Meseret Media
58.5K subscribers
579 photos
14 videos
113 links
መሠረት ሚድያ በኢትዮጵያ ለበርካታ አመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የሰሩ ባለሙያዎች ወቅታዊ መረጃዎችን ለህዝብ ለማድረስ በማለም ያቋቋሙት ዲጂታል ሚድያ ነው።
Download Telegram
#ዜናመሠረት ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም የታይም መፅሄት የአመቱ 100 ተፅእኖ ፈጣሪዎች ስብስብስ ውስጥ ተካተቱ

- በዘንድሮው ስብስብስ ውስጥ ዶናልድ ትረምፕ እና ኤሎን መስክ ተካተዋል

(መሠረት ሚድያ)- ዝነኛው እና ተፅእኖ ፈጣሪው ታይም መፅሄት በዘንድሮው የ '100 ተፅእኖ ፈጣሪዎች' ዝርዝር ውስጥ የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን ኢትዮጵያዊውን ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖምን አካተተ።

በዘንድሮው የታይም መፅሄት ዝርዝር ውስጥ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ፣ ባለሀብቱ ኤሎን መስክ እና የእንግሊዙ ጠ/ሚር ኬር ስታርመር መካተታቸው ታውቋል።

ዶ/ር ቴድሮስ በዚህ ዙርያ ማምሻውን የማህበራዊ ሚድያ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ሀሳብ "በዝርዝሩ ውስጥ መካተቴ በምሰራበት የአለም ጤና ድርጅት ውስጥ ለሚሰሩ ባልደረቦቼም እውቅና ነው" ያሉ ሲሆን በአለም ዙርያ በየቀኑ ግጭት ባሉባቸው ስፍራዎች ጭምር የጤና አገልግሎት ለማዳረስ የሚሰሩ ሰራተኞችን አስታውሰዋል።

በመፅሄቱ ላይ ስለ ዶ/ር ቴድሮስ ተጋባዥ ፀሀፊ በመሆን ያስነበቡት ዶ/ር ላሪ ብሪሊያንት የተባሉ የፈንጣጣ በሽታ ከአለማችን እንዲጠፋ ቁልፍ ሚና የተጫወቱ ሳይንቲስት መሆናቸውን መሠረት ሚድያ ተመልክቷል።

"ዶ/ር ቴድሮስ የአለም ጤና ድርጅት ሀላፊ ከሆኑ በኋላ የአለማችንን የጤና አገልግሎት ሽፋን ቀይረውታል፣ ይህ ደግሞ በበሳል አመራር እና ሳይንሳዊ በሆነ የውሳኔ አሰጣጥ የታገዘ ነበር። ዶ/ር ቴድሮስ ለአለም ጤና ስጦታ ናቸው" ያሉት ዶ/ር ላሪ በ194 ሀገራት የሚገኙ ሰዎችን ጤና የመጠበቅ ሀላፊነትን እየተወጡ የሚገኙ ብለዋቸዋል።

"አመራሩ መርህ ያለው ነው፣ ሀቀኛ ነው፣ ውጤት ተኮርም ነው። የአለማችን ህዝብ ከበፊት ግዜ በበለጠ ጤነኛ እንዲሆን አድርገዋል" በማለት ዶ/ር ላሪ ታይም መፅሄት ላይ አስነብበዋል።

በታይም መፅሄት መሪዎች (Leaders) ምድብ ከዚህ ቀደም ቀዳማዊ ሐይለ ሥላሴ እና ጠ/ሚር አብይ አህመድ ተካተው ነበር። ይሁንና 'የታይም የአመቱ ሰው (Time Person of the Year) የሚለውን ማዕረግ ግን ያገኙ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ቀዳማዊ ሐይለ ሥላሴ ሲሆኑ ግዜውም እ.አ.አ በ1936 ጃንዋሪ ወር ነበር።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia
#ዜናመሠረት "ስዩም ተሾመ ተሰውሮብኛል"- ፌደራል ፖሊስ

"ግለሰቡ በስም የሚታወቅ ስለሆነ ይሰወራል ብለን አናምንም፣ በቀጣይ  ተገዶ እንዲቀርብ"- ከፍተኛ ፍርድ ቤት

(መሠረት ሚድያ)- በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ የሽብር ወንጀል ምድብ ችሎት ጉዳያቸው እየታየ የሚገኘው  አቶ ዮሐንስ ቧያሌው እና አቶ ክርስቲያን ታደለ "ስዩም ተሾመ የተባለው ግለሰብ በሕግ ቁጥጥር ስር ሆነን ሳለ በማኅበራዊ ሚዲያ ስማችንን እያጠፋ ነው" በሚል ለችሎቱ አቤቱታ አቅርበው እንደነበር ቀደም ሲል መዘገባችን ይታወቃል።

ፍርድ ቤቱም በስም የተጠቀሰው ግለሰብ ችሎት ቀርቦ ጉዳዩን እንዲያስረዳ በፌዴራል ፖሊስ በኩል መጥሪያ ቢላክለትም ለሁለተኛ ጊዜ ስዩም ተሾመ ተሰውሮብኛል ሲል ዛሬ ምላሽ መስጠቱን መሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ ያሳያል።

አቶ ዮሐንስ ቧያለው በበኩላቸው "ከጂቡቲ ጎበዜ ሲሳይን አመጣሁ ብሎ የሚመፃደቀው የፌዴራል ፖሊስ ላፍቶ ሞል ቢሮ ከፍቶ በየቀኑ የፍርድ ቤት ዳኞችን ሲሳደብ የሚውልን ግለሰብ ተሰውሮብኛል ማለቱ አሳፋሪ ነው" ሲሉ ለችሎቱ አስረድተዋል ።

አቶ ዮሐንስ አክለውም "ይህንን ግለሰብ ቀደም ሲል በሌላ ችሎት በስም ማጥፋት ወንጀል ከስሼው ቅጣት የተጣለበት ቢሆንም እስካሁን ቅጣቱን የሚያስፈፅም የመንግስት አካል ባለመኖሩ ያንኑ የጥፋት ድርጊት ቀጥሎበታል" ሲሉ ተናግረዋል።

"የእኔን ስም በተደጋጋሚ ማጥፋቱ የተለመደ ቢሆንም አሁን ደግሞ የዚህን ችሎት ዳኞች ስም እያጠፋ እና በችሎቱ ላይ ግልፅ የሆነ ተፅዕኖ እየፈጠረ በመሆኑ ትክክለኛ ፍትሕ እናገኛለን ለማለት እንቸገራለን" ሲሉ አክለዋል።

አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው "ስዩም ተሾመ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ሚዲያ አማካሪ ሲሆን ፖሊስ ይህንን ሰው ማቅረብ ያልቻለው ስዩም አንደኛ ደረጃ ዜጋ ስለሆነ ነው። አንደኛ ደረጃ ዜጎች ከሕግ በላይ ሥለሆኑ  ፍርድ ቤት መቅረብ አይችሉም። ፍርድ ቤት ተገደው የሚቀርቡት ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዜጎች ብቻ ናቸው። ስዩም አማራ ቢሆን ኖሮ  ተገዶ ይቀርብ ነበር ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት አማራ ሶስተኛ ዜጋ ሆኗልና። ሁለት መቶ አማራዎችን ከወቅታዊ ጉዳይ ጋር በተገናኘ በሚል ጓዳ ጎድጓዳ ውስጥ ገብቶ በእስር ቤት እያጎረ ያለ ፖሊስ እና አቃቢ ሕግ ስዩም ተሾመን አዲስ አበባ ውስጥ ተሰውሯል ሲባል  ያሳፍራል" ሲሉ ነው ለችሎቱ ያስረዱት።

"ሞት በሚያስቀጣ አንቀፅ ተከሰን አቶ ስዩም የተባለው ግለሰብ ችሎቱን ከውጭ ሆኖ ተፅዕኖ የሚፈጥርበት ከሆነ ውጤቱ ከወዲሁ የሚታወቅ ነው" ብለዋል።

የሁለቱን አቤቱታ  ያደመጠው ችሎቱ "ስዩም የተባለው ግለሰብ በስም የሚታወቅ ስለሆነ ይሰወራል ብለን አናምንም። በቀጣይ  ግን ተገዶ እንዲቀርብ" ሲል ለሶስተኛ ጊዜ  ትዕዛዝ ሰጥቷል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia
#ዜናመሠረት "በሚቀጥለው ሳምንት በአክስዮን ሽያጩ ዙርያ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል"- ኢትዮ ቴሌኮም ለመሠረት ሚድያ

(መሠረት ሚድያ)- መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ኢትዮ ቴሌኮም በመጀመሪያ ዙር እያንዳንዳቸው 300 ብር ዋጋ ያላቸውን 100 ሚሊዮን መደበኛ አክሲዮኖች ከህዳር ወር ጀምሮ ማቅረቡ ይታወሳል።

ተቋሙ በሸጣቸው አክሲዮኖች ዙርያ ለህዝብ ተከታታይ መረጃ አለማድረሱ እና ቀጣይ መርሀ ግብሮች ተብለው በወቅቱ የተቀመጡት ቀናት በማለፋቸው በብዙዎች ዘንድ አግራሞትን እየፈጠረ ይገኛል፣ የመሠረት ሚድያ ተከታታዮችም በጉዳዩ ዙርያ ኢትዮ ቴሌኮምን እንድናናግር ተከታታይ ጥያቄ አቅርበዋል።

በዚህ ዙርያ በቅርቡ አስተያየታቸውን ያስነበቡት እውቁ የባንክ ባለሙያ አቶ ሙሼ ሰሙ ኢትዮ ቴሌኮም ከጃንዋሪ 31, 2025 ጀምሮ ተቀባይነት ያገኙ አክስዮን ገዢዎች እንደሚለይና ተቀባይነት ያላገኙ አክስዮን ገዢዎች ደግሞ እስከ ከኤፕሪል 14, 2025 ደረስ ገንዘባቸው መመለስ እንደሚጀምር መግለፁን አንስተዋል።

"እስከአሁን ድረስ ተቀባይነት ያገኙ አክስዮኖች አልተገለጹም... ቢያንስ ሕዝብን በማክበር ደረጃ የአክስዮን እውቅና መስጫ ጊዜው መራዘሙን አስመልክቶ አንድም ምክንያት አለመቅረቡ፣ መግለጫ አለመሰጠቱና ምንም እንዳልተፈጠረ በዝምታ ቀን መቆጠሩ የሚያስደምም ሆኖ አግኝቼዋለሁ" ያሉት አቶ ሙሼ "በጥቅሉ ገንዘባችሁን አግቼ፣ የአክስዮን እውቅና ሳልሰጥ፣ ወለድ ሳልከፍል፣ የጊዜ ሰሌዳውን ሳላሳውቃችሁ ገንዘባችሁ በግሽበት እየተመታ በፈለኩት ሁኔታና ጊዜ የገንዘባችሁን ቆይታ ማራዘም እችላለሁ ማለት ምን የሚሉት ውልና ከምን የመነጨ መብት እንደሆነ ግልጽ አይደለም" ብለዋል።

በዚህ ዙርያ መሠረት ሚድያ ኢትዮ ቴሌኮምን ያናገረ ሲሆን ተቋሙ ውጤቱን ለህዝብ የማሳወቁ ሂደት ግዜ መፍጀቱን አምኖ ይህም የተፈጠረው ሂደቱ ለተቋሙ የመጀመርያው ከመሆኑ ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅሷል።

"በቀጣይ ሂደት ዙርያ ከባለድርሻዎች ጋር ሰፋ ያለ ውይይት ማድረግ አስፈልጎ ነበር። በተጨማሪም አንዳንድ ዳታዎችን የማጥራት ስራ ላይ ትኩረት አርገን እየሰራን ነበር" በሚል ምላሹን ለሚድያችን የሰጠው ኢትዮ ቴሌኮም አሁንም ግልፅነት ያለው አሰራር ለመዘርጋት ፅኑ አቋም አለኝ ብሏል።

በሚቀጥለው ሳምንትም በዚህ ዙርያ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚኖር የገለፀው የቴሌኮም ኩባንያው በዚህ መግለጫ ላይ ስለ አክስዮን ሽያጩ እና ስለ ድልድል ውጤት ይፋ እንደሚደርግ አስታውቋል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia
#ዜናመሠረት ካርፉር ሱፐርማርኬትን ጨምሮ በርካታ የውጭ የግብይት ማዕከላት በኢትዮጵያ ስራ ሊጀምሩ እንደሆነ ተሰማ

- ድርጅቱ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ጠ/ሚር አብይ በቀጥታ ተቋሙን ሲያግባቡ ቆይተዋል

(መሠረት ሚድያ)- ግዙፉ የፈረንሳይ የሸቀጣ ሸቀጥ ግብይት ማእከል ካርፉር (Carrefour) ጨምሮ በርካታ ተመሳሳይ የውጭ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ስራ ለመጀመር እንደተስማሙ ታውቋል።

እንደ ኬንያ ባሉ ሀገራት ግዙፍ የሱፐርማርኬት ንግዶችን የሚያንቀሳቅሰው ካርፉር ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገባ ጠ/ሚር አብይ አህመድ የድርጅቱን ዋና ስራ አስፈፃሚ በቀጥታ ሲያነጋግሩ እና ሲያግባቡ እንደነበር መሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።

ካርፉር በሀገር ውስጥ ሊገኙ የማይችሉ እና በሀገር ውስጥ የሚገኙ ምርቶችን በስፋት እና በጥራት በማቅረብ የሚታወቅ ሲሆን በአለማችን ዙርያ በ40 ሀገራት ውስጥ 14,000 ሱፐርማርኬቶችን እንደሚያስተዳድር መረጃዎች ያሳያሉ።

"የካርፉር ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ለሌሎች ሱፐርማርኬቶችም ሆነ በሌላ ዝርፍ ላይ ላሉ ድርጅቶች መምጣት ምክንያት ይሆናል" ያሉን መረጃውን ለመሠረት ሚድያ ያጋሩ አንድ የመንግስት ሀላፊ በተለይ የመግዛት አቅማቸው ከፍ ያለ እና የውጭ ተቋማት ሰራተኞችን በከፍተኛ ደረጃ ይጠቅማል ብለዋል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia
#ዜናመሠረት የኢትዮጵያ ፖስታ ለትንሳኤ በዓል ከማናጀር በላይ ላሉ ሀላፊዎቹ ብቻ የሁለት ወር ደሞዝ ቦነስ መስጠቱ ታወቀ

(መሠረት ሚድያ)- የኢትዮጵያ ፖስታ (Ethio Post) በነገው እለት ለሚከበረው የትንሳኤ በዓል ከማናጀር በላይ ላሉ ሀላፊዎቹ ብቻ የሁለት ወር ደሞዝ ቦነስ መስጠቱን እየወጡ ያሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በርካታ የተቋሙ ሰራተኞች በትናንትናው እለት የሰሙት እና "እጅግ አሳዛኝ" ብለው የገለፁት ድርጊት የኑሮ ውድነት ተባብሶ ታች ያለው ሰራተኛ ሲቸገር ከፍ ያለ ደሞዝ ያላቸው ቦነስ ብለው ብር መከፋፈላቸው እንዳስቆጣቸው ገልፀዋል።

"ከጥበቃ ጀምሮ እስከ ሱፐርቫይዘር ድረስ ያለው ሰራተኛ በኑሮ ውድነት እየተጠበሰ፣ ደሞዝ ይጨመርልኛል ብሎ ሲያስብ ከማናጀር በላይ ላሉት ብቻ የ2 ወር ደሞዝ ቦነስ ተብሎ የተቋሙን ገንዘብ መቀራመታቸው አሳዝኖናል፣ እነሱ በቦነሱ ብቻ ከ80,000 እስከ 212,000 ሲከፋፈሉ ተራው ሰራተኛ ለበዓል ዶሮ መግዣ አጥቶ ይውላል" ብለው ለመሠረት ሚድያ የተናገሩት አንድ የተቋሙ ሰራተኛ ናቸው።

አሁን ላይ የኢትዮጵያ ፖስታ ከ2,200 በላይ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን የሰራተኞቹ ደሞዝ ከ4,000 ብር ጀምሮ እስከ 106,000 ብር እንደሚደርስ ለሚድያችን የደረሰ አንድ መረጃ ያሳያል።

አብዛኛው ሰራተኛ ጠቅላላ ደሞዙ ከ16,800 ብር በታች ሲሆን የሀላፊዎቹ ደግሞ ጥቅማ ጥቅም ሳይጨምር ማናጀር 40,300፣ ዳይሬክተር 56,400 ብር፣ ቺፍ ኦፊሰር 76,300 ብር እንዲሁም ዋና ስራ አስፈፃሚ 106,100 ብር እንደሚያገኙ ይህ መረጃችን ያሳያል።

"ከስራ አስኪያጅ ጀምሮ ለፋሲካ በዓል የሁለት ወር ጉርሻ ለራሳቸው ወስደው ሰራተኛውን የበዪ ተመልካች አድርገውታል" ያሉን ሌላ የድርጅቱ ሰራተኛ ከኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ ለሰራተኛው የተጨመረው ደመወዝ 10 ፐርሰንት እንደማይሞላ ጠቅሰዋል።

"ይህ በሆነበት ሁኔታ ነው እንግዲህ ለራሳቸው የሁለት ወር ደመወዝ ጉርሻ ተፈራርመው ለበዓላቸው የወሰዱት። እነሱ እየተዝናኑ ሰራተኛው ኑሮ አልገፋ ብሎት ሌት ተቀን እየታገለ ነው። ይህንን ጉድ የኢትዮጵያ ህዝብ ይስማው፣ ስሜ ሳይታይ አድርሱልን" ብለዋል።

በዚህ ዙርያ ከተቋሙ ምላሽ ከደረሰን ይዘን የምንመለስ ይሆናል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia
#ዜናመሠረት "እውነት ነው ለማኔጅመንት አባላት ቦነስ ከፍለናል። የተከፈለው የአንድ ወር ደመወዝ ብቻ ነው"- የኢትዮጵያ ፖስታ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ጋሻው መርሻ

- አቶ ጋሻው ለመሠረት ሚድያ ዘገባ ስድብ የተቀላቀለበት ምላሽ ሰጥተዋል

(መሠረት ሚድያ)- የኢትዮጵያ ፖስታ (Ethio Post) በነገው እለት ለሚከበረው የትንሳኤ በዓል ከማናጀር በላይ ላሉ ሀላፊዎቹ ብቻ የሁለት ወር ደሞዝ ቦነስ መስጠቱን መሠረት ሚድያ ማምሻውን መዘገቡ ይታወቃል።

በርካታ የተቋሙ ሰራተኞች በትናንትናው እለት የሰሙት እና "እጅግ አሳዛኝ" ብለው የገለፁት ድርጊት የኑሮ ውድነት ተባብሶ ታች ያለው ሰራተኛ ሲቸገር ከፍ ያለ ደሞዝ ያላቸው ቦነስ ብለው ብር መከፋፈላቸው እንዳስቆጣቸው ገልፀው ነበር።

ለዚህ ዜና በመሠረት ሚድያ የፌስቡክ ገፅ ላይ ስድብ የተቀላቀለበት ምላሽ ያስቀመጡት የኢትዮጵያ ፖስታ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ጋሻው መርሻ "እውነት ነው ለማኔጅመንት አባላት ቦነስ ከፍለናል። የተከፈለው የአንድ ወር ደመወዝ ብቻ ነው" ብለዋል።

መሠረት ሚድያ የተሰነዘረውን ስድብ ለማቅረብ ኤዲቶሪያ ፖሊሲው አይፈቅድም፣ ይሁንና አቶ ጋሻው ከስድብ ውጭ ያስቀመጡትን ፅሁፍ እንዲህ በቀጥታ ያቀርበዋል:

"እውነት ነው ለማኔጅመንት አባላት ቦነስ ከፍለናል። የተከፈለው የአንድ ወር ደመወዝ ብቻ ነው። ይኸው ቦነስ ለመላው ሰራተኛ በመስከረም ወር ተከፍሏል። ለማኔጅመንት አባላት እስካሁን ያልተከፈለው ከኦዲት ጋር በተያያዘ ብቻ ነበር። ኦዲቱ ሲጠናቀቅ አሁን ተከፈለ። ምንድን ነው ችግሩ?" ብለዋል።

"ከጥበቃ ጀምሮ እስከ ሱፐርቫይዘር ድረስ ያለው ሰራተኛ በኑሮ ውድነት እየተጠበሰ፣ ደሞዝ ይጨመርልኛል ብሎ ሲያስብ ከማናጀር በላይ ላሉት ብቻ የ2 ወር ደሞዝ ቦነስ ተብሎ የተቋሙን ገንዘብ መቀራመታቸው አሳዝኖናል፣ እነሱ በቦነሱ ብቻ ከ80,000 እስከ 212,000 ሲከፋፈሉ ተራው ሰራተኛ ለበዓል ዶሮ መግዣ አጥቶ ይውላል" ብለው ለመሠረት ሚድያ የተናገሩት አንድ የተቋሙ ሰራተኛ ናቸው።

አሁን ላይ የኢትዮጵያ ፖስታ ከ2,200 በላይ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን የሰራተኞቹ ደሞዝ ከ4,000 ብር ጀምሮ እስከ 106,000 ብር እንደሚደርስ ለሚድያችን የደረሰ አንድ መረጃ ያሳያል።

አብዛኛው ሰራተኛ ጠቅላላ ደሞዙ ከ16,800 ብር በታች ሲሆን የሀላፊዎቹ ደግሞ ጥቅማ ጥቅም ሳይጨምር ማናጀር 40,300፣ ዳይሬክተር 56,400 ብር፣ ቺፍ ኦፊሰር 76,300 ብር እንዲሁም ዋና ስራ አስፈፃሚ 106,100 ብር እንደሚያገኙ ይህ መረጃችን ያሳያል።

"ከስራ አስኪያጅ ጀምሮ ለፋሲካ በዓል የሁለት ወር ጉርሻ ለራሳቸው ወስደው ሰራተኛውን የበዪ ተመልካች አድርገውታል" ያሉን ሌላ የድርጅቱ ሰራተኛ ከኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ ለሰራተኛው የተጨመረው ደመወዝ 10 ፐርሰንት እንደማይሞላ ጠቅሰዋል።

"ይህ በሆነበት ሁኔታ ነው እንግዲህ ለራሳቸው የሁለት ወር ደመወዝ ጉርሻ ተፈራርመው ለበዓላቸው የወሰዱት። እነሱ እየተዝናኑ ሰራተኛው ኑሮ አልገፋ ብሎት ሌት ተቀን እየታገለ ነው። ይህንን ጉድ የኢትዮጵያ ህዝብ ይስማው፣ ስሜ ሳይታይ አድርሱልን" ብለዋል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia
ውድ የመሠረት ሚድያ ተከታታዮች፣

እንኳን ለትንሳኤ በዓል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ።

መልካም በዓል!

@MeseretMedia
#ዜናመሠረት መንግስት ከጀርመን የሚባረሩ 4 ሺህ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ለመቀበል ስምምነት ላይ መድረሱ ተሰማ

(መሠረት ሚድያ)- የጀርመን መንግስት በሀገሪቱ የሚገኙ ህገወጥ ስደተኞችን በግዴታ ማስወጣት መጀመሩን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት በጀርመን ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን መቀበል መጀመሩ ታውቋል።

መሠረት ሚድያ የተመለከተው አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶክመንት እንደሚያሳየው መንግስት ሊቀበላቸው የተዘጋጀውን መጀመርያዎቹን 110 ሰዎች ዝርዝር ለጀርመን መንግስት አሳውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አጣሪ ቡድን ባደረገው ፍተሻ ከእነዚህ 110 ሰዎች ውስጥ 87ቱ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ እንዳረጋገጠ፣ 21ዱ ኢትዮጵያውያን እንዳልሆኑ እንደተናገሩ እና 2ቱ ለመናገር ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ተጠቅሷል።

የመጀመሪያዎቹ 29 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ደግሞ በፍራንክፈርት አየር ማረፊያ በኩል በግዴታ የዛሬ ወር ገደማ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል።

"የኢትዮጵያ መንግስት ከአውሮፓ ሕብረት ተጥሎበት የነበረውን የቪዛ ገደብ፣ የእርዳታና ብድር ክልከላ ተከትሎ ችግር ውስጥ ገብቶ እንደነበር ይታወቃል። አሁን ስምምነት ላይ ተደርሷል፤ በስምምነቱም በአውሮፓ የሚገኙ ዜጎቹን መቀበል የሚል ነው" ያሉን ጉዳዩን የሚያውቁ አንድ የመረጃ ምንጫችን ናቸው።

ከጀርመን ብቻ ከአራት ሺ በላይ ኢትዮጵያውያንን ለመቀበል ከጀርመን መንግስት ጋር ስምምነት ላይ እንደተደረሰ የጠቆሙት ምንጫችን በሚቀጥሉት ቀናት ተጭነው ወደ ሀገር ቤት ሊላኩ የተዘጋጁ 24 ኢትዮጵያውያን እንዳሉም ጠቁመዋል።

አንዳንድ ሀገራት ከአውሮፓ እና ከሰሜን አሜሪካ ተገደው እየተባረሩ ያሉ ዜጎቻቸውን እንደማቀበሉ እያሳወቁ ሲገኝ አንዳንድ ሀገራት ደግሞ መቀበል ጀምረዋል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia
#ዜናመሠረት "ለድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቤቱታ ለማቅረብ ብንሞክርም ቢሯቸው ማግኘት አልቻልንም"- የከተማው የልማት ተነሺዎች

(መሠረት ሚድያ)- የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የልማት ተነሺ ፋይሎችን በማዘግየቱ እንዳሳሰባቸው የገለፁ ነዋሪዎች የፋይሎቹ ባለቤቶችና ህጋዊ ወኪሎች ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

ለድሬዳዋ ከንቲባ ቅሬታቸውን ለማቅረብ ቢሞክሩም ፈጽሞ እንደማይቻል እና የከንቲባው የአገልግሎት ቀን በግልጽ እንደማይታወቅም ጭምር ለመሠረት ሚድያ አስረድተዋል።

"የድሬዳዋ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሲያስተናግዳቸው የነበረውን የልማት ተነሺ ፋይሎች ለሁለት ዓመታት በማገድ የአስተዳደሩ የካቢኔ አባላት ቤተሰቦች እና ዘመዶች ግን እየተስተናገዱ ነው" በማለት ተናግረዋል።

"ህጋዊ ወኪል እና የፋይሉ ባለቤቶች ሲጠይቁ ግን ታግዷል ይባላሉ፣ ከንቲባው ነው ያገደው ምንም ማድረግ አንችልም እያሉ መልስ ይሰጣሉ" ብለው ለሚድያችን ቃላቸውን የሰጡ እነዚህ በርከት ያሉ ነዋሪዎች አብዛኛው የልማት ተነሺ፣ ህጋዊ የፋይሉ ባለቤቶችና ወኪሎች አቤቱታ የሚያቀርቡበት ቦታ አጥተው እየተንከራተቱ እንዳሉ ተናግረዋል።

"ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር አቤቱታ ለማቅረብ ብንሞክርም በተደጋጋሚ ፈጽሞ ማግኘት እንደማይቻልና በግልጽ የተቀመጠ የአገልግሎት ቀን ከንቲባው እንደሌለው ተነግሮናል" ብለው ለመሠረት ሚድያ የተናገሩት ነዋሪዎች ከንቲባው ባጋጣሚ ቢሮ ቢገኙ እና ለማናገር ቢሞክሩ እንኳን የድሬዳዋ ከተማ አድማ በታኝ ፖሊሶች ተገልጋዮችን እየደበደቡ እንደሚመልሱ ጠቁመዋል።

"ከንቲባውን ሊያገኙ የሚችሉት ሰዎች ጥቂት ባለሀብቶች እና የገጽታ ግንባታ ላይ ያሉ የሶሻል ሚዲያና የሚዲያ ሰዎች ብቻ ናቸው" ብለዋል። 

በርካታ መፈታት ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ የሚጠቅሱት ነዋሪዎቹ የልማት ተነሺዎች የምትክ መሬት ጉዳይ አስቸኳይ መፍትሄ እንደሚፈልግ እንዲሁም በአጠቃላይ የድሬዳዋ ህብረተሰብ የተለያዩ ቅሬታውን ማቅረብ ስላልቻለ የከንቲባው የአገልግሎት ቀን በግልጽ ማወቅ እንፈልጋለን በማለት ተናግረዋል።

በዚህ ዙርያ ከንቲባ ከድርን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፣ ምላሽ ከሰጡን ይዘን እንመለሳለን።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia
#የህዝብአስተያየት አቅመቢስ ሸማች ባለበት ሀገር  የኢኮኖሚ እድገትም ሆነ የፖለቲካ መረጋጋትም አይታሠብም

በአቶ አባ ጅሜ ለመሠረት ሚድያ የተፃፈ

(መሠረት ሚድያ)- በሀገራችን ከምርጫ 97 በኋላ መንግስት በተከታታይ ባለ ሁለት አኀዝ የኢኮኖሚ አድገት እንዳስመዘገበ ጆሯችን እስኪሠለች ሲነዛብን ነበር። አሁን ያለው መንግስትም ከባለሁለት አኀዝ ትንሽ ዝቅ ቢልም በእድገት አየር ላይ በብርሀን ፍጥነት እየበረረ ስለመሆኑ ብዙ ተብሏል።

ነገር ግን የነገሩ አልተገናኝቶም የሚገለጠው የሀገሪቱን ህዝብ ኑሮ ስናይ ነው። የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት የመጨረሻ መዳረሻው የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል ነው። ዜጎች መሠረታዊ ፍላጎታቸው ተሟልቶላቸው የተሻለ የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድ፣ የመብራት፣ የስልክ ወዘተ ተደራሽነት ተስፋፍቶ ማየት፣ ቀልጣፋ እና ፈጣን አገልግሎትን ማሟላት ነው። 

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ስናየው ነገርዮው የተገላቢጦሽ ነው። የዜጎች ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ነው። ኢኮኖሚው አደገ በሚባለው ልክ የዜጎች ኑሮ እየተሻሻለ ከመሄድ ይልቅ ኑሮው ቀንበር እየሆነ የመጣበት፣ መካከለኛ የኢኮኖሚ ክፍል ተብሎ የሚመደበው የሀገሪቱ ሲቪል ሰርቫንት እንኳ የወር ደመወዙ የቤት ኪራይ መሸፈን የማይችል የሆነበት፣ ዜጎች አይደለም መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት በቀን አንዴ መመገብ ወደማይችሉበት ደረጃ የወረዱበትና አንዳንድ የማህበረሰብ ክፍሎች "ይበሉት ያጡ ለመለመን ያፈሩ" የሚባሉበት ደረጃ ላይ የደረሱ ናቸው።

በአጠቃላይ ሸማቹ ማህበረሰብ በኢኮኖሚ አቅመቢስ የሚባልበት ደረጃ ላይ የደረሰበት ሀገር ሆናለች። እርግጥ ነው በአፍሪካ የሸማቾች አቅምና የኑሮ ሁኔታ በመሪዎች የሚገመገመው ከአለው የኢኮኖሚ ጥቅምና ጉዳት አንጻር ሳይሆን ከፖለቲካዊ ውጤቱ አንጻር ነው። በኢኮኖሚ የዳበረ፣ መሠረታዊ ፍላጎቱ የተሟላለት እና የተሻለ የመግዛት አቅም ያለው ዜጋ ቀጥሎ የነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትህ እና የመሳሰሉ የዲሞክራሲ ጥያቄ ይዞ መነሳቱ አይቀርም።

ስለዚህ የአፍሪካ መሪዎች የስልጣናቸውን ጊዜ ለማራዘም እና ሊነሡ የሚችሉ የፍትሀዊነት፣ እኩልነት እና ነጻነት ጥያቄዎችን ለማዳፈን ያላቸው አማራጭ ዜጎች ሁልጊዜ የዳቦ ጥያቄ ላይ እንዲወሰኑ ማድረግ ነው።

ነገር ግን አቅመቢስ ሸማች ባለበት ሀገር የኢኮኖሚ እድገት የማይታሠብ ነው። አቅም ያለው ሸማች በሌለበት ሀገር ምርታማነት ሊኖር አይችልም። የምርታማነት እድገት የሚጣው የፍላጎት መጠን ሲጨምር ነው። ፍላጎት የሚጨምረው ደግሞ የህዝብ ቁጥር ሲጨምር፣ አዳዲስ ወጣቶች የስራ እድል ሲፈጠርላቸው እና በዋናነት የሸማቹ የመግዛት አቅም ሲጎለብት ነው።

ይሄ ሲሆን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ  ይነቃቃል፣ ኢንቨስትመንት ይስፋፋል፣ እንዲሁም መንግስት ከአምራቹና ሠራተኛው የሚሠበስበው ገቢ ይጨምራል። በተለይ የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ ሀገራችን የሚመጣው ገበያ፣ ጥሬ ሀብት እና የሰው ኃይል ፍለጋ ነው። ስለዚህ የአገሪቱን ህዝብ የመግዛት አቅም ባላሣደግንበት ሁኔታ የውጭ ኢንቨስተር ወደኛ ሊመጣ አይችልም።

ስለዚህ ሊዘገይ ይችላል እንጅ የኢኮኖሚ ቀውስ እየጨመረ ሲሄድና ኑሮው ጣራ ሲነካ ችግሩ የፖለቲካ መሆኑ አይቀርም። "ከርሀብ ጦር ይሻላል" የሚል ትውልድ መነሳቱ አይቀርም።

ለምሳሌ ለሁለተኛው የአለም ጦርነት መነሻ ከሆኑት ችግሮች አንዱ ታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ (The Great Economic Depression) የሚባለው ነው። በወቅቱ ለነውጠኛ ፋሽስቶችና ናዚዎች ወደ ስልጣን መምጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ከአስር አመት በፊት የነበረው የኢኮኖሚ ቀውስ ታላላቆቹን እነ አሜሪካን ሳይቀር እንዴት እንዳመሠ የምናውቀው ነው። 

እኛ ዘጠና ዘጠኞች ነን (we are 99s) የሚለውን መፈክር እናስታውሳለን። ዜጎች በልተው ማደር ካልቻሉ ወደ ትግል መግባታቸው አይቀርም።

በሀገራችን ያለው አሁናዊ የፖለቲካ ቀውስም በከፊል የኢኮኖሚያዊ ችግሩ ውጤት ነው። ትጥቅ አንስተው የሚታገሉ አካላት ቢያንስ የሰው ኃይል ግብአታቸው ኢኮኖሚው የፈጠረው ስራ አጥ ወጣት ነው። ተምሮ መቀጠር ያልቻለ ወጣት፣ በተቀጠረበት ስራ ራሱንም ቤተሠቡንም ማስተዳደር ያልቻለ አካል ነፍጥ አንስቶ መታገልን አማራጭ አድርጎታል።

ይሄ ደግሞ ነገሮችን  ከድጡ ወደ ማጡ ያደርጋቸዋል። ያለውን ውስን ሀብት ለጦር መሳሪያ ግዥ እየዋለ ነው፤ መሠረተ ልማት እየወደመ ነው፤ አምራቹና ወጣቱ ኃይል የጥይት ሲሳይ ሆኗል፤ ሰላም የሚፈልገው ንግድና ኢንቨስትመንት ደግሞ በእንቅርት ላይ ጀሮ ገድፍ ሆኖበታል።

የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት የህዝቡን ኑሮ የበለጠ አናግቶታል። አለማት የኢኮኖሚ ቀውስን የሚፈቱት የሸማቹን አቅም ማጠናከር (empowering consumers) በሚሉት መንገድና አዳዲስ የስራ እድል በመፍጠር ነው። አንዳንዶች የመንግስት ለሠራተኛው የተሻለ ደሞዝ መክፈል የመንግስትን ወጪ የሚጨምረው ብቻ ይመስላቸዋል። ነገር ግን ይሄ የመንግስትን ገቢ ያሳድገዋል።

ነጋዴ ወጪው በጨመረ ቁጥር እና ኢንቨስትመንቱን ባሳደገ ቁጥር ገቢው ይጨምራል። መንግስትም እንደዚያው ነው። በአንድ መልኩ ከሠራተኛው የሚሠበስበው ግብር ይጨምራል። በሌላ መልኩ የሸማቾች የመግዛት አቅም እየጨመረ በመጣ ጊዜ ፍላጎት እያደገ አቅርቦት እያነሰ ይሄዳል። ይሄ ደግሞ ምርታማነት አንዲያድግ፣ አዳዲስ ኢንቨስተሮች ወደ ኢኮኖሚው እንዲቀላቀሉ እና አዳዲስ የስራ እድል እንዲፈጠር ያደርጋል።

በዚህ ሁሉ መሀል አትራፊው መንግስት ነው። ከአዲሡ ኢንቨስተርና ተቀጣሪ እንዲሁም እያደገ ከመጣው ምርታማነት የሚሠበስበው ግብር እያደገ ይመጣል።  የሸማቾች የመግዝት አቅም ሲያድግ የነጋዴው ትርፋማነት ያድጋል፣ ነገዴው በትርፉ ኢንቨስትመንቱን ያስፋፋል ወይም አዲስ ኢንቨስትመንት ላይ ይሳተፋል፣ ይሄ ደግሞ አዳዲስ የስራ እድል ይፈጥራል።

ከእነዚህ ሁሉ ደግሞ መንግስት ተጨማሪ ገቢ ይሰበስባል። ተያይዘን እናድጋለን ማለት ነው። 

ስለዚህ መንግስት ሆይ፣ አቅመቢስ ሸማች በአለበት ሀገር የኢኮኖሚ እድገትም ሆነ የፖለቲካ መረጋጋት አይታሠብም። ስለዚህ የሸማቹን የመግዛት አቅም በማሳደግ የኑሮ ቀንበሩን ማላላት ላይ ብታተኩር። ይሄ ደገሞ የሀገሪቱን ኢኮኖሚም ፖለቲካም ይታደጋል። አለበለዚያ ግን ተያይዘን እንወድቃለን።

* አቶ አባ ጅሜ በአሁኑ ሰዓት በሀገሪቱ ካሉ በአንዱ ዩኒቨርስቲ መምህር ሲሆኑ በቅርቡ የዶክትሬት ትምህርታቸውን አጠናቀው ተመርቀዋል።

@MeseretMedia
#የህዝብአስተያየት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ የመጣው ትምህርት የማግኘት ሰብአዊ መብት በኢትዮጵያ

በቶፊቅ ተማም ለመሠረት ሚድያ

(መሠረት ሚድያ)- በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ የቀጠሉት ግጭቶች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ዘርፈ ብዙ ጉዳት እያስከተሉ እንደሚገኙ ይታወቃል።

በተለይ በሀገሪቱ ባለው ግጭት ሳቢያ የማይተካው ውድ የሰው ህይወት ማለፉ በዋነኛነት ሲጠቀስ ከዚህ ባለፈ ሀገሪቱ ባልጠነከረ ኢኮኖሚ ላይ እንደመገኘቷ 'እንኳንም ዘንቦብሽ' እንዲሉ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ እንዲሳነው ብሎም የኋሊት እንዲጓዝ እያደረገ ሲገኝ ከዚህ ባለፈ በሌሎች የአገልግሎት ሰጪ የመንግስትም ሆነ የግል የትምህርት፤ የጤና፤ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ተቋማት እንዲሁም በርካታ መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ እና እጅግ አስከፊ ውድመት ከማድረሱ ባለፈ በቢሊየን የሚቆጠር ንብረት ለውድመት ተዳርጓል፣ ከፍተኛ ሰብአዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት አድርሷል።

ለመንደርደር ያህል ይህን ካልኩ ወደ ዋናው ጉዳይ ስገባ በሀገሪቱ ባሉ ግጭቶች ሳቢያ እጅጉን የተጎዳው እና ለቀውስ የተዳረገው የትምህርት ዘርፍ ሲሆን ይህም በአለም ላይ ከተከሰቱ የትምህርት ቀውሶች ቀዳሚው ሳያደርገው እንደማይቀር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ድርጅት /UNOCHA/ ያወጣው መረጃ ይገልጻል ፡፡

ሁለት አመት የፈጀው እና አሁን የረገበው የሰሜኑ ጦርነት ብቻ ከ2.3 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጪ ሲያደርግ በመላው ሀገሪቱ  ደግሞ 8,500 ገደማ ትምህርት ቤቶች ወድመዋል፣ 1,500 በላይ የሚሆኑት በሰሜን ኢትዮጵያ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል።

ከሰሜኑ ጦርነት በኋላም ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ እፎይታ ያላገኘው ክልል የአማራ ክልል ሲሆን በዚሁ ክልል እንደ ሌሎች ተጎጂ የህብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ ተማሪዎች እንዲሁም የትምህርት ዘርፉ ክፉኛ ተጎድቷል። በአማራ ክልል በ2017 ዓ/ም የትምህርት ዘመን ይመዘገባሉ ተብሎ ከታቀደው 7 ሚሊየን ተማሪዎች እስከ አሁን የተመዘገበው 1.5 ሚሊየን ተማሪዎች ብቻ ናቸው፣ ይህም ከእቅዱ 21 በመቶ ብቻ ሲሆኑ ትምህርት የጀመሩ እና ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሚማሩ ተማሪዎችም በግጭት ቀጠና ውስጥ ሆነው ለመማር ተገደዋል።

በዚሁ በአማራ ክልል አምና ዝግ የነበሩ ትምህርት ቤቶች ዘንድሮም አልተከፈቱም፣ ክልሉ ባጋጠመው የፀጥታ ችግር ሳቢያ አምና ከ 2.6 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ሳይማሩ ቀርተዋል። 

ይብዛም ይነስ በመላው ሀገሪቱ ያሉ ክልሎች በግጭት እና የሰላም እጦት በሚፈተኑባት ኢትዮጵያ ትምህርት የማግኘት ሰብአዊ መብትን በተመለከተ አፈጻፀሙን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባጠናው ጥናት መሰረት ከታች በሰንጠረዡ እንደሚታየው በሀገሪቱ ከአምስት ሺህ አምስት መቶ በላይ ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ ከነዚህ ውስጥ ከ 75 በመቶ በላይ የሚገኙት በአማራ ክልል ነው ፡፡

እንደ ትምህርት ሚኒስቴር መረጃ በ2015 ዓ/ም የትምህርት ዘመን 29.3 ሚሊየን ተማሪዎች ለመመዝገብ ቢታሰብም የተመዘገቡት 16.3 ሚሊየን ተማሪዎች ብቻ ናቸው፣ ይህም በርካታ ሚሊየን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መራቃቸውን ያሳያል።

አሁንም ቢሆን በተለይ በአማራ ክልል ትምህርት ለመጀመር አስቻይ ሁኔታዎች የሌሉበት ሁኔታ ሲገኝ የአስተዳደር ቢሮዎች ወድመዋል፣ የትምህርት እና የፋይናንስ ሰነድ ተቃጥሏል፣ ኮምፒውተር እና የላብራቶሪ እቃዎች ተዘርፈዋል።

ከዚህም ባለፈ የትምህርቱን ዘርፍ ለማገዝ የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ  ያልሆኑ ድርጅቶች የደህንነት ዋስትና ባለማግኘታቸው ሳቢያ ወደ ክልሉ መግባት ያልቻሉ ሲሆን በተለይ መምህራን፤ ር/መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች ስራቸውን ለመከወን ዋስትና ማግኘት አልቻሉም ፡፡

እነዚህ ከትምህርት ገበታ ውጪ ለመሆን የተገደዱ ተማሪዎች በተለይ ሴቶች ወደ ያለ እድሜ ጋብቻ ሲገቡ ሌሎቹ ታዳጊዎች ህፃናት በየሰፈሩ እና አልባሌ ቦታዎች ለመዋል ሲገደዱ ከትምህርት ገበታ የራቁ ተማሪዎችም ለረጅም ጊዜ ከትምርት ቤት በመራቃቸው ሳቢያ በአእምሮአቸው እድገት በትምህርት አቀባበል በትምህርት ስነ ልቦና የቀድሞ ትምህርት ትውስታቸው ላይ ጫና እንደሚፈጥር የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ ፡፡

በሀገሪቱ ከፍ ያለ ያለ አቻ ጋብቻ አለ ተብሎ የሚታመንበት የአማራ ክልል በተለይ በትምህርት መቋረጥ ሳቢያ ያለ እድሜ ገብቻ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል።

የአፍሪካ ህፃናት መብት ደህንነት ቻርተር አንቀፅ 21(2) ያለ እድሜ ጋብቻ የሚባለው ተጋቢዎች ሴት አሊያም ወንድ ወይም ሁለቱም ከአስራ ስምንት አመት በታች ሲሆኑ ነው። በዚህ ያለ እድሜ በሚፈፀሙ ጋብቻ በህይወት የመኖር መብት፤ ትዳር ጓደኛ የመያዝ መብት፤ የመማር መብት፤ በጤና የመኖር መብት በተለይ ካለ እድሜ ጋብቻ ጋር ተያይዞ በሚከሰት በዋነኛነት በወሊድ ጊዜ ረጅም ምጥ፤ ከፍተኛ ደም መፍሰስ እና ሌሎች የስነ ተዋልዶ በሽታዎች መጋለጥ እንዲሁም ከጎጂ ልማድ የመጠበቅ መብታቸውን ያጣሉ ፡፡

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ አንቀፅ 26/2 እና የኢኮኖሚ ማበራዊ እና የባህል መብቶች አለም አቀፍ ቃል ኪዳን አንቀፅ 13 ስር በግልፅ እንደተደነገገው የትምህርት አላማ የሰው ልጅን የተሟላ እድገት ለማራመድ እና የሰብአዊ መብቶችንና መሰረተዊ ነጻነቶችን ለማክበር የሚደረገውን ጥረት ማጠናከር ነው።

ከዚህ አንፃር ትምህርት የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ማለትም አካላዊ፣ አእምሮአዊ እና ስነ ልቦናዊ እድገት የማምጣት አላማ ያለው ቢሆንም ይህንን ሰብአዊ መብት በኢትዮጵያ በአግባቡ መተግበር አልተቻለም ፡፡

ከዚሁ የትምህርት ማግኘት መብት ትግበራ ጋር በተያያዘ ሌሎች ተጎጂ የሚሆኑት የትምህርት ማህበረሰብ አካላት በተለይ መምህራን ሲሆኑ እንደ ማህበረሰብ የሚሰጣቸው ቦታ አናሳ ሆኖ አመቺ ያልሆነ የስራ ሁኔታ አለመኖር፤ የአስተዳደር ችግር፣ የተከታታይ የሙያ ማጎልመሻ /Continuous Professional Development /እድል አናሳ መሆን፤ አነስተኛ ክፍያ እና ጥቅማጥቅም፤ የትምህርት መሰረተ ልማት ባልተሟላበት ሁኔታ ማስተማር እና ሌሎች ተግዳሮቶች ተቋቁመው ለማስተማር ራሳቸውን ቢያዘጋጁም  ወደ ስራቸው መመለስ አልቻሉም፣ ይህም መምህራን ለተለያየ ኢኮኖሚያዊ ፤ማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ጫና እየዳረጋቸው ይገኛል ፡፡

ጥራት ያለው ትምህርት የማግኘት መብት ከቅድመ አንደኛ አስከ መካከለኛ ደረጃ ነፃ ቢሆንም አሁን ባለው ነበራዊ ሁኔታ በወርሀ መስከረም አንጻራዊ በሆነ መልኩ  በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች ከተማ አስተዳደሮች በሁሉም እርከን የሚገኙ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ይገኛሉ ፡፡

የዜጎች ሰብአዊ መብት የሆነው ትምህርት የማግኘት መብት አክብሮ ከመተግበር ባለፈ የተሻለ የትምህርት አቀባበል ይኖራቸው ዘንድ በማሰብ ከትምህርት ቁሳቁስ ባለፈ ምገባ የጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሚገኙ አንድ ሺ 106 ት/ቤቶች ለሚማሩ ለስምንት መቶ ሺኅ ተማሪዎች ቁርስና ምሳ እያቀረቡ ሲገኝ ለዚህም ከ 8 ቢሊየን ብር በላይ  በጀት የመደበ ሲሆን ከዚህ ባለፈ 12.6 ሚሊየን ተማሪዎች መዝግቦ ወደ ትምህርት ያስገባው ኦሮሚያ ክልል ነው።
አምና 5.6 ሚሊየን ተማሪዎች መመገብ የቻለ ሲሆን ለዘንድሮ 10 ሚሊየን ተማሪዎች በተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም / School Feeding Program / ለማካተት አቅዷል ከምገባ ባለፈ የትምህርት ቁሳቁስ በተለይ ደብተር እንዲሁም የትምህርት ቤት ደንብ ልብስ በማቅረብ ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው ፡፡

አሁን ሀገሪቱ ባለችበት ጉራማይሌ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ አብዛኛው የሀገሪቱ ተማሪዎች በተለይ ከቅድመ አንደኛ አስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ ትምህርት ቢጀምሩም ሌሎች  ግን በፀጥታና ሰላም እጦት ሳቢያ ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል ይህም ሀገሪቱ በተለይ በትምህርት ተደራሽነት ረገድ ባለፉት አስርት አመታት ያሳየችውን እመርታ ወደ ኋላ የሚጎትት ሆኗል ፡፡

ለማጠቃለል ያህል በሀገሪቱ በሰላም እጦት ሳቢያ ከትምህርት ገበታ ውጪ ስለሆኑ ተማሪዎች ብዙ የተባለ ሊባል የሚችል ቢሆንም በተለይ የዘንድሮ የትምህርት ዘመን አካባቢያችሁ ሰላም ሆኖ በትምህርት ገበታችሁ ላይ መገኘት የቻላችሁ ተማሪዎች መምህራን እና ሌሎች የትምህርት አካላት መልካም የትምህርት ዘመን እየተመኙሁ እንደ እድል ሆኖ በትምህርት ገበታ መገኘት እየፈለጉ ያላገኙ በሚሊየን የሚቆጠሩ ጓደኞቻችሁ እንዳሉ ተገንዝባችሁ እንደ ሀገር ያገኛችሁትን ትምህርት የማግኘት ሰብአዊ መብት በአግባቡ ልትጠቀሙበት የሚገባ ሲሆን የእውቁ ከያኒ አለማየሁ እሸቴን
‹‹ተማር ልጄ ተማር ልጄ  ወገን ዘመድ የለኝ ሀብት የለኝም ከእጄ፣
ስማኝ ልጄ ሌት ፀሀይ ነው ላልተማረ ሰው ግን ቀኑ ጨለማ ነው ››
የሚለውን ዘመን አይሽሬ ሙዚቃ አዚመው ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ገበታ ለመሸኘት ቢፈልጉም ይህን ማድረግ ያልቻሉ በሚሊየን የሚቆጠሩ ወላጆች ይገኛሉ።

በአንፃሩ ልጆቻቸው በትምህርት ገበታ ላይ ያሉላችሁ ወላጆች እንዲሁም መምህራንና የትምህርት ማህበረሰብ አቅም የፈቀደውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ የተሻለ ዜጋ ይሆኑ ዘንድ ብዙ መስራት ይጠበቃል።

በመንግስት በኩል በግጭት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን ማቋቋም፤ ትምህርት ቤቶች በቋሚነት እስኪከፈቱ ድረስ ጊዜያዊ የመማርያ አማራጮችን ማዘጋጀት ፤ህፃናት እና መምህራን ጨምሮ የትምህርት ማህበረሰቡ አባላት የስነ ልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ የሚያጉኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት እና ሌሎች መሰል ተግባራትን መከወን ከመንግስት ሲጠበቅ ሀገር ሰላም ሆና ከትምህርት ገበታ የተፈናቀሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው የሚመለሱበትን ጊዜ ፈጣሪ እንዲያመጣ እየለመንን በያዝነው አዲስ አመት በትምህርት ገበታ ላይ ላላችሁ ሁሉ  መልካም የትምህርት ዘመን እየተመኘሁ በዚህ ላብቃ ፡፡

ቶፊቅ ተማም
                                              
@MeseretMedia
#ዜናመሠረት ለ650 ሺህ ኢትዮጵያውያን ሲደርስ የነበረ የምግብ እርዳታ ሊቆም መሆኑ ተሰማ

(መሠረት ሚድያ)- የአለም ምግብ ፕሮግራም (World Food Programme) 10 ሚልዮን ኢትዮጵያውያን ርሀብ እና የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ችግር አጋጥሟቸው እንደሚኝ ገልፆ ይህ እየሆነ ባለበት ወቅት በገንዘብ እጥረት ምክንያት ለ650 ሺህ ኢትዮጵያውያን ሲያደርስ የነበረውን የምግብ እርዳታ ሊያቆም መሆኑን ዛሬ አስታውቋል።

ከእነዚህ መሀል 3 ሚልዮን የሚሆኑት በጦርነት እና በከባቢ አየር ጠባይ መቀየር ምክንያት ተሰደው የሚገኙ መሆናቸውን የጠቆመው ይህ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካል የሆነ ተቋም 4.4 ሚልዮን የሚሆኑ እርጉዝ እና አጥቢ እናቶች እንዲሁም ህፃናት በከፍተኛ ደረጃ ለረሀብ ተጋልጠው ይገኛሉ ብሏል።

"በኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ትግራይ እና አፋር የህፃናት በምግብ እጥረት መዳከም ተከስቷል" ያለው የአለም ምግብ ድርጅት በኢትዮጵያ እና በቀጠናው ባሉ ሀገራት ያሉ ግጭቶች ችግሩን እያባባሱ እንደሚገኙ ይፋ አድርጓል።

ይህም አልበቃ ብሎ በመጪዎቺ ወራት በደቡብ-ምስራቅ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የዝናብ መጠን የተተነበየ ሲሆን ይህም በሶማሌ ክልል ድርቅ እንዳያስከትል እንደተፈራ ጨምሮ ገልጿል።

በአማራ ክልል የቀጠለው ግጭት፣ የእርዳታ እህል የጫኑ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚፈፀም ዝርፊያ መሬት ላይ ያሉ ችግሮች ተብለው በዛሬው መግለጫ ላይ የተነሱ ሲሆን የአለም አቀፍ እርዳታ መቀነስ በዋናነት ተጠቅሷል።

"አዲስ እርዳታ ካልተገኘ በቀር ለ3.6 ሚልዮን ኢትዮጵያውያን የምናቀርበውን እርዳታ በመጪዎቹ ሳምንታት ለማቋረጥ እንገደዳለን፣ አሁን ላይ ለ650 ሺህ ሰዎች ስናደርስ የነበረውን የነፍስ አድን እርዳታ እያቆምን ነው" ብሏል በመግለጫው።

ይህ አሳሳቢ ክስተት እንደ ቢቢሲ እና አልጀዚራ ባሉ አለም አቀፍ የሚድያ ተቋማት ሽፋን ቢያገኝም አንድም የመንግስት ሚድያ እስካሁን እንዳልዘገበው መሠረት ሚድያ ተመልክቷል፣ በመንግስት አካላትም የተሰጠ መግለጫ የለም።

ኢትዮጵያ ስንዴ ከራሷ ተርፎ ለውጭ ሀገራት መላክ እንደጀመረች ተደጋግሞ ቢገለፅም በርካታ ሚልዮን ዜጎች ርሀብ አጋጥሟቸው እንደሚገኙ የአለም አቀፍ ተቋማት መረጃዎች ያሳያሉ።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia
#ዜናመሠረት ኬንያ ዘንድሮ የምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት እንደምትሆን አይ ኤም ኤፍ ጠቆመ

(መሠረት ሚድያ)- በያዝነው የፈረንጆቹ 2025 ዓ/ም የኬንያ ኢኮኖሚ ከኢትዮጵያ እንደሚበልጥ አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (International Monetary Fund- IMF) ያወጣው የአመቱ የኢኮኖሚ እድገት ትንተና ያሳያል።

ኢትዮጵያ ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ በምስራቅ አፍሪካ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ሆና የነበረ ቢሆንም በቅርቡ በመንግስት ይፋ የሆነው እና በእነ IMF የተደገፈው ብርን የማዳከም ሂደት የኢኮኖሚውን የጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት እና አገልግሎት ዋጋ (GDP) በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ማድረጉ ታውቋል።

በዚህም መሰረት የኬንያ GDP 132 ቢልዮን ዶላር ሲሆን በብር መዳከም ምክንያት በብዛት ከአምናው የቀነሰው የኢትዮጵያ GDP ደግሞ 117 ቢልዮን ዶላር እንደሚሆን IMF እንደተነበየ መሠረት ሚድያ ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ የመገበያያ ገንዘቧን በማዳከሟ ብር ከ55 ፐርሰንት በላይ ዋጋውን እንዳጣ የሚታወስ ሲሆን ሀገሪቱ ይህን በማድረጓ ከ IMF 3.4 ቢልዮን ዶላር ገደማ ብድር እንደተፈቀደላት በወቅቱ ተነግሮ ነበር።

የብር ዋጋ መዳከም በተጨማሪም ሀገሪቱ ከውጭ አበዳሪዎች ጋር ያለባትን 28.9 ቢልዮን ዶላር ብድር ለማስተካከል እንዳገዘ ብሉምበርግ ዘግቧል።

የብር መዳከም የ GDP መቀነስ ብቻ ሳይሆን በተለይ ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማስከተሉ ይታወቃል።

በተቃራኒው የኬንያ መንግስት በርካታ የውጭ ብድር ያለበት ቢሆንም የሀገሪቱ መገበያያ ሽልንግ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር በ21 ፐርሰንት መጠንከሩ ታውቋል፣ የኢኮኖሚው መረጋጋት እና በርካታ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ዘርፎች መኖራቸውም ለኢኮኖሚው መጠንከር አስተዋፅኦ ማርረጋቸው ተጠቅሷል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia
#ዜናመሠረት በምሥራቅ ጎጃም በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸው ታወቀ

(መሠረት ሚድያ)- በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ሐሙስ ሚያዝያ 9/2017 ዓ.ም. በትምህርት ቤት ዙሪያ በደረሰ የድሮን ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።

በዞኑ እናርጅ እናውጋ ወረዳ ገደብ በተባለች አነስተኛ የገጠር ከተማ የትምህርት ቤት አጥር ለማጠር እና ቤት ለመሥራት 'ለልማት ሥራ' የወጡ "ሰላማዊ ሰዎች" በጥቃቱ መገደላቸውን ገልፀዋል።

የአካባቢው አስተዳደር ግን ጥቃቱ በአካባቢው ተሰብስበው በነበሩ የፋኖ ታጣቂዎች ላይ እንጂ በንፁሃን ነዋሪዎች ላይ አለመፈጸሙን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት ክትትል እያደረገ መሆኑን አመልክቷል። ነዋሪዎች እንደተናገሩት "ተሰብስበው" በከተማዋ ያለው ገደብ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አጥርን እያጠሩ በነበሩ የሰዎች ላይ ነው ጥቃቱ የተፈፀመው።
ጥቃቱ በተፈፀመበት አካባቢ በቅርብ ርቀት ላይ እንደነበሩ የተናገሩ ሌላ የዓይን እማኝ ወዲያው ጩኸት፣ ግርግር እና ድንጋጤ መፈጠሩን ጠቁመው "የሆነውን አናውቀውም" ሲሉ በቅፅበቱ የነበረውን ሁኔታ ገልፀዋል። እሳቸውን ጨምሮ ሥራ ላይ የነበሩ ሰዎች ጥቃቱ ወደተፈፀመበት አካባቢ ሲጠጉ "ሰው የሚባል አይለይም" ሲሉ ስለ ጉዳቱ ተናግረዋል።

"እንዳለ በሙሉ ጥቁር ነገር ነው የሆነው። አካባቢው በሙሉ ሰው የሚባል ነገር የለም። ከወደቀው ውስጥ የሚጮህ አለ፤ የሚንከባለል አለ። የተፈጠረው ነገር ይዘገንናል። ሰው ለሆነ እጅግ የሚዘገንን ድርጊት ነው" ብለዋል።

የፈረሰውን የትምህርት ቤቱን አጥር እያጠሩ እያለ ቀኝ እጃቸውን ተመትተው መቁሰላቸውን የተናገሩ ሌላ ነዋሪ "ከባድ ፍንዳታ" መከሰቱን ጠቅሰው "ብዙ ሰው ነው የተጎዳው" ብለዋል።

"ባሕር ዛፍ የሚቆርጥ፤ ሚስማር የሚመታ አለ፤ ማገር የሚቆርጥ አለ፤ የሚይዝ አለ" ሲሉ ማኅበረሰቡ መሰባሰቡን የገለፁ ሌላ የዓይን እማኝ የሟቾቹን ቁጥር "ብዛት ይኖረዋል" በማለት ገልፀዋል። አስከሬን ስለማንሳታቸው የተናገሩ ሌላ እማኝ ደግሞ አብዛኛው የጥቃቱ ተጎጂዎች ወዲያው ሕይወታቸው ማለፉን ገልፀው፤ ሟቾቹ በአብዛኛው ወጣቶች ናቸው ብለዋል።

ከ24 በላይ ቁስለኞችንም ወደ ሕክምና መወሰዳቸውን የገለፁት እማኞች፤ አብዛኞቹ በከተማዋ ወደሚገኘው ገደብ ጤና ጣቢያ ከደረሱ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።

ከ70 በላይ አስከሬን አንስተው በባጃጅ ወደ ቤተ ክርስቲያን ማመላለሳቸውን የተናገሩ አንድ የዓይን እማኝ፤ ታዳጊዎችን እና ሽማግሌዎችን ጨምሮ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 120 እንደሚደርስ ገልፀዋል። "ከ115 እስከ 120 የሚሆን አስከሬን ነው የተቀበረው። ያልታወቀም ይኖራል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ድንጋጤ ውስጥ ስለነበርን" ብለዋል።

ሌላ የዓይን እማኝ በበኩላቸው 57 አስከሬን እስከሚነሳ ድረስ እንደነበሩ ጠቁመው የሟቾቹ ቁጥር ከ100 በላይ እንደሚሆን ገምተዋል። አስከሬኖቹ ላይ ከባድ ጉዳት በመድረሱ ሟቾችን መለየት ከባድ እንደነበር የተናገሩት እማኞች በዚህ ምክንያት እና በስጋት እስከ ቀትር 08፡00 ድረስ ገደብ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በጅምላ እንደተቀበሩ ገልፀዋል።

"አሞራ እንዳይበላቸው ቅበሩ ሲባል ማኅበረሰቡ በፍጥነት አምስት የሚሆን መቃብር ውስጥ ነው የቀበራቸው" ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

የመንግሥት ኃይሎች ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ተከትሎ ስጋት ያደረባቸው አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች መሸሸታቸውን የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ ተጨማሪ ጥቃቶች መፈፀማቸውንም ጠቁመዋል።

ማኅበረሰቡ ከተረጋጋ በኋላ ለሟቾቹ ድንኳን እንደተጣለ እና ከቀናት በኋላ በአካባቢው "ፍራጅ" የሚባለው ማስተዛዘኛ መርሃ ግብር እንደተደረገም ነዋሪዎች ተናግረዋል። "ሰሞኑን ሲሸበር ነበር። ሕዝቡ በሙሉ ሽብር ላይ ነው ያለው" ሲሉ ዳግም የድሮን ጥቃት ይደርሳል በሚል የፋሲካ በዓልን በስጋት ማሳለፋቸውን "በዓል የሚባል ነገር የለም" ብለዋል።

"ከባድ ሐዘን ውስጥ ነው ያለው። በዓል ምንም አይመስልም ነበር። ለበዓል ከከተማ የሚመጡ ልጆች አልመጡም" ሲሉ አካባቢው በሐዘን ድባብ ውስጥ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ግጭት በ2015 ዓ.ም. መጨረሻ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ከተማዋ በፋኖ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር እንደሆነች ነዋሪዎች ተናግረዋል። ጥቃቱ ሲፈፀም ግን የፋኖ ታጣቂዎች ከተማዋ ውስጥ እንዳልነበሩ እና በአካባቢው ግጭት እንዳልነበረ ጠቁመዋል።

ታጣቂዎቹ "አንዳንድ ሥራ ለመሥራት ካልመጡ በቀር ከተማው ውስጥ አይታዩም" ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።
ነጋዴ እንደሆኑ የተናገሩ አንድ የዓይን እማኝ ሟቾቹ ንፁሃን ስለመሆናቸው ሲናገሩ "በርካቶቹን በንግድ ሥራቸው" የሚያውቋቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

"የፋኖ አባላት ቢሆኑ [አስከሬን ሲነሳ] ታጣቂ እናገኝ ነበር። ፋኖዎችን እና ማኅበረሰቡን [ለይተን] እናውቃቸዋለን። [ፋኖዎች] በአንድ ላይ ነው የሚንቀሳቀሱት" ሲሉ ሌላ ነዋሪ ተናግረዋል።

ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው "የተሰበሰው አጥር የሚያጥረው እና ቤት የሚሠራው ሰው በቀረፃው [የድሮን ቅኝት] የፋኖ ስብስብ ነው ተብሎ ታስቦ ይሁን ያወቅነው ነገር የለም። ምንአልባት ሲሰበሰብ ፋኖ ነው ተብሎ ታስቦ [ይሆናል] እንደዚያ ነው እኛ የተረዳነው" ሲሉ ጥቃት ሊፈጸም የቻለበትን ምክንያት ግምታቸውን ገልፀዋል።

የእናርጅ እናውጋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሙሉ ጌቴ ንፁሃን ሰዎች ተገደሉ መባሉን "የጠላት ወሬ" ያሉ ሲሆን፤ እርምጃው "ፅንፈኛ" ያሏቸው የፋኖ ታጣቂዎች ላይ መወሰዱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"እዚህ አካባቢ ቁጥሩ በርከት ያለ የኃይል ስብስብ አለ። ሰብስበው ሥልጠና ጭምር [እንደሚሰጡ] መረጃው አለኝ። የትምህርት ቤት አጥር፤ ቤት ሥራ የሚባለው ነገር ማሳመሪያ ነው . . ." በማለት ንፁሃን በፍንጣሪም ቢሆን አልተገደሉም ሲሉ አስተባብለዋል።

የፋኖ ታጣቂዎች በበኩላቸው በወረዳው በስፋት እንደሚንቀሳቀሱ ጠቁመው ገደብ ከተማ አካባቢ ላይ ግን በወቅቱ "ምንም ዓይነት የታጠቀ ኃይል" አልነበረም በማለት በጥቃቱ የተገደለ አባል እንደሌላቸው ተናግረዋል።

አካባቢውን ለሥልጠና እንደማይጠቀሙት የተናገሩት የአማራ ፋኖ በጎጃም ምክትል ሰብሳቢ አቶ አስረስ ማረ ዳምጤ "ሁሉም ግድያው የተፈፀመባቸው ሲቪሊያን ናቸው። አንድም የታጠቀ ኃይል በቦታው ላይ አልነበረም" በማለት ግድያውን ማኅበረሰቡን ከማሸበር ጋር አያይዘውታል።

ምንጭ: ቢቢሲ አማርኛ

@MeseretMedia
#ዜናመሠረት የህክምና ባለሙያዎችን ድምፅ ያስተጋቡ አንድ ዶክተር ከድሬዳዋ ከተማ ተሰናብተው ገጠር ሄደው እንዲሰሩ ተወሰነባቸው

- የድሬዳዋ ጤና ባለሞያዎች ድርጊቱን ተቃውመው ፊርማ ማሰባሰብ ጀምረዋል

(መሠረት ሚድያ)- በድሬዳዋ ከተማ በሚገኘው ሳቢያን አጠቃላይ ሆስፒታል ሰራተኛ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት እና ከሰሞኑ የጤና ባለሙያዎች ያሰሙትን ድምፅ ያስተጋቡ አንድ ጠቅላላ ሐኪም የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸው ገጠር ሄደው እንዲሰሩ እንደተወሰነባቸው ታወቀ።

መሠረት ሚድያ የተመለከተው እና ሚያዝያ 9/2017 ዓ/ም በድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ፅጌረዳ ክፍሌ የተፃፈው ደብዳቤ ዶ/ር ሀብታሙ አለሙ የተባሉት እኚህ የጤና ባለሙያ 'የሙያ ስነምግባርን የተፃረረ ድርጊት' መፈፀማቸውን ጠቅሶ ጉዳዩ ባለመታረሙ አሁን ከሚሰሩበት የድሬዳዋው ሳቢያን ሆስፒታል ወደ ለገኦዳ ጉዱንፈታ ጤና ጣብያ እንዲዛወሩ መደረጋቸውን ይገልፃል።

"የዛሬ ወር ገደማ ቋሚ ቅጥር ከሳቢያን ሆስፒታል ጋር ፈፅሜያለሁ። ይህ ሆኖ እያለ ከሰሞኑ እኛ የኢትዮጵያ የጤና ተቋማት ሰራተኞች ድምፅ እያሰማን መሆኑን ተከትሎ እኔም አንዳንድ ፅሁፎችን ስላወጣሁ ኢላማ ተደርጌያለሁ" ያሉት ዶ/ር ሀብታሙ ውሳኔው ከመተላለፉ በፊት ባሉት ቀናት ስልክ እየተደወለ በጤና ባለሙያዎች እንቅስቃሴ ዙርያ አስተያየት እንዳይሰጡ ማስፈራርያ ሲደርሳቸው እንደነበር ጠቅሰዋል።

"እኔ በበኩሌ ጉዳዩ የመኖር እና አለመኖር መሆኑን ጠቅሼ እንደማላቆም ነገሬያቸዋለሁ። የከተማው ጤና ቢሮ ሀላፊ የሆኑትን ዶ/ር ፅጌረዳን ለማናገር ብሞክርም ያልተገባ ነገር ተናግረውኝ ስልክ ዘግተውብኛል" የሚሉት የጤና ባለሙያው ከዚያም እኚህ ሀላፊ ዶ/ር ሀብታሙ ወደሚሰሩበት ሆስፒታል በመደወል ከስራቸው እንዲታገዱ ማድረጋቸውን መስማታቸውን ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።

ዶ/ር ሀብታሙ በቅርቡ 'Hakim' የተባለ የፌስቡክ ገፅ ላይ በርካቶች የተመለከቱት አንድ ፅሁፍ አጋርተው የነበረ ሲሆን እሱም "ስራዬ አድካሚ ቢሆንም፣ ደሞዜ ከ10,000ብር  በታች ቢሆንም፣ የአእምሮ እርካታ ይሰጠኛል። ሆኖም... እርካታ ቤት ኪራይ አይከፍልም። እርካታ በቀን 3 ጊዜ መብላት አያስችልም። እርካታ ልጆቼን ለማስተማር አያስችልም። እርካታ ልብስ እና ጫማ ለመቀየር አያስችልም። እርካታ ትዳር መመስረት አያስችልም። እርካታ ለታክሲ ወረፋ ከመጠበቅ አያድንም። ጥያቄያችን ለሁሉም ግልፅ የሆነ ነው። የሚገባንን እንኳን ባይሆን የሚያስፈልገን ይደረግልን። ትኩረት ለጤና ባለሞያዎች!" የሚል ነበር።

ዶ/ር ሀብታሙ ለመሠረት ሚድያ በሰጡት ቃል ተወልደው ባደጉበት የድሬዳዋ ከተማ እስካሁን እየሰሩ እንዲቆዩ የፈለጉበት ምክንያት በፅኑ ህመም አጋጥሟቸው የእለት ተእለት ክትትል የሚያስፈገልጋቸው የቤተሰብ አባል ስላላቸው በመሆኑ እና እሳቸውም ብቸኛ አስታማሚ መሆናቸውን አስረድተው ይህን የሚያሳይ የድል ጮራ ሆስፒታል ዶክመንት ለሚድያችን አሳይተዋል።

በተላለፈው የቅጣት ውሳኔ ላይ ለድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ቅሬታ እያስገቡ የሚገኙት የድሬዳዋ ጤና ባለሞያዎች ፊርማ ማሰባሰብ ጀምረዋል።

"የሞያ አጋራችን የሆኑት ዶ/ር ሀብታሙ አለሙ በሞያቸው የተመሰገኑ፣ ትሁት፣ ስራቸውን የሚወዱ እና ሀላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡ፣ በታካሚ እና በስራቸው ጉዳይ የማይደራደሩ ከዛም አልፎ ከስራቸው ውጪ በበርካታ የበጎ አድራጎት ስራዎቻቸው የሚታወቁ ከተማችን ወደፊት ከሳቸው ብዙ  ምትጠብቅባቸው ወጣት ሀኪም ናቸው" ያሉት የድሬዳዋ ጤና ባለሞያዎች ስማቸውን ከማይገናኝ ነገር ጋር በማያያዝ፤ በማጠልሸት እና የሌላቸውን ስብዕና በመስጠት አግባብ ያልሆነ የውሸት ክስ በመደርደር በድሬዳዋ ከተማ ጤና ቢሮ የተሰጠውን ውሳኔ ኮንነዋል።

"የተሰነዘረባቸው ከእውነት የራቀ የሀሰት ክስ ትክክል እንዳልሆነ እኛ በቅርበት አብረናቸው የምንሰራ እና የምናውቃቸው የጤና ባለሞያዎች እና የሞያ አጋሮቻቸው በቂ ምስክሮች ነን" በማለት የቀረበበት ክስ እውነት እንኳ ቢሆን ቀድሞ ክስ ሊያቀርብበት እና የስነምግባር ግድፈት ተገኝቶበታል ብሎ ውሳኔ ማስተላለፍ የሚችለው እየሰራ የሚገኝበት ሆስፒታል እንጂ ባለሞያውን በቅርበት የማያውቀው አካል አይደለም ብለዋል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia
#የህዝብአስተያየት "የፓስፖርት ቀጠሮ ጉዳይ እንኳን ሊያሻሻል ዘረፋው ዘምኖ ተጧጡፎ ቀጥሏል"

አቡ አብዱራህማን ለመሠረት ሚድያ

(መሠረት ሚድያ)- እኔ ዛሬ የማነሳው ሀሳብ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከፓስፖርት ጋር ተያይዞ በህዝብ ላይ እየፈፀመ ስለቆየውና አሁንም አሻሽያለሁ እያለ በሪፖርት እየለፈፈ ነገር ግን እንኳን ሊያሻሻል ዘረፋው ዘምኖ ተጧጡፎ ስለመቀጠሉ ነው።

አሁን ላይ ለፓስፖርት ቀጠሮ በኦላይን ፕላትፎርም አዘጋጅቶ ማህበረሰቡ ባለበት ቦታ በስልክ ወይም ኮምፒውተር ቀጠሮ ማስያዝና ለባዮሜትሪክ መረጃ ለመስጠት በቀጠሮ ቀን መቅረብ ብቻ እንዳለበት የታወቀና ሲሰራበት ነበር።

ይሁን እንጂ አስቸኳይ ፓስፖርት በ2 ቀን 25,000 ብር እና የ5 ቀን 20,000 ብር እንደሆነ እየታወቀ ሲስተሙን ማህበረሰቡ እንዳይጠቀም በመዝጋት ቀጠሮ ሊያስቀጥር ቢሮ ሲሄድ "እዚህ አይቀጠርም፣ ውጪ ሂድና አስቀጥረህ በቀጠሮ ቀን ለአሻራ ብቻ ና" ይባላል።

ውጪ በራሱ እንዳያስቀጥር ሲስተሙን ሎክ አድርገውታል፣ ውጪ እኛ እናስቀጥራለን የሚሉ ሰዎች አዘጋጅተው በእነሱ አማካኝነት የ2 ቀን 25,000 ብር የነበረውን እስከ 35,000 ብር፣ የ5ቀን 20,000 ብር የነበረውን እስከ 30,000 ብር ተቀብለው እነዛ ደላሎች ውስጥ ኢሚግሬሽን ለሚሰሩት መረጃ ልከው እንዲቀጥሩ ይደረጋል።

አሁን ያለው አሰራር ይህ ነው። ህዝቡ ተሰቃየ፣ ለማረጋገጥ ማንም በተቋሙ ፕላትፎርም ገብቶ 'Urgent Appointment' ቀጠሮ ደጋግሞ መሞከር ይችላል።

እነሱ ቢሮ ውስጥ ግን በገለፅኩት መልኩ ተመሳጥረው ይሰራሉ፣ የውሸት ሪፖርትና ዜና በየተቋማቱ መስማት ሰለቸን።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia
#ዜናመሠረት ተከሳሹ ወጣት በአቃቤ ህጉ በደረሰበት ድብደባ የጀርባ አጥንቱ መሰበሩን ገልፆ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲላክ ተማፀነ 

- ፍርድ ቤት ተከሳሹ ዛሬውኑ ወደ ቂሊንጦ የእስረኞች ማቆያ እንዲላክ እና ህክምና እንዲያገኝ አዟል 

(መሠረት ሚድያ)- ታሪኩ ተፈራ የተባለ የ24 ዓመት ወጣት በአዲስ አበባ ከተማ ከግብረ-አበሮቹ ጋር በመሆን የሽብር ወንጀል ሊፈፅም ሲል በቁጥጥር ስር መዋሉን ክሱ ያስረዳል።

ይሁን እንጂ ተጠርጣሪው በዛሬው ዕለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ የሽብር ወንጀል ችሎት ቀርቦ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው "ለምርመራ በሚል ፖሊስ ለዓቃቢ ሕግ አሳልፎ በመስጠት ከአራት ወራት በላይ ናትናኤል ስንታየሁ በተባለ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ቢሮ ውስጥ ተዘግቶብኝ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ሲፈፀምብኝ ነው የቆየው" ሲል ዛሬ ለችሎቱ አስረድቷል።

ታሪኩ አክሎም "አሰቃቂ ድርጊት ሲፈፅምብኝ የነበረውም እዚህ በግራ በኩል የቆመው ዓቃቢ ሕግ ናትናኤል ስንታየሁ ነው። በድብደባ ብዛት የጀርባ አጥንቴ ተሰብሯል፣ እንደምትመለከቱኝ ሰው ካልደገፈኝ መቆም አልችልም፣ ሽንቴን እንኳ መቆጣጠር አቅቶኝ ሰውነቴ ተበላሽቷል። እባካችሁ ከእገታ አስለቅቁኝ። ምርመራው አልቆ ክስ መስርቶብኛል። ከዚህ በኋላ ለምንድን ነው በቢሮው የሚያስቀምጠኝ። ዛሬውኑ ወደ ማረሚያ ቤት ላኩኝና ከሰው ጋር ልቀላቀል" ሲል ተናግሯል።

ችሎቱ በበኩሉ ግብረ አበሮቹ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩት ክስ ተመስርቶባቸው ቂሊንጦ የእስረኞች  ማቆያ ሲወርዱ ለምን ታሪኩ ተፈራን ነጥለው እንዳስቀሩት እና ሌሎቹ ተከሳሾች ከአራት ጊዜ በላይ በዚህ ችሎት ሲቀርቡ ለምን እሱን አላቀረባችሁትም የሚል ጥያቄ ያነሳ ቢሆንም "የጀርባ አጥንቱ ስለተጎዳ ሕክምና ለመውሰድ ነው ያቆየነው" ሲሉ ዓቃቢ ሕጉ አቶ ናትናኤል ስንታየሁ መመለሳቸውን የመሠረት ሚድያ ምንጮች ጠቁመዋል።

ፍርድ ቤቱም ታሪኩ ተፈራ ዛሬውኑ ወደ ቂሊንጦ የእስረኞች ማቆያ እንዲሄድ እና አስፈላጊውን ሕክምና እንዲያገኝ ሲል ለማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

መረጃን ከመሠረት!

@MeseretMedia