Wazema Media / Radio
48.9K subscribers
191 photos
36 videos
7 files
933 links
Wazema Radio other contents are available either in our website/social media or FM radio stations in Ethiopia. www.wazemaradio.com
Download Telegram
ለቸኮለ ማለዳ! ሐሙስ መስከረም 24/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የመንግሥት የጸጥታ ግብረ ኃይል በእሬቻ በዓል አከባበር ላይ "ግጭት ቀስቃሽ የኾኑ ጽሁፎችና መልዕክቶችን" መያዝ ክልል መኾኑንና ፍተሻም እንደሚኖር ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ፌዴራል ፖሊስ፣ "ጸረ ሰላም ኃይሎች" በበዓሉ አከባበር ላይ ጸጥታ ሊያደፈርሱ እንደሚችሉ "በልዩ ልዩ መረጃ" እና "ማስረጃ" ማረጋገጡን ገልጧል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ በበኩሉ፣ በዓሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ አብዛኛውን የሰው ኃይሉን በወንጀል መከላከል ሥራ ላይ ማሠማራቱን አስታውቋል።

2፤ በካርቱም የኢትዮጵያ ኢምባሲ የተፈጸመበትን የመሳሪያ ጥቃት አውግዟል። ኢምባሲው ጥቃቱ ዓለማቀፍ ሕጎችንና የቬይና ኮንቬንሽንን የሚጥስ መኾኑን ገልጦ፣ በጥቃቱ ግን በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ ጠቅሷል። የኢትዮጵያን መንግሥት ጥቃቱን የፈጸመውን ወገንና በጥቃቱ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለመለየት ምርመራ እንደሚያደርግና የምርመራውን ውጤት ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግም ኢምባሲው አስታውቋል።

3፤ በአፍሪካ ቀንድ የአውሮፓ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ አኒታ ዌበር በአውሮፓ ኅብረትና በኢትዮጵያ መካከል ላለው ግንኙነት "አዲስ መሠረት ተጥሏል" በማለት ተናግረዋል። ዌበር ይህን የተናገሩት፣ ትናንት ከውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ጋር በተነጋገሩበት ወቅት እንደኾነ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል። ዌበር አውሮፓ ኅብረት አኹንም ኢትዮጵያን በልማት መስክ መርዳት እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል ተብሏል። ደመቀ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኅብረቱ ጋር ያልተፈቱ አንዳንድ ጉዳዮችን በንግግር ለመፍታት ዝግጁ መኾኑን ለዌበር እንዳረጋገጡላቸው ተገልጧል።

4፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ የተሠራጨው መረጃ "ትክክለኛነት የሌለው" መኾኑን የከተማዋ አስተዳደር አስታውቋል። የከተማዋ አስተዳደር ነዋሪው ተጠራ የተባለው ሰልፍ "የከተማ አስተዳደሩ እውቅና የሌለው" እንደኾነ ገልጦ፣ የከተማዋ ነዋሪ መደበኛ እንቅስቃሴውን እንዲቀጥል አሳስቧል። ወልቂጤ ከተማ ጉራጌ ዞን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስር ተጠቃሎ አዲሱ ክልል እስከተመሠረተበት ቀን ድረስ ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፍ ሲደረግባት እንደነበር ይታወሳል።

5፤ ኬንያ አፍሪካ ኅብረት ቀደም ሲል ባስቀመጠው መርሃ ግብር መሠረት ወታደሮቿን ከሱማሊያ እንደምታስወጣ አስታውቃለች። ኬንያ ይህን ያለችው፣ በቅርቡ የተጀመረው የኅብረቱን ወታደሮች የማስወጣት ኹለተኛ ዙር በሦስት ወራት እንዲዘገይ ሱማሊያ ለተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ ነው። ኬንያ የሱማሊያን ጥያቄ ብትቀበልም፣ ከቀጣዩ ዓመት ታኅሳስ ወር በፊት ግን ወታደሮቿን ሙሉ በሙሉ ከአገሪቱ እንደምታስወጣ በድጋሚ አረጋግጣለች። ከኬንያ በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኡጋንዳና ቡሩንዲ የሱማሊያን ጥያቄ ደግፈዋል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሐሙስ መስከረም 24/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በዜጎች ላይ "ማንነትን መሠረት ያደረገ የጅምላ እስር" እና "በእስረኞች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት" አለ በሚል በደረሱት ጥቆማዎች መሠረት በሲዳማ ክልል ይርጋዓለም ከተማ በደቡብ ፓሊስ ማሠልጠኛ ተቋም ተገኝቶ ምልከታ ማድረጉን ገልጧል። መርማሪ ቦርዱ፣ የታሳሪዎችን ስም ዝርዝር፣ የሰብዓዊ አያያዝ ኹኔታ፣ የተጠርጣሪዎችን ብዛትና የተያዙበትን ምክንያት ለማጣራትና ከተጠርጣሪዎች ጋር ለመወያየት ወደ ቦታው ባቀናም፣ በቦታው ግን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ አማካኝነት በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች አላገኘኹም ብሏል። ኾኖም ከአንድ ወር በፊት በአዲስ አበባ ሊፈጠር ይችላል ከተባለ የጸጥታ ስጋት ሳቢያ፣ የወንጀል ስጋቶችን ለመከላከል ሲባል ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ግንኙነት በሌለው መንገድ ከከተማዋ ወደ ፖሊስ ማሠልጠኛ ጣቢያው የተወሰዱ ግለሰቦች እንደነበሩ ቦርዱ ጠቁሟል።

2፤ እናት ፓርቲ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አቤ ደንጎሮ ወረዳ ሎሚጫ በተባለ ቀበሌ የታጠቁ ኃይሎች ከማክሰኞ መስከረም 22 ከቀትር በኋላ ጀምሮ በነዋሪዎች ላይ ጥቃት ከፍተዋል ሲል ዛሬ ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ ከሷል። ፓርቲው፣ ጥቃቱን እያደረሱ የሚገኙት የታጠቁ ኃይሎች "የመከላከያ ሠራዊት ዩኒፎርም የለበሱ ናቸው" የሚል መረጃ እንደደረሰው ገልጧል። ፓርቲው፣ ጥቃቱ እስከ ዛሬው ዕለት ድረስ መቀጠሉን ከአካባቢው ነዋሪዎች ተረድቻለኹ ብሏል። መከላከያ ሠራዊት በጉዳዩ ላይ ማጣራት እንዲያደርግ የጠየቀው ፓርቲው፣ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ እየተፈጸመ ነው ያለው ጥቃት ባስቸኳይ እንዲቆም አሳስቧል።

3፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ ኢትዮጵያ የፕሪቶሪያውን የግጭት ማቆም ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንደምትተገብርና በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና መረጋጋት ቁልፍ ሚና መጫወቷን እንደምትቀጥል ለተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን አረጋግጠዋል። የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን አዲስ አበባ የገባው፣ በተመድና በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን መካከል ባለው ቅንጅትና ትብብር ዙሪያ ከኅብረቱ ጋር ለመምከር ነው። ደመቀ፣ የልዑካን ቡድኑ አባላት ላነሱላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ እንደሰጡ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል። የተመድ ጸጥታው ምክር ቤትን ከፍተኛ ልዑካን ቡድን የመሩት፣ የምክር ቤቱ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ሰርጊዮ ዳኔሳ ናቸው።

4፤ የአማራ ክልላዊ መንግሥት በድርቅ ለተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች የምግብ ዕርዳታ መግዣ የሚውል 430 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቋል። የክልሉ መንግሥት የምግብ ዕርዳታ ግዢ ለመፈጸም ያቀደው፣ በስምንት ዞኖች በ39 ቀበሌዎች በተከሰተው የዝናብ እጥረት ሳቢያ ለምግብ እጥረት ለተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው። የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ፣ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ወገኖች ዕርዳታ ለማቅረብ የክልሉ መንግሥት ግብረ ኃይል ማቋቋሙን መናገራቸውን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። በክልሉ የተፈጠረው ግጭት የምግብ ዕርዳታ በተለያዩ አካባቢዎች ለማጓጓዝ መሰናክል እንደኾነና፣ በዕርዳታ ቁሳቁሶች ላይ የዝርፊያ ሙከራዎች እየተደረገ መኾኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ተብሏል። የክልሉ መንግሥት ድርቁ ያደረሰውን ጉዳት ከለየ በኋላ፣ የምግብ ዕርዳታ ከሚያቀርቡ ረድዔት ድርጅቶች ድጋፍ እንደሚጠይቅ ተገልጧል። በክልሉ በዋናነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለድርቅና ድርቁ ላስከተለው ርሃብ የተጋለጡት በሰሜን ጎንደር ዞን አንዳንድ ወረዳዎችና በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ነው።

5፤ የናይጀሪያ የላይኛው ሕግ አውጪ ምክር ቤት ከ250 በላይ ናይጀሪያዊያን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደተገደሉ ወይም በእስር ላይ እንደሚገኙ መግለጡን የናይጀሪያው ኢንዲፔንደንት ጋዜጣ ዘግቧል። ኹለት የምክር ቤቱ አባላት "ሕገወጡ ግድያ" እና "እስራቱ" ባስቸኳይ እንዲጣራ የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ ማቅረባቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቡ፣ የምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይና የዲያስፖራ ኮሚቴ ከናይጀሪያ ፌደራል መንግሥት ጋር በመተባበር፣ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዞ በናይጀሪያዊያን ላይ ተፈጸመ የተባለውን "ሕገወጥ ግድያ" እና "እስራት" የሚያጣራ ኮሚቴ በአፋጣኝ እንዲያቋቁም ይጠይቃል ተብሏል። የናይጀሪያ መንግሥት በኢትዮጵያ እስር ቤቶች በሚገኙ ናይጀሪያዊያን ዙሪያ አቡጃ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ተባባሪ እንዲኾን እንዲጠይቅም ተጠይቋል። የኢትዮጵያ መንግሥትም ኾነ በአዲስ አበባ የናይጀሪያ ኢምባሲ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በጉዳዩ ዙሪያ ያሉት ነገር የለም። በአደገኛ ዕጽ ዝውውር፣ በሃሰተኛ ገንዘብ ሕትመትና ዝውውር እንዲኹም ሌሎች ወንጀሎች የተጠረጠሩ ናይጀሪያዊያን ቃሊት ማርሚያ ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ሲነገር ቆይቷል።

6፤ የእስራዔል ፖሊስ በአሽዶድ ከተማ ባንድ ኤርትራዊ ዜጋ ላይ "ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው" ግድያ ለመፈጸም ሲያሴሩ ደርሼባቸዋለኹ ያላቸውን ሦስት ኤርትራዊያን ማሠሩን የእስራኤል ጋዜጦች ዘግበዋል። ኤርትራዊያኑ የግድያ ሴራውን ሲያሴሩ የነበረው፣ በዋትሳፕ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ባደረጉት የመልዕክትና የምስል ልውውጥ እንደኾነ ፖሊስ መናገሩን ዘገባው ጠቅሷል። ባለፈው ቅዳሜ፣ በኔታኒያ ከተማ በኤርትራዊያን መካከል በተቀሰቀሰ የቡድን ግጭት፣ አንድ ኤርትራዊ ተገድሎ 11ዱ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸውና አራት ኤርትራዊያንም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ እንደታሠሩ በወቅቱ ተዘግቦ ነበር። በተመሳሳይ ቀን፣ ባንድ የውጭ ዜጋ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲሞክሩ ተይዘዋል የተባሉ 10 ኤርትራዊያን በቁጥጥር ስር መዋላቸው እንደተዘገበ ይታወሳል።

7፤ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ብሪታንያና ኖርዌይ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በሱዳኑ ጦርነት የሚፈጸሙ ጥሰቶችን ተከታትሎ ሪፖርት የሚያቀርብ የባለሙያዎች ቡድን እንዲያቋቁም ትናንት የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል። የአገራቱ የውሳኔ ሃሳብ፣ ምክር ቤቱ ሦስት አባላት የተካተቱበት የባለሙያዎች አጣሪ ቡድን እንዲቋቋም የሚጠይቅ ነው። በጄኔቫ የብሪታንያ ቋሚ መልዕክተኛ ሳይመን ማሊዝ፣ አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግና ግጭቱን ለማስቆም እውነታውን የሚያጣራ አንድ ገለልተኛ የተመድ አጣሪ አካል ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ለአሶሴትድ ፕሬስ ተናግረዋል። ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቡ በሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ገደማ ለምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ተገልጧል። ጀኔቫ ውስጥ ስብሰባ ላይ ለሚገኘው የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በጥሰቶችና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ለሚደረጉ ዓለማቀፍ ምርመራዎች ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ማቅረቢያው ቀነ ገደብ ትናንት መጠናቀቁ ይታወሳል።

8፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 55 ብር ከ2605 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 56 ብር ከ3657 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 63 ብር ከ9988 ሳንቲምና መሸጫው 65 ብር ከ2788 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ከ0622 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ2234 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ዓርብ መስከረም 25/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ፌደራል ፖሊስ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲና የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በአዲስ አበባ፣ ሸገር፣ ቢሾፍቱ፣ ሞጆ፣ አዳማ፣ ሀዋሳና ጅማ ከተሞች ከ73 በላይ የቴሌኮም ማጭበርበሪያ መሳሪያዎችንና 30 ተጠርጣሪዎችን "እጅ ከፍንጅ" መያዛቸውን ገልጸዋል። ለወንጀል የዋሉ ከ200 ሺህ በላይ የሳፋሪኮምና ኢትዮ ቴሌኮም ሲም ካርዶችም እንደተያዙ ተገልጧል። መሣሪያዎቹ በሕገወጥ መንገድ የገቡና ከውጭ ወደ የሚደወሉ ጥሪዎችን በሕገወጥ መንገድ ጠልፈው ለደንበኞች የሚያቀርቡ ነበሩ ተብሏል። በወንጀሉ ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ስድስት ወራት 500 ሚሊዮን ብር ገቢ እንዳጣ ተገልጧል። የተቋማቱ ግብረ ኃይል በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራውን ቀጥሏል ተብሏል።

2፤ የአሜሪካ ዓለማቀፍ ተራድዖ ድርጅት (ዩኤስአይዲ) በኢትዮጵያ አቋርጦት የነበረውን ዕርዳታ በ100 ሺዎች ለሚቆጠሩ ስደተኞች እንደገና ጀምሯል። ድርጅቱ፣ የዕርዳታ አቅርቦቱን የጀመረው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ራሱን ከዕርዳታ ሥርጭትና ክምችት ለማግለል መስማማቱን ተከትሎ እንደኾነ ተገልጧል። የኢትዮጵያ መንግሥት አኹንም የምግብ ዕርዳታ ለትክክለኞቹ ተረጂዎች እንዲደርስ ተጨማሪ ማሻሻያዎችን እንዲያደርግ ድርጅቱ መጠየቁን አሶሴትድ ፕሬስ ዘግቧል። ድርጅቱና የዓለም ምግብ ፕሮግራም የምግብ ዕርዳታ ዝርፊያ ተፈጽሟል በማለት የዕርዳታ ሥርጭት ያቋረጡት ባለፈው ዓመት ሰኔ ነበር።

3፤ አውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቱን ቀስ በቀስ የሚያሻሽለው በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የፍትህና ተጠያቂነት ቅድመ ኹኔታዎቹ ሲሟሉ ብቻ እንደኾነ ቃል አቀባዩ ነግረውኛል ሲል ሲኤንኤን ዘግቧል። የኅብረቱ ቃል አቀባይ፣ በኢትዮጵያ የዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽን ቆይታ ሊራዘም ያልቻለው፣ አውሮፓዊያን አገራት ተመሳሳይ አቋም ባለመያዛቸው እንደኾነም ገልጸዋል ብሏል። በኮሚሽኑ ቆይታ መራዘም ላይ የምክር ቤቱ አባላት የኾኑ የአፍሪካ አገራት ተቃውሞ ከጅምሩም በመባርታቱም፣ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ እንዳይቀርብ ምክንያት እንደኾነ በዘገባው ላይ ተገልጧል። መርማሪ ኮሚሽኑ ጥቅምት 2 በይፋ ይበተናል።

4፤ ተቃዋሚው የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ ምርጫ ቦርድ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በፓርቲው አባላት እስር ዙሪያ እስከ መስከረም 26 ድረስ ማብራሪያ እንዲሰጥ በደብዳቤ መጠየቁን መረዳቱን ገልጧል። ፓርቲው፣ ቦርዱ ጥያቄውን ያቀረበው፣ በአባሎቼ እስር ዙሪያ ያቀረብኩትን አቤቱታ መሠረት አድርጎ ነው ብሏል። ፓርቲው፣ የክልሉ መንግሥት ሦስት አባላቱን ከጥቂት ቀናት በፊት "በሕገወጥ መንገድ" እንዳሠረበት አስታውቆ ነበር።

5፤ የሱዳን ወታደራዊ መንግሥት የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አገሪቱ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶችንና ወንጀሎችን የሚያጣራ መርማሪ አካል ለማቋቋም ያቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ አድርጓል። ሱዳን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቡን ውድቅ ያደረገችው፣ የሱዳን ጦር ሠራዊትን የሚጎዳ እንደኾነና ባኹኑ ወቅት የሱዳን ተቀዳሚ ጥያቄ የጥሰት ምርመራ አለመኾኑን በመግለጽ ነው። ምክር ቤቱ ሦስት ባለሙያዎችን ያካተተ መርማሪ አካል እንዲያቋቁም የውሳኔ ሃሳቡን ያቀረቡት፣ አሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ ኖርዌይና ጀርመን ናቸው።

6፤ ፈረንሳይ ከተያዘው ሳምንት ጀምሮ ወታደሮቿን ከኒዠር ማስወጣት እንደምትጀምር አስታውቃለች። ፈረንሳይ ከቀድሞ ከኒዠር ወታደሮቿን ከወታደራዊ ጦር ሠፈሯ የምታስወጣው፣ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙት ወታደሮች በተደጋጋሚ ባደረጉባት ግፊት ነው። በቀድሞው ሲቪል መንግሥት የሥልጣን ዘመን የፈረንሳይ ወታደሮች እስላማዊ አክራሪ ኃይሎችን በመዋጋት ረገድ ለኒዠር እገዛ ያደርጉ ነበር። ፈረንሳይ 1 ሺህ 400 የሚገመቱትን ወታደሮቿን እስከ ታኅሳስ ጠቅልላ እንደምታስወጣ ቀደም ሲል መግለጧ ይታወሳል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ዓርብ መስከረም 25/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በከፍተኛ የወንጀል ድርጊቶች ላይ የተሠማሩ "ዓለማቀፍ የወንጀል ቡድን አባላት" ሲዳማ ክልል ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለዋል ብሏል። የወንጀል ቡድኑ አባላት "የአገር ደኅንነትንና ኢኮኖሚን በሚያቀጭጭ" ወንጀል ላይ የተሠማሩ ነበሩ ያለው ቢሮው፣ በቁጥጥር ስር የዋሉት የክልሉ ጸጥታ ግብረ ኃይል፣ መከላከያ ሠራዊትና ብሄራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባካሄዱት ክትትል እንደኾነ ገልጧል። የወንጀል ቡድኑ አባላት ከአልሻባብ፣ ከቦኮሃራም እና ከታጠቁ አማጺ ቡድኖች ጋር "ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር" እና "መረጃ በማቀበል" በተለያዩ አካባቢዎች ጥቃቶች እንዲፈጸሙ በመንቀሳቀስ ላይ ሳሉ "እጅ ከፍንጅ" እንደተያዙና ያቀዷቸውን ጥቃቶች ማክሸፍ እንደተቻለ ቢሮው ጨምሮ አስታውቋል። የተጠርጣሪዎቹ የሕግ ተጠያቂነትም በፌደራል ፍርድ ቤቶች ይታያል ተብሏል። ቢሮው፣ በቁጥጥር ስር የዋሉትን ተጠርጣሪዎች ብዛት፣ የተያዙባቸውን ቦታዎች እና መቼ እንደተያዙ ግን አላብራራም።

2፤ ንግድ ባንኮች በኦሮሚያ፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ከሚገኙ ቅርንጫፎቻቸው ጥሬ ገንዘብ ወደ ማዕከል ለመውሰድ መቸገራቸውን ዋዜማ ከምንጮቿ ተረድታለች። ባንኮቹ ገንዘቡን ለማጓጓዝ የተቸገሩት፣ ከጸጥታ ተቋማት በቂ ጥበቃ ባለማግኘታቸው እንደኾነ ምንጮች ገልጸዋል። በዚሁ ምክንያት ባንዳንድ የክልል ቅርንጫፎች ከ30 እስከ 40 ሚሊየን ብር ተከማችቶ ለረጅም ቀናት እንደቆየ የባንኮች ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል። ባንኮች የመንግሥት ጸጥታ ተቋማት ለምን የጸጥታ ጥበቃ ማድረግ እንዳልቻሉ ላቀረቡት ጥያቄ ግን ምላሽ እንዳላገኙ ምንጮች ጠቁመዋል። የአንዳንድ የባንክ ቅርንጫፎች ሥራ አስኪያጆችም ቀደም ሲል በየኹለት ቀኑ ከ2 እስከ 3 ሚሊዮን ብር ከማዕከሎቻቸው ይላክላቸው እንደነበር ጠቅሰው፣ ከቅርብ ወራት ወዲህ ግን ከ200 ሺህ የማይበልጥ ጥሬ ገንዘብ ብቻ እንደሚላክላቸው ተናግረዋል። ችግሩ፣ አዲስ አበባ በሚገኙ ባንኮች ዘንድ የጥሬ ገንዝብ እጥረት እንዲፈጠር አድርጓል ተብሏል።

3፤ ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሱሉልታ ከተማ ታጣቂዎች ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቀ በርካታ ሰዎችን በኃይል አግተው እንደወሰዱ ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። አጋቾቹ ታጣቂዎች የኦነግ ሸኔ ወይም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ሳይኾኑ እንደማይቀር ምንጮች ግምታቸውን ሰጥተዋል። የታጋቾች ቤተሰቦች ታጋቾችን በገንዘብ ለማስለቀቅ ከአጋቾች ጋር ድርድር እንደጀመሩም ተነግሯል።

4፤ የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሱማሌ፣ በአማራ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በትግራይ ክልሎች የምክክር ተሳታፊዎችን የመለየትና የማስወከል ሂደት ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መኾኑን አስታውቋል። በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የውክልና ሂደቱ ባልተጠናቀቀበት ደቡብ ኦሞ ዞን ሂደቱን የሚያጠናቅቁ ባለሙያዎች መላኩን ኮሚሽኑ ገልጧል። ኮሚሽኑ፣ በአፋርና ኦሮሚያ ክልሎች ተሳታፊዎችን በመለየት ሂደት አብረውት ለሚሠሩ አካላት ሥልጠና ለመስጠት መዘጋጀቱንም ጠቅሷል። ኮሚሽኑ የሥራ ክንውኑ በደረሰበት ደረጃ ዙሪያ ማክሰኞ'ለት ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር መወያየቱ ይታወሳል።

5፤ ዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የታክስ አስተዳደር ሥርዓተ ለማዘመን ድጋፍ ሊያደርግ መኾኑን ገቢዎች ሚንስቴር አስታውቋል። ገቢዎች ሚንስቴር እና የዓለም ባንክ ከፍተኛ አመራሮች የመንግሥትን የታክስ አስተዳደር ሥርዓት ለማዘመን በባንኩ ድጋፍ በሚተገበረው የፕሮጀክት ረቂቅ ሃሳብ ዙሪያ ትናንት መወያየታቸውን ሚንስቴሩ ገልጧል። ፕሮጀክቱ ሲተገበር፣ የአገሪቱን የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ጋር ያለውን ጥምርታ ለማሳደግ እንደሚያግዝና የታክስ ፓሊሲውን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ የማሻሻያ ሃሳቦችን ለማመንጨት እንደሚረዳ ተገልጧል። የገቢዎች ሚንስቴር እና የባንኩ ባለሙያዎች የፕሮጀክቱን ሃሳብ ለማዳበር በቅርቡ የተለያዩ ጥናቶችን ያካሂዳሉ ተብሏል።

6፤ ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ይፋዊ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ሰኞ መስከረም 28 ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ ምክር ቤቱ አስታውቋል። በዕለቱ፣ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ፌደሬሽን ምክር ቤት የዓመቱን ሥራ በይፋ መጀመራቸውን ካበሰሩ በኋላ፣ የፌደራል መንግሥቱን ዓመታዊ የሥራ ዕቅድ በጽሁፍ እንደሚያቀርቡ ተገልጧል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዓመታዊ ስብሰባውን በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት እንደሚጀምር በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል።

7፤ ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅት (ሲፒጄ) የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሠሩ ሦስት ጋዜጠኞችን "ባስቸኳይ እንዲፈቱ" ጠይቋል። ሲፒጄ፣ "የየኛ ቲቪ" በይነ መረብ ጣቢያ እና የምንሊክ ቴሌቪዥን አቅራቢና የፕሮግራም አዘጋጅ ቴዎድሮስ ዘርፉ በነሃሴ አጋማሽ እንደታሠረ መረዳቱን ገልጧል። ሲፒጄ፣ የ"የኛ ቲቪ" የፖለቲካ ተንታኝ ንጉሴ ብርሃኑም በተመሳሳይ ወር እንዲኹም የ"ትርታ" ኤፍ ኤም የፕሮግራም ዳይሬክተር የኋላሸት ዘሪሁን በጳጉሜ ወር መታሠራቸውን ከቤተሰቦቻቸው አረጋግጫለኹ ብሏል። ሦስቱ ጋዜጠኞች ከአዲስ አበባው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ከቆዩ በኋላ፣ አፋር ክልል ወደሚገኘው አዋሽ አርባ ወታደራዊ ማዕከል እንደተወሰዱ መረዳቱንም ሲፒጄ ጠቅሷል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋዜጠኞችን ማሠር "በእጅጉ እንደሚያሳስበው" የገለጠው ድርጅቱ፣ ጋዜጠኞቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ወይም ክስ ተመስርቶባቸው እንደኾነ ቤተሰቦቻቸውና ባልደረቦቻቸው ማወቅ እንዳልቻሉ አመልክቷል።

8፤ በእስራኤል የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ትናንት በቴላቪቭ ከተማ ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ የእስራኤል መንግሥት ቴላቪቭ የሚገኘውን የኤርትራ ኢምባሲ እንዲዘጋ ጠይቀዋል። ሰልፈኞቹ፣ የኤርትራ ኢምባሲ እንዲዘጋ የጠየቁት፣ በኤርትራዊያን መካከል ግጭት እንዲፈጠር ይሠራል በማለት እንደኾነ የእስራኤሉ ሐርቴዝ ጋዜጣ ዘግቧል። ሰልፈኞቹ፣ የእስራኤል ፖሊስ በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎችና በመንግሥት ተቃዋሚ ኤርትራዊያን መካከል በቅርቡ በተለይ በቴላቪቭ ከተማ የተፈጠሩ ግጭቶችን ለመቆጣጠር በቂ ጥረት አላደረገም በማለት ቅሬታቸውን እንዳሰሙም ዘገባው ጠቅሷል። ሰልፈኞቹ ባለፈው ሳምንት በቡድን ግጭት የተገደለውን የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚ ኃይሌ ማስፒን ፎቶ ይዘው ነበር ተብሏል።

9፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 55 ብር ከ2749 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 56 ብር ከ3804 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ1316 ሳንቲምና መሸጫው 65 ብር ከ4142 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ከ1602 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ3234 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። አንድ የቻይና ዩዋንም በ6 ብር ከ8507 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ6 ብር ከ9877 ሳንቲም እንደተሸጠ ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ቅዳሜ መስከረም 26/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ከተመድ ስደተኞች ኮሚሽንና ከስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ጋር ለስደተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎችና ተፈናቃዮች ዲጂታል መታወቂያ ለመስጠት መረጃዎችን የመጋራት ስምምነት ተፈራርሟል። ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ዲጂታል መታወቂያ ማግኘታቸው፣ የባንክ ሒሳብ መክፈትንና መንጃ ፍቃድ ማውጣትን ጨምሮ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ እንደሚያስችል የፕሮጀክቱ ሃላፊ ዮዳሄ ዘሚካዔል ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ በቀጣዮቹ ኹለት ዓመታት 90 ሚሊዮን ሰዎችን ለመመዝገብ ያቀደ ሲኾን፣ እስካኹን ሦስት ሚሊዮን ዜጎችን መዝግቧል።

2፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የኢትዮጵያ መንግሥት ያዘጋጀው የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ለሚንስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚጸድቅ አስታውቋል። የረቂቅ የሽግግር ፖሊሲው ዝግጅት ባኹኑ ወቅት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ሚንስቴሩ ገልጧል። መንግሥት ተዓማኒና አገራዊ በኾነ የሽግግር ፍትህ አማካኝነት "ተጠያቂነትን"፣ "እርቅን" እና "እውነትን ማፈላለግ" ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደኾነም ተገልጧል። ሚንስቴሩ ይህን ያለው፣ ዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽን የጊዜ ቆይታ ሳይራዘም መቅረቱ በታወቀ ማግስት ነው።

3፤ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አገረ ስብከት በቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን አባ ተክለዓብ እና ቀሲስ መሠረት "በአሰቃቂ ኹኔታ" እንደተገደሉ የቤተክርስቲያኗ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። መሪጌታ ፍሰሃ እና መርጌታ ተቅዋም የተባሉ አገልጋዮችም "ባልታወቁ ኃይሎች" ታፍነው ተወስደዋል ተብሏል። የአገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት፣ አኹንም መሰል ጥቃት ሊደገም ይችላል የሚል ስጋት እንዳለውና ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ጥብቅ ጥበቃ እንዲያደርግ እንደጠየቀ ተገልጧል።

4፤ ኬንያ ከቻይና 1 ቢሊዮን ዶላር አዲስ ብድር ለመበደርና የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲሸጋሸግላት ለመጠየቅ መወሰኗን አስታውቃለች። የፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ መንግሥት ብድሩን ለመጠየቅ የወሰነው፣ በገንዘብ እጥረት ላላለቁ መንገዶች ማጠናቀቂያ እንደኾነ የአገሪቱ ጋዜጦች ዘገበዋል። ፕሬዝዳንት ሩቶ ለዚኹ ዓላማ በተያዘው ወር መጨረሻ ወደ ቻይና ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል። ፕሬዝዳንት ሩቶ ለምርጫ ሲወዳደሩ፣ ኬንያ የውጭ ብድር መውሰድ እንድታቆም አደርጋለኹ በማለት ቃል ገብተው ነበር። ኬንያ ባኹኑ ወቅት 68 ቢሊዮን ዶላር ብድር አለባት።

5፤ ሩሲያ በቅርቡ ለአፍሪካ አገራት የምግብ እህል በነጻ እንደምትልክ አስታውቃለች። የአገሪቱ እርሻ ሚንስትር፣ በአንድ ወር ወይም በአንድ ወር ከግማሽ ጊዜ ውስጥ ነጻ እህል የጫኑ መርከቦች አፍሪካ ይደርሳሉ በማለት መናገራቸውን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ሩሲያ 25 እስከ 50 ሺህ ቶን ለሚገመት ነጻ የምግብ እህል ልገሳ የመረጠቻቸው አገራት፣ ኤርትራ፣ ሱማሊያ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ዚምባብዌ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክና ማሊ ናቸው። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ቅዳሜ መስከረም 26/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ በላኪነት የተሠማሩ የውጭ ኩባንያዎች ከወጪ ንግድ የሚያገኙትን ገቢ ሌሎች ሸቀጦችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እንዲያውሉት ለመፍቀድ ጥናት መጀመሩን ሪፖርተር ዘግቧል። ጥናቱን እያደረገ ያለው፣ ከንግድ ሚንስቴርና ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተውጣጣ ግብረ ኃይል እንደኾነና የጥናቱ ውጤት ለፖሊሲ አውጪዎች እንደሚቀርብ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን መስማቱን ዘገባው አመልክቷል። መንግሥት በጉዳዩ ላይ ጥናቱን የጀመረው፣ በርካታ ላኪ የውጭ ኩባንያዎች ኪሳራቸውን ለማካካስ ሌሎች ሸቀጦችን ከውጭ ለማስገባት እንዲፈቀድላቸው መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው። አኹን በሥራ ላይ ያለው ሕግ፣ በላኪነት የተሠማሩ የውጭ ኩባንያዎች በአስመጭነት ዘርፍ እንዳይሳተፉ ይከለክላል።

2፤ የዓለም ጤና ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ በኮሌራ በሽታ 300 ሰዎች ሞተዋል ሲል ትናንት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል። በሐምሌ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ብዛት 13 ሺህ 118 እንደነበር የጠቀሰው ድርጅቱ፣ ባኹኑ ወቅት ግን ቁጥሩ ወደ 24 ሺህ 197 ማሸቀቡን ድርጅቱ ገልጧል። በሽታውን በቁጥጥር ስር ማዋል በተቻለባቸው አንዳንድ ወረዳዎች እንደገና እያገረሸ መኾኑንም ድርጅቱ ጠቅሷል። በአገሪቱ የኮሌራ ወረርሽኝ በተለያዩ ክልሎች የተከሰተው ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ ሲኾን፣ እስካኹን በ10 ክልሎች በ113 ወረዳዎች ተሠራጭቷል።

3፤ ሱማሊያ አፍሪካ ኅብረት ወታደሮቹን የማስወጣቱ ሂደት በሦስት ወር እንዲዘገይላት ለተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ያቀረበችውን ጥያቄ የኅብረቱ ሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት አጽድቆታል። ሱማሊያ በሦስት ወር እንዲዘገይላት የጠየቀችው፣ ከሳምንት በፊት የተጀመረውና እስከ መስከረም መጨረሻ ሦስት ሺህ ወታደሮችን እንዲወጡ የታቀደበትን ኹለተኛውን ዙር ሂደት ነው። ኾኖም አፍሪካ ኅብረት ሱማሊያ ለጸጥታው ምክር ቤት ጥያውን ማቅረቧ በተሰማ ማግስት፣ ወታደሮቹን የማስወጫ መርሃ ግብሩን እንደማይቀይር ገልጦ ነበር። ሱማሊያ ጥያቄዋን ለኅብረቱ የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት በማቅረብ ፋንታ፣ ለተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ማቅረቧም በኅብረቱ ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩ በወቅቱ ተዘግቦ ነበር። ለኅብረቱ ወታደር ያዋጡት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ኡጋንዳና ቡሩንዲ የሱማሊያን ጥያቄ እንደደገፉት ቀደም ሲል ገልጸዋል።

4፤ በሱማሌላንድ ራስ ገዝ አወዛጋቢውን ሱል አውራጃ በውጊያ ከሱማሌላንድ ጦር አስለቅቀው የተቆጣጠሩት የጎሳ ታጣቂዎች ልዑካን ቡድናቸውን ወደ ሞቃዲሾ ልከዋል። የሱማሊያው ጠቅላይ ሚንስትር ሐምዛ ባሬ፣ የጎሳ ታጣቂዎቹን መሪ አብዲቃድር አሕመድ ዓሊን ዛሬ ሞቃዲሾ ውስጥ አነጋግረዋል። የአውራጃዋ የጎሳ ታጣቂዎች በሱማሌላንድ ወታደሮች ላይ በከፈቱት ውጊያ፣ የራስ ገዟ ወታደሮች ከአንድ ወር በፊት ከአውራጃዋ ዋና ከተማ ላስ አኖድና አካባቢዋ መልቀቃቸው ይታወሳል። የጎሳ ታጣቂዎቹ ውጊያውን የከፈቱት፣ ሱል አውራጃ በሱማሊያ ስር እንድትተዳደር እንፈልጋለን በማለት ነው። ሱማሌላንድ፣ የሱማሊያ ወታደሮችና የፑንትላንድ ራስ ገዝ ታጣቂዎች ከጎሳ ሚሊሻዎች ጋር ወግነው ወግተውኛል በማለት ትከሳለች።

5፤ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ትናንት ከካርቱም በስተምሥራቅ 30 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኝ አንድ የነዳጅ ማሠራጫ ማዕከል መቆጣጠሩን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ዘግቧል። "አል-አይላፉን" የተባለው የነዳጅ ማሠራጫ ማዕከል፣ ሱዳንና ጎረቤቷ ደቡብ ሱዳን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡት ነዳጅ የሚሠራጭበት ዋና ማዕከል ነው። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በጦርነቱ ምክንያት እስካኹን ነዳጅ ለውጭ ገበያ ማቅረባቸውን ያላቋረጡ ሲኾን፣ የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ተዋጊዎችም የነዳጅ ማሠራጫ ማዕከል ሲቆጣጠሩ የአኹኑ የመጀመሪያቸው ነው። የነዳጅ ማሠራጫ ጣቢያው ሥራ ካቆመ፣ በተለይ ደቡብ ሱዳን በፖርት ሱዳን ወደብ በኩል በምታስወጣው ነዳጅ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል። [ዋዜማ]
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፌዴራል እና የክልል ሕዝብ ተወካዮች በመረጣቸው ሕዝብ አመኔታ በሚያጡበት ጊዜ ውክልናቸው ስለሚሻርበት ሁኔታ መመሪያ ማርቀቁን ዋዜማ ተረድታለች፡፡

ቦርዱ ያረቀቀው መመሪያ ሕዝብ ይወክለኛል ብሎ በመረጠው የምክር ቤት አባል ላይ አመኔታ ባጣ ጊዜ፣ “የይውረድልኝ” ጥያቄ የሚያቀርብበትን ሁኔታና ውሳኔ የሚሰጥበትን ስርዓት ለመደንገግ ነው፡፡

መመሪያው የሕዝብ ተወካዮች ከመረጣቸው ሕዝብ የይውረድልም ጥያቄ ሲቀርብባቸው ቦርዱ በሚያካሂደው የይውረድልን ምርጫ ውጤቱ መሰረት የተሰጣቸው ውክልና እንዲነሳ ወይም እንዲጸና የሚያደርግ ነው፡፡ ዝርዝሩን ለማንበብ ሊንኩን ይከተሉ- https://wazemaradio.com/%e1%88%9d%e1%88%ad%e1%8c%ab-%e1%89%a6%e1%88%ad%e1%8b%b5-%e1%8b%a8%e1%88%95%e1%8b%9d%e1%89%a5-%e1%89%b0%e1%8b%88%e1%8a%ab%e1%8b%ae%e1%89%bd-%e1%8b%a8%e1%88%95%e1%8b%9d%e1%89%a5-%e1%8a%a0%e1%88%98/
ለቸኮለ ማለዳ! ሰኞ መስከረም 28/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ፌደሬሽን ምክር ቤት የ2016 ዓ፣ም የመጀመሪያውን የጋራ ስብሰባቸውን ዛሬ ከቀትር በኋላ ያካሂዳሉ። ፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ በኹለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ መክፈቻ ላይ የዓመቱን የመንግሥት ዕቅድ በጽሁፍ ያቀርባሉ። ኹለቱ ምክር ቤቶች ከክረምት እረፍት ሲመለሱ፣ በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት የአዲሱን ዓመት ሥራቸውን በይፋ እንደሚጀምሩ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል።

2፤ የውሃና ኢነርጂ ሚንስትር ሃብታሙ ኢታፋ መንግሥት በሕዳሴ ግድብ አቅራቢያ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ግድቡን ማዕከል ያደረገ አዲስ ከታማ ሊገነባ ማቀዱን ነግረውኛል ሲል ሪፖርተር ዘግቧል። ሚንስትሩ፣ የግድቡ ሰው ሠራሽ ሐይቅ አዲስ ለሚገነባው ከተማ የሃብት ምንጭ ይኾናል ተብሎ እንደታሰበ መግለጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ግድቡ የሚያመነጨው ኤሌክትሪክ ኃይል የአሳ ምርት ማቀነባበሪያዎችን ጨምሮ በአዲሱ ከተማ ለሚገነቡ አምራች ኢንዱስትሪዎች ግብዓት እንደሚኾን ሚንስትሩ ገልጸዋል ተብሏል። ሚንስትሩ፣ አዲስ በሚቋቋመው ከተማ "ማንኛውም ዜጋ" የመኖር መብት ይኖረዋል ማለታቸውም በዘገባው ተጠቅሷል።

3፤ ተቃዋሚው የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሲዳማ ክልላዊ መንግሥት ሕጋዊ እንቅስቃሴዎቹን "በሕገወጥ አካሄድ ለመግታት" የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም እንዲያደርግለት አቤቱታ ማቅረቡን አስታውቋል። ፓርቲው፣ ባኹኑ ወቅት 20 አመራሮቹና አባላቱ ታስረው እንደሚገኙም ገልጧል። የክልሉ ፖሊስ የፓርቲውን ሊቀመንበር ጨምሮ በ44 ያህል አባላቱ ላይ የወንጀል መጥሪያ ማውጣቱንም ፓርቲው ጠቅሷል። ፓርቲው፣ በአባላቱ ላይ የሚፈጸመውን እስራት አስመልክቶ ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ ማቅረቡንና ቦርዱም የክልሉ ፖሊስ ማብራሪያ እንዲሰጥ መጠየቁን ባለፈው ሳምንት ገልጦ ነበር።

4፤ የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐመድ በኤርትራ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ አሥመራ ገብተዋል። ፕሬዝዳንቱ በአሥመራ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተገናኝተው፣ በኹለትዮሽ፣ በጋራ ጥቅሞችና በቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገ/መስቀል በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሰኞ መስከረም 28/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ኢዜማ ሊቀመንበሩ ጫኔ ከበደ
ወደ አዋሽ አርባ እንደተወሰዱ ከቤተሰባቸው መረዳቱን ዛሬ አስታውቋል። ፌደራል ፖሊስ ተጠርጣሪውን ዛሬ በአካል ችሎት እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት በድጋሚ የሰጠውን ትዕዛዝ ሳያከብር መቅረቱንና ፍርድ ቤቱም ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለመስከረም 30 በአካል እንዲያቀርብ በድጋሚ ማዘዙን ፓርቲው ገልጧል። ከተጠርጣሪው ቤተሰቦች ጋር በመመካከር በተመሠረተው "አካልን ነጻ የማውጣት" ክስ፣ ፖሊስ ተጠርጣሪውን መስከረም 24 ችሎት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቶት እንደነበር ፓርቲው ጠቅሷል። ኾኖም ፖሊስ ተጠርጣሪውን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዳሠራቸውና እንደማይፈታቸው በጽሁፍ ለፍርድ ቤቱ ምላሽ ሰጥቶ እንደነበርም ፓርቲው አመልክቷል።

2፤ ምርጫ ቦርድ የፌደራልና የክልል የሕዝብ ተወካዮች በመረጣቸው ሕዝብ አመኔታ በሚያጡበት ጊዜ ውክልናቸው ስለሚሻርበት አግባብ መመሪያ ማዘጋጀቱን ዋዜማ ተረድታለች። መመሪያው፣ የሕዝብ ተወካዮች የመረጣቸው ሕዝብ የ"ይውረዱን" ጥያቄ ሲያቀርብባቸው ቦርዱ በሚያካሂደው የ"ይውረዱልን" ምርጫ ውጤት መሠረት የተሰጣቸው ውክልና እንዲነሳ ወይም እንዲጸድቅ የሚያደርግ ነው። የይውረድልን ጥያቄ በተነሳበት የሕዝብ ተወካይ ምርጫ ክልል የሚገኙ መራጮች ያቀረቡት "የይውረድልን" ጥያቄ በቦርዱ ተቀባይነት ካገኘ፣ መራጩ ሕዝብ ወሳኔ እንዲሰጥ የ"ይውረድልን" ምርጫ እንደሚካሄድ መመሪያው ያዛል። በምርጫው ኹለት ሦስተኛው ድምጽ ሰጪ ተወካዩ መነሳት አለበት የሚለውን ከደገፈ፣ የምክር ቤት አባሉ ከቦርዱ ተሰጥቶት የነበረው የተመራጭነት መታወቂያ ይመክናል። ቦርዱ ባዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ላይ በመጭው ረቡዕ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርግበት ዋዜማ ተረድታለች።

3፤ ትምህርት ሚንስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በ2015 ዓ፣ም ብሄራዊ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 845 ሺህ ገደማ ተፈታኞች መካከል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ነጥብ ያስመዘገቡት 27 ሺህ 267 እንደኾኑ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። 50 በመቶና ከዚያ በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ነጥብ ያገኙት ተፈታኞች ከጠቅላላዎቹ ተፈታኞች 3 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ መኾናቸውን ሚንስትሩ ገልጸዋል። አገር ዓቀፍ ፈተናውን ካስፈተኑት 3 ሺህ 106 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1 ሺህ 328 በሚሆኑት አንድም ተማሪ የማለፊያ ነጥብ አለማምጣቱን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል። አምስት ትምህርት ቤቶች፣ ያስፈተኗቸው ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ እንዳለፉላቸው የገለጡት ሚንስትሩ፣ ሌሎች አምስት ትምህርት ቤቶች ደሞ ካስፈተኗቸው ተማሪዎች 94 ነጥብ 5 የሚሆኑትን ማሳለፋቸውን ጠቅሰዋል። ሚንስትሩ፣ ዘንድሮም እንደ አምናው ኹሉ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለፉ ተማሪዎች ውስን በመኾናቸው የማካካሻ መርሃ ግብር እንደሚኖር አስታውቀዋል። የማካካሻ ትምህርት ላንድ ዓመት ብቻ እንደሚሰጥ ሚንስትሩ አምና ገልጠው የነበረ ሲኾን፣ ኾኖም ዘንድሮም የሚደገም በመኾኑ ይቅርታ እጠይቃለኹ ብለዋል።

4፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ፌደሬሽን ምክር ቤት የ2016 ዓ፣ም የመጀመሪያውን የጋራ ስብሰባቸውን ዛሬ አካሂደዋል። ፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ በምክር ቤቶቹ የጋራ ስብሰባ መክፈቻ ላይ የዓመቱን የመንግሥት ዕቅድ በጽሁፍ አቅርበዋል። ፕሬዝዳንቷ፣ መንግሥት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የዳቦ ማምረቻዎችን፣ የምገባ ማዕከላትንና የዕሁድ ገበያዎችን በማስፋፋት እንዲኹም የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ጠቁመዋል። አገራዊ ምክክሩ ሊያመልጥ የማይገባ ዕድል መኾኑን የገለጡት ፕሬዝዳንቷ፣ 'በኃይል ፍላጎትን ማስፈጸም በዘላቂነት አገር እንደማያስቀጥልና የመንግሥትን ሥልጣን በኃይል ለመንጠቅ" የሚደረጉ ሙከራዎችንም መንግሥት እንደማይታገስ ገልጸዋል። ፕሬዝዳንቷ፣ የትላንት ታሪክ የአብሮነት መገንቢያ እንጂ የልዩነት መነሻ ሊኾን እንደማይገባ በመጥቀስ፣ ለዘንድሮ የታሰበው አገራዊ ምክክር እገሪቱን እንዳያመልጣት አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል።

5፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለማቀፉ የፍልሰት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አሚ ፖፕ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ይፋዊ የራ ጉብኝታቸውን ለማድረግ ትናንት አዲስ አበባ ገብተዋል። አሚ ፖፕ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ኾነው የተሾሙት ከሳምንት በፊት ነበር። ዋና ዳይሬክተሯ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፣ በፍልሰት ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትና ከአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር ለመወያየት ነው። አሚ ፖፕ ከጉብኝታቸው በፊት፣ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን ጨምሮ ወደ ባሕረ ሰላጤው አገራት የሚገቡ ፍልሰተኞች ከፍተኛ ሰቆቃ እየተጋለጡ መኾኑን ባንድ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ተናግረው ነበር።

6፤ ባለፈው ቅዳሜ በእስራኤልና በፍልስጤማዊያን ታጣቂዎች መካከል እስራዔል ውስጥ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ዛሬ የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ባለፈው ሳምንት ከነበረበት ዋጋ ከአራት በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል። በዋጋ ጭማሪው መሠረት፣ የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በዓለም ገበያ በአማካይ ከ88 ዶላር በላይ መድረሱን ዓለማቀፍ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። በእስራኤል ጦርና በፍልስጤም ታጣቂዎች መካከል የተፈጠረው ጦርነት በቶሎ ካልቆመ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን የነዳጅ አቅርቦት ሊያስተጓጉለውና ዋጋውን ይበልጥ ሊያንረው ይችላል የሚል ስጋት ከአኹኑ አንዣቧል።

7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 55 ብር ከ2931 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 56 ብር ከ3990 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ0840 ሳንቲምና መሸጫው 65 ብር ከ3657 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ከ0522 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ2132 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ማክሰኞ መስከረም 29/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የአማራ ክልላዊ መንግሥት በክልሉ በተከሰተው ግጭት ሳቢያ ከሐምሌ ወዲህ 1 ሺህ 226 በላይ ኢንዱስትሪዎች ሥራ እንዳቆሙ አስታውቋል። አብዛኞቹ ኢንዱስትሪዎች ሥራ ያቆሙት፣ በሰሜን ሸዋ ዞን እና በምዕራባዊው የክልሉ አካባቢዎች እንደኾነ የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ መናገሩን ዶይቸቨለ ዘግቧል። በፋብሪካዎች መዘጋት ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ከሥራ ውጭ መኾናቸውንም ቢሮው ገልጧል ተብሏል። ምርት ባላቆሙ ፋብሪካዎች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና የመንገዶች መዘጋት ችግር እንደፈጠረም የክልሉ መንግሥት ሰሞኑን አስታውቆ ነበር።

2፤ በኤርትራ ይፋዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሐመድ በኤርትራ ሥልጠና በመውሰድ ላይ የሚገኙትን የአገራቸውን ወታደሮች እንደጎበኙ የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገ/መስቀል በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል። ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር በመኾን የጎበኟቸው ሠልጣኞች፣ ሜካናይዝድ ወታደሮች፣ ልዩ ኮማንዶዎችና የባሕርና አየር ኃይል ምልምሎች እንደኾኑ የማነ ጠቅሰዋል። ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ለጉብኝት አሥመራ የገቡት ዕሁድ'ለት ነበር።

3፤ የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአገሪቱ መንግሥት በሐይቲ ጸጥታ ለማስከበር የፖሊስ ኃይሉን ለማሠማራት ያሳለፈውን ውሳኔ ለጊዜው አግዷል። የፍርድ ቤቱ ጊዜያዊው እገዳ፣ የአገሪቱ መንግሥት በሐይቲ ብቻ ሳይኾን በየትኛው የውጭ አገር ፖሊሶችን ወይም ወታደሮችን እንዳያሠማራ ያግዳል። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው፣ ከኬንያዊያን የቀረበለትን አቤቱታ መሠረት አድርጎ ነው። ኬንያ የተደራጁ ታጣቂ ቡድኖች በተኩስ በሚንጧት ሐይቲ 1 ሺህ ፖሊሶቿን በማሠማራትና ዓለማቀፍ ጸጥታ አስከባሪ ኃይል በበላይነት በመምራት፣ በአገሪቱ ሕግና ሥርዓት ለማስከበር እንደምትፈልግ ቀደም ሲል ገልጣ ነበር። የተመድ ጸጥታው ምክር ቤትም፣ ለኬንያ ጥያቄ ይኹንታውን መስጠቱ ይታወሳል።

4፤ ሱዳንና ኢራን ለሰባት ዓመታት ያቋረጡትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደገና መጀመራቸውንና በቅርቡም አንዳቸው በሌላኛቸው ኢምባሲዎቻቸውን እንደሚከፍቱ አስታውቀዋል። ሱዳን ከኢራን ጋር ግንኙነቷን ያቋረጠችው፣ ቴህራን ውስጥ ኢራናዊያን ሰልፈኞች በሳዑዲ ዓረቢያ ኢምባሲ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ ነበር። ሳዑዲ ዓረቢያና ኢራን በቻይና አደራዳሪነት፣ በቅርቡ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር መስማማታቸው ይታወሳል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ማክሰኞ መስከረም 29/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ለሚገኙ 900 ሺህ ገደማ ስደተኞች የምግብ ዕርዳታ አቅርቦት ጀምሬያለኹ ብሏል። ድርጅቱ፣ በኢትዮጵያ በምግብ ዕርዳታ ላይ "መጠነ ሰፊ" ዝርፊያ ተፈጽሟል በማለት ባለፈው ሰኔ ወር የምግብ ዕርዳታ ካቋረጠ ወዲህ ስደተኞች ዕርዳታ ሲያገኙ የመጀመሪያቸው መኾኑን ገልጧል። የስደተኞች የምግብ ዋስትና ማሽቆልቆሉን፣ ስደተኞች ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት መዳረጋቸውንና በመጠለያዎቹ አከባቢ ከፍተኛ ውጥረት መስፈኑን የገለጠው ድርጅቱ፣ የምግብ ዕርዳታ ሥርጭቱ በሰባት ክልሎች በሚገኙ መጠለያዎች ይካሄዳል ብሏል። ድርጅቱ፣ በስደተኛ መጠለያዎች 24 መጋዘኖችን እያስተዳደረ እንደሚገኝና የተረጂዎችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ በተመድ ስደተኞች ኮሚሽን አማካኝነት የዲጂታል ምዝገባ እንደሚከናወን አውስቷል።

2፤ የፋይናንስ ሚንስትር አህመድ ሽዴ እና የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የመሩት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በሞሮኮ በዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅትና ዓለም ባንክ የጋራ ጉባዔ ላይ ተገኝቷል። ልዑካን ቡድኑ፣ ዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር በሚደግፍበት ኹኔታ ዙሪያ ከተቋሙ ኃላፊ ጋር ተወያይቷል። የዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ክርስታሊና ጆርጂቫ፣ ልዑካን ቡድኑ "የኢትዮጵያን አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ለማስቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት አደንቃለኹ" በማለት በ"ኤክስ" (በቀድሞው ትዊተር) ገጻቸው ላይ ባሠፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

3፤ በትግራይ ክልል አገር ዓቀፉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ብሄራዊ ፈተና ዛሬ ተጀምሯል። ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት ለሚቆየው ፈተና የተቀመጡት፣ በ2012 ዓ፣ም ፈተናውን ያልወሰዱ ተፈታኞች እንደኾኑ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገልጧል፡ ለፈተናው በጠቅላላው 9 ሺህ 514 ተፈታኞች የተቀመጡ ሲኾኑ፣ 6 ሺህ 513ቱ የተፈጥሮ ሳይንስ እንዲኹም 3 ሺህ ያህሉ የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች እንደኾኑ ቢሮው አመልክቷል። ፈተናው እየተሰጠ የሚገኘው፣ በመቀሌ፣ አክሱም፣ አዲግራት እና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ነው።

4፤ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ትናንት ይፋ በተደረገው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ አገር ዓቀፍ የፈተና ውጤት ላይ ቅሬታ ያላቸው ተፈታኞች ቅሬታቸውን እስከ ጥቅምት 5 ከቀኑ 11 ሰዓት ተኩል ድረስ ብቻ እንዲያቀርቡ አሳስቧል። ተፈታኞች ቅሬታ ለማቅረብ በአካል መቅረብ ሳያስፈልጋቸው፣ በተቋሙ ድረገጽ አማካኝነት ብቻ ማቅረብ እንደሚችሉ ተቋሙ ገልጧል። ትምህርት ሚንስቴር፣ ብሄራዊ ፈተናውን ከወሰዱ 845 ሺህ ገደማ ተማሪዎች መካከል 96 ነጥብ 8 በመቶዎቹ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ የተቀመጠውን ነጥብ ማምጣት እንዳልቻሉ ትናንት መግለጡ ይታወሳል።

5፤ የተመድ ፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) የኢትዮጵያዊያ መንግሥት ተመላሽ ፍልሰተኞችን፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችንና የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ለማቋቋም ለሚደረገው ጥረት የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ ለማድህግ ከሰላም ሚንስቴር ጋር የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም ተስማምቷል። ይህ የተገለጠው፣ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አሚ ፖፕ ዛሬ ከሰላም ሚንስትር ብናልፍ አንዷለም ጋር አዲስ አበባ ውስጥ በተወያዩበት ወቅት ነው። ዋና ዳይሬክተሯ፣ ከፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ጋር ጭምር በፍልሰትና ፍልሰተኞች ዙሪያ ዛሬ በአካል ተነጋግረዋል።

6፤ ፌደሬሽን ምክር ቤት ብሔራዊ የወጣቶች የዜግነት አገልግሎት ረቂቅ አዋጅን ዛሬ በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶታል። ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመራው፣ አዋጁ አገራዊ አንድነትንና ብሄራዊ መግባባትን ለማምጣት ይጠቅማል በሚል እምነት እንደኾነ ገልጧል። ረቂቅ አዋጁ፣ ወጣቶች በተለያዩ ብሄራዊ የዜግነት አገልግሎቶች እንዲሳተፉ የሚያስችል ነው። ፌደሬሽን ምክር ቤት ረቂቅ አዋጁን ከማጽደቁ በፊት፣ የወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚንስትር እርጎዬ ተስፋዬ በአዋጁ ዓላማና አስፈላጊነት ዙሪያ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

7፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በሞተር ብስክሌት፣ በባለ አራት እግርና ባለሦስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች ላይ የጣለውን የምሽት እንቅስቃሴ ገደብ ከዛሬ ጀምሮ አንስቷል። የመንቀሳቀስ ፍቃድ ተግባራዊ የሚኾነው ግን፣ እውቅና አግኝተው በማኅበር ለተደራጁና መስመርና ታፔላ ላላቸው ባጃጆች እንዲኹም ሰሌዳ ወስደው ሕጋዊ የመንቀሳቀሻ ፍቃድና ጂፒኤስ ላስገጠሙ የሞተር ሳይክሎች ብቻ እንደኾነ ቢሮው ገልጧል። ቢሮው፣ ከሕጋዊ እውቅናው ውጪ በሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ ርምጃ እወስዳለኹ በማለት አስጠንቅቋል። ቢሮው፣ በተሽከርካሪዎቹ እንቅስቃሴ ላይ ምክንያቱን ሳይገልጥ እገዳ የጣለው መስከረም 14 ቀን ነበር።

8፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 55 ብር ከ3042 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 56 ብር ከ4103 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ2501 ሳንቲምና መሸጫው 65 ብር ከ5351 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ከ2243 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ3888 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ረቡዕ መስከረም 30/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የተመድ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪ አሊስ ዋይሙሩ በኢትዮጵያ አኹንም የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸም የሚያስችሉ ኹኔታዎች አሉ ሲሉ አዲስ ባወጡት መግለጫ አስጠንቅቀዋል። በአገሪቱ "የቤተሰብ አባላት በሙሉ የሚገደሉበት" ኹኔታ እንዳለ የገለጡት ሃላፊዋ፣ ትግራይና አማራ ክልሎችን ጨምሮ ከአገሪቱ የሚወጡ የጥሰት ሪፖርቶች "እጅግ የሚረብሹ ናቸው" ብለዋል። በአገሪቱ የዘር ማጥፋት ወንጀልና ሌሎች ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ከአኹኑ መከላከል እንደሚያስፈልግም ሃላፊዋ አሳስበዋል። ሃላፊዋ፣ በአማራ ክልል ውስጥ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ጥሰቶች ባስቸኳይ እንዲቆሙም ጠይቀዋል።

2፤ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በአማራና አፋር ክልሎች "ከአጣዳፊ ኹኔታዎች" ያለፈ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መከሰቱን አዲስ ባወጣው ሪፖርት ገልጧል። በአማራ ክልል ሰሜንና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች፣ ዋግኽምራ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖችና የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ድርቅ መከሰቱን ቢሮው ገልጧል። በድርቁና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች፣ በአማራ ክልል የሕጻናት ያልተመጣጠነ የምግብ ጉዳት መጠን 21 በመቶ እንዲኹም የነፍሰጡር እናቶች ከ54 በመቶ በላይ መድረሱን ቢሮው ጠቅሷል።

3፤ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በኮሌራ የተያዙ ሰዎች አኹንም በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች እየተመዘገቡ መኾኑን አስታውቋል። በአማራ ክልል ኮሌራ በተስፋፋበት መተማ ወረዳ፣ በመስከረም መጨረሻ በመተማ የስደተኞች መግቢያ ጣቢያ አምስት እንዲኹም በኩመር የስደተኞች መጠለያ ስምንት ሰዎች በበሽታው እንደሞቱ ቢሮው ባወጣው ሪፖርት ጠቅሷል። ቢሮው፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኘው ኩርሙክ የስደተኞች መጠለያ 500 ሱዳናዊያን ስደተኞች እንዲኹም ከመተማ ቁጥራቸው ያልታወቀ ስደተኞች በቅርቡ ወደ ሱዳን መመለሳቸውንም ቢሮው አመልክቷል።

4፤ የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ
የአዳዲስ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባላትን ምርጫ ትናንት ተካሂዷል። ከአፍሪካ አሕጉር፣ ማላዊ፣ ኮትዲቯር፣ ቡሩንዲ እና ጋና ለቀጣዮቹ ኹለት ዓመታት የምክር ቤት አባል ኾነው ተመርጠዋል። ባለፈው ዓመት ከምክር ቤቱ የታገደችው ሩሲያ እስያ አሕጉርን ወክላ ብትወዳደርም፣ በቡልጋሪያና አልባኒያ በድምጽ ብልጫ ተሸንፋለች። ሩሲያ፣ ምክር ቤቱን እንዳልቀላቀል አሜሪካ የተቀናጀ ዘመቻ አድርጋብኛለች በማለት ከሳለች።

5፤ ፈረንሳይ ወታደሮቿን ትናንት ከኒጀር ጠቅልላ ማስወጣት ጀምራለች። ፈረንሳይ ወታደሮቿን ማስወጣት የጀመረችው፣ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን በያዘው የኒጀር ወታደራዊ ቡድን ትዕዛዝ ነው። ፈረንሳይ በቀድሞ ቅኝ ግዛቷ ኒጀር 1 ሺህ 500 ወታደሮች ነበሯት። ፈረንሳይ፣ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከተደረገባቸው ማሊ እና ቡርኪናፋሶ ቀደም ሲል ወታደሮቿ በግዳጅ አስወጥታለች። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ሐሙስ ጥቅምት 1/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዕዝ በባሕርዳር በጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ ከምሽቱ 12:00 ሰዓት እንዲጀምር ማዘዙን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች። ቀደም ሲል የነበረው የሰዓት እላፊ ገደብ፣ ከምሽቱ 2:00 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት የሚቆይ ነበር። በሰዓት ገደቡ ላይ ተደረገ የተባለውን ማሻሻያ፣ ማዕከላዊ ዕዙ በይፋ አላረጋገጠም። በሰዓት እላፊ ገደቡ ላይ ለምን ለውጥ እንደተደረገ ምንጮች አልገለጡም። ኾኖም ገዥው ብልጽግና ፓርቲ፣ በከተማዋ የከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ሥልጠና ማክሰኞ'ለት መጀመሩን ገልጾ ነበር።

2፤ በባሕርዳር ከተማ ሰባታሚት በተባለ አካባቢ ከማክሰኞ ጀምሮ በመንግሥት ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እንደተፈጠረ ዋዜማ ሰምታለች። በግጭቱ በሰው ሕይወት ላይ ስለደረሰው ጉዳት ግን ዋዜማ ማረጋገጥ አልቻለችም። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በባሕርዳር፣ ፍኖተሰላም፣ ደንበጫና ደብረ ማርቆስ ከተምች ከትናንት ጀምሮ የስልክ አገልግሎት በድጋሚ እንደተቋረጠ ታውቋል። በከተሞቹ የስልክ አገልግሎቱ እንደገና የተቋረጠው፣ ባንዳንድ አካባቢዎች ግጭት ማገርሸቱን ተከትሎ እንደኾነ ተሰምቷል።

3፤ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ቅበት ከተማ በቅርቡ ለተፈጠረው ግጭት መፍትሄ የሚያፈላልግ ቡድን ትናንት ወደ ሥፍራው ልኳል። የቡድኑ አባላት፣ በቅበት ከተማ የግጭቱ ተጎጂዎችንና በጉራጌ ዞን ቡታጅራ ከተማ የተጠለሉ የግጭቱ ተፈናቃዮችን በአካል ተዘዋውሮ አነጋግሯል። ቡድኑ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ፣ ለተፈናቃዮቹ የደኅንነት ዋስትና እንዲሰጣቸውና ጥፋት የፈጸሙ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ መጠየቁ ተሰምቷል። በቅበት ከተማ ሃይማኖታዊ ገጽታ ያለው ግጭት የተፈጠረው፣ ሙስሊም ተማሪዎች በትምህርት ደካማ የኾኑት የክርስትና እምነት ተከታይ ተማሪዎች "መተት" ስለደረጉባቸው ነው በሚል ምክንያት እንደኾነ በወቅቱ ተነግሯል።

4፤ የቀድሞው ደቡብ ክልል የመንግሥት ሠራተኞች ያነሷቸውን ቅሬታዎች ለመፍታት የተቌቋመው ኮሚቴ አቤቱታቸውን እንዳልፈታላቸው ቅሬታ አቅራቢዎች ተናግረዋል። የሠራተኞች ድልድል ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ፣ በጠቅላላው ከኹለት ሺህ በላይ ቅሬታዎችን ስለመቀበሉ መናገሩን ቪኦኤ ዘግቧል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ ግን፣ ለቅሬታቸው ምላሽ ያገኙት ሠራተኞች ከ120 እንደማይበልጡ ገልጸዋል ተብሏል። የክልሉ መንግሥት የቀድሞ ሠራተኞች በቅርቡ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ሲዳማ ክልሎች ተደልድለዋል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ አዲሱ ድልድል ቅጽ ላይ የሞሉትን ምርጫቸውንና የቤተሰባቸውን ኹኔታ ግምት ውስጥ ያላስገባ የዘፈቀደ ድልድል እንደኾነ ሲገልጡ ቆይተዋል።

5፤ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በሱዳኑ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶችን የሚያጣራ ዓለማቀፍ አጣሪ ቡድን ትናንት በድምጽ ብልጫ አቋቁሟል። አጣሪ ቡድኑ የተቋቋመው፣ በ19 ድጋፍ፣ በ16 ተቃውሞና በ12 ድምጸ ተዓቅቦ ነው። አጣሪ ቡድኑን የማቋቋሙ የውሳኔ ሃሳብ በድምጽ ያለፈው፣ ሱማሊያና ቻይና ሃሳቡን በመቃወማቸው ነው። አጣሪ ቡድኑ እንዲቋቋም የውሳኔ ሃሳብ ያቀረቡት፣ አሜሪካ፣ ብሪታንያና ኖርዌይ ነበሩ። የሱዳን መንግሥት ዓለማቀፍ የጥሰት አጣሪ ቡድን የማቋቋሙን ሃሳብን እንደማይቀበል ባለፈው ስምንት አስታውቆ ነበር። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ሐሙስ ጥቅምት 1/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን ታጣቂዎች በኦሮሚያ ከልል ሰሜን ሸዋ ዞን ዋጫሌ ወረዳ ሙከጡሪ ከተማ ማክሰኞ'ለት ምሽት ጥቃት መፈጸማቸውን ዋዜማ በከተማዋ ከሚኖሩ ምንጮች ተረድታለች። የቡድኑን ታጣቂዎች ጥቃት ተከትሎ፣ እስከ ሌሊቱ 9:00 ሰዓት ድረስ በቡድኑ ታጣቂዎችና በኦሮሚያ ክልል ጸጥታ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ እንደተደረገ ለማወቅ ተችሏል። በተኩስ ልውውጡ አንድ የዳሸን ባንክ የጥበቃ ሠራተኛ ሕይወቱ ማለፉን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኤቲኤም ማሽን ተሰብሮ መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብ መዘረፉንና ቁጥራቸው ከሦስት በላይ የሆኑ ሰዎች በታጣቂ ቡድኑ ታፍነው መወሰዳቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ የቡድኑ ታጣቂዎች በከተማዋ መሰል ጥቃቶችን ሲፈጽሙ የአኹኑ የመጀመሪያቸው እንዳልኾነ የዋዜማ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

2፤ ኢትዮጵያ የተመድ የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪ አሊስ ዋይሙሩ የኢትዮጵያን ኹኔታ አስመልክተው ያወጡት መግለጫ ሃላፊነት የጎደለው እና ግድየለሽ መግለጫ ነው በማለት አውግዛለች። በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ባወጣው መግለጫ፣ የልዩ አማካሪዋ መግለጫ የተመረኮዘበት የዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ትክክለኛውን የምርመራ ሂደት ያልተከተለ፣ መሬት ላይ ያለውን ኹኔታ የማይገልጽና ከትክክለኛ ምንጮች ያልተወሰደ ነው በማለት አጣጥሏል። የቋሚ መልዕክተኛው ጽሕፈት ቤት፣ ልዩ አማካሪዋ ተገቢ ያልኾነ ክስና አስተያየት ለመስጠት መምርጣታቸው የሚያሳዝን ነው በማለትም ወቅሷል። ልዩ አማካሪዋ በመንግሥትና ሕወሃት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት "ባብዛኛው ሳይሳካ ቀርቷል" ማለታቸው ስሕተት ነው ያለው የቋሚ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤት፣ ልዩ አማካሪዋ ከአገሪቱ ሠላም ግንባታ ጋር በመቃረን ያወጡትን መግለጫ እንዲያስተካክሉ አሳስቧል። ዋይሙሩ በኢትዮጵያ አኹንም የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸም የሚያስችሉ ኹኔታዎች አሉ በማለት ትናንት ማስጠንቀቂያ አውጥተው ነበር።

3፤ በሱዳን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ጉዳይ የሚከታተለው ብሄራዊ ግብረ ሃይል ገና ከአገሪቱ ያልወጡ ዜጎችን ለማስወጣት ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጧል። ግብረ ኃይሉ፣ ተመላሾች የኢትዮጵያን ደኅንነት ባስጠበቀ መልኩ እንዲመለሱና ከጦርነት ቀጠና እንዲወጡ ለማድረግ በሚቻልበት ኹኔታ ዙሪያ ትናንት ምክክር አድርጓል። የብሄራዊ ግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ በሱዳኑ ጦርነት ሳቢያ በአስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። የሱዳኑ ግጭት ከተጀመረ ወዲህ፣ እስከተያዘው ሳምንት መግቢያ 38 ሺህ 13 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችና ፍልሰተኞች በመተማና ኩርሙክ በኩል ተመልሰዋል።

4፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከጥቅምት 3 እስከ ጥቅምት 6 ድረስ ክልላዊ የሐዘን ቀናት እንዲኾኑ መወሰኑን የክልሉ ኮምንኬሽን ቢሮ አስታውቋል። በሦስቱ ክልላዊ የሐዘን ቀናት፣ የክልሉ ባንዲራ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደወሰነ ቢሮው ጨምሮ ገልጧል። "ለሕልውና የተከፈለ ውድ መስዕዋትነት" በሚል መሪ ቃል የሚታሰቡት ክልላዊ የሐዘን ቀናት፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርና የክልሉ ሕዝብ በትግራይና በፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች መካከል ለኹለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት የሞቱ ተዋጊዎችን ቤተሰቦች ለመርዳት ቃል የሚገቡበት ይኾናል ተብሏል።

5፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሚክሲኮ በሚገኘው የተቋሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ በ445 ሚሊዮን ዶላር ባለ 62 ወለል አዲስ የዋና መስሪያ ቤት ሕንጻ ሊያስገነባ መኾኑን አስታውቋል። የአዲሱ መስሪያ ቤት ሕንጻ በ20 ሺህ792 ካሬ ሜትር ላይ እንደሚያርፍና፣ በአራት ዓመታት ውስጥ ግንባታው ሲጠናቀቅ ሕንጻው 327 ነጥብ 5 ሜትር ከፍታ እንደሚኖረው ተቋሙ ገልጧል። ተቋሙ፣ የሕንጻው የዲዛይን ሥራ እየተከናወነ መኾኑም ገልጧል።

6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 55 ብር ከ3351 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 56 ብር ከ4418 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 64 ብር ከ9623 ሳንቲምና መሸጫው 66 ብር ከ2615 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ58 ከ6607 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ59 ብር ከ8339 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ዓርብ ጥቅምት 2/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ ዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያ መንግሥት የጠየቀውን የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት መውሰድ ባለበት ማሻሻያዎች ዙሪያ ከስምምነት ላይ ለመድረስ ያለመ ውይይት በቀጣይ ሳምንታት እንደሚደረግ አስታውቋል። ድርጅቱ ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ፣ ልዑካን ቡድኑ በአዲስ አበባ ያንድ ስምንት ቆይታ አድርጎ በመስከረም ወር መጨረሻ መመለሱን ጠቅሷል። ድርጅቱ የአገሪቱን የኢኮኖሚ መርሃ ግብር ማገዝ በሚችልበት ኹኔታ ዙሪያ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር አወንታዊ እድገት የታየበት ውይይት ማድረጉንም ገልጧል። መንግሥት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠርና ጥብቅ የበጀትና የገንዘብ ፖሊሲ መከተሉ አዎንታዊ ርምጃዎች መውሰዱንም ድርጅቱ አውስቷል።

2፤ የተመድ ዋና ጸሃፊ የውስጥ ተፈናቃዮች ልዩ አማካሪ ሮበርት ፓይፐር ተመድ በኢትዮጵያ የውስጥ መፈናቀል የፈጠራቸውን ችግሮች ለመፍታት መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ ትናንት ከውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደኤታ ምስጋኑ አረጋ ጋር በተወያዩበት ወቅት ቃል ገብተዋል። ፓይፐር ይህን ቃል የገቡት፣ ተመድ የኢትዮጵያ መንግሥት በጦርነቱ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባትና ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት እንዲደግፍ በጠየቋቸው ወቅት ነው። ምስጋኑ፣ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ዋናው ችግር ገንዘብ እንደኾነ ለፓይፐር እንደገለጡላቸው ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ገልጧል። ፓይፐር፣ ባለፉት ቀናት በትግራይ እና አፋር ክልሎች ጉብኝት አድርገው ነው ወደ አዲስ አበባ የተመለሱት።

3፤ የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኦስማን ሳላህና የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አማካሪ የማነ ገብረዓብ የመሩት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን ግብጽ ይገኛል። ልዑካን ቡድኑ ከግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳሚ ሽኩሪ ጋር የሱዳኑን ጦርነት ማስቆም በሚቻልበትና ለጦርነቱ የቀረቡ የሰላም ጥረቶችን ባንድ ላይ ማዋሃድ በሚችልበት አግባብ ዙሪያ እንደኾነ የኤርትራ መንግሥት ቃል አቀባይ የማነ ገብረ መስቀል በ"ኤክስ" (በቀድሞው ትዊተር) ገጻቸው አስታውቀዋል።

4፤ ኬንያ ከፍልስጤምና እስራኤል ጦርነት ጋር በተያያዘ አልሸባብ ጥቃት ሊፈጽም ይችላል በሚል ስጋት የጸጥታ ጥበቃዋን አጠናክራለች። ኬንያ የጸጥታ ጥበቃዋን ያጠናከረችው፣ አልሸበብ ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት እንደሚያደንቅ በይፋ መግለጡን ተከትሎ ነው። የኬንያ መንግሥት በበኩሉ፣ ሐማስ በእስራኤላዊያን ሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈጸመውን ጥቃት ወዲያውኑ አውግዟል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ዓርብ ጥቅምት 2/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በኢትዮጵያ ዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች መርማሪ ኮሚሽን ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ ለኢትዮጵያዊያን የግጭት ተጎጂዎች ተጠያቂነትንና ከጥቃት የመጠበቅ መብትን እንዲያስከብር ዛሬ ባወጣው የመጨረሻ ሪፖርቱ ጠይቋል። ኮሚሽኑ፣ በአገሪቱ ዓለማቀፍ ጥሰቶች ወደፊትም እንዳይፈጸሙ የሚያግድ ነገር የለም ብሏል። የኢትዮጵያና ኤርትራ መከላከያ ሠራዊቶችና የክልል ልዩ ኃይሎች "የጦር ወንጀል" እና "በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች" ሊባሉ የሚችሉ "የጅምላ ግድያ"፣ "የአስገድዶ መድፈር"፣ "የጾታ ጥቃት"፣ "በግዳጅ ማስራብ"፣ "የጅምላ ማፈናቀል" እና "የዘፈቀደ እስር" ወንጀሎችን በትግራይ ፈጽመዋል በማለት ከሷል። ኮሚሽኑ፣ የትግራይ ኃይሎችም ግድያና የጾታ ጥቃቶችን ያካተቱ "የጦር ወንጀሎችን" ፈጽመዋል ብሏል። በጊዜ እጥረት በሰሜኑ ጦርነት የተፈጸሙት ወንጀሎች "በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀጀሎች" ወይም "የዘር ማጥፋት ወንጀሎች" ስለመኾናቸው ድምዳሜ ላይ መድረስ እንዳልቻለ የገለጠው ኮሚሽኑ፣ በወንጀሎቹ ላይ የመጨረሻውን ፍረጃ ለመስጠት ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልግ ገልጧል። ኮሚሽኑ፣ የጊዜ ቆይታው አለመታደሱን ተከትሎ ዛሬ በይፋ ተበትኗል።

2፤ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በተፈጸመ የድሮን ጥቃት፣ ቁጥራቸው ከ10 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ ዋዜማ ከአካባቢው ምንጮች ሰምታለች፡፡ የድሮን ጥቃቱ መስከረም 26 እና 27 የተፈጸመው፣ በዞኑ ኮምቦልቻ እና ሀባቦ ጉዱሩ በተሰኙ ወረዳዎች እንደኾነ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ አካባቢው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እያለ የሚጠራው አማጺ ቡድን በስፋት የሚንቀሳቀስበት እንደኾነ የገለጹት ምንጮች፣ የድሮን ጥቃቱ የተፈጸመው ቡድኑን ዒላማ በማድረግ እንደኾነ ጠቅሰዋል፡፡ በአካባቢው በመንግሥት ኃይሎችና በቡድኑ ታጣቂዎች መካከል በሚካሄደው ግጭት፣ ከባድ መሳሪያዎች ጭምር ጥቅም ላይ መዋላቸውንና፣ በጥቃቱ በአርሶ አደሩ የእርሻና የግጦሽ መሬት ላይ ከፍተኛ ውድመትና ቃጠሎ መድረሱን ምንጮቹ አክለው ጠቁመዋል፡፡ የመንግሥት ሠራዊት ባኹኑ ወቅት በሀባቦ ጉዱሩ ወረዳ ደዱ ከተማ እና በኮምቦልቻ ወረዳ በብዛት ሠፍሮ እንደሚገኝም ታውቋል።

3፤ እናት ፓርቲ፣ መኢአድ፣ ኢሕአፓ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የአማራ ግዮናዊ ንቅናቄ በሰሜን ኢትዮጵያ ለተከሰተው ርሃብ ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ የምግብ ዕርዳታ እንዲያቀርብ ዛሬ በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል። ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው፣ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ "መንግሥት በአማራ ክልል የከፈተው ጦርነት በፈጠረው የእንቅስቃሴ ገደብ ሳቢያ ይበልጥ ተወሳስቧል" ብለዋል። የነፍስ አድን ድርጅቶች ርሃብ ባጠቃቸው አካባቢዎች በነጻነት መንቀሳቀስ የሚችሉበት ኹኔታ እንዲመቻችም ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል። መንግሥት ዜጎች በረሃብ እየሞቱ ባለሉት ወቅት "ምንም እንዳልተፈጠረ ለማስመሰል እየሰራ ይገኛል" ያሉት ፓርቲዎቹ፣ ችግሩ የዓለማቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት አግኝቶ አስቸኳይ መፍትሄ ካላገኘ ብዙዎች በርሃብ መሞታቸው አይቀሬ ነው በማለት አስጠንቅቀዋል።

4፤ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በምክክር አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ተሳታፊ የሚሆኑ ተወካዮችን በመጀመሪያው ዙር እያስመረጠ መኾኑን ገልጧል። ኮሚሽኑ፣ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮችን ከማኅበረሰቡ የተለያዩ ክፍሎች እያስመረጠ የሚገኘው፣ በአሶሳ ዞን 13 ወረዳዎች እንደኾነ አስታውቋል። ኹለተኛው ዙር የተወካዮች መረጣ ሂደት ከጥቂት ቀናት በኋላ በ14 ወረዳዎች እንደሚከናወንም ኮሚሽኑ ጠቅሷል። ኮሚሽኑ፣ በክልሉ በአጠቃላይ በ22 ወረዳዎችና በአምስት ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ እንደኾነ አውስቷል። መረጣው፣ ከእያንዳንዱ የማኅበረሰብ ክፍል አስር አስር ተወካዮች በድምሩ 2 ሺህ 700 የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተወካዮችን ያሳትፋል ተብሏል።

5፤ የናይጀሪያ ሕግ አውጭ ምክር ቤት በአዲስ አበባ በናይጀሪያዊያን ላይ ተፈጽሟል የተባለውን ጥቃትና እስር ለማጣራት ማቀዱን ትናንት አስታውቋል። ምክር ቤቱ ጉዳዩን ለማጣራት የሚያስችል ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ማጽደቁን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። አንዳንድ ናይጀሪያዊያን በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግላቸው እስር ቤቶች ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ የገለጠው ምክር ቤቱ፣ የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጋብዟል። ብዙዎች ታሳሪዎች የአውሮፕላን ተጓዦች እንደነበሩና ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያን እንደመተላለፊያ ሲጠቀሙ በግዳጅ ተይዘው ለእስር እንደተዳረጉ ማግኘቱን ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። የአገሪቱ የላይኛው ሕግ አውጭ ምክር ቤት ከ250 በላይ ናይጀሪያዊያን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደተገደሉ ወይም በእስር ላይ እንደሚገኙ ባለፈው ሳምንት ገልጦ ነበር። በናይጀሪያ ምክር ቤት ውንጀላ ዙሪያ፣ የናይጀሪያና የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴሮች ወይም በአቡጃ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ያሉት ነገር የለም።

6፤ የሱዳን ጦር ሠራዊትና የባላንጣው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ተወካዮች ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ በሚስጢር ተገናኝተው በጦርነቱ ዙሪያ መነጋገራቸውን ከምንጮች ሰምቻለኹ ሲል አሻርቅ አል-አውሳት ጋዜጣ ዘግቧል። በሚስጢራዊ ንግግሩ የሱዳን ወታደራዊ መንግሥትን የወከሉት የአገሪቱ ብሄራዊ የስለላ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ሌትናል ጀኔራል ኢብራሂም ሙፋዳል እንደኾኑ የጠቀሰው ዘገባው፣ ፈጥኖ ደራሹን ኃይል የወከሉት ደሞ የቡድኑ የሕግ አማካሪ ሞሃመድ አልሞክታር መኾናቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ዘገባው፣ ኹለቱ ወገኖች ጦርነቱ የአገሪቱን ደኅንነት አደጋ ላይ ሊጥል በሚችልበት ኹኔታ ዙሪያ ጥልቅ ውይይት ስለማድረጋቸው መስማቱንም ዘገባው አመልክቷል። ጀኔራል ኢብራሂም፣ የጦር ሠራዊቱ መሪዎች ጦርነቱን ለማስቆም ከፈጥኖ ደራሹ ኃይል ጋር ለመነጋገር ፍላጎት እንዳላቸው ለቡድኑ ተወካይ እንደነገሯቸውም ዘገባው ገልጧል። ጀኔራል ኢብራሂም ከንግግሩ በኋላ ወደ ካይሮ አቅንተዋል ተብሏል። ኹለቱ ወገኖች ተወካዮቻቸው አዲስ አበባ ውስጥ ተወያይተዋል ስለመባሉ በይፋ የሰጡት ማረጋገጫ የለም።

7፤ የኬንያ ፍርድ ቤት ልውጥ ዘረ መል የምግብ እህል ዘሮች ወደ አገሪቱ እንዲገቡና እንዲመረቱ መንግሥት ባሳለፈው ውሳኔ ላይ የቀረበውን የተቃውሞ አቤቱታ ውድቅ አድርጓል። ፍርድ ቤቱ የተቃውሞ አቤቱታውን ውድቅ ያደርገው፣ ልውጥ ዘረ መል የሰብል ዘሮች ወደ እገሪቱ ቢገቡና ቢመረቱ በተፈጥሮ ወይም በሰው ልጅ ጤና ላይ የሚያመጡት ጉዳት ስለመኖሩ አሳማኝ ማስረጃ አላገኘኹም በማለት እንደኾነ ደይሊ ኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል። የኬንያ መንግሥት ከ10 ዓመታት በላይ በልውጥ ዘረ መሎች ላይ አገሪቱ ጥላው የቆየችውን እገዳ ከአንድ ዓመት በፊት ያነሳው፣ ኬንያ በተደጋጋሚ ድርቅ መጠቃቷን በመግለጽ ነበር። የኬንያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ግን፣ መንግሥት እገዳውን ማንሳቱ "ሕገ መንግሥታዊ አይደለም" በማለት ፍርድ ቤቱ እንዲቀለብሰው አቤቱታ አቅርቦ ነበር። ኾኖም አኹን በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት፣ የልውጥ ዘረ መል ሰብል ዘሮችን አገሪቱ ውስጥ መዝራትና ማምረት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ቅዳሜ ጥቅምት 3/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት የአገሪቱ የገንዘብ ምንዛሬ በገበያ ብቻ እንዲወሰን ለማድረግ ዝግጁነታቸውን እንደገለጡ የዓለማቀፉ ገንዘብ ድርጅት ባለሥልጣናት በሞሮኮ በተካሄደ ስብሰባ ላይ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። የገንዘብ ምንዛሬ በገበያ ይወሰን የሚለው ጥያቄ፣ የዓለም ገንዘብ ድርጅት በተደጋጋሚ የሚያነሳው ጥያቄ ነው። ከቻይና የአንድ ዓመት የብድር መክፈያ እፎይታ ያገኘችው ኢትዮጵያ፣ ከሌሎች አበዳሪ አገራት ጭምር እፎይታ ልትጠይቅ እንደኾነ የድርጅቱ መናገራቸውንም ዘገባው ጠቅሷል። ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ ብድር ካጸደቀ፣ የዕዳ መክፈያ ጊዜ ሽግሽጉ በቶሎ ምላሽ ያገኛል ብሎ እንደሚያምን መግለጡንም ዘገባው ገልጧል። የድርጅቱ ባለሥልጣናት፣ የድርጅቱ ልዑካን ቡድን በቀጣይ ሳምንታት ቢያንስ አንድ ጊዜ ለድርድር ወደ ኢትዮጵያ ሊሄድ እንደሚችልም ተናግረዋል ተብሏል።

2፤ መከላከያ ሠራዊት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ጉጂና ምሥራቅ ቦረና ዞኖች አዋሳኝ አከባቢዎች ሚሊሻዎችን አሰልጥኖ ማስመረቁን ገልጧል። ሚሊሻዎቹ የሰለጠኑት፣ ሠራዊቱና የክልሉ ጸጥታ ኃይሎች ከአማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ጋር ለሚያደርጉት ውጊያ ድጋፍ እንዲሰጡ መኾኑን ሠራዊቱ አስታውቋል። ሠራዊቱ፣ ሰሞኑን አሰልጥኖ ያስመረቃቸውን ሚሊሻዎች ብዛት ግን አልገለጠም።

3፤ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ተቀማጭነቱ ለንደን ከኾነው ዓለማቀፉ የሰነድ መዋዓለ ንዋይና ኢንቨስትመንት ኢንስቲቲዩት ጋር በጋራ አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ሰሞኑን ለንደን ውስጥ ተፈራርሟል። ስምምነቱ፣ የለንደኑ ተቋም ለኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ የቁጥጥር ሥርዓት ለመዘርጋት፣ የባለሙያዎችን የመቆጣጠር አቅም ለመገንባት፣ ለካፒታል ገበያ ባለሃብቶች ዓለማቀፍ እውቅና ያለው የብቃት ማረጋገጫ እንዲሰጥ ያስችለዋል። በስምምነት ስነ ሥርዓቱ ላይ፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ እና የኢትዮጵያና የብሪታንያ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።

4፤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከትናንት ጀምሮ በጦርነቱ ለሞቱ ተዋጊዎች ቤተሰቦች መርዶ ማርዳት ጀምሯል። ኾኖም የክልሉ መንግሥት በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡት ተዋጊዎችን ብዛት ትናንት አልገለጠም። ከዛሬ ጀምሮ ደሞ ሟች ተዋጊዎችን ለማሰብ፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውሳኔ ለሦስት ቀናት የክልሉ ባንዲራ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል።

5፤ የሱዳን ጦር ሠራዊት የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በአገሪቱ ጦርነት የተፈጸሙ ዓለማቀፍ ወንጀሎችን የሚያጣራ መርማሪ አካል ለማቋቋም መወሰኑን ውድቅ አድርጓል። ተቃዋሚው የነጻነትና ለውጥ ኃይሎችና ፈጥኖ ደራሹ ኃይል በበኩላቸው፣ የአጣሪ ቡድን ማቋቋም ውሳኔውን ደግፈዋል። የነጻነትና ለውጥ ንቅናቄ፣ በጦርነቱ የተፈጸሙ ወንጀሎች ለዓለማቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት እንዲመሩ ጭምር ጠይቋል። ወታደራዊው መንግሥት የውሳኔ ሃሳቡን ያቀረቡት ብሪታኒያና አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት ምክር ቤቱን የራሳቸውን ዓላማ ማራመጃ አድርገውታል በማለት ከሷል። ጦር ሠራዊቱ፣ ዓለማቀፍ የጥሰት ምርመራ ማነጣጠር ያለበት በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ላይ ብቻ ነው ብሏል። [ዋዜማ]
ለቸኮለ! ቅዳሜ ጥቅምት 3/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጉራጌ ዞን ጸጥታ ዕዝ ትናንት በወልቂጤ ከተማ በተቀሰቀሰ ግጭት በሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል። የጸጥታ ዕዙ፣ በግጭቱ ንብረት መውደሙን ጭምር ገልጧል። ግጭቱን ተከትሎ፣ የጸጥታ ዕዙ በከተማዋ ዛሬ ከቀኑ 11:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ነገ ጧት 1:00 ሰዓት ድረስ የሰዓት እላፊ ገደብ ጥሏል። ጸጥታ ዕዙ፣ በሰዓት እላፊ ገደቡ የሰዌችንና ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ከልክሏል። የጸጥታ ዕዙ የግጭቱን መነሻ ምን እንደኾነ፣ በግጭቱ የተሳተፉትን ወገኖች ማንነትና በስንት ሰዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ ግን አልገለጠም። ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተመመረተ ወዲህ፣ በዞኑ ዋና ከተማ ወልቂጤና በቅርቡ ልዩ ወረዳ ኾኖ በተዋቀረው ቀቤና መካከል የአስተዳደር ወሰንን መሠረት ያደረገ ግጭት ካኹን ቀደምም ተፈጥሮ ነበር።

2፤ ገንዘብ ሚንስቴር መንግሥት ለጨረታ ላቀረባቸው ስምንት ስኳር ፋብሪካዎች ከተጫራቾች የፋይናንስና የቴክኒክ ምክረ ሃሳብ ሰነዶችን ባስቀመጠው ቀነ ገደብ መስከረም 24 መረከቡን አስታውቋል። ሚንስቴሩ፣ የባለሙያዎች ቡድን ባኹኑ ወቅት የተጫራቾችን የቴክኒክ ሰነዶች እየገመገመ መኾኑ ገልጧል። ከቴክኒክ አንጻር ለጨረታው ብቁ የኾኑ ተጫራቾች ዝርዝር ጥቅምት 9 ይፋ እንደሚደረግ የገለጠው ሚንስቴሩ፣ ቀጣዩ ሂደት የፋይናንስ ምክረ ሃሳቦችን መገምገም እንደኾነ ገልጧል። በጨረታው ለመሳተፍ ስንት ኩባንያዎች የቴክኒክና ፋይናንስ ምክረ ሃሳብ ሰነዶችን እንዳስገቡ ግን ሚንስቴሩ አልጠቀሰም።

3፤ ሰላም ሚንስቴር መንግሥት ኢትዮጵያ ቀይ ባሕር ላይ ያሏትን ብሄራዊ ስትራቴጂካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች እንዲያረጋግጥ የሚጠይቅ ረቂቅ ሰነድ ማዘጋጀቱን ሪፖርተር ዘግቧል። ረቂቅ ሰነዱ፣ ኢትዮጵያ ወደብ ለመገንባትና ለመጠቀም እንዲኹም በቀይ ባሕርና የኤደን ባሕረ ሰላጤ ቀጠና መውጫ በር የማግኘት መብት እንዲኖራት እንደሚጠይቅ ዘገባው አመልክቷል። ኢትዮጵያ ይህንኑ ጥቅሟን ለማስከበር፣ ከቀጠናው አገራት ጋር በመነጋገር ጅኦስትራቴጂካዊና የልማት ማነቆዋን መስበር አለባት የሚል ሃሳብ አካቷል ተብሏል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ወደብ እንደሚያስፈልጋት የተናገሩት ንግግር በዚህ ሳምንት በመንግሥታዊው ቴሌቪዥን በተላለፈ አንድ ዝግጅት ላይ ቀርቦ ነበር። ሰላም ሚንስቴር፣ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ማንነትና ብሄራዊ እሴቶች ልየታ የሚመለከት ረቂቅ ሰነድ ማርቀቁንም ጋዜጣው ዘግቧል።

4፤ በሰሜኑ ጦርነት ሕይወታቸውን ያጡ የትግራይ ተዋጊዎችንና ሌሎች ዜጎችን ለማሰብ ዛሬ በትግራይ ክልል የተለያየ ከተሞች የሐዘን ስነ ሥርዓቶች ሲከናወኑ ውለዋል። ዛሬ በመቀሌ በተካሄደውና በርካታ ነዋሪዎችና የክልሉ ባለሥልጣናት በተገኙበት የሐዘን ስነ ሥርዓት ላይ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ በሰማዕታት ሐውልት ስር የአበባ ጉንጉን አኑረዋል። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጀው የሦስት ቀናት ሐዘን መሠረት፣ የክልሉ ባንዲራም ከዛሬ ጀምሮ ዝቅ ብሎ እየተውለበለበ ይገኛል።

5፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በሰሜኑ ጦርነት በትግራይ ክልል ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች ሐዘናቸውን ገልጸዋል። ፓትርያርኩ በጦርነቱ ላለቁ የክልሉ ነዋሪዎችን ለማሰብ በክልሉ እየተካሄደ የሚገኘውን ሐዘን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ በጦርነቱ የደረሰው እልቂት እንዳይከሰት "ብዙ ተማጽኖ" ብናቀርብም "ሽበትና ክህነት የማይከበርበት" ዘመን ላይ በመድረሳችን ላኹኑ ሐዘን ተዳርገናል ብለዋል። ፓትርያርኩ፣ አኹን የተገኘው አንጻራዊ ሰላም ዘላቂ የሚኾንበትና ተፈናቃዮች ወደቀያቸው የሚመለሱበት ኹኔታ እንዲፈጠርም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

6፤ ኬንያ የኃይል ማመንጫ ግድቦቿ መቀነሳቸውን ተከትሎ ከኢትዮጵያ የምትገዛውን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን መጨመሯን ቢዝነስ ደይሊ ዘግቧል። ኬንያ ባለፉት ስምንት ወራት ከውጭ ከገዛችው 594 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ፣ 70 በመቶው ከኢትዮጵያ እንደኾነ ዘገባው ጠቅሷል። ኬንያ ከቀደመው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከገዛችው ኃይል ጋር ሲነጻጸር፣ ባለፉት ስምንት ወራት የገዛችው የ185 በመቶ ብልጫ እንዳለው ዘገባው ጠቅሷል። ኬንያ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መግዛት የጀመረችው ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ነበር። ኢትዮጵያ አንድ ኪሎ ዋት ሰዓት ኃይል ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለኬንያ ለመሸጥ የተስማማችበት ዋጋ 6 ነጥብ 5 የአሜሪካ ሳንቲም ነው።

7፤ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከቻይና 1 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ብድር ለመጠየቅ ዛሬ ወደ ቤጂንግ አቅንተዋል። ሩቶ ከቻይና 1 ቢሊዮን ዶላር ብድር የሚጠይቁት ፣ በገንዘብ እጥረት ላልተጠናቀቁና የቻይና ተቋራጮች ለሚገነቧቸው መንገዶች ማጠናቀቂያ ነው። ሩቶ፣ ከብድር ጥያቄ በተጨማሪ፣ ኬንያ ከቻይና ለተበደረችው ብድር የብድር መክፈያ ጊዜ ሽግሽግ እንዲደረግላት ይጠይቃሉ። ኬንያ ባኹኑ ወቅት፣ ከ8 ቢሊዮን ዶላር በላይ የቻይና ዕዳ አለባት። [ዋዜማ]
ለቸኮለ ማለዳ! ሰኞ ጥቅምት 5/2016 ዓ.ም የዋዜማ ዕለታዊ ዜናዎች

1፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በከተማዋና ቀቤና ልዩ ወረዳ መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት ፌደራል ፖሊስና የክልሉ ጸጥታ አካላት ከዞኑ አስተዳደር፣ ከቀቤና ልዩ ወረዳ፣ ከአባሽጌ ወረዳና ከወልቂጤ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ጋር ትናንት ውይይት አድርገዋል። የክልሉ ጸጥታ ቢሮ፣ በግጭቱ የተሳተፉትን አካላት አጣርቼ ለሕግ አቀርባለኹ ብሏል። በጦር መሳሪያ የታገዘው ግጭት ቅዳሜ ከቀትር በኋላ መባባሱን ተከትሎ፣ የዞኑ ጸጥታ ዕዝ በከተማዋ የሰዓት እላፊ አውጆ ነበር። ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከመቋቋሙ በፊት የቀቤና ወረዳ አስተዳደር መቀመጫው ወልቂጤ ነበር። ኾኖም ቀቤና በአዲሱ ክልል ስር በልዩ ወረዳነት ከየዋቀረ ወዲህ፣ ከወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ጋር የወሰን ውዝግብ ውስጥ መግባቱ የግጭት ምክንያት ኾኗል።

2፤ መንግሥት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ረቂቅ አዋጅ በአገር ደኅንነት ላይ አደጋ ይፈጥራሉ የሚላቸውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ከውጭ እንዳይገቡ የሚያግድ ሕግ እያዘጋጀ መኾኑን ሪፖርተር አስነብቧል። ረቂቅ ሕጉ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ተቆጣጣሪ አካል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ከፍርድ ቤት ፍቃድ ውጭ እንዲፈተሽ ሥልጣን ይሰጣል። የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር በሕገወጥ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ላይ ቁጥጥር የሚያደርጉ አካላትን እንዲሰይምና ያለ ፍርድ ቤት ፍቃድ በማናቸውም ቦታ ፍተሻ እንዲያደርግና የቴክኖሎጂ ምርቱን እንዲይዝ ሥልጣን እንደሚሰጥ ዘገባው አመልክቷል። ፍቃድ በሌላቸው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ማስገባት፣ መጠቀም ወይም ማስወጣት፣ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚያስቀጣ መደንገጉንም ዘገባው ጠቅሷል። ረቂቅ አዋጁ መከላከያ ሠራዊትን፣ የደኅንነት አገልግሎትንና ፌዴራል ፖሊስን አይመለከትም ተብሏል።

3፤ የሱማሌላንዱ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አማጺ የጎሳ ሚሊሻዎች በኃይል በተቆጣጠሯቸው ግዛቶች ራሱን የቻለ አስተዳደር ለመመስረት የሚያደርጉትን ጥረት ውድቅ አድርገዋል። ሱማሌላንድ አኹንም ታጣቂዎች በኃይል የያዙባትን አውራጃዎች በኃይል የማስመለስ እቅድ አላት። ግዛቶቹን ከሱማሌላንድ በውጊያ ነጥቀው የተቆጣጠሩት የጎሳ ሚሊሻዎች መሪዎች፣ ባለፈው ሳምንት ወደ ሞቃዲሾ አቅንተው ከፌደራል መንግሥቱ ፕሬዝዳንትና ጠቅላይ ሚንስትር ጋር መምከራቸው ይታወሳል። የጎሳ ሚሊሻዎቹ ዓላማ፣ ግዛቶቹ በሱማሊያ ስር እንዲተዳደሩ ማድረግ እንደኾነ ይገልጣሉ።

4፤ ደቡብ ሱዳን የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በጣለባት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ሳቢያ ወታደሮቿ ዱላ ለመያዝ እንደተገደዱ ገልጣለች። የአገሪቱ መንግሥት ወታደሮቹን ዱላ ለማስታጠቅ የተገደደው፣ በቅርቡ አሰልጥኖ ያስመረቃቸውን ከአማጺዎችና ከመንግሥት ጦር የተውጣጡትን የብሄራዊ ጦር ሠራዊት አባላት ነው። ብሄራዊ ሠራዊቱ በተያዘው ወር በአገሪቱ መሠማራት ይጀምራል። አገሪቱ በሰላም ስምምነቱ መሠረት፣ ከመንግሥትና ከአማጺው ቡድን የተውጣጣ ብሄራዊ ጦር ሠራዊት በማቋቋም ላይ ናት። [ዋዜማ]