ግጥም
5.6K subscribers
23 photos
1 video
6 links
በዚህ ቻናል በጣም ምርጥ እና መንፈስን የሚያድሱ ግጥሞች ፣ ተከታታይ ታሪኮች ፣ የኦንላይን ቢዝነስ ቲፖች ይቀርቡበታል

መርጣችሁ አብራችሁን ስላላችሁ እናመሰግናለን

Buy Ads https://telega.io/c/gitm_post

ADMIN 👉 @Big_jor
Download Telegram
#ጎዳናው_ይገርማል?!

ይገርማል መንገዱ
እግረኛው ይገርማል

ሸራ ጫማ ባ'ይነት
በነጫጭ ካልሲ
በሲኪኒ ሱሪ
ከመምህሩ ጋራ
አይስክሬም ሚልስ
የሀይስኩል ተማሪ

ፀባይኛ ወጣት
ጃንቦ ተከልሎ
በምርቃና ሆኖ
ሀሳብ የሚፈትል
አንዲት ሙ......ደኛ እናት
በ'ድሜ ከልጆቼ አንሳለው የምትል
ፒዛውን የሚገምጥ
ጭማቂ የሚመጥ
አራዳ አባወራ
በሚስቱ ትከሻ
በልጆቹ ምላስ
ቅምጥ የሚጣራ

አንድ ፍሬ ሴቶች
በተገዛ ቅንድብ
በተገዛ ፀጉር በተገዛ ጥፍር
በውሰት ወዘና የተብለጨለጩ
ማኪያቶ ከበው
ለውስኪ ሚንጫጩ
ጅናም ጅንሳም ወንዶች በሴቶች ጫጫታ የሚቁለጨለጩ

ይገርማል ጎዳናው ይገርማል መንገዱ....

ድንቡሽቡሽ ህፃናት
በቶም ኤንድ ጄሪ ሱስ
ቀልባቸው የከሳ
በአይፎኑ አጮልቆ
ያንጀሊናን ከንፈር የሚስም ጎረምሳ

ቀውጢ ዳያስፖራ

የሎቲው የቁምጣው የቲሸርቱ ጥለት የተንዘረፈፈው
አማርኛ ሲሸሽ "what's happen" የጠለፈው

ነቄ ብላቴና

ከዮፍታዬ ቀዬ
ካ'ዲስ አለማየሁ
ከመዝገቡ መንደር
የአዲስ አ'ባ ጥሪ
በቁምጣ ያበረረው
ከቅኔ ተጣልቶ
ከግዕዝ ተኳርፎ ሎተሪ ሚያዞረው

ፀዴ ብላቴና

ከባላገር ዘመን
ከጨለማ ዘመን
ወደ ብርሃን ጥግ ተሸጋገርኩ ብሎ
በሸንኮራ ምርኩዝ ከተማ ሚያካልል መቋሚያውን ጥሎ
ነብሱ እየሰለለች
በከተሜነት ወግ ባ'ራዳነት ልምሻ
ሲያዘግም የሚውል
ሊስትሮውን ጭኖ በታቦት ትከሻ

ፎቆቹ

በመስታወት ቁመት በቆርቆሮ ገፆች
ባ'ልሙኒየም ጥራዝ የተብረቀረቁ
የጌቶቻቸውን እድሜ ሚያሳብቁ
ሁሉም........ ሁሉም......ሁሉም ጥግ ናቸው
ለወደቀ ወገን ይራራል ልባቸው

ሁሉም
...... ሁሉም

ከዘለለት ጥድፊያ
ከሰርክ ውጣ ውረድ በተረፈች አንጀት
ለወደቀ ወገን ምርኩዝ ማበጃጀት
ሁሉም...... ሁሉም ይችላሉ
ስለ'ግዚአር ላለ ይመፀውታሉ

እኔ ግን........ እኔ ግን .........ቆጥራለው
የ'ድሜ ክቡር ጀንበር
በጎዳና ፅልመት ሲዋጥ አስተውላለው
ጡረታ መንገድ ዳር ሲከፈን አያለው

ቆጥራለው.....ቆጥራለው

ቆጥራለው አዛውንት
በየአቀበቱ በየቁልቁለቱ
ማረፊያ ፍለጋ የሚንከራተቱ
ቆጥራለው አዛውንት ከልጆቻቸው ፊት
የልመና መዝገብ የገለጡ አሮጊት
ቆጥራለው በየመንገዱ ዳር
እርጅና ሙሽራው ለምፅዋት ሲዳር
ቆጥራለው በየሸንተረሩ በየተፋሰሱ
አቀርቅሮ ሲያዘግም እርጅና ሞገሱ
ቆጥራለው በ'ያደባባዩ
የሽማግሌ አይኖች የልጅ ፊት እያዩ
ቆጥራለው በየሰርጣሰርጡ
በልመና ጉልበት ከሞት ሲፋጠጡ
የ'ርጅና መዳፎች እሾህ ሲጨብጡ

ቆጥሬ..... ቆጥሬ.......ቆጥሬ
በለማኝ አዛውንት ብዛት ተሳክሬ
የማሰንበቻ ስንቅ ከኪሴ ቆንጥሬ
ያፅድቆቴን ዋጋ በሳንቲም መንዝሬ
ባ'ዛውንት ምርቃት ከሀገር ከቀዬው ትርፌን ሳመሳስል
በጎዳናው ቀለም ፃድቅ መልኬን ስስል
ጎልቶ ሚታየኝ ግን የሚያሳፍር ምስል
በቀላል ጥያቄ የነተበ ምስል

ጥያቄ

የዲጄ ኳኳታ የደናሽ ጋጋታ
የድራፍት እርካታ ያ'ረቄ ድንፋታ
ባጣበበው መንገድ
እንደምን ይቻላል
ላ'ያት ሳንቲም ሰጥቶ በ'ርካታ መራመድ?

ለወጣት ሹክሹክታ ለገደል ዝምታ
ላስመሳይ ጫጫታ ላድርባይ እሪታ
በተሰራ መንገድ
እውነት ቀላል ነው ወይ
ላ'ያት ሳንቲም ሰቶ በ'ርካታ መራመድ?

ለቡቲክ ሰልፈኛ ለካፌ 'ድምተኛ
ለውስኪ ጭሰኛ ለበርገር ምርኮኛ
በተሰራ መንገድ
እንደምን ይቻላል
ላ'ያት ሳንቲም ሰቶ በ'ርካታ መራመድ?

አያት....አያት...አያትነት ማለት
በደማቅ አሻራ የሸመኑት ጥለት
ለተራኪ እድሜ የተሰጠ አንደበት
ባ'ባት በ'ናት ፅናት የማይደክም ጉልበት
በልጅ ልጅ መነፅር የማያረጅ ውበት
በልጅ ልጆች ጥበብ የሚታደስ እውቀት
.....................................የሚታደስ እውነት
አያት ሆኑ ማለት
ድርብ አባትነት
ድርብ እናትነት

በተለይ እዚህማ.......
በዚህች አይነት ሀገር
ጎጆዋን ላቆመች
በተጋድሎ ካስማ
ባርበኝነት ማገር
በዚህች አይነት ሀገር
ጥያቄና መልሷን
ባ'ዛን በቅዳሴ በምትሰራ መንደር
በዱአ በፀሎት
በምናኔ ምርኩዝ በከረመች ሰፈር
የአያትነት ዋጋው በልኩ ቢሰፈር
ለሳንቲም ምርቃት ባልተሻማን ነበር!

ታሪክ በመዳፉ ስላደላደለው
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንጉስ አያት አለው
የልጅ ልጆች ስባት ባያመነምነው
ያያቶቻችን መልክ ሁሌም አንድ አይነት ነው

እላለው... እላለው....

የልጆች ምፅዋት ያ'ያቶች ልመና
ያ'ባቶች ግርግር በሞላው ጎዳና
መንገዱ አይልቅም
ጎዳናው አያልቅም
ይሰፋል ይረዝማል ይሄዳል ይጓዛል
እግረኛው ሞኝ ነው
ሳንቲሙን ዘርዝሮ
ከወደቁ አዛውንት ምርቃት ይገዛል

መንገዱ ያስፈራል
መንገዱ ይጨንቃል
ልጆች ሳቅ ሲያንቃቸው
አያት እምባ ይጨምቃል
መንገዱ ያሰጋል መንገዱ ያረጃል
ከዘናጭ ልጆች ጎን እርዛት ያዘለ አያት ይወለዳል

ሰጪ ካለቀሰ ተበዳሪ ስቆ
ጌታ ከለመነ አማኙ 'ግር ወድቆ
ልዑል ከዘመረ ንጉሱ ተዋርዶ
ገፁ ተመሳቅሎ ሽፋኑ ካማረ
ወለሉ ተንቆ ምንጣፍ ከከበረ
ባ'ገርኛ ስሌት ማነው ያልከሰረ?

እላለው........እላለው

ከየጎዳናው ገፅ ጥያቄ አነሳለው
ጥያቄ እጥላለው
እርጅና ለማምሻው ጎዳናን ካመነ
አያት ከልጅ ልጁ ሳንቲም ከለመነ
ባገርኛ ስሌት ማነው ያልመከነ?

በ'ግዚኦታ ዘመን በምዕላ ዘመን
እመንገድ ዳር ወድቆ ትራፊ መለመን
በጥሞና ዘመን የሚያስቡት ማጣት
በማውረሻ እድሜ የሚሰጡት ማጣት
በማልበሻ ዘመን በ'ርዛት መቀጣት
በለጋሽነት ወቅት በማጉረሻ ዘመን
በጥማት መገረፍ በርሀብ መመንመን
ከሆነ እጣችን
ይጠየቅ ትርጉሙ የልጅነታችን
ይፈተሽ መንገዱ የልጅ ልጆቻችን

ግድ የለም እንመን

እንመን

በሰውኛ ስሌት ውጤቱ ሲሰራ
ትውልድ ያደኸያል ያያቶች ኪሳራ
በልጅ ልጆች ዓለም
እንደጉድ ቢደለቅ ቢዘመር ቢዘፈን
አባት ይወራጫል ባ'ያቶች መታፈን

አባት ሆይ

ለልጆችህ ርዕዮት
ትላንቱን የረሳ ተስፋ ሲደራረት
ህልሜ ነው ይልሀል ያ'ያቶቹ ቅዠት
ከልጅህ አንደበት
ቋንቋ እንደዶፍ ቢዘንብ
ትርጉም ቢንፎለፎል ሺ ቃላት ቢጎርፍም
የልጅ ልጅ አግባቢ ግማሽ ገፅ አይፅፍም
ከልጆችህ ባህር
አሳ የሚያጠግቡ ለአሳ ሚስማሙ
እፅዋት ተክሎች
እንደጉድ ቢራቡ እንደጉድ ቢያብቡ
ገበታው አይሞላም ተቀዷል መረቡ

ግድ የለም እንመን........እንመን

የስኬት ክብደቱ
የምቾት አይነቱ
የነገ ውበቱ ባሻው ቋት ቢለካ
በምንም ቢሰፈር ባሻው ቃል ቢነገር
ጀግና ልጅ አትወልድም
አያቶቿን ገድላ የምትሸልል ሀገር

ከፎቆቹ ጥላ....
ከያስፓልቱ ገላ ሲታተም ድምቀቴ
በመስታወት አጀብ ሲጠገን ጉልበቴ
ይኸው አነበብኩት
አያቶቼ ፊት ላይ ተፅፏል ሽንፈቴ
በመኪና ብዛት
በመስታወት አይነት ሲለካ ፍጥነቴ
በግንብ አጥር መአት
በፎቆች ጋጋታ ሲሰላ ስኬቴ
ይኸው ይታየኛል
አያቴ ገፅ ላይ ተስሏል ውድቀቴ
...................ተስሏል ሽንፈቴ!
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
  ✍ በረከት በላይነህ
❤17🥰8🔥2👌1
#ለምስኪን_ገጣሚ!

የእርሱን ብሶት ችሎ አዳፍኖ በልቡ፣
የሌላውን ስቃይ በብዕር ማጀቡ፣
ቃላት እያማጠ ስንኝን መውለዱ፣
ሌላውን አግባብቶ እርሱ ግን ማበዱ፣
በምቾት አይደለም በስቃይ አልጋ ነው
በእህ! እህ መከራ ግጥምን የሚጽፈው !
የሌሎችን ስቃይ ከፊት በማስቀደም
ከእርሱ ሸክም በላይ ቀድሞ በመሸከም
እህ! እህ ለሚሉ ዓለም ለናቃቸው
ጥበብን አምጦ ድምጽ ሊሆናቸው
ቃል ስለገባ ነው የጥበብ አደራ
እርሱ ከሰል መስሎ ለሌሎች ሊያበራ
እንጂማ ገጣሚው ስቃዩ ቢዳሰስ!!!
የእርሱ ታሪክ ነበር የእውነት የሚያስለቅስ!
በሌሎች እንባ ጎርፍ የእራሱን ደብቆ፣
ደስተኛ መስሎ በተስፋ ቃል ስቆ!
ጥቅስ እያጣቀሰ ሌሎችን ሲያጀግን፣
ለምስኪን ገጣሚስ ማን ይሆን የሚያዝን?
መገለልን ችለው ጥበብ ለሚያምጡ
እስኪ እንባ ማበሻ መጽናኛ ቃል አምጡ።
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
   ✍ ስንታየሁ ሀብታሙ
❤15👍3💯2👏1
ተጋፈጥኩ መከራዬን
ተፋላምኩ ፈተናዬን
ኃይሌን ጨረስኩ እንጂ መች አገኙሁ ውጤት
እኔ አለቅኩ እንጂ መች በቃሁ ለስኬት
ሩጫዬን ገታሁ አቆምኩ ትግሌን ላፍታ
ቃኘሁት ድክመቴን የሽንፈቴን ቃታ
ለካ
ብቻዬን ነው ምጓዝ እርቃኔን ወጥቼ
መከታ ጋሻዬን ረዳቴን ትቼ
ለካ
ውልክፍክፍ ስንኩልኩል ነበር አሯሯጤ
እውር ድንብር ነበር ሚወነጨፍ ውስጤ
ለካ
በዜሮ ተባዝቷል ሙከራ ጥረቴ
አንቺን ሳልይዝ ሂጄ ድንግል እመቤቴ

አፈገፈግኩ ወደ ኋላ
ተመለስኩ ወደ ቀልቤ
ሰአሊ ለነ እያልኩ ታጠቅኩሽ በልቤ

ይኸው ነጻ ጥርጊያው
ይኸው ቀና መንገዱ
ገና ሳልጠጋው
ሲያዘቀዝቅ አየሁ  የመከራ ቀንዱ
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
✍ ኤልዳን
❤23👍1🥰1🕊1
እኔ እወድሻለሁ
ብዙ ሺህ ዘመናት
እልፍ አዕላፍ ሌሊት
ሚሊዮን መሰለኝ
ፍቅሬ አንችን ስወድሽ ቀኑ ረዘመብኝ።
እኔ እወድሻለሁ
የሰማይ መሬቱን
የባህር ስፋቱን
የዓለም ዳርቻ የርቀቱን ያህል
እንደ ፅጌ-ረዳ
እንደ አደይ አበባ
እንደሎሚ ሽታ።
እንደእጣን ጢስ እንጨት፥ እንደከርቤ ብርጉድ፥ እኔ እወድሻለሁ፥
                      አበባ እንዳየ ንብ።
እንደቢራቢሮ ጫካ እንደሚያስሰው
ፍቅርሽን በፍቅሬ በፍቅርሽ ልቅመሰው
ማር ወለላዬ ነሽ ከረሜላ ስኩዋር
አማርኛ አይበቃ፤
           ወይጉድ!
                    ባለም ቁዋንቁዋ ሁሉ ቢወራ ቢነገር፥
እኔ እወድሻለሁ
                      እንደማታ ጀንበር።
እንደ ጨረቃ ጌጥ፥
        እንደንጋት ኮከብ፥
                    እኔ እማልጠግብሽ
ስወድሽ፥ ስወድሽ፥ ስወድሽ፥ ስወድሽ።
ጡት እንዳየ ህፃን ወተት እንዳማረው
ጠጋ በይ ዘመዴ አፍሽ ሀይወቴ ነው።
ጣይ እንዳየ ቅቤ
           ገላዬ ገላሽን ሲነካ የሚያልቀው፥
አፈር መሬት ትቢያ ወሃ እንደሚበላው፤
ፍቅሬ አንቺን ስወድሽ
          ብዙ ሺህ ዘመናት
እልፍ አዕላፍ ሌሊት
እኔ እወድሻለሁ፤
አይኖችሽን ባይኔ ተዳክሜ እያየሁ
ስወድሽ ስወድሽ
          እኔ እወድሻለሁ።
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
❤17👍6
#ያኔ_እንዳደረግነው!!!

እንታረቅ ውዴ በትንሽ ጣታችን
በለመድነው ኩርፊያ በልጅነታችን
ቂም በማይቋጥረው በለጋነት ውበት
ያኔ እንዳደረግነው ጥልቅ የፍቅር ስሜት
ዛሬም እንድገመው  ጣልቃ ሳናስገባ
በትንሽ ጣታችን እኛው እንግባባ
ኩርፊያችን የፍቅር
ይቅርታችን ከምር
የልጅነታችን
በትንሽ ጣታችን
ዛሬም እንታረቅ እሽ በይኝ ውዴ
ቂም መያዝሽን ተይ ይቅር መናደዴ
መጣላታችንን ማንም ሰው ሳይሰማ
እንደጥንቱ ዛሬም እኛው እንስማማ
ጣትሽን ሳሚልኝ ጣቴን እስማለሁ
ፈገግ በይልኝ እኔም እስቃለሁ
አድገን እንድገመው ያለሽማግሌ
ስሜትሽ ስሜቴ አካልሽ አካሌ!
የውሸት ተጣልተን የምር እንታረቅ
በንጹህ ፈገግታ ጥርሳችን ይፍለቅለቅ
አምላክም ብሎናል ህፃናት ምሰሉ
መጽደቅን ብትሹ ቂም አታንከባሉ
ልባችን የልጆች እድሚያችን የትልቅ
እንታረቅና እኛው ለኛ እንሳቅ!!
አምጭ ትንሿን ጣት
እኔም ልጎትታት
ፍቅር ማለት ለካስ ያኔ ነበር የእውነት
በከንፈር ተኳርፎ በጣት ለመግባባት
ያኮረፈን ከንፈር ፈልቅቆ ማላቀቅ
ያለሽማግሌ ተግባብቶ መታረቅ!!!
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
   ✍ ስንታየሁ ሀብታሙ
❤23👍7😢1🤨1👻1
#ያማል

ራሴን ልሰጥክ
ወስኛለሁ ብላ፤
ማታ ቀጠረችኝ
ከለመድናት ቦታ።
ሰአቴን ጠብቄ
ከቦታው ተገኘሁ፤
ቃሏን እያሰብኩኝ
ትእዛዝ እየሰጠሁ፤
ጥቂት እንደቆየሁ
እሷ መጣችና፤
በምግብ በመጠጥ
ትንሽ ጠገብንና፤
ወደክፍሉ አመራን
ወደያዝነው አልጋ፤
በፍቅር ቀለጥን
ለሊቱ እስኪነጋ።

ይሄ ውብ ቃላችን
እራስን የመስጠት፤
ችግር መሃል ገብቶ
ቃልን በቃል ሲያስት፤
በቃ አልፈልግህም
  ሂድልኝ አለችኝ፤

ለካስ የዛን ምሽት፤
አካሏን ነው እንጂ መች ልቧን ሰጠችኝ።
የስሜቱን ነገር
እንደውለታ ቆጥራ፤
ችግሩ ሲፈጠር
ቀረች ተሰውራ።
ችግሩ ምንድነው
መባል ስለማይቀር፤ ልናገር
(HIV)፤ positive ነኝ እኔ
በውልደቴ ጀንበር፤

በእኔ ጥንቃቄ፤
ጤነኛ መሆኗን እርግጠኛ ስትሆን፤
እራሷን ልሰጠኝ
ቃሏን እንዳልሰጠች፤
ህመምህ ህመሜ
ብላ እንዳላለች፤
የፍቅርን ትርጉም
እሷ መች አወቀች፤
ለወደዱት መሞት
እሷ ስላልቻለች፤
መልካም ናት አውቃለሁ
እርቃኝ ሄዳለች፤
ሌላ አፍቃሪ እንዲሞት
እድሉን ሰጥታለች፤
ፍቅርን ለሞት ጥላ
ሸሽታ ኮብልላለች፤
ቀድማኝ እንደማትሞት
ግምቷን ሰጥታለች።

አንድ ቀን ሲገባት፤
የማይገኝ ፍቅርን መሞት እንደቀማት፤
ሞት ግን ስለማይቀር
ያማል ፍቅር ማጣት።
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
❤17👀3
#በበላ_ልበልሀ

በሉ ተባባሉ ጉዳዩ ምድነው ?
በዳይ ተበዳይን ሰምተን እንወቀው
ሚዛናዊ ፍርዱን ውሳኔ እድንሰጠው
ከከሣሽ እንጀምር አቤት ባይ እሱነው።
ከሣሽ-አመሠግናለሁ ስለፈቀዱልኝ
በደሌ ይሄነው ልናገር አዳምጡኝ
እንክርዳዱን ጠምቃ ቀምሳ አጣጥማው
በቅላሏ ሞላችው ተዋዳ ከጠላው
እኔ ላላይባት ሰውራ አስቀምጣው
ወዳጄ እያልኳት አምኛት እንደሰው
መሀላ አፈረሰች በደሌ ይሄውው ነው፡፡
ተከሳሽ - እክርዳድ አይደለም ቅሌን የሞላሁት
ወቅጦ በሰጠኝ ነው ጠንስስሼ የጠመኩት
ከገንቦዬ ቅድሚያ እሱን ነው ያቀመስኩት
ከሳዘሬ ይመስክር ያለው ከጎተራ
ጠይም እንኳ የለው እንክርዳድ ሊያፈራ
ተከሣሽ-- የጠየመን ስንዴ እንክርዳድ ካለው
ከገንቦዬ ጠልቆ ከጠላው ባይቀምሰው
ሸንጎው ፍርዱን ይስጠኝ ጥፋቴ ምድነው?
   ዳኛው ከሣሽ ፣ተከሣሽን ሁሉንም ሠማነው
ማሳህ ያተ ሆኖ ስንዴ የዘራኸው
እንክርዳድ አይደለም ጠይሞ ብታየው
ይሄ አያጣላም ከጠላህ አፍቅረው
ይቅር በላት አሁን የህል ክፉ የለው።
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
     ✍ ግዛቸው ማሞ
❤11👍1
#መንፈሴን_አመመኝ!!!

ሰምቶ ለሚያሰማ ችግሬን ነግሬ
ስሜ አደባባይ ነው የሚውለው ዛሬ
ይረዳኛል ያልኩት ያመንኩት ቢከዳኝ
አልቅስ አልቅስ አለኝ በድንገት ሆድ ባሰኝ
ለካስ እህ እያለ ችግሬን መስማቱ
ሊረዳኝ አይደለም አቤት ሰው ክፋቱ
ደግፈኝ ያልኩት ሰው ገፍትሮ ቢጥለኝ
ከስጋዬ በላይ መንፈሴን አመመኝ።
ከአረገልኝ በላይ ያደረገኝ ብሶ
ሆዴን እየባሰው ይቀናኛል ለቅሶ።
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
   ✍ ስንታየሁ ሀብታሙ
💔12❤9😢3👍2
አሁን የራቀውን አቅርቤ ሳስበው
ወገን በየፊናው ፥
የሚሻል ፍለጋ፤ ካምና ከታች አምናው
የሁዋላውን  ትቶ ፥ ይሻማል የፊቱን
ዛፍ እንኳን፥ ሲታደስ ይጥላል ቅርፊቱን
ምን ሆኘ ነው እኔ?
ለሚመጣው ጊዜ፥ ጀርባየን ምሰጠው
በጥንቱ ደጃፍ ላይ፤ የምቀላውጠው
ስንት ጊዜ አለፈ? ሰንት ቀን? ስንት ሌት
አይመች ለስሌት
ዘመኑ በርክቶ
በርምጃ የኖርነው፥ ስንዝር ተለክቶ
ያደርግነው ሁሉ፥ ውብ ተረት ሲመስል
መውጊያሽ መናደፍያሽ ፤ ስለቱ ደንዞ
ያተምሽብኝ  ቁስል
እንዳልፎ- ሂያጅ ኮከብ ፥ እያደር ደብዝዞ
አሁን የራቀውን አቅርቤ፥ ሳስበው
የደስታ ጸዳል ነው፥ ፊቴን የሚከበው ::
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
✍ በእውቀቱ ስዩም
❤8👍4
#ተረሳሽ_ወይ

ምነው ተረሳሽ ወይ ያሳለፍነው ሁሉ፣
እኔ እንዳልረሳዉ ያቃጭላል ቃሉ፣

ውዴ ፣ ፍቅሬ ፣ የኔ ይህ ሁሉ ቀረና ፣
ሆድሽ ቂም አርግዞ ተለየሽኝና ፤
ጆሮሽ ማይወደውን የሰው ወሬ ሰምቶ ፣
የመጀመሪያውን የ'ውነት ፍቅሩን ረስቶ ፤

እስቲ ላስታውስሽ ተረሳሽ ወይ ፍቅሬ :

ታክሲ ተቀምጠሽ እያለሽ ከጎኔ ፣
ያንን ውብ አይንሽን እያየሁኝ በዐይኔ ፤
ወክ ያረግንባቸው እነዛ ምሽቶች
ሊነጥፉ የማይችሉ ውድ እንቁ ቀናቶች
የነፋሡ ቃና የወፎቹ ዜማ ፣
መች የሚረሳ ነው የፍቅራችን ሻማ ፡፡

እስቲ ላስታውስሽ ተረሳሽ ወይ ፍቅሬ ፡

ነገ ልንገናኝ ዛሬ ተቀጣጥረን ፣
እስከምንገናኝ እርስ በርስ ተናፍቀን
ና እኔ መጥቻለውሁ፣
በጣም ናፍቀህኛል ላገኝህ እሻለሁ ፤
ትይኝ ነበር ፍቅሬ
ስመሽኝ ፣ አቅፈሽኝ ፣ አውርተሽ ማትጠግቢኝ ፣
ኧረ እንዴት አስችሎሽ ጨክነሽ ረሳሽኝ ፤

እስቲ ላስታውስሽ ተረሳሽ ወይ ፍቅሬ ፡

እኔና አንቺ'ኮ _....
ስንተያይ ውለን ሌቱ የማይበቃን ፣
ስናወራ አድረን ቀኑ የሚያጥርብን ፤
ላፍታ ተራርቀን ናፍቆት 'ሚበርደን ፣
ላፍታ ተለያይተን ናፍቆት የሚቀጣን ፤

እስቲ ላስታውስሽ ተረሳሽ ወይ ፍቅሬ ፡

ላትከጅኝ ላልከዳሽ ፣
ላትርቂኝ ላልርቅሽ ፣
ጨረቃ ፊት ሆነን የማልነውን ተረሳሽ? ፤

እየተጎራረስን ፣ እየተሳሳቅን ፣
እየተጨዋወትን ፣ እየተሯሯጥን ፤
የሳለፍነው ጊዜስ ፣ ያሳለፍነው ደስታ ፣
ኧረ እንዴት ተረሳሽ ንገሪኝ በጌታ ፤

ፍቅሬ ፦
የኔና አንቺስ ፍቅር እንደዚ በወሬ ፤
ከዚህ እስከ ጨረቃ ሸራ ተዘርግቶ ፣
ዓለምን የሚያህል መፅሃፍ ተሰርቶ ፤
ተፅፎ ፣ ተነቦ ፣ ተስሎ መች ያልቃል ፤
በትረካ ቢቀርብ ከልጅ ልጅ ይደርሳል ፡፡
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
❤7👍5
#ልጫር_ልሞጫጭረው!!!

ቃላት አሽሞንሙኖ በፊደላት ደምቆ፣
በምሁር ቃል ጠቀስ ቢመጥቅ ተራቆ፣
ቅኔው ቢወሳሰብ አንባቢ ካልፈታው፣
ጠቢባዊው ሁሉ ለማነው የሚጽፈው ?
ህግጋት ጠብቆ ቀለማትን ቆጥሮ፣
ምጣኔን መጥኖ ሀረጋትን ቋጥሮ፣
ምሁሩ ወንድሜ ቅኝት ተከትሎ፣
እኔን ፊደላዊ ከጥበብ ነጥሎ፣
እርሱ ባወቀው ልክ መብቴን ከልሎ፣
ሲከሰኝ ይውላል እንዳትገጥም ብሎ።
አንተሙ ለተማሩት ለተመራመሩ፣
እኔም ለቢጤየ ፊደል ለሚገድፉት፣
በተሰጠን ድንበር እውቀታዊ ልኬት፣
አንተም እንዳዋቂ ሳድስን ዝለላት፣
እኔ ግን ስወዳት ስን እንዴት ልጣላት?
ለስሜ መጠሪያ ሁልጊዜም ከፊት ናት።
አንተም ለተማሩት ለተመራመሩ፣
ስንቴም እጭራለሁ ፊደል ለሚገድፉት፣
ግን ማወቅ ጥሩ ነው አለማወቅ ክፉ፣
ሳያውቁ አውቂያለሁ እረዘመ ሰልፉ፣
አንተ አስተምረኸኝ ለእውቀት እስከበቃ፣
ልጫር ልሞጫጭረው አትከልክለኝ በቃ!
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
   ✍ ስንታየሁ ሀብታሙ
❤11
#አስታምምሻለሁ

ደስስስስስ . . . ይለኛል ባንቺ፡፡
እንደአራጣ ብድር፣
ህግ ተላልፌ፤
አተርፋለሁ ብዬ፤
የእጄን በትኜ፣ በተስፋ ታጅዬ፤
ተአምር ያምረኛል፣ በፈጣሪ አምናለሁ፤
‹‹ማፍቀሬ ይባረክ››፣ ሱባኤ ገባለሁ፡፡
ተአምር ያምረኛል፤
ፍቅርሽ ደስስስ ይለኛል፡፡
ቅርርርርር . . .  ይለኛል ባንቺ፡፡
እንደክረምት ጎርፍ . . . .
ደመናው ሲገፍፍ፣
መስከረም ሲጠባ፣ አደዩ ሲረግፍ፤
ብትደርቂስ እያልኩ፣ ከልቤ ሸለቆ፤
ዛሬያችን ጸዳሉ፣
ነገ ላይ ደለሉ፣
ከአድማሴ ግርጌ፣ በእጦት ጨፍቆ፤
አቁሞ ያስቀረኛል፤
ፍቅርሽ ያስፈራኛል፡፡
እና ስለፍቅርሽ ...
ባንዱ ጎኔ ተስፋ፣
ባንዱ ጎኔ እጦት፣
እንደእርጥብ ሌጦ፣ ግራ ቀኝ ገድግዶኝ፤
አስታምምሻለሁ፣ አደርገው ቸግሮኝ፡፡
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
✍ በድሉ ዋቅጅራ
❤15👍2
#እስክትመጪ_ልበድ

ፍቅር አበደ አሉ መውደድ እንዴት ያብዳል፤
ማበድ የሚሉት ቃል ላበደው ይቀላል፡፡
ታችአምና መስከረም አንቺን እንደሸኘሁ፤
ማን አለብኝ ብዬ ራሴን ጥያለሁ፡፡
የኖርንበትም ቤት ሊበላኝ ደረሰ፤
የተጫወትንበት እቃቃው ፈረሰ፡፡
በትናንት ረመጥ ዙሪያዬን ታጥሬ፤
ከጎጆ የሸሸች ስደተኛ አፍቅሬ፡፡
ከጎዳና ልውጣ ልሩጥ ጨርቄን ልቅደድ፤
ማትቀሪ ከሆነ እስክትመጪ ልበድ፡፡

እብዱና ጤነኛው በሌበት ሀገር፤
ከአንድ ቤት ሲያድሩ ቀልድና ቁም-ነገር፡፡
ሰው በዚች ሀገር ላይ አ..በ..ደ ሚባለው፤
………………………….ጨርቁን የቀደደ፤
…………………………እርቃኑን የሄደ፡፡
…………………………ፀጉሩን ያጎፈረ፤
………………………..ጎዳና ያደረ፡፡
……………………….ከሰው ያልቀረበ፤
……………………….ምግብ የተራበ፡፡
……………………….ብቻውን ሳቀ፤
……………………….ዝናቡን ፀሀዩን በአንድ ላይ የሞቀ፡፡
……………………….መሆኑን አውቃለሁ፡፡
በእዚች ሀገር ሰው አ..በ..ደ ሚባለው፤
ከላይ ያልኳቸውን ፎርም የሚያሟላ ነው፡፡
……………………….እናልሽ ዓለሜ!
ማበዴ እንዲታወቅ ጨርቄን ቀድጃለሁ፤
……………………….እርቃኔን ሄጃለሁ፡፡
ፀጉሬን አጎፍሬ ጎዳና አድሬያለሁ፤
እብደቴ እንዲያሳምን ብቻዬን ስቄያለሁ፡፡
በሰው አሉባልታም ልቤ ከሚደማ፤
መኖር ይሻለኛል አብዶ በጨለማ፡፡
ፋኖስ እንዳለኩስ ይዘሽው ጠፍተሻል፤
አፍቃሪዬም ያልሽው ጨርቁን ጥሎልሻል፡፡
ከሰው ሳልስማማ ከሰው ሳልጠጋ፤
ክረምቱ አለፈና ደግሞ መጣ በጋ፡፡
ፀጉሬን አንጨበረርኩ ፂሜን አጎፈርኩኝ፤
ልብሴን ቀዳድጄ በናፍቆት አበድቁኝ፡፡
ከቆሻሻ ዋልኩኝ ገላዬ ከረፋ፤
በእብደት ስጠብቅሽ በጭላንጭል ተስፋ፣
ከመንገድ ባላይሽ አዲስ ጎህ ሲቀደድ፤
ሰው መቅረቤን ትቼ እስክትመጪ ልበድ።
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
❤22👌5👏1🐳1
#የእድሜ_ሌባ!!!

ከህይወት ሰሌዳ ከእድሜ ያልተማረ
በሽበቱ ደምቆ በአንቱ ያልከበረ
ኮረዳ ፍለጋ ዘቅጦ የዛከረ
የእድሜ " ፐ " ላይ ደርሶ ግን የደነቆረ
በቅሌት ጎዳና የሚመላለሰው
የትዳሩን ዋጋ አንሶ ያሳነሰው
ንሯል አትበሉኝ በከንቱ እድሜ ቁጥር
ሳይኖር የሞተ ነው ያልታደለ ፍቅር
ከልጆቹ እኩያ አስረሽ ምችው ዜማ
የሚርመሰመሰው በሀብት ከተማ
እድሜውን ዘንግቶ ቁልቁል የወረደ
ጤነኛ ምትሉት ግን እርሱ ያበደ
የምትሰግዱለት ሲወጣ ሲገባ
መሆኑን እወቁ እርሱ የእድሜ ሌባ።
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
   ✍ ስንታየሁ ሀብታሙ
👏15❤4🥰4
የማይወዳደር እኩያ የሚያጣ
ከልቤ ግርጌ ስር አንዳች ስሜት ወጣ
ተሰማኝ ወደድኩህ ያንተን ጣዕም ለየሁኝ
ቆዳዬ ቀመሰህ ምላሴን ከዳሁኝ
ከየትኛው አካሌ ፍቅርህ የወደቀው
የሚያርበተብተኝ ጥፍሬን የሚነዝረው
አካልስ አለ ወይ የሚታይ ሚቀመስ
ሴትነት ገላዬን ነክቶ ሚያጎለምስ
ንገረኝ አንተዬ ከደጅ እንዳያድር ዳስም ልጣልለት
እንዲህ ያለ ፍቅር አያድርም ከኔ ቤት
በአዳፋዬ ባያድፍ ንፁህ ጥሩ ፍቅርህ
ከቆሸሸ ገላ ከዚህ በድን ይሽሽ
እንዲህ ያለ ልመና ሚዛን አያነሳም
የፍቅር ባህሪ ዙፋንን አይሻም
የት ጋር ነው የሚሰማኝ ምኔን ነው የያዝከው
የት ጋር ነው ያገኘኸኝ ምኔን ነው ያጣኸው
ብቻ ከልቤ ስር ስሜቴ ይፈልቃል
የደረስክበትን ያልደረስክበትን
ረቂቁ ፍቅርህ እሱ ብቻ ያውቃል።
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
✍ ረድኤት ተረፈ
❤7🔥6
#እኔ_ልማልብሽ

አብሬሽ እያለሁ በፍቅር ሰክሬ
ልሙትልሽ ያልኩሽ ውዴ ቀባጥሬ
ዛሬ ፀፅቶኛል እውነቱን ልገርሽ
አንቺም እንዳታዝኝ በቃ ልኑርልሽ
ማይብኝ በስሜ ብየ የነገርኩሽ
ዛሬ ግን ሳስበው እኔ ልማልብሽ
አፅምሽ እንዳያዝን በብቸኝነቴ
በሀዘን ተጎድቶ ሳስቶ ሰውነቴ
ይረሳኛል ብለሽ አታስቢ ፍቅሬ
ከጓደኛሽ ጋራ ብኖር ነው አብሬ
ከዚያ ውጭ በፍጹም ከአንቺ ሌላ ማሬ
ድንገት እርሷም ብትሞት ከጓደኛዋ ጋር ብጀምር ነው ፍቅሬ።
እመኝኝ¡¡¡¡¡ ።
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
   ✍ ስንታየሁ ሀብታሙ
😁24❤10
#ማሪኝ_እንዳትለኝ

ውዴ ትዝ ይልሀል ያኔ እንደጀመርን
እኔና አንተ ሁነን ፍቅርን ስንወጥን
ወሬህ ማይጠገብ ንግግርህ ጣፋጭ
የጨዋታህ ለዛ ቃላቶችን መራጭ
በስሜንኳ አጠራኝ ቁልምጫህ የብቻ
አስተዋይነትክ የትም የለህ አቻ
ቀልቤን ማንነቴን እኔነቴን ወሰድክ
ልቤንም ሰጠሁህ ሁሉን ተቆጣጠርክ
ባሌ ብቶን ብዬም አብዝቼ ተመኘሁ
ያንተ ሆኜ ልኖር ህይወቴንም ሰጠሁ
አንተ ግን °°°
መሸነፌን  አይተህ ባንተ መረታቴን
 መውደዴን አቅለህ አሳንሰህ ፍቅሬን
ሌላ ሰው ሆንክብኝ የማላቀው ትናንት
ፍፁም ተቃራኒ  ካለፉት ግዚያት
   ያሳየኸኝ ነገር  ያ ሁሉ ቀነሰ
ፍቅሩም ቁልምጫውም እያደር አነሰ
መምረጡም ቀረና ቃላቱን ማሳመር
በእሾክ ንግግርህ ታሳምመኝ ጀመር
ልቤን ስለፈተሽክ የመውደዴን መጠን
የትም አቴድ ብለህ ጀመርክ መጨከን
       ምን አጠፋሁ ውዴ?
ታምኜልህ በኖርኩ ሁሉን ነገር ትቼ
ጥፋት ስተትህን በይቅርታ አጥፍቼ
            ሁሉን ረስቼ
ቁም ነገር ባሰብኩኝ ለነጋችን በሚል
አብረን እንድንኖር ጎጆ እንድንደለድል
ምነው የምወድህ ታድያ ምን አደረኩ
ነውር ሰራሁ እንዴ አንተን ስላፈቀርኩ
         ያ ሁሉ ሳያንሰኝ 
ላንተ ስል ደክሜ ላንተ ስል ታምሜ
ከሳቅ ተጣልቼ  ጠፍቶ  ያ ሰላሜ
በእንባ ስገፋ ዕልፍ  የሆኑ ቀናት
ሀዘን ያጀባቸው  ምሽትና ንጋት
አንተ ግን ጉዳቴን ሰምተህ ህመሜንም
እንዴት ሆነች እንኳ ብለህ አልጠየክም
       አንደምን አስቻለህ...?
       እንዴትስ አራራህ ...?
እንዲህ ነበር እንዴ ለኔ የሚገባው ?
ለፍቅርህ ለሆንኩት ምላሹና ዋጋው?
ብቻ እንዲ ስትገፋኝ ደርሰህ ስታርቀኝ
          ደስታ እንደናፈቀኝ
ባንተ ተስፋ ስቆርጥ ሁሉም ነገር አልፎ 
ልቤም  ከጉዳቱ ከስብራቱ አርፎ 
መከፋቴም ቀርቶ እምባዬም ሲደርቅ
ውስጤም ያንተን ፍቅር ከልቡ ላይ ሲፍቅ
ማሪኝ እንዳትለኝ ከረፈደ ገብቶህ
አዲስ ቀን ሲጀምር ልቤ አንተን ረስቶህ
ሂዎትን ሲቀጥል አንተን ላንተ ትቶህ።
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
❤26👍5👏3😢2🔥1
አንዳንዴ...
  ባልተገራ ፈረስ
በፈጣን ድንጉላ
ኑሮን ባቦ ሰጠኝ
ህይወትን በመላ
በዚህ በኩል ሲሉህ
ንጎድ ወደ ሌላ፤
እስከመቼ  ድረስ
ዳር ዳሩን መራመድ ፤ በጭምት ሰው ስሌት
በክብር ካልመጣ፤ ሞክረው በቅሌት
  ሰው  ቅፅር አይደለም፤ በእሾህ የታጠረ
እንድትጥሰው ነው፤ ህግ የተፈጠረ::
አይሰለቺህም ወይ
መኖር በተጠንቀቅ
አንዳንዴ
አየር ላይ ደንሰህ ፤ በግንባርህ ውደቅ
  አንዳንዴ
ኮርቻህን እርሳት
  ርካህብህንም ሳት
ፋይዳ አይጠፋምና፤ ወድቆ ከመነሳት !
በትቢያ ላይ ወድቀው
የተነሱ አሉና፤ በሉል ባልማዝ ደምቀው !
አንዳንዴ 
ልጉዋሙን ልቀቀው!
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
✍ በእውቀቱ ስዩም
❤14💯3
#እኔ_ሞኙ_ልጅሽ

አንችን ገላጭ ቅኔ አንች ገላጭ ዜማ
የውበትሽን ጥግ የክብርሽን ግርማ
ብሞክር ባስሞክር በስንኝ ቋጠሮ
ቤት ባልመታ ግጥም በቃል እጉርጉሮ
በሀገር መስዬ ላወድስሽ ብጥር
አልገልጽልህ አለኝ እኔስ ያንችን ፍቅር
አናት ከማለት ውጭ ሌላው ቀለለብኝ
ብጽፈው ባጽፈው ሚዛኑ አነሰብኝ!
የፍቅርሽን ልኬት የደግነት ጥልቀት
የትኛው ቃል ይሆን ገላጭ እናትነት
ቃል አዋቂ ፈለኩ የተማረ አብዝቶ
ከውስጡ የሚፈስ ዜማ ቅኔ ሞልቶ
ግን አላረካኝም ውበቱ አነሰብኝ
ለደግነትሽን ክብር በቂ ቃል አጣሁኝ
ያወቁ የበቁ ሽህ አመት ቢመክሩ
ቋንቋ ላይ ተራቀው አብዝተው ቢማሩ
እናት ነው ውብ ቃሉ  ረቂቅ ቀመሩ
ሌላ ስም የላትም አትመራመሩ!
አልኳቸው እናቴ እኔ ሞኙ ልጅሽ
ቢሳነኝ በቅኔ በዜማ ልገልጽሽ
ሌላ ቃል ፈልጌ አስፈልጌ ባጣ
ከደጋ እስከቆላ ወርጄ ስወጣ
ከፊደላት ድምር እናት የሚል መጣ
እየደጋገመ እርሱው ከአፌ ይውጣ።
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
   ✍ ስንታየሁ ሀብታሙ
❤15🥰6
#እኔ_ወድሻለሁ

እኔ ወድሻለሁ
ታስሮ እንደ መፈታት
እንደ ጣኦስ ውበት
እንደ ዝሆን ብርታት
ዳዊትን ከጎልያድ
ደርቦ እንደመምታት፤

እኔ ወድሻለሁ
ጦም ውሎ እንደመጉረስ
ወልዶ እንደመታረስ
ቶምቦላ እንደመድረስ
ካላሙዲ ንብረት
ግማሽ እንደመውረስ፤

እኔ ወድሻለሁ
እንደ መቅደስ እጣን
እንዳፍለኛ ስልጣን
ያንች ልዝብ ሰይጣን።
እኔ ያንች ቡዳ
ያንች ልዝብ ሰይጣን።
        @gitm_post
    ♡ ㅤ     ❍ㅤ        ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ     ˢʰᵃʳᵉ
✍ገብረ ክርስቶስ ደስታ
❤21🔥3
🌼እንኳን ለ 2019  አዲስ ዓመት በሰላም፣ በጤና እና በፍቅር አደረሰን!🌼

አዲሱ ዓመት፡ የጤና፣ የሰላም እና የፍቅር፤
የታሰቡት መልካም ምኞቶች ሁሉ የሚሳኩበት፤
የስኬት እና የበረከት ዓመት ይሁንላችሁ!
@gitm_post
    ♡ ㅤ   ❍ㅤ  ⌲            
   ˡᶦᵏᵉ    ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ   ˢʰᵃʳᵉ
🌼🌼🌼መልካም አዲስ አመት!🌼🌼🌼
🙏11❤5