፮ ኪሎ ግቢ ጉባኤ
2.43K subscribers
2.86K photos
42 videos
355 files
172 links
ይህ የ፮ ኪሎ ግቢ ጉባኤ ህጋዊ የቴሌግራም ቻናል ነው።
This is the official Channel of 6 kilo Gibi Gubae.
በግቢ ጉባኤው ላይ ያለዎትን አስተያየት ወይም ጥያቄ በ @fesehatsion12 ወይም @Hoping7 ላይ ይላኩልን።
Download Telegram
"ጌታ ሆይ እርሻውን አቃጥለህ ሰብሉን ብትባርክ ምን ይጠቅማል? ዛፉንስ ቆርጠህ ቅርንጫፉን ብትባርክ ምን ይረባል? እናቴ እርሻ ናት እኔ ሰብል ነኝ:: እናቴ ዛፍ ናት እኔ ቅርንጫፍ ነኝ:: እባክህን እናቴ ብትክድ እኔ ባምን ምን ይጠቅማል:: ጌታ ሆይ የእናቴን ልብ በሃይማኖት አጽናልኝ"

(ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ስለ እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ የጸለየው ጸሎት)

ቅዱስ ቂርቆስ ሆይ አንተ ሕፃን ሆነህ ትልቅ ነበርክ:: ትልቅ ሆነን ሕፃን የሆንን እኛን በምልጃህ አስበን!

"የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው፤ ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል" መዝ 19:7

(#ከዲያቆን_ሄኖክ_ኃይሌ_የተወሰደ)
††† እንኳን ለቅዱሳኑ ገብርኤል ሊቀ መላእክት: ቂርቆስ ወኢየሉጣ: በጥላን ጠቢብ እና ሰማዕታተ እስና ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱሳን ቂርቆስ ወኢየሉጣ: ወቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት †††

††† ቅድስት ኢየሉጣ እናታችን በዘመነ ሰማዕታት ከነበሩና በዚህ ስም ከሚጠሩ ቅዱሳት አንዷ ናት:: በወቅቱ ቅዱስ ቂርቆስ የሚባል ደግ ልጅ ወልዳ ባሏ ባለመኖሩ በመበለትነት ትኖር ነበር:: የዚያ ዘመን ክርስቲያኖች ለክርስቶስ የነበራቸው ፍቅር ከመነገር በላይ ነው:: በዛው ልክ ደግሞ መከራው በጸጉራቸው ቁጥር ልክ ነበር::

ከሮም ግዛት በአንዱ ከቅዱስ ልጇ ጋር የምትኖረው ቅድስት ኢየሉጣ የስደቱ ዘመን ሲመጣ እርሷም እንደ ሌሎቹ ክርስቲያኖች ተሰደደች:: እስክንድሮስ የተባለው ከሃዲ ንጉሥ ግን ያለችበት ድረስ ተከትሎ እንድትያዝና እንድትቀርብ አደረገ::

ወዲያውም "ስምሽ ማን ይባላል?" ቢላት "ክርስቲያን እባላለሁ" አለችው:: ንጉሡ ተቆጣ:: "መዋቲ ስሜን ከፈለክ ኢየሉጣ ይባላል" አለችው:: ንጉሡ መልሶ "አሁን ለጣዖት ካልሠዋሽ ሲጀመር ስቃይ: ቀጥሎም ሞት ይጠብቅሻል" ቢላት ቅድስቲቱ መልሳ "በከተማ ውስጥ የሦስት ዓመት ሕፃን አለና እርሱን አምጣው:: ማንን ማምለክ እንዳለብን ይነግረናል" አለችው::

አስፈልጐ ቅዱስ ቂርቆስን አስመጣው:: "ስምህ ማን ይባላል?" አለ ንጉሡ:: "ከማይደፈርስ ከንጹሕ ምንጭ የተቀዳ ጥሩ ምንጭ ስሜ ክርስቲያን ይባላል:: መዋቲ ስሜን ከፈለግህ ግን ቂርቆስ ይባላል" አለው::

ንጉሡ ሊያታልለው "ደስ የተሰኘህ ሕፃን" ቢለው ቅዱሱ ሕፃን "ትክክል ተናገርክ: ለእኔ በሰማያት ደስታ ይጠብቀኛል:: አንተ ግን እውነተኛው አምላክ ይፈርድብሃል" አለው:: በሦስት ዓመት ሕፃን አንደበት ዘለፋ የገጠመው ከሃዲ ተቆጣ::
እናትና ልጅን በብዙ መክፈልተ ኩነኔ አሰቃያቸው::

ሰውነታቸውን ቸነከረ: አካላቸውን ቆራረጠ: ዓይናቸውን አወጣ:: ሌላም ሊናገሩት የሚጨንቅ ስቃይን አሰቃያቸው:: በዚህች ቀን ግን ትልቅ ድስት አሰርቶ ባሩድ: አረር: ስብና የመሳሰሉትን ጨምረውበት በእሳት አፈሉት::

የእሳቱ ወላፈን አካባቢውን በላው:: በድስቱ ውስጥ ያለው ነገር እየፈላ ሲገላበጥ እንደ ክረምት ነጐድጓድ ይጮህ ነበር:: የስድስት ሰዓት የእግር መንገድ ድረስም ተሰምቷል:: ቅድስት ኢየሉጣ ይሔኔ ነበር ልቧ ድንግጥ ያለው:: ሕፃኑ ቂርቆስ የእናቱን ፍርሃት ሲመለከት ጸለየ::

"ፈጣሪዬ! ፍሬው ያለ ግንዱ አይቆምምና እኔን እንዳጸናሕ እናቴንም አጽናት" ሲል ለመነ::
"እግዚኦ ትፈቅድኑ ለፍሬሁ ተአልዶ:
እንዘ በእሳት ታውኢ ጉንዶ" እንዲል::
በዚያች ሰዓት ቅድስት ኢየሉጣ ዓይኖቿ ተከፍተው ሰማያዊ ክብርን ተመለከቱና ልቧ ወደ ድፍረቱ ተመለሰ::

ልጇንም "አንተ አባቴ ነህ: አንተን የተሸከመች ማኅጸኔ የተባረከች ናት" አለችው:: ከዚያም ሁለቱንም ወደ ፈላው ድስት ውስጥ ቢጨምሯቸው ፍጡነ ረድኤት ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወረደላቸው:: በበትረ መስቀሉ ባርኮ የፈላውን አቀዘቀዘው:: የነደደውን ውኃ አደረገው:: ቅዱሳኑ ቂርቆስና ኢየሉጣ ከብዙ መከራ በኋላ በሰማዕትነት አልፈዋል::

††† ቅዱስ በጥላን ጠቢብ †††

††† ቅዱሱ ከአሕዛብ ወላጆቹ ተወልዶ: ያደገውም በጣዖት አምልኮ ነው:: በሙያው እጅግ የተመሠከረለት ሐኪም ነበር:: የሃገሩ ሰዎች "ጠቢብ" እያሉም ይጠሩታል:: በጥላን ምንም ጣዖት አምላኪ ቢሆን በተፈጥሮው ተመራማሪና ቅን ነበር::

አንድ ካህንም በጐረቤቱ ነበርና ዘወትር ስለ ሃይማኖት ይከራከሩ ነበር:: ካህኑ ሌሊት ሌሊት ስለ በጥላን ተግቶ ይጸልይ ነበርና ተሳክቶለት አሳመነው::

አንድ ቀን በጥላን መንገድ ሲሔድ እባብ ሰው ነድፎ ለሞት ደርሶ አየውና ጸሎት አድርሶ ስመ ክርስቶስን ቢጠራ የተነደፈው ድኖ እባቡ ሞተ::

በዚህ ተዓምር ደስ ብሎት ወደ ካህኑ ሒዶ ተጠመቀ:: ከዚያም ጾም ጸሎትን ጀመረ:: በየቦታው እየዞረ ሕሙማንን እንደ ቀድሞው በመድኃኒት ሳይሆን በጸሎት ያድናቸው ነበር:: ስላዳናቸውም በርካቶቹ ወደ ክርስትና መጡ::

የአካባቢው ሰው: ወላጆቹን ጨምሮ ክርስቲያኖች ሆኑ:: በመጨረሻም ቅዱስ በጥላን: ቤተሰቦቹ: ካህኑና ከደዌ የዳኑት ወገኖቹ በአካባቢው ጣዖት አምላኪ ንጉሥ ፊት ቀርበው ክርስቶስን ሰብከው በሰማዕትነት ዐርፈዋል::

††† ቅዱሳን ሰማዕታተ እስና †††

††† እስና ማለት ግብጽ ውስጥ የምትገኝ የቀድሞ አውራጃ ናት:: በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን በከተማዋ በርካታ ክርስቲያኖች ይኖሩ ነበር:: የእንዴናው መኮንን መጥቶ "ክርስቶስን ካዱ: ለጣዖት ስገዱ" አላቸው:: ሕዝቡ በአንድ ድምጽ መለሱ:- "ይሕማ ፈጽሞ ሊደረግ አይችልም::" መኮንኑ ተቆጥቶ "ሁሉንም ግደሉ" አለ::

ወታደሮቹ ሰው አልመረጡም:: ከታዘለ ሕፃን አልጋ ላይ እስካለ ሽማግሌ: ከጤነኛ እስከ ሕመምተኛ: ሁሉንም ጨፈጨፏቸው:: ከተማዋ በደም ተነከረች:: ከከተማዋ ክርስቲያኖች ወሬ ለመንገር አንድ ሰው እንኳ አልተረፈም:: ሁሉም ስለ ክርስትና ደማቸውን አፈሰሱ::

††† ጌታችን ስለ ሰማዕታቱ ብሎ: ደማቸውንም አስቦ በሃይማኖታችን ያጽናን:: ከመከራም ይሰውረን:: በረከታቸውንም ያድለን::

††† ሐምሌ 19 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ቂርቆስ ወእሙ ኢየሉጣ
3.ቅዱስ በጥላን ጠቢብ ሰማዕት እና ማኅበሩ
4.ቅዱሳን ሰማዕታተ እስና

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ኤስድሮስ ሰማዕት
2.አቡነ ዓቢየ እግዚእ ጻድቅ
3.አቡነ ስነ ኢየሱስ
4.አቡነ ዮሴፍ ብርሃነ ዓለም

††† "ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ: ወይስ ጭንቀት: ወይስ ስደት: ወይስ ራብ: ወይስ መራቆት: ወይስ ፍርሃት: ወይስ ሰይፍ ነውን?
'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን:: እንደሚታረዱ በጐች ተቆጠርን::' ተብሎ እንደተጻፈው ነው::
በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን::" †††
(ሮሜ. ፰፥፴፭-፴፯)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
✥✥✥ታቦር ወአርሞንዔም በስመ ዚኣከ ይትፌስሑ✥✥✥
(መዝ.88÷12)

👉 በዚህ ርዕስ ሥር

1. በዓሉ የሚከበርበትን ምክንያት/
ከሐዋርያት ሦስቱ ሐዋርያት ብቻ መመረጣቸው ፤ ከነቢያት ሙሴና ኤልያስ መገለጣቸው ስለምን ነው?
2. ደብረታቦር የተመረጠበት ምክንያትና ምሳሌነቱ
3. የበዓሉ መጠሪያ ስሞች (ደብረ ታቦር / ቡሄ/ ቡሔ መባሉ ስለምንድ ነው?)
4. ችቦ የመብራቱ ፣ ሙልሙል ዳቦ የመጋገሩና የጅራፍ ማጮኽ ምክንያት እንመለከታለን፡፡

1. ይህ በዓል ከዘጠኙ ዐበይት በዓላት አንዱ ሲሆን የሚከበረው ጌታችን የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅነቱን ያስመሰከረበት፣ ጌትነቱን እና ክብሩን የገለጠበት በመሆኑ ነው፡፡ (ማቴ.17÷1 ማር.9÷2 ሉቃ.9÷28 2ጴጥ.1÷16-18)፡፡

👉 ጌታችን ሐዋርያትን ‹‹ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ብለው ይሉታል? ›› ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ ቅድስናህን ዓይተው ሙሴ ነህ ይሉሃል፤ የኃይል ሥራህን ድንግልናውንም ዓይተው ኤልያስ ነህ የሚሉህ አሉ ……… ብለውት ነበረና እግዚኣ ሙሴ ወኤልያስ (የነቢያት ጌታ) መሆንኑን ለመግለጥ፤ አንድም ጌታችንም መልሶ ‹‹ እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ? ›› አላቸው ቅዱስ ጴጥሮስም እስከ ክርቶስ ተብሎ የተነገረልህ ‹‹ አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነህ ›› አለው (ማቴ.16÷13-20/ ትን.ዳን.9÷25) ይህን በፍጡር አንደበት የተመሰከረውን ጌትነቱን በአብ ምስክርነት ለማጽናት እና በተግባር ለመግለጥ የሐዋርያትንም እምነታቸውን ለማጽናት አዕማደ ሐዋርያት የሆኑትን ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ቅዱስ ያዕቆብ፣ ቅዱስ ዮሐንስን ይዞ ወደ ቅዱሱ ተራራ አወጣቸው፡፡

👉 ስለምን እነዚህን ብቻ አወጣቸው ቢሉ ለፍቅሩ ይሳሳሉና በፍቅሩ ይናደዳሉና ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታ እሞታለሁ ቢለው " አንተስ አትሞትም እኔ እሞታለሁ እንጂ " ማለቱ እኒም እኔ የምጠጣውን ጽዋ (ሞት) ልትጠጡ ትችላላችሁን? ቢላቸው " አዎ እንችላለን " (ስለ አንተ እንሞታለን) ማለታቸው እጅግ ቢወዱት ነው ስለዚህ ሦስቱን መረጣቸው፡፡

👉 ቀሪዎችን ስምንቱ ሐዋርያትንና ይሁዳን ከእግረ ደብር አቆይቷቸዋል ከይሁዳም በስተቀር ከላይ ላሉት የተገለጠ ምሥጢር ከሥር ላሉትም ተገልጦላቸዋል፡፡ ይሁዳን ‹‹ያእትትዋ ለኃጥእ ከመ ኢይርአይ ስብሓተ እግዚአብሔር›› (የእግዚአብሔርን ክብር እንዳያይ ኃጢአተኛው ያስወግዱታል፡፡) (ትን.ኢሳ.26÷10) እንዲል ኋላ የሚሠራት ኃጢአት ይህን ምሥጢር እንዳያይ አድርጋዋለች ምሥጢር የማይገልጥለት ከሆነ ከሌሎች ሐዋርያት ጋር አብሮ እንዲሆን ለምን አስፈለገ ቢሉ ከእነርሱ ቢለየኝ በሞቱ ገባሁበት ብሎ ምክንያት እንዳያገኝ ነው፡፡

👉 መልኩም በፊታቸው ተለወጠ፤ ፊቱም ከፀሓይ ይልቅ አበራ፤ ልብሱም ልብስ አጣቢ ከሚያነጻው ይልቅ እንደ በረድ ፀዓዳ ሆነ፡፡ ‹‹ እነሆ ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው›› ቅዱስ ጴጥሮስም ጌታን ‹‹ አቤቱ በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ ሦስት ቤቶችን በዚህ እንሥራ፤ አንዱን ለአንተ÷ አንዱንም ለሙሴ÷ አንዱንም ለኤልያስ አለው›› በዚህ ቃል የትህትና እና የደካማነት ምልክት አለበት፡፡ ትህትና ያልነው ቅዱስ ጴጥሮስ ለራሱና ለባልንጀሮቹ ሐዋርያት ቤት ይሠራ ዘንድ ስለ አላሰበ ነው ራሱንና ባልንጀሮቹን እንደ ባሮች፤ ነቢያትን ደግሞ እንደ ጌቶች (የጌታ ባለማሎች) አድርጎ አስቧልና፡፡ ደካማነት የተባለው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችን ከሰማይ የወረደበትን (ሰው የሆነበት) ሥራ ትቶ በተራራ ላይ ይኖር ዘንድና
ራሱን የሚሰውርበትን ቤት ይሠራለት ዘንድ የተናገረው ነው፡፡ ስለዚህም ጌታችን ምድራዊ ቤት እንደማያስፈልገው ያስረዳው ዘንድ የክብሩ መገለጫ የሆነ ብሩህ ደመና መጥቶ እንደቤት ሁኖ ጋረዳቸው፡፡ ‹‹እነሆ በደመናው ውስጥም የምወደው በእርሱም ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት የሚል ቃል
መጣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው ደንግጠው በግንባራቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸው ተነሡ አትፍሩም አላቸው፡፡ ዓይናቸውንም አቅንተው ዓዩ ነገር ግን ከጌታችን ከኢየሱስ ብቻ በቀር ያዩት ማንም አልነበረም፡፡ ››

👉 ከነቢያት ሁሉ ለይቶ ሙሴና ኤልያስ እንዲገለጡ ማድረጉ ስለምንድን ነው ቢሉ ሙሴ ከአምላክ ጋር 570 ጊዜ ያህል ቃል ለቃል ተነጋግሮት ነበርና ባለማልነቴ ይገለጥ ዘንድ ባይህ እወዳለው አለው፡፡ አምላክም ፊቴን ዓይቶ አንድ ሰዓት ስንኳ መቆም የሚቻለው የለም ብሎ መለሰለት ሙሴም ይህ ካልሆነማ ባለሟልህ መባሌ ምኑ ላይ ነው በቃልማ ሌሎቹንስ ታናግር የለምን ቢለው አምላክም " ድኅረሰ ትሬኢ ገጽየ " መሥዋዕት ሁኜ በምቀርብበት ጊዜ (በዘመነ ሥጋዌ) እታይሃለሁ ብሎት ነበርና ይህ እንዲፈጸም፡፡ (ዘጸ.33÷18-23)፤ ኤልያስ ስለአምላክ እጅግ በመቅናቱ ተስፋ ተሰጥቶት ነበርና፡፡ ክብሩ በተገለጠ ጊዜ ግን ሙሴ ‹‹ትኄይሰኒ መቃብርየ›› (መቃብሬ ትሻለኛለች ብሏል)፤ ኤልያስም ወደ እሳት ሠረገላው ተመልሷል፡፡
• አንድም፡- ሙሴ ኤልያስ ይሉሃል ብለውት ነበረና እግዚኣ ሙሴ ወኤልያስ መሆኑን በራሳቸው አንደበት ለማስመስከር፡፡
• አንድም፡- የሕያዋን (ሞት ያላገኛቸው) የሙታን (ሞት ያገኛቸው) አምላክ መሆኑ ለማጠየቅ ነው ከእርሱ በቀር
የሙሴን መቃብር (ይሁ.ቍጥ.9)፤ ኤልያስም የተሰወረባት (ብሔረ ሕያዋንን) የሚያውቅ የለምና፡፡
• ፍጻሜው ግን፡- ደብረ ታቦር የቤተክርስቲያንና የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ እንድትሆን ነው፡፡

2. ደብረታቦር የተመረጠበት ምክንያትና ምሳሌነቱ፡-
• ደብረ ታቦር ማለት ደብር ተራራ ሲሆን ታቦር የቦታው ስም ነው ከኢያቦር ወገን የነበረ ቦር የሚባል ሰው ነበረና በሱ ስም ታቦር አሉት "ቦር" ማለት ትልቅ ማለት ሲሆን "ታ" ን ጨምረው ታቦር ብለውታል።

👉 በደብረ ታቦር ያደረገው በሌላ ያላደረገው ስለም ነው ቢሉ ትንቢቱ ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ ትንቢቱ ‹‹ ታቦር ወአርሞንዔም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ ›› (መዝ 88÷12) ያለው ነው። ምነው ክብሩን የገለጠ በታቦር አይደለምን አርሞንዔምንም አነሳ ቢሉ ብርሃኑ እስከ አርሞንዔም ደርሷልና ነው፡፡
ምሳሌው ፡- በዚህ ተራራ ላይ ነቢያቱ ዲቦራ ከባርቅ ጋር በመሆን የከነዓናውያን ንጉሥና የጦር መሪ ሲሳራንና ኢያቡስን በጦርነት ድል አድርገውበታል (መሳፍንት 4፥5–24) ጌታም በልበ ሐዋርያት ያደረ ሰይጣንን ድል ነሥቶበታልና፡፡
• ደብረ ታቦር የቤተክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ በዚህ ተራራ ላይ ብሉይን የሚወክሉ ነቢያት፤ ሐዲስንም የሚወክሉ ሐዋርያት እንዲሁም ሐጋጌ ሕግ የሆነም ጌታ እንደተገኙ በእግዚአብሔር ቤትም ብሉይና ሓዲስ እንደሚነገሩ ምእመናንም በእነዚህ ሕግ እንደሚመሩ ያስረዳል፡፡ መምህር ጳውሎስም ስለዚህ ነገር ሲያስረዳ ‹‹በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጻችኋልና፤ የሕንጻው የማዕዘን ራስ ድንጋይ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ እርሱም ሕንጻ ሁሉ የሚያያዝበት÷ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግንብ የሚያድግበት ነው፡፡ እናነተ በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ማደሪያ ልትሆኑ በእርሱ ታነጻችሁ፡፡›› አለ፡፡ (ኤፌ.2÷20-21)
• አንድም፡- የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ናት ነቢያትም ሐዋርያት አንድ ሁነው እንዲወርሷት፤ ከመዓስባን ሙሴን
ከደናግላን ኤልያስን አመጣ መዓስባንና ደናግላን አንድ ሁነው እንደሚወርሷት፤ ከምዉታን ሙሴን ከሕያዋን ኤልያስ አመጣ ሁሉም በትንሣኤ እንደሚወርሷት ለማጠየቅ፡፡
3. የበዓሉ መጠሪያ ስሞች (ደብረ ታቦር / ቡሄ/ ቡሔ መባሉ ስለምንድ ነው?)
👉 ደብረ ታቦር የተባለው ጌታ ክብሩን የገለጠበት ስፍራ ደብረ ታቦር ስለሆነ በዚሁ በዓሉ ስያሜውን አግኝቷል፡፡

👉 ቡሔ ይባላል ፡- ቡሄ ብርሃን ማለት ነው በደብረታቦር ቧ ብሎ የተገለጠውን የጌታችንን የፊቱን ብርሃን ጸዳል፤ የልብሱንም እንደ ነጭ በረዶ ጸዓዳ መሆን ያስረዳል፡፡
• አንድም፡- ቡሔ ማለት መላጣ (ገላጣ) ማለት ነው፡፡
ይኸውም በበዓሉ ዋዜማ ልጆች ‹‹ ቡሔ በሉ፤ ቡሔ መጣ ፣ ያ መላጣ፣ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ›› ይላሉ እዚህ ላይ ቡሄ ያለው ዳቦውን ነው፡፡
• አንድም፡- ‹‹ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት›› እንደሚባል ወቅቱ በሃገራችን የጸዓተ ክረምት ዋዜማ ስለሆነ የክረምቱ አፈናው ተወግዶ /ተጋምሶ/ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት ፤ በዶፉና በጎርፉ ተሸፍና የነበረች መሬት የምትገለጥበት በመሆኑ ነው፡፡
• አንድም፡- ቡሔ (ቡሔእየ) ተብሎ ይተረጎማል ይኸውም የደብረታቦር እለት እርሾ ሳይገባበት ተቦክቶ የሚጋገረውን
ኅብስት ያሳያል፡፡

4. ችቦ የመብራቱ ፣ የሙልሙል ዳቦ የመጋገሩና የጅራፍ ማጮኽ ምክንያት፡-

👉 መብራት የሚበራው 12 ለ13 ዋዜማ ሌሊት በ3 ሰዓት ነው ።
• የጌታችን ክብሩ በተገለጠበት ጊዜ ብርሃኑ የሌሊቱን ጨለማ ገፍቶት እስከ አርሞንዔም ደርሶ ነበርና በዚያ አካባቢ የነበሩ እረኞች በሁኔታው ተገርመው ቀንም መስሎአቸው ሌሊቱም ተዘንግቷቸው በዚያው ቆይተው ነበርና ቤተሰዎቻቸው ምን አግኝቷቸው ይሆን በማለት መብራት አብርተው (ችቦ ይዘው)፣ የሚመገቡትን ይዘው ወገኖቻቸውን ፍለጋ ወጥተዋል እረኞችም ያሉበትን ቦታ ለቤተሰዎቻቸው ጅራፍን በማጮኸ አመልክተዋቸዋልና ይህን ለማሰብ ነው፡፡
• ዋናው ምሥጢሩ ግን፡- የችቦው ብርሃን የጌታ ክብር መገለጡን፣ የጅራፋ ጩኸት ሐዋርያትን ያስደነገጣቸው የአብ የምስክርነቱ ቃል ምሳሌ ሲሆን፣ ኅብስቱ ጌታችን በመስቀል ላይ መሥዋዕት የመሆኑ (የሥጋ ወደሙ) ምሳሌ ነው፡፡
• ማስታወሻ፡- ከላይ እናዳየነው ጅራፋ መጮኹ የአብ የምስክርነቱ ቃል ምሳሌ ነው ይኸውም በታቦር ተራራ ላይ እንደሆነም ተገልጧል ስለዚህ ዛሬም ምሳሌነቱን ለማጉላት ጅራፍ የማጮኹን ሥርዓት በተራራ ማድረግ የተሻለ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን በርችትና በመሳሰሉት ማክበሩ ሃይማኖታዊ ትውፊት የለውም ይልቁንም ሰውን ለማስደንገጥ ተብሎ ርችትን በሰው ቦርሳ፣ ኪስ …. በመክተት ማስደንገጥ የበዓሉን ሥርዓት ማሳደፍም ከመሆኑም በላይ ከሃይማኖተኛ ሰው የማይጠበቅ የሰውንም መብትና ክብር መንካት ነው፡፡ ጌታችን በብርሃን ንስሓ እንመላለስ ዘንድ ዓይነ ልቡናችንን ብሩህ ያድርግልን፡፡ ይቆየን

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ


አምላካችን በዓሉን የበረከት የደስታ ያድርግልን!
"የህይወት እናት ድንግል ማርያም ሆይ ትንሳኤሽ ሳይሆን ሞትሽ ይደንቀኛል፤ እርገትሽ ሳይሆን ወደ መቃብር መውረድሽ ይገርመኛል፤ የብርሃን እናት ድንግል ማርያም ሆይ ትወጂኛለሽን? ብየ አልጠይቅሽም ፍቅርን የወለድሽ አንቺ ለአለሙ ሁሉ ፍቅርሽ የበዛ ነውና፤ አትናፍቂኝምን? ብየም አልጠይቅሽም ዘወትር እኔን ለመጠበቅ ከጎኔ እንደማትለይ አውቃለሁኝና፤ ሆኖም እመቤቴ ሆይ፦ እንደ ቶማስ አይሽ ዘንድ በእጅጉ እጓጓለሁ የቶማስ ንፅህናና ቅድስና ግን የለኝም እንደ ዮሃንስ ከጎንሽ ልሆን እጓጓለሁ የዮሃንስ ፀጋ ግን የለኝም።

እናቴ ሆይ፦ እንደ ኤልሳዕ የልቦናዬ አይን በርቶ ሰማያዊ ክብርሽን ላይ አልተቻለኝምና አዝናለሁ ኤልሳዕ በፀሎት ሃይል የግያዝን አይን እንዳበራ አንቺም አይኔን ታበሪልኝ ዘንድ ሃይልሽን በእኔ ላይ አበርቺ፡፡

ድንግል ሆይ፦ ይህን የምል የእምነት ማረጋገጫ ፈልጌ አይደለም በልጅሽ መሰረትነት የታነፅኩኝ በልጅሽ ስምም የተጠመቅኩኝ ነኝና፤ ነገር ግን ስለምትናፍቂኝ ይህን አልኩኝ ስለዚህም ነይ ነይ እምየ ማርያም እያልኩኝ እንደ እናቶቼም እለምንሻለሁ፡፡ የብርሃን ልብስሽን ለብሰሽ ነይ የክብር አክሊልሽን ደፍተሽ ነይ አንቺ ሱላማጢስ ሆይ ነይ እናይሽ ዘንድ ነይ፡፡"


እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእርገት በዓል አደረሳችሁ!!
ማኅበረ ቅዱሳን 19 የሕግ ታራሚዎችን ጨምሮ 24 ሠልጣኞችን አስመረቀ !

ነሐሴ 19 ቀን 2016 ዓ.ም (ተ.ሚ.ማ/አዲስ አበባ)

በማኅበረ ቅዱሳን የሐዋሳ ማዕከል የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ለስድስት ወራት በርቀት የተከታተሉ ሠልጣኞችን በሐዋሳ ከተማ ማረሚያ ቤት አስመርቋል፡፡

በትምህርቱ የሥነ ፍጥረት መግቢያ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መግቢያ፣ የትምህርተ ክርስትና መግቢያ፣ የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መግቢያ፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክና የክርስትያናዊ ሥነ ምግባር መግቢያን በመሠረታዊ የርቀት ትምህርት ኮርስ ማካተቱ ተገልጿል፡፡

የሕግ ታራሚዎች ማኅበሩ እስከ ማረሚያ ቤት ደርሶ የቤተ ክርስቲያን ትምህርትን በማስተማሩ የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ማኅበሩን አመስግነዋል።