ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ
802 subscribers
3.46K photos
104 videos
194 files
1.2K links
የየዕለቱ ስንክሳር እና ግጻዌ የሚቀርብበት ቻናል ነው፡፡

ለማንኛውም አስተያየት እና እርማት
@zetaodokos ላይ ይላኩልን።

👇👇የYoutube Channel ይቀላቀሉ👇👇
https://youtube.com/channel/UCupqpIYe_mMpSM7jMT3Njhw
Download Telegram
=>+"+ እንኩዋን ለእግዚእ ዓለም #ሥላሴ እና ለቅዱሳን
አበው #አብርሃም: #አባ_ሲኖዳ እና #አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋሥጫ
ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+

+"+ #ሥሉስ_ቅዱስ +"+

=>በአንድነቱ ምንታዌ (ሁለትነት): በሦስትነቱ ርባዔ (አራትነት)
የሌለበት የዘለዓለም አምላክ: የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ
#እግዚአብሔር ነው:: #አብ : #ወልድ : #መንፈስ_ቅዱስ
በስም: በአካል: በግብር ሦስትነት: በባሕርይ: በሕልውናና
በፈቃድ አንድነት የጸኑ ናቸው:: በዚህ ጊዜ ተገኙ: በዚህ ጊዜ
ያልፋሉ አይባሉም:: መጀመሪያም መጨረሻም እነርሱ ናቸውና::

+ርሕሩሐን ናቸውና በእናት ሥርዓት " #ቅድስት_ሥላሴ "
እንላቸዋለን:: የሚጠላቸው (የማያምንባቸውን) አይጠሉም::
የሚወዳቸውን ግን እጽፍ ድርብ ይወዱታል:: በቤቱም መጥተው
ያድራሉ::

+ከፍጥረታት ወገን ከእመቤታችን ቀጥሎ የአብርሃምን ያህል
በሥላሴ ዘንድ የተወደደ ፍጡር የለም:: አባታችን
#ቅዱስ_አብርሃም የደግነት ሁሉ አባት ነውና በኬብሮን
በመምሬ ዛፍ ሥር ሥላሴን ተቀብሎ አስተናግዷል:: ሥላሴ
አኀዜ ዓለም (ዓለምን በእጁ የያዘ) ነው:: ነገር ግን በፍቅር
ለሚሻው በፍቅር ይመጣል::

+አባታችን አብርሃም በ99 ዓመቱ: እናታችን ሣራ በ89 ዓመቷ
ሥላሴን በድንኩዋናቸው አስተናገዱ:: አብርሃም እግራቸውን
አጠበ:: (ወይ መታደል!) በጀርባውም አዘላቸው:: (ድንቅ አባት!)
ምሳቸውንም አቀረበላቸው:: እንደሚበሉ ሆኑለት:: በዚያው
ዕለትም የይስሐቅን መወለድ አበሠሩት:: #ቅድስት_ሣራ ሳቀች::
እንደ ዘንድሮ ወገኖቻችን የማሾፍ አይደለም:: ደስታና ጉጉት
የፈጠረው እንጂ:: ሥላሴ "ምንት አስሐቃ ለሣራ በባሕቲታ"
ብለው ነበርና በዚህም ምክንያት ነው " #ይስሐቅ" የተባለው::

+ሥላሴን ያስተናገደች ድንኩዋን (ሐይመት) የድንግል
እመቤታችን ማርያም ምሳሌ ናት:: በድንግል ላይ #አብ
ለአጽንኦ: #መንፈስ_ቅዱስ ለአንጽሖ: #ወልድ በተለየ አካሉ
ለሥጋዌ በእርሷ ላይ አርፈዋል / አድረዋልና::

+"+ #ታላቁ_አባ_ሲኖዳ +"+

=>የባሕታውን ሁሉ አለቃቸው ታላቁ ቅዱስ ሲኖዳ:-
¤በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የተወለደ
¤በእናቱ ማሕጸን ሳለ መላእክት በሰይፈ እሳት ይጠብቁት የነበረ
¤የታላቅነት ትንቢት የተነገረለት
¤ገና ሳይወለድ ሥውራን አበው የሰገዱለት
¤በሕጻን ሰውነቱ ጾምና ጸሎትን የጀመረ
¤የልጅነት ቁርስና ምሳውን ለነዳያን ያካፍል የነበረ
¤በ9 ዓመቱ ወደ በርሃ የመነነ
¤የአባ አብጐል ደቀ መዝሙር የሆነ አባት ነው::

+ሲመነኩስም በእግዚአብሔር ትእዛዝ #የሠለስቱ_ደቂቅ
አስኬማ: #የኤልያስ ቆብዕ እና የመጥምቁ #ዮሐንስ ቅናትን
(መታጠቂያ) ከያሉበት መላእክት አምጥተውለት የመነኮሰ
¤ዓለምን በሙሉ በጸሎቱ ይጠብቅ የነበረ
¤የግብፅን በርሃ በብርሃን የሞላ
¤በርካታ ድርሰቶችን የደረሰ
¤ያለ ማቇረጥ በየቀኑ ከ100 ዓመታት በላይ ከጌታችን ክርስቶስ
ጋር የተነጋገረ
¤ደመናትን ተጭኖ ይሔድ የነበረና
¤ያለ ዕረፍት ለ111 ዓመታት ከ2 ወራት ፈጣሪውን ያገለገለ
አባት ነው::

+በዚህም ምክንያት አንድ ቀን ገዳማውያን ሁሉ እየሰሙ
እንዲህ የሚል ቃል ከሰማይ መጣ:: "ሲኖዳ ተሠይመ
#አርሲመትሪዳ " (ሲኖዳ አርሲመትሪዳ ሆኗል:: ማለትም
ለባሕታውያን ሁሉ አለቃ ሁኖ ተመርጧል ማለት ነው:: )

+ቅዱሱ የጌታችንን እግር እያጠበም ይጠጣ ነበር::
+በዚህች ዕለት በ120 ዓመቱ ጌታችን ወርዶ ሲያሳርገው
#አቡነ_ኪሮስ "ታላቅ ምሰሶ (ታላቅ ዛፍ) ወደቀ" ብለው
አልቅሰዋል:: #ሲኖዳ ማለት "ደግ ሰው" ማለት ነው::

+"+ #አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋስጫ ( #GIYORGIS_OF_SEGLA )
+"+

=>ታላቁ ኢትዮዽያዊ ሊቅና ጻድቅ የተወለደው ወሎ #ጋስጫ
ውስጥ በ1358 ዓ/ም ነው:: ከልጅነቱ ትምሕርት አልገባሕ
ቢለውም በልቡናው ግን ቅን እና ታዛዥ ነበር:: መምሕሩ
"ትምሕርት አይገባውምና ውሰዱት" ቢላቸው "የእግዚአብሔር
ነውና ያገልግላችሁ" ብለው መለሱት:: መገፋቱን የተመለከተ
#አባ_ጊዮርጊስ #እመቤታችንን ከልቡ ይወዳት ነበረና
ይማጸናት ገባ::

+ቀን ቀን ገዳሙን ሲረዳ: እሕል ሲፈጭና ሲከካ: ላቡንም
ሲያፈስ ውሎ ሌሊት ደግሞ ሲጸልይ ያነጋ ነበር:: ድንግል
እመቤታችን ጸሎቱን ሰምታለችና #ቅዱስ_ዑራኤልን አስከትላ
መጣችለት:: በንጹሐት እጆቿ ባርካው ምሥጢርንም ነገረችው::
"ወነገረቶ ሐምስተ ቃላተ" እንዲል:: ጽዋዐ ልቡናን አጠጥታው
ተሠወረችው::

+ከዚህች ሰዓት ጀምሮ አባ ጊዮርጊስ ፍጹም ተለወጠ:: በጽድቁ
ላይ የሊቅነትን ካባ ደረበ:: ቅዱሳት መጻሕፍትን ይተነትናቸው:
መናፍቃንንም ምላሽ ያሳጣቸው ገባ:: የተረጐማቸውና
ያተታቸውን ሳይጨምር 41 ድርሰቶችን ደረሰ:: (መጽሐፈ
ሰዓታት: መጽሐፈ ምሥጢር: አርጋኖን: ኆኅተ ብርሃን: ውዳሴ
መስቀል: ወዘተ . . . የእርሱ ድርሰቶች ነበሩ)

+ስለ ሃይማኖትም ጠበቃ ነበር:: ስለ ቅድስናውና ውለታው የኢ/
ኦ/ተ/ቤ እንዲህ ትጠራዋለች:-
1. #ሊቀ_ሊቃውንት
2. #በላዔ_መጻሕፍት
3. #ዓምደ_ሃይማኖት
4. #ዳግማዊ_ቄርሎስ
5. #ጠቢብ_ወማዕምር

+ጻድቁ ሊቅ በተወለደ በ60 ዓመቱ በ1418 ዓ/ም በዚህች ቀን
ዐርፏል:: አባ ጊዮርጊስ የተወለደውም ያረፈውም ሐምሌ 7 ቀን
ነው::

=>የሥላሴ ቸርነት: የአብርሃም ደግነት: የአበው አባ ጊዮርጊስና
አባ ሲኖዳ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን::

=>ሐምሌ 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱሳን አብርሃምና ሣራ (ሥላሴን ያስተናገዱ)
2.ብሥራተ ልደተ ይስሐቅ
3.ታላቁ አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን ሁሉ አለቃ)
4.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ (ሊቀ ሊቃውንት: ኢትዮዽያዊ
የሃይማኖት ምሰሶ)
5.ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ (ምጥው ለአንበሳ)
6.አባ መቃቢስ
7.አባ አግራጥስ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
2.አባ ባውላ ገዳማዊ
3.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ

=>+"+ እግዚአብሔርም ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ:-
'በእውነት እየባረክሁ እባርክሃለሁ:: እያበዛሁም አበዛሃለሁ'
ብሎ ከእርሱ በሚበልጥ በማንም ሊምል ስላልቻለ በራሱ ማለ::
እንዲሁም እርሱ ከታገሠ በሁዋላ ተስፋውን አገኘ:: +"+ (ዕብ.
6:13)
=>+"+ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ: የእግዚአብሔርም ፍቅር:
የመንፈስ ቅዱስም ሕብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን:: አሜን:: +"+
(ቆሮ. 13:14)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለጻድቅ #አባ_ኅልያን ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

✞✞✞ አባ ኅልያን ገዳማዊ ✞✞✞

=>ጻድቁ ተወልዶ ያደገው ዐይነ ፀሐይ በምትባል የቀድሞ የግብፅ ክፍለ ሃገር ሲሆን ወላጆቹ ዲስጣና ካልሞና ይባላሉ:: እነርሱ መልካም ክርስቲያኖች ነበሩና ገና በልጅነት ይህንኑ አጥብቀው አስተምረውታል:: ቅዱሱ #ኅልያን ጾምን: ጸሎትን ብቻ ያይደለ በሥጋዊ ሙያውም የተመሰገነ አንጥረኛ ነበር::

+በወዙ በላቡ ሠርቶ ያገኘው ሃብት ነበረው:: በተለይ ወርቅና ብር እየሠራ ይተዳደር: ከገቢውም ነዳያንን ያስብ ነበር:: እንዲህ ባለ ግብር ሳለ አንድ ቀን ፈተና መጣበት:: አንዲት ዐረባዊት ሴት መጥታ የጀሮ ጌጥ (ጉትቻ) እንዲሠራላት ትጠይቀውና እርሱም ከወርቅ ይሠራላታል:: የጀሮ ጌጡን ከሰጣት በሁዋላ ግን "ዋጋውን አልሠጥህም" ትለዋለች::

+እርሱም "ምነው እህቴ! የደከምኩበትን ለምን አትከፍይኝም?" ሲላት ገላዋን አጋልጣ "ሴትነቴን ልስጥህ" ብላ ለዝሙት ጠየቀችው:: ድንግሉ ኅልያን ከአነጋገሯና ከድርጊቷ የተነሳ በጣም ደነገጠ:: ከፊቷ ላይ አማትቦ: ገስጿት ወደ ቤቱ ሔደ:: ሙሉ ሌሊት ሲያዝን አደረ:: ሊነጋጋ ሲል በልቡ ወሰነ:: ይሕችን ዓለም ሊተዋትም ቆረጠ::

+በወጣት ጉልበቱ ደክሞ ያፈራው ሃብቱ: ንብረቱ: ቤቱ: መሬቱ: ወርቁ: ብሩ አላሳሳውም:: ነዳያንን ሁሉ ወደ ቤቱ ጠርቶ ሙሉ ንብረቱን አካፈላቸው:: የተረፈችው የለበሳት ልብስ ብቻ ነበረችና ፈጽሞ ደስ እያለው ከተማውን ጥሎ ወደ በርሃ ተሰደደ:: ልቡናን የሚመረምር ጌታ ሊመራው ወዷልና 3 #ቅዱሳን ስውራንን ሰደደለት::

+ሦስቱም የብርሃን አክሊል ደፍተው: የብርሃን ካባ ላንቃ ለብሰው: የብርሃን ዘንግ ይዘው ተገለጡለት:: እየመሩም ወስደው በግራና በቀኝ ውሃ ከሚፈስባት: ደኗ ለዐይን ደስ ከምታሰኝ ዱር አደረሱት:: አካባቢው እንኩዋን ሰው እንስሳትም አልነበሩበትም:: 3ቱ ቅዱሳን ከቦታዋ እንደ ገቡ በላዩዋ ላይ ዕንቁ ያለባት የብርሃን ዘንግ ሰጥተውት "ወደ ፈጣሪ እንስገድ" አሉት::

+ሰግዶ ቀና ሲል ግን 3ቱም በአካባቢው አልነበሩም:: ተሠውረዋልና:: #አባ_ኅልያን ከቅዱሳኑ በመለየቱ ፈጽሞ አለቀሰ::

+ተጋድሎውን ግን በጾምና በጸሎት: በስግደትም አጠነከረ:: ቅዱሱ የሚመገበው: የሚለብሰውም ቅጠል ነበር:: በእርሱ ዘንድ ሌሊት የሚባል አልነበረም:: ምክንያቱም ያቺ ዘንግ ሲመሽ ግሩም የሆነ ብርሃን ታወጣ ነበርና ነው::

+መንገድ መሔድ በፈለገ ጊዜም ትመራው: ጐዳናውንም ታሳጥርለት ነበር:: እንዲህ ባለ ግብር ለበርካታ ዓመታት ከሰው ተለይቶ ኖረ:: አጋንንት በተለያየ መንገድ ፈተኑት:: ግን አልቻሉትም:: አቅም ሲያጥራቸው ወደ ከተማ ሔደው: በሰው አርአያ ሽፍቶችን አናግረው ሊያስገድሉት ሞከሩ:: ነገር ግን ከፊት ለፊት እያዩት ሽፍቶቹ ሲራመዱ ቢውሉም ሊደርሱበት አልቻሉም::

+#እግዚአብሔር በኪነ ጥበቡ መንገዱን ያረዝምባቸው ነበር:: በሁዋላ ግን ሽፍቶቹ በድካምና በውሃ ጥም ሊያልቁ ሆነ:: ጻድቁ ምንም እርሱን ለመግደል ቢመጡም አዘነላቸው:: ባሕሩን ያለ ታንኩዋ እየረገጠ ደረሰላቸው:: ከዱር ፍሬ አብልቶ: ንጹሕ ውሃም አጠጥቶ ሸኛቸው::

+እድሜው እየገፋ ሲሔድ አንድ ቀን እነዛ በፊት የተሠወሩ 3 ቅዱሳን እንደ ገና ተገለጡለት:: በደስታ ሲጨዋወቱ አድረው ሲነጋ አባ ኅልያን ወደ ምሥራቅ ሰግዶ ዐረፈ:: 3ቱ ቅዱሳንም ሥጋውን ገንዘው በበዓቱ ቀበሩት:: ዜና ሕይወቱንም ጽፈው አስቀመጡትና እንደ ገና ተሠወሩ::

=>የቅዱሳን አምላክ ለእኛም የአባቶችን ረድኤት ይላክልን:: ከጻድቁም በረከትን ይክፈለን::

=>ሐምሌ 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.አባ ኅልያን ገዳማዊ
2.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሰማዕት (ዘሐምስቱ አሕጉር)
3.ቅዱስ ታውድሮስ ሰማዕት
4.ሰማዕታት ሉክዮስና ድግናንዮስ (በንስሃ ለክብር የበቁ የጦር አለቆች)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ኁሉ አባት)
2.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮዽያዊ)
3."318ቱ" ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮዽያዊ)
6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)

=>+"+ ጌታ ኢየሱስም "አትግደል: አታመንዝር: አትስረቅ: በሐሰት አትመስክር: አባትህንና እናትህን አክብር: ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ" አለው:: ጐበዙም "ይህንማ ሁሉ ከሕጻንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ:: ደግሞስ የሚጐድለኝ ምንድር ነው?" አለው:: ጌታ ኢየሱስም "ፍጹም ልትሆን ብትወድ ሒድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ:: መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ:: መጥተህም ተከተለኝ" አለው:: +"+ (ማቴ. 19:18)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
✞✞✞✝️ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ✝️ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✝️ሐምሌ ፲፪✝️

✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱስ "ሚካኤል ሊቀ መላእክት"
የተአምር በዓልና ለሰማዕቱ "አባ ሖር" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*" ተአምረ ቅዱስ ሚካኤል "*+

=>ቅዱስ መጽሐፍ እንደ ነገረን በዚህች ዕለት የመላእክት
ሁሉ አለቃቸው: የቅዱሳንም ረዳታቸው የሆነው ደጉ
መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል ንጉሡን ሕዝቅያስን ግሩም
በሆነ ተአምር ከከተማው #ኢየሩሳሌም ጋር ታድጐታል::
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+ከመድኃኒታችን #ክርስቶስ ልደት 700 ዓመታት በፊት
#ሕዝቅያስ የሚባል ንጉሥ በይሁዳ ላይ ነግሦ ነበር::
ደጋጉ #ዳዊትና #ሰሎሞን ካረፉ በሁዋላ የሕዝቅያስን
ያክል ቅን እና የእግዚአብሔር ሰው በእሥራኤል ላይ
አልነገሰም:: ንጉሡ ጣዖት አምልኮን ነቃቅሎ አጥፍቶ
ሕዝቡ እግዚአብሔርን ብቻ እንዲያመልክ አድርጐም
ነበር::

+ነገር ግን ቅዱስ ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዓመት
የአሕዛብ (የአሦር) ንጉሥ ሰናክሬም በጠላትነት ተነሳበት::
ወደ አካባቢውም መጥቶ: ከቦ አስጨነቀው:: ሰናክሬም
በጦር እጅግ ኃይለኛ ነበር:: በዚያውም ላይ ጦር የሚመዙ
ከ185,000 በላይ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩትና ሕዝቅያስ
እንደማይችለው ተረድቶ መልእክተኛ ላከበት::

+"እገብርልሃለሁ:: የፈለግከውንም እሰጥሃለሁ:: ሃገሬን
ግን አታጥፋ:: ኢየሩሳሌምን አታቃጥል:: ሕዝቤንም
አትግደል" በሚል ለመነው:: እጅ መንሻ ግብሩንም
ከከተማዋ የተገኘውን ወርቅና ብር ሁሉ ጭኖ ላከለት::

+ሰናክሬም ግን ሰይጣን ያደረበት ነውና የሕዝቅያስን
ልመና ወደ ጐን ብሎ የእሥራኤልን አምላክ : ቅዱስ
ስሙንም ተገዳደረ:: ለሕዝቅያስም "ከእኔ እጅ የሚያድንህ
ማነው? ሕዝቡንም #እግዚአብሔር ያድናል ብለህ
አታታልላቸው" ሲል ላከበት:: ቅዱስ ሕዝቅያስ በዚህ ጊዜ
የፈጣሪው ስም ሲቃለል ሰምቷልና ፈጽሞ አዘነ::

+መልእክተኞችን ወደ ነቢዩ #ቅዱስ_ኢሳይያስ ልኮ እርሱ
ወደ ቤተ መቅደስ ገባ:: በእግዚአብሔር ፊት ልብሱን
ቀድዶ ማቅ ለበሰ:: ስለ ኢየሩሳሌምና ሕዝቡም ፈጽሞ
አለቀሰ:: በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የሰናክሬምን
መገዳደርና የሕዝቅያስን ልመና ሰምቷልና በኢሳይያስ
አንደበት እንዲሕ አለ:- "ስለ ባሪያየ ስለ #ዳዊት
ከተማዋን አድናታለሁ::"

+በዚያች ሌሊትም ድንቅ መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል
ከሰማያት በግርማ ወረደ:: ወደ ሰናክሬም የጦር ሠፈር
ደርሶ አንድ ጊዜ የእሳት ሰይፉን መዝዞ ቢያሳያቸው
ከአሕዛብ ሠራዊት 185 ሺ ኃያላን እንደ ቅጠል ረገፉ::
በለኪሶ የነበረው ሰናክሬም በጧት ቢነሳ ሠራዊቱ ሁሉ
ወደ አስከሬን ክምር ተቀይሯል::

+በድንጋጤ ወደ #ነነዌ ሒዶ ወደ ጣዖት ቤቱ ሲገባ የራሱ
ልጆች (አድራማሌክና ሳራሳር) ገደሉት:: ትዕቢተኛው
ሰናክሬም ለአሕዛብ ሁሉ መዘባበቻ ሆነ:: ቅዱስ ሕዝቅያስ
ግን በፈጣሪው ታምኗልና ቅዱስ ሚካኤል ሞገስ ሆኖ
የዓለም ነገሥታት ሁሉ ፈሩት:: (1ነገ. 18:13, 19:1)

+*" ቅዱስ አባ ሖር ሰማዕት "*+

=>ዳግመኛ በዚህ ቀን #አባ_ሖር ሰማዕቱ ይታሠባል::

+ቅዱሱ:-

¤ስርያቆስ በምትባል የግብጽ አውራጃ ተወልዶ ያደገ:
¤ገና በልጅነቱ መንኖ እግዚአብሔርን ያገለገለ:
¤ዘመነ ሰማዕታት በመጣ ጊዜም በመኮንኑ ፊት ቀርቦ
በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ያመነ:
¤ከመኮንኑም ብዙ ስቃይ የደረሰበት:
¤ብዙ ተአምራትን በመስራቱ ያሰቃየው የነበረውን መኮንን
ወደ ክርስትና መልሶ ለሰማዕትነት ያበቃ አባት ነው::

+እርሱም የሰማዕትነትን ክብር በእጅጉ ሽቷታልና ወደ ሌላ
ሃገር ሒዶ በዚህች ቀን አንገቱን ተሰይፎ የክብርን አክሊል
ተቀዳጅቷል:: በሐዋርያዊ አገልግሎቱ ያሳመናቸው 127
ወንዶችና 20 ሴቶችም አብረውት ተሰይፈዋል::

=>እግዚአብሔር በሊቀ መላእክት ክንፍ ሃገራችንን
ከአሕዛብ ስውር ጦር ይጠብቅልን:: ከሰማዕቱም በረከት
ያሳትፈን::

=>ሐምሌ 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ሕዝቅያስ ንጉሥ
2.ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
3.ቅዱስ አባ ሖር ሰማዕት
4."147" ሰማዕታት (የአባ ሖር ማሕበር)

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
3.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ድሜጥሮስ
5.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
6.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
7.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
8.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

=>+"+ እግዚአብሔር ይላል:- ስለ እኔም ስለ ባሪያየም
#ስለ_ዳዊት ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ::
በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ::
ከአሦራውያንም ሠፈር መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ገደለ::
ማለዳም በተነሱ ጊዜ እነሆ ሁሉ በድኖች ነበሩ:: +"+
(1ነገ. 19:34)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለነቢዩ #ቅዱስ_ዮናስ እና ለእናታችን #ቅድስት_አውፎምያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

✞✞✞ ቅዱስ ዮናስ ነቢይ ✞✞✞

=>በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ከ12ቱ #ደቂቀ_ነቢያት አንዱ የሆነው #ቅዱስ_ዮናስ ከክርስቶስ ልደት 800 ዓመታት በፊት እንደ ነበረ ይታመናል:: #ሊቃውንት እንዳስተማሩን ደግሞ እናቱ #ቅዱስ_ኤልያስን የመገበችው የሰራፕታዋ መበለት ናት:: ቅዱስ ዮናስ ገና ሕጻን ሳለ በእሥራኤል ምድር ዝናብ ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ተከልክሎ ነበር::

+ይሕንንም ያደረገው ደጉ ነቢይ ኤልያስ ለአምልኮተ እግዚአብሔር ቀንቶ ነው:: በወቅቱ ኤልያስ በሰራፕታ ሳለ ሕጻኑ ዮናስ ታሞ ሞተ:: ልጇ የሞተባት መበለትም ኤልያስን ለመነችው:: ኤልያስም ወደ ፈጣሪው ማልዶ ሕጻኑን ዮናስን ከሞት አስነስቶታል:: ትንሽ ከፍ ባለ ጊዜም ከጉዋደኞቹ (ከነቢያቱ) #አብድዩና #ኤልሳዕ ጋር ሆነው ታላቁን ነቢይ ኤልያስን ተከትለውታል::

+ኤልያስ ካረገ በሁዋላ ሁሉም በየተሰጣቸው አገልግሎት ተሠማርተዋል:: ቅዱስ ዮናስን #እግዚአብሔር "ወደ ነነዌ ሒደሕ ንስሃን ስበክ" አለው:: ዮናስ ግን የፈጣሪውን መሐሪነት ጠንቅቆ ያውቃልና አልሔድም አለ:: (ተመልከቱ የየዋሕነት ብዛት)

+እግዚአብሔር እየደጋገመ እንዲሔድ ሲነግረው ነቢዩ "እንዲሕ የሚዘበዝበኝ ከፊቱ ብቀመጥ አይደል" ብሎ ሊኮበልል ወጣ:: ነገር ግን አልቀናውም:: በእርሱ ምክንያት ማዕበል ተነሳ:: ሕዝቡም ሊያልቁ ሆነ:: ከእንቅልፉ የነቃው ዮናስ ከመርከቡ ላሉት አሕዛብ አምልኮተ እግዚአብሔርን ሰብኮላቸው: በእርሱ ጠያቂነት ሐምሌ 15 ቀን ወደ ባሕር ጥለውታል::

+አሣ አንበሪም ተቀብሎታል:: በግዙፉ አሣ ውስጥም ያለ እንቅልፍ በጾም: በጸሎትና በምስጋና 3 ቀን ቆይቷል::
ሙስና ሳያገኘውም በዚህች ቀን አሣ አንበሪው #ነነዌ ዳር ላይ ተፍቶታል:: ቅዱስ ዮናስ እግዚአብሔር እንዳዘዘው "እስከ ሠሉስ ዕለት ትትገፈታእ ነነዌ ዓባይ ሃገር" /እስከ ሦስት ቀን ድረስ ነነዌ ትገለበጣለች (ዮናስ 3:4)/ ብሎ አሰምቶ ሰበከ::

+የነነዌ ሰዎችም በስብከተ ዮናስ አምነው: ንስሃም ገብተው ድነዋል:: በዚህም ጌታችን በወንጌል ላይ አመስግኗቸዋል:: ቅዱስ ዮናስ መኮብለሉ #በሐዲስ_ኪዳን ለሚደረገው ምሥጢረ ትንሣኤ ጥላ (ምሳሌ) ነውና ይደነቃል:: (ማቴ. 12:38) ነቢዩ ግን በተረፈ ሕይወቱ ሕዝቡን ሲያስተምር: ፈጣሪውን ሲያገለግል ኑሮ በመልካም ሽምግልና ዐርፏል::

+"+ ቅድስት አውፎምያ ሰማዕት +"+

=>እናታችን #ቅድስት_አውፎምያ (ስሟ አፎምያ አይደለም:: በስሕተት "ው" መካከል ላይ የገባች እንዳይመስልዎ:: እስመ ከመዝ ስማ-ስሟ እንዲሁ ነው የሚጠራው) በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ከነበሩ ወጣት ክርስቲያኖች አንዷ ናት:: ገና ከልጅነቷ ልቧ በፍቅረ ክርስቶስ የተነደፈ ነበር::

+በዚህም ምክንያት ራሷን በጾምና በጸሎት ወስና ትኖር ነበር:: እድሜዋ ገና በአሥራዎቹ ቢሆንም በመንኖ ጥሪት መኖር ምርጫዋ ነበር:: ሊቃውንት አበው ከሰማዕትነቷ ደርበው "ጻድቅት አውፎምያ" እያሉም ይጠሯታል::

+አንድ ቀን ግን መንገድ ወጥታ ነበርና ክርስቲያኖች ሲሰቃዩ ተመለከተች:: ምንም ጥፋት ሳይገኝባቸው ክርስቶስን ስላመለኩ ብቻ ይሙት በቃ ተፈርዶባቸው ሊገደሉ እየተወሰዱ ነበር:: አሕዛብ ግብራቸው የአውሬ ነውና ርሕራሔ የላቸውም:: ሰማዕታቱ ደማቸው በየመንገዱ እየፈሰሰ ጥቁር ሰንሰለት በአንገታቸው: በእጃቸውና በእግራቸው ላይ አድርገው ይጐትቷቸው ነበር::

+ቅድስት አውፎምያ የተደረገውን ሁሉ ተመልክታ አምርራ አለቀሰች:: ፈጠን ብላም ወደ መኮንኑ ቀርባ ገሰጸችው::
"አንተ አእምሮ የጎደለህ! እንዴት ክርስቲያኖችን እንዲህ ታሰቃያለህ? አምላካቸው #ጌታ_ክርስቶስ ታጋሽ ባይሆን ኑሮ በቅጽበት ከገጸ ምድር ባጠፋህ ነበር" አለችው::

+በድፍረቷ የተገረመው መኮንኑ "አንቺስ ማንን ታመልኪያለሽ?" ሲል ጠየቃት:: እርሷም "ሰማይና ምድርን የፈጠረውን: ስለ እኛ ሲል በቀራንዮ አንባ የተሠዋውን #ኢየሱስ ክርስቶስን አመልካለሁ" ስትል መለሰችለት:: በዚያች ሰዓት የመኮንኑ ቁጣ በቅድስቷ ላይ ነደደ::

+ነገር ግን ቁጣውን ከቁም ነገር አልቆጠረችውምና እንዲያሰቃዩዋት አዘዘ:: ወታደሮቹ ሥጋዋን በብዙ አሰቃዩ:: ብላቴናዋ አውፎምያ ግን ጽንዕት ናትና አልቻሏትም:: በመጨረሻ በእሳት ተቃጥላ ትሞት ዘንድ ተፈረደባት::

+እሳቱ ከመሬት ከፍ ባለ ጊዜ ወደ ውስጥ ወረወሯት:: በእሳቱ መካከል ቁማ ለረዥም ጊዜ ጸለየች:: ከዚያም ነፍሷን አሳልፋ ሰጠች:: ምዕመናን በክብር ገንዘው ቀብረዋታል::

=>አምላካችን ከነቢዩና ከሰማዕቷ ወዳጆቹ በረከት ይክፈለን::

=>ሐምሌ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ዮናስ ነቢይ (ከአሣ አንበሪ ሆድ የወጣበት)
2.ቅድስት አውፎምያ (ጻድቅትና ሰማዕት)
3.ቅዱስ ዮስጦስ ሰማዕት (ታላቁ)
4.ቅዱስ ዘካርያስ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
4.አባ ገሪማ ዘመደራ
5.አባ ዸላሞን ፈላሢ
6.አባ ለትጹን የዋህ
7.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ)

=>+"+ በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና:- 'መምሕር ሆይ! ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን' አሉት:: እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው:- 'ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል:: ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም:: ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል:: የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዱበታል:: በዮናስ ስብከት ንስሃ ገብተዋልና:: እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ:: +"+ (ማቴ. 12:38)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱሳን ጻድቃን "እንድራኒቆስ ወአትናስያ" እና ለአቡነ "ፊልዾስ ዘደብረ ሊባኖስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*" ጻድቃን እንድራኒቆስ ወአትናስያ "*+

=>ሁለቱ ቅዱሳን ባል እና ሚስት (ባለትዳር) ናቸው:: የነበሩበት ዘመን 4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: እስኪ #እግዚአብሔር የቀደሰው ጋብቻ ምን እንደሚመስል እንመልከት::

+#እንድራኒቆስና_አትናስያ በዘመናቸው ከልጅነት ጀምረው ቃለ እግዚአብሔርን የሚሰሙ : ለወላጆቻቸው የሚታዘዙ ነበሩ:: ዘመኑ ደርሶ በሚገባው የተክሊል ሥርዓት ጋብቻቸውን ፈጸሙ:: 40 ቀን ከተፈጸመ በሁዋላ ከምንም ነገር በፊት 2ቱ ቁጭ ብለው ተወያዩ::

+የውይይታቸው ርዕስ ደግሞ "ፈጣሪያችን በምን እናስደስተው" የሚል ነበር:: ውይይታቸው የተጠናቀቀው በእነዚህ ውሳኔዎች ነው::

1.ሁልጊዜም እንግዳ መቀበል አለብን::

2.ነዳያን ከቤታችን ሊጠፉ አይገባም::

3.ጸሎት : ጾምና ስግደት በቤት ውስጥ አይቁዋረጥም::

4.አብሮ ለመተኛት መቸኮል የለብንም::

+እነርሱ መልካምን አስበዋልና አምላክ የሰጣቸውን ሃብት ሲመጸውቱ ኖሩ:: ከዘመናት የቅድስና ጉዞ በሁዋላ በፈቃደ እግዚአብሔር 2 ልጆችን አከታትለው ወለዱ:: ወንዱን "#ዮሐንስ" : ሴቷን ደግሞ "#ማርያም" አሏት::

+እነርሱን ከወለዱ በሁዋላ እንደ ገና ሌላ ውሳኔ አሳለፉ:: "ይህንን ላደረገልን ጌታ ከዚህ በሁዋላ አልጋ እንለያለን" ብለው ለ12 ዓመታት በጾምና በጸሎት ተወሰኑ::

+ሕጻናቱ ዮሐንስና ማርያም በቅንነት አድገው እድሜአቸው 12 ሲሆን 2ቱም በአንድ ቀን ታመው ሞቱ:: ይህ ለአንድ ወላጅ የመጨረሻው አሰቃቂ ፈተና ነው:: ሁሉቱም (እንድራኒቆስና ሚስቱ አትናስያ) ልጆቻቸውን ታቅፈው ወስደው ቀበሩ::

+#እንድራኒቆስ ከቀብር በሁዋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ምርር ብሎ አለቀሰ:: ግን እንዲህ አለ:-
"አምላከ #ኢዮብ! አንተ ሰጠኸኝ:: አንተም ነሳኸኝ:: ስምህ ለዘለዓለም ይባረክ" ብሎ ሔደ:: እናት #አትናስያ ግን ከሐዘን ብዛት ልቡናዋ ሊሠወር ጥቂት ቀረው::

+የልጆቿ መቃብር ላይ ተደፍታ ስታለቅስ ቅዱስ መልአክ ልቡናዋን ወደ ሰማይ አሳረገው:: ልጆቿ ዮሐንስና ማርያም በገነት ውስጥ ከቅዱሳን ጋር ሐሴትን ሲያደርጉም ተመለከተች:: ወዲያው ወደ ቤት ተመልሳ ለባሏ እንድራኒቆስ ያየችውን ነገረችውና ደስ አላቸው::

+እዛው ላይ "ለዚህ ውለታው ከነፍሳችን ውጪ የምንሰጠው የለም" ብለው ሊመንኑ ተስማሙ:: እጅግ ሃብታሞች ነበሩና ነዳያንን ሰብስበው : ሃብት ንብረታቸውን : ቤት ርስታቸውን አካፍለው ወደ ገዳመ አስቄጥስ ሔዱ::

+እርሷ ከሴቶች ገዳም : እርሱ ደግሞ ከወንዶቹ ገቡ:: ለ12 ዓመታት በፍጹም ተጋድሎ ለፈጣሪያቸው ተገዙ:: በእነዚህ ዘመናት ተያይተው : አንዱ ስለ ሌላው ሰምቶ አያውቅም:: በጸሎት ግን ያለማቁዋረጥ ይተሣሠቡ ነበር::

+ከ12 ዓመታት በሁዋላ የፍቅር አምላክ በሁለቱም ልቡና በተመሳሳይ ሰዓት : ተመሳሳይ ሐሳብን አመጣ:: እርሱ ከአበ ምኔቱ (#ታላቁ_አባ_ዳንኤል) : እርሷም ከእመ ምኔቷ አስፈቅደው ወደ #ኢየሩሳሌም ከቅዱሳት መካናት ለመባረክ ጉዞ ጀመሩ:: በየፊናቸው ጥቂት እንደተጉዋዙ እርስ በርስ ተያዩ::

+እርሷ ለየችው:: እርሱ ግን ጭራሽ ሊለያት አልቻለም:: ይህም ጥበበ እግዚአብሔር ነው:: 2ቱም እየተጫወቱ : እየጸለዩ በሰላም ተባርከው ወደ ግብጽ ተመለሱ:: በእነዚህ ጊዜያት ቅድስት አትናስያን የሚለያት አልነበረም:: አካሏ በገድል ከመለወጡ ባሻገር የለበሰችው እንደ ወንድ መነኮሳት ነበር::

+ወደ #ገዳመ_አስቄጥስ ሲደርሱ ጸጋው ተሰጥቶታልና #አባ_ዳንኤል ባልና ሚስት መሆናቸውን አወቀ:: "ለምን አብራችሁ አትኖሩም?" አላቸው:: "እኛ ደስ ይለናል" አሉት:: ከዚያ እርሷ እያወቀችው: እርሱ ሳያውቃት ለ12 ዓመታት አብረው በቅድስና ኖሩ::

+ከእነዚህ ዘመናት በሁዋላ ግን ሐምሌ 28 ቀን ቅድስት #አትናስያ ታመመች:: አባ ዳንኤል ሥጋውን ደሙን አቀብሏትም ዐረፈች:: ሊገንዟት ሲቀርቡ ቅዱስ #እንድራኒቆስ መልኩዋን ልብ ቢለው ሚስቱ ናት::

+በአንድ ጊዜ ሚስቱንና የሚወደውን ባልንጀራ በማጣቱ አለቀሰ:: እርሷን ቀብረው ወደ በዓቱ ተመልሶ "ጌታ ሆይ! ውሰደኝ?" አለ:: እርሱም ተከትሏት ዐረፈ:: አባ ዳንኤል እርሱንም ቀብሮ ጥዑም ዜናቸውን ጻፈ::

+*" አባ ፊልዾስ ዘደብረ ሊባኖስ "*+

=>ታላቁ ኢትዮዽያዊ ጻድቅ: ሐዋርያና ሰማዕት #አቡነ_ፊልዾስ የጻድቁ #አቡነ_ተክለ_ሃይማኖት ደቀ መዝሙር ሲሆኑ የተወለዱት በምድረ ሽዋ በ1266 ዓ/ም ነው:: ከልጅነታቸው ጀምረው ምሥጢር ተመራማሪና መጻሕፍትን መርማሪ የነበሩት ጻድቁ የመነኑት ገና በ15 ዓመታቸው ነበር::

+#በደብረ_ሊባኖስ በአመክሮ ለ3 ዓመታት ቆይተው መንኩሰዋል:: ለ22 ዓመታትም የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዝሙር ሆነው አገልግለዋል:: አቡነ ተክለ ሃይማኖት በ1306 ዓ/ም ነሐሴ 24 ቀን ሲያርፉ የተተኩት አባ ኤልሳዕ ቢሆኑም ለ3 ወራት ቆይተው ዐርፈዋል::

+በ1307 ዓ/ም አቡነ ፊልዾስ የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት (እጨጌ) ሁነዋል:: ገዳሙንም ለ28 ዓመታት መርተዋል:: ከዚያም በዘመነ አፄ ዓምደ ጽዮንና በአፄ ሰይፈ አርዕድ ብዙ ስደት: መከራ: እሥራትና ግርፋት ደርሶባቸዋል:: ምክንያቱ ደግሞ እውነትን መናገራቸውና ነገሥታቱን መገሰጻቸው ነበር:: በስደትም ለ6 ዓመታት ከ9 ወራት ቆይተዋል::

+ሃገሪቱን በስብከተ ወንጌል ካበሩ #12ቱ_ንቡራነ_እድ አንዱ የሆኑት #እጨጌ አባ ፊልዾስ በተወለዱ በ74 ዓመት ከ9 ወራቸው በ1341 ዓ/ም ዐርፈዋል:: የተቀበሩት #በደብረ_ዕንቁ ሲሆን ካረፉ በ140 ዓመት #አቡነ_መርሐ_ክርስቶስ ዐጽማቸውን አፍልሰዋል::

=>ከቅዱሳኑ እንድራኒቆስ ወአትናስያ እና ከጻድቁ አቡነ ፊልዾስ በረከትን ይክፈለን::

=>ሐምሌ 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱሳን ጻድቃን እንድራኒቆስና አትናስያ
2.አቡነ ፊልዾስ ጻድቅ (ዘደብረ ሊባኖስ)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.አማኑኤል ቸር አምላካችን
2.ቅዱሳን አበው (አብርሃም : ይስሐቅና ያዕቆብ)
3.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
4.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)

=>+"+ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል:: ከሚስቱም ጋር ይተባበራል:: ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ:: ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው:: እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ:: ሆኖም ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጐ ይውደዳት:: ሚስቱም ባሏን ትፍራ:: +"+ (ኤፌ. 5:31)

✞✞✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✞✞
††† እንኳን ለቅድስት ጾመ ፍልሠታ ለማርያም እና ለቅዱሳኑ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅድስት ጾመ ፍልሠታ ለማርያም †††

††† ቸር #እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጠው ጸጋ አንዱ #ጾም ነው:: የሰው ልጅ ከፈጣሪው ክብር እንዲደረግለት ክፋትን መስራት የለበትም:: መልካም መሆንም ይጠበቅበታል:: ለዚህ ምንጮቹ ደግሞ ጾም: ጸሎትና ስግደት ናቸው:: ያለ እነዚህ ምግባራት መቼም ወደ #ጽድቅ መድረስ አይቻልም::

ይቅርና እኛ ክፉዎቹ የሰማይና የምድር ፈጣሪ: የክብር ሁሉ ባለቤት ጌታችን #ኢየሱስ_ክርስቶስ ሥጋችንን በተዋሐደ ጊዜ የመጀመሪያ ሥራው ያደረገው ጾምን ነው:: ስለዚህም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን 7 አጽዋማትን በጉባዔ ሠርታ: በአዋጅ እንዲጾሙ ታደርጋለች:: ከእነዚህም አንዱ ጾመ ፍልሠታ ነው::

"ፈለሠ" - ሔደ: ተጉዋዘ እንደ ማለት ሲሆን " #ፍልሠታ" ማለት የእመቤታችን ቅድስት #ድንግል_ማርያምን የዕርገት ጉዞ የሚያዘክር ቃል ነው:: #እመ_ብርሃን በዚህ ዓለም ለ64 ዓመታት ኑራ ካረፈች በሁዋላ ሥጋዋ እንደ እኛ አልፈረሰም::

ለጊዜው በዕጸ ሕይወት ሥር ቆይታ እንደ ልጇ ትንሣኤ ተነስታ ዐርጋለች:: እርሷ በሁሉ ነገሯ ቀዳሚና መሪ ናትና:: ጾመ ፍልሠታን የጀመሩት አበው #ሐዋርያት ሲሆኑ እንድትጾምም ሥርዓት የሠሩ ራሳቸው ናቸው:: ከ7ቱ አጽዋማትም እጅግ ተወዳጅና እየተናፈቀች የምትፈጸም ናት::

ካህናትና ምዕመናንም ጾሟን እንደየአቅማቸው ክብር በሚያሰጥ መንገድ ይፈጽሟታል::
*የቻሉ ወደ ገዳማት ሔደው ጥሬ እየቆረጠሙ: ውሃ እየተጐነጩ ክብርን ያገኛሉ::
*ሌሎቹ ደግሞ ባሉበት ደብር አካባቢ እያደሩ ሌሊት ሰዓታቱን: በነግህ ኪዳኑንና ውዳሴ ማርያም ትርጉዋሜውን: በሰርክ ደግሞ ቅዳሴውን ይሳተፋሉ::
*የኔ ብጤ ደካማ ደግሞ ጠዋት ማታ ወደ ደጇ እየተመላለሰ "አደራሽን ድንግል" ይላታል::

††† በእርሷ አምነን አፍረን አናውቅምና ነጋ መሸ ሳንል እንማጸናታለን::

††† #ጽንዕት_በድንግልና: #ሥርጉት_በቅድስና #እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን:: አእምሮውን: ለብዎውን: ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን::
*ጾሙን የፍሬ: የትሩፋትና የበረከት ያድርግልን::*

††† ቅዱሳን ዮሴፍና ኒቆዲሞስ †††

††† እጅግ የተወደዱ: ሞገስ የሞላላቸውና ፈጣሪያቸውን በክብር ገንዘው የቀበሩ አባቶች ናቸው::

††† ቅዱስ ዮሴፍ ዘአርማትያስ †††

††† ቅዱሱ በእሥራኤል ምድር ተወልዶ ያደገ: ኦሪትን የተማረ ባለጠጋ ሰው ነው:: የተማረ ደግ ሰው ነውና የክርስቶስን መምጣት በተስፋ ይጠብቅ ነበር:: ባገኘውም ጊዜ በአዳኝነቱ (በመሲህነቱ) አምኖ በስውር ተከታዩ ነበር::

††† ቅዱስ ኒቆዲሞስ †††

††† ወንጌል እንደሚነግረን ይህ ሰው የአይሁድ አለቃ: መምህር: ዳኛ እና ሃብታም ሰው ነበር:: እነዚህ ሁሉ ማነቆዎች ግን እርሱን ከፈጣሪው ሊያስቀሩት አልቻሉም:: ሌሊት እየመጣ ከጌታችን እግር ይማር ዘንድም አድሎታል:: በመካከልም ከአይሁድ ጋር ብዙ ተጋጭቷል::

ሁለቱ አባቶች መድኃኒታችን ስለ እኛ ሲል ሞቶ ባለበት ሰዓት ላይ በእርሱ የደረሰ ይደርስብናል ሳይሉ በድፍረት ሥጋውን ከዺላጦስ ተካሠው ለመኑ:: እንባቸው በፊታቸው እየወረደ ከመስቀል አውርደው በዮሴፍ በፍታና በኒቆዲሞስ ሽቱ ገነዙት::

እንዲህ እያሉ:-
"ሙታንን የምታስነሳ ጌታ አንተ ሞትክን?! ደካሞችን የምታጸና ቸር አንተ ደከምክን?!"
*በዚያች ሰዓት ጐልጐታ አካባቢ ዝማሬ መላእክትን እየሰሙ የክብር ባለቤትን ቀብረውታል:: ጌታችንም ከተነሳ በሁዋላ በንጹሕ አንደበቱ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል::

"እየሳማችሁ አክብራችሁ እንደ ገነዛችሁኝ እኔም በሰማይ በእንቁ ዙፋን ላይ አስቀምጣቹሃለሁ" ብሏቸዋል:: "አነ አብረክሙ ዲበ መንበረ ሶፎር" እንዲል:: ጻድቃን አበው ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በተረፈ ዘመናቸው ወንጌልን ሰብከው: ከአይሁድ መከራን ታግሰው: በበጐ ሽምግልና ዐርፈዋል::

††† ቅዱስ አቦሊ ሰማዕት †††

††† ቅዱስ አቦሊ የሰማዕታቱ #ቅዱስ_ዮስጦስና #ቅድስት_ታውክልያ ልጅ ሲሆን በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ያበራ የቤተ ክርስቲያን ዕንቁ ሰማዕት ነው:: የሚገርመኝ ሦስቱ የግማሹ ዓለም አስተዳዳሪዎች ነበሩ:: ዮስጦስ ንጉሥ: ታውክልያ ንግሥት: አቦሊ ደግሞ ልዑል ነው::

ነገር ግን ይህንን ክብራቸውን #በክርስቶስ ፍቅር ጐን: ሚዛን ላይ ቢያኖሩት በጣም ቀሎ ታያቸው:: 3ቱም ከዙፋናቸው ወርደው: ወገባቸውንም ታጥቀው: ባሮቻቸው በነበሩ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ብዙ ተንገላቱ:: መራራ ሞትንም ታገሱ::

በተለይ ቅዱስ አቦሊ ከአንጾኪያ ወደ ግብጽ (ብስጣ) ይዘው አምጥተው ክርስትናውን እንዲተው ያላደረጉት የለም:: በቁሙ ቆዳውን ገፈው: በቆዳው አቅማዳ ሰፍተው: ያንንም አሸክመው: የተገፈፈ አካሉን ጨውና ኮምጣጤ እየቀቡ አዙረውታል::

እርሱ ግን ጌታ በላከለት ድንቅ መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል ረዳትነት ሁሉን ችሎታል:: በዘመኑ ብዙ ተአምራትን የሠራ ሲሆን አንድ ጊዜ ቤት ተንዶ 16 ሰዎች ቢያልቁ የተገፈፈ ቆዳውን እየጣለባቸው ተነስተዋል:: በተአምራቱና በተጋድሎውም ብዙ ሺህ አሕዛብን ለክርስትና: ብሎም ለሰማዕትነት አብቅቷል::

እርሱም ከብዙ የመከራ ጊዜያት በሁዋላ በዚህች ቀን አንገቱን ተከልሏል:: ጌታችን "ዜናሕን የጻፈውን: ያነበበውንና የሰማውን ይቅር እለዋለሁ" ብሎ ቃል ኪዳንን ሰጥቶታል::

††† ፈጣሪ ከጻድቃንና ሰማዕታት በረከትን አይለይብን:: ወርሐ ነሐሴንም ለበረከት ይቀድስልን::

††† ነሐሴ 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.በአተ ጾመ ፍልሠታ
2.አበው ሐዋርያት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ
3.ቅዱስ አቦሊ ሰማዕት
4.ታላቁ ቅዱስ ዸላሞን ገዳማዊ
5.ቅድስት ሐና (የእመ ብርሃን እናት)
6.ቅድስት ሐና ነቢይት (ወለተ ፋኑኤል)
7.ደናግል ቅዱሳት (የንግስት ሶፍያ ልጆች)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
4.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
5.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር

††† "የጌታ ኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረ የአርማትያስ #ዮሴፍ የጌታ ኢየሱስን ሥጋ ሊወስድ ዺላጦስን ለመነ:: ዺላጦስም ፈቀደለት:: ስለዚህም መጥቶ የጌታ ኢየሱስን ሥጋ ወሰደ:: ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ #ጌታ_ኢየሱስ መጥቶ የነበረ #ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ:: የጌታ ኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት::" †††
(ዮሐ. 19:38)

††† "በጽዮን መለከትን ንፉ:: ጾምንም ቀድሱ:: ጉባዔውንም አውጁ:: ሕዝቡንም አከማቹ:: ማሕበሩንም ቀድሱ:: ሽማግሌዎችንም ሰብስቡ:: ሕጻናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ:: ሙሽራው ከእልፍኙ: ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ::" †††
(ኢዩ. 2:15)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኩዋን ለጻድቃን ቅዱሳን #አባ_አብርሃም: #ቅዱስ_ዮሐንስ እና #አባ_ፊልዾስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †††

††† #አባ_አብርሃም_ክቡር ገዳማዊ †††

=>ጻድቁ ግብጻዊ ሲሆን በ4ኛው መቶ ክ/ዘ ከተነሱ ከዋክብት አንዱ ነው:: #ክርስቲያን ወላጆቹ በሥርዓት አሳድገው "ሚስት አግባ" አሉት:: እሺ እንዳይላቸው ከልጅነቱ ጀምሮ የተመኘው ምናኔ ሊቀርበት ሆነ:: እንቢ እንዳይላቸው ደግሞ ወላጆቹ ያዝናሉና የልቡን በልቡ ይዞ "እሺ" አላቸው::

+ሰርግ ተደግሶ: #ተክሊል ተደርሶ: ከአንዲት ክርስቲያን ጋር አጋቡት:: በጋብቻው ማግስት ግን ከነ ድንግልናው ጠፍቶ በርሃ ገባ:: በዚያም አንዲት በዓት አዘጋጅቶ ፈቃደ ሥጋውን እየቀጣ: ፈቃደ ነፍሱን እያለመለመ ለ10 ዓመታት ተቀመጠ::

+በነዚያ ሁሉ ዘመናት የሞቀ አልለበሰም: የላመ የጣመ ነገር አልበላም:: የፀሐይ ብርሃን እንኩዋ አልተመለከተም:: በዚያ ወራትም ወሬ ነጋሪ ወደ በዓቱ መጥቶ "ወላጆችህ ዐረፉ:: በቤት ውስጥ ከ6 ዓመት እህትህ ከማርያ በቀር ማንም የለምና የወላጆችህን ሃብት ውረስ" አለው::

+አባ አብርሃም የሚያደርገውን ያውቃልና ከበርሃ ወጥቶ ወደ ሃገር ቤት ሔደ:: ትንሽ እህቱን (6 ዓመቷ ነበር) ለቤተ ዘመድ አደራ ሰጥቶ: ሃብት ንብረቱን አንድ ሳያስቀር ለነዳያን በትኖ:ወደ በዓቱ ተመለሰ:: በዚያም እንዳስለመደ በጾምና ጸሎት ተወስኖ ለ10 ዓመታት ቆየ::

+ተጋድሎ በጀመረ በ20 ዓመቱ #እግዚአብሔር ለሌላ አገልግሎት ጠራው:: የግብጽ ሊቀ ዻዻስ #አባ_አብርሃምን አስመጥቶ ቅስናን ሾመውና "ሒደህ ወንጌልን ስበክ" አለው:: ችግሩ እርሱ የተላከባት ሃገር አንድም ክርስቲያን የሌለባት ከመሆኗ በባሰ እጅግ ጨካኝ ናቸው::

+ማንም ደፍሮ በዚያ ሃገር ውስጥ ነገረ እግዚአብሔርን የሚናገር ሰው አልነበረም:: አባ #አብርሃም ወደ ሃገር ገብቶ ወንጌልን ቢሰብክላቸው እንደ ልማዳቸው መሬት ላይ ጥለው ደበደቡት: አጥንቶቹንም ሰባበሩት:: ሞቷል ብለው ከከተማ ውጪም ጣሉት::

+እርሱ ግን በፈጣሪው ኃይል ጸንቶ ተነሳ:: ማስተማሩ ብቻውን መፍትሔ እንደማይሆን ተረድቷልና ስለ እነሱ ተግቶ ይጸልይ ጀመር:: አሕዛብ ጠዋት ቢመጡ በከተማዋ መሐል ላይ ሲጸልይ አገኙት:: ስለ ተናደዱ ድጋሚ አካሉን በዱላ ሰባብረው እየጐተቱ ከከተማ አስወጡት:: በዚያም ከነ ሕይወቱ ቀበሩት::

+ነገር ግን ጠዋት ሲመለሱ እዛችው ቦታ ላይ ሲጸልይ አገኙት:: ይሕ የሚደረገው ለእነርሱ ድኅነት መሆኑን አልተረዱምና እነርሱ በየቀኑ እየደበደቡና እያሰቃዩት እርሱ ስለ እነሱ እየጸለየ 10 ዓመታት አለፉ:: ቅዱሳን ተስፋ አይቆርጡምና በመጨረሻው ተሳካለት::

+የቅዱሱ የዘመናት ጸሎት ፍሬ አፍርቶ እግዚአብሔር በአሕዛብ ልቡና ያደሩ አጋንንትን አራቀለት:: አንድ ቀን ጠዋት የሃገሩ ሕዝብ ሁሉ (ወንዱ: ሴቱ: ትልቁ: ትንሹ) ወደ ጻድቁ መጸለያ መጡ:: ለእርሱስ የጠብ መስሎት ነበር:: እነርሱ ግን በአንድነት በፊቱ ተንበርክከው ሰገዱ:: ይቅር እንዲላቸውም ለመኑት::

+ቅዱሱ ይሕንን ሲመለከት ሐሴትን አደረገ:: ሁሉንም #በስመ_ሥላሴ አጥምቆ ክርስቲያን አደረጋቸው:: አብያተ ክርስቲያናትንም አነጸላቸው:: በሁዋላ ግን በጣም ሲወዱትና ሲያከብሩት ተመልክቷልና ከውዳሴ ከንቱ (#ስብሐት_ብጡል) መለየት ፈለገ:: ፈጣሪንም በቸርነቱ እንዲጠብቃቸው ለምኖ: በሌሊት ጠፍቶ ወደ ነበረበት በርሃ ገባ::

+እርሱ በበርሃ ሁኖ ስለ ትንሽ እህቱ #ማርያ ያስብ ነበርና አስጠራት:: "ምን ትፈልጊያለሽ?" አላት:: እርሷም "እንዳንተ መሆን" ስላለችው አስተምሮ: ፈትኖ አመነኮሳት:: ለጥቂት ዓመታት በሥርዓት ከኖረች በሁዋላ ግን ችግር ተፈጠረ::

+ከአንድ መነኩሴ ጋር በነበራት ያልተገባ ቅርርብ የዝሙት ፍላጐታቸውን መቆጣጠር ባለመቻላቸው በኃጢአት ወደቁ:: በዚህ ተስፋ ቆርጠው 2ቱም ቆባቸውን ጥለው ከተማ ገቡ:: ይልቁኑ እርሷ (ማርያ) ሴተኛ አዳሪ ሆነች::

+በዚያ ሰሞን ቅዱሱ አብርሃም ራዕይን ያያል:: ትልቅ ዘንዶ አንዲት ርግብን ሲውጣት: መልሶም ሲተፋት አይቶ እሕቱ መሆኗን ተረዳ:: ወዲያው ጥሩ ልብስና ፈረስ ተውሶ ተነሳና ወደ ከተማ ገባ:: የጦር መኮንን መስሎ እህቱ ቤት ገባ::

+ሸሽታ እንዳታመልጠው ቤቱን ዘጋና ራሱን ገለጠላት:: ደንግጣ እንደ በድን ብትሆንም እርሱ አረጋጋት:: "እህቴ! ንስሃ ግቢ: አምላክ ይራራልሻል" አላት:: ልቧ ወደ ምክሩ አዘንብሏልና የእህቱን ነፍስ ማርኮ ወደ ገዳም ተመለሰ::

+በዚያ በዓት ሠርቶላት: ቀኖናም ሰጥቷት ሔደ:: #ማርያም ስለ ኃጢአቷ ፈንታ የምትገርም የቅድስና ሰው ሆነች:: ያየ ሁሉ እየተደነቀባት ከዓመታት ተጋድሎ በሁዋላ ዐረፈች:: አባ አብርሃም በተረፈ ዘመኑ በንጹሕ ገዳማዊ ሕይወት ተጠምዶ ኑሯል::

+በዘመኑ ሁሉ በጥርሱ ስቆ: በከንፈሩም አልባሌ ነገርን ተናግሮ አያውቅም:: ልቡ በፈጣሪው ፍቅር የታሠረ ነበርና ሕማማተ ክርስቶስን እያሰበ እንባው ያለማቁዋረጥ ይፈስ ነበር:: ደግና ቅዱስ ሰው አብርሃም በዚህች ቀን ዐርፎ ተቀብሯል::

††† #ቅዱስ_ዮሐንስ_ጻድቅ †††

=>ይህ ቅዱስ የነበረው በዘመነ ሰማዕታት ቢሆንም እንደ ሰማዕታት ስቃይ አልደረሰበትም:: ክርስቲያኖችን እንዲገድሉና አብያተ ክርስቲያናትን እንዲያቃጥሉ ከተመደቡ ወታደሮች አንዱ ነበረ:: ታዲያ እንዲገድላቸው የሚሰጡትን ክርስቲያኖች እየወሰደ ይደብቃቸው ነበር::

+የመከራው ዘመን እስኪያልፍ ድረስም ይንከባከባቸው ነበር:: ሌሎች ወታደሮች እንዳይነቁበት ሁሌም "ክርስቲያኖችን በጣም እጠላለሁ" እያለ ያወራ ነበር:: እርሱ በሌሊት ሁሌም ለጸሎት ይተጋ ነበር:: በእንዲህ ያለ ግብር ኑሮም በዚህች ቀን በሰላም ዐርፏል::

††† #አባ_ፊልዾስ #ዘደብረ_ቢዘን †††

=>#ደብረ_ቢዘን በቀድሞ የኢትዮዽያ ክፍለ ሃገር (አሁን #ኤርትራ) ውስጥ የሚገኝ ታላቅ ገዳም ነው:: ገዳሙ #እመቤታችን_ድንግል_ማርያም በስደቷ ያረፈችበት: ጌታችን የባረከውና የመረጠው ቦታ ነው:: #አባ_ዮሐንስን: #አባ_ናርዶስንና ሌሎች ከዋክብት አበውን ያፈራ ሲሆን የአባ ፊልዾስን ያሕል ግን አልተገኘም::

+ጻድቁ በግል የተጋድሎ ሕይወታቸው: ገዳሙን በአበ ምኔትነት በመምራታቸውና በስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው ምስጉን ነበሩ:: እርሳቸው ቅዱስ ሆነው አልበቃቸውምና ብዙ ቅዱሳንን ወልደዋል:: ይሕች ዕለትም የዕረፍታቸው መታሰቢያ ናት::

=>አምላከ ጻድቃን ገዳማትን ከመከራ ይጠብቅልን:: ከአባቶቻችን ቅዱሳን ጸጋ በረከትንም ይክፈለን::

=>ነሐሴ 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አባ አብርሃም ገዳማዊ
2.ቅድስት ማርያ እህቱ
3.ቅዱስ ዮሐንስ ጻድቅ
4.አባ ፊልዾስ ዘደብረ ቢዘን

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
2.ቅዱስ ዻውሎስ ብርሃነ ዓለም
3.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
4.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
5.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
6.ቅድስት አውጋንያ (ሰማዕትና ጻድቅ)

=>+"+ በድካም: አብዝቼ በመገረፍ: አብዝቼ በመታሠር: አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ:: በድካምና በጥረት: ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት: በራብና በጥም: ብዙ ጊዜም በመጦም: በብርድና በራቁትነት ነበርሁ. . . የቀረውን ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው:: +"+ (2ቆሮ 11:23)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
††† እንኳን ለካህኑ ሰማዕት ቅዱስ አልዓዛር እና ለቅዱሳን ቤተሰቡ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ አልዓዛር ካህን †††

††† ይህ ቅዱስ #የብሉይ_ኪዳን_ሰማዕታት ተብለው ከሚታወቁት ዋነኛው ነው:: የነበረበት ዘመንም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ሲሆን " #ዓመተ_መቃብያን/ #ዘመነ_ካህናት" ይባላል::

በወቅቱ ሰሎሜ የምትባል ደግ ሴት አግብቶ ይኖር የነበረው ቅዱስ አልዓዛር በኢየሩሳሌም ተወዳጅ ነበር:: ሐረገ ትውልዱ ከአሮን ወገን ነውና በክህነቱ ተግቶ ያገለግል ነበር:: በዚያ ላይ ሊቀ ካህንነትን በመመረጡ ሕዝቡን ይሠራ: ያስተምር: ያስተዳድር ነበር::

ቅዱስ አልዓዛር ከተባረከች ሚስቱ ሰሎሜ 7 ወንዶች ልጆችን አፍርቷል:: እነርሱንም በሥርዓት አሳድጐ የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች እንዲሆኑ አድርጐ ነበር:: በዚያው ዘመን በኢየሩሳሌም አካባቢ የሚኖሩ 3 እኩያን (ክፉ) ካህናት ነበሩ::

እነዚሁም ሕዝቡን ከማስቸገር: ፈጣሪን ከማሳዘን ቦዝነው አያውቁም ነበር:: የክፋታቸው መጨረሻ ግን የገዛ ሃገራቸውን ማጥፋት ሆነ:: ነገሩ እንዲህ ነው:- 3ቱም ተመካክረው የአልዓዛርን የሊቀ ካህንነት ቦታ ሊቀሙ ወስነው ወደ እርሱ ሔዱና እንዲህ አሉት::

"ሹመት በተርታ: ሥጋ በገበታ" ሲሆን ያምራልና እኛ በተራችን በወንበሩ ላይ እንቀመጥ::"
እርሱ ግን "ሕዝቡን ጠይቃችሁ ተሾሙ" አላቸው:: እነርሱም ሕዝቡን ጠርተው "ሹመት ይገባናል" ቢሏቸው ሕዝቡ መልሶ "አልዓዛርን የሾመው እግዚአብሔር ነውና እናንተም ከፈጣሪ ጠይቃችሁ ተሾሙ" አሏቸው::

በዚህ ጊዜ 3ቱ እኩያን ተቆጡ:: ምክንያቱም እግዚአብሔር እንደ ማይሰጣቸው ያውቃሉና:: ወዲያው ግን 3ቱም ከአካባቢው ጠፉ:: ከኢየሩሳሌም ወጥተው ወደ ጨካኙ የግሪክ ንጉሥ አንጥያኮስ ሔዱ::

አንጥያኮስ ማለት "ቀኝ ዐይናችሁን ገብሩልኝ" የሚል ንጉሥ ነው:: እርሱን " #ኢየሩሳሌም ባለቤት የላትምና ሒደህ ውረራት" አሉት:: "አጥሩ ጥብቅ ነው:: በምን እገባለሁ?" ቢላቸው "እኛ በመላ እናስገባሃለን" አሉት:: እርሱም 240,000 ሠራዊት አስከትቶ ወረደ::

እነርሱ ቀድመው ወደ ኢየሩሳሌም ገብተው ያስወሩ ጀመር:: "እናንተ ሹመት ብትነሱንም እኛ ግን አንጥያኮስን ያህል ንጉሥ በእሥራኤል አምላክ አሳምነን መጣን" እያሉ ይሰብኩ ገቡ:: ቅዱስ አልዓዛር "አትስሟቸው:: በዚያም ላይ አሕዛብ የተቀደሰውን ምድር መርገጥ የለባቸውም" ብሎ ነበር::

ነገር ግን አንዳንድ ችኩሎች አይጠፉምና ፈጥነው የከተማዋን በር ከፈቱት:: ሠራዊቱን ደብቆ ትንሽ ራሱን የቆመ የመሰለው አንጥያኮስ በምክንያት: በክፋትና በመላ ሁሉን ሠራዊቱን አስገባ:: የሚገርመው በጊዜው የከተማዋ ሕዝብ 12 እልፍ (120,000) ሲሆን ንጉሡ ያስገባው ሠራዊት ግን 24 እልፍ (240,000) ሆኖ ተገኘ::

ወዲያው አንጥያኮስ ሕዝቡን ሰበሰበና አልዓዛርን ለብቻው ጠርቶ ተናገረው:: "አንተ አምላክህን እንደምትወድ ሰምቻለሁ:: አንተ የበጉን መሥዋዕት በልተህ: #ለሥዕለ_ኪሩብ ሰግደህ: ሕዝቡን ግን እሪያ (አሳማ) እንዲበላና ለፀሐይ እንዲሰግድ አድርግልኝ" አለው::

ቅዱስ አልዓዛር መለሰለት:- "እግዚአብሔር የሾመኝኮ በጐ ሃይማኖትን ላስተምር እንጂ ለክፋት አይደለም:: ለሕዝቤ የክፋት አብነት ፈጽሞ አልሆንም" አለው:: ያን ጊዜ ንጉሡ በቅዱሱ ላይ ተቆጣ:: "የምልህን ካላደረግህ ብዙ ግፍ ይደርስብሃል" ቢለው ቅዱሱ መልሶ "የፈለግኸውን አድርግ" አለው::

በዚያን ጊዜ ንጉሡ የቅዱሱን ሚስትና 7 ልጆች እንዲያመጡለት አዘዘ:: ቅዱሱ እያየ ከፊቱ ላይ 7ቱንም ልጆቹን በሰይፍ አስመታቸውና 7ቱም ወደቁ:: ለአንድ አባት ይህ የመጨረሻው መራራ ፈተና ነው:: #አልዓዛር ግን ምን አንጀቱ በኀዘን ቢቃጠልም ከልጆቹ ለእግዚአብሔር አድልቷልና ቻለው ታገሠው::

በዚህ ለውጥ እንዳልመጣ ያየው ንጉሡ ሌላ ፍርድ ተናገረ:: ቅዱሱንና ሚስቱን ( #ሰሎሜን) በፈትል ጠቅልለው በሠም ነከሯቸው:: (ጧፍ እንደሚሠራበት መንገድ ማለት ነው:: )

አሁንም ግን ከአምልኮታቸው ፈቀቅ ባለማለታቸው ትልቅ ብረት ምጣድ ተጥዶ: 2ቱም ከነነፍሳቸው እንዲቃጠሉ ተደረገ:: ቀጥሎም ሕዝቡን እንዲፈጁ አዋጅ ወጣ:: በከተማዋ ከነበረው ሕዝብ 40,000 ያህሉ ተገደሉ::

40,000 ያህሉ ሲማረኩ 40,000 ያህሉን ደግሞ #ይሁዳ የሚባል አርበኛ በር ሰብሮ ይዟቸው ሸሸ:: "እንሾማለን: እንሸለማለን" ብለው ሕዝባቸውን ያስፈጁ እነዚያ ካህናትም #እግዚአብሔር ፈርዶባቸው እነርሱም ተገደሉ:: ቅዱሱ የአልዓዛር ቤተሰብ ግን የክብርን አክሊል አግኝተዋል::

††† #የእሥራኤል_አምላክ ቸሩ እግዚአብሔር እንዲህ ካለው መከራ በኪነ ጥበቡ ይሰውረን:: ከቅዱሳኑ በረከትም አይለየን::

††† ነሐሴ 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አልዓዛር ካህን (ሰማዕት)
2.ቅድስት ሰሎሜ ሰማዕት (ሚስቱ)
3."7ቱ" ቅዱሳን ሰማዕታት (ልጆቹ)
4.ቅዱስ አሞን ሰማዕት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
3.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
4.አቡነ ኪሮስ
5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
6.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

††† "አቤቱ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ::
የቅድስናህንም #መቅደስ አረከሱ::
#ኢየሩሳሌምንም እንደ መደብ አደረጉአት::
የባሪያዎችህንም በድኖች ለሰማይ ወፎች መብል አደረጉ::
የጻድቃንህንም ሥጋ ለምድር አራዊት::
ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ውሃ አፈሰሱ::
የሚቀብራቸውም አጡ::" †††
(መዝ. 78:1)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
✞✞✞ 🌷በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞🌷

❖ ነሐሴ ፲፮ ❖

✞✞✞ እንኩዋን ለእመቤታችን
#ቅድስት_ድንግል_ማርያም ዓመታዊ የትንሣኤና የዕርገት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+"+ #🌷ዕርገተ_ድንግል_ማርያም🌷 +"+

=>ይሕች ዕለት እጅጉን ታላቅና ክብርት ናት:: ምክንያቱም
የድንግል ማርያም ሥጋዋ ተነስቶ ዐርጐባታልና:: ድንግል
እመቤታችን ተነሳች: ዐረገች ስንል እንደ እንግዳ ደርሶ:
እንደ ውሃ ፈሶ: ወይም በአጋጣሚ የተደረገ አይደለም::
ጥንቱን በአምላክ ልቡና ታስቦ: ሁዋላም ትንቢት
ተነግሮለት ነው::

¤ታሪኩ: ነገሩ: ምሥጢሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም
በአምላክ ልቡና ታስባ ትኖር ነበር:: ከነገር ሁሉ በፊት
#እግዚአብሔር እናቱን ያውቃት ነበር::

¤ዓለም ተፈጥሮ: አዳምና ሔዋን ስተው: መርገመ ሥጋና
መርገመ ነፍስ አግኝቷቸው: በኃዘን ንስሃ ቢገቡ
"እትወለድ እም ወለተ ወለትከ - ከ5 ቀን ተኩል (5500
ዘመናት) በሁዋላ ካንተ ባሕርይ ከምትገኝ #ንጽሕት_ዘር
ተወልጄ አድንሃለሁ" ብሎ ተስፋ ድኅነት ሰጠው::
¤ከአዳም አንስቶ ለ5500 ዓመታት አበው: ነቢያትና
ካህናት ስለ ድንግል ማርያም ብዙ ሐረገ ትንቢቶችን
ተናገሩ:: መዳኛቸውን ሱባኤ ቆጠሩላት:: ምሳሌም
መሰሉላት:: ከሩቅ ዘመን ሁነውም ሊያገኟት እየተመኙ
እጅ ነሷት::
"እምርሑቅሰ ርእይዋ: ወተአምኅዋ" እንዲል::

+"+ የድንግል ማርያም ሐረገ ትውልድ +"+

*ከአዳም በሴት
*ከያሬድ በሔኖክ
*ከኖኅ በሴም
*ከአብርሃም በይስሐቅ
*ከያዕቆብ በይሁዳና በሌዊ
*ከይሁዳ በእሴይ: በዳዊት: በሰሎሞንና በሕዝቅያስ
ወርዳ ከኢያቄም ትደርሳለች::

¤ከሌዊ ደግሞ #በአሮን: #አልዓዛር: #ፊንሐስ:
#ቴክታና_በጥሪቃ አድርጋ ከሐና ትደርሳለች::

¤አባታችን #አዳም ከገነት በወጣ በ5,485 ዓመት
#ወላዲተ_አምላክ ንጽሕና ሳይጐድልባት: ኃጢአት
ሳያገኛት: ጥንተ አብሶ ሳይደርስባት ከደጋጉ
#ኢያቄም_ወሐና ትወለዳለች:: (ኢሳ. 1:9, መኃ. 4:7)
"ወኢረኩሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ" እንዳለ::
(#ቅዱስ_ቴዎዶጦስ_ዘዕንቆራ)

¤ከዚያም ከእናት ከአባቷ ቤት ለ3 ዓመታት ቆይታ ወደ
#ቤተ_መቅደስ ትገባለች:: በቤተ መቅደስም ለ12
ዓመታት ፈጣሪዋን እግዚአብሔርን እያመሰገነችና
እያገለገለች: እርሷን ደግሞ #መላእክተ_ብርሃን
እያገለገሏት: ሕብስት ሰማያዊ: ጽዋዕ ሰማያዊ
እየመገቧት ኑራለች:: 15 ዓመት በሞላት ጊዜ ጻድቅ
#አረጋዊ_ዮሴፍ ያገለግላት ዘንድ ወደ ቤቱ ወሰዳት::

¤በዚያም መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዜና
ድኅነትን ነግሯት አካላዊ ቃልን በማሕጸንዋ ጸነሰችው::
ነደ እሳትን ተሸከመችው: ቻለችው:: "ጾርኪ ዘኢይትጸወር:
ወአግመርኪ ዘኢይትገመር" እንዳለ::
(#ሊቁ_ቅዱስ_ኤፍሬም #ለብሐዊ)

¤ወልደ እግዚአብሔርን ለ9 ወራት ከ5 ቀናት ጸንሳ:
እንበለ ተፈትሆ (በድንግልና) ወለደችው:: (ኢሳ. 7:14)
"#ኢየሱስ" ብላ ስም አውጥታለት በናዝሬት ገሊላ ለ2
ዓመታት ቆዩ::

¤አርዌ ሔሮድስ "እገድላለሁ" ብሎ በተነሳበት ወቅትም
ልጇን አዝላ በረሃብ እና በጥም: በላበትና በድካም:
በዕንባና በኃዘን ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ከገሊላ እስከ
#ኢትዮዽያ ተሰዳለች:: ልጇ ጌታችን 5 ዓመት ከ6 ወር
ሲሆነው: ለርሷ ለድንግል ደግሞ 21 ዓመት ከ3 ወር
ሲሆናት ወደ ናዝሬት ተመለሱ::

¤በናዝሬትም ለ24 ዓመታት ከ6 ወራት ልጇን ክርስቶስን
እያሳደገች: ነዳያንን እያሰበች ኑራለች::

እርሷ 45 ዓመት: ልጇ 30 ዓመት ሲሆናቸው ጌታችን
ተጠምቆ በጉባኤ ትምህርት: ተአምራት ጀመረ:: ለ3 ዓመታት ከ3 ወራትም ከዋለበት እየዋለች: ካደረበትም
እያደረች ትምህርቱን ሰማች::

¤የማዳን ቀኑ ደርሶ ልጇ ክርስቶስ ሲሰቀልም
የመጨረሻውን ፍጹም ሐዘን አስተናገደች:: አንጀቷ በኃዘን
ተቃጠለ:: በነፍሷም ሰይፍ አለፈ:: (ሉቃ. 2:35) ጌታ በተነሳ ጊዜም ከፍጥረት ሁሉ ቀድማ ትንሣኤውን አየች::
ለ40 ቀናትም ሳትለይ ከልጇ ጋር ቆየች::

¤ከልጇ #ዕርገት በሁዋላ #በጽርሐ_ጽዮን ሐዋርያትን
ሰብስባ ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ አበቃች:: በጽርሐ ጽዮን
ከአደራ ልጇ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ለ15 ዓመታት ኖረች::
በእነዚህ ዓመታት ሥራ ሳትፈታ ስለ ኃጥአን ስትማልድ:
ቃል ኪዳንን ከልጇ ስትቀበል: ሐዋርያትን ስታጽናና:
ምሥጢርም ስትገልጽላቸው ኑራለች::

¤ዕድሜዋ 64 በደረሰ ጊዜ ጥር 21 ቀን #መድኃኒታችን
አእላፍ ቅዱሳንን አስከትሎ መጣ:: ኢየሩሳሌምን
ጨነቃት:: አካባቢውም በፈውስ ተሞላ:: በዓለም ላይም
በጐ መዓዛ ወረደ:: እመ ብርሃን ለፍጡር ከዚያ በፊት
ባልተደረገ: ለዘለዓለምም ለማንም በማይደረግ ሞገስ:
ክብርና ተአምራት ዐረፈች:: ሞቷ ብዙዎችን አስደንቁአል::
"ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ:
ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ" እንዲል::

¤ከዚህ በሁዋላ መላእክት እየዘመሩ: ሐዋርያቱም
እያለቀሱ ወደ ጌቴሴማኒ: በአጐበር ሥጋዋን ጋርደው
ወሰዱ:: ይሕንን ሊቃውንት:-
"ሐራ ሰማይ ብዙኃን እለ አልቦሙ ሐሳበ:
እንዘ ይዜምሩ ቅድሜኪ ወመንገለ ድኅሬኪ ካዕበ:
ማርያም ሞትኪ ይመስል ከብካበ" ሲሉ ይገልጡታል::

¤በወቅቱ ግን አይሁድ በክፋት ሥጋዋን እናቃጥል ስላሉ
#ቅዱስ_ገብርኤል (ጠባቂ መልአክ ነው) እነርሱን ቀጥቶ
እርሷን ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ወስዶ በዕጸ ሕይወት ሥር
አኑሯታል::

በዚያም #መላእክት እያመሰገኗት ለ205 ቀናት
ቆይታለች::

¤#ቅዱስ_ዮሐንስ መጥቶ ለሐዋርያቱ ክብረ ድንግልን
ቢነግራቸው በጐ ቅንአት ቀንተው በነሐሴ 1 ሱባኤ
ጀመሩ:: 2ኛው ሱባኤ ሲጠናቀቅም ጌታ የድንግል
ማርያምን #ንጹሕ_ሥጋ ሰጣቸው:: እየዘመሩም
#በጌሴማኒ ቀብረዋታል::

¤በ3ኛው ቀን (ነሐሴ 16) እንደ ልጇ ባለ #ትንሣኤ
ተነስታ ዐርጋለች:: ትንሣኤዋንና ዕርገቷንም ደጉ ሐዋርያ
#ቅዱስ_ቶማስ አይቶ: መግነዟን ተቀብሏል:: ሐዋርያቱም
መግነዟን ለበረከት ተካፍለው: እንደ ገና በዓመቱ ነሐሴ
1 ቀን ሱባኤ ገቡ::

¤ለ2 ሳምንታት ቆይተው: በዚህች ቀንም ሁሉንም ወደ
ሰማይ አወጣቸው:: በፍጡር አንደበት ተከናውኖ
የማይነገር ተድላ: ደስታና ምሥጢርንም አዩ:: ጌታ ራሱ
ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው:: የበዓሉን ቃል ኪዳን
ሰምተው: ከድንግል ተባርከው ወደ #ደብረ_ዘይት
ተመልሰዋል::

=>ጽንዕት በድንግልና: ሥርጉት በቅድስና #እመቤታችን:
ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን:: አእምሮውን:
ለብዎውን: ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን::

+"+ #🌷ቅዱስ_ጊጋር_ሶርያዊ🌷 +"+

=>ይሕ ቅዱስ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን የሶርያ
መስፍን የነበረ ሲሆን #ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ
ሰምቷል:: እመ ብርሃን ለስደት ስትወጣ በመጀመሪያ
የሔደችው ወደ #ሊባኖስ ተራሮች ነው::
#መስፍኑ_ጊጋር ነበርና እርሱም የአምላክ እናትነቷን
አምኖ አክብሮ አስተናግዷታል::

+ሔሮድስም ይሕንን ሲሰማ ጦር አስከትቶ ወደ ጊጋር
ሔደ:: መስፍኑ ጊጋር ሔሮድስን እንደማይችለው ሲረዳ
ድንግል ማርያምን ወደ #ግብጽ ሸሽጐ አሸሻት::
ሔሮድስንም ፊት ለፊት ተገናኘው:: ከአቅሙ በላይ
ስለነበረም በወታደሮች ተማርኮ ወደ ሔሮድስ ቀረበ::
††† እንኳን ለሰማዕታት ቅዱስ እንጣዎስ እና ቅዱስ ያዕቆብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ እንጣዎስ አሞራዊ †††

††† ይሕ ቅዱስ በቀደመ ሕይወቱ ክርስቲያኖችን የሚጠላ አስቸጋሪ አረማዊ ነበር:: ሃገሩ #ሶርያ( #ደማስቆ) ሲሆን ግብሩ ጣዖት ማምለክና መስረቅ ነበር:: በቅድስት ቤተ ክርስቲያንና በምዕመናን ላይም ግፍን ፈጽሟል:: በሥጋዊ ጉልበቱ ኃይለኛ ስለ ነበር የተፈራ ነው::

ሁልጊዜ በጠዋት ወደ #ቤተ_ክርስቲያን ይሔዳል:: የሚሔደው ግን ንዋያተ ቅድሳትን ለመዝረፍ: አንድም ካህናትን ለመደብደብ ነበር:: የሚገርመው ግን የወቅቱ ምዕመናንና ካህናት ይህን ሁሉ እያደረገባቸው አይጠሉትም:: ይልቁኑ ይጸልዩለት ነበር እንጂ:: ምክንያቱም ክርስትና ማለት ጠላትን መውደድ ነውና:: (ማቴ. 7)

የእግዚአብሔር ትዕግስትና የምዕመናን ጸሎት ተደምሮ አንድ ቀን ፍሬ አፈራ:: እንጣዎስ እንደ ለመደው ለክፉ ሥራ ወደ #ቅዱስ_ቴዎድሮስ ቤተ ክርስቲያን ይሔዳል:: ከዚያም እንደ ደረሰ ወደ ውስጥ ገብቶ: የሚማታውን ተማቶ: የሚዘርፈውንም ዘርፎ: የተረፉትን ንዋያተ ቅድሳት በእሳት አቃጠላቸው::

#እግዚአብሔር ከዚህም በላይ ታጋሽ ነውና አላጠፋውም:: "ዘኢይፈቅድ ለኃጥእ ሞቶ" እንዲል የኃጢአተኛውን መመለስ እንጂ መሞቱን አይፈልግም:: ለዚያም ነው ዛሬ ይሔ ሁሉ ግፍ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየተሠራ እግዚአብሔር እንደማያይ ዝም የሚለው:: ለሁሉም ቀን አለውና በፈረደ ቀን ግን በፊቱ የሚቆም አይኖርም::

እንጣዎስ ግን የሠራውን ሠርቶ እወጣለሁ ሲል አልተሳካለትም:: ከበሩ አካባቢ ሲደርስ: ከወደ ሰማይ አካባቢ ድምጽ ሰምቶ ቀና ሲል መላእክት እንደሱ ዓይነት ኃጢአተኞችን አሰልፈው በጦርና በቀስት ሲወጉአቸው ተመለከተ::

ድንገት ግን ከመላእክቱ አንዱ ዘወር ብሎ አንድ ቀስት ወደ እንጣዎስ ወረወረ (ተኮሰ):: ቀስቷ አካሉ ውስጥ ገብታለችና እንጣዎስ መሬት ላይ ወድቆ ለሞት ደረሰ:: ላበቱ በግንባሩ ላይ በጭንቅ እየፈሰሰ ጮኸ::

"ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ማረኝ? ራራልኝ? ይቅር በለኝ? በድፍረት ባለ ማወቅም በድየሃለሁ:: ይቅር በለኝና ላምልክህ: ስምህንም ልሸከም" ሲል በጭንቀት ውስጥ ሆኖ አሰምቶ ጸለየ:: በዚያ የነበሩ ምዕመናን ማን: በምን እንደ ወጋው ባያውቁም ባዩት ነገር ግን እጅግ ደስ አላቸው:: እነርሱም የፈለጉትና የጸለዩለት ነገር ይሔው ነበርና::

ወዲያው ግን እንጣዎስ ከሞት ጫፍ ተመልሶ ተነሳ:: መጀመሪያ በቦታው የነበሩ ካህናትና ምዕመናንን "ይቅር በሉኝ?" አለ:: ቀጥሎም ወደ ዻዻስ ዘንድ ሔዶ "አጥምቀኝ" ሲል ጠየቀ:: እርሱ በሚጠመቅበት ቀን ብዙ አሕዛብና ክርስቲያኖች ተሰብስበው ነበር::

እርሱ በከተማዋ ዝነኛ ነበር:: ሥርዓቱ ሁሉ ተደርሶ ቅዱሱ ወደ ውሃ ገንዳው ሲገባ ሁሉ እያዩ የብርሃን ምሰሶ ከሰማይ ወረደ:: ይህንን በገሃድ የተመለከቱ ከ10,000 በላይ አሕዛብ ወዲያውኑ በክርስቶስ አምነው አብረውት ተጠምቀዋል::

ቅዱስ እንጣዎስ ከዚህ በሁዋላ ምስጉን ክርስቲያን ሆነ:: ስለ ቀደመ ሕይወቱ ፈንታ ጾምን: ጸሎትን: ፍቅርን: ምጽዋትን ገንዘብ አደረገ:: ሕይወቱም ለብዙ ሰዎች መስታወት ሆነ:: #እመቤታችን ድንግል ማርያምንም ይወዳት ነበርና ወደ ቅዱሳን ማሕበር ( #ኢየሩሳሌም) ወስዳው በሥጋዊ አንደበት ተከናውኖ ሊነገር የማይቻል ምሥጢርን ገልጣለታለች::

እነዚህን የቅድስና ጊዜያት በስኬት ያሳለፈው ቅዱስ እንጣዎስ መጨረሻው ሰማዕትነት ሆነ::
አረማውያን ወገኖቹና ቀድሞ የሚያውቁት ወደ ቀደመ ክፋትና ክህደት እንዲመለስ ጠየቁት:: "አይሆንም" አላቸው:: በአደባባይ ለፍርድ አቅርበው ደሙ እስኪፈስ ገረፉት::

ጥርሶቹን በሙሉ በድንጋይ አረገፏቸው:: ደሙና ጥርሶቹ መሬት ላይ ተዘሩ:: ነገር ግን ይሕ ስቃይ ቅዱሱን ከፍቅረ ክርስቶስ ሊለየው አልቻለም:: አሕዛብም ተስፋ ቆርጠው በዚህች ቀን ገድለውታል:: ቅዱስ እንጣዎስም ከሁዋለኛው ዘመን #ሰማዕታት እንደ አንዱ ተቆጥሯል::

††† ቅዱስ ያዕቆብ ግብጻዊ †††

††† ቅዱስ ያዕቆብ ተወልዶ ያደገው #መኑፍ (ግብጽ) ውስጥ ሲሆን ዘመኑም 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ወላጆቹ የተባረኩ ናቸውና እርሱ ሳይወለድ የነበሯቸውን 3 ሴቶች ልጆች "ተማሩ" ብለው ወደ ገዳም ቢያስገቧቸው በዚያው መንነው ቀሩባቸው::

በዚህ ሲያዝኑ #ቅዱስ_ያዕቆብ ተወልዶላቸዋል:: እነርሱም በቃለ እግዚአብሔርና በጥበብ አሳድገውታል:: ትንሽ ከፍ ሲል በአካባቢው ከነበረ አንድ ቅዱስ ሽማግሌ ጋር ተደብቀው ገድልን ይሠሩ ነበር:: ሁሌም መልካም ምግባራትን ከመፈጸም ባለፈ ሙሉውን ሌሊት ባሕር ውስጥ ሰጥመው ይጸልዩ ነበር::

ዘመነ ሰማዕታት በመጣ ጊዜም 2ቱ ተመካክረው ስመ ክርስቶስን በገሃድ ሰብከዋል:: በዚህ ምክንያት ቅዱሱን ሽማግሌ ወዲያው ሲገድሉት ቅዱስ ያዕቆብን ግን ብዙ አሰቃይተውታል:: በመጨረሻም በዚህች ቀን ተሰይፎ የክብርን አክሊል ተቀብሏል::

††† አምላከ ሰማዕታት ቤተ ክርስቲያንን ከመከራ ይጠብቅልን:: ከበረከታቸውም ያሳትፈን::

††† ነሐሴ 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ተዝካረ ፍልሠታ ለማርያም ድንግል
2.ቅዱስ እንጣዎስ አሞራዊ (ሰማዕት)
3.ቅዱስ ያዕቆብ ግብጻዊ (ሰማዕት)
4.ቅዱስ አክራጥስ ሰማዕት
5.አባ እለእስክንድሮስ ዘቁስጥንጥንያ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
4.አባ ገሪማ ዘመደራ
5.አባ ዸላሞን ፈላሢ
6.አባ ለትጹን የዋህ
7.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ)

††† "ኃጢአተኞችን ሊያድን #ክርስቶስ_ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው:: ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ:: ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ::" †††
(1ጢሞ. 1:15)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††