Wazema Media / Radio
48.9K subscribers
191 photos
36 videos
7 files
934 links
Wazema Radio other contents are available either in our website/social media or FM radio stations in Ethiopia. www.wazemaradio.com
Download Telegram
ለቸኮለ ማለዳ! ማክሰኞ ታኅሳስ 23/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይና የሱማሌላንድ ራስ ገዝ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ትናንት የተፈራረሙት የጋራ የትብብርና የአጋርነት መግባቢያ ሰነድ ለኢትዮጵያ በሊዝ ኪራይ ወታደራዊ ጦር ሠፈር ለማስገኘት እንደሚያስችል የጠቅላይ ሚንስትሩ የብሄራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን አስታውቀዋል። በመግባቢያ ስምምነቱ መሠረት፣ ሱማሌላንድ ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ጣቢያ 20 ኪሎ ሜትር የባሕር ዳርቻ እንደምትሰጥ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ተናግረዋል። ቢሂ፣ ኢትዮጵያ በምላሹ ለሱማሌላንድ የአገርነት እውቅናና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የባለቤትነት ድርሻ እንደምትሰጥ ገልጸዋል። ሬድዋን፣ በጉዳዩ ላይ ባንድ ወር ጊዜ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ ድርድር እንደሚደረግ ተናግረዋል።

2፤ የሱማሊያ መንግሥት ካቢኔ ኢትዮጵያና ሱማሌላንድ በደረሱበት የቀይ ባሕር በር ስምምነት ዙሪያ ለመምከር ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ ያደርጋል። ሱማሊያ፣ ሌሎች አገራት ከሱማሌላንድ ጋር የሚያደርጉትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ከባሕር በርና ወደብ ጋር የተያያዙ ስምምነቶችን አትቀበልም። ኢትዮጵያና ሱማሌላንድ የመግባቢያ የትብብር ስምምነቱን የተፈራረሙት፣ ሱማሊያና ሱማሌላንድ በመካከላቸው ያለውን ውዝግብ ለመፍታት የሚያስችላቸውን ውይይት ለመቀጠል በተስማሙ ማግስት ነው።

3- ፌደራል ፖሊስ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመተባበር ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ ከ5 ሺህ 500 በላይ የተለያዩ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ከሽጉጦች፣ ከተሠረቁ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል። ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው፣ በአፈና፣ በግድያ፣ በጦር መሣሪያ የተደገፈ ዝርፊያና ሌሎች ወንጀሎችን በመፈጸም የተጠረጠሩ እንደኾኑ አመልክቷል። በቲክቶክና ሌሎች ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች "ሐሰተኛ መረጃ" ያሠራጩ ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል። በተጠቀሱት ወንጀሎች የተሳተፉ የፖሊስ አመራሮችም በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ተገልጧል።

4- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ አካባቢ ለሚያስገነባው የኤርፖርት ከተማ መሬቱን በቅርቡ እንደሚረከብ መግለጡን ሪፖርተር ዘግቧል። አየር መንገዱ "አቦሴራ" በተባለ ሥፍራ ላይ ለሚያስገነባው የኤርፖርት ከተማ፣ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በመኾን ነዋሪዎችን ከይዞታቸው ማስነሳት መጀመሩን እንደተናገረ ዘገባው ጠቅሷል። አዲሱ የኤርፖርት ከተማ፣ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጋር በፈጣን ባቡር ይተሳሰራል ተብሏል። ለኤርፖርት ግንባታው ስንት አርሶ አደሮች ከይዞታቸው እንደሚነሱ ግን አልተገለጠም። አየር መንገዱ የኤርፖርት ከተማውን ግንባታ በአምስት ዓመት ውስጥ የማጠናቀቅ ዕቅድ እንዳለው ቀደም ሲል ገልጦ ነበር።

5፤ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በሚወዛገቡባት አቢዬ ግዛት የጎሳ ታጣቂዎች ትናንት የግዛቲቷን ምክትል አስተዳዳሪ ጨምሮ ስድስት ሰዎችን መግደላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል፣ የምክትል አስተዳዳሪው ጠባቂዎችና የግዛቲቷ ጸጥታ ተቋም ባልደረቦች እንደሚገኙበት ዘገባው ጠቅሷል። በነዳጅ ዘይት የበለጸገችውን ግዛት ላለፉት 12 ዓመታት የሚያስተዳድረው፣ ከኹለቱ አገራት የተውጣጣ ልዩ አስተዳደር ነው። ኹለቱ አገራት የግዛቲቷን ዕጣ ፋንታ በሕዝበ ውሳኔ ለመወሰን የሚያስችል ኹነኛ ድርድር ገና አላደረጉም። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ማክሰኞ ታኅሳስ 23/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች


1፤ ኢሰመኮ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጋሞ ዞን፣ አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ በሚያነሱ አካላትና በዞኑ አስተዳደር መካከል የተፈጠረው ውጥረትና ግጭት ሳይባባስ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲፈለግለት ጠይቋል። ከዞኑ ተነጥለው ልዩ ወረዳ ማቋቋም በሚፈልጉት ኤልጎ፣ ወዘቃ፣ ደምብሌና ጫሞ 01 ቀበሌዎች እና በዞኑ አስተዳደር መካከል ከጥቅምትጀመሮ አለመግባባቱና ውጥረቱ እየጨመረ መምጣቱን መረዳቱን ኢሰመኮ ጠቅሷል። ኢሰመኮ፣ አለመግባባቱ በነዋሪዎችና በጸጥታ ኃይል አባላት ላይ የሞት፣ የዘፈቀደ እስርና የንብረት ውድመት እየደረሰ ነው ብሏል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንዔል በቀለም፣ የፌዴራሉና የክልሉ መንግሥታት ከነዋሪዎችና ከዞኑ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት ውጥረቱን የሚያረግቡ ሰላማዊ ርምጃዎችን እንዲወስዱ፣ ለተፈናቃዮች አስቸኳይ ድጋፍ እንዲቀርብና በቀያቸው በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ኹኔታ እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።

2፤ የሱማሌላንድ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በሱማሌላንድና ኢትዮጵያ የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ለሱማሌላንድ የአገርነት እውቅና ለመሰጠት መስማማቷን አረጋግጧል። ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ፣ ሱማሌላንድ ከኢትዮጵያ የአገርነት እውቅና ለማግኘት ለረጅም ጊዜ ስትጥር መቆየቷን መግለጣቸውን ሚንስቴሩ ጠቅሷል። በመግባቢያ ስምምነቱ መሠረት፣ ሱማሌላንድ ለኢትዮጵያ 20 ኪሎ ሜትር የባሕር በር በ50 ዓመት የሊዝ ኪራይ ለመስጠት መስማማቷንም ሚንስቴሩ ገልጧል። ስምምነቱ፣ በኹለቱ አገሮች መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት እንደሚያረጋግጥም ሚንስቴሩ የጠቀሰ ሲኾን፣ ሱማሌላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የባለቤትነት ድርሻ እንድታገኝ እንደሚያስችላት ፕሬዝዳንት ቢሂ ትናንት የጠቀሱትን ነጥብ ግን አላነሳም። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደዔታ ምስጋኑ አረጋ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሱማሌላንድን መግለጫ እንደሚቀበለው በ"ኤክስ" ገጻቸው አረጋግጠዋል።

3፤ ሱማሊያ፣ ኢትዮጵያ ከሱማሌላንድ ራስ ገዝ ጋር የደረሰችበት የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት "ሉዓላዊነቴን የጣሰ" እና "ዋጋ ቢስ" የኾነ ስምምነት ነው በማለት አውግዘዋለች። ሱማሊያ በኢትዮጵያ የሚገኙትን አምባሳደሯን ባስቸኳይ የጠራች ሲኾን፣ አምባሳደር አብዱላሂ ዋርፋ ዛሬውኑ ወደ ሞቃዲሾ መሄዳቸው ታውቋል። አምባሳደሩ ለውይይት ባስቸኳይ እንዲጠሩ ውሳኔ ያሳለፈው፣ ኢትዮጵያና ሱማሌላንድ በደረሱበት የባሕር በር ስምምነት ዙሪያ ዛሬ ጧት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የመከረው የአገሪቱ ካቢኔ ነው። የካቢኔውን ልዩ ስብሰባ የመሩት የሱማሊያው ጠቅላይ ሚንስትር ሐምዛ ባሬ፣ መንግሥታቸው የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ ቁርጠኛ መኾኑን ገልጠዋል። ባሬ፣ የትኛውም አካል የሱማሊያን የየብስ፣ የባሕርና የአየር ሉዓላዊ የግዛት ወሰን መጣስ አይችልም በማለት አስጠንቅቀዋል።

4፤ የሱማሊያ ፓርላማ ኢትዮጵያና ሱማሌላንድ በደረሱበት የባሕር በር ስምምነት ላይ ዛሬ በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ መክሯል። ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ ለፓርላማው ባደረጉት ንግግር፣ የሱማሊያ የግዛት አንድነት ለድርድር የማይቀርብና የማይሸራረፍ ነው በማለት ተናግረዋል። ሱማሊያ አኹን ከድሮው በተሻለ ኹኔታ ውስጥ መኾኗን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፣ የኢትዮጵያ ድርጊት አልሸባብ እንደገና እንዲያንሠራራ ሊያደርግ የሚችል ነው ማለታቸው ተሰምቷል። ሱማሊያ፣ የኢትዮጵያ ድርጊት በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ላይ አደጋ የሚደቅን መኾኑን በመግለጥ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እና አፍሪካ ኅብረት በጉዳዩ ላይ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ እንዲቀመጡ ጠይቃለች። አልሸባብም፣ ስምምነቱን አውግዞ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት እንደሚፈጽም መዛቱን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል።

5፤ የሱዳን ሲቪል ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ጥምረት ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ዋና አዛዥ ጀኔራል መሃመድ ደጋሎ ጋር ትናንት በአዲስ አበባ ባካሄዱት ውይይት በጦርነቱ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራና ሰላማዊ ሰዎች ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስባቸው የሚያስችሉ ስልቶችን የሚቀይስ ኮሚቴ ለማቋቋም መስማማታቸውን የሱዳን ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ስብሰባው ጦርነቱን ለማስቆም በሲቪል ኃይሎች ጥምረት የቀረበውን የፍኖተ ካርታ የሚያጠና የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ለማቋቋምም ተስማምቷል። ውይይቱ ዛሬም እንደሚቀጥል ዘገባዎቹ አመልክተዋል። የውይይት ዓላማው፣ ሰላማዊ ሰዎችን ከጥቃት ለመጠበቅ፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ በቀላሉ ተደራሽ እንዲኾን ለማስቻልና ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ነው።

6፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ0255 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ1460 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ-ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 68 ብር ከ1057 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ4678 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ61 ከ8297 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ63 ብር ከ0663 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
Ethiopia-Somaliland deal triggers serious regional and global geopolitical ramifications

The US and China closely following the Ethiopia-Somaliland sea access deal. The US congress already approved a partnership with Somaliland that will pave the way for military and security cooperation. Ethiopia’s biggest economic partner, China, on the other hand, is opposed to Somaliland’s independence due to its implications on the Taiwan issue. Wazema Radio highlighted some important impacts of the latest deal, read here- http://tinyurl.com/42uy2aaa
የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ ስምምነት አዲስ የታሪክ እጥፋት?

አሜሪካና ቻይና በሶማሊላንድ ጉዳይ የተለያየ አቋም አላቸው። ይህ ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጥረት አጋዥም ፈታኝም እውነታ ነው። የአፍሪቃ ህብረት በተደጋጋሚ የቀረበለትን የሶማሊላንድ የዕውቅና ጥያቄ አልተቀበለም። ስምምነቱ በታቀደው መሰረት ከተጠናቀቀ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪቃ ቀንድ አዲስ የታሪክ እጥፋት እንደሚሆን በርከት ያሉ የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ። ዝርዝር መረጃዎችን ያንብቡ- http://tinyurl.com/22yhjjn9
#Somaliland
ለቸኮለ ማለዳ! ረቡዕ ታኅሳስ 24/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በቅርቡ ከአማራ ክልላዊ መንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት የፈረመው የቀድሞው አማጺ የአገው ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ አመራሮቹ በክልሉ መንግሥት መዋቅሮች ሥልጣን እንደሚሰጣቸው መግለጡን ዶይቸቨለ ዘግቧል። የቀድሞው አማጺ ከሕወሃት ጋር ወግኖ፣ በዋግኅምራ ዞን አበርገሌ እና ጻግብጂ ወረዳዎች ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲዋጋ ነበር። ንቅናቄው ከክልሉ መንግሥት ጋር በቅርቡ የተፈራረመውን የሰላም ስምምነት ትላንት በሰቆጣ ከተማ ለሕዝብ ይፋ ማድረጉን ዘገባው ጠቅሷል። ንቅናቄው ከሚያነሳቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ፣ የአገው ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቱ ሊከበርለት ይገባል የሚል ነው።

2፤ አውሮፓ ኅብረት ኢትዮጵያና ሱማሌላንድ የተስማሙትን የባሕር በር ስምምነት በተመለከተ፣ የሱማሊያን የግዛት አንድነት፣ ሉዓላዊነትና አንድነት ማክበር ያስፈልጋል ሲል በቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤቱ በኩል ባወጣው አጭር መግለጫ አቋሙን አስታውቋል። ኅብረቱ የሱማሊያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ከሕገመንግሥቷ እና ከአፍሪካ ኅብረትና ከተመድ ቻርተሮች አንጻር ማክበር፣ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ቁልፍ እንደኾነ ገልጧል።

3፤ የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ እና ከኳታሩ ኢሚር ታሚም አል ታኒ ጋር በኹለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት ማምሻውን በስልክ መወያየታቸውን ጽሕፈት ቤታቸው አስታውቋል። ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ከኹለቱ ወዳጆቻቸው ጋር በስልክ የተወያዩት፣ ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሱማሌላንድ የደረሱበትን የቀይ ባሕር የባሕር በር ስምምነት "የሱማሊያን ሉዓላዊነት የጣሰ ነው" በማለት ካወገዙ ከሰዓታት በኋላ ነው። ኾኖም ፕሬዚዳንቱ የባሕር በር ስምምነቱን በውይይታቸው ላይ ያንሱት ወይም አያንሱት አልተገለጠም።

4፤ የሱዳን ሲቪል ዲሞክራሲያዊ ኃይሎችና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት አዛዥ ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ አዲስ አበባ ውስጥ ለኹለት ቀናት ያደረጉትን ውይይት በስምምነት አጠናቀዋል። ኹለቱ ወገኖች የተፈራረሙት "የአዲስ አበባው መግለጫ" የተሰኘው ሰነድ፣ የሱዳኑ ጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ፣ ለተፈናቃዮች መመለሻ ደኅንነታቸው የተጠበቁ መተላለፊያዎች እንዲፈጠሩና ሲቪል ኃይሎች ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሚደረጉ ንግግሮች እንዲሳተፉ የሚጠይቅ ነው። በሰነዱ ላይ፣ የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ከሱዳን ጦር ሠራዊት ጋር በሚደረግ ድርድር ያለ ቅድመ ኹኔታ የተኩስ አቁም ለማድረግ ዝግጁ መኾኑን እንዳረጋገጠ ሮይተርስ ዘግቧል።[ዋዜማ]
ለቸኮለ! ረቡዕ ታኅሳስ 24/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሱማሌላንድ የአገርነት እውቅና መስጠትን ጉዳይ በሂደት በጥልቀት አጢኖ ውሳኔ ላይ እንደሚደርስ አስታውቋል። መንግሥት፣ ከሱማሌላንድ ጋር በተደረሰው የባሕር በር ስምምነት "የተጣሰ ሕግ" እንደሌለም ገልጧል። የአገሪቲ የርስበርስ ጦርነቱ በ1983 ዓ፣ም ሲያበቃ፣ ኢትዮጵያ "በታሪክም በሕግም ፊት በተፈጸመ ስህተት" የባሕር በር አልባ ኾነች ያለው መንግሥት፣ ይህን "የታሪክ ስብራትና የትውልድ ቁጭት" ለማከም ባለፉት አምስት ዓመታት አማራጮችን ሲፈትሽ መቆየቱን ጠቅሷል። በስምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ በኤደን ባሕረ ሰላጤ "ዘላቂና አስተማማኝ" የባሕር ኃይል ጦር ሠፈር እንደሚኖራትና ሱማሌላንድ ከሊዙ የሚታሰብ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንደሚኖራትም መንግሥት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

2፤ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረብርሃን ከተማ ከትናንት ሌሊት ጀምሮ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ዋዜማ ከነዋሪዎች ሰምታለች። በተለይ በደሴ መውጫ "ቀይት" በተባለ አካባቢ ከሌሊት ጀምሮ እንዲኹም "አርሴማ" በተባለ ሠፈር ከጠዋቱ 1:00 ሰዓት እስከ 2:00 ሰዓት የተኩስ ልውውጥ መስማታቸውን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል። ዛሬ ዕኩለ ቀን፣ በከተማዋ ቀበሌ 08 እና በአዲስ አበባ መውጫ "ጠባሴ" በተባለ ሠፈር፣ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበርም ነዋሪዎች ተናግረዋል። አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ፣ የፋኖ ታጣቂዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ከተማዋ መጠጋታቸውን ተከትሎ፣ በታጣቂዎችና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ለዋዜማ ተናግረዋል። ዛሬ እስከ እኩለ ቀን፣ በከተማዋ የግልና የመንግሥት ተቋማት ዝግ እንደነበሩ ዋዜማ ተረድታለች።

3፤ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የሚገኘው የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ፋብሪካው ከአንድ ዓመት በፊት ከስኳር ኮርፖሬሽን ወጥቶ በቦርድ መተዳደር ሲጀምር መንግሥት ለፋብሪካው የሠረዘው ከ531 ሚሊዮን ብር በላይ ዕዳ እንደገና አልተሰረዘም መባሉ ግራ እንዳጋባቸው ለዋዜማ ተናግረዋል። የፋብሪካው አስተዳደር፣ ዕዳውን ለመክፈል በዕረፍት ቀናት ጭምር ያለ ትርፍ ሰዓት ክፍያ እንዲሠሩ እንዳዘዛቸው ሠራተኞቹ ገልጸዋል። ሠራተኞቹ፣ ፋብሪካው ከኹለት ወር በላይ ደምወዝ ሊከፍል እንደማይችል ተነግሮናል ብለዋል። ፋብሪካው በስሩ ከ2ሺህ 700 በላይ ቋሚና ከ10 ሺህ በላይ ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉት። ዋዜማ በጉዳዩ ዙሪያ የፋብሪካውን አስተዳደር አስተያየት ለማካተት ያደረገችው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።

4፤ ሱማሊያ፣ የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ወርቅነህ ገበየሁ በኢትዮጵያና ሱማሊያ የሰሞኑ ግንኙነት ዙሪያ ዛሬ ላወጡት መግለጫ "ይቅርታ እንዲጠይቁ፣ መግለጫቸውን እንዲሰርዙና እርማት እንዲሰጡ" ጠይቃለች። ሱማሊያ በወርቅነህ መግለጫ ቅሬታ እንዳደረባት ገልጣ፣ መግለጫው ኢትዮጵያ የሱማሊያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጣሷን አላወገዘም በማለት ወቅሳለች። ሱማሊያ በመግለጫው እንደማትስማማና ለኢትዮጵያ ያደላ መግለጫ አድርጋ እንደምትቆጥረውም ገልጣለች። ሱማሊያ ለኢጋድ ይህን ምላሽ የሰጠችው፣ ወርቅነህ በኹለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው አዲስ ክስተት በእጅጉ እንዳሳሰባቸው በመግለጥ፣ አገራቱ ችግሩን በበሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱት ጥሪ ላቀረቡት መግለጫ ነው።

5፤ የሱማሌላንድ ሚንስትሮች ምክር ቤት ሱማሌላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችውን የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት አጽድቋል። የሱማሊያ መንግሥት በስምምነቱ ዙሪያ ያወጣቸውን መግለጫዎች ያወገዘችው ሱማሌላንድ፣ ሱማሊያ ከድርጊቷ እንድተቆጠብ አሳስባለች። ሱማሌላንድ፣ የሱማሊያ መንግሥት ድርጊቶች ካኹን ቀደም በሱማሌላንድና ሱማሊያ መካከል የተደረሱ ስምምነቶችን እንደሚጻረሩ ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ ሊገነዘብ ይገባል ብላለች። ሌሎች አገራት "የኢትዮጵያ ፈለግ በመከተል" የአገርነት እውቅና እንዲሰጧትም ሱማሌላንድ ጠይቃለች።

6፤ አውሮፓ ኅብረት ኢትዮጵያና ሱማሌላንድ ሰኞ'ለት የተፈራረሙትን የባሕር በር ስምምነት በተመለከተ በቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤቱ በኩል ባወጣው መግለጫ፣ የሱማሊያን የግዛት አንድነት፣ ሉዓላዊነትና አንድነት ማክበር ያስፈልጋል በማለት አቋሙን ገልጧል። ኅብረቱ፣ የሱማሊያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ከሕገመንግሥቷ እንዲኹም ከአፍሪካ ኅብረትና ከተመድ ቻርተሮች አንጻር ማክበር፣ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ቁልፍ ጉዳይ ነው ብሏል።

7፤ የሱማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ የመሩት የሱማሌላንድ መንግሥት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ዛሬ ለጉብኝት ጅግጅጋ ከተማ ገብቷል። ልዑካን ቡድኑ ጅግጅጋ ሲገባ፣ የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ መሐመድና ሌሎች የክልሉ ባለሥልጣናት አቀባበል አድርገውለታል። የሱማሌላንድና የሱማሌ ክልል አመራሮች፣ በንግድና በጋራ ድንበሩ አከባቢ ባሉ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል። ከኢትዮጵያ ፌደራል ክልሎች፣ ከራስ ገዟ ሱማሌላንድ ጋር የሚዋሰነው ሱማሌ ክልል ነው።

8፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ0361 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ1568 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 67 ብር ከ8296 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ1862 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ61 ከ5220 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ7524 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ሐሙስ ታኅሳስ 25/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ንግድ ሚንስቴር፣ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካን በባለቤትነት እንዲጠቀልል የቀረበለትን ጥያቄ ማጽደቁን ሪፖርተር አስነብቧል። ቢጂአይ የሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ሠራተኞችን ቅጥር፣ ጥቅማጥቅምና የቢራውን የንግድ ምልክት ማስቀጠል እንዳለበት ሚንስቴሩ አዟል ተብሏል። ቢጂአይ ኪሳራ ውስጥ የገባውን ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ከአንድ ዓመት በፊት ከዲያጎ ኩባንያ የገዛው በ64 ብር ሒሳብ ብቻ እንደኾነ ዘገባው ጠቅሷል።

2፤ ሱማሌላንድ፣ ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ ከኢትዮጵያ ጋር የፈረመችውን የባሕር በር መግባቢያ ስምምነት እንዲያከብርላት ጠይቃለች። ሱማሌላንድ፣ ዓለማቀፍና ቀጠናዊ አካላት በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ሚና እንዲገነዘቡላትና፣ ከሱማሊያ ነጥለው እንዲያይዋትም ትናንት ማምሻውን ባወጣችው መግለጫ ጠይቃለች። ከተለያዩ አገራት ጋር የተለያዩ ውሎችን መፈጸሟን የገለጠችው ሱማሌላንድ፣ በአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አካላት ለዓለማቀፍ ትብብር መርኾዎችና ለዲፕሎማሲያዊ አሠራሮች ተገዥ መኾን አለባቸው ብላለች።

3፤ ግብጽ፣ ሱማሊያ በግዛቷ ላይ ያላት ሉዓላዊነት ሊከበርላት እንደሚገባ አሳስባለች። የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ፣ ግብጽ የሱማሊያን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ማናቸውንም ድርጊት አትቀበልም ብሏል። በአፍሪካ ቀንድ አንዳንድ አገራት እየወሰዷቸው ያሉት ርምጃዎች ቀጠናውን አለመረጋጋት ውስጥ የሚከቱ እንደኾኑም ግብጽ ገልጣለች። አገራት በአፍሪካ ኅብረት ቻርተር መሠረት፣ ድንበሮችን ለማክበር የገቡትን ቃል እንዲያከብሩም ግብጽ ጠይቃለች። ግብጽ ይህኑ መግለጫውን ያወጣችው፣ ኢትዮጵያና ሱማሌላንድ ሰኞ'ለት የፈረሙትን የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት በማስታከክ ነው።

4፤ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ ትናንት ናይሮቢ ውስጥ ከኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር ተወያይተዋል። ፕሬዝዳንት ሩቶና ጀኔራል ደጋሎ ስላደረጉት ውይይት ዝርዝር መግለጫ አልሰጡም። ኾኖም ፕሬዝዳንት ሩቶ፣ ጀኔራል ደጋሎ የሱዳኑ ጦርነት እንዲያበቃ እያደረጉት ያለውን ጥረት አድንቀዋል። ጀኔራል ደጋሎ ወደ ኬንያ ያቀኑት፣ በኡጋንዳ፣ ጅቡቲና ኢትዮጵያ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ነው።

5፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኡጋንዳን ጨምሮ አራት የአፍሪካ አገራትን ከአሜሪካው የአፍሪካ የቀረጥ ነጻ ንግድ ዕድል (አጎዋ) በይፋ አግደዋል። ከኡጋንዳ በተጨማሪ ከአጎዋ በይፋ የታገዱት፣ ጋቦን፣ ኒጀር እና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ናቸው። የእገዳው ምክንያት፣ አገራቱ በአጎዋ ስምምነት መሠረት የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች ባለማክበራቸው እንደኾነ ተገልጧል። ኡጋንዳ ከአጎዋ የታገደችው፣ የአገሪቱ መንግሥት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት የሚያደርጉ ሰዎችን እስከ ሞት በሚደርስ ቅጣት ለመቅጣት ያወጣው አዲስ ሕግ ሰብዓዊ መብቶችን ይጥሳል በማለት ነው። ፕሬዝዳንት ባይደን አራቱን አገራት ከአጎዋ ለማገድ ያላቸውን ፍላጎት ለአሜሪካ ሕግ አውጭ ምክር ቤት የገለጡት ባለፈው ጥቅምት ነበር። ባይደን፣ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ያገዱበትን ውሳኔያቸውንም እስካኹን አላነሱም። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሐሙስ ታኅሳስ 25/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በኦሮሚያ ክልል አዲስ በተዋቀረው ምሥራቅ ቦረና ዞን፣ ጉሚ ኤልደሎ ወረዳ ማክሰኞ'ለት በመከላከያ ሠራዊትና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራው አማጺ ቡድን መካከል በተካሄደ ከባድ ውጊያ አራት ንጹሃን ሕይወታቸው ማለፉን ዋዜማ በሥፍራው ካሉ ምንጮቿ አረጋግጣለች። ውጊያው በወረዳው ልዩ ስሙ "ቦባ" በተባለ ሥፍራ መደረጉን የገለጡት ምንጮች፣ በውጊያው ሳቢያ ከነገሌ ቦረና ወደ ሞያሌ የሚወስደው ዋናው መንገድ ይህ ዜና እየተጠናቀረበት ዛሬ ዕኩለ ቀን ድረስ መዘጋቱን ዋዜማ ተረድታለች። በውጊያው፣ ከኹለቱም ወገን ቁጠራቸው በውል ያልታወቁ ተዋጊዎች እንደተገደሉም ምንጮች ገልጸዋል። ውጊያው፣ የመንግሥት ኃይሎች በአማጺ ቡድኑ ቁጥጥር ስር የሚገኙ አካባቢዎችን ለማስለቀቅ ያደርጉት እንደኾነ ዋዜማ ባደረገችው ተረድታለች።

2፤ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከትላንት ምሽት ጀምሮ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ በከፊል መቋረጡን ዋዜማ ካሰባሰበቻቸው መረጃዎች ተረድታለች። የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ከተገደበባቸው መስመሮች መካከል፣ ከአዲስ አበባ ወደ አምቦ በከፊል፣ ከአምቦ ወደ ነቀምት ሙሉ ለሙሉ፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን ወደ መንዲ፣ ነጆ እና ቂልጡ ካራ የሚወስደው መንገድ፣ ወደ ቄለም ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተማ እና ከድሬዳዋ ወደ ሐረር ከተማ የሚወስዱ መንገዶች እንደሚገኙበት ምንጮች ተናግረዋል። ወደ ኢሉባቦር ዞን የሚወስደው መንገድ በከፊል፣ ከአዲስ አበባ ወደ ምዕራብ ሸዋ ዞን አደአ በርጋ፣ ወልቂጤ፣ አቡና ግንደበረት እንዲኹም ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ ከተማ የሚወስዱ መንገዶችም ለተሽከርካሪዎች ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት እንዳለባቸውና በዚህም ሳቢያ ዝግ እንደኾኑ ዋዜማ ተረድታለች።

3፤ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አንዳንድ የኃይማኖት አባቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኃይማኖቶች መሠረታዊ ተልዕኮና ዓላማ ጋር በተጻረረ ኹኔታ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው፣ አፍራሽና ደም አፋሳሽ ስብከቶችን እያስተላለፉ ይገኛሉ ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ከሷል። አንዳንድ የኃይማኖት አባቶች የሚያስተላልፏቸው ስብከቶችና ንግግሮች ፖለቲካዊና ፖለቲከኞችን የሚደግፉ ወይም የሚተቹ መኾናቸውን የጠቀሰው ጉባዔው፣ አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ የቀስቃሽነት አዝማሚያ ያላቸው መኾናቸው በእጅጉ አሳሳቢ እንደኾነ ገልጧል። ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ስብከቶች የሰላም፣ የመከባበርና የአብሮነት እሴትን የሚጎዱ በመኾናቸው ከወዲሁ መታረም እንዳለባቸውና የኃይማኖት ተቋማት እንዲህ ዓይነት ስብከቶችን የሚሰብኩ አባቶችና አስተማሪዎች እንዲታረሙ እንዲያደርጉ ጉባዔው አሳስቧል። ጉባዔው፣ ፖለቲካዊና አፍራሽ ስብከቶችን የሰበኩ የኃይማኖት አባቶችን ስም ወይም ስብከቶቹ የተሰበኩባቸውን ቤተ ዕምነቶች በስም አልጠቀሰም።

4፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ያረቀቀው አዲሱ የዲፕሎማቲክ መብቶችና ጥቅሞች ረቂቅ አዋጅ ላይ ዛሬ በሚንስቴሩ ቅጥር ግቢ ውስጥ ውይይት ተደርጎበታል። ረቂቅ አዋጁ የተዘጋጀው፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት የአገሪቱን ሕጎች አክብረው ተልዕኳቸውን ባግባቡ እንዲወጡ ለማገዝና ኢትዮጵያዊያን ባለድርሻ አካላት የውጭ ዲፕሎማቶችን መብቶችና ጥቅሞች ተረድተው ለአፈጻጸማቸው እገዛ እንዲያደርጉ ለማስቻል እንደኾነ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በውይይቱ ላይ ተናግረዋል። በረቂቅ አዋጁ ላይ በተደረገው ውይይት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተሳትፈዋል። ረቂቅ አዋጁ በተጨማሪ ግብዓቶች ከዳበረ በኋላ፣ ለሚንስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል።

5፤ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ፣ ኢትዮጵያና ሱማሊያ በተረጋጋና በመከባበር ላይ በተመሠረተ መንፈስ ሰሞኑን በመካከላቸው የተፈጠረውን ውጥረት እንዲያረግቡና ችግሩን በውይይት እንዲፈቱ ጠይቀዋል። ፋኪ፣ ኹለቱ አገሮች በመካከላቸው ያለውን መልካም ግንኙነት ሊያበላሽ ከሚችሉ ማናቸውም ርምጃዎች እንዲቆጠቡም ዛሬ ባወጡት መግለጫ አሳስበዋል። የኢትዮጵያንና ሱማሊያን ጨምሮ የኹሉንም የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማክበር እንደሚገባ ፋኪ በመግለጫቸው አስምረውበታል።

6፤ አሜሪካ፣ ለሱማሌላንድ እውቅና እንደማትሰጥ አስታውቃለች። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር ኢትዮጵያ ቀይ ባሕር ላይ የባሕር በር ለማግኘት ከሱማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ፣ አሜሪካ በፈረንጆች በ1960 በተወሰነው የሱማሊያ ዓለማቀፍ ድንበር መሠረት የአገሪቱን ግዛትና ሉዓላዊነት እንደምትቀበል ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። አሜሪካ በምሥራቅ አፍሪካ በተፈጠረው አዲስ ውጥረት ትልቅ ስጋት እንዳደረባት የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ ኹሉም ባለድርሻ አካላት በዲፕሎማሲያዊ ውይይት ችግሩን እንዲፈቱ ጠይቀዋል። ሱማሌላንድና ሱማሊያ እኤአ በ1960 ከብሪታኒያና ጣሊያን ቅኝ ግዛትነት ነጻ ወጥተው ኹለት ሉዓላዊ አገሮች የነበሩ ሲኾን፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን ሱማሌላንድ በዚያው ዓመት ከሱማሊያ ጋር በፍቃዷ መዋሃዷ ይታወሳል።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ0456 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ1665 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 67 ብር ከ5735 ሳንቲም እና መሸጫው 68 ብር ከ9250 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ61 ከ1962 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ4201 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ኢትዮጵያ የብድር ወለድ ዕዳ አለመክፈሏ የሀገሪቱን የመበደር ተስፋና ባለሀብቶችን የመሳብ ዕድሏን አኮስሶታል። ለመሆኑ ሀገሪቱ 33 ሚሊየን ዶላር ለመክፈል እንዴት ተሳናት? በጉዳዩ ላይ ይህን ውይይት አድርገናል። ተጋበዙልን- https://youtu.be/YUZvsycaI78?si=qKBmtTBruYNfwPzB
ለቸኮለ ማለዴ! ዓርብ ታኅሳስ 26/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ትናንት በኦሮሚያ ክልል በርካታ ከተሞችና ዋና ዋና የመኪና መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ኾነው ውለዋል። በዕለቱ፣ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት እና የጭነት ተሽከርካሪዎች በበርካታ ከተሞችና ክልሎችን በሚያገናኙ መንገዶች ላይ ከእንቅስቃሴ ታቅበዋል። የሕዝብ ማመላለሻዎችና የጭነት ተሽከርካሪዎች አገልግሎት ከተቋረጠባቸው ክልል አቋራጭ መንገዶች መካከል፣ ከኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ ወደ ጋምቤላ ክልል ጋምቤላ ከተማ፣ ከኦሮሚያ ክልል ጊምቢ በነጆ ከተማ በኩል ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ፣ ከኦሮሚያ ክልል ነገሌ ቦረና ዉደ ሲዳማ ክልል አዋሳ ከተማ እንዲኹም ከአዲስ አበባ በወሊሶ በኩል ወደ ጂማ ከተማ የሚወስዱ መንገዶች ይገኙበታል። ተሽከርካሪዎች በተጠቀሱት መንገዶች ላይ ከጉዞ የታቀቡት፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኦሮሚያ ክልል የትራንስፖርት አድማ እንዲደረግ አቅርቦታል በተባለው ጥሪ ሳቢያ እንደኾነ ተነግሯል።

2፤ ንግድ ሚንስቴር ከታኅሳስ 26 ጀምሮ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ባለፈው አንድ ወር ሲሸጥበት በነበረው ዋጋ እንደሚቀጥል አስታውቋል። በሚንስቴሩ ተመን መሠረት፣ የአንድ ሊትር ቤንዚን 77 ብር ከ65 ሳንቲም፣ ኪሮሲን በሊትር 79 ብር ከ75 ሳንቲም፣ ጥቁር ናፍጣ በሊትር ብር ከ ሳንቲም፣ ነጭ ናፍጣ 79 ብር ከ75 ሳንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ በሊትር 62 ብር ከ36 ሳንቲምና ከባድ ጥቁር ናፍጣ በሊትር 61 ብር ከ16 ሳንቲም ሲሸጥ ቆይቷል።

3፤ ሱዳን፣ ኢትዮጵያና ሱማሌላንድ የደረሱበትን የባሕር በር ስምምነት እንደማትቀበለው አስታውቃለች። ለሱማሊያ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ያላትን ድጋፍ የገለጠችው ሱዳን፣ በስምምነቱ ዙሪያ የተፈጠረው ቀውስ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጠይቃለች። ቱርክም፣ የሱማሊያ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ሊከበር እንደሚገባው በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ በኩል አስታውቃለች።

4፤ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ዋና አዛዥ ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ ትናንት ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንተው በፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ጋር በሱዳኑ ጦርነት ዙሪያ መወያየታቸውን አስታውቀዋል። ጀኔራል ደጋሎ፣ በሱዳን ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን፣ ደቡብ አፍሪካና ፕሬዝዳንት ራማፎዛ መጫወት የሚችሉትን ሚና ጭምር ለራማፎዛ እንዳነሱላቸው ጀኔራል ደጋሎ ጠቅሰዋል። ውይይቱን ተከትሎ፣ ፕሬዝዳንት ራማፎዛ፣ በሱዳን አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግና ግጭት በዘላቂነት ማቆም የሚያስችል ንግግር እንዲጀመር ጥሪ አድርገዋል።

5፤ ሱዳን በኬንያ የሚገኙትን አምባሳደሯን ለምክክር ጠርታለች። ሱዳን አምባሳደሯን የጠራችው፣ የኬንያ መንግሥት ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ዋና አዛዥ ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ ኦፊሴላዊ አቀባበል አድርጓል በማለት ተቃውሞዋን ለመግለጽ እንደኾነ ገልጣለች። ጀኔራል ደጋሎ ከትናንት ወዲያ በፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር በሱዳኑ ጦርነት ዙሪያ ለመነጋገር ናይሮቢ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር። የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት፣ ኬንያ ለለፈጥኖ ደራሹ ኃይል ወገንተኛ ናት በማለት ሲከስ ቆይቷል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ዓርብ ታኅሳስ 26/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከማክሰኞ ምሽት ጀምሮ የተገደበው የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ዛሬም መቀጠሉን ዋዜማ ከየስፍራው ባሰባሰበችው መረጃ ተረድታለች። በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ኹሉንም ወረዳዎች ከዞኑ ዋና ከተማ ሻምቡ ጋር የሚያገናኙ መንገዶች፣ በቄለም ወለጋ ዞን ወደ ደምቢዶሎ ከተማ የሚወስዱ መንገዶች፣ ከአምቦ ወደ ምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምት ከተማ የሚወስደው ዋናው መንገድ እንዲኹም በምዕራብ ወለጋ ዞን መንዲ፣ ነጆ እና ጊምቢ በመሳሰሉ ከተሞች የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ዛሬም እንደተገደበ መኾኑን ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል። አልፎ አልፎ በሚደረጉ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ላይ፣ አሽከርካሪዎች ከፍተኛ የታሪፍ ጭማሪ እያደረጉ እንደኾነም ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። ክልሉን ከአጎራባች ክልሎች ጋር በሚያገናኙ አንዳንድ መንገዶች ላይ ጭምር የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ተገድቧል። የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ የተገደበው፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በክልሉ የትራንስፖርት አድማ እንዲደረግ አቅርቦታል በተባለው ጥሪ ሳቢያ እንደኾነ ተነግሯል።

2፤ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ ከተማ አሶሳ ወደ ካማሺ ዞን ዋና ከተማ ካማሽ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ከተቋረጠ ከአምስት ዓመት በላይ እንደኾነው ዋዜማ ሰምታለች። አንድ የክልሉ የጸጥታ ዘርፍ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ መንገዱ ከአምስት ዓመታት በላይ መዘጋቱን አረጋግጠው፣ አልፎ አልፎ በወታደር እጀባ የመንግሥት ኃላፊዎች በተሽከርካሪ ያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴም ካለፉት ኹለት ወራት ወዲህ ሙሉ በሙሉ መቋረጡን ለዋዜማ ተናግረዋል። መንገዱ መቼ እንደሚከፈት የምናውቀው ነገር የለም ያሉት ኃላፊው፣ ጉዳዩ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትን የሚመለከት እንደኾነ ጠቁመዋል። የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ክልሉን ከኦሮሚያ ጋር በሚያዋስኑት አከባቢዎች የፈጠሩት የጸጥታ ችግር፣ እስካኹንም እንዳልተፈታ ሃላፊው ገልጠዋል። አንድ የካማሽ ከተማ ነዋሪም፣ ቀደም ሲል ለትራንስፖርት 200 ብር ገደማ ይከፍሉ የነበሩ መንገደኞች፣ ሰሞኑን በተከፈተ አዲስ ተለዋጭ መንገድ ከ1 ሺሕ ብር በላይ ከፍለው ወደ አሶሳ እየተጓዙ መኾኑን ለዋዜማ ተናግረዋል። ከአሶሳ ዞን ወደ ካማሽ ከተማ የሚወስደው የመኪና መንገድ፣ ምዕራብ ወለጋ ዞን ውስጥ የሚገኙትን ነጆ እና መንዲ ከተሞችን ያቋርጣል።

3፤ የደብረ ብርሃን ከተማና የአካባቢው ጸጥታ ዕዝ በከተማዋ የሚታየውን ወቅታዊ የጸጥታ ኹኔታ ከግምት በማስገባት ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰኑ ቀናት በባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ላይ የእንቅስቃሴ እገዳ ጥሏል። የባጃጅ አሽከርካሪዎች ከዕውቅናው ውጭ ከማሽከርከር እንዲቆጠቡ ያሳሰበው የጸጥታ ዕዙ፣ እገዳውን በሚጥሱ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች ላይ አስፈላጊውን የሕግ ርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቋል። በደብረ ብርሃን ከተማ ታኅሥሣ 24 በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሳቢያ፣ በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት መድረሱን የጸጥታ ዕዙ አመልክቷል። ኾኖም የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ችግሩን በቁጥጥር ስር በማዋላቸው የመንግሥትና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው እንደተመለሱ ተገልጧል። የጸጥታ ዕዙ እገዳውን የጣለው፣ በከተማዋ ከማክሰኞ ሌሊት ጀምሮ እስከ ትናንት እኩለ ቀን ድረስ በመንግሥት ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት መካሄዱን ተከትሎ ነው።

4፤ የአማራ ክልላዊ መንግሥት በዘጠኝ ዞኖች በተከሰተው ከባድ ድርቅ ሳቢያ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ጠባቂ እንደኾኑ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ማስታወቁን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። የክልሉ አደጋ መከላከል ኮሚሽን፣ የክልሉ መንግሥት ለድርቁ ተጎጂዎች ከ4 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን ዛሬ ባሕርዳር ውስጥ በድርቁና በምላሽ አሰጣጡ ላይ በመከረ መድረክ ላይ መናገሩን ዘገባው ጠቅሷል። ድርቁ ላስከተለው ጉዳት አፋጣኝ ምላሽ ካልተሰጠ፣ የከፋ ጉዳት ሊደርስ ይችላል በማለት የክልሉ ግብርና ቢሮ ማስጠንቀቁንም ዘገባው አመልክቷል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን በበኩላቸው፣ በስም ያልጠቀሷቸው አንዳንድ አካላት ድርቁን ለፖለቲካዊ ፍጆታ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ በማለት ከሰዋል ተብሏል።

5፤ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ከሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐመድ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ ኅብረቱ ለሱማሊያ አንድነት፣ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሙሉ ድጋፉን እንደሚሰጥ በድጋሚ እንዳረጋገጡላቸው በ"ኤክስ" ገጻቸው አስታውቀዋል። ቦሬል፣ የአፍሪካ ቀንድ ተጨማሪ ውጥረቶችን አይፈልግም ብለዋል። ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሱማሌላንድ ሰኞ'ለት የተፈራረሙትን የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ፣ የአውሮፓ ኅብረት በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የሱማሊያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ማክበር ቁልፉ ጉዳይ ነው ሲል ማክሰኞ'ለት አቋሙን ገልጦ ነበር። ብሪታኒያም፣ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ሰሞኑን የተፈጠረው ውጥረት እንዳሳሰባት ገልጣ፣ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ጠይቃለች። ብሪታኒያ፣ የሱማሊያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ሙሉ በሙሉ እንደምታከብርም አስታውቃለች።

6፤ ኤርትራ፣ ትናንት ሩሲያ ቃል የገባችላትን 25 ሺህ ቶን ነጻ ስንዴ ምጽዋ ወደብ ላይ ተረክባለች። ኤርትራ ነጻውን የስንዴ ልገሳ የተረከበችው፣ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የምግብ ዋስትና ችግር አለባቸው ላሏቸው ስድስት ወዳጅ የአፍሪካ አገራት ለእያንዳንዳቸው እስከ 25 ሺህ ቶን የሚደርስ ስንዴ በነጻ እንደሚለግሱ ባለፈው ሐምሌ በገቡት ቃል መሠረት ነው። ከኤርትራ በተጨማሪ ለሩሲያ ነጻ የስንዴ ልገሳ የተመረጡት፣ ሱማሊያ፣ ማሊ፣ ዚምባብዌ፣ ቡርኪናፋሶና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ናቸው። ሱማሊያ፣ ማሊና ዚምባብዌ ባለፉት ኹለት ወራት ነጻውን ስንዴ ተረክበዋል።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ0501 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ1711 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 67 ብር ከ8465 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ2034 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ61 ከ3076 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ5338 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
የጠሚር ዐቢይ መንግስት ከ4 ዓመት በፊት "ሀገር በቀል" ነው ያለውን የኢኮኖሚ ዕቅድ ይፋ አድርጎ ነበር። ይህ ዕቅድ በእርግጥ "ሀገር በቀል" ስለመሆኑ፣ ብሎም አሁን ከገባንበት የኢኮኖሚ ፈተና ያወጣናል ወይ? ብለን ከባለሙያዎች ጋር ይህን አጭር ውይይት አድርገናል። ታጋበዙ -https://youtu.be/g06dKD6igKA?si=aK5yuNWhP2SHDe76
ለቸኮለ ማለዳ! ቅዳሜ ታኅሳስ 27/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ኦነግ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በኦሮሚያ ክልል የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ትደግፋላችኹ በማለት ሰላማዊ ዜጎችን ሰሞኑን ማሠሩንና መግደሉን ቀጥሎበታል ሲል አዲስ ባወጣው መግለጫ ከሷል። ኦነግ፣ ባለፈው ረቡዕ እና ሐሙስ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎችና የፋኖ ታጣቂዎች በአማራ ክልል ኦሮሚያ ልዩ ዞን ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ 17 ንጹሃን ሰዎችን ገድለው ሌሎች 78 ሰዎችን አቁስለዋል ብሏል። በምዕራብ ወለጋ ዞንም፣ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ታህሳስ 22 ቀን ስምንት ሰላማዊ ዜጎችን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ትደግፋላችኹ በሚል ሰበብ ካሠሯቸው በኋላ ጫካ ውስጥ ረሽነዋል በማለት ኦነግ ከሷል።

2፤ የአገው ብሄራዊ ሸንጎ አማጺው የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር ሰሞኑን የተፈራረመው የሰላም ስምምነት የአገው ብሄረሰብን ፍላጎት አያሳካም ሲል ውድቅ እንዳደረገው ዶይቸቨለ ዘግቧል። ስምምነቱ "በጫናና በግለሰቦች ፍላጎት" ላይ የተመሠረተ ነው በማለት የተቸው ሸንጎው፣ ስምምነት ኹሉንም ለአገው ሕዝብ የሚታገሉ ድርጅቶች ማካተት ነበረበት በማለት እንዳጣጣለው ዘገባው ጠቅሷል። የቀድሞው አማጺ ግን ትችቱን እንደማይቀበለው ገልጧል ተብሏል።

3፤ የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ ትናንት ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን ጋር በኢትዮጵያ እና ሱማሌላንድ የባሕር በር ስምምነት ዙሪያ በስልክ መወያየታቸውን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን፣ በሱማሊያና ኢትዮጵያ መካከል ሰሞኑን የተፈጠረው ውጥረት የሱማሊያን የግዛት አንድነት መሠረት አድርጎ እንዲፈታ እንደሚፈልጉ መግለጣቸውን ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ፕሬዝዳንት ሞሃመድ፣ ከኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቪኒ ጋር ጭምር በቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል ተብሏል።

4፤ የሱዳን ጦር ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል ቡርሃን ከፈጥኖ ደራሹ ኃይል ጋር እርቅ አይታሰብም ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። ጀኔራል ቡርሃን፣ ባላንጣቸው ጀኔራል ደጋሎ ሰሞኑን አዲስ አበባ ውስጥ ከሱዳን ሲቪል ኃይሎች ጋር የተፈራረሙትን የተኩስ አቁም የስምምነት ሰነድ ውድቅ ማድረጋቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ጀኔራል ቡርሃን፣ ጀኔራል ደጋሎን ሰሞኑን ተቀብለው ያስተናገዱትን ኢትዮጵያን፣ ኬንያንና ደቡብ አፍሪካን ወቅሰዋል ተብሏል። ጀኔራል ቡርሃን ከባላንጣቸው ጋር እርቅ እንደማይታሰብ የተናገሩት፣ ኢጋድ ኹለቱን ጀኔራሎች ፊት ለፊት ለማገናኘት ጥረት እያደረገ ባለበት ሰዓት ነው።

5፤ በዓለም ገበያ የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ትናንት በአማካይ የ1 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ዓለማቀፍ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። የነዳጅ ዋጋ ትናንት መጠነኛ ጭማሪ ያሳየው፣ በመካከለኛው ምሥራቅና ቀይ ባሕር አካባቢ በቀጠለው ግጭትና የነዳጅ ትራንስፖርት መስተጓጎል ሳቢያ እንደኾነ ዘገባዎቹ አመልክተዋል። የዋጋ ጭማሪውን ተከትሎ፣ ትናንት በአሜሪካ ገበያ "ብሬንት" የተሰኘው ድፍድፍ ነዳጅ በበርሜል ወደ 78 ብር ከ76 ሳንቲም እንደተሸጠ ተገልጧል። የኢትዮጵያ ንግድ ሚንስቴር፣ የጥር ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ በታኅሳስ ወር ዋጋ እንደሚቀጥል መግለጡ ይታወሳል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ቅዳሜ ታኅሳስ 27/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የብሄራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን ኢትዮጵያ ለሱማሌላንድ እውቅና በመስጠት ጉዳይ ላይ ከውሳኔ የምትደርሰው የመጨረሻው የባሕር በር ስምምነት ተፈርሞ የባሕር በሩን ስትረከብ እንደኾነ ለመንግሥታዊ ቴሌቪዥን በሰጡት ማብራሪያ አስታውቀዋል። ሬድዋን፣ ኢትዮጵያ ለባሕር ኃይልና ለባሕር ንግድ ማዕከል መገንቢያ እንደምታገኘው የሚጠበቀው ቦታ በበርበራና ዘይላ ወደቦች መካከል እንደሚገኝ ገልጸዋል። ቦታው ከኢትዮጵያ ድንበር ጋር በባቡርና የብስ መንገድ እንዲገናኝ ስምምነት ላይ እንደተደረሰም ሬድዋን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ በምላሹ ለሱማሌላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ብዛቱ ወደፊት የሚወሰን ድርሻ ለመስጠት መስማማቷን የገለጡት ሬድዋን፣ የድርሻው ብዛት የሚወሰነው ኢትዮጵያ ወደፊት ለባሕር በሩ ለመክፈል በምትስማማው የሊዝ ኪራይ መጠን ላይ እንደሚኾን ተናግረዋል።

2፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ከሱማሌላንድ ጋር በባሕር በር ዙሪያ በደረሱበት የመግባቢያ ስምምነት ሳቢያ ከሱማሊያ ጋር የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ወደ ሞቃዲሾ ስልክ ደውለው ምላሽ ሳያገኙ መቅረታቸውን ከኢጋድ ምንጮች ሰምቻለኹ ሲል ዘ ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ ዘግቧል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ ኢትዮጵያ የሱማሊያን የግዛት አንድነት የመጣስ ፍላጎት እንደሌላት ለሞቃዲሾ ባለሥልጣናት ለማስረዳት ፈልገው እንደነበር ዘገባው ጠቅሷል። ኢትዮጵያና ሱማሌላንድ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት ዝርዝር ይዘት በጽሁፍ እስካኹን ይፋ አላደረጉም።

3፤ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ከመቅደላው ጦርነት በኋላ የእንግሊዝ ወታደሮች ከመቅደላ የዘረፏቸውን ታሪካዊ ቅርሶች ዛሬ ተረክቧል። ለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ እንግሊዝ ውስጥ ከተለያዩ አካላት አስመልሶ ለባለሥልጣኑ ካስረከባቸው ቅርሶች መካከል፣ የአጤ ቴዎድሮስ ልጅ የልዑል ዓለማየሁ የጸጉር ዘለላ፣ ኹለት በብር የተለበጡ የቀንድ ዋንጫዎች፣ አንድ የቀንድ ዋንጫ፣ ስለ ልዑል ዓለማየሁ የተጻፉ የተለያዩ ደብዳቤዎችና በመቅደላው ጦርነት ወቅት አገልግሎት ላይ የዋለ የጦር ጋሻ ይገኙበታል። ከመቅደላ የተዘረፈ የመድሃኒዓለም ታቦትም ለንደን ውስጥ ለሚገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተሰጥቷል ተብሏል፡፡

4፤ የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ የኢትዮጵያ መሪዎች ከሱማሊያ ግዛት የባሕር በር አግኝተናል ብለው ሕዝባቸውን ከማሳሳት ቢቆጠቡ ይሻላል በማለት መናገራቸውን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ፕሬዝዳንት ሞሃመድ፣ ኢትዮጵያ በሱማሊያ ምድር የባሕር በር የማግኘቷ ጉዳይ ያልተደረገና ወደፊትም ሊደረግ የማይችል ነው ማለታቸውን ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ኢትዮጵያና ሱማሌላንድ ስምምነቱን መፈራረማቸውን ተከትሎ ለሱማሊያ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት አጋርነታቸውን ከገለጡት መካከል፣ አሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ ቱርክ፣ ግብጽ፣ አውሮፓ ኅብረትና ዓረብ ሊግ ይገኙበታል።

5፤ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ዋና አዛዥ ጀኔራል ሞሐመድ ደጋሎ የአፍሪካ አገራት ጉብኝታቸውን ዛሬም ቀጥለዋል። ጀኔራል ደጋሎ፣ ዛሬ ወደ ሩዋንዳ አቅንተው ከፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ጋር በሱዳኑ ጦርነት ዙሪያ ተወያይተዋል። ጀኔራል ደጋሎ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በቀጠሉበት ባኹኑ ወቅት፣ የአገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበርና የሱዳን ጦር ሠራዊት ዋና አዛዥ ጀኔራል ቡርሃን ከፈጥኖ ደራሹ ሠራዊት ጋር "እርቅ አይታሰብም" በማለት በውጊያው እንደሚገፉበት ተናግረዋል።

6፤ አንድ የአሜሪካዋ አላስካ ግዛት አየር መንገድ ንብረት የኾነ ቦይንግ 737 ማክስ 9 የመንገደኞች አውሮፕላን በመብረር ላይ ያለ ከኋለኛው ክፍሉ አንዱ መስኮቱ ተገንጥሏል። አውሮፕላኑ መስኮቱ አየር ላይ የተገነጠለው፣ 177 መንገደኞችንና የአየር መንገዱን ሠራተኞች አስፍሮ በመብረር ላይ ሳለ እንደኾነና አውሮፕላኑ በተጓዦቹ ላይ ጉዳት ሳይደርስ ወዲያውኑ ወደተነሳበት አየር ማረፊያ ተመልሶ ማረፉን ዓለማቀፍ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። ክስተቱን ተከትሎ፣ አየር መንገዱ ኹሉንም ማክስ 9 አውሮፕላኖቹን ከበረራ ማገዱ ተገልጧል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በርካታ አዳዲስ ቦይንግ ማክስ አውሮፕላኖችን በቅርቡ ማዘዙ ይታወሳል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ሰኞ ታኅሳስ 29/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በጎንደር ከተማ አካባቢ ቅዳሜ'ለት በመንግሥት ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እንደተከሰተ ዋዜማ ከምንጮች ሰምታለች። ግጭቱ የተከሰተው፣ አዘዞ እና በከተማው ቀበሌ 18 እንደኾነ ተነግሯል። በግጭቱ ሳቢያ፣ በከተማዋና አካባቢዋ የሰዎች የዕለት ተለት እንቅስቃሴ እንደተገደበ ለማወቅ ተችሏል።

2. በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ የወደብ ስምምነት ምክንያት በሶማሊያ በሚገኙ የኦሮሞ ማህበረሰብ አባላት ስደተኞች ላይ አደጋ ተጋርጧል፣ ይህን አደጋ ለማስቀረት አለማቀፉ ማህበረሰብና መንግስታት እንዲረባረቡ ሲል የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ጠየቀ። ኦነግ ትናንት ባወጣው መግለጫ ከኢትዮ ሶማሊላንድ ስምምነት ተከትሎ በሶማሊያና ሶማሊላንድ ያሉ ኢትዮጵያውያን የኦሮሞ ማህበረሰብ አባላትና ስደተኞች የጥቃት ኢላማ መሆናቸውን ገልጾ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ መንግስታት ያልተግባቡበትን ጉዳዩ በትዕግስትና በውይይት እንዲፈቱ ጠይቋል። ተመድ፣ የአፍሪቃ ህብረትና የአውሮፓ ህብረት በጉዳዩ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲያደርጉ አሳስቧል።

3፤ በትግራይ ክልል አበርገሌ ወረዳ በርሃብ 93 ሰዎች መሞታቸውን ከወረዳው መስማቱን ጠቅሶ ሪፖርተር ዘግቧል። በድርቁ ሳቢያ፣ ከወረዳው ከ11 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ ወረዳው መግለጡን ጋዜጣው አመልክቷል። ወረዳው ከድርቁ በተጨማሪ፣ ጊዜውን ባልጠበቀ ውርጭና ዝናብ፣ በተባይና በግብርና ግብዓት አቅርቦት እጥረት ችግር እንደተጎዳ ዘገባው አመልክቷል። ፈለገ ሕይወት፣ ስዩ፣ ተክለ ወይኒ እና ግራውር የተባሉ ቀበሌዎች በተለይ ከባድ የዝናብ ድርቅ እንደገጠማቸው ጋዜጣው በአካል መመልከቱን ገልጧል፡፡

4፤ የኬንያ ፖሊስ ወደ ሞምባሳ በጭነት ተሽከርካሪ በመጓዝ ላይ የነበሩ 47 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞችን ማሠሩን ዘ ስታር ጋዜጣ ዘግቧል። ኢትዮጵያዊያኑ በታንዛኒያ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ አስበው እንደነበር ፖሊስ ገልጧል ተብሏል። ፖሊስ ኢትዮጵያዊያኑ ሕጋዊ ሰነዶች እንደሌላቸው ገልጦ፣ ወደ አገራቸው እመልሳቸዋለኹ ማለቱን ዘገባው አመልክቷል። የተሽከርካሪው ሹፌር በቁጥጥር ስር የዋለ ሲኾን፣ ኢትዮጵያዊያኑን የሚያጓጉዘው ሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪ ግን ገና በፖሊስ እየተፈለገ መኾኑን ዘገባው አመልክቷል።

5፤ የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ ኢትዮጵያ እና ሱማሌላንድ የተፈራረሙትን የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ውድቅ የሚያደርግ አዲስ ሕግ ፈርመዋል። አዲሱ ሕግ ኢትዮጵያ በሱማሌላንድ የባሕር ኃይልና የባሕር ላይ ንግድ ጣቢያ መሬት እንዳታገኝ የሚያግድ እንደኾነ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ በ"ኤክስ" ገጻቸው ገልጸዋል። ፕሬዝዳንት ሞሃመድ፣ ሕጉ አንድነታችን፣ ሉዓላዊነታችንና የግዛት አንድነታችን ለመጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው ብለዋል። የአዲሱ ሕግ ዝርዝር ይዘት ግን አልተገለጠም።

6፤ የሱማሌላንድ መከላከያ ሚንስትር አብዲቃኒ ሞሃሙድ አትዬ ሥልጣናቸው በፍቃዳቸው መልቀቃቸውን የሱማሊያ ዜና ምንጮች ትናንት ዘግበዋል። ሚንስትሩ ከሃላፊነታቸው የለቀቁት፣ ሱማሌላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር ኃይልና የባሕር ንግድ ማዕከል መገንቢያ ቦታ ለመስጠት የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት በመቃወም እንደኾነ የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ሚንስትሩ ከሥልጣን በፍቃዳቸው ስለመልቀቃቸው፣ በ"ኤክስ" ገጻቸው ያሉት ነገር የለም።

7፤ የአሜሪካው የአቬሽን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በተወሰኑ የቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖች ላይ ፍተሻ እንዲደረግባቸው አዟል።
በዓለም ዙሪያ 171 ማክስ 9 አውሮፕላኖች ለጊዜው ከበረራ እንደሚታገዱ የገለጠው ባለሥልጣኑ፣ በእያንዳንዱ አውሮፕላን ላይ የሚደረገው የደኅንነት ፍተሻ ከአራት እስከ ስምንት ሰዓት ድረስ ሊወስድ ይችላል ብሏል። ባለሥልጣኑ ይህን ትዕዛዝ ያስተላለፈው፣ አንድ የአላስካ ግዛት አየር መንገድ ንብረት የኾነ ቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን ባለፈው ሳምንት ዓርብ በረራ በጀመረ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የኋላ መስኮቱ መገንጠሉን ተከትሎ ነው። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሰኞ ታኅሳስ 29/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ዛሬ ከሱማሊላንድ ራስ ገዝ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሜጄር ጄኔራል ኑህ ኢስማኤል ታኒ ጋር በኹለትዮሽ ወታደራዊ ትብብሮች ዙሪያ አዲስ አበባ ውስጥ ተወያይተዋል። ውይይቱ፣ ኢትዮጵያና ሱማሊላንድ በወታደራዊ ጉዳዮች ተባብረው በሚሠሩበት ኹኔታ ዙሪያ ያተኮረ እንደኾነ መከላከያ ሚንስቴር ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል። የሱማሊላንድ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት፣ የሱማሊላንድ መከላከያ ሚንስትር ሱማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችውን የባሕር በር ስምምነት በመቃወም ከሥልጣናቸው በፍቃዳቸው መልቀቃቸው በተነገረ ማግስት ነው።

2፤ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዓባይ ቴሌቪዥን ትናንት "ዋሸሁ እንዴ?" በተሰኘው አንድ ዝግጅቱ ላይ የሴቶችን ክብር የሚያጎድፍ እና በሴቶች ላይ የሚፈጸም ወንጀልን የሚያበረታቱ ሃሳቦችን አሰራጭቷል በሚል የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶታል። ባለሥልጣኑ፣ የቴሌቪዥን ጣቢያው በተደጋጋሚ የኅብረተሰቡን መልካም እሴት፣ ሰላምና ደኅንነት የሚያናጉ ዝግጅቶችን እና ዘገባዎችን ሲያሰራጭ ነበር በማለት ወቅሷል። ጣቢያው በዝግጅቶች ይዘት ላይ ማሻሻያ እንዲያደርግ ከኃላፊዎቹ ጋር ውይይት ማድረጉን የገለጸው ባለሥልጣኑ፣ ትናንት የተሠራጨው ፕሮግራምም የመገናኛ ብዙሃን አዋጅን የጣሰ መኾኑን ገልጧል። ባለሥልጣኑ፣ ጣቢያው ወደፊት ሕግን የሚጥሱ፣ ኃላፊነት የጎደላቸውና የሰውን ልጅ ስብዕና አደጋ ላይ የሚጥሉ ዝግጅቶችን ከማሰተላለፍ እንዲቆጠብ አሳስቧል።

3፤ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ለአባላቱ በሚሰጣቸው ሥልጠናዎች አባላቱ ያልኾኑ የፌደራል እና የክልሎች የመንግሥት ሠራተኞች እንዲሳተፉ እያደረገ ይገኛል ሲል ዛሬ ባወጣው መግለጫ ከሷል። ፓርቲው፣ የገዥው ፓርቲ አባል ያልኾኑ የመንግሥት ሠራተኞች የፓርቲውን ሥልጠናዎች እንዲወስዱ ጫናዎች እየተደረጉባቸው እንደኾነ መረጃዎች አግኝቻለኹ ብሏል። ድርጊቱ የሕግ ጥሰት መኾኑን የጠቀሰው ፓርቲው፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ድርጊቱን እንዲያስቆም ጠይቋል። ፓርቲው አክሎም፣ ለገዥው ፓርቲ ሥልጠናዎች የአበል፣ የትራንስፖርት፣ የሆቴልና ሌሎች ወጭዎች ከመንግሥት በጀት መኾኑም ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገው ገልጧል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ኹሉ፣ ገዥው ፓርቲ መዋቅሩን ከመንግሥታዊ መዋቅር እንዲለይ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ አሳስቧል።

4፤ በአማራ ክልል በሚካሄደው ግጭት ሳቢያ እስካኹን ትምህርት ያልጀመሩት ባሕርዳር፣ ደብረማርቆስ እና ደብረታቦር ዩንቨርስቲዎች ለነባርና ለአዲስ ተማሪዎቻቸው ጥሪ አድርገዋል። ባሕርዳር ዩንቨርስቲ ነባር ተማሪዎቹ ከጥር 15 እስከ 17 እንዲኹም አዲስ የሚገቡ ተማሪዎች ከጥር 21 እስከ 23 እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርቧል። ደብረማርቆስ ዩንቨርስቲም ነባር ተማሪዎች በኹለት ዙር ከጥር 16 እና 17 እንዲኹም ጥር 23 እና 24 እንዲመዘገቡና የአዲስ ተማሪዎች መመዝገቢያ ጊዜ የካቲት 6 እና 7 መኾኑንም ገልጧል። ደብረታቦር ዩንቨርስቲ በበኩሉ፣ የነባር ተማሪዎች መመዝገቢያ ጊዜ ጥር 2 እና 3 እንደኾነ አስታውቋል። ዩኒቨርስቲዎቹ ለተማሪዎቻቸው ጥሪ ያደረጉት፣ ትምህርት ሚንስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ከዩኒቨርስቲዎቹ ሃላፊዎችና ከክልሉ ባለሥልጣናት ጋር በጸጥታ ዙሪያ በቅርቡ ከተወያዩ በኋላ ነው።

5፤ የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ በኤርትራ የኹለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ አሥመራ ገብተዋል። ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በኹለትዮሽ፣ ቀጠናዊና ዓለማቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩ የኤርትራ ቃል አቀባይ የማነ ገ/መስቀል ገልጸዋል። ፕሬዝዳንት ሞሃመድ፣ ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሱማሌላንድ የተፈራረሙትን የባሕር በር መግቢያ ስምምነት ተከትሎ የግብጽ እና የኳታር መሪዎችን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት መሪዎች ጋር በስልክ ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ባለፈው መስከረም መጨረሻ በኤርትራ ባደረጉት ጉብኝት፣ የኤርትራ መንግሥት የሚያሰለጥናቸውን የሱማሊያ ወታደሮች መጎብኘታቸው ይታወሳል።

6፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ0591 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ1803 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 67 ብር ከ8200 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ1764 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ61 ከ2277 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ4523 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]

https://youtu.be/Bgj-j_yWHe8?si=q8q9n573-Wo0F2TE
Part 3
መንግስት በአንድ በኩል ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ራሱ ይገነባል ያንቀሳቅሳል በሌላ በኩል ደግሞ ስኬታማ የሚባሉ የመንግስት ድርጅቶችን ድርሻ ለውጪ መንግስታትና ባለሀብቶች ለመሸጥ ይታትራል። የዚህ ተቃርኖ ምክንያት የፖለቲካ ሀይሉ ኢኮኖሚውን የስልጣን ማስጠበቂያ አድርጎ መመልከቱ ነው ይላሉ ተወያዮቻችን። አድምጡት- https://youtu.be/XUtODTxL0z8?si=OT_3IB4eP1aLHwuf
ለቸኮለ ማለዳ! ማክሰኞ ታኅሳስ 30/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የጎንደር ከተማ ማዕከላዊ የጸጥታ ዕዝ የፋኖ ታጣቂዎች ባለፈው ሳምንት ቅዳሜና ዕሁድ ወደ ከተማዋ ለመግባት ያደረጉት ሙከራ ከሽፏል ሲል ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ገልጧል። የፋኖ ታጣቂዎች ለመግባት የሞከሩት፣ ወደ ከተማዋ ኹለት ቀበሌዎችና አንድ በከተማዋ ዙሪያ ወደሚገኝ የገጠር ቀበሌ እንደነበር ማዕከላዊ ዕዙ ገልጧል። ዋዜማ፣ በመንግሥት ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ቅዳሜ'ለት በጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 እና አዘዞ አካባቢ ግጭት እንደነበር ሰኞ'ለት መዘገቧ ይታወሳል። ማዕከላዊ ዕዙ በግጭቱ ስለደረሰው ጉዳት አልጠቀሰም።

2፤ ዓባይ ቴሌቪዥን፣ ዕሁድ'ለት ላስተላለፍኩት አንድ የመዝናኛ ዝግጅት የሰጠኹት ርዕስ "ያልተገባ መልዕክት" ለአድማጮች እንዲደርስ አድርጓል በማለት መጸጸቱን ገልጧል። በዩትዩብ ለተለቀቀው ዝግጅት የተሰጠው ርዕስ "የተሳሳተ ግንዛቤ" ፈጥሯል ያለው ጣቢያው፣ በተመልካቾች ዘንድ ለተፈጠረው "ብዥታ" ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለኹ ብሏል። ጣቢያው፣ ለዝግጅቱ የሰጠውን "ሴት ደፍሬ አውቃለኹ" የሚል ርዕስ ወዲያው መቀየሩንም ገልጧል። ጣቢያው ዛሬ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን የሰጠውን የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ "ተቀባይነት የሌለው" እና "ያልተገባ ጫና ውስጥ የሚያስገባ" በማለት አጣጥሎታል።

3፤ የቀድሞው የኢዜማ አመራር አባል ዳንኤል ሺበሺ ትናንት ምሽት "የመጨረሻ መጨረሻ ማስጠንቀቂያ" ተሰጥቷቸው ከእስር መለቀቃቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል። የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ከሌላ ቦታ ወደ አዲስ አበባ እንድተመለሱ ባለፈው ሳምንት ዓርብ ቄራ አካባቢ በቁጥጥር ስር እንዳዋሏቸው የጠቀሱት ዳንኤል፣ ታስረው የቆዩት ቄራ እሳት አደጋ ፖሊስ ጣቢያ እንደኾነ ገልጸዋል። ዳንኤል፣ የታሠሩበትን ምክንያት አላብራሩም። የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ታኅሳስ 13 "ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ" በሌሉበት መኖሪያ ቤታቸውን እንደፈተሹ ዳንኤል ቀደም ሲል ገልጠው ነበር።

4፤ ጅቡቲ፣ በኢትዮጵያና ሱማሊያ መካከል ሰሞኑን የተፈጠረው ውጥረት እንዳሳሰባት ትናንት ምሽት ባወጣችው መግለጫ አስታውቃለች። ጅቡቲ፣ ኹለቱ አገራት ውጥረቱን በንግግር እንዲያረግቡም ጠይቃለች። በአፍሪካ ኅብረትና በኢጋድ ቻርተሮች ላይ በተደነገገው መሠረት፣ ለአገራት ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ነጻነትና የግዛት አንድነት ልዩ ቦታ እንደምትሰጥ ጅቡቲ ጨምሮ ገልጣለች።

5፤ የሱማሊላንድ ፓርላማ፣ የፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ መንግሥት ለኢትዮጵያ የባሕር በር ቦታ በመስጠት በምላሹ ከኢትዮጵያ የሉዓላዊ አገርነት እውቅና ለማግኘት የተፈራረመውን የመግባቢያ ስምምነት የሚመለከት አዲስ ሕግ ትናንት አጽድቋል። አዲሱ ሕግ፣ ሱማሊያ በሱማሊላንድ የባሕር ወሰን ጉዳይና ሱማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በተፈራረመችው የባሕር በር ቦታ የመግባቢያ ስምምነት ላይ የምታደርገውን ጣልቃ ገብነት ውድቅ የሚያደርግ እንደኾነ የሱማሊላንድ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

6፤ ሰሞኑን ከሥልጣን የለቀቁት የሱማሊላንድ የቀድሞ መከላከያ ሚንስትር አብዲቃኒ ሞሃመድ አቲዬ፣ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር በባሕር በር ዙሪያ የመግባቢያ ስምምነት ከመፈራረማቸው በፊት ሚንስትሮቻቸውን አላማከሩም በማለት ላንድ የሱማሌ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃል ከሰዋል። አብዲቃኒ፣ የሱማሊላንድ ሚንስትሮች ስለ ስምምነቱ መፈረም የሰሙት ከመገናኛ ብዙኀን ነው ማለታቸውን የተለያዩ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። አብዲቃኒ ሱማሊላንድ ለኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ጣቢያ መገንቢያ ለመስጠት ከተስማማችበት "ሉጋያ" ከተባለው አከባቢ የወጡ ናቸው።

7፤ የአሜሪካው ዩናይትድ አየር መንገድ ሰሞኑን ፍተሻ ባደረገባቸው በርካታ ቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖቹ በሮች ላይ "ባግባቡ ያልታሠሩ" ቡለኖች ማግኘቱን አስታውቋል። አየር መንገዱ 79 ማክስ 9 አውሮፕላኖች ያሉት ሲኾን፣ በስንቶቹ ላይ የላሉ ቡለኖች እንዳገኘ አለመግለጡን ሲቢቤስ ዘግቧል። የአሜሪካው አላስካ አየር መንገድ ባለፈው ዓርብ አንድ ማክስ 9 አውሮፕላኑ ገና መብረር ከመጀመሩ የኋለኛው በሩ በመገንጠሉ፣ ማክስ 9 አውሮፕላኖቹን በሙሉ ለጊዜው ከበረራ ማገዱ ይታወሳል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ማክሰኞ ታኅሳስ 30/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወርዳ ልዩ ስሙ ኢላላ በተባለ ቦታ የታጠቁ ኃይሎች ትናንት ከንጋቱ 11:00 ሰዓት ገደማ በፈጸሙት ጥቃት ሦስት ከባድ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። በጥቃቱ በሰዎች ላይ ሞት ወይም የአካል ጉዳት ስለመድረሱ የተሰማ ነገር አለመኖሩን ምንጮች ተናግረዋል። ጥቃቱ የደረሰባቸው ተሽከርካሪዎች፣ የኦሮሞ ነጻነት ሡራዊት ባለፈው ሳምንት ጠርቶታል የተባለውን የተሽከርካሪዎች የሥራ ማቆም አድማ የተላለፉ መኾናቸውን ዋዜማ ተረድታለች። ምንጮቹ፣ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎችም ታጣቂዎችን ደብቃችኋል በሚል ባካባቢው ነዋሪዎች ላይ ዛቻና ድብደባ ይፈጽማሉ ብለዋል። ባለፈው ሳምንት፣ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች አማጺው ቡድን ጠርቶታል ከተባለው የትራንስፖርት አድማ ጋር በተያያዘ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እንደተገደበ ዋዜማ ዘግባ ነበር።

2፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የብቃት መመዘኛ ፈተና ከወሰዱ 15 ሺሕ 151 ሠራተኞች፣ ባለሙያዎችና አመራሮች መካከል ማለፊያ ነጥብ ያመጡት 6 ሺሕ 517 ብቻ መኾናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ዛሬ አስታውቋል። ለብቃትና ባሕሪ መመዘኛ ፈተናው የተመዘገቡት ሠራተኞችና አመራሮች 15 ሺሕ 592 ሲኾኑ፣ ለምዘናው የተቀመጡት ግን 15 ሺሕ 151 መኾናቸው ተገልጧል። ምዘናውን 4 ሺሕ 213 አመራሮች እንደተፈተኑና፣ 1 ሺሕ 422 ወይም 34 በመቶ ያህሉ ማለፊያውን ነጥብ እንዳመጡ ቢሮው ገልጧል። ከ10 ሺሕ 257 ሠራተኞች መካከል፣ 5 ሺሕ 95 ወይም 50 በመቶ ገደማ ያህሉ ማለፊያ ነጥብ አምጥተዋል ተብሏል። 681 ለምዘናው የተቀመጡ ሠራተኞች፣ በተለያዩ የደንብ ጥሰቶች ሳቢያ ፈተናው እንዳልታረመላቸው ተገልጧል። ለሠራተኞች የተቀመጠው ማለፊያ ነጥብ 50 በመቶ፣ ለአመራሮች ደሞ 60 በመቶ ነው።

3፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ኤርትራዊያን ስደተኞች ከሕግ አግባብ ውጭ እየታሠሩ መኾኑን የሚገልጡ ተደጋጋሚ አቤቱታዎች እየደረሱት መኾኑን መናገሩን ኢትዮ ኤፍኤም ዘግቧል። የኮሚሽኑ የስደተኞች፣ የፍልሰተኞችና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች ክፍል ዳይሬክተር እንጉዳይ መስቀሌ፣ ኮሚሽኑ በጉዳዩ ላይ ተደጋጋሚ አቤቱታዎች እንደሚደርሱት መናገራቸውንና በአቤቱታዎቹ መሠረት ምርመራ እያካሄደ መኾኑን መግለጣቸውን ዘገባው አመልክቷል። መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን በቅርብ ይፋ እንደሚያደርግ ኮሚሽኑ ገልጧል ተብሏል።

4፤ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ፓርቲ፣ በትግራይ ክልል ለተከሰተው የርሃብ አደጋ አስቸኳይ ምላሽ የሚሰጥ ኹሉን አካታች አካል እንዲቋቋም ዛሬ ጠይቋል። በ33 ወረዳዎች ከባድ ርሃብ ተከስቷል ያለው ፓርቲው፣ ዓለማቀፉ ኅብረተሰብና ረድዔት ድርጅቶች ርሃቡን ለመግታት ባስቸኳይ ጣልቃ እንዲገቡ ተማጽኗል። ፓርቲው፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ለሰብዓዊ ቀውሱ ምላሽ የመስጠት አቅሙ ደካማ መኾኑና የረድዔት ድርጅቶች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለወራት መቋረጡ፣ በርካቶች በርሃብ እንዲሞቱ ምክንያት ኾኗል በማለት ወቅሷል። ፓርቲው፣ የክልሉ መንግሥት ከሳምንታት በፊት ስላቋቋመው አስቸኳይ ጊዜ የርሃብ ምላሽ ሰጭ ኮሚቴ ያለው ነገር የለም።

5፤ የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐመድ በአሥመራ በነበራቸው የኹለት ቀናት ጉብኝት ከፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር በኹለትዮሽ፣ በቀጠናዊና ዓለማቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊና ጥልቅ ውይይት ማድረጋቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስቴር አስታውቋል። ኹለቱ መሪዎች በኹለትዮሽና በጋራ የትብብር መስኮች ላይ ሰፋ ባለ ቀጠናዊ የትብብር ማዕቀፍ ለመስራት መስማማታቸውን የገለጠው ሚንስቴሩ፣ በትግዕስትና በቀና መንፈስ በመጓዝና "ከተንኳሽ አጀንዳዎች በመራቅ" ቀጠናዊ ትብብራቸውን ለማሳደግ መስማማታቸውን ጠቅሷል። ኤርትራ ከሱማሊያ ጋር ባላት የኹለትዮሽ ግንኙነትና በቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ በቅርቡ ዝርዝር መግለጫ እንደምታወጣም ሚንስቴሩ ገልጧል።

6፤ የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ ግብጽን እንዲጎበኙ ይፋዊ ግብዣ እንደቀረበላቸው የፕሬዳንቱ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ግብዣው የቀረበላቸው፣ ከግብጽ መንግሥት ከፍተኛ ተልዑካን ቡድን ጋር ሰኞ'ለት በሞቃዲሾ በተገናኙበት ወቅት መኾኑን ጽሕፈት ቤቱ ገልጧል። የግብጽ ልዑካን ቡድን፣ ግብጽ ለሱማሊያ አንድነት፣ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የማይቀለበስ ድጋፍ እንዳላት ለፕሬዝዳንት ሞሃመድ በድጋሚ እንዳረጋገጠላቸውና የሱማሊያን ሉዓላዊነት የሚጥስ ማናቸውንም ርምጃ ግብጵ እንደምትቃወም እንደገለጠላቸው ተጠቅሷል።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 56 ብር ከ0630 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 57 ብር ከ1843 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረ ገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 68 ብር ከ0442 ሳንቲም እና መሸጫው 69 ብር ከ4051 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ61 ከ3666 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ5939 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]

https://youtu.be/24cD01xwNN8?si=Cw3h7iiL94x8Do6W
ለቸኮለ ማለዳ! ረቡዕ ጥር 1/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የትግራይ ትምህርት ቢሮ በክልሉ 222 ሺህ 940 ተማሪዎች በድርቅና ርሃብ ሳቢያ ከትምህርት ገበታ ውጭ የመኾን አደጋ እንዳንዣበበባቸው አስታውቋል። ቢሮው፣ ለርሃብ አደጋ የተጋለጡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መቀጠል እንዲችሉ ዓለማቀፉ ኅብረተሰብና ሌሎች አካላት ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲያቀርቡና የትምህርት ቤት ምገባ እንዲጀምሩ ተማጽኗል። ለተማሪዎቹ የስድስት ወር የትምህርት ቤት ምገባ የሚያስፈልገው ወጪ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር መኾኑን ቢሮው ጨምሮ ገልጧል።

2፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት አገሪቱን እየገዛ ለመቀጠል የሚያስችለውን የውስጥ ድጋፍ ለማግኘት ሲል በአፍሪካ ቀንድ በግዴለሽነት አለመረጋጋት በመፍጠር የንጹሃንን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል በማለት ከሰዋል። ኦዳ ተርቢ፣ የዐቢይ መንግሥት በቀጠናው ሰላም ዋነኛ ስጋት ነው ብሏል። ሰሞኑን በኢትዮጵያና ሱማሊያ መካከል የተፈጠረው ችግር በኦሮሞ ብሄረሰብና ሱማሌ ሕዝብ መካከል ያለውን ትስስር እንደማይበጥሰውም ኦዳ ተርቢ ገልጸዋል።

3፤ ከትናንት ወዲያ በኦሮሚያ ክልል ከመተሃራ ከተማ ወጣ ብሎ መንገድ ላይ ታጣቂዎይ በተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ፈጽመው አራት ተሽከርካሪዎችን እንዳቃጠሉ ዶይቸቨለ የኢትዮጵያ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማሕበርን ጠቅሶ ዘግቧል። ፌደራል ፖሊስ፣ ጥቃቱን የሚፈጽመው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መኾኑን ገልጦ፣ ዓላማው ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ መስመር ላይ የትራንስፖርት መስተጓጎል መፍጠር መኾኑን መግለጡን ዘገባው አመልክቷል። በክልሉ ተሽከርካሪዎች የሚቃጠሉት፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጠርቶታል በተባለው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ አድማ ሳቢያ እንደኾነ ይነገራል።

4፤ በአዲሲ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎችና ነዋሪዎች ባለፈው ስምንት ተጋጭተው ሰባት ሰዎች እንደተገደሉ መስማቱን ቪኦኤ ዘግቧል። ከጸጥታ ኃይሎች ጋር የተጋጩት፣ የልዩ ወረዳ መዋቅር እንዲሰጣቸው የሚጠይቁ አካላት እንደኾኑ ዘገባው አመልክቷል። ፖሊስ በበኩሉ፣ ጸጥታ ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የኃይል ርምጃ አልወሰዱም ማለቱ ተገልጧል። ኾኖም በጸጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በተባሉ አካላት ላይ የአጸፋ ርምጃ እንደወሰደ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል። [ዋዜማ]