ቃለ ጽድቅ ዘመካነ ሕይወት | የመ/ሕ/ሰ/ት/ቤት ሰሌዳ መጽሔት ንዑስ ክፍል
1.02K subscribers
2.78K photos
44 videos
102 files
781 links
ይኽ በፈረንሳይ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን መካነ ሕይወት ሰ/ት/ቤት መንፈሳዊ ጽሑፎችና መልእክቶች የሚለቀቁበት ሚዲያ ነው።
https://linktr.ee/kaletsidkizm
Download Telegram
በዚህ የጥምቀት በዓል የምንማራቸውና የምንረዳቸው ቁም ነገሮች፦
💧 #ኢየሱስ_ክርስቶስ_ለምን_ተጠመቀ?
እርሱ ጸጋን የሚሰጥ እንጂ የሚቀበል ባለመሆኑ በመጠመቁ የሚያገኘው ጸጋ የለም፤ ስለሆነም የተጠመቀበት ምክንያት፦
ሀ. #ለእኛ_አርዓያ_ለመሆን፦ እርሱን አብነት አድርገን እኛ እንድንጠመቅና በጸጋ የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን ነው፡፡
ለ. #ለቀድሶተ_ማያት፦ የምንጠመቅበትን ውኃ ለመባረክና ለመቀደስ ነው፡፡
ሐ. #የሥላሴን_አንድነትና_ሦስትነት_ለማስረዳት፦ እርሱ በተጠመቀ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀምጧል፤ አብም በደመና ሆኖ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው›› ብሎ መስክሮአልና ምሥጢረ ሥላሴ በኋላ በተረዳ ነገር ተገልጧል፤ ‹‹ሰማያት ተከፈቱ›› ተብሎ የተነገረውም ይህን የሥላሴ ምሥጢር የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስን መገለጥ ለማስረዳት ነው፡፡

💧ለምን በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ?
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎች ብዙ ወንዞች እያሉ የዮርዳኖስን ወንዝ የመረጠበት ምክንት የተነገረው ትንቢትና የተመሰለው ምሳሌ እንዲፈጸም ነው፡፡
#ትንቢቱ፦ ‹‹ባሕር አየች፤ ሸሸችም፤ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ››፤ (መዝ 113÷3) ተብሎ የተነገረው ነው፡፡
#ምሳሌው፦ የዮርዳኖስ ወንዝ ምንጩ አንድ ሲሆን ዝቅ ብሎ በደሴት ይከፈላል፤ ከዚያም በወደብ ይገናኛል፡፡ የዮርዳኖስ ወንዝ ምንጩ አንድ እንደሆነ የሰው ሁሉ ዘር መገኛም አንድ አዳም ነው፡፡ ዝቅ ብሎ በደሴት እንዲከፈል እስራኤል በግዝረት አሕዛብ በቁልፈት (ባለመገረዝ) ተለያይተዋል፡፡ ከታች ወርዶ በወደብ እንዲገናኝ ሕዝብና አሕዛብም በክርስቶስ አምነው ተጠምቀው አንድ ሆነዋል፡፡ እስራኤልም ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ምድረ ርስት ገብተዋል፤ (ኢያ 3÷17)፡፡ ኤልያስም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ ብሔረ ሕያዋን ገብቷል፤ (2ነገ 2÷8)፡፡ ንዕማንም በዚሁ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቆ ከለምጹ ድኖአል፤ (2ነገ 5÷14)፡፡ የዚህ ሁሉ ምሳሌ ማጠቃለያም ዲያብሎስ በአዳምና በሔዋን ላይ የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ ስቃይ አጸናባቸው፤ ከዚያም ስመ ግብርናቸውን (የእርሱ ባሪያ) መሆናቸውን ‹‹ጽፋችሁ ብትሰጡኝ ስቃዩን አቀልላችሁ ነበር›› አላቸው፤ እነርሱም ጽፈው ሰጡት፤ (ይሁንብን አሉ)፡፡ እርሱም ያንን የሰጡትን የዕዳ ደብዳቤ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል ጥሎት ነበርና በዮርዳኖስ የጣለውን ጌታችን ሲጠመቅ እንደ ሰውነቱ ረግጦ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶላቸዋል፤ በሲኦል የጣለውንም በዕለተ ዓርብ በአካለ ነፍስ ወርዶ አጥፍቶላቸዋልና በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበት ምክንያት ይህ ነው፡፡

💧ለምን በውኃ ተጠመቀ?
ለጥምቀት ውኃን የመረጠበት ምክንያት ትንቢቱ እንዲፈጸም ነው፤ አስቀድሞ በነቢዩ ሕዝቅኤል ‹‹ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ፤ እናንተም ትጠራላችሁ››፤ (ሕዝ 36÷25) ተብሎ ተነግሮ ነበርና ያ የትንቢት ቃል እንዲፈጸም ነው፡፡ ሌላው ምክንያት ውኃ የተሰጠው ለሁሉም ነው፤ ጻድቁም ኃጥኡም፣ ትንሹም ትልቁም፣ ድኃውም ሀብታሙም እኩል ያገኘዋል፡፡ ጥምቀትም የተሰራው ለሁሉ ነው፤ ውኃ ከሥጋዊ እድፍ ያነፃል ጥምቀትም ከነፍስ እድፍ ከኃጢአት ያነፃል፡፡

💧ለምን ወደ ዮሐንስ ሔዶ ተጠመቀ?
የእርሱ መንገድ ጠራጊ ሆኖ የተላከውን ቅዱስ ዮሐንስን መጥተህ አጥምቀኝ ማለት ሲችል ወደ እርሱ ሔዶ የተጠመቀበት ምክንያት ትሕትና ለማስተማር እና ሥርዓት ለመሥራት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ መምህረ ትሕትና ነውና ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔዳችሁ ከአባቶች ካህናት ዘንድ ተጠመቁ በማለት ትሕትናንም ሥርዓትንም ለማስተማር ነው፡፡

💧ለምን በሠላሳ ዘመኑ ተጠመቀ?
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲጠመቅና ማስተማር ሲጀምር ዕድሜው ሠላሳ እንደነበር ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ መዝግቦት እናገኘዋለን፤ (ሉቃ 3÷23)፡፡ ስለዚህ በሠላሳ ዘመኑ የተጠመቀበት ምክንያት፦
ሀ. በብሉይ ኪዳን ሥርዓት መሠረት ለቤተ እግዚአብሔር ተልዕኮና አገልግሎት የሚመረጡ ካህናት ሠላሳ ዓመት ሲሞላቸው፣ በዕድሜና በእውቀት የበሰሉ ሲሆኑና ተልዕኮአቸውን ለመወጣት የበቁ ሲሆኑ ስለነበር ያንን ሥርዓት ለመፈጸም ነው፡፡
ለ. የሰው ሁሉ መጀመሪያ አዳም የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ በዐርባኛው ቀን ተሰጥቶት የነበረውን የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን ጸጋ ትእዛዘ እግዚአብሔርን በማፍረሱ አጥቶት ነበርና ያንን የልጅነት ጸጋ ለመመለስ ነው፡፡

💧የበዓሉ አከባበር በኢትዮጵያ
በሀገራችን ኢትዮጵያ ይህ ታላቅ በዓል በየዓመቱ በሚከበርበት ጊዜ ዋዜማው ማለትም ጥር 10 ቀን ‹‹ከተራ›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ‹‹ከተራ›› የሚለው ቃል ከተረ፣ ከበበ ከሚለው የግእዝ ግሥ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም የተከተረ፣ የተከበበ ወይም የተገደበ ማለት ነው፡፡ ይህም ለበዓለ ጥምቀቱ ማክበሪያ የሚሆን ምንጭ ወይም ወንዝ በሚገኝበት ቦታ የሚገደበውን ወይም የሚከተረውን ውኃ የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ በዚህም ዕለት የቃል ኪዳኑ ታቦት ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ተነስተው በሊቃውንት፣ በካህናት፣ በመዘምራንና በምእመናን ታጅበው ባሕረ ጥምቀቱ ወደ ተዘጋጀበት ስፍራ ሔደው ያርፋሉ፤ ይህም የሚሆነው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መሔዱን ለማሰብ ነው፡፡ ከዚያም የቃል ኪዳኑ ታቦታት ከአደሩበት ቦታ ስብሐተ እግዚአብሔር ሲደርስ ያድርና በማግስቱ ጥር 11 ቀን ጠዋት ባሕረ ጥምቀቱ ጸበል ከተረጨ በኋላ የቃል ኪዳኑ ታቦታት ከቦታው ተነስተው በዝማሬ በምስጋና ታጅበው ወደየመጡበት ቤተ ክርስቲያን በክብር ይመለሳሉ፡፡ ከበዓለ ጥምቀቱ በረከት እንድንሳተፍ አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን፡፡ አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
ምንጭ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ፣ ስንክሳር ዘጥር 11
   •════•💧🕊💧•════•

   •════•💧💧💧•════•