ሰንፔር ሚዲያ Sapphire Media
434 subscribers
297 photos
4 videos
8 files
109 links
መንፈሳዊ መጣጥፎችን ግጥሞችን ወጎችን አጫጭር ልቦለዶች አስደናቂ ታሪኮችን ትምህርታዊ ፅሁፎችን ለማግኘት ይቀላቀሉን።

"ትውልድ ሆይ ወደ እግዚአብሔር ቃልና ወደ ተሰቀለው ክርስቶስ ተመልከቱ!!!"


https://youtu.be/KRKo3x7iYNw

http://Instagram.com/sapphiremedia4god

tiktok.com/@sapphiremedia1
Download Telegram
ከትንሽነቴ ሰልፍ ይበዛብኛል
እንቅፋቱ በዝቶ ያቆሳስለኛል
እፎይ የምልበት የእረፍቴ ሰዓት
ለዓይኔ አይታየኝም ለአእላፍ ቀናት

ጌታ ሆይ
ምክንያቱን አላውቅም መስቀሌ ብዙ ነው
ትከሻዬን አስፋው ችዬ እንድሸከመው

በግፈኞችም እጅ ወድቄ አልቅሻለሁ
መንገዴን አጥብበው ብዙ ታግያለሁ
ስጋዬ በሕመም ደቆ ተንጋልዬ
ቀናት ተፈራርቀው አለሁኝ በአልጋዬ

ጌታ ሆይ.....

በቃልህ ከሆነ ሀሞት እቀምሳለሁ
የሚያስችል ኃይልህን እከናነባለሁ
የማታ የማታ ባለድል እሆናለው
የፀና ስምህን በእምነት እጠራለሁ

ጌታ ሆይ......

ሰገነት ላይ ብቆም እንደደረቀ ሳር
ፈታኜ ይጠውልግ ይገፍተር ወደዳር
ብሩህ ቀን የደስታ አዲስ ቀን አያለሁ
አንተን ተደግፌ ድሌን አውጃለሁ

ጌታ ሆይ.......

ደረጀ 🩶🩶🩶
በብዙ ከተጠቀምንበት ፤ አኹንም እየተጠቀምንበት ካለው ከተወደደው ወንደማችንና አገልጋይ ፋሲል ጥጋቡ (ፋዮ) ጋር ልዩ የስልጠና ጊዜ ተዘጋጅትዋል፡፡ አንገብጋቢ በሆኑ ሁለት ርዕሰ ጉዳዮችና ተያያዥ ሀሳቦች ጋር ስልጠና ይሰጠናል፡፡ እግዚአብሔር መልካም ጊዜ ይሰጠናል ታዳጊዎችና ወጣቶች በፍፁም አይቀርም፡፡
በብዙ ከተጠቀምንበት ፤ አኹንም እየተጠቀምንበት ካለው ከተወደደው ወንደማችንና አገልጋይ ፋሲል ጥጋቡ (ፋዮ) ጋር ልዩ የስልጠና ጊዜ ተዘጋጅትዋል፡፡ አንገብጋቢ በሆኑ ሁለት ርዕሰ ጉዳዮችና ተያያዥ ሀሳቦች ጋር ስልጠና ይሰጠናል፡፡ እግዚአብሔር መልካም ጊዜ ይሰጠናል ታዳጊዎችና ወጣቶች በፍፁም አይቀርም፡፡
ዛሬም ይቀጥላል
በተሞላ ነገር ላይ ለመጨመር መሞከር ትርፉ ማፍሰስ ነው!ዓለማዊነት እና ምኞቱ  የማይዘልቀን በእግዚአብሔር ቃል ስንሞላ ነው!ጌታ ኢየሱስ የዲያብሎስን ፈተና አሸንፎ ያሳየን ጥቅስ እየጠቀሰ ነው...''እንዲህ ተብሎ ተፅፏል''...።ጌታን ለመምሰል የሚያስፈልገን ፀጋ እና ሁሉ ነገር ተሰቶን ሳለ ደካማ የሆነው ለምን ይመስላችኃል?ዋርካ ትልቅ ዛፍ ከመሆኑ በፊት ዘር ነበር!ያለዘር ዕድገት ሆነ ፍሬ የለም!ስለዚህ ነው ጳውሎስ እኔ ተከልኩ አጵሎስ አጠጣ እግዚአብሔር ያሳድጋል ያለው።እምነት በቃሉ ነው ጊዜ ይጠብቅ እንጂ ዕድገትም በቃሉ ነው!!
ያለ እናት ጡት ወተት ህፃን እንዴት ያድግ ይሆን??

“ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።”
  — 1ኛ ጴጥሮስ 2፥2-3

ዓለማዊ ምኞትን የምናሸንፈው በትግል ሳይሆን ቃሉን በመሞላት ነው!!

© ጌዴዎን ጡሚሶ (ዶ/ር)
በአፋችን ባንናገረውም በኑሮአችን ከምንገልጣቸው ሀቆች መሀል አንዱ ከእግዚአብሔር ይልቅ  የኛ መንገድ የፈጠነ ፣ የተሻለ እንደሆነ ማሰባችን ነው!ከሰከንዶች በኃላ ምን እንደሚሆን ማናውቅ ፍጥረቶች አልፋ እና ኦሜጋ እኔ ነኝ ያለውን ጌታችንን ማመን ያቅተናል!ያመነ ያርፋል የተጠራጠረ ይቅበዘበዛል!በራሱ መንገድ የፈጠነ ደርሶም አይደርስም!አብርሃም ለሎጥ ቅድሚያ ሰጥቶ ያስመረጠው  ከለምለሙ ቦታ ይልቅ እምነቱ እግዚአብሔር ስለነበረ ነው!!

ኢሳይያስ 40
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
³⁰ ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል፥ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ፤
³¹ እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም።
የዛሬ 508 ዓመት፣ በዛሬዋ ዕለት፣ በኦክቶበር 31፣ 1517 አመተ እግዚ አንድ ብዙም የማይታወቅ መነኩሴ በአንዲት ትንሽ የጀርመን ዩኒቨርስቲ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ፕሮፌሰር የነበረ ሰው በዩኒቨርስቲው ቅጥር ውስጥ በሚገኘው የቤተ ክርስትያን በሮች ላይ የተወሰኑ ወረቀቶችን ለመለጠፍ መዶሻ አነሳ። እነዚያን ወረቀቶች በቤተ ክርስትያን አደባባይ ላይ የለጠፈበት ምክንያት የቤተ ክርስትያኑ በር/አደባባዩ ለዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ እንደ ማስታወቅያ ሰሌዳ ያገለግል ስለነበር በርከት ያለ ሰው እንዲመለከተውና ውይይት እንዲያጭር አስቦ ነበር።

በለጠፈው ወረቀት ውስጥ 95 አናቅጽት (Thesis) 'የኢንደልጀንስን' [indulgence] (የኃጢአት ይቅርታ ሰነድ) የመሸጥ ልምምድ ከጳጳሱ ፍቃድ ያገኘና አንድ ሰው 'ፑርጋቶሪ' [Purgatory] (ነፍስ ወደ ገነትም ሆነ ሲኦል ከመውረዷ በፊት የምትሆንበት ስፍራ) ውስጥ በምድር በሕይወት እያለ ስላጠፋው ስለሃጢያቱ የሚቆይበትን ጊዜ (ወደ መንግስተ ሰማይ ከመግባቱ በፊት) በሚገዛው 'ኢንደልጀንስ' መቀነስ ይችል ነበር የሚለውን ፀረ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሃሳብ የሚገዳደር ነበር። ይህ 'ኢንደንጀልስ' በወረቀት የሰፈረና የቤተ ክርስትያንን ይሁንታ አግኝቶ መግዛት ለቻለ ሁሉ የቀረበ ነበር። ህዝቡም ኢንደልጀንሱን ይገዛ ዘንድ 'በቅቤ አቅልጥ' ደላላ አሻሻጮች ይጎተጎት ዘንድ ቤተ ክርስቲያን ይሁንታዋን ሰጥታ ነበር። ህዝቡ ለራሱ፣ ለዘመዱና ለወዳጁ ይገዛ ነበር፤ በሞቱት ስም እንኳን ሳይቀር ይቸበችቡታል።

ሉተር 95 አናቅጽቱን ጽፎ ሲለጥፋቸው ዩኒቨርስቲ ውስጥ ባሉት ፕሮፌሰሮች መሃል ውይይት እንዲፈጥር በማሰብ ነበር። ነገር ግን ዘጠና አምስቱ አናቅጽት ከቪተንበርግ ፕሮፌሰሮች ከባቢ በዘለለ በመላው የጀርመን ግዛቶችና በጠቅላላው የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ዘንድ ታላቅ ሁካታን ለመፍጠር በቃ። በአጭር ጊዜ ውስጥም ብዙ ህዝብ የዚህን መነኩሴ ስም ማወቅ ጀመረ፣ በቪተንበርግ ዩኒቨርስቲ የሥነ መለኮት ዶክተሩን ማርቲን ሉተርን።

ህዝብን በማወክና ባለመታዘዝ ቤተክርስትያን ከሰሰቸው፣ በጀርመን ንጉስ ፊትም ራሱን እንዲከላከልና ያደረገው ሃሰት መሆኑን አውቆ እንዲያስወግድ ታዘዘ። ያደረገው ስህተት መሆኑን ባለመቀበሉና ህሊናው ለቅዱሳት መጽሐፍት ተገዢነታቸውን በማጽናቱ ምክንያት የውጤቱን ስሜት 500 አመታትን ተሻግሮ ዛሬ እኛም ይሰማናል።
.
«ስቻለሁ የምለው አንዳች ነገር የለኝም፤ ኅሊናዬ ከሚያዘኝ ውጪ መሆን ትክክልም ሆነ አግባብ አይደለም። እነሆ፤ እዚሁ ቆሜያለሁ፤ ከዚህ ውጪ ምንም ላደርግም አይቻለኝም። እግዚአብሔር ሆይ እርዳኝ። አሜን።»
.
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እንዳሉት፣ "አሕይዎና ተሐድሶ (Revival and Renewal or Reformation) ተደላድሎና ተመቻችቶ በተቀመጠ ሥርዐት (Establishement) ውስጥ የዛገና የሚራገፍ ነገር የሚያይ የአእምሮ ችሎታና የተፈጥሮ ተሰጥዎ ካላቸው ታላላቅ ሰዎች ዘንድ የሚመጡ ሐሳቦች ናቸው።" በዚህ ሰው ለመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት በታማኝነት መታዘዝና መሰጠት ምክንያት የቤተክርስቲያን መልክ እንደ ቀደሞው ላይሆን ተለውጧል።
.
ተሐድሶ ብቻ መቆምን ይጠይቃል። ዘመንን መረዳትን፣ መጽሐፍትን መመርመርን፣ ለእግዚአብሔርና ለህሊናችን ታማኝ መሆንን ይጠይቃል። ተሐድሶ ወደ አባቶችና አያቶች ለመንፀሪያ መመልከትን አንደ ቄንጥ አያይም። የድነትን መኸከለኛ፣ የእምነትን ፈፃሚ፣ የእግዚአብሔርን መገለጥ፣ ትምሕርተ ክርስቶስን አደብዛዥን ሁሉ ለመቃወም ሁለቴ አያስብም። ተሐድሶ ቃለ–እግዚአብሔር ማሕደረ–ክርስቶስ በተባለችው ቤተክርስቲያን ሲደፈጠጥ ጥሪውን በማማ ላይ ያሰማል፤ እነሆኝ ለህሊናዬም ለቃሉም ቆሜያለሁ ይላል። እግዚአብሔር ልጁን በገለጠበት ቃል በኩል ለኅሊናዬ ብቻዬን እንኳን ቢሆን እቆማለሁ የሚል እውነትና ፅናት ያድለን።
.
የተሐድሶው ውጤት ተራ የነገረ መለኮት ክርክር ሳይሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአግባቡ ማወቅም እና ተግባራዊ የሆነ ክርስቲያናዊ ግብርም ነው።

መልካም እለተ ተሐድሶ!

© አማኑኤል አሰግድ
የዚህን ልጅ ዝማሬ ግን እየሰማችሁት ነው? እኔ ወድጄው እየሰማሁት ነው።

ያ ስሰማው ሰማይ የሚያስናፍቀኝ «በሰማይ ታላቅ ምስጋና ይሆናል» የሚለውም ዝማሬ ተካቷል

«የሰማይን ኮከብ» የሚለውን ዝማሬ ስትሰሙት «ልቤ ቀራኒዮ መክተም ጀምሯል» አኹንማ «ቃል የለኝ ለስጦታህ» "እኔም ስጦታህን መቁጠር አይከብደኝ አንተም መስጠት አታቆም" ያስብላችኋል

«ወደ መስቀል ወጥተህ ከመስቀል ወረድኩኝ
ለሞት ታዘዝክና በሞት ጀርባ ቆምኩኝ
ላማ ሰበቅታኒ ያልክልኝ ኤሎሄ
ፍቅርን ያስቆጠርከኝ የመውደድን ሆሄ»
እያላችሁ አብራችሁ እያቀነቀናችሁ እውነትም «አንተን ቀምሼ ወደ ኋላ አልልም» ትላላችሁ

ደግሞ «የንጋት ኮከቤ» የሚለው ዝማሬ ስትሰሙ እፎይታችሁ የሆነውን ክርስቶስን እያሰባችሁ አብራችሁ እንዲህ ታቀነቅናላችሁ

«ምስክሬ አዲስ ዜናዬ
ማወድስህ በማለዳዬ
አንተ እንድትልቅ አንስልኻለሁ
በመዝሙሬ እሰብክኻለሁ»
(ማነህ ሰምተኸኛል መዝሙር የሆነ የፕሮግራም ማዳመቂያና ማስጨፈሪያ አይደለም ወይም የናይት ክለብ አምሮትህን በዳንስ የምትወጣበት አይደለም ክርስቶስን በዜማ የምትሰብክበትና የምትገልጥበት ነው)

«ሰማይ» የሚለው ዝማሬው ደሞ ምን ይልሃል መሰለህ «አዲስ ምድር አለ አዲስ ሰማይ አለ ሙሽራህን ክርስቶስን የምታይበት በደሙ የተገነባ ሰማይ አለ» ይልሃል «ልኖር ነው የምሞተው፤ ያመንኹት ልነሳ ነው» የማለት አቅሙ ካለህ ና "ሰማይ" የሚለውን መዝሙር አብረን እንዘምር

«በትግሉ ሜዳ በመስቀል ውሎ
ነጻ አወጣኝ ገዳዬን ገድሎ
ይኸው መዳኔን አረጋገጥኩኝ
በጨረሰው ላይ ኑሮ ጀመርኩኝ»
የሚለውን ስትሰማማ እውነትም ምንም የምቆጥበው የለኝም ብለህ በገናህን ከሰቀልክበት አውርደህ

«መዝሙሬ ለካህኔ ለመካከለኛዬ
ከሞት ፍርድ ላስመለጠኝ ለሆነኝ ዋስትናዬ» ትላለህ ምነው ሲሉህ በነፍሱ ተወራርዶ ያዳነህ አምላክ እንዳለህ እንዲህ ትተርካለህ
«ብይን አግኝቷል የጥንቱ ክሴ
ሊቀካህኔ ሆኖልኝ ዋሴ»

ደሞ... ደሞ
«ስለኔ የደማው መዳፉ
የጀርባው ቁስል የጅራፉ
በደም የተሸፈነው ፊቱ
የእጁ ችንካር እትራቱ
የተከፈለው ለነፍሴ ካሳ
የደሙ ዋጋ እንዴት ሊረሳ» የሚለውን ስትሰማማ በቃ ነፍስም አይቀርልህም

«ልጅ ነኝ» ይልህና ደሞ «ወራሽ» መሆንህን ይነግርሃል እናም አትጠራጠር «ካስማህ» ክርስቶስ ነው ብሎህ ልብህን ያፀናዋል ብቻ ግን ያ የተሰቀለውን ክርስቶስን የሚሰብክ ዝማሬ ነው ይዞልን የመጣው። «አይነጥፍም ዜማዬ» ቢልም እውነት አለው «ከሕይወት ውሃ ምንጭ ከሆነው ከክርስቶስ የቀዳ» አገልጋይ ዜማው አይነጥፍም ዜማውም ክርስቶስ ነው።

ዝማሬዎቹን እንድታደምጡ አለመጋበዝ ንፉግነት ነው።

ብቻ ብቻ የሚደመጡ የዝማሬ ሰንዱቆች እየበዙልን ነው መሰለኝ . . . ጆሮኣችንን ከኳኳታና ከጩኸት የሚያሳርፉ ዝማሬዎች እየቀረቡልን ነው። እግዚአብሔር ይመስገን🙏🙏🙏

እና ይህችን መዝሙሩን ደሞ ጋበዝኳችሁ

"በሠንሰለቱ የታሠረልኝ
በርባንነቴን ሻረልኝ
30 ዲናር ነበር ዋጋዬ
ተቤዥኝ እንጂ ቤዛዬ
እንደፍቅሩ ማያባራ
እንደመልኩ የሚያበራ
በእሳት መሀል ሰጠኝ ቅኔ
የሚንኳለል ከልሳኔ"

https://youtu.be/15J3fpB1Wag?si=TqbJfker0uJjuYKj

Habtamu Shibru ፀጋ ይብዛልህ🖤🙏🖤
“ራሷን ያለስስት በመሥዋዕትነት የሰጠቸ የቪተንበርግ የማለዳ ኮከብ”


" . . . ለጌታ የምትደክሙት በከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ።" (1 ቆሮ. 15፥58)
¤¤¤¤¤¤¤¤

የሉተር ባለቤት የነበረቸው ካታሪና ቮን ቦራ (Jan. 29, 1499 – Dec. 20, 1552) አንዷ የእምነት ጀግና ሚስትና በመከራ የታገሠች እናት እንዲሁም የወንጌል ዐርበኛ ነበረች። የሉተር የተሐድሶ መንገድ ያለ እርሷ አጋርነት የሚቻል አልነበረም።ዝክሯ ሊታሰብ፤ ለትደነቅ፣ ልትከበር፣ ልትመሰገንም ይገባል።

ካታሪና የቀሬናው ሰምዖንን ታስታውሰኛለች። በግርፋትና በአደባባይ ውርደት የደቀቀው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሰለኀጢአታችንና በደላችን የሚሰቀልበትን መስቀል በመሸከም እንዳገዘው የቀሬናው ሰምዖንን፣ ያለ ካታሪና ሉተር የራሱን የመከራ መስቀል በመሽከም የተሐድሶ መንገዱን በጽናት መጨረስ አይችልም ነበር። በሰፊው ትከሻዋ ሉተርንም ኾነ ተሐድሶው የጠየቀውን መከራ በለጋ ዕድሜዋ ተሸክማለች። ስለዚህም ነው፣ ሉተር “ራሷን ያለስስት በመሥዋዕትነት የሰጠቸ የቪተንበርግ የማለዳ ኮከብ ያላት።” እግዚአብሔር የባረካት!

ትጉህን ነበረች። በላይ በላይ የተወለዱ የስድስት ልጆች ባተሌ እናት! በማለዳ በመነሣት የቤቱን ብቻ ሳይኾን፣ በዕርሻና የጓሮ አትክልት ሥራ ቤተ ሰቧንና ስደተኞችን ትመግብ ነበር። ሉተር ፕሮፌሰር እንደመሆኑ መጠን፣ በየጊዜው ቤታቸው እየመጡ በግል የሚማሩ፣ የሚያማክራቸውና ምጋቢያዊ አገልግሎት የሚሰጣቸው ተማሪዎች ነበሩት። አንዳንዴም ጦሟን እያደረች (የሴት ምራቋ ወፍራም ነው ይባል የለ!) ታሰተናግድ ነበር። ያውም ያለማጉረምረምና በፍቅር! ኑሮ ሲከብድ፣ የሚበላ ሲጠፋ፣ ልጆች ሲታመሙ፣ ኹለት ልጆቿን በሕጻንነታቸው ስትቀብር፣ የቅርብ ጓደኛ ሲከዳ፣ ጤና ሲጓደል፣ ሉተር ከድባቴ (depression) የተነሣ ዐመሉ ሲለዋወጥ፣ ሕይወት ሲጨልምና ሲከበድ፣ በልበ ስፋትና በምስጋና ነበር የምታሳልፈው።

ባሏ ሉተር፣ በሕመም እስከሞተበት ቀን ድረስ ኑሮው በሙሉ በሞት ዐዋጅ ጥላ ውስጥ ነበር። ማንም ሰው ቢያገኘው፣ እንዲገድለው ሕጋዊ ፈቃድ የሰጠው የቻርልስ አምስተኛ የሞት ዐዋጅ እንዲህ ይል ነበር፡-"

“. . . በመንግሥቴ ግዛት ያለ አስተዳደርና ዜጋ ኹሉ ሉተርን ከምድር ገጽ እንዲያጠፋው አዝዣለሁ።" (Heiko A. Oberman, Luther: Man Between God and the Devil, 29.)።

ሉተር እጅግ ስለከበደው የአገልግሎት መንገድ እንዲህ በማለት ገልጾታል፤ “የመከራ ጐርፍና ማዕበል አብረው፣ እምነቴን የሚፈትን ድቅድቅ የቀን ጨለማ ውስጥ ከተውኛል።” (ዕለተ August 2, 1527 የጻፈው

በወርሃ August 1527፣ ማርቲን ሉተር ያገለግልባት የነበረቸው የቪተንበርግ ከተማ በወረርሽኝ በሽታ ምክንያት ጨልማ ነበር። ባለቤቱ ካተሪና ቮን ቦራ ነፈስ ጡር ነበረች። መከራና ስደት ላስጨነቃቸው ሉተርና ካታሪና፣ ወረርሽኙ ድንገት የመጣ የመከራ ጐርፍ ነበር። ተከትሎት የመጣውን ጥቁር ሞት (Black death) ለማምለጥ ብዙዎች ሽሽት ሄደው ጭር ከማለቷ ይተነሳ፣ ቪተንበርግ የጨለማው መናፍስት መኖሪያ መስላለች። ወዳጁ የሳክሰኒ (Saxony) ልዑል ዮሐንስ (The Steadfast John)፣ ሉተርም እንዲሽሽ የግድ ብሎት ነበር። ኾኖም ብዙ ዐቅመ ደካሞችና በእምነታቸው ምክንያት መከራው ውስጥ የነበሩትና በወረርሽኙ የተያዙን አማኞች ትቶ መሸሽን አልመረጠም። በተለይም ካተሪና። ሉተር እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፤-

"መልካም እረኛ፣ ምንደኛ አይደለም። በመከራና በሞት ጥላ መካከል ለመንጋው ጥንካሬ፣ ጽናትና መጸናናት እንዲኾን [ታላቁ እረኛ] ክርስቶስ የጠብቀብታል።" (Luther, Whether One May Flee From A Deadly Plague, 1527 Translated by Carl J. Schindler [Vol. 43, Page 117]).

ካተሪና የክርስቶስ ማኅብረ ሰብ በመከራ ውስጥ ለእግዚአብሔር ክብር እንዴት መኖር እንዳለበት በማስተማር፣ በመጸለይና የርኅራኄ አገልግሎት ከሉተር ጋር በታማኝነት በመስጠት ዐደራዋን ተወጥታለች። የታመሙትንና በሞት አፋፍ ላይ የነበሩትን፣ በአንዲት ሕይወታቸው ላይ ፈረደው በክርስቶስ ፍቅር አገልግለዋል። በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ (August 2-19)፣ ከቅርብ የሥጋ ዘመዶቹና አብረዋቸው ከሚገለግሉት መካከል 18 ሰዎች ቀብረዋል። የከተማዋ ከንቲባ ቲሎ ዴን (Tilo Dene) ባለቤት ከሞት አፋፍ ላይ የተመለሰችው በእነርሱ እንክብካቤ ነበር።

በእግዚአብሔር ቸርነት ዓመት ከሁለት ወር የነበረው የመጀመሪያ ልጃቸው ኻንስ (ዮሐንስ) ከሞት ተርፏል። ኾኖም ግን ወረርሽኙ ጋብ እንዳለ ከአራት ወራት በኋላ December 10, 1527 የተወለደችው ኹለተኛ ልጃቸው ኤልሳቤጥ በስምነት ወሯ ሞታባቸዋለች። ሉተር፣ የልቡን ስብራት እንዲህ በማለት ገልጦታል፦

"ሕጻን ልጄ ኤልሳቤጥ ሞተችብኝ! ልቤ በእጅጉን ደሞቷል፤ ታሟልም። መሸከም የማልችለውን ሐዝን ትታብኝ ሄዳለች . . . እጅግ ከብዶኛል። ወደ ጌታ ጸልዮልኝ።” (Luther’s Works 49:203).

እናት ካተሪና ደግሞ በበኩሏ እንዲህ ስትል ከትባለች፤

“መልካሙ ጌታ፣ ውቧን ኤልሳቤጥ ከቸርነቱ ሰጦቶኝ ነበር። በዚህ እጅግ ደስተኛ ነበርሁ፤ ጌታንም ባርኬ አመስግኜዋለሁ። ሞት ይዞ የመጣው ወረርሽኙ ራሱ ወቅቱን ጠብቆ [በእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት] ሞቶ ተቀብሯል! ይኹን እንጂ ቁጣው ልጄ ከመወለዷም በፊት እጁን ያሳረፈባት ይመስለኛል። በስምንት ወሯ ውዷ ኤልሳቤጥ አባቷንና እናቷን ተሰናብታ ወደ ክርስቶስ ሄዳለች። (Bainton, Roland H. Women of the Reformation in Germany and Italy. Augsburg: Fortress Publishers (1971).

ለካታሪና፣ ሐዋርያው ጳዉሎስ በመከራ ሲያልፍ፣ የተጽናናበት መጽናናት ድጋፏ ነበር፦

"በሕይወት ለመኖር እንኳ ተስፋ እስከምንቈርጥ ድረስ ከዐቅማችን በላይ የሆነ ጽኑ መከራ ደርሶብን ነበር። በርግጥም የሞት ፍርድ እንደ ተፈረደብን ይሰማን ነበር፤ ይህም የሆነው ሙታንን በሚያስነሣ በእግዚአብሔር እንድንታመን እንጂ፣ በራሳችን እንዳንታመን ነው።" (2 ቆሮ.1፥8-9)

ጳውሎስንም በመከተል፣ በሕይወት በመኖርም፣ መሞትም፣ በመከራም በዕረፍትም ለጌታ ለመኖረ የቈረጠች ታማኝ የወንጌል አገልጋይ ነበረች። “ከእኛ ማንም ለራሱ የሚኖር፣ ለራሱም የሚሞት የለምና። ብንኖር ለጌታ እንኖራለን፤ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን፤ ስለዚህ ብንኖርም ብንሞትም የጌታ ነን። (ሮሜ 14፥7-8)።

ካታሪና በግምት የ9 ዓመት ሕፃን ከነበረችበት ጊዜ ጀምሮ ነበር በደናግላን ገዳም ውስጥ የምትኖረው። በኒብሸን ገዳም (Nimbschen) በነበረችበት ጊዜ፣ በሉተር የተጀመረው ተሐድሶ ከምድረ ጀርመን ዐልፎ በአውሮፓ እንደ ሰደድ እሳት እየተባዛ ነበር። ስለ ሉተር፣ በተለይም "ድነት በእምነት፣ በጸጋ፣ በክርስቶስ ብቻ፤ ቅዱስት መጻሕፍት ደግሞ የመጨረሻ ባለሥልጣንነት" ትምህርት በየገደማቱ በምስጢር ይገቡ ነበር። በ24 ዓመቷ፣ ካታሪና እና ጥቂት ጓደኞቿ ተሐድሶው ለመቀላቀል ከገዳም ጠፍተው አመለጡ። ምንም እንኳን በ16 ዓመት ታላቋ የነበረ ቢሆንና የተሻለ ሰው እንድታገባ ጫና ቢደረገባትም፣ በተገኘበት እንዲገደል ከተፈረደበት ማርቲን ሉተር ጋር ለመኾን ወሰነች። ይኽም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር። June 13, 1525 ተጋቡ። ከስደት የተነሣ ኑሮአቸው፣ በድኽነት፣ በሰቀቀንና በሥጋት የተሞላ ነበር። ክርስቶስንም ባሏንም
የምትወድና የምታከብር ትከሻ ሰፊ የእግዚአብሔር ሰው ነበረች - በእውነትኛ አግባቡ!

ባሏን፣ "ጌታ ዶክተር (Sir Doctor) በማለት ስትጠራው፣ እርሱ ደግም በተራው፣ "የልቤ ማር፣ ሆዴ፣ ውዴ ካቲ" ነበር ምላሹ። የትዳራቸው መሠረት የወንጌል እውነት ነበር። በዘመኑ ከነበሩት ከጥቂቶች ጋር፣ ከእውነትና ጽድቅ ጋር የቆመች ጀግና! ከስድስት ልጆች ማሳደግ፣ የማያቋርጥ የእንግዶች መስተንግዶና፣ ከሉተር ኅላፊትነት ጋር ቀኑኑ ሁሉ ስትባክን ብትውልም፣ ብርቱ የጸሎት እናት ነበረች። ሉተር ሲጨነቅ፣ እርሷም ግራ ሲገባት ብዙ ጊዜ ያቆማት፣ መዝሙር 31፥2-3 ነበር፦

"ጆሮህን ወደ እኔ መልሰህ ስማኝ፤
ፈጥነህ አድነኝ፤
መጠጊያ ዐለት ሁነኝ፤
ታድነኝም ዘንድ ምሽግ ሁነኝ።
አንተ ዐለቴና መጠጊያዬ ነህና፣
ስለ ስምህ ስትል ምራኝ፤
መንገዱንም ጠቍመኝ።"

ሉተር ታሞ በድንገት በሞት ሲለያት፣ ሐዘን እጅግ ከብዶባት ነበር። የቀን ጨለማ ነበር የሆነባት። ለወንድሟ ሚስት (ክርስቲና ቮን ቦራ) የጻፈቸው ደብዳቤ፣ ለሉተር የነበራትን፣ ጥልቅ ፍቅር፣ ትልቅ አክብሮት፣ እንዲሁም ዐጥንቷ ውስጥ ዘልቆ የገባው ሐዘን ይገልጻል፤-

“ክርስቲና፣ ሐዘን ለጐዳን ለእኔና ለድኾች ልጆቼ ያለሽን ጥልቅ ርሕራሔና ፍቅር ከደብዳቤሽ ተርድቻለሁ። ውዴ ሉተር ለከተማውና ለአገሩ ብቻ ሳይሆን ለመለው ዓለም ሁሉ ራሱን ሳይሰስት ሰጥቷል። እውነት ነው - ሐዘኔ ዐጥንቴ ውስጥ ዘልቆ ገብቷል። የልቤን ስብራት ልገልጽ የምችልበት ቃል የለኝም። የሚስማኝን፣ እንዲሁም አእምሮዬ፣ ልቤና መንፈሴ ያሉበትን ኹኔታ ማስረዳት አልችልም . . . እንደ ሉተር ያለ እግዚአብሔርን የሚፈራና የተከበረ ባል አጥታ፣ ልቧ እጅጉን የማይሰበርና የማይከፋት ሴት የለችም። መብላትም ሆነ መጠጣት አልቻልሁም . . . በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ እንቅልፍ እንቢ ብሎኝ በጭንቅ ነው ለሌቱ የሚነጋው። ዓለምን ሁሉ የምገዛ ቢሆንና አሁን ደግሞ ድንገት ያጣኋት ቢሆን ኖሮ እንኳን ይህን ያኽል ሐዘን አይጐዳኝም ነበር። ይልቁንም ዓለምን ሁሉ አጥቼ ፍቅሬን ሉተርን ባገኘው ምንኛ ደስ ባለኝ! እግዚአብሔር ውዴን ከእኔ፣ ከልጆቼና ከቅዱሳን እጅ ወስዷል። እግዚአብሔር በደንብ እንደሚያውቀው ይህን ባሰብኩ ቁጥር ሐዘኔ ይከብዳል - የማያቋርጥ እንባ ከዐይኖቼም ከልቤም ይፈስሳል።" (Martin Treu, Katharina von Bora, the Woman at Luther's Side, Lutheran Quarterly, Volume XIII (1999), 157.)

በሌላ ወረርሽኝ እስከ ሞተችበት 1552 ድረስ ለስድስት ዓመታት ያህል መከራና ድኽነት እጅግ በከፋ መልኩ እይተፈራርቁ አሠቃይተዋታል። በዚሁ ኹሉ ልጆቿን በፍቅርና በእግዚአብሔር ቃል ለብቻዋ አሳድጋለች። ሐዘንና ችግር ሲያቆራምቷት፣ ከዳዊት ጋር አብራ፦ "መጠጊያ ዐለት ሁነኝ . . . " ብላ በመዘመር፣ ልቧን ደግፋለች። ድንቅና ምስጋና የሚገባት የተባረከች የእግዚአብሔር ሰው!

በመከራ ውስጥ እያለፋችሁ፣ ለምታገለግሉ ጸጋና ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን። በርቱ፤ ብድራታችሁ ታላቅ ነውና!

"ነገር ግን ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ደስታችሁ ታላቅ እንዲሆን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ።" (1 ጴጥ. 4፥13)

አሜን!

© ግርማ በቀለ
በአማኑኤል ካቦድ አጥቢያ እንገናኝ 🙏🙏🙏
አንዳንድ ጊዜ በብዙ ነገር ግራ ተጋብተን አቅጣጫ ሲጠፋብን የሕይወት ውጣ ውረድ ልባችንን አዝሎ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ተቀምጠን እናቃለን።

ነቢዩ ኤርሚያስ እንዳለው ተሰምቶንም ይሆናል

"ሕይወቴን በጕድጓድ አጠፉ፥ በላዬም ድንጋይ ጣሉ። በራሴ ላይ ውኆች ተከነበሉ፤ እኔም፦ ጠፋሁ ብዬ ነበር።" (ሰቆ 3:53-54)

ጠፋን ያልንባቸው ጊዚያቶች ሁሉ የተሻገርናቸው ሊያጠፉን ስላልቻሉ ሳይሆን የሚደግፈን የሚሟገትልን ስላለ ነው። አይታለፍም ባልነው አስፈሪ በመሠለን ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ሆነን እንኳን ልንጠራው የምንችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው።

" አቤቱ፥ በጠለቀ ጕድጓድ ውስጥ ሆኜ ስምህን ጠራሁ። ድምፄን ሰማህ፤ ጆሮህን ከልመናዬ አትመልስ። በጠራሁህ ቀን ቀርበህ፦ አትፍራ አልህ። ጌታ ሆይ፥ ስለ ነፍሴ ተምዋግተህ ሕይወቴን ተቤዠህ።" (ሰቆ 3:55-58)

በጠለቀ ጉድጓድ ውስጥ እንሆን ይኾናል። በሚያስደነግጥ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እናልፍ ይኾናል። ተስፋ በሚያስቆርጥ ዘመን ውስጥ ተስፋ ልናደርግበት የምንችለው እግዚአብሔር ግን አለ። በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ላለ ቀርቦ አይዞህ የሚል ድምፁን የሚያሰማ አትፍራ የሚል የሚቤዥ።

በሕይወታችን ብዙ ብዙ ሆኖ ይኾናል። በተራራውም በሸለቆውም በብርሃኑም በጨለማውም በከፍታውም በዝቅታውም በደስታችንም በሀዘናችንም አብሮን የነበረ አብሮን የቀረ በጠለቀ ጉድጓድ ውስጥ ሆነን ስንጠራው ድምፃችንን የሰማ ግን እግዚአብሔር ብቻ ነው።

"እንዴት ይታለፋል፥ እንዴት ይዘለቃል
ያልኩትን ተራራ አደላድለኸዋል
ያልኩትን ጨለማ ጌታ ገፈኸዋል
ኩራቴ ማረፊያ እወድሃለሁ
ሌላማ ምን እልሃለሁ" የሚል ድንቅ መዝሙር አለች የዘማሪ Denberu Bayleyegn

© ቢት ነኝ
ዛሬ 28ኛው መርሃ ግብራችን ይደረጋል ይምጡ!
°ፍቅር ግድ ይለዋል°

ብዙ ጊዜ ከመተኛቴ በፊት እና ጠዋት ከእንቅልፌ ሲነቃ ራሴን ቆንጆ መዝሙር የመጋበዝ ልምዱ ነበረኝ፤ከዶ/ር ደረጄ መዝሙሮች ዝም ብዬ አንዱን መዥረቅ አድርጌ ማጫዎት ጀመርኩ...

ገና ቢቱ ሲጀምር ከሁሉም መገጣጠሚያዎቼ ጋር ላላሁ፤ልክ መዝሙሩን ሲጀምር አቅሜ ከዳኝ፣እንደት ከተቀመጥኩበት ሙሽሽ ብዬ ከወንበሩ ላይ ወርጄ ከመሬት እንደተነጠፍኩ አላውቅም...ስስ በሆነ Old ሜሎዲ ከብዙ ትዝታ ጋር የግጥሞቹ ክብደት ሁለንተናዬን ጠፍሮ ይዞታል።

"ፊቱን መለስ አርጎ እምባዬን ባ'ይኑ ሲያይ ፈውስ ይሆንልኛል
እሩሩህ ነው ፍፁም ነፍሴን ካ'ንድ ሁለቴ አድኖ ሠጥቶኛል"

.. ሲል ቃል በቃል ግጥሙን እያስተዋልኩ፣ ድምጽ አውጥቼ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፣ንፍርቅ እያልኩ።

(ፊቱን መለስ አርጎ ዕንባዬን በዓይኑ ሲያይ ፈውስ ይኾንልኛል)

ከምል ዜማ ጋር ነፍሴ ሲቃዋን ጮኻ ታሰማለች፣ ድንገት ነፍሴ ቆሽቴዋ ተነካ፣ለካ ክፉኛ ተጎድታ ነበር፤ ፊቱ እንደራባት፣ የለመደችው ምቾት እንደራቃት፣ በደንብ ታሳብቃለች፣ፊቱ ፈውስዋ መኾኑን ጠንቅቃ ታውቃለች፣ እንደዚያ ቦታ የትም ምቾት የሰጣት እንደለለ እየጮኸች ነገረችኝ።

በገሃዱ ዓለም ስስቅ የተደላደልኩ የመሰለኝ ለካ መስሎኝ ነው፤ ነፍሴ ታማብኛለች፤እርር አለች በገነች፣ባዕንባዋ የኾዱዋን ብሦት ዝርግፍ ታደርጋለች፣ ደረጄ ቀለል አድርጎ መዝሙሩን ይዘምረዋል፣ እኔ ግን እኔን አይደለሁም።

የኾነ ቁጥር አለ ደግሞ ስሜን መጥራት የቀረው፣ ይኼ ቁጥር Shocked ያረገኛል፣ ደንግጬ ዝም ነው ያልኩት።

"የኃጢአቴን መጠን
ቆጥሮ ቢመዝነው
ምህረት አይገባኝም
በውድቅት ለሊት
የከበረ ሥሙን
መጥራት መብት የለኝም"

ይኼ ስንኝ በቃ ከአቅሜ በላይ ነበር፣ በቅጽበት ስንት ጊዜ እንደማረኝ ትውስ ይለኝ ነበር፤ ከበደሌ ብዛት ሁሌ ማረኝ ታክቶኝ ጥቂት ቀናትን ብሪቅ፣ በጽድቄ አፍሬ ብሸሸው፣ ስሙን ልጠራ ክንድ ሳጣ፦

ግን ደግሞ ከርሱ በቀር ከነ ግሳንግሴ የሚያስጠጋኝ እንደሌለኝ ስገባኝ…ስንቴ በዕምባ ፉቱ ድፍት እንደምል፣ስንቴ እቅፍ አድርጎኝ እንዳስጠጋኝ ትዝ ስለኝ፣የዕንባዬ መዓት ከጉንጮቼ ዘልቆ ልብሴን እስኪያያረጥበው ይጎርፍ ነበር።

በእንባዬ መሓል እኔ <<ዛሬ እንኳን እንደኹል ጊዜዬ ይቅር በለኝ የምልህ ድፍረት የለኝም፤ ይህን ኹሉ ጊዜ ፍቅርህን ቀምሼ፣ አጠገቤ ካለው ሰው ይልቅ ዳስሼኽ፣ግን ደጋግሜ እልፍ ጊዜ ስበድልኽ፦ እንደት እስካሁን አላጠፋኸኝም?፣ እስከመቼ ትታገሰኛለኽ?>>

እያልኩ ድክመቴ አድክሞኝ ስንሰቀሰቅ ደግሞ እንዲህ ይላል…

ነገር ግን አምላኬ
እንደ ሠው አይደለም
ዘላለም የሚጥል
አልተኛም ለሊቱን
ደጁን አንኳኳለሁ
እጅ እግሬ እስከሚዝል"

ኦኦ ጌታ ኾይ ይኼን የዘመረው የደረጄ ሕይወት ከኔ ሕይወት በእጥፍ እንደሚሻል ተስፋ አደርጋለሁ፣ እሱ ሌላው ቢቀር፦ ብዙ መዝሙሮቹ ውስጥ እንዳየኹት ለሊት እንቅልፉን ሰውቶ ላምላኩ ጉዋዳውን የሚያስጎበኝ ጠንካራ ሰው ነው፤ ድካሙን በአደባባይ የሚዘምር ትሁትም ነው፤ እኔ ግን ዘውትር ስለ ጉብዝናዬ እንዲወራልኝ የሚሻ፣ ጥቂት ሳልተጋ ብዙ የምሰብክ ሸንጋይ ነኝ።

ብቻ እንቅልፌን እስኪሰዋልኽ እኔንም ሰዋኝና ወድጄህ ልሙት፣ ዕድሜዬ ያልሆንኩትን በማውራት አይለቅብኝ፤ የሆንክልኝን በማውራ፣ የሆንኩልህን በመደበቅ አሳድገኝ።

….
ተስፋ ያጣሁ መስዬ
ማን ይቀበለኛል
ወዴት እሄዳለሁ

ግድ ያለው ለነፍሴ
ኢየሱስ ነውና
ሥሙን እጠራለሁ

ዶሮ ሲጮህ ያኔ
እጁ ይዳስሠኛል
ፍቅር ግድ ይለዋል

መድኃኒት የሆነኝ
እድሜዬን ቀጣዩ
መቼ ያስችለዋል…

አሜን!

© ብሩክ ጴጥሮስ
ያን ያህል አፍቃሪ አይደለሁም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቃላቶቼ ፍጹምነት ሲያጠቃቸው ፈራኃቸው፣ በዝምታ ልተካቸው ሞከርኩኝ፣ ካንተ የሚሠወር ሚሥጢር የለኝም ታውቃለህ።

"እወድሃለሁ" እልህና ግን ደግሞ "የምር እወደዋለሁ?" ብዬ ሳስብ ላንተ ያለኝን ፍቅር በከንፈሬ እንጂ ከተግባሬ ውስጥ ፈልጌ አጠዋለሁ።

ያ'ላንተ እኔነቴ ትርጉሙ ምንም መሆኑን ጠንቅቄ ባውቅም በተግባሬ ግን ያን ያህል የ አንተ ጥገኛ አይደለሁም።

ሆኖም ግን ዝምታዬን ጥሼ ስምህን ሳልጠራ የማልውለው ነፍሴ የዳነችበቱ፣ የስምህ በከንፈሬ ላይ መጣፈጡ፣ ጣዕሙ ዕረፍት ነስቶኝ ነው እንጂ ስምህን ልጠራ እንኳ የተገባሁ ሆኜ አይደለም።

ልርቅህ ያልቻልኩ ልኖርልህም፣ እኔ መቼ ይሆን "እወድሃለሁ" በምትል ቃሌ ልክ ልወድህ የምችለው ጌታዬ!?

በቅዱሳን ህብረት ውስጥ ተቀምጬ ቃልህ ሲነገር፣ ምን ያህል እንደወደድከኝ፣ ምን ያህል ይቅር እንዳልከኝ፣ ማዳንህን በመንፈሴ ነፍሴ ስትዳስስ፣ ጥርሴን ነክሼ እያነባሁ፦

"የምትወደውን ልወድ የምትጠላውን ልጠላ፣ እንደማርከኝ ልምር እርዳኝ እንጂ! ቃልህን በየዕለቱ አነበዋለሁ፣ ለተ ቀን በፊትህ ጸሎት አደርጋለሁ፣ እንደወደድከኝ እወድሃለሁ" ያላልኩህ ጊዜ ጥቂት አይደለም።

አንተ ግን በነዚያ ክዳኖቼ ውስጥ ከ ፉከራ የዘለለ አንዳች የህፃን ፍቅር፣ በዛለ በተፍረከረከ ጉልበት አንተን ለማስደሰት መፍጨርጨሬን አይተህ ካልሆነ በቀር፦

ሽንገላዬ ምን ያህል አቁስሎህ ይሆን?

መውደዴ እያለቀብኝ ይሁን ወይ እየደበዘዘብኝ አላውቅም ብቻ ዘውትር አልወድህም፣ የምጠላህም ቀን አለ፣ የምትመቸኝም ቀን አለ፣ ስላንተ መስማትም መናገርም የሚያስጠላኝ ጊዜ አለ፣ ያንተ ፍቅር ብቻ የሚቆጣጠረኝም ጊዜ አለ።

አንተ ዘውትር መልካም ሆነህ ሳለህ እኔ ዘውትር ልወድህ አለመቻሌ እና እኔ ክፉ ሆኜ አንተ እኔን ዘውትር መውደድህ ሁሌም ይገርመኛል።

ስለወደድከኝ አመሠግናለሁ!

© ብሩክ ጴጥሮስ