ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ
803 subscribers
3.46K photos
104 videos
194 files
1.2K links
የየዕለቱ ስንክሳር እና ግጻዌ የሚቀርብበት ቻናል ነው፡፡

ለማንኛውም አስተያየት እና እርማት
@zetaodokos ላይ ይላኩልን።

👇👇የYoutube Channel ይቀላቀሉ👇👇
https://youtube.com/channel/UCupqpIYe_mMpSM7jMT3Njhw
Download Telegram
#የካቲት_18

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

የካቲት ዐሥራ ስምንት በዚች ቀን ታማኝ የከበረ አባት የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት #አባ_መላልዮስ አረፈ፣ ከ72ቱ አርድእት አንዱ የሆነ የጌታችን ወንድም የተባለ የአረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ ልጅ የሐዋርያ #ቅዱስ_ያዕቆብ መታሰቢያው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_መላልዮስ_ጻድቅ

የካቲት ዐሥራ ስምንት በዚች ቀን ታማኝ የከበረ አባት የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት አባ መላልዮስ አረፈ። ይህም ቅዱስ አዋቂና አስተዋይ ነበረ በታናሹ ቈስጠንጢኖስም ዘመነ መንግሥት በአንጾኪያ ሀገር ሊቀ ጵጵስና ተሾመ።

ከተሾመም እስከ ሠላሳ ቀን ኖረ ከዚህም በኋላ አርዮሳውያንን አወገዛቸው በአንጾኪያም ካለች ቤተ ክርስቲያን ሁሉንም አሳደዳቸው። ንጉሡም በሰማ ጊዜ ከመንበረ ሢመቱ ሊቀ ጳጳሳቱን አሳደደው እርሱ ንጉሡ አርዮሳዊ ነውና።

የአንጾኪያ አገርም ታላላቆችና ኤጲስቆጶሳት ካህናቱም ተሰበሰቡ ስለ ሊቀ ጳጳሳቱ ይመልስላቸው ዘንድ የልመና ደብዳቤ ጽፈው ላኩ ንጉሡም ልመናቸውን ተቀብሎ መለሰላቸው። ይህም አባት በተመለሰ ጊዜ አርዮሳውያንን ወደ ማውገዙ ተመለሰ በቃላቸው የሚያምኑትንም ስሕተታቸውንና ስድባቸውን ግልጽ እያደረገ ወልድ ከአብ ባሕርይ እንደ ተወለደ በመለኮቱም ትክክል እንደሆነ ለሁሉ የሚሰብክ የሚያስተምር ሆነ።

ዳግመኛም አርዮሳውያን ተነሡ የንጉሡን ልብ ወደእሳቸው እስከ መለሱት ድረስ ይህን አባት እየወነጀሉ ወደ ንጉሥ ጻፉ ዳግመኛም ልኮ ከፊተኛው ወደሚርቅ አገር አሳደደው። ወደ ተሰደደበትም አገር በደረሰ ጊዜ መልእክቶቹን ጽፎ በመላክ ከወገኖቹ ጋር እንዳለ ሆነ ከእርሳቸውም ሥውር የሆነውን የመጻሕፍትን ቃል ይተረጉምላቸው ነበር በአንጾኪያ ላሉ መንጋዎቹም ይደርሳቸዋል አዋቂዎች የሆኑ ኤጲስቆጶሳትንና ቀሳውስትን ልዩ በሆነች ሦስትነት ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንቱ አባቶቻችን ያስተማሩዋት የቀናች ሃይማኖትን እንዲአስተምሩ ያዛቸዋል እንዲህም እያደረገ እስከ ዐረፈባት ቀን ድረስ በተሰደደበት ብዙ ዘመናት ኖረ።

ዮሐንስ አፈወርቅም አመስግኖታል የምስጋና ድርሰቶችንም ደረሰለት ስለ ቀናች ሃይማኖትም ብዙ መከራ ስለ ደረሰበት ክብሩና ግርማው ከከበሩ ሐዋርያት ክብር እንደማይጎድል ተናገረ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሐዋርያው_ቅዱስ_ያዕቆብ

በዚችም ዕለት ከ72ቱ አርድእት አንዱ የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ የጌታችን ወንድም የተባለ የአረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ ልጅ የሐዋርያ ቅዱስ ያዕቆብ መታሰቢያው ነው።

ይህም ቅዱስ የጠራቢው የዮሴፍ ልጅ ነው። እርሱም ከልጆቹ ሁሉ የሚያንስ ነበር። እርሱም ንጹሕ ድንግል ነበር ከጌታችንም ጋራ አደገ ስለዚህም ክብር ይግባውና የጌታችን ወንድም ተባለ። ከጌታችን ዕርገትም በኋላ ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ላይ ኤጲስቆጶስ አድርገው ሾሙት። ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አስተምሮ ብዙዎችን ወደ ቀናች ሃይማኖት መለሳቸው የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው።

እግዚአብሔርም በእጆቹ ታላላቅ ድንቆችንና ተአምራቶችን አደረገ። በአንዲት ዕለትም በጐዳና ሲጓዝ አንድ ሽማግሌ አገኘ። ቅዱስ ያዕቆብም ሽማግሌ ሆይ በቤትህ ታሳድረኛለህን አለው። አረጋዊውም እሺ እንዳልክ ይሁን አለ በአንድነትም ሲጓዙ ጋኔን ያደረበት ሰው አገኘው በአየውም ጊዜ የክርስቶስ ሐዋርያ ሆይ እኔ ካንተ ጋር ምን አለኝ ልታጠፋኝ መጣህን ብሎ ጮኸ ሐዋርያውም በናዝሬቱ ኢየሱስ ስም ተጠጋ ከሰውዬውም ውጣ አለው። ወዲያውም ያ ጋኔን ከሰውዬው ላይ ወጣ።

ያ ሽማግሌም ይህን ድንቅ ተአምር አይቶ ደነገጠ ከሐዋርያው እግር በታችም ወድቆ እንዲህ አለው። ወደ ቤቴ ልትገባ አይገባኝም ነገር ግን እድን ዘንድ ቤተሰቦቼም ሁሉ ይድኑ ዘንድ ምን ላድርግ አለ ያን ጊዜም ሐዋርያው አቤቱ ጌታዬ ሆይ መንገዴን አሳምረህልኛልና አመሰግንሃለሁ ብሎ ጌታችንን አመሰገነው። ወደ ሽማግሌውም ተመልሶ የድኅነትን ነገር ነገረው ክብር ይግባውና ስለ ጌታችን ሰው መሆን ስለ መከራው ስለ ሞቱና ስለ መነሣቱ አስተማረው።

ከዚህም በኋላ ያ ሽማግሌ ሐዋርያውን ወደ ቤቱ አስገባው ቤተሰቦቹም ሁሉ ወደርሱ ተሰበሰቡ ቅዱስ ያዕቆብም አስተምሮ የክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው። ሥጋውንና ደሙንም አቀበላቸው።

የከተማው ሰዎችም በሰሙ ጊዜ በሽተኞችን ሁሉ ወደርሱ አመጡ ሁሉንም አዳናቸው ለእነርሱም ሃይማኖትን አስተምሮ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸው፡፡ ቀሳውስትንና ዲያቆናትንም ሾመላቸው ያንን ሽማግሌም ኤጲስቆጶስ አድርጎ ሾመው ክብር ይግባውና የጌታችንንም ወንጌል ሰጣቸው ከዚህም በኋላ ያስተምር ዘንድ ወደ ሌሎች አገሮች ወጥቶ ሔደ።

አንዲት መካን ሴት ነበረች እግዚአብሔር ልጅን ይሰጣት ዘንድ ስለርሷ እንዲጸልይላት ቅዱስ ያዕቆብን ለመነችው። እርሱም ጸለየላትና ወንድ ልጅን ወለደች ስሙንም ያዕቆብ ብላ ጠራችው ልጅዋንም ተሸክማ ወደ ሐዋርያው መጥታ ሰላምታ አቀረበችለት ከልጅዋም ጋር ከእርሱ ተባረከች።

ከዚህም በኋላ በአንዲት ቀን ብዙዎች አይሁድ ወደርሱ ተሰበሰቡ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስም የማን ልጅ እንደሆነ ይነግራቸው ዘንድ ጠየቁት እነርሱ እርሱ ጌታን የዮሴፍ ልጅ እንደሆነ እርሱም ወንድሙ እንደሆነ እንደሚነግራቸው አስበው ነበርና።

ቅዱስ ያዕቆብም በሦስተኛ ደርብ ላይ ወጥቶ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነም ከአብ ጋራም ትክክል እንደሆነ ይገልጽላቸው ጀመረ። ይህንንም በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቄጡ ከደርቡ ላይ አውርደው የጸና ግርፋትን ገረፉት ከእነርሱም ውስጥ የልብስ ማጠቢያ የዕንጨት ገበታ የያዘ አንድ ሰው መጣ በዚያ ዕንጨትም ቅዱስ ያዕቆብን ራሱ ላይ መታው ያን ጊዜም ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።

ስለ እርሱም ወይን እንዳልጠጣ፣ ደም ካለው ወገን እንዳልበላ፣ በራሱም ላይ ምላጭ እንዳልወጣ፣ በውሽባ ቤት እንዳልታጠበ፣ ሁለት ልብስንም እንዳልለበሰ፣ ሁልጊዜም እንደሚቆምና እንደሚሰግድ ተጽፎአል። ከመቆም ብዛት የተነሣም እግሮቹ አብጠው ነበር፤ ከዚህም በኋላ አረፈና በቤተ መቅደሱ ጐን ቀበሩት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት)