ቃለ ጽድቅ ዘመካነ ሕይወት | የመ/ሕ/ሰ/ት/ቤት ሰሌዳ መጽሔት ንዑስ ክፍል
1.02K subscribers
2.74K photos
44 videos
102 files
768 links
ይኽ በፈረንሳይ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተክርስቲያን መካነ ሕይወት ሰ/ት/ቤት መንፈሳዊ ጽሑፎችና መልእክቶች የሚለቀቁበት ሚዲያ ነው።
https://linktr.ee/kaletsidkizm
Download Telegram
#እንደ_ወሮቻችን_ኑ_በእርሷ_እንጀምር
(ዲ/ን ሕሊና በለጠ)

የወር መጀመሪያ የእርሷ ልደት ነው። ወሮቻችን ኹሉ በእርሷ ልደት ጀምረው በመጨረሻው የብሉይ ኪዳን ነቢይና የሐዲስ ኪዳን መንገድ ጠራጊ በመጥምቁ ዮሐንስ ያበቃሉ። እርሱ የብሉይን ማለፍና የሐዲስን መምጣት በማብሰር መንገድ እንደ ጠረገ ፣ የብሉይ ምሳሌ የኾነውን የአሮጌውን ዓመት ማለፍና የሐዲስ ምሳሌ የሚሆነውን የአዲሱን ዓመት መምጣት ያበሥር ዘንድ መስከረም አንድ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲባል ኾነ። ልክ እንዲሁ ደግሞ የአሮጌው ወር መጨረሻ ላይ ወርኀዊው መታሰቢያው በመሆኑ በእርሱ ትምህርት ላይ ቆመው፣ እርሱ መንገድ ጠርጎላቸው ሐዲስን እንዳዩት የብሉይ ኪዳን ሰዎች፣ እኛም በእርሱ መታሰቢያ በዓል ላይ (በ30) ላይ ቆመን ሐዲስ ወርን እናያለን። እነርሱ በእርሱ ትምህርት ጸንተው የአሮጌውን ኪዳን መጨረሻነት ተረድተው የሐዲስ ኪዳንን ሐዲስ ሕይወት "1" ብለው እንደ ጀመሩ፣ እኛም 30 ላይ ቆመን የአሮጌው ወር ብልየታችንን መጨረሻነት ተረድተን የአዲሱን ወር ሐዲስ ሕይወት "1" ብለን እንጀምራለን። "1" ደግሞ ልደታ ለእግዝእትነ ነው - የኹሉ ነገር ጅማሬ የኾነችው የእመቤታችን ልደት።

ወሮቻችን ኹሉ በእርሷ ልደት ስለሚጀምሩ ቀና ናቸው። ወሩን እርሷን አክብሮ፣ ዘክሮ ስሟን ጠርቶ የሚጀምር ሰው መንገዱ የቀና ነው። በእርሷ ጀምሮ ያፈረ የለም።

የአዳም የመዳን ተስፋ "እምወለተ ወለትከ" በሚለው እርሷን በሚያነሣው ቃል ኪዳን ተጀምሮ ፍጻሜው ያማረ ሆነ። ኖሕ ከጥፋት ውኃ መዳኑን ለእርሷ ምሳሌ በሚሆን መርከቡ ጀምሮ አላፈረም። ሙሴ እስራኤልን ከፈርዖን የማዳን ሥራውን የጀመረው ሐመልማሉ እሳቱን ሳያጠፋው እሳቱም ሐመልማሉን ሳያቃጥለው ባየው ድንቅ ምሥጢር ነው፤ ይህ ደግሞ እሳተ መለኮት ሐመልማል የሆነች እርሷን ላለማቃጠሉና ላለመዋጡ፣ በእርሷ የተፈጸመውን ተዋሕዶ የሚያሳይ ነው።

ሠለስቱ ዮሐንሶችም እንዲሁ ናቸው። ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ የፍቅር እናትን ተቀብሎ የጀመረው ሕይወት "ነባቤ መለኮት" አስብሎታል። ዮሐንስ መጥምቅ በእናቱ ማህጸን ሳለ ለእርሷ ሰግዶ የጀመረው ሕይወት "ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከእርሱ የሚበልጥ አልተነሣም" አስብሎታል። (ማቴ.11:11)። አፈ በረከት ዮሐንስ ስለ እርሷ አመሥጥሮ የጀመረው ሕይወቱ "አፈ ወርቅ" አስብሎታል። (ግንቦት 1 ዓመታዊ በዓሏ እንደ ሆነው ግንቦት 12 የሊቁ ፣ ግንቦት 16ም የሐዋርያው በዓል መሆኑን ልብ ይሏል)

እርሷ የወራችን ብቻ ሳይሆን የሰማይና የምድርም መጀመሪያ ናት። (ሰማይና ምድር በውስጣቸውም ያሉት ስላንቺ ተፈጠሩ እንዲል ድርሳነ ማርያም)። ሰማይና ምድር ሳይጋፉ ፣ ሳይራበሹ "ይህ የኔ ክልል ነው፣ ይህ የኔ ወሰን ነው" ሳይባባሉ ሺህ ዘመናትን በፍቅር የጸኑት እርሷን መጀመሪያቸው ስላደረጉ ይሆን?

እርሷ የአዳምና ሔዋን መጀመሪያ ናት። ስለ እርሷ አዳምና ሔዋን ተፈጥረዋል። (መላእክትን ከፈጠረ በኋላ በጸፍጸፈ ሰማይ ቀጥሎ ማንን እንደሚፈጥር ያሳያቸው ነበር። ቀጥሎ የሚፈጠረው ሰው: አምላኩን እንደሚክድ ሲያዩ መላእክቱ "አትፍጠረው" አሉ። ድንግልን አሳያቸው፤ ሊያዩት የሚጓጉለትን አምላክን መውለዷን ሲያዩ "ይህችን ፍጠርልን" ብለው ተማጸኑ። "ካለ እርሱ (አዳም) እርሷ አትገኝም" ቢላቸው "እንግዲያውስ ስለ እርሷ እርሱን ፍጠርልን" አሉ። \ትርጓሜ. ኢዮብ? ኩፋሌ?)። ነገረ ልደቱ በእርሷ የጀመረለት አዳም ነገረ ልደቱ በእርሷ እንዳልጀመረለት ሳጥናኤል ወድቆ አልቀረም - ተነሣ እንጂ።

በእርሷ የሚጀምር ቢወድቅ እንኳን ይነሣል።

መጽሐፍ ቅዱስ ካምና ያፌትን ትቶ የሴም የትውልድ ሐረግን ለምን ተረከ? እመቤታችን ከሴም ዘር ስለምትወለድ ነው። ከሌሎች ሕዝቦች መኻል እስራኤልን መርጦ ለምን ቀጠለ? እመቤታችን ከእስራኤል ስለምትወለድ ነው። የካም ዘር የሆነውን መልከጼዴቅን ትቶ የሴም ዘር ስለ ሆነው ስለ አብርሃም እየተረከ ለምን ቀጠለ? አብርሃም ስለሚበልጥ ነውን? አይደለም። መልከጼዴቅ ታላቅ አብርሃም ታናሽ እንደ ሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ነግሮናል። (ዕብ.7)። ታዲያ ምክንያቱ ምንድን ነው? እርሷ ከአብርሃም ዘር ስለምትወለድና ጌታችንና አምላካችንም ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም ስለሚሆን ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችን እንኳን እርሷን በሩቅ ዐይቶና በእርሷ ላይ ተመሥርቶ የተጻፈ ነው።

ድኅነታችን በእርሷ ምክንያትነት የተገኘ ነው። "አንዲት ዘር" የሆነች እርሷን ባያስቀርልን ኖሮ ከምድር በታች መውደቃችን ለመቀበር እንጂ ተዘርቶ ለማበብ አይሆንም ነበር።

ኢትዮጵያውያን በእርሷ በመጀመር አንታማም። በእርሷ እየጀመርን ከብዙ ውድቀትም ተርፈናል፣ ተነሥተናል።

እርስ በእርስ የመባላታችንም ሆነ የመጠላላታችን ነገር ምናልባት የፍቅር እናት የሆነች እርሷን ዘንግተን የመጡብን ይሆኑ ይሆን? ምናልባትም እርሷን የማይጠሩ ዜጎች በርክተው እኛም በዚህ ደክመን ይሆን?

ልክ እንደ ወሮቻችን በእርሷ እንጀምር። ያለፈውን ብልየት ኹሉ በመጥምቁ ትምህርት ላይ ቆመን እንሻገርና እርሷን ይዘን እንጀምር

ባለፈው ወር ያለቀስን፣ ያዘንን፣ የወደቅን፣ የከፋን፣ ያቄምን፣ የሞትን፣ የዘረፍን፣ የገደልን፣ የዘሞትን በክፋትና በሥጋ ሥራ ያረጀን ኹሉ በመጥምቁ ትምህርት ላይ እንቁምና ብሉዩን እንሰናበተው፤ ሐዲሱን ሕይወት ልክ እንደ ወሮቻችን "1" ብለን በእርሷ እንጀምር