ወኔ እና ቅኔ -(ፈይሠል አሚን)
9.44K subscribers
240 photos
4 files
45 links
ሐበሻ ቅኔን ያለ ምክንያት አልፈጠረም፤ በወኔ የማይነገሩ ሐሳቦቹን ሊገልጽበት እንጂ!
.
ዳገት አቀበቱን በወኔው አለፈ፤
ወኔውን ሲነጥቁት ቅኔ ፈለሰፈ!😉
Download Telegram
ትዳር መያዜን ሰምታችሁ ግሩፕ ውስጥ መልካም ምኞታችሁን የገለፃችሁልኝ ሰዎች እንደ ቤተሰብ የምንቆጣጠርበት ቻናል ውስጥ ማሳወቅ እንደነበረብኝ እንዲሰማኝ አድርጋችሁኛል። ምንም እንኳ የግል ጉዳይ ቢኾንም ከግል ሕይወት በመነሳት የምጽፋቸውንም ጽሑፎች ስታነቡ፣ስትነጋገሩበት፣ሐሳብ ስትጨምሩበት ቆይታችኋል። በዚህም ምክንያት አሁን ማግባቴን እንደ ቤተሰብ ቆጥሬ ለመናገር ተገድጃለሁ። አከብራችኋለሁ🙏
የድመቴ ጉዳይ!
.
"ድመትህን ጨክነህ አባረርከው?" የሚሉ ጥያቄ የሚመስሉ ውንጀላዎች ደርሰውብኛል😄 እርግጥ ተገቢ ጥያቄያዊ ውንጀላ ነው። ቢኾንም ግን እኔ ለዓመታት እንደ ልጄ አቅብጬ ያሳደግኩትን ድመት፣ በተመጣጠነ ምግብ እና በተመጣጠነ እንቅልፍ አሞላቅቄ ያኖርኩትን ድመት፣ መክሬ እና ዘክሬ ለአቅመ አዳም ያደርስኩትን ድመት. . . ሚስት አገባሁ ብዬ ባባርር ሚስቴ ራሱ ምን ትላለች? "ለድመትህ ካልኾንክ ለእኔም አትመለስም?" ብላ አትሰጋምን?
.
የተፈጠረው ነገር አሳሳቢ ነው። ድመቴ ግቢውን እንደ ግቢው ቆጥሮ አከራዬም እኔም ጋር እየተመላለሰ በነፃነት የሚኖር ቀበጥ ድመት ነው። አሁን ግቢውን እንደምለቅ ስታውቅ ድመቱን ይዤው እንደማልሔድ አስጠንቅቃ ነገረችኝ። ምክንያቷ ደሞ "ድመቶች አዲስ ቦታ የመልመድ ችግር ስላለባቸው ወደዚህ ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት የመኪና እራት ይኾናል("የመኪና እራት" ማለት ግን ምን ማለት ነው? መኪና ነዳጅ እንጂ ድመት አይበላም ልበላት እንዴ?🙄 ፣ በዚያ ላይ ደሞ ይኼ ግቢ ካለ እሱ አይኾንም ጭር ይላል!" የሚል ነው መከራከሪያ ነጥቧ! ተከራክራኛለች።
.
እኔ አዲሱን ቤት ለመልመድ ተቸግሮ የመኪና እራት ቢኾን የሚለው ቢያሰጋኝም፣ ያሳደግኩትንና እኔን ብሎ ያን ግቢ የለመደን ድመት ጥዬ መሔድ አልችልም። ድመቴን እስካልሠጠሽኝ ድረስ የቤቱን ቁልፍ አልመልስም በማለት ክርክሩን ወደ ሌላ ምዕራፍ አሸጋግሬዋለሁ። ይኽ የድመት ይገባኛል ጥያቄ እየከረረ ሔዶ ፍርድ ቤት እንዳይደርስ በመስጋት ላይ እገኛለሁ😁 (አስባችሁታል ለድመት ጠበቃ ሳቆም😅)
.
በርግጥ አከራዬ ለድመቱ የተለየ ፍቅር አላት፣ ትንከባከበዋለች። ግን እኔ ደሞ እዚህ ድረስ አብሬው የመጣሁትን ድመት ጥሎ መውጣት ያስወቅሰኛል። እስቲ እንወያይበት....እርስዎ ቢኾኑ ምን ያደርጋሉ?😁
.
@huluezih
@huluezih
ለተመራቂዎች:-
.
• ዩኒቨርሲቲ ስትገቡ የቀይ ዳማ መልክ ይዛችሁ ገብታችሁ እንደ ዳማ መጫወቻ ጥቁርና ነጫጭባ ኾናችሁ የወጣችሁ…

• የካፌ ምግብ ጨጓራችሁን አስረጅቶ በከዘራ ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ጨጓራ ባለቤት ያደረጋችሁ. . .

• 4 D 3C እና 2 F በመያዝ በቀጣይ ዓመት Add ለማድረግ ወደ ዪኒቨርሲቲ የምትመለሱና ቤተሰብ ጉዱን ሳያውቅ በሬ ጥሎ የደገሰላችሁ ተመራቂዎች. . .

• ሁሌ ከክላስ እየቀራችሁ፣ አስተማሪ ለምን ክላስ እንደማትገቡ ሲጠይቃችሁ ‹‹ብዙ ትኩረት መሣብ ስለማልወድ ነው!›› ስትሉ ተማሪዎች….
.
• አንዳንድ የሰላም መደፍረስ ያለባቸው ዩኒቨርሲቲ ገብታችሁ ካጠናችሁት ኮርስ በላይ ስልታዊ ማፈግፈግና ወታደራዊ ስትራቴጂ ተምራችሁ የወጣችሁ. . .

• የበሶ ውለታ ያለባችሁ ተመራቂዎች. . .

• በቴንሽንና በተመጣጠነ ምግብ እጦት ፈተና በደረሰ ቁጥር ፌንት እየበላችሁ ብዙ ተሸካሚ ወንድምና እህቶች ያፈራችሁ. . .
.
እናም ሌሎችም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንኳን ለዚህ አበቃችሁ. . .እንኳን ደስ አላችሁ!
.

በተለያየ ዓመትና በተለያየ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ብንማርም ሁላችንም ዩኒቨርሲቲ የገባን ተማሪዎች አንድ ዓይነት ታሪክ እንጋራለን፡፡ በዚህም ምክንያት ወጣቶች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ እስኪወጡ ድረስ ምን ሊገጥማቸው ይችላል የሚለውን በመጽሐፍ መልክ በማዘጋጀት ትውልዱን ከመደናገር ለመታደግ አስቤያለሁ፡፡ርእሱም ‹‹እኛም እንናገር፣ተመራቂ አይደናገር!›› የሚል ነው፡፡
.
ከመጀመሪያው ስንጀምር. . . ሁላችንም ዩኒቨርሲቲ እንደደረሰን ስናረጋግጥ መጀመሪያ ላይ መጥተው ‹‹ምትፈልገውን ማንኛውም ነገር ካለ ንገረኝ! አትደብቀኝ! እኔ አሟላልሃለሁ!›› የሚሉ አጎቶችና አክስቶች አሉን፡፡ እንዲህ ካሉን በኋላ ግን ጠፍተው የምርቃታችን ቀን ነው በዓይነ ሥጋ የምናያቸው፡፡ አንዳንዴ ቸግሮን ስንደውልላቸው የማይገናኝ ምክንያት የሚያቀርቡ ዘመዶች ሁላችንም ጋር አሉ፡፡ ደውለን ‹‹የምትፈልገው ነገር ካለ ንገረኝ ብለኸኝ ነበር….›› ስንል ‹‹እቴኑ እኮ ሞተች!›› ብለው ወሬ የሚያስቀይሱ ዘመዶች እናንተ ጋር ብቻ ሳይኾን እኛም ጋ ነበሩ፡፡ ዘመን አይሽሬ ናቸው፡፡
.
እንደ ልማዳቸው የምርቃት ቀን ይመጡና ‹‹እንኳን ለዚህ አበቃህ! አሁን ሥራ ነው ሚያስፈልግህ…..በሰው በሰው አፈላልገን አንድ ቦታ እንሸጉጥሃለን!›› ብለው ሌላ ቃል ይገቡልሃል፡፡ ከዚያ አንተ በባስና በባቡር እየተሸጎጥክ ሥራ ፈልገህ ስታጣ ደውለህ…ቃል ገብተህ ነበር ስትለው. . .እንደ ልማዱ ‹‹እቴኑ እኮ ሞተች!›› ብሎ ወሬ ያስቀይሳል፡፡ እኔ ፍሬሽ ተመራቂ እያለሁ ይኼን የሚነግረኝ ሰው ቢኖር ደስ ይለኝ ነበር፡፡
.
የዚህ ዘመንን የዩኒቨርሲቲ ሕይወት ከእኛ ዘመን ትንሽ የሚለየው ሁለት ነገር ይመስለኛል፡፡አንደኛው በፊት ዩኒቨርሲቲ ገብተን ስንወጣ ነበር የምንመረቀው….አሁን አሁን ደሞ ቤተሰብ መርቆን ካልገባን በሰላም ለመውጣት እንቸገራለን፡፡
.
ሌላው ልዩነት ዩኒቨርሲቲዎች አዳዲስ ተማሪዎችን ለመጥራት የሚያወጡት ማስታወቂያ ይመስለኛል፡፡ ሐገሪቱ ባለችበት ሁኔታና እውነታ ምክንያት ዩኒቨርሲቲዎች አሁን አሁን ተማሪ አጠራራቸው ራሱ ያስደነግጣል፡፡
.
‹‹ማስታወቂያ ደብረ-ጤዛ ዩኒቨርሲቲ ለደረሳችሁ አዲስ ገቢ ተማሪዎች በሙሉ፡-
‹‹ደብረ-ጤዛ ዩኒቨርሲቲ የቀጣይ ዓመት መደበኛ ተማሪዎችን ከመጪው ማክሰኞ ጀምሮ ተቀብሎ የሚመዘግብ በመኾኑ ማንነታችሁን የሚገልጽ ሁለት ጉርድ ፎቶ ግራፎችን በመያዝ፣ ከላይ ከተጠቀሰው ውጪ አንሶላ፣ብርድልብስ፣ ሻንጣ እና በቆይታችሁ የምትጠቀሟቸውን ተጓዳኝ ምግቦች ሽፍታዎች ሊቀሟችሁ ስለሚችሉ ባትይዙ ይመረጣል፡፡በማስታወቂያ ላይ የተጠቀሱትን አሟልታችሁ ፈጣሪ ብሎ ድንገት በሕይወት ወደ መመዝገቢያ ስፍራው ከደረሳችሁ በአስቸኳይ የምናስተናግድዎ ይኾናል(በሕይወት ካለን!)፡፡ፈጣሪ በኪነ-ጥበቡ ይጠብቃችሁ!››
.
እንዲህና መሰል መከራዎችን አልፎ የተመረቀ ተማሪ በምርቃቱ ቀን ምንም ቢያደርግ ወዙ ሊመጣ አይችልም፡፡ ሁላችንም በምርቃታችን ቀን ሰቀቀኑ አክስቶንና አጥቁሮን፣በዲፌንስ ድንጋጤ ዓይናችን ቦግ ብሎ ቀርቶ፣አስተማሪ ሚመስል ሰው ባየን ቁጥር እየተደናበርን…… በምርቃታችን ቀን የተመረቀ ሰው ሳይኾን የመረቀነ ሰው ነው ምንመስለው፡፡
.
ለመጀመሪያ ጊዜ ዩኒቨርሲቲ የሔድኩት የኦረንቲየሽን ቀን ነበር፡፡ሁሉም ዲፓርትመንቶች በተወካያቸው በኩል አዳዲስ ተማሪዎች እንዲቀላቀሏቸው ሲያማልሉ ደረስኩ፡፡ እንደ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የመጀመሪያውን ሳክስ እና ግነት የምትሰሙት ኦረንቲየሽን ላይ ነው፡፡ በስስ ጎናችን በኩል ጀንጅነው፣ ሥራ አለ ብለው ያለ ፍላጎታችን ዲፓርትመንታቸውን እንድንቀላቀል የማይሉት ነገር የለም፡፡ የዚያን ቀን የአርኪዮሎጂ ዲፓርትመንትን ወክሎ የመጣው ሰውዬ እንዲህ አለ፡-
‹‹እንግዲህ እኛ ብዙ ራሳችንን ማስተዋወቅ የለብንም፤ጥሩ ነገር ማስታወቂያ አይፈልግም፡፡ የእኛ ዲፓርትመንት በጣም ሰፊ የሥራ ዕድል ያለው ዘርፍ ነው፡፡ እንደምታውቁት እስካሁን ሉሲ ብቻ ናት ሙሉ ለሙሉ የተገኘችው፡፡ገና አባትና እናቷ፣ ባለቤቷ እና ጎረቤቶቿ ስላልተገኙ እናንተ እነሱን በማግኘት ከበርቴ ልትኾኑ የምትችሉበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ የእኛ ተማሪዎች ጥንታዊ ቅሪተ-አካሎችን ለማግኘት የልምምድ ቁፋሮ በሚያደርጉበት ወቅት በድንገት ነዳጅ አግኝተው የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት ቀይረዋል፡፡ ስለዚህ እናንተም ከጸጋ በረከቱ ትቋደሱ ዘንድ እነሆ ተቀላቀሉን!››
.
እውነት ነዳጅ አገኛለሁ ብለህ ስትገባ ….ራስህን አስተማሪው ጀሪካን ሰጥቶ ለመኪናው ነዳጅ እንድታመጣ ሲልክህ ታገኘዋለህ!
.
በመጨረሻ የሚመር እውነት ሹክ ልበላችሁ፡፡ አሁን እየተሰማችሁ ያለው ስሜት እኛም ስንመረቅ ተሰምቶናል፡፡አሁን እያሰባችሁ ያላችሁትን ነገር እኛ አስበነው ነበር፡፡ ከምታስቡት ሐሳቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-
‹‹አሁን ተመርቄያለሁ! ሥራ ይዤ ለፍቶ ያስተማረኝን ቤተሰቤን እየደጎምኩ፣ ከማገኘው ደሞዝ ቆጥቤ ዕዳዬን ከፍዬ ማስተርሴን እቀጥላለሁ!›› ብላችሁ የምታስቡ አላችሁ አይደል?
.
ሌሎቻችሁ ደሞ ‹‹ትምህርቱ ይበቃኛል፣ የራሴን ነገር ጀምሬ…ድርጅት አቋቁሜ ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል እፈጥራለሁ›› ብላችሁ እያሰባችሁ ነው፡፡
.
የተቀራችሁት ደሞ ‹‹ስኮላርሺፕ አግኝቼ…ከሐገር ወጥቼ፣ በአውሮፓ ወይ በአሜሪካ ትምህርቴን ተምሬ፣ጥሩ ሥራ ይዤ ከኢትዮጵያ ሚስት አስመጥቼ ጥሩ ቤተሰብ መሥርቼ እኖራለሁ!››

እንደዚህ የምታስቡ አላችሁ አይደል! ይኼን ሐሳባችሁን እኛ ስንሰማ ምን እንደምንል ታውቃላችሁ? ‹‹ወላሂ! ኧረ? እንደዛ ነው!››
.
ሐቅ ሐቁን እናውራ ከተባለ….በተማርንበት ሙያ ላንሠራ እንችላለን፡፡ በኢንጂነሪንግ የተመረቀ ጓደኛዬ በሐገሪቱ ሁኔታ ምክንያት እሳት የላሰ ደላላ ኾኗል፡፡ ከየት እንዳመጣው ባላውቅም አሁን እንደሱ ሰውን የማሳመን ችሎታ ያለው ሰው የለም፡፡ ባለፈው የኾነ ቤት ሊያከራይ ደንበኞችን ይዞ ሲሔድ ቤቱ ሽንት ቤት የለውም፡፡ ‹‹ቤቱ እኮ ሽንት ቤት የለውም!›› ሲሉት ‹‹ችግር የለውም! ለጊዜው በዳይፐር ትጠቀማላችሁ!›› ብሏል፡፡
.
ጥሩው ነገር ግን እዚህ መድረሳችሁ ነው፡፡ዩኒቨርሲቲ የቀለም ትምህርት ብቻ ሳይኾን ሕይወትን የተማራችሁበት፣ከሰው ጋር እንዴት መኖር እንደሚቻል ያወቃችሁበት፣ የሕይወት ዘመን ጓደኞች ያፈራችሁበት፣ ከቤተሰብ ርቃችሁ ብዙ ነገር የተጋፈጣችሁበት ሥፍራ እንደመኾኑ ይኽን ሁሉ ይዛችሁ እዚህ መድረሳችሁ ሊያኮራችሁ ይገባል! ተስፋ ሳትቆርጡ፣ የጀመራችሁትን ሳታቋርጡ እዚህ ስለደረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ! ለራሳችሁ ሞራል ሥጡ!
በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ!
.
(#ፈይሠል_አሚን)
.
@huluezih
@huluezih
ተዓምር ነው 'ምጠብቀው!
.
(#ፈይሠል_አሚን)
.
ጨረቃን ባሰላ፣ ከዋክብትን ብቆጥር፤
ዕጣና እድሌን፣ የነገዬን ሚስጥር፤
ማወቅ አይቻለኝም ያላንዳች ጥርጥር!
ምንጩን. . .
አመጣጡን. . .
ቀኑን የማላውቀው፣
ተዓምር ነው 'ምጠብቀው!
.
ሰው በዕውቀት ቢረ'ቅም፣
በልህቀት ቢጠልቅም፤
"ሰው" ሰው ብቻ ነው. . .
ነገውን አያውቅም!
እያንሰላሰለ. . .
እያመሳሰለ. . .
በምኞት ያመሻል፣በተስፋ ያነጋል፣
የሰው ልጅ አፈር ነው. . .
ተዓምር ይፈልጋል።
.
እኔም. . .
እንዴታውን ባላውቅም. . .
የደበተኝ አዚም ይተ'ናል እንደ ጠል፤
ማመን ነው ትርጉሙ ሕይወትን መቀጠል!
የእንቆቅልሼ ትብታብ፤
የፍርሃቴ ኪታብ፤
እያደር ይረግረባል፣ይፈ'ታል በኪኑ
ያልፋል ይኼ ሁሉ፣አምናለሁ በጽኑ!
.
ከሕይወት ትርጉም ውስጥ. . .
ብዙ ነው 'ማላውቀው፣
ብቻ ከልቤ ውስጥ
ተስፋ ነው 'ሚፈልቀው፣
ሰበብ አመጣጡን. . .
ቀኑን የማላውቀው፣
ተዓምር ነው ምጠብቀው!
.
@huluezih
@huluezih
የወላድ አንጀት፣ ሲለበለብ
እንባ እንደ ወተት ጠዋት ማታ ሲታለብ
ፍትሕ ይባላል ወይ
በዳይ አስሮ መቀለብ?
ምን ቋንቋ ይግለፀው?
ከየት ይምጣ ፊደል?
ሞት ብቻ ያንሰዋል የአንዳንድን ሰው በደል!
.
(#ፈይሠል_አሚን)
.
@huluezih
@huluezih
ያልወለደ "እፎይ" የሚልበት ዘመን. . .
የወለደ ከዓለም ጦርነት ሚገጥምበት ጊዜ. . .
ወልዶ በሰቀቀን ያሳደገ "ጀግና" የሚባልበት. . .
እናቶች የጊዜውን መረንነት፣የሰውን ጭራቅነት ዐይተው ልጆቻቸውን ሆዳቸው ለመመለስ የተመኙበት ጥቁር ወቅት. . .
"ሰው" ሰው መኾኑን የጠላበት፣
"ወንድነት" መሰደቢያ የተደረገበት፣
ዓለም ከዚህ ወዲያ ብዙ ዕድሜ ይቀራት ይኾን? አይመስለኝም!
.
(#ፈይሠል_አሚን)
.
@huluezih
@huluezih
ቢንገዳገድ እንጂ. . .
በአምላኩ ምትሐት፣ሚዛኑን ጠብቆ፤
ቢታገል ነው እንጂ. . .
ወደፊት ለማዝገም፣ወገቡን አጥብቆ፤
አያውቅም በጭራሽ. . .
"የተገፋ ሰው" ወደ ኋላ ወድቆ!

(ለመጣል አስበው ላነሡን
ለመስበር ሲሉ ለጠገኑን
ሊያሳፍሩን ብለው ላኮሩን
ሊወነጅሉ ጥረው ላነፁን
አመስግኑ አሁን!🙏)
.
(#ፈይሠል_አሚን)©
.
@huluezih
@huluezih
ትናንት፣ዛሬ እና ነገ ሌላ ነኝ!
.
(#ፈይሠል_አሚን)
.
ነጻነት ነበረኝ፤ ኣርነት!
ወፎች የሚመኙት፣
ሚስጥር ነበርኩ፤ ረቂቅ!
ሊቃን የሚቀኙት፣
"ሰሜ"ን ሲረዱት ነው፤
"ወርቄ"ን የሚያገኙት!
.
"ነበር!"
'ነበር!"
"ነበር!" ብቻ ኾነ፤
ማንነቴ ላይ የተጻፈው ምስል፤
ትናንትና ብቻ የሚያምር ይመስል!
ራሴን ለመግለጽ ምን አቅም ቢሳነኝ፤
ትናንት፣ዛሬ እና ነገ በርግጥ ሌላ ሰው ነኝ!
.
ልቤ ምስኪኑ. . .
ትናንቱ ገዝፎበት መልኩን እያጠረው፤
ያለፈውን ብቻ. . .
እንደ "ሕይወት" እየቆጠረው፤
"ማነህ?" ብለው ሲሉት. . .
"መቼ?" እያለ ነው መልሱን 'ሚጀምረው!
.
@huluezih
@huluezih
ተዓምራዊው ዓመት
.
(#ፈይሠል_አሚን)
.
ይኽ ዓመት ለእኔ በጥሩ ሁኔታ አልጀመረም። አመጣጡ የማዕበል ያክል የምሳሳላቸውን እና የምወዳቸውን ነገሮች ደረማምሷል፣ሰባብሯል። በስብራት ላይ ስብራት፣ በድንጋጤ ላይ ድንጋጤ ተደራርበው 2016ቴን ባርከው አስጀመሩት።
.
በዚህ ዓመት ከምወደው ጋዜጠኝነት ለመውጣት ወስኜ ጫፍ ደርሼ ተመልሻለሁ።(ከውስጤ በወጣ ምክንያት ካልኾነ በቀር በውጫዊ ግፊቶች መውጣት እንደሌለብኝ ተምሬያለሁ) ፤ ከማከብራቸው ሰዎች ክብሬን የሚነኩ ቃላት የሰማሁበት፤ አስተዋይ የምላቸው ጭፍን ኾነው ያየሁበት፣ ዝምድና በሥራ ዓለም ተቀዳሚ ምርጫ ኾኖ አናት ላይ መቀመጡን ያስተዋልኩበት....፣ ከእልፍ ሰናይ ምግባር ይልቅ አንዲት "ስህተት" ምትመስል ነገር አብሮ መብላትን አስረስታ ከጠላት እንደምታስፈርጅ የታዘብኩበት፣ አልተመቸው ኾኖ እንጂ ሁሉም ሥልጣን ያገኘ ቀን አቅሙን ለማሣየት የሚሔድበትን ርቀት ሳልፈልግ የተማርኩበት. . . .ብዙ ብዙ...ሌላ ሌላም!
.
ከዚያ ዓመቱ ሲጋመስ በስብራቴ መጠን ካሣዎች የመጡበት ጊዜ ኾነ። በአሃዝ ሲቆጠሩ ትንሽ ቢኾኑም ለእኔ በኾኑልኝ ነገር ሲለኩ ግን የአላህን ተዓምራት ማሣያ "ሳምፕሎች" የኾኑ ወዳጆች እንዳሉኝ የተረዳሁበት፣ አቅሜን ችሎታዬን የፈተሽኩበት፣ ከነበርኩበት እርከን ከፍ ያልኩበት፣ ወደ 'ምወደው ሬድዮ የተመለስኩበት፣ ከሁሉም በላይ ሕይወቴ የተረጋጋና ሣቅ የበዛበት ያደረገችዋን ግራ ጎኔን ያገኘሁበት ነበር።
.
በአላህ ያለኝ እምነት ከባድ ውሳኔ እንድወስን፣ ለሰዎች ጭራ እንዳልቆላ፣ ለማይሞላ ሆድ ብዬ ጫማ እንዳ'ልስ ብርታት ሠጥቶኛል። ባልተጻፈ ሕግ እንዳልቀጣ፣በእኔ ቦታ ኾኖ፣በጫማዬ ቆሞ እውነቴን ለማየት ያልሞከረን ለማስረዳት እውነታውን እንዳልስት ዓይኔን ገልጦልኛል።
.
በዚህ ዓመት አቅጄው ያልተሳካልኝ መጽሐፌን የማሳተም ጉዳይ ነው። የገዙኝ ሰዎች ብዛትና የሚያስፈልገው ማሳተሚያ አለመመጣጠኑና በየጊዜው የወረቀት ዋጋ እየጨመረ መምጣቱ አንዱ እክል ነው። ሙሉ ዓመት ከተጨመረልን ለቀጣይ ዓመት የምናሳድረው የቤት ሥራ ይኾናል። ከዚህ የተሻለ ዓመት እንደሚኾን፣ እኛም ከዚህ የተሻልን ሰዎች እንደምንኾን አልጠራጠርም!
.
በዚህ ዓመት የተማርኩት ትልቁ ትምህርት ሕይወት ሙሉ ለሙሉ እንድትቀየር አንድ ውሳኔ ብቻ በቂ መኾኑን ነው። ድፍረት ካለን እንደምናስበው ሕይወት ውስብስብ አይደለችም! ወንዙ ጋር ሳንደርስ መሻገሪያው ስለሚያስጨንቀን ነው። መጀመሪያ ወንዙ ጋር መድረስ ይቀድማል። ወንዙን ስንደርስ እንሻገረዋለን።
.
እናንተስ? በዚህ ዓመት የተማራችሁት ትልቁ ትምህርት ምንድነው?
.
@huluezih
@huluezih
መስከረምን እወዳታለሁ! (6)
.
(በዓመት አንዴ ብቻ የሚነበበው ታሪክ እነሆ ክፍል 6)
.
(#ፈይሠል_አሚን)
.
የዓመት ሙሉ እንባዬን የማፈስበት በቂ ገንዳ የለም። ድፍን አንድ ዓመት የኾንኩትን ሁሉ ዘርዝሬ የምጽፍበት መዝገብ የለም፤ ቢኖርም ቃላት ለመግለጽ ድፍረው ልሣኔ ላይ አይሳፈሩም። ዝም ብዬ ጀምሬ ዝም ብዬ የጨረስኩት ዓመት ነበር።ዕድሜ ለመስከረም!
.
"እንዳስቀመጡት የሚያገኙት የለም!" ብለው የተረቱት አበው እኔን መቼ ዐዩ? ወርሃ መስከረም ቄንጠኛ አበቦችን ጠርቶ፣ የውርጭ ሠራዊትን ጥሶ፣ የዝናብ ቋትን እየደፈነ በጳጉሜ በር አልፎ ደጄ የቆመ ዕለት የደነገጥኩት ድንጋጤ ዓመቱ ሙሉ ፋታ ሳይወስድ ዛሬም ድረስ ልቤን ያርገበግባል። ከጃጀ መስከረም እስከ እንቡጥ መስከረም ልቤን በወረሰችው መስከረም ሳቢያ እፎይ የምልበት አንዲት ቅጽበት ተነፍጌ ይኸው ዘመን ስለውጥ!
.
ዘንድሮ ከሌላው ጊዜ በተለየ ስለ መስከረም የማወራው እልፍ ነገር ቢኖረኝም ለማውራት አቅምና ፍላጎት ያጥረኛል። ውስጤ ማመንዠጉን ለምጄበታለሁ። መብሰክሰክ እና ወደ ውስጥ መዋጥ ከማውራት በተሻለ መልኩ ስሜት ይሠጠኛል። እስከ ዛሬ አውርቼ የት ደረስኩ? ተናግሬ ምን አመጣሁ? ቁስል ማከክ ለመድማት፤ መግል ማፍረጥ ለመግማት! ሌላ ምን ጥቅም አለው?
.
አምና መስከረም የአልጋ ቁራኛ ስትኾን ብቸኛ አስታማሚዋ ኾኜ አልጋዋ እግር ሥር አልጠፋሁም። ህመሟ ከጤናዋ ቀጥሎ ሥራዬን ክብሬን እና ሥሜን ነጠቀኝ። አልደነቀኝም። የከፈልኩት መስዋዕትነት ራሴን አሳጣኝ። "ከበሽታዋ ስታገግም ውለታዬን ትረዳ'ለች፣ ልቧን ያሻከረው ህመሟ ሲሽርላት ፍቅሬ ልቧ ላይ የማይለ'ካ ሥፍራ ይወርሳል!" በሚል ቀብጸ-ተስፋ የማይከፈለው ሎሌ፣ የማይደክመው አሽከር ኾንኩላት። የኾነው ግን የተገላቢጦሽ ነው። ብቻ ስለ መስከረም ማውራት አልፈልግም! ቁስል ማከክ ለመድማት፣መግል ማፍረጥ ለመግማት!
.
ከበሽታዋ የዳነች የመጀመሪያወሰ ንጋት ላይ የተኛችበትን አልጋ እና እኔን ከአዕምሮዋ ሰሌዳ ሰረዘችን። ረሳችኝ። ታመው ወዳልጠየቋት ጓደኞቿ ተመልሳ "ጓደኝነቷን" አደሰች። አግብቶ ወደ ፈታው የቀድሞ ፓይለት ፍቅረኛዋ ዘንድ ካቆመችበት ቀጠለች። "እኔ ግን ለመስከረም ምኗ ነኝ?" ብዬ አስብ የነበርኩት ሰውዬ "መስከረም ግን እኔን እንደ ሰው ትቆጥረኛለች?" ወደ ሚል አስቀያሚ ጥያቄ ተሸጋገርኩ። ብቻ ስለሷ ማውራት አልፈልግም!
.
"ቂል አደረገችኝ ጃሌውን ሰውዬ!" አለ ዘፋኙ! ከዕውቀት ዕውቀት አላነሰኝ፤ ቀጥ ያለ ኩሩ ሥም ነበረኝ። አማራጮቼም ተቆጥረው የሚያልቁ አልነበሩም። ፈጣሪ ብዙ ነገር ሳይሰስት ይሠጥና የሠጠውን ነገር ሁሉ አደጋ ላይ የሚጥል የሚያሟልጭ ጠጠር የሠጠን ጋን ሥር ይሰነቅራል። ጋን በጠጠር እንደሚደገፈው ሁሉ ጠጠርም ጋንን ያክል ንብረት አሣስቆ ይጥላል። ትንንሽ ነገሮች ትልልቅ ነገሮችን በዋዛ ወደ መውደቂያው ይወረውራሉ። አንዲት ክብሪት ደን እንደ ምታነደው፣ አንዲት ዛቢያ ዛፍ እንደምትገነድሰው፣ አንዲት ጉንዳን አንበሳ እንደምታዘልለው....መስከረምም የተከበርኩትን ሰውዬ ሥም አልባ፣ መጠን አልባ አደረገችኝ። አዎ መስከረም ትንሽ ናት እያልኩ ነው። ትንሽዬ አዕምሮ ይሉኝታ ከሌለው ልብ ጋር የተሸከመች!
.
የጊዜን ኃያልነት የምረዳው በመስከረም እኩይነት ውስጥ ነው። እንደ ማዕበል በሚተራመስ ፈጣን ጊዜ ውስጥ ይኽን ሁሉ ዓመት አንዱ ላይ ሳይረጉ፣ "ይኽን አደረግኩ!" የሚሉት ታሪክ ሳይመዘግቡ እንደ ጋማ ከብት ዕድሜን በማይረባ ንዝህላልነት ማሳለፍ ትንሽነትን ከማሣየት ሌላ ምን ያሣያል? መስከረም የአባቷን ፍላጎት ሳታሟላ አባቷብ አጣች፣ ሕይወት ሊያስተምራት ሽቶ አልጋ ላይ ዓመቱን ሙሉ ሲያቆያት ክፉና ደጉን ሳትለይ ተሽሏት ተነሣች፤ የሚፈልጋትንና የሚያፈቅራትን ሰው ገፍታ የተዋትን ሕይወት መልሳ አሳደደች፣ ዛሬመረ።መስከረም ትንሽ ናት! ቢኾንም ስለሷ ማውራት አልፈልግም!
.
ዛሬ ጠዋት አንድ ሕጻን ልጅ በሬን አንኳኩቶ አደይ አበባ የያዘ መልዓክ ያለበት ሥዕል ግዛኝ ሲል ጠየቀኝ። ሥዕሉን የምገዛበት አምስት ብር እንዳጣሁ ሳውቅ በሩ ሥር ቁጭ ብዬ ሥዕሉን እያየሁ አነባሁ። ለመስከረም ስንት ነገር ልጣ? ልጁ ለቅሶዬን ፈርቶ ሥዕሉን ትቶልኝ ሔደ።
.
ከቀትር በኋላ መስከረም ደወለችልኝ። "በዓል ነው ዛሬ...ወጣ ብለን ኬክ አንበላም?" አለችኝ። ኬክ ከእኔ ጋር መብላት የመጨረሻ አማሯጯ እንደኾነ አልጠፋኝም። ፓይለቱ ሰውዬዋ በረራ ላይ መኾኑን ነገረችኝ። ይኽን ሁሉ ዓመት ታሪኬን የነገርኳችሁ ሁሉ እንደምታውቁት ከጠራችኝ እንደምሔድ ታውቃላችሁ። ጥቅም የሌለው ጊዜ ከሷ ጋር ላሳልፍ ልወጣ ነው። ከቁብ የማልቆጠርበት እና ወዲያው የምትዘነጋው ጊዜ ዕድሜዬ ላይ ልጨምር ልሔድ ነው! ማን ያውቃል ምናልባት ቀጣይ ዓመት በዚህ ሰዓት ሌላ ሰው ልኾን እችላለሁ! በሕይወት ካለሁ! መስከረም ለእኔ የተከለከለች በለስ መኾኗን ስብዕናዋ ይነግረኛል። በእሷ ካገኘሁት ሽረት ይልቅ ያተረፍኩት ቁስል ይበልጣል! ቢኾንም አሁን ስለሷ ማውራት አልፈልግም! ቁስል ማከክ ለመድማት፣ መግል ማፍረጥ ለመግማት!
.
የቀጣይ ዓመት ሰው ይበለን ብቻ!
.
@huluezih
@huluezih
በዓል ከሌላ ማህበራዊ ጉዳይ ጋር ተደርቦ ባይመጣ! (ርዕሱ ነው!)
.
(#ፈይሠል_አሚን)
.
እንደሚታወቀው ‹‹መውሊድ›› ታላቁ ነብይ (ዐ.ሰ.ወ) የተወለዱበት ተዓምራዊ ቀን ነው፡፡ በዓለም ላይ ሰዎች እንደየ ባሕላቸውና እንደየ ወጋቸው በዓሉን በተለያዩ መንገዶች ያከብሩታል፡፡ በሐገራችን ‹‹መውሊድ›› በአብዛኛው በድምቀት የሚከበረው በየመስጂዶች ነው፡፡
.
እኔም ታዲያ ትናንት ማታ ነገ በዓሉን አስመልክቶ ከእረፍቴ ጋር አዋህጄ ስለ ነብያችን እያነበብኩ ለመዋል አቅጄ የማነባቸውን መጽሐፍት አዘጋጅቼ ተኛሁ፡፡ መቼም ሰውና የራይድ መኪና ባሰበበት አይውልምና ሌሊት ከሰዓት ላይ ክፉ ሕልም ክው አድርጎ ቀሰቀሰኝ፡፡
.
በሕልሜ የሩቅ ጎረቤቴ የኾት ጋሽ ተዘራ ባዶ ሜዳ ላይ ተዘርረው ሞተው ዐየሁ፡፡በሚገርም ሁኔታ ላለፉት ሦስት ሳምንታት እኚህ ሰውዬ በተከታታይ ሦስት የተለያዩ አደጋዎች ሲደረሱባቸው ዐይቻለሁ፡፡ በሕልሜ የጋሽ ተዘራ መዘረር አዲስ ነገር አይደለም፡፡
.
የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ጋሽ ተዘራ ማንም ሳይነካቸው በአናታቸው ሲደፉ ዐየሁ፣ በሳምንቱ ዛፍ ተገንድሶ ሲወድቅባቸው…በሦስተኛው ሳምንት ደሞ የፕራንክ ቪድዮ እሠራለሁ ብለው ባስደነገጡት ሰው ተደብድበው ሲዘረሩ ዐየሁ፡፡ቢጨንቀኝ ጎረቤቴ ያሉትን እማማ ሸንኮሬን አማከርኩ፡፡ እንደምታውቁት ሐበሻ ሕልሙን ማሳካት እንጂ ሕልሙን የማስፈታት ችግር የለበትም፡፡ማንም መንገደኛ ነው ሕልምህን ሚፈታልህ፡፡ እማማ ሸንኮሬ ሦስቱንም ሕልም ከሰሙ በኋላ ‹‹ሲሳይ ነው!›› ብለው ፈተቱት፡፡ ሕልሜን ፈተው ሲያበቁ ግን አመናጨቁኝ፡፡ ሕልም ሣይ እማማ ሸንኮሬ ለምን እንደሚበሳጩና ሳያብራሩ እንደሚፈቱልኝ አይገባኝም፡፡ ሕልም መፍታት አይችሉም እንዳልል የሰፈሩ ሰው የመሰከረላቸው ፈቺ ናቸው፡፡
እንደውም በሕልም ፍቺ ጥበባቸው ሲያሞኳሷቸው ‹‹እሳቸው እኮ የሕልም ጋራዥ ናቸው!›› ይሏቸዋል፡፡ ለተከታታይ ሦስት ሳምንታት ያየኋቸውን ተመሳሳይ ሕልሞች ስነግራቸው ቀንተው ነው መሰለኝ ‹‹ቆይ አንተ ግን ሁሌ እንዲህ እንደ አህያ ፊት አንድ ዓይነት ሕልም ምታየው ሰብስክራይብ አድርገህ ነው እንዴ?›› ብለው አሽሟጠጡብኝ፡፡
.
ይኸው ዛሬ ለሊት ጥሩንባ ተነፍቶ የጋሽ ተዘራ መርዶ ደረሰን፡፡አምሽተው ሲገቡ በማጅራት መቺዎች ተወግተው መገደላቸውን ሰማን፡፡
ያኔ እማማ ሸንኮሬ ሕልሜን ‹‹ሲሳይ ነው!›› ብለው ሲፈቱልኝ አምኜያቸው ነበር፡፡ዛሬ ሌሊት እንደደረሰን መረጃ ከኾነ ግን ጋሽ ተዘራን ‹‹ሲሳይ›› የሚባል የመንደራችን ዕውቅ ማጅራት መቺ እንደወጋቸው ሰማሁ፡፡
.
እነሆ! ከበዓሉ ዋዜማ በፊት የገጠመ የሩቅ ጎረቤት ለቅሶ ላይ ተገኝቻለሁ፡፡ እንደ ሕዝብ ለቅሶ ላይ አጉል አመል እንዳለብን ያስተዋልኩት እዚህ ለቅሶ ላይ ነው፡፡ አንዱ ለቀስተኛ የሟች ልጅ ጋር ጠጋ ብሎ ‹‹ታመው ነበር?›› ይላል፡፡ አባትዬው በማጅራት መቺ ተወግተው መገደላቸውን እያወቀ ነው ይኼን ሚጠይቀው፡፡ ልጁ ተናዶ ‹‹አዎ! የዛሬ ስምንት ዓመት ስኳር ይዞት ነበር!›› አለው፡፡ ልጁ ግን መጠየቁን አላቆመም፡፡ ‹‹ዶክተር ተኮላ ጋር እኮ ብትወስዷቸው አይሞቱም ነበር!››፡፡ እኔም ተናደድኩና ‹‹ዶክተር ተኮላ የማጅራት መቺ መድኃኒት ሠርተዋል?!›› አልኩት፡፡
ደንገጥ ብሎ ‹‹ያው ቢያንስ ከስኳራቸው አገግመው ቢኾን ሮጠው ማምለጥ አያቅታቸውም ለማለት ፈልጌ ነው!!›› ነው ብሎ አድበሰበሰ፡፡
.
ጋሽ ተዘራ በበዓል ቀን ቀብራቸው መፈፀሙ ለብዙዎቻችን ገርሞናል፡፡በዓል ሲነሣ አብረው ሚነሡ ሰው ናቸው፡፡ በዓል እጅግ ከመውደዳቸው የተነሣ ‹‹የበዓል አኒቨርሰሪ›› ሁሉ የሚያክብሩ ሰው ናቸው፡፡ ‹‹ቆንጆ ገና ያሳለፍንበት አራተኛ ዓመት!›› ይሉና ጳጉሜ ላይ ድል ያለ ድግስ ሊያሳናዱ ይችላሉ፡፡ ‹‹ጎረቤቶቼ›› የአረፋ በዓልን ክፍለ ሐገር ሔደው በማክበራቸው አብረናቸው ስላላከብርን ይሉና አረፋን ያለ ወቅቱ በሙክት ያከብሩልን ነበር፡፡
.
አንድ ጊዜ ድንገት ተሥተው ዛሬ በዓል ነው ብለው ዶሮ ገዝተው ሊ,ያርዱ ተሰናዱ፡፡ ዶሮው ግን የዋዛ አልነበረም፡፡ባርከው ሲያርዱት አንገቱን እዚያው ጥሎ ተነሥቶ በደመ-ነፍስ እግሬ አውጪኝ አለ፡፡ ክንፉን ዘርግቶ ያለ አንገት ቀጥ ብሎ ሲሮጥ አንገቱን የቆረጥንበት ሳይኾን ኮፍያ ያወለቅንበት ነበር የሚመስለው፡፡ ሳፋ ያለው ሳፋውን ይዞ፣ ሳፋ የሌለው ሰልፊውን ደግኖ ተከተለው፡፡
ዶሮው በዋዛ ሊያዝ አልቻለም፡፡ከምንም ጋር ሳይጋጭ ቀጥ ብሎ መንገዱን ይዞ ሩጫውን ቀጠለ፡፡ በዚህ ሁኔታ የተጨነቁት ጋሽ ተዘራ ከጭንቀት የመነጨ አስቂኝ ሐሣብ አመነጩ፡፡ ሮጦ የራቀው ዶሮ አንገቱን ግቢው ውስጥ ጥሎ ስለሮጠ ዓይኑ ቢሸፈን ተደናቅፎ ይወድቃል በማለት ‹‹ዓይኑን ያዙልኝ! በሕግ አምላክ ዓይኑን ጋርዱልኝ! ሲሉ ጮኹ፡፡
ይኼን የመሰለ ትዝታ ትተው ዛሬ ራሳቸው ጋሽ ተዘራ ዓይናቸው ለዘላለም ተሸፈነ፡፡
.
እነሆ. . .ዘመድ አዝማዱ መጥቶ ጋሽ ተዘራን ወደ ማይቀረው ቤታቸው ለመሸኘት ተሰብስበን በሐዘን ተቀምጠናል፡፡ እኔም ከቀብር በኋላ የበዓል እቅዴን ለማሳካት እያሰብኩ ነው፡፡ እግረ መንገድ ለቅሶው ላይ ሰዎችን እየታዘብኩ ነው፡፡
አንዱ ቲክቶክ ላይ ላይቭ ገብቶ ስለ ጋሽ ተዘራ መልካም ባሕሪ እያወራ ነው፡፡ ለጎረቤት ያላቸው ቅርበት፣ተጫዋችነታቸው የልጅነት ታሪካቸው ሁሉ አልቀረውም፡፡ በነገራችን ላይ ይኽ ላይቭ የገባው ልጅ ከአራት ቀናት በፊት እዚያ ማዶ ያለው ኮንዶሚኒየም ተከራይቶ የገባ ሰው ነው፡፡ ጋሽ ተዘራን በአካል ቀርቶ በፎቶም ያለዛሬ ያያቸው አይመስለኝም፡፡
.
አንዳንዶች ደግሞ እስኪነጋ ከሚደብረን ብለው አስከሬን ሳይወጣ ካርታ መጫወት ጀምረዋል፡፡ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ጋሽ ተዘራ ቤት ወደ አራት ለቅሶዎች ተከስተዋል፡፡ የባለፈው ለቅሶ ላይ አንዱ ቁማርተኛ ካርታ ሲጫወት ተበልቶ ያለውን ሰምቼ ሳላበቃ ዛሬም ዓይኑን በጨው አጥቦ እየተጫወተ ነው፡፡የባለፈው ለቅሶ ላይ ተሸንፎ ብሩን ሲበላ ጮክ ብሎ ‹‹ኤጭ! የዚህ ቤት ለቅሶ ደሞ አይቀናኝም!›› ማለቱን ነግረውኛል፡፡
.
በበዓሉ ቀን የጋሽ ተዘራ ግብዓተ-መሬት ተፈጽሞ ተመለስን፡፡ ከድንኳኑ ቀስ ብዬ ወጥቼ ቤቴ ሔጄ አረፍ ልል ሳስብ አያቴ ስልክ ደወለች፡፡ ‹‹በዓልም አይደል? ብቅ አትልም እንዴ?›› ብላ ጠየቀችኝ፡፡ በርግጥ ጥያቄ ይመስላል እንጂ ትዕዛዝ ነው፡፡
ወንዱ አያቴ በመውሊድ ቀን ወዳጆቻቸውን እና ቤተ-ዘመዱን ሰብስበው ታላቁ ነብይ ላይ ሰለዋት እያወረዱና እየዘከሩ የማሳለፍ ልምድ አላቸው፡፡ መንዙማው በላይ በላይ ሰለዋቱ ይከተላል፡፡ እኔ የሔድኩ እንደው ግን አያቴ እኔን ጎሸም የሚያደርግ ግጥም ጣል እያደረጉ ይዝናኑብኛል፡፡ስናደድ ደስ እላቸዋለሁ መሰለኝ፡፡ ባለፈው ዓመት የመውሊድ ቀን ተጠርቼ አርፍጄ ብገኝ. . . እኔን እያዩ እንዲህ ሚል ግጥም አወረዱ፡-

‹‹ለሰለዋት ብንጠራው፣ቀረ…ነገር መስሎት፤
የአንጎሉን ሽሆና ድፍን አር´ጎ ፈጥሮት!››
.
ታዲያ በአሽሙር ‹‹የአዕምሮህ ሽሆና ክፍት ነው!›› ማለታቸው ለጨዋታ መኾኑ ገብቶኝ እኔም ለጨዋታ አንድ ግጥም ጣል አደረግኩ፡፡ እንዲህ አልኩ. . .
ከባዳ አገኘሁት፤የጉንፋኑን ሳል
ከመንገደኛ መጣ፣ያሰቃየኝ ሳል፤
የሽኾና ክፍተት ግን ከአያት ይወረሳል!››
.
ይኽቺ ለጨዋታ የሰነዘርኳት ግጥም እንደ ሐገር ክህደት ወንጀል ታይታብኝ ከሞቀ በዓል ላይ ተባረርኩ፡፡‹‹ምንም መቀለድ የማይቻልበት ቤት!›› ብዬ እያጉረመረምኩ ወጣሁ፡፡ለእነሱ ሲኾን ጨዋታ ለእኛ ሲኾን ‹‹ነገር›› ነው መቼስ! ይኼን አስቤ ነው እንግዲህ ዛሬም ሔጄ ከምባረር ብዬ ወደ ቤቴ ለመሔድ የወሰንኩት፡፡
.
ቤቴ ስደርስ አከራዬ በዓልን ምክንያት በማድረግ ቤቴን ከፍተው አጽድተው፣እንደ ቋንጣ በገመድ ላይ ያንጠለጥልኳቸውን ካልሲዎቼን ዘፍዝፈው፣ አጫጭሰው ቡና እያፈሉ ደረስኩ፡፡ ደስ አለኝ፡፡ግን በግማሽ ልቤ. . .ቁልፌን አስቀርፀዋል ማለት ነው? ገመናዬን ደብቄ የዘጋሁበት ቤቴን ሊከፍተው የሚችል ሌላ ሰው መኖሩ አስፈራኝ፡፡የቤቴ ሳይኾን የገመናዬ ቁልፍ እሳቸው እጅ መኖሩ አስደነገጠኝ፡፡ግን ይኹን ጉርብትናው ይሻላል!›› ብዬ እያሰብኩ አከራዬ ‹‹ስማ!›› አሉኝ፡፡ አቤት ስላቸው. . . ‹‹ቁልፍህን ያስቀረጽኩበትን ገንዘብ ከቀጣይ ኪራይ ጋር አስበህ ትሠጠኛለህ!››
‹‹እንዴ! ጭራሽ እኔ ነኝ እንዴ ምከፍለው?›› ብዬ ተቆጣሁ……በሆዴ!
.
@huluezih
@huluezih
ወደ ሰማይ መውደቅ!
.
(#ፈይሠል_አሚን)
.
ስዘል "ወደቀ"
ስዘም "ታጠፈ"
ዝም ብል "ፈራ" አሉ!
ብተው "ጨነገፈ"
በጠላቴ አፍ ላይ፣ቂም ስለታቀፈ
የሠራሁት ተጥሎ፣ያጠፋሁት ተጻፈ!
.
ሰው ነኝ!
ምሉዕ አይደለሁም፣ብዙ ነው የኔ እንከን
ስወድቅ ስነሣ ነው የወጣሁት እርከን!
ለናንተ ለናንተ. . .
ውድቀቴ አርክቶ፣ቢያበግን መነሣቴ
ዛሬም ሆድ ይሞላል፣አልጠፋም እሳቴ!
.
አትርሱት! አትርሱት!
የውድቀቴን ዐዋጅ በነጋሪት ስትጎስሙት
ለሣር ቅጠል ሳይቀር ለዓለም ስታሰሙት
ሳትዘነጉ አንሡት፣ ይኽ አወዳደቄን
ዐውቄበት በቅጡ፣ወደ ላይ መውደቄን!
.
@huluezih
@huluezih
"የማለዳ ማስታወሻ ለምን ቀረ?"
🗣 ማለዳ መነሣት ስላቆምኩ!
.
"ግጥም በፎቶ ለምን አቆምክ?"
🗣 ስልኬ ስለተበላሸ!
.
"ክባዳም ትረካዎች ለምን ቀረ?"
🗣 ለመድረክ እያልኩ ስለምቆጥብ
.
መልሶቼ ለእኔም በቂ ምክንያት አይደሉም። የኾነ ጥልቅ ስንፍና ውስጥ መኾኔን ዐውቃለሁ። በተለያዩ ምክንያቶች ጽሑፍ መጻፍ እንደ ወትሮው ቀላል አልኾልኝም። በዚህ ሁሉ መሐል እስካሁን ስላላችሁ በጣም እኮራለሁ።ከልቤ አመሠግናችኋለሁ። በፍጥነት ወደ ራሴ ተመልሼ ዳግም ቶሎ ቶሎ እንደምጽፍ እና እስከዛ ድጋፋችሁ እንደማይለየኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ክበሩልኝ🙏
.
(#ፈይሠል_አሚን)
.
@huluezih
የዕጣ ፈንታ ጭፍራ
.
(#ፈይሠል_አሚን)
.
አልሜ አልተወለድኩም፣
ሥርፋ፣ዘመን፣ ሐረግ አልመረጥኩም!
በበልግ በክረምቱ፣
ደሞም በመከራው
እንደ ዱር ዛፍ. . .
የተጻፈልኝን ነው የማፈራው!
.
ታዲያ. . . ሳጠነጥን፣
እንደ ልደቴ ሁሉ . . .
ሞቴም አይደለም. . .የኔ ውጥን. . .

ምሕዋሩን ብናምስ፣ዳግም ብንወጥነው፤
እንደ "ሳብነው" እንጂ አይኾን እንዳሰብነው!
ለየቅል ተኾነ. . .
የሞት እና ሕይወት
የዕጣ ፈንታ ጭፍራው
"መኖርንስ" ለመድኩት. . .
ሞትን ለምን ልፍራው?
.
@huluezih
@huluezih