መዝገበ ቅዱሳን
18.6K subscribers
1.91K photos
9 videos
5 files
25 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
ገብርኄር
Forwarded from 🟢ናታኒም ፖሮሞሽን🟢
🔹 ✥● ከሚከተሉት ውስጥ ቅድስት ሃገራችን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ከሚለው መጠርያ ስሟ ሌላ በየትኛው ትጠራ ነበር?? ✥●
† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †

እንኳን አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

† ሚያዝያ 6 †

=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህች ዕለት እነዚህን ታላላቅ ቅዱሳን ታስባለች:-

† ቅድስት ማርያም ግብፃዊት †

† በዚች ቀን በበረሀ የምትኖር ግብፃዊት ማርያም አረፈች። ይቺም ቅድስት ከእስክንድርያ አገር ሁና ወላጆቿ ክርስቲያን ናቸው። እድሜዋ አስራ ሁለት አመት በሆናት ጊዜ የመልካም ስራና የሰው ሁሉ ጠላት ሸንግሎ አሳታት በእርሷም የማይቆጠሩ የብዙዎችን ነፍስ አጠመደ እርሱ ሰይጣን ስለ ዝሙት ፍቅር ያለ ዋጋ ስጋዋን እስከ መስጠት አድርሷታልና ።

በዚህም በረከሰ ስራ ውስጥ ኖረች በየእለቱም የኃጢአት ፍቅር በላይዋ ይጨመርባት ነበር። ሰውን የሚወድ የእግዚአብሄርም ቸርነት ወደ ክብር ባለቤት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ሊባረኩ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ የሚሹ ሰዎችን ገለጠላት።

ከእሳቸውም ጋራ ትሄድ ዘንድ ልቧ ተነሳሳ ከብዙ ሰዎችም ጋራ በመርከብ ተሳፈረች። ባለ መርከቦችም የመርከብ ዋጋ በጠየቋት ጊዜ ስለ መርከብ ዋጋ ያመነዝሩባት ዘንድ ሰውነቷን ሰጠቻቸው ኢየሩሳሌምም እስከ ደረሰች ይህን ስራ አልተወችም።

የክብረ ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ወደ አለች ቤተ ክርስቲያን ትገባ ዘንድ በወደደች ጊዜ መለኮታዊት ኃይል መግባትን ከለከለቻት። እርሷም ከሚገቡ ሰዎች ጋራ ትገባ ዘንድ ብዙ ጊዜ ደከመች ነገር ግን ከለከላት እንጂ የጌታ ኃይል አልተዋትም።

ከዚህም በኃላ ስለ ረከሰ ስራዋ አሰበች በልቧም እያዘነችና እየተከዘች ወደ ሰማይ ወደ እግዚአብሄር አይኖቿን አቀናች በማንጋጠጥዋም ውስጥ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ስእል አየች።

በፊቷም አለቀሰች ፍጥረቶችን ሁሉ የምትረጅአቸው አምላክን የወለደሽ እመቤቴ ተዋሽኝ ከሁሉ ሰዎች ጋራ ገብቼ የመጣሁበትን ስራዬን የፈፀምኩ እንደሆነ ያዘዝሽኝን ሁሉ እኔ አደርጋለሁ ብላ በማመን ለመነቻት።

ቤተ ክርስቲያን ፈጥና ገባች በገባችም ጊዜ የበአሉን ስራ ፈፀመች። ከዚህም በኃላ አምላክን ወደ ወለደች ወደ እመቤታችን ወደ ከበረች ድንግል ማርያም ስእል ተመልሳ ወደ እርሷ መሪር ልቅሶ እያለቀሰች ረጅም ፀሎትን ፀለየች ነፍሰዋን ለማዳን እርስዋ ወደ ወደደችው ትመራት ዘንድ አምላክን ከወለደች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ስእል ከዮርዳኖስ በረሀ ብትገቢ አንቺ እረፍትንና ድኀነትን ታገኚ አለሽ የሚል ቃል ወጣ።

ከእመቤታችን አምላክን ከወለደች ከቅድስት ድንግል ማርያም ስእል ይህን ቃል ተቀብላ ወድያውኑ ወጣች። በውጪም አንድ ሰው አግኝታ ሁለት ግርሽ ሰጣትና አምባሻ ገዛችሸት።

ከዚያም በኃላ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግራ ፅኑእ ተጋድሎ እየተጋደለች በበረሀው ውስጥ አርባ ሰባት አመት ኖረች ሰይጣንም አስቀድማ በነበረችበት በዝሙት ጦር ይዋጋት ነበር።

እርሷ ግን በተጋድሎ ፀናች ከዚያም ከገዛችው አምባሻ ብዙ ቀን ተመገበች። ሁለት ሁለት ቀን ሶስት ሶስት ቀን ፁማ ከዚያ አምባሻ ጥቂት ትቀምስ ነበር በአለቀም ጊዜ የዱር ሳር ተመገበች።

በዚያችም በዮርዳኖስ በረሀ እየተዘዋወረች አርባ አባት አመት ሲፈፀምላት እንደ ገዳሙ ልማድ የከበረች አርባ ፆምን ሊፈፅም ቅዱስ ዘሲማስ ወደዚያች በረሀ መጣ። በሱ ደብር ላሉ መነኲሳት ልማዳቸው ስለሆነ በየአመቱ ወደ በረሀ ወጥተው የከበረች የአርባ ቀን ፆም እስከ ምትፈፀም በፆምና በፀሎት ተፀምደው በገድል ይቆያሉ ።

ስለዚህም ዘሲማስ ወደ ዮርዳኖስ በረሀ በወጣ ጊዜ የሚፅናናበትን ያሳየው ዘንድ እግዚአብሄርን ለመነው። በበረሀውም ውስጥ ሲዘዋወር ይቺን ቅድስት ሴት ከሩቅ አያት የሰይጣን  ምትሀት መሰለችው በፀለየም ጊዜ ከሰው ወገን እንደሆነች ተገለጠለችለት።

ወደርሷም ሄደ እርሷ ግን ከእርሱ ሸሸች ወደርሷም ይደርስ ዘንድ ከኃላዋ በመሮጥ ተከተሉት። ከዚህም በኃላ ዘሲማስ ሆይ ከእኔ ጋራ መነጋገር ከፈለግህ ጨርቅን በምድር ላይ ጣልልኝ እከለልበት ዘንድ ብላ በስሙ ጠራችው።

በስሙ በጠራችውም ጊዜ እጅግ አድንቆ ጨርቁን ጣለላት ያን ጊዜም ለብሳ ሰገደችለት እርሱም ሰገደላት እርስበርሳቸውም ሰላምታ ተሰጣጥተው በላዩዋ ይፀልይላት ዘንድ ለመነችው እርሱ ካህን ነውና ካህን ሰለሆነ።

ከዚህም በኃላ ገድሏን ታስረዳው ዘንድ ቅዱስ ዘሲማስ ለመናት ከእርሷ የሆነውን ሁሉ ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ነገረቸው። እርሷም በሚመጣው አመት የክብር ባለቤት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስጋውንና ደሙን ከእርሱ ጋራ ያመጣላት ዘንድ ለመነችው እርሱም እሺ አላት።

አመትም በሆነ ጊዜ ስጋውንና ደሙን በፅዋ ውስጥ ያዘ ደግሞ በለስ ተምርንና በውኃ የራሰ ምስርን ይዞ ወደርሷ ወደ ዮርዳኖስ በረሀ መጣ ቅድስት ማርያምን በዮርዳኖስ ወንዝ ዳር ስትሄድ አያት ወደርሱም ደርሳ እርስበርሳቸው ሰላምታ ተሰጣጡ በአንድነትም ፀለዩ ከዚህም በኃላ ስጋውንና ደሙን አቀበላት።

በለሱን ተምሩንና ምስሩንም አቀረበላትና ትመገብለት ዘንድ ለመናት ስለ በረከት ከምስሩ በእጇ ጥቂት ወሰደች። ደግሞም በሁለተኛው አመት ወደእርሷ ይመለስ ዘንድ ለመነችው ።ሁለተኛ አመትም በሆነ ጊዜ ወደዚያ ወደ ዮርዳኖስ በረሀ መጣ ያቺ ቅድስት ሴት ሙታ አገኛት በራስጌዋም ድኀዪቱን ግብፃዊት ማርያምን ከተፈጠረችበት አፈር ውስጥ ቅበራት የሚል ፅሁፍ አገኘ።ከፅሁፉ ቃልም የተነሳ አደነቀ።

ያን ጊዜም ከግርጌዋ አንበሳን ሲጠብቃት አየ እርሱ መቃብርዋን በምን እቆፍራለሁ ብሎ ያስብ ነበር በዚያም ጊዜ ያ አንበሳ በጥፍሮቹ ምድሩን ቆፈረ የከበረ ዘሲማስም በላይዋ ፀሎት አድርጎ ቀበራት ።

ወደ ገዳሙም ተመልሶ ለመነኮሳቱ የዚችን የከበረች ግብፃዊት ማርያምን ገድሏን እንዳስረዳችው ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ነገራቸው እጅግም አደነቁ ምስጉን ልኡል እግዚአብሄርንም አመስገኑት። መላው እድሜዋም ሰማንያ አምስት ሆኗታል።

ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ †

በዚች እለት የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሳኤው ሳምንት ለሀዋርያው ቶማስ ተገለጠለት በእጆቹና በእግሮቹ ውስጥ የችንካሮቹን ምልክትም አሳየው የቶማስንም እጅ ይዞ በመለኮታዊ ጉኑ ውስጥ አኖረውና በጦር የተወጋበትን ቦታ አሳየው ቶማስም  ጌታዬና ፈጣሪዬ መነሳትህን አመንኩ አለ።

ጌታችንም ብታየኝ አመንከኝ የሚመሰገንስ ሳያየኝ የሚአምንብኝ ነው ብሎ መለሰለት። በትርጓሜ ወንጌልም እንዲህ ይላል ቶማስ በመድኀኒታችን ጐን ውስጥ እጁን በአስገባ ጊዜ እጁ በመለኮት እሳት ተቃጠለ ፣በመለኮቱም ደግሞ በታመነ ጊዜ እጁ ከመቃጠል ዳነች ።

" አባታችን አዳም "

=>አባታችን አዳም የመጀመሪያው ፍጥረት (በኩረ ፍጥረት) ነው:: አባታችን አዳም:-

*በኩረ ነቢያት
*በኩረ ካኅናት
*በኩረ ነገሥትም ነው::
*በርሱ ስሕተት ዓለም ወደ መከራ ቢገባም ወልድን ከዙፋኑ የሳበው የአዳም ንስሃና ፍቅር ነው::

+አባታችን ለ100 ዓመታት የንስሃ ለቅሶን አልቅሷል:: ስለዚህ አባታችን አዳም ቅዱስ ነው:: ከሌሎቹ ቅዱሳን ቢበልጥ እንጂ አያንስም::

+ለአባታችን አዳም የተናገርነው ሁሉ ለእናታችን ሔዋንም ገንዘቧ ነው:: ዛሬ የሁለቱም የዕረፍታቸው መታሠቢያ ነው::

=>አባታችን ቅዱስ ኖሕም ከላሜሕ የተወለደው በዚሁ ቀን ነው::
=>አምላካችን እግዚአብሔር ለሰማይ ለምድሩ በቅድስናቸው ከከበዱ ወዳጆቹ በረከትን ያድለን::=>ሚያዝያ 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱሳን አዳምና ሔዋን (የዕረፍታቸው መታሠቢያ)
2.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት (ልደቱ)
3.አባታችን ቅዱስ ኖኅ (ልደቱ)
4.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ (የጌታችንን ጐኑን የዳሰሰበት)
5.ቅድስት ማርያም ግብፃዊት (ከኃጢአት ሕይወት ተመልሳ በፍፁም ቅድስናዋ የተመሠከረላት እናት)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
2.እናታችን ሐይከል
3.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
4.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
5.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
6.ቅድስት ሰሎሜ
7.አባ አርከ ሥሉስ
8.አባ ጽጌ ድንግል
9.ቅድስት አርሴማ ድንግል

=>+"+ እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ: ስለ ሶምሶንም: ስለ ዮፍታሔም: ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም: ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና::

እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ:: ጽድቅን አደረጉ:: የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ:: የአንበሶችን አፍ ዘጉ:: የእሳትን ኃይል አጠፉ:: ከሰይፍ ስለት አመለጡ:: ከድካማቸው በረቱ:: በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ:: የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ:: +"+ (ዕብ. 11:32-35

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
✝️ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላክ✝️

=>ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- "እግዚአብሔር ለዳዊት በእውነት ማለ: አይጸጸትም::" (መዝ. 131:11) አሁን በእግዚአብሔር መጸጸት ኑሮበት አይደለም:: ቅዱስ ዳዊት የማያጸጽት ፍጹም ወዳጅ መሆኑን ሲገልጥ ነው እንጂ:: ጌታ ቅዱስ ዳዊትን "እንደ ልቤ የሆነ: ፈቃዴን የሚፈጽም: ባሪያየን ዳዊትን አገኘሁት" (መዝ. 88:20) ብሎ ሲናገር ሰምተን እጅግ አደነቅን::

+እንደ አምላክ ልብ ሆኖ መገኘት ምን ይረቅ?! ምንስ ይደንቅ?! ለዚህ አንክሮ ይገባል !! ጌታ ይቀጥልና ደግሞ "ዳዊትን እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልሁ" (መዝ. 88:35) ይላል:: አቤት አባታችን ዳዊት ክብር: የክብር ክብር: ውዳሴና ስግደትም ላንተ በጸጋ ይገባል እንላለን::

+ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ዳዊት 7 ሃብታት ሲኖሩት:-
1.ሃብተ ትንቢት
2.ሃብተ መንግስት
3.ሃብተ ክህነት
4.ሃብተ በገና (መዝሙር)
5.ሃብተ ፈውስ
6.ሃብተ መዊዕ (ድል መንሳት)
7.ሃብተ ኃይል ተብለው ይታወቃሉ::

+በ7ቱ ስሞቹም:-
1.ጻድቅ
2.የዋህ
3.ንጹሕ
4.ብእሴ እግዚአብሔር
5.ነቢየ ጽድቅ
6.መዘምር እና
7.ልበ አምላክ ተብሎ ይጠራል::

+"+ ልደት +"+

=>ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ስለ ልደቱ ሲናገር "እስመ ናሁ በኃጢአት ተጸነስኩ-በኃጢአት ተጸነስኩ" ይላል (መዝ. 50:5) አበው እንደ ነገሩን የቅዱስ ዳዊት አባት ደጉ እሴይ ከነገደ ይሁዳ የኢዮቤድ ልጅ ነው::

+ሚስቱን ሰሊብን አንድ ጐልማሳ በዝሙት ዐይን ሲፈልጋት ተመልክቶ ነበር:: አንድ ቀንም መንገድ ሔድኩ ብሎ ግን ያንን ጐልማሳ መስሎ ተመልሶ አብሯት አድሯል:: በዚያች ሌሊትም ቅዱስ ዳዊት ተጸንሷልና እንዲህ ብሏል::

+"+ ዕድገት +"+

=>ቅዱስ ዳዊት ከሕጻንነቱ ጀምሮ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ነበር:: ሕጸን ሳለ በእረኝነት በጐቹን አያስነካም ነበር:: አንበሳውን በጡጫ: ድቡን በእርግጫ: ነብሩን በሩጫ የያዙትን ያስጥላቸው ነበር:: በጥቂቱ በበግ እረኝነት ስለ ታመነ ለእሥራኤል እረኛ ሊሆን ተመርጧል::

+"+ መቀባት +"+

+እግዚአብሔር ሳዖልን ከናቀው በሁዋላ ከእሴይ ልጆች መካከል "እንደ ልቤ የሆነውን ቀብተህ አንግስልኝ" ቢለው ነቢዩ ሳሙኤል ቤተ ልሔም ገብቷል::

+በዚያም ከኤልያብ እስከ አሚናዳብ: 7ቱን የእሴይን ልጆች ቢፈትን አልሆነም:: በቅዱስ ሚካኤል ጠቁዋሚነት ግን ከእረኝነቱ ዳዊት ተጠራ:: ገና ከርቀት ሲመጣ የዘይት ቀርኑ ቦግ ብሎ ተከፈተ::

+በቅዱስ ዳዊት ራስ ላይም እንደ እሳት ፈላ:: በአምላክ ምርጫም በ12 ዓመቱ ንጉሥ ተባለ::

+"+ ዳዊትና ጐልያድ ++

=>ኢሎፍላውያን በጠላትነት በተነሱባቸው ጊዜም ጐልያድ የሚሉት የጌት ሰው እሥራኤልን ሲያስጨንቅ ለ40 ቀናት ቆይቶ ነበር:: ለአምላኩ ስምና ክብር የሚቀና ቅዱስ ዳዊት ግን በድፍረት ገጥሞ በፈጣሪው ኃይል: በጠጠር ጥሎታል:: ከእሥራኤልም ሽሙጥን አርቁዋል:: ግን ቅዱሱ ብላቴና: ጐልያድ ደግሞ 6 ክንድ (3 ሜትር) የሚረዝም ሰው ነበር::

+"+ ስደት +"+

=>ቅዱስ ዳዊት ንጉሥ እንዲሆን ተቀብቶ ዙፋን አልጠበቀውም:: ጠላታቸውን ጥሎ ስላዳናቸው ፈንታ: ሳዖልን በገና እየደረደረ ስለ ፈወሰው ፈንታም ሊገደል ተፈለገ:: ፈጣሪው ከእርሱ ጋር ባይሆንም ይገድሉት ነበር::

+እርሱ ግን ለ18 ዓመታት በትእግስት ተሰደደ:: ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ጠላቱን ሳዖልን አሳቻ ሥፍራ ላይ አግኝቶ በምሕረት ተወው:: በዚህ የዋሕነቱም በብሉይ ሆኖ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ" የምትለውን ሕግ ፈጸማት:: (ማቴ. 7:45, መዝ. 16:4)

+"+ ንግሥና +"+

=>ቅዱስ ዳዊት የስደት ዘመኑ ሲፈጸም ሳዖል ሞተ:: ምን ጠላቱ ቢሆን 'የሳዖል ገዳይ ነኝ' ያለውን ተበቀለ:: ስለ ጠላቱም አለቀሰ:: 30 ዓመት ሲሆነው ነግሦ ለ7 ዓመታት በኬብሮን: ለ33 ዓመታት በኢየሩሳሌም (ጽዮን) ሕዝበ እግዚአብሔርን ጠብቁዋል::

+በዘመኑም ጠላቶቹን ሁሉ ድል አድርጉዋል:: በልጁ አቤሴሎም እጅ መሰደድን: በሳሚ ወልደ ጌራ መሰደብንም ታግሷል::

+"+ ንስሃ +"+

=>ቅዱሱ ንጉሥ ሁሉ ነገር የተሰጠው አባት ነው:: ሁሉ ሕይወቱም ለእኛ ት/ቤት ነው:: ሰው ነውና የኦርዮን ሚስት ቀምቶ: ኦርዮን አስገድሎ ነበር:: ጉዳዩን ነቢዩ ናታን በምሳሌ ሲነግረው ፍጹም ተጸጸተ::

+ማቅ ለብሶ: አመድ ነስንሶ አለቀሰ:: መሬትንም በእንባው ክንድ አራሳት:: ሐረግ እስከ ማብቀልም ደረሰ:: እግዚአብሔርም ንስሃውን ተቀብሎ ከፍ ከፍ አደረገው:: በንስሃ ለምትገኝ ጸጋም ምሳሌ ሆነ::

+"+ ነቢይነት +"+

=>በቤተ ክርስቲያን ትምሕርት ቅዱስ ዳዊትን የሚያህል ነቢይ (ምሥጢር የበዛለት) አልተገኘም:: 'ከዓለም በፊት እንዲህ ነበረ' ብሎ: ከዚያ ከስነ ፍጥረት እስከ ዳግም ምጽዓት የተናገረ እርሱ ነው::

+ስለ መላእክት: ነቢያት: ሐዋርያት: ጻድቃን: ሰማዕታት: ደናግልና መነኮሳት ሁሉ መናገሩ ይደነቃል:: ስለ ድንግል ማርያምና ስለ መድኃኒታችን ክርስቶስም አምልቶ: አስፍቶ ተናግሯል:: 150 ምዕራፎች ባሉት መጽሐፈ ትንቢቱ ኃላፍያትንና መጻዕያትን ተመልክቷል::

+ስለዚህም አበው:-
"አልቦ ምስጢር ወአልቦ ትንቢት:
ዘኢተናገረ አቡነ ዳዊት" ይላሉ::

+"+ መዝሙር +"+

=>ቅዱሱ ነቢይና ንጉሥ በጣም የሚታወቀው በዝማሬው ነው:: ለራሱ ባለ 10 አውታር : ለመዘምራኑ ደግሞ ባለ 8 አውታር በገናን አዘጋጅቶ ፈጣሪውን ያመሰግን ነበር:: 24 ሰዓት ሙሉ ስብሐተ እግዚአብሔር እንዳይቁዋረጥ 288 መዘምራንን በአሳፍ መሪነት መድቦ ነበር::

+ራሱም በፍጹም ተመስጦ: ማር ማር እያለው እግዚአብሔርን ያመሰግነው ነበር:: "ቃልህ ለጉረሮየ ጣፋጭ ነው" እንዲል:: (መዝ. 118:103) የዳዊት መዝሙሩ ለአጋንንት ትልቅ ጠላት ነው:: ቅዱሳን መላእክትም በዳዊት መዝሙር ይዘምራሉ::
"በዘቦቱ ይሴብሑ ሰማያውያን ወምድራውያን" እንዲል::

+"+  #‎ዳዊትና  ጽዮን +"+

=>ቅዱስ ዳዊት ጽዮንን አንጾ ጽላተ ኪዳኑን አመጣ:: ለአምላከ ያዕቆብ ማደሪያን ሊፈልግም ዐይኑ ከእንቅልፍ ተከለከለ:: (መዝ. 131:2) የፈጣሪውን ፈቃድ ሊጠይቅ ሱባኤ ቢገባ "አኮ አንተ ዘትነድቅ ሊተ ቤተ - አንተ ሳትሆን የሚሠራልኝ ልጅህ ነው" አለው::

*አያይዞም የምሥጢረ ሥጋዌን ነገር ቢገልጥለት "ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ - እነሆ በኤፍራታ ሰማነው" ሲል ተናግሯል:: (መዝ. 131:6) የኪዳኑ ጽላት (ጽዮን) ከአቢዳራ ቤት ስትመጣ ከዙፋኑ ወርዶ: ከተራው ሕዝብ ጋርም ተቀላቅሎ በበገናና በመሰንቆ ተጫወተ::

*ስለ ፈጣሪው ክብሩን ተወ:: ከዳን እስከ ቤርሳቤህ የሚገዛ ኃያል ንጉሥ ነበርና:: በጽዮን ፊት እየወደቀ: እየተነሳ: እየታጠቀ: እየፈታ ሲዘምርም ሚስቱ ሜልኮል ናቀችው:: እግዚአብሔር ግን ከፍ ከፍ አደረገው:: (ሳሙ. 6:16)

+"+ ክብረ  #‎ዳዊት  +"+

=>እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲል ኢየሩሳሌምን ብዙ ጊዜ ታድጉዋል:: ሰሎሞንና ሕዝቅያስን (ነገሥታቱን) ይቅር ያላቸው ስለ ባለሟሉ ስለ ዳዊት ነው::

*የሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያዋ ቃል "የዳዊት ልጅ . . . " የምትል ናት:: (ማቴ. 1:1) ጌታችን "ወልደ ዳዊት" መባልን ወዷልና:: እንዲያውም ራሱ "እኔ የእሴይ ሥርና የዳዊት ዘር ነኝ" ሲል ተናግሯል:: (ራዕ. 22:16)

+"+ ዕረፍት +"+=>ነቢየ ጽድቅ: ልበ አምላክ ቅዱስ #ዳዊት እሥራኤልን ለ40 ዓመታት መርቶ አረጀ:: 'ምነው ያ ኃያል የእግዚአብሔር ሰው ቶሎ አረጀ?' ቢሉ ከገድሉ ጽናት ሰውነቱ ተቀጥቅጦ ነበርና::
*በዚያውም ላይ አንድ ቀን ስለ ሕዝበ አሥራኤል ቤዛ ይሆናቸው ዘንድ በቀሳፊ መልአክ ፊት ቆሞ ነበርና (ዜና. 21:16) ሰውነቱ ደከመ:: በዚህ ጊዜም ልጁን ሰሎሞንን አንግሦ በ70 ዓመቱ ከክርስቶስ ልደት ሺህ ዓመት በፊት ዐርፏል::

+"+ #ዳዊት በሰማይ +"+

=>በራዕየ ጐርጐርዮስ እንደ ተጻፈው ቅዱስ ዳዊትን በሰማይ 99ኙ ነገደ መላእክት ከበውት ያመሰግናል:: ከርሱ ዝማሬ ግርማ የተነሳ የሰማያት ግዘፋቸው ይናወጻል:: በገድለ አቡነ ኪሮስ እንደ ተጻፈው ደግሞ ቅዱሳን ነፍሳቸው ከሥጋቸው የምትለየው በዳዊት በገና ጣዕመ ዝማሬ ነው::

*በነገረ ማርያም ትምሕርት ደግሞ የቅዱስ ዳዊት ቤቱ ከልዑል አምላክ መንበር ሥር ነው::

*እንግዲህ ምን እላለሁ! ስለ ቅዱስ ዳዊት ከዚህም በላይ መጻሕፍት ብዙ ይላሉ:: ክብሩ ታላቅ ነውና::

<< በእውነት . . . በእውነት . . . በእውነት . . . ያለ ሐሰት ለዳዊት ክብርና ምስጋና ይገባል >>

=>+"+ እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ: ስለ ሶምሶንም: ስለ ዮፍታሔም: ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም: ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና::

እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ:: ጽድቅን አደረጉ:: የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ:: የአንበሶችን አፍ ዘጉ:: የእሳትን ኃይል አጠፉ:: ከሰይፍ ስለት አመለጡ:: ከድካማቸው በረቱ:: በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ:: የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ:: +"+ (ዕብ. 11:32-35

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †††

††† እንኩዋን ለጻድቅ ሰው "ቅዱስ ኢያቄም" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †††

+*" ቅዱስ ኢያቄም "*+

=>ቅዱስ ሰው ኢያቄም የሰማይና የምድር ንግስት እመቤታችን ድንግል ማርያም አባት ነው:: ቅዱሱ ከቅስራ አባቱ የተወለደ የቅዱስ ዳዊት ዘመድ ሲሆን "ኢያቄም : ሳዶቅ እና ዮናኪር" በሚባሉ 3 ሰሞቹ ይታወቃል::

+ቅዱስ ኢያቄም እንደ ኦሪቱ ሥርዓት አድጎ : ከነገደ ሌዊ የተወለደች : የማጣትና ("ጣ" ጠብቆ ይነበብ) ሔርሜላን ልጅ ሐናን አግብቷል:: ሁለቱም በንጽሕናና በምጽዋት እንደ ሕጉ ቢኖሩም መውለድ የማይችሉ መካኖች ነበሩ::

+በዚሕ ምክንያት ከወገኖቻቸው ሽሙጥን ታግሰው በታላቅ ሐዘን ኑረዋል:: ከጊዜ በሁዋላ ግን ስም አጠራሯ የከበረ : ደም ግባቷ ያማረ ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔር መረጣቸውና ከተባረከ ሰውነታቸው ድንግል ማርያምን ወለዱ::

+እርሷ "ወላዲተ አምላክ" ተብላ እነርሱን "የእግዚአብሔር የሥጋ አያቶች" አሰኘቻቸው:: ቅዱስ ኢያቄም እመቤታችንን ቤተ መቅደስ ካስገቡ ከጥቂት ዓመታት በሁዋላ በመልካም ሽምግልና አርፎ ከቅድስት ሐና ጋር በጌቴሴማኒ ተቀብሯል::

+ቅዱሱ ሰው ያረፈበት ዓመት ግልጽ ባይሆንም ድንግል እመቤታችን 8 ዓመት ሲሞላት 2ቱም ቅዱሳን ወላጆቿ በሕይወተ ሥጋ እንዳልነበሩ አበው ነግረውናል:: በማረፍ ደግሞ ቅድስት ሐና ትቀድማለች:: መቃብሩ ዛሬ ድረስ አለ:: ያደለው ከቦታው ደርሶ ይሳለመዋል::

=>አምላካችን ከቅዱስ ኢያቄም በረከት ያሳትፈን::

=>ሚያዝያ 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ኢያቄም (የድንግል ማርያም አባት)
2.ቅዱስ አጋቦስ ሰማዕት
3.ቅድስት ቴዎድራ ሰማዕት
4.ቅዱስ አባ መቅሩፋ ጻድቅ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
2.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
3.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
4.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
5.አባ ባውላ ገዳማዊ
6.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
7.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)

=>+"+ መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው::
ከያዕቆብ ድንኩዋኖች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል::
የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ በአንቺ የተደረገው ነገር ድንቅ ነው . . .
ሰው እናታችን ጽዮን ይላል::
በውስጥዋም ሰው ተወለደ::
እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት:: +"+ (መዝ. 86:1-6)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
እንኩዋን ለቅዱሳት ደናግል ዓመታዊ የሰማዕትነት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" ቅዱሳት ደናግል "*+

=>ቅዱሳት ደናግሉ አጋሊዝ (አጋሊስ): ኢራኒና ሱስንያ ይባላሉ:: በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ አካባቢ ተሰሎንቄ የምትባል ሃገር ውስጥ ይኖሩ ነበር:: ሦስቱም እጅግ ቆንጆዎችና ከብዙ ወንዶች ዐይን የሚገባ መልክ ቢኖራቸውም የእነርሱ ምርጫ ግን ሰማያዊ ሙሽርነት ነበርና በጾምና በጸሎት ተወሰኑ::

+ለብዙ ዓመታትም ደናግሉ በሚኖሩበት ደብር ውስጥ በቅድስና ኑረዋል:: ከቆይታ በሁዋላ ያ የመከራ ዘመን (ዘመነ ሰማዕታት) ሲመጣ ለጊዜውም ቢሆን ወደ በርሃ ሸሽተው ተቀመጡ::

+ያሉበትን ቦታ የምታውቅ አንዲት ደግ ባልቴት እየሔደች ትጎበኛቸው : በእጃቸው የሚሠሩዋቸውን የተለያዩ እቃወችንም እየሸጠች እኩሉን በስማቸው መጽውታ በተረፈው ለራት የሚሆን ደረቅ ቂጣ ትገዛላቸው ነበር::

+አንድ ቀን ግን አንድ አረማዊ ሰው ተከትሏት መጥቶ በማየቱ 3ቱንም ደናግል ወደ ከሐዲው ንጉሥ አቀረባቸው:: ንጉሡ ሃይማኖታቸውን ቢክዱ የሐብትና የስልጣን ተስፋ እንዳላቸው ነገራቸው:: ደናግሉ ግን በፍቅረ ክርስቶስ በመጽናታቸው ከብዙ ስቃይ በሁዋላ በዚሕች ቀን አስገድሏቸዋል::

=>የጌታችን በጐ ምሕረቱ በሁላችን ትደርብን:: ከደናግሉ በረከትን ያሳትፈን::

=>ሚያዝያ 8 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱሳት ደናግል አጋሊዝ: ኢራኒና ሱስንያ
2."150" ቅዱሳን ሰማዕታት (ፋርስ (ኢራን) ውስጥ የተሰየፉ)
3.አባ ጢሞቴዎስ ሊቀ ዻዻሳት

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
2.ኪሩቤል (አርባዕቱ እንስሳ)
3.አባ ብሶይ (ቢሾይ)
4.አቡነ ኪሮስ
5.አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን
6.ቅዱስ ማትያስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)

=>+"+ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ: ወይስ ጭንቀት: ወይስ ስደት: ወይስ ራብ: ወይስ ራቁትነት: ወይስ ፍርሃት: ወይስ ሰይፍ ነውን?
'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን:: እንደሚታረዱ በጐች ተቈጠርን'
ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው::
በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን:: +"+ (ሮሜ. 8:35-38)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

https://t.me/zikirekdusn
††† እንኳን ለብጹዐን ጻድቃን: ቅዱስ ዞሲማስ እና አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ብጹዐን ጻድቃን †††

††† በዚህ ቀን ብሔረ ብጹዐን ውስጥ የሚኖሩ ጻድቃን ይታሠባሉ::
በሃይማኖት ትምሕርት 5 ዓለማተ መሬት አሉ:: እነሱም አቀማመጣቸው ቢለያይም ከላይ ወደ ታች:-
1.ገነት (በምሥራቅ)
2.ብሔረ ሕያዋን (በሰሜን)
3.ብሔረ ብጹዐን (ብሔረ - አዛፍ - እረፍት) {በደቡብ}
4.የእኛዋ ምድር (ከመሐል) እና
5.ሲዖል (በምዕራብ) ናቸው::

††† ከእነዚሕ ዓለማት ባንዱ የሚኖሩ የብሔረ ብጹዐን ጻድቃን:-
*ኃጢአትን የማይሠሩ::
*ለ1,000 ዓመታት የሚኖሩ::
*ሐዘን የሌለባቸው::
*በዘመናቸው 3 ልጆችን ወልደው (2 ወንድና አንድ ሴት) ሁለቱ ለጋብቻ: አንዱን ለቤተ እግዚአብሔር አገልግሎት የሚያውሉ ሰዎች ናቸው::

††† ቅዱሳኑ ወደዚሕ ቦታ የገቡት በነቢዩ ኤርምያስ እና በቅዱስ እዝራ ዘመን ሲሆን አንዴ የተወሰኑት በዘመነ ሰማዕታት ወጥተው በዚሕ ቀን ተሰይፈዋል::

††† በመጨረሻ ግን በሐሳዌ መሲሕ ዘመን ወጥተው ሰማዕትነትን ይቀበላሉ::

††† የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረቱና ይቅርታው ለምናምን ሁሉ ይደረግልን:: ከደግነታቸውም በረከትን አይንሳን::

+*" አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ "*+
=>አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ አባታቸው መልአከ ምክሩ :
እናታቸው ወለተ ማርያም ይባላሉ፡፡ የተወለዱበት ልዩ
ቦታው ወሎ ክፍለ ሀገር ዳውንት ነው፡፡ በተወለዱ ዕለት
ተነስተው በእግራቸው ቆመው ሦስት ጊዜ "ስብሐት ለአብ
: ስብሐት ለወልድ : ስብሐት ለመንፈስ ቅዱስ" ብለው
አመስግነዋል፡፡
+የስማቸው ትርጓሜ "የአብ : የወልድ : የመንፈስ ቅዱስ
እስትንፋስ" : አንድም "የክርስቶስ እስትንፋስ" ማለት ነው፡፡
ቅዱስ ሚካኤል እየጠበቃቸውና በመንገዳቸው ሁሉ
እየመራቸው ነው ያደጉት፡፡ መንፈስ ቅዱስ ልቡናቸውን
ብሩህ አድርጎላቸው በ5 ዓመታቸው የቅዱሳት መጽሐፍት
ቃላትን፣ ብሉያትንና ሐዲሳትን፣ ድርሳናትንም ጠንቅቀው
ዐውቀዋል፡፡
+በተወለዱ በ14 ዓመታቸው ወደ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ
ደብረ ሐይቅ ገዳም ሄደው ከባሕር ዳር ቆመው የሙሴን
ጸሎት ወደ እግዚአብሔር በጸለዩ ጊዜ የታዘዘ መልአክ
መጥቶ ባህሩን አሻግሯቸው ወደ ቤተክርስቲያን
ገብተዋል፡፡ ለ3 ዓመትም በኃይቅ ገዳም ለመነኮሳት
እንጨት በመልቀምና ውሃን በመቅዳት : ለአባቶች
መነኮሳት ምግብ ሊሆናቸው ከባህር ውስጥ አሳን
በማውጣት አገልግለዋል፡፡
+አባታችን እስትንፋሰ ክርስቶስ 40 መዓልትና 40 ሌሊት
ከጾሙ በኋላ ምንም እህል ሳይቀምሱ ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ አስቀድሞ ለሙሴ በደብረ ሲና እንደሰጠው
ለአባታችንም ወደ እርሳቸው መጥቶ ዓሥሩን ቃላተ ኦሪትና
ስድስቱን ቃላተ ወንጌል በውስጣቸው የተጻፈባቸው ሁለት
ጽላቶችን ሰጥቷቸዋል፡፡
+አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ከሠሩ በኋላ
ዕለቱን ስንዴ ዘርተው፣ ወይን ተክለው፣ ጽድን ወይራንና
ግራርን ተክለው በአንዲት ቀን ለቤተ ክርስቲያን
አገልግሎት ዕለቱን አድርሰዋል፡፡ ስንዴውን ለመስዋዕት
ወይኑን ለቁርባን በታምራት አድርሰዋል፡፡
+አባታችን በጸሎት ላይ እንዳሉ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል
ተልኮ መጥቶ አባታችንን በደመና ጭኖ ወስዶ ከጌታችን
ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ፊት አቆማቸው፡፡
ጌታንም በቅዱሳኖቹ ሁሉ እንዲባረኩ ካደረጋቸው በኋላ
መልአኩን ‹‹ወደ ተወለድኩባትና ወደ ኖርኩባት ቦታ ወደ
ኢየሩሳሌም አድርሰው›› ብሎት ኢየሩሳሌምን አሳልሞ
ሀገራችን መልሶ አምጥቷቸዋል፡፡ ሁሉንም የኢትዮጵያን
ቅዱሳት ገዳማትንም ተዘዋውሮ ሲጎበኙ በሕይወተ ሥጋ
የሌሉት የየገዳማቱ ቅዱሳን ሁሉ በአካል ይገለጡላቸው
ነበር፡፡
+ጎጃም ውስጥ እያስተማሩ፣ እያጠመቁ፣ የታመሙትን
እየፈወሱ፣ የዕውራንን ዐይን እያበሩና ሙታንን እያስነሱ
ብዙ ካገለገሉ በኋላ ለዘጠኝ ዓመታት በባሕር ውስጥ
ገብተው ቁልቁል ተዘቅዝቀው ለኢትዮጵያ ጸልየው
የምሕረት ቃልኪዳን ተቀብለዋል፡፡ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ
ጌታችን መጥቶ ‹‹ከመነኮሳት ሁሉ ብልጫ ያለህ ወዳጄ
እስትንፋሰ ክርስቶስ ሆይ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን
ምሬልሃለሁ ከዚህች ባሕር ውጣ›› በማለት በሞት
የሚያርፉበትን ቦታ ነግሯቸዋል፡፡
+ጻድቁ ወደ ደብረ አስጋጅ በሚሄዱበት ጊዜ ጸሐይ
ልትገባ ስትል ‹‹በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም
አውግዤሻለሁ፡፡ ለመስፍን ኢያሱ በገባኦን እንደቆምሽ
አሁን ቀጥ ብለሽ ቁሚ›› ብለው ገዝተው ፀሐይን
አቁመዋል፡፡
+አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስም ደብረ አስጋጅ ሲደርሱ
ፀሐይ አፍ አውጥታ ‹‹አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ሆይ እገባ
ዘንድ ፍታኝ›› ስትላቸው ‹‹እግዚአብሔር ይፍታሽ›› ባሏት
ጊዜ ጠልቃለች፡፡ ጻድቁ ሌላው በእጅጉ የሚታወቁበት
አንድ ትልቅ ቃል ኪዳን አላቸው፡፡
+በአምላክ ፣ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ፣
በቅዱስ ሚካኤልና በቅዱስ ገብርኤል ልቡና የሚገኝ እንደ
መልክአ ኢየሱስ ያለች እጅግ አስገራሚ ጸሎት አለቻቸው፤
እርሷን ጸሎት በጸለዩ ጊዜ እልፍ ነፍሳትን ከሲኦል
ያወጣሉ፡፡ ጸሎቷም የመድኃኔዓለምን የሰውነት ክፍሎች
በሙሉ እየጠቀሰች እያንዳንዱ የሰውነት ክፍሎቹ
የተቀበሉትን ጸዋትዎ መከራዎች ሁሉ ታዘክራለች፡፡
በእያንዳንዱ ክፍልም የጸሎት ማሳረጊያ አቡነ ዘበሰማያት
ይደግማሉ፡፡
+ንስሓ የገባ ኃጢአተኛ ሰው እንኳን ቢሆን ይህችን የአቡነ
እስትንፋሰ ክርስቶስን ጸሎት በጸለየ ጊዜ ሺህ ነፍሳትን
ከሲኦል እንደሚያወጣ ጌታችን በማይታበል ቃሉ
ለአባታችን ነግሯቸዋል፡፡ እያንዳንዱን የመድኃኔ ዓለምን
የሰውነት ክፍሎች በሙሉ እየጠቀሰች መከራዎቹን
የምታዘክረውን ይህቺን በአምላክ ልቡና ያለች ግሩም
የሆነች ጸሎት "ነፍሳትን ከሲኦል አታወጣም" ብሎ
የሚጠራጠር ቢኖር ግን መንግስተ ሰማያትን አያያትም፡፡
+ጻድቁ አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ታህሳስ 9 ቀን ተወልው
ሚያዝያ 9 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፈዋል፡፡ (ገድለ አቡነ
እስትንፋሰ ክርስቶስ)
=>አምላከ ቅዱሳን በጻድቁ አማላጅነት ሃገራችንን
ይጠብቅልን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::

††† ሚያዝያ 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱሳን የብሔረ ብጹዐን ጻድቃን
2.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ ጻድቅ (ኢትዮዽያዊ)
3.ቅዱስ ዞሲማስ ገዳማዊ (ብሔረ ብጹዐንን ያየ እና ዜናቸውን የጻፈ አባት)
4.ቅዱስ ኤስድሮስ ሕጻን ሰማዕት (ገና በ10 ወር ዕድሜው ሰማዕት የሆነ)
5.አባ ሱንቱዩ ሊቀ ዻዻሳት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ኁሉ አባት)
2."318ቱ" ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
3.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮዽያዊ)

††† "ስለዚህ የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁና በመጠን ኑራችሁ: ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ የምታገኙትን ጸጋ ፈጽማችሁ ተስፋ አድርጉ:: እንደሚታዘዙ ልጆች ባለ ማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ:: ዳሩ ግን 'እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ' ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ::" †††
(1ዼጥ. 1:13-15)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
†††  እንኳን ለአባ ይስሐቅ ጻድቅ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አባ ይስሐቅ ጻድቅ †††

††† ጻድቁ ግብጻዊ ሲሆኑ የነበሩት በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: በጊዜው ዝነኛ ከነበሩት ከታላቁ አባ ዕብሎ (ቅዱስ ዕብሎይ) ተምረዋል:: መማር ብቻ ሳይሆንም ለ25 ዓመታት ያለ መታከት በተልዕኮ አገልግለዋል::

በእነዚህ ጊዜያትም ትሕርምትን : ተጋድሎን : ትምህርተ ቅድስናንና ሌሎች አስፈላጊ መንፈሳዊ ስንቆችን ሰንቀዋል:: በመታዘዛቸው በምድር አበውን : በሰማይ እግዚአብሔርን አስደስተዋል:: በዚህም ከእግዚአብሔር ጸጋውን : ከአበው ምርቃትን አትርፈዋል::

ጊዜው ደርሶም ታላቁ ዕብሎ ሲያርፉ አባ ይስሐቅ በዓት ለይተው ደንበኛውን ተጋድሎ ጀምረዋል:: አምላካቸውን ለማስደሰትና በቅድስና ለመዝለቅም የአርምሞ ሰው ሁነዋል:: ለሚገባው ነገር ካልሆነ በቀር አያወሩም:: ምላሽም አይሰጡም:: "ለምን?" ሲባሉ
1."ለሁሉም ጊዜና ቦታ አለው::"
2."ሰው በከንቱ በማውራቱ ከጸጋ እግዚአብሔር ይርቃል" ይሉ ነበር::

አባ ይስሐቅ የክርስቶስ መድኃኒታችንን ሕማማት ለማዘከር ሁሌ ያነቡ (ያለቅሱ) ነበር:: ቅዳሴ ሲያስቀድሱ እጃቸው የሁዋሊት ታስሮ ነበር:: ቅዱሱ ሰው ለአዝማናት እንዲህ ተመላልሰው በመልካም ዕርግና ያረፉት በዚህ ቀን ነው::

††† አምላከ ቅዱሳን ከበረከታቸው አይለየን::

††† ሚያዝያ 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ይስሐቅ ገዳማዊ (የታላቁ ዕብሎይ ደቀ መዝሙር)
2.አባ ገብርኤል ሊቀ ዻዻሳት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
2.ቅዱስ ኒቆላዎስ ዘሃገረ ሜራ
3.ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ጻድቅ ንጉሥ
4.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
5.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
6.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
7.ቅዱስ ዕፀ መስቀል

††† "የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ: የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ በእግዚአብሔር አብ ተወደው: ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ:
ምሕረትና ሰላም: ፍቅርም ይብዛላችሁ::
ወዳጆች ሆይ! ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኩዋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ::" †††
(ይሁዳ. 1:1)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††