ገድለ ቅዱሳን
6.49K subscribers
18.5K photos
384 videos
53 files
794 links
@Gedelat
ለተለያዩ አስተያየት እና ጥቆማ ማድረስ ከፈለጉ በአድራሻችን ቢያደርሱን ይደርሰናል፡፡
በአድራሻችን @Mnfesawi_bot
Download Telegram
Audio
"በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

            #ሰኔ ፯ (7) ቀን።

እንኳን #ለኢትዮጵያዊው_ጻድቅ ለታላቁ አባት #አቡነ_ተክለ_ሃይማኖት_ከሾሟቸውና_በሀገራችን ለስብከተ ወንጌል ካሰማሯቸው #ከ47ቱ ቅዱሳን አንዱ ለሆኑት #ለአቡነ_ማቴዎስ_ዘእንደርታ_ለዕረፍታቸው መታሰቢያ በዐልና ለታላቁ አባት #ለጻድቁ_ለሐዋርያም ለደራሲም ለመላእክት በዐል የሚቀደሰው ከ14_ቅዳሴ አንዱ የሆነ በስሙ የተሰየመው ቅዳሴ ለደረሰ ለተከራካሪ መምህርም #ለያዕቆብ_ዘሥሩግ_ለዕረፍት_በዐል እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።

                         ✝️ ✝️ ✝️
#አቡነ_ማቴዎስ_ዘእንደርታ፦ እኚህ ጻድቅ ትውልድ አገራቸው እንደርታ ሲሆን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሾሟቸውና በሀገራችን ለስብከተ ወንጌል ካሰማሯቸው ከ 47ቱ ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው። ጻድቁ መላ ሰውነታቸው እንደ እሳት ያቃጥል ነበር። ወንጌልን በመስበክና በተአምራታቸው ድውያንን እየፈወሱ ብዙ ያገለገሉ ታላቅ አባት ናቸው። መዝገበ ቅዱሳንና ቅዱሳን በዓላት ላይ።

                         ✝️ ✝️ ✝️
#አቡነ_ያዕቆብ_ዘሥሩግ፦ አገሩ ሶርያ ሲሆን አባቱ ሊቀ ካህናት ነበር። በኤጲስ ቆጶስነት የተሾመባት አገር በጤግሮስና በኤፍራጥስ መካከል በምትገኝ ሥሩግ በምትባል አገር ስለሆነ ያዕቆብ ዘሥሩግ ተባለ። በ 3 ዓመቱ እናቱ ቤተ መቅደስ ስትወስደው መልአክ እጁን ይዞ በሊቀ ጳጳሱ እጅ እንዲቆርብ አድርጎታል። በዚህም ጊዜ ምሥጢራት ሁሉ ተገልጠውለታል። ገና በ 7 ዓመቱ ስለ ሦስት ነገሮች በእጅጉ ያለቅስ ነበር። "ነፍሴ ከሥጋዬ ተለይታ ስትወጣ ከጌታችን ጋር ስትገናኝና መጨረሻውን ፍርድ ስሰማ እነዚህን ሦስት ነገሮች በእጅጉ እፈራለሁ" እያለ ያለቅስ ነበር።

በ 12 ዓመቱ ብሉይንና ሐዲስን አጠናቆ ተመምሮ ጨርሷል። ጸጋውን ዐውቀው 5 ቱ ታዋቂ ሊቃነ ጳጳሳት መጥተው እጅ ነስተውት አዲስ ድርሰት ድረስልን ቢሉት እርሱም በፍጹም ትሕትና "በእናንተ ፊት እንኳን አዲስ ድርሰት ልደርስ ቀርቶ የተደረሰውንም መናገር አልችልም"። አላቸው። እርሱ በነበረበት ዘመን በሮማው መናፍቅ ልዮን አማካኝነት ቤተ ክርስቲያን ለመጀመርያ ጊዜ ለሁለት የተከፈለችበት ጊዜ ነበርና እነ ዲዮስቆሮስ "የውሾች ጉባኤ" ከተባለው ከኬልቄዶን ጉባኤ ተለይተው ሃይማኖትን ሲያጸኑ ልዮንንም ማውገዛቸውን ያዕቆብ ሲሰማ በዲዮስቆሮስ ጽናት በእጅጉ ተደስቶ ደብዳቤ ጽፎ አመስግኖታል። እነ ልዮንን ግን አውግዞ እረግሟቸዋል። ልዮንም ተከታይ ባገኘ ብሎ "እኔን ምሰል" በማለት ለያዕቆብ ደብዳቤ ጻፈለት። ያዕቆብም "ሳጥናኤል ከመላእክት ጋር ምን አንድ አደረገው? አንተ ርኩስ ነህ፤ የዲዮስቆሮስን ጥርስ አስወልቀህ፣ ጢሞን አስነጭተህ፣ ሃይማኖትህን የቀየርህ ከሁለት ዓለም ስደተኛ ጋር አልተባበርም፣ ይልቅስ ንስሓ ግባ፣ ንስሓ ባትገባ ግን አንተ ዲያብሎስ ነህ ተከታዮችህም አጋንንት ናቸው። በማለት መልሱን ጽፎለታል። እምቢ ብሎ በክህደቱ ቢጸናበትም አውግዞ እረግሞ ንጽሕናውን ቅድስናው እንደ መላእክት ነው የተባለለት ያዕቆብ ዘሥሩግ ጻድቅም ሐዋርያም ደራሲም ተከራካሪ መምህርም ነው። ሦስት ድርሰቶች ያሉት ሲሆን በስሙ የተጠራው ቅዳሴም አለው። ዕረፍቱ ሰኔ 7 ቀን ነው። ከአባታችን ከአቡነ ያዕቆብ ዘሥሩግ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎቱም ይማረን። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን።

                @Teamihokidusan
1
1
"በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

             #ሰኔ ፯ (7) ቀን።

እንኳን #አምላክን_ለወለደች_ለእመቤታችን #ለድንግል_ማርያም_ቤተ ክርስቲያን_ለተከፈተበትና ለከበረችበት፣ ቀሊን ከምትባል አገር ቅዱስና ቡሩክ ድል አድራጊም ለሆነ #ለአባ_አበስኪሮን_ሰማዕትነት ለተቀበሉበት #ለዕረፍታቸው_በዐል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚህ ቀን ከሚታሰቡ፦ መኰንን አርማንዮስ ካሠቃያቸው #ከአስራ_ስድስት_ሺህ_ሰማዕታት ከዕረፍታቸው መታሰቢያና ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

                          ✝️ ✝️ ✝️
#በዚች_ዕለት_አምላክን_የወለደች_የእመቤታችን_የድንግል_ማርያም_ቤተ_ክርስቲያን_የተከፈተበትና_የከበረችበት ነው። እርሷም ዌላ በሚባል አደባባይ ያለች ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ተዘግታ የኖረች ነበረች። ይኸውም በአንድ ሽህ ሃያ ዓመተ ሰማዕታት ነው። ከእመቤታችን ድንግል ማርያም ሰው ለሆነ ሕይወትና መድኃኒት አድርጎ እርሷን ለሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።

                            
                           ✝️ ✝️ ✝️
#አባ_አበስኪሮስ፦ ይህም ቅዱስ ከእንዴናው ገዥ ከአርያኖስ ጭፍራ ውስጥ ነበር የከሀዲው ንጉሥ የዲዮቅልጥያኖስ ስለ አምልኮ ጣዖት የሆነች ትእዛዝ በደረሰችው ጊዜ። ወዲያውኑ ይህ በሕዝብ መካከል ተነሥቶ ንጉሡን ረገመው ጣዖታቱንም ሰደበ ወታደር ስለ ሆነም ያሠቃየው ዘንድ ማንም አልደፈረም ነገር ግን በንጉሥ አዳራሽ ውስጥ አሠሩት።

መኰነንኑም ወደ አገረ አስዩጥ በሔደ ጊዜ ወደ ንጉሥ ላከው ከእርሱም ጋራ ሌሎች ወልደፍዮስ፣ አርማንዮስ፣ አርኪያስ፣ ጴጥሮስና ቀራንዮስ የተባሉ ነበሩ እሊህም ክብር ይግባውና ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደማቸውን ሊአፈሱ ከአባ አበስኪሮስ ጋር ተስማሙ። በንጉሡም ፊት በቆሙ ጊዜ በጌታችን ታመኑ ንጉሡም ትጥቃቸውን ይቆርጡ ዘንድ በየአይነቱ በሆነ ሥቃይም እንዲአሠቃዩአቸው አዘዘ ንጉሡ እንዳዘዘም አደረጉባቸው። ከእኒህ ከአምስቱ ግን ራሶቻቸውን የቆረጡአቸው አሉ የሰቀሉአቸውም አሉ እንዲህም ገድላቸውን ፈጽመው የሕይወት አክሊል ተቀበሉ።

የከበረ አበስኪሮስን ግን ታላቅ ግርፋትን እንዲገርፉት አዘዘ ከዚያም በኋላ ከራሱ እስከ አንገቱ ቆዳውን እንዲገፉ በፈረስ ጅራትም አሥረው በከተማው ውስጥ እንዲጐትቱት አዘዘ። ይህንም ሁሉ አደረጉበት። ከዚህም በኋላ በብረት ምጣድ ውስጥ አድርገው በላዩ አፉን ዘግተው ተሸክመው ወስደው በውሽባ ቤት ማንደጃ ውስጥ ጨመሩት በሥቃዩም ውስጥ ሁሉ የእግዚአብሔር መልአክ ወደርሱ ይመጣና ያጽናናው ነበር ያስታግሠውም ነበር ያለ ምንም ጉዳት አድኖ በደኅና ያስነሣው ነበር።

ከማሠቃየቱም በደከመ ጊዜ ከሥራየኞች ሁሉ የሚበልጥ በሥራዩም ወደ አየር ወጥቶ ከአጋንንት ጋራ የሚነጋገር ሥራየኛ አመጣለት። እርሱም የውሽባ ቤቱን ዘግተው ሽንት እንዲረጩበት አዘዘ እንዲሁም አደረጉ። እባብንም ይዞ በላዩ አሾከሾከና ለሁለት ክፍልም ሁኖ ተሠነጠቀ መርዙንና ሆድ ዕቃውን ወስዶ በብረት ወጭት አድርጎ አበሰላቸው በውሽባ ቤቱ ውስጥ ወደ አባ አበስኪሮን አቅርቦ ያንን መርዝ ይበላ ዘንድ ሰጠው ቅዱሱም በላ ግን ምንም ምን ጉዳት አልደረሰበትም። ያም መሠርይ "የመኳንንተ ጽልመት አለቃቸው ሆይ በዚህ ክርስቲያናዊ ላይ ኃይልህን አድርግ" ብሎ ጮኸ ምንም ምን ጥፋት ባልደረሰበት ጊዜ መሠርዩ አደነቀ። ቅዱስ አበስኪሮንም መሠርዩን "የሚራዳህ ሰይጣንህስ በክብር ባለበት በጌታዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል አንተን ይቀጣሃል" አለው። ወዲያውኑ ጥሎ የሚያንከባልለው ክፉ ሰይጣን ተጫነበት ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ታመነ ድረስ አሠቃየው። መኰንኑም የመሠርዩን ራስ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘና በሰማዕትነት ሞተ። በቅዱስ አበስኪሮን ላይ ግን ቁጣና ብስጭትን በመጨመር ጽኑዕ ሥቃይን አሠቃየው አባለ ዘሩንም እንዲቆርጡ አዘዘ እርሱ ግን በመከራው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግን ነበር። ከዚህም በኋላ ራሱን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘና ሰኔ 7 ቀን ቆረጡት የድል አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

ከቅዱስ አበስኪሮን ተአምራትም አንዱን እንነግራችኋለን በግብጽ ደቡብ በስሙ የታነፀች ቤተ ክርስቲያን ነበረች ካህናቷም ክፉ ሥራ የሚሠሩ ክፉዎች ነበሩ ቅዱስ አበስኪሮንም ከክፋታቸው ተመልሰው ንስሓ ቢገቡ ብሎ ጠበቃቸው። ባልተመለሱ ጊዜ ግን የንዳድ በሽታ አምጥቶ ሁሉም በአንዲት ጊዜ ሞተ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ አበስኪሮን በፈረስ ተቀምጦ የላዕላይ ግብጽ የሆነች ብያሁ ወደምትባል አገር ደረሰ የአገር ሰዎችም በደጃቸው ተቀምጠው ሳይተኙ በጨረቃ ብርሃን እርስ በርሳቸው ያወሩ ነበር። የከበረ አበስኪሮንም ከፊታቸው ደርሶ "ሰላም ለእናንተ ይሁን" አላቸው በአዩትም ጊዜ የሰላምታውን አጸፋ እየመለሱ ተነሥተው ተቀበሉት ሁለተኛም "ያቺን የሚሻትን ምድር እያመለከታቸው ከምድራችሁ ጥቂት እንድትሰጡኝ እሻለሁ" አላቸው። እነርሱም "ጌታችን እንደወደድክ ይሁንልህ" አሉት መቶ የወርቅ ዲናርም ሰጥቷቸው ተሠወራቸው። እነርሱም ከዚህ ራእይ የተነሣ አደነቁ።

ከተኙ በኋላም ቤተ ክርስቲያኒቱን አፍልሶ ከግብጽ ደቡብ ወደ ላይ ግብጽ ብያሁ ወደምትባል አገር በመቶ የወርቅ ዲናር ወደ ገዛት ምድር ከንዋየ ቅዱሳቷ ሁሉና ከዐፀዷ ጋር አምጥቶ በዚያ አቆማት። የአገር ሰዎችም በጥዋት ነቅተው ወደ ውጭ በወጡ ጊዜ ቤተ ክርስቲያቱን በደጃቸው አገኙዋት እጅግ ፈጽሞም አደነቁ ምስጉን እግዚአብሔርንም አመሰገኑት። ከዚያች ጊዜ ጀምሮ ድንቅ ተአምር የሚደረግባት ሆነ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በሰማዕቱ በአባ በአበስኪሮን ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የሰኔ 7 ስንክሳር።



                   @Teamihokidusan
3
"በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"።

እንኳን #ለሐዋርያት_ሰኔ_ጾም_ሁለተኛ_ሳምንት #ስለ_ዕርገቱና_ስለ_ጰራቅሊጦስ ለሚነገርበት ዕለተ ሰንበት እግዚአብሔር አምላክ በሰላምና በጤና አደረሰን።


                        ✝️ ✝️ ✝️
#የዚህ_ሳምንት_መዝሙር፦ሃሌ ሉያ በ፫ "#ዐረገ_እግዚአብሔር_በቃለ ቀርን #በይባቤ_ዐርገ ወበቃለ ቀርን ወነበረ በየማነ አቡሁ (ዐርገ) አዝ፣ #ዐርገ_በስብሐት_ውስተ_ሰማያት ተኰነኑ ሎቱ መላእክት (ዐርገ) አዝ፣ ተኰነኑ ሎቱ መላእክት ኵሉ ኃይል ወኵሉ ፍጥረት (ዐርገ) አዝ፣ ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ ለንጉሥነ። ትርጉም፦ እግዚአብሔር በመለከት #ድምፅ_ዐረገ በዕልልታና #በመለከት_ድምፅ ዐረገ፤ በአባቱ ቀኝ ተቀመጠ፤ በክብር በምስጋና በጌትነት #ወደ_ሰማያት_ዐረገ፤ መላእክት ተገዙለት ኃይል ሁሉ ፍጥረት ሁሉ ተገዙለት፤ ለአምላካችንም ዘምሩ፤ አመስግኑ ለንጉሣችን ዘምሩ አመስግኑ። #ሊቁ_ቅዱስ_ያሬድ_በድጓው_ላይ

                         ✝️ ✝️ ✝️
#የዚህ_ሳምንት_የዕለቱ_ምስባክ፦ "ልበ ንጹሐ ፍጥር ሊተ እግዚኦ። መንፈሰ ርቱዓ ሐድስ ውስተ ከርሥየ። ኢትግድፈኒ እምቅድመ ገጽከ"። መዝ 50፥10-11። የሚነበቡት መልዕክታት 1ኛ ቆሮ 12፥1-12፣ 1ኛ ዮሐ 2፥20-ፍ.ም፣ የሐዋ ሥራ 2፥14-22። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 14፥22-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ። መልካም ዕለተ ሰንበትና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።

                 @Teamihokidusan
✝️ #ነገ_ሰኔ_7_ቀን_ሰንበተ_ሰንበታት

✝️ በዓመት ውስጥ አራት ሰንበተ ሰንበታት አሉ ። እነዚህ ቀናት የሚሰሉት #የዓመቱን_365_ቀናት_ለ4 በመክፈል (#91_ቀናት በመቁጠር) ነው።

✝️ የ2018 ዓ.ም የሰንበተ ሰንበታት ቀናት
መስከረም 1 ቀን ሐሙስ ስለዋለ፣ በዚህ ዓመት የሚውሉባቸው ቀናት እንደሚከተለው ይሆናሉ፡
1ኛው ሰንበተ ሰንበታት  #መስከረም_4
2ኛው ሰንበተ ሰንበታት  #ታኅሣሥ_5
3ኛው ሰንበተ ሰንበታት  #መጋቢት_6
4ኛው ሰንበተ ሰንበታት  #ሰኔ_7 ይሆናል ።

✝️ በሌላ ቀላል ዘዴም ማወቅ ይቻላል ይኸውም መስከረም ፣ ታህሳስ ፣ መጋቢት ፣ ሰኔ በእነዚህ 4 ወራት የመጀመሪያው እሁድ ሰንበተ ሰንበታት ይሆናል።

የእነዚህ የ4ቱ ዕለታት ማሳረጊያ ደግሞ ጳጕሜን 3 ናት።
-> በእነዚህ ዕለታት ርኆተ ሰማይ የሚሆንባቸው በመሆናቸው  የዚህ ዓመት 4ኛው ሰንበተ ሰንበታት #ሰኔ_7 ስለሆነ ከወትሮው በተለየ መልኩ  እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት፣ ምህረትን የምንለምንበት እና ለራሳችንና ለሀገራችን ሰላም የምንጸልይበት ታላቅ ዕለት ነው።

ጸሎታችንና ምልጃችን በፊቱ ይድረስ!። ምንጭ፦ አምኃ ሥላሴ (መኩሪያ ተስፋዬ)።

                  @Teamihokidusan
🕊

[ † እንኳን ለታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ፣ አደረሰን። † ]

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †


🕊  † ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ †  🕊

† በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በደራሲነታቸው : በወንጌል አገልግሎታቸውና በቅድስናቸው ከተመሠከረላቸው ዐበይት ሊቃውንት አንዱ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ነው::

ሊቁ የተወለደው መጋቢት ፳፯ [27] ቀን በ፬፻፴፫ [433] ዓ/ም ሲሆን ሃገሩ ሶርያ ነው:: ወላጆቹ ክርስቲያኖች ለዚያውም አባቱ ሊቀ ካህናት ነበር:: ቅዱስ ያዕቆብ ገና በልጅነቱ ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔር የጠራው ነውና በብዙ ነገሩ የተለየ ነበር::

አንድ ቀን በዕለተ ሰንበት : ገና በ ፫ [3] ዓመቱ : እናቱ አቅፋ ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደችው:: ምዕመናን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበሉ ሕጻኑ ያዕቆብም ይቆርብ ዘንድ ቀረበ:: ሊቀ ዻዻሱ ደሙን በዕርፈ መስቀል ሊያቀብለው ሲል መልአኩ መጥቶ "በጽዋው ጋተው" አለው:: የጌታን ደም በጽዋ ቢጠጣ ምስጢር ተገለጸለትና "አንሰ እፈርሕ ሠለስተ ግብራተ - እኔስ ፫ [3] ነገሮች ያስፈሩኛል" ሲል አሰምቶ ተናገረ::

† ዻዻሱና ሕዝቡ ወደ ሕጻኑ ያዕቆብ ቀርበው "ምን ምን?" አሉት:: እርሱም :-

፩. ነፍሴ ከሥጋየ ስትለይ::
፪. ቅድመ እግዚአብሔር ለፍርድ ስቀርብ::
፫. ከፈጣሪየ የፍርድ ቃል ሲወጣ" አላቸው::
ያን ጊዜ ሕዝቡና ሊቀ ዻዻሳቱ "እግዚአብሔር በዚሕ ሕጻን አድሮ ዘለፈን" እያሉ ለንስሃ በቅተዋል::

ቅዱስ ያዕቆብ ፯ [7] ዓመት ሲሞላው ይማር ብለው ወደ ጉባዔ አስገቡት:: በ፭ [5] ዓመታት ብሉይ ከሐዲስ ጠንቅቆ በ፲፪ [12] ዓመቱ ሊቅ ሆኗል:: በዚህ ወቅት የነበሩ ታላላቅ ሊቃነ ዻዻሳት ወደ እርሱ ተሰበብስበው "እንግዳ ድርሰት ድረስልን:: አዲስ ምሥጢር ንገረን" አሉት:: እርሱ ግን ሲቻለው ስለ ትሕትና "አልችልም" አላቸው::

"እንግዲያውስ ትንቢተ ሕዝቅኤልን ተርጉምልን" ቢሉት ባጭር ታጥቆ አመሥጥሮላቸው ተደስተዋል:: ፈጣሪንም አመስግነዋል::

ቅዱስ ያዕቆብ ከዚህ በኋላ ወደ ገዳም ገብቶ ትሕርምተ አበውን : ዕጸበ ገዳምን : ሕይወተ ቅዱሳንን በተግባር ተምሯል:: በድንግልናው ጸንቶ : ጾምና ጸሎትን እያዘወተረ ኑሯል:: በፈቃደ እግዚአብሔር የሥሩግ [በኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች መካከል የምትገኝ የሶርያ ግዛት ናት] ኤዺስ ቆዾስ ሆኖ ተሹሟል::

† በዘመኑም :-

፩. የ፬፻፶፩ [451] ን የኬልቄዶን ጉባኤ አውግዟል::
፪. ብዙ መናፍቃንን ተከራክሮ ምላሽ አሳጥቷል::
፫. በወንጌል አገልግሎት መልካም እረኝነቱን አሳይቷል::
4፬. ዛሬ የምንገለገልበትን መጽሐፈ ቅዳሴውን ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል::

በመጨረሻም ከብዙ የተጋድሎና የቅድስና ዓመታት በኋላ በተወለደ በ፸፪ [72] ዓመቱ በ፭፻፭ [505] ዓ/ም በዚሕች ቀን አርፏል:: አንዳንድ ምንጮች ደግሞ ሰኔ ፳፯ [27] ቀን እንዳረፈ ይናገራሉ:: ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ለቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ተወዳጅ ልጇ ነውና በእጅጉ ታከብረዋለች::

† አምላከ ቅዱሳን ከታላቁ ሊቅ በረከት ይክፈለን::

🕊

[ † ሰኔ ፯ [ 7 ] ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት ]

፩. ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ
፪. ቅዱስ : ቡሩክና አሸናፊ አባ አበስኪሮን [ታላቅ ሰማዕትና ባለ ብዙ ተአምራት ነው]
፫. ፲፮ ሺህ "16,000" ሰማዕታት [በአንድ ቀን የተገደሉ]
፬. የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን የተከፈተበት በዓል (ከ1ሺ ዓመታት በፊት ምስር [CAIRO] ውስጥ]

[ † ወርሐዊ በዓላት ]

፩. ሥሉስ ቅዱስ [ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ]
፪. አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
፫. አባ ሲኖዳ [ የባሕታውያን አለቃ ]
፬. አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
፭. አባ ባውላ ገዳማዊ
፮. ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
፯. ቅዱስ አግናጥዮስ [ ለአንበሳ የተሰጠ ]

" ይሕንን እዘዝና አስተምር :: በቃልና በኑሮ : በፍቅርም : በእምነትም : በንጽህናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው:: እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር : ለማስተማርም ተጠንቀቅ:: " † [፩ጢሞ.፬፥፲፩] (4:11)

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †
† ወለወላዲቱ ድንግል †
† ወለመስቀሉ ክቡር †

[ ዲ/ን ዮርዳኖስ አበበ  ]

         †              †               †
▬▬▬▬▬ ▬▬▬ ▬▬▬▬▬
💖                   🕊                    💖
1
Audio