Wazema Media / Radio
48.9K subscribers
191 photos
36 videos
7 files
933 links
Wazema Radio other contents are available either in our website/social media or FM radio stations in Ethiopia. www.wazemaradio.com
Download Telegram
ግጭት ባለባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ለሁለት ወገን ግብር እንዲከፍሉ የተገደዱ አርሶ አደሮች “ግብር ካልከፈላችሁ ማዳበሪያ አታገኙም” መባላቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሮች የግብርና ማዳበሪያ ለማግኘት ግብር መክፈል እንደግዴታ በመቀመጡና ግብር እንክፈል ሲሉ የሚሰበስብ አካል በመጥፋቱ የአዝመራው ወቅት ሊያልፋቸው መሆኑንም ያስረዳሉ።
አርሶ አደሮቹ በተለይ የፋኖ ታጣቂዎች በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ታጣቂዎቹ አስቀድመው ግብር እየሰበሰቡ መቆየታቸውን ገልፀው፣ ድጋሚ ለመንግስት ግብር ከፍለው ማዳበሪያ ለማግኘት የጠየቁ አርሶ አደሮች ግብር የሚሰበስብ አካል አለማግኘታቸውን ነግረውናል። ክልሉ ምላሽ አጥቷል። ዝርዝሩን ያንብቡት- https://tinyurl.com/4ncw2zc4
ለቸኮለ ማለዳ! ሰኞ ሰኔ 24/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ኢትዮጵያ እና ሱማሊያ በባሕር በርና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በቱርክ አሸማጋይነት አንካራ ውስጥ እንደሚነጋገሩ የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የሱማሊያው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አሕመድ ሙዓሊም ፊቂ ለንግግሩ ትናንት ወደ አንካራ ማቅናታቸውን መስሪያ ቤታቸው በ"ኤክስ" ገጹ ላይ ባወጣው አጭር መግለጫ ገልጦ እንደነበር ዘገባዎች ጠቅሰዋል። ኾኖም ሚንስቴሩ መግለጫውን ቆየት ብሎ እንዳነሳው ዘገባዎቹ አመልክተዋል። በኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ሳቢያ በተፈጠረው ውዝግብ ዙሪያ ያተኩራል የተባለው ንግግር የታቀደው ትናንት ሲኾን፣ በትክክል ንግግሩ ስለመካሄዱ ግን ነጻ ምንጮች አላረጋገጡም።

2፤ የጸለምቲ ወረዳ የጦርነት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ መጀመራቸውን ቪኦኤ ዘግቧል። ቅዳሜ'ለት ማይ ዓይኒ፣ ማይ ኣንበሳ፣ መድኃኔዓለም እና ውሕደት ወደተባሉ የወረዳው ቀበሌዎች ከ1 ሺሕ 500 በላይ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንደተመለሱ ዘገባው ገልጧል፡፡ የወረዳው ከተማ ማይጸብሪ እና የስድስት ቀበሌዎች ነዋሪዎች ደሞ ትናንት እና ዛሬ ወደቀያቸው እንደሚመለሱ መስማቱንም ዘገባው ጠቅሷል። የጸለምት ወረዳ ከጦርነቱ ወዲህ በአማራ ክልል ሥር የቆየ ሲኾን፣ በአማራ ክልል ሥር የተዋቀረው የወረዳው ጊዜያዊ አስተዳደር የጸጥታ መዋቅር ሰሞኑን ፈርሷል ተብሏል።

3፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለካንሰር በሽታ ሕክምና ሊያገለግሉ የሚችሉ በርካታ የዕጽዕዋት ዓይነቶች መኖራቸውን የአሜሪካው ጆርጂያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች አስታውቀዋል። ተመራማሪዎቹ የካንሰር በሽታን ሊከላከሉ በሚችሉ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚበቅሉ ዕጽዕዋት ላይ ምርምር እያደረጉ እንደኾነ ተናግረዋል። ተመራማሪዎቹ ትኩረታቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ በሚበቅሉ እጽዕዋት ላይ ያደረጉት፣ ኢትዮጵያዊያን የባሕላዊ ሕክምና አዋቂዎች ለብዙ መቶ ዓመታት እጽዕዋቶችን ለካንሰር ሕክምና ሲጠቀሙ በመኖራቸው እንደኾነ ተገልጧል።

4፤ አልሸባብ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ተዋጊዎች ብርጌድ ማደራጀቱንና ለቀጠናው አገራት ከምንጊዜውም በላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀኑን ከአፍሪካ ኅብረት ሚስጢራዊ ሰነድ መመልከቱን ጠቅሶ ዘ ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ አስነብቧል። የውጭ ተዋጊዎች የተካተቱበት የቡድኑ ብርጌድ "ሙሃጅሪን" እንደሚሰኝ የጠቀሰው ዘገባው፣ አብዛኞቹ ተዋጊዎች ኢትዮጵያዊያን፣ ኬንያዊያንና ታንዛኒያዊያን እንደኾኑና የኡጋንዳ፣ የኮንጎ፣ የቡሩንዲና የሩዋንዳ ዜጎችም እንደሚገኙበት አመልክቷል። የሙሃጅሪን ተዋጊዎችን ክንፍ የሚመራው፣ ኬንያዊ ዜግነት ያለው የአልሸባብ ተዋጊ እንደኾነ ተገልጧል። የኅብረቱ ሰነድ፣ አልሸባብ በብዙ መስኮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መሄዱንም ያብራራል ተብሏል።

5፤ በሱማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ ትናንት ተጨማሪ የጦር ሠፈር ለአገሪቱ ጦር ሠራዊት አስረክቧል። የትናንቱ የወታደራዊ ጦር ሠፈር ርክክብ፣ ተልዕኮው በተያዘው ወር ከጀመረው ርክክብ አምስተኛው ነው። ትናንት የጦር ሠፈራቸውን ለሱማሊያ ጦር ያስረከቡት፣ በተልዕኮው ሥር የሚገኙ የጅቡቲ ወታደሮች ናቸው። የኅብረቱ ተልዕኮ በተያዘው ሦስተኛ ዙር ከአገሪቱ ለማስወጣት ያሰበው 4 ሺህ ነው። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሰኞ ሰኔ 24/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ቱርክ፣ ኢትዮጵያንና ሱማሊያን በባሕር በር ውዝግባቸው ዙሪያ ዛሬ አንካራ ውስጥ እንዳደራደረች ከባለሥልጣናት ምንጮች መስማቱን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል። ኾኖም ኹለት ለድርድሩ ቅርብ የኾኑ ምንጮች የድርድሩ ግብ ምን እንደኾነ ግልጽ እንዳልኾነና ከድርድሩ ኹነኛ ውጤት የመገኘቱ እድሉ ዝቅተኛ መኾኑን መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል። የኢትዮጵያ፣ ሱማሊያና ቱርክ ባለሥልጣናት በቱርክ-መራሹ ድርድር ዙሪያ አስተያየት ከመስጠት እንደተቆጠቡ ዜና ምንጩ ገልጧል። የሶማሊላንድ ራስ ገዝ መንግሥት ቃል አቀባይ ግን፣ ሶማሊላንድ በቱርክ አደራዳሪነት በሚካሄደው ድርድር ውስጥ ተሳታፊ እንዳልኾነች ተናግረዋል ተብሏል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ከሱማሊያ ጋር በቱርክ አመቻቺነት ዛሬ ይደረጋል ስለተባለው ንግግር ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ያለው ነገር የለም። 

2፤ ግጭት ባለባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ለኹለት ወገን ግብር እንዲከፍሉ የተገደዱ አርሶ አደሮች “ግብር ካልከፈላችሁ ማዳበሪያ አታገኙም” እንደተባሉ ለዋዜማ ተናግረዋል። ኾኖም ድጋሚ ለመንግሥት ግብር ከፍለው ማዳበሪያ ለማግኘት የጠየቁ አርሶ አደሮች፣ ግብሩን የሚሰበስብ አካል እንዳላገኙ ገልጸዋል። አንዳንድ አርሶ አደሮች መንግሥት 4 ሺህ 200 ብር የሚሸጠውን ማዳበሪያ ከአጎራባች አካባቢዎች በ8 ሺህ 800 ብር  ከነጋዴ በውድ ዋጋ እየገዙ መኾኑን ጠቁመዋል። የክልሉ ግብርና ቢሮ ስለ አርሶ አደሮቹ ቅሬታ ተጠይቆ፣ እንደዚያ ዓይነት ኹኔታ ሊያጋጥም እንደሚችል ጠቅሶ፣ ግብር ካልከፈላችሁ ማዳበሪያ አታገኙም ማለት ግን ስህተት እንደኾነና በጉዳዩ ላይ መመሪያ አስተላልፎ እንደነበር ለዋዜማ ገልጧል። ማዳበሪያ በነጋዴዎች እጅ መግባቱን በተመለከተ፣ ለችግሩ ተጠያቂው የክልሉ ጸጥታ ኃይል እንደኾነ ቢሮው ተናግሯል።

3፤ በፌደሬሽን ምክር ቤት የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የወልቃይት፣ ጠለምት እና የራያ አካባቢ ሕዝቦች በማንነትና የአስተዳደር አከላለል ዙሪያ ላነሷቸው ጥያቄዎች በጸጥታ ምክንያት ምላሽ መስጠት እንዳልተቻለ ዛሬ ለምክር ቤቱ ባቀረበው የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት መግለጡን ሸገር ዘግቧል። ቋሚ ኮሚቴው፣ ጥያቄዎቹን ባነሱት ማኅበረሰቦች አካባቢዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ገልጦ፣ ኾኖም በተጠቀሱት አካባቢዎች ተገኝቶ ተጨማሪ መረጃዎችን ለመሰብሰብ የጸጥታ ኹኔታው እንዳልፈቀደለት በሪፖርቱ መጥቀሱን ዘገባው አመልክቷል። ቋሚ ኮሚቴው፣ ወደፊት ጥያቄዎች ባሏቸው አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ኹኔታ ተሻሽሎ ኹኔታዎች ሲፈቅዱ፣ ምላሽ ወደመስጠት እንደሚገባ ገልጧል ተብሏል።

4፤ የኢትዮጵያ ግብርና ሚንስቴር፣ ኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ ኅብረት አገራት የምትልካቸው ምርቶች አውሮፓ ኅብረት ያወጣቸውን መሥፈርቶች ያሟሉ እንዲኾኑ ከአመራረት ጀምሮ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ መጀመሩን እንዳስታወቀ ሪፖርተር ዘግቧል። አውሮፓ ኅብረት ባወጣው አዲስ የቁጥጥር መሥፈርት መሠረት፣ ኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ ከምትልከው አጠቃላይ ምርት ውስጥ 25 በመቶው በመዳረሻዎቹ ላይ ምርመራ እንደሚደረግበት ባለሥልጣናት መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። የግብርና ወጪ ንግድ የሚመለከታቸው አካላት የኅብረቱን መስፈርቶች የማያሟሉ ምርቶች ለኅብረቱ ገበያ ሳይቀርቡ እንደሚያስቀሩና ጥብቅ መሥፈርቶችን በተደጋጋሚ ያላሟሉ የግብርና ምርቶች ወደ አውሮፓ ገበያ እንዳይላኩ ጨርሶ እስከማገድ እንደሚደርሱ መስማቱን ዜና ምንጩ ጨምሮ አመልክቷል።

5፤ መንግሥት ከትናንት ጀምሮ ለቀጣዮቹ 15 ቀናት ከጅቡቲ የሚነሱ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች በሙሉ ማዳበሪያ ብቻ እንዲያጓጉዙ ማዘዙን ካፒታል ጋዜጣ ዘግቧል። መንግሥት ይህን ትዕዛዝ ለትራንስፖርት ማኅበራትና የግል አንቀሳቃሾች ያስተላለፈው፣ ማዳበሪያ የጫኑ አራት መርከቦች በተከታታይ ጅቡቲ ወደብ መድረሳቸውን ተከትሎ እንደኾነ ዘገባው አመልክቷል። ጉምሩክ ኮሚሽን፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከጅቡቲ ወደ መሃል አገር ከማዳበሪያ ውጭ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎችን እንዳያስተናግድ መታዘዙን ከምንጮች መስማቱን ዘገባው ጨምሮ ጠቅሷል። እስካለፈው ሳምንት አጋማሽ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ እንደገባ መረጃዎች ያመለክታሉ።

6፤ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ በተከሱበት የንጹሃን ሰዎች ግድያ በቂ ማስረጃ አልቀረበባቸውም በማለት ዛሬ በነጻ እንዳሰናበታቸው የአገር ውስጥ ዜና አውታሮች ዘግበዋል። ፍርድ ቤቱ ኹለት የክልሉ ጸጥታ ኃይል አባላትንም በነጻ ያሰናበተ ሲኾን፣ ሌሎች 12 ተከሳሾችን ግን ጥፋተኛ ኾነው እንዳገኛቸው ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ፍርድ ቤቱ በጥፋተኞቹ ላይ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለሐምሌ 10 ቀጠሮ ሰጥቷል ተብሏል። አቡላ ኡቦንግ፣ የቀድሞው የክልሉ ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ቱት ኮር እና 13 የፖሊስ አባላት ከኹለት ዓመታት በፊት በክልሉ ከተፈጸሙ የንጹሃን ሰዎች ግድያ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ባለፈው ዓመት መጋቢት ነበር። የክልሉ ጸጥታ ኃይሎች፣ ከኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ጋር አብራችኋል በማለት በጠረጠሯቸው ሰዎች ላይ በወሰዱት የኃይል ርምጃ፣ ከ50 በላይ ንጹሃን እንደተገደሉ ኢሰመኮ በወቅቱ ባወጣው ሪፖርት ገልጦ ነበር።

7፤  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 57 ብር ከ3380y ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 58 ብር ከ4848 ሳንቲም ኾኖ እንደዋለ በድረ ገጹ አስታውቋል። ባንኩ፣ የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 69 ብር ከ3015 ሳንቲም እና መሸጫው 70 ብር ከ6875 ሳንቲም እንደኾነም አመልክቷል። በተመሳሳይ፣ አንድ ዩሮ በ61 ከ4147 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ6430 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ማክሰኞ ሰኔ 25/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በቱርክ አደራዳሪነት ትናንት አንካራ ውስጥ የተነጋገሩት ኢትዮጵያና ሱማሊያ ነሃሴ 27 በድጋሚ ለመነጋገር መስማማታቸውን የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሐካን ፊዳን ትናንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫም፣ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ታዬ አጽቀሥላሴ እና የሱማሊያው አቻቸው አሕመድ ፊቂ በኹለቱ አገሮች ልዩነት ዙሪያ በተናጥል ግልጽነት የተሞላበት ውይይት እንዳደረጉና ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በንግግር ለመፍታት እንደተስማሙ ገልጧል። የኹለቱን የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ንግግር የመሩት፣ የቱርኩ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሐካን ፊዳን ናቸው።

2፤ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ከአንዳንድ ቀበሌዎች ነዋሪዎች የታጣቂዎችን ጥቃት በመሸሽ ከቀያቸው እየለቀቁ እንደኾነ ቪኦኤ ዘግቧል። በወረዳው ታጣቂዎች በሚያደርሱት ጥቃት፣ ሰላማዊ ሰዎች እየተገደሉ መኾኑን ነዋሪዎች መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል። የዞኑ አስተዳደር፣ በደራ ወረዳ እና በአጎራባቾቹ ወረዳዎች ለቀጠለው ጥቃት፣ የፋኖ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎችን ተጠያቂ አድርጓል ተብሏል። ባካባቢው የመንግሥት ኀይሎች ከኹለቱም ቡድኖች ጋራ ግጭት ላይ እንደኾኑ አስተዳደሩ መግለጡንም ዜና ምንጩ ጠቅሷል።

3፤ የምግብ ዘይት አምራቾች ማኅበር፣ መንግሥት በቅርቡ የከለሰውን የተጨማሪ እሴት ታክስ ደንብ እንደገና እንዲያጤነው መጠየቁን ካፒታል ዘግቧል። ማኅበሩ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያው በአገሪቱ የሚታየውን የዋጋ ንረት ያባብሰዋል በማለት ማስጠንቀቁን ዘገባው አመልክቷል። መንግሥት ባደረገው ማሻሻያ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ የነበሩት የምግብ ዘይትና የቅባት እህሎች ምርቶች በተጨማሪ እሴት ታክሱ ተካተዋል። የምግብ ዘይት፣ የቅባት እህሎች ውጤቶችና የእንስሳት መኖ ከእሴት ታክስ ነጻ አለመደረጋቸው፣ በተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይ አምራቾችና ታክሱን በማይከፍሉ ነጋዴዎች መካከል ፍትሃዊ ያልኾነ ውድድር ይፈጥራል ሲል ማኅበሩ ለገንዘብ ሚንስቴር ቅሬታውን አቅርቧል ተብሏል።

4፤ መንግሥት ያቋቋመው ብሄራዊ ኮሚቴ፣ ትናንት ሳዐዲ ዓረቢያ ውስጥ ባስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ የነበሩ 1 ሺህ 195 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞችን መመለሱን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል። ከተመላሾቹ መካከል፣ 76ቱ ሴቶች፣ 15ቱ ጨቅላ ሕጻናት እንደኾኑና እድሜያቸው ከአስራ ስምንት ዓመት በታች የኾኑ 43 ታዳጊዎችም እንደሚገኙበት ሚንስቴሩ ገልጧል። ኮሚቴው ከሚያዚያ 4 ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስ ከ54 ሺህ በላይ ፍልሰተኞችን መልሷል።

5፤ በኬንያ ከግብር አዋጅ ጋር በተያያዘ በተቀሰቀሰው አገር ዓቀፍ ተቃውሞ በኹለት ሳምንት ውስጥ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 39 መድረሱን የአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተቋጣጣሪ ኮሚሽን አስታውቋል። በተቃውሞው ሌሎች 361 ሰዎች የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ኮሚሽኑ ገልጧል። መንግሥት ከተቃውሞ ጋር በተያያዘ የተገደሉት ሰዎች 19 ብቻ እንደኾኑ ዕኹድ'ለት አስታውቆ ነበር። መንግሥት ተቃውሞውን ተከትሎ አዲሱን የግብር አዋጅ ባለፈው ሳምንት ቢያነሳም፣ ተቃዋሚ ወጣቶች ግን ዛሬ በድጋሚ ወደ አደባባይ እንደሚወጡ መግለጣቸውን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ማክሰኞ ሰኔ 25/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ኢትዮጵያ እና ሱማሊያ በቱርክ አመቻቺነት በልዩነቶቻቸው ዙሪያ ትናንት አንካራ ውስጥ "ግልጽ እና ወዳጅነት የተሞላበት" የሃሳብ ልውውጥ እንዳደረጉ አስታውቋል። ኹለቱ አገራት ልዩነቶቻቸውን በንግግር ለመፍታት፣ ነሃሴ 27 በድጋሚ ተገናኝተው ለመነጋገር እንደተስማሙም ሚንስቴሩ ገልጧል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ ድርድሩ ያለ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ራስ ገዝ ጋር የተፈራረመችውን የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ለመሰረዝ ምልክት አላሳየችም በማለት ከሰዋል። ከሱማሊያ ጋር ለመደራደር ጥያቄ ያቀረበችው ኢትዮጵያ ናት ያሉት ፕሬዝዳንት ሞሃመድ፣ ንግግሩ በቱርክ ባለሥልጣናት በኩል እንጂ የኹለቱ አገራት ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ፊት ለፊት የቀጥታ ንግግር አላካሄዱም ብለዋል።

2፤ የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) በሱማሌ ክልል ዶሎ ዞን በኹለት ንዑስ ጎሳዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ግጭት ውስጥ የገቡትን ንዑስ ጎሳዎች በስም ያልጠቀሰው ኦብነግ፣ ግጭቱ ባስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ አድርጓል። የክልሉ ሽማግሌዎች ጣልቃ ገብተው ኹለቱን ንዑስ ጎሳዎች እንዲያሸማግሉም ኦብነግ ጠይቋል። ኦብነግ አባላቱ በግጭቱ ተሳታፊ እንዳይኾኑ እንዲኹም የክልሉ መንግሥት ለግጭቱ ፈጣን መፍትሄ እንዲሰጥ አሳስቧል።

3፤ ጤና ሚንስቴር፣ በሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ምንም ዓይነት ክትባት ሳይወሰዱ የቀሩ እና ክትባት ጀምረው ያቋረጡ ከ1 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ ሕጻናት በአገሪቱ እንደሚገኙ አስታውቋል። ሚንስቴሩ፣ እነዚህ ሕጻናት ክትባት ለመስጠት ለ10 ተከታታይ ቀናት የክትባት ዘመቻ መጀመሩን ዛሬ በሰጠው መግለጫ ገልጧል። በክትባት ዘመቻው፣ የሳምባ ምች፣ የፖሊዮና የኩፍኝ ክትባቶች ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለኾኑ ሕጻናት እንደሚሰጣቸው ሚንስቴሩ አመልክቷል። የክትባት ዘመቻው ያተኮረው፣ በግጭትና በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች በሚኖሩ ሕጻናት ላይ እንደኾነና የአርብቶ አደር አካባቢዎችን ሕጻናትንም ለማዳረስ እንደታሰበ ተገልጧል።

4፤ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ አማረ ሰጤ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት በአማራ እና ትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ላለፉት አራት ዓመታት ለምን የፌደራል ድጎማ ሳይመድብላቸው እንደቀረ ማብራሪያ እንዲሰጥ መጠየቃቸውን ሸገር ሬዲዮ ዘግቧል። የክልሉ ምክትል አፈ ጉባዔ፣ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን በሚነሳባቸው የተወሰኑ አካባቢዎች የመብራት፣ የባንክ፣ የሞባይል ኔትዎርክና ሌሎች አገልግሎቶች እንደተቋረጡ መግለጣቸውን ዘገባው አመልክቷል። የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘው ተሻገር ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ፣ የወልቃይት ጠገዴ እና ሌሎች የማንነት ጥያቄዎች የሚነሳባቸውን አካባቢዎች የበጀት ጥያቄ በፌደራል በጀት ቀመር መኾኑ ቀርቶ ገንዘብ ሚንስቴር በበጀት አስተዳደር እንዲያስተናግደው ምክር ቤቱ ለሚንስቴሩ ደብዳቤ እንደጻፈና ጉዳዩን ተከታትሎ ማስፈጸም የክልል መንግሥት ኃላፊነት እንደኾነ መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

5፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስትር ደዔታ ፍስሃ ይታገሱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አድርገው እንደሾሙ ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ፍስሃን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አድርገው የሾሟቸው፣ ኹለት ዓመት ላልሞላ ጊዜ በሃላፊነት ላይ የቆዩትን አክሊሉ ታደሠን በማንሳት ነው። ዐቢይ፣ በስድስት ዓመታት ውስጥ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲሾሙ የአኹኑ አራተኛ ጊዜያቸው ነው። በኮርፖሬሽኑ ሥር በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ አስተዳደር እንዲኹም በክልሎች 12 ኢንዱስትሪ ፓርኮች ይገኛሉ። ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን የተነሱት አክሊሉ ታደሠ፣ የቱሪዝም ሚንስቴር ደዔታ ኾነው ተሹመዋል።

6፤ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ በኤርትራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ልዩ ራፖርተር ሞሃመድ አብድልሰላም ባቢከር የቆይታ ጊዜ እንዲራዘም ጠይቋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ የሚሰጠው በቀጣዩ ሳምንት ነው። ሩሲያ፣ ኢራን እና የተወሰኑ የምክር ቤቱ አባል አገራት የልዩ ራፖርተሩ የቆይታ ጊዜ እንዳይራዘም እንደሚፈልጉ ድርጅቱ ገልጧል። የልዩ ራፖርተሩ መቀጠል አኹንም እጅግ አስፈላጊ መኾኑን የጠቀሰው ድርጅቱ፣ የምክር ቤቱ አባል አገራት የኤርትራን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሲቪል ማኅበረሰቦች ጥሪ እንዲሰሙና ከጎናቸው እንዲቆሙ ጠይቋል። ልዩ ራፖርተሩ በቅርቡ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት፣ የኤርትራ መንግሥት አስከፊ የሰብዓዊ መብት አያያዙን ለማሻሻል የወሰደው ርምጃ እንደሌለ ገልጠው ነበር።

7፤ በኬንያ ከግብር አዋጅ ጋር በተያያዘ የተቀሰቀሰው አገር ዓቀፍ ተቃውሞ ዛሬም ተካሂዷል። ዋና ከተማዋን ናይሮቢን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች ዛሬ የአደባባይ ተቃውሞዎች የተደረጉ ሲኾን፣ ተቃዋሚዎችም ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል። ካለፈው ሳምንት መገባደጃ ጀምሮ የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠር በመላ አገሪቱ ተሠማርቷል። ተቃውሞው ከተቀሰቀሰ ወዲህ ኹለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 39 መድረሱን የአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተቋጣጣሪ ኮሚሽን አስታውቋል። በተቃውሞው ሌሎች 361 ሰዎች የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ኮሚሽኑ ገልጧል። መንግሥት ተቃውሞውን ተከትሎ አዲሱን የግብር አዋጅ ባለፈው ሳምንት ቢያነሳም፣ ተቃዋሚ ወጣቶች ግን ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሥልጣን እንዲለቁ በመጠየቅ ላይ ናቸው። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ረቡዕ ሰኔ 26/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በአማራ ክልል ሥር የተቋቋሙት የጠለምት እና ማይጸብሪ አስተዳደሮች ሙሉ በሙሉ እንደፈረሱና ቢሮዎቻቸው እንደታሸጉ ቢቢሲ አማርኛ የአካባቢውን ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል። በጦርነቱ ከአካባቢዎቹ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው በመመለስ ላይ እንደኾኑም ዘገባው ገልጧል። ሰሞኑን የፈረሱት ጊዜያዊ አስተዳደሮች፣ የምሥራቅ ጠለምት ወረዳ፣ የምዕራብ ጠለምት ወረዳ እንዲኹም የማይጸብሪ ከተማ ተብለው በሰሜን ጎንደር ዞን ሥር የተዋቀሩ አስተዳደሮች ናቸው። መዋቅሮቹ የፈረሱት፣ ከአማራ ክልል መንግሥትና ከፌደራሉ መንግሥት ተወካዮች ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ መኾኑንና የፖሊስና ሚሊሻ አባላትም ከቅዳሜ ጀምሮ እንዲወጡ እንደተደረገ መስማቱን ዘገባው አመልክቷል።

2፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ከኢምግሬሽን ጋር የተያያዙ ኹለት ረቂቅ አዋጆችን አጽድቋል። ምክር ቤቱ፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ በአራት ድምጸ ተዓቅቦ ማጽደቁን ገልጧል። ረቂቅ አዋጁ የተዘጋጀው፣ ጠንካራ የቅድመ ጉዞ መረጃዎችን በማዘጋጀትና ከአገራት ጋር ውጤታማ የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ወንጀለኞችን ለመያዝ የሚያስችል ሥርዓት ለመዘርጋት ነው ተብሏል። ምክር ቤቱ፣ ኢትዮጵያዊያን ከአገር እንዳይወጡ የማገድ ሥልጣን ለኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የበላይ ኃላፊ የሰጠውን ሌላኛውን ረቂቅ አዋጅም አጽድቆታል።

3፤ በትናንቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የግል እና የውጭ መገናኛ ብዙሃን እንዳይገቡ እንደታገዱ ዶይቸቨለ ዘግቧል። ምክር ቤቱ የግልና የውጭ መገናኛ ብዙኀን ለምን እንዳይገቡ እንዳገደ አለመግለጡን ዘገባው አመልክቷል። ምክር ቤቱ ትናንት የተወያየው፣ በ2017 የፌደራል ረቂቅ በጀት እና የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትን በሚመለከት በቀረቡለት ረቂቅ አዋጆች ላይ ነበር። ምክር ቤቱ የዕለቱን ውይይት በማኅበራዊ ትስስር ገጾቹም በቀጥታ አላስተላለፈውም።

4፤ ጅቡቲ፣ በሱማሌላንድ ግጭት እንዲቀሰቀስ በማድረግ ላይ ናት በማለት ሱማሌላንድ ያቀረበችባትን ውንጀላ "ሐሰት" እና "መሠረተ ቢስ" በማለት አስተባብላለች። ጅቡቲ በጎረቤቶቿ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደማትገባ የገለጡት የአገሪቱ ባለስልጣናት፣ ሱማሌላንድም በጅቡቲ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳትገባ አሳስበዋል። ጅቡቲ ይህን ምላሽ የሰጠችው፣ ከሱማሌላንድ እንገነጠላለን የሚሉትን የአውዳል ግዛት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በማስተናገድ ላይ ትገኛለች በማለት ሱማሌላንድ መክሰሷን ተከትሎ ነው። [ዋዜማ]
በአዳማ ከተማ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ቢያንስ 7 ሰዎች ተገደሉ- https://tinyurl.com/yzetzskn
ለቸኮለ! ረቡዕ ሰኔ 26/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በኦሮሚያ ክልል በአዳማ ከተማ አሮሬቲ እና ቶርበን ኦቦ በተባሉ ቀበሌዎች ዛሬ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ላይ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች በተኮሱት ጥይት አንዲት ነፍሰ ጡርን ጨምሮ 7 ሰዎች እንደተገደሉና ቁጥራቸው ያልታወቁ ሌሎች ሰዎች እንደቆሰሉ ዋዜማ ከነዋሪዎች ሰምታለች። ተቃውሞው የተቀሰቀሰው፣ የከተማዋ አስተዳደር 1 ሺሕ 500 ገደማ መኖሪያ ቤቶችን ሕገወጥ ናቸው በማለት ማፍረስ ሲጀምር መኾኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ፣ መሬቶቹን ከአካባቢው አርሶ አደሮች ገዝተው ከ2005 ዓ፤ም ጀምሮ ለከተማዋ አስተዳደር ግብር ሲከፍሉ መቆየታቸው ገልጸዋል። ነዋሪዎቹ ቀደም ሲል ለጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት፣ ጉዳዩ በይደር እንዲታይ ተወስኖላቸው እንደነበርም ዋዜማ ተረድታለች። ዋዜማ በክስተቱ ዙሪያ የከተማዋን አስተዳደር ለማነጋገር ያደረገችው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

2፤ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች በአማራ ክልል ከሚካሄደው ግጭት ጋር በተያያዘ በጤና ባለሙያዎች፣ በታማሚዎችና በጤና ተቋማት ላይ የጦር ወንጀል ሊባሉ የሚችሉ መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን ፈጽመዋል በማለት አዲስ ባወጣው ሪፖርት ከሷል። የኢትዮጵያ አጋሮች በክልሉ በጤና አገልግሎቶች ላይ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች ተጠያቂነት እንዲሠፍንና ጥቃቶች እንዲቆሙ ግፊት እንዲያደርጉ ድርጅቱ ጠይቋል። ድርጅቱ፣ የመንግሥት ወታደሮች የሆስፒታሎችን ሥራ እንደሚያስተጓጉሉ፣ የጤና ባለሙያዎችን ቁስለኞችን አክማችኋል በማለት እንደሚደበድቡ፣ በዘፈቀደ እንደሚያስሩና እንደሚያስፈራሩ፣ የአምቡላንሶችን አገልግሎትና የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን እንደሚያስተጓጉሉ እንዲኹም ታማሚዎችን የፋኖ ታጣቂዎች ደጋፊ ናችሁ በማለት እንደሚያስሩ በሪፖርቱ አብራርቷል። በግጭቱ ሳቢያ ከፍተኛ የሕክምና አቅርቦቶች እጥረት እንደተከሰተም ሪፖርቱ ገልጧል። ሂውማን ራይትስ ዎች፣ መንግሥት የጤና ተቋማትን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችል የተለየ ሕግ እንዲያወጣም ጠይቋል።

3፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር እንዲኹም የባሕልና ስፖርት ሚንስትሮችን ዛሬ ከሥልጣን አንስተዋል። ዐቢይ በቀድሞው የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስትር ገብረመስቀል ጫላ ምትክ፣ በሚንስቴሩ ሚንስትር ደዔታ የነበሩትን ካሳሁን ጎፌን ሹመዋል። በቀድሞው የባሕልና ስፖርት ሚንስትር ቀጀላ መርዳሳ ምትክ ደሞ፣ ሽዊት ሻንካ ተሹመዋል። ቀጀላ፣ የጠቅላይ ሚንስትሩ የወጣቶችና ስፖርት አማካሪ ኾነው እንደተሾሙ የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ገልጧል።

4፤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፣ በሱዳን የሚካሄደው ጦርነት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደተጠለሉባቸው በምሥራቃዊ ሱዳን ወደሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች እየተቃረበ ነው በማለት ስጋታቸውን በ"ኤክስ" ገጻቸው ባሠፈሩት መልዕክት ገልጸዋል። ጦርነት እየተቃረበ ያለው፣ በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተሰደዱ የትግራይ ተወላጆች ወደተጠለሉባቸው "ተኔድባ" እና "ኡምራኩባ" ወደተባሉ መጠለያዎች እንደኾነ ጌታቸው ገልጸዋል። ጌታቸው፣ ተፋላሚ ወገኖች ግጭቱን ባስቸኳይ እንዲያቆሙና የሲቪሎችን ደኅንነት እንዲያስጠብቁ ዓለማቀፍና ቀጠናዊ አጋሮች ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ መንግሥትም፣ በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ሰቆቃቸው እንዲያበቃ ጥረት እንዲያደርግ ጌታቸው አሳስበዋል።

5፤ መንግሥት፣ አዲስ ጀማሪ ነዳጅ አከፋፋዮች በኹለት ዓመታት ውስጥ 500 ሺህ ሊትር ነዳጅ የሚያጠራቅም ዴፖ፣ አራት ነዳጅ ማደያዎች እንዲኹም በሦስት ዓመታት ውስጥ ተጨማሪ ስድስት ማደያዎችን እንዲገነቡ ግዴታ ሊጥል እንደኾነ ሪፖርተር ዘግቧል።  መንግሥት ያዘጋጀው ረቂቅ የነዳጅ አዋጅ፣ ነዳጅ አከፋፋዮች በሥራቸው የሚያስተዳድሩት ነዳጅ ማደያ የነዳጅ ውጤቶችን ለመጨረሻዎቹ ተጠቃሚዎች ባግባቡ ማሠራጨቱን ማረጋገጥ እንዳለባቸው መደንገጉን ዘገባው አመልክቷል። የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን፣ አዋጁን የሚጥሱ አካላትን የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀቶች ወይም የግንባታ ፍቃዶች ሊያግድ ወይም ሊሰርዝ እንደሚችል በረቂቅ አዋጁ ላይ ሠፍሯል ተብሏል። ነባር የነዳጅ ግብይት ተዋናዮችም አዋጁ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ በ6 ወራት ውስጥ መሥፈርቶችን አሟልተው የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ካላገኙ የንግድ ፍቃዳቸው ይሰረዛል የሚል ድንጋጌ እንደተካተተ ዘገባው ጠቅሷል።

6፤ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እና ከጋዜጣዋ መስራቾች አንዱ የነበረው ነቢይ መኮንን ዛሬ በ68 ዓመት ዕድሜው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ነቢይ፣ ባደረበት ሕመም አዲስ አበባ ውስጥ ሕክምና ሲከታተል ቆይቶ ሕይወቱ እንዳለፈ ታውቋል። ነቢይ፣ ለበርካታ ዓመታት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በዋና አዘጋጅነት ከመስራቱ ባሻገር፣ በገጣሚነቱ እና ደራሲነቱ ከፍተኛ እውቅና ያተረፈ የስነ ጽሁፍ ሰው ነበር። ነቢይ፣ በቀድሞው መንግሥት በኢሕአፓ አባልነቱ ለበርካታ ዓመታት ለእስር ተዳርጎ እንደነበር ይታወሳል። ዋዜማ፣ በዚህ አጋጣሚ ለነቢይ ቤተሰቦች፣ ለሥራ ባልደረቦቹና ወዳጆቹ መጽናናትን ትመኛለች።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 57 ብር ከ3540 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 58 ብር ከ5011 ሳንቲም ኾኖ እንደዋለ በድረ ገጹ አስታውቋል። ባንኩ፣ የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 69 ብር ከ2769 ሳንቲም እና መሸጫው 70 ብር ከ6624 ሳንቲም እንደኾነም አመልክቷል። በተመሳሳይ፣ አንድ ዩሮ በ61 ከ4835 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ7132 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
የትግራይ ታጣቂዎች ከራያ አላማጣ አካባቢዎች እንዲወጡ ትዕዛዝ ተሰጣቸው- ዝርዝር መረጃ ይኸው- https://tinyurl.com/3zhkwak9
ለቸኮለ ማለዳ! ሐሙስ ሰኔ 27/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ዛሬ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በ2016ቱ የፌደራል በጀት አፈጻጸም ዙሪያ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ይሰጣሉ። ምክር ቤቱም፣ በቀጣዩ ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ የበጀትና ፕላን ቋሚ ኮሚቴ በሚያቀርብለት ሪፖርት ላይ ከተወያየ በኋላ ረቂቅ በጀቱን እንደሚያጸድቅ ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል።

2፤ ፍትህ ሚንስቴር፣ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲውን ለማስፈጸም የዓለማቀፍ ወንጀሎችና የሽግግር ፍትህ ልዩ ችሎት ማቋቋሚያ አዋጆችን እንደሚያወጣ አስታውቋል። በፖሊሲው መሠረት ሕጋዊ ተቋማት እስኪቋቋሙ፣ የሽግግር ፍትሕ ጊዜያዊ የተቋማት ቅንጅታዊ አመራር መድረክ ሃላፊነቱን ተረክቦ እንደሚቆይ ሚንስቴሩ መግለጡን የመንግሥት ዜና አውታሮች ዘግበዋል። ሰው የማሰቃየት፣ መሰወር፣ ጾታዊ ጥቃትና የጦር ወንጀሎች በአዲስ የሕግ ማዕቀፍ እንደሚቀረጹና በፌደራል ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ጉልህ ጥሰቶችን ማየትን በተመለከተ አዋጅ እንደሚወጣ ሚንስቴሩ ገልጧል ተብሏል።

3፤ አሜሪካ፣ የኢትዮጵያ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት እና የተመድ ስደተኞች ኮሚሽን ሱዳናዊያን ስደተኞችን ምዕራብ ጎንደር ዞን ውስጥ ለደኅነታቸው አስተማማኝ ወደኾነ አዲስ መጠለያ ለማዛወር እያደረጉት ያለውን ጥረት እንደምትደግፈው አስታውቃለች። በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ ባሠራጨው መግለጫ፣ አሜሪካ ለስደተኞች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ ያጋጠመውን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ ከአጋሮች ጋር ጥረት እንደምታደርግ ገልጧል። በስደተኞች ላይ ጥቃቶችን የሚያደርሱ ወገኖችም ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ አሜሪካ አሳስባለች።

4፤ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ በአማራ ክልል ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ባስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ለታሠሩ 47 ተጠርጣሪዎች ትናንት ከ20 ሺሕ እስከ 30 ሺሕ የሚደርስ የገንዘብ ዋስትና መፍቀዱን ፋና ብሮድካስት ዘግቧል። ፍርድ ቤቱ ዋስትናውን የፈቀደው፣ መርማሪ ፖሊስ ለሦስተኛ ጊዜ 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ እንዲሰጠው ያቀረበውን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ እንደኾነ የዜና ምንጩ ጠቅሷል። ፍርድ ቤቱ፣ በ14 ተጠርጣሪዎች ላይ ደሞ 15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ለመርማሪ ፖሊስ እንደፈቀደ ዘገባው አመልክቷል።

5፤ መንግሥት ያቋቋመው ብሄራዊ ኮሚቴ ትናንት በሦስት ዙር ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ባስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ የነበሩ 1 ሺህ 178 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞችን ወደ አገራቸው መመለሱን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል። ከተመላሾቹ መካከል፣ ዕድሜያቸው ከአስራ ስምንት ዓመት በታች የኾኑ 14 ታዳጊዎች እንደሚገኙበት ሚንስቴሩ ገልጧል። ኮሚቴው ከሚያዝያ 4 ጀምሮ ከሳዑዲ ዓረቢያ የመለሳቸው ዜጎች ቁጥር ከ55 ሺህ በላይ ደርሷል ተብሏል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሐሙስ ሰኔ 27/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የትግራይ ኃይሎች በቅርብ ወራት መልሰው ከተቆጣጠሯቸው ራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረም፣ ዛታ፣ ዋጃ እና ጥሙጋ እስከ ሰኔ 30 እንዲወጡ ፌደራል መንግሥት ማዘዙን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች፡፡ በግጭት ማቆም ስምምነቱ መሠረት ተፈናቃዮች ወደቀያቸው እንዲመለሱ፣ መከላከያ ሠራዊትና ፌደራል ፖሊስ የትግራይ ታጣቂዎች በቀነ ገደቡ እንዲወጡ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በትዕዛዙ መሠረት፣ ከሰኔ 25 ጀምሮ የትግራይ ኃይሎች ከዋጃ እና ጥሙጋ አንዳንድ አካባቢዎች መውጣት መጀመራቸውንና በአላማጣ ከተማ ግን እስከ ሰኔ 26 ሲንቀሳቀሱ መታየታቸውን ዋዜማ ከነዋሪዎች ሰምታለች፡፡ በከተማዋ ሰላማዊ ሰልፎች የታገዱ ሲኾን፣ የባጃጅ እንቅስቃሴም ከቀኑ 12 ስዓት በኋላ እንዲኹም ከምሽቱ ኹለት ሰዓት ጀምሮ የሰዎች እንቅስቃሴና የምግብ ቤቶችና መዝናኛ ቤቶች አገልግሎት አንዳይኖር ገደብ እንደተጣለ ታውቋል፡፡ Link- https://tinyurl.com/3zhkwak9

2፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ መንግሥት የሕሊና እስረኞችን ለመፍታትና የጅምላ ግድያን ጨምሮ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማቆም ምን እንደወሰነ ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። የአብን ተወካይ አበባው ደሳለው፣ የመንግሥት ኃይሎች አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተገን አድርገው በርካታ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የጅምላ ግድያዎችን ፈጽመዋል በማለት ከሰዋል። የምክር ቤት አባሉ፣ በፍኖተሰላም፣ መርዓዊ፣ ደብረ ኤሊያስ፣ ጅጋ፣ ደብረሲና፣ ጎንደር እና ወሎ ተፈጽመዋል ያሏቸውን ግድያዎች ጠቅሰዋል። ዐቢይ ግን፣ መከላከያ ሠራዊት ሕዝብን በጅምላ አልገደለም በማለት ክሱን አስተባብለዋል። የምክር ቤት አባሉ፣ በሕዝብ ተመራጮች፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ ጅምላ እስሮች እንደተፈጸሙ አብራርተዋል። አማራ ክልልን በፌደሬሽን ምክር ቤት የወከሉት ሐብታሙ በላይነህ፣ በመንግሥት ኃይሎች ከተወሰዱ በኋላ ላለፉት አራት ወራት የት እንደደረሱ እንደማይታወቅም የምክር ቤት አባሉ ገልጸዋል።

3፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ ለቀጣዩ በጀት ዓመት 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በጀት አጽድቋል። መንግሥት ከበጀቱ 451 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ያህሉን የመደበው ለመደበኛ ወጪዎች እንዲኹም 283 ነጥብ 2 ቢሊዮኑን ለካፒታል ወጪዎች ሲኾን፣ 236 ነጥብ 7 ቢሊዮኑ ደሞ ለክልሎች ድጎማ የተመደበ ነው። ከበጀቱ 139 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የአገሪቱን ዕዳ ለመክፈል ተመድቧል። በጀቱ ከዘንድሮው ዓመት በጀት በ21 ነጥብ 1 በመቶ ብልጫ አለው። የ2017 ዓ፣ም በጀት የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አካል በኾነው ከ2016 እስከ 2018 በሚቆየው የልማትና ኢንቨስትመንት እቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችን እና ከ2017 እስከ 2021 ዓ፣ም የሚቆየውን የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚና የፊስካል ማዕቀፍ ለማስፈጸም የተዘጋጀ ነው።

4፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ የተሻሻለውን የወጪ ንግድ የቀረጥ ማበረታቻ አዋጅ አጽድቋል፡፡ የተሻሻለው የወጪ ንግድ ማበረታቻ አዋጅ፣ የዓለማቀፍ ገበያ በመቀዝቀዙ ምክንያት ያመረቱትን ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ያልቻሉ አምራቾችን እንዲኹም መንግሥት በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ አገር ባስገቧቸው ጥሬ እቃዎች ምርት ለማምረት እና ወደ ውጪ ገበያ ለመላክ ያልቻሉትን ላኪዎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጧል። አዋጁ፣ የቀረጥ ማበረታቻው ተጠቃሚዎች በጥሬ እቃው ምርት አምርተው ወደ ውጭ ላለመላክ በቂ ምክንያት የኾኑ ችግሮች እስከሚወገዱላቸው ድረስ ጉምሩክ ኮሚሽን የጊዜ ገደቡን እንዲያራዝምላቸው ይፈቅዳል ተብሏል። ምክር ቤቱ፣ በዕቃዎችና አገልግሎቶች ፍጆታ ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ የሚጥለውን አዋጅም አጽድቋል።

5፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ከተፈጸሙ ብሄር ተኮር ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ ያሳለፈባቸው የቀድሞ የዞኑና የፌደራል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በልዩ ምኅረት ከእስር እንደተፈቱ ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል። በምኅረት የተለቀቁት፣ የዞኑን የቀድሞው ሰላምና ጸጥታ ኃላፊ ፋንቻ አንሳያን ጨምሮ ከ20 እስከ 22 ዓመት የእስር ቅጣት የተላለፈባቸው የወረዳ አመራሮች የሚበዙባቸው 86 ሰዎች እንደኾኑ የዞኑ ባለሥልጣናት መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል። በፌደራል መንግሥቱ ውሳኔ ለፍርደኞቹ ምኅረት የተሰጠው፣ የሌሎች ክልሎች መንግሥታት እንዳደርጉት ለሕዝብ ጥቅም ሲባልና የክልሉ መንግሥትም ከቀድሞ ታጣቂዎች ጋር እርቅ በማውረዱ እንደኾነ ባለሥልጣናቱ መግለጣቸውንም ዘገባው ጠቅሷል። በምኅረት የተለቀቁት ሰዎች ወደቀድሞ የመንግሥት ሥራቸው ሊመለሱ ይችላሉ ተብሏል።

6፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 57 ብር ከ3597 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 58 ብር ከ5069 ሳንቲም ኾኖ እንደዋለ በድረ ገጹ አስታውቋል። ባንኩ፣ የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 69 ብር ከ5851 ሳንቲም እና መሸጫው 70 ብር ከ9768 ሳንቲም እንደኾነም አመልክቷል። በተመሳሳይ፣ አንድ ዩሮ በ61 ከ7248 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ62 ብር ከ9593 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ዓርብ ሰኔ 28/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የጋራ ድንበር አስተዳዳሪዎች ስብሰባ ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ ተጀምሯል። ስብሰባው፣ በጋራ የድንበር መሠረተ ልማት፣ በልማት ትብብርና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ዙሪያ እንደሚያተኩር ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል። ስብሰባው ለኹለት ቀን ይቆያል ተብሏል። ከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ ክልል የሚገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽሙ መቆየታቸው ይታወሳል።

2፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ የአከራይና ተከራይ ውል የምዝገባ የጊዜ ገደብን ከሰኔ 30 ወደ ሐምሌ 24 ማራዘሙን አስታውቋል። ቢሮው፣ የምዝገባውን ቀነ ገደብ ያራዘመው፣ በርካታ ተመዝጋቢዎች በመኖራቸውና ቀነ ገደቡ እንዲራዘም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄ በማቅረባቸው እንደኾነ ገልጧል። ቢሮው ከሰኔ 1 እስከ ሰኔ 26 ቀን ድረስ ከ248 ሺሕ በላይ የኪራይ ውል ማስፈጸሙን ተናግሯል። ቢሮው የአከራይና ተከራይ ውል የሚያስፈጽመው፣ አስተዳደሩ ያወጣውንና አከራዮች በዓመት አንድ ጊዜ ካልኾነ በስተቀር የመኖሪያ ቤት ኪራይ እንዳይጨምሩ የሚያግደውን የመኖሪያ ቤት ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ ነው።

3፤ የኤርትራ መንግሥት ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ሴቶችንና ሕጻናትን ጨምሮ በእምነታቸው የተነሳ 218 የክርስትና እምነት ተከታዮችን ማሠሩን ተቀማጭነቱን ብሪታንያ ያደረገው "ሪሊዝ ኢንተርናሽናል" የተሰኘ ድርጅት አስታውቋል። በተያዘው ዓመት የታሠሩትን ጨምሮ፣ የኤርትራ መንግሥት ባጠቃላይ ከእምነታቸው ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት ሳያቀርብ ያሠራቸው ክርስቲያኖች ብዛት 400 መድረሱን ድርጅቱ ገልጧል። ድርጅቱ፣ ከጥር እስካለፈው ግንቦት ወር ብቻ 110 ክርስቲያኖች ታስረዋል ተብሏል። የኤርትራ መንግሥት እውቅና የሰጠው፣ ለኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ ወንጌላዊት ሉተራን ቤተክርስቲያናትና ለእስልምና እምነት ብቻ ሲኾኑ ባብዛኛው ለእስር የሚዳረጉት የፕሮቴስታንትና የይሐዋ ምስክር እምነቶች ተከታዮች እንደኾኑ ይነገራል። የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ልዩ ራፖርተርም፣ ኤርትራ የሐይማኖት ነጻነትን እንደምትደፈጥጥ በተደጋጋሚ ገልጧል።

4፤ የአውሮፓ ኅብረት የባሕር ኃይል መርከቦች ሰሞኑን ከሱማሊያዋ ፑንትላንድ ራስ ገዝ የባሕር ዳርቻ ደርሰዋል። ኅብረቱ መርከቦቹን ወደ ፑንትላንድ ጠረፍ የላከው፣ የባሕር ላይ ወንበዴዎችን ጥቃትና ባሕር ላይ የሚፈጸም ሽብርን ለመከላከል፣ ሕገወጥ የአሳ ማጥመድ ድርጊቶችን፣ ሕገወጥ የጦር መሳሪያና የአደንዛዥ እጽ ንግድን ለመቆጣጠር ነው። የየመን ኹቲ ኃይሎች ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችንና የጦርነት ቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን በሱማሊያ የባሕር ጠረፍ በኩል ለአልሸባብ እንደሚልኩ ዓለማቀፍ የዜና ምንጮች መዘገባቸው አይዘነጋም። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ዓርብ ሰኔ 28/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ኢሰመኮ፣ በአማራ ክልል ከታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት በኋላም እስር እና የእንቅስቃሴ ገደቦች መቀጠላቸውን ዛሬ ይፋ ባደረገው ሦስተኛው ዓመታዊ ሪፖርቱ አስታውቋል። ሪፖርቱ፣ ከሰኔ 2015 እስከ ሰኔ 2016 ዓ፤ም ባለው ጊዜ፣ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶችን፣ የተፈናቃዮችን፣ የስደተኞችና የሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሰብዓዊ መብቶች የሚሸፍን እንደኾነ ኮሚሽኑ ገልጧል። ኮሚሽኑ፣ ታጣቂዎችና የመንግሥት ኃይሎች የሚወስዷቸው ርምጃዎች በሲቪሎች ላይ የሚያደርሱት የሞትና የአካል ጉዳትና ከሕግ ውጪ የኾነ ግድያ እንዲኹም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በሲቪሎች ላይ የሚፈጸሙ እገታዎች አሳሳቢነታቸው መቀጥሏል ብሏል። በቀጣዩ ዓመት የትጥቅ ግጭቶች በሰላማዊ ውይይት እንዲፈቱ ማድረግ፣ የምክክርና የሽግግር ፍትሕ ሂደቶችን አተገባበር ተዓማኒነት ማረጋገጥ እና ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ የታሠሩ ሰዎች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ ወይም ዋስትናቸው እንዲከበር ማድረግ ትኩረት ከሚሹ ጉዳዮች መካከል እንደኾኑ ኮሚሽኑ ጠቅሷል።

2፤ ላለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ኾነው ያገለገሉት ዳንዔል በቀለ የሥራ ጊዜያቸው በማብቃቱ ከዋና ኮሚሽነርነት ተሰናብተዋል። የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመኾኑ፣ ዳንዔልን ያሰናበቷቸው የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ታገሠ ጫፎ ናቸው። ኮሚሽኑ በዳንዔል አመራር ወቅት፣ መንግሥታዊ አካላት የሚፈጽሟቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች በሚጠቀሙት ከመጠን ያለፈ ኃይል እና ግድያዎችንና ከሕግ ውጭ የኾኑ እስሮችን ጨምሮ በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ጥልቅ ምርመራ ሲያካሂድ እና ሪፖርት ሲያወጣ ቆይቷል። ዳንዔል ከኮሚሽነርነታቸው የተሰናበቱት፣ ኮሚሽኑ ዓመታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርቱን ባወጣበት ቀን ላይ ነው።

3፤ የኢሰመኮ ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ከዓለማቀፍ ድርጅቶች ወይም አጋር አገራት የገንዘብ ድጋፍ ማግኘታቸው ነጻነታቸውን የሚቃረን ተደርጎ መወሰድ የለበትም በማለት ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። ዳንዔል ይህን የተናገሩት፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከውጭ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙ የሰብዓዊ መብት ተቋማትን አሠራር እንደገና መፈተሽ ያስፈልጋል በማለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡ ማግስት ነው። ዛሬ የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁት ዳንዔል፣ ኢሰመኮ ከውጭ አጋሮች የገንዘብ ድጋፍ በማግኘቱ ማናቸውም ዓይነት ተጽዕኖ ደርሶበት እንደማያውቅ ተናግረዋል። ዳንዔል ፌደራል መንግሥቱም ከዓለማቀፍ አጋሮቹ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያገኝ ጠቅሰው፣ ከውጭ ድርጅቶችና አገራት የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት ከተቋማዊ ነጻነት ጋር እንደማይቃረን አብራርተዋል።

4፤ ታጣቂዎች ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በሦስት አውቶብሶች ሲጓዙ የነበሩ ከ100 በላይ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችንና ሌሎች መንገደኞችን ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ገርበ ጉራቻ ከተማ አካባቢ ረቡዕ'ለት እንዳገቱ መስማቱን ጠቅሶ ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል። በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ ከሚገኘው ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ እና ከባሕር ዳር የተነሱት ተማሪዎችና ሌሎች ተጓዦች ላይ እገታ የተፈጸመው፣ በጎሃ ጽዮን እና በቱሉ ሚልኪ ከተሞች መካከል እንደኾነ ከእገታው ያመለጡ ተማሪዎች መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል። የእገታው ፈጻሚዎች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ተማሪዎቹ ተናግረዋል ተብሏል። ዘገባው፣ ታጣቂዎቹ ለታጋቾች ማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቅ መጀመራቸውን መስማቱንም ጠቅሷል።

5፤ የተመድ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ባኹኑ ወቅት በግጭትና በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የተፈናቀሉ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የውስጥ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ አስታውቋል። ቢሮው፣ ለረጅም ጊዜ የተፈናቀሉ ተፈናቃዮች የሚገኙት በኦሮሚያ፣ ሱማሌና ትግራይ ክልሎች እንደኾነ ገልጧል። ከግማሽ በላይ የሚኾኑት ተፈናቃዮች፣ ከአንድ ዓመት በላይ፣ ከ23 በመቶ በላይ የሚኾኑት ከኹለት እስከ አራት ዓመት እንዲኹም 11 በመቶዎቹ ተፈናቃዮች ለአምስት ዓመት ያህል ከቀያቸው የተፈናቀሉ እንደኾኑ የቢሮው ሪፖርት አመልክቷል። 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተፈናቃዮች ከጥር 2014 ዓ፤ም ወዲህ ወደ ቀያቸው እንደተመለሱ የገለጠው ቢሮው፣ ለበርካታ ዓመታት የቆዩ ተፈናቃዮች የጸጥታ ኹኔታዎች ሲፈቅዱ ድጋፍ ተደርጎላቸው እንዲመለሱ ወይም ካስጠለሏቸው ማኅበረሰቦች ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ ማድረግ እንደሚቻል ጠቅሷል።

6፤ የኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የጋራ ድንበር አስተዳዳሪዎች ስብሰባ ትናንት እና ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዷል። ስብሰባው፣ በጋራ የድንበር መሠረተ ልማት፣ በልማት ትብብርና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ዙሪያ ያተኩረ እንደኾነ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል። የጋራ የድንበር አካባቢ አስተዳዳሪዎች ስብሰባ ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ተገልጧል። ከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ ክልል የሚገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽሙ መቆየታቸውና ይህም በኹለቱ አገራት መንግሥታት መካከል አንድ መነጋገሪያ አጀንዳ ኾኖ መቆየቱ ይታወሳል።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 57 ብር ከ3701 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 58 ብር ከ5175 ሳንቲም ኾኖ እንደዋለ በድረ ገጹ አስታውቋል። ባንኩ፣ የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ 69 ብር ከ8498 ሳንቲም እና መሸጫው 71 ብር ከ2468 ሳንቲም እንደኾነም አመልክቷል። በተመሳሳይ፣ አንድ ዩሮ በ61 ከ9425 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ63 ብር ከ1814 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ቅዳሜ ሰኔ 29/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር ወደ ኢትዮጵያና ጅቡቲ ሊጓዙ እንደኾነ የአገሪቱ ውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል። አምባሳደር ሐመር በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ቆይታ፣ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች የግጭት ማቆም ስምምነቱን ተግባራዊነት በሚገመግመው የአፍሪካ ኅብረት ኹለተኛ ስብሰባ ላይ እንደሚሳተፉ መስሪያ ቤቱ ገልጧል። የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ፣ አሜሪካ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የኢትዮጵያ መንግሥትንና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን እንደምትደግፍ፣ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ለማስፈታት፣ ለመበተንና ከኅብረተሰቡ ጋር መልሶ ለማዋሃድና ለማቋቋም ድጋፍ እንደምታደርግ እንዲኹም የሽግግር ፍትሕና ተጠያቂነት እንዲሰፍንና ተፈናቃዮቹ እንዲመለሱ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቋል። ሐመር፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያለውን ግጭት በንግግር በመፍታት ዙሪያ ከባለሥልጣናት ጋር ይነጋገራሉ ተብሏል። ሐመር መቼ ኢትዮጵያ እንደሚገቡና ስንት ቀን እንደሚቆዩ ግን አልተገለጠም።

2፤ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አስተዳደር፣ ዋና አስተዳዳሪው አሕመድ ዓሊ ኢብሬ በተተኮሰባቸው ጥይት እንደተገደሉ አስታውቋል። አሕመድ የተገደሉት፣ ትናንት ከሚሴ ከተማ በሚገኘው መስጅድ ጁምአ ሶላት ሰግደው ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ ሳሉ በተተኮሰባቸው ጥይት እንደኾነ ገልጧል። አስተዳደሩ በዋና አስተዳዳሪው ላይ ግድያውን የፈጸሙት፣ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው ብሏል።

3፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ በአዲስ አበባ ለኹለት ቀናት የተካሄደው የመጀመሪያው የኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የጋራ የድንበር አስተዳዳሪዎች ስብሰባ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ትናንት ምሽት መጠንቀቁን አስታውቋል። የምክክር መድረኩ፣ በኹለቱ አገሮች የጋር ድንበር አካባቢ የሚከሰቱ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫ እንዳስቀመጠ ተገልጧል። ስብሰባው፣ የጋራ ደኅንነትን ለማጎልበት፣ የስደተኞችን ዝውውር ለመቆጣጠር፣ የጋራ ልማት፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር፣ የጎሳ ግጭቶችንና ድንበር-ዘለል የከብት ዝርፊያዎችን ለመቅረፍ የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጧል ተብሏል።

4፤ መንግሥት ያቋቋመው ብሄራዊ ኮሚቴ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ በችግር ውስጥ የነበሩ 1 ሺሕ ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞችን ትናንት በሦስት ዙር በረራ ወደ አገራቸው እንደመለሰ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል። ከተመላሾቹ መካከል 19ኙ ጨቅላ ሕጻናት እንደኾኑና 48ቱ ደሞ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የኾኑ ታዳጊዎች እንደሚገኙበት ሚንስቴሩ ገልጧል። ብሄራዊ ኮሚቴው ወደ አገራቸው የመለሳቸው ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች ብዛት ከ56 ሺሕ በላይ አልፏል።

5፤ የተመድ ዋና ጸሃፊ የሱዳን ልዩ መልዕክተኛ ራማኔ ላማምራ፣ የሱዳን ጦር ሠራዊት እና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪዎች ጀኔቫ ውስጥ ቀጥተኛ ያልኾነ ንግግር እንዲያደርጉ እንደጋበዙ የሱዳን ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ቀጥተኛ ያልኾነው ንግግር ዓላማው፣ ሲቪሎችን ከጥቃት ለመከላከል እና ጦርነቱ የፈጠረውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመፍታት እንደኾነ ልዩ መልዕክተኛው መግለጣቸውን ዘገባው አመልክቷል። ንግግሩ፣ በጀኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን እና ጀኔራል ሞሃመድ ደጋሎ መካከል ከሐምሌ 3 ጀምሮ እንደሚካሄድና ኹለቱ ጀኔራሎች በንግግሩ መሳተፍ አለመሳተፋቸውን አስቀድመው ማረጋገጫ እንዲሰጡ በደብዳቤ እንደተጠየቁ ተገልጧል። የሱዳን ጦር ሠራዊት ግን፣ ከንግግር በፊት የፈጥኖ ደራሹ ኃይል በቅድሚያ ከከተሞች መውጣት አለበት የሚል አቋሙን ካኹን ቀደም ሲያንጸባርቅ መቆየቱ ይታወሳል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ቅዳሜ ሰኔ 29/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ምርጫ ቦርድ፣ በአራት ክልሎች ሰኔ 16 የድጋሚና ቀሪ ምርጫዎች ባካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች ገዥው ብልጽግና ፓርቲ በከፍተኛ ድምጽ አብዛኞቹን ወንበሮች ማሸነፉን ዛሬ ይፋ አድርጓል። ቦርዱ ዛሬ ይፋ ባደረገው ውጤት፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ አራት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ሲያገኝ፣ ተቃዋሚዎቹ ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) እያንዳንዳቸው አንድ መቀመጫ አሸንፈዋል። ከክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎች ደሞ፣ ብልጽግና ፓርቲ 60 መቀመጫዎችን ሲያሸንፍ፣ ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሦስት እንዲኹም ጉሕዴን ስምንት መቀመጫዎችን አሸንፈዋል። ብልጽግና ፓርቲ፣ በአፋር ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኹለት፣ ለክልል ምክር ቤት 27፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሦስት የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን እንዲኹም በሱማሌ ክልል ሰባት የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን እንዳሸነፈ ተገልጧል።

2፤ ከግጭት ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ውስጥ የሚፈጸሙ ዓለማቀፍ ወንጀሎችን ለመዳኘት የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ በኹለት ወራት ውስጥ ለሚንስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ይፋ ካልኾነ የፍትሕ ሚንስቴር ሰነድ መመልከቱን ጠቅሶ ሪፖርተር ዘግቧል። ረቂቅ አዋጁ፣ የጦር ወንጀሎች፣ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንዲኹም አስገድዶ የመሠወር፣ የጾታዊ ጥቃትና የግርፋት ወንጀሎችን እንደሚሸፍንና ወደኋላ ተመልሶ እንደሚሠራ በሰነዱ ላይ እንደሠፈረ ዘገባው አመልክቷል። ፍትሕ ሚንስቴር፣ ለሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ማስፈጸሚያ የልዩ ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ፣ የልዩ ፍርድ ቤት ዳኞች አመራረጥ እንዲኹም የልዩ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጆችን እያዘጋጀ እንደኾነም ዘገባው ጠቅሷል። በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ማዕቀፍ ሥር የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን ለማቋቋም፣ የዳኞች፣ የወንጀል መርማሪዎችና ባለሙያዎች ቡድን ልምድ ለመቅሰም ወደ ሩዋንዳና ሔግ ወደሚገኘው ዓለማቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እንዲሄድም ታስቧል ተብሏል።

2፤ አምስት ሺሕ የሚጠጉ የማይጸብሪ ከተማ እና የጸለምት ወረዳ የጦርነት ተፈናቃዮች ትናንት ወደ ቀያቸው እንደተመለሱ አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል። ተፈናቃዮችን በቅርቡ የመመለሱ ሂደት ከተጀመረ ወዲህ፣ የትናንቱ ሦስተኛው ዙር ነው። በመጀመሪያው ዙር፣ 1 ሺሕ 500 ተፈናቃዮች እና በኹለተኛው ዙር 2 ሺሕ ያህል የአካባቢው ተፈናቃዮች ወደቀያቸው መመለሳቸው እንደተዘገበ ይታወሳል። ባጠቃላይ ከ8 ሺሕ 500 እስከ 10 ሺሕ የሚገመቱ ተፈናቃዮች ይመለሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ተፈናቃዮችን እስከ ሰኔ 30 ለመመለስ እንቅስቃሴ እያደረገ መኾኑ ቀደም ሲል መግለጡ ይታወሳል።

4፤ የሱዳን ወታደራዊ መሪ ጀኔራል ቡርሃን፣ በርካታ አገራት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የሚፈጽማቸውን ወንጀሎች "በቸልታ ይመለከታሉ" በማለት ትናንት ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ወቅሰዋል። ጀኔራል ቡርሃን፣ በሱዳን ሕዝብ ላይ እየተፈጸሙ ያሉትን ወንጀሎች በዝምታ የሚያልፉና ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ድጋፍ የሚያደርጉ አገራት ኹሉ "ጠላቶች ናቸው" ብለዋል። ኾኖም ቡርሃን ክስና ወቀሳ ያቀረቡባቸውን አገራት በስም አልጠቀሱም። ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ባኹኑ ወቅት የሱዳን ወታደራዊ መንግሥትና የዓለማቀፍ ድርጅቶች ጊዜያዊ መቀመጫና የአገሪቱ ዋነኛ ወደብ ወደኾነችው ፖርት ሱዳን በመቃረብ ላይ እንደኾነ ተነግሯል። ጀኔራል ቡርሃን ግን የሱዳን ጦር ሠራዊት "ፈጽሞ ሊሸነፍ አይችልም" በማለት ተናግረዋል።

5፤ ትናንት ሥልጣን የተረከበው አዲሱ የብሪታንያ መንግሥት፣ የቀድሞው መንግሥት ወደ አገሪቱ በሕገወጥ መንገድ ገብተዋል ያላቸውን ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ ለመላክ የጀመረውን አወዛጋቢ ሂደት እንደማይገፋበት አስታውቋል። አዲሱ መንግሥት፣ ከሩዋንዳ ጋር የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ ሊኾን እንደማይችል ጠቅሶ ውድቅ አድርጎታል። የቀድሞው መንግሥት "ሕገ-ወጥ" ያላቸውን ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ያወጣውን ፖሊሲ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ቢያግደውም፣ ወግ አጥባቂው ፓርቲ የሚቆጣጠረው የቀድሞው ፓርላማ ግን ፖሊሲውን ባለፈው ሚያዝያ አጽድቆት ነበር። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሰኞ ሐምሌ 1/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የአንበጣ መንጋ መከሰቱንና በዚህም ምክንያት አርሶ አደሮች ለከፍተኛ ስጋት መጋለጣቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለዋዜማ ተናግረዋል። የአንበጣ መንጋው መነሻ ከሰሜናዊ የኬንያ ሳይሆን እንዳልቀረ የገለጹት ነዋሪዎች፣ አንበጣው የደረሱ ሰብሎችን ሊያወድምና ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ብለው መስጋታቸውን አስረድተዋል። መንጋው ባካባቢው የታየው ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ‘ለት መኾኑን ምንጮች የገለጡ ሲኾን፣ በዞኑ በተለይም ድሬ በተባለ ወረዳ በስፋት መታየቱን ተናግረዋል። ነዋሪዎች፣ የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል መንግሥታዊ አካላት ጥረት እያደረጉ እንዳልኾነና፣ ጉዳዩ ችላ ከተባለ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ሊዛመት ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ለዋዜማ አስረድተዋል።

2፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፣ በኢትዮጵያ በሲቪሎችና ተማሪዎች ላይ የሚፈጸሙ እገታዎች መቆም. እንዳለባቸው አሳስበዋል። በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ ዛሬ ባሠራጨው የአምባሳደሩ አጭር መልዕክት፣ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚፈጸሙት ተደጋጋሚ እገታዎች የተራዘሙ ግጭቶች ወንጀለኞችን ምን ያህል እንደሚያበረታቱና የሕግ የበላይነትን ምን ያህል እንደሚያዳክሙ ያሳያል በማለት አምባሳደሩ መናገራቸውን ጠቅሷል። አምባሳደሩ፣ ባለፈው ሳምንት ከ100 በላይ ተማሪዎች እና ሌሎች መንገደኞች ለማስለቀቂያ ገንዘብ ሲባል መታገታቸውን ገልጸዋል።

3፤ የፕላንና ልማት ሚንስቴር፣ በአገሪቱ ከመጭው መስከረም ጀምሮ ላንድ ዓመት የሚቆይ የግብርና ናሙና ቆጠራ ሊያካሂድ መኾኑን ሪፖርተር ዘግቧል። በአገር ዓቀፉ የግብርና ናሙና ቆጠራ፣ የእርሻና የእንስሳት ሃብቶችን ጨምሮ ኹሉም በግብርናው ዘርፍ የሚገኙ ሃብቶች እንደሚቆጠሩ ዘገባው አመልክቷል። ለግብርና ናሙና ቆጠራው በመላ አገሪቱ 62 ሺሕ ሠራተኞች እንደሚሰማሩ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት አስታውቋል ተብሏል። ቆጠራው፣ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች፣ ሰፋፊ የኢንቨስትመንት እርሻዎችና በማኅበር እየለሙ የሚገኙ መሬቶችን እንደሚያካትት ተገልጧል። በአገሪቱ የመጨረሻው የግብርና ናሙና ቆጸራ የተካሄደው 22 ዓመታት በፊት ነበር።

4፤ የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ፣ በኤርትራ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ አሥመራ ገብተዋል። ፕሬዝዳንት ሞሐመድ በአሥመራ ቆይታቸው፣ ዛሬ ምሽት ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በኹለትዮሽና የጋራ በሚሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ እንደሚመካከሩ የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገብረመስቀል በ"ኤክስ" ገጻቸው አስታውቀዋል። ፕሬዝዳንት ሞሐመድ፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት በተፈራረሙ ማግስትም፣ በአሥመራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

5፤ ትናንት በእስራኤሏ ቴላቪቭ ከተማ በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚ ኤርትራውዊያን መካከል በተፈጠረ ግጭት አንድ ኤርትራዊ እንደሞተና ሌላ አንድ ኤርትራዊ እንደቆሰለ የእስራኤል ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የከተማዋ ፖሊስ በብጥብጡ ተሳትፈዋል ያላቸውን ስምንት ኤርትራዊያን ይዞ እንዳሠረ ዘገባዎቹ አመልክተዋል። የግጭቱ መነሻ ለጊዜው ግልጽ እንዳልኾነ ፖሊስ ገልጧል ተብሏል። ባለፈው ግንቦት አንድ ኤርትራዊ በተመሳሳይ የቡድን ብጥብጥ የተገደለ ሲኾን፣ መስከረም ላይ ደሞ በኹለቱ ቡድኖች መካከል በተቀሰቀሰ ኹከት ፖሊሶችን ጨምሮ 170 ሰዎች መቁሰላቸው ተዘግቦ ነበር።

6፤ ቦይንግ ኩባንያ፣ ኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያ ውስጥ ከተከሰከሱት ኹለት ማክስ 8 አውሮፕላኖች ጋር በተያያዘ በአሜሪካ ፌደራል ፍርድ ቤት ሊመሠረትበት የሚችለውን የወንጀል ክስ ለማስቀረት የማጭበርበር ወንጀል መፈጸሙን እንዳመነ የአሜሪካ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ቦይንግ፣ ከአሜሪካ ፍትህ መስሪያ ቤት ጋር በደረሰበት አዲሱ ስምምነት መሠረት 243 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ቅጣት ለመክፈል፣ ለሦስት ዓመታት ገለልተኛ የአውሮፕላን ደኅንነት ተቆጣጣሪ እንዲመደብበትና የደኅንነት ማረጋገጫዎቹን አስተማማኝ ለማድረግ 455 ሚሊዮን ዶላር ሙዓለ ንዋይ ለማፍሰስ እንደተስማማ ዘገባዎቹ አመልክተዋል። ኩባንያው ጥፋተኝነቱን ያመነው፣ በማክስ አውሮፕላኖቹ ላይ ማሻሻያ እንዲያደርግ ፍትህ መስሪያ ቤቱ ቀደም ሲል የሰጠውን የሦስት ዓመት የጊዜ ገደብ ባለማክበሩ ነው። የኹለቱ አውሮፕላን አደጋዎች ሟች ቤተሰቦችን የወከሉ ጠበቆች ግን፣ ፍርድ ቤት አዲሱን የቅጣት ስምምነት እንዳያጸድቅ ጠይቀዋል ተብሏል።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 57 ብር ከ3752 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 58 ብር ከ5227 ሳንቲም ኾኖ እንደዋለ በድረ ገጹ አስታውቋል። ባንኩ፣ የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ 70 ብር ከ0423 ሳንቲም እና መሸጫው 71 ብር ከ4431 ሳንቲም እንደኾነም አመልክቷል። በተመሳሳይ፣ አንድ ዩሮ በ62 ከ0685 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ63 ብር ከ3099 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ማክሰኞ ሐምሌ 2/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ብሄራዊ ባንክ፣ የሰኔ ወር የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ወደ 19 ነጥብ 9 በመቶ መውረዱን አስታውቋል። ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወር የተመዘገበው የዋጋ ንረት 29 ነጥብ 3 በመቶ ነበር። ምግብ ነክ ያልኾኑ ሸቀጦች የዋጋ ንረት ከ31 ነጥብ 4 በመቶ ወደ 15 ነጥብ 3 በመቶ መቀነሱን የጠቀሰው ባንኩ፣ ምግብ ነክ የኾኑት ሸቀጦች የዋጋ ንረት ደሞ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወር ከነበረበት 28 በመቶ ወደ 22 ነጥብ 7 በመቶ ወርዷል ብሏል። ባንኩ፣ የዋጋ ንረቱ የቀነሰው፣ መንግሥት በወሰዳቸው የገንዘብ ፖሊሲ ርምጃዎች ሳቢያ እንደኾነ ገልጧል። የባንኩ እቅድ፣ በቀጣዩ ዓመት ሰኔ የአገሪቱን አጠቃላይ የዋጋ ንረት ከ10 በመቶ በታች ማውረድ ነው።

2፤ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ ኢትዮጵያ በሰኔ ወር 46 ሺህ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረቧን አስታውቋል። አገሪቱ በወሩ ለውጭ ገበያ ያቀረበችው ቡና ክብረወሰን የሰበረ ነው ያለው ባለሥልጣኑ፣ ከቡና ሽያጩ 218 ሚሊዮን ዶላር እንደተገኘ ገልጧል። በጠቅላላ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ የቀረበው ቡና 298 ሺሕ 500 ቶን ሲኾን፣ ከወጪ ንግዱ የተገኘው ገቢ 1 ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር እንደኾነ ተገልጧል። ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር፣ የዘንድሮው በጀት ዓመት የቡና የወጪ ንግድ መጠኑ የ20 በመቶ ብልጫ እንዲኹም ከገቢ አንጻር የ7 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ አለው ተብሏል።

3፤ ባለፈው ሳምንት ከ100 በላይ ተማሪዎችንና መንገደኞችን ያገቱት ታጣቂዎች ላንድ ታጋች 1 ሚሊዮን ብር እየጠየቁ እንደሚገኙ መስማቱን ሮይተርስ ዘግቧል። የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አዝመራው ዘገዬ፣ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መታገታቸውን እንዳረጋገጡና ነገር ግን ዝርዝር መረጃ ከመስጠት እንደተቆጠቡ ዘገባው አመልክቷል። ከእገታው ያመለጠ አንድ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ፣ ታጣቂዎቹ ኦሮሚኛ ቋንቋ ይናገሩ እንደነበርና በጸጉራቸው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች እንደሚመስሉ ተናግሯል ተብሏል። ሮይተርስ፣ ፌደራል መንግሥቱ፣ የክልሉ መንግሥት እና የአማጺው ቡድን ቃል አቀባዮች በጉዳዩ ዙሪያ ላነሳው ጥያቄ ምላሽ እንዳልሰጡት ገልጧል።

4፤ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ 25 ሲቪክ ድርጅቶች፣ በክልሉ በሴቶች ላይ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች የጊዜያዊ አስተዳደሩ የጸጥታና ፍትሕ ተቋማት አስፈላጊውን ምላሽ እየሰጡ እንዳልኾነ አይደለም በማለት ወቅሰዋል። የፍትሕና ጸጥታ አካላት፣ በቅንነት፣ በገለልተኛነትና ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ ኹኔታ በሴቶች ላይ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች በአፋጣኝ ሕግ የማስከበር ሃላፊነታቸው ሊወጡ እንደሚገባም ድርጅቶቹ አሳስበዋል። ድርጅቶቹ ትናንት በጋራ ባወጡት መግለጫ፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙት ጥቃቶች እንዲቆሙ ጠይቀዋል። በክልሉ ከጦርነቱ ወዲህ፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙት ግድያዎች፣ እገታዎችና ሌሎች ጥቃቶች ተባብሰው ቀጥለዋል ተብሏል።

5፤ መንግሥት ያቋቋመው ብሄራዊ ኮሚቴ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ ባስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ የነበሩ 1 ሺሕ 174 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞችን ትናንት ወደ አገራቸው እንደመለሰ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል። ከተመላሾቹ መካከል፣ 79ኙ ሴቶች እንደኾኑና ዕድሜያቸው ከአስራ ስምንት ዓመት በታች የኾኑ 21 ታዳጊዎች እንደሚገኙበት ሚንስቴሩ ገልጧል። ኮሚቴው፣ ከሚያዚያ 4 ጀምሮ ወደ አገራቸው የመለሳቸው ፍልሰተኛ ዜጎች ቁጥር ከ58 ሺሕ በላይ ደርሷል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ማክሰኞ ሐምሌ 2/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ ኢትዮጵያ በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ከልብ እንደምትሠራ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሠፈሩት መልዕክት ገልጸዋል። ዐቢይ፣ "የወንድም የሱዳን ሕዝብ ችግር የእኛም ችግር፣ ሰላማቸውም ሰላማችን በመኾኑ፣ ለሱዳን ሕዝብ እፎይታና የብልጽግና ጉዞ ዛሬም እንደትናንቱ ከልባችን እንሠራለን" ብለዋል። ዐቢይ ከሱዳን ወታደራዊ መሪ ጀኔራል ቡርሃን ጋር በዝግ ባካሄዱት ውይይት፣ ጀኔራል ቡርሃን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እየፈጸመ ነው ያሉትን "በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል" ለዐቢይ አብራርተውላቸዋል። ካርቱም በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ቁጥጥር ሥር ከገባች ጀምሮ፣ ሰሜናዊቷ ፖርት ሱዳን የአገሪቱ ወታደራዊ መንግሥት፣ የዲፕሎማቶች እና የዓለማቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ ኾናለች።

2፤ አፍሪካ ኅብረት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሃት ኹለተኛውን ዙር የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት ትግበራ ሂደት ስትራቴጂክ ግምገማ ዛሬ በኅብረቱ ጽሕፈት ቤት ማካሄዳቸውን አስታውቋል። የኅብረቱ የፖለቲካ፣ ሰላምና ጸጥታ ሃላፊ አምባሳደር ባንኮሌ፣ የትግራይ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ለማስፈታት፣ ለመበተንና ከኅብረተሰቡ ጋር ለማዋሃድ ለተያዘው እቅድ እና ተፈናቃዮችንና ስደተኞችን ለማቋቋም ጠቀም ያለ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ በስትራቴጂክ ግምገማው ላይ ተገኝተዋል። አሜሪካም፣ የግጭት ማቆም ስምምነቱን ትግበራ ሂደት መደገፏን እንደምትቀጥልና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚካሄዱ ግጭቶች በንግግር እንዲፈቱ እንደምታበረታታ አስታውቃለች። ኹለቱ ወገኖች የመጀመሪያውን ዙር ስትራቴጂክ ግምገማ ያካሄዱት ባለፈው መጋቢት ነበር።

3፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል ከኹለት ሳምንት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ስለተቋረጠበት አገልግሎቱን ለማቆም ሊገደድ እንደሚችል ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል። በአሶሳ ከተማና በበርካታ ወረዳዎች ኤሌክትሪክ ኃይል የተቋረጠው፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን ታጣቂዎች ባንድ የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ላይ ባደረሱት ጉዳት እንደሆነ የአሶሳ ዞን ማስታወቁን ዘገባው አመልክቷል። የዞኑ ዘጠኝ ወረዳዎች እንዲኹም አሶሳ እና ባምባሲ ከተሞች ባኹኑ ወቅት ኤሌክትሪክ ኃይል እያገኙ እንዳልሆነ የአሶሳ ዞን አስተዳደር መግለጡንም ዘገባው ጠቅሷል። ሆስፒታሉ፣ ኤሌክትሪክ ኃይል ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ ለጄኔሬተር በየቀኑ ከ180 እስከ 200 ሊትር ነዳጅ በመጠቀም፣ ከፊሉን የሆስፒታሉን አገልግሎት ማንቀሳቀስ ተችሎ ቆይቷል ተብሏል።

4፤ የመቐለ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት፣ ባለፉት 11 ወራት በከተማዋ በ12 ሴቶች ላይ ግድያ እንደተፈጸመ መናገሩን የአገር ውስጥ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። በከተማዋ በተጠቀሰው ወር በሴቶች ላይ 80 የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች እንደተመዘገቡ እንዲኹም 10 እገታዎች እና 178 የግድያ ሙከራ ወንጀሎች እንደተፈጸሙ ፖሊስ መግለጡንም ዘገባዎቹ አመልክተዋል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ፣ በሴቶች ላይ ግድያ ከፉጸሙት መካከል ከአንዱ ግድያ በስተቀር በሌሎቹ ላይ ተጠርጣሪዎቹ እንደተያዙ ተናግሯል ተብሏል።

5፤ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ፣ ነገ በሚጀመረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ አገር ዓቀፍ ፈተና የክልሉ ተፈታኞች ቁጥር በግማሽ እንደሚቀንስ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ቢሮው በተያዘው ዓመት ከ200 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ለፈተናው እንደሚቀመጡ ታቅዶ እንደነበር ጠቅሶ፣ ለነገው ፈተና የሚቀመጡት ግን 96 ሺሕ ተማሪዎች ብቻ እንደኾኑ ገልጧል፡፡ ቀሪዎቹ 106 ሺሕ ያህል ተማሪዎች በቀጣዩ ዓመት መስከረም ለፈተናው  እንዲቀመጡ ታቅዷል ተብሏል። ለነገው ፈተና የሚቀመጡት ተማሪዎች ቁጥር በግማሽ የቀነሰው፣ በክልሉ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በሚካሄደው ግጭት ሳቢያ ነው።

6፤ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና የሱማሊያው አቻቸው ሐሰን ሞሃመድ የኹለቱን አገራት የኹለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከርና በጋራ ባሏቸው ጥቅሞች ዙሪያ ውይይት እንዳደረጉ የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገብረመስቀል በ"ኤክስ" ገጻቸው አስታውቀዋል። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ ኹለቱ አገሮች በወታደራዊ፣ በጸጥታ፣ በፖለቲካ፣ ባሕልና ማኅበራዊ ዘርፎች ትብብራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው እንዳሳሰቡ የማነ ገልጸዋል። ፕሬዝዳንት ሞሐመድ በበኩላቸው፣ ኤርትራ የሱማሊያን ጦር ሠራዊት መልሶ ለመገንባት እያደረገች ያለችውን ጥረት አድንቀዋል ተብሏል። በተደጋጋሚ በኤርትራ ኦፊሴላዊ ጉብኝት ያደረጉት ፕሬዝዳንት ሞሐመድ፣ ኤርትራ የምታሰለጥናቸውን የሱማሊያ ምልምል ወታደሮች ዛሬ ጧት ከጎበኙ በኋላ የኹለት ቀናት ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 57 ብር ከ3867 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 58 ብር ከ5344 ሳንቲም ኾኖ እንደዋለ በድረ ገጹ አስታውቋል። ባንኩ፣ የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ 70 ብር ከ2975 ሳንቲም እና መሸጫው 71 ብር ከ7035 ሳንቲም እንደኾነም አመልክቷል። በተመሳሳይ፣ አንድ ዩሮ በ62 ከ1383 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ63 ብር ከ3811 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ረቡዕ ሐምሌ 3/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ብሄራዊ ባንክ፣ በወለድ ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ መከተል መጀመሩን አስታውቋል። ባንኩ አዲሱን ፖሊሲ ያወጣው፣ በማክሮ ኢኮኖሚና በባንክ ዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደኾነ ገልጧል። ባንኩ፣ ለንግድ ባንኮች ብድር የሚሰጥበት የወለድ መጠንም 15 በመቶ እንዲኾን ወስኗል። ከተያዘው ሳምንት ጀምሮ፣ ከባንክ ገበያው ትርፍ ገንዘብ ለመሰብሰብ ወይም ተጨማሪ ገንዘብ ለመልቀቅ የሚያስችለውን ጨረታ በወር ኹለት ጊዜ እንደሚያወጣና ባንኮች ርስበርስ መበዳደር እንዲችሉ የኤሌክትሮኒክ የገንዘብ ግብይት እንደሚጀምርም ባንኩ ጨምሮ ገልጧል።

2፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ጠበቆች ማኅበርን ጨምሮ 205 ሲቪል ማኅበራት ሕጋዊ ሕልውናቸው አክትሞ እንደፈረሱ ማስታወቁን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል። የግሉ ዘርፍ የሐኪሞች ማኅበርና የማኅበረሰብ ሬድዮ ጣቢያዎች ማኅበርም ከፈረሱት መካከል እንደሚገኙበት መረዳቱን ዘገባው ጠቅሷል። ማኅበራቱ ለባለሥልጣኑ በተሰጠው አዋጅ መሠረት የፈረሱት፣ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የሥራ ክንውንና ኦዲት ሪፖርት ለባለሥልጣኑ ማቅረብ ባለመቻላቸው ነው። ባለሥልጣኑ፣ ሪፖርት ያላቀረቡ ማኅበራት ሕልውናቸውን እንዲያረጋግጡ ቀደም ሲል እስከ ሰኔ 30 ቀነ ገደብ ሰጥቷቸው ነበር።

3፤ ዛሬ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ አገር ዓቀፍ ፈተና ይጀምራል። የአገር ዓቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ድርጅት፣ ማጠናቀቂያ ፈተናው የሚሰጠው በወረቀትና በበይነ መረብ እንደኾነ ቀደም ሲል አስታውቋል። በትግራይ ክልል ግን አገር ዓቀፉ ፈተና የተጀመረው ትናንት ነው። ለዘንድሮው አገር ዓቀፍ ፈተና፣ በመላ አገሪቱ ከ700 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

4፤ ፐርፐዝ ብላክ ኩባንያ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ፕሮጀክቶቹን ማጠፍና ሠራተኞቹን መቀነስ መጀመሩን እንደገለጠ ካፒታል ጋዜጣ ዘግቧል። በግብርናው ዘርፍ መሠማራት ጀምሮ የነበረው ኩባንያው ይህን ርምጃ ለመውሰድ የተገደደው፣ ገንዘብ እንዳያንቀሳቅስ መንግሥት እገዳ ከጣለበት ወዲህ ነው። ኩባንያው አኹን ትኩረቱን በሪልስቴት ተገጣጣሚ ቤቶች ላይ እንደሚያደርግ ገልጧል ተብሏል። የኩባንያው ባለቤት ዶ/ር ፍስሃ እሸቱ፣ በመንግሥት ተጽዕኖ ከአገር ለመውጣት ተገድጃለኹ በማለት በቅርቡ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።

5፤ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ፖሊሲ ሃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ሰሞኑን በጎረቤት ጅቡቲ ጉብኝት አድርገዋል። ቦሬል፣ ጅቡቲ ቀጠናዊ የግጭት ፈቺነትና ሰላም የማስፈን ፖሊሲ ትከተላለች በማለት አድንቀዋል። ቦሬል፣ የውቅያኖስ ውሃ ለጅቡቲያዊያን ለመጠጥነትና ለሌሎች አገልግሎቶች እንዲውል የተጀመረውን ፕሮጀክት አውሮፓ ኅብረት በገንዘብ መደገፉን እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ ባኹኑ ወቅት ለ1/3ኛው የአገሪቱ ሕዝብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማቅረብ እንደሚችል የገለጡት ቦሬል፣ በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ግን 60 በመቶውን ሕዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ረቡዕ ሐምሌ 3/2016 ዓ፣ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፣ በትናንቱ አፍሪካ ኅብረት-መር የፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ግምገማ ላይ የፌደራል መንግሥቱና የሕወሓት ተወካዮች በፖለቲካዊ ውይይት፤ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት፣ በመበተንና ከኅብረተሰቡ ጋር መልሶ በማቀላቀል እንዲኹም ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው በመመለስ አስፈላጊነት ዙሪያ መምከራቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል። ስትራቴጂክ ግምገማው "በመግባባት መንፈስ" እንደተካሄደ የጠቀሱት ጌታቸው፣ ኹለቱ ወገኖች የሕዝቡን በተለይም የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮችን ጥያቄዎች በተሟላ መልኩ ለመፍታት ተፈናቃዮችን የመመለሱን ሂደት ማፋጠን እንደሚያስፈግ አስምረውበታል ብለዋል። ጌታቸው፣ በሱዳን የሚገኙ የትግራይ ስደተኞችን የመመለሱ ጉዳይ በግምገማው ላይ መነሳቱንም ጠቅሰዋል። ኹለቱ ወገኖች፣ በስምምነቱ አተገባበር ዙሪያ ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ገለጻ ማድረጋቸውን ጌታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

2፤ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ በሱዳን የሚካሄደው ጦርነት በምሥራቃዊ ሱዳን ግዛቶች በተጠለሉ ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን ስደተኞች ላይ ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከ40 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ያስጠለለችው ገዳሪፍ ግዛት አጎራባች በኾነችው ሴናር ግዛት በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ጥቃት እንደፈጸሙ የጠቀሰው ድርጅቱ፣ በተመሳሳይ በዚችው ግዛት አጎራባች በኾነችው ከሰላ ግዛት በርካታ ኤርትራዊያን ስደተኞች እንደሚገኙ ገልጧል። ድርጅቱ፣ የተወሰኑ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በጸጥታ ስጋት ገዳሪፍ ከሚገኙ መጠለያዎች እንደወጡ ጠቅሷል። ፈጥኖ ደራሹ ኃይል በተለይ የትግራይ ኃይሎች ከሱዳን ጦር ሠራዊት ጎን ተሰልፈው ተዋጋተዋል የሚል ውንጀላ ማሰማቱና የሱዳን መንግሥትም የተወሰኑ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን ገዳሪፍ ውስጥ አስሯል መባሉ ስጋቱን ይበልጥ አሳሳቢ እንዳደረገው ድርጅቱ አውስቷል። ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች በፍቃዳቸው እንዲመለሱ፣ የሱዳንና የኢትዮጵያ መንግሥታት እንዲሁም ዓለማቀፍ ድርጅቶች ትብብር እንዲያደርጉም ሂውማን ራይትስ ዎች ጠይቋል።

3፤ የተመድ የሕጻናት ድርጅት (ዩኒሴፍ)፣ በኢትዮጵያ ባኹኑ ወቅት 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንደኾኑ አዲስ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል። ድርጅቱ፣ 5 ሺህ 430 ትምህርት ቤቶች በድርቅና ግጭት ሳቢያ እንደተዘጉና 9 ሺሕ 178 ትምህርት ቤቶች በዋናነት በግጭቶች ሳቢያ እንደወደሙ ገልጧል። በአማራ ክልል 4 ሺህ 178 ትምህርት ቤቶች በግጭት ሳቢያ ባኹኑ ወቅት ተዘግተው እንደሚገኙ የገለጠው ድርጅቱ፣ በምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃምና ደቡብ ጎንደር ዞኖች 89 በመቶዎቹ ትምህርት ቤቶች ዝግ ናቸው ብሏል። በሌላ በኩል፣ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ለሕጻናትና እናቶች የነፍስ አድን ድጋፍ ለማድረግ ከያዘው 535 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ፣ እስካሁን ያገኘው የገንዘብ ልገሳ 32 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ወይም 12 በመቶውን ብቻ እንደኾነ ዩኒሴፍ ገልጧል። ,ድርጅቱ፣ በበርካታ ክልሎች ሕጻናት በምግብ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ እንደተጠቁ አስታውቋል።

4፤ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር፣ ከዛሬ ምሽት ጀምሮ ከአውሮፕላን ነዳጅ በስተቀር በኹሉም የነዳጅ ውጤቶች የችርቻሮ ዋጋ ላይ ጭማሪ አድርጓል። በአዲሱ የዋጋ ጭማሪ መሠረት፣ በአዲስ አበባ የሚኖረው የቤንዚን ዋጋ በሊትር 82 ብር ከ60 ሳንቲም የሚሸጥ ሲኾን፣ ነጭ ናፍጣ ደሞ 83 ብር ከ74 ሳንቲም እንዲሸጥ ተወስኗል። በተመሳሳይ፣ ኬሮሲን በሊትር 83 ብር ከ74 ሳንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ በሊትር 65 ብር ከ48 ሳንቲም እንዲኹም ከባድ ጥቁር ናፍጣ በሊትር 64 ብር ከ22 ሳንቲም ኾኗል።

5፤ ዛሬ በተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቅጥር ግቢ ውስጥ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ አገር ዓቀፍ ፈተና በወረቀትና በበይነ መረብ ለተፈታኞች ሲሰጥ ውሏል። በትግራይ ክልል ግን በቀድሞው ሥርዓተ-ትምህርት ለተማሩ በ2013 እና በ2014 የትምህርት ዘመን ፈተናውን መውሰድ የነበረባቸው ተፈታኞች፣ ፈተናውን መውሰድ የጀመሩት ትናንት ነው። ባጠቃላይ ዘንድሮ የ12,ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ አገር ዓቀፍ ፈተናውን የሚወስዱት ከ700 ሺሕ በላይ ተፈታኞች እንደኾኑ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ድርጅት አስታውቋል።

6፤ ኢትዮ-ቴሌኮም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 93 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ እና 21 ነጥብ 79 ቢሊዮን የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። 39 ነጥብ 4 በመቶው የኩባንያው ገቢ ከድምጽ አገልግሎት የተገኘ ሲኾን፣ 27 ነጥብ 7 በመቶው ደሞ ከኢንተርኔት አገልግሎቶች እንደተገኘ ኩባንያው ገልጧል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተገኘው ገቢ፣ ካለፈ በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ16 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወይም የ21 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ኩባንያው ጠቅሷል። ኩባንያው ይህን ገቢ ያገኘው፣ ከእቅዱ በላይ 103 ነጥብ 6 በመቶ በማሳካት ነው ተብሏል። የኩባንያው ደንበኞች ብዛት 78 ነጥብ 3 ሚሊዮን እንደደረሰና ካለፈው ዓመት በ8 ነጥብ 9 በመቶ እንደጨመረም ተገልጧል።

7፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 57 ብር ከ3919 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 58 ብር ከ5397 ሳንቲም ኾኖ እንደዋለ በድረ ገጹ አስታውቋል። ባንኩ፣ የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ 70 ብር ከ1394 ሳንቲም እና መሸጫው 71 ብር ከ5422 ሳንቲም እንደኾነም አመልክቷል። በተመሳሳይ፣ አንድ ዩሮ በ62 ከ0636 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ63 ብር ከ3049 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]