ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ
800 subscribers
3.46K photos
104 videos
194 files
1.2K links
የየዕለቱ ስንክሳር እና ግጻዌ የሚቀርብበት ቻናል ነው፡፡

ለማንኛውም አስተያየት እና እርማት
@zetaodokos ላይ ይላኩልን።

👇👇የYoutube Channel ይቀላቀሉ👇👇
https://youtube.com/channel/UCupqpIYe_mMpSM7jMT3Njhw
Download Telegram
እንኳን ለጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓመታዊ የጽንሰት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

†††
#በዓለ_ጽንሰት †††

††† ይሕች ቀን ለቤተ ክርስቲያን በእጅጉ ልዩ ናት:: በዓመቱ ከሚከበሩ በዓላትም አንደኛውን ሥፍራ ትይዛለች::

በዚሕ ዕለት አምላካችን እግዚአብሔር:-

1.ሰማይና ምድርን ፈጠረ:: (ዘፍ. 1:1)

2.በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት በድንግል ማርያም ማኅፀን አደረ (ተጸነሰ):: በዓሉም "በዓለ ትስብእት" ይባላል:: "አምላክ ሰው : ሰው አምላክ የሆነበት" ማለት ነው:: (ሉቃ. 1:26)

3.የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ:: (ማቴ. 28:1፣ ማር. 16:1፣ ሉቃ. 24:1፣ ዮሐ. 20:1)

4.ጌታችን ዳግመኛ ለፍርድ በዚሕች ቀን ይመጣል:: (ማቴ. 24:1)

††† በነዚሕ ታላላቅና ድርብርብ በዓላት ምክንያት ቀኑ "ርዕሰ በዓላት" (የበዓላት ራስ) : "በኩረ በዓላት" እየተባለም ይጠራል::

††† ቸሩ እግዚአብሔር ዓለምን ከመፍጠሩ : ከጽንሰቱ : ልደቱና ትንሣኤው በረከትን ይክፈለን:: በጌትነቱም ሲመጣ በርሕራሔው ያስበን::

††† ዳግመኛ በዚህች ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እልዋሪቆን ገብቷል:: ይህች ሃገር የምድራችን መጨረሻ ናት:: ከዚያ በኋላ ሰውና ሃገር የለም:: እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን የሰበከ ሐዋርያ የለም::

††† ከቅዱሱ ሐዋርያ ትጋት : ቅናት : መንፈሳዊነትና ንጽሕና አምላካችን ይክፈለን::

††† መጋቢት 29 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት


1.ጥንተ ዕለተ ፍጥረት (ዓለም የተፈጠረችበት)
2.በዓለ ትስብእት (የጌታችን ጽንሰቱ)
3.ጥንተ በዓለ ትንሣኤ
4.ዳግም ምጽዐት
5.ቅድስት ማርያም መግደላዊት
6.ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ
7.ቅዱሳት አንስት (ትንሣኤውን የሰበኩ)
8.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ (ጽንሰታ)
9.አብርሃ ወአጽብሐ (ጽንሰታቸው)
10.ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ (ጽንሰቱ)
11.ቅዱስ ላሊበላ (ጽንሰቱ)
12.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ (ጽንሰታቸው)

††† ወርኀዊ በዓላት

1.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
2.ቅድስት አርሴማ ድንግል
3.ቅዱስ ጴጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
4.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
5.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)

††† "እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል:: ዓይንም ሁሉ: የወጉትም ያዩታል:: የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ:: አዎን አሜን::
ያለውና የነበረው: የሚመጣውም: ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ: አልፋና ኦሜጋ እኔ ነኝ ይላል::" †††
(ራእይ ፩፥፯)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ (🕊Dawit🕊)
#መጋቢት_29

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም

መጋቢት ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን #ለእመቤታችን_ለቅድስት_ድንግል_ማርያም #የከበረ_መልአክ_ገብርኤል የምሥራች የነገረበት ነው፣ ደግሞ #በመድኃኒታችን በከበረችና ልዩ በሆነች #ትንሣኤው የዓለም ድኅነት ሆነ፣ የከበረ #ሐዋርያ_ቅዱስ_ጳውሎስ የምድር ዳርቻ በሆነች አልዋሪቆን በምትባል አገር ደርሶ አስተማረ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#በዓለ_ወልድ (#የጌታችን_ጽንሰት)

መጋቢት ሃያ ዘጠኝ በዚህች ቀን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የከበረ መልአክ ገብርኤል የምሥራች የነገረበት ድኅነትን የተመላች ታላቅ በዓል ናት በዚህም የከበረ ወንጌል ምስክር ሁኗል እንዲህ ሲል፦ ኤልሳቤጥ ከፀነሰች በኋላ በስድተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል የገሊላ ክፍል የሆነች ናዝሬት ወደምትባል አገር ከዳዊት ወገን ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ።

የድንግሊቱም ስም ማርያም ነው። መልአኩም ወደርሷ ገብቶ ደስተኛ የሆንሽ ደስ ይበልሽ ጸጋን የተመላሽ ሆይ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋራ ነው አንቺ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ አላት። እርስዋም አይታ ከንግግሩ የተነሣ ደንግጣ እንዴት እንዲህ ያለ ሰላምታ ይቀበሏል ብላ አሰበች።

መልአኩም እንዲህ አላት ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ እርሱ ታላቅ ነው የልዑል እግዚአብሔር ልጅም ይባላል።

እግዚአብሔር አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል ለያዕቆብ ወገንም ለዘላለም ነግሦ ይኖራል ለመንግስቱም ፍጻሜ የለውም።

ማርያምም መልአኩን ወንድ ሳላውቅ ይህ እንደምን ይሆናል አለችው።መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት መንፈስ ቅዱስ መጥቶ ያድርብሻል የልዑል ኃይልም ያጸናሻል ከአንቺ የሚወለደው ከሶስቱ አካል አንዱ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ይባላል።

እነሆ ዘመድሽ ኤልሳቤጥም እርስዋ ደግሞ በእርጅናዋ ፀንሳለች ወንድልጅም አገኘች ለእርስዋም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና። ማርያምም እነሆኝ የእግዚአብሔር አገልጋይ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለችው።

ያን ጊዜም ድንግል ስትሆን ረቂቅ ፅንስን ተቀበለች የእግዚአብሔር አካላዊ ቃል ወልድ ዋህድ ለኩነተ ሥጋ ወርዶአልና ይህም አንድ ባሕርይ አንድ ህልውና ሲሆን ከሦስቱ አካላት አንዱ ነው ከዓለም መፈጠር አስቀድሞ የነበረ በማይመረመር ድንቅ በሆነ ተዋሕዶ እንዴትም እንደሆነ በማይታወቅ በቅድስት ድንግል ማርያም ማሕፀን አደረ ፅንስ ሆኖ ኖረ።

በዚያን ጊዜም የኋላ ኋላ መለየት ከቶ የሌለውን ፍጹም ሰውነት ነሥቶ ተዋሐደ መለኮቱ ከትስብእቱ ጋራ ያለ መለያየት አንድ ሆኖአልና። ይቺም ዕለት የበዓላት ሁሉ በኵር ናት በእርሷም የዓለም ድኅነት ተጀምሮዋልና።

ዳመኛም በዚህች እለት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽንሰት በተጨማሪ የቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ፣የቅዱሳን አብርሃ ወአጽብሐ፣ የቅዱስ ኢያሱ ነቢይ፣ የቅዱስ ላሊበላ፣ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጽንሰታቸው ታስቦ ይውላል፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#በዓለ_ትንሳኤ

በዚህችም ዕለት ደግሞ በመድኃኒታችን በከበረችና ልዩ በሆነች ትንሣኤው የዓለም ድኅነት ሆነ፡፡ በረቀቀ ጥበቡ ሠላሳ ሦስት ዓመት ያህል በምድር ላይ ሥራውን ሠርቶ በፈጸመ ጊዜ በፈቃዱ ሕማማተ መስቀልን ተቀብሎ ሙቶ ከተቀበረ በኋላ በሦስተኛው በዚች ቀን በሃያ ዘጠኝ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷልና።

በዚች ቀን አስቀድሞ ደጅ ለሚጠኑት በዓለም ላሉ ሰዎች ሰው በመሆኑ ድኅነታቸውን አበሠራቸው እንዲሁም ደግሞ በዚች ዕለት ከሲኦል በመዳን ሙታንና ሕያዋን ደስ አላቸው።

በዚህም በጌታችንና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መነሣት መነሣታቸውን አረጋገጡ። የከበረ ጳውሎስ በመነሣቱ ክርስቶስ የሙታን በኵር ሆነ እንዳለ እርሱ ለሙታን በኵራቸው ነውና።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሐዋርያ_ቅዱስ_ጳውሎስ

በዚህችም ቀን የከበረ ሐዋርያ ጳውሎስ አልዋሪቆን ከምትባል አገር ደርሶ አስተማረ ይቺም የምድር ዳርቻ ናት። ራሱ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ አለ ከዚያም በእግዚአብሔር መልአክ ትእዛዝ ወደ ዚያች አገር ሔድኩ ሀገሪቱም እንደ ሮሜ አማሳል ታላቅ የሆነች እጅግ ውብ ናት ፍሬዋም የበዛ ነው።

በውስጡ የሚታለፍበት ስሙ ገርጋ የሚባል ባሕር ግን አግድመቱ ሦስት መቶ ምዕራፍ ነው። መጋቢት ሃያ ሰባት ቀንም መጀመሪያ ከዚያ ከባሕሩ ዳርቻ ደረስኩ ለሀገሩም ሰዎች በዓላቸው ነበር የጽጌ ረዳ አክሊልም እየታቱ በጣዖቶቻቸው ራስ ላይ ያኖራሉ ከስንዴአቸውም አዲስ እሸትን ለጣዖቶቻቸው ያቀርባሉ።

የአገር ጠባቂ የሚሉትም በጠልሰም የተቀረጸ ሥዕል በአገሩ ቅጽር ላይ ተደርጓል ወደዚያች አገር የሚመጣ እንግዳ ሰው ሲያይ በላዩ ያደረ ርኵስ መንፈስ በታላቅ ድምፅ ይጮኻል። የአገር ሰዎችም የዚያን ጠልሰም ጩኸቱን በሚሰሙ ጊዜ ወደ አገራቸው የመጣውን እንግዳ ወጥተው ይገድሉታል ሕጋቸው እንዲህ ነውና ወደ አገራቸው ይገባ ዘንድ ማንንም አይተዉም አያሰናብቱም።

እኔም ወደዚያች አገር ደርሼ ወደ ባሕሩ በቀረብኩ ጊዜ ያ ጠልሰም እነሆ እንግዳ ወደ እናንተ ደረሰ ብሎ በአገራቸው ቋንቋ ጮኸ። የአገር ሰዎችም ድምፁን ሰምተው ከንጉሣቸው ጋራ ብዙ ሰራዊት መጡ በዚያን ጊዜ ስለ በዓላቸው ተሰበስበው ነበርና ፈለገኝ እኔ ግን በአየኋቸው ጊዜ ሸሽቼ የቀበሮዎችና የእሽኮኮዎች መሸሻ ወደ ሆነ ዋሻ ገባሁ። ከዚያም ገብቼ በረሀብና በጥም ስለተሠቃየሁ አለቀስኩ። በዚያን ቀን የፀሐይ ትኩሳት ከመጽናቱ የተነሣ ሐሩር ሆኖ ነበርና በዚያም እስከ ሌሊት ቆይቼ ከዚያ ወጥቼ ከባሕሩ ውኃ ጠጣሁ ቁሜም ወደ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስም ጸለይኩ።

ንጋትም በሆነ ጊዜ ከዚያ ዋሻ ወጥቼ ወደ አገር ለመግባት ፈለግሁ። ያ ጠልሰም አሁንም መምጣቴን እየገለጠ ሁለተኛ እንደታላቅ ነጐድጓድ ጮኸ ለባሕሩም ልማድ አለው ጠልሰሙ በሚጮኸ ጊዜ ይታወካል ማዕበሉም ይነሣል ያን ጊዜም ያገር ሰዎች ሊገድሉኝ መጡ።

ከሩቅ በአየኋቸውም ጊዜ ፈራሁ እንደቀድሞውም በዚያ ዋሻ ደግሜ ተሸሸግሁ ጌታ ክርስቶስንም እለምነው ዘንድ ጀመርኩ በአባት ጴጥሮስም ጸሎት የማፀንኩ በወንድሞቼ በሐዋርያትም ጸሎት። ይልቁንም ንጽሕት ድንግል በሆነች በብርሃን እናት በእመቤታችን ማርያም በአማላጅነቷ ተማፀንኩ በሌሊቱ ርዝመት ሁሉ ስጸልይ አደርኩ።

በነጋም ጊዜ ወደ ባሕሩ ዳር ወጣሁ ያም ጠልሰም እንደ ልማዱ ጮኸ ተራራዎችም እስቲናወጹ ጩኸቱን አበዛ የባሕሩም ማእበል ታወከ። ውኃውም እንደ ደም ሆነ የአገሩም ሰዎች ከሠራዊቶቻቸው ጋራ እንደ ቀድሞው ወጡ ባሕሩም መርከቦችን ተመላ እኔም ልሠወር ሮጥኩ።

በዚያን ጊዜም የብርሃን እናት እመቤታችን ድንግል ማርያምን በባሕሩ ላይ ቁማ አየኃት። ጳውሎስ ሆይ ወዴት ትሸሻለህ አምላክህ ክርስቶስ እንዲህ እንድትሸሽ አዘዘህን እርሱ ራሱ ሥጋችሁን የሚገድሉትን አትፍሩአቸው ነፍሳችሁን ግን መግደል አይችሉምና ያለ አይደለምን። አንተም በቦታህ ጸንተህ ቁም እኔም ከአንተ ጋራ አለሁ እጄንም ከአንተ አላርቅም በርታ ጠንክርም የዚችን አገር ሰዎች ሁሉንም በዚህ የባህር ውኃ እንደምታጠምቃቸው ዕወቅ በእጅህም አምነው ሙታን በሚነሡባት ዕለት ዕድላቸው ከአንተ ጋር ይሆናል ባሕሩም ቃልህን ሰምቶ ይታዘዝልሃል አለችኝ።
Forwarded from ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ (🕊Dawit🕊)
ምሕረትንና ርኅራኄን የተመላች እመቤቴ የብርሃን እናት ድንግል ማርያም ይህን ስትናገረኝ እነሆ በእጃቸው የጦር መሣሪያ የያዙ ኃይለኞች ሰዎችን የተሞሉ መርከቦችን በቅርብ አየኋቸው እጅግም ፈራሁ እመቤቴ ማርያምም ተሠወረችኝ። ነገር ግን ከደመና ውስጥ ጳውሎስ ሆይ ሰዎችን አጥምቅ ማጥመቅንም አታቋርጥ የሚለኝን ቃል እሰማ ነበር። እኔም በታላቅ ቃል ፈጣሪዬ ሆይ ይህን የባሕር ውኃ ለእሊህ ለተጣሉ በጎች ሰይጣንም ለማረካቸው ጥምቀትን አድርገው ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በዚህ ባህር ጥምቀት እሊህን ሰዎች በሦስትነትህ ስሞች የልጅነትን ክብር የሚቀበሉ አድርጋቸው በማለት አሰምቼ ተናገርኩ።

እንዲህም ይህን እያልኩ ከባሕሩ ውኃ ዘግኜ ሰዎች በአሉባቸው መርከቦች በላያቸው ረጨሁት የሰዎቹም ቁጥራቸው አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ነው። እኔ ወደአለሁበት የባሕር ዳር በደረሱ ጊዜ ከመርከባቸው ወጥተው ፈለጉኝ እኔም እመቤቴ የብርሃን እናት እንዳዘዘችኝ በፊታቸው ቆምኩ በረድኤቷ ተማምኛለሁና አልፈራሁም። በአዩኝም ጊዜ ሁሉም በፊቴ ሰገዱ በአንድ ቃልም ቅዱስ ጳውሎስ ሆይ ፍቅር አንድነት ለአንተ ይሁን ወደአንተ ከመድረሳችን በፊት በመርከቦች ውስጥ እያለን እኛ ያየነውን አየህን አሉኝ።

እኔም አዲስ የተወለዳችሁ ልጆች ሆይ ምን አያችሁ አልኋቸው የሰማይ ደጆች ተከፍተው የቀኝ እጅ እንደ እሳት ነበልባል ተዘርግታ አየን ደግሞ የፊቷ ብርሃን ከፀሐይ ሰባት እጅ የሚበራ ሴት አየን። እርሷም ከደመና በታች የምትረጨውን ውኃ ተቀብላ በላያችን ትረጨዋለች ትስመናለች ታቅፈናለችም። በራሲቻችንም ላይ የብርሃን አክሊሎችን ታደርጋለች አሉኝ። ይህንንም በሰማሁ ጊዜ ፈጽሞ ደስ አለኝ በስሙ በምንሠራው ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንዳለ ተረዳሁ።

ከዚህም በኋላ ሌሎች መርከቦች መጡ ኃይለኞች ሰዎችን ከጦር መሣሪያ ጋር የተመሉ ናቸው እንዲህም እያሉ ዛቱበኝ። አንተ ሥራየኛ ጥበበኞች ሕርምስና በለንዮስ ታምራት የሚያደርጉባቸው የጠልሰም መጻሕፍቶች ከእኛ ጋራ እንዳሉ ዕወቅ በማለት እኔም ቸር ፈጣሪዬ ሆይ የቀደሙትን በጎች ይቅር እንዳልካቸውና በውስጣቸው ኃይልህን እንደገለጥክ ለእነዚህም እንዲሁ ኃይልህን ግለጥ ይቅርም በላቸው አልኩ።

ከዚያም በኋላ ከባሕሩ ውኃ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥምቀትን ይሁናችሁ አልኩ ወዲያውኑ መርከቦች ከባሕሩ ዳር ደረሱ። ሁሉም ሰዎች ከመርከብ ወጥተው በፊቴ ሰገዱ የቸር አምላክ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሆይ እናመሰግንሃለን አሉኝ።

ይህንንም ድንቅ ተአምር ከቀደሙት ባልንጀሮቻቸው ጋራ ተነጋገሩ ዜናዬም በዚያች አገር ንጉሥ ዘንድ ተሰማ እርሱም ከሰራዊቱ ጋር ተነሳ በመርከቦችም ተጭነው ወደእኔ መጡ። እኔም ዐይኖቼን ወደ ሰማይ አቅንቼ የፈጣሪዬን ስም ጠራሁ ባሕርዋንም በመስቀል ምልክት አማተብኩባት። እንዲህም አልኳት አንቺ ባሕር በእግዚአብሔር ልጅ በጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ትከፈዪ ዘንድ አዝሻለሁ ምድሩም ይገለጥ መርከቦችም በየብስ ውስጥ ይቁሙ።

ነገሬንም ሳልጨርስ ባሕርዋ ተከፈለች በውስጥዋም ዐሥራ ሦስት ጎዳናዎች ተገለጡ መርከቦቹም ውኃ በሌለው ምድር ላይ ቆሙ ይህንንም አይተው ሰይፎቻቸውን መዘዙ ዕንጨቶችም ሆነው አገኙአቸው እኔም ከሕህሩ ውኃ ዘግኜ በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እያልኩ በላያቸው ረጨሁ። በዚያን ጊዜ እሊያ መርከቦች ነፋስ ተሸክሟቸው ያለ ውኃ ከምድር ከፍ ከፍ ብለው ተጓዙ ሰዎችም ከውስጣቸው ወጥተው ወደእኔ መጥተው ሰገዱ። ከእነሱም የቀደሙ ሰዎች ሰላምታ እንዳቀረቡልኝ ንጉሡም ከሀገር ሰዎች ሁሉ ጋር በፊቴ ሰገደ።

ከዚያም በኋላ ከእርሳቸው ጋር ወሰዱኝ ወደ ከተማውም በደረቅ ያለ መርከብ ገባን በምኵራባቸውም ውስጥ በጽጌ ረዳ አክሊል ጣዖቶቻቸው ተከልለው የሥንዴ እሸትም እንደ መስዋዕት ሆኖ ተጥሎ አየሁ ይህንንም አይቼ እጅግ አዘንኩ።

የአገር ሰዎችም ክብር መምህር ሆይ በዚች ዕለት ለአማልክት በዓል የምናደርግበት እንደ ነበረ ዕወቅ አሁን አንተ ለማን ታዝናለህ ለአብ እንድርገውን ወይም በወልድ ስም ወይም በመንፈስ ቅዱስ ስም በስማቸው ያጠመቅከን ስለሆነ አሉኝ። እኔም እግዚአብሔርን ያመልኩት ዘንድ የሚገባቸውን ሃይማኖትን አስተማርኳቸው መጻሕፍትንም በእጄ ጻፍኩላቸው።

በአማላጅነቷ ከርኵስ ሰይጣን ተገዥነት ስለዳኑ ያንን በዓል የብርሃን እናት በሆነች በእመቤታችን በድንግል ማርያም ስም እንዲያደርጉት አዘዝኋቸው ዕለቱም የእግዚአብሔርን ልጅ እንደምትፀንሰውና በሥጋ እንደመትወልደው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ያበሠረበት ስለሆነ።

እኔም አምላካዊ ትምርትን አስተማርኳቸው በቀናች ሃይማኖትም እንዲጸኑ አደረግኋቸው ውኃው በተከፈለበትም ላይ በእመቤታችን በድንግል ማርያም ስም ታላቅ ቤተ ክርስቲያን እንዲሰሩ አዘዝኳቸው። በክብር ባለቤት በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድንቆች የሆኑ ብዙ ተአምራቶችንም አደረኩላቸው ከዚያ በኋላ ከእነርሱ ዘንድ ወጥቼ መጣሁ።

ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መጋቢት)
Forwarded from ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ (🕊Dawit🕊)
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ዻውሎስ
መጋቢት29
{ለስብከት . . . የምድር መጨረሻ ናት ወደሚባልላት ሃገረ እልዋሪቆን ገብቷል::
በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችንም አሳምኖ : አጥምቆ : በድንግል ማርያም ስም ደብር አንጾላቸዋል::}

<< ከበረከቱ : ከክብሩ ይክፈለን !! >>
#ደብረ_ዘይት
(የዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት)

የዐቢይ ጾም የአምስተኛው ሳምንት ደብረ ዘይት ይባላል፡፡ ጌታ በደብረ ዘይት የዳግም ምጽአቱን ነገር ማስተማሩ ይነገርበታል፡፡ ደብረዘይት የስሙ ትርጓሜ የዘይት ተራራ ማለት ነው ስያሜ የተሰጠው በቦታው ብዙ ወይራ ተክል ይበቅልበት ስለ ነበር ነው፡፡
እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀመዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድን ነው?›› አሉት (ማቴ. 24፥3፣  ዘካ. 14፥5 ፤ ሐዋ. 1፥11 ፤ 1ኛ ተሰ. 4፥16 ፤ ራዕ. 22፥7)

#አመጣጡስ_እንዴት_ነው?

ጌታ ይህንን ዓለም ለማሳለፍ ለሁሉም እንደ ሥራው ለመክፈል በግርማ መለኮቱ በክበብ ትስብዕቱ ይመጣል፡፡ ጊዜው ዘመነ ዮሐንስ ወርሃ መጋቢት ዕለት እሑድ መንፈቀ ሌሊት እንደሆነ ሊቃውንት ተናግረዋል፡፡ ምነው የሚያውቀው የለም ይባል የለምን? ቢሉ እውነት ነው የሚያውቀው የለም ብዙ የዮሐንስ ዘመን፤ ብዙ የመጋቢት ወር፤ ብዙ የእሑድ ዕለት አለና ለይቶ የሚያውቅ የለም፡፡ ሞት ለማንም አይቀርምና ሁሉም ይሞታል፡፡ ዘፍ. 3፥19 በዕለተ ምጽአት ቅዱስ ገብርኤል ስምንቱን ነፋሳተ መዓት ከየመዛግብታቸው ያወጣቸዋል፡፡ ዛፏን ነቅለው ደንጊያውን ፈንቅለው ምድርን እንደ ብራና ይዳምጧታል፡፡ ቅዱስ ሚካኤል መለከት ይነፋል፡፡ 1ኛ መቃ. 9፥8 ቅዱስ እግዚአብሔር ዘያነቅሖሙ ለሙታን ሲል በዱር በገደል በባሕር በየብስ በመቃብር ውስጥ ያሉት በአውሬ ሆድ ውስጥ ያሉ ሁሉ ይሰበሰባሉ፡፡ በሁለተኛው ነጋሪት ሲመታ አጥንትና ሥጋ አንድ ሆነው ፍጹም በድን ይሆናሉ፡፡ ሦስተኛው ነጋሪቱን መቶ (ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት) ንቃሕ መዋቲ ዘትነውም ባለ ጊዜ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ደጉ ደግነቱን ክፉውም ክፋቱን ይዞ ይነሳል፡፡    

ወንዱ የ30 ዓመት ሴቲቱ የ15 ዓመት ሆነው ጻድቃን ብርሃን ለብሰው ብርሃን ተጎናጽፈው ከፀሐይ 7 እጅ አብርተው ማቴ.13፥43 ኃጥአን ጨለማ ለብሰው ፍጹም ዲያቢሎስን መስለው ይነሳሉ፡፡ ጻድቃን ስለሠሩት መልካም ሥራ ኑ የአባቴ ቡሩካን ብሎ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳቸዋል፡፡ ኃጥአንን ስለ ክፉ ሥራቸው (ከኔ ሂዱ) ገሃነም ይሰዳቸዋል፡፡ ጻድቃን ደስ ይላቸዋል ኃጥአን ግን ያዝናሉ፤ ዋይ ዋይ ይላሉ፤ ደረት ይደቃሉ እንባቸው ያፈሳሉ፡፡ የማይጠቅም ለቅሶ የማይጠቅም ሐዘን ሰቅለው የገደሉትም አይሁድ ክብሩን አይተው ላይጠቀሙ ይጸጸታሉ፡፡    

#ምልክቱስ_ምንድን_ነው? ብለው ጌታን ሲጠይቁ ‹‹ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፡- ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ አትደንግጡ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው፡፡ ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሳል፤ ረሃብም ቸነፈርም መናወጥም በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል ይገድሉአችሁማል፤ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ›› አላቸው፡፡ በዳግም ምጽአቱ ጊዜ ከቅዱሳኑና ከሰማዕታቱ ጋር ለመቆም ያብቃን፡፡

#የዕለተ_ሰንበት_መዝሙር_ከጾመ_ድጓ
እንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ወይቤሎሙ ለአርዳኢሁ ዑቁኬ ኢያስሕቱክሙ ወንበሩ ድልዋኒክሙ ብዙኃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ ወዘአዝለፈ ትዕግሥቶ ውእቱ ይድኅን ወአመ ምጽአቱሰ....
(ጌታችን በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ ተዘጋጅታችሁም ኑሩ፤ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ እስከ መጨረሻው የጸና እርሱ ይድናል፡፡....)

#የዕለቱ_ምንባባት
1ኛ ተሰሎንቄ 4÷13-ፍጻ፡-
ወንድሞቻችን ሆይ÷ ስለ ሞቱ ሰዎች÷ ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች እንዳታዝኑ ልታውቁ እንወዳለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ እንደ ተነሣ ካመንን እንዲሁ እግዚአብሔር ሙታንን በኢየሱስ ያስነሣቸዋል ከእርሱም ጋር ያመጣቸዋል፡፡.....

2ኛ ጴጥ.3÷7-14፡-
አሁንም ሰማይና ምድር በዚያ ቃል ለእሳት ተዘጋጅተዋል፤ ኃጥኣን ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀንም ተጠብቀዋል፡፡ነገር ግን ወንድሞቻችን ሆይ÷ ይህን አትርሱ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ አንዲት ቀን እንደ አንድ ሺህ ዓመት÷ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን ነውና፡፡.....

ሐዋ. 24÷1-21፡-
በአምስተኛውም ቀን ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከመምህራኑና ጠርጠሉስ ከሚባል አንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ ጳውሎስንም በአገረ ገዢው ዘንድ ከሰሱት፡፡..... (ተጨማሪ ያንብቡ)

#የዕለቱ_ምስባክ
መዝ. 49÷2
እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽእ
ወአምላክነሂ ኢያረምም
እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፡፡
ትርጉም፦
እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል፡፡
አምላካችንም ዝም እይልም፤
እሳት በፊቱ ይነድዳል በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ፡፡

#የዕለቱ_ወንጌል
ማቴ. 24÷1-25፡-
ጌታችን ኢየሱስም ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው የቤተ መቅደሱን የሕንጻ አሠራር አሳዩት፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም፡፡.....” (ተጨማሪ ያንብቡ)

#የዕለቱ_ቅዳሴ፦ ቅዳሴ አትናቴዎስ

ምንጭ፡-
(የማቴዎስ ወንጌል 24፥1 ትርጓሜ፣ መዝገበ ታሪክ ቁጥር 2፣ ግጻዌ)
🕊🕊🕊🕊🕊🕊🕊🕊🕊🕊🕊🕊

        🕐 ​መጋቢት 30/07/2016 ዓ.ም🕖
 
   በዕለቱ ቅዳሴ ሰዓት የሚነበቡ
   መልዕክታት፣ወንጌልና ምስባክ

ዘነግህ
📖ምስባክ
መዝ ፻፭፥፲፪(105፥12)
ወተአመኑ በቃሉ
ወሰብሕዎ በስብሐቲሁ
ወአፍጠኑ ረሲዐ ምግባሩ

📖ወንጌል
ወንጌል ዘማርቆስ ፲፮፥፲፪-፲፭(16፥12-15)
ወእምዝ አስተርአዮሙ ለ፪ቱ...

ምንባባት ዘቅዳሴ

           👉  ዲያቆን
📖ኀበ ሰብእ ዕብራውያን ፲፩፥፴፪-፴፭(11፥32-35)
ምንተ እንከ እብል…

            👉ንፍቅ ዲያቆን
📖ጴጥሮስ ፪ ም ፫፥፫-፮(3÷3-6)
ወዘንተኒ ቅድሙ አእምሮ…

             👉ንፍቅ ካህን
📖ግብረሐዋርያት ፲፪፥፮-፲፰(12÷6-18)
ወበይእቲ ሌሊት እንተ ጸቢሖ…

            📜ምስባክ ዘቅዳሴ

በቅድመ መላእክቲከ እዜምር ለከ
ወእሰግድ ውስተ ጽርሐ መቅደስከ
ወእገኒ ለስምከ

               👉ትርጉም

መዝሙረ ዳዊት ም. ፻፴፯ ቊ. ፩ - ፪

፩ አቤቱ፥ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፥ የአፌን ነገር ሁሉ ሰምተኸኛልና፤ በመላእክት ፊት እዘምርልሃለሁ።

፪ በቤተ መቅደስህም እሰግዳለሁ፤ ስለ ምሕረትህና ስለ እውነትህም ስምህን አመሰግናለሁ፥ በሁሉ ላይ ቅዱስ ስምህን ከፍ ከፍ አድርገሃልና።


         

            📜ወንጌል ዘቅዳሴ

የሉቃስ ወንጌል ም. ፩ ቊ. ፳፮ - ፴፱
ወበሳድስ ወርኅ ተፈነወ...

        📜ቅዳሴ


👉ግሩም አው ዘእግዝእትነ


☘️ ☘️☘️☘️☘️☘️☘️☘️☘️☘️☘️
† እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ሶምሶን (መስፍነ እስራኤል) ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

†††# ቅዱስ_ገብርኤል †††


††† ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል:-

*ከ7ቱ ሊቃናት አንዱ::
*በራማ አርባብ በሚባሉ 10 ነገደ መላእክት ላይ የተሾመ::
*በመጀመሪያዋ የፍጥረት ቀን መላእክትን ያጸና::
*ቅዱሳንን ሁሉ የሚረዳ::
*ሠለስቱ ደቂቅን : ዳንኤልን : ሶስናን ከሞት የታደገ ታላቅ መልዐክ ነው::

ከምንም በላይ ግን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዱሱን መልዐክ "መጋቤ-ሐዲስ" ብላ ታከብረዋለች:: ቅዱስ ገብርኤል የስሙ ትርጉዋሜ "አምላክ ወሰብእ - እግዚእ ወገብር" ነውና ለሥነ ፍጥረት ሁሉ የሚሆን ሐዲስ ዜናን ወደ እመቤታችን ድንግል ማርያም አምጥቷል::

መልዐኩ እመቤታችንን ከመጸነሷ ጀምሮ ባይለያትም መጋቢት 29 ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ አብስሯታል:: ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በማግስቱ በድምቀት እንዲከበር በወሰኑት መሠረት ዛሬ (በ30) ይከበራል::

††† #ሶምሶን_ረዓይታዊ †††

†††  እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን: ሀያ ሁለቱን ሥነ ፍጥረትን ፈጥሮ አዳምን ገዢ አደረገው:: አክሎም በነፍስ ሕያው አድርጐ: በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ: ነቢይና ካህን አድርጐ: ካንዲት ዕፀ በለስ በቀር በፍጥረት ሁሉ ላይ አሰለጠነው::

አባታችን አዳም ግን ስህተት አግኝቶት ከገነት ወጣ:: መከራና ፍዳም አገኘው:: በኋላም ለ100 ዓመት አልቅሶ ንስሃ ገባ:: ጌታም ንስሃውን ተቀብሎ "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ተስፋ ድህነትን ሰጠው::

ስለዚህም ምክንያት ለ5,500 ዓመታት ትንቢት ሲነገር: ሱባኤ ወደ ታች ሲቆጠር: ምሳሌም ሲመሰል ኖረ:: ከደግ ፍጥረት አዳም እስከ ኖኅ ድረስ: የሴት ልጆች እግዚአብሔርን በንጽሕና ሁነው በደብር ቅዱስ አመለኩ::

ትንሽ ቆይተው ግን ስለተቀላቀሉ ከቃየን ልጆች ጋር በማየ ድምሳሴ ጠፉ:: በጻድቅ ሰው ኖኅ የተጀመረው ትውልድም እግዚአብሔርን ለመዘንጋት ጊዜ አልፈጀበትም:: ነገር ግን ከሴም ዘር ቅንና ጻድቅ ሰው አብርሃም ተገኘ::

ከእርሱም ይስሐቅ: ከዚያም ያዕቆብ (ደጋጉ) ተገኙ:: ያዕቆብም "እሥራኤል" ተብሎ: በልጆቹ "ሕዝበ እግዚአብሔር" የተባለ ነገድ ተመሠረተ:: በተስፋይቱ ምድር በከነዓን እንዳይኖሩም ርሃብ ምድረ ግብጽ አወረዳቸው::

በዚያም ለ215 ዓመታት በጭንቅ የባርነትን ሕይወትን አሳለፉ:: እግዚአብሔርም ስለ ወዳጁ አብርሃም ሲል እሥራኤልን አሰባቸው:: የዋሕና ጻድቅ ሰው ሙሴን አስነስቶ እሥራኤልን ከግብጽ ባርነት አዳናቸው::

ይኸውም በጸናች እጅ: በበረታችም ክንድ: በ9 መቅሰፍት: በ10ኛ ሞተ በኩር: በ11ኛ ስጥመት ግብጻውያንን አጥፍቶ ነው:: በየመንገዱም ጠላቶቻቸውን እየተበቀለላቸው ነው:: ከዚህ ዘመን ጀምሮም እሥራኤል በመሳፍንትና በካህናት የሚተዳደሩ ሆኑ::

አስቀድሞ ሙሴ በምስፍና: አሮን በክህነት መሯቸው:: ቀጥሎም በቅዱስ ሙሴ ኢያሱ: በአሮን አልዓዛር ተተኩ:: እንዲህ እንዲህ እያለም ከኃያል ሰው ሶምሶን ረዓይታዊ ደረሱ:: ይኸውም ከዓለም ፍጥረት 4,200 ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው::

በጊዜው እሥራኤል ጣዖትን እያመለኩ እግዚአብሔርን ስላሳዘኑት ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር:: የአካባቢው መንግስታት እነ አሞን: አማሌቅ: ኢሎፍሊ ስንኳ ያኔ ዛሬም ቢሆን እንደምትመለከቱት ዶሮና ጥሬ ናቸው::

በጊዜውም የእሥራኤል ኃጢአት ስለ በዛ ኢሎፍላውያን (ፍልስጤማውያን) 40 ዓመት በባርነት ገዟቸው:: ንስሃ ሲገቡ ደግሞ ልጅ በማጣት ያዘኑ ማኑሄ እና ሚስቱ (እንትኩይ) : በቅዱስ ሚካኤል ተበሥረው ኃያሉን ሶምሶንን ወለዱላቸው::

እርሱም ናዝራዊ (ከእናቱ ማኅጸን ለጌታ የተለየ) ነበርና ፍልስጤማውያንን ቀጥቶ ወገኖቹን እስራኤልን ከባርነት : በአምላኩ ኃይል ታደገ:: ከኃይሉ ብዛት የተነሳም:-
¤አንበሳን እንደ ጠቦት ይገድል (መሣ. 14:5)
¤300 ቀበሮዎችን አባሮ ይይዝ (መሣ. 15:3)
¤በብርቱ ገመዶች ሲያስሩት እንደ ፈትል ይበጣጥሰው (መሣ. 15:14)
¤በአህያ መንጋጋ ሽህ ሰው ይገድል (መሣ. 15:15)
¤ጠባቂዎችን ከነ መቃናቸው ተሸክሞ ይወረውር ነበር:: (መሣ. 16:3)

ውኃ ሲጠማውም ከአህያ መንጋጋ ላይ ፈልቆለት ጠጥቷል:: (መሣ. 15:18) በፍጻሜው ግን ደሊላ በምትባል ሴት ተታልሎ ምሥጢሩን በመግለጡና ጸጉሩ በመላጨቱ ኃይሉን አጥቷል:: ጠላቶቹም ዐይኑን አውጥተው መዘባበቻ አድርገውታል::

በፍጻሜው ግን ኃይሉ እንዲመለስለት ፈጣሪውን ለምኖ : አሕዛብ ለጣኦት በዓል እንደተሰበሰቡ የአዳራሹን ምሰሶ አፍርሶ አጥፍቷቸው ዐርፏል:: (መሣ. 13--16)
ቅዱስ ሶምሶን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥላ (ምሳሌ) ነው::

†††  "ክፉ ናችሁ: ኃጢአታችሁ በዝቷል" የማይል ጌታ በመከራችን ሁሉ ተራዳኢ መልዐክን (ቅዱስ ገብርኤልን) ይዘዝልን:: ወርኀ መጋቢትን በሰላም እንዳስፈጸመ ወርኀ ሚያዝያን በምሕረቱ ይባርክልን::

††† መጋቢት 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት


1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት (እመቤታችንን ያበሠረበት መታሠቢያ)
2.ቅዱስ ሶምሶን (መስፍነ እስራኤል)
3.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ (ፍልሠቱ)
4.ቅዱስ ዮሐንስ ዘአክሱም (ድርሳነ ሚካኤልን መጻፉ የሚነገርለት አባት)
5.እግዚአብሔር ውሃን ከ3 ከፈለው (ጠፈርን ፈጠረ)

††† ወርኀዊ በዓላት

1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ (ሐዋርያ)
3.አባ ሣሉሲ ክቡር
4.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
5.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት

††† ". . . በአምላኬም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ተቀደሰው ስለ አምላኬ ተራራ ስለምን: ገናም በጸሎት ስናገር አስቀድሜ በራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ:: በማታም መሥዋዕት ጊዜ ዳሰሰኝ:: አስተማረኝም . . ." †††
(ዳን. 9፥20)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ (🕊Dawit🕊)
የሥነ ፍጥረት ፪ኛ ቀን

=>ቸሩ እግዚአብሔር በዚህች ቀን ውሃን ከ፫ ከፈለ፤ ጠፈርንም ፈጠረ፡፡ (ዘፍ. ፩፤ አክሲማሮስ)

" ቸርነቱ ፈጥኖ ይደረግልንና!


" ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"::/የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ) እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::  አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ /መጽሐፈ ምሥጢር/
Audio
"ስለእግዚአብሔር ፍቅር ስንል መጥፎ ጠባያችንን ልንለውጥ ይገባናል"
††† እንኳን ከተባረከ ወር ሚያዝያ እና ከሰማዕቱ አባታችን ቅዱስ ክርስቶፎሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

†††
#ቅዱስ_ክርስቶፎሮስ †††

††† ክርስቶፎሮስ ትርጉሙ "ለባሴ ክርስቶስ" እንደ መሆኑ በሐዋርያት ዘመን የነበሩ ብዙ ቅዱሳን በዚህ ስም ይጠሩ ነበር:: ከነዚህ አንዱ ቅዱስ ክርስቶፎሮስ ሃገሩ በላዕተ ሰብእ (ሰውን የሚበሉ) ውስጥ ነበር::

ይህች ሃገር አሁን የት እንዳለች በውል ባይታወቅም የቅዱስ ማትያስ ሃገረ ስብከት በመሆኗ አውሮፓና እስያ ድንበር አካባቢ እንደሆነች ይገመታል::

የአካባቢው ሰዎች ከሰው ሥጋ ውጪ እህልን አይቀምሱም ነበር:: ቅዱስ ማትያስ በነርሱ ያደረውን ርኩስ መንፈስ አስወጥቶ አሳምኗቸዋል::

ከሃገሩ ሰዎችም አንዳንዱ ገጻተ ከለባት (የውሻ መልክ ያላቸው) ነበሩ:: ክርስቶፎሮስም ከነርሱ አንዱ ነበር:: በክርስቶስ አምኖ ከተጠመቀ በሁዋላ በስብከቱ ብዙዎችን አሳምኖ : ስለ ሃይማኖትም ብዙ ጸዋትወ መከራ ተቀብሎ በዚህች ቀን በሰማዕትነት አርፏል::

††† ከሰማዕቱ በረከት አምላኩ ያድለን::

††† ሚያዝያ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት


1.ቅዱስ ክርስቶፎሮስ (ሐዋርያና ሰማዕት)
2.አባ ስምዖን ዘሃገረ ሐሊባ
3.ቅዱስ መላልኤል (የያሬድ አባት - ከአዳም 5ኛ ትውልድ)
4.እግዚአብሔር ፀሐይን : ጨረቃን : ከዋክብትን ፈጠረ

††† ወርኀዊ በዓላት

1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
4.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
5.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
6.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
7.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

††† "ስለዚሕ ወንድሞቼ ሆይ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ:: ልባሞች እንደመሆናችሁ እላለሁ:: በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ:: የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? . . . እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን:: ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና::" †††
(1ቆሮ. 10፥14-18)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††