መዝገበ ቅዱሳን
24.2K subscribers
1.97K photos
9 videos
6 files
26 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
#አባ_አንበስ_ኢትዮዽያዊ
ከቅድስናው የተነሣ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሰው በአንበሳ ላይ ተጭኖ ነው፡፡ ተአምራትን በማድረግና ወንጌልን በማስተማር በጾም ጸሎት አብዝቶ የደከመ ሲሆን ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሌት ተቀን በጸሎት ይተጋ የነበረ ታላቅ አባት ነው፡፡ አቡነ አንበስ ትውልዱ ትግራይ አድዋ በእንጭጮ ወረዳ ነው፡፡ በስሙ ትግራይ አድዋ "እንጭጮ አቡነ አንበስ ገዳም" እና በትግራይ ሽሬ ሁለት ትላልቅ ገዳማት አሉት፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድርሰቱ ደጋግሞ የጠቀሳቸው ሲሆን የያሬድንም የድርሰቱን የአቋቋም ሥርዓት ያመጡት አቡነ አንበስ ናቸው፡፡

አቡነ አንበስ በአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና በአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ጊዜ የነበሩ ሲሆን እሳቸውንም አንበሶች ያገለግሏቸው ነበር፡፡ ጻድቁ አቡነ አንበስ ከአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጋር የተገናኘ ትልቅ ታሪክ አላቸው፡፡ የላዕላይ ግብጹ አባ ብንያም፣ በአቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ እና የሐዘሎው አቡነ አንበስ እነዚህ 3ቱ ቅዱሳን ከየአሉበት በአንበሳቸው ተጭነው ዝቋላ አቡዬ ዘንድ እንደደረሱ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንበሶች የ3ቱንም ቅዱሳን አንበሶች ዋጡዋቸው፣ አቡዬም በዚህ አዝነው ከበዓታቸው ወጥተው አንበሶቻቸውን ‹ትፉ› ብለው የበሉአቸውን አንበሶቻቸውን አስተፍተዋቸው ለ3ቱም ቅዱሳን የተበሉባቸውን አንበሶቻቸውን መልሰውላቸዋል፡፡ ይኸውም የሆነው እኝዲህ ነው፡- አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በዝቋላ 7ቱ ሊቃነ መላእክት እየረዷቸው 70 ሺህ እልፍ አጋንንትን በእሳት ሰይፍ ፈጅተው ካጠፏቸው በኋላ ወደ ምድረ ከብድ ተመለሱ፡፡ ከዚህም በኀላ መንፈስ ቅዱስ የጠራቸው ሦስቱ ቅዱሳን አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ አቡነ አንበስ ዘሐዘሎ እና የላዕላይ ግብጹ አቡነ ብንያም በአንበሶቻቸው ሆነው ወደ ጻድቁ አባት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዘንድ ምድረ ከብድ ገዳም መጡ፡፡

አባታችን ግን ስለተሰወራቸው እስከ 7 ቀን ድረስ በምህላ ሰነበቱ፡፡ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንበሶችም መጥተው የ3ቱን ቅዱሳን አንበሶች በልተውባቸው ተሰወሩ፡፡ 3ቱም ቅዱሳን ፈጽመው ደነገጡ፡፡ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስም የቅዱሳኑን ሀዘንና ድንጋጤ ተመልክተው በታላቅና በሚያስፈራ ግርማ ሆነው ስልሳ ነብሮችንና ስልሳ አንበሶችን አስከትለው ተገለጡላቸው፡፡ ቅዱሳኑም ከአቡነ ገብረ መንፈስቅዱስ ግርማ የተነሣ ስለደነገጡ እንዳይፈሩም አረጋጉአቸው፡፡

ከዚህም በኃላ አባታችን "በምን ምክንያት ወደዚህ ገዳም ወደ እኔ መጣችሁ?" አሏቸው፡፡ ሦስቱ ቅዱሳን እንዲህ አሉ፡- "ጸሎትህ ቅድስት እንደሆነች ባወቅን ጊዜ ወደ አንተ መጣን፤ አንተ በሁሉ ርእሰ ባሕታውያን ነህና የእግዚአብሔርን ሥራ ትነግረን ዘንድ መጣን፤ ባላገኘንህም ጊዜ እስከ 7ቀን አለቀስን" አሉት፡፡

ዳግመኛም "አንበሶችህ መጥተው አንበሶቻችንን ደማቸውን ጠጡ ቆዳቸውንም በጥፍራቸው በጣጠሱ" ብለው ነገሯቸው፡፡ አባታችንም ይህንን ሲሰሙ አንበሶቻቸውን "እስከ ዕለቴ ሞቴ ድረስ በእግሬ ከረገጥኩት ትቢያ በቀር ምንም እንዳትበሉ ታዛችሁ የለምን? እግዚአብሔር ያላዘዛችሁትን ለምን በላችሁ? በሉ አሁንም የበላችሁትን ትፉ" አላቸው፡፡ እነዚያም አንበሶች አፋቸውን ከፍተው አንዳች ሳያስቀሩ አጥንታቸውን ሥጋቸውን በሙሉ ተፉአቸው፡፡ ጻዲቁ አባታችንም ወደ ምሥራቅ ተሠልሰው እግዚአብሔርን ከለመኑ በኃላ በአንበሶቹ ሥጋ ላይ ባረኩና "በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ተነሡ" አሏቸው፡፡ አንበሶቹም እንደ ዐይን ፈጥነው ተነሥተው እንደ ቀድሞው ሆኑ፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ለዘላለሙ ከእኛ ጋር ትኑር አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም እና #ከገድላት_አንደበት)
@petroswepawulos
@petroswepawulos
@petroswepawulos
#መስከረም_6

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
መስከረም ስድስት በዚች ቀን ታላቅ ነቢይ የአሞጽ ልጅ #ቅዱስ_ኢሳይያስ አረፈ፣ #የአቡነ_ሳሙኤል_ዘዋልድባ ዐፅማቸው ከዋልድባ አብረንታንት ወደ ደብረ ዓባይ የፈለሰበት ዕለት ነው፣ #ቅድስት_ሰብልትንያ በዲዮቀልጥያኖስ ዘመን በሰማዕትነት ሞተች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ነቢዩ_ኢሳይያስ

መስከረም ስድስት በዚች ቀን ታላቅ ነቢይ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ አረፈ። ይህም ነቢይ ለይሁዳ በነገሡ በአምስቱ ነገሥታት ዘመን አስተማረ ትንቢትም ተናገረ እሊህም አዝያን ኢዮአታም አካዝ ሕዝቅያስና ምናሴ ናቸው።

በአካዝ ዘመንም እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ። እነሆ ስለዚህ እግዚአብሔር ምልክትን ይሰጣችኋል። እነሆ ድንግል ፀንሳ ወንድ ልጅን ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች። ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ አንድ ሆነ ማለት ነው።

እርሱም በኃጢአታቸው ከሚመጣባቸው ፍዳ ወገኖቹን የሚያድናቸው ወደ ሃይማኖቱም የሚአስገባቸው እንደሆነ የእስራኤልንም ልጆች መሥዋዕታቸውንና ክህነታቸውን እንደሚሽር ከሐዲስ ወገኖችም የሚያመሰግኑት ካህናትን እንደሚሾም ተናገረ።

የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬምም ኢየሩሳሌምን ከቦ የስድብ ቃልን በክብር ባለቤት በእግዚአብሔር ላይ በተናገረ ጊዜ የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬምን ያጠፋው ዘንድ እግዚአብሔር እንዳለው ለሕዝቅያስ ትንቢትን ተናገረ።

በዚያች ሌሊትም እግዚአብሔር የላከው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደ ሠናክሬም ሰፈር መጥቶ ከፋርስ ሠራዊት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ አርበኞችን ገደለ። የለኪሶ ሰዎች ሲነጋ በተነሡ ጊዜ የሞቱትን ሰዎች ሬሳ ሁሉ አዩ።

ሕዝቅያስም ታሞ ለሞት በተቃረበ ጊዜ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደርሱ መጥቶ እግዚአብሔር ትሞታለህ እንጂ አትድንም ብሏልና ቤትህን አዘጋጅ አለው። ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ ወደ እግዚአብሔር ለመነ ፈጽሞ ጽኑ ልቅሶንም አለቀሰ።

ይህን ከነገረው በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ነቢዩ ወደ ኢሳይያስ መጣ ሒደህ ለሕዝቅያስ የአባትህ የዳዊት ፈጣሪ እግዚአብሔር ጸሎትህን ሰማሁ ዕንባህንም አየሁ። እነሆ በዘመንህ ላይ ዐሥራ አምስት ዓመት ጨመርኩልህ አለ በለው።

ዳግመኛም ስለ እስራኤል መማረክና ከምርኮ ስለ መመለሳቸው ትንቢት ተናገረ የፈሳሽ ውኃን ምንጭ በማፍሰስ በእጆቹ ላይ እግዚአብሔር ምልክትን ገለጠ።

ክብር ይግባውና ስለ መድኃኒታችን ክርስቶስ መከራ ትንቢት ተናገረ እንዲህም አለ። እርሱም በመከራው ጊዜ ነገርን አልተናገረም እንደ በግ ይታረድ ዘንድ መጣ በግ በሚሸልተው ሰው ፊት እንደ ማይናገር እንዲሁ በመከራው ጊዜ አልተናገረም።

ከዚህም በኋላ ደግሞ በሕዝቅያስ ልጅ በንጉሥ ምናሴ ላይ ትንቢት ተናገር ጣዖትን ስለማቆሙና ስለማምለኩ ገሠጸው። ስለዚህም ንጉሥ ምናሴ ተቆጥቶ በዕንጨት መሰንጠቂያ መጋዝ በራሱና በእግሮቹ መካከል ሠነጠቀው ምስክርነቱንም በዚህ ፈጸመ።

ትንቢት እየተናገረ የኖረበትም ዘመን ሰብዓ ዓመት ከዚያም በላይ ይሆናል። እርሱም ያስተማረው ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት በዘጠኝ መቶ ዐሥራ ሦስት ዓመት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አባ_ሳሙኤል_ዘዋልድባ

ዳግመኛም በዚህች ቀን የዋልድባው የአቡነ ሳሙኤል ዐፅማቸው ከዋልድባ አብረንታንት ወደ ደብረ ዓባይ የፈለሰበት ዕለት ነው፡፡ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ትውልዳቸው ከካህናቱ ወገን አክሱም ነው አባታቸው እስጢፋኖስ እናታቸው አመተ ማርያም ይባላሉ። ለመምህር ሰጥተዋቸው ሲማሩ አድገው በኋላም ወላጆቻቸው በሞት ሲለዩአቸው ደብረ በንኰል ገዳም ገብተው ሥርዓተ ምንኩስናን ከአበው እያጠኑ ለትልቁም ለትንሹም በትሕትና እየታዘዙ ውሃ እየቀዱ እንጨት እየሰበሩ በትኅርምት በጽሞና በጸሎት ይኖሩ ነበር።

ሰይጣን በውዳሴ ከንቱ ጾር ቢመጣባቸው ከማሕበረ መነኮሳቱ ተለይተው በተባሕትዎ ለመኖር ሽተው ወጥተው ሲሔዱ ተከዜ ደረሱ። ወንዙ ሞልቶ የማያሻግራቸው ቢሆን ውሃውን በትምህርተ መስቀል ባርከው በአንድ እጃቸው መጽሐፍ በአንድ እጃቸው መብራት እንደያዙ ገብተው መብራቱ ሳይጠፋ መጽሐፉ ሳይበላሽ ተሻግረዋል። ዋልድባ ሲደርሱ ጌታ እዚህ ተቀመጥ ስላላቸው ገዳም መሥርተው ሥርዓተ ምንኩስናን እያስተማሩ ተቀመጡ። ዛሬ በዋልድባ የሚያመሰግኑበት ውዳሴ ማርያም ቅዳሴ ማርያምን ከተከዜ ወዲህ ያመጡ እሳቸው ናቸው። ይህንን እየጸለዩ ሲሔዱ ክንድ ከስንዝር መሬት ለቀው ይታዩ ነበር። አንድ ቀንም ይህንን ጸሎት ደግመው ውኃውን ቢባርኩት ኅብስተ ሕይወት ሆነላቸው ከነደቀ መዛሙርቶቻቸው ተመግበውታል።

እመቤታችንም የፍቅር መግለጫ ዕጣን፣ ወርቅ፣ እንቁ ሰጥታቸዋለች። ውዳሴዬን ከቅዳሴዬ አንድ አድርጎ የደገመውን አንተ ከገባህበት መካነ ሕይወት አስገባዋለሁ ብላ ቃልኪዳን ሰጥታቸዋለች። ጊዜ እረፍታቸው ሲደርስ ጌታን በስብሐተ መላእክት ተገልጦ በስምህ የተማጸነውን በጎ የሰራውን፣ ዜና ገድልህን የጻፈውን፣ ያስጻፈውን፣ ያነበበ፣ የተማረ፣ ያስተማረ፣ እስከ አሥር ትውልድ ድረስ ምሬልሃለሁ። በዚህ ቦታ በዋልድባ የሚሰበሰቡ ልጆችህን ከእዳ ከፍዳ እሰውርልሃለሁ አላቸው። እንኪያስ ቦታዋን ባርክልኝ ብለው እንደ መሶብ አንስተው አስባርከዋታል ጌታችንም እህል አይብቀልብሽ ኃጢአት አይሻገርብሽ ብሎ ቃል ኪዳን ገባላት ለገዳመ ዋሊ። አባታችን አቡነ ሳሙኤል በበዓታቸው ውስጥ ጸንተው ሲኖሩ ታህሣሥ 12 ቀን ያረፉ ሲሆን ዛሬ መስከረም 6 ግን ፍልሰተ አጽማቸው የተከናወነበት እለት ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሰብልትንያ

በዚህችም ቀን ቅድስት ሰብልትንያ በከ*ሀዲ ንጉሥ ዲዮቀልጥያኖስ ዘመን በሰማዕትነት ሞተች። ይችንም ቅድስት ዕድሜዋ ዘጠኝ ዓመት ሲሆን ከሀ*ድያን ያዙዋት እጆቿንና እግሮቿንም አሥረው ከሚነድ እሳት ውስጥ ጣሏት የክብር ንጉሥ በሆነ በእግዚአብሔርም ኃይል ከእሳት ዳነች።

ውኃን በተጠማች ጊዜ እግዚአብሔርን ለምናው ውኃን አፈለቀላትና ጠጣች ክብር ምስጉን የሆነ ጌታችንንም አመሰገነችው። ከዚህም በኋላ ነፍሷን በእግዚአብሔር እጅ አደራ ሰጥታ ራሷን ከእሳት ውስጥ ወረወረች ምስክርነቷንም ፈጸመች።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_መስከረም እና #ከገድላት_አንደበት)
@petroswepawulos
@petroswepawulos
@petroswepawulos
ጌታችን ለዮሐንስ ያልነገረው እርሱም ያላስተማረው ምሥጢር የለም፡፡ ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር "በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ…" ብሎ የጌታችን ነገር ተመራምሮ ለመድረስ ሲል በመሀል መልአኩን በዮርዳኖስ ባሕር ላይ ሲሄድ አገኘው፡፡ መልአኩም የዮርዳኖስን ባሕር በእንቁላል ቅርፊት እየጨለፈ ወደ ውጭ ሲያፈስ ተመለከተው፡፡ ዮሐንስም ተገርሞ "ምን ማድረግህ ነው" አለው፡፡ መልአኩም "የዮርዳኖስን ባሕር ቀድቼ እየደፋሁ ልጨርሰው ነው" ሲለው ዮሐንስም መልሶ "ታዲያ በእንቁላል ስባሪ ነውን?" አለው፡፡ መልአኩም "አዎን" አለው፡፡ ዮሐንስም "በከንቱ ደከምክ" አለው፡፡ ይህን ጊዜ መልአኩም መልሶ "አንተስ እንጂ ደግሞ የአምላክን መገኘት፣ አኗኗሩንም ተመራምረህ በጥበብ ለማግኘት ብለህ 'በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ..' ብለህ ጀምረህ የለምን? አንተ ጌታን ተመራምረህ ካገኘህና ከደረስክበት እኔም የዮርዳኖስን ወንዝ በዚህ እንቁላል ቅርፊት ቀድቼ እጨርሰዋለሁ" አለው፡፡ ዮሐንስም ይህን ጊዜ ደንግጦ ዝቅ ብሎ "ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ…" ብሎ ሀሳቡን ለወጠና ሌላ ታሪክ ቀጠለ፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ክርስቲያኖችን ሁሉ ወክሎ እመቤታችንን በአደራ የተቀበለ እርሱም ለመቤታችን በአደራ የተሰጠ ሲሆን እመቤታችንን ከወሰዳት በኋላ ለ16 ዓመት እየተንከባከበ ጠብቋታል፡፡ እናቱም በሕፃንነቱ ስለሞተች እመቤታችን ናት እየተንከባከበች ያሳደገችው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በመልኩም ከጌታችን ጋር ይመሳል ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ሥዕል የመሳል ተሰጥኦም ነበረው፡፡ ጌታችን በተሰቀለበት ዘመን የነበረው ጢባርዮስ ቄሳር ልጁ በሽተኛ ነበር፡፡ የጌታችንን የማዳን ሥራ እየሰማ እነ ጲላጦስም ስለጌታችን የሚጽፉለትን ይሰማ ስለነበር ልጁን ከጌታችን መቃብር ላይ እንዲያኖሩለት ላከው፡፡ ልጁም ፈጥኖ ተፈወሰለት፡፡ ጢባርዮስ ቄሳርም በልጁ መዳን ምክንያት የጌታችንን ውለታ ማስቀመጥ ፈልጎ የጌታችንን ሥዕሉን የሚሥልለትን ሲያጠያይቅ ዮሐንስን አገናኙት፡፡ ዮሐንስም ጌታችንን ልክ በዕለተ ዓርብ እንደተሰቀለ አድርጎ በመሣል ለጢባርዮስ ቄሳር ሰጠው፡፡ ሲሥለውም በመጀመሪያ ጌታችንን ልክ እንደተሰቀለ አድርጎ ራቁቱን ነበር የሳለው፡፡ ዮሐንስ የሳለው የጌታችን ሥዕልም አፍ አውጥቶ "በመጀመሪያ አይሁድ በኢየሩሳሌም ራቁቴን ሰቀሉኝ፣ አሁን ደግሞ አንተ ድጋሚ በሮም ራቁቴን ትሰቅለኝን?" ብሎ ተናገረው፡፡ ዮሐንስም እጅግ ደንግጦ "እንዴት አድርጌ ልሳልህ?" ብሎ የሳለውን ሥዕል ቢጠይቀው ሥዕሉም "ከለሜዳ አልብሰህ ሳለኝ" አለው፡፡ ዮሐንስም እንዳለው ከለሜዳ አልብሶ ከሳለው በኋላ ሥዕሉን ትኩር ብሎ ተመልክቶ ቢስመው ከንፈሩ አንድ ቀን ተኩል ያህል ተጣብቆ ቆይቷል፡፡ ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የምትጠቀምባቸውን የጌታችንን ስነ ስቅለት የሚያሳዩ ሥዕሎች መገኛቸው ይህ ወንጌላዊው ዮሐንስ የሳለው ሥዕል ነው፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ በተለያዩ ስሞች ይጠራል፦
በሕይወቱና በኑሮው ሁሉ ጌታችንን ለመምሰል ይጥር ነበርና ጌታችንም እጅግ ይወደው ስለነበር "#ፍቁረ_እግዚእ" ተባለ፣ የታላቁ ያዕቆብ ታናሽ ወንድም ስለሆነና አባቱም ዘብድዮስ ስለሚባል "#ዮሐንስ_ወልደ_ዘብድዮስ" ተባለ፣ ለጌታችን ባለው ቅናትና ከወንድሙ ጋር ሆነው ባሳዩት የኃይል ሥራ እንዲሁም የጌታችንን አምላክነት በመግለጡ "#ወልደ_ነጎድጓድ" ተብሏል፣ ነገረ መለኮትን ከሌሎቹ በበለጠ ሁኔታ አስፍቶና አምልቶ በማስተማሩ "#ነባቤ_መነኮት ወይም #ታኦሎጎስ" ተብሏል፣ ኃላፊውንና መጻዒውን ጊዜ በራእዩ ስለገለጠ "#አቡቀለምሲስ" ተባለ፣ ይህም በግሪክኛ #ባለራእይ ማለት ነው፣ የጌታችንን መከራ መስቀሉን እያስታወሰ 70 ዘመን ሙሉ እያለቀሰ ስለኖረና ፊቱም በሀዘን ስለተቋጠረ "#ቁጹረ_ገጽ" ተብሏል፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኅ_መስከረም እና #ከገድላት_አንደበት)
@petroswepawulos
@petroswepawulos
@petroswepawulos