TIKVAH-ETHIOPIA
1.51M subscribers
57K photos
1.42K videos
206 files
3.9K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
Download Telegram
#EthiopianCargo 🇪🇹

በትላትናው ዕለት በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ፣ #ዱባይ በተካሄደ የ " አረቢያን ካርጎ አዋርድ " በደንበኞች ምርጫ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ " በአፍሪካ ምርጥ የካርጎ አየርመንገድ " ተብሎ ተመርጧል።

በዚሁ የሽልማት ዘርፍ በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ  ኦፕሬት የሚያደርጉት አየር መንገዶች በእጩነት ቀርበው የነበረ ቢሆንም አየር መንገዱ ሁሉንም በመብለጥ ነው በአፍሪካ - ምርጡ የካርጎ አየር መንገድ ተብሎ የተሸለመው።

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
" ህዝቡ ለም መሬት ይዞ መራቡ እጅግ አሳዛኝ ነው "

የምዕራብ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች አንዳንድ ወረዳዎች የከፋ ረኀብ መከሰቱን ነዋሪዎች ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ ዞኖች አንዳንድ ወረዳዎች፣ በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ለዓመታት በዘለቀው ግጭት ምክንያት ለከፋ ረኀብ መጋለጣቸውን ነዋሪዎች መግለፃቸውን ቪኦኤ ሬድዮ ጣቢያ ዘግቧል።

በምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ አለማየሁ ጋቢሳ ለረኃቡ መከሰትና መባባስ ዋናው ምክንያት የጸጥታ ችግር መሆኑን ያነሳሉ። "የመንግስት የጸጥታ ኃይሎችም ታጣቂዎችም ነዋሪዎችን ያዋክባሉ" ያሉት አቶ አለማየሁ "በእነርሱ የተኩስ ልውውጥ ምክንያት ብዙ ንጹሐን ይሞታሉ የተረጋጋ ነገር የለም " ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም፥ " ባለፈው ዓመት ሰው ያለውን ሲበላ ነበር፤ አሁን በእጁ ያለውን ጨርሶ ተርቧል። ህዝቡ ለም መሬት ይዞ መራቡ እጅግ አሳዛኝ ነው" ሲሉ ነው ሀሳባቸውን የሰጡት።

አቶ አለማየው ስላለው ሁኔታ ሲያስረዱም፥ " ከተማ ላይ ዉጊያ ሲኖር ገጠር ውስጥ ታጥቀው ህብረተሰቡን የሚዘርፉ አሉ፤ ውጊያው ከከተማ ወጣ ካለ ደግሞ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎችን ልብስ በመልበስ ተመሳስለው ዘረፋ የሚፈጽሙ አሉ። ለነዋሪዎች አስቸጋሪ ሆኗል።" ሲሉ አስረድተዋል።

ሌላኛው በቄለም ወለጋ ጋኦ ጊቤ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ከማል ሰይድ በበኩላቸው " ህጻናት በረኀብ ተጎድተው ህይወታቸውን እያጡ ነው። የለቅሶ ድንኳን በየቦታው ተተክሏል። አሁንስ ተስፋ ቆርጠናል፤ ማረስ እየቻልን ልጆቻችንን እጃችን ላይ እያጣን ነው።" ሲሉ የገለጹ ሲሆን " ከዚህ በላይ አስከፊ ነገር አለ?" ሲሉ ጠይቀዋል።

በምዕራብ ወለጋ ቆንዳላ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ታምሩ ኡጋሳ እስካሁን ምንም ዓይነት የሰብዓዊ ዕርዳታ አለመድረሱን ጠቅሰው "መንግስት ለህብረተሰቡ ጭንቀት የሰጠው መልስ የለም፤ ለህብረተሰቡ ቶሎ እርዳታው ካልደረሰ ጉዳቱ የከፋ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ ከምዕራብ ወለጋ እና ከቄለም ወለጋ ዞኖች የጤና ተቋማት እና ቡሳ ጎኖፋ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ኮምዩኒኬሽን ቢሮ እና ቡሳ ጎኖፋ፣ ምላሽ እንዲሰጡ ጥረት ቢደረግም አለመሳካቱን ሬድዮ ጣቢያው በዘገባው ጠቅሷል።

@tikvahethiopia
#MoE

የትምህርት ሚኒስቴር ፤ በአካዳሚክ ጉዳዮች ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ኤባ ሚጄና አማካኝነት ለሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በላከው ደብዳቤ በ2016 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ለሚሰጠው የመውጫ ፈተና ዝግጅት ለማድረግ እንዲቻል ለፈተናው የሚቀመጡ ተማሪዎች መረጃ በአስቸኳይ እንዲላክለት ጠይቋል።

ሚኒስቴሩ ፤ ተቋማት መረጃው እጅግ ቢዘገይ እስከ ጥቅምት 16 ቀን 2016 ዓ.ም እንዲልኩ ያሳሰበ ሲሆን የማያሳውቅ ዩኒቨርሲቲ " ተፈታኝ ተማሪ የለውም " በሚል ተይዞ የሚታቀድ መሆኑን በጥብቅ አስገንዝቧል።

በ2015 ዓ/ም ለመጀመሪያ ጊዜ በተሰጠው የመውጫ ፈተና በመንግስት ተቋማት ለፈተናው ከተቀመጡት 77,981 ተማሪዎች ውስጥ 50 እና ከዚያ በላይ በማምጣት ያለፉት 48,632 ተማሪዎች ወይም 62.37 በመቶ መሆናቸው አይዘነጋም።

በግል ተቋማት ደግሞ ለፈተና ከተቀመጡት 72,203 ተማሪዎች ውስጥ 50 እና ከዚያ በላይ ውጤት አምጥተው ያለፉት 12,422 ተማሪዎች ወይም 17.2 በመቶ ብቻ ነበሩ።

በድምሩ ከአጠቃላይ 150,184 የመውጫ ፈተና ተፈታኞች ፈተናውን ያለፉት 61,054 ብቻ ወይም 40.65 በመቶ ናቸው።

የትምህርት ሚኒስቴር የመውጫ ፈተና አስተዳደር መመሪያ እንደሚያሳየው ከሆነ ፈተናው በዓመት ሁለት ጊዜ ይሰጣል። የመጀመሪያው በአመቱ መጨረሻ ሲሆን ሁለተኛ በአመቱ አጋማሽ ነው።

የመጀመሪያውን የመውጫ ፈተና ያላለፉ ተማሪዎች በዚህ አመት አጋማሽ ላይ በሚዘጋጀው ሌላ ፈተና መፈተን የሚችሉ ሲሆን ከዚህ ቀደም ትምህርት ሚኒስቴር  ተፈታኞች ዳግም ፈተና ለመውሰድ መጀመሪያ ሲማሩበት ወደነበረበት ተቋም መሄድ ሳይጠበቅባቸው ባሉበት አካባቢ ባሉ ተቋማት ፈተናውን እንደሚወስዱ የሚደረግበት ስርዓት እንደሚዘረጋ መግለፁ አይዘነጋም (በዚህ ጉዳይ ወደፊት የሚወጣ መረጃ ካለ ተከታትለን እናሳውቃለን)።

#TikvahEthiopia

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#ENDF🇪🇹

በሀገር ደረጃ ዛሬ 116ኛው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀን በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ ተከብሯል።

ለመሆኑ በዓሉ ለምንድነው " ለ116ኛ ጊዜ " እየተባለ የሚከበረው ?

ይህ ቀን / ጥቅምት 15 የተመረጠው ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1900 ዓ/ም ያቋቋሙትን የጦር ሚኒስቴርን ታሳቢ በማድረግ ነው።

ከዚህ ቀደም የ " መከላከያ ሰራዊት ቀን " ተብሎ ሲከበር የነበረው ኢህአዴግ በ1987 ዓ/ም አዲስ የመከላከያ ሰራዊት ማቋቋሚያ አዋጅ አዘጋጅቶ በተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀበት ወቅት ነው።

በዚህ መነሻ የካቲት 7 ቀን በየዓመቱ ሲከበር ነበር።

ኢህአዴግ በውስጡ የነበሩት አመራሮች አጠቃላይ ሀገራዊ ለውጥ ካደረጉ በኃላ / በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የሀገር አስተዳደር የቀድሞው ውሳኔው " ከ1987 በፊት የነበረውን የኢትዮጵያ ሰራዊት እና የዘመኑ ትውልድ ተጋድሎን ውድቅ ያደረገና ቆርጦ ያስቀረ ነው " በማለት ቀኑን ወደ ጥቅምት 15 ቀይሮታል።

ቀኑ እንዲቀየር በተደረገው ጥናት ለበዓሉ መከበር መነሻ የሀገር ሰራዊት በቋሚነት ተደራጅቶ እንደ ተቋም የተመሰረተበት ቀን ሊመረጥ ችሏል።

ይህም ቀን ጥቅምት 15 /1900 ዓ/ም የአፄ ሚኒሊክ የጦር ሚኒስትር መ/ቤት ያቋቋሙበትና መስሪያ ቤቱን እንዲመሩ ሚኒስትር የሰየሙበት ቀን ነው።

ጥቅምት 15 /1900 ዓ/ም የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የጦር ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ፊትአውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ / አባ መላ ነበሩ።

የዘንድሮው የሰራዊት ቀን ለምን በወታደራዊ ሰልፍ ትርኢት ለማክበር ተፈለገ ?

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና የተኩስ አመራት ኃላፊ ሌ/ጄነራል ዓለምእሸት ደግፌ ዛሬ በመስቀል አደባባር በተካሄደው ዝግጅት ላይ ባሰሙት ንግግር " በዓሉ በወታደራዊ ሰልፍ ትርኢት እንዲከበረ የተፈለገው ለእይታ ስለሚማርክ ብቻ ሳይሆን ዋናው እሳቢያችን ዛሬም ነገም ሰላማችንን ለማወክ የሚመኙ ካሉ ሁሌም ዘወትር ዝግጁ መሆናችንን ከወዲሁ ለማሳሰብ ነው " ብለዋል።

በመስቀል አደባባይ በተካሄደው የሰራዊት ቀን በዓል ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የጦር ሰራዊት አመራር እና አባላት፣ የክልል ባለስልጣናት፣ ጥሪ የተደረገላቸው የአፍሪካ ሀገራት የጦር መሪዎች ...እና ሌሎችም ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተው ነበር።

@tikvahethiopia
" ጥገናው አልቆ ኃይል ለመስጠት እስከ ሦስት ቀን ድረስ ሊወስድ ይችላል " - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ሙሉ በሙሉ በጭለማ እንዲዋጥ ያደረገ ስርቆት መፈፀሙ ተነገረ።

ከመንዲ አሶሳ በተዘረጋው ባለ 132 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ በተፈፀመ ስርቆት ምክንያት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሙሉ በሙሉ የኃይል አቅርቦት መቋረጡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ጋይል አሳውቋል።

በክልሉ " መንደር 48  " በተለምዶ አንበሳ ጫካ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶ አካላት ላይ በተፈፀመ ስርቆት መስመሩን የሚሸከሙ ሁለት የብረት ምሰሶዎች ወይም ታወሮች ወድቀዋል፡፡

በዚሁ የተነሳ ከመስመሩ ኃይል ሲያገኙ የነበሩት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መዲና አሶሳ ከተማ እና የአሶሳ ዞን ወረዳዎች በሙሉ የኃይል አቅርቦት ተቋርጧል።

ከዚህ በፊትም በክልሉ ባምባሲ በተባለ አካባቢ በሥርቆት የተነሳ ኃይል ተቋርጦ የነበረ ሲሆን አሁን ለኃይል መቋረጥ ምክንያት የሆነው አካባቢ ከአሶሳ ከተማ ወደ 30 ያህል ኪሎ ሜትሮች ርቀት እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡

የወደቁ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን በጊዜያዊነት በእንጨት ምሰሶዎች ለመተካት ጥረቶች የተጀመሩ ሲሆን ጥገናውን አጠናቆ ለአካባቢዎቹ ኃይል ለመስጠት እስከ ሦስት ቀን ድረስ ሊወስድ ይችላል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ፤ የኤሌክትሪክ መሰረተልማቶችን መጠበቅ በየደረጃው ያሉ የሁሉም መስተዳድር አካላት ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝቦ የመስተዳድር አካላቱ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አድርጓል።

ጥገናው ተጠናቆ ወደአገልግሎት እስኪመለስ ድረስ  ህብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠብቀም ጠይቋል።

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
በአዲስ አበባ ተዘግተው የነበሩ መንገዶቹ ተከፍተዋል።

በመስቀል አደባባይ የተከበረው የመከላከያ ሠራዊት ቀን በሠላም መጠናቀቁን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል አስታውቋል።

የቀኑን መከበር ተከትሎ ለተሽከርካሪ ዝግ የነበሩ መንገዶች ተከፍተው መደበኛ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑ ተገልጿል።

መረጃው ከአዲስ አበባ ፖሊስ ነው የተገኘው።

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#ETHIOPIA

" ኢትዮጵያ በኃይልና በወረራ ማሳካት የምትፈልገው አንዳችም ነገር የለም " - የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እና ጠቅላይ ሚኒስትር

ካለፉት ሳምንታት አንስቶ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሰፊ የመወያያ አጀንዳ እንደሆነ ይታወቃል።

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር እና ከሕንድ ውቅያኖስ በቅርብ ርቀት ላይ እንደመገኘቷ የባሕር በር የማግኘት #ሃሳብ " የሕልውና ጉዳይ ነው " የሚል ንግግር ካደረጉ በኃላ በርካቶች የግላቸውን አስተያየት ሲሰጡ ነበር።

ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባህር በር ለማግኘት ከጦርነትና ግጭት ውጭ የሆኑ ለጋራ ጥቅም የሰጥቶ መቀበል መንገዶችን ቢያብራሩም አንዳንዶች በዚሁ በባህር በር ጉዳይ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ወደ ጦርነት ትገባለች የሚል ስጋታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።

እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች ፤ በባህር በር ጉዳይ ከየትኛውም የጎረቤት ሀገር ጋር ወደ ጦርነት መግባት እንደማያስፈልግ በመግለፅ መሰል ሃሳቦች ካሉ መታቀብ እንደሚገባ ሲጠይቁ ነበር።

ከሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በዚሁ በኢትዮጵያ በኩል ስለተነሳው የባህር በር ጉዳይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ከነበሩት ውስጥ የጎረቤት ሀገር ዜጎችም የሚገኙበት ሲሆን #የወረራ_ስጋት እንዳላቸው ሲናገሩም ተደምጧል።

ሰሞኑን ስለሚሰነዘሩት አስተያየቶች ይመስላል የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ዛሬ በተከበረው የመከላከያ ሰራዊት ቀን በዓል ላይ አጭር ነገር ተናግረው አልፈዋል።

ምን አሉ ?

" ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በአንዳንድ ጉዳዮች ውይይት ያስፈልገናል የሚል ጥያቄ ስታነሳ ወረራ ሊካሄድ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ ይደመጣል።

ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እና ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በዚሁ በተከበረ ቀን መግለፅ የምፈልገው ኢትዮጵያ በኃይል እና በወረራ ማሳካት የምትፈልገው አንዳችም ነገር የለም።

ለጋራ ጥቅም ፣ ለጋራ እድገት ፣ ለጋራ ብልፅግና ሁሉም አሸናፊ በሚያደርጉ ጉዳዮች ከወንድሞቻችን ጋር ተወያይተን የጋራ ጥቅም የምናስከብር እንጂ በኃይል ፍላጎቶቻችንን ለማሳካት ወንድሞቻችን ላይ ቃታ የምንሰነዝር እንዳልሆንን በአፅንኦት ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ " ነው ያሉት።

@tikvahethiopia