ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ
854 subscribers
3.46K photos
103 videos
194 files
1.2K links
የየዕለቱ ስንክሳር እና ግጻዌ የሚቀርብበት ቻናል ነው፡፡

ለማንኛውም አስተያየት እና እርማት
@zetaodokos ላይ ይላኩልን።

👇👇የYoutube Channel ይቀላቀሉ👇👇
https://youtube.com/channel/UCupqpIYe_mMpSM7jMT3Njhw
Download Telegram
† እንኳን ለታላቁ ነቢይና ጻድቅ ቅዱስ ዳንኤል ዓመታዊ በዓለ ዕረፍት በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ
ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

†††
#ቅዱስ_ዳንኤል †††

††† ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር): መጻዕያትን (ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::

ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: (ሐዋ. 11:27) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ::

ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: (ቅዳሴ ማርያም)

የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::

ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: (ዮሐ. 4:36)

ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ" እንዳለ ጌታ በወንጌል:: (ማቴ. 13:16, 1ጴጥ. 1:10) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::

††† ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት: አራቱ ዐበይት ነቢያት: አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትና ካልአን ነቢያት ተብለው በአራት ይከፈላሉ::

††† "አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት" ማለት:-
*ቅዱስ አዳም አባታችን
*ሴት
*ሔኖስ
*ቃይናን
*መላልኤል
*ያሬድ
*ኄኖክ
*ማቱሳላ
*ላሜሕ
*ኖኅ
*አብርሃም
*ይስሐቅ
*ያዕቆብ
*ሙሴና
*ሳሙኤል ናቸው::

††† "አራቱ ዐበይት ነቢያት"
*ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
*ቅዱስ ኤርምያስ
*ቅዱስ ሕዝቅኤልና
*ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::

††† "አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት"
*ቅዱስ ሆሴዕ
*አሞጽ
*ሚክያስ
*ዮናስ
*ናሆም
*አብድዩ
*ሶፎንያስ
*ሐጌ
*ኢዩኤል
*ዕንባቆም
*ዘካርያስና
*ሚልክያስ ናቸው::

††† "ካልአን ነቢያት" ደግሞ:-
*እነ ኢያሱ
*ሶምሶን
*ዮፍታሔ
*ጌዴዎን
*ዳዊት
*ሰሎሞን
*ኤልያስና
*ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው::

††† ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::
*የይሁዳ (ኢየሩሳሌም):
*የሰማርያ (እሥራኤል)ና
*የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ::

††† በዘመን አከፋፈል ደግሞ:-
*ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት):
*ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)
*ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት):
*ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ::
ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳንኤል ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ600 ዓመታት አካባቢ ከይሁዳ ነገሥታት ዘር ተወለደ:: ገና በሕፃንነቱ ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ : ሕዝቡን ማርኮ ወደ ባቢሎን ሲያወርዳቸው አብሮ ወርዷል::

ከሕፃንነቱ ጀምሮ በአምላኩ ፍቅር የታሠረ : ከሦስቱ ጓደኞቹ (አናንያ : አዛርያና ሚሳኤል) ጋር ጾምና ጸሎትን ያዘወትር ነበር:: በዘመኑ እንደርሱ ያለ መተርጉመ-ሕልም አልተገኘምና ለወገኖቹ ሞገሳቸው ነበር::

ኃይለኛውን ንጉሥ ናቡከደነጾርን ጨምሮ የባቢሎንና ፋርስ ነገሥታት ያከብሩት : ይወዱትም ነበር::

ቅዱስ ዳንኤል በጥበብና በሃይማኖት የአሕዛብን አማልክት ድል ነስቷል:: አሕዛብ በተንኮል ወደ አናብስት ጉድጓድ ውስጥ ቢያስጥሉት እግዚአብሔር የአናብስቱን አፍ ዘግቷል:: ዕንባቆምንም አምጥቶ መግቦታል::

ቅዱስ ዳንኤል የብሉይ ኪዳኑ "አቡቀለምሲስ" ይባላል:: ስለ ጌታችን የማዳን ሥራና ስለ ዳግም ምጽዐቱ በግልጥ ተናግሯል:: ሐረገ ትንቢቱም 12 ምዕራፍ ነው:: የዘመኑ አይሁድ ክርስቶስ ገና አልተወለደም ለማለት ዳንኤልን ጠልተውታል::

ታላቁ ነቢይና ጻድቅ ቅዱስ ዳንኤል እስራኤል ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ አብሯቸው አልመጣም:: ከ70 ዓመታት በላይ በጸጋ ትንቢት ኑሮ እዛው ባቢሎን ውስጥ አርፏል::

††† ፈጣሪ ከበረከቱ ለሁላችን ያድለን::

††† በዚህች ቀን ክፉዎች አይሁድ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይገድሉ ዘንድ በቤተ ቀያፋ መከሩ::

††† እርሱ ቸሩ አምላክ ከክፉ መካሪዎች ይሠውረን::

††† መጋቢት 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት


1.ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳንኤል (የስሙ ትርጓሜ- እግዚአብሔር ፈራጅ ነው ማለት ነው::)

††† ወርኀዊ በዓላት

1.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
2.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
3.ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እስራኤል
4.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
5.አባ ሳሙኤል
6.አባ ስምዖን
7.አባ ገብርኤል

††† "የዚያን ጊዜም ንጉሡ አዘዘ:: ዳንኤልንም አምጥተው በአንበሶች ጉድጓድ ጣሉት . . . ድንጋይም አምጥተው በጉድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙት . . . በነጋውም ንጉሡ ማልዶ ተነሳ . . . ወደ ዳንኤል በቀረበ ጊዜ በኀዘን ቃል ጠራው . . . ዳንኤልም ንጉሡን . . . በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና . . . አምላኬ መልዐኩን ልኮ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ:: አንዳችም አልጐዱኝም አለው . . . ዳንኤልም ከጉድጓድ ወጣ:: በአምላኩም ታምኖ ነበርና አንዳች ጉዳት አልተገኘበትም::" ††† (ዳን. ፮፥፲፮-፳፫)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from 🕊ኢዮአታም🕊
የምታዩት ቦታ #ሱሳ (Susa) የሚባል ሲሆን የታላቁ ነቢይ #ቅዱስ_ዳንኤል መቃብር እንደ ሆነ ይታመናል:: የሚገኘው ደግሞ #ኢራን (Iran) ውስጥ ነው:: የነቢዩ ዕረፍት ምሥጢር ነው::

<< ምናልባት ግን ሊቁ በመልክአ ኢየሱስ "ለኩርናዕከ" ላይ:-
"ኢየሱስ ክርስቶስ ሞገሰ ዳንኤል ነቢየ ሱሳ" (የሱሳ ነቢይ የዳንኤል ሞገሱ አንተ ኢየሱስ ክርስቶስ ነህ) ያለው ይህንን ሊነግረን ይሆን? >>

<< መድኃኒታችን ከታላቁ ነቢይ በረከቱን ያሳትፈን !! >>