀረጸውን ስትራቴጂ ተግባራዊ ላይ የማዋልና ጦርነቱ ቆሞ ኹሉን አካታችና ዘላቂ የሰላም ሂደት እንዲጀመር ኹኔታዎችን የማመቻቸት ኃላፊነት አለበት። ሦስት አባላት ያሉትን የኅብረቱን ከፍተኛ ቡድን የሚመሩት፣ በአፍሪካ የኅብረቱ የግጭት ማቆም ከፍተኛ ተወካይ ሞሃመድ ቻምባስ ናቸው። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሰኞ ጥር 27/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ትላንት እና ዛሬ በመቀሌ ከተማ ሊያደርገው የነበረውን ጠቅላላ ጉባዔ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መከልከሉን ፓርቲው ለዋዜማ ገልጧል። የፓርቲው መስራች እና ሊቀመንበር አረጋዊ በርሄ ለዋዜማ እንደተናገሩት፣ ፓርቲያቸው ለሁለት ቀናት ሊያደርገው ያሰበው ጠቅላላ ጉባዔ መስተጓጎሉን ተናግረው፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ግን የጉባዔውን መካሄድ አልከለከልኩም በማለት እያስተባበለ ይገኛል ብለዋል። ፓርቲያቸው ጉዳዩን እየተከታተለ እንደኾነ የገለጹት አረጋዊ፣ ፓርቲው በቀጣዮቹ ሁለት እና ሦስት ቀናት በጉዳዩ ላይ አንድ እልባት ላይ እንደሚደርስ ተናግረዋል። የጉባዔው ዓላማ፣ በክልሉ ያለው የመልካም አሥተዳደር እጦትና የምግብ እጥረት ለፖለቲካ ፍጆታ መዋሉ ንጹሃንን እየጎዳ እንደሆነ ለመግለጽ ያለመ እንደኾነ ዋዜማ ተረድታለች።

2፤ የብሪታንያ የዓለማቀፍ ልማት ሚንስትር ደዔታ አንድሪው ሚቸል፣ በኢትዮጵያ የተከሰተው ከፍተኛ የምግብ እጥረት ከባድ የሰብዓዊ ቀውስ ስጋት ፈጥሯል ማለታቸውን ፋይናንሻል ታይምስ ዘግቧል። ሚቸል፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ሦስት ሚሊዮን ሰዎች ከፍተኛ የርሃብ አደጋ እንዳንዣበበባቸው የገለጡት፣ ባለፈው ሳምንት በትግራይ ጉብኝት አድርገው ከተመለሱ በኋላ በሰጡት ቃል ነው። የብሪታንያ መንግሥት ነፍሰ ጡር እናቶችን ጨምሮ ለሦስት ሚሊዮን ተረጅዎች የተመጣጠነ ምግብ እና መድሃኒት ለማቅረብ የሚውል 100 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡን ሚቸል መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ሚቸል፣ በኢትዮጵያ ያንዣበበው የርሃብ አደጋ በዩክሬን፣ ጋዛ እና ሱዳን ባሉ ሰብዓዊ ቀውሶች ተውጧል ማለታቸውንም ጋዜጣው አውስቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በሰሜኑ ክፍል ርሃብ እንዳልተከሰተ በመግለጽ፣ ድርቁን ለፖለቲካዊ ዓላማ የሚያውሉ አካላት አሉ በማለት ይከሳል።

3፤ ተቃዋሚው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከዓላማው በተቃራኒ ቆመዋል በማለት ያሰናበታቸው ስድስት የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮቹ በስሙ ለሚያደርጉት ሕገወጥ እንቅስቃሴ ኃላፊነት እንደማይወስድ አስታውቋል። ስድስቱን የቀድሞ አመራሮች ከሦስት ዓመታት በፊት ማገዱን የጠቀሰው ኦነግ፣ ይሁንና አመራሮቹ በዚያው ዓመት የፓርቲውን ዋና ጽሕፈት ቤት የመቆጣጠርና አመራሮችን በሌላ የመተካት ሙከራ ማድረጋቸውን ገልጧል። የቀድሞዎቹ አመራሮች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በኅብረተሰቡ ዘንድ ግርታን መፍጠሩንና ማናቸውም እንቅስቃሴያቸው ግን ፓርቲውን እንደማይወክል ኦነግ አስታውቋል።
ግለሰቦቹን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በተደጋጋሚ በቃል እንደነገራቸው የገለጠው ፓርቲው፣ ከእንቅስቃሴያቸው አልቆጠብ ሲሉ ግን መግለጫ ለማውጣት መገደዱን ግንባሩ ገልጿል። ግለሰቦቹ ጉዳያቸው በፓርቲው ሕግና ሥነምግባር ኮሚቴ እየታየ እንደኾነነ ኦነግ ጠቁሟል። ከስድስቱ ግለሰቦች መካከል፣ ቀጀላ መርዳሳ እና አራርሳ ቢቂላ ይገኙበታል።

4፤ ዘንድሮ ለ11ኛ ጊዜ በባሕርዳር ከተማ በሚካሄደው የጣና ፎረም ስብሰባ ዝግጅት ዙሪያ የፎረሙ ሴክሬታሪያት ከአማራ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ጋር ዛሬ መወያየቱን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል። የውይይቱ ትኩረት፣ በጉባዔው ዝግጅትና በጉባዔው ዝግጅት በሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት መካከል የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ዙሪያ እንደኾነ ሚንስቴሩ ገልጧል። ከሚያዝያ 11 እስከ 13 በአፍሪካ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚመክረው ዓመታዊው የጣና ፎረም ስብሰባ ዘንድሮ ሊካሄድ የነበረው ባለፈው ጥቅምት ወር ነበር። ኾኖም የስብሰባው አዘጋጅ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተቋም "ያልተጠበቁ ኹኔታዎች" እንዳጋጠሙት በመግለጽ፣ ስብሰባውን ወደ ሚያዝያ ማዘወሩን መግለጡ ይታወሳል።

5፤ የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በብሪታንያ መንግሥት ላይ ያለውን ቅሬታ ለመግለጽ በአሥመራ የብሪታንያ ጉዳይ አስፈጻሚን መጥራቱን የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገ/መስቀል በ"ኤክስ" ገጻቸው አስታውቀዋል። የብሪታንያ ጉዳይ አስፈጻሚ ማብራሪያ እንዲሰጡና የአሥመራን ቅሬታ ለመንግሥታቸው እንዲያስተላልፉ የተጠሩት፣ የብሪታንያ ባለሥልጣናት በኤርትራ ላይ የ"ሐሰት" ውንጀላ" ማቅረብ በመቀጠላቸው እንደኾነ የማነ ገልጸዋል። ጉዳይ አስፈጻሚው የተጠሩት፣ የብሪታንያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደዔታ አንድሪው ሚቸል ባለፈው ሳምንት በትግራይ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ስለመጠየቃቸው በተዘገበ ማግስት ነው።

6፤ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የሱዳን ሲቪል ኃይሎች ስብስብ እና የሱዳኑ ወታደራዊ መሪዎች ንግግር እንዲጀምሩ ለማስተባበር ቃል መግባታቸውን የሱዳን ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ፕሬዝዳንት ኪር ይህን ቃል የገቡት፣ የሲቪል ኃይሎቹ ስብስብ ልዑካን ቡድን ባለፈው ሳምንት ዓርብ ወደ ጁባ ተጉዞ ጥያቄውን ካቀረበላቸው በኋላ ነው። የስብስቡ ልዑካን ቡድን፣ ጦርነቱን ለማስቆም በሚያስችል ፍኖተ ካርታ ዙሪያ ከጀኔራል ቡርሃን ጋር መምከር እንደሚፈልግ ለፕሬዝዳንቱ ገልጦላቸዋል ተብሏል። የቀድሞው የሱዳን ሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ የሚመሩት ስብስቡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ እንደተመሠረተ ይታወሳል።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ2067 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ3308 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 68 ብር ከ4763 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ8458 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ61 ከ1585 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ3817 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
Audio/Video ⬇️

https://youtu.be/dvuUP4LAEbw?si=VsUshOb5SdZHk39o
ለቸኮለ ማለዳ! ማክሰኞ ጥር 28/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በሱማሊያ ዕሁድ ምሽት ባልታወቁ ታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ ስድስት ኢትዮጵያዊያን መገደላቸውን የሱማሊያ ዜና ምንጮች የዓይን እማኞችን ጠቅሰው ዘግበዋል። ዘገባዎቹ፣ በጥቃቱ ሌሎች ስድስት ኢትዮጵያዊያን እንደቆሰሉ አመልክተዋል። ጥቃቱ የተፈጸመው፣ በኢትዮጵያ እና ሱማሊያ ድንበር በለድ-ሃዎ ከተማ በኢትዮጵያዊዋኑ መኖሪያ ቤተ ውስጥ እንደኾነ ተገልጧል።

2፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፌደራል መንግሥቱ ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት በአዋዛጋቢ አካባቢዎች "ሕዝበ ውሳኔ" እንዲካሄድ ከትግራይና አማራ ክልሎች አመራሮች ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር በማለት ያወጣውን መግለጫ ውድቅ አደርጎታል። የቃለ አቀባዩ መግለጫ “ተቀባይነት የለውም” ያለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ መግለጫው ከፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት መንፈስ ጋር የሚጋጭ መኾኑን ገልጧል። አንዳንድ "ትክክለኛ ተፈናቃዮች ወደቀያቸው ተመልሰዋል" መባሉንም “አደገኛ አባባል” በማለት፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ውድቅ አድርጎታል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ በኃይል በተያዙ አካባቢዎች ሕገወጥ አስተዳዳሪዎች ከቦታቸው ሳይነሱ፣ እንደዚህ ዓይነት መግለጫዎች መስጠት ፌደራል መንግሥቱ ከመፍትሄው ይልቅ "የችግሩ አካል" መኾን የሚፈልግ አስመስሎበታል በማለትም ተችቷል። የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚቃወሙ ወገኖች “የተሳሳተ" አቋማቸውን እንዲገፉበት የሚያበረታቱ መግለጫዎች አደገኛ መዘዝ ያስከትላሉ በማለትም ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስጠንቅቋል።

3፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ዛሬ በ14ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የምክር ቤቱ አባላት ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ይሰጣሉ። ዐቢይ በምክር ቤቱ ተገኝተው ምላሽና ማብራሪያ የሚሰጡት፣ ምክር ቤቱ በአማራ ክልል የታወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለአራት ወራት ባራዘመ ማግስት ነው። ዐቢይ፣ ከሶማሊላንዱ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ጋር ከአንድ ወር በፊት በተፈራረሙት አወዛጋቢ የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ዙሪያ እስካኹን ለሕዝብ ይፋዊ ማብራሪያ እንዳልሰጡ ይታወቃል።

4፤ ንግድ ሚንስቴር የየካቲት ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ በጥር ወር እየተሸጠበት በሚገኘው ዋጋ እንደሚቀጥል አስታውቋል። በተያዘው ወር ያለው የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ፣ ቤንዚን በሊትር 77 ብር ከ65 ሳንቲም ሲኾን፣ ኬሮሲን በሊትር 79 ብር ከ75 ሳንቲም ነው። በተመሳሳይ፣ ነጭ ናፍጣ በሊትር 79 ብር ከ75 ሳንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ በሊትር 61 ብር ከ16 ሳንቲም እንዲኹም ቀላል ጥቁር ናፍጣ በሊትር 62 ብር ከ36 ሳንቲም በመሸጥ ላይ ይገኛል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ማክሰኞ ጥር 28/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የመንግሥት የጸጥታ ሃይሎች ዛሬ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሃፊና የኒውዮርክና አካባቢው አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጴጥሮስ ቦሌ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ እንዳይገቡ መከልከላቸውን የቤተክርስቲያኗ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ አስታውቋል። ሕዝብ ግንኙነት መምሪያው፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ሊቀ ጳጳሱ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሃፊ መኾናቸውን ከግምት በማስገባት ወደ አገር እንዲገቡ እንዲፈቅዱ ቤተክርስቲያኗ መጠየቋን ገልጧል። ይህንኑ ተከትሎ ሊቀ ጳጳሱ በምን ኹኔታ ላይ እንዳሉ፣ ቤተክርስቲያኗ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ተጨማሪ መረጃ አልሰጠችም። አቡነ ጴጥሮስ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለቤተክርስቲያኗ ሐዋሪያዊ ተልዕኮ ወደ ሰሜን አሜሪካ መጓዛቸውን ሲኖዶሱ ገልጦ እንደነበር ይታወሳል።

2፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከአማራ ክልል ለሚነሳው የሕገመንግሥት ማሻሻያ ጥያቄ በአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አማካኝነት ምላሽ ለመስጠት መንግሥት እየሠራ መኾኑን ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ተናግረዋል። በአማራ ክልል በተደረጉ ውይይቶች በዋናነት የሕገመንግሥት ማሻሻያ፣ የወሰንና የልማት ጥያቄዎች መነሳታቸውን የጠቀሱት ዐቢይ፣ መንግሥት የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎችን በውይይትና ዘላቂ ሰላምን በሚያረጋግጥ አኳኋን እንዲፈቱ ይፈልጋል ብለዋል። ዐቢይ፣ የትግራይና የአማራ ምሁራን ለአስተዳደር ወሰን ውዝግቡ የተሻለ ሰላማዊ መፍትሄ ካመጡ፣ ፌደራል መንግሥቱ ለመተባበር ዝግጁ እንደኾነም ገልጸዋል። ዐቢይ ከወራት በፊት ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ፣ በአወዛጋቢ ግዛቶች ሕዝበ ውሳኔ ማካሄድ የተሻለ አማራጭ እንደኾነ ገልጠው እንደነበር ይታወሳል። የኦሮሚያ፣ ሶማሌና አፋር ክልሎችም፣ የሕገመንግሥት ጥያቄ እንደሚያነሱ ዐቢይ ጠቅሰዋል።

3፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ እስካኹን በአገሪቱ በርሃብ የሞተ ሰው አለመኖሩን ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ላይ ተናግረዋል። ዐቢይ፣ በርሃብ ላይ ሌሎች ችግሮች ሲጨመሩ ሰዎች መቋቋም አቅቷቸው ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ግን በማብራሪያቸው ገልጸዋል። መንግሥት ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ለተረጂዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ 15 ቢሊዮን ብር ማውጣቱን የገለጡት ዐቢይ፣ መንግሥት ድርቁን ችላ ብሎታል የሚባለው ስህተት ነው ብለዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ በትግራይ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች እንዲኹም በምስራቅ ኢትዮጵያ ድርቅ መኖሩን በመጥቀስ፣ በኢትዮጵያ በርሃብ የሚሞት ሰው ከኾነ መንግሥት የልማት ፕሮጀክቶችን አጥፎ ሕይወት ለመታደግ እንደሚሠራ ገለጸዋል።

4፤ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚንስቴር የግሉ ዘርፍ በደረቅ ወደብ ልማት እንዲሰማራ የሚፈቅድ ረቂቅ መመሪያ ማዘጋጀቱን ካፒታል ዘግቧል። የጭነት አስተላላፊዎች ግን ረቂቅ መመሪያው እውነታውን ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው የሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ረቂቅ መመሪያው ደረቅ ወደቦች በሚሰጡት አገልግሎት ልክ፣ ለግል ኩባንያዎች ሊኖራቸው የሚገባውን የመሬት ስፋት ዘርዝሮ አስቀምጧል ተብሏል። የአገር ውስጥ ወይም የውጭ ባለሃብቶች እንደሚሰጡት አገልግሎት ፍቃድ ለማግኘት፣ በራሳቸው ይዞታ ሥር የሚገኝ ከ2 እስከ 80 ሄክታር መሬት ለፈቃድ ማቅረብ እንዳለባቸው በረቂቁ ላይ እንደተገለጠ ዘገባው ጠቅሷል። ኾኖም ከትልላቅ ባለሃብቶች ወይም የውጭ አልሚዎች በስተቀር፣ በመመሪያው መሠረት በጭነት ማስተላለፍ ሥራ የተሰማሩ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች በዘርፉ ለመሳተፍ ይከብዳቸዋል የሚል ቅሬታ መቅረቡን ዜና ምንጩ አውስቷል። እስካኹን ባለው አሠራር፣ ደረቅ ወደቦችን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ድርጅት ነው።

5፤ እናት ፓርቲ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ2015 ዓ፣ም ጀምሮ በጣለው የጣሪያና ግድግዳ ወይም የንብረት ገቢ ግብር ላይ ለመሠረተው ክስ፣ ፍርድ ቤት ለየካቲት 20 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን አስታውቋል። የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ፣ የክስ ሂደቱ በመገናኛ ብዙሃን መዘገቡ የሕዝብን ጥቅም ይነካል በማለት ፍርድ ቤቱ በመገናኛ ብዙኀን ላይ እገዳ እንዲጥል መጠየቁን ፓርቲው ጠቅሷል። ቢሮው ባቀረበው የክስ መቃወሚያ ላይ ትናንት የቃል ክርክር መካሄዱን ፓርቲው ገልጧል። ኾኖም ፓርቲው ቢሮው የክርክሩ ሂደት በመገናኛ ብዙኀን እንዳይዘገብ ፍርድ ቤቱ እግድ እንዲጥል ባቀረበው አቤቱታ ላይ መቃወሚያ ካለው በጽሑፍ እንዲያቀርብ መታዘዙንና ፍርድ ቤቱም በዚሁ ጉዳይ ላይ የካቲት 4 ብይን እንደሚሰጥ መግለጡን ፓርቲው ጨምሮ አመልክቷል።

6፤ ፌደራል ፖሊስ፣ ኮኬይን የተባለውን አደገኛ ዕፅ ውጠው የተገኙ የብራዚልና የኢንዶኔዥያ ዜግነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች ቦሌ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ዛሬ አስታውቋል። የብራዚል ዜግነት ካላት አንዲት ተጠርጣሪ መንገደኛ በእንክብል መልክ የተዘጋጀ 2 ነጥብ 9 ኪሎ ግራም ኮኬይን እንደተያዘ የገለጠው ፌደራል ፖሊስ፣ ሰባት ፍሬ ኮኬይን ደሞ ከሆዷ መውጣቱን ጠቅሷል። በተመሳሳይ የኢንዶኔዥያ ዜግነት ያለው አንድ ተጠርጣሪ፣ በሆዱ ከዋጠው የኮኬን እንክብሎች በተጨማሪ 6 ነጥብ 7 ኪሎ ግራም ኮኬይን በሻንጣ ውስጥ ሰፍቶ ለማለፍ ሲሞክር በቁጥጥር ሥር ውሏል ተብሏል። ቦሌ ላይ በኤክስሬይ ምርመራ የታያዙት ኹለቱም ተጠርጣሪዎች፣ ከብራዚል እና ኢንዶኔዥያ የተነሱ እንደኾኑ ተገልጧል።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ2236 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ3481 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 67 ብር ከ4605 ሳንቲም እና መሸጫው 68 ብር ከ8097 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ60 ከ4347 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ61 ብር ከ6434 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ረቡዕ ጥር 29/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ኢሰመጉ፣ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን መርዓዊ ከተማ በመንግሥት ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ጥር 20 ቀን የተካሄደውን ግጭት ተከትሎ የመንግሥት ጸጥታ ሃይሎች በበርካታ ንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ፣ የአካል ጉዳት ማድረስና ድብደባ ፈጽመዋል በማለት ከሷል። ጸጥታ ሃይሎች በከተማዋ የቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ በግጭቱ ምንም ዓይነት ተሳትፎ የሌላቸውን በርካታ ሰዎች መግደላቸውን ኢሰመጉ ዓይን እማኞችን ጠቅሶ ገልጧል። ኢሰመጉ፣ በግጭቱ ወቅት በነበረው የተኩስ ልውውጥና በጸጥታ ኃይሎች ግድያ፣ ኹለት ሴቶችንና አንድ የ17 ዓመት ታዳጊን ጨምሮ በጠቅላላው ከ80 በላይ ንጹሃን መገደላቸውን ጠቅሷል። ጸጥታ ኃይሎች በርካታ ወንዶችን ከቤታቸው ካወጡ በኋላ በአደባባይ እንደረሸኗቸውና በማግስቱ በጅምላ መቃብር እንደተቀበሩ የዓይን እማኞች መናገራቸውን የገለጠው ኢሰመጉ፣ ድርጊቱን ተከትሎ ነዋሪዎች ከከተማዋ እየሸሹ ነው ብሏል።

2፤ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በመንግሥት ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭቶች መቀጠላቸውን ዋዜማ ከምንጮች ሰምታለች። በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማ ዙሪያ ትናንት ግጭት መካሄዱን ምንጮች ተናግረዋል። በደቡብ ወሎ፣ በደቡብ ጎንደርና በሰሜን ጎንደር ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎችም ግጭቶች መካሄዳቸው ተሰምቷል። ግጭቶች መቀጠላቸው የተሰማው፣ የፌደራልና የተለያዩ ክልሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት በክልሉ 15 ከተሞች በክልሉ ሕዝብ ጥያቄዎችና በመፍትሄ ሃሳቦች ዙሪያ ከሕዝቡ ጋር ውይይት ማድረጋቸው በተገለጠ ማግስት ነው።

3፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ በኢትዮጵያ የርሃብ አደጋ ላንዣበበባቸው ሦስት ሚሊዮን ሰዎች በቅርቡ የምግብ ዕርዳታ ሥርጭት ለመጀመር ጥረቱን ማጠናከሩን አስታውቋል። ኹለት ሚሊዮኑ ተረጂዎች በትግራይ ክልል እንደሚገኙ ድርጅቱ ገልጧል። ድርጅቱ፣ እስከ ሰኔ ወር የምግብ ዕርዳታ ጉድለቱን ለመሙላት ተጨማሪ 142 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው አመልክቷል። ተጨማሪውን ገንዘብ ካላገኘኹ ሚያዝያ ወር በአገሪቱ ለተጠለሉ ስደተኞች የማቀርበውን የምግብ እርዳታ ለማቋረጥ እገደዳለኹ ያለው ድርጅቱ፣ ከሱዳን 200 ሺህ ተጨማሪ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ ይችላሉ ብሏል። ድርጅቱ፣ አዲስ የተረጂ ልየታ ሥርዓት ከዘረጋ ወዲህ፣ በትግራይ፣ አማራ፣ አፋርና ሱማሊያ ክልሎች 6 ነጥብ 2 የአደጋ ተጋላጮችን መመዝገቡንም ጠቅሷል።

4፤ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኩባንያ እስካለፈው ታኅሳስ መጨረሻ ከኤምፔሳ አገልግሎቱ 280 ሺህ 625 ዶላር ገቢ ማግኘቱን ዘ ስታር ጋዜጣ አስነብቧል። በኢትዮጵያ የኩባንያው የኤምፔሳ አገልግሎት ተመዝጋቢዎች ቁጥር ወደ 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ማሻቀቡንና የኤምፔሳ ገንዘብ ዝውውር መጠኑም 115 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን ዘገባው አመልክቷል። ኩባንያው፣ የድምጽ፣ የመልዕክት ልውውጥና ዳታን ጨምሮ ባጠቃላይ በዘጠኝ ወራት ከአገልግሎቶቹ ያገኘው ገቢ 30 ሚሊዮን ዶላር መድረሱንም ዘገባው ጠቅሷል። ይህ ገቢ ኩባንያው በ2023 በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ካገኘው ገቢ የ74 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል።

5፤ የዓለማቀፉ ፍልሰት ድርጅት (አይ ኦ ኤም) ምክር ቤት ሊቀመንበር አምባሳደር ካታሪና ስታስች ከትናንት ጀምሮ በኢትዮጵያ የሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው። ስታስች፣ ትናንት ከአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ሺፈራው ተ/ማርያም ጋር በፍልሰትና ፍልሰተኞች ዙሪያ ተወያይተዋል። ሃላፊዋ፣ ከአፍሪካ ኅብረትና ከተመድ ባለሥልጣናትና ከለጋሽና የልማት አገራት ተወካዮች ጋር በፍልሰትና በፍልሰት ምላሽ አሰጣጥ ዙሪያ እንደሚወያዩም ድርጅቱ አመልክቷል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ረቡዕ ጥር 29/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ነገ አዲስ ሚንስትሮች እንዲሾሙላቸው ዕጩ ተሿሚዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባሉ። ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚያቀርቡትን የሚንስትሮች ሹመት ለማጽደቅ በነገው'ለት እንደሚሰበሰብ ዛሬ ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል። ዐቢይ ከሚያቀርቧቸው አዲስ ዕጩ ተሿሚዎች መካከል፣ ከኹለት ሳምንት ገደማ በፊት ከሥልጣን የተሰናበቱትን የምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ምትክ እንደሚገኙበት ይጠበቃል። ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የሜዳይ፣ ኒሻንና ሽልማት እንዲኹም የሕዝባዊ በዓላትን አከባበር ለመወሰን በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ እና በሌሎች ረቂቅ አዋጆች ላይ እንደሚወያይ ገልጧል።

2፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በቀጣዮቹ ሳምንታት በኢትዮጵያ በግጭት፣ ድርቅና ጎርፍ ለተጎዱ ሦስት ሚሊዮን ሰዎች የምግብ ድጋፍ ለማቅረብ በፍጥነት እንቅስቃሰ መኾኑን አስታውቋል። በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና እያሽቆለቆለ መሄዱ በእጅጉ ያሳስበኛል ያለው ደርጅቱ፣ ሠራተኞቹ የርሃብ አደጋ ላንዣበበባቸው ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መኾኑን አመልክቷል። ድርጅቱ፣ ባለፈው ታኅሣሥ ወር መጀመሪያ የምግብ አቅርቦት ሥራውን እንደገና ከጀመረ ወዲህ፣ በአፋር፣ አማራ፣ ትግራይና ሱማሌ ክልሎች ለ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ ዕርዳታ ማሠራጨቱን ገልጿል። ድርጅቱ አዲሱን አሠራሩን ከዘረጋ ወዲህ፣ በተጠቀሱት ክልሎች ለአደጋ ተጋላጭ የኾኑ 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሰዎችን በዲጅታል መመዝገቡንም ጠቁሟል። እስከ ሰኔ ወር ተጨማሪ 142 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ያመለከተው ድርጅቱ፣ ገንዘብ ካልተገኘ በሚያዝያ ወር ለስደተኞች የሚያቀርበውን የምግብ እርዳታ ለማቋረጥ እገደሚገደድ አስጠንቅቋል።

3፤ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ከየካቲት 04 ዓ.ም ጀምሮ ለካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፍቃድ መስጠት እንደሚጀምር ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ባለሥልጣኑ፣ ከመጭው ሰኞ ጀምሮ 15 አዳዲስ የካፒታል ገበያ ፍቃዶችን መስጠት እንደሚጀምርም ገልጿል። ባለሥልጣኑ፣ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፍቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር መመሪያ አዘጋጅቼ ወደ ሥራ ገብቻለኹ ብሏል። በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢንቨስትመንት ባንኮች ፍቃድ መስጠት እንደሚጀመር የገለጸው ባለሥልጣኑ፣ አምስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችም በዚህ ማዕቀፍ ለመካተት ዝግጅት ማድረጋቸውን አመልክቷል። ሦስት የውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮች በአገሪቱ መስራት በሚችሉበት ኹኔታ ዙሪያ ጥያቄ አቅርበው፣ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል ተብሏል።

4፤ መከላከያ ሠራዊት፣ በሕገወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ የነበረ 30 በርሚል ነዳጅ መያዙን ዛሬ ገልጧል። ነዳጁን የጫነው ኮድ 3 የኾነ ተሽከርካሪ፣ ከሶማሌ ክልል ከአፍዴር ዞን፣ ዶሎ ባይ ከተማ በመነሳት ወደ ጎረቤት ሱማሊያ ጁባላንድ ራስ ገዝ አስተዳደር ሊሻገር ሲሞክር በሥፍራው በነበሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በቁጥጥር ስር መዋሉን ሠራዊቱ አመልክቷል። በሕገወጥ መንገድ ወደ ሱማሊያ ሊወጣ የነበረው ነዳጅ 750 ሺሕ ብር የሚገመት ዋጋ ያለው እንደኾነም ሠራዊቱ ጠቅሷል። መከላከያ ሠራዊት፣ በአገሪቱ ውስጥ የዋጋ ንረትን በመፍጠር የአገርን ጥቅም የሚያሳጡ ነጋዴዎችን በኹሉም ዓለማቀፍ የድንበር መግቢያና መውጫዎች ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መኾኑንም ጠቁሟል። ነዳጁን ወደ ሱማሊያ ያጓጉዙ የነበሩት አካላት በቁጥጥር ሥር ስለመዋላቸው ወይም አለመዋላቸው ሠራዊቱ አልገለጠም።

5፤ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኩባንያ እስካለፈው ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ከአገር ውስጥ ምንጮች የሰበሰበው የብድር መጡን 117 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን ቢዝነስ ደይሊ ዘግቧል። ኩባንያው፣ ከኢትዮጵያ የፋይናንስ ገበያ የተበደረው የገንዘብ መጠን ባለፈው ሰኔ ወር 95 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ዘገባው አመልክቷል። ኩባንያው፣ በብድር ያገኘውን ገንዘብ በኢትዮጵያ ለሚያስፋፋው አገልግሎትና ለሥራ ማስኬጃ እንደሚያውለው ዘገባው ጠቅሷል። ኩባንያው እስካለፈው ታኅሳስ መጨረሻ ከኤምፔሳ አገልግሎቱ 280 ሺህ 625 ዶላር ገቢ እንዳገኘና በኢትዮጵያ የኩባንያው የኤምፔሳ አገልግሎት ተመዝጋቢዎች ቁጥርም ወደ 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን እንዳደገ ተገልጧል። ኩባንያው እስካለፈው ታኅሣሥ ወር መጨረሻ ከአገሪቱ ጠቅላላ ሕዝብ ለአንድ ሦስተኛው ተደራሽ መኾን መቻሉንም ዘገባው አመልክቷል።

6፤ ብሔራዊ ባንክ፣ በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ውስጥ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂ ናቸው ያላቸው 12 የቀድሞ የባንኩ የቦርድ አባላት ለስድስት ዓመታት በአገሪቱ በየትኛውም የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ እንዳያገለግሉ ባለፈው ሳምንት በጻፈው ደብዳቤ ማገዱን ሪፖርተር ዘግቧል። ብሔራዊ ባንክ በባንኩ የቦርድ አመራሮች ላይ ዕገዳውን የጣለው፣ ግለሰቦቹ ባንኩ ለገባበት ችግር በጋራም ኾነ በተናጠል ተጠያቂነት እንዳለባቸውን በምርመራ አረጋግጫለኹ በማለት ነው። የንብ ባንክ የቀድሞ የቦርድ አመራሮች እገዳ የተጣለባቸው፣ የገንዘብ አስቀማጮችን ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶችንና ሌሎች ግድፈቶችን ፈጽመዋል ተብለው ነው። ከታገዱት መካከል፣ የቀድሞው የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር ወልደ ተንሳይ ወልደ ጊዮርጊስ ይገኙበታል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ሐሙስ ጥር 30/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የሚያቀርቡለትን የአዳዲስ ሚንስትሮች ሹመት ያጸድቃል። ዐቢይ ከሚያቀርቧቸው አዲስ ዕጩ ተሿሚዎች መካከል፣ ከሥልጣን የተሰናበቱት የምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ምትክ እንደሚገኙበት ይጠበቃል። ምክር ቤቱ፣ የኢትዮጵያ የሜዳይ፣ ኒሻንና ሽልማት እንዲኹም የሕዝባዊ በዓላትን አከባበር ለመወሰን በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅና በሌሎች ረቂቅ አዋጆች ላይ ጭምር እንደሚወያይ ገልጧል።

2፤ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትና እናት ፓርቲን ጨምሮ አምስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ጥር 20 ቀን በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን መርዓዊ ከተማ ከ50 በላይ ንጹሃን ዜጎችን ገድለዋል ወይም ረሽነዋል በማለት በጋራ ባወጡት መግለጫ ከሰዋል። በድርጊቱ ሕጻናት፣ ሴቶች፣ አዛውንቶችና ካህናት ጭምር እንደተገደሉና እንደተረሸኑ መረዳታቸውን ፓርቲዎቹ ገልጸዋል። የመንግሥት ጸጥታ ሃይሎች ርምጃውን የወሰዱት፣ በከተማዋ በመንግሥት ወታደሮችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መካሄዱን ተከትሎ እንደኾነ ተገልጧል። ፓርቲዎቹ ድርጊቱ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ የጠየቁ ሲኾን፣ በክልል የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተራዘመው “የክልሉን ሕዝብ ስቃይ ለማራዘም ነው” በማለትም ከሰዋል።

3፤ በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ከትግራይ መቀሌ ከተማ ሞሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ኮዱ 3 በኾነ ተሽከርካሪ ወደ አማራ ክልል ባሕርዳር ሲጓጓዝ የነበረ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ትናንት አስታውቋል። የአስተዳደሩ ኮምንኬሽን ቢሮ፣ ጦር መሳሪያው በቁጥጥር ሥር የዋለው ወልድያ ከተማ ኬላ ላይ ነው ብሏል። በቁጥጥር ሥር ከዋለው ጦር መሳሪያ መካከል፣ 48 የሞርታር ቅንቡላዎች፣ 855 የዲሽቃና 389 የብሬን ጥይቶች እንደሚገኙበት ተገልጧል።

4፤ የኢትዮጵያ እስልምናን ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ የመሩት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ትናንት በመቀሌ በተካሄደ የሰላም ኮንፈረንስ ላይ መሳተፉን ምክር ቤቱ አስታውቋል። ልዑካን ቡድኑ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰበትን ነጃሺ መሰጂድም ጎብኝቷል ተብሏል። ልዑካን ቡድኑ ትናንት ወደ መቀሌ ያቀናው፣ ጠቅላይ ምክር ቤቱ እና የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በመካከላቸው ተፈጥሮ የነበረውን መቃቃር በእርቅ መፍታታቸውን ተከትሎ ነው።

5፤ የዓለማቀፉ የፍልሰት ድርጅት ምክር ቤት ሊቀመንበር ጀርመናዊቷ አምባሳደር ካታሪና ሳስች ትናንት ወደ መቀሌ አቅንተው ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳና ከዓለማቀፍ አጋር ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል። ውይይቱ፣ ለትግራይ የድርቅ ተጎጂዎች እየቀረበ በሚገኘው ሰብዓዊ ዕርዳታ ዙሪያ እንደኾነ አይ ኦ ኤም ገልጧል። ሃላፊዋ፣ በመቀሌ የሚገኝ በአይ ኦ ኤም ዕርዳታ ለ9 ሺህ 300 ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያደርገውን የተፈናቃዮች ጣቢያ ጎብኝተዋል ተብሏል። ካትሪን ኢትዮጵያ የገቡት፣ ለሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት ነው።

6፤ የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ከፍተኛ ልዑካን ቡድኖች ባሕሬን ውስጥ ባለፉት ጥቂት ቀናት ሦስት ጊዜ እንደተገናኙና በመርሆዎች መግለጫ ላይ እንደተስማሙ መስማቱን ሮይተርስ ዘግቧል። ቀደም ሲል ጅዳ ላይ ከተካሄዱት ንግግሮች በተለየ በባሕሬኑ ስብሰባ ላይ በጦር ሠራዊቱ በኩል ጀኔራል ሸምሰዲን ካባሺ እንዲኹም በፈጥኖ ደራሹ ኃይል በኩል የጀኔራል መሃመድ ደጋሎ ወንድም ሐምዳን ደጋሎ እንደተገኙ ተገልጧል። በስብሰባው ላይ፣ የኹለቱ ባላንጣ ወገኖች ደጋፊዎች የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶችና የግብጽ ባለሥልጣናት ጭምር ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተገኙ ዘገባው አመልክቷል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሐሙስ ጥር 30/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ላለፉት ሦስት ዓመታት የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር ኾነው በማገልገል ላይ የሚገኙትን ተመስገን ጥሩነህን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አድርጎ ሹሟል። ተመስገን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ኾነው የተሾሙት፣ ከኹለት ሳምንት በፊት ከሥልጣናቸው በፍቃዳቸው በለቀቁት ደመቀ መኮንን ምትክ ነው። ለበርካታ ዓመታት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና በኋላም የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አማካሪ የነበሩት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ደሞ በደመቀ መኮንን ምትክ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኾነው ተሹመዋል። በተመሳሳይ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከጤና ሚንስትርነታቸው ባነሷቸው ዶክተር ሊያ ታደሠ ምትክ ዶክተር መቅደስ ዳባን አቅርበው አስሹመዋል። ዶክተር መቅደስ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር ረዳትና የድርጅቱ ባለሙያ የነበሩ ናቸው። ሦስቱም ሹመቶች በሙሉ ድምጽ እንደጸደቁ ምክር ቤቱ ገልጧል።

2፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪያቸውን ሬድዋን ሁሴንን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አድርገው ሹመዋል። ሬድዋን የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ኾነው የተሾሙት፣ የቀድሞው የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ተመስገን ጥሩነህ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ኾነው መሾማቸውን ተከትሎ ነው። ዐቢይ በተመሳሳይ፣ ትዕግስት ሃሚድን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ወይም በምሕጻረ ቃሉ የኢንሳ ዋና ዳይሬክተር አድርገው ሹመዋል።

3፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለፉት ስድስት ወራት ለጎረቤት አገራት ከሽጠው ኤሌክትሪክ ኃይል 47 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን አስታውቋል። ኩባንያው በ6 ወራት ለኬንያ፣ ለሱዳንና ለጅቡቲ 1 ሺህ 82 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ በመመሸጥ 66 ነጥብ 27 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ እንደነበር ገልጧል። አገራቱ የገዙት ግን፣ 762 ነጥብ 8 ጊጋ ዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ እንደኾነና ይህም የዕቅዱ 71 በመቶ ብቻ እንደኾነ ኩባንያው ጠቅሷል። ለሱዳን የ11 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ታቅዶ እንደነበር የጠቀሰው ኩባንያው፣ በአገሪቱ በሚካሄደው ጦርነት ሳቢያ የተሸጠው ግን የ8 ሚሊዮን ዶላር ኤሌክትሪክ ብቻ እንደኾነ ገልጧል። ለኬንያ የተሸጠው ኃይልም፣ የ20 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደኾነ ኩባንያው ጠቅሷል። ኬንያ አንድ ኪሎ ዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ የምትገዛው በ6.5 የአሜሪካ ሳንቲም ነው።

4፤ ኦነግ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከነበሩት ለማ መገርሳ እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከነበሩት ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ከአምስት ዓመት በፊት አሥመራ ላይ የደረስንበትን ስምምነት ያፈረሰው የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት ነው በማለት ከሷል፡፡ ዐቢይ ማክሰኞ'ለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው፣ "ኦነግ ሥራውን በሠላማዊ መንገድ እየሠራ ነው፤ የታጠፈ ቃል የለም"ማለታቸው እንዳሳዘነው ኦነግ ገልጧል፡፡ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ መከልከሉንና ከፍተኛ አመራሮቹ እስከ ዛሬ ድረስ በእስር ላይ መኾናቸውን የጠቀሰው ኦነግ፣ በአዲስ አበባ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን ዋና ጽሕፈት ቤቱን ጨምሮ በርካታ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቹ ተዘግተው በመንግሥት ኃይሎች እየተጠበቁ እንደኾነ ገልጧል፡፡ መንግሥት፣ በአሥመራ ከኦነግ አመራሮች ጋር ተደረሰበት የተባለው ስምምነት ይዘቱ ምን እንደኾነ ይፋ አድርጎ አያውቅም።

5፤ በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ወደ ኬንያ የገቡ ሦስት ኢትዮጵያዊያን ትናንት ሜሩ አውራጃ ውስጥ በተሽከርካሪ አደጋ ሕይወታቸው ማለፉን ዘ ስታር ጋዜጣ ፖሊስን ጠቅሶ ዘግቧል። በአደጋው ሌሎች ስምንቱ ከባድ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸውና ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱ ዘገባው አመልክቷል። በተያያዘ፣ ባለፈው ማክሰኞ በሰሜን ምሥራቅ ኬንያ ኢሴሎ አውራጃ ወደ ናይሮቢ በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት በታጠቁ ግለሰሶች ታጅበው በሞተር ሳይክል ሲጓዙ የነበሩ ስምንት ኢትዮጵያዊያን በፖሊስ እንደተያዙና ሌሎች ሰባት ኢትዮጵያዊያን ግን በታጠቁ አጃቢዎቻቸውና በፖሊስ መካከል የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ ከአካባቢው እንዳመለጡ ተገልጧል። በመርሳቢት ግዛትም፣ በተመሳሳይ በታጣቁ ግለሰቦች ታጅበው ሲጓዙ የነበሩ 25 ኢትዮጵያዊያን ተይዘዋል ተብሏል።

6፤ በጎረቤት ሱማሊያ ጌዶ አውራጃ ዶሎው ከተማ አካባቢ የሠፈሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች በከተማዋ የሌሊት እንቅስቃሴ ገደብ እንደጣሉ የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የኢትዮጵያ ወታደሮች በከተማዋ ላይ የሰዓት ገደብ የጣሉት፣ ባለፈው ሳምንት ዕሁድ በአካባቢው በለድ ሃዎ በተባለች ከተማ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ስድስት ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን መግደላቸውን ተከትሎ ነው። በኢትዮጵያዊያኑ ላይ ተፈጸመ ለተባለው ግድያ፣ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ሃላፊነት የወሰደ አካል የለም። በግድያው ዙሪያ፣ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴርም ኾነ በሞቃዲሾ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ያሉት ነገር የለም።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ2517 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ3767 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 67 ብር ከ8166 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ1729 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ60 ከ5606 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ61 ብር ከ7718 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]