መዝገበ ቅዱሳን
23.5K subscribers
1.96K photos
9 videos
6 files
26 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
ነበር፡፡ አያይዘውም በዚሁ በሹመት ሽኩቻ ምክንያት ወደፊት የሚፈጠረውን ነገር በመንፈስ ቅዱስ መነፅርነት አይተውት የሚከተለውን ትንቢት ተናግረዋል፡- ‹‹እውነት እላችኋለሁ በመጨረሻው ዘመን ደጋጎች ሰዎችን ክፉዎችና ተሳዳቢዎች የሚያደርጉ፣ ሐሰተኞችና ዋዛ ፈዛዛ የሚወዱትን ደጋጎች የሚያደርጉ ሰዎች ይመጣሉ፡፡

በመጨረሻው ዘመን ኃጥአን በጻድቃን ይመሰላሉ፣ ጻድቃንን ኃጢአተኞች ያደርጓቸዋል፡፡ በዚያን ዘመን እውነተኛዎቹ መምህራን አይሾሙም፣ ኃጢአተኞች መማለጃ ሰጥተው ወሬ እያቀበሉ ይሾማሉ፣ እንደ እባብ ክፉ ነገርን ለማድረግ ፍላፃቸውን ያሾሉ ደጋግ ሰዎችን በነገር ያጠፏቸው ዘንድ በእውነት ንጹሕ የሆኑትን ሰዎች አመፅን በተመላ አንደበታቸው ሹመትን ከመውደድ የተነሣ በቅናት ያጠፏቸዋል፡፡ በዚያን ዘመን መጻሕፍትን የሚያውቁ አይሾሙም፣ ነገርን የሚያመላልሱና የአገሮችን ቋንቋ የሚያውቁ ከመኳንንትና ከነገሥታት ዘንድ ሔደው ነገርን የሚሠሩ ሰውን የሚያጣሉ በአመፅ ሹመትን የሚያገኙ ብቻቸውን ይሾማሉ እንጂ ደጋጎች አይሾሙም፡፡ በሚመረጡበትም ጊዜ ከአባታቸው ከሰይጣን ጋር ሆነው ‹እገሌ መጻሕፍትን ያውቃል፣ የአገሮችን ቋንቋ የሚያውቅ ይሾም› ይላሉ፡፡ ያንጊዜም አመፅ ይበዛል፣ ፍቅርም ትጎድላለች፡፡ ከእኔ በኋላ የሚሆነውን እነሆ ነገርኳችሁ ይህንንም አውቃችሁ በልቡናችሁ ያዙ፡፡››
ጌታችን ለአቡነ ፊሊጶስ የገባላቸው ልዩ ቃልኪዳን፡- ‹‹ገድልህንና ስለ እኔ የታገስከካቸውን መከራዎችህን የጻፈውን ከሁላቸው ከቅዱሳንና ከሰማዕታት ጋር በሰማያዊት ኢየሩሳሌም በወርቀ ቀለም ለዘለዓለሙ ስሙን እጽፍልሃለሁ፡፡ ሥጋህ ከተቀበረበት ቦታ ይቅርታዬንና ቸርነቴን አደርጋለሁ፡፡ መቃብርህ የበረከት ቦታ ትሆናለች፡፡››

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_ጻድቃን_እንድራኒቆስና_አትናስያ

በዚህች ቀን ክርስቶስን የሚወዱ የእንድራኒቆስና የሚስቱ የአትናስያ መታሰቢያቸው ነው። እነርሱም ከአንጾኪያ ከተማ ነበሩ። በወርቅና በብርም የከበሩ ባለጸጎች ነበሩ ከገንዘባቸውም ለድኆችና ለችግረኞች ይሰጡ ነበር። 

ከዚህም በኃላ አንድ ወንድ ልጅና አንዲት ሴት ልጅን ወለዱ ወንዱን ዮሐንስ ሴቲቱንም ማርያም ብለው ሰየሟቸው ልጆችም አደጉ እንዱራኒቅስና ሚስቱም እንግዳ በመቀበል ለድኆችና ለምስኪኖች በመመጽወት በጎ ሥራን አበዙ እነርሱም መገናኘትን ትተው ሰውነታቸውን በንጽሕና ጠበቁ። 

ልጆቻቸውም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆናቸው ጊዜ የሆድ ዝማ በሽታ ታመው በአንዲት ቀንም ሞቱ እንዲራኒቆስም አይቶ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥዕል ፊት ራሱን ጥሎ እንዲህ ብሎ አለቀሰ ከእናቴ ማሕፀን ራቁቴን ወጣሁ ወደ እግዚአብሔርም ራቁቴን እሔዳለሁ እርሱም ሰጠ እርሱም ወሰደ የእግዚአብሔር የጌትነቱ ስም የተባረከ ይሁን ለዘላለሙ አሜን። 

እናታቸውም ለሞት እስከምትደርስ እጅግ አዘነች ልጆቿ ወደ ተቀበሩበት ወደ ዐፀደ ቤተ ክርስቲያን ሔደች ከኀዘንዋም ብዛት የተነሳ አንቀላፋች በእንቅልፏም ውስጥ በልጆችሽ ሞተ አታልቅሺ እነርሱ ግን በሰማያት ደስ እያላቸው ናቸው እያለ በመነኰስ አምሳል ሲነግራት አየች። ይህንንም ሰምታ ሒዳ ለባሏ ነገረችው። 

ከዚህም በኃላ ይህን ዓለም ይተዉ ዘንድ ተስማሙ ገንዘባቸውንም ሁሉ ምንም ሳያስቀሩ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጡ በሌሊትም ወጥተው ወደ እስክንድርያ ከተማ ደረሱ ሚስቱንም በዚያ ትቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ በአባ ዳንኤል ዘንድ መነኰሰ። ከዚያም ተመልሶ ሚስቱ አትናስያን ወደ ሴቶች ደናግል ገዳም ወሰዳት በዚያም ተዋት። 

ከዐሥራ ሁለት ዓመትም በኃላ እንድራኒቆስ ከቅዱሳት መካናት ይባረክ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሔድ አባ ዳንኤልን ለመነው ፈቀደለትም በመድኃኒታችንም ቸርነት ሚስቱ አትናስያ በወንድ አምሳል በጉዞ ላይ ተገናኘችው ሚስቱ እንደሆነችም አለወቀም እርሷ ግን አወቀችው ነገር ግን ሚስቱ እንደሆነች አልገለጠችለትም። 

ወደ ቅዱሳት መካናትም በደረሱ ጊዜ ሥራቸውን ፈጽመው ወደ አባ ዳንኤል በአንድነት ተመለሱ። አባ ዳንኤልም ሚስቱ እንደሆነች በመንፈስ ቅዱስ አውቆ እንድራኒቆስን ባልንጀራ ካደረግኸው ከዚህ መነኰስ ጋራ በአንድ ቦታ ኑሩ እርሱ ቅዱስ ነውና አለው። ዐሥራ ሁለት ዓመትም በአንድነት ኖሩ ማንም የአወቀ አልነበረም። 

አባ ዳንኤልም ይጎበኛቸውና ስለ ነፍሳቸው ጥቅም ያስተምራቸው ነበር። ከዚህም በኃላ አትናስያ በታመመች ጊዜ ለእንድራኒቆስ አባታችንን አባ ዳንኤልን ጥራልኝ አለችው ሒዶም ለአባ ዳንኤል እንዲህ ብሎ ነገረው ባልንጀራዬ ታሞ ለመሞት ተቃርቧልና ትጎበኘው ዘንድ ና። በደረሰም ጊዜ በታላቅ ሕመም ላይ አገኛት እርሷም ታቆርበኝ ዘንድ እሻለሁ አለችው ያን ጊዜም ተፋጠነና ሥጋውንና ደሙን አቀበላት ከዚህም በኃላ አረፈች በሚገንዟትም ጊዜ ሴት እንደሆነች አገኙ ዳግመኛም ታሪኳንና ለባሏ የረወቻቸውን ምልክቶች አገኙ። 

እንድራኒቆስም በአነበበ ጊዜ እርሷ ሚስቱ እንደሆነች አወቀ ደንግጦም ልቡ ተሠወረ ፊቱንም እየጻፈ ጮኸ ያለቅስ ጀመረ።ከጥቂት ቀን በኃላም ታመመ አረጋውያንም መጥተው በረከቱን ተቀበሉ ሥጋውንና ደሙንም ተቀበሉ በሰላም አረፈ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ እና #ከገድላት_አንደበት)
@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5
#ሐምሌ_29

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ሐምሌ ሃያ ዘጠኝ በዚች ቀን #አቡነ_ዮሐንስ_ዘጠገሮ ዕረፍታቸው ነው፣ #የቅዱስ_ሐዋርያ_ታዴዎስ የሥጋው ፍልሰት ሆነ፣ #ቅዱስ_ወርስኖፋ በሰማዕትነት አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#እጨጌ_አባ_ዮሐንስ_ዘጠገሮ (ዘጐንድ)

ሐምሌ ሃያ ዘጠኝ በዚች ቀን አቡነ ዮሐንስ ዘጠገሮ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ጻድቁ አባታችን የተወለዱት በኢየሩሳሌም አውራጃ ልዩ ስሙ ሳሬራ በሚባል ቦታ ነው፡፡ የካቲት 28 ቀን ተፀንሰው ህዳር 29 ተወለዱ፡፡ አባታቸው ድላሶር እናታቸው እምነ ጽዮን ይባላሉ፡፡ ሲወለዱ በወላጆቻቸው ቤት ውስጥ ብርሃን ወርዷል፡፡ ወላጆቻቸውም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ አባታችን ገና በተወለዱ በ5 ዓመታቸው ወላጆቻቸው ወደ እግዚአብሔር ቤት ይዘዋቸው የእመቤታችንን ሥዕል ተመልክተው በደስታ ተመልተው ሳቁ፡፡ አምላክን የወለደች የብርሃን እናቱ እመቤታችንም ከምሥሉ ወጥታ ‹‹በምን አውቀኸኝ ነው?›› ብላ አቅፋ ሳመችውና ‹‹ከእንግዲ ወዲህ የልጄ አገልጋይ ትሆናለህ ኑሮህም እንደ መላእክት ይሆናል በአንተ ምክንያት ብዙ ሰዎች ይድናሉ በምድር ላይም 500 ትኖራለህ…›› ብላ ባርካው ተሰወረች፡፡

ከዚያችም ቀን ጀምሮ አባ ዩሐንስ ለክርስቶስ ተላልፎ ተሰጠ፡፡ 50 ዓመትም በበረሃ ሲጋደል ኖሮ ከ50 ዓመት በኃላ በደመና ተጭኖ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል መሪነት ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ጻድቁ አባታችን በአቡነ ተክለሃይማኖት ዘመን መጨረሻ የመጡ ሲሆን ምንኩስና ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተቀብለው በዚያው በድብረ ሊባኖስ ገዳም ለ50 ዓመት በጾምና በጸሎት በተጋድሎ ኖዋል፡፡ ከዚኽም በኋላ አባ ዩሐንስ ወደ ተዘጋቸላቸው ምድር በቅዱስ ገብርኤል አሳሳቢነት ወደ ጠገሮ መጡ፡፡ ይኽም ጠገሮ ያለው ገዳማቸው በሰሜን ሸዋ በመንዝና ይፋት ክልል መዘዞ በሚባል ቦታ ሲደርሱ በእግር አንድ ሰዓት ከተጓዙ በኃላ ይገኛል፡፡

ሕዝቡ በተለምዶ እጨ ዮሐንስ እያለ ይጠራቸዋል እንጂ ስማቸው እጨጌ ዮሐንስ ነው፡፡ አቡነ እጨጌ ዮሐንስ መስቀል ከሰማይ የወረደላቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ መስቀሉም ሁልጊዜ ተአምር ይሠራል፡፡ በልደታቸው ቀን ኅዳር 29 ቀን መስቀሉ ከመቅደሱ ወጥቶ በካህናቱ ታጅቦ ወደ ጸበሉ ሲወርድ ከየት እንደመጣ ሳይታሰብ ደመና መጥቶ ከመስቀሉ ላይ ብቻ እረቦና እንደ ጃንጥላ ተዘርግቶ አብሮ ወደ ጸበሉ ይወርዳል፡፡ እዛው ቆይቶ መስቀሉ ሲመለስም አብሮ አጅቦ ይመለስና መስቀሉ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲገባ ደመናው ወዴት እንደተበተነ ሳይታወቅ ይጠፋል፡፡ ይህ በዘመናችንም ጭምር እየታየ ያለ ታላቅ ተአምር ነው፡፡ 

አባታችን በታላቀ ተጋድሎ ሣሉ ሰይጣን የሀገሩን ሰዎች በጠላትነት እንዲነሡባቸው አደረገ፡፡ ሰዎቹም አባታችንን እንዴት እንደሚያጠፏቸው ይማከሩ ጀመር፡፡ ሊገድሏቸው ፈልገው ቅድስናቸው በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነውና ፈሩ፡፡ ከዚኽም በኋላ ‹‹ለምን ከመንደራችን ከወንድ ያረገዘች ሴት ፈልገን እሳቸው አስረገዟት ብለን በሐሰት እንከሳቸው?›› ብለው ተማከሩ፡፡ ብዙ ወርቅና ብርም ለአንዲት ሴት ሰጥተው በሐሰት ከእርሱ አርግዣለሁ ብላ እንድትመሰክር አደረጓት፡፡ አባታችንም በሕዝብ ፊት በሐሰት ተከሰሱ፡፡ ጻድቁም ‹‹አንቺ ሴት ከእኔ ነው ያረገሽው?›› አሏት እርሷም ‹‹አዎ ከአንተ ነው ልትክድ ነው እንዴ?›› አለቻቸው፡፡ አባታችንም በዚህ አዝነው ‹‹በአንቺና በእኔ መካከል እግዚአብሔር ይፍረድ›› ሲሉ ያች ሴት ወዲያው ለሁለት ተሰንጥቃ ሞተች፡፡ የአገሩ ሰዎችም እጅግ ፈሩ፡፡ አባታችንም ምድሪቱን እረገሟት፡፡ ‹‹የተዘራው ዘር አይብቀልብሽ፣ የተተከለው አይፅደቅ፣ ብርድና ውርጭ ይፈራረቅብሽ›› ብለው እረግመዋት በደመና ተጭነው ወደ ሰሜን ጎንደር እስቴ ጉንደ ተክለተሃማኖት ሔዱ፡፡

አቡነ ዩሐንስ በመላው ኢትዮጵያ ወንጌልን እየተዘዋወሩ ያስተማሩ ሲሆን ከቅድስናቸው የተነሣ በፀሐይ ላይ 50 ዓመት፣ በጨረቃ ላይ 50 ዓመት፣ በደመና ላይ 50 እንዲሁም ዓለምን በክንፋቸው በመዞር በደመና ላይ 50 የኖሩ ከሰው ተወልደው ከመላእክት የተደመሩ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፡፡ በይፋት ጠግሮ በዓለወልድ፣ በአፋር አዘሎ፣ በመንዝ ፍርኩታ ኪዳነምሕረት፣ በደብረ ሊባኖስ፣ በጎንድ ተክለ ሃይማኖት በሌሎችም ቦታዎች በመዘዋወር በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡ አባታችን ከሰማይ መስቀል የወረደላቸው ሲሆን ዛሬም በገዳማቸው የሔደ ሰው በወረደው በእጃቸው መስቀል እየተዳበሰ ቆመው በጸለዩበት ባሕር በጠበላቸው ይጠመቃል፡፡ በተጨማሪም ይይዙት በነበረውም  መቋሚያቸው በመዳበስ በረከትን ማግኘት ይቻላል፡፡ ቆመው ከጸለዩበት ባሕር ውስጥ ደረቅ አሸዋ ይወጣል፡፡ አባ ዩሐንስ 500 ዓመት ከኖሩ በኃላ እረፍተ ዘመናቸው ሲደርስ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከ15 ነቢያት፣ ከ12 ሐዋሪያት፣ ሄሮድስ ያስፈጃቸው ከመቶ አርባ አራት ሺ ሕፃናት፣ ከአብርሃም ከይስሐቅ፣ ከዕቆብ ጋር ሁሉንም ነገደ መላእክትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን ሁሉ አስከትሎ መጥቶ ታላቅ ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ‹‹ስምህን የጠራ ገዳምህን የረገጠ፣ መባ የሰጠ፣ ቤተ ክርስትያንህን የሠራ ያሠራ የረዳ፣ ገድልህን የሰማ ያሰማ ያስተረጎመ፣ መታሰቢያን ያደረገ እስከ 10 ትውልድ እምርልሀለው፤ ንስሀ ሳይገባ አይሞትም፣ ልጅ መውለድ ባይችል እኔ ልጅ እሰጠዋለሁ፤ ገድልህን በቤትህ ያስቀመጠ እርኩስ መንፈስ፣ ክፉ አጋንንት ቸነፈር ወባ መልአከ ጽልመት አይነካውም፡፡ በገዳምህ መነኩሴ ቢቀበር በሰማይ ክንፍ አበቅልለታለሁ፤ አይሁድም አረማዊም ያላመነ ያልተጠመቀ በገዳምህ መጥቶ ቢያርፍ ይቅር እልልሃለሁ፣ እንደ መቃብሬ ጉልጎታ እንደተቀበረ አድርጌ እቆጥርልሃለሁ…›› የሚል ቃል ኪዳን ከሰጣቸው በኃላ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡

ቅዱስ አባታችንም በ500 ዓመታቸው ሐምሌ 29 ቀን ዐርፈው በጎንድ ተክለ ሃይማኖት ተቀብረዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር የሚገኘውን ይህንን ገዳም ጻድቁ ራሳቸው ናቸው የመሠረቱት፡፡ ነገር ግን የገዳሙን ስያሜ በአባታቸው በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም አድርገውታል፡፡

አቡነ ዮሐንስ ካረፉ በኋላ በእርግማናቸው መሠረት በመንዝና በይፋት ብርዱ ድርቁ ስለበዛባቸው አንድ ብቁ ባሕታዊ ከበዓታቸው ወጥተው ‹‹በሐሜታችሁ ምክንያት እጨ ዮሐንስ ስለረገማችሁ ነው የእርሱን ዐፅም ካላመጣችሁ ብርዱ ውርጩ ድርቁም አይጠፋላችሁም›› አሏቸው፡፡ ሕዝቡም አባታችን በጉንድ አቡነ  ተክለ ሃይማኖት ከተቀበሩ ከ134 ዓመት በኃላ በቅዱሳን እየተመሩ ሄደው በሌሊት ግማሽ ዐፅማቸውን አምጥተው በሀገራቸው አምጥተው ስላስቀመጡ ብርዱና ውርጩ በመንዝ እየቀነሰላቸው መጥቷል፡፡ ዛሬም በሀገሩ ብርዱና ውርጭ ሲበዛ የጻድቁን ታቦት ሲያወጡ ውርጩ ይጠፋል፡፡

ጠገሮ በሚባለው ገዳማቸው ውስጥ የሚገኘው ጠበላቸው እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ ግማሽ ዐፅማቸውን ከጉንደ ተክለሃይማኖት አምጥተው አርባ ሐራ መዳኒዓለም አጠገብ በላይ በፍሩክታ ኪዳነምሕረት መጋቢት 18 ፍልሰተ ዐፅማቸው ተከናወነ፡፡ ምድሪቷም ተባረከች፣ የዘሩትንም አበቀለች፣ ውርጩም ብርዱም ቀነሰ፣ ዝናብ አልዘንብ ሲል ወይም ሰብል የሚጨርስ አንበጣ ሲመጣ ታቦታቸው ወጥቶ ምህላ ይያዛል-ወድያውም መቅሰፍት ይርቃል፣ ዝናብም ይዘንባል፡፡ ጻድቁ ደመናን፣ ጨረቃንና ፀሐይን በእጃቸው እየያዙ ይጸልዩ ነበር፡፡
#ነሐሴ_1

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ አንድ በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም እናቷ #የቅድስት_ሐና መታሰቢያዋ ነው፣ የዮስጦስ ልጅ #ቅዱስ_አቦሊ በሰማዕትነት አረፈ፣ የከበሩ ሰዎች #ቅዱሳን_የዮሴፍና_የኒቆዲሞስ መታሰቢያቸው ነው።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሐና (የእመ ብርሃን እናት)

ነሐሴ አንድ በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም እናቷ የሐና መታሰቢያዋ ነው። ይህችም ቅድስት ከኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ትውልድ የሌዊ የሜልኪ ልጅ ለሆነ ለማጣት (ጣ ጠብቆ ይነበብ) ልጁ ናት። ለማጣትም ሦስት ሴቶች ልጆች አሉት የታላቂቱም ስሟ ማርያም ናት ሁለተኛዋም ስሟ ሶፍያ ሦስተኛዪቱም ስሟ ሐና ናት ታላቂቱ ማርያምም ለባል ተድራ አዋላጅ የሆነች ሰሎሜን ወለደቻት እርሷም መድኃኒታችንን ከወለደችበት ጊዜ ጀምሮ በስደቷም ወራት ከአረጋዊ ዮሴፍ ጋር እመቤታችንን ድንግል ማርያምን ያገለገለቻት ናት።

ሶፍያም ለባል ተድራ ለመጥመቁ ዮሐንስ እናቱ የሆነች ቅድስት ኤልሳቤጥን ወለደቻት። ይችንም ቅድስት ሐናን ከይሁዳ ነገድ ለሆነ ጻድቅ ስሙ ኢያቄም ለሚባል አጋቧት። (ሰሎሜና ኤልሳቤጥ ለቅድስት ሐና የእኅትማማች ልጆች ናቸው።)

ቅድስት ሐና ኢያቄምን አግብታ ስትኖር የቴክታና እና የጴጥሪቃ ምክነት በዘር ወርዶ መክና በመኖሯ  የዐይኗ ማረፊያ የልቧ ተስፋ የሚሆን ልጅ እንዲስጣት ፈጣሪዋን ስትማጸን ኖራለች።

የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን የማይነሳ አምላክ ልመናዋን ሰምቶ ሐምሌ ፴ ራእይ አየች። ራእዩንም ከባሏ ከኢያቄም ጋር ተወያየተው ምንጣፍ ለይተው ሱባኤ ገቡ።

ከአንድ ሱባኤ በኋላ ነሐሴ ፯ ቀን ጌታ ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ እንደሚወልዱ አበሠራቸው። ከዚያም እመቤታችን ጸንሳ ልዩ ልዩ ተአምራትን አድርጋለች። ሳምናስን ከሞት አስነስታለች። በርሴባን ዐይኗን አብርታለች። ከዚያም በአይሁድ ተንኮልና አሳዳጅነት ወደ ሊባኖስ ተራራ ተሰዳ ድንግል ማርያምን ወልዳለች። በመውለዷም ሕዳሴ አካል አግኝታ ከኖረች በኋላ ዐርፋለች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አቦሊ

በዚህችም ቀን የዮስጦስ ልጅ ቅዱስ አቦሊ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ አቦሊ ከመንግሥት ልጆች ውስጥ ነበር ዐላውያንን ወግቶ በተመለሰ ጊዜ ዲዮቅልጥያኖስን ክብር ይግባውና ክርስቶስን ክዶ አገኘው። 

ያም አቦሊና አባቱ ዮስጦስ ሌሎችም የመንግሥት ልጆች ሁሉ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስን ሊያጠፉትና መንግሥትን ከእርሱ ሊወስዱ ችሎታ ሲኖራቸው የማታልፍ ሰማያዊት መንግሥትን አሰቡ። 

ከዚህም በኋላ ቅዱስ አቦሊ ወደ ንጉሡ ቀርቦ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም አብዝቶ አባበለው። እንዲሁም አባቱ ዮስጦስንና የከበረች እናቱ ታውክልያን አባበላቸው እነርሱ ግን አልሰሙትም ልባቸው በመድኅን ክርስቶስ ፍቅር ተነድፏልና። ንጉሡም እነርሱን በዚያ ማሠቃየትን ፈራ ስለዚህም ከመልእክት ደብዳቤ ጋር ወደግብጽ ስሙ ኄርሜኔዎስ ወደሚባል የእስክንድርያ ገዥ ላካቸው በመልእክቱም እንዲህ አለው ዮስጦስና ሚስቱ ታውክልያ ልጃቸው አቦሊም ወደአንተ በሚደርሱ ጊዜ አባብላቸው አለዚያም እየአንዳንዳቸውን ለያያቸው። 

በዚያችም ሌሊት ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዮስጦስና ለሚስቱ ታውክልያ ለልጃቸው አቦሊም ተገልጦላቸው አጽናናቸው ከእነርሱም የሚሆነውን ነገራቸው የጸና ቃል ኪዳንም ሰጣቸው። 

ወደ መኰንኑ ኄርሜኔዎስም በደረሱ ጊዜ ስለእነርሱ እጅግ አደነቀ እነርሱ መንግሥታቸውን ትተዋልና ክፋ ነገርንም ሊናገራቸው አልደፈረም ከምክራቸው ይመለሱ ዘንድ በለሰለሰ ቃል ሸነገላቸው እንጂ ነገር ግን አልሰሙትም። 

ከዚህም በኋላ በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ ለእየብቻቸው ለያያቸው ቅዱስ ዮስጦስን ወደ እንዴናው ከተማ ሚስቱን ታውክሊያን ፃ ወደ ሚባል አገር ልጃቸው አቦሊንም ብስጣ ወደ ሚባል አገር ሰደዳቸው ለእያንዳንዳቸውም የሚአገለግላቸው አንዳንድ አገልጋይ ሰጣቸው።  ቅዱስ አቦሊም ወደ ሀገር ብስጣ በደረሰ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመኰንኑ ፉት ታመነ። መኰንኑም ጽኑ ሥቃይን በእሳት ቃጠሎና በመንኰራኵር አሰቃየው ሕዋሳቱንም ቆራርጦ ለአንበሶች ጣለው ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስም ከሥቃዩ ሁሉ አድኖ ያለ ጉዳት በጤና አነሣው። 

ብዙዎች ሰዎችም ስቃዩንና ዳግመኛ መዳኑን በአዩ ጊዜ እጅግ አደነቁ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም አምነው ሰማዕታት ሆኑ። 

መኰንኑ ግን እጅግ ተቆጥቶ የቅዱስ አቦሊን ቆዳውን እንዲገፍፉትና ጨውና መጻጻን በማቅ አምጥጠው ቍስሉን እንዲያሹ አዘዘ ይህንንም ሁሉ አደረጉበት። 

ከዚህም በኋላ ቆዳውን አሸክመው በከተማ ውስጥ ሁሉ አዞሩት ወደ ጌታችንም እንዲህ ብሎ ጸለየ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ርዳኝ ከዚህ ሥቃይም አድነኝ። ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደርሱ መጣ ሁለመናውንም ዳስሶ አዳነው። 

መኰንኑም በእርሱ ላይ የሚያደርገውን እስኪያስብ ከእሥር ቤት እንዲጨምሩት አዘዘ። ቅዱስ አቦሊም ቁሞ ጸለየ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና ጌታችን ተገለጠለትና የመረጥኩህ አቦሊ ሰላም ለአንተ ይሁን እኔም ከአንተ ጋር እኖራለሁ አለው ጌታችንንም በአየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው ክብር ይግባውና ለጌታችንም ሰገደለት።

ስሙ አብስኪሮን የሚባል አንድ ባለ ጸጋ ነበር የቤቱንም ግድግዳ አፍርሰው አዲስ ይሠሩለት ዘንድ ሠራተኞችን አመጣ ሥራቸውንም እስኪጨርሱ ከዚያ ይቆሙ ዘንድ ሁለቱን ልጆቹን አዘዛቸው። 

ከግርግዳውም ላይ በወጡ ጊዜ ግርግዳው ተደርምሶ ዐሥራ ስድስት ሰዎችና ሁለቱ ልጆቹ ሞቱ። ባለጸጋውም የሆነውን በአየ ጊዜ ልብሱን ቀደደ ጩኾም አለቀሰ ወደ ቅዱስ አቦሊም ሒዶ ከእግሩ በታች ሰገደለት እንዲህም አለው ራራልኝ ሁለቱ ልጆቼ ሙተዋልና ከእነርሱም ጋራ ዐሥራ ስድስት ሰዎች ሞቱ። ከሞትም ብታሥነሣቸው እኔ በአምላክህ አምናለሁ። 

ያን ጊዜም ቅዱስ አቦሊ ተነሣ እንዲህ ብሎ ጸለየ ስለ ቅዱስ ስምህ መከራን እቀበል ዘንድ የመረጥከኝ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በእኒህ በሞቱ ሰዎች ላይ ኃይልህን ግለጥ። እኒህ ሰዎች ሁሉ እንዲአምኑ ያለ አንተም ሌላ አምላክ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ ከሞት አንሣቸው። ላንተም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

ከዚህም በኋላ የተገፈፈ ቆዳውን ወስዶ በሞቱት ሰዎች ላይም ዘረጋውና በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከሞት ተነሡ አለ። ወዲያውም ሁሉም ድነው ተነሡ በዚያ ያሉ ሕዝብም ይህን ድንቅ ሥራ በአዩ ጊዜ የክርስቲያን አምላክ የቅዱስ አቦሊም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ነው እኛም እናምንበታለን ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለምና እያሉ ጮኹ። 

ባለ ጸጋው አብስኪሮንም መጥቶ ለቅዱስ አቦሊ እንዲህ እያለ ሰገደ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይግባውና እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ዛሬ አወቅሁ እኔም አምንበታለሁ። ከቤተሰቦቹም ሁሉ ጋር አመኑ መኰንኑም አፈረ።
#ነሐሴ_2


አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ሁለት በዚች ቀን መኑፍ ከሚባል አገር #ቅድስት_አትናስያ አረፈች፣ ከነገሥታት ወገን የሆነች #ቅድስት_ኢዮጰራቅስያ አረፈች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_አትናስያ_ቡርክት

ነሐሴ ሁለት በዚች ቀን መኑፍ ከሚባል አገር ቅድስት አትናስያ አረፈች። 

የዚችም ቅድስት ወላጆቿ ባለጸጎች ነበሩ እነርሱም በሞቱ ጊዜ ቤቷን ለእንግዳ ማደሪያ ታደርግ ዘንድ በጎ ኃሳብ አሰበች ወደርሷም የሚመጡትን እንግዶች ሁሉ ትቀበላቸው ነበር። በገዳም ለሚኖሩ መነኰሳትም የሚያስፈልጓቸውን ትሰጣቸው ነበር ስለ በጎ ሥራዋም ይወዷት ነበር። 

ከዚህም በኋላ ግብራቸው የከፋ ክፉዎች ሰዎች ወደርሷ ተሰብስበው ኃሳቧን ወደ ኃጢአት ሥራ መለሱትና ኃጢአትን አብዝታ ትሠራ ጀመር። በአስቄጥስ ገዳም በሚኖሩ አረጋውያን ቅዱሳን ዘንድም ወሬዋ ተሰማ ስለእርሷም እጅግ አዘኑ አባ ዮሐንስ ሐጺርንም ጠርተው ስለርሷ የሆነውን ነገሩት አስቀድማም ከእነርሱ ጋራ በጎ ስለ ሠራች ወደ እርስዋ ይሔድ ዘንድ ነፍስዋንም ለማዳን ይወድ ዘንድ ለመኑት። 

እርሱም ትእዛዛቸውን ተቀበለ በጸሎታቸውም እንዲረዱት ለመናቸው ያን ጊዜም አባ ዮሐንስ ሐጺር ተነሥቶ ሔደ አትናስያ ወዳለችበት ቦታ ደረሰ ለበረኛዋም ለእመቤትሽ ስለእኔ ንገሪ አላት። በነገረቻትም ጊዜ ለረከሰ ሥራ እንደሚፈልጓት ሰዎች ሁሉ የመጣ መሰላትና አጊጣ በዐልጋዋ ላይ ሁና ጠራችው። ወደርሷም ገባ እርሱም እንዲህ እያለ ይዘምር ነበር በሞት ጥላ ውስጥ ብሔድም እንኳ ክፉን አልፈራውም አንተ ከእኔ ጋራ ነህና። 

ከእርሷ ጋራም አስቀመጠችው ያን ጊዜም ራሱን ዘንበል አድርጎ አለቀሰ ለምን ታለቅሳለህ አለችው እርሱም ሰይጣናትን በላይሽ ሲጫወቱ አየኋቸው ክብር ይግባውና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ለምን አሳዘንሺው የቀድሞ በጎ ሥራሽን ትተሽ ወደ ጥፋት ሥራ ተመልሰሻልና አላት። 

ቃሉንም ሰምታ ደነገጠችና ተንቀጠቀጠች ምን ይሻለኛል አለችው ንስሐ ግቢ አላት እርሷም እግዚአብሔር ይቀበለኛልን አለችው እርሱም አዎን አላት እርሷም ወደምትሔድበት ከአንተ ጋራ ውሰደኝ አለችው እርሱም ነዪ ተከተይኝ አላት።

ያን ጊዜም ፈጥና ተነሥታ በኋላው ተከተለችው ከገንዘቧም ምንም ምን አልያዘችም። በመሸም ጊዜ ለማደር ወደ ጫካ ውስጥ ገቡ በዚያም ለእርስዋ ቦታ አዘጋጅቶ እስኪነጋ በዚህ አረፍ ብለሽ ተኚ እኔም ወደዚያ እሆናለሁ አላት። ይህንንም ብሎ ከእርሷ ጥቂት ተገልሎ እየጸለየ ብቻውን ተቀመጠ። 

በሌሊቱ እኩሌታም ሊጸልይ ተነሣ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ አየ የእግዚአብሔርም መላእክት የከበረች ነፍስን ተሸክመው ሲወጡ አይቶ አደነቀ። በነጋም ጊዜ ወደ ርሷ ሔደ ሙታም አገኛት እጅግም አዘነ ስለ ርሷም ያስረዳው ዘንድ እየሰገደ ወደ እግዚአብሔር ለመነ። 

ወደርሱም እንዲህ የሚል ቃል መጣ ከቤቷ በወጣች ጊዜ እግዚአብሔር ንስሓዋን ተቀብሎ ኃጢአትሽ ተሠረየልሽ ብሎአታል። ከዚህም በኋላ ሒዶ ለአረጋውያን የሆነውን ሁሉ ነገራቸው እነርሱም እርሱ እንዳያት ማየታቸውን ነገሩት የኃጢአተኛን ወደ ንስሐ መመለሱን እንጂ ሞቱን የማይሻ እግዚአብሔርን አመሰገኑት።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ኢዮዸራቅስያ_ድንግል

በዚህችም ቀን ከነገሥታት ወገን የሆነች ቅድስት ኢዮጰራቅስያ አረፈች። የእርስዋም የአባቷ ስም ኢጣጎኖስ ነው የንጉሥም አማካሪ ነበር የእናቷም ስም ኢዮጰራቅስያ ነው እነርሱም ደጎች ነበሩ ጾምና ጸሎትንም ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡ ነበሩ። ይችንም ቅድስት በወለዷት ጊዜ በእናቷ ስም ኢዮጰራቅስያ ብለዉ ጠሩዋት። 

ከጥቂት ጊዜ በኋላም አባቷ አረፈ ዕድሜዋም ስድስት ዓመት በሆነ ጊዜ እናቷ ወደ ደናግል ገዳም ከእርሷ ጋር ወሰደቻት ይህችም ቅድስት ደናግሉ ሲያገለግሉ አይታ ስለ ምን እንዲህ ደክማችሁ ትሠራላችሁ አለቻቸው እነርሱም ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ ነው ብለው መለሱላት ወደ ዲያቆናዊትም ሒዳ ያመነኲሷት ዘንድ ለመነች እነርሱም ለእናቷ ነገሩዋት እናቷም ለዲያቆናዊተዋ ሰጠቻት በደናግሉም ሁሉ ዘንድ አደራ ሰጠቻት ከጥቂትም ቀኖች በኋላ እናቷ አረፈችና ቀበሩዋት። 

ከዚህም በኋላ ቅድስት ኢዮጰራቅስያ የምንኲስና ልብስን ለበሰች በጾም በጸሎትና በሰጊድ ተጋድሎ ጀመረች በየሰባት ቀንም ትጾም ነበር ሰይጠንም በእርሷ ላይ ቀንቶ ሊፈትናት ጀመረ ወደ ውኃ ውስጥ እርስዋን የሚጥልበት ጊዜ ነበር እንጨትም ስትፈልጥ በምሳር የሚአቊስልበት ጊዜ ነበር። የፈላ ውኃም በላይዋ የሚያፈሰበት ጊዜ ነበር ነገር ግን ምንም ምን የጐዳት የለም። 

ለደነግሎችም ስታገለግል ብዙ ዘመናት ኖረች ምንም አትታክትም ነበር በምድርም ላይ አትተኛም መላዋን ሌሊት ቁማ በጸሎት ታድር ነበር እንጂ ከገድሏ ጽናትም የተነሣ ደናግሉ እስከሚያደንቁ ድረስ አርባ ቀን ቁማ ትፈጽም ነበር። 

ከዚህም በኋላ ጌታችን በሽተኞችን በማዳን አጋንንትን በማስወጣት የዕውሮችን ዐይን በመግለጥ የአንካሶችንም እግር በማስተካከል ድንቆችንና ተአምራቶችን በእጆቿ ገለጠ። 

ዲያቆናዊት ኢዮኤልያም ለኢዮጰራቅስያ መጸሐፍትንና የምንኵስናንም ሥርዓት አስተማረቻት በሥራም ሁሉ ትሳተፋት ነበር እጅግም ይፋቀሩ ነበር እርሷም ሰማያዊ ሙሽራ ወደአለበት የመንግሥት አዳራሽ የማያልቅ ተድላ ደስታም ወደአለበት ኢዮጵራቅስያን ሲያወጧት ራእይን አየች። 

በነቃችም ጊዜ ለደናግል ነገረቻቸው ወደርሷ ሲሔዱም በትኩሳት በሽታ ታማ አገኟት ስለእነርሱም እንድትጸልይ ለመኑዋት እርሷም ደግሞ በጸሎታቸው እንዲአስቧት ለመነቻቸው ያን ጊዜም ጸሎት አድርጋ መረቀቻቸውና በሰላም አረፈች በእናቷም መቃብር ውስጥ ቀበሩዋት። 

ወዳጅዋ ኢዮኤልያም ወደ መቃብርዋ ሒዳ ጸለየችና በሦስተኛው ቀን አረፈች ከእርሷም ጋር ተቀበረች።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ)
@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5
#ነሐሴ_8

ነሐሴ ስምንት በዚህች ቀን #ቅዱስ_አልዓዛር_ካህን ከሚስቱ እና ልጆቹ ጋር በሰማዕትነት ሞቱ፣ ዳጋ እስጢፋኖስን የመሠረቱት ታላቁ #ጻድቅ_አቡነ_ኂሩተ_አምላክ ዕረፍታቸው ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አልዓዛር_ካህን

ነሐሴ ስምንት በዚች ቀን አልዓዛርና ሚስቱ ሰሎሜ አንኤም አንጦኒኃስ ዖዝያ አልዓዛር አስዮና ስሙና መርካሎስ የሚባሉ ልጆቻቸውም ሰባቱ በሰማዕትነት ሞቱ። 

ይህም አረጋዊ አልዓዛር ከመምህራነ ኦሪት አንዱ ነው እርሱም ለሕዝቡ አለቃና ሊቀ ካህናትም ነው በፈሪሀ እግዚአብሔርም ሁኖ ያስተዳድራቸው ነበር። ከዚህም በኋላ ዳታንና አቤሮን በሙሴና አሮን ላይ እንደተነሡባቸው ከዘመዶቹ ወገን ሦስት ካህናት በእርሱ ላይ ቀንተው ተነሡበት። 

የእሊህም ስማቸው ስምዖን አልፍሞስ መባልስ ይባላል ሹመቱንም እንዲለቅላቸው ፈለጉ ሕዝቡ ግን የአልዓዛር ሹመቱ ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰው አይደለም ብለው ከለከሉአቸው።

ስለዚህም ነገር ወደ ግሪክ አገር ወርደው ንጉሥ አንጥያኮስን አነሳሡት መጥቶም የእስራኤልን መንግሥት እንዲወስድ ቀሰቀሱት። በመጣ ጊዜም ወደ ከተማቸው በተንኮል እንዲገባ አደረጉት።

በገባ ጊዜም ሊቀ ካህናቱ አልዓዛርን ይዞ የእሪያ መሥዋዕትን ለሕዝቡ እንዲሠዋ አዘዘው እምቢ ባለውም ጊዜ ሰባቱን ልጆቹን ገደላቸው። እርሱንና ሚስቱን በእሳት በአጋሉት ብረት ምጣድ ላይ አስተኙአቸው እንዲህም ምስክርነታቸውን ፈጸሙ። 

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ኂሩተ_አምላክ_ዘጣና

ዳግመኛም በዚህች ቀን ዳጋ እስጢፋኖስን የመሠረቱት ታላቁ ጻድቅ አቡነ ኂሩተ አምላክ ዕረፍታቸው ነው፡፡

አቡነ ኂሩተ አምላክ ሰባቱ ከዋክብት ከተባሉት ቅዱሳን አንዱ አቡነ ኂሩተ አምላክ ሲሆኑ እሳቸውም ታላቁን ገዳም ዳጋ እስጢፋኖስን የመሠረቱት ናቸው፡፡ እርሳቸውም የዐፄ ይኩኖ አምላክ የወንድም ልጅ ናቸው፡፡ ከደብረ ሊባኖሱ አቡነ ተክለሃይማኖት ጋር ሆነው በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ከአባ ኢየሱስ ሞዐ ሥርዓተ ምንኩስናን ተምረዋል፡፡ ንጉሡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ለመላዋ ኢትዮጵያ ሊቀ ካህናት፣ አቡነ ኂሩተ አምላክን ደግሞ ዓቃቤ ሰዓት አድርገው ሾሟቸው፡፡

አቡነ ኂሩተ አምላክም በዓቃቤ ሰዓትነት ለጥቂት ጊዜ ካገለገሉ በኋላ በዓለም በመንግሥት ተቀምጦ ከማገልገል ይልቅ ከከተማ ወጥቶ ከሰው ተለይቶ እግዚአብሔርን ማገልግል ይበልጣል በማለት የተቀበሉትን መዓርገ ሢመት ንቀው በመተው አልባሌ መስለው ታቦተ እስጢፋኖስን ከሐይቅ ይዘው መልአክ እየመራቸው ወደ ጣና ባሕር ዳርቻ ደረሱ፡፡ ሁለት ድንጋዮችንም በተረአምራት እንደ ታንኳ አድርገው በመጠቀም ባሕሩን በበትረ መስቀላቸው እየቀዘፉ ዳጋ ወደተባለው ደሴት ገብተው ጥቂት ዕረፍትን አድርገዋል፡፡ እሳቸው ያን ጊዜ ያረፉበት ቦታ ዛሬም ድረስ ‹‹ዓቃቤ ሰዓት›› እየተባለ በመዓርግ ስማቸው ይጠራል፡፡

የጣናን ባሕር እንደ ታንኳ ተጠቅመው የተሻገሩባቸው እነዚያ ሁለት ትላልቅ ድንጋዮችም ዛሬ በገዳሙ ውስጥ የጻድቃን ማረፊያ (ምዕራፈ ጻድቃን) ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ በክብር ተቀምጠው ይገኛሉ፡፡ አቡነ ኂሩተ አምላክ በቦታው ላይ ሥርዓቱን አጽንተው ተጋድሎአቸውን ጨርሰው ነሐሴ 8 ቀን በክብር ዐርፈዋል፡፡

ዳጋ እስጢፋስ ገዳምን ከዐፄ ዳዊት ጀምሮ እስከ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ድረስ የተነሡት ነገሥታት እየተሳለሙት የከበሩ ቅርሶችንና የወርቅ ዘውዳቸውን በስጦታ አበረክተውላታል፡፡ 900 ዓመት ያስቆጠሩ የብራና መጻሕፍትና ሌሎች አስደናቂ ቅርሶች የሚገኙበት ገዳም ነው፡፡ የዐፄ ዳዊት፣ የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ፣ የዐፄ ፋሲልና የሌሎቹም ቅዱሳን ነገሥታት ዐፅም በዚህ ገዳም በክብር ተቀምጦ ይገኛል፡፡ የዐፄ ሱስንዮስም ዐፅም በዚሁ በታላቁ ገዳም ዳጋ እስጢፋኖስ ከብዙ ቅዱሳን ነገስታት ዐፅም ጋር ይገኛል፡፡ ዐፄ ሱስንዮስ የፖርቱጋልን እርዳታ ለማግኘት ሲሉ የካቶሊክን የክህደት እምነት አምነው በሀገራችንም ላይ አውጀው ከ8 ሺህ በላይ ካህናት ምእመናንን ካስገደሉ በኋላ ምላሳቸው ተጎልጉሎ በክፉ አሟሟት ሊሞቱ ሲሉ ልጃቸው ፋሲል ቅዱሳን አባቶችን በመለመን በጸሎታቸው እንዲፈወሱ አድርጓቸዋል፡፡ እነ አቡነ ምእመነ ድንግል እና አቡነ ዓምደ ሥላሴ ጋር በጸሎታቸው የንጉሡን የተጎለጎለ ምላሳቸውን መልሰውላቸው ከሕመማቸውም ፈውሰዋቸዋል፡፡ ‹‹ፋሲል ይንገስ ካቶሊክ ይፍለስ…ተዋሕዶ ይመለስ…የዐፄ ሱስንዮስ ምላስ ይመለስ…እግዚአብሔር ይፍታ›› ሲል ተጎልግሉ የነበረው ምላሳቸው ተመልሰ፡፡ በዚያን ጊዜ ዐፄ ሱስንዮስ ‹‹ብቆይ ዓመት ብበላ ገአት/ገንፎ›› ብለው በመናገር ማላሳቸው እንደቀድሞው ሆነላቸው። ለንስሐ ሞት በቅተው መንግስታቸውን ለልጃቸው አውርሰው በክብር አርፈዋል፡፡ ለዚህም ነው የዐፄ ሱስንዮስ ዐፅም በታላቁ ገዳም ዳጋ እስጢፋኖስ ከብዙ ቅዱሳን ነገስታት ዐፅም ጋር አብሮ መገኘቱ፡፡

አቡነ ኂሩተ አምላክ የጌታችንን ቅዱስ መስቀል ወደ ሀገራችን ለማምጣት ብዙ የደከሙ አባት ናቸው፡፡ ንጉሡ ዐፄ ዳዊት በዘመናቸው ርሀብ ስለነተሳ የዘደብረ ቢዘኑን ታላቁን ጻድቅ አቡነ ፊሊጶስን ከገዳማቸው አስጠርተው ‹‹ምን ባደርግ ይሻለኛል?›› ብለው አማከሯቸው፡፡ እኚህም የዘደብረ ቢዘኑ አቡነ ፊሊጶስ የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብን መወለድ በትንቢት የተናገሩ ናቸው፡፡ ንግሥቲቱ የዐፄ ዳዊት ሚስት የአቡነ ፊሊጶስን እግራቸውን አጥባቸው ስትጨርስ የእግራቸውን እጣቢ በእምነት ጠጣችው፡፡ በዚህም ጊዜ አቡነ ፊሊጶስ ንግሥቲቱን ‹‹ከማኅፀንሽ ፍሬ ታላቅ ጻድቅ ልጅ ይወጣል›› ብለው ትንቢት ከነገሯት በኋላ በትንቢታቸው መሠረት ታላቁ ጻድቅ ንጉሥ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ተወልደዋል፡፡ ዐፄ ዳዊትም በዘመናቸው ስለተነሣው ርሀብ አቡነ ፊሊጶስን ሲያማክሯቸው ጻድቁ ሱባዔ ገብተው በጸሎት ከጠየቁ በኋላ ‹‹የጌታችንን መስቀል ያስመጡ›› ብለው ንጉሡን መከሯቸው፡፡ ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም ከኢየሩሳሌም፣ ከቁስጥንጥንያና ከእስክንድርያ መንግሥታት ጋር ተጻጽፈው ዓሥሩን ታላላቅ የሀገራችንን ቅዱሳን ይዘው ሄደው መስቀሉን መስከረም 10 ቀን አምጥተውታል፡፡ ቅዱስ መስቀሉን ካመጡት ዓሥሩ ታላላቅ ቅዱሳን ውስጥም አንዱ የጣና ደሴቱ አቡነ ኂሩተ አምላክ ናቸው፡፡ የተቀሩት ዘጠኙ ደግሞ የደብረ ቢዘኑ አቡነ ፊሊጶስ፣ የጣና ደሴቱ አቡነ እንድርያስ፣ አቡነ በትረ ማርያም፣ አቡነ ዮሐንስ፣ አቡነ ታዴዎስ፣ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ፣ አቡነ ዘካርያስ፣ አቡነ ያሳይና አቡነ ቶማስ ናቸው፡፡

አቡነ ኂሩተ አምላክ ወደ ግብፅ ሄደው ግማደ መስቀሉን ይዘው ከግብፅ ስለመጡ አንዳንድ ሰዎች ግብፃዊ ናቸው ይሏቸዋል ነገር ግን ለሀገራቸው ለቅድስት ኢትዮጵያ ትልቅ ውለታ የዋሉ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፡፡ የትውልድ ሀገራቸውም ወሎ ልዩ ቦታው መርጦ እንደሆነ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ እና #ከገድላት_አንደበት)
@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5
#ነሐሴ_10

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥር በዚህች ቀን የታላቁ ጻድቅና ገዳማዊ #አባ_ዓቢየ_እግዚእ ዓመታዊ የተአምር በዓል ነው፣ #ቅዱስ_መጥራ በሰማዕትነት ሞተ፣ #ቅዱስ_ሐርስጥፎሮስ በሰማዕትነት ሞተ፣ የከበሩ #ቅዱሳን_ቢካቦስና_ዮሐንስ በሰማዕትነት ሞቱ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አባ_ዓቢየ_እግዚእ_ኢትዮዽያዊ

ነሐሴ ዐሥር በዚህች ቀን የታላቁ ጻድቅና ገዳማዊ አባ ዓቢየ እግዚእ ዓመታዊ የተአምር በዓል ነው። አባ ዓቢየ እግዚእ የተወለዱት በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ትግራይ ተንቤን (መረታ) ውስጥ ነው። የተባረኩ ወላጆቻቸው ያፍቅረነ እግዚእ እና ጽርሐ ቅድሳት ይባላሉ። አጥምቀው "ዓቢየ እግዚእ" ሲሉ ስም ያወጡላቸው የወቅቱ ጳጳስ ሰላማ መተርጉመ መጻሕፍት ናቸው። ትርጉሙም 'በጌታ ዘንድ ታላቅ ሰው' ማለት ነው።

ዓቢየ እግዚእ በሕፃንነታቸው ሌሊት ሌሊት ባሕር ውስጥ ሰጥመው ሲጸልዩ አድረው ቀን ቀን እየተማሩ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቁ። ገና በወጣትነታቸው ወደ ታላቁ መነኮስ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ (ደብረ በንኮል) ሔደው መንኩሰዋል።

በገዳሙ በጾም በጸሎትና በስግደት ተወስነው ከኖሩ በኋላ ወደ ዋልድባ ሔደው የተሰወረች ቤተ ክርስቲያን አግኝተዋል። በጊዜው በአርባ ቀን አንዲት ቅጠል ብቻ ለቁመተ ሥጋ ይበሉ ነበር።

ከዚያም ወደ ሃገራቸው ተንቤን ተመልሰው ዛሬም ድረስ ድንቅ ሆኖ የሚታየውን ገዳም መሥርተው ብዙ መናንያንን አፍርተዋል። ዓቢየ እግዚእ ገዳማዊና ጻድቅ ብቻ ሳይሆን ሐዋርያዊ አባትም ነበሩ። ከትግራይ እስከ ደንቢያ ደግሞ ሃገረ ስብከታቸው ነው።

አንድ ጊዜ ደቀ መዛሙርትን አስከትለው ለስብከት ሲንቀሳቀሱ ተከዜ ወንዝ አካባቢ ደረሱ። ቀኑ ነሐሴ ዐሥር ነውና ተከዜ እስከ ገደፉ ሞልቶ ለሦስት ቀናት ባለመጉደሉ ከአንድ ሺ በላይ ሰዎች ሲያለቅሱ ደረሱ። ጻድቁ በአካባቢው የነበሩት ኢ-አማንያን (አሕዛብ) ቢሆኑም ራርተዋልና "አምላከ ሙሴ" ብለው ጸልየው ወደ ጥልቁ ውስጥ ገቡ።

ቅዱስ ሚካኤል አብሯቸው ነበርና ተከዜ ግራና ቀኝ ተከፍሎ መሃሉ የብስ ሆነ። ይሕን ድንቅ ያዩ ከዘጠኝ መቶ አርባ በላይ አሕዛብም አምነው በጻድቁ እጅ ተጠምቀዋል። ይሕም ዘወትር ነሐሴ ዐሥር ቀን በቤተ ክርስቲያናቸው (ጐንደር) ይከበራል።

ከዚያም እያስተማሩ ጐንደር ደረሱ። ያኔ ጐንደር በቀሃና አንገረብ ወንዞች የታጠረች አንዲት መንደር ነበረች። ጻድቁ ቀን ቀን እየሰበኩ ማታ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናቸው የታነጸበት ሥፍራ ላይ ሲጸልዩ ያድሩ ነበር።

በዚያ ዘመን ጐንደር ውስጥ ጅብ እባብና መሠል አራዊት ገብተው ሕዝቡን ጨረሱት። ይሕንን የተመለከቱት አባ ዓቢየ እግዚእ ወደ እግዚአብሔር አለቀሱ። በፍጹም ልባቸውም ስለ ሕዝቡ ለመኑ። የለመኑትን የማይነሳ ጌታ ወደ ጻድቁ ቀርቦ "በስምሕ የተማጸኑ በቃል ኪዳንህ ያመኑ: በምድር አራዊት አይሠለጥኑባቸውም። በሰማይም እሳትን አያዩም። ጐንደርንም አራዊት ገብተው ሰውን አይጐዱም።" ብሏቸው አርጓል።

አባ ዓቢየ እግዚእ በገዳማቸው ተንቤን ለብዙ ዘመናት በቅድስና ኑረው ሦስት ሙታንን አስነስተው ብዙ ድውያንን ፈውሰው ብሔረ ብጹዓንን ጎብኝተው የድኅነት ቃል ኪዳንም ተቀብለው በመቶ አርባ ዓመታቸው ግንቦት ዐሥራ ዘጠኝ ቀን አርፈዋል። የጻድቁ ክብር ለሁሉ ነውና እናስባቸው።

ይህች ዕለት ባሕረ ተከዜን ከፍለው ሕዝቡን ያሻገሩባት አሕዛብንም ያጠመቁባት ናትና በገዳማቸው ጐንደር ውስጥ በሚገኘው ቤተ ክርስቲያናቸውም ይከበራል።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_መጥራ

በዚህች ቀን በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በቅዱስ ዲሜጥሮስ ዘመንና በከሀዲው ንጉሥ በዳኬዎስ ዘመነ መንግሥት ቅዱስ መጥራ በሰማዕትነት ሞተ። 

ይህም ቅዱስ የክብር ባለቤት ክርስቶስን ክደው ለጣዖት መስገድን የሚያዝ የንጉሡን ደብዳቤ በሰማ ጊዜ ይህ ቅዱስ ወዲያውኑ ሒዶ ከወርቅ የተሠራ የአጵሎንን ክንድ ሰረቀ በየጥቂቱም ሰባብሮና ቆራርጦ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጣቸው። 

የጣዖቱም አገልጋዮች ክንዱ ተቆርጦ አጵሎንን በአገኙት ጊዜ ስለርሱ ብዙዎችን ሰዎች ያዟቸው። በዚያንም ጊዜ ወደ መኰንኑ ቀርቦ ክርስቲያን እንደሆነ በፊቱ ታመነ ሁለተኛም የአጵሎንን የወርቅ ክንድ የወሰድኩ እኔ ነኝ ለድኆችና ለችግረኞችም ሰጠኃ ኋቸው አለው።

መኰንኑም በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ አስጨናቂ የሆነ ታላቅ ሥቃይንም አሠቃየው ከዚህም በኋላ ከእሳት ውስጥ ጨመሩት እግዚአብሔርም አዳነው ያለ ጥፋትም በጤና አወጣው።

ከዚህም በኋላ እጆቹንና እግሮቹን ቆረጡ ብዙ ደም ከአፍንጫው ወደ ምድር እስከ ሚወርድ ዘቅዝቀው በዕንጨት ላይ ሰቀሉት። 

በዚያንም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ ቅዱስ መጥራንን ፈታው ከተሰቀለበትም አውርዶ በመዳሠሥ አዳነው። አንድ ዕውር ሰውም መጣ ከአፍንጫው ከወረደውም ደም ወስዶ ዐይኖቹን ቀባ ወዲያውኑ አየ። መኰንኑም ከማሠቃየቱ የተነሣ በሰለቸ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። የምስክርነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀዳጀ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሐርስጥፎሮስ

በዚህችም ቀን ዳግመኛ በከሀዲ መክስምያኖስ እጅ ቅዱስ ሐርስጥፎሮስ በሰማዕትነት ሞተ። በንጉሥ መክስምያኖስ ፊት በአቆሙት ጊዜ ለአማልክት ሠዋ አለው። የከበረ ሐርስጥፎሮስም እንዲህ ብሎ መለሰለት እኔ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን አመልከዋለሁ ለእርሱም እሠዋለሁ። ንጉሡም ተቆጥቶ ሥጋው ተቆራርጦ በምድር ላይ እስቲወድቅ በበትር ይደበድቡት ዘንድ አዘዘ እንዲሁም አደረጉበት።

ከዚህም በኋላ ወደ ወህኒ ቤት ጣሉት በላህያቸውም እንዲአስቱት ሁለት ሴቶችን ንጉሡ ወደርሱ ላከ ቅዱሱ ግን የክርስቶስን ሃይማኖት አስተማራቸው የዛሬ የሆነ የዚህንም ዓለም ኃላፊነት አስገነዘባቸው ወደ መክስምያኖስም በተመለሱ ጊዜ እንዴት አደረጋችሁ አላቸው። 

እነርሱም እንዲህ አሉት በከበረ ሐርስጥፎሮስ አምላክ የክብር ባለቤት በሆነ በክርስቶስ እኛ እናምናለን ንጉሡም ሰምቶ አንዲቱን በዕንጨት ላይ ሰቅለው እንዲአቃጥሏት ሁለተኛዋን በአንገቷ ደንጊያ አንጠልጥለው ቊልቊል እንዲሰቅሏት አዘዘና ምስክርነታቸውን እንዲህ ፈጸሙ። 

ከዚህም በኋላ ዕንጨቶችን ሰብስበው በማንደጃው ውስጥ አድርገው አነደዱ የከበረ ሐርስጥፎሮስን እጅና እግሩ እንደ ታሠረ ከውስጡ ጨመሩት ያን ጊዜም በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አለ እሳቱ ከቶ ምንም አልነካውም። ሕዝቡም ይህን አይተው የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ዐሥር ሺህ ያህል ሰዎች አምነው በሰማዕትነት ሞቱ።

ሁለተኛም የብረት ሠሌዳዎችን በእሳት አግለው አመጡ ቅዱሱንም በላያቸው በአስተኙት ጊዜ ምንም ምን የነካው የለም። ይህንንም ድንቅ ሥራ አይተው በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃያ ሺህ አንድ መቶ ሰዎችና አርባ ሕፃናት አምነው ምስክር ሁነው ሞቱ። 

ንጉሥ መክስምያኖስም አይቶ እጅግ ተቆጣ የቅዱስ ሐርስጥፎሮስንም ራስ በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ።ከንጉሡም ዘንድ በወጣ ጊዜ ጸሎትን አደረገ ፊቱንም በመስቀል ምልክት አማተበ ከዚህም በኋላ ምስክርነቱን ፈጸመ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_ቢካቦስና_ዮሐንስ

በዚህችም ቀን እስሙናይን ከሚባል አገር የከበሩ ቢካቦስና ዮሐንስ ሌሎችም ከእሳቸው ጋራ በሰማዕትነት ሞቱ። ይህም ቅዱስ ቢካቦስ ክርስቲያን ሲሆን በሥውር ወታደር ሆነ። አንጥያኮስ ለሚባል መኰንንም ስለ ዮሐንስና ስለ ኤጲስቆጶስ አባ አክሎግ ከተርሴስ አገር ስለ ናሕር ስለ አባ ፊልጶስም እነርሱ ክርስቲያኖች እንደሆኑ ነገር ሠሩባቸው።
#ከተራራው ግርጌ

ከቅዱሱ ተራራ ግርጌ ዘጠኙ ደቀ መዛሙርት ተቀምጠዋል፡፡ ነቢዩ “አቤቱ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰውስ ተራራህ ማን ይኖራል” / መዝ.14፥1/ በማለት ጠይቆ ወደ ተቀደሰው ተራራ የሚወጡ ሰዎች ምን ዓይነት ሕይወት ያላቸው ሊሆን እንደሚገባ ሲገልጥ “… በአንደበቱ የማይሸነግል፤ በባልንጀራው ላይ ክፉትን የማያደርግ … በንፁሑ ላይ መማለጃን የማይቀበል ….” በማለት የጠቀሳቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ /መዝ. 14፥1-5/ ወደ ቅድስናው ስፍራ ወጥቶ ምስጢር ለማየት ብቃት ያልነበረው ይሁዳን ለመለየት አምላክ ባወቀ ዘጠኙን ከተራራው ግርጌ አቆይቷቸዋል፡፡
“የኃጥእ ዳፋ ጻድቁን ያዳፋ” የሚል ብሂል አለ፡፡ ይህ አባባል ግን ከተራራዉ ግርጌ ለቀሩት ደቀ መዛሙርት አይሆንም፡፡ ይሁዳን በጥበብ ከምስጢር ለየው እንጂ ጌታ ስምንቱ ደቀ መዛሙርቱን የምስጢሩ ተካፋይ አድርጓቸዋል፡፡ ለጥፋቱ ምክንያት እንዳያገኝ ከምስጢሩ ቢለየኝ ከሞቱ ገባሁበት እንዳይል በጥበብ ይህን አደረገ፡፡ ስምንቱ ደቀ መዛሙርት ግን በንጹሕ ልቡና ከተራራው ግርጌ ተቀምጠውም ምስጢር አልተከለከላቸውም፡፡ ምክንያቱም “ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና” /ማቴ.5/፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ እግዚአብሔርን ለማየት ለሚወዱ “ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚቻለው የለምና” እንዲል፡፡ /ዕብ.11/፡፡

#ሙሴና ኤልያስ ለምን ተመረጡ?

ሙሴንና ኤልያስን ወደ ደብረ ታቦር እንዲመጡ ያደረገበት ምክንያት የባሕርይ አምላክ መሆኑን እንዲመሰክሩ ነው፡፡ ሙሴን ከመቃብር ተነሥቶ ስለጌታችን እንዲህ የሚል ምስክርነት ሰጥቷል፡- “እኔ ባሕር ብከፍልም፤ ጠላት ብገድልም፤ ደመና ብጋርድም፤ መና ባወርድም እስራኤልን ከክፋታቸው መልሼ ማዳን ያልተቻለኝ ደካማ ነኝ፤ የእኔን ፈጣሪ እንዴት ሙሴ ይሉሃል? የሙሴ ፈጣሪ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!” ኤልያስም ደግሞ ከብሔረ ሕያዋን መጥቶ “እኔ ሰማይ ዝናብ እንዳይሰጥ ብለጉም፣ እሳት ባዘንብም፣ እስራኤልን ከክፋታቸው ማዳን የማይቻለን ነኝ እንዴት የእኔን ፈጣሪ ኤልያስ ነህ ይሉሃል? የኤልያስ ፈጣሪ እግዚአብሔር ይበሉህ እንጂ!” ብለው የባሕርይ አምላክነቱን በደብረ ታቦር ላይ መስክረዋል፡፡ በማቴ.16፡14 ላይ “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት።” ይላልና፡፡
ሙሴና ኤልያስ የተመረጡበት ሌላው ምክንያት ሙሴ “ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም” ተብሎ ስለተነገረለት /ዘጸ.33፡23/ ኤልያስ “በኋለኛው ዘመን ምስክሬ ትሆናለህ” ስለተባለ ያንን ለመፈጸም ነው፤ ካገቡት ሙሴን ከደናግል ኤልያስ ያመጣቸው መንግሥተ ሰማያት በሕግ የተጋቡ ሕጋውያንና ሥርዐት ጠብቀው የሚኖሩ ደናግላን እንደሚወርሷት ለማስተማር ሁለቱን መርጧቸዋል፡፡
@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5
#ነሐሴ_13

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ ሦስት #ጌታችን_መድኃኒታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን #በደብረ_ታቦር የገለጠበት ዕለት ነው፣ #የቅዱስ_ሙሴ_ሊቀ_ነቢያት ልደቱ ነው፣ ተጋዳይ #አባ_ጋልዩን አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ደብረ_ታቦር

ነሐሴ ዐሥራ ሦስት በዚች ቀን ክብር ይግባውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅና ክቡር በዓል ነው።

በዚች ቀን መድኃኒታችን ሦስቱን ደቀ መዛሙርቶቹን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ ላይ አወጣቸው። መልኩም በፊታቸው ተለወጠ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ። ስለ እነርሱም ጌታችን የሰው ልጅ በጌትነቱ ሲመጣ እስከሚያዩት ድረስ በዚህ ከቆሙት መካከል ሞትን የማይቀምሱት አሉ አለ።

ሰዎች ሁሉ እርሱ ለሙሴ ጌታውና ከሞት ያስነሣው እንደሆነ ለኤልያስም ፈጣሪው እንደሆነና ካሳረገበትም ያወረደው እርሱ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ እነሆ ከጌታ ከኢየሱስ ጋራ እየተነጋገሩ ሙሴና ኤልያስ ወደርሱ መጡ።
ስለዚህም ጴጥሮስ ጌታችንን እንዲህ አለው አቤቱ በዚህ ትኖር ዘንድ ትወዳለህን ሦስት ሰቀላዎችንም አንድ ላንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ እንሠራ ዘንድ።

በዚህም ቃል የደካማነትና የትሕትና ምልክት አለበት። ደካማነት የተባለ ጴጥሮስ ጌታችን ከሰማይ የወረደበትን ሥራ ትቶ በተራራ ላይ ይኖር ዘንድና ራሱን የሚሠውርበትን ቤት ይሠራለት ዘንድ የተናገረው ነው። ትሕትና ያልነውም ጴጥሮስ ለራሱና ለባልንጀሮቹ ሐዋርያት ቤት ይሠራ ዘንድ ስለ አላሰበ ነው። ራሱንና ባልንጀሮቹ ሐዋርያትን እንደ ባሮች ነቢያትን ደግሞ እንደ ጌቶች አድርጎ አስቧልና።

ሰለ ሐዋርያትም የእውቀት ማነስ አታድንቅ በዚያን ጊዜ ፍጹማን አልሆኑምና። እንዲህም በሚልበት ጊዜ ጌታችን በሰው እጅ የተሠራ ማደሪያን የማይሻ መሆኑን ለጴጥሮስ ያሳየው ዘንድ እነሆ ደመና ጋረዳቸው።

የጌታችንን ጌትነቱን የሚገልጽ በሐዋርያትም ልቡና እምነትን የሚያጸና እንዲህ የሚል ቃል ከደመና ውስጥ መጣ። ይህ የምወደው በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው እርሱንም ስሙት።

ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋራ ሲነጋገሩ ተሰሙ ስለ ርሱ መምጣት የተናገሩትን ትንቢታቸውንም በቸርነቱ አረጋገጠ። ወደ ተራራ ላይ በመውጣቱም ነቢያትና ሐዋርያት ደስ አላቸው።

ሁለተኛም የአብን ቃል በሰሙ ጊዜ ከእነርሱ ሥውር የነበረ የወልድ ዋሕድን በእውነት ሰው መሆን በዚያን ጊዜ ተረዱ ያን ጊዜ የጌትነቱ ክብር ተገልጦአልና። ሐዋርያትም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው የሆነ እርሱ ሙሴን ከመቃብር ያስነሣው ኤልያስንም ያሳረገው አውርዶም ያመጣው እርሱ እንደሆነ አወቁ። ከእርሱ በቀር ማንም ማን የሙሴን መቃብር የሚያውቅ የለምና ከዐሳረገው ከእርሱ በቀር ማንም ማን ኤልያስ ያለበትን የሚያውቅ የለምና። በሰማይና በምድር ሥልጣን ካለው ከሁሉ ጌታ በቀር ሙታንን አድኖ ሊአስነሣቸው ማንም አይችልም።

ደብረ ታቦርም የቤተ ክርስቲያን አምሳል ሆነች ከብሉይና ከሐዲስ በውስጧ ሰብስባለችና። የአብንም ቃል በሰሙ ጊዜ በግምባራቸው ፍግም ብለው በምድር ላይ ወደቁ እንደ ሙታንም ሆኑ። ከዓለም አስቀድሞ ከእርሱ ጋራ በህልውና እንዳለ ለልጁ አብ ምስክርን ሆነ ወዲያውኑ ሙሴ ወደ መቃብሩ ኤልያስም ወደ ቦታው ተመለሱ።

ሐዋርያትንም በአነቃቸው ጊዜ ከብቻው ጌታችን በቀር ማንንም አላገኙም። ከባሕርያችን የተዋሐደና ሥጋችንን የለበሰ ፍጹም አምላክ እንደሆነ በዚህ ሐዋርያት አስተማሩ።

እንግዲህ እናስተውል ሰው ካልሆነ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታቸንን ድንግል ማርያምን በአበሠራት ጊዜ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋራ ነው እንዴት አላት። አምላክ ካልሆነስ ለመንግሥቱ ፍጻሜ የለውም እንዴት አላት። ሰው ካልሆነ በበረት እንዴት አስተኙት። አምላክስ ካልሆነ መላእክት ከሰማይ ወርደው ለእግዚአብሔር በሰማያት ምስጋና በምድርም ሰላም ለሰውም ግዕዛኑ ሊሰጠው እያሉ እንዴት አመሰገኑ።

ሰው ካልሆነ ዮሐንስ በውኃ እንዴት አጠመቀው አምላክስ ካልሆነ አልዓዛርን ከመቃብር እንዴት ሊያስነሣው ቻለ። ይህ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው እንድ ልጅ አካላዊ ቃል እግዚአብሔር እርሱ ያለ መለወጥ ያለ መለየት አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው እንደሆነ እናምንበታለን። እርሱም ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ሁል ጊዜ አንድ ህላዌ ነው ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሙሴ_ሊቀ_ነቢያት

በዚችም ቀን የቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት ልደቱ ነው።

ዓለም በተፈጠረ በ3,600 ዓመት እሥራኤል በረሃብ ምክንያት ያዕቆብ ወደ ምድረ ግብፅ ወረደ:: በዚያም ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ለ215 ዓመታት ተከብረው ለ215 ዓመታት ደግሞ በባርነት በድምሩ ለ430 ዓመታት በምድረ ግብፅ ኑረዋል። በባርነት ዘመናቸውም 'ራምሴና ጋምሴ' የሚባሉ 2 ከተሞችን (ዛሬ ፒራሚዶች የምንላቸውን) በደም ገንብተዋል። ግፋቸው እየበዛ ሲሔድ ግን ጩኸታቸው ቅድመ እግዚአብሔር ደረሰ። ያድናቸውም ዘንድ አንድ ቅዱስ ሰው እንዲወለድ አደረገ። ይኽም ሰው ሙሴ ይባላል።

ወላጆቹ መታመናቸውን በፈጣሪያቸው ያደረጉ ዮካብድና  እንበረም ሲሆኑ ከሌዊ ነገድ ናቸው፡፡ ከሙሴ ውጪም አሮንና ማርያምን ወልደዋል። ቅዱስ ሙሴ በተወለደበት ወራት ወንድ የእሥራኤል ሕጻናት ይገደሉ ነበር። ጌታ ግን በገዳዮቹ ልቡና ርሕራሔን አምጥቶ አትርፎታል።

በተወለደ በ3 ወሩ ወንዝ ላይ ጥለውት ተርሙት (የፈርኦን ልጅ) ወስዳ በቤተ መንግስት አሳድጋዋለች:: ሙሴ ያለችውም እርሷ ናት። 'ዕጓለ ማይ (ከውሃ የተገኘ) ለማለት ነው። ወላጆቹ ያወጡለት ስም ግን 'ምልክአም' ይባላል። ገና ሲወለድ ፊቱ እንደ መልአክ ያበራ ነበርና።

ቅዱስ ሙሴ 5 ዓመት በሆነው ጊዜ ፈርኦንን በጥፊ በመማታቱ ለፍርድ ቀርቦ እሳትን በመብላቱ አንደበቱ ኮልታፋ ሆኖ ቀርቷል። እናቱ ዮካብድ ሞግዚት ሆና ስላሳደገችው 40 ዓመት በሆነው ጊዜ የፈርኦንን ቤት ምቾትና የንጉሥ ልጅ መባልን ናቀ። ቅዱስ ዻውሎስ እንደሚለው በአሕዛብ ቤት ካለ ምቾት ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን ሊቀበል ወዷልና። (ዕብ. 11÷24)

አንድ ቀንም ለዕብራዊ ወገኑ ተበቅሎ ግብጻዊውን ገድሎት ወደ ምድያም ሸሸ። በዚያም ለ40 ዓመታት የካህኑን ዮቶርን በጐች እየጠበቀ ኢትዮዽያዊቱን ሲፓራን አግብቶ ኖረ። ልጆንም አፈራ። 80 ዓመት በሞላው ጊዜ እግዚአብሔር በደብረ ሲና ተናገረው። ሕዝቡንም ከባርነት ቀንበር እንዲታደግ ላከው፡፡ ሙሴም ከወንድሙ ጋር ግብጻውያንን በ9 መቅሰፍት በ10ኛ ሞተ በኩር መታ። እሥራኤልንም ነጻ አወጣ፡፡

ሊቀ ነቢያት የሠራቸው ሥራዎች ተዘርዝረው የሚያልቁ አይደሉም፦ እርሱ ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ ሕዝቡን በደረቅ አሻግሯል፣ ግብጻውያንን ከነሠረገሎቻቸው በባሕር ውስጥ አስጥሟል፣ ለሕዝቡ መና ከደመና አውርዷል፣ ውሃን ከጨንጫ (ከዓለት) ላይ አፍልቁዋል፣ በብርሃን ምሰሶ መርቷቸዋል፣ በ7 ደመና ጋርዷቸዋል፣ ጠላቶቻቸውን ሁሉ ድል ነስቶላቸዋል፣ ቅዱስ ሙሴ ለ40 ዓመታት ሕዝቡን ሲመራ ከእግዚአብሔር ጋር ለ570 ጊዜ ተነጋግሯል።

ከጸጋው ብዛትም ፊቱ ብርሃን ስለ ነበር ሰዎች እርሱን ማየት አይችሉም ነበር። ታቦተ ጽዮንንና 10ሩ ቃላትን ተቀብሎ ጽላቱ ቢሰበሩ ራሱ ሠርቶ በጌታ እጅ ቃላቱ ተጽፈውለታል፡፡ ቅዱስ ክቡር ታላቅ ጻድቅ ነቢይና ደግ ሰው ቅዱስ ሙሴ በ120 ዓመቱ ዐርፎ በደብረ ናባው ሊቃነ መላእክት ቅዱሳን ሚካኤል ገብርኤልና ሳቁኤል ቀብረውታል። መቃብሩንም ሠውረዋል። (ይሁዳ 1÷9)

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ነሐሴ_14

አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
ነሐሴ ዐሥራ አራት በዚህች ቀን የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ በእስክንድርያ ሀገር ድንቅ ተአምርን አደረገ፣ #የአባ_ስምዖንና የወዳጁ #የአባ_የዮሐንስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ሆነ፣  #ቅዱስ_ባስሊቆስ በሰማዕትነት ሞተ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_መስቀለ_ክርስቶስ

ነሐሴ ዐሥራ አራት በዚህች ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእስክንድርያ ሀገር ድንቅ ተአምርን አደረገ። ስለርሱም ከአይሁድ ብዙዎች አምነው በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት በአባ ቴዎፍሎስ እጅ ተጠመቁ እርሱም ለቅዱስ ቄርሎስ የእናቱ ወንድም ነው። ይህም እንዲህ ነው በእስክንድርያ አገር ስሙ ፈለስኪኖስ የሚባል አይሁዳዊ ባለጸጋ ሰው ይኖር ነበር እርሱም እንደ አባቶቹ የኦሪትን ሕግ የሚጠብቅና እግዚአብሔርን የሚፈራ ነው።

ዳግመኛም ሙያተኛዎች ሁለት ድኃዎች ክርስቲያኖች አሉ በአንደኛውም ላይ ሰይጣን የስድብ መንፈስ አሳድሮበት ጓደኛውን ወንድሜ ሆይ ክርስቶስን ለምን እናመልከዋለን እኛ ዶኆች ነን ይህ ክርስቶስን የማያመልክ አይሁዳዊ ፈለስኪኖስ ግን እጅግ ባለጸጋ ነው አለው።

ጓደኛውም እንዲህ ብሎ መለሰለት ዕወቅ አስተውል የዚህ ዓለም ገንዘብ ከእግዚአብሔር የሆነ አይደለም ምንም አይጠቅምም ጥቅም ቢኖረው ጣዖትን ለሚያመልኩ ለአመንዝራዎች ለነፍሰ ገዳዮች ለዐመፀኞች ሁሉ ባልሰጣቸውም ነበር።

አስተውል የከበሩ ነቢያት ድኆች ችግረኞችም እንደነበሩ ሐዋርያትም እንደርሳቸው ችግረኞች እንደነበሩ። ጌታችንም ድኆችን ወንድሞቼ ይላቸው እንደነበረ። ሰይጣን ግን የጓደኛውን ምክር እንዲቀበል ምንም ምን አልተወውም ሃይማኖቱን ምንም ምን አልተወውም ሃይማኖቱን ለውጦ ነፍሱን እስከማጥፋት ድረስ አነሣሣው ቀሰቀሰው እንጂ።

ከዚህም በኋላ ወደ ፈለስኪኖስ ሒዶ በአንተ ዘንድ እንዳገለግል ተቀበለኝ አለው። ፈለስኪኖስም እንዲህ ብሎ መለሰለት በሃይማኖቴ የማታምን አንተ ልታገለግለኝ አይገባም ከቤተ ሰቦቼም ጋራ የማትተባበር ልቀበልህ አይገባኝም። ሁለተኛም ይህ ጐስቋላ ወዳንተ ተቀበለኝ እኔም ወደ ሃይማኖትህ እገባለሁ ያዘዝከኝንም ሁሉ አደርጋለሁ አለው።

አይሁዳዊው ባለጸጋም ከመምህሬ ጋር እስከምማከር ጥቂት ታገሠኝ ብሎ ከዚያም ወደ መምህሩ ሒዶ ድኃው ክርስቲያናዊ ያለውን ሁሉ ነገረው መምህሩም ክርስቶስን የሚክድ ከሆነ ግረዘውና ተቀበለው አለው።

አይሁዳዊውም ተመልሶ መምህሩ የነገረውን ለዚያ ድኃ ነገረው ያም ምስኪን የምታዙኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለ። ከዚህም በኋላ ወደ ምኵራባቸው ወሰደው የምኵራቡም አለቃ በሕዝቡ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ጠየቀው። ንጉሥህ ክርስቶስን ክደህ አይሁዳዊ ትሆናለህን እርሱም አዎን እክደዋለሁ አለ።

የምኵራቡም አለቃ መስቀል ሠርተው በላዩ የክርስቶስን ሥዕል እንዲአደርጉ መጻጻንም የተመላች ሰፍነግ በዘንግ ላይ አሥረው ከጦር ጋራ እንዲሰጡት አዘዘ ከዚያም ከተሰቀለው ላይ ምራቅህን ትፋ መጻጻውንም አቅርብለት ክርስቶስ ሆይ ወጋሁህ እያልህ ውጋው አሉት።

ሁሉንም እንዳዘዙት አድርጎ በወጋው ጊዜ ብዙ ውኃና ደም ፈሰሰ ለረጂም ጊዜም በምድር እየፈሰሰ ነበር በዚያን ጊዜም ያ ከሀዲ ደርቆ እንደ ደንጊያ ሆነ። በአይሁድ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሀት ወደቀባቸው በእውነት የአብርሃም ፈጣሪ ስለእኛ ተሰቅሏል እኛም ዓለምን ለማዳን የመጣ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እርሱ እንደሆነ አመንበት እያሉ ጮኹ።

ከዚህም በኋላ አለቃቸው ከዚያ ደም ወስዶ የአንድ ዕውር ዐይኖችን አስነካው ወዲያውኑ አየ ሁሉም አመኑ ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ ሒደው የሆነውን ሁሉ ነገሩት። ሊቀ ጳጳሳቱም ከካህናቱ ሁሉ ጋራ ተነሣ አባ ቄርሎስ ከእርሱ ጋራ አለ። ወደ አይሁድ ምኵራብም ሒዶ ውኃና ደም ከእርሱ ሲፈስ መስቀሉን አገኘው ከዚያም ደም ወስዶ በግንባሩ ላይ ቀብቶ በረከትን ተቀበለ ሕዝቡንም ሁሉ ግንባራቸውን በመቀባት ባረካቸው።

ያንንም መስቀል አክብረው ተሸክመው እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስደው ያኖሩት ዘንድ አዘዘ። ደም የፈሰሰበትንም ምድር አፈሩን አስጠርጎ ለበረከትና ለበሽተኞች ፈውስ ሊሆን በሸክላ ዕቃ ውስጥ አኖረው።

ከዚህም በኋላ ፈለስኪኖስ ከቤተ ሰቦቹ ሁሉ ጋራ ሊቀጳጳሳት ቴዎፍሎስን ተከተለው ከአይሁድም ብዙዎቹ የቀደሙ አባቶቻቸው በሰቀሉት የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ የክርስትና ጥምቀትንም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው ከእርሱ ጋራ አንድ አደረጋቸው ሥጋውንና ደሙንም አቀበላቸው። ከዚህም በኋላ ለዘላለሙ ክብር ምስጉን የሆነ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ወደየቤታቸው ገቡ። እኛንም ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን በመስቀሉ ኃይል ያድነን አሜን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_አባ_ስምዖንና_አባ_ዮሐንስ

ዳግመኛም በዚህች ቀን የአባ ስምዖንና የወዳጁ የዮሐንስ የዕረፍታቸው መታሰቢያ ሆነ። እሊህ ቅዱሳንም በአማኒው ዮስጦንስ ዘመን መንግሥት የነበሩ ናቸው እሊህም ወንድሞች የከበሩ ክርስቲያን ናቸው።

ከዚህ በኋላ ለከበረ መስቀል በዓል ቅዱሳት መካናትን ሊሳለሙ ወደ ኢየሩሳሌም ሔዱ ሥራቸውንም አከናውነው ወደ አገራቸው ሲመለሱ በፈረሶቻቸው ተቀምጠው ወደ ኢያሪኮ ቀረቡ።

ዮሐንስም በዮርዳኖስ በረሀ ያለውን የመነኰሳቱን ገዳም አይቶ ወንድሙ ስምፆንን ወንድሜ ሆይ ለእሊህ ገዳማት እኮ የእግዚአብሔር መላእክት ይኖራሉ አለው ዮሐንስም ከእርሳቸው ጋራ ከሆን አወን ልናያቸው እንችላለን አለው።

ከዚያም ከፈረሶቻቸውን ወርደው ለሰዎቻቸው ሰጥተው እስከምናገኛችሁ በየጥቂቱ ተጓዙ ብለው እንደሚጸዳዱ መስለው ወደ ዱር ገቡ።

የዮርዳኖስንም ጐዳና ተጒዘው ከሰዎቻቸው በራቁ ጊዜ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ ጸሎት እናድርግ ከእኛም አንዳንችን ወደ መነኰሳቱ ገዳም በምታደርስ ጐዳና ቁመን ዕጣ እንጣጣል እግዚአብሔር ከፈቀደ ዕጣችን ወደ ወጣበት እንሔዳለን።

ከዚህም በኋላ ስምፆን በዮርዳኖስ ጐዳና ቆመ ዮሐንስም ወደ ሀገራቸው በሚወስድ ጐዳና ላይ ቆመ ዕጣውንም በአወጡበት ጊዜ ዮርዳኖስ ጐዳና ላይ ወጣ እጅግም ደስ አላቸውና ስለ ደስታቸው ብዛት እርስ በእርሳቸው ተያይዘው ተሳሳሙ።

አንዱም አንዱ ወደኋላ እንዳይመለስ ስለጓደኛው ይጠራጠርና ይፈራ ነበር አንዱም ሁለተኛውን ይመክረውና ለበጎ ሥራ ያተጋው ነበር።

ዮሐንስ ስለ ስምፆን ይፈራ ነበር ስለ ወለላጆቹ ፍቅር አንዳይመለስ ስምፆንም ስለ ዮሐንስ ይፈራ ነበር እርሱ በዚያ ወራት መልከ መልካም የሆነች ሚስት አግብቶ ነበርና።

ከዚህም በኋላ ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ እንዲህም አሉ በውስጧ እንመነከኵስ ዘንድ ለኛ የተመረጠች ገዳም ደጃፍዋ ክፍት ሆኖ ብናገኝ ምለክት ይሆናል።

የገዳሙም አለቃ ኒቆን የሚሉት በተሩፋት ፍጽም የሆነ ድንቆች ተአምራትን የሚያደርግ ሀብተ ትንቢት የተሰጠጠው ሲሆን በዚያች ሌሊት በጎቼ ይገቡ ዘንድ የገዳሙን በር ክፈተት የሚለውን ራእይ አየ።

ወደርሱም በደረሱ ጊዜ የክርቶስ በጎች ሆይ መምጣታችሁ መልካም ነው አላቸውና ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ተላኩ ሰዎች አድርጎ ተቀበላቸው።

ከዚህም በኋላ አበ ምኔቱን የምንኵስናን ልብስ ያለብሳቸው ዘንድ ለመኑት እነርሱ በቆቡ ላይ የብርሃን አክሊል አድርጎ መላእክትም ከበውት አንዱን መነኰስ አይተዋልና ሰለዚህም ፈጥነው ይመነኵሱ ዘንድ ተጉ።
ከዚያም በማግስቱ አበ ምኔቱ የምንኲስናን ልብስ አለበሳቸው በቀን እንደሚተያዩ በሌሊትም እርስበርሳቸው የሚተያዩ እስቲሆኑ በፊታቸው ላይ የመንፈስ ቅዱስ ብርሃን በራ ሁለተኛም በዚህ መነኵስ ላይ እንደሰዩ በራሶቻቸው ላይ የብርሃን አክሊል አዩ።

ከዚህም በኋላ ከመነኰሳቱ መካከል ተለይተው ወደ በረሀ ይገቡ ዘንድ ኀሳብ መጣባቸው። በዚያችም ሌሊት ብርሃንን የለበሰ ሰው ለአበ ምኔቱ ተገልጾ የክርስቶስ በጎች እንዲወጡ የገዳሙን በር ክፈት አለው በነቃም ጊዜ ወደ በሩ ሒዶ ተከፍቶ አግኝቶት እያዘነና እየተከዘ ሳለ ሊወጡ ፈለገው እሊህ ቅዱሳን መጡ በፊታቸውም በትረ መንግስትን አየ።

በአያቸውም ጊዜ ደስ ብሎት ተገናኛቸው እነርሱም በልባቸው ያሰቡትን ነግረውት እንዲጸልይላቸው ለመኑት ለረጅም ጊዜም አለቀሰ ከዚህም በኋላ ፊቱን ወደ ምሥራቅ መልሶ በቀኙና በግራው አቆማቸው እጆቹንም ወደ ሰማይ ዘርግቶ ጸሎት አድርጎ ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቃቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር አደራ አስጠበቃቸው።ከዚያም በፍቅር አሰናበታቸው።

ከዚህም በኋላ አርጋኖን ወደ ምባል ወንዝ ሔዱ በዚያም አንድ ገዳማዊ በዚያን ወራት ያረፈ በውስጡ የኖረበትን በዓት አገኙ በውስጡም ያ ሽማግሌ ገዳማዊ ሲመገበው የነበረ ለምግባቸው የሚያስፈልጋቸውን የእህል ፍሬዎችን አገኙ ምግባቸውን በአዘጋጀላቸው በእግዚአብሔርም እጅግ ደስ አላቸው።

በድንግያ ውርወራ ርቀት መጠን አንዱ ከሁለተኛው የተራራቁ ሁነው ሰፊ በሆነ ተጋድሎ ቡዙ ዘመናት ኖሩ። ሰይጣንም ቡዙ ጊዜ ይፈታተናቸው ነበር ግን አባታቸው ቅዱስ ኒቅዮስ በራእይ ወደ እሳቸው መጥቶ ስለ እነርሱ ይጸልያል ተኝተውም ሳሉ የዳዊትን መዝሙር ያስተምራችዋል በነቁም ጊዜ ያስተማራቸውን ሁሉ በትክክል ያነቡታል እጅግም ደስ ይላቸዋል።

አምላካዊ ራእይም ተሰጣቸው ተአምራትንም ያደርጋሉ በዚያችም በረሀ የክብር ባለቤት በሆነ በክርስቶስ ኃይል ሰይጣንን ድል እስከ አደረጉት ድረስ የቀኑን ሐሩር የሌሊቱን ቊር ታግሠው ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነሩ።

ከዚህም በኋላ ስምዖን ወንድሙ ዮሐንስ እንዲህ አለው በዚህ በረሀ በመኖራችን ምን እንጠቃማለን ና ወደ አለም ወጥተን ሌሎችን እንጥቀማቸው እናድናቸውም ዮሐንስም መልሶ እንዲህ አለው ወንድሜ ሆይ ይህ ኀሳብ ከሰይጣን ቅናት የተነሣ ይመስለኛል።

ስምዖን እንዲህ አለው ከሰይጣን አይደለም በዓለም ላይ እንድዘበትበት እግዚአብሔር አዞኛልና ነገር ግን ና እንጸልይ ያን ጊዜም በአንድነት ጸለዩ ልብሳቸውንም እስከ አራሱት ድረስ እርስበርሳቸው ተቃቅፈው አለቀሱ። ከዚህም በኋላ ስምዖን እስከሚሞትባት ቀን ሥራውን ይሠውርለት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እየጸለየ ጎዳናውን ተጓዘ።

ወደ ዓለምም ገብቶ ራሱን እንደ እብድ አደረገ እብዶችንም የፈወሰበት ጊዜ አለ እሳትን በእጁ የሚጨብጥበትም ጊዜ አለ። ከዚህም በኋላ ከከተማው በር የሞተ ውሻ አግኝቶ በመታጠቂያውም አሥሮ እየጐተተ እንደሚጫወት ሆነ ሰዎች እስከሚሰድቡትና እስከሚጸፉት ድረስ።

በአንዲት ቀን እሑድ ከቅዳሴ በፊት የኮክ ፍሬ ይዞ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ መቅረዞችንም ሰበረ።ሴቶችንም መትቶ ከእርሳቸው ጋራ እንደሚተኛ ጐተታቸው ባሎቻቸውም ደበደቡት።

ዕረፍቱም ሲቀርብ የእግዚአብሔር መልአክ የእርሱንም የወንድሙ የዮሐንስንም የዕረፍታቸውን ጊዜ ነገረው ወደ ወይን ሐረግ ሥር ገብቶ ከወንድሙ ዮሐንስ ጋራ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ባስሊቆስ

በዚህችም ቀን ቅዱስ ባስሊቆስ በሰማዕትነት ሞተ። በእሥር ቤትም እርሱ ሳለ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦለት እንዲህ አለው የምስክርነትህ ፍጻሜ ደርሷልና ሒደህ ዘመዶችህን ተሰናበታቸው።

ከዚህም በኋላ ወታደሮችን ከእርሱ ጋራ ወደ ቤቱ ይሔዱ ዘንድ ለመናቸው ሒደውም ወደ ቤቱ ገቡ እናቱንና ዘመዶቹንም ተሰናበታቸው። በማግሥቱም የከበረ ባስሊቆስን ወደ ፍርድ ሸንጎ አቀረቡትና በሁለት ምሰሶዎች መካከልም አሥረው ሲደበድቡት ዋሉ በእግሮቹም ችንካሮችን አደረጉበት ደሙም በምድር ላይ ፈሰሰ ያየው ሁሉ አለቀሰለት።

ከዚህም በኋላ ከደረቀ ዕንጨት ላይ አሠሩት ዕንጨቱም በቀለና ቅርንጫፍና ቅጠሎችን አወጣ።ሰዎችም የልብሱን ጫፍ ለመንካት የሚጋፉ ሆኑ በበሽተኞችና በዚህ ዕንጨት ላይ ያደረገውን ተአምር አይተዋልና።

ከዚህም በኋላ ዋርሲኖስ ወደሚባል አገር በመርከብ ወሰዱት ወታደሮችም እንዳትሞት እህልን ብላ አሉት እርሱም እኔ ከሰማያዊ መብል የጠገብኩ ነኝ ምድራዊ መብልን አልመርጥም አላቸው።

ወደ መኰንኑም በአቀረቡት ጊዜ ለአማልክት መሥዋዕትን አቅርብ አለው የከበረ በስሊቆስም እኔ አንድ ለሆነ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የምስጋና መሥዋዕትን አቀርባለሁ አለው።

ሁለተኛም ወደ ጣዖታቱ ቤት እንዲአስገቡት አዘዘ እርሱም ቁሞ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ያን ጊዜ እሳት ወርዶ ጣዖታቱን አቃጠላቸው መኰንኑም ፈርቶ ሸሽቶ ወደውጭ ወጣ። ቁጣንም ተመልቶ ይገድሉት ዘንድ ያ መኰንን አዘዘ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ባስሊቆስ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ መከራውን ይሳተፍ ዘንድ ስለ አደለውም አመሰገነው።

ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡት ብዙዎችም መላእክት ነፍሱን ሲያሳርጓት አዩዋት ጌታችን ኢየሱስም ወዳጄ ባስሊቆስ ወደ እኔ ና እኔ የምዋሽ አይደለሁም ተስፋ ያስደረግሁህን እፈጽምልሃለሁ ብሎ ጠራው። እንዲህም ተጋድሎውን ፈጸመ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ)
@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5