ነአምን media
43.3K subscribers
1.79K photos
139 videos
9 files
950 links
Buy adds:- https://telega.io/c/neamn_media

<< ነአምን በአሐዱ አምላክ እግዚአበሔር!>>
ይህ ቻናል ኦርቶዶክሳዊ
#ትምህርቶች
#ዝማሬዎችና
#ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ስነ-ፅሁፎች
የሚለቀቁበት ቻናል ነው።

ለሁሉም መረጃና አስተያየትና በቻናሉ ላይ ለመፃፍና ለመሳተፍ @theofloss ያናግሩን መረጃውንም ያካፍሉን።
Download Telegram
✞       በሰሙነ  ሕማማት  ይህንን  አድርጉ    ✞

         ( በሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ )
                   -------------------------
          ለኹሉም እንዲዳረስ ሼር ይደረግ !

ሰሙነ ሕማማት አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ሁሉ ቤዛ ሆኖ ተላልፎ መሰጠቱን የምናስታውስበት ሳምንት ነው።

ይህንን ምክንያት በማድረግ የሥርዓት ለውጥ ሲደረግ ሲመለከቱ ግራ የሚጋቡና ሥርዓተ አምልኮውን በሚገባ ከመከታተል ይልቅ ሥርዓት የጣሱ እየመሰላቸው የሚጨነቁ ስላሉ ልናደርገው የሚገባንን እጽፍላችኋለሁ።

1️⃣.  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብሎ ፊትንና መላ ሰውነትን በትዕምርተ መስቀል {በመስቀል ምልክት} ማማተብ አይከለከልም። ከካህን እጅ ቡራኬ አንቀበልም በካህኑ እጅ ያለውን መስቀል አንሳለምምና ማማተብም የለብንም በሚል ፍልስፍና ካልሆነ ማማተብ ክልክል ነው ተብሎ የተጻፈበት ቦታ የለምና።

2️⃣.   የሚከለከል ጸሎት የሌለ መሆኑን አውቃችሁ ያስለመዳችሁትን ጸሎት በትጋት ጸልዩ። መሥዋዕት ካለመሠዋታችን ቅዳሴ ካለመቀደሳችን በቀር በዚህ ሳምንት ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጀምሮ እስከ ሊቃውንት ድርሳናት ድረስ በቤተ ክርስቲያን የማይጸለይ ጸሎት የለምና።

3️⃣.  ሰላምታ መስጠት ከጸሎተ ሐሙስ ዕለት በቀር አልተከለከለም፤ እሱም ቢሆን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በይሁዳ ሰላምታ ተላልፎ መሰጠቱን ለማስተዎስ እንጅ ሌላ የተለየ ምክንያት ስለሌለው በመርሳት ወይም በሌላ ከድፍረት በተለየ ምክንያት ሰላምታ ያቀረበላችሁን ሰው ልታስደነግጡና ትልቅ ኃጢአት እንደሠራ አድርጋችሁ ልታስጨንቁት አይገባም።

4️⃣.  “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ” ብሎ መጻሕፍትን ማንበብ ወይም ሌላ ሥራን መጀመር ይቻላል። ስመ እግዚአብሔር መጥራት የምንከለከልበት ጊዜ መቸም የለምና።

5️⃣.  የጌታችንን ሕማሙንና ሞቱን የሚያስታውሱ መጻሕፍትን በማንበብና በመስማት ጊዜአችንን መወሰን ይገባናል።

6️⃣.  በዚህ ሳምንት ተድላ ደስታን ሲያደርጉ መገኘት ከአይሁድ ጋር እንደ መተባበር የሚያስቆጥር ስለሆነ አብዝቶ በመብላትና በመጠጣት፣ ያማረውንና ጌጠኛውን ልብስ በመልበስ፣ ባልና ሚስት በምንጣፍ በመገናኘት እንዲሁም በልዩ ልዩ ምክንያት ከምናደርጋቸው ተድላ ደስታዎች መራቅ ይገባናል። ቅዱሳን በዘመናቸው ሁሉ ባሰቡት ጊዜ የሚያስጨንቃቸውን የክርስቶስን መከራ እያሰብን ለጥቂት ጊዜም እንኳን ቢሆን የክርስቶስን መከራ በሰውነታችን ማሰብ ይገባናል።

የተቻለው እንደ ጴጥሮስ የራሱን ኃጢአት እያሰበ እንደ ማርያም መግደላዊት የክርስቶስን ሞት እያዘከረ ሊያለቅስ ይገባዋል።
በወዲያኛው ዓለም ከማልቀስ የሚያድነን ዛሬ የራሳችንን ኃጢአት አስበን የክርስቶስን ሞት አዘክረን የምናለቅሰው ለቅሶ ነው እንጅ ዛሬ ከተደሰትን ደስታችንን በዚህ ዓለም ማድረጋችን አይደለምን?

7️⃣.  በተቻለን መጠን በቤተ ክርስቲያን መዋል ይገባናል፤ ሕማማተ መስቀልን የሚያስታውሱ መጻሕፍት የሚነበቡበት ሳምንት ስለሆነ ነው። ነገር ግን በልዩ ልዩ ምክንያት በቤተ ክርስቲያን መዋል እንኳን ባይቻላችሁ ባላችሁበት ቦታ ሁናችሁ እየዋሻችሁ በሐሰት የከሰሱትን፣ እየቀማችሁ ልብሱን የገፈፉትን፣ ሰው እየደበደባችሁ በጅራፍ የገረፉትን፣ በወንድሞቻችሁና በእኅቶቻችሁ ላይ እየፈረዳችሁ በክርስቶስ ላይ የፈረዱበትን፣ በሰዎች ላይ እየተዘባበታችሁ የተዘባበቱበትን፣ በሳቅና በሽንገላ ሰውን እየሸነገላችሁ ሽንገላ በተሞላበት ሰላምታ ጌታውንና መምህሩን አሳልፎ የሰጠ ይሁዳን ልትመስሉ አይገባም።

ይልቁንም በአይሁድ እጅ ተላልፎ ቢሰጥም ንጹሓ ባሕርይ መሆኑን በማመን እስከ ቀራንዮ የተከተሉትን ደቀመዛሙርት ልትመስሉ ይገባል። እግራችሁ በመቅደሱ ውስጥ ባይቆምም ልባችሁን ከመቅደስ ልታወጡት አይገባም። እያዘናችሁ ባላችሁበት ቦታ ዋሉ።

8️⃣.  በቤታችሁም ሆነ በቤተ ክርስቲያን አብዝታችሁ ስገዱ። ስለሁላችንም ቤዛ የሚሆን ክርስቶስ በፊታችን መስቀል ተሸክሞ ሲወድቅ እያያችሁት ትቆማላችሁን? አይሁድ ገፍተውት አንድ ጊዜ ወደ ምድር በወደቀ ጊዜ ለወደቀው መውደቅ ዘመናችንን ሙሉ ብንወድቅ ብንነሣ ውለታ መክፈል እንችል ይመስላችኋል?
ቅዱሳን ሳያቋርጡ ሲሰግዱ የሚኖሩት ክርስቶስ በፊታቸው በአይሁድ እጅ እየተገፋ መስቀሉን እንደተሸከመ ሲወድቅ በዓይነ ሕሊናቸው ስለሚያዩት ነው።
በስንክሳር ተጽፎ የምናገኘው ዜና ሞታቸው እየሰገዱ ሳሉ ሞት ነፍሳቸውን ከሥጋቸው ለይቶ እንደሚወስዳትና ለስገደት ታጥቀው እንደተንበረከኩ እንደሚገኙ ይነግረናል። የተሰቀለውን ክርስቶስን የሚያስብ ሰው ለሰውነቱ ዕረፍትን አይሻም።

9️⃣.  ከሁሉም ሰው ጋር ፍቅርን አድርጉ። ሰውን ለመውደድ ምክንያት አታብጁ። ክርስቶስ አሳልፎ የሰጠውን ይሁዳን “ወዳጄ” ብሎ ሲጠራው አትሰሙትም?

እግዚአብሔርን አንተን ያለ ምክንያት እንደ ወደደህ አንተም ያለ ምክንያት ሰውን መውደድ ልመድ። ክርስቶስ አንተን ጠላቱ ሆነህ ሳለ ፍቅርን ካላጎደለብህ ለጠላትህ ፍቅርን አታጉድልበት።

ክርስቶስ ይሁዳን ‘’ወዳጀ’’ ብሎ ከጠራው አንተም ይሁዳዎችህን ወዳጀ ብለህ ጥራቸው። አውቃለሁ ጠላትን መውደድ መራራ ሐሞትን ከመጠጣት በላይ መራራ ነው። ነገር ግን እኔም ለይሁዳዎቻችን ፍቅርን እንስጥ ማለቴ መራራ ሐሞት የጠጣ ክርስቶስን እንድንመስለው ነው።

1️⃣0️⃣.  ለሁሉም መስጠት በምትችሉት መጠን ስጡ እንጅ አትቀበሉ። ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነውና በመስጠታችሁ ብፁዓን ተብለው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገቡት ትቆጠራላችሁ።

ምናልባትም የምትሰጡት ገንዘብ ባይኖራችሁ ዕዳ ይሆንባችሁም ቢሆንም ገንዘብ ለሰጧችሁ ባለጠጎች የምትሰጡት ጸሎት ሊኖራችሁ ይገባል። ከምንጊዜውም የበለጠውን ስጦታ የተቀበልንበት ሳምንት መሆኑን እያሰባችሁ አንዳች የምጸጡት ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ስጦታ የሌላችሁ ባዶዎች እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ።

ከሁሉ በላይ የሆነውን ስጦታ የጌታን ሥጋና ደም እነሆ ተቀብለናል።  
  
ክርስቶስ መድኃኒነ
መጽአ ወሐመ በእንቲአነ
ወበሕማማቲሁ ቤዘወነ

          ( ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ )
https://t.me/neamn_media
4
የሰሙነ ሕማማት ሰኞ

መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው


ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ አድሮ በማግሥቱም ከቢታኒያ ሲመጡ ተራበ፡፡ (ማር.11፤11-12) ቅጠል ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳች ፍሬ አላገኘባትም፡፡ ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረገማት። በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ናት፤ ፍሬ የተባለች ሃይማኖትና ምግባር ናት፤ ከእስራኤል ፍቅርን፤ ሃይማኖትን፤ ምግባርን ፈለገ አላገኘም፤ እስራኤል (ሕዝበ እግዚአብሔር) መባልን እንጂ፤ ደግ ሰው አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፤ በመርገሙ ምክንያት እርሱ ከለያቸው በስተቀር ደግ ሰው ጠፋባት፡፡

በለስ ኦሪት ናት፤ ኦሪትን በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ በማለት ፈጸማት፤ ሕገ ኦሪትን ከመፈጸም በቀር በእርሷ ድኅነት አላደረገባትምና፤ ፍሬ በአንቺ አይሁን አላት፤ ደኅነት በአንቺ አይደረግብሽ ብሏታልና እንደመድረቅ ፈጥና አለፈች፡፡

በለስ ኃጢአት ናት፤ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነች ሁሉ ኃጢአት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል፤ ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሰሩት ደስ ደስ ያሰኛል፤ ኋላ ግን ያሳዝናል፤ ወደ እርሷም ሄዶ ማለትም ከኃጥአን ጋር ዋለ፤ ኃጥእ ከመባል በቀር በአንደበቱ ሐሰት፤ በሰውነቱ ክፋት እንዳልተገኘበት ለማመልከት ፍሬ አላገኘባትም አለ፤ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚለውም፤ በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ለማለት ነው፤ ስትረገም ፈጥና መድረቋም፣ በአዳም ምክንያት ያገኘችን ዕዳ በደል በእርሱ ካሣነት እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡

አንጽሆተ ቤተ መቅደስ የተፈጸመበት ዕለት ነው

ጌታችን በለስን ከረገማት በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፤ ቤተ መቅደስ፣ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምስያጥ (የንግድ ቤት) ሆኖ ቢያገኘው ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች፤ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸው፤ ገርፎም አስወጣቸው፤ ይህም የሚያሳየው ማደሪያው ቤቱ የነበርን የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡

በዚህ በሰሙነ ሕማማት ካህናትና ምእመናን በቤተክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፤ በሠለስተ፣ በስድስቱ ሰዓት፤ በተሰዓቱ ሰዓትና በሠርክ መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፤ በተለይም ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፤ ምክንያቱም የደረሰብን መከራ ኀዘኑን እና 5ሺ ከ5መቶ ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ይኖር እንደነበረ ለማዘከር ነው፡፡
🥰2

ድርሳን በእንተ ሕማማቲሁ ለክርስቶስ


የተወደዳችሁ የክርስቶስ ወዳጆች ሆይ ስለገነት የተባለው ነገር ሐሰት አይደለም፡፡ ልቡናችንን የሚያበራ የጽድቅ ፍሬ እግዚአብሔርን በማወቅ አግኝተናልና፡፡ የማይጠወልግ አበባ የማይረግፍም ቅጠል ወጣልን፡፡ እነሆ ዛሬ የማይጠፋና የማያልቅ ፍሬን አገኘን፡፡ ወንድሞች ሆይገነት (ዕፀ በለስ) ከዕፀ ሕይወት በስተምሥራቅ እንደ ተተከለች በተረዳ ነገር እነግራችኋለሁ፡፡

ስለዚህ ስለ ዕፀ በለስ እግዚአብሔር ከእርሱ በበላችሁ ቀን የሞት ሞት ትሞታላችሁ አለ፡፡ ስለዚህ ዕፀ ሕይወት ግን መንፈስ ቅዱስ በዳዊት ላይ አድሮ እግዚአብሔርቸር እንደሆነ ቀምሳችሁ ዕወቁት አለ፡፡ መልኩ ያማረ ሲበሉትም የሚጣፍጥ ሰፊም እንደ ሆነ፡፡ እርሱም እንደ ወይራ ፍሬ ቅባቱ ብዙ ነው፡፡ እንደ ዘንባባ ዝንጣፊም ቁመቱ ረጅም ነው፡፡ እንደ ወይንም ፍሬው የበዛና የጣፈጠ ነው፡፡

ከእርሱም ከትንሣኤ በኋላ በሉ፡፡ እግዚአብሔር ቸር እንደሆነ ቀምሳችሁ ዕወቁት፡፡ ወንድሞች ሆይ በዚቺ ዕለት በዚህ ዕፅ ምክንያት አይሁድ እንደ አፈሩ ምእመናን ደግሞ እግዚአብሔርን እንዳመሰገኑት አስተውሉ። በመንፈስ ቅዱስ ሀብት የተነገረውን የነቢዩ የዳዊትን ትንቢት ስሙ፡፡ በፈሳሽ አጠገብ እንደተተከለች ዕንጨት ፍሬዋን በየጊዜው እንደምትሰጥ ቅጠሎቿም እንደማይረግፉ ነው አለ፡፡ ከውኃ ዳር የተተከለች ይህቺ ዕፅ የሰጠችው ፍሬ ምንድን ነው? ፍሬ የተባሉትስ እነዚህ በከበረች ጥምቀት የተጠመቁት ናቸው፡፡

በየጊዜው ያለውም ከክርስቶስ ጋር በመስቀል በተሰቀለ ጊዜ የተገለጸው የፈያታዊ ዘየማን ሃይማኖት ነው፡፡ ጌታም እውነት እውነት እልሃለሁ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ አለው፡፡ ቅጠሎቿ አይረግፉም ያለውም በጸናች ሃይማኖት የበቀሉ ሕዝበ ክርስቲያን ናቸው፡፡

ወንድሞች ሆይ እናንተ ሁላችሁ በሰማይ እንዳሉ ወፎች ከዚች ዕፅ በታች እንደ ሆናችሁ አስቡ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ በፈቃዱ ታሟልና፡፡ በንጉሥ ራስ እንዳለ የመመኪያ ዘውድ እና የጦር ዕቃ ችንካሮችን ታገሠ፡፡ ጌታ ሞትን ወደ እርሱ ይመጣ ዘንድ በፈቃዱ ባዘዘው ጊዜ ደቀመዛሙርቱን እውነት እውነት እላችኋለሁ በዚች ሌሊት ሁላችሁ ትክዱኛላችሁ:: እረኛውን እመታለሁ፤ መንጎችም ይበተናሉ፤ ተብሎ በነቢይ ተነግሯልና አላቸው፡፡.....

ይቀጥላል...

(ድርሳነ ሠለስቱ ሊቃውንት በመምህር ቃለጽድቅ ሕግነህ የተተረጎመ ገጽ 153-179)

ድርሳን በእንተ ሕማማቲሁ ለክርስቶስ


...ደቀመዛሙርቱ ይህን በሰሙ ጊዜ ፈጽመው አዘኑ፡፡ እነርሱ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ሞቱን አላመኑም ነበርና ይህን አደነቁ፡፡ በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በሐሳቡ በመንፈሳዊ ቅናት ተናደደ፡፡ ጌታ ሆይ ሁሉም ደቀመዛሙርት ቢክዱህ እኔ ግን አልክድህም፡፡ እንደ እነርሱ አድርገህ አትቁጠረኝ፡፡ እኔንስ ከደቀመዛሙርት ሁሉ አብልጨ እንደምወድህ አንተ ታውቅ የለምን? በመርከብ ላይ በአንድነት ተቀምጠን ሳለ በውኃው ላይ ስትሂድ እኔ ብቻዬን ደፍሬ ወደ ባሕሩ ገባሁ ወደ አንተም መጣሁ፡፡ ያንጊዜ እንደወደድኩህ አሁንም እንደ ባዕድ አልክድሕም፡፡ ከአንተ ጋር እሞታለሁ በእኔ ላይም ምንም ምን አመፃም አልተገኘብኝም፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መልሶ እንዲህ አለው:: ጴጥሮስ ሆይ በራስህ አትመካ፡፡ ወደ ባሕር በገባህ ጊዜም አላመንከኝም፡፡ በዚህም ምክንያት ወደ ባሕርልትሰጥም ወደደህ፡፡ እኔ ግን ይቅር አልሁህ፡፡ እጄን ዘርግቼም አነሣሁህ፡፡

ጴጥሮስ ሆይ አንተ አብሬህ እሞታለሁ ትላለህ፡፡ ነገርግን አብረኸኝ አትሞትም፡፡ ይልቁንም ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፡፡ ከደቀመዛሙርቶቼ ያንተን ያክል የሚክደኝ የለም:: አሁንም የምነግርህን ምልክት አስተውል፡፡ ሁሉንም ከመሆኑ በፊት ማወቅ የሚችል ሥልጣንም እንዳለኝ ዕወቅ፡፡ እውነት እውነት እልሃለሁ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ፡፡

ጌታችን ይህን ሲለው የአራት ቤት ጭፍሮች ሾተልና ጎመድ ይዘው ሊይዙት መጡ፡፡ ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢም ወሰዱት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸው ቃል ይፈጸም ዘንድም በዚህ ጊዜ ደቀመዛሙርቱ በየራሳቸው ተበተኑ፡፡ ጴጥሮስ ግን ብቻውን ጌታ ኢየሱስን ይከተለው ነበር፡፡ ከጭፍሮች ጋራም ተቀመጠ፡፡ ወቅቱ ብርድ ነበርና እሳት አንድደው ይሞቁ ነበር፡፡

ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር አብሮ ይሞቅ ነበር። በዚያም ጊዜ አንዲት ሴት አገልጋይ ወደ እርሱ መጣች:: ወደ ጴጥሮስም ቀርባ ለተያዘው ለኢየሱስ ተማሪውና ወዳጁ ነህ አለችው፡፡ ጴጥሮስም ያቺን ሴት ይህንን ሰው አላውቀውም ከእኔ ራቂ፡፡ እኔስ ከደቀመዛሙርቱ ወገንም አይደለሁም ብሎ መለሰላት፡፡

ሴትዮዋም ጴጥሮስን ሐሰትን ተናገርህ በእውነት አንተ ከእርሱ ወገን ነህ፡፡ አነጋገርህም ያሳውቅብሃል፡፡ በፍቅርም ወደ እርሱ ትመለከታለህ በማለት መለሰችለት፡፡ ጴጥሮስ ግን ይህንን ሰው እንደማያውቀው ይክድና ይምል ጀመር፡፡ ጴጥሮስም አንቺ ሴት ስለምን ታስጨንቂኛለሽ? ሌላ ሰው መስዬሽ ይሆናል፡፡ ከደቀመዛሙርቱ ወገን ብሆን ኑሮስ ነፍሴን አድናት ዘንድ ከዚህ በሸሸሁ ነበር፡፡ እዚህም ባልቆምሁ ነበር፡፡ ይህ ቢሆንስ ከእርሱ ጋር በያዙኝ ነበር አላት፡፡

ያች ሴትም መልሳ ጴጥሮስን ልትሸነግለኝ አትችልም፡፡ በእውነት አንተ ከእርሱ ወገን ነህ አለችው፡፡ ያን ጊዜም ጴጥሮስ ብዙ ሕዝብ ከዚያች ሴት ጋር የሚነጋገረውን ቃሉን ይሰሙት ዘንድ ወደ እርሱ ሲመጡ ዐየ፡፡ እርሱም ራሱን እየወቀሰ ያንንም ሰው እንደማያወቀው እየማለ አንቺ ሴት ያለ በደሌ ስለምን ወደ መከራ ትስቢኛለሽ አላት፡፡......

ይቀጥላል...

(ድርሳነ ሠለስቱ ሊቃውንት በመምህር ቃለጽድቅ ሕግነህ የተተረጎመ ገጽ 153-179)
1

ድርሳን በእንተ ሕማማቲሁ ለክርስቶስ


....ጴጥሮስ ከዚች ሴት ጋር በሕዝብ ሁሉ ፊት እንደዚህ እያለ በተነጋገረ ጊዜ ጌታ ኢየሱስ አሩቅ ሆኖ ዐየው። በፍጥነትም ጴጥሮስ ሆይ ከጥቂጥ ጊዜ በፊት ከአንተ ጋር እሞታለሁ አልክድህም ስትል የነበርህ አንተ ራስ አልነበርክምን? በማለት ተናገረው፡፡

ጴጥሮስ ሆይ ድፍረትህ፤ የቃልህ ጽናትና የበዛው ፍቅርህ ወዴት አለ? የዚች የተናቀች አገልጋይ ነገሯ ከተሳለ ሰይፍ ይልቅ አስፈራህ፤ ሥጋህም ሳይቈስል ካድኸኝ፡፡ ጴጥሮስ ሆይ በሰው ፊት የሚያምነኝን እኔ በአባቴ ፊት አምነዋለሁ ያልሁትን ቃል አልሰማህምን? ጴጥሮስ ሆይ እኔ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እንደሆንሁ የተናገርህ አንተ አልነበርህምን? ጴጥሮስ ሆይ ፍጹም ደስታ በነበረ ጊዜ ታፈቅረኛለህ፡፡ ኀዘንና መከራን ባየህ ጊዜ ደግሞ ትጠላኛለህ፡፡

ጌታችን ጴጥሮስን እንዲህ እያለ ሲገሥጸው ያን ጊዜ ዶሮ ጮኸ፡፡ ጴጥሮስም በእርሱ ላይ የሆነውን ባሰበ ጊዜ ወደ ውጭ ወጥቶ መራራ ልቅሶን አለቀሰ፡፡ የክሕደቱን እድፍም በዕንባው አጠበ፡፡ የጴጥሮስ ዕንባው ወደ መጀመሪያ አነዋወሩ መለሰችው፡፡ ያን ጊዜም አይሁድ ጌታ ኢየሱስን ወስደው ሰቀሉት፡፡ ልብሱንም ተካፈሉት፡፡ ዕጣም ተጣጣሉበት፡፡ ይህም ልብሴን ለራሳቸው ተካፈሉት፤ ዕጣም ተጣጣሉበት፤ ያለው የነቢዩ የዳዊት ቃል ይደርስ ይፈጸም ዘንድ ሆነ፡፡

አይሁድም ጌታችንን ኢየሱስን ክርስቶስን በመስቀል ላይበሰቀሉት ጊዜ ስለ ሰቀሉት ሰዎች አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይህን ኃጢአት ይቅር በላቸው:: አባት ሆይ በፈቃዳቸው እጃቸውን በእኔ ላይ አልዘረጉምና ይህንን ኃጢአት ይቅር በላቸው፡፡ አባት ሆይ ይህንን በደል ተውላቸው፡፡ እነርሱ በቅናት ሰክረዋልና፡፡ አባት ሆይ ይህን ሁሉ እቀበል ዘንድ እኔ በፈቃዴ መጥቻለሁና ይህን ኃጢአት አጥፋላቸው እያለ ጸለየ፡፡

ይህ ሽፍታም በመስቀል ተሰቅሎ በነበረ ጊዜ አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ አለው፡፡ ደቀመዛሙርት ከብዙ ፍርሀት የተነሣ ከግርፋት ራሳቸውን ሠወሩ፤ በየራሳቸው ተበታተኑ። ይህ ሽፍታ ግን በመስቀል ተቸንክሮ ሳለ  ወደ ቃለ የሕይወት ቃልን የሚሰብክ ሐዋርያ ሆነ፡፡.....

ይቀጥላል...

(ድርሳነ ሠለስቱ ሊቃውንት በመምህር ቃለጽድቅ ሕግነህ የተተረጎመ ገጽ 153-179)
የሰሙነ ሕማማት ረቡዕ

ምክረ አይሁድ ይባላል፦

ምክንያቱም የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው ምክር ያጠናቀቁበት ቀን ነውና፡፡ በዚህ ምክራቸው ላይ በጣም ትልቅ ጭንቀት ነበር፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት ቀን የተቃረበ በመሆኑ ብዙው ሕዝብም በጌታችን ትምህርት የተማረኩ ተአምራቱንም የሚያደንቁ ስለ ነበር ሁከት እንዳይፈጠር ነው፡፡ በዚህ ጭንቀት ሳሉ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ በመካከላቸው በመገኘት የምክራቸው ተባባሪ ሆኖ ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል፡፡ (ማቴ. 26÷1-14፣ ማር. 14÷1-2፣ ሉቃ. 22÷1-6) የሐዲስ ኪዳን ካህናትና ምእመናን በዚሁ ዕለት በቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው መላ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔር አስገዝተው የሞት ፍርዱን በማሰብና በማልቀስ ሐዋርያት ከጌታችን መያዝ በኋላ በኀዘን በፍርሐት እንደነበሩ እያሰቡ መጻሕፍትን በማንበብ በጾም በጸሎትና በስግደት ተወስነው ይቆዩና ከአሥራ ሁለት ሰዓት በኋላ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡

የመልካም መዓዛ ቀንም ይባላል
ምክንያቱም ጌታችን በዚህ ዕለት በቤተ ስምዖን ዘለምጽ ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት (ባለሽቱዋ ማርያም) "ከእንግዲህ ወዲህ በኃጢአት ተበላሽቶ ይኖር የነበረውን ሕይወቴን እንደዚህ መልካም ሽቱ የሚያጣፍጥ ኃጢአትን ይቅር የሚል አምላክ መጣ" ስትል ዋጋው እጅግ በጣም ውድ የሆነ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ የሚያወጣ በአልባስጥሮስ ብልቃጥ የተሞላ ሽቱ ይዛ በመሔድ በጠጉሩ (በራሱ) ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባችው ረቡዕ የመዓዛ ቀን ይባላል፡፡

የእንባ ቀንም ይባላል
ማርያም እንተ እፍረት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በእንባዋ እግሩን አጥባዋለችና በጠጉሯም በእንባዋ ያጠበችውን እግሩን አብሳዋለችና። (ማቴ. 26÷6-13፣ ማር. 14÷9፣ ዮሐ. 12÷8) ኃጢአትን በማሰብ ማልቀስና ራስን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ማቅረብን ከምታስተምረን ማርያም እንተ እፍረት እንባን ለንስሐ ሕይወት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
👏1

ድርሳን በእንተ ሕማማቲሁ ለክርስቶስ


.....በግራ የተሰቀለውን ሽፍታም አንተ እግዚአብሔርን አትፈራውምን ለእኛስ ይህ በእኛ ላይ የመጣው ፍርድ ይገባናል፡፡ ይህ ጻድቅ ግን ምንም ምን የሠራው ክፉ ነገር የለም አለው፡፡ ይህ ድንቅ ታላቅ ነው:: ወንበዴው እጅግ ጥበበኛን ሆኗልና፡፡ ነፍሰ ገዳዩም ከፍጹም ኃጢአቱ ድኖ በአንዲት ቃል ባለ ሃይማኖት ሆኗልና፡፡

በግራ የተሰቀለውን ወንበዴ ባለንጀራውን እንዲህ ብሎ አሳፈረው፡፡ አንተ ሰነፍ ሆይ የእግዚአብሔር ልጅ ባይሆን ኑሮስ ፀሐይ ባልጨለመ ነበር፡፡ ከኃጢአት ሁሉ ንጹሕ ባይሆን ኑሮስ የቤተ ምኵራቡ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ክፍል ባልተቀደደም ነበር፡፡ የሰማይና የምድር ጌታ ባይሆን ኑሮስ መቃብራት ባልተከፈቱም ነበር፡፡

አንተ ወንበዴ ሆይ አሁን እንኳ እስኪ ከስሕተትህ ተመለስ፡፡ ለመሞት ተቃርበሃል ጊዜህም ደርሷልና፡፡ ነፋሳት በታላቅ ኃይል እንዴት እንደሚነፍሱ አታይምን? የሰማያትና የምድር ኃይላት እንዴት እንደሚርዱ አትመለከትምን? የፀሐይስ ብርሃኑ እንዴት እንደ ጠፋ አታይምን? ከዋክብትስ እንዴት እንደ ወደቁ አትመለከትምን? ባሕርንስ እንዴት እንደታወከች አትመለከታትምን?

አንተ ወንበዴ ሆይ ጌታ አባት ሆይ ይህንን ኃጢአት ይቅር በላቸው ብሎ በታላቅ ቃል ባይናገር ኑሮስ ከዐይን ጥቅሻ ፈጥነው በጠፉ ነበር። ወንበዴው ሆይ ዝም በል። ይህ ጻድቅ ምንም ምን ክፉ ሥራ አልሠራምና። ነገርግን አይሁድ በቅናት ሰቀሉት እንጂ፡፡ የቀኙ ሽፍታ በግራ ለተሰቀለው ሽፍታ እንደዚህ በማለ ተናገረ፡፡

ከዚህም በኋላ የቀኙ ሽፍታ ወደ ጌታ ኢየሱስ ተመልሶ አቤቱ ጌታዬ እና አምላኪየ ነፍሴን ከዚህ ከሓዲ ጋር አታጥፋት፡፡ ነገር ግን በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ እንጂ አለ፡፡ እነሆ አሁን በጌትነትህ ክብር የግርማህን ታላቅነት ዐይቻለሁ፡፡ አቤቱ አንተ ያልካደኝ ብፁዕ ነው ብለሃልና፡፡ እኔ ከጌትነትህ ኃይል የተነሣ ከተቀደደው ከቤተ ምኵራቡ መጋረጃ በዕውቀት የተሻልሁ አይደለሁም፡፡....

ይቀጥላል...

(ድርሳነ ሠለስቱ ሊቃውንት በመምህር ቃለጽድቅ ሕግነህ የተተረጎመ ገጽ 153-179)

ድርሳን በእንተ ሕማማቲሁ ለክርስቶስ


....አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ፡፡ አቤቱ ከሓዲ፣ ነፍሰ ገዳይ፣ የረከስሁና ሥራህን የምጠላ የነበርሁ እኔን ወንበዴውን አስበኝ፡፡ አቤቱ ከሕዝቦችህ መካከል ብዙዎችን ያጠፋሁ እኔን አስበኝ፡፡ ብዙ ሰዎችን በሥውርገድዬ ያለ ልቅሶ የቀበርሁ ነኝና አቤቱ እኔን በቸርነትህ አስበኝ፡፡ አቤቱ በደለኛ የሆንሁ እኔን ኃጢአተኛውን አስበኝ፡፡ አቤቱ በቸርነትህና በምሕረትህ አስበኝ፡፡ አቤቱ በፍርድህ ዐደባባይ አስበኝ፡፡

አቤቱ የቀደመ በደሌን አታስብብኝ፡፡ አንተ ከነውርና ከኃጢአት ሁሉ ንጹሕ የሆንህ ጌታ ነህና፡፡ አቤቱ በሥጋህ በተቀበልኸው ሕማምህ እንድሳተፍ እዳደረግኸኝ ሁሉ እንዲሁም የመንግሥት ወራሽ አድርገኝ፡፡ አቤቱ ግሩም ንጉሥ ሆይ በጌትነትህ ዙፋን ለፍርድ በተቀመጥህ ጊዜ አስበኝ፡፡ አቤቱ የሰማይ ሠራዊት በፊትህ በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ በሚቆሙባት ሰዓት አስበኝ፡፡

አቤቱ መቃብራት ተከፍተው ነፍሳት ሁሉ ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ሰው በሚነሡበት በዚያ ጊዜ አስበኝ፡፡ አቤቱ ጻድቃንና ኃጥአን በፍርድህ ዐደባባይ በታላቅ ፍርሀት በሚቆሙበት ዕለት አስበኝ፡፡ አቤቱ በሰማያት ባለችው የሰርግ ቤት አስበኝ፡፡ አንተ ሰማያዊ ሙሽራ ነህና፡፡ አቤቱ ቸሩ ሆይ እኔን ሽፍታውን ወደ አንተ እንዲያመጡኝ፣ በአንተም እንዳምን መላእክትን ትነግራቸው ዘንድ እለምንሃለሁ፤ እማልድሃለሁ፡፡

ያንጊዜም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለሰለት፡፡ በቀኙ የተሰቀለውንም እውነተኛው ሆይ ታላቅ አደርግሃለሁ፡፡ አንተ ዛሬ በእኔ አመንህ፤ እኔም በመንግሥቴ ስመጣ አስብሃለሁ አለው፡፡ አንተ በሕማሜ ተካፍለሃልና ልመናህን አልተውም ቸልም አልልም፡፡ እውነተኛው ምስክር ሆይ በእውነት ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ፡፡

ዳግመኛም የሰውን ጸሎቱን የምሰማ እኔ ነኝ። የበደልና የኃጢአት ሥርየትን የምሰጥ እኔ ነኝ፡፡ ሁሉን የማዝዝ የአዘዝሁት ሁሉም በሰማይም በምድርም የሚሆንልኝ እኔ ነኝ፡፡ በውኑ ይህ እንጨት ፈቃዴን ይከለክለኛልን? በውኑ ይህስ መስቀል ትእዛዜን ይሽራልን? በውኑ ይህ ሕማም ወደ መለኮቴ ይቀርብ ዘንድስ ይችላልን? እንደዚህ ይሆን ዘንድ አይችልም፡፡ ነገር ግን የችንካሮች ሕማም ለሥጋዬ ብቻ ነው እንጂ ወደማይመረመረው መለኮታዊ ኃይሌ ይቀርብ ዘንድ አይችልም አለው፡፡

በመስቀል ላይ እንዳለሁ የፈለግኸውን ሁሉ እሠጥህ ዘንድ ሥልጣን አለኝ፡፡ እውነተኛው ሆይ እነሆ አሁን ልመናህን ሰማሁ፤ መሻትህንም እፈጽምልሃለሁ፡፡ በውንብድና ኑረህ ነበር፤ ዛሬ ግን ጻድቅ አደርግሃለሁ፡፡ ለአንተ ያደረግሁትንም ዳግመኛም በእኔ ለአመኑ ሁሉ አደርግላቸዋለሁ፡፡....

ይቀጥላል...

(ድርሳነ ሠለስቱ ሊቃውንት በመምህር ቃለጽድቅ ሕግነህ የተተረጎመ ገጽ 153-179)
፮ (መጨረሻ)
ድርሳን በእንተ ሕማማቲሁ ለክርስቶስ


.....ፈያታዊ ሆይ አባትህ አዳም ትቷት ወደ ወጣ ወደ ጌታህ ደስታ ወደ ገነት ግባ፡፡ ፈያታዊ ሆይ ወደ ገነት ግባ፡፡ ከሚትጠብቃት የእሳት ሰይፍ የተነሣም አትፍራ፡፡ በስሜ የሚያምነውን ሁሉ ከእንግዲህ በኋላ አታቃጥለውምና፡፡ ፈያታዊ ሆይ በአሸናፊነት ኃይል ወደ ገነት ግባ፡፡

በመስቀሉ ደስታ ፈያታዊው ዳነ። መስቀል ኃጥአንን ወደ ጽድቅ መለሰ፡፡ አይሁድን ግን አሳፈራቸው፡፡ እነሆ ዛሬ ታላቅ ድንቅ ነገር ሆነ፡፡ ወንበዴው ድኅነትን አግኝቶ ወደ ገነት ገብቷልና፡፡ ደቀመዝሙር የነበረው ይሁዳ ደግሞ በጥፋቱ ወደ ሲኦል ገባ፡፡ በውኑ ፈያታዊ ዘየማን ጌታ ኢየሱስን በባሕሩ ላይ በየብስ ላይ እንደሚራመድ ሰው ሲሄድ ዐይቶታልን? ወይንስ ጌታ ባርያውን እንደሚያዝዘው ባሕርንና ነፋሳትን ሲገሥጽ ዐይቷልን?

በውኑ ፈያታዊው ክርስቶስ እጁን ሲዘረጋ እና ሙታንን ፈጥኖ ሲያስነሣ ዐይቷልን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ጉንጮችን በጥፊ ሲመታ ከማየት በቀር ከተአምራት ወገን ምንም ምን አላየም፡፡ ዳግመኛም በላዩ ላይ ሲሳለቁበት፣ ጎኑን በጦር ሲወጉት፣ ራሱንም በዘንግ ሲመቱት እና ሆምጣጣ ሲያጠጡት ዐየ እንጂ፡፡ ይህንንም ሁሉ ተመልክቶ በእርሱ አመነ፡፡ ጌታችንም ፈጥኖ ጸሎቱን ሰማው፡፡ ልመናውንም ተቀበለው፡፡

የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ እነሆ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ወደ ዓለም እንደመጣ ከኃጢአት ቀንበርም ነፃ ያወጣን ዘንድ ስለ እኛ እንደ ታመመ ከእንግዲህ ዕወቁ፡፡ ነቢዩ ኢሳያይስ “እንደ በግ ሊታረድ መጣ" ያለውን ስሙ፡፡ ዳግመኛም እንደሚሸልቱት በግ፤ እርሱ ግን በሸላቾቹ ፊት በሕማሙ አፉን አልከፈተም፡፡

ይህንንም በግ አይሁድ፣ ሊቃውንቶቻቸውና የሕግ መምህሮቻቸው አረዱት። እኛ ግን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙንም በላን ጠጣን፡፡ ነፍሳችንም ዳነች፡፡ ልቡናችንን አበራልን፡፡ ከኃጢአታችን አነፃን፡፡ በከበረች ጥምቀትም ለመንገሥተ ሰማያት የበቃን አደረገን፡፡ ኖኅን እና ልጆቹን ከጥፋት ውኃ ያዳናቸው በግ ይህ ነው፡፡ ዓለምንም ሁሉ ያዳነው በግ ይህ ነው፡፡ በኦሪት እንደ ተጻፈው ምድራዊው በግ ለእስራኤል ትምክሕታቸው ሆነ፡፡ ሰማያዊው በግ ክርስቶስ የክርስቲያኖች መመኪያ ሆነ።

አይሁድ አስቀድመው በጉን ያርዱታል የቤታቸውንም ደጃፍ ደሙን ይቀቡታል፡፡ እኛም አማናዊውን በግ እንሠዋለን ነፍስና ሥጋችንንም ቀደሰን፡፡ አይሁድ የአባቶቻቸውን የበዓል መታሰቢያ ያከብራሉ፡፡ እኛ ግን የጌታችን የመድኃኒታች የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ ልዩ የምትሆን የፋሲካን በዓል እናከብራለን፡፡

አይሁድ ከእውነት መንገድ ሳቱ፡፡ ዘመናቸውም በከንቱ አለፈ፡፡ ከኢየሩሳሌም ውጭ በዓል አያድርጉ ተብሏልና፡፡ እኛ ግን በምድር ሁሉ የፋሲካን በዓል በፍጹም ደስታ እናደርጋለን፡፡ ነቢይ ምድር በመላዋ ለእግዚአብሔር ናት፡፡ ዓለምና በውስጧ ያለ ሁሉ የእርሱ ነው ያለውን ስሙ:: አይሁድ የኤርትራን ባሕር ተሸገሩ፡፡ ትእዛዙንም በመሻር እግዚአብሔርን አስቈጡት፡፡ እኛ ግን ልዩ በምትሆን በጥምቀት ከኃጢአታችን ነጻን፡፡

ነቢዩ ኃጢአታቸው የተተወላቸው ንዑዳን ክቡራን ናቸው፡፡ እግዚአብሔር በደላቸውን የማይቈጥርባቸው ንዑዳን ክቡራን ናቸው በማለት የተናገረውን የደስታ ቃል ስሙ፡፡ አይሁድ ከሥጋ ሕግ ተወልደዋልና ሥጋዊ የሆነ ሀብት ተሰጣቸው፡፡ እኛ ግን ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ተወለድን፡፡ ስለዚህም መንፈሳዊ ሀብት ተሠጠን፡፡

እነርሱን የእሳት ዐምድ መራቸው፡፡ እኛን ግን የጽድቅ ፀሐይ መራን፡፡ ለእነርሱ ሙሴ አላቸው፡፡ ለእኛ ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አለን፡፡ ለእነርሱ የድንጋይ ጽላት አላቸው፡፡ ለእኛ ግን ቅዱስ ወንጌል አለን፡፡ ለእነርሱ የወርቅ መሶብ አላቸው፡፡ ለእኛ ግን የተቀደሰው ታቦት አለን፡፡ ለእነርሱ መብራት አላቸው፡፡ ለእኛ ግን የብርሃናት ሁሉ ጌታ አለን፡፡ ለእነርሱ ጸናጽል አላቸው፡፡ ለእኛ ግን የከበሩ ቅዱሳን ሰማዕታት አሉን፡፡

ለእነርሱ አበባን ያበበች የአሮን በትር አለቻቸው፡፡ ለእኛ ግን የሕይወት ፍሬን ያፈራ ክቡር መስቀል አለን፡፡ ይህ የሕይወት ፍሬም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

ለእርሱ ክብር ምስጋናና አምልኮት ይገባል፡፡ ዛሬም ዘወትርም እስከ ዘለዓለሙ ድረስ አሜን፡፡

(ድርሳነ ሠለስቱ ሊቃውንት በመምህር ቃለጽድቅ ሕግነህ የተተረጎመ ገጽ 153-179)
ዐቢይ ጦም ሊጠናቀቅ ሲል የተሰጠ ምዕዳን

እነሆ የተቀደሰውን ወርኃ ጦም ወደ ማጠናቀቅ ተቃርበናል፤ የጦሙን ጉዞ ወደ ማገባደድ ደርሰናል፤ እግዚአብሔር ረድቶንም ወደ ወደቡ ልንደርስ ተጠግተናል፡፡

ነገር ግን እንዲህ በመኾኑ ልል ዘሊላን ልንኾን አይገባንም፤ ይህን ምክንያት አድርገን ከከዚህ በፊቱ ላይ ትጋታችንንና ንቃታችንን እጅጉን እንጨምር እንጂ፡፡

የመርከብ አለቆች ብዙ ባሕረኞችንና ዕቃ ጭነው ረጅም የባሕር ላይ ጉዞ ካደረጉ በኋላ ወደ ወደቡ ሊደርሱ ሲሉ መርከባቸው ከዓለት ጋር እንዳትጋጭና ድካማቸውን ኹሉ ከንቱ ላለማድረግ ከፍ ያለ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ ሯጮችም እንደዚሁ ወደ መጨረሻው መስመር ሊቃረቡ ሲሉ ኃይላቸውን ኹሉ አሟጥጠው ተጠቅመው ሽልማቱን ለመውሰድ ይጥራሉ፡፡ ትግለኞችም ምንም እንኳን ስፍር ቊጥር የሌለው ቡጢ ቢደርስባቸውም፣ ምንም እንኳን ብዙ ጊዜ ተመትተው ቢወድቁም ሽል ማቱን ይወስዱ ዘንድ የመጨረሻውን ዙር ትግል እጅግ ከፍ ባለ ጉልበ ት ይታገላሉ፡፡

ስለዚህ የመርከብ አለቆች፣ ሯጮችና ትግለኞች ድል ወደ ማድረግ ሲቃረቡ እጅግ ከፍ ያለ ትጋትና ጥንቃቄ ኃይልም እንደሚጠቀሙ፥ እኛም ወደ ታላቁ ሳምንት ደርሰናልና እግዚአብሔር ስለረዳን እያመሰገንን ጸሎታችንን፣ ተአምኖ ኃጢአታችንን፣ በጎ ምግባራችንን፣ ምጽዋ ታችንን፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለን መስተጋብራችንን፣ ራስን የመግዛት ጠባያችንን፣ እንደዚሁም ይህን የመሰለው ሌላው ምግባራችንን ከፍ ባለ ትጋትና ጥንቃቄ ልንፈጽም ይገባናል፡፡ እነዚህን በጎ በጎ ነገሮችን ወደ ጌታ ቀን (ወደ በዓለ ትንሣኤ) የምንደርስ ከኾነ ከጌታችን ዘንድ ባለሟልነትን እናገኛለን፤ ከማዕዱ ዘንድ መሳተፍ ይቻለናል፡፡ 

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አምስቱ የንስሐ መንገዶች፣ ገጽ 148)
የሰሙነ ህማማት ሐሙስ

ጸሎተ ሐሙስ

በቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ስያሜዎች ያሏቸው በርካታ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ዕለት ነውና ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፡፡  የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ፣ መሆኑን ለመግለጥና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ነውና ጸሎተ ሐሙስ ተባለ፡፡ (ማቴ. 26፥36-46 ዮሐ.17)

ሕፅበተ ሐሙስ ይባላል፡-
ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀመዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ይህም የሚያሳየው የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳት፣ የደብር አስተዳዳሪዎች፤ «በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ እኛም የአንተን አርአያ አንዘነጋም የሌላውን እግር እናጥባለን፤» ሲሉ በቤተ ክርስቲያን የተገኙትን ምእመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡

የምስጢር ቀን ይባላል፡-
ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷልና፡፡ ይኸውም «ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ ብሉ» ጽዋውንም አንስቶ አመሰገነ «ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱም ጠጡ» በማለት፤ እኛ ከእርሱ ጋር፣ እርሱ ከእኛ ጋር አንድ የምንሆንበትን ምስጢር ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ፣ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ሥያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል ይዘጋጃል፡፡

የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡-
ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ «ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱ ጠጡ» በማለቱ ይታወቃል (ሉቃ. 22፥20) ኪዳን ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለሆነ የሐዲስ ኪዳስ ሐሙስ ተባለ፡፡

የነጻነት ሐሙስ ይባላል፡-
ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ፣ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ጌታችን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር «ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም ባርያ ጌታዉ የሚያደርገውን አያውቅምና ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ» በማለት (ዮሐ. 15፥15)፤ ከባርነት የወጣንበት ልጆች የተባልንበትን ቀን የምናስብበት በመሆኑ ሊቃውንቱ የነጻነት ሐሙስ አሉት፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያንም ከኃጢአት ባርነት ርቆ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን መምራት ይኖርባታል፡፡ ባሮች አልላችሁም ተብለናልና፡፡
1
Forwarded from Quality button
ትስቡጣ ማለት ገዢ ማለት ነው።
"ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።"

ኢሳይያስ 53፥7
የክርስቶስ 13ቱ ሕማማት👇
ነአምን media
የክርስቶስ 13ቱ ሕማማት👇
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐሥራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል በዕለተ ዓርብ ተቀብሏል እነዚህም👇

1) ተአስሮተ ድኅር ( የኋሊት መታሰር )
👉 የዮሐንስ ወንጌል ( ም 18 ÷ 12 )
👉 ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ ( ም  1 ÷ 46 )
👉 ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ብንያሚ ( ም 89 ÷ 15 )


2) ተጸፍዖ መልታሕት ( ፊትን በጥፊ መመታት )
👉 የማቴዎስ ወንጌል ( ም 26 ÷ 67 )
👉 የማርቆስ ወንጌል ( ም 14 ÷ 65 )
👉 የሉቃስ ወንጌል ( ም 22 ÷ 64 )
👉 የዮሐንስ ወንጌል ( ም 18 ÷ 22 )

👉 ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወርቅ ( ም 1 ÷ 49 )
👉 ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ ( ም 103 ÷ 14 )
👉 ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዘዮሐንስ ( ም  113 ÷ 9 )
👉 ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዘዮሐንስ ( ም 114 ÷ 25 )
👉 ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤጲፋንዮስ ( ም 55 ÷ 35 )
👉 ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አትናቴዎስ ( ም 30 ÷ 37 )
👉 ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቴዎዶስዮስ ( ም 82 ÷ 21-23 )

3) ወሪቀ ምራቅ (ምራቅ መተፋት)
👉 ትንቢተ ኢሳይያስ ( ም 50 ÷ 6 )
👉 የማቴዎስ ወንጌል ( ም 26 ÷ 67 )
👉 የማቴዎስ ወንጌል ( ም 27 ÷ 30 )
👉 የማርቆስ ወንጌል ( ም 10 ÷ 34 )
👉 የማርቆስ ወንጌል ( ም 14 ÷ 65 )
👉 የማርቆስ ወንጌል ( ም 15 ÷ 19 )
👉 ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ሄሬኔዎስ ( ም 7 ÷ 25 )

👉 ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ዮሐንስ ( ም 103 ÷ 14 )
👉 ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤጲፋንዮስ ( ም 55 ÷ 35 )
👉 ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አትናቴዎስ ( ም 30 ÷ 37 )
👉 ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቴዎዶስዮስ ( ም 82 ÷ 21-23 )

4) ተኰርዖተ ርዕስ (ራስ በዘንግ መመታት)
👉 ትንቢተ ኢሳይያስ ( ም 1 ÷ 5 )
👉 የማቴዎስ ወንጌል ( ም 27 ÷ 30 )
👉 የማርቆስ ወንጌል ( ም 15 ÷ 19 )


5) ተቀሥፎ ዘባን (ጀርባን መገረፍ)
👉 ትንቢተ ኢሳይያስ ( ም 50 ÷ 6 )
👉 የማቴዎስ ወንጌል ( ም 20 ÷ 19 )
👉 የማቴዎስ ወንጌል ( ም 27 ÷ 26 )
👉 የሉቃስ ወንጌል ( ም 23 ÷ 16 )
👉 የዮሐንስ ወንጌል ( ም 19 ÷ 1 )
👉 1ኛ የጴጥሮስ መልዕክት ( ም 2 ÷ 24 )
👉 ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ኤጲፋንዮስ ( ም 55 ÷ 35 )
👉 ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አትናቴዎስ ( ም 30 ÷ 37 )


6) አክሊለ ሦክ ( የእሾህ አክሊል መድፋት )
👉 የማቴዎስ ወንጌል ( ም 27 ÷ 29 )
👉 የዮሐንስ ወንጌል ( ም 19 ÷ 2 - 5 )
👉 ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ቴዎዶስዮስ ( ም 82 ÷ 21 )


7) ጸዊረ መስቀል ( መስቀል መሸከም )
👉 የሉቃስ ወንጌል ( ም 23 ÷ 26 )
👉 የዮሐንስ ወንጌል ( ም 19 ÷ 17 )
👉 መጽሐፈ ምስጢር ( ም 14 ÷ 27 )


8) ሰትየ ሐሞት (አሞት / ሆምጣጤ መጠጣት )
👉 መዝሙረ ዳዊት ( ም 68 ÷ 21 )
👉 የማቴዎስ ወንጌል ( ም 27 ÷ 34 - 48 )
👉 የማርቆስ ወንጌል ( ም 15 ÷ 36 )
👉 የሉቃስ ወንጌል ( ም 23 ÷ 36 )
👉 የዮሐንስ ወንጌል ( ም 19 ÷ 28 - 30 )


የተቀሩት አምስቱ ቅንዋተ መስቀል ናቸው። ስማቸውም የዕብራይስጥ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አራቱ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈ ምስጢር በተሰኘው መጽሐፋቸው ጠቅሰዋቸዋል ( መጽሐፈ ምስጢር 14 ÷ 27 ) እነርሱም 👇

👉 ሳዶር | የመጀመሪያ :- ሁለቱን መስቀል በማያያዝ የተቸነከረ ነው።

👉 አላዶር | ሁለተኛ :- ቀኝ እጁን የተቸነከረበት ችንካር ነው።

👉 ዳናት | ሦስተኛ :- ግራ እጁን የተቸነከረበት ችንካር ነው።

👉 አዴራ | አራተኛ :- እግሮቹን አጣምረው የቸነከሩበት ችንካር ነው።

👉 ሮዳስ | አምስተኛ :- ኢናንአ (ኢየሱስ ናዝራዊ ንጉሠ አይሁድ) የሚለውን ጲላጦስ በዕብራይስጥ ፣ በሮማይስጥ ፣ በግሪክ ተፅፎ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራስ በላይ የተሰቀለበት ችንካር ነው።
Forwarded from 💠ኢዮራም ፕሮሞሽን💠
ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ ግራ ጎኑን የወጋው ወታደር ማን ነው ⁉️
የምትወዱት ሰዎች ፈጽሞ አልቅሱለት፡፡

ወየው ወየው ወየው አማኑኤል አምላካችን፡፡

ወየው ወየው ወየው መድኃኒታችን ኢየሱስ፡፡

ወየው ወየው ወየው መድኃኒታችን ኢየሱስ፡፡

ወየው ወየው ወየው ንጉሣችን ክርስቶስ፡፡

ወየው ወየው ወየው ጻድቁን ከዕንጨት አወረዱት፡፡

ሥጋውንም ለመገነዝ ከርቤ የሚባል የጣፈጠ ሽቱንና ንጹሕ በፍታን አመጡ፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት የማይለወጥ፡፡

ከድንግል ማርያም የተወለደ አቤቱ ይቅር በለን፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ የማይሞት የማይለወጥ በዮርዳኖስ የተጠመቀ በመስቀልም የተሰቀለ አቤቱ ይቅር በለን፡፡"

#ቅዳሴ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
1
ቄጠማ በግንባራችን ለምን እናስራለን ?

ቄጠማ የምሥራች ምልክት ነው ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖኅ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማቆራኘት ነው ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ኾነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል
(ዘፍ. ፱፥፩-፳፱)

ቄጠማ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደ ኾነ ዅሉ

አሁንም ‹‹በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ፤›› ስትል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡

ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የኾነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ዅሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን፤ ከዋዕየ ሲኦል (የሲኦል ቃጠሎ) ወደ ጥንተ ማኅደራቸው ገነት መመለሳቸውን በዚህ አኳኋን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡

                           መ/ር ነቢዩ ኤልያስ

https://t.me/neamn_media