ስንክሳር ወግጻዌ ዘተዋሕዶ
853 subscribers
3.46K photos
103 videos
194 files
1.2K links
የየዕለቱ ስንክሳር እና ግጻዌ የሚቀርብበት ቻናል ነው፡፡

ለማንኛውም አስተያየት እና እርማት
@zetaodokos ላይ ይላኩልን።

👇👇የYoutube Channel ይቀላቀሉ👇👇
https://youtube.com/channel/UCupqpIYe_mMpSM7jMT3Njhw
Download Telegram
✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ፡፡ ✞

✞ ጥር 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ✞

+"
#ቅዱስ_ጊዮርጊስ_ልዳዊ "+

=> መጽሐፈ ገድሉ እንደሚለው የሰማዕታት አለቃቸው:
አንድም ሞገሳቸው ታላቅና ክቡር ሰማዕት ቅዱስ
ጊዮርጊስ ከ7 ዓመታት
ስቃይ በኋላ ተሰይፏል:: ይህስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ:-

+ቅዱሱ የተወለደው ከአባቱ ዘረንቶስ (አንስጣስዮስ) እና
ከእናቱ ቴዎብስታ የድሮው ፋርስ ግዛት ፍልስጥኤም
(ልዳ) ውስጥ
ነው:: የተባረኩ ወላጆቹ ክርስትናን ጠንቅቀው
አስተምረውት አባቱ ይሞታል::

+ቅዱስ ጊዮርጊስ 20 ዓመት ሲሞላው የአባቱን ስልጣን
እጅ ለማድረግ ሲሔድ የቢሩት (የአሁኗ ቤይሩት-ሊባኖስ)
ሰዎች
ዘንዶ/ደራጎን ሲያመልኩ አገኛቸው:: እርሱ ግን
የከተማውን ሕዝብ አስተምሮ: አሳምኖ: ደራጎኑንም
በፈጣሪው ኃይል ገድሎ
መንገዱን ቀጥሏል::

+ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱድያኖስና 70 ነገሥታት ዘንድ
ሲደርስ ክርስቶስ ተክዶ ለጣዖት ይሠገድ ነበር:: በዚያች
ሰዓት
ድንግል እመቤታችን ወደ ሰማዕቱ መጥታ መከራውንና
ክብሩን ነገረችው:: እርሱም በክርስቶስ ስም መሞት
ምርጫው ነበርና
ከእመቤታችን ተባርኮ ወደ ምስክርነት አደባባይ (ዐውደ
ስምዕ) ደረሰ::

+ከዚያም ለተከታታይ 7 ዓመታት ብዙ ጸዋትወ
መከራዎችን ተቀበለ:: 3 ጊዜ ሙቶ ተነሳ:: ከሰው ልጅ
የተፈጥሮ ትዕግስት
በላይ የሆነ ስቃይን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በመቀበሉ
የሰማዕታት አለቃቸው: ፀሐይና የንጋት ኮከብ በሚል
ይጠራል::
"ተውላጠ ጻማሁ ወሕማሙ:
ዘተለዐለ ሞገሰ ስሙ" እንዲል መጽሐፍ::

+ከ7 ዓመታት መከራ በኋላም ከብዙ ተዓምራት ጋር
ተሰይፎ ደም: ውሃና ወተት ከአንገቱ ፈሷል:: 7
አክሊላትም
ወርደውለታል::

+" #ዝርወተ_ዓጽሙ "+

+ይህቺ ዕለት ለሰማዕቱ 'ዝርወተ አጽሙ' ትባላለች::
በቁሙ 'አጥንቱ የተበተነበት' እንደ ማለት ነው:: ቅዱስ
ጊዮርጊስን ለዘመናት በብዙ ስቃያት ሲያስጨንቁት ኖረው
በጽናቱ አሸነፋቸው:: 70 ነገሥታትን ከነ ሠራዊታቸው
ከማሳፈሩ
ባሻገርም በርካታ (በመቶ ሺ የሚቆጠሩ) አሕዛብን ማርኮ
ለሰማዕትነት አበቃ::

+በዚህ የተበሳጨ ዱድያኖስም ኮከበ ፋርስ ቅዱስ
ጊዮርጊስን እንዲቆራርጡት አዘዘ:: ወታደሮቹም ቅዱሱን
ቆራርጠው: በብረት
ምጣድ ላይ ጠበሱት:: ያለ ርሕራሔም አካሉን አሳረሩት::
ቀጥለውም ፈጭተው አመድ አደረጉት::

+በአካባቢው ወደ ነበረው ትልቅ ተራራ ጫፍ (ደብረ
ይድራስ) ወጥተውም በነፋስ በተኑት::
"ሐረድዎ ወገመድዎ: ወዘረዉ ሥጋሁ ከመ ዓመድ"
እንዲል:: (ምቅናይ)

+እነርሱ ይህንን ፈጽመው ዘወር ሲሉ ግን የቅዱሱ ዓጽም
ባረፈባቸው ዛፎች: ቅጠሎችና ድንጋዮች ሁሉ "ቅዱስ
ጊዮርጊስ ሊቀ
ሰማዕታት" የሚል ጽሑፍ ተገኘ:: ስለዚህም ይህቺ ዕለት
ቅዱሱ አለቅነትን የተሾመባት ናት ማለት ነው::

+ወዲያው ግን ኃያል ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ
ከተበተነበት ተነስቶ ወታደሮችን አገኛቸውና "በክርስቶስ
እመኑ" ብሎ:
አስደንቆ ወደ ሕይወት መራቸው:: 70ው ነገሥታት ግን
አፈሩ::

+" #ቅዱስ_ባኮስ_ጃንደረባው "+

+'ጃንደረባ' የሚለው ቃል በግዕዙ 'ሕጽው' ተብሏል:: ይህ
ስም በቤተ ክርስቲያን የተለመደ እንጂ እንግዳ አይደለም::
መድኃኒታችን እንዳለው በተፈጥሮ የሆኑ: ሰዎች እንዲያ
ያደረጉዋቸውና ራሳቸውን ስለ ጽድቅ ጃንደረባ ያደረጉ
ብዙዎች ናቸውና::

+ኢትዮዽያዊው ጃንደረባ ቅዱስ ባኮስም (አንዳንዴ
አቤላክ / አቤሜሌክም ይባላል):-
*በ1ኛው መቶ ክ/ዘመን በሃገራችን ኢትዮዽያ ተወልዶ
ያደገ
*ነገሥታቱንና ሃገሩን በሙያው ያገለገለ
*በተለይ ከ34 እስከ 46 ዓ/ም ለነገሠችው ንግሥት
ሕንደኬ ገርስሞት በገንዘብ ሚንስትርነት ያገለገለ
*በገንዘቧ ላይ ሁሉ አዛዥ (ታማኝ) የነበረ
*ጃንደረባ በመሆኑ ለንግሥቲቱና ቤተሰቧ ቅርብ የነበረ
*መጻሕፍትን የሚያነብና የሚመረምር
*ዘወትር ወደ ኢየሩሳሌም እየሔደ ከቅዱሳት መካናት
የሚሳለም በጐ ሰው ነበር::

+በግብረ ሐዋርያት ምዕ. 8:26 ላይ እንደ ተጠቀሰው
ቅዱሱ ከኢየሩሳሌም ለፋሲካና ለእሸት በዓል ነበር
የሔደው::
ሲመለስ መንፈስ ቅዱስ ከፊልዾስ ጋር በጋዛ አገናኝቶታል::
በዚያም ምሥጢረ ክርስትናን ተምሮ: በክርስቶስ
አምላክነትና
አዳኝነት አምኖ ተጠምቁዋል::

+ክርስትናን ለኢትዮዽያ በ34 ዓ/ም አምጥቷል::
"ጃንደረባው ለወገኖቹ ሐዋርያ ሆነ" ሲል ቅዱስ ዮሐንስ
አፈ ወርቅ
እንደ ተናገረው ወደ ሃገራችን ተመልሶ: ስለ ክርስቶስ
ሰብኮ በርካቶችን አሳምኗል::

+ቀጥሎም ሃብቱን ንቆ (መንኖ): ከኢትዮዽያ እስከ ሕንድ
ወንጌልን ሰብኮ በዚህች ዕለት በሰማዕትነት ዐርፏል::
(ተሰውሯል የሚሉም አሉ)

<< በእውነት ለቅዱስ ባኮስ ክብር ይገባል:: >>

+" #ቅዱስ_ያዕቆብ_ዘንጽቢን "+

+ይህ ቅዱስ ሰው:--
*እጅግ የተመሠከረለት ሊቅ
*በፍጹም ትሕርምት የኖረ ገዳማዊ
*በርካቶችን ወደ ክርስትና ያመጣ ሐዋርያዊ
*ለአእላፍ ምዕመናን እረኛ የሆነ የንጽቢን (ሶርያ) ዻዻስ
*ለጀሮ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን የሠራ ገባሬ መንክራት
*ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊን ጨምሮ በርካታ ሊቃውንትን
ያፈራ ታላቅ መምሕር
*ለክርስቶስና ለእመቤታችን ታጥቆ የተገዛ የፍቅር ሰው
*እጣቶቹ እንደ ፋና የሚያበሩለት ማኅቶት
*ራሱን ዝቅ አድርጐ በቆሸሸ ልብስ የሚኖር የትህትና ሰው
ነው::

+በ325 (318) ዓ/ም: በኒቅያ 318ቱ ሊቃውንት
ሲሰበሰቡና አርዮስን ሲያወግዙ እርሱ አንዱ ነበር::
በሥፍራውም ሙት
አስነስቶ ሕዝቡን አስደምሟል:: በዚያም የቤተ ክርስቲያንን
ሥርዓት ሠርቶ ወደ ሃገሩ ተመልሶ በቅድስና ኑሮ በዚህች
ቀን
ዐርፎ በክብር ተቀብሯል::

+"+ #ደናግል_ማርያ_ወማርታ +"+

+በዘመነ ሐዋርያት በተመሳሳይ 'እንተ ዕፍረት-ባለ ሽቱ'
ተብለው የሚጠሩ 2 እናቶች ነበሩ:: 2ቱም ስማቸው
ማርያም ስለ
ነበር ለመለየት እንዲያመች አንደኛዋን 'ማርያም ኃጥዕት-
ከኃጢአት የተመለሰች': 2ኛዋን ደግሞ 'ማርያም እኅተ
አልዓዛር-በቢታንያ የነበረችው ብለው አበው
ይጠሯቸዋል::

+በሉቃስ ወንጌል ላይ የምትገኘው ከኃጢአት ሕይወት
የተመለሰችው ስትሆን በዮሐንስ ወንጌል 12:1 ላይ
ያለችው የአልዓዛር
እህት (ድንግሊቱ) ናት:: ዛሬም የምናስባት ይህቺውን
እናታችን ነው::

+ቅድስት ማርያም መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም
መጥቶ በሚያስተምርበት ዘመን በቢታንያ አካባቢ ትኖር
የነበረች
ድንግል ወጣት ናት:: ወላጆች ባልነበረበት ቤት ውስጥ
ታላቆቿ አልዓዛርና ማርታ አሳድገዋታል::

+በቤተሰብ ደረጃ እንግዳን ይቀበሉ ነበርና ጌታችን
ወደዳቸው::
አልዓዛርን ከ72ቱ አርድእት: ማርያምና ማርታን ደግሞ
ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ቆጥሯቸዋል:: ወንድማቸው
አልዓዛር በታመመ
ጊዜ ወደ ጌታ ልከው ነበር::

+ያለ ጊዜው የማይሠራ ጌታ ባይመጣ አልዓዛር ሞተ::
በ4ኛው ቀን አምላክ ሲመጣ ቅድስት ማርያም በጌታ ፊት
ሰግዳ
"እግዚእየ ሶበሰ ኀሎከ ዝየ እምኢሞተ እሑየ-አንተ በዚህ
በኖርክስ ወንድሜ ባልሞተ ነበር" ብላ አለቀሰች:: (ዮሐ.
11)