መዝገበ ቅዱሳን
24.2K subscribers
1.97K photos
9 videos
6 files
26 links
የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው! መ/ሳ 1÷7
Bewust mesimer lemanegager
@Yesadkusitota
የሰማነውን እንናገራለን
ያየነውን እንመሰክራለን
Download Telegram
#ሐምሌ_27

ሐምሌ ሃያ ሰባት በዚህች ቀን #ቅዱስ_አሞን በሰማዕትነት ዐረፈ፣ ኢትዮጵያዊቷ #ቅድስት_መስቀል ክብራ ዕረፍቷ ነው፣ የአዳም ልጅ #ቅዱስ_ሴት ዕረፍቱ ነው፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ሰማዕቱ_ቅዱስ_አሞን

ሐምሌ ሃያ ሰባት በዚህች ቀን ቅዱስ አሞን በሰማዕትነት ዐረፈ፡፡ ይኸውም ቅዱስ ተርኑጥ ከሚባል አገር የተገኘ ሰማዕት ነው፡፡ ወደ ላይኛው ግብጽ በሄደ ጊዜ የእንዴናው ገዥ ሰማዕታትን ይዞ በጽኑ ሲያሠቃያቸው ተመለከተ፡፡ እርሱም በመኮንኑ ፊት ቀርቦ የጌታችንን አምላክነት መሰከረ፡፡ መኮንኑም ይዞ ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው፡፡ ሥጋውን ሁሉ ሰነጣጥቆ ከጣለው በኋላ ዳግመኛ በትላልቅ ችንካሮች ቸነከረው፡፡ ነገር ግን ጌታችን አጽናንቶ ከቁስሉ ፈውሶ ጤነኛ አደርጎ አስነሣው፡፡

መኮንኑም ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ ቅዱስ አሞንን ወደ እስክንድርያ ከተማ ላከው፡፡ በዚያም ሳለ ጌታችን ተገለጠለትና ስሙን ለሚጠራና ገድሉን ለሚጽፍ በሕይወት መጽሐፍ እንደሚጽፍ ቃልከዳን ከገባለት በኋላ ሰማዕትነቱን በድል እንዲፈጽም ነገረው፡፡

ወዲያውም ይዘው ጽኑ በሆኑ ልዩ ልዩ ሥቃዮች አሠቃዩት፡፡ ጌታችንም ከመከራው እያዳነው ልዩ ልዩ ተአምራትን ስላደረገለት ይህንን ያዩ ብዙዎች ‹‹በቅዱስ አሞን አምላክ አምነናል›› እያሉ በመመስከር ሰማዕትነትን ተቀበሉ፡፡ እነርሱም ውስጥ ቲዮጲላ የምትባል ድንግል ነበረች፡፡ እርሷም ወደ መኮንኑ ዘንድ በመሄድ በጌታችን ታመነች፡፡ መኮንኑም እቶን እሳት ውስጥ ከተታት ነገር ግን እሳቱ አላቃጠላትም፡፡ በመጨረሻም ራሷን በሰይፍ ቆረጡትና የሰማዕትነት አክሊልን ተቀዳጀች፡፡

ከዚህም በኋላ አባለ ዘሩንና አካሉን ሁሉ በሰይፍ እየቆረጡ ቅዱስ አሞንን እጅግ ካሠቃዩት በኋላ አንገቱን በሰይፍ ቆረጡትና የሰማዕትነቱ ፍጻሜ ሆነ፡፡ በመንግሥተ ሰማያትም የክብር አክሊልን ተቀዳጀ፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_መስቀል_ክብራ

በዚህችም ቀን ኢትዮጵያዊቷ ቅድስት መስቀል ክብራ ዕረፍቷ ነው፡፡ ይኽችም ቅድስት የቅዱስ ላሊበላ ባለቤት ስትሆን የትውልድ ሀገሯ ወሎ ላስታ ቡግና ነው፡፡ የታላቁ ጻድቅ ንጉሥ የቅዱስ ላሊበላ ሚስት ናት፡፡ ከእርሱም ደገኛውን ይትባረክን ወልዳለች፡፡ ቅዱስ ላሊበላን እና ቅድስት መስቀል ክብራን ሁለቱ እንዲጋቡ ያዘዛቸው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ቅዱስ ላሊበላን ወደ ሰማይ ነጥቆ ወስዶ የሚያንጻቸውውን የሕንጻ ዲዛኖችና ሌሎችንም ብዙ ምሥጢራትን ካሳየውና ወደ ምድር ከመለሰው በኃላ ድጋሚ ተገልጦለት "እንዳንተ የተመረጠች ናት እንደ ልብህም ትሆናለች፣ ሥራዋም ከሥራህ አያንስም እርሷ የተመረጠች የእግዚአብሔር አገልጋይ ናትና" በማለት መልአኩ የቅድስት መስቀል ክብራን ንጽሕናና ቅድስና መስክሮላታል፡፡

ቅዱስ ላሊበላ 11 እጅግ አስደናቂ የሆኑ ፍልፍል ቤተ መቅደሶቹን ከመላእክት ጋር ሲያንጽ ብታየው ልቧ በመንፈሳዊ ተመስጦ ተመልቶ እርሷም እግዚአብሔር ፈቅዶላት አስደናቂውን የአባ ሊባኖስን ቤተመቅደስ ራሷ እንዳነጸችው መጽሐፈ ገድሏና ገድለ ቅዱስ ላሊበላ ያስረዳል፡፡

ቅድስት መስቀል ክብራን ወደ ትግራይ እየመራ የወሰዳት መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ እርሷን በትግራይ ቅዱስ ሚካኤል እንዲጠብቃት ከተዋት በኃላ ቅዱስ ላሊበላን ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ መንግሥተ ሰማያት አውጥቶታል፡፡

ቅድስት መስቀል ክብራም በትግራይ ሆና መልአኩ እየጠበቃት ከሰው ተለይታ በታላቅ ተጋድሎ ኖረች፡፡ በቀን እልፍ እልፍ እየሰገደች በታላቅ ተጋድሎ ስትኖር ጌታችን ተገልጦ ክብሯ ከ36ቱ ቅዱሳት አንስት ጋር እኩል መሆኑን ነግሯታል፡፡

ይኽችም ቅድስት ብዙ ሐዋርያዊ አገልግሎት ፈጽማለች፡፡ ለምሳሌ በመስቀል ጦርነት ጊዜ እስላሞች ከባሕር ማዶ እየፈለሱ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በፍቅር እየተቀበለችና እያስተናገደች ሃይማኖትንና ሕገ እግዚአብሔርን እያስተማረች ወደ ክርስትና እንደገቡና እንዱጠመቁ አድርጋለች፡፡

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ሴት_ነቢይ

ዳግመኛም በዚህች ቀን የአዳም ልጅ ሴት ዕረፍቱ ነው፡፡ እርሱም ሁለት መቶ አምስት ዓመት ኖረ፡፡ ሔኖስንም ወለደው፡፡ ሔኖስንም ከወለደ በኋላ ሰባት መቶ ሰባት ዓመት ኖረ፡፡ ወንዶችንና ሴቶች ልጆችንም ወለደ፡፡ መላ ዕድሜውም ዘጠኝ መቶ ዐሥራ ሁለት በሆነ ጊዜ በሰላም ዐረፈ፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ እና #ከገድላት_አንደበት)
††† እንኳን ለአበው ቅዱሳን ሴት : ሕዝቅኤል ነቢይ እና ዮሐንስ ወንጌላዊ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††

††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

††† ቅዱስ ሴት ነቢይ †††

††† አባታችን ሴት የመጀመሪያዎቹ ፍጥረቶች የአዳምና ሔዋን የተባረከ ልጅ ነው:: ቀደምተ ፍጥረት አዳም እና ሔዋን በዕጸ በለስ ምክንያት ከገነት ከተባረሩ በኋላ በመጀመሪያ ቃየን እና አቤልን ከነ መንትያዎቻቸው ወልደው ነበር::

ነገር ግን የልጅ ደስታቸው ቀጣይ ሊሆን አልቻለም:: ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ቃየን ሲሆን ወንድሙን አቤልን በጾታዊ ፍላጐት ምክንያት በመግደሉ ነበር:: የአቤል ሞት ለአባታችን አዳም መራር ዜና ነበር:: ወላጅ እንኳን ደጉን ይቅርና ክፉ ልጁም እንዲለየው አይፈልግምና::

ቅዱስ አዳም ቅዱስ አቤልን ቀብሮ: ፈጽሞ አለቀሰ:: ልቅሶውም እንዲሁ የወርና የሁለት ወር አልነበረም:: አራት ኢዮቤልዩ (ሃያ ስምንት ዓመታት) ነበር እንጂ:: ይህንን ሐዘንና ልቅሶ የተመለከተ እግዚአብሔር ደግሞ ደግ ፍሬን በሔዋን ማኅጸን ውስጥ አሳደረ::

ይሕ ሕፃን በተወለደ ጊዜ "ሴት" ብለው ስም አወጡለት:: ትርጉሙም "የአቤል ምትክ" እንደ ማለት ነው:: ሴት ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በብዙ ነገሩ አዳምን የሚመስል ነበረ:: ደም ግባቱ: ቅንነቱ: ታዛዥነቱ: ደግነቱ ሁሉ ልዩ ነበር:: በዚህም አዳምና ሔዋን ተጸናንተዋል::

ትልቁ ነገር ደግሞ ዓለም የሚድንባት እመቤት ድንግል ማርያም ከስልሳ በላይ የአዳም ልጆች ተመርጣ ለቅዱስ ሴት መሰጠቷ ነው:: ይሕንን ምሥጢርና የሴትን ማንነት ያስተዋለው ሊቁ አባ ሕርያቆስ እመ ብርሃንን እንዲህ ሲልም አመስግኗታል::
"ሒሩቱ ለሴት - የሴት ደግነቱ: በጐነቱ: ቅንነቱ አንቺ ነሽ" (ቅዳሴ ማርያም)

አባታችን ሴት በሚገባው ትዳር ተወስኖ ቅዱስ ሔኖስንና ሌሎች ብዙ ልጆችን ወልዷል::

አባታችን አዳም ባረፈ ጊዜ የዚህን ዓለም እረኝነት (በደብር ቅዱስ ላሉት) ተረክቧል:: አዳምም ልጆቹንና ወርቅ እጣን ከርቤውን አስረክቦታል:: ሴት እንባው እንደ ዥረት እየፈሰሰ አስቀድሞ አዳምን: አስከትሎም ሔዋንን ገንዞ በክብር ቀብሯቸዋል::

ወርቅ: እጣን: ከርቤውን ከሥጋቸው ጋራ በቤተ መዛግብት (በተቀደሰው ዋሻ) ውስጥ አኑሮታል:: የአገልግሎት ዘመኑ በተፈጸመ ጊዜ ደጉ ሴት ኃላፊነቱን ለልጁ ሔኖስ ሰጥቶ በዘጠኝ መቶ አሥራ ሁለት ዓመቱ ዐርፏል:: እርሱም ከወላጆቹ አዳምና ሔዋን ጋር ተቀላቅሏል::

††† ቅዱስ ሕዝቅኤል ነቢይ †††

††† ነቢዩ ቅዱስ ሕዝቅኤል የነበረው ቅ/ል/ክርስቶስ በ500 ዓመት አካባቢ ሲሆን የጼዋዌ (ምርኮ) አባልም ነበር:: እሥራኤልና ይሁዳ ወደ ባቢሎን በምርኮ ሲወርዱ አብሮ ወርዷል:: ቅዱሱ ከአራቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ ሲሆን ሐረገ ትንቢቱም በአርባ ስምንት ምዕራፎች የተዋቀረ ነው::

በዘመኑ ሁሉ ቅድስናን ያዘወተረው ቅዱሱ ከደግነቱ የተነሳ በጸጋማይ (ግራ) ጐኑ ተኝቶ ቢጸልይ ስድስት መቶ ሙታንን አስነስቷል:: ወገኖቹ እሥራኤልንም ያለ መታከት አስተምሯል:: ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህች ዕለት ታላቁን ራዕይ እንዳየ ታስተምራለች:: ነቢዩ በፈለገ ኮቦር ካያቸው ምሥጢራት እነዚህን ያነሷል:-
1.እግዚአብሔርን በዘባነ ኪሩብ ተቀምጦ ሲሠለስና ሲቀደስ አይቶታል:: የኪሩቤልንም ገጸ መልክእ በጉልህ ተመልክቷል:: (ሕዝ. 1:1)

2.በመጨረሻው ቀን ትንሣኤ ሙታን : ትንሣኤ ዘጉባኤ እንደሚደረግም ተመልክቷል:: (ሕዝ. 31:1)

3.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ኆኅት ኅትምት/ኆኅተ ምሥራቅ (የምሥራቅ ደጅ) ሁና አይቷታል::

ይሕ የምሥራቅ ደጅ (በር) ለዘላለም እንደታተመ ይኖራል:: የኃያላን ጌታ ሳይከፍት ገብቶ: ሳይከፍት ወጥቷልና:: (ሕዝ. 44:1)
በመጨረሻ ሕይወቱ እሥራኤል ለክፋት አይቦዝኑምና ነቢዩን አሰቃይተው ገድለውታል::

††† ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ †††

††† አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ እንደነገረን በመንግስተ ሰማያት ታላቁ ሰው ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው::

ቅዱሱ ሐዋርያ ከዘብዴዎስ እና ከማርያም ባውፍልያ ተወልዶ : በገሊላ አካባቢ አድጐ : ገና በወጣትነቱ መድኃኔ ዓለምን ተከትሎታል:: ቅዱስ ዮሐንስ ከሐዋርያት ቀድሞ ጌታን ከመከተሉ ባሻገር በምንም ምክንያት ከጐኑ አይጠፋም ነበር:: ስለ ንጽሕናውና በጐ የፍቅር ሕሊናው ሕፃን ሳለ በወንድሞቹ ሐዋርያት ዘንድ ሞገሱ ከፍ ያለ ነው::

ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ድንግል እመቤታችንን ተቀብሏል:: ከእርሷ ጋር ለአሥራ አምስት ዓመታት ቢቀመጥ መዝገበ ምሥጢር ሆነ:: ስንኳን ከሰው ልጆች ይቅርና ከልዑላኑ መላእክትም ማዕረጉ ከፍ አለ:: ሰው ቢበቃ መላእክትን ሊያይ ይቻለዋል:: ቅዱስ ዮሐንስን ግን መላእክት ሊያዩት ይከብዳቸዋል:: ከፍጥረት ወገን ከእመ ብርሃን ቀጥሎ ክቡር እርሱ ነው::

በዚህ ቀንም ቅዱስ ዮሐንስ በታናሽ እስያ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መስበኩ ይታሰባል:: ቅዱሱ ከጌታችን ዕርገት በኋላ ለሰባ ዓመታት በዚህ ምድር ሲኖር አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው በኤፌሶን አካባቢ ነው:: ሕዝቡን ወደ ክርስትና ለማምጣት በአፍም : በመጽሐፍም ደክሟል::

ሦስት መልዕክታት : ራዕዩንና ወንጌልን ጽፎላቸዋል:: ሕይወትን ስለ ሰበከላቸው በፈንታው ብዙ አሰቃይተውታል:: ከእሳት እስከ ስለት : እስከ መጋዝም በስተእርጅና ደርሶበታል:: እርሱ ግን በትእግስቱ ገንዘብ አድርጓቸዋል:: ዳግመኛ ይሕች ዕለት ለሐዋርያው ቅዳሴ ቤቱ ናት::

††† እናት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን ስትጠራው እንዲሕ ነው:-
¤ወንጌላዊ
¤ሐዋርያ
¤ሰማዕት ዘእንበለ ደም
¤አቡቀለምሲስ(ምሥጢራትን ያየ)
¤ታኦሎጐስ (ነባቤ መለኮት)
¤ወልደ ነጐድጓድ
¤ደቀ መለኮት ወምሥጢር
¤ፍቁረ እግዚእ
¤ርዕሰ ደናግል (የደናግል አለቃ)
¤ቁጹረ ገጽ
¤ዘረፈቀ ውስተ ሕጽኑ ለኢየሱስ (ከጌታ ጎን የሚቀመጥ)
¤ንስር ሠራሪ
¤ልዑለ ስብከት
¤ምድራዊው መልዐክ
¤ዓምደ ብርሐን
¤ሐዋርያ ትንቢት
¤ቀርነ ቤተ ክርስቲያን
¤ኮከበ ከዋክብት

††† በቅዱስ ዮሐንስ ላይ ያደረ የእመቤታችን ድንግል ማርያምና የአንድ ልጇ ፍቅር በእኛም ላይ ይደር:: የሴት ደግነቱ : የሕዝቅኤልም በረከቱ ይደርብን::

††† ሐምሌ 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ሴት ነቢይ (ወልደ አዳም)
2.ቅዱስ ሕዝቅኤል ነቢይ
3.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ (ቅዳሴ ቤቱ)
4.ቅዱስ አሞን ሰማዕት

††† ወርኀዊ በዓላት
1.የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ ስቅለት
2.አቡነ መብዐ ጽዮን ጻድቅ
3.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)
4.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
5.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
6.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
7.ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት

††† ". . . "እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም" ይላል ጌታ እግዚአብሔር:: "የእሥራኤል ቤት ሆይ! ተመለሱ:: ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ:: ስለ ምንስ ትሞታላችሁ?" በላቸው::" †††
(ሕዝ. ፴፫፥፲፩)

††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
#ሐምሌ_28

ሐምሌ ሃያ ስምንት በዚህች ቀን የደብረ ሊባኖሱ #አቡነ_ፊሊጶስ ዕረፍታቸው ነው፣ ክርስቶስን የሚወዱ #የቅዱስ_እንድራኒቆስና የሚስቱ #የቅድስት_አትናስያ መታሰቢያቸው ነው።


✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አቡነ_ፊልዾስ_ጻድቅ (ዘደብረ ሊባኖስ)

ሐምሌ ሃያ ስምንት በዚህች ቀን የደብረ ሊባኖሱ አቡነ ፊሊጶስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ የደብረ ሊባኖሱ አቡነ ፊሊጶስ፡- በተወለዱ በ15 ዓመታቸው በምናኔ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገቡ፡፡ ከብዙ ጊዜ አገልግሎትም በኋላ በአቡነ ተክለሃይማኖት እጅ መንኩሰው ከእርሳቸውም ዕረፍት በኋላ ሦስተኛ አበምኔት ሆነው አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከተወለዱት የመጀመሪያ ፓትርያርክ ሆነዋል፡፡

አባታቸው ቅዱስ ተክለሃይማኖትም በመንፈቀ ኢትዮጵያ ጳጳስ ሆነው ነበር፡፡ በመጀመሪያ የአቡነ ፊሊጶስን የጽድቅ ሕይወትና ሹመታቸውን በተመለከተ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድልና በራሳቸው በአቡነ ፊሊጶስ ገድል ላይ የተጻፈውን እንመልከት፡- ‹‹ክቡር አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ከዚህ ዓለም ተለይቶ የሚሄድበት ጊዜ ሲደርስ ‹ከአንተ በኋላ አንተን ተክቶ በዙፋንህ የሚቀመጥ ማነው?› አሉት፡፡ እርሱም ‹ብዙ ዘመን አይኖርም እንጂ ኤልሳዕ በእኔ ተተክቶ ይቀመጥ› አለ፡፡ ስለ ፊሊጶስ ግን አላነሳም፣ ኤልሳዕ ካረፈ በኋላ በእርሱ ተተክቶ አባት ይሆን ዘንድ ጌታችን የተሸለመ ፊሊጶስን እንደመረጠው ስም አጠራሩ ለልጅ ልጅ ዘመን እንደሚጸና ያውቅ ነበርና ስለዚህ ‹አልሳዕ በእኔ ተተክቶ አባት ይሁናችሁ› አለ፡፡ ክቡር አባታችንም በታላቅ ክብር ዐረፈ፡፡

አንድ ቀን አንድ ዲያቆን ዐረፈና ሬሳውን ገንዘው አጠቡት፣ ይቀብሩትም ዘንድ አስክሬኑን ይዘው ሲሄዱ በአልጋ ላይ ሳለ አስክሬኑ ተንቀሳቀሰ፡፡ የተሸከሙትም ደንግጠው መሬት ላይ አስቀመጡትና ከመግነዙ ፈቱት፡፡ እርሱም ተነሥቶ ሦስት ጊዜ ተነፈሰ፡፡ ወንድሞችም ‹ምን እያልክ ነው?፣ ወዴትስ ነበርክ?› አሉት፡፡ ያ የከበረና የተመረጠ ዲያቆንም ‹ክቡር አባታችን ተክለሃይማኖት ‹ኤልሳዕ ወደኔ ይምጣ፣ ፊሊጶስ ስለ እኔ ተሹሞ በወንበሬ ይቀመጥ እርሱ ለብዙዎች አሕዛብ አባት ይሆናልና የክርስቶስንም መንጋ በጽድቅና በቅን ይጠብቃል› ብሎኛል› ብሎ ይህን ተናግሮ ተመልሶ ዐረፈ፡፡ ወንድሞችም ኤልሳዕ እንደልማዱ ጎኑን ሳያሳርፍ በወንበር ላይ እንደተደገፈ በሞት ማረፉን አላወቁም ነበር፡፡››
ወደ ጻድቁ የልጅነት ገድላቸው እንመለስና አቡነ ፊሊጶስ በእግዚአብሔር ተመርጠው የመንፈስ ቅዱስም ማደሪያ ሆነዋልና ገና በሕፃንነታቸው በተወለዱባት ሰላሌ ክፍለ ሀገር ዝማ በምትባል ልዩ ቦታ ውስጥ ሰይጣን በጠንቋይ ላይ አድሮ በነደደ በእሳት ውስጥ በመግባትና የተለያዩ ተአምራትን በማድረግ በአካባቢው ራሱን ያስመልክ የነበረን ሰይጣን በእሳት ውስጥ እንዳለ በስመ ሥላሴ አማትበውበት አመድ አድርገውታል፡፡ በዚህ በአቡነ ፊሊጶስ ድንቅ ተአምር የጠንቋዩ ቤተሰቦችና የአካባቢው ሰዎችም አምነው ሊጠመቁ ችለዋል፡፡ ይህንንም ያደረገው ገና ሕፃን ሳለ ነው፡፡ መልአከ እግዚአብሔር ተገልጦለት የትውልድ መንደሩን ትቶ ወደ ግራርያ ሀገር ደብረ አስቦ ሄዶ ቅዱስ ተክለሃይማኖትን እንዲያገኝ በነገረው መሠረት አንድ ቀን ያህል ተጉዞ ተክለሃይማኖትን አገኛቸውና ባርከውት ከመነኮሳት ጋር እንዲያርፍ አደረጉት፡፡ ሦስት ዓመት እነርሱን በመልካም ሥራ ፍጹም ሆኖ ሲያገለግላቸው ከቆየ በኋላ ‹‹ሁሉም በአንድነት አሁን ልብሰ ምንኩስና ይገባዋል›› አሉ፡፡ ቅዱስ አባታችን ተክለሃይማኖትም የምንኩስናን ሥራ የሚያሠራ ቅድስናን ሰጠው፡፡

በሌላም ጊዜ ቅስናን ይቀበል ዘንድ ወደ ጳጳሱ ዘንድ ላኩት፡፡ አቡነ ፊሊጶስ በንጉሥ አምደ ፅዮን ዘመነ መንግሥት ሥጋቸው አልቆ አጥንታቸው እስኪቀር ድረስ ሲገረፉ ደማቸው እሳት ሆኖ ገራፊዎቻቸውን ያሳደደ ቅዱስና ጻዲቅ አባት ናቸው፡፡ ንጉሥ አምደ ጽዮን በክፉ ጠንቋዮች ምክር ተታሎ ‹‹ያልወለደችህን የአባትህን ሚስት ብታገባ መንግሥትህ ትፀናለች›› ብለው ክፉ ምክርን መክረውት የእንጀራ እናቱን አገባትና ንግሥት አደረጋት፡፡ አቡነ ፊሊጶስም ይህን ሲሰሙ ነቢዩ ኤልያስ ንጉሡ አክአብንና አልዛቤልን በድፍረት እንደገሠጻቸው እርሳቸውም በቀጥታ ሄደው ንጉሡን ዘልፈው ገሠጹት፡፡ ወደ ንጉሡም ከመሄዳቸውም በፊት በዚህ ምክንያት ሰማዕት እንደሚሆኑ አውቀውት ነበርና ልጆቻቸውን ተሰናብተውና የሚተካቸውን ሰው ነግረዋቸው ነው የሄዱት፡፡ ንጉሡ አምደ ጽዮንም አጥንታቸው እስኪቀር ድረስ አስገረፋቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቶቻቸውም መሬት ላይ እየተቆረሰ የወደቀውን ሥጋቸውን እያነሱ ለበረከት ወሰዱት፡፡ ደማቸውም እንደ እሳት ሆኖ ገራፊዎቻቸውን ያቃጥላቸው ነበር፡፡ 300 አንስራ ውኃ አምጥተው ከደሙ በወጣው እሳት ላይ ቢያፈሱትም የውኃው ብዛት እሳቱን ማጥፋት አልቻለም፡፡ ንጉሡም በፍርሃት ከዙፋኑ ላይ ወርዶ ሸሸ፡፡

የንጉሡ ጭፍሮች ግን በጋለ ማረሻ ጀርባና ግንባራቸውን ደረታቸውንም ተኮሷቸው፡፡ ኃፍረታቸውንም እንዳይሸፍኑ እጆቻቸውን ወደ ኋላ አስረው ራቁታቸውንም በከተማው ሁሉ ሲያዞሯቸው ዋሉ፡፡ ማታም ንጉሡ ‹ታስረው ለኖሩ ኃይለኛ ውሾች ስጡት› ብሎ በማዘዝ ውሾቹ እንዲቦጫጭቋቸው ቢያደርጉም ውሾቹ ግን ከእግራቸው ስር ሰግደዋል፣ እርሳቸውም በእግራቸው ባረኳቸው፡፡ አማካሪዎቹም ንጉሡን ‹‹ከዚህ መነኩሴ ጋር ምን አጨቃጨቀህ በግዞት አርቀህ ስደደው ብለው›› ብለው መክረውት ‹‹እስከ ቆርቆራ አገር አውጥታችሁ ወደ ትግሬ አገር ውሰዱት›› ብሎ አዘዘ፡፡ እርሳቸውም ንጉሡን ከ3 ዓመት በኋላ ትሞታለህ ብለው ትንቢት ነገረውት በወታደሮች ተወሰዱ፡፡

በግርፋት ብዛት የተቆረሰ ሥጋቸው ድውያንን ይፈውስ ነበር፡፡ ደማቸውም አስረው የሚወስዷቸውን የአንዱን ወታደር አንድ ስውር ዐይኑን ፈወሰለትና ወታደሮቹም አምነው ከእርሳቸው ጋር በዚያው ተሰደው መከራን ተቀብለዋል፡፡ እሳቸው በትግራይ ታላላቅ ተአምራትን እያደረጉ ሲያስተምሩ በትንቢታቸው መሠረትም ንጉሡ ከሦስት ዓመት በኋላ ሞተና ልጁ ነገሠ፡፡ ልጁም አባታችንን ከስደት መለሳቸውና ከተክለሃይማኖት መቃብር ደብረ አስቦ ገቡ፡፡ የነገሠውንም ልጅ አንድ ክፉ ሰው ‹‹ከአንድ በላይ ማግባት ትችላለህ፣ በገና ወቅትም ረቡዕና አርብን መጾም ተገቢ አይደለም›› ብሎ ስለመከረው ጳጳሱን ወደ ሀገራቸው ግብፅ እንዲሰደዱ ሲያደርግ አቡነ ፊሊጶስን ደግሞ ‹‹ረቡዕና አርብን በጠዋት ካልቀደስክ›› ብሎ ወደ ደራ ተሰደው እንዲሄዱ አደረገ፡፡

አባታችን በአጠቃላይ አምስት ጊዜ ተሰደው በትግራይ፣ በደራ፣ በዝዋይ ባሕረ ደሴት፣ በዳሞት ገማስቄ እና በወለቃ በስደት ቆይተዋል፡፡ ጳጳሱን አባ ሰላማን በአቃሊት ቅበረኝ ብለዋቸው በቃሬዛ አድርጎ ከጌርጌሳ ወደ አቃሊት ወሰዷቸው፤ እዚያም ሐምሌ 28 ቀን በሰላም ዐረፉ፡፡ አጽማቸውም ከተቀበረ ከ140 ዓመት በኋላ በመጋቢት 23 ቀን ወደ ደብረ ሊባኖስ በክብር መጥቶ ዐርፏል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰባት አክሊላት አቀዳጅቷቸዋል፡፡

ስለ አሁኑ ዘመን የአቡነ ፊሊጶስ ትንቢት!፡- በወቅቱ የነበሩት ጳጳስ አባ ያዕቆብ በብዙ ልመናና ምክር አቡነ ፊሊጶስን ጳጳሱ ራሱ የሚለብሰውን የክብር ልብስ አልብሶ በሸዋ አገር ላይ ኤጲስ ቆጶስነት ሾመው፡፡ ከተሾሙም በኋላ አቡነ ፊሊጶስን ‹ሌሎችን ሹምልን› የሚሉ በርካቶች ሲያስቸግሯቸው እሳቸው የሰጡት ምላሽ ‹‹በሥልጣን ፍለጋ ምክንያት ይህችን የትርህምትና የፅሙናን ቦታ (ደብረ ሊባኖስን) የጨዋታ የተድላ ቦታ እናደርጋታለን›› በማለት በወቅቱ ማንንም አልሾምም ብለው ነበር፡፡ አያይዘውም በዚሁ በሹመት ሽኩቻ ምክንያት ወደፊት
የሚፈጠረውን ነገር በመንፈስ ቅዱስ መነፅርነት አይተውት የሚከተለውን ትንቢት ተናግረዋል፡- ‹‹እውነት እላችኋለሁ በመጨረሻው ዘመን ደጋጎች ሰዎችን ክፉዎችና ተሳዳቢዎች የሚያደርጉ፣ ሐሰተኞችና ዋዛ ፈዛዛ የሚወዱትን ደጋጎች የሚያደርጉ ሰዎች ይመጣሉ፡፡

በመጨረሻው ዘመን ኃጥአን በጻድቃን ይመሰላሉ፣ ጻድቃንን ኃጢአተኞች ያደርጓቸዋል፡፡ በዚያን ዘመን እውነተኛዎቹ መምህራን አይሾሙም፣ ኃጢአተኞች መማለጃ ሰጥተው ወሬ እያቀበሉ ይሾማሉ፣ እንደ እባብ ክፉ ነገርን ለማድረግ ፍላፃቸውን ያሾሉ ደጋግ ሰዎችን በነገር ያጠፏቸው ዘንድ በእውነት ንጹሕ የሆኑትን ሰዎች አመፅን በተመላ አንደበታቸው ሹመትን ከመውደድ የተነሣ በቅናት ያጠፏቸዋል፡፡ በዚያን ዘመን መጻሕፍትን የሚያውቁ አይሾሙም፣ ነገርን የሚያመላልሱና የአገሮችን ቋንቋ የሚያውቁ ከመኳንንትና ከነገሥታት ዘንድ ሔደው ነገርን የሚሠሩ ሰውን የሚያጣሉ በአመፅ ሹመትን የሚያገኙ ብቻቸውን ይሾማሉ እንጂ ደጋጎች አይሾሙም፡፡ በሚመረጡበትም ጊዜ ከአባታቸው ከሰይጣን ጋር ሆነው ‹እገሌ መጻሕፍትን ያውቃል፣ የአገሮችን ቋንቋ የሚያውቅ ይሾም› ይላሉ፡፡ ያንጊዜም አመፅ ይበዛል፣ ፍቅርም ትጎድላለች፡፡ ከእኔ በኋላ የሚሆነውን እነሆ ነገርኳችሁ ይህንንም አውቃችሁ በልቡናችሁ ያዙ፡፡››
ጌታችን ለአቡነ ፊሊጶስ የገባላቸው ልዩ ቃልኪዳን፡- ‹‹ገድልህንና ስለ እኔ የታገስከካቸውን መከራዎችህን የጻፈውን ከሁላቸው ከቅዱሳንና ከሰማዕታት ጋር በሰማያዊት ኢየሩሳሌም በወርቀ ቀለም ለዘለዓለሙ ስሙን እጽፍልሃለሁ፡፡ ሥጋህ ከተቀበረበት ቦታ ይቅርታዬንና ቸርነቴን አደርጋለሁ፡፡ መቃብርህ የበረከት ቦታ ትሆናለች፡፡››

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_ጻድቃን_እንድራኒቆስና_አትናስያ

በዚህች ቀን ክርስቶስን የሚወዱ የእንድራኒቆስና የሚስቱ የአትናስያ መታሰቢያቸው ነው። እነርሱም ከአንጾኪያ ከተማ ነበሩ። በወርቅና በብርም የከበሩ ባለጸጎች ነበሩ ከገንዘባቸውም ለድኆችና ለችግረኞች ይሰጡ ነበር።

ከዚህም በኃላ አንድ ወንድ ልጅና አንዲት ሴት ልጅን ወለዱ ወንዱን ዮሐንስ ሴቲቱንም ማርያም ብለው ሰየሟቸው ልጆችም አደጉ እንዱራኒቅስና ሚስቱም እንግዳ በመቀበል ለድኆችና ለምስኪኖች በመመጽወት በጎ ሥራን አበዙ እነርሱም መገናኘትን ትተው ሰውነታቸውን በንጽሕና ጠበቁ።

ልጆቻቸውም ዐሥራ ሁለት ዓመት በሆናቸው ጊዜ የሆድ ዝማ በሽታ ታመው በአንዲት ቀንም ሞቱ እንዲራኒቆስም አይቶ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሥዕል ፊት ራሱን ጥሎ እንዲህ ብሎ አለቀሰ ከእናቴ ማሕፀን ራቁቴን ወጣሁ ወደ እግዚአብሔርም ራቁቴን እሔዳለሁ እርሱም ሰጠ እርሱም ወሰደ የእግዚአብሔር የጌትነቱ ስም የተባረከ ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

እናታቸውም ለሞት እስከምትደርስ እጅግ አዘነች ልጆቿ ወደ ተቀበሩበት ወደ ዐፀደ ቤተ ክርስቲያን ሔደች ከኀዘንዋም ብዛት የተነሳ አንቀላፋች በእንቅልፏም ውስጥ በልጆችሽ ሞተ አታልቅሺ እነርሱ ግን በሰማያት ደስ እያላቸው ናቸው እያለ በመነኰስ አምሳል ሲነግራት አየች። ይህንንም ሰምታ ሒዳ ለባሏ ነገረችው።

ከዚህም በኃላ ይህን ዓለም ይተዉ ዘንድ ተስማሙ ገንዘባቸውንም ሁሉ ምንም ሳያስቀሩ ለድኆችና ለጦም አዳሪዎች ሰጡ በሌሊትም ወጥተው ወደ እስክንድርያ ከተማ ደረሱ ሚስቱንም በዚያ ትቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ በአባ ዳንኤል ዘንድ መነኰሰ። ከዚያም ተመልሶ ሚስቱ አትናስያን ወደ ሴቶች ደናግል ገዳም ወሰዳት በዚያም ተዋት።

ከዐሥራ ሁለት ዓመትም በኃላ እንድራኒቆስ ከቅዱሳት መካናት ይባረክ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሔድ አባ ዳንኤልን ለመነው ፈቀደለትም በመድኃኒታችንም ቸርነት ሚስቱ አትናስያ በወንድ አምሳል በጉዞ ላይ ተገናኘችው ሚስቱ እንደሆነችም አለወቀም እርሷ ግን አወቀችው ነገር ግን ሚስቱ እንደሆነች አልገለጠችለትም።

ወደ ቅዱሳት መካናትም በደረሱ ጊዜ ሥራቸውን ፈጽመው ወደ አባ ዳንኤል በአንድነት ተመለሱ። አባ ዳንኤልም ሚስቱ እንደሆነች በመንፈስ ቅዱስ አውቆ እንድራኒቆስን ባልንጀራ ካደረግኸው ከዚህ መነኰስ ጋራ በአንድ ቦታ ኑሩ እርሱ ቅዱስ ነውና አለው። ዐሥራ ሁለት ዓመትም በአንድነት ኖሩ ማንም የአወቀ አልነበረም።

አባ ዳንኤልም ይጎበኛቸውና ስለ ነፍሳቸው ጥቅም ያስተምራቸው ነበር። ከዚህም በኃላ አትናስያ በታመመች ጊዜ ለእንድራኒቆስ አባታችንን አባ ዳንኤልን ጥራልኝ አለችው ሒዶም ለአባ ዳንኤል እንዲህ ብሎ ነገረው ባልንጀራዬ ታሞ ለመሞት ተቃርቧልና ትጎበኘው ዘንድ ና። በደረሰም ጊዜ በታላቅ ሕመም ላይ አገኛት እርሷም ታቆርበኝ ዘንድ እሻለሁ አለችው ያን ጊዜም ተፋጠነና ሥጋውንና ደሙን አቀበላት ከዚህም በኃላ አረፈች በሚገንዟትም ጊዜ ሴት እንደሆነች አገኙ ዳግመኛም ታሪኳንና ለባሏ የረወቻቸውን ምልክቶች አገኙ።

እንድራኒቆስም በአነበበ ጊዜ እርሷ ሚስቱ እንደሆነች አወቀ ደንግጦም ልቡ ተሠወረ ፊቱንም እየጻፈ ጮኸ ያለቅስ ጀመረ።ከጥቂት ቀን በኃላም ታመመ አረጋውያንም መጥተው በረከቱን ተቀበሉ ሥጋውንና ደሙንም ተቀበሉ በሰላም አረፈ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ እና #ከገድላት_አንደበት)
#ሐምሌ_29

ሐምሌ ሃያ ዘጠኝ በዚች ቀን #አቡነ_ዮሐንስ_ዘጠገሮ ዕረፍታቸው ነው፣ #የቅዱስ_ሐዋርያ_ታዴዎስ የሥጋው ፍልሰት ሆነ፣ #ቅዱስ_ወርስኖፋ በሰማዕትነት አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#እጨጌ_አባ_ዮሐንስ_ዘጠገሮ (ዘጐንድ)

ሐምሌ ሃያ ዘጠኝ በዚች ቀን አቡነ ዮሐንስ ዘጠገሮ ዕረፍታቸው ነው፡፡ ጻድቁ አባታችን የተወለዱት በኢየሩሳሌም አውራጃ ልዩ ስሙ ሳሬራ በሚባል ቦታ ነው፡፡ የካቲት 28 ቀን ተፀንሰው ህዳር 29 ተወለዱ፡፡ አባታቸው ድላሶር እናታቸው እምነ ጽዮን ይባላሉ፡፡ ሲወለዱ በወላጆቻቸው ቤት ውስጥ ብርሃን ወርዷል፡፡ ወላጆቻቸውም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ደጋግ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ አባታችን ገና በተወለዱ በ5 ዓመታቸው ወላጆቻቸው ወደ እግዚአብሔር ቤት ይዘዋቸው የእመቤታችንን ሥዕል ተመልክተው በደስታ ተመልተው ሳቁ፡፡ አምላክን የወለደች የብርሃን እናቱ እመቤታችንም ከምሥሉ ወጥታ ‹‹በምን አውቀኸኝ ነው?›› ብላ አቅፋ ሳመችውና ‹‹ከእንግዲ ወዲህ የልጄ አገልጋይ ትሆናለህ ኑሮህም እንደ መላእክት ይሆናል በአንተ ምክንያት ብዙ ሰዎች ይድናሉ በምድር ላይም 500 ትኖራለህ…›› ብላ ባርካው ተሰወረች፡፡

ከዚያችም ቀን ጀምሮ አባ ዩሐንስ ለክርስቶስ ተላልፎ ተሰጠ፡፡ 50 ዓመትም በበረሃ ሲጋደል ኖሮ ከ50 ዓመት በኃላ በደመና ተጭኖ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል መሪነት ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ መጡ፡፡ ጻድቁ አባታችን በአቡነ ተክለሃይማኖት ዘመን መጨረሻ የመጡ ሲሆን ምንኩስና ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ተቀብለው በዚያው በድብረ ሊባኖስ ገዳም ለ50 ዓመት በጾምና በጸሎት በተጋድሎ ኖዋል፡፡ ከዚኽም በኋላ አባ ዩሐንስ ወደ ተዘጋቸላቸው ምድር በቅዱስ ገብርኤል አሳሳቢነት ወደ ጠገሮ መጡ፡፡ ይኽም ጠገሮ ያለው ገዳማቸው በሰሜን ሸዋ በመንዝና ይፋት ክልል መዘዞ በሚባል ቦታ ሲደርሱ በእግር አንድ ሰዓት ከተጓዙ በኃላ ይገኛል፡፡

ሕዝቡ በተለምዶ እጨ ዮሐንስ እያለ ይጠራቸዋል እንጂ ስማቸው እጨጌ ዮሐንስ ነው፡፡ አቡነ እጨጌ ዮሐንስ መስቀል ከሰማይ የወረደላቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ መስቀሉም ሁልጊዜ ተአምር ይሠራል፡፡ በልደታቸው ቀን ኅዳር 29 ቀን መስቀሉ ከመቅደሱ ወጥቶ በካህናቱ ታጅቦ ወደ ጸበሉ ሲወርድ ከየት እንደመጣ ሳይታሰብ ደመና መጥቶ ከመስቀሉ ላይ ብቻ እረቦና እንደ ጃንጥላ ተዘርግቶ አብሮ ወደ ጸበሉ ይወርዳል፡፡ እዛው ቆይቶ መስቀሉ ሲመለስም አብሮ አጅቦ ይመለስና መስቀሉ ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲገባ ደመናው ወዴት እንደተበተነ ሳይታወቅ ይጠፋል፡፡ ይህ በዘመናችንም ጭምር እየታየ ያለ ታላቅ ተአምር ነው፡፡

አባታችን በታላቀ ተጋድሎ ሣሉ ሰይጣን የሀገሩን ሰዎች በጠላትነት እንዲነሡባቸው አደረገ፡፡ ሰዎቹም አባታችንን እንዴት እንደሚያጠፏቸው ይማከሩ ጀመር፡፡ ሊገድሏቸው ፈልገው ቅድስናቸው በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነውና ፈሩ፡፡ ከዚኽም በኋላ ‹‹ለምን ከመንደራችን ከወንድ ያረገዘች ሴት ፈልገን እሳቸው አስረገዟት ብለን በሐሰት እንከሳቸው?›› ብለው ተማከሩ፡፡ ብዙ ወርቅና ብርም ለአንዲት ሴት ሰጥተው በሐሰት ከእርሱ አርግዣለሁ ብላ እንድትመሰክር አደረጓት፡፡ አባታችንም በሕዝብ ፊት በሐሰት ተከሰሱ፡፡ ጻድቁም ‹‹አንቺ ሴት ከእኔ ነው ያረገሽው?›› አሏት እርሷም ‹‹አዎ ከአንተ ነው ልትክድ ነው እንዴ?›› አለቻቸው፡፡ አባታችንም በዚህ አዝነው ‹‹በአንቺና በእኔ መካከል እግዚአብሔር ይፍረድ›› ሲሉ ያች ሴት ወዲያው ለሁለት ተሰንጥቃ ሞተች፡፡ የአገሩ ሰዎችም እጅግ ፈሩ፡፡ አባታችንም ምድሪቱን እረገሟት፡፡ ‹‹የተዘራው ዘር አይብቀልብሽ፣ የተተከለው አይፅደቅ፣ ብርድና ውርጭ ይፈራረቅብሽ›› ብለው እረግመዋት በደመና ተጭነው ወደ ሰሜን ጎንደር እስቴ ጉንደ ተክለተሃማኖት ሔዱ፡፡

አቡነ ዩሐንስ በመላው ኢትዮጵያ ወንጌልን እየተዘዋወሩ ያስተማሩ ሲሆን ከቅድስናቸው የተነሣ በፀሐይ ላይ 50 ዓመት፣ በጨረቃ ላይ 50 ዓመት፣ በደመና ላይ 50 እንዲሁም ዓለምን በክንፋቸው በመዞር በደመና ላይ 50 የኖሩ ከሰው ተወልደው ከመላእክት የተደመሩ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፡፡ በይፋት ጠግሮ በዓለወልድ፣ በአፋር አዘሎ፣ በመንዝ ፍርኩታ ኪዳነምሕረት፣ በደብረ ሊባኖስ፣ በጎንድ ተክለ ሃይማኖት በሌሎችም ቦታዎች በመዘዋወር በታላቅ ተጋድሎ ኖረዋል፡፡ አባታችን ከሰማይ መስቀል የወረደላቸው ሲሆን ዛሬም በገዳማቸው የሔደ ሰው በወረደው በእጃቸው መስቀል እየተዳበሰ ቆመው በጸለዩበት ባሕር በጠበላቸው ይጠመቃል፡፡ በተጨማሪም ይይዙት በነበረውም መቋሚያቸው በመዳበር በረከትን ማግኘት ይቻላል፡፡ ቆመው ከጸለዩበት ባሕር ውስጥ ደረቅ አሸዋ ይወጣል፡፡ አባ ዩሐንስ 500 ዓመት ከኖሩ በኃላ እረፍተ ዘመናቸው ሲደርስ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከ15 ነቢያት፣ ከ12 ሐዋሪያት፣ ሄሮድስ ያስፈጃቸው ከመቶ አርባ አራት ሺ ሕፃናት፣ ከአብርሃም ከይስሐቅ፣ ከዕቆብ ጋር ሁሉንም ነገደ መላእክትን፣ ጻድቃን ሰማዕታትን ሁሉ አስከትሎ መጥቶ ታላቅ ቃልኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ‹‹ስምህን የጠራ ገዳምህን የረገጠ፣ መባ የሰጠ፣ ቤተ ክርስትያንህን የሠራ ያሠራ የረዳ፣ ገድልህን የሰማ ያሰማ ያስተረጎመ፣ መታሰቢያን ያደረገ እስከ 10 ትውልድ እምርልሀለው፤ ንስሀ ሳይገባ አይሞትም፣ ልጅ መውለድ ባይችል እኔ ልጅ እሰጠዋለሁ፤ ገድልህን በቤትህ ያስቀመጠ እርኩስ መንፈስ፣ ክፉ አጋንንት ቸነፈር ወባ መልአከ ጽልመት አይነካውም፡፡ በገዳምህ መነኩሴ ቢቀበር በሰማይ ክንፍ አበቅልለታለሁ፤ አይሁድም አረማዊም ያላመነ ያልተጠመቀ በገዳምህ መጥቶ ቢያርፍ ይቅር እልልሃለሁ፣ እንደ መቃብሬ ጉልጎታ እንደተቀበረ አድርጌ እቆጥርልሃለሁ…›› የሚል ቃል ኪዳን ከሰጣቸው በኃላ ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡

ቅዱስ አባታችንም በ500 ዓመታቸው ሐምሌ 29 ቀን ዐርፈው በጎንድ ተክለ ሃይማኖት ተቀብረዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር የሚገኘውን ይህንን ገዳም ጻድቁ ራሳቸው ናቸው የመሠረቱት፡፡ ነገር ግን የገዳሙን ስያሜ በአባታቸው በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ስም አድርገውታል፡፡ አቡነ ዮሐንስ ካረፉ በኋላ በእርግማናቸው መሠረት በመንዝና በይፋት ብርዱ ድርቁ ስለበዛባቸው አንድ ብቁ ባሕታዊ ከበዓታቸው ወጥተው ‹‹በሐሜታችሁ ምክንያት እጨ ዮሐንስ ስለረገማችሁ ነው የእርሱን ዐፅም ካላመጣችሁ ብርዱ ውርጩ ድርቁም አይጠፋላችሁም›› አሏቸው፡፡ ሕዝቡም አባታችን በጉንድ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከተቀበሩ ከ134 ዓመት በኃላ በቅዱሳን እየተመሩ ሄደው በሌሊት ግማሽ ዐፅማቸውን አምጥተው በሀገራቸው አምጥተው ስላስቀመጡ ብርዱና ውርጩ በመንዝ እየቀነሰላቸው መጥቷል፡፡ ዛሬም በሀገሩ ብርዱና ውርጭ ሲበዛ የጻድቁን ታቦት ሲያወጡ ውርጩ ይጠፋል፡፡ ጠገሮ በሚባለው ገዳማቸው ውስጥ የሚገኘው ጠበላቸው እጅግ አስደናቂ ነው፡፡ ግማሽ ዐፅማቸውን ከጉንደ ተክለሃይማኖት አምጥተው አርባ ሐራ መዳኒዓለም አጠገብ በላይ በፍሩክታ ኪዳነምሕረት መጋቢት 18 ፍልሰተ ዐፅማቸው ተከናወነ፡፡ ምድሪቷም ተባረከች፣ የዘሩትንም አበቀለች፣ ውርጩም ብርዱም ቀነሰ፣ ዝናብ አልዘንብ ሲል ወይም ሰብል የሚጨርስ አንበጣ ሲመጣ ታቦታቸው ወጥቶ ምህላ ይያዛል-ወድያውም መቅሰፍት ይርቃል፣ ዝናብም ይዘንባል፡፡ ጻድቁ ደመናን፣ ጨረቃንና ፀሐይን በእጃቸው እየያዙ ይጸልዩ ነበር፡፡ በጠገሮ፣ በአዘሎ፣ በፍርኩታና በሌሎቹም ታላላቅ ቦታቦዎች ላይ በእያንዳንዱ ገዳም ሃምሳ ሃምሳ ዓመት በጸሎት ኖረው በአጠቃላይ በ500 ዓመታቸው ነው ያረፉት፡፡ ዐፅማቸው መንዝ ከአርባ ሐራ መድኃኔዓለም አጠገብ ፍርኩታ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ውስጥ ይገኛል፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ታዴዎስ_ሐዋርያ (ፍልሠቱ)

በዚህችም ቀን ከሶሪያ አገር ወደ ቁስጥንጥንያ ከተማ የቅዱስ ሐዋርያ ታዴዎስ የሥጋው ፍልሰት ሆነ። ይህም የሆነ ክርስቶስን የሚወድ ጻድቅ ቁስጠንጢኖስ በነገሠ ጊዜ ነበር። በሱ ትእዛዝም የቅዱስ ሐዋርያ ታዴዎስን ሥጋ አፈለሱ ያማረች ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ሥጋውን በውስጧ አኖሩ።

በዚችም ቀን አከበሩዋት ከእርሱም ብዙ የሆኑ ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዋርስኖፋ_ሰማዕት

በዚህችም ቀን ቅዱስ ወርስኖፋ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅድስ አዋቂ ሃይማኖቱ የቀና የዋህና በገድል የተጠመደ ሰው ነበረ። ኤጲስቆጶስነት ሊሾሙት በፈለጉት ጊዜ ከእርሳቸው ሸሸ ወደ አንዲት አገርም ደርሶ እግዚአብሔርን በሚወዱ ሁለት መነኰሳት ዘንድ አደረ።

በዚያቺም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለት ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲ ታመን የሰማዕትነትንም አክሊል እንዲቀበል አዘዘው። በነቃም ጊዜ ለእኒህ ለሁለቱ ወንድሞች ያየውን ነገራቸው። እነርሱም ከእርሱ ጋር በሰማዕትነት ይሞቱ ዘንድ ተስማሙ። ከዚህም በኃላ መኰንኑ ወደ አለበት ሔዱ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ ታላቅ ሥቃይንም አሠቃያቸው ከዚያም ሰንዑር ወደሚባል አገር እስከሚሔድ ድረስ በወህኒ ቤት ጨመራቸው።

የሚሔድበትም ሰዓት በደረሰ ጊዜ ከእርሱ ጋራ ወሰዳቸው በዚያም ታላቅ ሥቃይን አሠቃያቸው በሚያሠቃያቸውም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ያጸናቸውና ቁስላቸውን ይፈውስ ነበር።

ከዚህም በኃላ ፃ ወደሚባል አገር ወሰዳቸው። በዚያም ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃያቸው ብዙዎች አማንያንንም ሰብስቦ ስለ አምልኮ ጣዖት የሚያዝዝ የከሃዲውን ንጉሥ ደብዳቤ አነበበላቸው። ይህም ቅዱስ ወርስኖፋ ተነሥቶ ያቺን ደብዳቤ ከአንባቢው እጅ ነጥቆ ቀደዳት መኰንኑም አይቶ እጅግ ተቆጣ እሳትንም እንዲያነዱና ቅዱስ ወርስኖፋን በውስጡ እንዲያነዱና ቅዱስ ወርስኖፋን በውስጡ እንዲጨምሩት አዘዘ። ሰማዕትነቱንና ተጋድሎውን በእሳቱ እቶን ውስጥ ፈጸመ።

እነዚህንም ሁለት ወንድሞች ራሶቻቸውን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዝዞ ቆረጧቸው የሰማዕትነትንም አክሊል በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ እና #ከገድላት_አንደበት)
#ሐምሌ_30

ሐምሌ ሠላሳ በዚች ቀን ቅዱሳን የገሊላ ሰዎች #ቅዱሳን_መርቆሬዎስና_ኤፍሬም በሰማዕትነት አረፈ፣ ክብርንና ብልጽግናን ንቆ የተወ #ቅዱስ_ጳውሎስ_መናኒ አረፈ፣ #ቅዱስ_ሐዋርያ እንድርያስ ተአምራትን አደረገ፣ የንጉሥ ናዖድ ሚስት #ንግሥት_ማርያም ክብራ አረፈች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱሳን_መርቆሬዎስና_ኤፍሬም (ሰማዕታት)

ሐምሌ ሠላሳ በዚች ቀን ቅዱሳን የገሊላ ሰዎች መርቆሬዎስና ኤፍሬም በሰማዕትነት አረፈ። እሊህም ከአክሚም ከተማ የመጡ የሚዋደዱ በመንፈስ ቅዱስ ወንደማሞች በሥጋም ዘመዳሞች ነበሩ መንፈሳዊ ስምምነትንም ተስማምተው በላይኛው ግብጽ ካሉ ገዳማት በአንዱ ገዳም መነኰሱ በጾም በጸሎትና በስግደት እየተጋደሉ በገዳሙ ውስጥ ሃያ ዓመት ያህል ኖሩ።

ከዚህም በኃላ ጠላት ሰይጣን በአብያተ ክርስቲያናት ላይ ከአርዮሳውያን ችግርን በአመጣ ጊዜ አርዮሳውያኑ በአርዮሳዊ ንጉሥ ትእዛዝ መሥዋዕትን ሊሠው ወደ ኦርቶዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገቡ ቀንተው ወደ ቤተ ክርስቲያን ገቡና አርዮሳውያን ያኖሩትን መሥዋዕት በተኑት።

እንዲህም አሏቸው በሥሉስ ቅዱስ ስም ያልተጠመቀ መሥዋዕትን ያሳርግ ዘንድ አይገባውም። ያን ጊዜም አርዮሳውያን ይዘው ደበደቧቸው ታላቅ ግርፋትንምገረፏቸው ዐጥንቶቻቸውም እስኪሰበሩ ድረስ በምድር ላይ ጥለው ረገጧቸው ነፍሶቻቸውንም በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ ሰጡ የሰማዕትነትንም አክሊል ተቀበሉ ምእመናንም መጥተው ሥጋቸውን ወሰዱ በአማሩ ልብሶችም ገንዘው በመልካም ቦታ አኖርዋቸው ከእነሱም ለበሽተኞች ታላቅ ፈውስ ሆነ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_ዻውሎስ_መናኒ

በዚህችም ቀን ክብርንና ብልጽግናን ንቆ የተወ ጳውሎስ አረፈ። ይህም ቅዱስ ባለጸጋ ነበር። ደግ የሆነች ሚስትና የተባረኩ ልጆችም ነበሩት። መነኮስ ሊሆን ወደደ ሚስቱንና ልጆቹንም ጠርቶ እነሆ ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ ፍቅር እሸጣችሁ ዘንድ ወደ ዱኩ አላቸው እነርሱም አሳዳሪያቸን ነህና የወደድከውን አድርግ አሉት።

ከዚህም በኋላ ገንዘቡን ሁሉ ወስዶ ለድኆችና ለችግረኞች በተነ ሚስቱንም ወደ ደናግል ገዳም ወሰዳት እመምኔቷንም ጠራትና እንዲህ አላት ለገዳምሽ አገልጋይ ትሆን ዘንድ ሚስቴን ልሸጥልሽ እወዳለሁ እርሷም እሺ አለችው የመሸጫዋንም ደብዳቤ ጻፈ የሺያጭዋን ዋጋ ተቀብሎ ለድኆች ሰጠ ልጆቹንም ወደ አበ ምኔቱ ወስዶ እንደ እናታቸው ሸጣቸው ለአበ ምኔቱም አሳልፎ ሰጣቸው።

ከዚህም በኃላ ወደ ሌላ ቦታ ሔደ ራሱንም ለገዳሙ አለቃ ሸጠ አለቃውንም ወደ ቤተ ክርስቲያን ብቻዬን ልገባ እሻለሁ አለው በገባም ጊዜ በሩን በላዩ ዘጋ። እጆቹንም ዘርግቶ ቆመ በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብሎ ጮኸ አቤቱ በፍጹም ልቡናዬ ወዳንተ እንደ መጣሁ አንተ ታውቃለህ።

ወደርሱም እንዲህ የሚል ቃል መጣ ሀሳብህን ሁሉ አውቅሁ በፍጹም ልቤም ተቀበልኩህ። ከዚህም በኃላ መነኮስ አስጨናቂ የሆኑ የገዳሙን ሥራዎች ሁሉ እንደ ባሪያ እየሠራ ኖረ ራሱንም ከሁሉ እጅግ አዋረደ ነገር ግን ስለ መዋረዱ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ አደረገው። ከእርሱም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራቶች ተገለጡ ከዚህም በኃላ በሰላም አረፈ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_እንድርያስ_ሐዋርያ

በዚችም ቀን ቅዱስ ሐዋርያ እንድርያስ ተአምራትን አደረገ። እንድርያስ በጽርዕ አገር እያለ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ተገልጦ እንዲህ አለው ማትያስን ከእሥር ቤት ታወጣው ዘንድ ሰውን ወደሚበሉ ሰዎች አገር ሒድ የዚያች አገር ሰዎች ከሦስት ቀን በኃላ ሊበሉት ያወጡታልና ።

እንድርያስም ጌታችንን እንዲህ አለው የቀረው ሦስት ቀን ከሆነ እንዴት እደርሳለሁ ነገር ግን ፈጥኖ የሚያወጣውን ከመላእክት አንድ ላክ እንጂ።

ጌታችንም ለእንድርያስ እንዲህ ብሎ መለሰለት ስማ ሀገሪቱን ወደዚህ ነዪ ከልዃት በውስጧ ከሚኖሩ ሁሉ ጋር ትመጣለች አንተና ደቀ መዘሙሮችህ ግን ጠዋት በሆነ ጊዜ ተነሥታችሁ ወደ ባሕር ሒዱ የተዘጋጀ መርከብንም ታገኛላችሁ እርሱም ያደርስሃል ይህንንም ብሎ ከእርሱ ዘንድ በክብር ዐረገ። በነጋ ጊዜም እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ተነሥቶ ወደ ወደብ ደረሰ ጥሩ መርከብንም አየ ጌታችንንም በሊቀ ሐመር አምሳል አየው ጌታችን እንደሆነ አላወቀም ሊቀ ሐመር ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን አለው ጌታም የእግዚእብሔር ሰላም ይደርብህ አለው እንደርያስም ደግሞ በዚህ መርከብ ወዴት ትሔዳለህ አለው ሰውን ወደ ሚበሉ ሰዎች አገር እሔዳለሁ አለው እንድርያስም ሊቀ ሐመሩን ወንድሜ ሆይ ከአንተ ጋር ትጭነኝ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው ሊቀ ሐመሩም እሺ ብሎ ወደ መርከቡ አወጣቸው። በባሕሩ ላይም ሲጏዙ ጌታችን እንድርያስን እንዲህ ብሎ ጠየቀው ጌታህ ምን ኃይል አደረገ እንድርያስም ጌታችን ከአደረጋቸው ተአምራቶች ለነግረው ጀመረ ጌታችን እንደሆነ አላወቀም ነበርና።

ከዚህም በኋላ ሊቀ ሐመሩ እነደሚአንቀላፋ ሰው ሆነ ያንጊዜም እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ተኛ በዚያን ጊዜም ጌታችን እንድርያስንና ሁለቱን አርድእቱን ይሸክሙአቸው ዘንድ መላእክትን አዘዛቸውና ወስደው በባሕሩ ዳርቻ አኖሩዋቸው። እንድርያስም ከእነቅልፍ በነቃ ጊዜ መረከብን አላገኘም እጅግም አደገቀ ለደቀ መዛሙርቱም እንድህ አላቸው ልጆቼ ሆይ በመርከብ ውስጥ ከጌታችን ጋር ነበርን ግን አላወቅንም።

ከዚህም በኋላ እንድርያስ ተነስቶ ጸለየ ክብር ይግባውና ጌታችንም በመልካም ጎልማሳ አምሳል ተገለጸለት እንዲህም።

አለው ወዳጄ እንድርያስ አትፍራ እኔ ይህን አድርጌአለሁና አንተ በሦስት ቀን አልደርስም ብለህ ነበር ስለዚህ በፍጥረት ሁሉ ላይ ኃይል እንዳለኝ የሚሳነኝምእንደሌለ ተውቅ ዘንድ እንግድህም ወደ ከተማው ገብተህ ማትያስን ከእሥር ቤት አውጣው ከእርሱ ጋር ያሉትንም ሁሉ።

ከዚህም በኋላ እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተነሥቶ ወደ ከተማ ገባ ማትያስ ወዳለበትም እስር ቤት ሔደ። በደረሰም ግዜ የወሀኒ ቤቱ ደጀ ራስዋ ተከፈተች በገባ ጊዜም ማትያስን ተቀምጦ ስዘምር አገኘው እርስ በርሳቸውም ሰላምታ ተሳጣጡ እንድርያስም ማትያስን ከሁለት ቀን ቡኋላ አውጥተው እንደ እንስሳ አርደው ይበሉኛል አልክ አንተ በጌታችን ዘንድ ያየናትን ያቺን ምሥጥር ረሰሃትን በምንናገረት ጊዜ ሰማይና ምድርን ይናወጣሉ አለው። ማትያስም ወንድሜ ሆይ እንሆ ይህን አወቅሁ ነገር ግን በዚች ከተማ ውስጥ ሥራዬን እንድፈጽም የጌታችን ፍቃድ እንደ ሆነ እኔ እናገራሎህ እርሱ ራሱ እንሆ እኔ እንደ በጎች በተኲላዎች መካከል እንኳችኃሎህ ብሏልና ወደ ዝህም እሥር ቤት በጨመሩኝ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችንን ጠራሁት እርሱም ሃያ ሰባት ቀን ሲፈጸም ወንድምህ እንድርያስን ወዳንተ እልከዋሎህ እርሱም ከእሥር ቤት ያወጣሃል ከአንተ ጋራ ያሉትን ሁሉ ያወጣችዋል ብሎ ገለጠልኝ እንሆም ደርሰሃል የምትሠራውን አስተውል አለው።

እንድርያስም ወደ እስረኞች በተመለከተ ጊዜ እንደ እንስሳ ሥር ሲበሉ አይቶ አዘነ አለቀሰም ሰይጣንንም ከሠራዊቱ ጋር አሥረው ከዝህ በኃላ አንድርያስና ማትያስ ተነሥተው ወደ እግዚአብሔር ማለዱ እጆቻቸውንም በእሥረኞች ሁሉ ላይ ጫኑ አእምሮአቸውም ተመለሰ ከከተማው ውጭ ወጥተው በዝያ በአንድነት እንድቀመጡ አዘዙአቸው።
እኒያ ሐዋርያትም የሚሆነውን ያዩ ዘንድ ወጥተው በሀገሩ ጎዳና ዳር ተቀመጡ የከተማው ሰዎችም እነደ ልማዳቸው የሚበሉትን ከእሥረኘች ውስጥ ሊአመጡ መጡ የእሥር ቤቱን ደጅ ክፍት ሆኖ አገኙ እሥረኞችም አልነበሩም ደነግጠውም በእኛ የደረሰብን ምንድነው ወዮልን አሉ ያን ጊዜም ሰይጣን በሰው መስሎ ሐዋርያት ይህን እንዳደረጉ ነገራቸው የአሉበትንም አመለከታቸው የከተማው ሰዎችም በመቀዳደም ሮጡ እንድርያስንና ማትያስንም ይዘው በከተማው ጥጋጥግ አስጎተቱአቸው በሌሊትም በእሥር ቤት ያሳድሩአቸው ነበር ሦስት ቀናትም እንዲህ አደረጉባቸው ደማቸውም እንደ ውኃ ፈሰሰ።

ከዚህም በሗላ ሰለ ከተማዋ ሰዎች ድኀነት ወደ እግዚአብሔር ጸለዪ ጸሎታቸውንም በፈጸሙ ጊዜ በላዩ ምስል ወደአለበት የዕብነ በረድ ምሶሶ ቀርበው በመስቀልመ ምልክት አመተቡት እንዲህም አሉት አንተ ምሶሶ ፍራ ከበታችህም እንደ ጥፋት ውኃ ያለ ብዙ ውኃን በዚች ከተማ ላይና በውስጧ የሚኖሩ ሁሉ ላይ አውጣ ያን ጊዜም ከምሶሶው ሥር ብዙ ውኃ መነጨ የከተማው ሰዎችንም ያሠጥማቸው ዘንድ ገነፈለ ሰዎችም ከከተማው ወጥተው ሊሸሹ ወድደው ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ያዙ ውኃውም በዝቶ ከበባቸው ማምለጥም አልቻላቸውም ውኃውም እስከ እስከ አንገታቸው ደረሰ ያን ጊዜም አለቀሱ እንዲህም አሉ ወዮልን ይህ ሁሉ በእኛ ላይ የመጣው በእነዚህ በተመረጡ ሰዎች በእግዚአብሔር አገልጋዮች ምክንያት ነው እኛም በአምላካቸው እናምናለን። እንድርያስም የዕብነ በረደ ምሰሶ እንግዲህስ በቃህ እነሆ የጥፋት ጊዜ አለፈ ያን ጊዜም ውኃው ተገታ ውኃውም እንደተገታ የከተማው ሰው አይተው ወደ ሐዋርያት ሔዱ ስለዚያች ከተማ ሰዎች ድኅነትም ቁመው እጆቻቸውን ዘርግተው ወደ እግዚአብሔር ሲጸልዩ አገኙአቸው ሐዋርያትን ይቅር በሉን ብለው ለመኑአቸው። ሐዋርያትም በሕያው እግዚአብሔር እመኑ እንጂ አትፍሩ አሏቸው ሐዋርያትም ሁለተኛ ጸለዩ በውኃ ስጥመት የሞቱትንም ሙታን አስነሡአቸው በዚያም ውኃ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው። ሥጋውንና ደሙንም አቀበሏቸው ቤተ ክርስቲያንንም ሠሩላቸው። ሕግንና ሥርዓትንም ሁሉ አስተምረው በቀናች ሃይማኖት አጸኑአቸው እንዲህም አሏቸው ያዘዝናችሁን ጠብቁ ከእናንተ በኃላ ለሚነሡ ልጆቻችሁም አስተምሯቸው።

ከዚህም በኃላ የአራዊትን ጠባይ ከእነርሱ ያርቅ ዘንድ እግዚአብሔርን ለመኑት ክብር ይግባውና ጌታችንም ይህን የአራዊት ጠባይ አራቀላቸው። ሰዎች የሚመገቡትንም የሚመገቡ የዋሆች ሆኑ። አባቶቻችን ሐዋርያትም ብዙ ተአምራትን አደረጉ በሽተኞችን ሁሉ ፈወሱ ከዚህም በኃላ እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ ግሪክ አገር ተመለሰ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#እናታችን_ማርያም_ክብራ

በዚህችም ቀን የንጉሥ ናዖድ ሚስት ንግሥት ማርያም ክብራ አረፈች። እርሷም መንፈሳዊ የሆነ በጎ ተግባርን ሁሉ የጠበቀች ትሩፋትንና መጋደልንም በጾምና በጸሎት የፈጸመች ነበረች በደብረ ሊባኖስም ተቀበረች።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባቶቻችን ነቢያትና ሐዋርያት በጻድቃንና በሰማዕታት በደናግልና በመነኮሳት በቅዱሳን መላእክትም በተመረጡ ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት በቀሳውስትና በዲያቆናት ሃይማኖታቸው በቀና በአእሩግና ሕፃናት በእነዚህ ሁሉ ጸሎት ይማረን።

አምላክን የወለደች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በረከቷ በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ጳውሎስ በሁሉም ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት እንዲሁም በሁላችን በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ላይ ይደር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ሐምሌ)
#ነሐሴ_1

ነሐሴ አንድ በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም እናቷ #የቅድስት_ሐና መታሰቢያዋ ነው፣ የዮስጦስ ልጅ #ቅዱስ_አቦሊ በሰማዕትነት አረፈ፣ የከበሩ ሰዎች #ቅዱሳን_የዮሴፍና_የኒቆዲሞስ መታሰቢያቸውን።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሐና (የእመ ብርሃን እናት)

ነሐሴ አንድ በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያም እናቷ የሐና መታሰቢያዋ ነው። ይህችም ቅድስት ከኢየሩሳሌም አገር ከሌዊ ነገድ ከካህኑ አሮን ትውልድ የሌዊ የሜልኪ ልጅ ለሆነ ለማጣት (ጣ ጠብቆ ይነበብ) ልጁ ናት። ለማጣትም ሦስት ሴቶች ልጆች አሉት የታላቂቱም ስሟ ማርያም ናት ሁለተኛዋም ስሟ ሶፍያ ሦስተኛዪቱም ስሟ ሐና ናት ታላቂቱ ማርያምም ለባል ተድራ አዋላጅ የሆነች ሰሎሜን ወለደቻት እርሷም መድኃኒታችንን ከወለደችበት ጊዜ ጀምሮ በስደቷም ወራት ከአረጋዊ ዮሴፍ ጋር እመቤታችንን ድንግል ማርያምን ያገለገለቻት ናት።

ሶፍያም ለባል ተድራ ለመጥመቁ ዮሐንስ እናቱ የሆነች ቅድስት ኤልሳቤጥን ወለደቻት። ይችንም ቅድስት ሐናን ከይሁዳ ነገድ ለሆነ ጻድቅ ስሙ ኢያቄም ለሚባል አጋቧት። (ሰሎሜና ኤልሳቤጥ ለቅድስት ሐና የእኅትማማች ልጆች ናቸው።)

ቅድስት ሐና ኢያቄምን አግብታ ስትኖር የቴክታና እና የጴጥሪቃ ምክነት በዘር ወርዶ መክና በመኖሯ የዐይኗ ማረፊያ የልቧ ተስፋ የሚሆን ልጅ እንዲስጣት ፈጣሪዋን ስትማጸን ኖራለች።

የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን የማይነሳ አምላክ ልመናዋን ሰምቶ ሐምሌ ፴ ራእይ አየች። ራእዩንም ከባሏ ከኢያቄም ጋር ተወያየተው ምንጣፍ ለይተው ሱባኤ ገቡ።

ከአንድ ሱባኤ በኋላ ነሐሴ ፯ ቀን ጌታ ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ እንደሚወልዱ አበሠራቸው። ከዚያም እመቤታችን ጸንሳ ልዩ ልዩ ተአምራትን አድርጋለች። ሳምናስን ከሞት አስነስታለች። በርሴባን ዐይኗን አብርታለች። ከዚያም በአይሁድ ተንኮልና አሳዳጅነት ወደ ሊባኖስ ተራራ ተሰዳ ድንግል ማርያምን ወልዳለች። በመውለዷም ሕዳሴ አካል አግኝታ ከኖረች በኋላ ዐርፋለች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅዱስ_አቦሊ

በዚህችም ቀን የዮስጦስ ልጅ ቅዱስ አቦሊ በሰማዕትነት አረፈ። ይህም ቅዱስ አቦሊ ከመንግሥት ልጆች ውስጥ ነበር ዐላውያንን ወግቶ በተመለሰ ጊዜ ዲዮቅልጥያኖስን ክብር ይግባውና ክርስቶስን ክዶ አገኘው።

ያም አቦሊና አባቱ ዮስጦስ ሌሎችም የመንግሥት ልጆች ሁሉ ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስን ሊያጠፉትና መንግሥትን ከእርሱ ሊወስዱ ችሎታ ሲኖራቸው የማታልፍ ሰማያዊት መንግሥትን አሰቡ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ አቦሊ ወደ ንጉሡ ቀርቦ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመነ ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም አብዝቶ አባበለው። እንዲሁም አባቱ ዮስጦስንና የከበረች እናቱ ታውክልያን አባበላቸው እነርሱ ግን አልሰሙትም ልባቸው በመድኅን ክርስቶስ ፍቅር ተነድፏልና። ንጉሡም እነርሱን በዚያ ማሠቃየትን ፈራ ስለዚህም ከመልእክት ደብዳቤ ጋር ወደግብጽ ስሙ ኄርሜኔዎስ ወደሚባል የእስክንድርያ ገዥ ላካቸው በመልእክቱም እንዲህ አለው ዮስጦስና ሚስቱ ታውክልያ ልጃቸው አቦሊም ወደአንተ በሚደርሱ ጊዜ አባብላቸው አለዚያም እየአንዳንዳቸውን ለያያቸው።

በዚያችም ሌሊት ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዮስጦስና ለሚስቱ ታውክልያ ለልጃቸው አቦሊም ተገልጦላቸው አጽናናቸው ከእነርሱም የሚሆነውን ነገራቸው የጸና ቃል ኪዳንም ሰጣቸው።

ወደ መኰንኑ ኄርሜኔዎስም በደረሱ ጊዜ ስለእነርሱ እጅግ አደነቀ እነርሱ መንግሥታቸውን ትተዋልና ክፋ ነገርንም ሊናገራቸው አልደፈረም ከምክራቸው ይመለሱ ዘንድ በለሰለሰ ቃል ሸነገላቸው እንጂ ነገር ግን አልሰሙትም።

ከዚህም በኋላ በእነርሱ ላይ ተቆጥቶ ለእየብቻቸው ለያያቸው ቅዱስ ዮስጦስን ወደ እንዴናው ከተማ ሚስቱን ታውክሊያን ፃ ወደ ሚባል አገር ልጃቸው አቦሊንም ብስጣ ወደ ሚባል አገር ሰደዳቸው ለእያንዳንዳቸውም የሚአገለግላቸው አንዳንድ አገልጋይ ሰጣቸው። ቅዱስ አቦሊም ወደ ሀገር ብስጣ በደረሰ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመኰንኑ ፉት ታመነ። መኰንኑም ጽኑ ሥቃይን በእሳት ቃጠሎና በመንኰራኵር አሰቃየው ሕዋሳቱንም ቆራርጦ ለአንበሶች ጣለው ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስም ከሥቃዩ ሁሉ አድኖ ያለ ጉዳት በጤና አነሣው።

ብዙዎች ሰዎችም ስቃዩንና ዳግመኛ መዳኑን በአዩ ጊዜ እጅግ አደነቁ ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም አምነው ሰማዕታት ሆኑ።

መኰንኑ ግን እጅግ ተቆጥቶ የቅዱስ አቦሊን ቆዳውን እንዲገፍፉትና ጨውና መጻጻን በማቅ አምጥጠው ቍስሉን እንዲያሹ አዘዘ ይህንንም ሁሉ አደረጉበት።

ከዚህም በኋላ ቆዳውን አሸክመው በከተማ ውስጥ ሁሉ አዞሩት ወደ ጌታችንም እንዲህ ብሎ ጸለየ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ርዳኝ ከዚህ ሥቃይም አድነኝ። ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደርሱ መጣ ሁለመናውንም ዳስሶ አዳነው።

መኰንኑም በእርሱ ላይ የሚያደርገውን እስኪያስብ ከእሥር ቤት እንዲጨምሩት አዘዘ። ቅዱስ አቦሊም ቁሞ ጸለየ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና ጌታችን ተገለጠለትና የመረጥኩህ አቦሊ ሰላም ለአንተ ይሁን እኔም ከአንተ ጋር እኖራለሁ አለው ጌታችንንም በአየው ጊዜ እጅግ ደስ አለው ክብር ይግባውና ለጌታችንም ሰገደለት።

ስሙ አብስኪሮን የሚባል አንድ ባለ ጸጋ ነበር የቤቱንም ግድግዳ አፍርሰው አዲስ ይሠሩለት ዘንድ ሠራተኞችን አመጣ ሥራቸውንም እስኪጨርሱ ከዚያ ይቆሙ ዘንድ ሁለቱን ልጆቹን አዘዛቸው።

ከግርግዳውም ላይ በወጡ ጊዜ ግርግዳው ተደርምሶ ዐሥራ ስድስት ሰዎችና ሁለቱ ልጆቹ ሞቱ። ባለጸጋውም የሆነውን በአየ ጊዜ ልብሱን ቀደደ ጩኾም አለቀሰ ወደ ቅዱስ አቦሊም ሒዶ ከእግሩ በታች ሰገደለት እንዲህም አለው ራራልኝ ሁለቱ ልጆቼ ሙተዋልና ከእነርሱም ጋራ ዐሥራ ስድስት ሰዎች ሞቱ። ከሞትም ብታሥነሣቸው እኔ በአምላክህ አምናለሁ።

ያን ጊዜም ቅዱስ አቦሊ ተነሣ እንዲህ ብሎ ጸለየ ስለ ቅዱስ ስምህ መከራን እቀበል ዘንድ የመረጥከኝ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በእኒህ በሞቱ ሰዎች ላይ ኃይልህን ግለጥ። እኒህ ሰዎች ሁሉ እንዲአምኑ ያለ አንተም ሌላ አምላክ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ ከሞት አንሣቸው። ላንተም ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

ከዚህም በኋላ የተገፈፈ ቆዳውን ወስዶ በሞቱት ሰዎች ላይም ዘረጋውና በሕያው እግዚአብሔር ልጅ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከሞት ተነሡ አለ። ወዲያውም ሁሉም ድነው ተነሡ በዚያ ያሉ ሕዝብም ይህን ድንቅ ሥራ በአዩ ጊዜ የክርስቲያን አምላክ የቅዱስ አቦሊም አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ነው እኛም እናምንበታለን ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለምና እያሉ ጮኹ።

ባለ ጸጋው አብስኪሮንም መጥቶ ለቅዱስ አቦሊ እንዲህ እያለ ሰገደ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይግባውና እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ዛሬ አወቅሁ እኔም አምንበታለሁ። ከቤተሰቦቹም ሁሉ ጋር አመኑ መኰንኑም አፈረ።

ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱስ አቦሊ ተገለጠለት እንዲህም ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠው። በመከራ ውስጥ ያለ ሰው በስምህ ርዳታ ቢለምን እኔ እሰማዋለሁ ልመናውን ፍላጎቱንም እፈጽምለታለሁ። በስምህ ቤተ ክርስቲያን ለሠራም እኔ በሰማያት ብርሃናዊ ማደሪያ ቤት እሠራለታለሁ የገድልህን መጽሐፍ የሚጽፈውን ወይም የሚያነበውን ወይም የሚሰማውን እኔ በኪሩቤል ክንፎች ላይ ስሙን እጽፉለሁ በአብርሃም በይስሐቅና በያዕቆብ እቅፍም አሳርፈዋለሁ ተድላ ደስታ ካለባት ከገነት ፍሬዎችም
እመግበዋለሁ።

ብዙ ኃጢአትን ሠርቶ የበደለውንም በስምህ ወደኔ እየለመነ ንስሐ ቢገባ በደሉን ሁሉ ይቅር እለዋለሁ። ከጻድቃንም ጋርም እቈጥረዋለሁ ሰላሜም ካንተ ጋራ ይሁን ይህንንም ብሎ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ።

መኰንኑም ከማሠቃየቱ የተነሣ በደከመ ጊዜ ራሱን በሰይፍ ይቆርጡት ዘንድ አዘዘ የከበረች ራሱን ቆረጡት የሕይወት አክሊልንም ተቀበለ። ሥጋውም ከምስር ከተማ ውጭ ሕንቅ በሚባል ገዳም ይኖራል ከእርሱም ብዙዎች ድንቆችና ተአምራት ተገለጡ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#አበው_ሐዋርያት_ዮሴፍና_ኒቆዲሞስ

በዚህችም ቀን ለአምላካዊት ምሥጢር አገልጋዮች ሊሆኑ የተገባቸው የከበሩ ሰዎች የዮሴፍና የኒቆዲሞስ መታሰቢያቸውን እናደርግ ዘንድ የቤተ ክርስቲያን መምህራን አባቶች አዘዙ።

በፈቃዱ መከራ ተቀብሎ ስለ ደኅንነታችን በሞተ ጊዜ የደኅንነታችንንም ምሥጢር በፈጸመ ጊዜ የሕያው እግዚአብሔርን ልጅ የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ እነርሱ ከመስቀል ላይ አውርደዋልና። የአይሁድም መገርመም ከጲላጦስ ዘንድ የመድኃኒታችንን ሥጋ እስከ ለመኑ ድረስ አላስፈራቸውም።

ጴላጦስም በፈቀደላቸው ጊዜ የእጆቹንና የእግሮቹን ችንካሮች ነቅለው ከመስቀል አውርደው በትክሻቸው ተሸከሙት ሲገንዙትም እንዲህ የሚል ቃል ከበድኑ ሰሙ። ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደ አቤቱ ይቅር በለን።

ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት በዮርዳኖስ የተጠመቀ በእንጨት መስቀልም የተሰቀለ አቤቱ ይቅር በለን። ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ የተነሣ በክብር ወደ ሰማያት ያረገ በአባቱም ቀኝ የተቀመጠ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ የሚመጣ አቤቱ ይቅር በለን።

ለአብ ምስጋና ይገባል ለወልድ ምስጋና ይገባል ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን አሜን ይሁን ይሁን። ልዩ ሦስት ሕያው እግዚአብሔር ይቅር በለን።

ይህንንም በሰሙ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖታቸው ጸናች። ዮሴፍም በፍታ ኒቆዲሞስም ሽቶዎችን አምጥተው ጌታችንን ገነዙት በአዲስ መቃብር ውስጥም ቀበሩት።

ይህ ዮሴፍም ለሰማዕታት መጀመሪያ ለእስጢፋኖስ ዘመድ ለሆነው ለቀለዮጳ ወንድሙ ለኒቆዲሞስ ዘመዱ ነው ኒቆዲሞስም የአይሁድ አለቃ ፈሪሳዊ ነበር እርሱም ወደ ጌታ ኢየሱስ አስቀድሞ በሌሊት የሔደና ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣ ያመነ ነበር። ጌታችንም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንደማይችል የነገረው ነው።

ይህ ኒቆዲሞስም የጌታችንን ቃል በሚአቃልሉ ጊዜ አይሁድን ይገሥጻቸው ነበር። ከተነሣ በኋላም በኢማሁስ መንገድ ሲሔድ ጌታችን ኢየሱስ የተገናኛቸው እሊህ ኒቆዲሞስና ቀለዮጳ ናቸው። እነርሱም ሳያውቁት በእርሱ ላይ የሆነውን ሁሉ ነገሩት። እርሱም ስለ ሞቱና ስለ ትንሣኤው ነቢያት ትንቢት እንደ ተናገሩ አስተማራቸው።

ከዘህም በኋላ እርሱ መሆኑን ባወቁት ጊዜ ተሠወራቸው እነርሱም ተመልሰው ለደቀ መዛሙርቱ ነገሩ። ክብር ይግባውና የጌታችንን ሥጋ ስለ ቀበረ ሊገድሉት ፈልገው አይሁድ ዮሴፍን በወህኒ ቤት አሠሩት። የወህኒ ቤቱም በር በሊቃነ ካህናቱና በጲላጦስ ማኅተም ተቆልፎ ሳለ ጌታችን በኪሩቤል ሠረገላ ተቀምጦ ዮሴፍ ወደ አለበት ገባ ከእርሱ ጋርም እልፍ አእላፋት መላእክት ነበሩ። ሱራፌልም በዙሪያው ቁመው በፊቱ ያጥናሉ በቀኝ በኩል ተሰቅሎ የነበረ ወንበዴውም ብሩህ ልብስ ለብሶ በቀኝ ቁሞአል ባለሟልነትን በልዑል ፊት አግኝቶአልና ስለ ኃጢአተኞች ይማልድ ነበር።

የወህኒ ቤት ጠባቂዎችም በአዩ ጊዜ ደነገጡ ፈርተውም መንቀጥቀጥ ያዛቸው ጌታችንም ዮሴፍን ጠርቶ እንዲህ አለው ከአይሁድ ግርማ የተነሣ አትፍራ ከማሠሪያህ ልፈታሕ እኔ መጣሁ አንተ መከራዬን የተሳተፍከኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ እኔ ነኝ አኔ ጌታህና የዓለሙ ሁሉ ጌታ እንደሆንሁ ፈጽመህ ታውቅ ዘንድ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን የተወጋ ጐኔንም እይ።

ከዚያም ዮሴፍን ነጥቆ ወደ አገሩ አርማትያስ ወሰደው። የወህኒ ቤቱ ጠባቂዎችም ሔደው ጌታችን ያደረገውን ሁሉ ዮሴፍንም ይዞ ከእርሱ ጋር እንደወሰደው ለካህናት አለቆች ነገሩ። የካህናት አለቆችም በሔዱ ጊዜ የወህኒ ቤቱ በር ተቆልፎ አገኙ እሽጉም አልተለወጠም ነበር። እሊህ ቅዱሳንም ከሐዋርያት ጋር ወንጌልን እየሰበኩ ኖሩ ብዙ መከራም አገኛቸው። ከዚህም በኋላ በሰላም አረፉ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ)
☞ ሱባዔ_ምንድ_ነው ?

ሱባኤ በሰዋሰው ትርጉሙ "ሰባት"ማለት ሲሆን በመንፈስ አተረጋጎም አንድ ሰው ከዚህ ቀን እስከ ዚህ ቀን በጸሎት ከፈጣሪየ ጋር እገናኛለሁ ብሎ የሚያቅደው መንፈሳዊ ዕቅድ ነው ፡፡ ሰባት ቁጥር በእስራኤላውያን ዘንድ በሥራም በቃልም የሚገለጥ ፍጹም ቁጥር ነው፡፡ ለምሳሌ ፦ ፈጣሪ አለማት እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ሥነ ፋጥረትን ከመፋጠር ማረፋ ፥ለጸሎት የሚተጉ ምዕመናን በቀን ለሰባት ጊዜ ማመስገናቸው የሰባት ቁጥር ፋጹምነት ያመለክታል ፡፡ [ዘፍ 2*2 , መዝ 118*164 ] አንድ ሰው 7 ቀናት ቢጾም "አንድ ሱባኤ ጾመ" ይባላል ፡፡

☞ ሱባኤ መቼ ተጀመረ ?

የተጀመረው ከውድቀት በሓላ በመጀመርያው ሰው በአዳም ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት አዳምን ጸሎት እንዳስተማሩት የቤተ ክርስቲያናችን መዛግብት ያስረዳሉ በምላሹም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ስጋን ለብሼ ከ 5 ቀን ተኩል በኋላ አድንሃለሁ የሚለውን ቃል ኪዳን የሰማው ሱባኤ በመግባቱ ነው፡

☞ ሱባዔ_ለምን?

የሰው ልጅ ሓጢአት በሚስማማው የሥጋ ሰውነቱ ዘወትር ፈጣሪውን ይበድላል ፡፡ በፈፀመው በደል ኀሊናው ይወቅሰዋል ይጸጸታል ፡፡በመጀመርያ ደፋሮ በሰራው ሀጥያት በኋላ ይደነግጣል ይህ በማንኛውም ሰብአዊ ፋጥረት ኀሊና ውስጥ የሚፈራረቅ ክስተት ነው ፡፡ በዚህ ግዜ የፈጣሪውን ይቅርታ ለማግኝት ያስባል ይተክዛል፡፡ ሰው በደፋርነቱ የኃያሉን አምላክ ትእዛዝ ተላልፎ አለም ሲያስጨንቀው ሸክሙን የሚያቃልልበትና የሚያስወግድበት መንፈሳዊ ጥበብ ከቸሩ ፈጣሪ ተሰጥቶታል፡፡ ይህውም በጥቂት ድካም ሥጋ ያልተወሰነ ጸጋ እግዚአብሔር የሚያገኝበት ሥርዓት ሱባኤ ነው፡፡
➊ እግዚአብሔርን_ለመማጸን ፦
ማንኛውም ሰው ሱባኤ ሲገባ በቁርጥ ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማፅኖ ሊኖረው ይገባል ፡፡ ምንም የምንጠይቀው ( የምንማፀነው) ነገር ሳይኖር ሱባዔ ብንገባ የምናገኝው መልስ አይኖርም ፡፡ ስለዚህ ሱባኤ ከመግባታችን በፊት ፦ሱባዔ የምንገባው ለምንድን ነው ? በማለት እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል ፡፡
➋ የቅዱሳንን_በረከት_ለመሳተፍ
ቅዱሳን አባቶችና እናቶች የተጋደሉትን ተጋድሎ በማዘከር ቃል ኪዳን በተሰጣቸው ገዳማትና አድባራት የሚገባ ሱባኤ የቅዱሳን በረከት ተካፋይ ያደርጋል፡፡ በጾመ ነብያት የነብያትን ፤ በጾመ ሀዋርያት የሀዋርያትን ፤በጾመ ፋልሰታ የእመቤታችንን በረከት ለመሳተፋ ሱባኤ መግባት የነበረ ነው፡፡

☞ የሱባኤ_አይነቶች

1 የግል ሱባኤ ( ዝግ ሱባኤ) ፦ አንድ ሰው ብቻውን አመች ቦታ ማንም ሳያየው በግሉ የጸሎት በአቱን ዘግቶ በሰቂለ ኀሊና ሆኖ ፈጣሪው ብቻ እንዲያየው በኀቡዕ የሚፈፅመው ሱባኤ ነው ፡፡
2 ,የማህበር ሱባኤ ፦ ካህናት ምዕመናን ወንዶች ሴቶች ሽማግሌወች ፤ወጣቶች ፤በአንድ ሆነው በቤተ ክርስትያንና አመች በሆኑ ቦታወች ሁሉ ተሰብስበው የሚገብት ሱባዔ ነው፡፡
3 , የአዋጅ ሱባዔ ፦ በሀገር ላይ ድንገተኛ አደጋ ፤ አባር ቸነፈር ጦርነት ሲነሳ እንዲሁም በማህበረ ምዕመናን ላይ አስጊ የሆነ መቅሰፋት ሲከሰት እግዚአብሔር መዓቱን በምህረት ቁጣውን በትዕግስት እንዲመልስ የሚያዝ የሱባዔ አይነት ነው፡፡

☞ቅድመ_ዝግጅት
ሱባኤ ከመግባታችንም ሆነ ከገባን ግዜ እንዲሁም ከጨረስን በኋላ ምእመናን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይገባናል ፡፡
➊ ሱባኤ_ከመግባት_አስቀድሞ
፩ በመጀመርያ ሱባዔ የምንገባበትን ምክንያት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል ፡፡
፪ ሱባኤ ለመግባት የወሰንበትን ምክንያት ከለየን በኋላ ምክንያታችንን ይዘን የንስሃ አባታችንን ማማከር ያስፈልጋል፡፡
፫ ለምን ያህል ቀናት መቆየት እንዳለብን መወሰን ያስፈልጋል ፡፡ሱባኤ ከዚህ እስከዚህ እቆያለሁ ብለን ዕቅድ የምንይዝበት ነው፡፡
፬ ወቅትና ቦታ መምረጥ ተገቢ ነው፡፡በቤተ ክርስቲያናችን በአብዛሀኛው ግዜ ሱባኤ የሚገባው በአጽዋማት ወቅት በመሆኑ ይህንን መለየት ነው ፡፡ምክንያቱም በጾም ወቅት ብዙ አባቶች ጸሎት የሚይዙበት ስለሆነ ፀሎታችን ከእነርሱ ጋር አብሮ ያርግልናልና ነው፡፡ እዚህ ላይ በማንኛውም ግዜ ሱባኤ አይያዝም ለማለት አይደለም በማንኛውም ግዜ ፈተና ያጋጠመው ሰው ሱባዔ ሊይዝ ይችላል፡፡
➋ በሱባኤ_ግዜ
ሀ. በጸሎት ሰአት ዓምድና ግድግዳ ሳይደገፉ መቋሚያ ሳይዙ በሁለት እግር ቀጥ ብሎ በመቆም መጸለይ ይኖርብናል፡፡ እንዲሁም ፊትን ወደ ምስራቅ መልሶ መቆም ወደ ግራ ወደ ቀኝ አለመዟዟር በሰቂለ ህሊና ኾኖ መጸለይ ይገባል፡፡
ለ . በቅደም ተከተል መፀለይ ይገባል በመጀመርያ አአተብ ከሚለው ተጀምሮ አቡነ ዘበሰማያትን ጠቅሶ ጸሎተ ሀይማኖትን መጨረስ ፡፡ሰግዱ እና ስለ መስቀል በሚያነሳው ላይ እየሰገዱና እያማተቡ መጸለይ ፡፡ በማስቀጠል አቡነ ዘበሰማያት ፤መዝሙረ ዳዊት ውዳሴ ማርያም ሌሎችንም ማስከተል ከዚያ 41 ግዜ ኪራላይሶ ይባላል ፡፡
ሐ. በሱባዔ ግዜ ከተሐራሚው የሚጠበቀው ነገር ሐጢአቱን እያሰበ ማዘን ማልቀስ ለእያንዳንዱ በደል ማልቀስ ማዘን ይገባዋል ፡፡
መ. በመጨረሻም ሱባዔ የገባው ሰው ሱበዔውን ሳይጨርስ ወይም አቋርጦ ከማንኛውም ሰው ጋር ፈፅሞ መገናኝት የለበትም ፡፡
➌ ከሱባዔ_በኋላ
ላቀረብነው ተማፅኖ እግዚአብሔር የሚያደርግልንን ነገር መጠበቅ ይኖርብናል ፡፡ "ሱባዔ" የገባ ሰው ሁሉ ራዕይ ላያይ ይችላል፡፡ምክንያቱም የእግዚአብሔር መልስ አሰጣጥ ለማንም ግልጽ አይደለም ፡፡ ከሱባዔ በኋላ መጀመሪያ የምናገኝው የህሊና ሰላም ነው ፡፡ ይህ ትልቅ የአምላክ ስጦታ ነው ፡፡ ከዚህ ባሻገር ሱባኤ ገብተን ያሰብነውን ካላገኝን ዳግመኛ ተዘጋጅተን እስከ መጨረሻው ሰዓት በመማፀን መጽናት ይኖርብናል፡፡፡

በመጭው አርብ ዕለት ጀምሮ ጾመ ፋልሰታ ( የመቤታችን ጾም ) በመባል የሚታወቀው እና ቤተ ክርስቲያናችን አበይት አጽዋማት ብላ ከደነገገቻቸው ወስጥ አንዱ ነው ፡፡ በዚህ ወራት ብዙዎቹ አባቶቻችንና እናቶቻችን በረከተ ስጋ ወነፍስ ያገኙበት የበረከት ጾም ነው እኛም ቢቻለን በሱባኤ ባይቻለን አቅማችን የፈቀደውን እየጾምን በጸሎት አምላካችንን መጠየቅ እንዲሁም እመቤታችን በምልጃዋ ታስበን ዘንድ መማፅን ያስፈልገናል ፡
✥✥✥ ሱባኤ ለመግባት ✥✥✥

→ ሱባዔ መግባት የሚፈልግ ምእመን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ያለምንም ዝግጅት ሱባዔ መግባት ለፈተና ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ /ሱባዔ ከመግባት ኣስቀድሞ/፣ ጊዜ ሱባዔ/ በሱባዔ ጊዜና ድኅረ ሱባዔ /ከሱባዔ በኋላ/ ዝግጅት ኣስፈላጊ ነው፡፡

ቅድመ ዝግጅት

ቅድመ ሱባዔ /ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ/
በመጀመሪያ ሱባዔ የምንገባበትን ምክንያት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ኣንድ ሰው ሱባዔ የሚገባበትን ዓላማ ለይቶ ካስቀመጠ ከሱባዔ በኋላ የሚጠበቀውን ነገር ማግኘት ኣለማግኘቱን ይረዳል፡፡ ይህ ሳይሆን ሱባኤ ቢገባ ከሱባኤው በኋላ የጠየቀው ነገር ስለሌለ ትርጉም ያጣል፡፡ ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት ለምን ሱባኤ ለመግባት እንዳሰብን ለይተን ማወቅ ይኖርብናል፡፡

- ሱባዔ ለመግባት የወሰንበትን ምክንያት ከለየን በኋላ ምክንያታችንን ይዘን የንስሓ ኣባታችንን ማማከር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በምክረ ካህን መጓዝ መጀመር ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በኣባትነታቸውና በሕይወት ልምዳቸው ምን ማድረግ እንደሚገባን ምክር ለማግኘት እገዛ ያደርግልናል፡፡ ቅድመ ሱባኤ ከንስሐ ኣባት ጋር መመካከር ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ኣንድ ሰው በሱባዔ ወቅት የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙት የተሰጠውን ምክር በመጠቀም ፈተናውን ለመቋቋም ይችላል፡፡ እንዲሁም የንስሓ ኣባቱ በሱባዔ ወቅት በጸሎት እንዲያስቡት መማከር የራሱ የሆነ ድርሻ አለው፡፡

- ሱባዔ ለመግባት ስናስብ ለምን ያህል ቀናት መቆየት እንዳለብን መወሰን ያስፈልጋል፡፡ ሱባዔ ከዚህ እስከዚህ እቆያለሁ ብለን ዕቅድ የምንይዝበት ነው፡፡ እንደ ኣቅማችንና እንደ ችሎታችን ከዚህ ቀን እስከዚህ ብለን በመወሰን ሱባዔ መግባት ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፡- ምንም ዓይነት ልምድ ሳይኖረው ኣንድ ሰው «በዋሻ እዘጋለሁ» ቢል ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡ ምክንያቱም በሱባዔ ወቅት ፈተና ስለሚበዛ የሚመጣበትን ፈተና መቋቋም ባለመቻል ሱባዔው ሊቋረጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ ዓቅምንና ችሎታን ኣገናዝቦ መወሰን ተገቢ ነው፡፡

- ሌላው ቅድመ ሱባዔ ለሱባዔ ተስማሚ የሆነ ወቅትና ቦታ መምረጥ ተገቢ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን በኣብዛኛው ሱባዔ የሚገባው ኣጽዋማትን ተከትሎ ነው፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንገባበት ወቅት የጾም ወቅት መሆን ኣለመሆኑን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በኣጽዋማት ወቅት የሚያዝ ሱባዔ ለተሓራሚ ጠቀሜታው እጅግ የጐላ ነው፡፡ ምክንያቱም በኣጽዋማት ወቅት ብዙ ኣባቶች ሱባዔ ስለሚይዙ ከኣባቶች ጸሎት ጋር ልመናችንና ጸሎታችን ሊያርግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ወቅትን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

- እዚህ ላይ «ከወርኃ አጽዋማት ውጭ ሱባዔ ኣይያዝም» የሚል ኣቋም ለመያዝ ኣይደለም፡፡ ኣንድ ሰው ፈተና ከኣጋጠመው በማንኛውም ጊዜ ሱባዔ ሊገባ እንደሚችል እዚህ ላይ ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ ከዚህም ባሻገር ሱባዔ የምንይዝበትን ቦታ መምረጥ ኣለብን፡፡ ለሱባዔ የምንመርጣቸው ቦታዎች ለፈተና የማያጋልጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም ሱባዔ ከተገባ በኋላ ኅሊናችን እንዳይበተን እገዛ ያደርግ ልናል፡፡ ጫጫታና ግርግር የሚበዛበት ቦታ በሰቂለ ኅሊና ለመጸለይ ኣያመችም፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንይዝባቸው ቦታዎች ከከተማ ራቅ ያሉ ገዳማትና ኣድባራት ተመራጭ ናቸው፡፡

ጊዜ ሱባዔ /በሱባዔ ጊዜ/

- በጸሎት ሰዓት ዓምድና ግድግዳ ሳይደገፉ መቋሚያ ሳይዙ በሁለት እግር ቀጥ ብሎ በመቆም መጸለይ ይኖርብናል፡፡ እንዲሁም ፊትን ወደ ቤተ ክርስቲያን ወይም ወደ ምሥራቅ መልሶ መቆም ወዲያና ወዲህ ወደ ግራ ወደ ቀኝ ኣለመዟዟር በሰፊሐ እድ በሰቂለ ኅሊና ኾኖ መጸለይ ይገባል፡፡ መዝ.5፡3፤ መዝ.133፡2፤ ዮሐ.11፡41፡፡

በሱባዔ ወቅት በቅደም ተከተል መጸለይ ኣለብን፡፡ መጀመሪያ «በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሐዱ ኣምላክ ኣኣትብ ገጽየ ወኩለንታየ በትእምርተ መስቀል በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣንዱ ኣምላክ መላ ሰውነቴን በትእምርተ መስቀል ኣማትባለሁ» እያለ ሰጊድን ከሚያነሣው ሲደርስ መስገድ መስቀልን ከሚያነሣ ላይ ስንደርስ ማማተብ ይገባል፡፡
በማስከተል አቡነ ዘበሰማያት፣ መዝሙረ ዳዊት፣ ውዳሴ ማርያምና ሌሎች በመዝገበ ጸሎት የተካተቱትን መጸለይ፤ ቀጥሎ ኣቡነ ዘበሰማያት፣ ጸሎተ እግዝእትነ ማርያምን፣ ጸሎተ ሃይማኖትን ከጸለይን በኋላ ኣቡነ ዘበሰማያት መድገም፤ ከዚያ 41 ጊዜ ኪርያላይሶን ይባላል፡፡ ሌላው በሱባዔ ጊዜ ከተሓራሚ የሚጠበቀው ነገር ኃጢኣቱን እያሰበ ማዘን ማልቀስ ነው፡፡ ሲያለቅስም ለእያንዳንዱ በደል እንባ ማፍሰስ ያስፈልጋል፡፡
በመጨረሻም ሱባዔ የገባ ሰው ሱባዔውን ሳይጨርስ ወይም ሱባዔውን አቋርጦ ከማንም ሰው ጋር ፈጽሞ መገናኘት የለበትም፡፡

ድኅረ ሱባዔ /ከሱባዔ በኋላ/

ለቀረበ ተማኅፅኖ እግዚኣብሔር የሚያደርግልንን ነገር መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ እግዚኣብሔር ላቀረብንለት ምልጃና ጸሎት እንደ ልባችን መሻት እንደ እርሱ ቸርነት እርሱ በወደደ ጊዜ ያደርግልናል፡፡ ሱባዔ የገባ ሰው ሁሉ ራእይ ላያይ ይችላል፡፡ ምክንያቱም የእግዚኣብሔር መልስ ኣሰጣጥ ለማንም ግልጽ ኣይደለም፡፡ ከሱባዔ በኋላ መጀመሪያ የምናገኘው የኅሊና ሰላምን ነው፡፡ ይህ ትልቅ የኣምላክ ስጦታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሱባዔ ገብተን ያሰብነውን ካላገኘን ዳግመኛ ተዘጋጅተን እስከ መጨረሻው ሰዓት መማፀን መጽናት ይኖርብናል፡፡
#ነሐሴ_2

ነሐሴ ሁለት በዚች ቀን መኑፍ ከሚባል አገር #ቅድስት_አትናስያ አረፈች፣ ከነገሥታት ወገን የሆነች #ቅድስት_ኢዮጰራቅስያ አረፈች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_አትናስያ_ቡርክት

ነሐሴ ሁለት በዚች ቀን መኑፍ ከሚባል አገር ቅድስት አትናስያ አረፈች።

የዚችም ቅድስት ወላጆቿ ባለጸጎች ነበሩ እነርሱም በሞቱ ጊዜ ቤቷን ለእንግዳ ማደሪያ ታደርግ ዘንድ በጎ ኃሳብ አሰበች ወደርሷም የሚመጡትን እንግዶች ሁሉ ትቀበላቸው ነበር። በገዳም ለሚኖሩ መነኰሳትም የሚያስፈልጓቸውን ትሰጣቸው ነበር ስለ በጎ ሥራዋም ይወዷት ነበር።

ከዚህም በኋላ ግብራቸው የከፋ ክፉዎች ሰዎች ወደርሷ ተሰብስበው ኃሳቧን ወደ ኃጢአት ሥራ መለሱትና ኃጢአትን አብዝታ ትሠራ ጀመር። በአስቄጥስ ገዳም በሚኖሩ አረጋውያን ቅዱሳን ዘንድም ወሬዋ ተሰማ ስለእርሷም እጅግ አዘኑ አባ ዮሐንስ ሐጺርንም ጠርተው ስለርሷ የሆነውን ነገሩት አስቀድማም ከእነርሱ ጋራ በጎ ስለ ሠራች ወደ እርስዋ ይሔድ ዘንድ ነፍስዋንም ለማዳን ይወድ ዘንድ ለመኑት።

እርሱም ትእዛዛቸውን ተቀበለ በጸሎታቸውም እንዲረዱት ለመናቸው ያን ጊዜም አባ ዮሐንስ ሐጺር ተነሥቶ ሔደ አትናስያ ወዳለችበት ቦታ ደረሰ ለበረኛዋም ለእመቤትሽ ስለእኔ ንገሪ አላት። በነገረቻትም ጊዜ ለረከሰ ሥራ እንደሚፈልጓት ሰዎች ሁሉ የመጣ መሰላትና አጊጣ በዐልጋዋ ላይ ሁና ጠራችው። ወደርሷም ገባ እርሱም እንዲህ እያለ ይዘምር ነበር በሞት ጥላ ውስጥ ብሔድም እንኳ ክፉን አልፈራውም አንተ ከእኔ ጋራ ነህና።

ከእርሷ ጋራም አስቀመጠችው ያን ጊዜም ራሱን ዘንበል አድርጎ አለቀሰ ለምን ታለቅሳለህ አለችው እርሱም ሰይጣናትን በላይሽ ሲጫወቱ አየኋቸው ክብር ይግባውና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ለምን አሳዘንሺው የቀድሞ በጎ ሥራሽን ትተሽ ወደ ጥፋት ሥራ ተመልሰሻልና አላት።

ቃሉንም ሰምታ ደነገጠችና ተንቀጠቀጠች ምን ይሻለኛል አለችው ንስሐ ግቢ አላት እርሷም እግዚአብሔር ይቀበለኛልን አለችው እርሱም አዎን አላት እርሷም ወደምትሔድበት ከአንተ ጋራ ውሰደኝ አለችው እርሱም ነዪ ተከተይኝ አላት።

ያን ጊዜም ፈጥና ተነሥታ በኋላው ተከተለችው ከገንዘቧም ምንም ምን አልያዘችም። በመሸም ጊዜ ለማደር ወደ ጫካ ውስጥ ገቡ በዚያም ለእርስዋ ቦታ አዘጋጅቶ እስኪነጋ በዚህ አረፍ ብለሽ ተኚ እኔም ወደዚያ እሆናለሁ አላት። ይህንንም ብሎ ከእርሷ ጥቂት ተገልሎ እየጸለየ ብቻውን ተቀመጠ።

በሌሊቱ እኩሌታም ሊጸልይ ተነሣ ከምድር እስከ ሰማይ የሚደርስ የብርሃን ምሰሶ አየ የእግዚአብሔርም መላእክት የከበረች ነፍስን ተሸክመው ሲወጡ አይቶ አደነቀ። በነጋም ጊዜ ወደ ርሷ ሔደ ሙታም አገኛት እጅግም አዘነ ስለ ርሷም ያስረዳው ዘንድ እየሰገደ ወደ እግዚአብሔር ለመነ።

ወደርሱም እንዲህ የሚል ቃል መጣ ከቤቷ በወጣች ጊዜ እግዚአብሔር ንስሓዋን ተቀብሎ ኃጢአትሽ ተሠረየልሽ ብሎአታል። ከዚህም በኋላ ሒዶ ለአረጋውያን የሆነውን ሁሉ ነገራቸው እነርሱም እርሱ እንዳያት ማየታቸውን ነገሩት የኃጢአተኛን ወደ ንስሐ መመለሱን እንጂ ሞቱን የማይሻ እግዚአብሔርን አመሰገኑት።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ኢዮዸራቅስያ_ድንግል

በዚህችም ቀን ከነገሥታት ወገን የሆነች ቅድስት ኢዮጰራቅስያ አረፈች። የእርስዋም የአባቷ ስም ኢጣጎኖስ ነው የንጉሥም አማካሪ ነበር የእናቷም ስም ኢዮጰራቅስያ ነው እነርሱም ደጎች ነበሩ ጾምና ጸሎትንም ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡ ነበሩ። ይችንም ቅድስት በወለዷት ጊዜ በእናቷ ስም ኢዮጰራቅስያ ብለዉ ጠሩዋት።

ከጥቂት ጊዜ በኋላም አባቷ አረፈ ዕድሜዋም ስድስት ዓመት በሆነ ጊዜ እናቷ ወደ ደናግል ገዳም ከእርሷ ጋር ወሰደቻት ይህችም ቅድስት ደናግሉ ሲያገለግሉ አይታ ስለ ምን እንዲህ ደክማችሁ ትሠራላችሁ አለቻቸው እነርሱም ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ ነው ብለው መለሱላት ወደ ዲያቆናዊትም ሒዳ ያመነኲሷት ዘንድ ለመነች እነርሱም ለእናቷ ነገሩዋት እናቷም ለዲያቆናዊተዋ ሰጠቻት በደናግሉም ሁሉ ዘንድ አደራ ሰጠቻት ከጥቂትም ቀኖች በኋላ እናቷ አረፈችና ቀበሩዋት።

ከዚህም በኋላ ቅድስት ኢዮጰራቅስያ የምንኲስና ልብስን ለበሰች በጾም በጸሎትና በሰጊድ ተጋድሎ ጀመረች በየሰባት ቀንም ትጾም ነበር ሰይጠንም በእርሷ ላይ ቀንቶ ሊፈትናት ጀመረ ወደ ውኃ ውስጥ እርስዋን የሚጥልበት ጊዜ ነበር እንጨትም ስትፈልጥ በምሳር የሚአቊስልበት ጊዜ ነበር። የፈላ ውኃም በላይዋ የሚያፈሰበት ጊዜ ነበር ነገር ግን ምንም ምን የጐዳት የለም።

ለደነግሎችም ስታገለግል ብዙ ዘመናት ኖረች ምንም አትታክትም ነበር በምድርም ላይ አትተኛም መላዋን ሌሊት ቁማ በጸሎት ታድር ነበር እንጂ ከገድሏ ጽናትም የተነሣ ደናግሉ እስከሚያደንቁ ድረስ አርባ ቀን ቁማ ትፈጽም ነበር።

ከዚህም በኋላ ጌታችን በሽተኞችን በማዳን አጋንንትን በማስወጣት የዕውሮችን ዐይን በመግለጥ የአንካሶችንም እግር በማስተካከል ድንቆችንና ተአምራቶችን በእጆቿ ገለጠ።

ዲያቆናዊት ኢዮኤልያም ለኢዮጰራቅስያ መጸሐፍትንና የምንኵስናንም ሥርዓት አስተማረቻት በሥራም ሁሉ ትሳተፋት ነበር እጅግም ይፋቀሩ ነበር እርሷም ሰማያዊ ሙሽራ ወደአለበት የመንግሥት አዳራሽ የማያልቅ ተድላ ደስታም ወደአለበት ኢዮጵራቅስያን ሲያወጧት ራእይን አየች።

በነቃችም ጊዜ ለደናግል ነገረቻቸው ወደርሷ ሲሔዱም በትኩሳት በሽታ ታማ አገኟት ስለእነርሱም እንድትጸልይ ለመኑዋት እርሷም ደግሞ በጸሎታቸው እንዲአስቧት ለመነቻቸው ያን ጊዜም ጸሎት አድርጋ መረቀቻቸውና በሰላም አረፈች በእናቷም መቃብር ውስጥ ቀበሩዋት።

ወዳጅዋ ኢዮኤልያም ወደ መቃብርዋ ሒዳ ጸለየችና በሦስተኛው ቀን አረፈች ከእርሷም ጋር ተቀበረች።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ)
#የቅዳሜ_ውዳሴ_ማርያም_ትርጓሜ

በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይነጠፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናም ሊቁን ባርካው ምስጋናዉን ጀምሯል፡፡

፩. ንጽሕት ነሽ፤ ብርህት ነሽ፡፡ በአፍአ በውስጥ ንጽሕት ነሽ፡፡ ሊቁ “ዲያተሳሮን” በተባለው የወንጌል ትርጓሜ መጽሐፉ የእመቤታችንን ንጽሕና ሲናገር፡- “የማርያም ሰውነት የምድር ላይ መቅደስ ነው፡፡ በዚሁ መቅደስም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በኀጢአት፣ በሞትና በርግማን ፈንታ የበረከትን ዘር ሊዘራ መጣ፡፡ የኤልሳቤጥም ሰላምታ ይህንን አረጋገጠ፡፡… አንተና እናትህ ብቻ በማንኛውም ረገድ ንጹሐን ናችሁ፡፡ ጌታ ሆይ! በአንተ ውስጥ ምንም ነቅዕ የለም፤ በእናትህም ውስጥ ምንም ምልክት የለም” ብሏል። ጌታን በማኽል እጅሽ የያዝሽው ሆይ! ምልዕተ ክብር ሆይ! (ተፈስሒ) ደስ ይበልሽእያሉ ፍጥረት ኹሉ ከአንቺ ጋር ደስ ይላቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ከአንቺ ጋር አንድ ባሕርይ ቢኾን ባለሟልነትን አግኝተሻልና (ተፈስሒ) ደስ ይበልሽ፡፡ ግርምት ድንግል ሆይ! ክብርሽን ገናንነትሽን ዕፁብ ዕፁብ እያልን እናመሰግናለን (እናደንቃለን)፡፡ ከማኅፀንሽ ፍሬ የባሕርያችን ድኅነት ተገኝቷልና ከመልአኩ ጋር እንደ መልአኩ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ የማኅፀንሽ ፍሬ ከአባቱ ጋር አስታርቆናልና እንደ መልአኩ ምስጋና እናቀርብልሻለን፡፡ ሊቁ ቅድም በጠቀስነው መጽሐፉ፡- “… መልአኩ ወደ አንዲት ድንግል ተላከ፡፡ ወደ እርሷ ገብቶም “እነሆ ድንግልናሽ ሳይነዋወጽ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” አላት/ሉቃ.፩፡፴፩//፡፡ ይኸውም በሥጋ ተገልጦ ሊመጣ ስላለው ስለ አካላዊ ቃል ሲናገር ነው፡፡ ሲነግራት “ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” አላት እንጂ “ኢየሱስ የተባለው” እንዳላላት ልብ በሉ፡፡ ይኸውም የሰው ልጆች ወልደ እግዚአብሔር በለበሰው ሥጋ የሚድኑበት ስም መኾኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ ማለት በዕብራይስጥ “መድኅን” ማለት ነውና፡፡ መልአኩ “ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” ሲላት መድኅን ትዪዋለሽ ማለቱ ነው፡፡ ለምን? ሕዝቡን ኹሉ ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና” ብሏል /ማቴ.፩፡፳፩/፡፡ ከአባቱ ጋር ካስታረቀን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፪. አባ ሕርያቆስ፡- “እግዚአብሔር አብ በሰማይ ኾኖ ምሥራቅንና ምዕራብን ሰሜንና ደቡብን ዳርቻዎችንም ኹሉ በእውነት ተመለከተ፤ እንደ አንቺ ያለ አላገኘም፡፡ የአንቺን መዓዛ ወደደ፤ የሚወደው ልጁንም ወደ አንቺ ሰደደ” እንዲል /ቅዳ.ማር. ቁ.፳፬/x እንደ ሰርግ ቤት አደፍ ጉድፍ የሌለብሽ ኾነሽ ቢያገኝሽ መንፈስ ቅዱስ አድሮብሻልና፤ ኃይለ ልዑል ወልድም ሥጋሽን ለብሷልና አንድም መንፈስ ቅዱስ ከሦስቱ ግብራት ከልክሎሻልና ኃይለ ልዑል ወልድም ከሦስቱ ግብራት ከልሎሻልና ለዘለዓለሙ ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃልን ወለድሽልን /ሃይ.አበ.፻፲፡፳፱/፡፡ ሰው ኾኖ ከኃጢአት አዳነን /ማቴ.፩፡፳፩/፡፡ ሰው ኾኖ ከኃጢአታችን ፍዳ ካዳነን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፫. መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ ወልደሽልናልና ከዳዊት ሥር የተገኘሽ ባሕርይ አንቺ ነሽ /ሉቃ.፩፡፴፪/፡፡ ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ከአብ ባሕርይ ዘእም ባሕርይ አካል ዘእም አካል የተወለደ፣ ተቀዳሚ ተከታይ (ታላቅም ታናሽም) የሌለው አካላዊ ቃል ባሕርዩን በሥጋ ሠወረ፡፡ ከአንቺም አርአያ ገብርን ነሣ /ፊል.፪፡፯/፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “አካላዊ ቃል አርአያ ገብርን ነሥቶ (የባሪያን መልክ ይዞ)በሰውም ምሳሌ ኾኖ ራሱን ባዶ አደረገ ሲል ምን ማለት ነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ራሱን ባዶ አደረገ ሲል የእኛን ባሕርይ ገንዘብ ባደረገ ጊዜ ባሕርየ መለኮቱ ተለውጧል ማለት አይደለም፡፡ ባሕርየ መለኮቱን ትቶ መጣ ማለትም አይደለም፤ በፈቃዱ ደካማ ባሕርያችንን ገንዘብ አደረገ ማለት ነው እንጂ፡፡ ወልደ እግዚአብሔር ራሱን ባዶ ያደረገው በመቅድመ ወንጌል “ከጥንት ዠምሮ በባሕርያችን እስኪሠለጥን ድረስ ሰይጣን በተንኰል በሥጋ ከይሲ እንደተሠወረ፤ እኛም ከፍዳ መዳናችን ቃለ እግዚአብሔር በባሕርያችን በመሠወሩ ኾነ” ተብሎ እንደተጻፈ የእኛን ባዶነት በጸጋው ለመሙላት ነው፡፡ ሰው የኾነው እኛን አማልክት ዘበጸጋ ያደርገን ዘንድ ነው፡፡” የባሪያውንመልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ኾኖ ስለ እኛ ብሎ ራሱን ባዶ ካደረገ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፬. አደፍ ጉድፍ ሳይኖርብሽ አምልክን የወለድሽው እመቤታችን ሆይ! በኃጢአት ብርድ የተያዘውን ዓለም ኃጢአቱን ያርቅለት ዘንድ ፀሐየ ጽድቅ ጌታ ከአንቺ ተወልዷልና፤ ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው እንደተናገሩም ዘር ምክንያት ሳይኾንሽ፣ መለወጥ ሳያገኝሽ ወልደሸዋልና ከምድር በላይ ያለሽ ኹለተኛ ሰማይ አንቺ ነሽ፡፡ ኢትዮጲያዊው ቄርሎስም፡- “ኦ ሰማይ ዳግሚት ዘወለደቶ ለፀሐየ ጽድቅ ዘውእቱ ብርሃነ ቅዱሳን ዘሰደዶ ለጽልመት - ጨለማን ያሳደደውን (ያስወገደውን) የቅዱሳን ብርሃን የሚኾን አማናዊ ፀሐይን የወለደች ኹለተኛይቱ ሰማይ ሆይ! …” እያለ ያወድሳታል /አርጋኖን ዘረቡዕ/፡፡ ዘር ምክንያት ሳይኾንሽ ከወለድሽው ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፭. ከተለዩ የተለየሽ፣ ከከበሩ የከበርሽ በውስጧም ሕግ የተጻፈበት ኪዳን ያለብሽ የተሠወረ መና ያለበት መሶበ ወርቅ ያለብሽ ደብተራ (ድንኳን) አንቺ ነሽ /ዘጸ.፳፮፡፩-፴/፡፡ ይኸውም መና የተባለው ሰው ኾኖ በማኅፀንሽ ያደረው ወልደ እግዚአብሔር ነው፡፡ መተርጕማኑ ይህን የበለጠ ሲያብራሩት፡- “ድንኳኗ የእመቤታችን ምሳሌ፤ ቅድስት የነፍሷ፤ ቅዱሳን የሥጋዋ፤ ታቦቱ የመንፈስ ቅዱስ፤ ጽላት የልቡናዋ፤ ቃሉ በመንፈስ ቅዱስ የተገለጸላት ምሥጢር ምሳሌ ነው፡፡ አንድም ቅዱሳን የሥጋዋና የነፍሷ፤ ቅድስት የልቡናዋ፤ ታቦት የማኅፀኗ፤ ጽላት የትስብእት፤ ቃሉም የመለኮት ምሳሌ ነው” ይላሉ /ውዳሴ ማርያም ንባቡና ትርጓሜው፣ ገጽ ፻፸፬/፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በአርጋኖን ዘሐሙስ ላይ፡- “ተፈሥሒ ኦ ደብተራ ብርሃን ማኅደሩ ለዐቢይ ሊቀ ካህናት - የታላቁ ሊቀ ካህናት ማደርያ የብርሃን ድንኳን ሆይ! ደስ ይበልሽ” በማለት የሊቀ ካህናት የባሕርይ አምላክ የክርስቶስ እናት አማናዊት ድንኳን መኾኗን አስተምሯል፡፡ አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾነ፡፡ የክብር ባለቤት እርሱን በዚህ ዓለም ወለደችው፡፡ ለዘለዓለሙ ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃል ሰው ኾኖ ከኃጢአታችን ፍዳ አድኖናልና ሰው ኾኖ ያዳነን የነባቢ በግዕ (የሚናገር በግ የክርስቶስ) እናቱ ደስ ይላታል /ዮሐ.፩፡፳፱/፡፡ ለዘለዓለሙ ጸንቶ የሚኖር አካላዊ ቃል ሰው ኾኖ ከኃጢአታችን ፍዳ ካዳነን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፮. እርሱን ከወለድሽ በኋላ ማኅተመ ድንግልናሽ ሳይለወጥ ኑረሻልና የክርስቶስ እናቱ ተባልሽ፡፡ ድንቅ በሚያሰኝ ተዋሕዶ አማኑኤልን ወልደሸዋልና ባለመለወጥ አጸናሽ፡፡ ታላቁ የቤተ ክርስቲያን መምህር ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ለማንም ሴት ያልተሰጠ ለድንግል ማርያም ብቻ የተሰጠ ድንግልና ከእናትነት ጋር አስተባብራ ስለ መገኘቷ ሲገልጥ “ወሰቦሂ ወለደቶ ዐቀበ ድንግልና፣ ዘእንበለ ርኩስ ከመ በፀንሳ መንክር ትኩን መራሂተ ለሃይማኖት ዐባይ - ከድንግል ተወለደ፤ በወለደችውም ጊዜ ድንግልናዋ ያለመለወጥ አጸና፡፡ ድንቅ የሚኾን ፅንሷ ለደገኛው ሃይማኖት መሪ ትኾን ዘንድ” በማለት ቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን ስትወልድው ማኅተመ ድንግልናዋ እንዳልተለወጠ ጌታም ሰው ሲኾን ባሕርየ መለኮቱ ላለመለወጡ፣ እርሷ ድንግል ወእም (ድንግልም እናትም) ስትባል እንደምትኖር አካላዊ ቃል ክርስቶስም አምላክ ወሰብእ (ሰው የኾነ አምላክ) ሲባል የሚኖር የመኾኑን የተዋሕዶ ልዩ ምሥጢርን ያወቅንባት የተረዳንባት እርሷ ብቻ መኾኗን አስተምሯል /ሃይ.አበ.፷፮፡፴፪/፡፡ እንዲህ ካለ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፯. ከምድር እስከ ሰማይ ደርሳ፣ በላይዋ ዙፋን ተነጽፎባት፣ በዚያ ላይ ንጉሥ ተቀምጦባት፣ መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ያዕቆብበፍኖት ሎዛ ያያት የወርቅመሰላል አንቺ ነሽ /ዘፍ.፳፰፡፲-፳፪/፡፡ሰው ከመኾኑ አስቀድሞ ሰውም ከኾነ በኋላ የማይመረመር እርሱን በተፈትሖ በማይታወቅ በማኅፀንሽ ችለሸዋልና እኛን ስለማዳን ከአንቺ ሰው ከኾነ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሰዋስው (አማላጅ) ኾንሽን፡፡ እኛን ስለማዳን ከአንቺ ሰው ከኾነ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፰. ጽርሐ ንጽሕት ሆይ! እነሆ ጌታ የፈጠረውን ዓለም ኹሉ በቸርነቱ ብዛት ያድን ዘንድ ከአንቺ ተወለደ፡፡ ቸር ሰው ወዳጅ ነውና በአፍአ በውስጥ እናመስግነው፡፡ ቸር ሰው ወዳጅ ከኾነ ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፱. አደፍ ጉድፍ የሌለብሽ ድንግል ምልዕተ ክብር ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ ከእናትሽ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ጠብቆሻልና የዓለም ኹሉ መክበሪያ ንጽሕት ጽዋዕ ነሽ (ከሥላሴ ለምንጠጣው ክብር ምክንያት አንቺ ነሽ)፡፡
እንደ ደብተራ ኦሪቷ ማለትም ሙሴና አሮን በቀዳማይ ሰዓተ ሌሊት አብርተው በቀዳማይ ሰዓተ መዓልት እንደሚያጠፏት ፋና ያይደለሽ የማትጠፊ ፋና ነሽ /ዘጸ.፳፭፡፴፩-፵/፡፡
እንደ ቀደመችው የኦሪት ቤተ መቅደስ ያይደለሽ የማትፈርሺ መቅደስ ነሽ /፩ኛ ነገ.፯፡፵፰-፶/፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊሥ ዘጋሥጫም፡- “አንቲ ውእቱ መቅደስ ዘሐነጸ ሰሎሞን ወአስቀጸላ በሜላትሮን ወለበጠ ዳቤራ በውሳጥያተ መቅደስ፤ … - ሰሎሞን ያሠራት እንደ ዝናር እንደ ዐምድ ባለ ወርቅ የጠፈሯን ዙርያ ያስጌጣት፤ በመቅደስ ውስጥ ያለቺውን ቅድስተ ቅዱሳንዋን ዐውደ ምሕረቷን ግድግዳዋን በጥሩ ወርቅ ያስጌጣት፤ ቁመቱ ሃያ ክንድ፤ ክንፉ ዐሥራ አምስት ክንድ የሚኾን ኪሩብን በውስጧ ያሣለባት ቤተ መቅደስ አንቺ ነሽ” በማለት በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ የጸናች እመቤታችን ሰሎሞን ባሠራት የወርቅ ቤተ መቅደስ መስሎ ኹለንተናዋ በንጽሕና በቅድስና ያጌጠች የተዋበች መኾኗን አስተምሯል /አርጋኖን ዘዐርብ/፡፡ ዳሩ ግን እመቤታችን በንጽሕናዋ በቅድስናዋ በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ብትመሰልም ሊቁ (ኤፍሬም) እንዳለው ክብሯ የላቀ ነው፤ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ናትና የማትፈርስ መቅደስ ናት /መዝ.፹፮፡፩-፭/፡፡

የማትለወጥ የቅዱሳን ሃይማኖታቸው (ቅዱሳን የሚያምኑበት ክርስቶስን የወለድሽላቸው አንቺ) ነሽ፡፡ ድንግል ሆይ! በውስጥ በአፍአ በነፍስ በሥጋ ይቅር ይለን ዘንድ፣ ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ከልጅሽ ዘንድ አማልጅን፡፡ኃጢአታችንን ከሚያስተሠርይልን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

አነሣሥቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈጸመን ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን!!!
ነሐሴ 3

ነሐሴ ሦስት በዚህች ቀን በገድል የተጠመደ መስተጋድል የከበረ #አባ_ስምዖን_ዘዓምድ አረፈ፣ ከመንግሥት ወገን የሆነች #ቅድስት_ሶፍያ አረፈች።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ታላቁ_አባ_ስምዖን_ዘዓምድ

ነሐሴ ሦስት በዚህች ቀን በገድል የተጠመደ መስተጋድል የከበረ አባ ስምዖን ዘዓምድ አረፈ። ለዚህም ቅዱስ ስድስት ዓመት በሆነው ጊዜ አባቱ የበጎቹ ጠባቂ አደረገው። ወደ ቤተ ክርስቲያንም በመሔድ ሁል ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍትን ይሰማ ነበር የእግዚአብሔርም ቸርነት አነሳሥቶት ወደ አንድ ገዳም ሒዶ መነኰሰ ብዙ ዘመናትም በገድል ተጠምዶ ሲጋደልና ሰውነቱን ሲያስጨንቅ ኖረ።

ከዚህም በኋላ ገመዱ ሥጋውን ቆርጦ እስቲገባ ድረስ በወገቡ ላይ ገመድን አሠረ። ሥጋውም ተልቶ ከእርሱ ክፉ ሽታ ይወጣ ነበር ስለ ክፉ ሽታውም መነኰሳቱ አዘኑ ተጸየፉትም ወደ አበ ምኔቱም ተሰብስበው ይህን መነኰስ ስምዖንን ከእኛ ዘንድ ካላወጣኸው አለዚያ አንተን ትተን ወደሌላ እንሔዳለን አሉት እርሱም ምን አደረገ አላቸው እነርሱም ጥራውና አንተ ራስህ እይ አሉት።

ጠርቶትም መጥቶ በፊቱ በቆመ ጊዜ ደም ከመግል ጋራ በእግሮቹ ላይ ሲፈስ አየ አበ ምኔቱንም እጅግ አስጨነቀው። ልብሶቹንም ገልጦ በሥጋው ውስጥ የገባውን ያንን ገመድ አየው አበ ምኔቱም በእርሱ ላይ ተቆጥቶ ይህን ታደርግ ዘንድ እንዴት ደፈርክ አለው በታላቅ ድካምም ያንን ገመድ ከሥጋው ውስጥ አወጡት ቍስሉም እስከሚድን መድኃኒት እያደረጉለት ኃምሳ ቀኖች ያህል ኖረ።

ከዚህም በኋላ አበ ምኔቱ እንዲህ አለው ልጄ ስምዖን ሆይ እንግዲህስ ወደ ፈለግኸው ቦታ ሒድ ከዚያም ወጥቶ ሔደ በደረቅ ጕድጓድ ውስጥም ገብቶ ከእባቦችና ከጊንጦች ጋራ ኖረ።

ከዚህም በኋላ አገልጋዩ ስምዖንን ለምን ሰደድከው አሁንም ፈልገህ መልሰው በፍርድ ቀን እርሱ ከአንተ ይሻላልና ብሎ ሲገሥጸው አበ ምኔቱ ራእይን አየ። አባ ስምዖንንም ከገዳሙ ስለመውጣቱ ገሠጸው።

በነጋም ጊዜ አበ ምኔቱ ራእይን እንዳየ ስለ አባ ስምዖንም እንደገሠጸው ለመነኰሳቱ ነገራቸው ወንድሞችም ደንግጠው እጅግ አዘኑ እስከምታገኙትም ሔዳችሁ በቦታው ሁሉ ፈልጉት አላቸው ሔደውም ፈለጉት ግን አላገኙትም። ከዚህም በኋላ መብራትን አብርተው ወደ ጕድጓድ ውስጥ ገቡ ያለ መብልና መጠጥም ከእባቦችና ከጊንጦች ጋራ ተቀምጦ አዩት።

ገመድም አውረዱለትና ከዚያ አወጡት በፊቱም ሰግደው በአንተ ላይ ያደረግነውን በደላችንን ይቅር በለን አሉት እኔንም ስለ አሳዘንኳችሁ ይቅር በሉኝ አላቸው። ከዚህም በኋላ ወደ ገዳማቸው ወሰዱት በብዙ ገድልም ተጠምዶ ሲያገለግል ኖረ።

ከዚህም በኋላ ከዚያ ገዳም በሥውር ወጥቶ ወደ አንዲት ዐለት ቋጥኝ ደረሰ። በእርስዋም ላይ ሳያረፍና ሳይተኛ ስልሳ ቀን ቆመ። ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ ስለ ብዙ ሰዎች ድኅነት እግዚአብሔር እንደ ጠራው ነገረው። ከዚያም ሔዶ ቁመቱ ሠላሳ ክንድ የሚሆን የድንጋይ ምሰሶ አገኘ ድንቅ ተአምራትን እያደረገ በሽተኞችንም እየፈወሰ ወደርሱ የሚመጡትንም እያስተማረ ዐሥራ ሁለት ዓመት በድንጋይ ምሰሶው ላይ ቆመ።

አባቱም ፍልጎት ነበር ግን ሳያየው ሞተ እናቱ ግን ወሬውን ሰምታ ከብዙ ዘመናት በኋላ ወደርሱ መጣች በድንጋይ ምሰሶውም ላይ ቁሞ አገኘችው አይታውም አለቀሰች ከድንጋይ ምሰሶውም በታች ተኛች። ቅዱስ ስምዖንም ጌታችን በጎ ነገርን ያደርግላት ዘንድ ስለርሷ ለመነ ያን ጊዜም እንደተኛች አረፈችና ከደንጊያው ምሰሶ በታች ቀበሩዋት።

ሰይጣንም በእርሱ ላይ ቀንቶ እግሩን መታው ከእግሩ ትል እየወደቀ በአንዲት እግሩ ብዙ ዓመታት ኖረ። ከዚህም በኋላ የሽፍቶች አለቃ ወደርሱ መጥቶ ንስሐ ገባ ጥቂት ቀኖችም ኑሮ አረፈ በጸሎቱም ሕይወትን ወረሰ። ወደርሱ ስለሚመጡ ብዙ ሕዝቦችም የውኃ ጥማት እንዳያስጨንቃቸው ወደ እግዚአብሔር ለምኖ ከድንጋይ ምሰሶው በታች ውኃን አፈለቀላቸው።

ዳግመኛም ወደ ሌላ ምሰሶ ተዛወረ በእርሱም ላይ እየተጋደለ ሠላሳ ዓመት ኖረ። ብዙዎች አረማውያንንና ከሀድያንን ካስተማራቸውና ወደ ፈጠራቸው እግዚአብሔር ከመለሳቸው በኋላ ክብር ይግባውና ወደ ወደደው ክርስቶስ ሔደ በሰላምም አርፎ የዘላለም ሕይወትን ወረሰ።

ከዚህም በኋላ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አባ ስምዖን እንዳረፈ በሰማ ጊዜ ካህናትን ዲያቆናትንና የአገሩን መኳንንቶች ከእርሱ ጋራ ይዞ የቅዱስ አባ ስምዖን ሥጋው ወዳለበት ደረሰ በታላቅ ክብርም ተሸክመው እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ እስክንድርያ አድርሰው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖሩት ከሥጋውም ድንቆችና ተአምራቶች ታላቅ ፈውስም ተገለጡ።

✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞

#ቅድስት_ሶፍያ_ቡርክትና_ደናግል_ልጆቿ

በዚችም ቀን ከመንግሥት ወገን የሆነች ሶፍያ አረፈች። ለዚችም ቅድስት ብዙ ሀብትና ብዙ ጥሪት ነበራት ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ ፍቅር የክርስቶስን መከራ መስቀል አንሥታ ትሸከም ዘንድ ከሦስት ሴቶች ልጆቿ ጋራ ወደ ሮም ከተማ ሔደች።

ንጉሥ እንድርያሰኖስም ክርስቲያን እንደ ሆነች አውቆ ከልጆቹ ጋራ ወደ አደባባይ አስቀረባትና ስለ ሀገርዋና ስለ ስሟ ጠየቃት እርሷም የሚቀደመው ስሜ ክርስቲያን ነኝ ወላጆቼ ያውጡልኝ ስም ሶፊያ ነው እኔም በኢጣልያ ባለ ብዙ ወገን ነኝ ክብር ይግባውና በክርስቶስ ፈቃድም ልጆቼን መሥዋዕት አድርጌ ላቀርብ ወደ አገርህ መጣሁ አለችው። ከዚህም በኋላ የከዳተኛው ንጉሥ ሥቃዩ እንዳያስፈራቸው ልጆቿን አበረታቻቸው።

ምስክርነታቸውንም ፈጽመው ከሞቱ በኋላ ገንዛ ከሮሜ ከተማ ውጭ ቀበረቻቸው።

በሦስተኛውም ቀን መታሰቢያቸውን ታደርግ ዘንድ ልጆቿ ወደ ተቀበሩበት ከብዙዎች ከከተማው ሴቶች ጋራ ሔደች እንዲህ ብላም ጸለየች አክሊላትን የተቀዳጃችሁ የምታምሩ ፍጹማት የሆናችሁ ልጆቼ ሆይ እኔንም ከእናንተ ጋራ ውሰዱኝ ይህንንም እንዳለች ወዲያውኑ አረፈች ከልጆቿም ጋር ተቀበረች።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ነሐሴ)