መዝገበ ቅዱሳን
25.3K subscribers
1.97K photos
9 videos
6 files
26 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
Forwarded from Josy Quality Button
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስንት መልእክታትን ጽፏል??
Forwarded from 💎Super📣ፕሮሞሽን
መላእክት ቁጥር አላቸዉ
Forwarded from Quality button
የዐቢይ ጾም ሦስተኛ ሳምንት ምን በመባል ይጠራል?
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† እንኩዋን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልዓዛርን ከሞት ላስነሳበት ደግ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ †††

+*" ሐዋርያ ቅዱስ አልዓዛር "*+

=>ከቀናት በፊት ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ አልዓዛር አረፈ ብለን ነበር:: ለስም አጠራሩ ስግደት: ክብር: ጌትነት ይድረሰውና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ አልዓዛር ባረፈ በአራተኛው ቀን ወደ ቢታንያ ደረሰ::

+ማርታ ቀድማ ወጥታ ከእንባ ጋር ተቀበለችው::
"አዳም ወዴት ነህ" ያለ (ዘፍ. 3:10) የአዳም ፈጣሪ "አልዓዛርን ወዴት ቀበራችሁት" አለ:: ቸርነቱ: ባሕርዩ ያራራዋልና ማርያም ስታለቅስ ባያት ጊዜ አብሮ አለቀሰ::

+ከዚያም በባሕርይ ስልጣኑ "አልዓዛር! አልዓዛር!" ብሎ አልዓዛርን አስነሳው:: ይሕች ተአምርም በአይሁድ ዘንድ ግርምት ሆነች:: ለጌታም የሞት ምክንያት አደረጉዋት:: ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ እንዲህ ታስተምራለች::
(ዮሐ. 11:1-ፍጻሜው)

+ቅዱስ አልዓዛር ጌታችን ካስነሳው በሁዋላ በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ (ቁጥሩ ከ72ቱ አርድእት ነውና) : ለ40 ዓመታት ወንጌልን አስተምሮ : በ74 ዓ/ም አካባቢ ቆዽሮስ ውስጥ አርፏል::

=>የጌታችን ቸርነቱ : የአልዓዛር በረከቱ ይድረሰን::

=>መጋቢት 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አልዓዛር ጻድቅ ሐዋርያ (የጌታ ወዳጅ)
2.ቅድስትና ብጽዕት ሰማዕት አስጠራጦኒቃ (ከታላላቅ ሰማዕታት አንዱዋ)
3.ቅዱሳን ሰማዕታት (የቅ/አስጠራጦኒቃ ማሕበር)
4.እናታችን ቅድስት ጽጌ-ሥላሴ (ኢትዮዽያዊት)
5.ቅዱስ አስቃራን ሰማዕት
6.አባ ሚካኤል ሊቀ ዻዻሳት

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሊቀ ሠራዊት (ሰማዕት)
2.ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
3.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
4.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
5.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
6.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት

=>+"+ ጌታ ኢየሱስም 'ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን?' አላት . . . ይሕንም ብሎ በታላቅ ድምጽ 'አልዓዛር ሆይ ወደ ውጭ ና' ብሎ ጮኸ:: የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ:: ፊቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበረ:: ጌታ ኢየሱስም 'ፍቱትና ይሂድ ተውት' አላቸው:: +"+ (ዮሐ. 11:40-44)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
Forwarded from 🟢ናታኒም ፖሮሞሽን🟢
🧗የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ቤተ ክርስቲያን ላይ -
ከትናንት እስከ ዛሬ


     🔺 𝒔𝒖𝒃𝒔𝒄𝒓𝒊𝒃𝒆 𝒏𝒐𝒘🔺‌‌
🤗ኦርቶዶክሳዊ ዝማሬ🤗
❤️በናታኒም ቲዩብ❤️
👳🏽‍♂ በግሩም እና በተወዳጅ ዘማሪያን ይቀርባል ከታች
ባለው ሊንክ ሰብስክራቭ በማድረግ ቤተሰብ ይሁኑ።
         👇🏽👇🏽
https://youtu.be/PYhgHxupzLI?si=pQaqogjyjDUcNXW
https://youtu.be/PYhgHxupzLI?si=pQaqogjyjDUcNXW
✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡
አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞  እንኩዋን ለጌታችን "ኢየሱስ ክርስቶስ" ዓመታዊ በዓልና ለእመቤታችን "ቅድስት ድንግል ማርያም" ወርኀዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*" ቅዱሱ ቤተሰብ እና ጌታ "*+

=>ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና የዓለም ሁሉ ጌታ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚች ቀን ወደ ቢታንያ ሔዶ: እነ ቅዱስ አልዓዛርና ቤተሰቦቹ እንግድነት ተቀብለውታል::

+በዚያም ቅድስት ማርታ በጌታ ፊት ስታገለግል: ቅዱስ አልዓዛር ከጌታ ጐን ተቀምጦ: ቅድስት ማርያ በ300 ዲናር የገዛችውን ሽቱ በጌታ ላይ አፈሰሰች:: እግሩንም በጠጉሯ አበሰች:: (ዮሐ. 12:1)

+ለዛ የተባረከ ቤተሰብም ታላቅ በረከት ሆነ:: በርግጥም ድንቅ ነው:: ጌታን በቤት ማስተናገድ ፍፁም መታደል ነው::

=>ዳግመኛ በዚህ ቀን ይሁዳ በ300 ዲናሩ ሽቱ አመካኝቶ በጌታ ላይ አንጎራጎረ:: አይሁድ ደግሞ አልዓዛርን ይገድሉት ዘንድ ተማከሩ:: ምክንያቱም ጌታችን በርሱ ላይ የሠራትን ድንቅ እያዩ ከአይሁድ ወገን ብዙዎቹ ያምኑ ነበርና::

=>ቤተ አልዓዛርን የባረከ ጌታ በቸርነቱ የኛንም ይባርክርልን::

=>መጋቢት 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱሱ ቤተሰብ (አልዓዛር: ማርያና ማርታ)
2.አባታችን ላሜኅ (የማቱሳላ ልጅ-የጻድቁ ኖኅ አባት)
3.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሰማዕት
4.ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሰማዕት

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም
2.አበው ጎርጎርዮሳት
3.አቡነ ምዕመነ ድንግል
4.አቡነ አምደ ሥላሴ
5.አባ አሮን ሶርያዊ
6.አባ መርትያኖስ ጻድቅ

=>+"+ የወንድማማች መዋደድ ይኑር:: እንግዶችን መቀበል አትርሱ:: በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና:: ከእነርሱ ጋር እንደታሰረ ሆናችሁ እስሮችን አስቡ:: የተጨነቁትንም ራሳችሁ ደግሞ በሥጋ እንዳለ ሆናችሁ አስቡ:: +"+ (ዕብ. 13:1)

✞✞✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✞✞
††† እንኳን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ በዓለ ሆሳዕና በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ጥንተ በዓለ ሆሳዕና †††

††† "ጥንተ በዓል" ማለት በዓሉ : ተአምሩ (የማዳን ሥራው) የተፈፀመበት የመጀመሪያው ቀን ማለት ነው:: በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሆሳዕና ጀምሮ እስከ ዸራቅሊጦስ ድረስ ያሉ ዐበይት በዓላትን ሁለት ጊዜ ታከብራለች::
1ኛው. "ጥንተ በዓል" ሲሆን
2ኛው. ደግሞ "የቀመር በዓል" ይሠኛል::
መሠረቱ የቅዱሳን ሐዋርያት ቀኖና እና የአባታችን የድሜጥሮስ መንፈሳዊ ቀመር ነው::

ስለሆነም ዓለም ከተፈጠረ በ5,534 ዓመት : የዛሬ 1,974 ዓመት : ልክ በዛሬዋ ቀን (መጋቢት 22) ስም አጠራሩ ከፍ ከፍ ይበልና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ትሕትና በአህያዋና በውርንጫዋ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም (ቤተ መቅደስ) ገብቷል::

ታላቅ የምስጋና መስዋዕትም ከመላዕክት : ከሐዋርያት : ከሕጻናት : ከአረጋውያን : ከፀሐይ : ከጨረቃ : ከከዋክብት : ከቢታንያ ድንጋዮች . . . በአጠቃላይ ከፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ቀርቦለታል:: ጌትነቱንም በገሃድ ገልጧል::

††† ከበዓሉ በረከት ይክፈለን:: እኛንም ለጣዕመ ምስጋናው የተዘጋጀን ያድርገን::

††† መጋቢት 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱሳን ሐዋርያት : ንጹሐን አርድእትና ቅዱሳት አንስት (የጌታችን 120 ቤተሰቦች)
2.ቅዱስ ቄርሎስ መንፈሳዊ (የቅድስት ሃገር ኢየሩሳሌም ዻዻስ የነበረ : ንጽሕናው የተመሠከረለት አባት ሲሆን በ381 ዓ/ም በቁስጥንጥንያ ከተሠበሠቡ 150 ቅዱሳን ሊቃውንት አንዱ ነው:: ብዙ ድርሳናትንም ጽፏል:: )

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
3.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
4.አባ እንጦንዮስ (አበ መነኮሳት)
5.አባ ዻውሊ የዋህ

††† "አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ:: አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ እልል በዪ:: እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው:: ትሑትም ሆኖ በአህያም: በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል::" †††
(ዘካ. 9:9)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
† እንኳን ለጻድቁ አባታችን ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ዓመታዊ በዓለ ፅንሰት በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያዊ †††

††† ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዐይን ናቸው:: ጻድቁን መንካት የቤተ ክርስቲያንን ዐይኗን መጠንቆል ነው::

ተክለ ሃይማኖት እንደ ሊቃውንት ሊቅ: እንደ ሐዋርያት ሰባኬ ወንጌል: እንደ ሰማዕታት ብዙ ግፍ የተቀበሉ: እንደ ጻድቃን ትሩፋት የበዛላቸው: እንደ ደናግል ንጽሕናን ያዘወተሩ: እንደ ባሕታውያን ግኁስ: እንደ መላዕክትም ባለ ክንፍ አባት ነበሩ:: ለዚሕ ነው ተክለ ሃይማኖትን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዐይኔ የምትላቸው::

††† ልደት †††

††† መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ያፈራልና ተክለ ሃይማኖትን የወለዱት ደጋጉ: ጸጋ ዘአብ ካህኑና እግዚእ ኃረያ ናቸው:: እርሱ በክህነቱ: እርሷ በደግነቷ: በምጽዋቷ ጸንተው ቢኖሩ እግዚአብሔር ጣፋጭ ፍሬን ሰጥቷቸዋል::

በዳሞቱ ገዢ በሞተለሚ አደጋ ቢደርስባቸው ቅዱስ ሚካኤል: ጸጋ ዘአብን ከሞት: እግዚእ ኃረያን ከትድምርተ አረሚ (ከአረማዊ ጋብቻ) አድኗቸዋል:: በኋላም የቅዱሱን መወለድ አብስሯቸዋል::

ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የተጸነሱት መጋቢት 24 ቀን በ1206 ዓ/ም ሲሆን የተወለዱት ደግሞ ታኅሣሥ 24 ቀን በ1207 ዓ/ም ነው:: በተወለዱበት ቀንም ብዙ ተአምራት ተገልጸዋል:: ቤታቸውም በበረከት ሞልቷል::

ዕድገት

የጻድቁ የመጀመሪያ ስማቸው "ፍሥሃ ጽዮን" ይሰኛል:: ይሕንን ስም ይዘው: አባታቸው ጸጋ ዘአብን ተከትለው አድገዋል:: በተለይ ቅዱሳት መጻሕፍትን (ብሉያት: ሐዲሳትን) ተምረዋል:: በሥጋዊው ጐዳናም ብርቱ አዳኝ እንደ ነበሩ ይነገራል:: ዲቁናም ከወቅቱ ጳጳስ አባ ጌርሎስ ተቀብለዋል::

መጠራት

አንድ ቀን ፍሥሃ ጽዮን ለአደን ወጥቶ ሲያነጣጥር ድንገት ከሰማይ አስደንጋጭ ድምጽ ተሰማ:: የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አእላፍ መላእክት እያመሰገኑት በሚካኤል ክንፍ ተቀምጦ ወረደ::

የወጣቱን አዳኝ ፍርሃቱን አርቆ ጌታችን ተናገረ:: "ከዛሬ ጀምሮ ስምህ ተክለ ሃይማኖት (ተክለ ሥላሴ) ይሁን:: ከዚህ በኋላ አራዊትን ሳይሆን ነፍሳትን ታድናለህ:: ዘወትር ካንተ ጋር ነኝ" ብሎ በግርማ ዐረገ:: ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ጊዜ በኋላ ሰዓትን አላጠፉም:: ንብረታቸውን ለነዳያን በትነው በትር ብቻ ይዘው ቤታቸው እንደ ተከፈተ ወደ ምናኔ ወጡ::

አገልግሎት

ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከጳጳሱ ቅስና ተቀብለው የወንጌል አገልግሎትን ጀመሩ:: በመጀመሪያ ስብከታቸው እዚያው ሽዋ (ጽላልሽ) አካባቢ ብቻ በ10ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን አሳምነው አጠመቁ:: ያን ጊዜ ኢትዮጵያ 2 መልክ ነበራት::

1ኛ. ዮዲት (ጉዲት) በፈጠረችው ጣጣና በእስላሞች ተጽዕኖ ወደ ደቡብ አካባቢ ያለው ነዋሪ አንድም ሃይማኖቱን ክዷል: ወይም በባዕድ አምልኮ ተጠምዷል::
2ኛ. በዛግዌ ነገሥታት ጥረት ክርስትናና ምናኔ ተነቃቅቶ ነበር::

ግማሹ ሃገር በጨለመበት ወቅት የደረሱት ሐዲስ ሐዋርያ አባ ተክለ ሃይማኖት በወጣት ጉልበታቸውና በኃይለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ቦታዎችን አደረሱ:: ሕዝቡን: መሣፍንቱን ወደ ሃይማኖት መልሰው: ማርያኖችን (ጠንቋዮችን) አጥፍተዋል::

ገዳማዊ ሕይወት

ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት በወንጌል ብርሃን ኢትዮጵያን ከማብራታቸው ባለፈ ገዳማዊ ሕይወትንም አስፋፍተዋል:: እርሳቸው ከሁሉ የተሻሉ ሳሉም በ3 ገዳማት በረድዕነት አገልግለዋል::

እነዚህም በአቡነ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ለ12 ዓመታት: በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ ገዳም ለ7 ዓመታት: በደብረ ዳሞ ከአቡነ ዮሐኒ ጋር ለ7 ዓመታት: በአጠቃላይ ለ26 ዓመታት አገልግለዋል::

በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ ከመነኮሱ በኋላም ወደ ምድረ ሽዋ (ዞረሬ) ተመልሰው በአንዲት በዓት ውስጥ ለ22 ዓመታት ቆመው ጸልየዋል:: በተሰበረ እግራቸውም 6 ጦሮችን በግራና በቀኝ ተክለው ለ7 ዓመታት ጸልየዋል::

ስድስት ክንፍ

ኢትዮጵያዊው ጻድቅና ሐዋርያ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው ከቅዱሳት መካናት ተባርከዋል:: ጻድቁ ምድረ እሥራኤል የገቡት በየመንገዱ መንፈሳዊ ዘርን እየዘሩ: እያስተማሩና እያሳመኑ ነበር::

የወቅቱ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ጋርም ተገናኝተው ቡራኬን ተሰጣጥተዋል:: ዋናው ጉዳይ ግን ከዚህ በኋላ ነው:: ጻድቁ እመቤታችንና ጌታችን ከጽንሰታቸው እስከ ዕርገታቸው የረገጧቸውን ቦታዎች ሲመለከቱ በፍጹም ተደሞ እንባቸው ይፈስ ነበር::

ምክንያቱም እግዚአብሔር ስላበቃቸው ተክለ ሃይማኖት የሚያዩት ቦታውን አልነበረም:: በገሃድ:-
-በቤተ መቅደስ ብስራቱን
-በቤተ ልሔም ልደቱን
-በቤተ ዮሴፍ ግዝረቱን
-በፈለገ ዮርዳኖስ ጥምቀቱን
-በቤተ አልዓዛር ተአምራቱን ይመለከቱ ነበር::

የጉብኝታቸው የመጨረሻ ክፍል ወደ ሆነው ቀራንዮ ደርሰው ጌታቸውን እንደ ተሰቀለ ሆኖ ቢመለከቱት ከዓይናቸው ይፈስ የነበረው ቁጡ እንባ መልኩን ቀየረና ዓይናቸው ጠፋ::
በዚያች ቅጽበት ስም አጠራሯ የከበረ እመቤታችን ድንግል ማርያም ፈጥና ደርሳ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖትን ወደ ሰማይ አሳረገቻቸው::

በዚያም:-
*የብርሃን ዐይን ተቀብለው
*ስድስት ክንፍ አብቅለው
*የወርቅ ካባ ላንቃ ለብሰው
*ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው
*ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይም ተደምረው
*ሥላሴን በአንድነቱና ሦስትነቱ ተመልክተው
*"ስብሐት ወክብር ለሥሉስ ቅዱስ ይደሉ" ብለው መንበረ ጸባኦትን አጥነው ወደ መሬት ተመልሰዋል::

ተአምራት

የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተአምራት እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ነው::
*ሙት አንስተዋል
*ድውያንን ፈውሰዋል
*አጋንንትን አሳደዋል
*እሳትን ጨብጠዋል
*በክንፍ በረዋል
*ደመናን ዙፋን አድርገዋል::

ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተው ደብረ ሊባኖስን መሥርተዋል:: በዚያም ሴትና ወንድ መነኮሳት እንደ ሕፃናት አብረው ኑረዋል:: በዘመናቸው ሰይጣን ታሥሯልና::

ዕረፍት

ጻድቅ: ሰማዕትና ሐዋርያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ብርሃን ሆነው መከራን በብዙ ተቀብለው: እልፍ አእላፍ ፍሬን አፍርተው: በተወለዱ በ99 ዓመት: ከ8 ወር: ከ1 ቀናቸው ነሐሴ 24 ቀን በ1306 ዓ/ም ዐርፈዋል:: ጌታ: ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ወርደው ተቀብለዋቸዋል:: 10 ትውልድ የሚያስምር ቃል ኪዳንም ተቀብለዋል::

=>ይህች ዕለት ለጽንሰታቸው መታሰቢያ በዓል ናት፡፡
††† አምላከ ቅዱሳን ከጻድቁ አባታችን በረከትን ይክፈለን::

††† መጋቢት 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ተክለ ሃይማኖት (ጽንሰቱ)
2.ቅዱሳን እግዚእ ኃረያና ጸጋ ዘአብ
3.ቅዱስ አባ መቃርስ ሊቀ ጳጳሳት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ አጋቢጦስ ጻድቅ
2.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
3.ቅዱስ ሙሴ ፀሊም
4.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
5.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
6.ሃያ አራቱ ካኅናተ ሰማይ

††† "በረከት በጻድቅ ሰው ራስ ላይ ነው:: የኀጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል:: የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው:: የኀጥአን ስም ግን ይጠፋል::" †††
(ምሳሌ ፲፥፮)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለዘመነ ሐጋይ (በጋ) የመጨረሻ ዕለትና ለሐዋርያው ቅዱስ አንሲፎሮስ በዓለ ዕረፍት በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† አምላካችን እግዚአብሔር ሁሉን ስነ ፍጥረት የፈጠረ ለሰው ልጆች ጥቅም ነው:: ጌታ አዝማናትን : ወሮችን : ሳምንታትን : ቀኖችንና ሰዓታትን ፈጥሮ : ወስኖ ሰጥቶናል:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት እንደ መሆኗ ሁሉ ነገሯ በሥርዓት ይፈፀማል::

በራሷ የዘመን ቀመር ስሌት መሠረትም አንድ ዓመት በአራት ወቅቶች ይከፈላል:: አባታችን ሊቁ ቅዱስ ያሬድም እነዚህን ወቅቶች መሠረት አድርጎ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል::

እነዚሕ አዝማናት (ወቅቶች):-
1.ዘመነ ክረምት (ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25)
2.ዘመነ መፀው (ከመስከረም 26 እስከ ታኅሣሥ 25)
3.ዘመነ ሐጋይ (ከታኅሣሥ 26 እስከ መጋቢት 25)
4.ዘመነ ፀደይ (ከመጋቢት 26 እስከ ሰኔ 25) መሆናቸው ይታወቃል::

ዘመነ ሐጋይ (በጋን) የባረከ አምላክ ዘመነ ፀደይ (መከርን) እንዲባርክልን : የንስሐ ጊዜም እንዲያደርግልን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን::

††† ቅዱስ አንሲፎሮስ †††

††† በዚህች ዕለት ጌታችንን በሃገረ ናይን የተከተለ : ከዋለበት ውሎ : ካደረበት ያደረ : ከሰባ ሁለቱ አርድእት የተቆጠረ ሐዋርያው ቅዱስ አንሲፎሮስ አርፏል::

††† ዳግመኛ በዚህ ዕለት አይሁድ ለመጨረሻ ጊዜ ጌታችንን ሊገድሉት ተስማሙ:: ይሁዳም በ30 ብር ይሸጠው ዘንድ ከአይሁድ ጋር ተዋዋለ::

††† የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅርታውና ምሕረቱ ከሁላችን ጋር ይሁን::

††† መጋቢት 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አንሲፎሮስ ሐዋርያ (ከሰባ ሁለቱ አርድእት)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት
3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት
4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ
5.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)
6.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ

††† "ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ: ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዘመናትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን:: እርሱም . . . ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ::" †††
(ዕብ. ፩፥፩)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለጥንተ በዓለ ምሴተ ሐሙስ እና ኢዮጰራቅስያ ድንግል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ምሴተ ሐሙስ †††

††† ስም አጠራሩ ከፍ ከፍ ይበልና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከ1978 ዓመታት በፊት "ምሴተ ሐሙስ" በምትባለው በዚሕች ዕለት:-
1.በወዳጁ በዓልዓዛር ቤት የዓለማት ፈጣሪ ሲሆን በትሕትና ዝቅ ብሎ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቧል::
2.ለእኛ ድኅነት ይሆነን ዘንድ ቅዱስ ሥጋውን : ክቡር ደሙን ለመጀመሪያ ጊዜ ሰጥቷል::
3.በጌቴሴማኒ ላበቱ እንደ ደም እየተንጠፈጠፈ ጸልዮ "ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ" ሲል አስተምሯል::
4.ምሽት 3 ሰዓት አካባቢ ይሁዳ ሊቃነ ካህናቱን አስከትሎ መጥቶ ለ30 ብር አሳልፎ ሰጥቶታል:: (ማቴ. 26:26 / ዮሐ. 13:1)

ይሕ ሁሉ ለእኛ ድኅነት ተፈጽሟልና ምስጋናና ክብር ለፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይሁን::

††† ኢዮጰራቅስያ ድንግል †††

††† ዳግመኛ በዚህ ዕለት እናታችን ቅድስት ኢዮጰራቅስያ ድንግል አርፋለች::

ቅድስቲቱ በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረች እናት ስትሆን ገና በ9 ዓመቷ ምድራዊ ሐብትን ንቃ መንናለች:: ምክንያቱም ዘመዶቿ የሮም ነገሥታት እነ አኖሬዎስ ነበሩና:: ድንግል ኢዮጰራቅስያ በገዳም : በጾምና በጸሎት : በፍፁም ትሕትናና ታዛዥነት : እንዲሁም በፍቅር ኑራ በዚህች ቀን አርፋለች::

††† ከቅድስት እናታችን በረከት አምላኩዋ ይክፈለን::

††† መጋቢት 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱሳን ሐዋርያት
2.ቅድስት ድንግል ኢዮጰራቅስያ
3.ቅዱስ ፍርፍርዮስ ሰማዕት

††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
2.አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ
3.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
4.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
5.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

††† "ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው:: እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ:: ሥጋዬ እውነተኛ መብል: ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና:: ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል:: እኔም በርሱ እኖራለሁ::" †††
(ዮሐ. 6:53-56)

††† "እግራቸውን አጥቦ: ልብሱንም አንስቶ ዳግመኛ ተቀመጠ:: እንዲሕም አላቸው:- 'ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምሕርና ጌታ ትሉኛላችሁ:: እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ:: እንግዲህ እኔ ጌታና መምሕር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባል::' " †††
(ዮሐ. 13:12-14)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ዓመታዊ የስቅለት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† መድኃኔ ዓለም †††

††† ጌታችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ለእኛ ሲል በፈጸመው የማዳን ሥራ በዚሕ ዕለት ክፉዎች አይሁድ ከምሽቱ 3:00 ጌቴሴማኒ ውስጥ ያዙት::
ሙሉውን ሌሊት ከቀያፋ ወደ ሐና: ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት: አስረው ሲደበድቡት አድረዋል::

*ዝም ቢላቸው ዓይኑን ሸፍነው በጥፊ መቱት:: ምራቃቸውን ተፉበት:: ዘበቱበት:: ራሱንም በዘንግ መቱት:: እርሱ ግን ሁሉን ታገሰ::

*በጧት ከገዢው ዘንድ ሞት እንዲፈረድበት አቀረቡት:: በሠለስት (ሦስት ሰዓት ላይ) አካሉ እስኪያልቅ እየተዘባበቱ 6,666 ገረፉት:: ሊቶስጥሮስ አደባባይ ላይ እርጥብ መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ ወሰዱት::

*ስድስት ሰዓት ላይ በረዣዥም ብረቶች አምስት ቦታ ላይ ቸንክረው ሰቀሉት:: ሰባት ታላላቅ ተአምራት በምድርና በሰማይ ታዩ::
ዓለም በጨለማ ሳለች ጌታ በመስቀል ላይ ሰባት ቃላትን ተናገረ::

*ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በባሕርይ ሥልጣኑ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ:: በዚያች ሰዓትም ወደ ሲዖል ወርዶ የታሠሩትን ሁሉ ፈታ:: አሥራ አንድ ሰዓት ላይ ደጋጉ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከታላቅ ክብርና ሐዘን ጋር በአዲስ መቃብር ቀበሩት::

*በዚያች ቀን ድንግል ማርያም ልቧ በሐዘን ተቃጠለ:: ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስም ፍፁም ለቅሶን አለቀሰ:: ቅዱሳት አንስት በዋይታ ዋሉ:: (ማቴ. 27:1, ማር. 15:1, ሉቃ. 23:1, ዮሐ. 19:1)

††† ለእኛ ለኀጥአን ፍጡሮቹ ሲል ይህንን ሁሉ መከራ የታገሰ አምላክ ስለ አሥራ ሦስቱ ኅማማቱ: አምስቱ ቅንዋቱ: ስለ ቅዱስ መስቀሉ: ስለ ድንግል እናቱ ለቅሶና ስለ ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስ ብሎ ይማረን::

††† ከቅዱሳኑ በዚሕች ዕለት:-

††† ከ80 ዓመታት በላይ በገዳም የኖረ: የገዳማውያን ሞገሳቸው: የመነኮሳትም ሁሉ አለቃ ታላቁ ቅዱስ መቃርስ አርፏል::

††† ዳግመኛ በዚህ ቀን ንግሥናን ከሊቅነት: ጽድቅን ከሰማዕትነት ጋር የደረበው ሰማዕቱ ቅዱስ ገላውዴዎስ አንገቱን ተከልሏል:: ቅዱስ ገላውዴዎስ የጻድቁ ዐፄ ልብነ ድንግል ልጅ ነው::

††† መድኃኔ ዓለም ከወዳጆቹ ጸጋ ክብርን ያድለን::

††† መጋቢት 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ (ፍቁረ እግዚእ)
2.ቅዱሳት አንስት (ከእግረ መስቀሉ ያልተለዩ)
3.ቅዱሳን ባልንጀሮች (በጌታ ስቅለት ጊዜ ከሞት የተነሱ)
4.ቅዱሳን ዮሴፍና ኒቆዲሞስ
5.ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት አለቃ)
6.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት (የኢትዮዽያ ንጉሥ)
7.ቅዱስ ዕፀ መስቀል

††† ወርኀዊ በዓላት
1.አቡነ መብዐ ፅዮን ጻድቅ
2.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
3.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
4.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት

††† "የተጠራችሁለት ለዚህ ነው:: ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና:: እርሱም ኃጢአት አላደረገም:: ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም:: ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም:: መከራንም ሲቀበል አልዛተም . . . እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ::" †††
(፩ጴጥ. ፪፥፳፩-፳፭)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
††† እንኳን ለታላቁ ክርስቲያናዊ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ †††

††† ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ለቤተ ክርስቲያን የፈፀመውን መልካም ተግባር ያሕል መሥራት የቻለ ንጉሥ በሐዲስ ኪዳን የለም:: ጻድቁ ንጉሥ ከቅድስት እናቱ እሌኒና ከአረማዊ አባቱ ቁንስጣ በበራንጥያ ተወለደ::

ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ (የመከራ ጊዜ) ወይም የሰማዕታት ዘመን በመሆኑ ክርስቲያኖች በግፍ የሚጨፈጨፉበት ወቅት ነበር:: ክርስቲያኖችን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት በተደረገው የ40 ዓመታት ዘመቻ አብያተ መቃድስና መጻሕፍት ተቃጠሉ:: ብዙዎቹ በየበርሃው ተሰደዱ:: ሚሊየኖች በግፍ አለቁ::

የዚሕን ዘመን መከራ በውል ያልተረዳ ሰው ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን ሊያከብር አይችልም:: ምክንያቱም ይህን የመከራ ዘመን በፈቃደ እግዚአብሔር አስቁሞ : ቀርነ ሃይማኖት የቆመው : ብዙ ሥርዓት የተሠራው : ቤተ ክርስቲያንም ያበራችው በዘመኑ ነውና::

ቅዱሱ ንጉሥ ለሁሉም ነቢያት : ሐዋርያትና ሰማዕታት አብያተ ክርስቲያናትን ራሱ በመሠረታት በቁስጥንጥንያ አንጿል:: በዘመኑ ቤተ ክርስቲያን በሰላም ኖራለት : በኃይለ መስቀሉ ጠላት ጠፍቶለት ኑሮ በዚህች ቀን አርፏል:: "ቆስጠንጢኖስ" ማለት "ሐመልማል" ማለት ነው::

††† ዳግመኛ በዚሕ ቀን የዓለማት ፈጣሪ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ በሆነው ሞቱ በመቃብር ውስጥ አድሯል::

††† ጌትነት ያለው አምላካችን በይቅርታው ይጐብኘን:: መልካም መሪንም ይስጠን::

††† መጋቢት 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ (ጻድቅ ንጉሥ)
2.ቅድስት እሌኒ ንግስት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.አማኑኤል ቸር አምላካችን
2.ቅዱሳን አበው (አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ)
3.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
4.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
5.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)

††† "እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ: ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር: ልመናና ጸሎት: ምልጃም: ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ: ስለ ነገሥታትና መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ:: ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው::" †††
(፩ጢሞ. ፪፥፩-፬)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
እንኳን ለጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓመታዊ የጽንሰት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

††† በዓለ ጽንሰት †††

††† ይሕች ቀን ለቤተ ክርስቲያን በእጅጉ ልዩ ናት:: በዓመቱ ከሚከበሩ በዓላትም አንደኛውን ሥፍራ ትይዛለች::

በዚሕ ዕለት አምላካችን እግዚአብሔር:-

1.ሰማይና ምድርን ፈጠረ:: (ዘፍ. 1:1)

2.በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት በድንግል ማርያም ማኅፀን አደረ (ተጸነሰ):: በዓሉም "በዓለ ትስብእት" ይባላል:: "አምላክ ሰው : ሰው አምላክ የሆነበት" ማለት ነው:: (ሉቃ. 1:26)

3.የክብር ባለቤት መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ:: (ማቴ. 28:1፣ ማር. 16:1፣ ሉቃ. 24:1፣ ዮሐ. 20:1)

4.ጌታችን ዳግመኛ ለፍርድ በዚሕች ቀን ይመጣል:: (ማቴ. 24:1)

††† በነዚሕ ታላላቅና ድርብርብ በዓላት ምክንያት ቀኑ "ርዕሰ በዓላት" (የበዓላት ራስ) : "በኩረ በዓላት" እየተባለም ይጠራል::

††† ቸሩ እግዚአብሔር ዓለምን ከመፍጠሩ : ከጽንሰቱ : ልደቱና ትንሣኤው በረከትን ይክፈለን:: በጌትነቱም ሲመጣ በርሕራሔው ያስበን::

††† ዳግመኛ በዚህች ቀን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እልዋሪቆን ገብቷል:: ይህች ሃገር የምድራችን መጨረሻ ናት:: ከዚያ በኋላ ሰውና ሃገር የለም:: እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን የሰበከ ሐዋርያ የለም::

††† ከቅዱሱ ሐዋርያ ትጋት : ቅናት : መንፈሳዊነትና ንጽሕና አምላካችን ይክፈለን::

††† መጋቢት 29 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
1.ጥንተ ዕለተ ፍጥረት (ዓለም የተፈጠረችበት)
2.በዓለ ትስብእት (የጌታችን ጽንሰቱ)
3.ጥንተ በዓለ ትንሣኤ
4.ዳግም ምጽዐት
5.ቅድስት ማርያም መግደላዊት
6.ቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ
7.ቅዱሳት አንስት (ትንሣኤውን የሰበኩ)
8.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ (ጽንሰታ)
9.አብርሃ ወአጽብሐ (ጽንሰታቸው)
10.ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ (ጽንሰቱ)
11.ቅዱስ ላሊበላ (ጽንሰቱ)
12.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ (ጽንሰታቸው)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.የፈጣሪያችንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት
2.ቅድስት አርሴማ ድንግል
3.ቅዱስ ጴጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
4.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
5.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ (ጻድቅና ሰማዕት)

††† "እነሆ ከደመና ጋር ይመጣል:: ዓይንም ሁሉ: የወጉትም ያዩታል:: የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ:: አዎን አሜን::
ያለውና የነበረው: የሚመጣውም: ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ: አልፋና ኦሜጋ እኔ ነኝ ይላል::" †††
(ራእይ ፩፥፯)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
† እንኳን ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ሶምሶን (መስፍነ እስራኤል) ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ገብርኤል †††

††† ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል:-

*ከ7ቱ ሊቃናት አንዱ::
*በራማ አርባብ በሚባሉ 10 ነገደ መላእክት ላይ የተሾመ::
*በመጀመሪያዋ የፍጥረት ቀን መላእክትን ያጸና::
*ቅዱሳንን ሁሉ የሚረዳ::
*ሠለስቱ ደቂቅን : ዳንኤልን : ሶስናን ከሞት የታደገ ታላቅ መልዐክ ነው::

ከምንም በላይ ግን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዱሱን መልዐክ "መጋቤ-ሐዲስ" ብላ ታከብረዋለች:: ቅዱስ ገብርኤል የስሙ ትርጉዋሜ "አምላክ ወሰብእ - እግዚእ ወገብር" ነውና ለሥነ ፍጥረት ሁሉ የሚሆን ሐዲስ ዜናን ወደ እመቤታችን ድንግል ማርያም አምጥቷል::

መልዐኩ እመቤታችንን ከመጸነሷ ጀምሮ ባይለያትም መጋቢት 29 ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ አብስሯታል:: ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በማግስቱ በድምቀት እንዲከበር በወሰኑት መሠረት ዛሬ (በ30) ይከበራል::

††† ሶምሶን ረዓይታዊ †††

††† እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን: ሀያ ሁለቱን ሥነ ፍጥረትን ፈጥሮ አዳምን ገዢ አደረገው:: አክሎም በነፍስ ሕያው አድርጐ: በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ: ነቢይና ካህን አድርጐ: ካንዲት ዕፀ በለስ በቀር በፍጥረት ሁሉ ላይ አሰለጠነው::

አባታችን አዳም ግን ስህተት አግኝቶት ከገነት ወጣ:: መከራና ፍዳም አገኘው:: በኋላም ለ100 ዓመት አልቅሶ ንስሃ ገባ:: ጌታም ንስሃውን ተቀብሎ "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ተስፋ ድህነትን ሰጠው::

ስለዚህም ምክንያት ለ5,500 ዓመታት ትንቢት ሲነገር: ሱባኤ ወደ ታች ሲቆጠር: ምሳሌም ሲመሰል ኖረ:: ከደግ ፍጥረት አዳም እስከ ኖኅ ድረስ: የሴት ልጆች እግዚአብሔርን በንጽሕና ሁነው በደብር ቅዱስ አመለኩ::

ትንሽ ቆይተው ግን ስለተቀላቀሉ ከቃየን ልጆች ጋር በማየ ድምሳሴ ጠፉ:: በጻድቅ ሰው ኖኅ የተጀመረው ትውልድም እግዚአብሔርን ለመዘንጋት ጊዜ አልፈጀበትም:: ነገር ግን ከሴም ዘር ቅንና ጻድቅ ሰው አብርሃም ተገኘ::

ከእርሱም ይስሐቅ: ከዚያም ያዕቆብ (ደጋጉ) ተገኙ:: ያዕቆብም "እሥራኤል" ተብሎ: በልጆቹ "ሕዝበ እግዚአብሔር" የተባለ ነገድ ተመሠረተ:: በተስፋይቱ ምድር በከነዓን እንዳይኖሩም ርሃብ ምድረ ግብጽ አወረዳቸው::

በዚያም ለ215 ዓመታት በጭንቅ የባርነትን ሕይወትን አሳለፉ:: እግዚአብሔርም ስለ ወዳጁ አብርሃም ሲል እሥራኤልን አሰባቸው:: የዋሕና ጻድቅ ሰው ሙሴን አስነስቶ እሥራኤልን ከግብጽ ባርነት አዳናቸው::

ይኸውም በጸናች እጅ: በበረታችም ክንድ: በ9 መቅሰፍት: በ10ኛ ሞተ በኩር: በ11ኛ ስጥመት ግብጻውያንን አጥፍቶ ነው:: በየመንገዱም ጠላቶቻቸውን እየተበቀለላቸው ነው:: ከዚህ ዘመን ጀምሮም እሥራኤል በመሳፍንትና በካህናት የሚተዳደሩ ሆኑ::

አስቀድሞ ሙሴ በምስፍና: አሮን በክህነት መሯቸው:: ቀጥሎም በቅዱስ ሙሴ ኢያሱ: በአሮን አልዓዛር ተተኩ:: እንዲህ እንዲህ እያለም ከኃያል ሰው ሶምሶን ረዓይታዊ ደረሱ:: ይኸውም ከዓለም ፍጥረት 4,200 ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው::

በጊዜው እሥራኤል ጣዖትን እያመለኩ እግዚአብሔርን ስላሳዘኑት ለጠላቶቻቸው አሳልፎ ይሰጣቸው ነበር:: የአካባቢው መንግስታት እነ አሞን: አማሌቅ: ኢሎፍሊ ስንኳ ያኔ ዛሬም ቢሆን እንደምትመለከቱት ዶሮና ጥሬ ናቸው::

በጊዜውም የእሥራኤል ኃጢአት ስለ በዛ ኢሎፍላውያን (ፍልስጤማውያን) 40 ዓመት በባርነት ገዟቸው:: ንስሃ ሲገቡ ደግሞ ልጅ በማጣት ያዘኑ ማኑሄ እና ሚስቱ (እንትኩይ) : በቅዱስ ሚካኤል ተበሥረው ኃያሉን ሶምሶንን ወለዱላቸው::

እርሱም ናዝራዊ (ከእናቱ ማኅጸን ለጌታ የተለየ) ነበርና ፍልስጤማውያንን ቀጥቶ ወገኖቹን እስራኤልን ከባርነት : በአምላኩ ኃይል ታደገ:: ከኃይሉ ብዛት የተነሳም:-
¤አንበሳን እንደ ጠቦት ይገድል (መሣ. 14:5)
¤300 ቀበሮዎችን አባሮ ይይዝ (መሣ. 15:3)
¤በብርቱ ገመዶች ሲያስሩት እንደ ፈትል ይበጣጥሰው (መሣ. 15:14)
¤በአህያ መንጋጋ ሽህ ሰው ይገድል (መሣ. 15:15)
¤ጠባቂዎችን ከነ መቃናቸው ተሸክሞ ይወረውር ነበር:: (መሣ. 16:3)

ውኃ ሲጠማውም ከአህያ መንጋጋ ላይ ፈልቆለት ጠጥቷል:: (መሣ. 15:18) በፍጻሜው ግን ደሊላ በምትባል ሴት ተታልሎ ምሥጢሩን በመግለጡና ጸጉሩ በመላጨቱ ኃይሉን አጥቷል:: ጠላቶቹም ዐይኑን አውጥተው መዘባበቻ አድርገውታል::

በፍጻሜው ግን ኃይሉ እንዲመለስለት ፈጣሪውን ለምኖ : አሕዛብ ለጣኦት በዓል እንደተሰበሰቡ የአዳራሹን ምሰሶ አፍርሶ አጥፍቷቸው ዐርፏል:: (መሣ. 13--16)
ቅዱስ ሶምሶን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥላ (ምሳሌ) ነው::

††† "ክፉ ናችሁ: ኃጢአታችሁ በዝቷል" የማይል ጌታ በመከራችን ሁሉ ተራዳኢ መልዐክን (ቅዱስ ገብርኤልን) ይዘዝልን:: ወርኀ መጋቢትን በሰላም እንዳስፈጸመ ወርኀ ሚያዝያን በምሕረቱ ይባርክልን::

††† መጋቢት 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት (እመቤታችንን ያበሠረበት መታሠቢያ)
2.ቅዱስ ሶምሶን (መስፍነ እስራኤል)
3.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ (ፍልሠቱ)
4.ቅዱስ ዮሐንስ ዘአክሱም (ድርሳነ ሚካኤልን መጻፉ የሚነገርለት አባት)
5.እግዚአብሔር ውሃን ከ3 ከፈለው (ጠፈርን ፈጠረ)

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ማርቆስ ዘአንበሳ (ሐዋርያ)
3.አባ ሣሉሲ ክቡር
4.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
5.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት

††† ". . . በአምላኬም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ተቀደሰው ስለ አምላኬ ተራራ ስለምን: ገናም በጸሎት ስናገር አስቀድሜ በራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ:: በማታም መሥዋዕት ጊዜ ዳሰሰኝ:: አስተማረኝም . . ." †††
(ዳን. 9:20)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
✞✞✞ እንኩዋን ከተባረከ ወር "ሚያዝያ" እና ከጻድቁ አባታችን "ቅዱስ ስልዋኖስ" "ወቅዱስ አሮን ካህን" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*" አባ ስልዋኖስ "*+

=>ጻድቁ አባ ስልዋኖስ ግብፃዊ ሲሆኑ ከታላቁ መቃርስ
መንፈሳዊ ልጆች አንዱ ናቸው:: ገና በሕጻንነታቸው ወደ
ገዳም ገብተው ጾምን : ጸሎትን : ትሕርምትን ገንዘብ
በማድረግ ታላቅ የንጽሕና ሰው ሁነዋል::

+ከመካከለኛ እድሜአቸው ጀምረው ደግሞ የገዳመ
አስቄጥስ አበ ምኔት ሆነው በመልካም እረኝነት
አገልግለዋል:: ጻድቁን ለየት የሚያደርጉዋቸው አንዳንድ
ተግባራት ነበሩ::

+እርሳቸውን ጨምሮ ሁሉም ገዳማዊ ከጾምና ከጸሎት
ባሻገር ሥራ ሠርቶ ማታ መመጽወት አለበት:: ያ ማለት
ያለ ምጽዋት ውሎ ማደር አይፈቀድም ነበር:: ይሕም
መነኮሳቱን ከጽድቅ ባለፈ ታታሪና ባተሌ አድርጉዋቸዋል::

+አባ ስልዋኖስ በተሰጣቸው ጸጋ መላእክትን : ገነትና
ሲዖልን ያዩ ነበር:: በዚሕ ምክንያት ስለ ኃጥአን ከማልቀስ
ዐይናቸው ቦዝኖ አያውቅም:: የዚሕን ዓለም ብርሃን
አላይም ብለው ቆባቸውን ዓይናቸው ላይ ጥለው
በመልካም ሽምግልና በዚሕች ቀን አርፈዋል::

=>አምላካችን ከጻድቁ በረከት ያሳትፈን::

+*" ቅዱስ አሮን ካህን "*+

=>ቅዱስ አሮን:-
~የሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴ ወንድም::
~የነቢዪት ማርያም ታናሽ::
~የዮካብድና ዕንበረም ልጅ::
~የእግዚአብሔር ካህን እና
~የብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናት ነው::

+እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን የነበረው የክህነት
አገልግሎት ከእርሱ ዘር እንዳይወጣ ምሎለታል:: ዳታን :
አቤሮንና ቆሬ ይህንን ቢቃወሙ ከነ ሕይወታቸው መሬት
ተከፍታ ውጣቸዋለች:: በድፍረት "እናጥናለን" ብለው ወደ
ደብተራ ኦሪት የገቡትንም እሳት ከሰማይ ወርዶ
በልቷቸዋል::

+ቅዱስ አሮንም በጌታ ትእዛዝ በትሩ ለምልማ : አብባና
አፍርታ ተገኝታለች:: ይህም ለጊዜው ክህነት ከሱ ልጆች
እንዳይወጣ ሲያደርግ በፍጻሜው ለድንግል ማርያም
ምሳሌ ሆኗል::

+የአሮን በትር ሳይተክሏት : ሳይደክሙባትና ውሃ
ሳያጠጣት አብባና አፍርታ እንደተገኘች ድንግል ማርያምም
የወንድ ዘር ምክንያት ሳይሆናት ፍሬ አፍርታለች
(ክርስቶስን ወልዳለችና)::

+አባ ሕርያቆስ "ጸናጽል ዘውስተ ልብሱ ለአሮን ካህን::
ወዓዲ በትር እንተ ሠረጸት : ወጸገየት : ወፈረየት" እንዳለ::
(ቅዳሴ ማርያም)

+ቅዱስ አሮን በማዕጠንቱና በመስዋዕቱ ፈጣሪውን
አገልግሎ : ድውያንንም ፈውሶ : እስራኤል በበርሃ ሳሉ
አርፎ ተቀብሯል:: (ዘኁ. 20:25)

(ለተጨማሪ ንባብ 3ቱን ብሔረ ኦሪት (ከኦሪት ዘጸአት
ምዕራፍ 4 ጀምረው እስከ ኦሪት ዘኁልቁ ምዕራፍ 20
ድረስ) ያንብቡ)

=>ክብሩ : በረከቱ ይደርብን::

=>ሚያዝያ 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አሮን ካህን (የሊቀ ነቢያት ሙሴ ወንድም)
2.አባ ስልዋኖስ ጻድቅ
3.ቅዱሳን መነኮሳት
4.ቅድስት መጥሮንያ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላዕክት
4.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ
5.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር

=>+"+ ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ
ደግሞ መስዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል::
እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም
ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም:: +"+ (ዕብ. 5:3)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
††† እንኳን ለሰማዕቱ ቅዱስ ክርስቶፎሮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††

††† ቅዱስ ክርስቶፎሮስ †††

††† ክርስቶፎሮስ ትርጉሙ "ለባሴ ክርስቶስ" እንደ መሆኑ በሐዋርያት ዘመን የነበሩ ብዙ ቅዱሳን በዚህ ስም ይጠሩ ነበር:: ከነዚህ አንዱ ቅዱስ ክርስቶፎሮስ ሃገሩ በላዕተ ሰብእ (ሰውን የሚበሉ) ውስጥ ነበር::

ይህች ሃገር አሁን የት እንዳለች በውል ባይታወቅም የቅዱስ ማትያስ ሃገረ ስብከት በመሆኗ አውሮፓና እስያ ድንበር አካባቢ እንደሆነች ይገመታል::

የአካባቢው ሰዎች ከሰው ሥጋ ውጪ እህልን አይቀምሱም ነበር:: ቅዱስ ማትያስ በነርሱ ያደረውን ርኩስ መንፈስ አስወጥቶ አሳምኗቸዋል::

ከሃገሩ ሰዎችም አንዳንዱ ገጻተ ከለባት (የውሻ መልክ ያላቸው) ነበሩ:: ክርስቶፎሮስም ከነርሱ አንዱ ነበር:: በክርስቶስ አምኖ ከተጠመቀ በሁዋላ በስብከቱ ብዙዎችን አሳምኖ : ስለ ሃይማኖትም ብዙ ጸዋትወ መከራ ተቀብሎ በዚህች ቀን በሰማዕትነት አርፏል::

††† ከሰማዕቱ በረከት አምላኩ ያድለን::

††† ሚያዝያ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ክርስቶፎሮስ (ሐዋርያና ሰማዕት)
2.አባ ስምዖን ዘሃገረ ሐሊባ
3.ቅዱስ መላልኤል (የያሬድ አባት - ከአዳም 5ኛ ትውልድ)
4.እግዚአብሔር ፀሐይን : ጨረቃን : ከዋክብትን ፈጠረ

††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
4.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
5.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
6.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
7.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ

††† "ስለዚሕ ወንድሞቼ ሆይ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ:: ልባሞች እንደመሆናችሁ እላለሁ:: በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ:: የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? . . . እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን:: ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና::" †††
(1ቆሮ. 10:14-18)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
እንኩዋን ለጻድቁ አባታችን "ቅዱስ መርቄ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

+*" ጻድቁ ቅዱስ መርቄ "*+

=>ቅዱስ መርቄ በሁለት ዓለም የተሳካለት ደግ ሰው ነው:: ነገሩ እንዲህ ነው:-

+ቅዱሱ በዓለም የሚኖር ታዋቂ ነጋዴ ነው:: ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር እንደ አስቸጋሪ ከሚታዩ የሥራ ዘርፎች አንዱ የንግድ ሥራ ቢሆንም እርሱ ግን "ቅዱሱ ነጋዴ" ለመባል በቅቷል::

+ለዚህም ምክንያቱ 2 ነገሮች ናቸው:-
1.በንግድ ሕይወቱ ማንንም ሳያጭበረብር ከመኖሩ ባለፈ ፍጹም ጸሎትን ጾምንና ምጽዋትን ያዘወትር ነበር::
2.ለንግድ በተዘዋወረባቸው ሃገራት ሁሉ ስለ ክርስቶስ ያለማቁዋረጥ የሚሰብክ በመሆኑ በርካቶችን አሳምኖ ሐዋርያዊ ክብርን አግኝቷል::

+ቅዱስ መርቄ በሕይወቱ ይሕንን ከፈጸመ በሁዋላ አንድ አረማዊ ጉዋደኛ ነበረውና : ሐብት ንብረቱን ሰብስቦ "ጌታችን ክርስቶስ ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስላለ ለርሱ ስጥልኝ" ብሎ ላከው::

+አረማዊው ጉዋደኛውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍፁም ግርማ አግኝቶ ንብረቱን ከእጁ ተቀብሎታል::

+አረማዊውም በዚህ ምክንያት ከ75 ቤተሰቦቹ ጋር አምኖ ተጠምቁዋል:: ቅዱስ መርቄ በርሃ ውስጥ ባረፈ ጊዜ ቅዱስ ዳዊት ከሰማይ ወርዶ ዘምሮለታል:: መላዕክት በምስጋና ገንዘውት አንበሶች ቀብረውታል::

=>አምላክ ከቅዱሱ በረከትን ያድለን::

=>ሚያዝያ 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ መርቄ ጻድቅ (ክርስቲያናዊ ነጋዴ)
2.ቅዱስ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም
3.አባ ሚካኤል ዘእስክንድርያ
4.እግዚአብሔር:- በእግር የሚራመዱ : በክንፍ የሚበሩና በልብ የሚሳቡ : በየብስ የሚኖሩ ፍጥረታትን ፈጠረ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ
2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና
3.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)
4.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ
5.አቡነ ዜና ማርቆስ
6.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዘደብረ በንኮል

=>+"+ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም:: መብራትንም አብርተው በዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል:: በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል:: መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ:: +"+ (ማቴ. 5:14-16)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
ገብርኄር
Forwarded from 🟢ናታኒም ፖሮሞሽን🟢
🔹 ✥● ከሚከተሉት ውስጥ ቅድስት ሃገራችን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ከሚለው መጠርያ ስሟ ሌላ በየትኛው ትጠራ ነበር?? ✥●